ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን የዉሸት ወሬዎች እና የማወናበጃ መረጃዎችን በመዋጋት  እናግዛቸው!

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ 

የጸሀፊው ማስታወሻ፡ ከጥቂት ቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ቅንነት የሌላቸው እና የተዛቡ ወሬዎች በሶማሊ ክልል ሰብአዊ ቀውስ ላይ ነዳጅ ይጨምራሉ፡፡“

ትላንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ በማለት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸውን መክረዋል፣ “ቅንነት የሌላቸውን እና የተዛቡ ወሬዎችን በመቀበል አታሰራጩ፡፡ ቅንነት የሌላቸውን እና የተዛቡ ወሬዎችን በፍጹም አናሰራጭ ምክንያቱም በዚሁ ሰበብ በርካታ ሰዎች እየተጎዱ ነው፡፡ የመረጃ እና የወሬ ምንጮችን አስተማማኝነት በሰከነ እና ጥንቃቄ በተመላበት ሁኔታ ማገናዘብ አለብን፡፡ ቅንነት የሌላቸውን እና የተዛቡ ወሬዎችን ተቀብሎ እንዳያሰራጭ እያንዳንዱ ሰው ጥንቁቅ እና ንቁ በመሆን የዕለት ከዕለት ህይወቱን እንዲመራ እጠይቃለሁ፡፡

በጦርነት ጊዜ እውነት የመጀመሪያው የጉዳት ሰለባ ነው፡፡ ይህም እውነት ከሳይበር የመረጃ ጦርነቶች የበለጠ በየትኛውም ቦታ የጉዳት ሰለባ ሊሆን አይችልም፡፡

የጨለማው ጎን ኃይሎች ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በተቃራኒው ጎራ በመቆም በኢትዮጵያ ላይ እየመጣ ያለውን ሰላማዊ የለውጥ ማዕበላችንን ለማደናቀፍ እና ወደ ዱሮው የጭቆና፣ የአፈና እና የጨለማ አገዛዛቸው ለመመለስ ሲሉ የማህበራዊ መገናኛዎችን/ሜዲያዎችን በመሳሪያነት፣ በመከፋፈያነት፣ በግድየለሽነት፣ በጎሰኝነት እና በአናሳነት በመጠቀም የሳይበር (ኢንተርኔት) የመረጃ ጦርነቶችን በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ የማህበራዊ መገናኛ/ሜዲያ ተዋጊዎች በሙሉ የዉሸት ወሬዎች፣ የተዛቡ የሀሰት መረጃዎችን እና የሸፍጥ ህልወቶችን ሁሉ በማጋለጥ እና በመዋጋት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጎን በጽናት በመቆም እና በማገዝ ውድ ሀገራችሁን እንድትታደጉ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡

የጨለማው ጎን ኃይሎች የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን መንግስት ለመጉዳት፣ ሕጋዊነቱን ለማሳጣት እና በሀገሪቱ ውስጥ ያልተረጋጋ ሁኔታን ለመፍጠር ሲሉ ቅንነት የሌላቸውን ወሬዎች፣ የተዛቡ የሀሰት መረጃዎችን እና የሸፍጥ ህልወቶችን በመሳሪያነት መጠቀምን ምርጫቸው በማድረግ የስነ ልቦና እና የመረጃ ማዛባትን እኩይ ተግባራት(ጦርነት) እውን ለማድረግ ሌት ከቀን በመዋተት ላይ ይገኛሉ፡፡

ቅንነት የሌላቸውን ወሬዎች የማሰራጨት ዓላማቸው ቀላል እና ግልጽ ነው፡፡ እንዲህ በሚለው የዱሮ አባባል ላይ የተመሰረተ ነው፣ “ውሸት ተደጋግሞ ሲነገር እውነት ይሆናል“ ወይም ደግሞ ማኦ ዜዱንግ በአንድ ወቅት እንዳሉት “አንድ መቶ ጊዜ የተነገረ ውሸት እውነት ይሆናል” እንደማለት ነው፡፡

በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሳይበር ጦርነት (ማህበራዊ መገናኛ/ሜዲያ) ቋንቋ የዉሸት ወሬዎች “ስሌታዊ ፕሮፓጋንዳ” በመባል ይጠራሉ፡፡

በኢትዮጵያ እና በዲያስፖራው ውስጥ ያሉ የጨለማው ጎን ኃይሎች በትንሹ እንኳ ሲታሰብ የሚያሰራጩት መረጃ ለምንም የማይውል ቆሻሻ መሆኑ ቢታወቅም ነገሮች ሁሉ የበለጠ ታማኝነት ያላቸው በማስመሰል በርካታ የሆኑ መሰረተ ቢስ እና እርባና ቢስ መረጃዎችን በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ፡፡

የጨለማው ጎን ኃይሎች የሀሰት የማወናበጃ መረጃዎችን የማሰራጨት ዘመቻዎችን እያካሄዱ እንዳሉ ቀደም ሲል ጽፊያለሁ፡፡

የሀሰት የማወናበጃ መረጃ ሆን ተብሎ ታስቦበት እና ታቅዶ የሚሰራጭ የውሸት ወይም ደግሞ ትክክለኛ ያልሆነ የተዛባ መረጃ ነው፡፡

የሀሰት የማወናበጃ መረጃ የማሰራጨት ዋና ዓላማው የለየላቸውን ቅጥፈቶች እና ተራ ውሸቶች እውነት እንደሆኑ አድርጎ በማቅረብ ሌሎችን ሰዎች ለማሳመን ነው፡፡ ዓላማውም በሕዝቡ ውስጥ ስጋት፣ ፍርሀት እና  ጭንቀት ለመፍጠር ነው፡፡

የሸፍጥ ህልወት/conspiracy theory በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል በሚል ከንቱ ተስፋ እውነትነት የሌለው ወይም ደግሞ ያልተለመደ እና ልዩ የሆነ በተከታታይነት የሚደረግ ግምታዊ ትንበያ ነው፡፡

ለተጠናከረ የስነ ልቦና እና የሀሰት የማወናበጃ መረጃ ጦርነት ስርጭት ዋና ዒላማዎች እና ሰለባዎች የሚሆኑት ደግሞ ከቴክኖሎጂ ጋር ቅርርብ የሌላቸው ወይሞ ደግሞ የበርካታ መረጃዎች ምንጮች ተደራሽነት የሌላቸው እና መልካም ሀሳብ ያላቸው ተራ ኢትዮጵያውያን እና የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ደጋፊዎች ናቸው፡፡

በመሆኑም በእነዚህ ከኢንተርኔት ጋር ግንኙነት የሌላቸውን፣ ከበርካታ የመረጃ ምንጮች ጋር ተደራሽነታቸው በጣም ትንሽ የሆኑ እና በማህበራዊ መገናኛ እና በመረብ ግንኙነት በሚተላለፉ ቆሻሻ ዜናዎች እና እውነትን መሰረት ባደረጉ በጣም ወሳኝ ዘገባዎች መካከል ያለውን ልዩነት መለየት ያልቻሉትን ወገኖች ዒላማ በማድረግ ቅንነት የሌላቸውን እና የተዛቡ ወሬዎችን፣ የሀሰት የማወናበጃ መረጃዎችን እና የሸፍጥ ህልወቶችን በማሰራጨት እኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት ይጠቀማሉ፡፡

