የስደት መንግስት ለኢትዮጵያ?

ከፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም    

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

Ethiopia Map2መግቢያ

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ስለ የስደት መንግስት መስፈርት በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት ለአንድ የኢትዮጵያ የሲቪክ ማህበረሰብ ቡድን ቃለ መጠይቅ ሰጥቸ ነበር፡፡

ስለስደት መንግስት ጽንሰ ሀሳብ እና ስላለው ተሞክሮ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው ወይም የሌለው ስለመሆኑ ያለኝን አስተያየት እንድሰጥ ተጠይቄ ነበር፡፡

ቀጥታ ያልሆነው እና ዘወር ያለው ጥያቄ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ነግሶ በሚገኘው እና እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እያለ በሚጠራው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ላይ ኢትዮጵያውያን ሕጋዊ ዕውቅና ያለው የስደት መንግስት ማቋቋም ይችላሉ ወይ የሚል ነበር፡፡

አሁን እያቀረብኩት ስላለው ትችት ዓላማ ጥቂት ቃላትን ልወርውር፡፡

አሁን በዚህ ትችት ትንታኔዬ ዓላማ አድርጌ የተነሳሁት አንድ የተወሰነ ቡድን በኢትዮጵያ ላይ የስደት መንግስት እንዲያቋቁም ያቀደውን ዕቅድ ለማጽደቅ ወይም ደግሞ ላለማጽደቅ ወይም ደግሞ በኢትዮጵያ የስደት መንግስት አካል ለመሆን አይደለም፡፡

እንደዚሁም ደግሞ በኢትዮጵያ ህዝብ ስብዕና ላይ መቋጫ በሌለው መልኩ እየፈጸሙት ስላለው ወንጀል፣ እስከ አፍንጫቸው ስለተዘፈቁበት ሙስና፣ እንደ መንግስት ስለአስተዳደራቸው ብቃትየለሽነት እና ድንቁርና የህወሀት የፖለቲካ ተቀናቃኝ በመሆን የትችት ትንተና ለማቅረብም አይደለም፡፡

ስለእነዚህ ጉዳዮችማ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሁልጊዜ ሰኞ በጽናት ትችቶቼን ሳቀርብ ቆይቻለሁ፡፡

የዚህ የአሁኑ ትችቴ ዋና ዓላማ ስለስደት መንግስት ማቋቋም ጥያቄ ጉዳይ ጥልቅ ፍላጎት ላላቸው ኢትዮጵያውያን ከሕግ አንጻር ስላለኝ አስተያያት ሀሳብ ለመፈንጠቅ ነው፡፡

እንደ ተከላካይ የሕግ ባለሙያነቴ ስለሕግ ጉዳዮች የተለየ አመለካከት አለኝ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ አድልኦ እንደሚያደርግ እና ከሕግ አግባብ ውጭ የአንዱን ወገን እንደሚደግፍ ዳኛ የማስመሰል ስራ አልሰራም፡፡

እኔ ለማምንበት ነገር ሁሉ ጽናት ባለው መልኩ ድጋፌን የምሰጥ ሰው ነኝ፡፡

ሆኖም ግን እንደ አካዳሚ እና እንደ ሰብአዊ መብት ተሟጋች የእኔ ዋና ተልዕኮ እውነቱን ፍርጥርጥ አድርጎ መናገር፣ ምንም ዓይነት የፍትህ አድልኦ አለመፈጸም እና የሰው ልጆችን ከጨካኝ የሰብአዊ መብት ደፍጣጭ አምባገነኖች መጠበቅ ነው፡፡

ለዚህም ነው በከፈትኩት የግንኙነት ድረ ገጼ የመጀመሪያ ገጽ አናት ላይ “ሰብአዊ መብቶችን እንጠብቅ፡፡ በስልጣን ላይ ላሉት ሁሉ እውነቱን ፍርጥ ፍርጥርጥ አድርገን እንናገር“ የሚል መፈክር ያስቀመጥኩት፡፡

ላፉት ዘጠኝ ዓመታት በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ እና በሌሎችም የዓለማችን የተለያዩ ክፍሎች ለሚገኙት በዝባዦች፣ ስልጣናቸውን ከሕግ አግባብ ውጭ ለሚጠቀሙ አምባገነኖች እና በስልጣን ለባለጉ አረመኔዎች እውነቱን ፍርጥርጥ በማድረግ እስከ አፍንጫቸው ድረስ ልክ ልካቸውን ስነግራቸው ቆይቻለሁ፡፡

የጆርጅ ቡሽን አባባል በመዋስ “በኢትዮጵያ ስልጣናቸውን ከሕግ አግባብ ውጭ በመጠቀም በሰው ልጆች ላይ የሰብአዊ መብትን በደፈጠጡ አምባገነኖች እና ለእነዚህ አምባገነኖች ከለላ እና ድጋፍ በመስጠት ለእኩይ ምግባሮቻቸው ተባባሪ በሆኑት አስመሳዮች መካከል ለእኔ ምንም ዓይነት ልዩነት አልሰጥም ፡፡“

በዓለም ላይ ለሁሉም ሰይጣናዊ ድርጊቶች እና ስቃዮች ዋና መሰረቱ የፖለቲካ ስልጣንን ከሕግ አግባብ ውጭ መጠቀም እና ስልጣንን የተቆናጠጡ ስልጣናቸውን የሕግ አግባብነት ለሌለው ተግባር የማዋላቸው ጉዳይ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከዚህ ባለፈ ፍጹም  ገንዘብ  የሰይጣናዊ ድርጊቶች የደም ስር ነው አንድሉት አይደለም (Money is the root of all evil.)

ለዚያም ነው ኢትዮጵያ በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አሳር ፍዳዋን እየተቀበለች እንዳለችው ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ በአሳድ/ISIL/ISIS የመከራ እና የስቃይ ሰለባ ሆነው ባሉት ለሶሪያ ስደተኞች መብትም እየተሟገትኩ ያለሁት እና ወደፊትም በጽናት የምሟገተው፡፡

እኔ ለሰው ልጆች ክብር ያለኝ ስጋት በአንድ ብሄራዊ ሀገር ህዝብ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ትግሌ እና ድጋፌ ሁሉ ለሁሉም የሰው ልጆች መብት ከመከበር ጉዳይ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡

ሁልጊዜ ለማለት እንደምወደው የእኔ ትኩረት ሁሉ ስለአንድ ሰው ወይም ሰለአንዲት ሴት ብሄራዊነት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ታላቁ ጉዳዬ ሆኖ የሚሽከረከረው ስለወንዶች እና ሴቶች የሰብአዊ መብት መጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡

ለአስርት ዓመታት ገደማ ያህል ሁሉም አንባቢዎቼ እንደሚገነዘቡት በኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የሰብአዊ መብት ጥበቃ ጉዳዮች ላይ እራሴን አላስገባሁም ነበር፡፡

ሆኖም ግን እኔ ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ እና የሰብአዊ መብት ጥበቃ ጉዳዮች ዘው ብዬ የገባሁት እ.ኤ.አ በ2005 በኢትዮጵያ ተደርጎ በነበረው ሀገር አቀፍ ምርጫ ወቅት የምርጫው ውጤት በጠራራ ጸሐይ መዘረፉን ተከትሎ ተከስቶ በነበረው ውዝግብ ምክንያት በሰላማዊ መንገድ ቅሬታቸውን ለኢትዮጵያ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሰላማዊ ሰልፍ ለመግለጽ በወጡ ንጹሀን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ አረመኔው መለስ በአጻፋው ደም የጠማቸውን ወሮበላ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች በሀገሪቱ ማዕከል ከተማ በሆነችው በአዲስ አበባ በማሰማራት በፈጸመው እልቂት ምክንያት ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ2005 የተደረገውን ምርጫ ተከትሎ አሁን በህይወት የሌለው አረመኔው እና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ሸፍጥን በተላበሰ መልኩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለመታወጁ ዋናው ምክንያት የእርሱ ፓርቲ የሆነው የዘራፊ ቡድን ስብስብ በዝረራ የተሸነፈ በመሆኑ ነበር፡፡

