ማስታዋሻ ቁጥር 6፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለእምነት አባቶች የሰጡት እምነትን በስራ ትምህርት!

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም 

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን (ኢኦተቤ) ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመገናኘት በስደት ከሚኖረው ከዲያስፖራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አመራሮች ጋር ዕርቀ ሰላም እንዲያወርዱ በአጽንኦ ተማጽነዋል፡፡ ይህንንም በማስመልከት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዲህ ብለዋል፡

“በኃይማኖት መሪዎች መካከል በተለያዩ  ምክንያቶች በርካታ ልዩነቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን  ሊፈቱ የማይችሉ ልዩነቶች አይደሉም፡፡ የቤተክርስቲያን መሪዎችን ያጋጠማቸው ትልቁ ችግር እነዚህ የእምነት መሪዎች የህብረተሰቡ ችግሮች ተደርገው የሚቆጠሩትን ችግሮች የእራሳቸው ችግሮች አድርገው መፍታት አለመቻላቸው ነው፡፡ ሁለቱን ቤተክርስቲያኖች ወደ አንድ ለማምጣት በግል እና ባለን መንግስታዊ የስልጣን አቅም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን፡፡ ሁላችሁም ወደፊት በማለት ለሌሎቻችን አርዓያ መሆን አለባችሁ፡፡“

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኢኦተቤ ወደ ፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲገባ ስራው የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ አጋማሽ በወታደራዊው አገዛዝ (ደርግ) ሲሆን ሙሉ በሙሉ ወደ ፖለቲካ መሳሪያነት የተቀየረው ግን አሁን በሕይወት በሌለው በመለስ ዜናዊ አገዛዝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ አምባገነናዊው ወታደራዊው አገዛዝ እ.ኤ.አ በ1974 ዓ.ም ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ እና ህብረተሰባዊነትን እንደ ስርዓት እና መመሪያው አድርጎ ባወጀ ጊዜ ኢኦተቤ ይፋ መንግስታዊ ቤተክርስቲያን የመሆን ተስፋዋ አከተመ፡፡ የኢኦተቤ መሪ የነበሩት ፓትሪያርክ በአምባገነኑ ወታደራዊው አገዛዝ ታፍነው ወደ እስር ቤት ተጋዙ፡፡ ወዲያው በማስከተልም ተገደሉ፡፡ አምባገነኑ ወታደራዊ አገዛዝ በኢኦተቤ ሲኖዶስ (የቤተክርስቲያኗን ቀኖና የሚወስን አስተዳደራዊ እና ድርጅታዊ አካል) ተቀባይነት የሌለውን እና የቤተክርስቲያኗን ቀኖና እና መርህ በመጣስ የእራሱን ፓትሪያርክ መሪ አድርጎ ሾመ፡፡ ፓትሪያርኩን ከመንበረ ስልጣኑ ማስወገድ የሚችለው ሲኖዶሱ ብቻ ነው፡፡ እናም ይህንን የቤተክርስቲያኗን ስልጣን ወደ ጎን በመጣል ወታደራዊው አምባገነን አገዛዝ ሌላ ፓትሪያርክ በመሾሙ ምክንያት አዲሱ ተተኪ ፓትሪያርክ ሕጋዊ እውቅና እንደሌላቸው ተደርገው ይቆጠሩ ነበር፡፡

የአምባገነኑን ወታደራዊ አገዛዝ በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) መወገድ ተከትሎ በወታደራዊው አምባገነን አገዛዝ ተመርጠው የነበሩት ፓትሪያርክ በጡረታ እንዲገለሉ ተደረጉ፡፡ ህወሀት የእራሱን ፓትሪያርክ በማዘጋጀት መርጦ በመንበሩ ላይ አስቀመጠ፡፡ በጡረታ የተገለሉት ፓትሪያርክ ለስደት ተዳረጉ፡፡ መሰደዳቸውን ተከትሎም ፓትሪያርኩ ለስደት የተዳረጉት በህወሀት ጫና ተገደው እንደሆ ለሕዝብ ይፋ አደረጉ፡፡ በርካታ ጳጳሶችም ፓትሪያርኩን ተከትለው በመሰደድ በኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ እውቅና ያለውን ሌላ የተለየ ሶኖዶስ በውጭ ሀገር አቋቋሙ፡፡ የመለስ አገዛዝ በወቅቱ የነበሩትን ፓትሪያርክ ማባረሩን እና እንዲባረሩ ትዕዛዝ የሰጡት በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አሁን ላይ በጸጸት እየተናገሩት መሆኑ እና ይህንንም ተከትሎ ቤተክርስቲያኗ ለሁለት የመከፈሏ ጉዳይ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ (ይህንን ጉዳይ በማስመልከት ዋለ እንግዳየሁ ስለክስተቱ እና ይህንን ተከትሎም ሲኖዶሱ ወደ ሁለት የመከፈሉን ሁኔታ በዝርዝር እና በጥልቀት አቅርበዋል፡፡)

የኢኦተቤን ፈውስ፣ ዕርቅ እና እንደገና አንድ መሆነን በመማጸን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን እና በሀገር ውስጥ ባሉት ኢትዮጵያውያን መካከል አንድነት እና እርቀ ሰላም እንዲወርድ ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለቤተክርስቲያኗ አባቶች ያስተላለፉት መልዕክት ስለአንድነታችን በተለያዩ አጋጣሚዎች ይፋ የሚያደርጓቸው እና ስለኢትዮጵያዊነታችን የሚሰብኳቸው ጉዳዮች ብቻ ሳይሆኑ ስለአምልኮም አንድነታችን መገለጫዎች ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እራሷን ለሁለት የከፈለች ሀገር እራሷን ችላ ለመቆም እንደማትችል  ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ እራሷን ለሁለት የከፈለች ቤተክርስቲያንም እራሷን ችላ ለመቆም የማትችል መሆነኗን መናገራቸውን አምናለሁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከእርሳቸው አመራር በፊት በነበሩት 27 ዓመታት ውስጥ በአገዛዙ ተከፋፍላ ስቃይ ሲደርስባት የቆየችውን ሀገር ለመፈወስ የሚያደርጉት ጥረት አንዱ አካል እንደሆነ አምናለሁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የእምነት መሪዎች ወደ አንድነት እንዲመጡ እና ሀገሪቱን በይቅርታ፣ በእርቅና እና በሰላም ጎዳና ለመምራት እያደረጓቸው ያሉትን ጥረቶች አደንቃለሁ፡፡

