ኢትዮጵያ፡ የምንወድሽ ሀገራችን ደግመሽ አልቅሽ!

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም    

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ 

የኢትዮጵያውያን/ ህይወት ያሳስበናል! 

እ.ኤ.አ በ2005 ልክ የዛሬ 10 ዓመት በያዝነው ወር ገደማ አሁን በህይወት የሌለው እና እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እያለ የሚጠራው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አድራጊ ፈጣሪ አምባገነን መሪ የነበረው መለስ ዜናዊ በዚያን ዓመት ተካሂዶ የነበረውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ተከስቶ በነበረው ሁከት የደህንነት እና የጦር ኃይሉን በእራሱ ቁጥጥር ስር በማዋል በሰላማዊ እና ባልታጠቁ ንጹሀን ዜጎች ላይ ጭካኔ የተሞላበት እልቂት እና መከራን ያዘለ ዘመቻ አካሂዷል፡፡

እ.ኤ.አ ግንቦት 16/2005 መለስ ዜናዊ የፖሊስ፣ የደህንነት እና ወታደራዊ ኃይሉን በእራሱ ቁጥጥር ስር በማደረግ እና የአዲስ አበባ ከተማን የፖሊስ ኃይል ከፌዴራል ፖሊስ እና ከልዩ ኃይል ጋር በማቀናጀት ሁሉንም የህዝብ ስብሰባዎች ህገወጥ ናቸው በማለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ነበር፡፡ በቀጣዮቹ ሳምንታት የመለስ የጭፍጨፋ ኃይሎች አረመኒያዊ ጭፍጨፋ በማካሄድ 193 ሰላማዊ ንጹሀን ዜጎችን ግንባራቸውን እና ደረታቸውን በጥይት እያነጣጠሩ በመምታት የገደሉ ሲሆን ሌሎች 800 የሚሆኑ ወገኖቻችንን ደግሞ በጽኑ እንዲቆስሉ አድርገዋል፡፡ ምንም ዓይነት ትጥቅ ያልነበራቸው ሰላማዊ አመጸኞች ያንን ሸፍጥ እና ተንኮል የተሞላበትን የተጭበረበረ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ በመቃወማቸው እና መብታቸውን ለመጠቀም በመምረጣቸው ብቻ በየመንገዶች እና በየቤቶቻቸው እንደ አውሬ እየታደኑ ያለምንም ርህራሄ በጥይት እየተደበደቡ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲገደሉ ተደርገዋል፡፡ እነዚያ ጀግኖች ሰላማዊ አማጺ ወገኖቻችን በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን በጽናት ታግለው ውድ ህይወታቸውን በመገበር ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማበብ ሲሉ መስዋዕት ሆነዋል፡፡

ያ የአረመኔዎች እና የፈሪዎች አሰቃቂ ዕልቂት ላለፉት አስርት ዓመታት በየዕለቱ የእራስ ምታት፣ የልብ ቁስል፣ የሆድ ቁርጠት እና የደረት ውጋት ሆኖብኝ ቆይቷል፡፡ ይህንንም ከግንዛቤ በማስገባት ስለዚሁ ጉዳይ አንዲትም ሳምንትሳታልፈኝ በማዘጋጀው ትችቴ ለበርካታ ዓመታት ሳስተምር እና ስሰብክ ቆይቻለሁ፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 የተካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ተከስቶ በነበረው ውዝግብ የመለስን እልቂት በመቃወም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የሰብአዊ መብት ትግል ተቀላቅዬ በመታገል ላይ እገኛለሁ፡፡ የመለስ እልቂት ሰለባዎች የፍትህ ያለህ እያሉ በመጮህ ላይ ይገኛሉ፡፡ እኔ የእነርሱ ድምጽ ነኝ፡፡

ያ በሰላማዊ እና ንጹሀን ዜጎች ላይ በመለስ ትዕዛዝ ተካሂዶ የነበረው ሰይጣናዊ አሰቃቂ ዕልቂት የተፈጸመበት አስር ዓመት ከመሙላቱ ከአንድ ወር በፊት እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2015 እራሱን የኢራቅ እና የሊባኖስ እስላማዊ መንግስት (ኢሊእመ)/Islamic State of Iraq and the Levant (ISIL) (እንደዚሁም ደግሞ የኢራቅ እና የሶርያ እስላማዊ መንግስት (ኢሶእመ)/Islamic State of Iraq and Syria (ISIS) እያለ የሚጠራው አሸባሪ ቡድን በሊቢያ 30ኢትዮጵያውያንወገኖቻችንን አሳዛኝ እና አስደንጋጭ በሆነ መልኩ ያረደ መሆኑን በቪዲዮ ምስል ተመልክቻለሁ፡፡ (በዚህ በቀሪው ትችቴ ይህንን እየተስፋፋ የመጣውን ነቀርሳ/ካንሰር አሸባሪ ድርጅት “አሸባሪ ቡድን/ድርጅት/the terrorist group/organization“ እያልኩ እጠራዋለሁ ምክንያቱም በዓለም ላይ ከሚገኙ ታላላቅ ኃይማኖቶች መካከል አንዱ በሆነው የእስልምና እምነት ኃይማኖት ስም እየማለ እና እየተገዘተ ሆኖም ግን በተግባራዊ እንቅስቃሴው ግን የኃይማኖቱን ቅዱስነት ያዋረደ፣ የማያስብ፣ ኋላቀር፣ ደም የጠማው፣ ጨካኝ እና ስብዕና የሌለው አሸባሪ ቡድን ከእስላም ሃይማኖት ጋር አየገናኝም፡፡)