የኢንተርኔት ጅቦች የሆኑት የጨለማው ጎን ኃይሎች ስለአብይ ደህንነት እና ሰላምነት ጥያቄ ውስጥ በሚያስገባ መልኩ ሕዝብ በእርሳቸው ላይ ያለውን ከፍተኛ ፍቅር ለማስለወጥ እና ከፍተኛ ከሆነ ስሜታዊነት ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ ሌት ከቀን በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡

ባለፈው ሳምንት ስለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ደህንነት፣ ከእይታ መጥፋት፣ ጤንነት፣ የት እንዳሉ፣ ወዘተ በርካታ ሰዎች እየተገናኙ ጠይቀውኛል፡፡  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዩኤስ አሜሪካ ከተመለሱ በኋላ በይፋ አልታዩም፣ እናም ሁሉም የሚጠይቁኝ ሰዎች “የሆነ መጥፎ ነገር አጋጥሟቸዋል” ይላሉ፡፡

ጥቂቶች ደግሞ እንባ አውጥተው አልቅሰዋል፡፡

በእርግጥ እኔ አውነታውን ብቻ ልነግራቸው ችያለሁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፍጹም በሆነ ደህንነት በጤና በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ወደ አሜሪካ ካደረጉት ፈጣን ጉዞ በኋላ የሚገባቸውን ረፍት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ዕለት በዕለት ይፋ የመንግስት የቢሮ ስራቸውን በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል የተከሰተውን ሰብአዊ ቀውስ ለመፍታት በመስራት ላይ ናቸው፡፡ እርሳቸው ደህና ናቸው፡፡ አመሰግናለሁ!

** ይህ ጽሁፍ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ በማህበራዊ መገናኛዎች እና በመረብ ግንኙነት በስፋት እና በተደጋጋሚ ይሰራጫል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና በኢትዮጵያ ላይ በየዕለቱ የሚካሄዱትን ቅንነት የሌላቸውን ወሬዎች፣ የሀሰት የማወናበጃ መረጃዎች እና የሸፍጥ ህልወቶች በመዋጋት መልዕክቶችን በማሰራጨት በሚደረገው ዘመቻ እንድትቀላቀሉኝ ሁሉንም የሳይበር ጓደኞቼን፣ የድረ ገጽ አርታኢዎችን እና ሌሎችንም ኢትዮጵያውያን ወገኖቼን ሁሉ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡**

====   ============ ============= ============== ===============

 በአብይ ላይ ከልክ ያለፈ ፍቅር እና የአብይ ሱስ፡ ሕዝቡ በአብይ አሕመድ ላይ ያለውን ፍቅር መገንዘብ፣

ለምንድን ነው በርካታ ኢትዮጵያውያን ስለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚጨነቁት እና የሚያስቡት? እንዲሁም እርሳቸውን በየዕለቱ በአደባባይ ካላዩ ለምንድን ነው ለወረበሎች እና ለተዛቡ ወሬዎች በቀላሉ ሰለባ የሚሆኑት?

መልሱ ቀላል ነው፡፡

በአብይ ፍቅር መጠመድ! የአብይ ሱስ!

መልካም ሀሳብ እና እምነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአብይ አሕመድ ላይ በፍቅር አብደዋል በማለት ብናገር ማንም አጋነንክ ብሎ ሊከሰኝ አይችልም፡፡ ይህንን ጉዳይ ለመግለጽ ከዚህ የተሻለ ሌላ መንገድ የለም፡፡ እንደ እራሳቸው ልጅ፣ ወንድም፣ አጎት፣ የአጎት ልጅ፣ ምርጥ ጓደኛ እና ወዘተ ይወዷቸዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ደጋፊዎች እርሳቸውን በየዕለቱ በቴሌቪዥን የሚያዩአቸው ካልሆነ በድንጋጤ ወደ በድንነት ይቀየራሉ፣ እናም የእብድነት ምልክት ያሳያሉ፡፡ እናም ማንኛውም ቆሻሻ መረጃ በተወረወረ ቁጥር በእርሳቸው ላይ መጥፎ ነገር ደርሶባቸው ነው በማለት በብስጭት ቀልባቸውን ያጣሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በአብዛኛው ሕዝባቸው በቅንነት ይወደዳሉ፡፡

ሆኖም ግን ይህ መወደድ በጨለማው ጎን ኃይሎች ዘንድ ግንዛቤን አላገኘም፡፡

እነርሱም አብይ አሕመድን ይወዷቸዋል፡፡

ፍቅራቸዉን የሚያሳዩት በጥላቻ ነው።

ሆኖም ግን ሊወገድ የማይችል የአብይ አህመድ የሱስ ነገር ሁላችንም ብይዘንም ስለአብይ አሕመድ አራት ነገሮችን ማስታወስ አለብን፡፡ እነርሱም፣

1ኛ) አብይ አሕመድ እንደሌሎቻችን ሁሉ ሰብአዊ ፍጡር ናቸው፡፡ ከስጋ እና ከአጥንት እንጅ ከአረብ ብረት የተሰሩ አይደሉም፡፡ እንደ ሁላችንም ይደክማሉ፡፡ እረፍት ይፈልጋሉ፡፡ ዩኤስ አሜሪካንን ለመጎብኘት ከኢትዮጵያ በለቀቁበት ጊዜ እና ወደ ኢትዮጵያ በተመለሱበት መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ ከሁለት ሰዓት የበለጠ እንቅልፍ እንኳ አላገኙም፡፡ ለዚህም ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የዓይን ምስክር ናቸው፡፡ ሎስ አንጀለስን ሲጎበኙ ከእርሳቸው ጋር ባሳለፍኩት ጊዜ አንድ ጊዜ ተቀምጠው ምሳ ለመብላት እንኳ ጊዜ አልነበራቸውም፡፡

2ኛ) አብይ አሕመድ የፖለቲካ መሪ ናቸው፡፡ የሆሊውድ ተዋንያን አይደሉም፤ ወይም ደግሞ የሲኤንኤን ፕሮግራም መሪ ጋዜጠኛ አይደሉም፡፡ ስለሆነም በየዕለቱ ይፋ የሆነ እይታ የማድረግ ግዴታ የለባቸውም፡፡ በቢሯቸው ውስጥ የሚያከናውኗቸው በርካታ ስራዎች አሏቸው፡፡

3ኛ) አብይ አሕመድ እንደማንኛውም ሰው ግለኝነትን ይፈልጋሉ፤ የግል ቦታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመሆን ጊዜ ያስፈልጋቸዋል፡፡

4ኛ) ለጥቂት ጊዜ በአደባባይ በይፋ ካላየናቸው አንድ መጥፎ ነገር ገጥሟቸው ነው በማለት ማሰብ የለብንም፡፡

በሰላማዊ የለውጥ ሂደታችን ላይ ቅንነት የሌላቸው እና የተዛቡ የሀሰት መረጃ ጦርነቶችን በመክፈት በርካታ ጉዳቶችን ለማድረስ የመረጃ ጦርነት ውሾች በመጮህ ላይ ናቸው፡፡

በጁሊየስ ቄሳር ሸክስፒር የማርክ አንቶኒን ገጸ ባህሪ በመላበስ ሲያደርጉት በነበረው ንግግር ለቂም እና ለበቀል የሚቋምጠውን የቄሳርን ሰይጣን ከጋነም በመጥራት ጉዳት ለማድረስ የጦርነት ውሾችን ፈታቸው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከዙፋን የተበረሩት የኢትዮጵያ ንጉሶች ሰላማዊ የለውጥ ሂደታችንን ለመቀልበስ የሰይጣን በቀላቸውን ለማድረግ ታጥቀው ተነስተዋል።

ሆኖም ግን ውሾቻቸው የሳይበር ጦርነትን እንዲያደርጉ በመጮህ ላይ እንዲገኙ ብቻ አይደለም የፈቀዱላቸው፡፡ በእርግጥ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭትን፣ ጥላቻን፣ ሞት እና ውድመትን በተቀነባበረ መንገድ በመምራት ተግባራዊ በማድረግ ላይም አሰርማርተዋቸዋል።

ለዚህ አነጠራጠር !