የኢኦተቤ የክፍፍል ሁኔታ በእኔ የግንዛቤ እይታ፣

ከጥቂት የቤተክርስቲያኗ አባቶች ጋር በመወያየት ባገኘሁት ግንዛቤ መሰረት የቤተክርስቲያኗ ለሁለት መከፈል ዋናው ምክንያት የመለስ አገዛዝ ሆን ብሎ እና በስሌት ተደግፎ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ለማድረግ እና ድጋፍ ለማግኘት በማሰብ የቀመረው ዕኩይ ምግባር ነው፡፡ የቤተክርስቲያኗ አመራሮች ምንም ዓይነት የገንዘብ ድጋፍ እንዳያገኙ የመለስ አገዛዝ እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል ይባላል፡ “ከመለስ አገዛዝ በፊት የነበሩትን ፓትሪያርክ ከመንበረ ስልጣናቸው አባር ወይም ደግሞ የቤተክርስቲያኗን እንቅስቃሴ መምራት እንዳይችሉ እና ምንም ዓይነት መፈናፈኛ እንዳይኖራቸው የገንዘብ ምንጫቸውን አድርቅ፡፡ የቤተክርስቲያኗ መሪዎች ለወደፊቱ በገንዘብ እጦት ቀውስ ውስጥ እንዲወድቁ በማድረግ እና አቅም በማሳጣት የፓቲሪያርኩን መወገድ በግድ እንዲቀበሉ ማድረግ የሚል ነው፡፡“

የመለስ አገዛዝ የእራሱን ፓትሪያርክ መርጦ በመንበረ ስልጣን ላይ ካስቀመጠ በኋላ “የወያኔ ፓትሪያርክ” በስልጣን ላይ ነው የሚል ግንዛቤ ማደግ ጀመረ፡፡ የመለስ አገዛዝ የኢኦተቤን ነጻነት ሙሉ በሙሉ በመግፈፍ የእራሱ የፖለቲካ ክንፍ በማድረግ ለአገዛዙ አገልግሎት ይጠቀምበት ጀመር ተብሎ ይታመን ነበር፡፡ የቤተክርስቲያኗ መሪዎች በኃይማኖት ሽፋን ወገናዊ የጎሳ ፖለቲከኞች እንደሆኑ በሕዝቡ ላይ ግንዛቤ ተወሰደ፡፡ እነዚህ ሰዎች የክርስቶስን ወንጌል የሚሰብኩ አልነበሩም፡፡ ሆኖም ግን የጎሳ ልዩነትን እና የመለስ አገዛዝ ጥላቻን ይሰብኩ ነበር፡፡

በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ የዘር አገዛዝ ስር እንደነበረው ቤተክርስቲያን ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ የኢኦተቤ የጨቋኞች ቤተክርስቲያን እና የተጨቋኞች ቤተክርስቲያን በሚል ለሁለት በመከፈል ተገለለች፡፡ በስደት ላይ ያለችው ኢኦተቤ የተጨቋኞች ቤተክርስቲያን እንደሆነች አመነች፡፡

ባለፉት 27 ዓመታት በሀገር ውስጥ ባለችው እና በውጭ ሀገር በስደት ባለችው ኢኦተቤ መካከል ይፋ ባልሆነ መልኩ እውነተኛ እርቅ እና አንድነት እንዲመጣ ለማድረግ የውይይት ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ የመሻሻል ምልክቶች እየታዩ በሚሄዱበት ጊዜ የመለስ ታማኝ ደጋፊዎች ጣልቃ እየገቡ አንድነት እንዳይፈጠር ሲደረጉ የቆዩትን ጥረቶች ሁሉ ሁልጊዜ ለማምከን የተለያዩ መንገዶችን ሲፈልጉ ቆይተዋል፡፡

የኢኦተቤንን ለእርቀሰላም እና ለአንድነት ለማብቃት የማያስችሉ ሁለት እንቅፋቶች ተደቅነው እንደሚገኙ ተነግሮኛል እኔም አምናለሁ፡፡ እነዚህም አንደኛ መንግስት እጁን ከኃይማኖት ጣልቃ ገብነት ሙሉ በሙሉ ማውጣት አለበት፡፡ የኃይማኖት መሪዎች የእራሳቸውን ጉዳዮች እና ችግሮች እራሳቸው መፍትሄ እንዲሰጡ መንግስት መፍቀድ አለበት፡፡ ሁለተኛ የዲያስፖራው ማህበረሰብ የሚደረገው እርቅ በአገዛዙ የሚደረግ የፖለቲካ ጨዋታ ዓይነት ነገር እንደሆነ አድርጎ መቁጠር እንደሌለበት ግንዛቤ ሊወስድ ይገባል፡፡ በስደት የሚገኘው የኢኦተቤ አመራር ከእምነቱ አማኞች የሀሳብ ግብአቶችን ሳያይ እና ሳያስጸድቅ ምንም ዓይነት ውሳኔዎችን ማሳለፍ የለበትም፡፡

በቀላሉ ለመግለጽ የኢኦተቤንን የመጨረሻ ፈውስ ለመስጠት በጎሳ ልዩነት ላይ በተዋቀረው የፖለቲካ ስርዓት በመተብተብ ተይዞ ይገኛል፡፡

በስደት የሚገኘው የኢኦተቤ መንግስት እና ኃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን ሊያረጋግጥ የሚችል ማስረጃ እና መተማመኛ እንዲሰጠው ይፈልጋል፡፡ በቤተክርስቲያን ጉዳዮች ላይ መንግስቱ ጣልቃ እንዳይገባ እና የማይታይ እጁን እንዲያስገባ አይፈልጉም፡፡ እንዲህ የሚለውን አምላካዊ ቃል እጠቅሳለሁ፣ “የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሄርን ለእግዚአብሄር፡፡“ የኢትዮጵያ ቄሳሮች በኃይማኖቱ ላይ ጣልቃገብነታቸውን በመተው የመንፈሳዊውን ህይወት ለእምነቱ መሪዎች እና ለሕዝበ ክርስቲያኑ ይተውት፡፡

እነዚህ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ሁለት ሁኔታዎች ተግባራዊ የሚደረጉ ከሆነ ሁለቱ ቤተክርስቲያኖች ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት ብዙ ጊዜ የማይወስድባቸው መሆኑን አምናለሁ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚፈልጉት ጠንካራ የተባበሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርሰቲያን አንድ ሆኖ ማየት ይችላሉ፡፡