አምባገነኑ መለስ በማንኛውም ሕጋዊም ይሁን ሕገወጥ መንገድ ስልጣኑን በመያዝ በስልጣን ኮርቻ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ ለመኖር በጽናት ታግሎ ነበር፡፡

በህዝቡ ፈቃደኝነት ላይ በተመሰረተ መልኩ አምባገነኑ መለስ ስልጣን መያዝ የማይችል ከሆነ እርሱ በመረጠው መንገድ በጠብመንጃ አፈሙዝ ተግባራዊ ያደርገዋል፡፡

አምባገነኑ መለስ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን በመግለጽ ላይ በነበሩት ንጹሀን ወገኖቻችን ዘንድ ወሮበላ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮቹን በማዘዝ እና በማሰማራት የእሩምታ ተኩስ እንዲከፍቱ በማድረግ ወደ 200 ገዳማ የሚሆኑ ንጹሀን ዜጎች እንዲገደሉ እና ወደ 800 የሚሆኑት ንጹሀን ዜጎች ደግሞ የከባድ ቁስለኛ ሰለባ እንደሆኑ እራሱ ያቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን አረጋገጠ፡፡

(በድህረ 2005 ምርጫ የነበሩት የሟቾቹ እና የቁስለኞቹ ቁጥር ከዚያ የበለጠ እንደሚሆን የማያወዛግቡ መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ሆኖም ግን በአምባገነኑ መለስ ትዕዛዝ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን እንዲያጣራ የታዘዘው በተወሰኑ ጥቂት ቀናት ብቻ የሞቱትን እና የቆሰሉትን ብቻ ነበር፡፡)

በእርግጠኝነት አረመኔው እና አምባገነኑ መለስ ያንን የመሰለ በሰው ልጆች ላይ እልቂትን ፈጽሞ ከፍትህ አካል ለማምለጥ ጥረት አድርጓል፡፡

ሆኖም ግን ከፈጸማቸው ወንጆሎች እና ሰይጣናዊ ድርጊቶቹ ከፍትህ አምልጧልን?!

በአረመኔው በመለስ እልቂት ተሳትፎ የነበራቸው የመለስ ታዛዥ ሎሌዎች በሰው ልጆች ላይ በፈጸሟቸው አስፈሪ የሰው ልጅ እልቂቶች ለፍትህ አካል ይቀርባሉን?

ሆኖም ግን በጨካኙ እና በአምባገነኑ መለስ እልቂት ምክንያት “የአልማርያም/Al Mariam ትችቶች” ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት አንድም ሳምንት ሳያሳልፍ በየሳምንቱ ሰኞ ያልወጣበት አንድም ሳምንት የለም፡፡

ሆኖም ግን በአረመኔው እና በአምባገነኑ መለስ እልቂት መለስ በህወት እያለም ሆነ ከሞተ በኋላ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በየሳምነቱ ሰኞ በሚቀርበው ትችት በዓለም አቀፉ የሀሳብ ፍርድ መሰረት እስከ አሁን ድረስ ለፍትህ አልቀረቡም፡፡

ሆኖም ግን ለአረመኔው እና ለአምባገነኑ ለመለስ እና ለእርሱ ታዛዥ ወሮበላ ሎሌዎቹ እልቂት ሲል ባለፉት አራት አስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ እናት ሀገሩን ትቶ የሄደ እንድም የአካዳሚ ሰው እስከ አሁን ድረስ አልተሰማም፡፡

የእኔ የሙያ ኃይማኖት “የሕግ የበላይነት” ነው ለማለት እደፍራለሁ፡፡ እናም እንደ ሕገ መንግስት ባለሙያነቴ በፍርድ አደባባይ ስለሰብአዊ መብት መጠበቅ በጽናት መታገል እና የችግሩን አሳሳቢነት ለዓለም አቀፉ ማሰህበረሰብ የህሊና ዳኝነት ማቅረብ ሙያዊ ግዴታዬ ነው፡፡

የሕግ የበላይነት በተግባር ምን ማለት እንደሆነ ለማወቅ ለሚፈልጉ ወገኖች በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛው አስርት ዓመታት 90 የህል የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመዝግበው በሚንቀሳቀሱባት እና አንድ ብቸኛ ፓርቲ 100 በመቶ በማሸነፍ ጠቅላላ የፓርላማውን ወንበር ተቆጣጥሮ ባለበት አገር ሁኔታ እንዲሁም የዓለም የነጻ ህዝብ መሪ ነው እየተባለ የሚወራለት መሪ ተብዬ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ነው በማለት አስመሳይነቱን እና ሸፍጠኛነቱን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ አስመስክሮ ባለበት ሁኔታ የሚገኘውን ድባብ በመመልከት በጭልፊቶቹ የምላስ ቁልምጫ ብቻ እንጅ በተጨባጭ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሕግ የበላይነት ያልተከበረ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

የነጻው ሀገር መሪ ተብዬ የህግ የበላይነት መከበርን በየሚገኝበት የዲስኩር አደባባይ ሁሉ እንደበቀቀን የሕግ የበላይነት ስለመከበር በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ እየደጋገመ ሲደሰኩር ይደመጣል፣ በተግባር ግን ዜሮ መሆኑን ከዚህ በላይ እንደተጠቀሰው መሆኑን ያመላክታል፡፡ የሕግ የበላይነት በሰፈነበት ሀገር በምንም ዓይነት መልኩ አንድ ፓርቲ 100 በመቶ ምርጫን ሊያሸንፍ አይችልም፡፡

መቶ በመቶ የምርጫ ድል አድራጊነት እውን እና ትክክል ሊሆን የሚችለው “በጫካ ወሮበላሎች አገዛዝ”” ወይም ደግሞ (በጫካ ልትሉት ትችላላችሁ) ምርጫ አደባባይ ብቻ ነው፡፡

በሌላ አገላለጽ መቶ በመቶ የምርጫ ድል አድራጊነት እውን ሊሆን የሚችለው በወሮበላ የዘራፊ መንግስት አገዛዝ ማለትም አንድ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በሸፍጥ የዘራፊውን ስርዓት ለታዕይታ ብቻ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንደሆነ አስመስሎ የሚያየቀርብበትን የሸፍጥ እና ገልቱ ስርዓት በመያያዝ ለመግለጽ ብዬ በተጠቀምኩበት ስርዓት ውስጥ ብቻ ነው፡፡

በወሮበላ የዘራፊ መንግስት ስርዓት የሚመረጡ የይስሙላ ዴሞክራሲ ተወካዮች ዋናው ዓላማቸው በዴሞክራሲ ስም ተመረጥን በማለት ስልጣኑን ከተቆጣጠሩ በኋላ ህዝብን እንደ ብረት ቀጥቅጠው እንደ ሰም አቅልጠው በመግዛት የስልጣን እድሚያቸውን ማራዘም እና የሕዝቡን አንጡራ ሀብት በመዝረፍ የእራሳቸውን እና የእነርሱን ታዛዥ ሎሌዎች ኪሶች በመሙላት ተግባራት ላይ መረባረብ ብቻ ነው፡፡

ከዚህ በላይ ያቀረብኩትን ሁሉ ለመግለጽ የፈለግሁት አራት ቀላል የሆኑ እውነታዎችን ለማስቀመጥ በማሰብ ነው፡፡ እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡፡ 

1ኛ) ለኢትዮጵያ የስደት መንግስት ሆኖ ሊሮጥ እና ሊወዳደር የሚችል ጠንካራ ሯጫ እና ብቁ የሆነ የተደራጀ አካል እስከ አሁን አላየሁም፡፡ 