የጨለማው ጎን ኃይሎች የዘረፉትን በቢሊዮኖች የሚቆጠር የኢትዮጵያን የሕዝብ ገንዘብ በመጠቀም የኢትዮጵያን ሰላማዊ የለውጥ ሂደት በመቀልበስ ወደነበረበት የጭቆና እና አፈና የአገዛዝ ስርዓት ለመመለስ በይፋ እና በስውር ጥቃት በመሰንዘር ላይ ይገኛሉ፡፡

ፍልስፍናቸው እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ካለችው አህያ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ከስልጣን ዙፋናቸው የተባረሩት የዘመኑ ንጉሶች ፍልስፍናቸው ኢትዮጵያ የእነርሱ የመጫወቻ ሜዳ ካልሆነች ገሀነም ትግባ የሚል ነው!

በእርግጥ ላለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያን ገሀነም አድርገዋት ለቆዩት ለእነዚህ መቅነቢስ ዘራፊ ወሮበሎች ይኸ ቀላል ነገር ነው፡፡

የሳይበር ጦርነት ውሾች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን በማጥቃት ላይ ናቸው፣

 የሳይበር ጦርነት ውሾች የጨለማው ጎን ኃይሎች በዚህ ባለፈው ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ላይ የፍርሀት እና የማጠልሸት ዘመቻ በመክፈት ሰርግ እና ምላሽ አድርገው ቆይተዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ደጋፊዎች ላይ ጭንቀት፣ ፍርሀት እና ስጋት በመልቀቅ አፎቻቸውን እስከ ጆሮ ግንዳቸው ድረስ በመለጠጥ ሲገለፍጡ ተስተውለዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ደጋፊዎች ላይ ጉዳት ያደረሱ፣ ግራ ያጋቡ እና ጭንቀትን የፈጠሩ በእነዚህ ቅንነት በሌላቸው ወሬዎች፣ በተዛቡ የማወናበጃ መረጃዎች እና በሸፍጥ ህልወቶች በጨለማው ጎን ኃይሎች ፕሮፓገንዳ የተሰሩባቸው ቅጥፈቶች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባለፈው ሳምንት በይፋ አልታየም ምክንያቱም ከዩኤስ አሜሪካ ከተመለሰ በኋላ በጠና ታሟል፡፡ እናም ለሕክምና በአውሮፕላን ወደ ሳውዲ አረቢያ (የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ) ሄዷል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የደህንነት ጥበቃ ጥቃት ሰንዝሮበታል/ መርዞታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በጅግጅጋ በተፈጠረው ግጭት ላይ መግለጫ አልሰጠም ምክንያቱም ታሞ ስለነበር ነው፡፡

በዚያ የተገኘውን የነዳጅ ጥቅም በብቸኝነት ለመቆጣጠር የፌዴራል መንግስት በጅግጅጋ የጎሳ ግጭትን ለመለኮስ ይፈልጋል፡፡

የፌዴራል መንግስት በጅግጅጋ ጣልቃ መግባቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አምባገነን መሆኑን ያረጋግጣል፡፡

የፌዴራል መንግስት በጅግጅጋ ለዜጎች ጥበቃ ባለማድረጉ ምክንያት ሕዝቦች ለሞት እና እልቂት ተዳርገዋል፡፡

የፌዴራል መንግስት በጅግጅጋ ለተቃጠሉ ቤተክርስቲያኖች ተጠያቂ ነው፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት የነበረው አብዲ መሀመድ ኦማር (አብዲ ኢሌ) በቁጥጥር ስር በመዋል ለፍትህ ሊቀርብ አይችልም፤ ምክንያቱም ያለመከሰስ መብት አለው፡፡

አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆኑ ምክንያት ኢትዮጵያ የጨነገፈች ሀገር ሆናለች የሚሉት ከበርካታዎቹ ጥቂቶች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ በብሄራዊ አንድነት መንግስት ብቻ መጠበቅ ትችላለች (የጨለማው ጎን ኃይሎች ብቸኛ ገዥዎች በሆኑበት ሁኔታ) ፡፡

ቅንነት የሌላቸውን ወሬኞች እና የሀሰት የማወናበጃ መረጃ አሰራጭዎችን እውነታ ማረጋገጥ፣

የሳይበር ጦርነት አራማጅ ውሾች ምንም ዓይነት ማስረጃ አይሰጡም፡፡ ፍላጎቶቻቸውን የሚደግፍ ምንም ዓይነት ነገር አያሳዩም፡፡ ሆኖም ግን በበርካታ የማይጠበቁ ኢትዮጵያውያን አእምሮዎች እና ህሊናዎች ውስጥ አደጋን ያስቀምጣሉ፡፡

ቅንነት የሌላቸውን ወሬዎች፣ የሀሰት የተዛቡ የማወናበጃ መረጃዎችን እና የሸፍጥ ህልወቶችን በማሰራጨት እና በመጠቀም ዘለቄታዊ በሆነ መልኩ የስነ ልቦና ጦርነት በማካሄድ የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደሚያዳክሙ እና እንደሚረቱ ያስባሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ አሜሪካ ጉዞ ባደረጉበት እና በሚመለሱበትም ጊዜ ቢሆን የደህንነት የጥበቃ አባሎቻቸው እርሳቸውን የሚጎዳ ምንም ዓይነት ሙከራ እንዳላደረጉ እውነታውን አውቃለሁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከዩኤስ አሜሪካ ከተመለሱ በኋላ እንዳልታመሙ እና ወደ ሳውዲ አረቢያም እንዳልሄዱ እውነታውን አውቃለሁ፡፡

ሁሉም ነገሮች ቅንነት የጎደላቸው የፈጠራ ወሬዎች ወይም ደግሞ የበለጠ በትክክል ለመግለጽ የቆሻሻ ስብስቦች ናቸው!