እኔ በግሌ በጣም የሚያሳዝነኝ እውነታ ቢኖር አገዛዙ በሚሊዮኖች ዜጎች ላይ አሰቃቂ እልቂት ሲፈጽም፣  ሲያስር እና ስቅይትን ሲፈጽም በሀገር ውስጥ ያለው የኢኦተቤ መሪዎች ድርጊቱን ሳይቃሙ እና ሳያወግዙ ዝም ብለው የመመልከታቸው ሁኔታ ነው፡፡ ለድሆች እና ለተጨቆኑት መቆም የሚገባቸው የሃይማኖት አባቶች ህገ ወጥና ፍትህ አልባ ስራ ሲሰራ እያዩ ዝም ሲሉ የነሱን ቦታ እነ እስክንድር ነጋ፣ አንዷለም አራጌ፣ በቀለ ገርባ፣ አቡባከር አህመድ እና ሌላዎችም ወስደው በደልና ስቃይ ሲደርስባቸው ሳይ አገረምና አዝን ነበር፡፡

የቤተክርስቲያን መሪዎች በአንድ ወቅት ህዝቦቻቸው ሲሰቃዩ ከመመልከት ይልቅ መሞትን ይመርጡ እንደነበር ወጣቱ ትውልድ እንዲያውቀው እፈልጋለሁ፡፡

አቡነ ጴጥሮስ የወቅቱ ማህተመ ጋንዲ በእራሳቸው ፈቃድ ሰላማዊ ተቃውሞን እና ሕዝባዊ እምቢተኝነትን የሚያራምዱ ታላቅ መንፈሳዊ ሰው ነበሩ፡፡ እኒህ ታላቅ መንፈሳዊ መሪ እ.ኤ.አ በ1930ዎቹ ኢትዮጵያን ወርራ የነበረችውን ጣሊያንን በመቃወም ሕዝባዊ እምቢተኝነትን እና ለጣሊያን ፋሽስት ወታደሮች ትብብር እንዳይደረግ በመስበካቸው ብቻ በሞት እንዲቀጡ ተደርገዋል፡፡

ጣሊያኖች አቡነ ጴጥሮስ ሕዝባችን ለጣሊያን እንዳይገዛ ወይም ጥላቻውን እንዲያሳይ መስበካቸውን እንዲያቆሙ በሚጠይቅበት ጊዜ እኒህ ታላቅ መንፈሳዊ መሪ እንዲህ የሚል ቀላል መልስ ነበር የሰጡት፣ “በመርዝ ጋዝ [ከሰማይ በምታዘንቡባቸው] የሚገደሉት የሀገሬ ሕዝቦች ጩኸት እና የግድያ እልቂት መሳሪያዎቻችሁን እየተመለከትኩ የእናንተን ማስጠንቀቂያ በመቀበል ዝም እንድል ህሊናዬ የሚፈቅድልኝ አይደለም፡፡ ለእንደዚህ ዓይነቱ ወንጀል ዓይኔን ጨፍኜ አላየሁም በማለት ባልፈው እንዴት አድርጌ ነው የአምላኬን ፊት ለማየት የምችለው?“ ነበር ያሉት እውነተኛው መንፈሳዊ መሪ፡፡ ታዲያ አሁን እንደዚህ ያለ መንፈሳዊ መሪ ማግኘት ቀርቶ መታሰብ ይችላልን?

አቡነ ጴጥሮስ እ.ኤ.አ በ1936 ዓ.ም በፋሽስቶች ከመገደላቸው በፊት የሀገራቸው ህዝቦች ለፋሽስቶች ትብብር እንዳያደርጉ፣ ከሩቅ የመጡት እና ደካማዋን እና ሰላማዊዋን የእኛን ኢትዮጵያን በኃይል የወረሯትን የዘራፊ ወታደሮች እንዳይቀበሉ ይመክሩ ነበር፡፡ ከመገደላቸው በፊት የመጨረሻ ቃሎቻቸው እንዲህ የሚሉ ነበሩ፣ “አምላክ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ጽናቱን እንዲሰጣችሁ እና ለፋሽስት ወታደሮች እና ጨካኞች በፍጹም እንዳታጎበድዱ እማጸናችኋለሁ“ የሚል ነበር፡፡

ሆኖም ግን ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ የሚገኙት የኢኦተቤ መሪዎች በመለስ አገዛዝ በሰው ልጆች ስብዕና ላይ ሲፈጸም የቆየውን እና ለመናገር የሚዘገንን ጭፍጨፋ ሲፈጸም አላየሁም፣ አልሰማሁም በማለት ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ቆይተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለአጋዚ ወታደሮች እና አውሬዎች በፍጹም የማያጎበድድ ጥንካሬ እና መገዳደርን ተጎናጽፈዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የቅድመ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን አገዛዝ የጥላቻ ርዕዮተ ዓለም ጠልተዋል፣ አክ እትፍ ብለው ጥለውታል፡፡ ይልቁንም ስለፍቅር፣ አንድነት፣ ሰላም እና እርቅ በመዘመር እውን እንዲሆን በትጋት ይሰራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የፍቅር፣ የአንድነት እና የእርቅን መንገድ እንዲከተሉ ማሳየት የኃይማኖት መሪዎች ዋና ተግባር ነው፡፡

ሰላማዊ የኃይማኖት አብሮ መኖር በኢትዮጵያ፣

ኃይማኖት የህብረተሰብ  አንዱ ዋና ምሰሶ ምናልባትም ከማንም በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የበለጠ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የክርስትና እና የእስልምና ኃይማኖቶች ሀገር ናት፡፡

ጥንታዊው የአክሱም ግዛት (ከ3ኛው – 6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ) በአሁኑ ጊዜ ላለችው ኢትዮጵያ የፖለቲካ እና ለንግስት ሳባ አፈታሪክ መሰረት ነው፡፡ የአክሱም ንጉስ የነበሩት ኢዛና በ4ኛው ክፍለ ዘመን ክርስትና የመንግስት ኃይማኖት እንዲሆን አደረጉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአስር ሚሊዮኖች የሚሆኑ ኢትዮጵያውን ክርስቲያኖች አክሱም ሁለተኛዋ ቅዱስ የእየሩሳሌም ቦታ እንደሆነች አድርገው ያምናሉ ምክንያቱም ጽላቱ በአክሱም ጽዮን ካቴድራል ውስጥ እንዳለ ያምናሉ፡፡