2ኛ) አሁን በስልጣን እርካብ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ በሚገኘው የወያኔ ወሮበላ የዘራፈ ቡድን ስብስብ ላይ ሌላ አማራጭ ኃይል በመሆን እና በቀጣይነትም ይህንን ጨቋኝ እና አምባገነን መንግስት የጭቆና ቀንበር ከሕዝቡ ጫንቃ ላይ ለማስወገድ የኢትዮጵያ የስደት መንግስት ማቋቋምን በማስመልከት ዓለም አቀፉ ሕግ ይፈቅዳል፡፡

 3ኛ) በዴሞክራሲያዊ መንገድ ስልጣንን የተረከበ መንግስት በመለስ ዜናዊ እልቂት የፈጸሙትን ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች እና ለእልቂት ትዕዛዝ የሰጡትን ወንጀለኞች ከያሉበት በመልቀም ለፍትህ አካል የማቅረብ እና ሕጋዊ ብይን እንዲሰጣቸው ማድረግ እንዳለበት እምናለሁ፡፡ 

4ኛ) በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ ለሚገኘው ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አገዛዝ ውሱን የሆነ አማራጭ የአስተዳደር ስርዓት እንደሚኖር አምናለሁ፡፡

የሕግ የበላይነት በጫካ ወሮበላ የዘራፊዎች አገዛዝ ሕግ ላይ የበላይነቱን እንዲቆጣጠር ለማድረግ ጥረት ከማድረግ ውጭ የፖለቲካ ስልጣን ፍላጎት የሌለኝ መሆኔን በድጋሜ ላረጋግጥ እና ላሰምርበት እፈልጋለሁ፡፡

የፖለቲካ ስልጣንን በሚመለከት በሸክስፒር ጁሊዬስ ቄሳር እንዲህ ከሚለው የብሩቱስ መግለጫ ጋር ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ፡ “ታላቅነት ከሕግ አግባብነት ውጭ በስራ ላይ የሚውለው ከስልጣን ጋር በሚለያዩበት ጊዜ ነው፡፡ እናም እውነታውን ለቄሳር ለመናገር የእርሱ ስሜቶች እና ዝንባሌዎች ከሚያቀርባቸው አመክንዮች የበለጡ ተወዛዋዥ እና ዋዣቂዎች ለመሆናቸው የማውቅበት መንገድ የለኝም፡፡“

በቀላል አነጋገር ብሩቱስ ስልጣንን የሚወዱ ሁሉ ለእውነተኝ ፍቅር እና ቅርርብ እውሮች ናቸው፡፡ እነዚህ ግብዞች “የፖለቲካ ስልጣን ከጠብመንጃ አፈሙዝ ይመነጫል“ አይሉም ትላላችሁ?

የለም! የፖለቲካ ስልጣን ከህዝቦች ስምምነት እና መልካም ፈቃድ የሚመነጭ ነው፡፡

አንድ ነጠላ የፖለቲካ ፓርቲ ምርጫን መቶ በመቶ በሚያሸንፍበት ዕለት ያ ዕለት አሳሞች ክንፍ አውጥተው የሚበሩበት ዕለት ነው፡፡ ወይ ጉድ! በ እ.ኤ.አ ግንቦት 24/2015 አሳሞች በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ በረራ አላደረጉምን?

ብሩቱስ ስልጣን ስለጠማቸው እና ስለራባቸው ሰዎች እንዲህ ይላል፡ “አንድ ሰው ደግነቱ እየጠፋ የመሰሪነትን ተግባር እያከናወነ ባለበት ጊዜ ልክ እንቁላሉ እየተፈለፈለ እንዳለ እባብ አድርገህ አስበው –…“

እኔ በበኩሌ እንዲህ የሚሉትን የአልበርት ሽዌዘርን መርሆዎች ለመከተል እሞክራሉ፡ “የሰው ልጆች ዋና ግብር ሰዎችን ማገልገል፣ ለሌሎች ሰዎች ፍቅር ማሳየት እና እገዛ ማድረግ ነው፡፡“

በዚህ ላይ እንዲህ የሚል ነገር ብቻ ለመጨመር እውዳለሁ፣ “…የወንጀሎች ሰለባ ለሆኑት እና ፍትህን ላጡ ህዝቦች  ፍትህን መጎናጸፍ እንዲችሉ ማቋረጫ በሌለው መልኩ ጥረት እናድርግ“ ነው።

እናም እኔ በጣም ትንሽ በሆነች መንገድ በየቀኑ መልካም ነገር ለማድረግ አሞክራለሁ።

በዚህ ትችት የእኔ ብቸኛው ፍላጎት ለሰው ልጆች አገልግሎት ለመስጠት (በእርግጠኝነት ኢትዮጵያዊ እና አፍሪካዊ ለመሆን)፣ ሌሎችን ለማገዝ እና በኢትዮጵያ ሰብአዊ ክብራቸው ተደፍጥጦ የወንጀሎች ሰለባ የሆኑ ወገኖችን ለመርዳት እንዲቻል ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር የስደት መንግስት መርሆ እና ተሞክሮ ምን እንደሚመስል ምርምር ማድረግ ነው፡፡

ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር “የስደት መንግስት” ምንድን ነው?

በአጠቃላይ መልኩ ሲታይ “የስደት መንግስት” ዜጎች ለእራሳቸው ሀገሮች ሲሉ በውጭ ሀገር ሆነው ቡድን መስርተው የሚያቋቁሙት የፖለቲካ ክስተት ነው፡፡

እንደዚህ ዓይነት ቡድኖች በእርግጠኝነት በሀገራቸው ያለውን በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ሕጋዊነት በማስወገድ እነርሱ ሕጋዊ መንግስት እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ፡፡ እነዚህ በስደት ላይ ሆነው መንግስትን የሚመሰርቱ ቡድኖች የመጨረሻው ዓላማቸው ወደ ትውልድ ሀገራቸው በመመለስ በመደበኛነት የመንግስትነት ስልጣናቸውን በመያዝ ለሕዝቡ ጠቃሚ የሆነ አመራር ለመስጠት ነው፡፡

በዓለም አቀፉ የሕግ መስፈርት መሰረት ብቃት ያለው የስደት መንግስት ለማቋቋም የተለዩ የሕግ መስፈርቶች የሉም፡፡

ቡድኖች የስደት መንግስት ለማቋቋም ወይም የተለየ መንግስታዊ አወቃቀር ለማካተት እንዲችሉ በሚል የሚጣልባቸው ምንም ዓይነት ሕጋዊ ማዕቀብ የለም፡፡

በስደት ላሉ መንግስታት ዕውቅና ለመስጠት ዕውቅና በሚሰጡት መንግስታት ሊደረጉ የሚችሉ በርካታ ነገሮች እና ለዚህ በስደት ላለው መንግስት ሕጋዊነት ሊገመግሙ የሚችሉ ነገሮች እና ይህ የስደት መንግስትም ሀገሪቱን ለመወከል የሚያስችል ሕጋዊነት እንዲሁም በቂ የሆነ አቅም ያለው እና የሌለው መሆኑን ገንዛቤ በመውሰድ የሚፈጽሟቸው የፖለቲካ ሂደቶች ናቸው፡፡

በስደት ላይ ያለን መንግስት ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር ሕጋዊነቱን በመመርመር ለማወቅ መሞከር የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖር ያግዛል፡፡

በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት አንድ ቡድን የስደት መንግስት መስፈርትን ያሟላል ለማለት በመጀመሪያ ደረጃ ያች ሀገር ሉዓላዊ ሀገር መሆን አለባት፡፡