ስለጅግጅጋ የሀሰት መረጃ የማወናበጃ ዘመቻ እውነታነት ልዩ ትኩክረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ የጅግጅጋ የሀሰት መረጃ የማወናበጃ ዘመቻ ዋና ዓላማ የጨለማው ጎን ኃይሎች ከድርጊቱ ጀርባ በመቆም በጅግጅጋ ግጭት እና ሰብአዊ ቀውስ ለመፍጠር እያካሄዱት ያለው ሸፍጥ በሕዝብ ዘንድ እንዳይታወቅ ለማድረግ እያደረጉት ያለ የእግር ኮቴ እና የጣት አሻራ የማጥፋት ዘዴ ነው፡፡ ይህ ያገጠጠ እና ያፈጠጠ እውነታ በጅግጅጋ መንገዶች የሚራመዱ ወንዶች እና ሴቶች በግልጽ የሚያውቁት እና የሚናገሩት እውነታ ነው፡፡

በቅርቡ በቁጥጥር ስር የዋለው እና የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት የነበረው አብዲ ኢሌ በቁጥጥር ስር እንዳይውል የጨለማው ጎን ኃይሎች ሲያደርጉት የነበረው እኩይ ጥረት እነዚህ ኃይሎች በሰው ልጆች ላይ ወንጀል እንዲፈጸም ሲያደርጉ እንደቆዩ በእራሳቸው ላይ የመሰከሩ ፍጡሮች ስለመሆናቸው በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል በቅድመ አብይ በነበረው ዋና እና አስፈሪ የደህንነት እና ጥበቃ ልዩ ኃይል አማካይነት በቀጥታ ችግር ለመፍጠር ጥረት አድርጓል፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በቅርቡ ባወጣው ዘገባው እንዲህ ብሏል፣ “የኢትዮጵያ መንግስት [የህወሀት አገዛዝ] እ.ኤ.አ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በሶማሊ ክልል መጠነ ሰፊ የሆኑ የሰብአዊ መብቶችን የሚጥስ ልዩ ፖሊስ የሚባል ኃይል መስርቷል፡፡ ይህ ልዩ ፖሊስ ተጠሪነቱ አብዲ ኢሌ እየተባለ ለሚጠራው ለክልሉ ፕሬዚዳንት ለአብዲ መሀመድ ኦማር ነው፡፡“

እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት/ተመድ ቀደም ሲል በዚህ ዓመት እንዲህ በማለት ደምድሟል፣ በሶማሊ እና በኦሮሞ ማህበረሰቦች መካከል በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ድንበር ተከስቶ በነበረው ውጥረት እና ግጭት ሳቢያ 1.070 ሚሊዮን ሰዎች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን በውስጣዊ ችግሩ የተፈናቀሉት ዜጎች ቁጥር ከ85 በመቶ በላይ ይሆናል“  ብሏል፡፡ በሶማሊ እና በኦሮሞ ማህበረሰቦች መካከል በተደረገው ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተገድለዋል፡፡

ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ንጹሀን ዜጎች እንዲፈናቀሉ እና በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ እንዲገደሉ እና እንዲቆስሉ ለተደረገበት ወንጀል ተጠያቂው ማን ነው?

ለመሆኑ በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል ጅግጅጋን ጨምሮ እየተካሄደ ባለው ግጭት እና ጥላቻ ላይ ነዳጅ እያርከፈከፈ እና ግጭቱን እና ጥላቻውን በገንዘብ እየደገፈ ከጀርባ ሆኖ አይዟችሁ አለሁ እያለ እኩይ ድርጊቱን በማስፈጸም ላይ የሚገኘው ማን ነው?

ለዚህ ጥያቄ ቁርጥ ያለው መልስ አብዲ ኢሌ እራሱ በአንደበቱ አሁን በቅርቡ ካመነው፣ ከተናገረው እና እንዲህ ከሚለው ዝባዝንኬ ኑዛዜው ቁልጭ ብሎ ይገኛል፡፡ እነሆ!

“የህወሀት መሳሪያ ነበርኩ፡፡ እነርሱ [ህወሀቶች] ሁልጊዜ በጭንቅላቴ ላይ ጠብመንጃ ደግነውብኝ ነው የቆየሁ፡፡ ማንኛውንም የክልሉን በጀት ሳንቲም ሳትቀር በእጅ መንሻነት ስሰጥ ነበር የቆየሁት… ዛሬ ሁሉንም ነገር እነግራችኋለሁ፡፡ ለመግደል ወይም ሰብአዊ ቀውስ ለመፍጠር ማንኛውም ትዕዛዝ የሚመጣው ከእነርሱ [ከህወሀቶች]  ነበር፡፡ ግድያዎችን ሁሉ የሚያዝዙ እነርሱ እራሳቸው [ህወሀቶች]  ነበሩ፡፡ እራሴን ለመጠበቅ ስል ሁሉንም ነገር ሳደርገው ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ ውስጥ ይፈጸም የነበረው እያንዳንዱ እልቂት በጌታቸው አሰፋ [በቁችት ቃል ነበር ይህንን የተናገረው] ትዕዛዝ ነበር የሚፈጸመው፡፡ እርሱ [ጌታቸው አሰፋ፣ የህወሀት በጥባጭ እና ደም የጠማው የመረጃ እና ደህንነት ዋና ኃላፊም] በኦሮሞ- ሶማሊ ግጭት ላይ እጁ አለበት፡፡ ኦሮሞዎች እና ሶማሊዎች ከበስተጀርባ ሌላ ኃይል ከሌለ በስተቀር ወደ ጦርነት ይሄዳሉ ብላችሁ ታስባላችሁን? ” (አጽንኦ ተሰቷል፡፡)

አሁን የጨለማው ኃይል የሳይበር ጦርነት ውሾች በሶማሊ ክልል ለረዥም ጊዜ በእራሳቸው እብሪት ሲፈጽሟቸው የቆዩአቸውን ሰብአዊ ወንጀሎች እና በአሁኑ ጊዜም ከኢትዮጵያ ሕዝብ በዘረፉት ገንዘብ ቅጥረኞችን በመግዛት ቀጥለውበት ካለው የውክልና የእልቂት ጦርነት እራሳቸውን ነጻ በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ተጠያቂ ለማድረግ ሲውተረተሩ እና ሲዳክሩ ይታያሉ፡፡

ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባ! የእምዬን ወደ አብዬ ማለት መሆኑ ነው፡፡

የጨለማው ጎን ኃይሎች  በድንቁርናችን፣ በሞኝነታችን እና  በአስፈራሪዎች እንዴት እንደምንስተናገድ እየተጫወቱብን ያለ ጨዋታ፣

የጨለማው ጎን ኃይሎች ከአሜሪካ የትንሿ ዶሮ ተረት ትምርትን በመውሰድ ቆሻሻ እና የዉሸት ወሬዎችን፣ የሀሰት፣ የተዛቡ የማወናበጃ መረጃዎችን እና የሸፍጥ ህልወቶችን ለኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በመመገብ ኢትዮጵያውያን በማህበራዊ መገናኛዎች/ሜዲያዎች በመሞኘት ላይ ያሉትን መገንዘብ እንችላለን፡፡

አንድ ቀን ትንሿ ዶሮ በጫካዎች መካከል ትጓዝ ነበር፡፡ በመካከሉ ከዛፉ ላይ ፍሬ ይወድቅ እና ጭንቅላት ይመታዋል፡፡ ደንግጣ “ኦ፣ ኦ ሰማዩ ወደቀ፡፡” ብላ በሩጫ ወደፊት በመገስገስ ስለዚህ ጉዳይ ለአንበሳ መናገር አልብኝ አለች፡፡

በመንገድ በመሮጥ ላይ እያለች ሄኒ ፔኒ የተባለች ዶሮን አገኘቻት እና ሰማይ መውደቁን ነገረቻት፡፡ ሄኒ ፔኒን ትንሽዋን ዶሮ እንዲህ በማለት ጠየቀቻት፣ “ እንዴት አወቅሽ ሰማይ መውደቁን?“ ትንሿ ዶሮ እንዲህ በማለት መለሰች፣ “ጭንቅላቴን መታኝ፣ እናም ከሰማይ ስባሪ ሌላ ሊሆን አይችልም” አለች።