የነብዩ መሀመድ ተከታዮች ስቅይት በሚደርስባቸው ጊዜ ነብዩ መሀመድ መካን በመተው በክርስቲያን ንጉስ በምትገዛ እና ፈሪሀ እግዚያብሄር ወዳደረበት ፍትሀዊ ንጉስ አቢሲኒያ (ኢትዮጵያ) ወደምትባል ሀገር በመሄድ ተጠለሉ በማለት ነበር ያዘዛቸው፡፡

የአክሱም ንጉስ እና ሐበሻዎች (ኢትዮጵያውያን) ስቃይ የደረሰባቸውን ሙስሊሞች እ.ኤ.አ በ615 ዓ.ም በመልካም መስተንግዶ በመቀበል መጠለያ በመስጠት ጠላቶቻቸው ተመልሰው እንዲሰጧቸው በጠየቁ ጊዜ በመቃወም አሳልፈው ሳይሰጡ በመልካም ሁኔታ አስተናገዷቸው፡፡

 ለኃይማኖት ነጻነት እና መቻቻል ያለኝ ጥበቃ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ኃይማኖትን ፖለቲካዊ ማድረግን ስለመቃወም፣

 ኢትዮጵያውያን እና ሙስሊሞች ለሺህ ዘመናት በሰላም አብረው ኖረዋል፡፡ ሆኖም ግን ባለፈው ሩብ ምዕተ ዓመት ኃይማኖት በቅድመ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አገዛዝ በጎሳ እየለያየ እንደሚጠቀም ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ኃይማኖትንም ህዝቦችን ለመለያየት እንደ ፖለቲካ መሳሪያ ስልት እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢኦተቤ ያለው ልዩነት አገዛዙ ለያይቶ ለመግዛት እንዲመቸው እና ኃይሉን በማጠናከር በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣበቆ ለመኖር ኃይማኖትን ፖለቲካዊ የማድረግ ዓላማ ዋና መገለጫው ነው፡፡

የኢትዮጵያ የመጨረሻ ነጉሥ የነበሩት ንጉሰ ነገሥት ኃይለሥላሴ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ኃይማኖት የግል ሀገር የጋራ ነው፡፡“ እንደዚሁም ሁሉ ኃይማኖት የፖለቲካ መጠቀሚያ መሳሪያ እንዳይሆን እና አላግባብ በስራ ላይ እንዳይውል ግንዛቤው የነበራቸው እና የማይፈቅዱ ነበሩ፡፡ ይህንንም በማስመልከት እንዲህ ብለው ነበር፣ “በሰዎች ፍጹም ያለመሆን ምክንያት ኃይማኖት የሙስና፣ የፖለቲካ፣ የልዩነት እና የስልጣን መጠቀሚያ ሆኗል፡፡”

መንግስት ዜጎች በነጻነት እምነቶቻቸውን ማራመድ እንዳይችሉ በእምነት ጣልቃ በመግባት እና የአሸባሪነት ሕጉን ከሕግ አግባብ ውጭ በመጠቀም የኢትዮጵን ሕዝቦች በመነጣጠል ለማጠልሸት እና ለማሰቃት የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት በመቃወም ለኃይማኖት ነጻነት እና ኃይማኖትን ለፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ሁሉ በመቃወም ጠንካራ አቋም ወስጃለሁ፡፡

 እ.ኤ.አ ታህሳስ 2011 ዓ.ም አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያን ሙስሊሞች ለመጉዳት እና ፍርሀት ለመልቀቅ በማሰብ “አኬልዳማ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ እርባና ቢስ ዘጋቢ ፊልም በቴሌቪዥን እንዲለቀቅ ተዕዛዝ ሰጥቶ የተላለፈውን አሳፋሪ ዘጋቢ ፊልም አይቻለሁ፡፡ በዚያ እርባና ቢስ ፊልም የመለስ አገዛዝ ዓለም አቀፍ አሸባሪዎች በኢትዮጵያውያን ተቃዋሚዎች ስም በኢትዮጵያ ውስጥ የሽብር ድርጊት ይፈጽማሉ የሚል እርባና ቢስ መልዕክት ለማስተላለፍ እና ሙስሊሙን ህብረተሰብ ከሌላው ወገኑ ለመለየት የተጠቀሙበት እርባና ቢስ ዘዴ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ሴራው አልሰራም፡፡

እ.ኤ.አ ሰኔ 2012 ዓ.ም “ኢትዮጵያ፡ አንድነት በእምነት“ በሚል ርዕስ አዘጋጅቸው በነበረው ትችቴ በክርስትና እምነት ተከታዮች እና በሙስሊሙ ማህበረሰብ መካከል ጥላቻን ለመፍጠር እና ሀገር በቀል ሙስሊም አሸባሪዎች በማለት የሀሰት እና የሸፍጥ ክስ መስርቶባቸው የነበረውን እና አሁን በህይወት የሌለውን መለስ ዜናዊን ተዋግቻለሁ፡፡ ከጭራቆች ጋር በሚደረገው ትግል የሙስሊም እና የክርስትና እምነት መሪዎች እርስ በእርሳቸው ለመገናኘት እና የአንድነት ድልድይን እየገነቡ በመሆናቸው የነበረኝን አድናቆት ከፍ ባለ ስሜት ገልጫለሁ፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኘው ጥንታዊው የዋልድባ ገዳም በውጭ ኢንቨስተሮች እንዳይወድም በቶሮንቶ የክርስትና እና የእስልምና ኃይማኖት መሪዎች ያሳዩትን የትግል አጋርነት በመደገፍ የእምነቱን መልዕክት ሙሉ በሙሉ አጽድቂያለሁ፡፡

የእምነቱ መሪዎች ዋና መልዕክት ደስ የሚያሰኝ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች ለብዙ ዘመናት በሰላም እና በአንድነት ተቻችለው ይኖሩ እንደነበር የሚያመላክት ማስረጃ ነበር፡፡

በስደት የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከፍተኛ አመራር የሆኑት ሊቀ ካህናት መሰለ እንግዳ በቶሮንቶ ተደርጎ በነበረው ጉባኤ ላይ በመገኘት የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞችን አንድነት እንዲህ በማለት በድጋሜ አረጋግጠዋል፡