እ.ኤ.አ በ1933 በተደረገው የመንግስታት መብቶች እና ኃላፊነቶች ስምምነት (የሞንቴቪዲዮ ስምምነት) መሰረት “አንድ መንግስት ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር የሚከተሉትን ነገሮች ማሟላት ይጠበቅበታል፡ ቋሚ ህዝብ፣ የተወሰነ የመልክዓ ምድር ወሰን ያለው፣ መንግስት ያለው እና ከሌሎች መንግስታት ጋር ግንኙነትን ለመፍጠር የሚያስችል ብቃት ያለው“

ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር አንድ መንግስት ዓለም አቀፍ ውሎችን እና ስምምነቶችን ጨምሮ መንግሰታት ለዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች እና መድረኮች የተደራሽንነት ጥቅምን የማግኘት፣ በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት ግዴታዎችን የመፈጸም እና ጥቅሞችን የማግኘት እና ከሌሎች ሀገሮች ፍርድ ቤቶች ከለላ የማግኘት መብቶች እና ጥቅሞችን ይጎናጸፋሉ፡፡

ሁሉም ሉዓላዊ ሀገሮች የእራሳቸውን ሉዓላዊ መንግስት ጥቅም ባስከበረ መልኩ ከሌሎች መንግስታት ጋር ግንኙነት ለመመስረት ነጻ ናቸው፡፡ ማንም የውጭ መንግስት በስደት ላይ ላለ መንግስት ዕውቅና በመስጠት በሌሎች ሀገሮች የውስጥ ጣልቃ ገብነት ድርጊቶችን መፈጸም እንደሌለበት ስምምነት ያለ ቢሆንም በዚህ መንግስት በተመረጠው መርሆም ላይ ጣልቃ እንዳይገባ የሚከለክል የሕግ አስገዳጅነት የለም፡፡

እርግጥ በስደት ላይ ያለ መንግስት ሉዓላዊነትን ስለማይገልጽ እና ከሕጋዊ መንግስት ጋር ያልተያያዘ ከመሆኑ አንጻር የዓለም አቀፍ ሕግ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህም ማለት በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት ሀገር ሳይኖር መንግስት ሊኖር አይችልም፡፡

በእርግጥ በስደት ላይ ያለ መንግስት አንድ ሀገር በውጭ ኃይል ወረራ በተፈጸመበት ጊዜ፣ ግዛቱ በተያዘ እና በተወረረ ጊዜ በስደት ላይ ባለው የስደት መንግስት ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖ አይኖርም፡፡

ሆኖም ግን በስደት ላይ ባሉ መንግስታት ባህሪ መሰረት ሊተገበሩ የማይችሉ ነገሮች እና ልዩ ልዩ ሕጎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ነጻ አውጭ ግንባር መንግስት ሳይሆን በስደት ላይ እንዳለ መንግስት አድርጎ እራሱን መሰየም ይችላል፡፡ የአንደ ሀገር ክልል እራሱን በእራሱ የማስተዳደር እና የስደት መንግስት በማለት ማወጅ ይችላል፡፡ እነዚህን እና እንደዚህ ባሉ ጉዳዮች ላይ መወያየት ለሌላ ጊዜ የሚተላለፉ ይሆናል፡፡

በአንድ በተወሰነ ሀገር ውስጥ ስልጣን የያዘ መንግስት ባለበት ሁኔታ በስደት ላይ ላለ መንግስት ዕውቅና በመስጠት ስልጣንን ይዞ እንዲንቀሳቀስ ዕውቅና መስጠት ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር ሕገወጥ እና ጣልቃገብነትን ያመላክታል በማለት የሚከራከሩ የሕግ ህልዮት ተከታዮች አሉ፡፡

ሌሎች በዓለም ሕግ ላይ ትችት የሚያቀርቡ ሰዎች ደግሞ በስደት ላይ ያለ መንግስት ሕጋዊነት ቢያንስ በአራት መስፈርቶች ማለትም የሕዝብ ወካይነትን፣ በፖለቲካ ነጻነት ጉዳይ፣ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ሕገ ወጥነት እና የአንድ መንግስት መገለጫ የሆኑ ባህሪያቱን አካትቶ በመያዝ የሚወሰን ይሆናል በማለት ሀሳብ ያቀርባሉ፡፡

በስደት ላይ ላለ መንግስት ከምናቀርበው ትንታኔ አንጻር የሕጋዊነት ቁልፍ መስፈርት በዓለም ዓቀፍ ሕግ መሰረት ስምምነት የተደረሰባቸው መስፈርቶች በውል ተይዘው የማይገኙ በመሆኑ የሕጋዊነት ትርጉምም በግልጽ ምን ማለት እንደሆነ ባልተብራራበት ሁኔታ ችግር ማጋጠሙ የሚጠበቅ ነው፡፡

የአንድ ቡድን አስተሳሰብ በስደት ላይ ያለ መንግስት በዴሞክራሲያዊ ህጋዊነት ላይ የተመሰረተ መሆን ይኖርበታል የሚል ሀሳብ ያቀርባል፡፡ በሌላ አባባል በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ ቡድን ብቻ በስደት ላይ እስካለ ድረስ እንደ ሕጋዊ መንግስት መቆጠር አለበት የሚል ሀሳብን ያራምዳሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ አንድ በስደት ላይ ያለ መንግስት ሕጋዊ ስለመሆን እና አለመሆኑ እያንዳንዱ መንግስት ሊያተኩርበት የሚገባው የእራሱ የሆነ ነጻነት አለው ብለው ያምናሉ፡፡

በስደት ላይ ላለ መንግስት ዕውቅና መስጠት የግዛት ሌዓላዊነትን እና በሌሎች ሀገሮች ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ያለመግባት ጉዳዮች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖን በማሳረፍ  የዓለም አቀፍ ሕግን መሰረታዊ መርሆዎች እንደመጻረር ይቆጠራል ብለው የሚከራከሩም አሉ፡፡

ጥቂት በዓለም አቀፍ ሕግ ላይ ትችት የሚያቀርቡ ባለሙያዎች በስደት ላይ ላለ መንግስት በሌሎች ሀገሮች ድጋፍ በወረራ እና አማጺ ቡድኖችን በመደገፍ ከስልጣኑ በኃይል ለሚወገድ መንግስት ዕውቅና የመስጠቱ ጉዳይ ውሱን መሆን አለበት ብለው ያምናሉ፡፡

በዚህም ምክንያት ነው በሰላም ጊዜ ከሚኖሩት ይልቅ በጦርነት ጊዜ የሚኖሩ የስደት መንግስታት ቁጥር ከፍ ብሎ የሚታዬው፡፡

በዓለም አቀፍ ሕግ መስፈርት መሰረት አንድ ዓይነት ስምምነት የተደረሰበት አንድ ነጠላ የሆነ የስደት መንግስት መስፈርት የለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለስደት መንግስት አንድ ዓይነት መርሆ ወይም ስምምነቶች የሉም፡፡

በእርግጥ በስደት ስላለ መንግስት ሕግ ሆነው የተዘጋጀ እና የተመደበ ዓለም አቀፍ ሕግ የለም በማለት ትችት የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች አሉ፡፡ በመጨረሻም እንዲህ የሚል ሀሳብ ያቀርባሉ፣ በስደት ላይ ያሉ መንግስታት ሕጋዊ ሰውነት በተቋቋመው የስደት መንግስት እና ቀደም ሲል ዕውቅና ባላቸው መንግስታት መካከል በሚኖረው የሕዝቡን ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ ባላቸው ግንኙነት የሚወሰን ይሆናል፡፡

በስደት ላይ ያለን መንግስት ሊደግፍ የሚችል በቂ የሆነ ልማድ ወይም ደግሞ የመንግስት ተሞክሮ እና  የሕግ ሀሳብ እንዳለ በመግለጽ መከራከር እችላለሁ፡፡ ግልጽ ለማድረግ የተወሰኑ ሁኔታዎች ባጋጠሙ ጊዜ መንግስታት በይፋም ሆነ ይፋ ባልሆነ መልኩ ለስደት መንግስት ዕውቅና ሊሰጡ እና ድጋፍ ለማድረግ የሚችሉባቸው ከፖለቲካ፣ ከሕግ ወይም ደግሞ ከሞራል ስብዕና አኳያ ውጭ በሆነ መልኩ በቂ የሆኑ የመንግስት ልምዶች አሏቸው፡፡