ይኸ በሊቢያ የሚገኘው ጨካኝ አሸባሪ ቡድን የወጣት ኢትዮጵያውያንን አንገት በማረጃ ቤት ውስጥ እንደሚታረድ የበግ ጠቦት እየቀነጠሰ አርዶ ጥሏል ምክንያቱም እነዚህ የኢትዮጵያ ወጣቶች ከኢትዮጵያ ጠላቶች በተለዬ መልኩ የክርስትና ኃይማኖት እምነት ተከታዮች የሆኑ እና እምነታቸውን ለመቀየር እምቢ አሻፈረኝ በማለት በእምነታቸው የጸኑ ዜጎች ናቸው፡፡ እነዚህ 30 ወጣት ኢትዮጵያውያን ለክርስትና ኃይማኖት እምነት ሲባል መስዋዕትነትን የተቀበሉ ብቻ አይደሉም፣ ሆኖም ግን ከዚህም በተጨማሪ ለሰው ልጆች እምነቶች እና አስተሳሰቦች ሲሉ ጭምር እንጅ፡፡ እነዚህ ወጣቶች ትክክለኛውን እምነታቸውን በመከተል የአምላክ የበግ ጠቦት በመሆን መስዋዕትነትን ተቀብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ወጣት ወንዶች እና በሌሎችም ከግብጽ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ፣ ከእንግሊዝ፣ ከጃፓን፣ ከኢራቅ እና ከሶርያ የመጡ ወጣቶችን ጨምሮ ሰለባ ያደረገው ይኸ ምንም ዓይነት ርህራሄ የሌው አረመኔ እና ጨካኝ አሸባሪ ቡድን ከፊል ኢራቅን፣ ሶርያን፣ ሊቢያን እና ናይጀሪያን ተቆጣጥሯል፡፡ እ.ኤ.አ ሰኔ 2014 ያ አሸባሪ ቡድን በነብዩ መሀመድ ቦታ አቡ ባከር አል ባግዳድን መሪ በማድረግ እራሱን ዓለም አቀፍ የእስልምና ኃይማኖት መንግስት አድርጎ አውጇል፡፡

ያ አሸባሪ ድርጅት የተለያዩ ሰብዕናየለሽ ቡድኖችን፣ ጀብድ ፈላጊዎችን እና ሌሎችን ከመካከለኛው ምስራቅ እና ከአውሮፓ ደስተኛ ያልሆኑትን እና መብታቸውን የተነፈጉትን  ሰብስቦች እየሳበ እንደሚጠቀምባቸው አምናለሁ፡፡ የዚህ ድርጅት አባላት በዓለም ላይ ጉዳት ለማድረስ በስሜታዊነት የተሞሉ ናቸው፡፡ የሮምን ወታደር (በተለምዶ በሮም ጳጳስ የተላኩ ተዋጊዎች ወይም ደግሞ የበለጠ በሚመሳሰል መልኩ እምነት የሌላቸው የምዕራብ ወታደሮች በዳቢቅ እና በሶርያ በሚገናኙበት ጊዜ የዓለምን ፍጻሜ የመጀመሪያ ምዕራፍ ይጠብቃሉ፡፡ እርግጠኛ ለመሆን ለዚያ አሸባሪ ቡድን እምነት የሌላቸውን እና ለአሸባሪ ድርጅቶች ርዕዮት ዓለም ድጋፍ የማያደርጉትን የሻአ ሙስሊሞችን እና ሌሎችን ሙስሊሞች እንዲሁም ማንኛውንም የሙስሊም መንግስት ያካትታል፡፡ ያ አሸባሪ ቡድን በአሁኑ ጊዜ በኢራቅ፣ በሶርያ፣ በሊቢያ እና በናይጀሪያ ተቆጥረው ለማያውቁ እልቂቶች ቀጥታ ተጠያቂ ነው፡፡ በዳቢቅ አሸባሪዎቹ እምነት የላቸውም ብለው የሚያስቧቸውን ማለትም ክርስቲያኖችን፣ ሙስሊሞችን እና ሌሎችን በማሸነፍ የእስልምና ግዛታቸውን በዓለም ላይ ሁሉ ለማስፋፋት እና ኃያል ሆነው ለመውጣት ይፈልጋሉ፡፡ ኋላቀርና  ኢ-ሰባዊ ድርጊትን ማራመድ የዚያ አሸባሪ ቡድን መለያ ፍልስናው ነው፡፡ ፍልስናው የእነርሱን ዓይነት የሙስሊም እምነት የማያራምደውን የእስልምና እምነት ተከታይ፣ ምንም ዓይነት እምነት የሌለውን ወይም ደግሞ ይዞት የቆየውን እምነቱን ያቆመውን ሰው ለመግደል እንደምክንያት የሚጠቀሙበት ነው፡፡ የእነዚህ የተንሸዋረረ ፍልስፍና የያዙት አሸባሪዎች ዓለምን ለማጽዳት የሚቻለው እነርሱ አማኞች አይደሉም ብለው የሚያስቧቸውን ሰዎች መግደል ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት በአሸባሪ ቡድኑ ተቀርጾ በተለቀቀው የቪዲዮ ምስል የወጣት ኢትዮጵያውያን ወንዶችን ጭንቅላት ለመቅላት/አንገታቸውን ለመቁረጥ እጆቻቸውን ይዘው በረሀውን በማቋረጥ ወደ ባህሩ ዳርቻ ሲወስዷቸው ነበር፡፡ ጥቂቶቹ ወጥ የሆነ ብርቱካናማ ልብስ ለብሰው ነበር፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ጥቁር ልብስ ነበር የለበሱት፡፡ አሸባሪዎቹ የወጣት ኢትዮጵያውያንን ጭንቅላት ለመቅላት እንደ ምክንያት ማስረጃ አድርገው የሚያቀርቡት ጠላታቸው የሆነቸው የእትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እምነት የሆነውን የክርስትና ኃይማኖት እምነት ተከታይ የመሆናቸው ጉዳይ ብቻ ነው፡፡