“…የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑት ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ሁልጊዜ ሀገራችንን በመጠበቅ ረገድ ትልቅ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ በርካታ የሙስሊም አባቶች ሀገራችንን በመጠበቅ የተዋጉ እና ስቃይን የተቀበሉ ለመሆናቸው የተመዘገበ ታሪክ ያሳየናል፡፡ ሙስሊሞችና እና ክርስቲያኖች በታሪክ በሰላም ለዘመናት አብረው ኖረዋል፡፡ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ ችግር ባጋጠመ ጊዜ ሙስሊም ወገኖቻችን ችግሩን ለመጋፈጥ አብረውን ይነሳሉ፡፡ በዛሬው ዕለት የሙስሊም መሪ ከቶሮንቶ አብሮን ቆሟል፡፡ እንደምታውቁት ሁሉ በዚህ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ሙስሊም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ከፍተኛ መከራን ተጋፍጠው ይገኛሉ…ሆኖም ግን ሁላችንም በአንድነት ቆመናል…“ ነበር ያሉት፡፡

በስደት በቶሮንቶ የሚገኙት ታዋቂው የሙስሊም መሪ ሐጅ መሀመድ ሰይድ ለኢትዮጵያ አንድነት ጠንካራ እምነት እንዲኖር አጽንኦ በመስጠት “ሀገር ከሌለ ኃይማኖት የለም“ በማለት አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ ንግግራቸውንም በመቀጠል እንዲህ ብለዋል፡

“…ሁላችሁም እንደምታውቁት ኢትዮጵያ የተለያዩ ኃይማኖቶች አሏት፡፡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች  እና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች እርስ በእርሳቸው ተዋድደው የሚኖሩባት የተመዘገበ ታሪክ ያላት ሀገር ናት፡፡ በእኛ እድሜ እንኳ ከ50 – 60 ዓመታት እንደዚህ ያለ ስቃይ እና መከራ ሲደርስባት አይተን አናውቅም፡፡ ኃይማኖት የግል ነው ሀገር ግን የጋራ ነው፡፡ ሀገር ከሌለ ኃይማኖት የለም፡፡ ሀገር ሲኖረን ብቻ ነው የፈለግነውን ነገር ሁሉ ማግኘት የምንችለው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኃይማኖት ጠንካራ ሆና የቆየችው ኢትዮጵያ ተከፋፍላ እና ተበታትና ትገኛለች፡፡ ሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች እንዲዋጉ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ ለዚህ ድርጊት ተግባራዊነት ለብዙ ጊዜ የቅስቀሳ ዘመቻ ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ግን አልሰራም፡፡ ኦሮሞ ከአማራ ጋር እንዲዋጋ ለማድረግ ሲሞክሩ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ያም አልሰራም…በታሪክ አንድ ዓይነት ብቻ ሙስሊም ነው የምናውቀው – እርሱም ቃሉን የሚያከብረው፡፡ ይህም ማለት ሙስሊሙ በቃሉ ጸንቶ ካልቆየ እና ዝናቡ ካልዘነበ ያ ለሀገሪቱ መጥፎ ዕጣ ፈንታ ነው፡፡ አዲስ ኃይማኖት አምጥተዋል እናም በኢትዮጵያ ብጥብጥ ፈጥረዋል…

…አሁን የቀረ ኢትዮጵያዊ ትውልድ አለን? በዩኒቨርስቲዎች የገቡ ተማሪዎች ሞራላቸው ዳሽቋል፣ አእምሯቸው አደንዛዥ እጽ በማኘክ እና ሲጋራ በማጤስ ተጎድቷል፡፡ እነርሱ (ገዥዎች) ትውልድን ገድለዋል፡፡ በእውነት በዜጎቹ ላይ እንደዚህ ያለ እልቂት (በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ እንደሚካሄደው ዓይነት) የሚፈጽም መንግስት ወይም አስተዳደር በታሪክ በፍጹም አንብቤ አላውቅም፡፡ እያንዳንዳችን በሕዝቡ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ስቃይ እና መከራ ለመናገር አንድ ሙሉ ቀን ቢሰጠንም እንኳ በቂ አይሆንም“ በማለት ሀሳባቸውን አጠናቀዋል፡፡

እ.ኤ.አ የካቲት 2013 “ኢትዮጵያ፡ የፍርኃት እና የማጠልሸት ፖለቲካ“ በሚል ርዕስ አቅርቤው በነበረው ትችቴ በመለስ አገዛዝ በሙስሊሞች ላይ ያነጣጠረ ሌላ ፕሮፓጋንዳ ጥቃት አጋጠመኝ፡፡ “የጅሀዳዊ ሀራካት“ እርባና ቢስ ዘጋቢ ፊልም የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ኢላማ በማድረግ ለማሰቃየት እና ለማዋረድ የተዘጋጀ ቆሻሻ ዘገባ ነበር፡፡ የእርባና ቢሱ ዘጋቢ ፊልም ዋና መልዕክት መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩ እና በእምነት ጉዳዮቻቸው ላይ መንግስት ጣልቃ እንዳይገባባቸው ከመጠየቅ ውጭ ያለፈ ደም የጠማቸው አሸባሪ ቡድኖች እንደ ቦኮሀራም (ናይጀሪያ)፣ አንሳር አል ዲን (ማሊ)፣ አልቃይዳ፣ አልሻባብ፣ ሀማስ የሀገር ውስጥ ቅርንጫፎች ናቸው እንደሚለው አልነበረም፡፡

የኃይማኖት ነጻነቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመከታተል እንዲቻል በአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና በፕሬዚዳንቱ የተቋቋመው እና የዓለም አቀፍ ኃይማኖቶች ነጻነት የዩኤስ ኮሚሽን የኢትዮጵያን ሙስሊሞች ሕጋዊ ጥያቄዎች እንዲህ በማለት አረጋግጧል፤

እ.ኤ.አ ከሀምሌ 2011 ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስት በተለምዶ የሀገሪቱ ሙስሊሞች የሱፊ ዓይነት እምነትን በሚያራምደው የማህበሰብ ክፍል ላይ የአል-አህባሽን እስልምና ለመጫን ፈልጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መንግስት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትን (ኢእጉም) ምርጫ ፐውዞታል፡፡ ቀደም ሲል ነጻ ተቋም የነበረው ኢእጉም በአሁኑ ጊዜ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያለ ተቋም ሆኗል፡፡ በቁጥጥር ስር የዋሉት የአሸባሪነት ክስ እና ኢእጉምን መውሰድ በኢትዮጵያ ውስጥ የእምነት ነጻነት መሸርሸርን እና እየተዳከመ መምጣትን የሚያመላክት ተጨማሪ ማስረጃ እንደሆነ ያመላክታል፡፡ በመላ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ኢትዮጵያውን ሰላማዊ ተቃውሞ በማድረጋቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ጥቅምት 29 ቀን የኢትዮጵያ መንግስት በሽብር ማካሄድ እና የእስልምና መንግስት ለመመስረት አቅዳችኋል በሚል ውንጀላ በ29 ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ ክስ መሰረተ፡፡“