በስደት ላይ ላለ መንግስት በቂ የሆነ ዓለም አቀፍ ሕግ ስለመኖር እና አለመኖር ጉዳይ በማስመልከት ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች የክርክር ጭብጥ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት በስደት ላይ ላለ መንግስት ዕውቅና መስጠት የሚያስችል በቂ የሆነ የመንግስታት ተሞክሮ አለ የሚለውን በመያዝ የክርክር ጭብጤን ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡

በስደት ላይ ላሉ መንግስታት አነስተኛ የሆነ የቀጣይነት እና የአንድ ዓይነት የሁለቱም ደረጃ አመሰራረት እና ዕውቅና የመስጠት ጉዳይን በማስመልከት እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ በስደት ላይ ስላሉ መንግስታት አመሰራረት እና ዕውቅና አሰጣጥ ጉዳይ በጊዜ የተቀመረ ማስረጃ አለ፡፡

በአሁኑ ጊዜ ካለው ሁኔታ አንጻር በርካታ መንግስታት የዓለም መንግስታት የጸጥው ምክር ቤትን ጨምሮ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ በወቅቱ ካሉ ዓለም አቀፍ ሁኔታ እና የየሀገሮቻቸውን ጥቅም ከማስከበር አንጻር አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች አኳያ በተጣጣመ መልኩ ለበርካታ የስደት መንግስታት ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡

ከተወሰነ የሕግ ማዕቀፍ አንጻር በስደት ላይ ያሉ መንግስታትን ሕጋዊነት መቀበልም ሆነ አለመቀበል በሚመለከት ምንም ዓይነት ሕጋዊ ማስገደጃ የሌለ መሆኑን የሚገልጽ የህግ ሀሳብ የሌለ መሆኑን በማንሳት የክርክር ጭብጥ ማንሳት ይቻላል፡፡ በሌላ አባባል በስደት ላይ ባሉ መንግስታት ላይ በአጠቃላይ እንደ ሕግ ተቀባይነት ያለው ልማድ ወይም ተሞክሮ የለም፡፡ (ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት/International Court of Justice (ICJ) አንቀጽ 38 (1) (b)፡፡)

በስደት ላይ ስላሉ መንግስታት በቂ ማስረጃ እና አጠቃላይ የሆነ ተሞክሮ የሌለበት ሁኔታ እንደ ሕግ በተያዘበት ሁኔታ የስደት መንግስታትን ከማቋቋም እና ዕውቅና ከመስጠት ተሞክሮ አኳያ የተወሰኑ ዓለም አቀፍ ሕጎች እና ተሞክሮዎች እንዳሉ የክርክር ጭብጥ ማቅረብ እችላለሁ፡፡ በሌላ አባባል የስደት መንግስታትን ለማቋቋም እና ሕጋዊ ዕውቅና ለመስጠት አንድ ዓይነት የሆነ የመንግስታት ልምድ እንዳለ አምናለሁ፡፡

በስደት ላይ ያሉ መንግስታት በዋናነት የሀያኛው ክፍለ ዘመን ክስተቶች ቢሆኑም ቅሉ ከአንድ ሀገር መልክዓ ምድራዊ ግዛት ውጭ በሆነ መልኩ መንግስትን ከትውልድ ሀገር ውጭ የመመስረቱ ጉዳይ ከላይ የተጠቀሰውን ሐረግ ትርጉም እንዲይዝ ያደርገዋል፡፡

የስደት መንግስትን ከማቋቋም አንጻር ንጉስ ዳቪድ (ዳዊት) የመጀመሪያው የስደት መንግስት መሪ እንደነበር የክርክር ጭብጤን አቀርባለሁ፡፡

አንዳንድ የቅዱሳን መጽሐፍት ምሁራን እንደሚያቀርቡት የክርክር ጭብጥ የዳቪድ ልጅ የሆነው አብሳሎም አባቱን በመገልበጥ ንጉስ ለመሆን ወሰነ እና ንጉስ ሆነ፡፡

ያንን ዓላማ ለማራመድ አብሳሎምን የገፋፋው ወደ እየሩሳሌም ከተማ በር በመሄድ ህዝቡ በአባቱ አስተዳደር ላይ የሚያቀርበውን ቅሬታ ከሰማ እና ካስተዋለ በኋላ ነው፡፡

ይህንን ድርጊት ለጥቂት ዓመታት ከሰራ በኋላ አብሳሎም የሕዝቡን ፍቅር አገኘ፡፡ ለአባቱ ለተወሰነ ጊዜ አልኖርም በማለት የማታለል ስራ ሰራ፡፡

አብሳሎም ወዲያውኑ ንጉስ እንደሆነ በይፋ አወጀ፡፡ ዳቪድ መፈንቅለ መንግስት መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ከደጋፊዎቻቸው ጋር ወደ እየሩሳሌም በመሄድ የስደት መንግስት አቋቋሙ፡፡ ከዚያ በኋላ ልጃቸውን በጦርነት ድል በማድረግ እንደገና በአሸናፊነት ወደ ሀገራቸው ተመሰሉ፡፡

ለበርካታ ዘመናት ስደተኛ ንጉሶች እና የዘር ገዥዎች የስደት መንግስታትን (የስደት ፍርድ ቤቶችን) አቋቁመዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የእንግሊዝ እና የፈረንሳይ ንጉሳውያን ገዥዎች በወቅቱ ከፈነዳው አብዮት በማምለጥ ይህንን መንግስት ለማቋቋም ችለዋል፡፡

በ20ኛው ክፍለ ዘመን በርካታ የስደት መንግስታት በጦርነት ወረራ በሚፈጸምባቸው ጊዚያት ሁሉ የስደት መንግስታትን ሲያቋቁሙ ቆይተዋል፡፡

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መንግስታት፣ የተቃዋሚ ቡድኖች እና ንጉሳዊ ዝርያዎች ከዴንማርክ፣ ከግሪክ፣ ከፖላንድ፣ ከኖርዌ፣ ከዩጎስሎቪያ፣ ከኔዘርላንድ፣ ከሉክሰምበርግ፣ ከቤልጂየም፣ ከቸኮስሎቫኪያ የስደት መንግስታትን በለንደን አቋቁመዋል፡፡ በርካታዎቹ እነዚህ የስደት መንግስታት በእንግሊዝ መንግስት ለተወረሩባቸሀው ሀገራቸው ሕጋዊ ዕውቅና ያላቸው መሆናቸውን በማመን ዕውናቅናን አግኝተዋለል፡፡

ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወዲህ በጣም ታላቅ ታዋቂ የሆነው ዓለም አቀፍ ሕግ በኢትዮጵያ በአጼ ኃይለ ስላሴ ተቋቁሞ ስለነበረው የስደት መንግስት በማስመልከት የክርክር ጭብጤን ማቅረብ እችላለሁ፡፡

እ.ኤ.አ ጥቅምት 1935 ፋሽስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ ታላቋ እንግሊዝ እና ሌሎች የአውሮፓ መንግስታት በኢትዮጵያ ያለውን የኢጣሊያ የውክልና አገዛዝ ሕጋዊነት ተቀበሉ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ ለአጼ ኃይለ ስላሴ ለሉዓላዊት ኢትዮጵያ የስደት መንግስት አገዛዝ ግምገማ ካካሄዱ በኋላ ሕጋዊ እውቅና ሰጡ፡፡