ስለዚሁ ጉዳይ ለአንበሳ ለመንገር በመሮጥ ላይ እንዳሉ ከደኪ ሉኪ ዶሮ ጋር ተገናኙ፡፡ “ሰማይ ወደቀ” አለች ሄኒ ፔኒ፡፡ ስለዚሁ ጉዳይ ለአንበሳ ለመናገር ነው በመጓዝ ላይ ያለነው አለች፡፡

ደኪ ሉኪ እንዲህ በማለት ጠየቀች፣ “ይህንን እንዴት አወቃችሁ?“ ሄኒ ፔኒ እንዲህ በማለት መለሰች፣ “ትንሿ ዶሮ ከጭንቅላቷ አንድ ነገር መታት፡፡“

ደኪ ሉኪ ከሩጫው ጋር በመቀላቀል ፎክሲ ሎክሲ ምትባል ቀበሮን እስከሚያገኙ ድረስ አብረው ተጓዙ፡፡ ፎክሲ ሎክሲም እንዲህ የሚል ጥያቄ አቀረበች፣ “እናንተ ሁላችሁም ወዴት ነው የምትሄዱት?“

ደኪ ሉኪ እንዲህ አለች፣ “ሰማይ ወድቋል፤ እናም ስለዚሁ ጉዳይ ለአንበሳ ለመናገር ነው በመጓዝ ላይ ያለነው፡፡“

ፎክሲ ሎክሲ እንዲህ በማለት ጠየቀች፣ “ለመሆኑ አንበሳው የት እንደሚኖር ታውቃላችሁ?“ አንበሳው የት እንደሚኖር አንዳቸውም የሚያውቁት ነገር የለም፡፡  “እኔ አውቃለሁ፡፡ ከእኔ ጋ ኑ፣ እኔ አንበሳው የት እንደሚኖር መንገዱን አሳያችኋለሁ“ አለች ፎክሲ ሎክሲ፡፡ እናም ወደ አንበሳው ጎሬ በአንድነት ሆነው ሄዱ፡፡ ሁሉም በአንድነት ገቡ ሆኖም ግን ከዚያ አንዳቸውም በፍጹም ሳይወጡ ቀሩ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ሰላማዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ለመቀልበስ የጨለማው ጎን ኃይሎች በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ደጋፊዎች ላይ የትንሿ ዶሮ ጉዳይ ነው፡፡

እነዚህ አስፈራሪዎች በፌስ ቡክ ላይ አንድ ቁራጭ የዉሸት ወሬን በመልቀቅ እና እንደ ትንሿ ዶሮ ህዝብን ያተራምሳሉ። ሁኔታውን በሞኝነት በማራገብ “ኦ በአብይ አህመድ ላይ ሰማይ ወደቀ ይላሉ፡፡ ታሟል፡፡ ሳውዲ አረቢያ ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ለዓለም ማሳወቅ አለብን፡፡ የዓለም ፍጻሜ እየመጣ ነው” ይላሉ፡፡

በጣም የሚያስደንቀው ነገር የጨለማው ጎን ኃይል አስፈራሪዎች በእያንዳንዷ ቀን ቅንነት ስለሌላቸው ወሬዎቻቸው፣ ስለሀሰት እና የተዛቡ የማወናበጃ መረጃዎቻቸው ማታለል ጉዳይ መንገድ አላቸው፡፡

በየዕለቱ ከእኛ ከመካከላችን የሚሞኙ ወገኖቻችንን ሲያወናበዱ ይኖራሉ፡፡

ከኢትዮጵያውያን ትንሿ ዶሮች ጋር የእኔ የተለመዱ ውይይቶች፣

እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ግን በርካታ ኢትዮጵያውያን በጨለማው ጎን ኃይሎች ቆሻሻ እና ቅንነት የሌላቸው ወሬዎች እና የሀሰት እና የተዛቡ የማወናበጃ መረጃዎች ሰለባ ሆነዋል፡፡ ምክንያቱም በሰከነ መንገድ የአእምሯቸውን የማሰብ ክህሎት በመጠቀም ነገሮችን ከመመርመር ይልቅ ስሜታዊ መሆንን መርጠዋል፡፡

ብዙዎቹ ያዙኝ ልቀቁኝ በማለት ከልባቸው እና ከአንጀታቸው እያለቀሱ እኔን ጠይቀውኛል፡፡

እነርሱን ካዳመጥኩ በኋላ እንዲህ የሚሉ ጥቂት ጥያቄዎችን ጠየቅሁ፡

ጥ. “የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የደህንነት ጥበቃ አባላት እርሳቸውን የመመረዝ ሙከራ አድርገዋል የሚለውን መረጃ ከየት አገኘሽው?”

መ. “ስለዚያ ጉዳይ በፌስ ቡክ እንዳገኙት ይናገራሉ፡፡ እኔ በዩቱዩብ አንድ ነገር ተመልክቻለሁ፡፡”

ጥ. “በፌስ ቡክ ላይ ስለዚህ ጉዳይ እየተናገረ ያለው ማን ነው? ቪዲዮውን የሰራው ማን ነው?”

መ. “እኔ አላውቅም፡፡ ሕዝብ ነው፡፡ በእርግጥ እኔ እራሴ በግሌ በፌስ ቡክ አላየሁትም፡፡ ሆኖም ግን በቪዲዮ ሰምቸዋለሁ፡፡”

ጥ. “ታሪኩ እውነት ወይም ውሸት ስለመሆኑ ለመወሰን እንድትችይ ሌሎችን የመረጃ ምንጮች ለማየት ሞክረሻል?”

መ. “አንተን ነው የጠራሁህ ምክንያቱም እውነት ከሆነ አንተ ትነግረኛለህ ብዬ አስባለሁ፡”

ጥ. “እኔ የምለውን ማንኛውንም ነገር የምታምኝው ለምንድን ነው?”

መ. “ጸጥ፡፡“

ጥ. “በማህበራዊ መገናኛዎች/ሜዲያዎች የምትሰሚውን ወይም የምታነቢውን እያንዳንዱን ነገር ታምኛለሽ?”

መ. “ደአያይ! የለም፡፡ በየዕለቱ ስለዚሁ ጉዳይ ስለሚወራ ይኸ ነገር እውነት መሆን አበለት ብዬ አሰብኩ፡፡”

ጥ. “ይህ ትረካ ለአንቺ ትርጉም ይሰጥሻል?”

መ. “የለም አይሰጠኝም፡፡ ሆኖም ግን እያንዳንዱ ሰው ስለዚሁ ጉዳይ ነው የሚያወራው፡፡ ስለዚህ እውነት አይደለምን?”