መንፈሳዊ ፈውስ፣ እርቅ እና የእምነት መሪዎች ጠቀሜታ በሂደት፣

ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ኃይማኖት የግል ሀገር የጋራ ነው በሚለው ምልከታቸው ላይ ትክክል ነበሩ፡፡ በእርግጥ በሙስሊሞች እና በክርስቲያኖች መካከል ለዘመናት የቆየው በሰላም አብሮ የመኖር ልምድ በዚህ ዋና መርህ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ይህንን መርህ ተግባራዊ ለማድረግ የኃይማኖት እና ሌሎችን ማናቸውንም ዓይነት ጽንፈኛ ቡድኖች መቃወም እና ማውገዝ የዜጎች የሲቪክ እና የሞራል ግዴታ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የኃይማኖት መሪዎች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ለደሀው እና ለተጨቆነው ሕዝብ በመቆም የመናገር የሞራል ግዴታ አለባቸው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የኃይማኖት መሪዎች ከሕዝቡ ትልቅ እምነት እና ከበሬታ አላቸው፡፡ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች የኃይማኖት ቅራኔን ለመስበክ በሚሞክሩበት ጊዜ ይህንን ለመስበክ እና ለማስተማር ትዕግስቱ ያላቸው የኃይማኖት መሪዎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ችግሮች ከእምነት ልዩነቶች የመጡ አይደሉም፡፡ የኢትዮጵያ ችግሮች የሚመነጩት ኃይማኖትን እና ጎሳን መሳሪያ በማድረግ ኃይማኖትን ፖለተካዊ ለማድረግ በሚፈልጉ ሰዎች እና ቡድኖች አማካይነት ነው፡፡

የኃይማኖት መሪዎች በዓለም ላይ ባሉ እምነቶች ላይ ልዩ የሆነ ኃይል የመጫን ስልጣን አላቸው፡፡ እንደ መንፈሳዊ መሪ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ስሜቶች የማዘዝ እና የመሳብ ኃይል አላቸው፡፡ ሁልጊዜ የሲቪል ሰላምን የማምጣት እና የእርስ በእርስ ጦርነት የማቀጣጠል የጨዋታ ሚና አላቸው፡፡ በታሪክ የኃይማኖት ጦርነቶች የበርካታ ስቃዮች እና መከራዎች ምንጮች ናቸው፡፡

የኃይማኖት ተቋማት እና አስተምህሮዎች ውድቀት ቢኖርም በእኛ ጊዜ በርካታ የኃይማኖት መሪዎች ለእኩልነት እና ለፍትህ ትግል የድርሻቸውን አበርክተዋል፡፡ ለምሳሌ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ አሜሪካንን እና ዓለምን በፍቅር፣ ሰላም እና እርቅ መልዕክታቸው ከፍ ወዳለ ደረጃ አሸጋግረዋል፡፡ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ በደቡብ አፍሪካ የእውነት እና እርቅ ኮሚሽንን መርተዋል፡፡ በሚናገሩበት ጊዜ ድምጾቻቸው ይሰማሉ እናም መልዕክቶቻቸው በሰዎች አእምሮ ውስጥ ዘልቀው የመግባት ኃይል አላቸው፡፡

የእምነት መሪዎች በዘር፣ በመደብ እና በብሄር የተለያየውን አንድ የማድረግ ውስጣዊ የሆነ ችሎታ አላቸው፡፡ የግል የማህበራዊ እሴቶችን ለመቅረጽ፣ ግንዛቤን ከፍ ለማድረግ እና በአመለካከቶች ፣ ባህሪዎች እና ልምዶች ላይ ተጽእኖ ለማሳረፍ ይችላሉ፡፡ በህብረተሰቡ እና በፖለቲካ አባላት ዘንድ ተሰሚነት እና የመከበር ኃይል አላቸው፡፡

አንድ ሀገር ግጭትን ለማቆም እና እውቅናን ለማግኘት ብቻ አይደለም ስኬታማ የምትሆነው ሆኖም ግን የኢኮኖሚ፣ የልማት እና የሀገር ግንባታ ለማካሄድ የሞራል ጉዳይ እንደሚያስፈልጋት አምናለሁ፡፡ በእኔ አስተያየት በደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ወደ ዴሞክራሲ በሰላማዊ መንገድ ሽግግር ተደርጎ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከተለያዩ አቅጣጫዎች የእምነት መሪዎች ኃይልን ለመከላከል እና እርቅ ለማምጣት በአንድነት ሰርተዋል፡፡ የእምነት መሪዎች አንድነትን ለማጠናከር ለማህበረሰቡ፣ ለማምለኪያ ቦታዎች ለተጨቆነው ህዝብ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በመጮህ የሰብአዊ መብት አጠባበቅ እፎይታን አጎናጽፈዋል፡፡

በእኔ አመለካከት ለማ መገርሳ እንዲህ በማለት በአባቶች እምነት አምሳል ተናግሯል፡

“… በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍቅር እንፈልጋለን፡፡ ፍቅር እንፈልጋለን፡፡ ፍቅርን በመፈክር፣ ጥሩምባ በመንፋት ወይም በፕሮፓጋንዳ ልናመጣው አንችልም፡፡ ፍቅር እርስ በእርሳችን ስንተሳሰብ፣ አንዳችን ሌላችንን ስንከባከብ ይመጣል፡፡ አንዳችን ሌላችንን ስንንከባከብ ፍቅር ይመሰረታል፡፡ ፍቅር በሚኖረን ጊዜ ጠንካራ ኢትዮጵያን እናገኛለን፡፡ ፍቅር በሚኖርበት ጊዜ ጠንካራ ኢትዮጵያዊነት ይኖረናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከምንጊዜውም በላይ ፍቅርን ለማምጣት፣ በአሁኑ ጊዜ ፍቅርን ለመገንባት አንዱ ሌላኛውን መንከባከብ እና እርስ በእርስ መተሳሰብ እጅግ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ ይኸ ግዴታ ነው፡፡ አለበለዚያ ግን ሁላችንም ልናደርገው የምንችለው ነገር ችገሮቻችንን ማራዘም እና የትም ርቀን መሄድ እንደማንችል ነው“ ነበር ያለው፡፡

