ማስታዋሻ ቁጥር 1፡ ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ለኢትዮጵያ አቦሸማኔው (ወጣቱ) ትውልድ፣ 

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም  

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

የጸሐፊው ማስታወሻ፣ ባለፈው ሳምንት “ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተጻፈ የግል ደብዳቤ“ በሚል ርዕስ አቅርቤው በነበረው ትችቴ የወደፊት ምልከታዎቼ ሰላምን ብሄራዊ ዕርቅን፣ አንድነትን እና የኢትዮጵያን ሕዝቦች አጠቃላይ ደህንነት ለማጎልበት በሚመለከቱ ጉዳዮች እና ርዕሶች ላይ ትኩረት እንደማደርግ ቃል ገብቼ ነበር፡፡ አሁን የእርስ በእርስ መካሰስ ውግዘት እና ተገሳጽ ጊዜው አልፏል፡፡ አሁን ጊዜው የመገንባት፣  አብሮ በአንድነት የመቆም እና የመተሳሰብ፣ እርስ በእርስ መካሰስን የማቆም፣ የማስማማት፣ የማዋቀር፣ የማጽዳት፣ የመረጋጋት፣ የማገናኘት፣ ቅርጽ የመስጠት፣ የመጀመር እና አንድ የማድረግ ነው፡፡

እኔ የጥንት ባህላችንን የምከተል ሰው ነኝ፡፡ ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ ትንሽ ቅላጼውን ለወጥ በማድረግ ብቻ ያንኑ የጥንቱን መዝሙር በመዘመር ላይ እገኛለሁ፡፡ በእኔ በልጅነት ዘመን ከሕዝብ ጋር አብረን በመሳተፍ አብረን እንዘምር ነበር፡፡ ዝማሬው አንደዚህ ነበር-

ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ወደፊት!

ህዝብን በሄድክበት ቦታ ሁሉ ታገኛቸዋለህ፣

ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ወደፊት!

እኛ የምናውቃቸው ምርጥ ሕዝቦች ናቸው.

ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አብሮ ለመቆም ጊዜው አሁን ነው!

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሹመታቸው ዕለት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በኢትዮጵያውያን ላይ ተንሰራፍተው የሚገኙትን መጠነ ሰፊ የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በማስወገድ ከድህነት፣ ከበሽታ እና ከድንቁርና ጋር በሚደረገው ትግል ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ከጎናቸው በመሰለፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ እስከ አሁን ድረስ በዲያስፖራው ማህበረሰብ የምንገኝ ብዙዎቻችን ይህንን ነገር ለመቀበል በጣም ስንቸገር ቆይተናል፡፡ አሁን ግን የተናገርነውን ወደ ተግባር ለመለወጥ ፈቃደኞች፣ ችሎታው ያለን እና ዝግጁዎች የሆን አንገኛለን፡፡

ላለፉት አስራሶስት ዓመታት ገደማ ያህል የእኔ ዋናው ትኩረቴ እና ጥረቴ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰብአዊ መብት አያያዝ እንዲሻሻል፣ ቢያንስ 75 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚወክሉት የኢትዮጵያ ወጣቶች መብት መከበር ላይ መስራት እና አንድነት፣ ሰላም እና ብሄራዊ ዕርቅ እንዲሰፍን ታላቅ ተጋድሎ ማድረግ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሁላችንም አንድ ብሄራዊ የኢትዮጵያ ቡድን የመሆን ዕድሉን ተጎናጽፈናል፡፡

እንደ ፖለቲካል ሳይንቲስት፣ የአካዳሚክ ሰው፣ የሕግ ባለሙያ፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች እና የቢሮክራሲ ጥበብ ባለሙያ እንደመሆኔ መጠን በተከታታይ በማቀርባቸው “ማስታዎሻዎች” በተለያዩ መስኮች ያሉኝን ሀሳቦች አካፍላለሁ የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ሆኖም ግን በተከታታይ በማቀርባቸው ማስታዎሻዎች ላይ የእኔ ዓላማ ዝም ብሎ ስብከት ማካሄድ ወይም ደግሞ ሌሎችን የማስተማር ወይም ምክር መስጠትን የመውደድ ጉዳይ አይደለም፡፡ የእኔ ዋናው ዓላማ ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ጠቃሚ በሆኑ መጠነ ሰፊ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች እና ርዕሶች ላይ ጥልቅ፣ በሳል እና አንገብጋቢ የሆኑ ወይይቶችን ለመፈንጠቅ ነው፡፡

በማስታዋሻ ቁጥር 1 ትችቴ ላይ “ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ምን ዓይነት አመራር ያስፈልጋታል?” በሚል ጥያቄ ዙሪያ ጥልቅ ውይይት እና የክርክር መድረክ እፈነጥቀላሁ ብየ አስባለሁ፡፡

ይህ ርዕሰ ጉዳይ በጣም ወቅታዊ ነው ምክንያቱም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ብቃት፣ ችሎታ እና ቅንነት ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች ስላሉ ነው፡፡

እዚህ ላይ እንዲህ የሚለውን የአማርኛ አባባል መጥቀሱ ተገቢነት አለው፣ “ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው“ እናም ለመብረር ቀላል ነው ብሎ ያውጃል፡፡

መሪዎች ዓለምን የልዩነት ሀገር ያደርጓታል፡፡ ለምሳሌም ያህል እ.ኤ.አ በ1994 ዓ.ም የደቡብ አፍሪካ ምርጫ በተቃረበ ጊዜ ሀገሪቱ በመንታ ጎዳና ላይ ነበረች፡፡ ዕጣ ፈንታዋ በመውደቅ ወይም ደግሞ በመዳን ላይ የተንጠለጠለ ነበር፡፡ የጥቂት ነጮች የበላይነት ዘረኝነት በሽብርተኝነት ተግባር ላይ በመሰማራት እና ደቡብ አፍሪካ አውዳሚ ወደሆነ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ እንድትዘፈቅ በማድረግ የዘረኝነት ጦርነትን ለመጫር ፈልገው ነበር፡፡ የጎሳ ቡድኖች ተበሳጭተው እና ጦርነት ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ነበሩ፡፡ አንድ ሰው በእርስ በእርስ ጦርነት እና በሰላም መካከል ቆሞ ነበር፡፡ ኔልሰን ማንዴላ ጊዜውን በመቀየር በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሰላም እና ዕርቅ እንዲሰፍን አድርገዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ እንዳደረጉት ሁሉ ሌላ ማንኛውም ሰው ያንን አስደማሚ የሆነ ነገር ያደርገው ነበር ብሎ ማሰቡ አጠራጣሪ ነገር ነው፡፡

በአፍሪካ መልካም መሪዎች በቀላሉ ሊገኙ የማይችሉ ብርቅዬ ነገሮች ናቸው፡፡ ማህበረሰቡ የታደለ ወይም የለውጥ በረከትን የተጎናጸፈ ከሆነ ከስንት ትውልዶች በኋላ አንድ ጊዜ ብቅ የሚሉ ናቸው፡፡ በርካታ የአፍሪካ መሪዎች መልካም ነገርን በመመኘት፣ ፍትሀዊ እና እውነተኛ በመምሰል የመሪነት ስራቸውን ይጀምራሉ፡፡ ሆኖም ግን መልካም መሪዎች ስልጣንን ካጣጣሙ እና በአመራር የስካር መንፈስ ውስጥ ከተዘፈቁ በኋላ መጥፎዎች ይሆናሉ፡፡ ስልጣን ለእነርሱ እንደ አደንዛዥ ዕጽ ይሆን እና የማይለቅ ሱስ በመሆን ይጠናወታቸዋል፡፡ በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ለመቆየት ሲሉ ማንኛውንም ነገር ያደርጋሉ፡፡ የስልጣን ሱሳቸው የመጨረሻውን እና ከፍተኛውን ቦታ ሲይዝ ፍጹማዊ ስልጣናቸውን መግለጽ ይጀምራሉ፡፡ እንግዲህ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ነው ስልጣንን ለሙስና መጠቀም የሚመጣው እና ፍጹማዊ ስልጣን ፍጹማዊ ሙስና ሊሆን የሚችለው፡፡