የእኛ ችግር፡ የእንስሳት አስተሳሰብ እና በቡድን ማሰብ፣

የእንስሳት አስተሳሰብ (herd  mentality) ወዴት እንደሚሄድ የማያውቅ እና መንጋውን ብቻ ተከትሎ እንደሚሄደው በግ ዓይነት ነው ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ምክንያቱም መንጋ የሚሰራው እንደዚህ ዓይነት ድርጊት ነው፡፡ ሕዝብ በስሜት ከሚነዳ ይልቅ በምክንያታዊነት እና በትክክለኛ አስተሳሰብ መመራት አለበት፡፡ ለምን የሚሉትን ጥያቄዎች ከመጠየቅ ይልቅ ዝም ብሎ በነሲብ መንጋውን ይከተላሉ፡፡

የቡድን አስተሳሰብ (group think) ቡድኑ ትክክለኛ ነው በሚል እምነት ግለሰቦች የእራሳቸውን አቋም የሚይዙበት ሂደት ነው በማለት መግለጽ ይቻላል፡፡ ወሳኝ የሆነ ምክንያት ወይም ደግሞ ማስረጃ ሳይኖር በሀሳብ ላይ ብቻ ይስማማሉ፡፡

ደንቆሮ ሰዎች በቀላሉ በቁጥጥር ስር ሊውሉ እና ለሚፈለገው ዓላማ ሊፐወዙ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም በቂ የሆነ እውቀት የሌላቸው በመሆናቸው በይበልጥ የማገናዘብ ክህሎት የላቸውም፡፡ እንዲሁም ትክክለኛውን መልስ ለማግኘት ትክክለኛው ጥያቄ እንዴት መጠየቅ እንዳለበት ማወቅ አለባቸው፡፡

የጨለማው ጎን ኃይሎች በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና በሰላማዊ የለውጥ ሂደታችን ላይ ቅንነት የሌላቸው ወሬዎች እና የሀሰት እና የተዛቡ የማወናበጃ መረጃዎችን በተቀናጀ እና በታቀደ መልኩ በማሰራጨት ላይ የሚገኙት እኛ ደንቆሮዎች በመሆናችን ምክንያት ብቻ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ከዚህም በላይ የከፋን በመሆናችን ጭምር እንጅ፡፡

ይህንን ጉዳይ ከዚህ ቀደም ለበርካታ ጊዜ ስናገረው ነበር፣ አሁንም እናገራለሁ፡፡

የጨለማው ጎን ኃይሎች ለመግዛት እነርሱ ቀልጣፋዎች እና ብሩሆች እንዲሁም የተመረጡ እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ፡፡

የስትራቴጅክ ዕቅድ አሳቢዎች እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ፡፡ በእነርሱ አሰተሳሰብ እኛ ምንም ነገር የማናደርግ ጅሎች እንከፎች እንደሆንን አድርገው ይቆጥራሉ፡፡

እነርሱ ጠንካሮች እኛ ደካሞች እንደሆንን አድርገው ያስባሉ፡፡

እነርሱ ብቻ ደፋሮች እና እኛ ደግሞ ዝም ብለን የምናነፈንፍ ቦቅቧቃ ፈሪዎች እንደሆንን አድርገው ያምናሉ፡፡

እኛ አህዮች፣ አስተሳሰበ ድሁሮች፣ የወረድን ዝቅተኞች፣ ሞኞች እና ደደቦች እንደሆንን አድርገው ያስባሉ፡፡

በዚህ በሳይበር ዘመን ኢትዮጵያውያን መልካም አእምሯዊ አስተሳሰባቸውን ይዘው ለመቀጠል በጥንቃቄ በማሰብ በየጊዜው ከሚደርስ ከመረጃ የመጥለቅለቅ ጎርፍ ፍሬውን ከገለባ መለየት አለባቸው፡፡

ኢትዮጵያውያን በትክክል እንደሚያስብ ሰብአዊ ፍጡር ስለሚያነቡት እና ስለሚሰሙት ነገር ትንሽ ጥያቄ ማቅረብ አለባቸው፡፡

በትንሹ የሚያነቡት እና የሚሰሙት ነገር ትንሹን የማሳለፊያ ፈተና ማለፉን መጠየቅ አለባቸው፡፡

በሚያነቡት እና በሚሰሙት ነገር ላይ ሁልጊዜ እንደ አይጥ ወይም ደግሞ የበለጠ ለመግለጽ የጅብ ጠረን ማሽተት አለባቸው፡፡

ያገኙትን መረጃ ወደኋላ በመሄድ መገምገም እና ምክንያታዊ መሆኑን ለመወሰን መሞከር፣ መረጃው ድጋፍ የሚሆን ማስረጃ ያለው ስለመሆኑ እና በተራ አስተሳሰብም ሊሆን የሚችል እና የማይችል መሆኑን ማገናዘብ ነው፡፡

ዜጎች በተጠራጣሪነት መርህ መኖር አለባቸው፡፡ አሳማኝ የሆነ ምክንያት ማስረጃ እና አስገዳጅ አመክንዮ ከሌለ በስተቀር ማንኛውንም የሰሙትን እና ያነበቡትን ሁሉ ነገር ሁሉ ማመን የለባቸውም፡፡

ከዚህም የበለጠ ማንኛውንም የሚሰሙትን እና የሚያነቡትን ነገር ለማጣራት ወደ ማህበራዊ መገናኛዎች/ሜዲያዎች መውሰድ አለባቸው፡፡

የጨለማው ጎን ኃይሎች የሆኑትን የኢንተርኔት ጅቦችን እንዴት እንደምንዋጋ፣

እ.ኤ.አ መስከረም 2016 ዓ.ም የውሸት እና የሀሰት የማወናበጃ መረጃን በእውነት ዘመቻ ድል እንድናደርግ የሚል ጥሪ አቅርቤ ነበር፡፡

ቅንነት የሌላቸው የውሸት መረጃዎች ሀገሪቱን ወዳልተረጋጋ አደገኛነት ሁኔታ እንደሚወስዳት በመግለጽ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተሰጠው የቅርብ ጊዜ መግለጫ የኢትዮጵያ ማህበራዊ መገናኛዎች ተጠቃሚዎች ዜጎቻችሁን ለማስተማር እና የሀሰት እና የማወናበጃ መረጃዎችን ለማስወገድ ጠንክራችሁ እንዲትሰሩ የቀረበ አስቸኳይ የድርጊት መርሀ ግብር ጥሪ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እነዚህን የሀሰት፣ የተዛቡ መረጃዎችን እና የሸፍጥ ህልወቶችን የሚያሰራጩትን የቅጥፈት መረጃ ጦርነቶች እንዴት እንደምንዋጋቸው አልገለጹም፡፡

ሆኖም ግን ለማህበራዊ መገናኛዎች እና ለኢንተርኔት መረጃዎች ጦርነቶች እንዲህ የሚሉ “የጦር ዕቅዶች” አሉኝ፡፡ እነርሱም፣

1ኛ) የሀሰት፣ የተዛቡ መረጃዎችን እና የሸፍጥ ህልወቶችን በማህበራዊ መገናኛዎች በመልቀቅ የመረጃ ጦርነቶችን የሚከፍቱብንን ለመዋጋት ተመራጩ መሳሪያ እውነት ብቻ መሆን አለበት፡፡ የጨለማው ጎን ኃይሎች እውነትን መጋፈጥ በፍጹም አይችሉም፡፡ ላለፉት 13 ዓመታት በእያንዳንዱ ሳምንት አንድም ሳምንት ሳላቋርጥ እውነትን ለእነርሱ ስሰብክ ቆይቻለሁ፡፡ አንዳቸውም ያቀረብኩትን እውነት ሊሟገቱ አልቻሉም!

