ስለጡት ካንሰር ለኢትዮጵያኖች የጥሞና ማሳሰቢያና ማስገንዘቢያ
ወርሃ ኦክቶበር (ጥቅምት)በአለም የጡት ካንሰር ማሳሰቢያና ማስገንዘቢያ ወቅት ነው፡፡ ወሩን በሙሉ በዓለም ላይ ሕዝባዊና የግል ድርጅቶች የፕሮግራሞቻቸውና የእንቅስቃሴዎቻቸው ትኩረት ሁሉ በጡት ካንሰር መንስኤ ላይ በማትኮር፤ አደጋውን ለመቀነስ፤ ቅድመ ጥንቃቄ ስለማድረግ፤ ህክምናና ምርምር በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ በእርግጠኝነት በተረጋገጠው መሰረት በአብላጫ በዓለም ላይ ሴቶችን በማጥቃት ላይ ያለው የጡት ካንሰር ነው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች በበሽታው በየዓመቱ ሲለከፉ ከነዚህም መሃል በሢ የሚቆጠሩት ለሞት ይዳረጋሉ፡፡ኮመን ፎር ዘ ኪዩር የተባለው የአሜሪካ ድርጅት እንደአስቀመጠው በአሜሪካን የሚገኙ አብላጫዎቹ አፍሮ አሜሪካውያን መሃል ሁለተኛው ገዳይ በሽታ የጡት ካንሰር እንደሆነ ያረጋግጣል፡፡ በአፍሪካ ስለዚህ ገዳይ በሽታ የታማሚ መጠንና ስለሚያደርሰውም አደጋ አያም ስለሚሰጠው ትኩረትና ህክምና በትክክል እንዲህ ነው ለማለት ዘገባም ሆነ መግለጫ ስለሌለ ብዙ ማለት ያስቸግራል፡፡ በአፍሪካ የበሽታው ሁኔታ ሊታወቅ የሚችለው ታማሚው በበሽታው ተይዞ ለህክምና ወይም ለመመርመር ወደ ጤና ጣቢያ አለያም ህክምና ማእከል ሲሄድ ብቻ ነው፡፡ አብላጫው የሴቶች ቁጥር በሚኖርበት የገጠሩ ክፍል ስለበሽታው ሁኔታ መዝግቦ መያዝና ማስረጃዎችን ማሰባሰቡ በብዙም የተለመደ ወይም ሁኔታ የተፈጠረለትም አይደለም፡፡ ስለበሽታው ሁኔታ ክትትልና ዘገባም ሆነ ስለበሽተኞቹ ሁኔታ ጥናት ማካሄድን ከምር ይዘው በማስኬድ ላይ የሚገኙት ጥቂት የአፍሪካ ሃገራት ናቸው፡፡