ይህ በሊቢያ እና እንደእርሱ ባሉት በሌሎች ሀገሮች የሚገኙት የደንቆሮ ስብስብ ወሮበላ የአሸባሪ ቡድን አባላት ከስቃይ እና መከራ እንዲሁም ከነብዩ ትምህርት በመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩትን የመጀመሪያዎችን የእስልምና እምነት ተከታዮች በኢትዮጵያውን ህዝቦች ተደርጎላቸው የነበረውን የአቀባበል መስተንግዶ ሙልጭ አድርጎ ረስቶታል፡፡ በቅርቡ አንድ ግለሰብ በሰጠው ቃለ መጠይቅ መሰረት በኢራቅ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው እና ለዕኩይ ምግባራቸው ስኬታማነት በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙት የአሸባሪ ቡድኑ አባላት የትምህርት ደረጃቸው ከአንደኛ ደረጃ ያልዘለለ መሆኑን ግልጽ አድርገዋል፡፡ እስላም ምንድን ነው ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፣ “ሕይወቴ ነው፡፡’ ስለቁራን ወይም ደግሞ ስለቁራን ባህላዊ ስብስቦች ወይም ስለድሮው ነብይ ኦማር እና ኦትማን ምንም የሚያውቁት ነገር የላቸውም፣ ሆኖም ግን ስለእስልምና ከአልቃይዳ እና ከአይሲስ ፕሮፓጋንዳ፣ እንዲሁም ሙስሊም ያልጠራውን እምነት ቀደም ብሎ ያልጠራውን እምነት ካላስተማረ እርሱም የእምነቱ ተከታዮች እንዳልሆኑት ሰዎች ሁሉ መወገድ እንዳለባቸው እና ዒላማ ውስጥ እንደሚወድቁ አሳምረው ያውቃሉ፡፡“ እነዚህ የአሸባሪ ቡድን አባላት እንዲህ በማለት ተናግረዋል፣ “ሳዳም ሁሴን ከወደቀ በኋላ በገሀነም ዓይነት የማያቋርጥ የሽምቅ ውጊያ ያደጉ፣ ቤተሰቦቻቸው የሞቱባቸው እና የተበታተኑባቸው እንዲሁም ከቤቶቻቸው መውጣት የማይችሉ ወይም ደግሞ እስከ ወሩ መጨረሻ ምንም ዓይነት መጠለያ የሌላቸው መሆናቸው ታውቋል፡፡“

ሌሎች የአሸባሪ ቡድን አባላትም ከዚህ የተለዬ የተሻለ ስብዕና የላቸውም፡፡ በአብዛኛው በህይወታቸው በሽግግር ላይ ያሉ ወጣቶች ማለትም ተማሪዎች፣ ስደተኞች፣ ስራ ለመስራት የማይፈልጉ አውደልዳዮች፣ ቤተሰቦቻቸውን የተው ወይም ደግሞ ለመተው የተዘጋጁ እና አንድ ዓይነት ጥቅም ሊያስገኝላቸው የሚችል ሌላ ዓይነት የጓደኝነት ቤተሰብ ለመመስረት ሲሉ ጥረት የሚያደርጉ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ የተለመደው የኃይማኖት ትምህርት እውቀት የላቸውም፣ እናም ጥብቅ በሆነ እና በጠባብ የማህበራዊ ፍልስፍና እምነት የታሰሩ ናቸው፣ ሆኖም ግን እነዚህ የአሸባሪ ቡድን አባላት ዓለምን ሊገምድ በሚችል የኃይማኖት ተልዕኮ ስሜት የተሞሉ ናቸው፡፡

እነዚህ በድንቁርና ተቀፍድደው የተያዙት አሸባሪዎች እና ከነባራዊ ሁኔታው ጋር መራመድ የማይችሉ ጉዶች ኢትዮጵያ ለነብዩ መሐመድ እምነት ተከታዮች የመጀመሪያው የእስልምና ኃይማኖት እምነት ስደተኞች ተቀባይ ገነት ስለመሆኗ ምንም ዓይነት ፍንጭ የላቸውም፡፡ ነብዩ መሐመድ በዚያ የመከራ ስደት ወቅት ለተከታዮቻቸው እንዲህ ብለው ተናግረው ነበር፣ “መካን መልቀቅ እና በዚያን ጊዜ በክርስቲያን ንጉስ ትተዳደር በነበረች እና ንጉሷም ፈሪሀ እግዚአብሔር ያደረበት እና ፍትህን የሚከተል ስለሆነ በአቢሲኒያ ሀገር (ኢትዮጵያ) በጥገኝነት መቆየት አለባችሁ፡፡“ የአክሱሙ ንጉስ እና የሐበሻ ህዝብ (ኢትዮጵያውያን) ከክርስቶስ ልደት በኋላ  በ615 ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ በስቃይ እና በመከራ ሸሽተው የመጡትን ሙስሊሞች ተቀብለው በመልካም ሁኔታ አስተናገዱ፡፡ እናም ታላቅ የሆነ መስተንግዶ አደረጉላቸው፣ እንዲሁም አባራሪዎቻቸው እና ጠላቶቻቸው ተመልሰው ወደ ሀገራቸው እንዲላኩላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ተንከባክበው እና ደግፈው አስተማማኝ መጠለያ በመስጠት ሊሰነዘርባቸው ከሚችለው አስከፊ አደጋ አድነዋቸዋል፡፡  እነዚህ ወሮበላ የአሸባሪ ቡድን አባላት ነብዩ መሐመድ የሀበሻን (አቢሲኒያ) ህዝብ ማመስገናቸውን እና እንዲህ የሚለውን ንግግራቸውን ፍጹም በሆነ መልኩ ረስተውታል፣ “እርምጃ እስካልወሰዱባችሁ ድረስ ሐበሻዎችን አትንኳቸው!“ ከዚህም በተጨማሪ ነብዩ መሐመድ እንዲህ በማለት አስተምረዋል፣ “አምላክ ለሌሎች ምህረትን ለማያደርጉ ምህረትን አይሰጥም፡፡“