የእኔን የእምነት ምክር ቤቶች ማዕከልነት ጥሪ ማስታወስ ለብሄራዊ እርቅ ቁልፍ የስኬት መዳረሻ፣

በሀገር ውስጥ እና በዲያስፖራ ያለው ኢኦተቤ አባላት መካከል ፈውስ እና እርቅን ለመፍጠር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ያቀረቡትን ጥሪ ክልብ እደግፋለሁ፡፡ ቤተክርስቲያኗ ለእርቅ እና ለሰላም ዋናውን መንገድ እንድትመራ ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የቢሮ ስልጣናቸውን ከያዙ ጀምሮ ለብሄራዊ እርቅ እያደረጉት ካለው ጩኸት አንጻር በእምነት ምክር ቤቶች መካከል እርቅ እንዲኖር ጥሪ እንደሚያስተላልፉ አልጠራጠርም፡፡ ሆኖም ግን ለሚያደርጉት ጥሪ ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ሀሳብ ለማበርከት ለእምነት ምክር ቤት በመቋቋም ኢትዮጵያ ጠንካራ፣ ሙስሊም እና ሌላ የኃይማኖት ተቋማት በመያዝ ብዝሀነት ባለው መልኩ ህዝቦቿን እንድታገለግል የእኔን ሀሳቦች አካፍላለሁ፡፡

ኢትዮጵያ ከፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ፈውስ በፊት የመንፈሳዊ ፈውስ እንደሚያስፈልጋት አምናለሁ፡፡ ዶ/ር ኪንግ በፍቅር መንፈስ ትግላችንን ወደ ፍትህ ማዞር አለብን፡፡ እ.ኤ.አ. በ1954 “የእግዚአብሄር ፍቅር” በሚል ርዕስ በዴክስተር አማኝ ቤተክርስቲያን ጎዳና ባደረጉት ንግግር ስለዚህ ጉዳይ ተናግረዋል፡፡

ሀገሪቱን በመንፈሳዊ ፈውስ ለመፈወስ በኢትዮጵያ እና በዲያስፖራው ላሉት የኢኦተቤ የእምነት ምክር ቤቶች የፈውስ ጥሪዬን በማቅረብ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን መደገፍ እፈልጋለሁ፡፡

እ.ኤ.አ ሰኔ 2012 “ኢትዮጵያ፡ አንድነት በእምነት“ በሚል ርዕስ አቅርቤው በነበረው ትችቴ የእምነት ምክር ቤቶች እንዲቋቋሙ እንዲህ የሚል የክርክር ጭብጤን አቅርቤ ነበር፣

“በዩኤስ በይበልጥም በሌሎች ሀገሮች የእምነት ማህበረሰቦች የእምነት ምክር ቤቶችን ያደራጃሉ፡፡ እነዚህ ምክር ቤቶች አብሮ ለመስራት፣ ጠንካራ መግባባትን ለመመስረት  እና የተለያዩ እምነቶችን በሚያራምዱ ሕዝቦች መካከል መከባበርን ለመፍጠር  እና የማህበረሰቡን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት ብዙ የእምነት ማህበረሰቦችን ያመጣሉ፡፡ እንደዚህ ያሉ በርካታ የእምነት ምክር ቤቶች ከክርክር እና ከሀሳብ ፍንጠቃ በላይ ዘልቀው በመሄድ የህብረተሰቡን ፍላጎቶች ለማሟላት የማህበራዊ አገልግሎቶችን እና ፕሮጀክቶችን በመተግበር ፍላጎቶቻቸው እንዲሟሉ ያደርጋሉ፡፡ አድልአዊነትን እና የኃይማኖትን እና የእምነት ተቋማትን የሚያሳንሱትን በማውገዝ የኃይማኖት ነጻነቶቻቸውን ለመጠበቅ በአንድነት ይቆማሉ፡፡ ኢትዮጵያውን የእራሳቸውን የእምነት ተቋማት የማያቋቁምበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም፡፡“

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2012 “አንድነት፡ በእምነት“ በሚል ርዕስ አቅርቤው በነበረው ትችቴ በሙስሊሞች የኃይማኖት ነጻነት ላይ የሚደረጉ ዛቻዎች በክርስቲያኖች የኃይማኖት ነጻነት ላይ የሚደረጉ ዛቻዎች ናቸው በማለት ተከራክሪያለሁ፡፡ የኢትዮጵያ የሙስሊም እና የክርስቲያን እምነቶች መሪዎች ግጭቶችን በመከላክል እና የመግባባት፣ የጋራ መከባበርን እና በጋራ የመስራት ግንኙነቶችን በማጠናከር ጠቃሚ ሚናዎችን እንዲጫወቱ ተማጽእኖዬን አቅርቤ ነበር…፡፡ በዩኤስ እንደተቋቋሙት ዓይነት የእምነት ምክር ቤቶች እንዲቋቋሙ ሀሳብ አቅርቤ ነበር፡፡ እነዚህ የእምነት ምክር ቤቶች የተለያዩ ማህበረሰቦችን ወደ አንድነት በማምጣት አብረው እንዲሰሩ በማድረግ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ያሟላሉ፡፡

እ.ኤ.አ መጋቢት 2013 ዓ.ም “በኢትዮጵያ የጸረ አፓርታይድ ንቅናቄ የሞራል እኩልነት“ በሚል ርዕስ አቅርቤው በነበረው ትችቴ የእምነት ተቋማት ምክር ቤቶች ለብሄራዊ እርቅ እና ሰላም በጣም አስፈላጊ ናቸው በማለት የክርክር ጭብጤን አቅርቤ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የኃይማኖት ነጻነት እንዲኖር እምነት ያላቸው ኢትዮጵያ አሜሪካውያን ማድረግ ያለባቸው  የእምነት ምክር ቤት በማቋቋም በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት በእምነት ጉዳዮች ላይ መስራት ነው፡፡

በዩናይትድ ስቴትስ እና በሌሎች ሀገሮች የሚገኙ የሁለቱ እምነት ማህበረሰቦች በጋራ እንዲሰሩ አሁንም ደግሜ ደጋግሜ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ የኃይማኖት ነጻነት በኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ብቻ የሚያሳስብ ጉዳይ አይደለም፡፡ በቅርቡ በመሪዎቻቸው ምርጫ ላይ የምርጫ ጣልቃገብነት እየተስተዋለ ያለበት ተመሳሳይ ሁኔታ ለክርስቲያን ኢትዮጵያውያን ሁሉ በእኩል ደረጃ የሚያሳስባቸው ጉዳይ ነው፡፡

የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር በክርስቲያን እና በሙስሊም ኢትዮጵያ አሜሪካውያን መካከል እውነተኛ እና ግልጽ ውይይት በማድረግ የኃይማኖት ነጻነት እና እኩልነትን በሁሉም ረገድ ማስፈን ነው፡፡ የእነዚህ ሁለት የእምነት ማህበረሰቦች የኃይማኖት ነጻነታቸውን፣ ማንኛውንም ዓይነት ጽንፈኝነት ለማስወገድ እና የረዥም ጊዜ አብሮነት ኑሯችንን ለማረጋገጥ፣ በተባበረች ሀገር ውስጥ በሕግ የበላይነት ብዝሀነት እና ስምምነትን ለማምጣት በታሪካዊ ስብሰባ በጋራ ነጻነታቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ የትብብር እና የማደራጀት ስራዎች መርሆዎችን በጋራ ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ የጠባብነት ቡድናዊ ጽንፈኝነት ፍላጎቶችን በአመራር ቦታ ሆነው ስብዕናቸውን ሸጠው ለአምባገነኖች ጥቅም የሚቆሙትን በጋራ በአንድነት እየታገሉ ማስወገድ አለባቸው፡፡ በጋራ መከባበር ላይ በመመስረት እያንዳንዳቸው እርስ በእርሳቸው በፍቅር መንፈስ እና በመተማመን ግንኙቶቻቸውን ማጠናከር አለባቸው፡፡

ምናልባትም እንደዚህ ያለው ውይይት ተቋሞች በሌሉበት ሁኔታ በቀላለሉ የሚፈጸም ላይሆን ይችላል፡፡ የሁሉቱም እምነቶች መሪዎች በአንድነት ሆነው ህብረት በመፍጠር በኢትዮጵያ አሜሪካ ሙስሊሞች እና በክርስቲያን ኢትዮጵያ አሜሪካውያን ክርስቲያኖች መካከል ጉዳዮችን የሚያጠና እና የመፍትሄ ሀሳቦችን የሚያቀርብ ግብረ ኃይል መቋቋም አለባቸው፡፡ የክርስቲያን እና የሙስሊም መንፈሳዊ ባለስልጣኖች እና ተራው ሕዝብ በኃይማኖት ነጻነት ጉዳዮች እርስ በእርስ አንዲጠባበቅ ብቻ ሳይሆን የቡድናዊነት፣ የጽንፈኝነት፣ የግጭት እና ያለመግባባት አደጋዎችን በመቀነስ ዘላቂ የሆነ ውይይት በማድረግ የረዥም ጊዜ መፍትሄ በማምጣት በአንድነት እንዲሰራ ሊበረታታ ይገባል፡፡

የእምነት ምክር ቤት የጋራ ጉባኤዎችን፣ ስብሰባዎችን፣ ወርክሾፖችን፣ ሴሚናሮችን፣ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን እና የመረጃ የመገናኛ ብዙሀን ዘመቻዎችን በሁለቱም የእምነት ማህበረሰቦች ማድረግ የማቻልበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም፡፡ የነገይቱ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ባሉ ሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች ጠንካራ የውይይት መሰረት ላይ ይገነባል፡፡ ውይይት ለብሄራዊ እርቅ ቀዳሚ ጉዳይ ነው፡፡

የእምነት ምክር ቤት ኢትዮጵያን ወደ እርቅ ሽግግር ለመውሰድ እና ፍትሀዊ እና እውነተኛ ማህበረሰብን እውን ለማድረግ በርካታ ነገሮችን ለማድረግ ይችላል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብትን በመጠበቅ ትልቅ ሚና የሚጫወት የእምነት ምክር ቤትን ማሰብ እችላለሁ፡፡ እንደዚህ ያለ አመራር በስብእናችን ላይ መንፈሳዊነትን የሚሰብክ መልዕክት በመጨመር በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ መቻቻልን እና እኩልነትን በማራመድ ትምህርታዊ ሚና ለመጫወት ይችላል፡፡ የእምነት መሪዎች የጎሳ ውጥረትን በመቀነስ እና የማህበረሰብ ፍቅርን እና ማህበራዊ ትስስርን በመጨመር ቁልፍ የሆነ ሚና ለመጫወት ይችላል፡፡ የቡድናዊ ጽንፈኝነትን ለመከላከል ይችላሉ፡፡ የህብረተሰብ መረብ በመገንባት እና ጥብቅ ትስስርን ያጠናክራሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ከኢትዮጵያ ሕዝቦች 75 በመቶ የሚይዘውን ወጣቱን ሊያሳትፉ እና ሊደግፉ ይችላሉ፡፡

አብይ ከእርስዎ ጋር ነን፡፡ የማንዴላ መንፈስ ከእርስዎ ጋር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከእርስዎ ጋር ናት፡፡ የብርሀናማው ኃይል ከእርስዎ ጋር ነው፡፡

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2015 አቅርቤው በነበረው ማስታዋሻ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዲህ በማለት ጽፌ ነበር፣

“አብይ  የማንዴላን እርምጃ በመከተል እውነተኛ የኢትዮጵያ ጀግና ለመሆን ልዩ ክብር እና መልካም አጋጣሚ አላቸው፡፡ የአፍሪካ ጀግና ይሆናሉ፡፡ ሆኖም ግን በማንዴላ እርምጃ መጓዝ እንዲህ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ መራመድ አለብዎት፡፡ በሰላም፣ በዴሞክራሲ እና በነጻነት ጎዳና ላይ ረዥም ጉዞ ማድረግ አለባቸው፡፡ ብቸኛ ጥያቄ ሆኖ የሚቀርበው እነዚህን ሁሉ መንገዶች ብቻቸውን፣ ከኢትዮጵያ የአቦሸማኔው ትውልድ እና ከማንዴላ መንፈስ ጋር፣ በስደት ከሚኖሩት የዲያስፖራ ማህበረሰብ ጋር፣ ከደከሙት፣ ከድሆች እና የነጻነት አየር ለመተንፈስ ከሚታገለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ወይስ…?“

ግንቦት 20 የእራሴን ጥያቄ መለስኩ፡፡ አብይ ብቻዎትን አይደሉም፡፡ እኛ አንድ መቶ ሚሊዮን የሆንን ጠንካራ ኢትዮጵያውያን ከእርስዎ ጋር እንጓዛለን፡፡ የማንዴላ መንፈስ ከእርስዎ ጋር ይጓዛል፡፡ የብርሀናማው ኃይል ከእርስዎ በእርስዎ ዙሪያ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት ዛሬ፡፡

ኢትዮጵያዊነት ነገ፡፡

ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!    

ግንቦት 15 ቀን 2010 ዓ.ም