በእንግሊዝ የአጼ ኃይለ ስላሴ የስደት መንግስት ሕጋዊ እውቅና በእንግሊዝ ፍርድ የፍትህ አካላት ስርዓት ተፈተሾ በጠቅላይ ፍርድ ቤትም እንዲጸድቅ ተደረገ (በእንግሊዝ ፓርላማ ውሳኔ ወይም ደግሞ በሌላ በሚኒስቴር መስሪያ አካል ሳይሆን)፡፡

እ.ኤ.አ በ1934 በኢትዮጵያ መንግስት ንጉሰ ነገስት አጼ ኃይለ ስላሴ እና በሽቦ ገመድ እና በሽቦ አልባ ኃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅት መካከል የሬዲዮ እና የቴሌግራፍ አገልግሎት ኮንትራት ስምምነት ተደርጎ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ በ1936 አጼ ኃይለ ስላሴ ወደ እንግሊዝ ተሰደዱ እና የኢጣሊያ ንጉስ እራሱን የኢትዮጵያ ንጉስ በማድረግ አወጀ፡፡

እ.አ.አ በ1937 ንጉስ ኃይለ ስላሴ የሽቦ ገመድን እና ሽቦ አልባ ሃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅት ላይ 10,600 ፓውንድ የይገባኛል ጥያቄ በማቅረብ እንዲከፍል ክስ በመመስረት በእንግሊዝ ፍርድ ቤት እንዲቆም አደረጉ፡፡ የኢጣሊያ መንግስትም ያንን ገንዘብ ይገባኛል በማለት አቤቱታ አቀረበ፡፡

ከጥቂት ጊዜ የክርክር ሂደት በኋላ ፍርድ ቤቱ እ.ኤ.አ በ1938 ለአጼ ኃይለ ስላሴ ፈረደ፡፡

ያ ፍርድ ቤት የእንግሊዝ መንግስት እስከዚያ ድረስ ለኢትዮጵያ ንጉስነት ሕጋዊ ዕውቅና ያላቸው  አጼ ኃይለ ስላሴ እንጅ የኢጣሊያ ንጉስ ሕጋዊ የኢትዮጵያ ንጉስ አይደለም ማለት በማለት የመደምደሚያ ውሳኔውን ሰጠ፡፡

ያም ሆነ ይህ በሽቦ ገመድ እና በሽቦ አልባ ኃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅት ሁለተኛ አቤቱታ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ቢሮ እ.ኤ.አ ጥቅምት 1938 እንዲህ የሚል እውቅና ሰጠ፣ “የተከበረው መንግስት ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ ሕጋዊ የኢትዮጵያ ንጉስ አይደሉም እናም በአሁኑ ጊዜ የኢጣሊያ ንጉስ የኢትዮጵያ ሕጋዊ ንጉስ ናቸው፡፡“

ጉዳዩ በይግባኝ ውድቅ ተደረገ፣ ሆኖም ግን እስከዚያም ጊዜ ድረስ ቢሆን በተተኪው መንግስት እና በስደት ላይ ባለው መንግስት መካከል ያልተፈቱ አወዛጋቢ ጉዳዮች ገና እልባት አላገኙም ነበር፡፡

ከዚህ ተጻራሪ በሆነ መልኩ ደግሞ  ኢጣሊያ እ.ኤ.አ ሰኔ 1940 ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በገባች ጊዜ የእንግሊዝ መንግስ በስደት ላለው ለኢትዮጵያ መንግስት ዕውቅና ሰጠ፡፡

በ20ኛው ክፍለ ዘመን ለመንግስታት ሕጋዊ ዕውቅና ለመስጠት በርካታ ሙከራዎች ነበሩ፡፡

የኢስትራዳ መርህ/Estrada Doctrine (ሜክሲኮ) የውጭ መንግስታት በሌሎች ሀገሮች የውስጥ ጉዳይ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መልኩ ጣልቃ በመግባት ስለመንግስታት ወይም ስለሚደረገው ለውጥ መወሰን የለባቸውም፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ ያሉት ጉዳዮች የሀገሮችን ሉዓላዊነት ከመዘለፍ አንጻር የሚታዩ የሆናልና ነው፡፡ ይህ መርህ የሜክሲኮን ጉዳይ ከማዬት አኳያ ከሞራል እና ከፖሊተካ ጥያቄ አንጻር ትክክል ስለመሆን አለመሆን እና ስለአምባገነኖች መመስረት ገለልተኛ የመሆን አቋምን የሚያመላክት ነው፡፡

የቶባር መርህ/Tobar Doctrine በመካከለኛው አሜሪካ በሕገ መንግስት ድንጋጌ ካልሆ በስተቀር በሌላ በማንኛውም መንገድ ስልጣንን ከአንዱ መንግስት በኃይል መንጠቅ እንደማይቻል በግልጽ ያስቀምጣል፡፡

የስቲምሰንን መርህ/Stimson Doctrine ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስ ስለዓለም አቀፍ ግዛት እና በኃይል ስለሚደረጉ የመንግስታት ለውጥ ምንም ዓይነት ዕውቅና እንደማትሰጥ አወጀች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የስቲምሰን መርህ በተወረሩ ሀገሮች ያሉ ስደተኛ መንግስታት ዓለም አቀፍ ዕወቅና ያላቸው ተዋናዮች እንደሆኑ በማድረግ ሙሉ ዕውቅና ሰጥታለች፡፡

በሰላም ጊዜ በስደት ላይ ያሉ መንግስታትን ከመደገፍ አኳያ በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት ኢላማ በሆነው ሀገር የውስጥ ጉዳዮች ላይ ቀጥተኛ የሆነ ጣልቃገብነት እስካልተደረገ ጊዜ ድረስ ከሕግ አንጻር በትክክለኛ መንገድ መደገፍ እንዳለባቸው ለመሞገት እወዳለሁ፡፡ በኮርፉ ቻኔል ጉዳይ (1949) ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት እያንዳንዱ ሉዓላዊ መንግስት ከምንም ዓይነት የውጭ ኃይል ጣልቃገብነት ነጻ የመሆን መብት እንዳለው በሕግ አረጋግጧል፡፡

ሆኖም ግን ከኮርፉ ቻኔል ሕግ አንጻር የሰብአዊ መብትን ጨምሮ በርካታ የልዩነት ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ በ1999 በኮሶቮ ቀውስ ጊዜ የሰሜን ቃልኪዳን ሀገሮች ድርጅት/ኔቶ ከሞራል አንጻር እና የሩሲያ፣ ቻይና እና የሌሎች በርካታ ሀገሮች ተቃውሞ ቢኖርም ቅሉ የሰርቢያን የጎሳ ማጽዳት ለማቆም አፋጣኝ ወታደራዊ እርምጃ ወሰደ፡፡

በስደት ስላለ መንግስት የዓለም አቀፉ የፍትህ አካል የሚሰጠው ሕጋዊ ሰውነት በአብዛኛው መንግስታት ዕውቅና ለማሰጠት ስትራቴጂካዊ በሆኑ መገሮች ላይ የሚወሰን ነው፡፡

አንድን ቡድን የስደት መንግስት ነው ብሎ ዕውቅና ለመስጠት መንግስታት በርካታ ነገሮችን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል በትውልድ ሀገር ላይ ያሉት ቡድኖች የስደት መንግስት ዕውቅና በሚጠይቁበት ጊዜ መንግስታት በቂ የሆኑ መስረጃዎችን ይመለከታሉ፡፡

በስደት ላይ ያለ መንግስት በስልጣን ላይ ያለ መንግስት የሚያደርጋቸውን በርካታ ነገሮችን በተጨባጭ በማቅረብ የእርሱን ሕጋዊ ህልውና ለማረጋገጥ ይችላል፡፡ እነዚህ ድርጊቶች ሕገ መንግስት የማርቀቅን፣ በሌሎች መንግስታት የዲፕሎማሲ ዕውቅና የማግኘትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከመያዝ አንጻር፣ የአንድ ዓለም አቀፍ የስምምነት ውል አባል መሆንን እና ከዚህም በላይ ደግሞ የማንነት መታወቂያን ከማተም አንጻር ያሉትን በመጨመር አካትቶ ይይዛል፡፡