በሊቢያ አሸባሪዎች አንገታቸውን የተቀሉት ኢትዮጵያውያን በማንም ዘንድ ጥቃትን አላደረሱም ነበር፡፡ እነዚህ ወጣቶች ሁሉም ድሆች እና ምንም ዓይነት ተስፋ የሌላቸው ሊቢያን እንደመሸጋገሪያ አድርገው መድረሻቸውን ወደ አውሮፓ ሀገሮች ያደረጉ ስደተኞች ነበሩ፡፡ ምህረትን፣ መጠለያን ማግኘት እና አንገታቸው እንዳይቀላ ይፈልጉ ነበር፡፡ እነዚህ እምነቱን ያዋረዱ አሸባሪዎች የኢትዮጵያውያንን አንገት መቅላት ሲጀምሩ ነብዩ መሐመድ ሲያስተምሩ የነበሩትን ትምህርት ወደ ጎን አሽቀንጥረው ጣሉት፡፡ ለእነዚህ የሽብር እና የነውጥ ተዋንያን አላህ ምህረቱን አይሰጣቸውም! እነዚህን ምስኪን እና ጨዋ ኢትዮጵያውያን የአላህ ዓይን ይጎበኛቸዋል! አላህ አክብር ሞት ለአሸባሪዎች እና ለግፈኞች!

መለስ እና እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እያለ የሚጠራው ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እ.ኤ.አ በ2005 የተደረገውን ሀገር አቀፍ ምደርጫ ውዝግብ ተከትሎ በተፈጠረው ሁከት ሰላማዊዎቹን ኢትዮጵያውያን አንገታቸውን አልቀሉም፣ ሆኖም ግን በአልሞ ተኳሾች እያነጣጠሩ ጭንቅላቶቻቸውን በጥይት ነበር የደበደቡ እንጅ አንገት አልቀሉም ነበር፡፡ በአንድ በቪዲዮ በተቀረጸ ቃለ መጠይቅ መለስ በዚያን ጊዜ ለፈጸመው እልቂት ምክንያት ለመስጠት እስከ 194 ሰዎች ላለቁበት እኩይ ምግባር እንዲህ የሚል ማሳመኛ ለመስጠት ሞክሮ ነበር፣ “በኢትዮጵያ ህገመንግስታዊ ትዕዛዝን ለመፈጸም ህገመንግስታዊ ተግዳሮት ነበር፣ እናም ያ ተግዳሮት አጋጥሞን ነበር፡፡“ በሌላ አባባል ሰላማዊ ሰዎች እልቂት እንዲፈጸምባቸው አድርጓል ምክንያቱም የእርሱን ህግ ተገዳድረዋልና፡፡ አምባገነኑ መለስ እንዲህ ብሎ ነበር፣ “ያ ዕልቂት የዓለም መሪዎችን አስተያየት በመቀየር ወደ እርሱ የሚያደላ መሆኑን ተጠራጥሮ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በግልጽ የኢትዮጵያን ገጽታ ጥላሸት ቀብቶ ነው የሄደው፡፡“

በእራሱ በመለስ ዜናዊ የተሾሙት እና የአጣሪ ኮሚሽኑ ሊቀመንበር የነበሩት የዳኛ ፍሬህይወት ዘገባ ፍጹም በሆነ መልኩ ሰላማዊ አመጸኞችን ነጻ በማድረግ አጠቃላይ ኃላፊነቱን እንዲህ በማለት በመለስ አገዛዝ ላይ ደፍድፎታል፡

የጦር መሳሪያ ጠብመንጃ ያነገበ ወይም ደግሞ የእጅ ቦምብ የታጠቀ አንድም ሰው አልነበረም፣ (የመንግስት መገናኛ ብዙሀን እንደገለጹት ጥቂት ሰላማዊ አመጸኞች ጠብመንጃ እና ቦምብ ታጥቀው ነበር፡፡) የአጣሪ ኮሚሽኑ አባላት በመንግስት ኃይሎች የተተኮሱት ጥይቶች ሰላማዊ አመጸኞችን ለመበተን አልነበረም፡፡ ሆኖም ግን የሰላማዊ ሰልፈኞችንጭንቅላት እና ደረት በአልሞ ተኳሾች እያነጣጠሩ በመምታት ለመግደል የተደረገ ድርጊት ነበር፡፡ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

እ.ኤ.አ በ2005 የተካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ በተፈጠረው ውዝግብ እና ሁከት በሰላማዊ ዜጎች ላይ እልቂት የፈጸሙት ወሮበላ ነብሰገዳይ ፖሊሶች እና የጸጥታ ኃይሎች ማንነት በትክክል ታውቆ እና ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ “በኢትዮጵያ የውስጥ የደህንነት ጥበቃን ማዘመን” በሚል ርዕስ በተዘጋጀ ዘገባ ላይ የጸረ ሽብር ባለሙያ የሆኑት እና የእግሊዝ ወታደራዊ ኃይል አባል የሆኑት ኮሎኔል ሚካኤል ደዋር የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ወርቅነህ ገበየሁ እንዲህ በማለት የገለጹላቸውን በመጥቀስ ተናግረዋል፣ “እ.ኤ.አ በ2005 በተካሄደው አመጽ 237 ፖሊስ አባላትን ከመደበኛ ስራቸው አባረዋል፡፡“ ምንም ዓይነት መሳሪያ ባልታጠቁ በኢትዮጵያ ንጹሀን ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ያሳስበናል! እ.ኤ.አ በ2005 የተካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ተፈጥሮ በነበረው ውዝግብ በርካታ ሰላማዊ ወገኖቻችንን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በጥይት እየደበደቡ እልቂት ሲፈጥሩ የነበሩት ወሮበላ ቅጥር ነብሰገዳዮች በአሁኑ ጊዜ ደረታቸውን ነፍተው በዋና ዋና መንገዶች ላይ ሲንገዳወሉ ይውላሉ፡፡ ያንን የመሰለ ዘግናኝ እልቂት የፈጸሙት ወይም ደግሞ እልቂቱ እንዲፈጸም ትዕዛዝ የሰጡት አንዳቸውም ወንጀለኞች እስከ አሁን ድረስ ለፍትህ አካል አልቀረቡም፡፡