በአመራር ላይ ባደረግሁት ጥናት አዳዲስ መሪዎች በጥሩ ፍላጎት የአመራር መስጠት ስራቸውን እንደሚጀምሩ እና ከጊዜ በኋላ ግን የመነሻ ዕይታ እና የመጀመሪያ ተልዕኳቸውን እንደሚያጡ ተገንዝቢያለሁ፡፡ እነርሱ እራሳቸው ቸልተኛ፣ እብሪተኛ፣ ተጣጣፊ እና ፍጹማዊ የሆነ ስልጣንን የሚያራምዱ ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያ ያለፉት 27 የመከራ እና የስቃይ ዓመታት ለዚህ ጉዳይ ተጨባጭ ማስረጃዎች ናቸው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አዳዲስ መሪዎች እራሳቸውን ችለው እራሳቸው የሚሰሯቸውን፣ በውጭ ተጽዕኖ የሚሰሯቸውን እና የሚጠብቋቸውን ነገሮችም ተረድቻለሁ፡፡ እነዚህ ተጽዕኖዎች ደግሞ በወጣት መሪዎች ላይ የጠነከሩ እንደሚሆኑ አምናሁ፡፡ የ41 ዓመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም ከእንደዚህ ዓይነት ተጽዕኖዎች ነጻ ይሆናሉ ብዬ አላምንም፡፡ በተጽዕኖዎች እና በተጻራሪ ፍላጎቶች መስራት ሁልጊዜ ስህተቶችን፣ ተስፋ መቁረጥን እና በአጠቃላይም የሞራል ስብዕናን በማዳሸቅ ለመጨረሻ ውድቀት ይዳርጋሉ፡፡

ከዚህ ቀደም ሲል ለቀረቡት የአመራርነት ሰጭነት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት በርካታ ጉዳዮችን በተለይም በአዳዲስ አመራሮች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ጉዳዮችን እደስሳለሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡

እንደዚሁም ሁሉ ሌሎችም ይህንን ጥያቄ ለመመለስ አስተያየቶቻቸውን በሀሳብ ገበያ ላይ በማቅረብ ለሌሎችም ማካፈል እንደሚችሉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

የአመራርነት ዕቅዴ በኢትዮጵያ፡ የማንዴላ ሞዴል

ኢትዮጵያ ባለፉት ዘመናት የነበሯትን የአመራርነት ዓይነቶችን በማሰላስልበት ጊዜ ብርታትን ሳይሆን ደስታን አጣለሁ፡፡

ታሪክ እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ ነገሥታት በእግዚአብሄር መለኮታዊ ኃይል እንደተቀቡ እና እንደተሾሙ አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ ለምንም ዓይነት ምድራዊ ኃይል ወይም ደግሞ ለማንኛውም ሰው ሰራሽ ሕግ የማይገዙ መሆናቸውን አውጀዋል ምክንያቱም እነርሱ ተጠሪነታቸው ለመለኮታዊ ኃይል ነበር፡፡ እነርሱ እራሳቸውን ከማንም በላይ ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ምድራዊ ሕግ አውጭዎች እንደሆኑ አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ ይህንን በማስመልከት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሲነገር የቆየው የቀድሞ አባባል እንዲህ የሚል ነበር፣ “ሰማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ“

አሁን በቅርቡ ታሪካችን ወታደራዊ መኮንኖች በሶስቱ ማለትም በማርክስ በኤንግልስ እና በሌኒን መጽሐፍ ቅዱስ እና ቀኖናዊ እምነት እየተመሩ “የወዛደሩን አምባገነናዊ አገዛዝ“ በመመስረት ሀገሪቱን ልትወጣው ከማትችለው የእርስ በእርስ ጦርነት እና የመገንጠል አደጋ ላይ የሚጥል አመራርን አውጀው ሲተገብሩ ነበር፡

ላለፉታ 27 ዓመታት አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ገዥዎች እንደ መዥገር በስልጣን ላይ ተጣብቀው ለመቆየት ሲሉ የከፋፍለህ ግዛ ስልትን በስራ ላይ በማዋል “ብሄር ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች“ የሚል ስብከትን ተጠቅመዋል፡፡ እንዲህ የሚል ሕግም በስራ ላይ እንዲውል አድርገዋል፣ “የፖለቲካ ስልጣን የሚገኘው ከጠብመንጃ አፈሙዝ ነው“ ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ በማለት አውጀዋል፣ ”በምርጫ ሳጥን ውስጥ የድምጽ መስጫ ካርድ በመጨመር በጫካ ውስጥ ታግለን ደማችንን አፍስሰን ያገኘነውን ስልጣን ማንም አይወስደውም“ ነበር ያሉት እና አሁንም እያሉ ያሉት፡፡

በአሁኑ ጊዜ የድሮውን ሻጋታ አመራር በማስወገድ አዲስ አመራር ሊሰጡ የሚችሉ እና እንዲህ የሚለውን መርህ ለመተግበር የሚችሉ ወጣት መሪዎችን የማግኘት ዕድሉ አለን፣ “ይህች ቆንጆ የሆነች ሀገር በፍጹም በፍጹም እንደገና አንዱ በሌላው የማትጨቆን እና የዓለም ሁሉ ውራጅ እንዳትሆን ጠንክረን መስራት አለብን፡፡”

አዎ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ኔልሰን ማንዴላን ሊተካ የሚችል ዓይነት ግልባጭ ያላቸው እና በየቦታው መብቶቻቸውን ለማስከበር በሰላማዊ መንገድ የሚጠይቁ ወጣቶች ታድላለች፡፡ መብቶቻቸውን ለመጠየቅ እና በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው የሚገኙትን ባለስልጣኖች ለሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ሕዝባዊ እምቢተኝነት እና ሰላማዊ ተቃውሞን በመሳሪያነት ይጠቀማሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ለማ መገርሳ በርካታ ሚሊዮኖች ወንዶች እና ሴቶች ኢትዮጵያውያን የሰላማዊ ታጋይ አብዮተኞች ሁሉ የማንዴላ ዓይነት ግልባጭ ያላቸው እንደሆኑ አድርጌ አምናለሁ፡፡

ላለፉት አስራ ሶስት ዓመታት የእኔ ህልሜ እና ፍላጎቴ ኢትዮጵያ በማንዴላ ግልባጭ ዓይነት ኢትዮጵያውያን ተጥለቅልቃ ማየት ነው፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያዊነትን የአርበኝነት መዝሙር የሚዘምሩ እና ስለአንድነት ስለሰላም ስለብሄራዊ ዕርቅ፣ ስለእኩልነት እና ስለፍትህ የሚሰብኩ እያየሁ እና እየሰማሁ ነው፡፡

መላዕክ ይሉኛል እኔ ግን መላክ ኃጢያተኛ ከሆነ አላቸዋለሁ።

ማንዴላ እ.ኤ.አ በ1918 ዓ.ም ተወልደው የእድሚያቸውን ምርጥ ዓመታት (ከ1964 – 1990) በእስር ቤት አሳለፉ፡፡ በርካታ ሰዎች ወርቃማውን እድሚያቸውን በሚጨርሱበት ጊዜ ማንዴላ ሰባሁለት ዓመታት እስኪሞላቸው ድረስ በእስር ቤት ነበሩ፡፡ ማንዴላ ፍጹም ተስፋ አልቆረጡም ነበር፡፡ ማንዴላ በ70ዎቹ እና በ80ዎቹ እድሜ ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ደቡብ አፍሪካን ወደ ነጻነት፣ ሰላም እና ዴሞክራሲ መሩ፡፡ እድሜ ቁጥር እንጅ ሌላ ምንም ነገር ያለመሆኑ ትክክል ነው፡፡