በስደት ላይ ያለ መንግስት ተግባራዊ ባህሪ በዋናነት ከሚኖረው አጠቃላይ ወይም ደግሞ የተወሰነ  ኗሪ  ህዝብ እና ከውጭ መንግስታት ቀጥታ ወይም ደግሞ ቀጥተኛ ባልሆኑ ድጋፎች ላይ የሚወሰን ይሆናል፡፡ እነዚህ ሁለት ነገሮች በስደት ላይ ያለ መንግስት አንጸባራቂ ኃይል ሆኖ ይቀጥላል ወይም ደግሞ በትውልድ ሀገር ላይ በስልጣን ላይ ተጣብቆ ለሚገኘው ገዥ አካል የማይበገር እና ብቃት ያለው ጠንካራ ኃይል ሆኖ መንግስቱን ይገዳደራል፡፡

ስለስደተኛ መንግስታት ጥቂት ምሳሌዎች፣

የቲቤት የስደት መንግስት የተመራው በቅዱስነታቸው 14ኛ ዳላይ ላማ ቴንዚን ጊያትሶ (ዳላይ ላማ) ነው፡፡ በዚህም መሰረት የቻይና በቲቤትያውያን ላይ እያራመደች ላለችው ጭቆና እምቢ አሻፈረኝ በማለት  ቻይና እ.ኤ.አ ከ1959 ጀምሮ በቲቤት ላይ ያደረገችውን ወረራ አወገዙ፡፡

የቲቤት ማዕካለዊ አመራር/The Central Tibetan Administration (CTA) ወይም ደግሞ መሰረቱን በሕንድ ሀገር ውስጥ ባደረገው በስደት ላይ ያለው መንግስት ዓላማ አድርጎ የተነሳው የቲቤት ስደተኞች እንዲያገግሙ ማድረግ እና በቲቤት ነጻነት እና ደስታ ተመልሰው ቦታቸውን እንዲይዙ በማድረግ ጉዳይ ላይ ያነጣጠረ ነበር፡፡

ሲቲኤ/CTA በቲቤት ሀገር ውስጥ ስልጣን እንዲቆጣጠር ዕቅድ አልነበረም፡፡ ከዚህ ይልቅ በቲቤት ውስጥ በቲቤትያውያን የቲቤትያውያንን ጥቅም የሚያስከብር መንግስት በቲቤት ውስጥ ነጻነት እንደተመለሰ ወዲያውኑ የሚፈርስ ይሆናል፡፡

የካምፑቻ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ጥምረት/The Coalition Government of Democratic Kampuchea (CGDK) በሶስት የካምቦዲያ አማጺ የፖለቲካ ቡድኖች ስብስብ የተመሰረተ የስደት መንግስት ጥምረት ነበር፡፡ CGDK በቬትናም አሻንጉሊት አገዛዝ ላይ የተቋቋመ እና በተባበሩት መንግስታት ካምቦዲያን ሊወክል የሚችል ሕጋዊ እውቅና ያለው የስደት መንግስት ነበር፡፡ CGDK የተባበሩት መንግስታት ለተመለሰው የካምቦዲያ የስደት መንግስት እውቅና ከሰጠ በኋላ እ.ኤ.አ 1993 ስልጣኑን ለተመለሰው መንግስት አስረክቦ እንዲፈርስ ተደረገ፡፡

በስደት ላይ የነበረው የኩዌት የስደት መንግስት እ.ኤ.አ በ1990 ኢራቅ ኩዌትን መውረሯን ተከትሎ የተመሰረተ የስደት መንግስት ነበር፡፡ ሳውዲ አረቢያ በስደት ላለው መንግስት መሪ ለኢሚር ጃበር አል አህመድ አል ጃበር ሳባህ ቢሮዎችን እና ፋሲሊቲዎችን በማሟላት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ሬዲዮ ጣቢያዎች እና ግንኙነቶች ተቋቁመው ብቃት ባለው ሁኔታ የኩዌት ሕጋዊ መንግስት ተግባራት ቀጣይ እንዲሆኑ ድጋፏን ሰጥታለች፡፡ በርካታዎቹ መንግስታት በስደት ላይ ላለው መንግስት ዕውቅናቸውን መስጠታቸውን ይፋ በሆነ መልኩ አውጇል፡፡

የሐይቲ መንግስት ፕሬዚዳንት የነበረው ጂን ቤርትራንድ አሪሰታይድ እ.አ.አ በ1991 ከስልጣን ከተወገደ በኋላ በቀጣዮቹ ጊዚያት የባሀሚያን መንግስት በሕገ መንግስቱ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ የተመረጠ መንግስት ሆኖ እውቅና ተሰጥቶት ቀጥሏል፡፡ የኔሽን መጽሔት ዊኪሊስን ጠቅሶ ባቀረበው ዘገባ መሰረት ዩኤስ አሜሪካ እ.አ.ኤ፣ ከ2004 መፈንቅለ መንግስት በኋላ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ የተመረጡት የሐይቲ መንግስት መሪ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እና አመራራቸውን እንዲቀጥሉ ሰፊ መሰረት ያለው ዘመቻ አካሂዳለች፡፡

ሩሲያውያን እ.ኤ.አ በ2000 ግሮዝኒን በወረሩበት ጊዜ የቸቸን የስደት መንግስት እንዲቋቋም ሆኖ በበርካታ የአረብ ሀገሮች፣ በእንግሊዝ፣ በዩኤስ ኤ እና በፖላንድ እየተዘዋወረ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

የበርማ ብሔራዊ የጥምረት መንግስት አንድነት/The National Goverenment of the Union of Burma (NCGUB) እ.ኤ.አ በ1995 በስዊድን ሀገር ውስጥ ዋና መስሪያ ቤቱን በሜሪላንድ ውስጥ በማድረግ እ.ኤ.አ መስከረም 2012 ከመፍረሱ በፊት የስደት መንግስት በመሆን ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኝ ጠይቋል፡፡

NCGUB እንዲፈርስ የመደረጉ ሁኔታ በበርማ በዘለቄታዊነት አስፈላጊ የሆነው እና ለብሄራዊ ዕርቅ ስኬታማነት አስተዋጽኦ የሚያደርገው እና ሁሉም ተሳታፊዎች ወደ አንድነት ወደሚያደርሰው ብሄራዊ የፖለቲካ ፕሮግራምን ለማቋቋም እንደሚያስፈልግ እምነት አለው፡፡

የኢኳቶሪያል ጊኒ ተራማጅ ፓርቲ/The Progress Party of Equatorial Guinea (PPEG) እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በዚያች ሀገር የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕጋዊነት መሆንን ተከትሎ ተመሰረተ፡፡

በመንግስት ስቃይ ምክንያት የPPEG አመራር በስፔን ሀገር የስደት መንግስት ለመቋቋም አወጀ፡፡

እ.ኤ.አ 2015 በሰሜን የመን በሀውዚ ሺያ ጎሳ አመጽ በኋላ የየመን መንግስት የስደት መንግስት ለመሆን ችሏል፡፡ እ.ኤ.አ መጋቢት በ2015 የሀውዚ ኃይሎች ኃይላቸውን እያጠናከሩ በመጡበት ጊዜ ፕሬዚዳንት አብድ ራቡ ማንሱር ሀዲ ወደ ኤደን ከዚያም የሳውዲ አረቢያ ማዕከል ወደሆነችው ሪያድ ተሰደዋል፡፡ እ.ኤ.አ መስከረም 2015 ታማኝ አመጸኞች በሳውዲ አረቢያ ተዋጊዎች እየተደገፉ በኢራንያውያን የሀውዚ ሀይሎች ትብብሮች ተይዘው የነበረውን ወደብ መልሰው በመቆጣጠር የየመን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ካሌድ ባሃህ ከስድስት ሚኒስትሮች ጋር በመሆን ወደ ደቡብ የኤደን ወደብ ተመልሰዋል፡፡

ሶርያ ጥብቅ እና በተግባር የተካነ የስደት መንግስት ብታቋቁም ኖር አሁን ካለችበት የእርስ በእርስ የጦርነት ጥፋት እራሷን መከላከል ትችል ነበርን?