በዚህ በያዝነው ሳምንት ከአንድ ዓመት በፊት እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እያለ የሚጠራው የወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ በኩል በ80 ማይሎች ርቀት ላይ በምትገኘው የአምቦ ከተማ ቢያንስ በ47 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እና በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ እልቂት ፈጽሟል፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አገዛዝ ይህንን አሰቃቂ እልቂት ሙልጭ አድርጎ በመካድ ዓይኑን በጨው በመታጠብ “ጥቂት ጸረ ሰላም ኃይሎች የለኮሱት እና ያቀነባበሩት አመጽ ነው” ብሎታል፡፡ በዚያን ጊዜ እንዲህ በማለት ተቃውሞዬን አሰምቸ ነበር፣ “በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ አዝኛለሁ፡፡ እነዚህ እምቦቃቅላ ሰላማዊ ወጣት ተማሪዎች በጥይት እየተደበደቡ በእንደዚህ ያለ አሰቃቂ ሁኔታ እልቂት የተፈጸመባቸው በመሆኑ በጣም አዝኛለሁ፡፡ በእነዚህ ለኢትዮጵያ ባለብሩህ ተስፋ ባለለቤቶች ላይ በተፈጸመው እልቂት ላይ እጅግ በጣም አዝናለሁ፡፡ ለእነዚህ የእኩይ ምግባር ሰለባ ለሆኑት ወጣቶች ቤተሰቦች እና ጓደኞቻቸው ሁሉ የማይሳነው አምላክ መጽናናቱን እንዲሰጣቸው እመኛለሁ፡፡“  የኢትዮጵያ ወጣቶች ህይወት ያሳስበናል!

በአምቦ ከተማ በንጹሀን ወገኖቻችን ላይ በጠራራ ጸሐይ ጥይት ያርከፈከፉት እነዚህ አረመኔ ቅጥር ነብሰ ገዳዮች በአሁኑ ጊዜ ያለምንም ተጠያቂነት በዋና ዋና መንገዶች ላይ ደረቶቻቸውን ገልብጠው በነጻነት ከወዲያ ወዲህ እያሉ ሲንገዳወሉ ይውላሉ፡፡ ይህንን ሰይጣናዊ የእልቂት ምግባር የፈጸሙት እና እልቂቱም እንዲፈጸም ትዕዛዝ የሰጡት ወሮበላ ባለስልጣኖች ለሕግ ሳይቀርቡ ያለምንም ተጠያቂነት እጆቻቸው በሰው ልጆች ደም ተጨማልቀው ይገኛሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ2013 በሳውዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን ሰራተኞች እና ስደተኞች ላይ የሽብር እና የእልቂት ዘመቻ ተከፈተባቸው፡፡ የሳውዲ ፖሊስ፣ የደህንነት ኃይል ባለስልጣኖች፣ ዱርዬዎች እና ወሮበሎች ለአንድ ሙሉ ቀን ያህል በየመንገዶች ኢትዮጵያውያንን እያደኑ እና እየያዙ ሲደበድቡ፣ ሲያሰቃዩ እና ሲገድሉ ነበር፡፡ በዩቱቤ ቪዲዮ የተለቀቀው ምስል እንደሚያሳየው የሳውዲ አረቢያ ፖሊስ በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ ሲፈጽም የነበረው ዘግናኝ ድርጊት እጅግ በጣም አስደንጋጭ፣ ለህሊናም የሚዘገንን እንዲሁም ምንም ዓይነት ማብራሪያ የማያስፈልገው የፈሪዎች እኩይ ምግባር ነበር፡፡ እንደዚህም ሆኖ ጥቂት የኢትዮጵያ ዜጎች በመንፈሰ ጠንካራነት በጽናት በመቆም የኢትዮጵያን ባንዲራ በራሳቸው ላይ ጠምጥመው እስከመጨረሻው በመታገል በሳውዲ አረቢያ ፖሊሶች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ የጥንት የትውልድ ዘሮቻቸውም እንደዚሁ በኩራት የተወጠሩ እና ለነጻነታቸው ቀናኢ የሆኑ ጀግኖች ነበሩ፡፡!

የወባ ትንኝ ተመራማሪው እና በብርህን ፍጥነት ከጤና ጥበቃ ሚኒስትርነት ወደ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የተተኮሰው ቴዎድሮስ አድኃኖም በዚያን ጊዜ እንዲህ የሚል ንግግር አድርጎ ነበር፣ “የወገኖቻችን መጋዝ እና መሞት እጅግ በጣም አሳስቦኛል፡፡“ አድኃኖም በኢትዮጵያ ለሚገኘው ለሳውዲ አረቢያው አምባሳደር እንዲህ የሚል የተማጽዕኖ ጥሪ አስተላልፎ ነበር፣ ኢትዮጵያ የሳውዲ አረቢያ ባለስልጣኖች ህገወጥ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ ሀገርለመመለስ እያደረገችያለችውን የማጋዝ እቅስቃሴ መሰረት በማድረግ ላስተላለፈቻቸው ውሳኔዎች የተሰማትን አድናቆት ትገልጻለች፡፡ በዚህ አጋጣሚ በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን ግድያ እና በዜጎቻቸው ላይ እየተተገበረ ያለውን ተገቢ ያልሆነ አያያዝ እናወግዛለን፡፡“ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