ማንዴላ መጥፎ ስሜት ይሰማቸው የነበርበትን ጊዜ እንዲህ በማለት ገልጸው ነበር፣ “27 ዓመታት ያህል ለበዓል ተጉዠ ነበር፡፡ አሳዛኝ ልምድ ቢሆንም ቅሉ ከእራሴ ርቄ ቆሜ የነበረበት ጊዜ እና ስራዎቻችንን ብቻ እመለከት የነበረበት ጊዜ ነው ፡፡ ሆኖም ግን በጣም ጠቃሚ ነበር ምክንያቱም የሰራናቸውን ስህተቶች እና ስኬቶች በጥሩ ሁኔታ እንድንቃኝ እና በጥሩ ሁኔታ ተዘጋጅተን እንድንወጣ አስችሎናል…” ነበር ያሉት፡፡

ማንዴላ በእስር ቤት በነበሩበት ጊዜ ደቡብ አፍሪካን ከአፓርታይድ ወደ ዴሞክራሲ ሽግግገር አዘጋጅተዋት ነበር፡፡

ከኔልሰን ማንዴላ ጋር ለመገናኘት ዕድሉ ቢኖረኝ እመኝ ነበር፡፡ በርካታ ጥያቄዎችን በተለይም ስለድህነት እና በአፍሪካ ተከስቶ ስለሚገኘው ስለፖለቲካ አመራር ክስረት እጠይቅ ነበር፡፡

በእርግጥ ከኔልሰን ማንዴላ ጋር ተገናኝቼ ቃለ መጠይቅ አደረግሁላቸው፡፡

ይህንንም ቃለ መጠይቀ ያደረግሁላቸው እ.ኤ.አ ግንቦት 11 ቀን 2011 ዓ.ም ከእርሳቸው ጋር በነበረኝ ምዕናባዊ ውይይት ነው፡፡

ያደረግነውም ውይይት በአጠቃለይ ስለ አመራር እና አፍሪካ ለምን በአምባገነኖች፣ ፍጹማውያን ባለስልጣኖች እና ጨቋኞች ሰይጣናዊ አመራር እንደወደቀች ነው፡፡

እ.ኤ.አ ታህሳስ 2013 ማንዴላ ከዚህ ዓለም በሞት በተለዩ ጊዜ እንባዬን አውጥቼ አልቅሻለሁ፡፡

“የእኔ አፍሪካዊ ጀግና ልዑል ስንብት” በሚል ርዕስ አዘጋጅቸው በነበረው ትችቴ ከእኔ ጋር በግንባር ተገናኝተን ስለሲቪክ ተዋጊነት እና ስለአፍሪካ ወጣቶች ምን እንደሚወክሉ በአርአያነት ሲያደርጉት ስለነበረው ጉዳይ ጥልቅ ሀዘን ውስጥ ገብቸ ነበር፡፡

ኔልሰን ማንዴላ ድልድይ ገንቢ ነበሩ፡፡ በዘር፣ በጎሳ እና በመደብ ልዩነቶች መካከል ድልድዮችን ገንብተዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ የእሳት አደጋ ሰራተኛ ነበሩ፡፡ የጎሳ እና የዘር ግጭት እሳት ነበልባልን በማጥፋት የደቡብ አፍሪካን ቤት ከመቃጠል አድነውታል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ መንገድ ቀያሽ ነበሩ፡፡ ወደ ነጻነት ረዥም ጉዞ ለመጓዝ  እንዲቻል መልካም ነገር እና ዕርቅ የሚባሉ ሁለት መንገዶችን ቀይሰዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ አርክቴክት ነበሩ፡፡በአፓርታይድ አመድ ላይ የብዙሀን ዴሞክራሲን ውብ ማማ/ህንጻ ገንብተዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ አስማተኛ ነበሩ፡፡ ነጭ እና ጥቁር ዳካዬዎችን ከባርኔጣ ላይ በአንድ ጊዜ በመልቀቅ በነጻነት እንዲበሩ አድርገዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ እስከ ዛሬ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ እጅግ የላቀ የኬሚስትሪ ባለሙያ ነበሩ፡፡ ጥላቻን ወደ ፍቅር፣ ፍርሀትን ወደ ድፍረት፣ ጥርጣሬን ወደ እምነት፣ አለመቻቻልን ወደ ታጋሽነት፣ ቁጣን ወደ መግባባት፣ ጥላቻን ወደ ስምምነት እና ውርደትን ወደ ክብር ለውጠዋል፡፡

እንደሁልጊዜው ስለኢትዮጵያ ወጣቶች በተለይ እና ስለ አፍሪካ ወጣቶች በአጠቃላይ አዕምሮዬን ስለሚያስጨንቁኝ ጉዳዮች ጥያቄዎቼን አዘጋጀሁ፡፡ እንዲህ በማለት እራሴን ጠየቅሁ፣ “ብልሁ የአፍሪካ አንበሳ ለእረፍት የለሾቹ የኢትዮጵያ ወጣት አቦሸማኔዎች ምን ይላል?”

የእርሳቸው መልዕክት ለኢትዮጵያ ወጣቶች ታላቅ ድፍረትን ይሰጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ ህብረተሰቡን ከመለወጥ በፊት እራሳችሁን ለውጡ፡፡ ጀግናይቱን አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር በገባችሁት ቃልኪዳን መሰረት ደግማችሁ ደጋግማችሁ ሞክሩ በምንም ዓይነት እጅ እንዳትሰጡ፡፡ አንድነትን አጠናክሩ፡፡ የዓላማ ጽናት ይኑራችሁ፡፡ አርበኞች ሁኑ፡፡ ደፋሮች ሁኑ፡፡ ታላቅ ነገርን አልሙ፡፡ ከኋላ ሆናችሁ ምሩ፡፡ መከራ እና ስቃይ ሊኖር እንደሚችል ጠብቁ፡፡ ከጠላቶቻችሁ ጋር ሰላምን አውርዱ፡፡ ድህነትን ተዋጉ፡፡ ከመርህ ዝንፍ እንዳትሉ፡፡ ብሩህ ተስፋ እና የዓላማ ጽናት ያላችሁ ሁኑ፡፡ የአፍሪካ ወጣቶች ብሩህ ተስፋ ያላቸው እንደሆኑ ማንዴላ ይነግሯቸዋል ምክንያቱም የአፍሪካ መልካም ቀኖች በመምጣት ላይ ናቸው፡፡ ከሕዝቡ ተማሩ እንዲሁም ሕዝቡን አስተምሩ፡፡ በፍጹም ግድየለሾች አትሁኑ፡፡ ወደ ነጻነት፣ ወደ ዴሞክራሲ እና ወደ ሰብአዊ መብት መከበር ቀላል የሚባል ጉዞ የለም፡፡ ሁልጊዜ መልካም ነገሮችን አድርጉ፣ ይቅርታ ማድረግን፣ እርቀ ሰላም ማውረድን…

በአፍሪካ የመልካም አመራር መለኪያ ኔልሰን ማንዴላ እንደሆኑ አምናለሁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የኢትዮጵያ የአቦሸማኔው ትውልድ (ወጣቱ ትውልድ)፣ ስለአመራር ሰጭነት  ዕቅዳችሁ ምንድን ነው?

ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ እ.ኤ.አ በ1967 በፊላደልፊያ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች “የህይወታችሁ ዕቅድ ምንድን ነው?“ በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ በነበረው መሳጭ ንግግራቸው (እዚህ ጋ በመጫን ያዳምጡ) እንዲህ ብለው ነበር፣ “አንድ ሰው መንገድ አንዲያጸዳ የሚጠራ ቢሆን ሚካኤል አንጀሎ እንደሳለው ስዕል ወይም ቤት ኦቨን እንዳዘጋጀው ሙዚቃ ወይም ሸክስፒር እንደጻፈው ግጥም ቆንጆ አድርጎ መንገዱን በጥሩ ሁኔታ ማጽዳት  አለበት፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ የማጽዳት ስራውን በመልካም ሁኔታ የሚያጸዳ ከሆነ በቤተ ሰማያት እና በምድር ላይ ያሉ ፍጡሮች ሁሉ እዚህ ስራውን በጥሩ ሁኔታ የሚሰራ አንድ መልካም መንገድ ጠራጊ/አጽጅ አለ በማለት ይነገርለታል፡፡

ዛፍ ለመሆን ባትችል እንኳ ቁጥቋጦ ሁን፡፡ አውራ ጎዳና ለመሆን ባትችል እንኳ ጥርጊያ መንገድ ለመሆን ሞክር፡፡ ፀሐይ ለመሆን ባትችል እንኳ ኮከብ ሁን፡፡ የምታሸንፈው ወይም ደግሞ የምትወድቀው በመጠን እንዳልሆነ ሁሉ ምንጊዜም ምርጥ ለመሆን ጥረት አድርግ፡፡

ስለሆነም ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ለኢትዮጵያ አቦሸማኔው ትውልድ የማቀርበው ጥያቄ እንዲህ የሚል ይሆናል፣ “ጠቅላይ ሚኒስትር ተብሎ የሚጠራ ሰው የአመራር ዕቅድ ምን መሆን ይኖርበታል? የኢትዮጵያ አቦሸማኔዎች የአመራር ዕቅድ ምን መሆን ይኖርበታል?“

ለእኔ ፈጣኑ ምላሸ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የእመርታዊ ለውጥ መሪ መሆን አለባቸው የሚል ነው፡፡ ልክ እንደ ኔልሰን ማንዴላ፡፡ ዓለም በአሁኑ ጊዜ ልክ እንደ ማርቲን ሉተር ኪንግ መልካም የመንገድ ጠራጊ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ማንዴላ ምርጥ የሞራል እና የፖለቲካ መሪ ናቸው በማለት ያውጃል፡፡ ማንዴላም እራሳቸውም መልካም የመንገድ ጠራጊ ነበሩ፡፡ የደቡብ አፍሪካን መንገዶች ከአፓርታይድ፣ ከዘረኝነት፣ ከአድሏዊነት እና  ከኢፍትሀዊነት ሰይጣናዊ ድርጊት አጽድተዋል፡፡ በእኔ አስተያያት አፍሪካ እስከ አሁን ድረስ ካሏት መንገድ ጠራጊዎች ተመራጭ ነበሩ፡፡

እስቲ ወደ ኋላ መለስ በማለት ነገሩን ግልጽ ላድርገው፡፡ የእራሴን ጥያቄ ከእራሴ አመለካከት አንጻር በማየት ምላሽ የምሰጥበት ቢሆን ኖሮ ሄንሪ ዴቪድ ቶሪዬ “ለሕዝባዊ እምቢተኝነት” ከሰጡት እንዲህ ከሚለው መልስ ጋር ተመሳሳይ ይሆን ነበር፣ “ትንሽ የሚገዛ ወይም አመራር የሚሰጥ መንግስት ተመራጭ ነው“ ቶሪዬ በመንግስት ላይ እምነት የለውም፡፡ እናም ግለሰቦች ትክክለኛውን ከስህተቱ ለመለየት የሞራል ግዴታ አለባቸው ብሎ ያምናል፡፡ እንዲህ በማለትም ጽፏል፣ “መንግስት አንዳንድ ጊዜ በእራሱ መንገድ የማይገኝ ከሆነ በአሜሪካ ሕዝቦች ውስጥ ያሉ ባህሪያት ሁሉን ነገር ያደርጋሉ፣ እንዲያውም ከዚያም የበለጠ መስራት በቻሉም ነበር፡፡“

በኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ ያሉ ነባራዊ ባህሪያት ማለትም ባህሪዎቻቸው እሴቶቻቸው፣ እምነቶቻቸው እና ልምዶቻቸው ለሺህ ዘመናት የተከናወኑትን ሁሉ አከናውነዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከዚህም የበለጠ በርካታ ነገሮችን ማከናወን በቻሉ ነበር፣ ሆኖም ግን በእነዚህ መብት ደፍጣጮች እና ጨቋኝ ገዥዎች አማካይነት በወታደራዊ ኃይል መብቶቻቸው፣ ርዕዮተ ዓለማቸው እና ሌሎች መብቶቻቸው ሁሉ ስለሚደፈጠጡ ነው፡፡

እንደ ቶሪዬ ሁሉ መንግስት የለም ወይም መሪዎች የሉም አልልም ሆኖም ግን የተሻለ መንግስት እና የተሻሉ መሪዎች እንዲኖሩ ጥረት አደርጋለሁ፡፡

እያንዳንዱ ሰው ምን ዓይነት አክብሮት የሚሰጥ መንግስት እንደሆነ ማወቅ እና ያንን ለማግኘት ይህ ወደፊት የሚደረግ አንድ እርምጃ  ነው፡፡

ቶሪዬ እንደሚያምነው ሁሉ ምርጥ መንግስት ማለት ትንሽ የሚያስተዳድር ነው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በኢትዮጵያ  ውስጥ ምርጥ መንግስት የሚባለው ሕዝቡን የሚያከብር እና ትንሽ አመራር የሚሰጥ ነው፡፡ እንደ ኔልሰን ማንዴላ ሁሉ እርሳቸው ከኋላ ሆነው ሌሎችን ከፊት እንዲመሩ መፍቀድ ማለት ነው፡፡ ማንዴላ እንዲህ ነበር ያሉት፣ “ከኋላ ሆኖ መምራት የተሻለ ነው ሌሎች ደግሞ ከፊት ሆነው እንዲመሩ በተለይም በዓላት በሚከበሩበት እና መልካም ነገሮች በሚከሰቱበት ጊዜ ማድረግ መልካም ነገር ነው፡፡ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ግን ፊት በመሆን የመሪነት ቦታውን መያዝ ተገቢ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ሕዝቡ አመራራችሁን ያደንቃል“ ነበር ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ መልካም መሪ ማለት ወጣቶችን ከፊት በማድረግ እርሱ ከኋላ ሆኖ የሚመራ መሆን እንዳለበት አምናለሁ፡፡

ሕዝቦቻቸውን በማይፈሩ እና ለሕዝቦቻቸው ክብር በማይሰጡ መንግስታት እና መሪዎች ላይ ቶሪዬ ሕዝባዊ እምቢተኝነትን እንደተማጸነ ሁሉ እኔም ላለፉት አስራ ሶስት ዓመታት ገደማ ያህል ስታገልለት እንደቆየሁት ማድረግ ነው፡፡

እንግዲህ ስለመንግስታት እና መሪዎች እስከ አሁን ድረስ ያቀረብኩት የግል ምርጫዬ ይህን ይመስላል፡፡

ጥያቄ ሆኖ የሚቀርበው በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ክብር የሚሰጥ እምነታቸውን ሊያገኝ የሚችል እና ሙሉ እምነት ሊጥሉበት የሚችል አመራር እና መንግስት ነው የሚለው ነው፡፡

ፕሮፌሽናል ሞያችን መንግስትን ፖለቲካን እና መሪዎችን የሚያጠና ሞያ ያለን ሰዎች መሪዎች በተለያዩ መንገዶች የተለያዩ መርሆችን ይዘው እንደሚመጡ እናጠናለን፡