ስለሆነም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና በሰላማዊ የለውጥ ሂደታችን ላይ እያራመዱት ስላለው ስለእነርሱ ሀሰት፣ ውሸት እና ተራ ቅጥፈት ሌላ ምንም ነገር ሳይሆን እውነትን ለሁሉም በመናገር መዋጋት አለብን፡፡

2ኛ) አንድ የቀድሞ አባባል እንዲህ ይላል፣ “ውሸት ዓለምን ስትዞር እውነት ገና ጫማዋን ታስራለች፡፡ ስለሆነም የጨለማውን ጎን ኃይሎች ውሸት፣ ሁሉንም ቅጥፈት፣ እና ተራ ቅጥፈት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሁሉ በማጋለጥ መዋጋት አለብን፡፡

3ኛ)  መልካም አስተሳስብ እና እምነት ያላቸውን ዜጎቻችንን ማስተማር አለብን፡፡ ማንዴላ እንደህ ብለው ነበር፣ “ትምህርት ዓለምን ለመለወጥ ልትጠቀሙበት የምትችሉት ጠንካራ መሳሪያ ነው፡፡“

ቁጣችንን እንግለጽ፡፡ ዜጎቻችንን ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስለሚሰሩት መልካም ነገር እና የሰላማዊ ለውጡ ስለሚያስገኘው ውጤት ብቻ አይደለም ማስተማር ያለብን፡፡ ሆኖም ግን ከዚህም የበለጠ በጨለማው ጎን ኃይሎች ሲሰሩ ስለነበሩት የሰብአዊ መብቶች ድፍጠጣም ማሳወቅ እና ማስገንዘብ ተገቢ ነገር ነው፡፡

ለማስተማር እና ለማጠናከር የማህበራዊ መገናኛዎችንን መጠቀም አለብን፡፡ ከጨለማው ጎን ኃይሎች ጋር የስድብ እና የዘለፋ ልውውጦችን ማድረግ በከንቱ ጊዜን እንደሚያጠፋ፣ የህይወትን ጣዕም እንደሚያጠፋ ቆም በማለት በሰከነ መንፈስ ማሰብ ይኖርብናል፡፡ ወገኖቻችንን ለማስተማር እና ህብረት እንዲኖር ለማድረግ የማህበራዊ መገናኛዎችን መጠቀም ይኖርብናል፡፡

4ኛ) የጨለማውን ጎን ኃይል አሉታዊ መልዕክቶች በእራሳችን አዎንታዊ መልዕክቶች መቀየር አለብን፡፡ አንድ ሰው በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር፣ “በየዕለቱ 1,440 ደቂቃዎች አሉ፡፡ ይህም ማለት አዎንታዊ ፋይዳ ያለው ነገር ለማምጣት 1,440 ዕለታዊ አጋጣሚዎች አሉን ማለት ነው፡፡“ በፌስ ቡክ እና በትዊተር ለ10 ደቂቃ ወይም ደግሞ ለአንድ ሰዓት ያህል ስንቆይ እኛን ለሚያነቡን አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖራቸው እናድርግ፡፡ አሉታዊ ሃይላችንን በመጠቀም እና ለኢንተርኔት ጂቦች በመመገብ ጊዚያችንን በከንቱ አናጥፋ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን እና ሰላማዊ የለውጥ ሂደታችንን ለማደናቀፍ ሲሉ የጨለማው ጎን ኃይሎች በእያንዳንዱ አሉታዊ ቅንነት የሌላቸው ወሬዎች እና የውሸት የማወናበጃ መረጃ ባሰራጩ ቁጥር እኛ ደግሞ ቢያንስ ሶስት አዎንታዊ የሆኑ መረጃዎችን መልቀቅ አለብን፡፡

5ኛ) የጨለማው ጎን ኃይል የኢንተርኔት ጅቦችን አትመግቡ፡፡ የጨለማው ጎን ኃይሎች የእኛን ቁጣ፣ ሀዘን፣ ፍርሀት እና ስጋት ይመገባሉ፡፡ ብርህን የሆነውን ጎናችንን ብቻ እናሳያቸው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና በሰላማዊው የለውጥ ሂደት ደስተኛ የመሆናችንን እውነታ እየነገርን እናሸማቃቸው፡፡

6ኛ) ስሜታዊ ምሁርነትን ማዳበር አለብን፡፡ የእራሳችንን ስሜታዊነት እና በአቅርቢያችን ያሉትን የሌሎችን ስሜታዊነት ለመቆጣጠር የሚያስችል ችሎታ ማዳበር አለብን፡፡ አንድ ሰው አንድ የማይረባ ነገር በተናገረ ብቻ ስሜታዊ በመሆን ዝም ብሎ በመቀበል ስሜታዊ ሆነን ሌሎችንም በዙሪያችን የሚገኙትን ወገኖች ስሜታዊ በማድረግ ችክን ሊትልን መሆን የለብንም፡፡ በጨለማው ጎን ኃይሎች ለዘለቄታ የስሜታዊ መፐወዣ ዒላማ መሳሪያ እንዳንሆን የእራሳችንን ንቃተ ህሊና ከፍ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ በቀላሉ የምንሞኝ እና ጅሎች አንሁን፡፡ በጨለማው ጎን ኃይል የኢንተርኔት ጅቦች ማታለያ በቀላሉ ሀሳባችን የሚሰረቅ መሆን የለብንም፡፡

7ኛ) ለእራሳችን ለማሰብ እንማር፡፡ የጨለማው ጎን ኃይል የኢንተርኔት ጅቦች የእኛን አእምሮዎች እና ልቦች እንዲቆጣጠሩ በፍጹም መፍቀድ የለብንም፡፡ አንድ ጊዜ ወይም ደግሞ ሁለት ጊዜ ሊያሞኙን ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን እንዲህ በሚል በአንድ በዱሮ አባባል መኖር የለብንም፣ “አንድ ጊዜ ብታሞኘኝ አንተ ታፍራለህ፤ ሁለት ጊዜ ብታሞኘኝ ግን እኔ ማፈር አለብኝ፡፡“

8ኛ) ሰይጣናዊነት በፍጹም አይተኛም፡፡ የጨለማውን ጎን ኃይል ሰይጣናዊ ኃይሎች ድል ለማድረግ የሚከፈለው ዋጋ ምንጊዜም ነቅቶ መጠበቅ ብቻ ነው፡፡ ይህም ማለት በጨለማው ጎን ኃይሎች ላይ እረፍትየለሾች፣ ቁጡዎች፣ አይበገሬዎች፣ የማያወላውሉ እና አንድ ዓላማ ያላቸው መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንንም ጉዳይ ባለፉት 13 ዓመታት በተግባር አረጋግጨዋለሁ!