ለአድኃኖም እና ለእርሱ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ቡድን ኢትዮጵያውያን በሳውዲ አረቢያ ወሮበሎች ስለሚደርስባቸው የስብዕና እጦት፣ የሰብአዊ መብት ረገጣ እና ግድያ ጉዳያቸው አይደለም፡፡ ይኸ ጉዳይ ለእነርሱ ምንም ዓይነት የሚያናድዳቸው ነገር አይደለም፡፡ በዚያን ጊዜ “የሰው የዝውውር መጨናነቅ የታየበት ዋና ጊዜ” በሚል ርዕስ እጅግ በጣም በመናደድ ጽሑፍ አውጥቸ ነበር፡፡ የቤት ስራዎቻቸውን ሳይሰሩ ወደ ክፍል የሚመጡ ተማሪዎች እጅግ በጣም ያናድዱኛል፡፡ ደሜን እንዲፈላ ያደርጉታል፡፡ የሳውዲን ፖሊስ በሰው ልጆች ላይ የሚያደርገውን የሰብአዊ መብት ረገጣ፣ ኃላቀርነት እና አረመኔነት በተመለከትኩበት ጊዜ ግን እንደ እሳት ተቀጣጥዬ ነበር፡፡ የሳውዲ ወሮበሎች እና ዱርየዎች ሲያከናውኗቸው በነበሩት ድርጊቶች ላይ ከብስጭት ብዛት ከቁጥጥር ውጭ ሆኘ ነበር፡፡ የሳውዲ አገዛዝ በኢትዮጵያውያን ስደተኛ ወገኖቻችን ላይ ሲፈጽም የነበረው መጠነሰፊ ወንጀል እና የሰብአዊ መብት ረገጣ ላይ እጅግ በጣም ደንግጨ እና ተበሳጭቸ ነበር፡፡ በሳውዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው የሰብአዊ መብት ረገጣ አድሃኖምን ብዙም ያላሳሰበው እና ያላበሳጨው መሆኑ በንዴት ላይ ንዴት ተጨምሮብኝ የበለጠ እንድበሳጭ አድርጎኛል፡፡

እ.ኤ.አ ከ2013 ጀምሮ ስለኢትዮጵያውያን ጉዳይ ከመካከለኛው ምስራቅ እና ከደቡብ አፍሪካ የሚወጡ ዜናዎች አሳዛኝ እና ተመሳሳይነት ያላቸው ናቸው፡፡ (በደቡብ አፍሪካ ወሮበሎች እና ዘራፊዎች በኢትዮጵያውያን እና በሌሎች አፍሪካውያን ወገኖቻችን ዘንድ እየፈጸሙ ያሉትን ህገወጥ ወንጀል ወደፊት የማቀርበው ይሆናል፡፡) አሁን በቅርቡ ከሳምንት ባልበለጠ ጊዜ በመካከለኛው ምስራቅ አሰሪዋ በኢትዮጵያዊት የቤት ሰራተኛ ላይ የተፈጸመውን ህገወጥ ድርጊት በመቃወም እራሷን ያጠፋችውን ወይም ደግሞ ሌላ እራስን የሚያሰቃይ ድርጊት ወይም ክብርን የሚነካ ድርጊት የፈጸመችውን ኢትዮጵያዊት ስንመለከት እንደ ኢትዮጵያዊነታችን የሚሰማን መንፈስን የሚሰብር ድርጊት አለ፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት የ23 ዓመት እድሜ ያላት ኢትዮጵያዊት የቤት ሰራተኛ በቤይሩት ሊባኖስ እራሷን ሰቅላ ተገኝታለች፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ በንጹሀን ኢትዮጵያውያት የቤት ሰራተኛ ወገኖቻችን ህይወት ላይየሚደረገው አስፈሪ እናአስደንጋጭ ሁኔታ ያሳስበናል!

በአሁኑ ጊዜ በሳውዲ አረቢያ እና በሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ ኢሰብአዊነት ድርጊት እየፈጸሙ ያለምንም ተጠያቂነት ደረታቸውን ገልብጠው በዋና ዋና መንገዶች ላይ ሲንገዳወሉ ይታያሉ፡፡ በዚህ ሁሉ የሰብአዊ መብት ረገጣ ማለትም ድብደባ፣ ማሰቃየት እና ግድያ ሲፈጽሙ በነበሩት የዕኩይ ምግባር አራማጅ የሰብአዊ መብት ደፍጣጮች ወደ ህግ ሳይቀርቡ እና ምንም ዓይነት ተጠያቂነት ሳይኖርባቸው ነጻ ሆነው ይኖራሉ፡፡

እ.ኤ.አ ጥቅምት 2007 መለስ ዜናዊ እና የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በኦጋዴን የሽምቅ ውጊያ ሲያካሂዱ በነበሩት ዜጎች ላይ መጠነሰፊ የሆነ ጥቃት በመሰንዘር ወዲያውኑ ብዙም ሳይቆይ የጥቃት አድማሱን በማስፋት በሲቪሉ ህዝብ ላይ የጅምላ ጥቃት ፕሮግራም ተግባራዊ እንዲሆን ተደረገ፡፡ የመለስ ተዋጊ ጦር የኦጋዴንን መንደሮች በሙሉ አወደመ፣ የአስገድዶ መድፈር ተግባራትን ፈጸመ፣ ግድያ እና አጠቃላይ ዘረፋዎችን ፈጸመ፡፡ ህዝቡን ለማስፈራራት እና ለማሸማቀቅ በሚል እኩይ ሀሳብ ዜጎችን በማነቅ እና አንገታቸውን በመቅላት በአደባባይ እንዲጣሉ ተደረጉ፡፡ ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅት ለዩኤስ አሜሪካ የአፍሪካ የውጭ ጉዳዮች እና ለዓለም ጤና ጥበቃ ንኡስ ኮሚቴ የሚከተለውን ተናግሮ ነበር፣ “ኦጋዴን ዳርፉር አይደለችም፡፡ ሆኖም ግን በኦጋዴን ያለው ሁኔታ አስደንጋጭ የሆነ ተመሳሳይ የሆነ አስፈሪ ነገርን ያመላክታል፡፡“ በኦጋዴን ያሉወገኖቻችን ህይወትም ያሳስበናል፡፡!  