“የዘመናዊ ፖለቲካ አባት” እየተባለ የሚጠራው ኒኮሎ ማኪያቬሊ (ልዑል በተባለው መጽ ሐፍ ምዕራፍ 17 ላይ) እንደህ በማለት የክርክር ጭብጡን አቅርቧል፣ “መሪዎች ከሚፈቀሩ ይልቅ ቢፈሩ የተሻለ ነው“ የስልጣን ፍቅር ከፍቅር ኃይል የበለጠ ኃይለኛ ነው የሚል እምነት አለው፡፡

ልዑል ሁለት ምርጫዎች ብቻ እንዳሉት ያምናል፣ እነርሱም መልካም ነገር እና ውድመት ናቸው፡፡ የውድመት ኃይል ከፍቅር ኃይል ይልቅ መንግስትን የመያዝ ኃይል ነበረው ብሎ ያምናል፡፡

ጋንዲ ለማኪያቬሊ እንዲህ የሚል መልስ አላቸው፣ “በታሪክ አምባገነኖች እና ገዳዮች ለጊዜው የማይበገሩ ኃይለኞች መስለው ይታያሉ፡፡ ሆኖም ግን በመጨረሻ ተሸንፈው ይወድቃሉ ሁልጊዜ“ ነበር ያሉት፡፡

እኛ  ባለንበት በአሁኑ ጊዜ ተቃራኒው እውነት እንደሆነ እናውቃለን፡፡ የፍቅር ኃይል በስልጣን ኃይል ላይ ድልን ይቀዳጃል፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ እና ማንዴላ ይህንን እውነታ በተጨባጭ አረጋግጠውታል፡፡

እንደዚሁም ሁሉ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ሐዋርያ የሆነው ቴዎድሮስ (ቴዲ አፍሮ) ካሳሁን) “ፍቅር ሁሉንም ያሸንፋል“ በማለት አቀንቅኗል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የአቦሸማኔው ትውልድ ሊመርጧቸው የሚችሉ በርካታ የአመራር ሞዴሎች አሉ፡፡ ከሁሉም በላይ የእራሳቸውን እና የሀገራቸውን ዕጣ ፈንታ ሊቆጣጠሩ የሚችሉበት ጊዜው አሁን ነው፡፡ የሚሻለውን ለመምረጥ ነጻ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ የአቦሸማኔው ትውልድ አባላት ላለፉት 27 ዓመታት በፈላጭ ቆራጭ እና በአምባገነናዊ አገዛዝ መከራቸውን እና ስቃያቸውን ሲያዩ ቆይተዋል፡፡ በጭካኔ በኃይል እና በፍርሀት የሚገዙ አናሳ የማስተዳደር ብቃት ባላቸው ገዥዎች መገዛትን አይፈልጉም፡፡ የሕዝብን ስሜት የሚያነሳሱ፣ የሚያነቃቁ እና የሕዝብን ሀሳብ የሚያሰባስቡ መሪዎችን መፍራት ይፈልጋሉ፡፡ በተለያዩ መስኮች ሞያ ያላቸውን ቴክኒካዊ መሪዎችን መምረጥ ይፈልጋሉ፡፡ ለመምረጥ ነጻ ናቸው ምክንያቱም ህይወታቸው፣ የወደፊት ዕድላቸው እና ዕጣ ፈንታቸው ነው፡፡

ሕዝብ ኔልሰን ማንዴላን በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ እንደ ሞዴል መሪ አድርጎ በመውሰድ የሚከተል ከሆነ እውነተኛ መሪ ይነሳል፡፡

ኔልሰን ማንዴላ በኢትዮጵያ ውስጥ የአመራር እና የመሪነት ብቃት ናሙና መሆን አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ማንዴላ የእመርታዊ ለውጥ መሪ ነበሩ፡፡ የእርሳቸው የአመራር ዘይቤ እና ተግባር ደቡብ አፍሪካን እንደ ሀገር ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሸጋገር ብቻ አልነበረም፣ ሆኖም ግን እራሳቸው ምሳሌ ሆነው ጥቁር እና ነጭ ደቡብ አፍሪካውያንን በማስማማት ለመጨው ትውልድ ዘላለማዊ ቅርስ አስቀምጠው በማለፋቸው ጭምር እንጅ፡፡

ማንዴላ ምንም ማድረግ በማይቻልበት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ከባቢ ሁኔታ ላይ ሆነው የሰሩ መሪ ናቸው፡፡ ሁሉም የምጽአት ቀን ትንበያ ነቢያት ሁሉ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የደም ጎርፍ ይፈሳል በማለት ተንብዬው ነበር፡፡

ማንዴላ የማይቻል የሚመስለውን ነገር እንዴት ተግባራዊ ለማድረግ ቻሉ? የተወሰኑ መርሆዎችን በመተግበር፣ የተወሰኑ እምነቶችን በመከተል እና የተወሰኑ አመለካከቶችን በመያዝ አሸናፊ ለመሆን በቅተዋል፡፡

ማንዴላ ሁሉ አቀፍ አሳታፊነትን ተግብረዋል፡፡ እያንዳንዱ ደቡብ አፍሪካዊ ዜጋ ስለሀገሩ አንድ ዓይነት ርዕይ እንዲኖረው በማድረግ የአፓርታይድን የጭቆና አገዛዝ ድል ለማድረግ ችለዋል፡፡ ዘልዳ ግራንጌ የተባለችዋ ወጣት እና በአፓርታይድ ክብካቤ ውስጥ ያደገችው ነጭ ደቡብ አፍሪካዊ ዜጋ የማንዴላ ግላዊ እረዳት እና የሚስጥር ተካፋይ የነበረችው በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ጊዜ ብቻ አልነበረም፡፡ ሆኖም ግን ከዚህም ባለፈ ሁኔታ ስልጣን ከለቀቁም በኋላ አልተለየቻቸውም ነበር፡፡ እንዲህ በማለት ስለማንዴላ ተናግራ ነበር፣ “በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ሕዝቦች መልካም ዕድልን እንደሚጎናጸፉ ለዓለም ሕዝብ ለማሳየት ሞክረዋል“ ብላለች፡፡ አንድ መሆናችንንም ለዓለም ሕዝብ አሳይተዋል” በማለት አስተያየቷን ደምድማለች፡፡

ማንዴላ ሕዝቦቻቸውን ያከብራሉ፡፡ ሕዝቡ እስከ አሁን ድረስ ከእርሳቸው ከግላቸውም ሆነ ከአጠቃላይ የጋራ አመራር በላይ አዋቂ እና ብልህ እንደሆነ በሚገባ ያውቁታል ይግባቡታልም፡፡ ለዚህም ነው ሕዝቡን ከኋላ ሆነህ ምራ የሚሉት፡፡

ማንዴላ ከመልካም አስተዳደር ርዕይ በላይ የዘለቁ ህልሞች ነበሯቸው፡፡ አንዱ ታላቁ ህልማቸው ሰላሟ የተጠበቀ አንዲት የአፍሪካ አህጉርን በእራሷ ቆማ ማየት ነው፡፡

ማንዴላ በእውቀት ኃያልነት ያምኑ ነበር፡፡ ይህንንም በማስመልከት እንዲህ ብለው ነበር፣ “ትምህርት ዓለምን ለመቀየር የምትችልበት ታላቅ መሳሪያ ነው“ ነበር ያሉት፡፡

ማንዴላ እምነታቸውን ለማራመድ ድፍረት ነበራቸው፡፡ እንዲህ በማለት ተናግረዋል፣ “ከጠላቶቻችሁ ጋር ሰላምን ለማምጣት ከፈለጋችሁ ከጠላቶቻችሁ ጋር አብራችሁ መስራት አለባችሁ፡፡ ከዚያም ጠላቶቻችሁ ተቀይረው ወዳጆቻችሁ ይሆናሉ“ ነበር ያሉት፡፡