9ኛ) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይቅር እንባባል ይላሉ፡፡ ትክክል ናቸው፡፡ እንዲህ ተብሏል፣ “ጠላቶችህን ሁልጊዜ ይቅር በላቸው፡፡ እንደዚህ አድርጎ የሚያበሳጫቸው ምንም ነገር የለም፡፡“

ስለሆነም ለጨለማው ጎን ኃይሎች ለጋስ መሆን አለብን፡፡ እነርሱን ለመረዳትም መሞከር ይኖርብናል፡፡ በአንድ ወቅት የዓለሙ ሁሉ ጌቶች የነበሩ በሌላ ጊዜ ደግሞ በመሬት ላይ በስሜት የሚንፈራገጡ፣ የተናቁ እና የሚያሳዝኑ ምስኪኖች መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆን እስቲ ልዩነቱን ለመገንዘብ እንሞክር፡፡

10ኛ) ለጨለማው ጎን ኃይሎች ለመቀበል ሊቃወሙት የማይችሉት እና እንዲህ የሚል ስጦታ እንስጣቸው፣ “እነርሱ ስለእኛ ውሸት መናገርን የሚያቆሙ ከሆነ እኛም ስለእነርሱ እውነት መናገራችንን እናቆማለን፡፡“ ይኸ ጉዳይ ፍትሀዊ ስምምነት ነው እላለሁ፡፡

11ኛ) ከጨለማው ጎን ኃይሎች ጋር በግንኙነት መረብ/ኢንተርኔት ውስጥ አትዋኝ፡፡ ይኸ አባባል በርናንድ ሻው በአንድ ወቅት ስለአሳማ እንዲህ በማለት ከተናገሩት ጋር መሳ ለመሳ ነው፣ “ከከአሳማ ጋር በፍጹም ትግል አትጋጠም የሚል ትምህርት ተምሪያለሁ፡፡ ትግል ብትጋጠም ግን አንተ ቆሻሻ  ጭቃ ትሆናለህ ዓሳማው ግን ይህንን ይወደዋል፡፡“ ነበር ያሉት፡፡

ከጨለማው ጎን ኃይል የኢንተርኔት ጅቦች ጋር በፍጹም የመጠለሻሸት ስራ እና የጥላቻ ድርጊትን አትፈጽም፡፡ ምክንያቱም ከዚህ የንግድ መስተጋብር ውስጥ የምትከስረው አንተ ነህ፡፡

12ኛ) የዩቲዩብ የግንኙነት መስመሮችን በመጫን በፍጹም ሰለባ አትሁን፡፡ ምክንያቱም ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ቀስቃሽ የሆኑ የቪዲዮ ምስሎችን የሚለቁ ቆሻሻ የዩቲቢ የግንኙነት መስመሮች አሉ፡፡ የቪዲዮ ምስሎቻቸውን እንዲህ የሚል ርዕስ እና ስያሜ ይሰጧቸዋል፣ “ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከምግብ ምረዛ ሙከራ ለጥቂት አለመጠ“፡፡ ለዚህ ዋናው ዓላማቸው ወደ ቆሻሻው ዩቲዩብ የግንኙነት መስመሮች እንድትገቡ ለማድረግ ነው፡፡ የእነርሱን የዩቲዩብ ቆሻሻ የግንኙነት መስመሮችን በተጫናችሁ ቁጥር እነርሱ ገንዘብ ያገኛሉ፡፡ እናንተ ለባችሁ ይቆስላል። እያንዳንዱ ሰው እነዚህን ቆሻሻ የዩቲዩብ የግንኙነት መስመሮች እንዳይጫን እማጸናለሁ!

ለማህበራዊ መገናኛ ተዋጊዎች የቀረበ ጥሪ፣

ላለፉት 13 ዓመታት በሳምንታዊ ትችቶቼ የጨለማው ጎን ኃይሎችን ተዋግቻለሁ፡፡ አንድም ሳምንት ሳላሳልፍ በሳምንት አንድ ጊዜ በማወጣቸው አንዳንድ ጊዜ ከዚህ የበለጠ በሚወጡት ትችቶቼ ውሸቶቻቸውን፣ ቅንነት የሌላቸውን የሀሰት ወሬዎቻቼውን፣ የተዛቡ የማወናበጃ መረጃዎቻቼውን እና የሸፍጥ ህልወቶቻቼውን በጽናት ስዋጋ ቆይቻለሁ፡፡

በአሁኑ ጊዜ ደግሞ እነዚህ የጨለማው ጎን ኃይሎች የጥላቻ፣ የክፍፍል፣ የብጥብጥ እና የትርምስ መልዕክቶቻቸውን ለማስተላለፍ መጥፎውን ፊታቸውን ወደ ማህበራዊ ግንኙነቶች እና ወደ ድረ ገጽ የግንኙነት መስመሮች አዙረዋል፡፡

የጨለማውን ጎን ኃይሎች በፌስ ቡክ፣ በትዊተር እና በዩቲዩብ የግንኙነት መስመሮች ለመዋጋት ለሁሉም የኢትዮጵያ የማህበራዊ መገናኛ/ሜዲያ ተዋጊ ወገኖቼ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በጨለማው ጎን ኃይሎች አዲስ ጦርነት ተከፍቶብናል፡፡

ይኸ ልዩ የሆነ ጦርነት ነው፡፡

የስነ ልቦና ጦርነት ነው፡፡ የስነ ልቦና መጉዳት እኛን እንገታችንን እንድንደፋ ለማድረግ የሚደረግ የስነ ልቦና ጦርነት ነው፡፡ አእምሮን ለመፐወዝ፣ ልብን ለመስበር፣ በእራስ መተማመንን ለማሳጣት እና ህሊናን ለማጥፋት የሚደረግ ጦርነት ነው፡፡

በመሪዎቻችን መካከል ጥርጣሬን ለመፍጠር የሚደረግ ጦርነት ነው፡፡ በሰላማዊ የለውጥ ሂደታችን ላይ አጠራጣሪ ነገሮችን ለመፍጠር የሚደረግ ጦርነት ነው፡፡

በፌስ ቡኮቻችን፣ በትዊተር ገጾቻችን እና በዩቲዩቦቻችን አማካይነት በሳይበርስፔስ፣ በትምህርት ቤቶች፣ በኮሌጆች፣ በዩኒቨርስቲዎች፣ በመንገዶች፣ በከተማ እና በገጠራማ አካባቢዎች፣ በአምልኮት ስፍራዎች እና ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች፣ በእያንዳንዱ ጎጥ፣ መንደር፣ የገጠር ከተማ እና ከተማ ሁሉ የጨለማውን ጎን ኃይሎችን መውጋት አለብን፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን እና ባለፉት በርካታ ወራት በኢትዮጵያ ውስጥ ያመጡትን ሰላማዊ የለውጥ ሂደት ለምትደግፉ ሁሉ ከጨለማው ጎን ኃይሎች ጋር በሳይበር ስፔስ የጥላሸት መቀባባት ባህር ውስጥ ሳይገባ ወይም ደግሞ የሳይበር ዘራፊ ወሮበሎችን ሳናስፈራራ ሆኖም ግን በሕዝባዊ ውይይቶች እና በማህበራዊ መገናኛዎች ኢትዮጵያውያንን በማስተማር፣ በማንቃት እና ከፍ ወዳለ የሰለጠነ ደረጃ በማድረስ፣ ጓዳዊነት፣ መከባበር ኃላፊነትን አጥብቆ በመያዝ በጨለማው ጎን ኃይሎች ላይ ድልን እድንንቀዳጅ በጎ ለምታስቡ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ሁሉ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ሰላማዊ የለውጥ ሂደት በመደገፍ ከጨለማው ጎን ኃይሎች በተቃራነኒው በመቆም ቅንነት የሌላቸውን ሀሰተኛ ወሬዎች፣ የውሸት እና  የተዛቡ የማወናበጃ መረጃዎችን እና የሸፍጥ ህልወቶችን ለመዋጋት ኃይሎቻችንን ሁሉ አሁኑኑ እናስተባብር፡፡

ድል ለኢትዮጵያውያን!

እንደመር፣ አንቀነስ፣ እንባዛ፣ አንከፋፈል!

ኢትዮጵያዊነት ዛሬ!

ኢትዮጵያዊነት ነገ!

ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም!

 

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ነሀሴ 8 ቀን 2010 ዓ.ም     

Let’s Help PM Abiy Ahmed Fight Fake News and Disinformation!