በምስራቅ ኢትዮጵያ በኦጋዴን አካባቢ በሰው ልጆች ላይ እልቂትን፣ የዘር ማጥፋት ወንጀልን የፈጸሙ እና ወንጀሉ እንዲፈጸምም ትዕዛዙን የሰጡት ኃላፊዎች ምንም ዓይነት እርምጃ ሳይወሰድባቸው እና አንዳቸውም ለህግ ሳይቀርቡ እስከ አሁንም ድረስ በነጻነት በየመንገዶች ደረቶቻቸውን ነፍተው በመንገዋለል ላይ ይገኛሉ፡፡

እ.ኤአ. ታህሳስ 2003 መለስ ዜናዊ እና የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በምዕራብ ኢትዮጵያ በጋምቤላ ህዝቦች ላይ መጠነ ሰፊ የሆነ ጦርነት እንዲካሄድባቸው የጦር ኃይላቸውን በማዘዝ 400 የአኟክ ህዝቦች እንዲገደሉ ሲደረግ ከ1,000 በላይ የሚሆኑ ቤቶች ደግሞ እንዲወድሙ ተደርገዋል፡፡ በቀጣይነትም የመለስ አገዛዝ እንዲህ የሚል መግለጫ አውጥቶ ነበር፣ “በዚህ ጉዳይ ላይ ፈጣን የሆነ እርምጃ ባለመወሰዱ ይቅርታ እየጠየቅን ወደፊት ግን የጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት ወገኖች ጎን በጽናት በመቆም አጥፊዎቹ ለህግ እንዲቀርቡ እናደርጋለን፡፡“ በዚያን ጊዜ አገዛዙ በአኟክ እልቂት ላይ ተዋንያን የነበሩ እና እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ በደርዘኖች የሚቆጠሩ ተጠርጣሪዎች ተለይተው ነበር፡፡ እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ ማናቸውም ቢሆኑ ለህግ አልቀረቡም፡፡ በጋምቤላ ያሉ ወገኖቻችን ህይወትም ያሳስበናል፡፡! በምዕራብ ኢትዮጵያ በጋምቤላ አካባቢ በሰው ልጆች ላይ እልቂትን፣ የዘር ማጥፋት ወንጀልን የፈጸሙ እና ወንጀሉ እንዲፈጸምም ትዕዛዙን የሰጡት ኃላፊዎች ምንም ዓይነት እርምጃ ሳይወሰድባቸው እና አንዳቸውም ለህግ ሳይቀርቡ እስከ አሁንም ድረስ በነጻነት በየመንገዶች ደረቶቻቸውን ገልበጠው በመንገዋለል ላይ ይገኛሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን በማገልገል ላይ የሚገኝ ምንም ዓይነት ወታደር፣ ፖሊስ፣ የደህንነት ኃላፊ እና ሌላ የሲቪል ባለስልጣን በህግ ፊት እንዲቀርብ ተደርጎ የተቀጣ፣ ላጠፋው ጥፋት ተጠያቂ የሆነ ወይም ደግሞ ለፈጸማቸው ግድያዎች፣ ወንጀሎች እና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች፣ የጦር ወንጀሎች ወይም ጦrኝነት ተጠያቂ ሆኖ አያውቅም፡፡

በኢትዮጵያውያን/ እና በኢትዮጵያዊ/ያት ስደተኛ ላይ እየተካሄደ ያለው ነጻ የሰው አደን መቆም አለበት!

የንዴት ሞት እና በኢትዮጵያውያን መሞት ላይ ያለው ንዴት፣ 

ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ምንም ዓይነት ርህራሄ በሌለው አሸባሪ ቡድን እንደ በግ የመታረዳቸው ሁኔታ በዓለም ህዝብ ዘንድ ታላቅ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡ ጳጳስ ፍራንሲስ እንዲህ ብለዋል፣ “ሰላማዊ በሆኑ የክርስትና እምነት ተከታዮች ላይ በሊቢያ በጨካኝ ሸፍጠኞች የተደረገው እልቂት በጣም አስደንጋጭ እና አሳዛኝ ነገር ነው፡፡“ በመቀጠልም እንዲህ በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል፣ “በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና በጥቂት የኤስያ ሀገሮች በዚህ ዓይነት ቀጣይነት ባለው እንደዚህ ባለ ጭካኔ በተመላበት የክርስቲያኖች መስዋዕትነት ከልብ የሆነ መንፈሳዊ ትብብር አስፈላጊ ነው፡፡“ ጳጳሱ እነዚህ አሸባሪ ቡድኖች ከሰይጣን ጎን የቆሙ ናቸው በማለት እንዲህ ብለዋል፡፡ “የእኛ የክርስቲያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ደም በእያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ ገብቶ በመጮህ በደግ ነገር እና በሰይጣናዊ ድርጊት መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ የሚሰማ ምስክርነት ነው፡፡“

የኦባማ አሰተዳደር በአይኤስአይኤል/ISIL እና ተባባሪዎቹ በሊቢያ በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመውን ጭካኔነት የተሞላበት የሽብር የግድያ እልቂት ጠንካራ በሆነ መልኩ አውግዘዋል፡፡ እነዚህ አሸባሪዎች የጥቃት ሰለባዎቹ በአሸባሪዎች ላይ ባላቸው እምነት፣ ጦረኝነት፣ እደገኛነት እና ጨካኝነት ምክንያት ብቻ እነዚህን ወንዶች ገድለዋቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት እየተባለ የሚጠራው የአምባገነን ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በመጀመሪያ ይህንን አሸባሪዎች የጥቃት ሰለባዎችን አንገት እየቀሉ አሰቃቂ በሆነ መልኩ የገደሏቸውን ዜጎች ኢትዮጵያውያን ናቸው ብሎ ለመቀበል እና ዕውቅና ለመስጠት ተቃውሞውን አሰምቶ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባይ የሆነው ሬድዋን ሁሴን የእርሱ መንግስት የጥቃቱ ሰለባ የኢትዮጵያ ዜጎች መሆናቸውን ገና ማረጋገጥ ሳይችል የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን በሰው ልጆች ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ድርጊት ያወግዛል ብሏል፡፡