ማንዴላ ምንም ዓይነት ቂምን ሳይዙ የይቅርታ ምህረትን ያደርጉ ነበር፡፡ ለዚህ በጎ ምግባራቸውም ማረጋገጫ ይሆን ዘንድ እንዲህ ብለው ነበር፣ ”በአሁኑ ጊዜ ቀደም ሲል ወደ እስር ቤት ወርውረውኝ ከነበሩት፣ ባለቤቴን ካሰቃዩአት፣ ልጆቼን ከአንዱ ትምህርት ቤት ወደ ሌላው ሲያሳድዱ… ከነበሩ ሰዎች ጋር አብሬ በመስራት ላይ እገኛለሁ፡፡ እናም እንዲህ ከሚሉት ሰዎች መካከል አንዱ ሆኛለሁ፣ ‘ያለፈውን እንርሳው፣ ስለአሁኑ ብቻ እናስብ’“ ነበር ያሉት፡፡

ማንዴላ በእውነት እና በእርቅ ያምኑ ነበር፡፡ ከእስር ቤት ከተፈቱ በኋላ ይጨነቁባቸው እና ቅድሚያ ይሰጧቸው ከነበሩት ጉዳዮች መካከል አንዱ እውነትን በመናገር በሀገሪቱ ውስጥ እውነተኛ ፈውስን ማምጣት ነበር፡፡ የደቡብ አፍሪካ የእውነት እና የዕርቅ ሞዴልነት በሁሉም የዓለም ሀገሮች ላይ ተቀድቷል፡፡

ማንዴላ በዴሞክራሲ ያምኑ ነበር፡፡ እንዲህም ይሉ ነበር፣ “ብዝሀነታችን አይደለም እንድንከፋፈል ያደረገን፣ ወይም ደግሞ የጎሳ ስብጥራችን አይደለም፣ ወይም ኃይማኖታችን ወይም ባህላችን አይደለም እንድንከፋፈል ያደረገን፡፡ ነጻነታችንን ተጎናጽፈን ስለምንገኝ በመካከላችን አንድ ክፍፍል ብቻ አለ- ይህም ማለት ዴሞክራሲን በሚያራምዱ እና በማያራምዱት መካከል“ ነበር ያሉት፡፡

ማንዴላ በእኩልነት እና በፍትሀዊነት ያምኑ ነበር፡፡ ይህንንም በማስመልከት እንዲህ ብለው ነበር፣ “ዘረኝነትን እጠላለሁ ምክንያቱም ከጥቁር ወይም ከነጭ ሰው እንደመጣ አረመኔነት አድርጌ ስለምመለከተው ነው“ ነበር ያሉት፡፡

ማንዴላ በፍቅር ኃይል ያምኑ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ከአንድ የምርጫ የስልጣን ዘመን በኋላ ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው ሲለቁ የስልጣን ፍቅር የሌላቸው መሆናቸውን አስመሰከሩ፡፡ ማንዴላ እንዲህ ብለው ነበር፣ “በቆዳው ቀለም፣ ወይም በማንነቱ ወይም ደግሞ በኃይማኖቱ ምክንያት ማንም ማንንም እንዲጠላ ሆኖ የተፈጠረ የለም፡፡ ሕዝቦች መጥላትን መማር አለባቸው:: መጥላትን መማር ከቻሉ ደግሞ ፍቅርን መማር አለባቸው፡፡ ፍቅር ለሰው ልጅ ልብ በተፈጥሮ ከተቃራኒው ይልቅ የቀረበ በመሆኑ ነው” ነበር ያሉት፡፡

ማንዴላ ከፍተኛ የሆነ ምሁራዊነት ስሜት ነበራቸው፡፡ ከእራሳቸው እና ከሌሎችም ጋር ሰላም ነበራቸው፡፡ ርህራሄ ነበራቸው፡፡ ከእራሳቸው ጎሳ አልፈው ሰውን በሰውነቱ ብቻ ይወዱ ነበር፡፡ ኃይል ያለውን የጥላቻን ስሜታዊነት ድል አድርገዋል፡፡ ከእስር ቤቱ ቅጥር ግቢ በመውጣት ወደ በሩ በደረስኩ ጊዜ ነጻ ለመውጣት መቃረቤን ተገነዘብኩ፡፡ በቀልን እና ጥላቻን ጥየ እስካልወጣሁ ድረስ እዚያው እስር ቤት ውስጥ መቆየት አለብኝ ነበር ያሉት፡፡

ማንዴላ ጥሩ አድማጫ ነበሩ፡፡ ሁሉንም በእርጋታ ያዳምጡ ነበር፣ እናም የጥድፊያ ውሳኔ ለመስጠት አይቸኩሉም ነበር፡፡ ትህትናን የተላበሱ ሰው ነበሩ፡፡

ማንንዴላ ጥልቅ አሳቢ ነበሩ፡፡ ነገሮችን ከብዙ አቅጣጫ መመርመር የሚችሉ መሪ ነበሩ፡፡ ትልቁን እና ትንሹን ስዕል ማየት የሚችሉ መሪ ነበሩ፡፡

ማንዴላ ጠንካራ እምነት የነበራቸው መሪ ነበሩ፡፡ እንዲህ በማለት የተናገሩትን በተግባር ፈጽመዋል፣ “በህይወት ዘመኔ እራሴን ለአፍሪካ ሕዝቦች ትግል መስዋዕት አድርጊያለሁ፡፡ የነጮችን እና የጥቁሮችን የበላይነት በጽናት ተዋግቻለሁ፡፡ ሁሉም ሕዝቦች በፍቅር እና በእኩል እድል በአንድነት የሚኖሩበትን ለዴሞክራሲ እና ነጻ ሕዝብ እታገላሉ፡፡ ይህን መርህ ለመኖር እና እውን ለማድረግ ተስፋ የማደርገው ነገር ነው… አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ለመሞት ዝግጁ የሆንኩበት እምነቴ ነው“ ነበር ያሉት፡፡

ማንዴላ የበቁ የመልካም ግንኙነት አለቃ ነበሩ፡፡ ይህንን አስመልክቶም እንዲህ ብለው ነበር፣ “አንድን ሰው በሚገባው ቋንቋ የምታናግረው ከሆነ ወደ ጭንቅላቱ ይገባል፡፡ በሚገባው ቋንቋ የምታናግረው ከሆነ ወደ ልቡ ይገባል፡፡“

ማንዴላ በሰው ማንነት ላይ በፍጹም ተስፋ አልቆረጡም ነበር፡፡ እንዲህም ብለው ነበር፣ “የእኔ እምነት በሰው መሆን ላይ በጥብቅ በሚፈተንበት ጊዜ በጣም ጨለማ ክስተቶች ነበሩ ሆኖም ግን ለተስፋየለሽነት እጀን አልሰጠሁም ወይም መስጠት አልቻልኩም ነበር፡፡ ያ መንገድ መሸነፍ እና ሞትን ያመጣል“ ነበር ያሉት፡፡

ማንዴላ በወጣቶች ይመሰጡ ነበር፡፡ እንዲህም ብለው ነበር፣ “ወጣቶች በሚቀሰቀሱበት ጊዜ የጭቆናን ማማ ለማውረድ እና የነጻነትን ባነር ለመስቀል ብቁ ናቸው፡፡ በእርግጥም እውነት ነው!“ ነበር ያሉት::

ማንዴላ የተግባር ሰው ነበሩ፡፡ አመጸኛ፣ ተዋጊ እና መሪ ነበሩ፡፡ ከ27 ዓመታት የእስር ቤት ቆይታ በኋላ ማንዴላ ከእስር ቤት ወጡ እና አፓርታይድን ድል አደረጉ፡፡