የሶርያ ጦርነት የአረብ የጸደይ አብዮት በተጀመረበት እና ተቃዋሚዎች በመንግስት በኩል የማሻሻያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እና የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞችም እንዲፈቱ ጥያቄ ባቀረቡበት ጊዜ እ.ኤ.አ መጋቢት 2011 ተጀመረ፡፡

የባሽር አላሳድ አገዛዝ አመጽ ቀስቃሾችን በማጥፋት የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ አመጽም ማዳፈን እና ማጥፋት ይቻላል የሚል እምነት አለው፡፡

ተቃውሞዎች እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠሉ ወደ ህዝባዊ አመጽነት ለመሸጋገር ችለዋል፡፡ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የአሳድ ወታደሮች የብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን፣ ከባድ መሳሪያዎችን እና የጦር አውሮፕላኖችን በመጠቀም ከተሞችን እና አካባቢዎችን በመውረር ከፍተኛ የሆነ ጥቃት መሰንዘር ጀመሩ፡፡

የደማስቆስ አመጽ በተቀሰቀሰ ጊዜ ገና በመጀመሪያዎቹ ወራት የሶርያ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚ፣ የሲቪክ እና ሌሎች አመራሮች፣ ቡድኖች እና ማህበራት በአንድነት ሆነው የስደት መንግስት ቢያቋቁሙ ኖሮ አሁን እየታዬ ካለው ውድመት ልትጠበቅ ትችል ነበርን?

የሶርያ ብሔራዊ ምክር ቤት/The Syrian National Council (SNC) የተባበረ የቡድን ማዕቀፍ ለማቋቋም ዓላማ ሰንቆ ከተነሳው እና ከሌላ በሶርያ ውስጥ ከሚገኘው ዋና የጸረ አሳድ አመጾች መመስረት ከወራቶች በኋላ ተመሰረተ፡፡

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2012 SNC ወደ 17 በሚሆኑ ሀገሮች (ዩኤስ አምሪካንን፣ እንግሊዝን እና ፈረንሳይን ጨምሮ) እና በአውሮፓ ህብረት የሶርያ ህዝቦች ሕጋዊ ተወካይ (የስደት መንግስት?) በመባል እውቅና አግኝቷል፡፡

በSNC የውስጥ ችግሮች እና ግልጽ የሆነ የፕሮግራም እና የስትራቴጂ ብቃት ማነስ ምክንያት እና ከሌሎች ተቃዋሚ ቡድኖች ጋር ተባብሮ መስራት አለመቻሉ እና ሌሎች አዳዲስ ቡድኖች በአስቸኳይ እየጠቋቋሙ በመሆኑ በርካታ ሀገሮች ለSNC የሚሰጧቸውን ሙሉ ድጋፎች ከመስጠት እያቋረጡ እና ወደ ኋላ በማፈግፈግ ላይ ይገኛሉ፡፡

እ.ኤ.አ ጥቅምት 2012 ዩኤስ አሜሪካ SNC በግልጽ የሚታይ የተቃዋሚዎች ዋና ስብስብ ሊሆን እንደማይችል እና በአሁኑ ጊዜ ነጻነታቸውን ለማረጋገጥ በጦር መስር ሆነው እየተዋጉ ያሉትን እና ዕለት በዕለት እየሞቱ የሚገኙትን ተቃዋሚዎች ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማገዝ እንዲቻል ለሌሎች አዲስ ተቃወሚዎች ምስረታ ጥሪ ያቃርባሉ፡፡

SNC በቀጣይነት የሶርያ ብሔራዊ አብዮታዊ ጥምረት ከሌሎች የተቃዋሚ ኃይሎች ጋር ህብረት በመፍጠር ትግሉን ያጧጡፋል፡፡

እ.ኤአ ሚያዝያ 2012 የሶርያ አመጽ ከተቀሰቀሰ ከአንድ ዓመት በኋላ 200 አካባቢ በሚሆኑ የሶርያ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ የኃይማኖት፣ ወታደራዊ እና የሲቪክ ማህበረሰብ ቡድኖች እና ድርጅቶች ሶርያን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሸጋገር የስደት መንግስት ማቋቋምን ዓላማ ባደረገ መልኩ በኢስታንቡል ለሶስት ቀናት የቆዬ ጉባኤ አካሂደው ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ጥቅምት 2012 በሶርያ የፖለቲካ እና የስትራቴጂ ጥናቶች ማዕከል/Syrian Center for Political and Strategies፣ የሶርያ ተቃዋሚ ቡድኖች የርዕዮት ዓለም ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው በስደት ላይ የሚገኝ የስደት መንግስት ለመቋቋም ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

በሶርያ የሚገኘው የፖለቲካ እና የስትራቴጂ ጥናቶች ማዕከል/Syrian Center for Political and Strategies በድህረ አሳድ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል የፖለቲካ እና አስተዳደራዊ ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችሉ ወሳኝ የሆኑ የመፍትሄ ሀሳቦችን አቅርቧል፡፡

በምርጫ ስርዓቱ እና በፓርቲዎች ሕግ ላይ የማሻሻያ ሀሳቦች ቀርበው ነበር፡፡ በሶርያ ከድህረ አሳድ በኋላ ስኬታማ የሆነ ሽግግር ለማካሄድ “ከፕሮጀክቱ ዕለት በኋላ” የሚባል ድርጅት እንዲመሰረት ተደረገ፡፡ የዚህ ድርጅት ዋና ዓላማ አዲስ ብሄራዊ ማንነትን እና የሕግ የበላይነትን ለማስፋፋት፣ የተረጋጋ አስተዳደር ለመዘርጋት፣ በሶርያ አንድነትን እና ብዝሀነትን ለማጠናከር፣ የመሰረት ድናጋይ በሆኑት እሴቶች እና በዋና ዋና መርሆዎች መካከል የጋራ መግባባት እንዲኖር፣ የኃይማኖት ጽንፈኝነትን ለማስወገድ እና ሁሉም የሶርያ እና ሌሎች ሀገሮች ሁሉ አንድነት እንዲኖራቸው ጥረት ማድረግ የሚል ነው፡፡

በሀገር ውስጥ ባለው አለመረጋጋት ምክንያት የሶርያ ተቃዋሚዎች በዋናነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ የሆኑ ስራዎችን ለማከናወን የሚችል የስደት መንግስት ለማቋቋም በፍጹም አልቻሉም፡፡

በአሁኑ ጊዜ ሩሲያ የአሳድን የተቃዋሚዋሚ ቡድኖች፣ የISIS/ISIL አሸባሪ ኃይሎች ለማጥቃት የሚያስችል የጦር መሳሪያ እርዳታ ለአሳድ አገዛዝ እያቀረበች የሶርያ የእርሰ በእርስ ጦርነት በአስከፊ ሁኔታ ቀጥሎ ይገኛል፡፡

እንደ አልጃዚራ ዘገባ ከሆነ የሩሲያ የአየር ላይ የጦርነት ውጊያ የሲቪሉ ማህበረሰብ በሚገኙባቸው የሆምስ እና የአሌፖ አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ ጉዳት በማስከተል ላይ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ልትጠበቅ ትችላለችን…

(ይቀጥላል…)

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ጥቅምት 8 ቀን 2008 ዓ.ም