ማንዴላ ሁሉንም ነገር ይቻላል የሚል መንፈስ ነበራቸው፣ እናም ሁልጊዜ በተስፋ እና በብሩህ አመለካከት የተሞሉ ነበሩ፡፡

ማንዴላ የክቡር መንፈስ ባለቤት ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ በ1964 ዓ.ም በሮቢን ደሴት በእስር ላይ በነበሩበት ጊዜ በሪቮኒያ የፍርድ ቤት ችሎት ላይ የሞት ቅጣት በይኖባቸው የነበረውን ዳኛ ሌሎች በእርሳቸው ላይ መከራ እና ስቃይ ያደረሱባቸውን ሰዎች የፕሬዚዳንትነት የመክፈቻ ስነስርዓት በዓላቸው በሚከበርበት ዕለት እንዲገኙ ዋና ተጋባዥ እንግዳ በማድረግ ጠርተዋቸው ነበር፡፡ እንደህ ብለው ነበር፣ “ከእስር ቤቱ ቅጥር ግቢ በመውጣት ወደ በሩ ስደርስ ወደ ነጻነት  የሚመራኝ መሆኑን አውቅ ነበር፡፡ በቀልተኝነትን እና ጥላቻን እዚያው ጥየው የማልወጣ ከሆነ እስከአሁንም ድረስ እዚያው እስር ቤት ውስጥ መሆን አለብኝ“ ነበር ያሉት፡፡

ማንዴላ ጽኑ አቋም ያላቸው መሪ ነበሩ፡፡ እንዲህ በማለትም መክረዋል፣ “ሰዎች ሁሉ በእናንተ ላይ እምነት እንዲጥሉ እርግጠኞች ሁኑ፡፡ ስለእነርሱ እንደምትጨነቁ እና እያንዳንዱ የምታከናውኑት ነገር ሁሉ በትክክል እና ስለእነርሱ በማሰብ መሆኑን እንዲያውቁት አድርጉ፡፡ በእምነት ላይ የተመሰረተ የእራሳችሁን ቡድን አቋቁሙ“ ነበር ያሉት፡፡

አብይ አህመድ እንደማንዴላ ግልባጭ?

መቸም ቢሆን አንድ ኔልሰን ማንዴላ ብቻ ነው የሚኖረው፡፡

ቀሪዎች ሌሎች የእርሳቸውን የእግር ኮቴ ለመከተል ጥረት ማድረግ አለብን፡፡ እድለኞችም ከሆንን የእርሳቸው ግልባጭ መሆን አለብን፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ በርካታ የሆኑ የማንዴላ ዓይነት እሴቶችን እመለከታለሁ፡፡

በቪዲዮ ንግግር ሲያደርጉ ተመልክቻለሁ፡፡

በፍርድ ቤት ችሎት ላይ ዳኞች ምስክሮችን በመጥራት ስለእውነታው ለማጣራት እንደሚያደርጉት ጥናት እና ግምገማ ሁሉ እንደዚሁም በተመሳሳይ መልኩ የእርሳቸውን ንግግሮች እና ሕዝብ በተሰበሰበበት ሁሉ እየተገኙ የሚያሰሟቸውን ዲስኩሮች ለመገምገም ከበቂ በላይ እድሎችን አግኝቻለሁ፡፡

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ባደረግሁት ምልከታ አብይ አህመድ መንገድ ለመገንባት ጥረት ሲያደርጉ አይቻለሁ፡፡ የሰላም ጠበቃ ናቸው፡፡ በጎሳ፣ በኃይማኖት፣ በቋንቋ እና በክልላዊ መስመሮች ላይ ሰላም እንዲኖር የማሳለጥ ስራን የሚሰሩ ናቸው፡፡ ስለአንድነት፣ ሰላም፣ ነጻነት እና ዴሞክራሲ ጎሳ እና ኃይማኖትን ሳይለዩ ለሁሉም አንድ ዓይነት መልዕከት አላቸው፡፡ እንዲህ ይላሉ፣ “አንድ ሕዝብ ነን፡፡ አንድነታችን ጥያቄ ሊቀርብበት የሚችል ጉዳይ አይደለም፡፡ ችግር ፈጣሪዎች በስልጣን ላይ ያሉት መሪዎች ናቸው፡፡ መፍትሄውም በሕዝቡ እጅ ነው ያለው፡፡ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ በኢትዮጵያ ሕዝቦች እጅ ነው፡፡ መሪዎች የሕዝቡን እምነት የማያገኙ ከሆነ ካሉበት የስልጣን መንበር ላይ መወገድ አለባቸው“ ነው ያሉት፡፡

እኔ የእርሳቸውን ቀጥተኛ የሆነ ንግግር እወድላቸዋለሁ፡፡ የሚያደርገውን የሚናገር፣ የሚናገረውን የሚተገብር ሰው እወዳለሁ፡፡

እኔ እስከ አሁን ባየሁት እና በሰማሁት ነገር በጣም ተበረታትቻለሁ፡፡

በቅርቡ በመቀሌ ከተማ በመገኘት አካሂደውት በነበረው ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የማንዴላ ዓይነት እሴቶች ተንጸባርቀውባቸዋል፡፡

እንግዳ በሚመስል ዓይነት በስልጣን ላይ ላሉት እውነታውን ይናገሩ ነበር ምክንያቱም እርሳቸውም ሆኑ ጓደኞቻቸው በስልጣን ላይ ናቸውና፡፡

ችግሩ ያለው ከኢትዮጵያ ሕዝቦች አይደለም፣ ሆኖም ግን ችግሩ ያለው የኢትዮጵያ መሪዎች እየሆንን ሳይሆን እየመሰልን በምንመራ አመራሮች ላይ ነው፡፡ ችግሩ ያለው ወደ ስልጣን ሲመጡ ቃል ገብተውት የነበረውን በማክበር ባለመስረቅ ባለመስረቅ (ሁለት ጊዜ አጽንኦ ተሰጠ) መምራት በማይችሉ መሪዎች ነው፡፡

“ንግግራቸውን በመቀጠል እንዲህ ብለዋል፣ “አብዛኞቹ በስልጣን ላይ ያሉት ሌቦች ናቸው፡፡ ጠቂቶቹ የሚዘርፉ ከሆነ እና በዘረፉት ሀብታም ሆነው ሌሎቹ የሚራቡ ከሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ሊኖር አይችልም፡፡“ እንዲህ በማለት ገልጸዋል፣ “ሕዝብን በመዝረፍ ሀብታም የሆኑ ሰዎች መርዝን አግኝተዋል፡፡ ልጆቻችንን ያወድማል፡፡ ደኃውን በመዝረፍ ገንዘቡን ወደቤት ማምጣት ማለት ለልጆቻችን መርዝ እንደመመገብ ማለት ነው፡፡“

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ቁጥር 1 ሥራ ብሄራዊ አንድነታችንን ለመገንባት በአንድነት መስራት ነው ብለዋል፡፡ “ከአንድነት ይልቅ በማንነታችን ላይ የበለጠ ትኩረት በማድረግ ጊዚያችንን በከንቱ አባክነናል፡፡ ለወጣቶች ስለኢትዮጵያዊነት በማስተማር እና በመስበክ እርስ በእርስ በጥላቻ ዓይን እንዳንተያይ በትጋት መስራት ፍጹም የሆነ አስፈላጊ ነገር ነው“ ነበር ያሉት፡፡

ንግግራቸውን በመቀጠል እንዲህ ብለዋል፣ “በሕዝቦች መካከል ጥላቻ እና ግጭትን በመፍጠር የገንዘብ ጥቅም የሚያገኙ ሰዎች አሉ፡፡ እኛን በመከፋፈል እና ስምምነትን በማጥፋት ከመካከላችን የሚነግዱ እና ጥቅም የሚያገኙ አሉ፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ነው የዕለት እንጀራቸውን የሚያገኙት“ ነበር ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አለቆቻችን ለመሆናቸው እውቅና መስጠት አለብን፡፡ ወሬን በማውራት ብቻ ስራችንን በአግባቡ መስራት ካልቻልን ቦታውን እኛን በማስወገድ ስራውን በትክክል ለሚሰሩ መሪዎች ይሰጣሉ፡፡ በሕዝቦች መካከል ግጭት እና ክፍፍልን በመፍጠር ስልጣንን መያዝ አይቻልም፡፡ ሕዝቦች የሚከፋፍሏቸውን እና በመካከላቸው ጥላቻ የሚፈጥሩትን አይፈልጉም፡፡ ሕዝቦች እራሳቸው መበየን የሚችሉ ዳኞች ናቸው፡፡

መሪዎች ነን እያሉ ከሚመጻደቁት ይልቅ ህዝቦች የበለጠ ብልህ እንደሆኑ እውቅና ሰጥተዋል፡፡ ህዝቦች የእራሳቸውን ችግሮች እራሳቸው ያውቃሉ፡፡ አርሶ አደሮች የሌሎችን አርሶ አደሮች ችግሮች ያውቃሉ፡፡ ደኃ ህዝቦች የደኃ ህዝቦችን ችግሮች ያውቃሉ፡፡ መሪዎች ግን የእራሳችንን ሚና እረስተናል፡፡ ይህ የእራሳችን ችግር እና ስህተት ነው ብለዋል፡፡

እንደዚሁም ሁሉ የእራሳቸውን አመራርነት እንዲህ በማለት አስጠንቅቀዋል፣ “በሽታው ያለው ከእኛው ከመሪዎች ጋር ነው፡፡ እራሳችንን ቀጥተኛ በምናደርግበት ጊዜ ሕዝቡ ለረዥም ዘመናት አብሮት በቆየው ባህላዊ የችግር አፈታት ዘዴ መሰረት ለችግሮቹ መፍትሄ ይሰጣል፡፡ ህዝቡ ለዘመናት አብሮ በፍቅር እና በሰላም የኖረ ሕዝብ ነው፡፡ በጋብቻ እና በደም ተሳስሯል“ነበር ያሉት፡፡

እርሳቸው ያለምንም አሻሚነት ሀሳባቸውን እንዲህ በማለት ግልጽ አድርገዋል፣ “ኢትዮጵያን በሰላም እና በዴሞክራሲ ስርዓት ማስተዳደር ብቸኛው መንገድ ነው ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ በጽኑ የሚዋደዱ ሊለያዩ የማይችሉ ህዝቦች ናቸው፡፡ ከሕግ አግባብ ውጭ መብቶቻቸው የሚደፈጠጡ እና የሚጨቆኑ ከሆኑ ይህንን በጽናት ይቋቋማሉ፡፡ መብቶቻቸውን የሚደፈጥጡትን እና ከእራሳቸው የሚሰርቁትን አይወዱም“ ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍቅር ሁሉን ያሸንፋል ብለዋል፡፡ እራሳቸውን መሪዎች ነን እያሉ በሚጠሩ እና በህዝቦች መካከል የክፍፍል እና የጥላቻ ዘርን የሚዘሩ መሪዎችን ህዝቡ ካሸነፈ ወደ ቀድሞው እርስ በእርሱ የመከባበር፣ እንግዳ ተቀባይነቱ እና በአንድነት ተካፍሎ ወደሚበላበት ባህሉ ይለመለሳል፡፡ የእኔ ፍርሀት እኛ መሪዎቹ ከዚያ በኋላ ከትልቅ ችግር ላይ እንወድቃለን፤ ማታለያዎችን እየደረደርን ለብዙ ጊዜ መቆየት አንችልም ነበር ያሉት፡፡

ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው በመምጣት እንዲጎበኙ እና እራሳቸው በዓይናቸው እንዲመለከቱ ጋብዘዋል፡፡ ህዝቦች ትምህርት ቤቶችን መንገዶችን እና የጤና ክሊኒኮችን ይፈልጋሉ፡፡ ህዝቦች እገዛ በመፈለግ ላይ ናቸው፡፡ እርዳታ ይፈልጋሉ፡፡

ጋንዲ እንዲህ በማለት አስተምረዋል፣ “እምነቶቻችሁ ሀሳቦቻችሁ ይሆናሉ፡፡ ሀሳቦቻችሁ ቃሎቻችሁ ይሆናሉ፡፡ ቃሎቻችሁ ድርጊቶቻችሁ ይሆናሉ፡፡ ድርጊቶቻችሁ ደግሞ ልማዶቻችሁ ይሆናሉ፡፡ ልማዶቻችሁ እሴቶቻችሁ ይሆናሉ፡፡ እሴቶቻችሁም ዕጣ ፈንታችሁ ይሆናሉ፡፡“

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን እምነቶች እወዳቸዋለሁ ምክንያቱም እራሴን ያሳዩኛልና፡፡ የእርሳቸውን ቃሎች እወዳቸዋለሁ ምክንያቱም እንደ እኔ ቀጥተኛ የሆነ ንግግር ስለሚያደርጉ ነው፡፡ የእርሳቸው ቃሎች ተግባሮች እንደሚሆኑ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለኝም ምክንያቱም የማይሆኑ ከሆኑ ይወድቃሉና፡፡ እናም ውድቀት ለእርሳቸውም ሆነ ለእኛ አማራጭ እንደማይሆን ይገነዘባሉና፡፡ የእርሳቸው የኢትዮጵያዊነት አንድነት፣ እኩልነት፣ ፍትህ ለሁሉም፣ ሰላም፣ ዕርቅ፣ የሰብአዊ መብት መከበር፣ የሕግ የበላይነት መረጋገጥ እና የዴሞክራሲ እሴቶች መጎልበት የእርሳቸው እና የእኛ ዕጣ ፈንታዎች ናቸው፡፡

በሌሎች ተቀባይነት የማያገኝ ስራ በመሪዎች ፈጽሞ አይሰራም፡፡

ማንዴላ ሚሊዮኖችን ያነቃቁ ጀግና መሪ ናቸው፡፡

ማንዴላ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ታላቁን ኮረብታ ከወጣችሁ በኋላ ሌሎች መወጣት የሚኖርባቸው በርካታ ኮረብታዎችን ታገኛላችሁ፡፡“

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስኬታማ ሆኖ በድል አድራጊነት ለመውጣት ለቁጥር የሚያዳግቱ ኮረብታዎችን እና ተራሮችን መውጣት እና በርካታ ሸለቆዎችን እና በረሀዎችን ማቋረጥ ይኖርባቸዋል፡፡

እናም ሊሸከሙት የሚገባቸው መስቀል ከፊታቸው አለ፡፡ ይህንን መስቀል ተሸክመው ተራሮችን ሲወጡ እና ሸለቆዎችን ሲያቋርጡ የማገዝ ግዴታ አለብን፡፡

አብይ የማንዴላን እግር ኮቴ በመከተል እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ጀግና ለመሆን ልዩ ክብር እና መልካም አጋጣሚ አላቸው፡፡ የአፍሪካ ጀግናይሁኑ፡፡

ሆኖም ግን በማንዴላ እግር ኮቴ መጓዝ ቀላል ነገር አይደለም፡፡

መጓዝ አለባቸው፡፡ በሰላም፣ ዴሞክራሲ እና ነጻነት መንገድ ላይ ረዥም ጉዞ መጓዝ አለባቸው፡፡

ብቸኛ ጥያቄ ሆኖ የሚቀርበው ግን እነዚህን መንገዶች የሚጓዙት ብቻቸውን ነው፣ ከአቦሸማኔው ትውልድ እና ከማንዴላ መንፈስ ጋር ነው ወይስ ደግሞ በስደት ከሚገኙት ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን፣ ከደከሙት፣ ከድሆች እና ደስታ ከራቃቸው እና የነጻ አየር ለመተንፈስ ተሰባስበው በመታገል ላይ ካሉት ኢትዮጵያውያን ጋር ነው የሚለው ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት (አንድ ኢትዮጵያ) ዛሬ! 

ኢትዮጵያዊነት ነገ!

ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም!

 

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!   

ሚያዝያ 9 ቀን 2010 ዓ.ም