አንገታቸውን እየተቀሉ የተገደሉት የጥቃቱ ሰለባዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው የሚለውን ዘገባ ሲኤንኤን/CNN የተባለው ዓለም አቀፍ የዜና ወኪል ቢዘግብም እንኳ ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ጉዳዩ አይደለም፡፡ አልጃዚራ/Al Jazeera የተባለው ዓለም አቀፍ የዜና ወኪል አንገታቸውን እየተቀሉ እንዲገደሉ የተደረጉት ዜጎች ኢትዮጵያውያን ናቸው የሚል ዘገባ ቢያቀርብም ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ምኑም አይደለም፡፡ ሬውተርስ/Reuters፣ ኤጀንስ ፍራንስ ፕሬስ/Agence France Press ቢቢሲ/BBC፣ ቪኦኤ/VOA እንደ ኒዮርክ ታይምስ ያሉ የዜና ወኪሎች በሙሉ በአሸባሪዎች ዕኩይ ምግባር የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑት ኢትዮጵያውያን ዕውቅና በመስጠት ሀዘናቸውን የገለጹ ሲሆን የእኛዎቹ ፈጣጣዎች ግን እውነታውን በመቀበል ዕውቅና ለመስጠት ባለመፈለግ አሻፈረኝ ብለዋል፡፡ ለመሆኑ እነዚህ ደንታቢሶች ስለምን ጉዳይ ነው ሊያሳስባቸው የሚችል? አንገታቸውን እየተቀሉ የተገደሉ የሌላ ሀገር ዜጎች መሆናቸውን በስህተት የገለጹ በመሆናቸው ምክንያት ቀደም ሲል ስለዚህ ጉዳይ መረጃው ነበራቸውን? በዓለም ላይ በየትኛውም ቦታ ቢሆን የማንም ጨዋ ሀገር መንግስት በዓለም አቀፍ የዜና ወኪሎች በተደጋጋሚ የተገለጸን እውነታ በጥሬው እንዳለ እውነት ነው ብሎ መውሰድ እና ቁጣውን እና የሚያሳስበው መሆኑን መግለጽ የለበትምን!?

እውነታው ግን፡ ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ምንም ዓይነት ደንታ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ ደም በጠማቸውአሸባሪ ዘራፊዎች ስለጠፋውይህ የወጣት ኢትዮጵያውያን ዕልቂት ለወያኔ ምኑም አይደለም!!! 

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እነዚህ የጥቃቱ ሰለባዎች አንድ ጊዜ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ካረጋገጠ በኋላ የአዞ እንባ በማንባት እንዲህ የሚል መግለጫ አወጣ፣ “ጭካኔ በተሞላበት መልኩ ምንም ነገር በሌላቸው በንጹሀን ዜጎቻችን ላይ በተፈጸመው እኩይ ድርጊት ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶናል፡፡”

ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በሊቢያ አሸባሪዎች በግፍ ያለቁት የጥቃቱ ሰለባ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ከታወቀ በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት የሶስት ቀናትየሀዘን ቀን በማለት አውጇል፡፡ 

አድኃኖም እና የእርሱ የወረቀት አለቃው እና የኢትዮጵያ የይስሙላው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በሊቢያ ለቀሩት ኢትዮጵያውያን ወገኖች አስተማማኝ ደህንነት ሲባል ምንም ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ ሳይወስድ ለይስሙላ እንኳ ለታዕይታ ያህል ምንም ነገር ሳይደርግ ዝም በማለት አልፎታል፡፡ ምንም ዓይነት ዲፕሎማሲያዊ ተቃውሞ እንኳ አልተደረገም፡፡ አስገዳጅ በሆነው የዲፕሎማሲ አካሄድ መንገድ እንኳ ለመንቀሳቀስ አልተሞከረም፡፡ በሊቢያ ለቀሩት ኢትዮጵያውያን ደህንነት ሲባል ለተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር መጠለያ በመስጠት እርዳታ እንዲደረግላቸው እንኳ አስቸኳይ የሆነ ጥያቄ አላቀረበም፡፡ ኃይለማርያም እና አድኃኖም የእነርሱ ቃል አቀባይ ሁሉንም ንግግር እንዲናገር በመተው በቤተክርስቲያን ውስጥ እንዳሉ አይጦች ጸጥ በማለት አልፈውታል፡፡ ይኸ ጉዳይ የሚያስደንቅ አይደለም ምክንያቱም የኢትዮጵያ ስደተኞች የትም ሀገር እንዲሄዱ አይፈልጉም!

ለታሪክ ምዝገባ ያህል አድኃኖም እና የእርሱ የወረቀት አለቃው ኃይለማርያም ደሳለኝ እ.ኤ.አ ጥቅምት 2013 በአፍሪካ ህብረት የስብሰባ አዳራሽ በመገኘት የእነርሱ የምግባር ጓደኛ የሆነው ኡሁሩ ኬንያታ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በመከሰሱ ምክንያት ያዙኝ ልቀቁኝ በማለት ድርጅቱ ሰው ገዳይ እና ዘር አዳኝ እንደሆነ አድርገው ቡራ ከረዩ ሲሉ የነበሩትን ሁኔታ ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ በዚያ ስብሰባ ወቅት ሁሉም ሀገሮች የሮምን ስምምነት በመጠቀም ስብሰባውን ረግጠው ከድርጅቱም እንዲወጡ ለማድረግ ግንባር ቀደም የመድረክ ላይ ተዋናይ ሆነው ታይተዋል፡፡

ዛሬ ወገኖቻቸው በሊቢያ እና በመካከለኛው ምስራቅ የተለያዩ ቦታዎች እንደ አውሬ እየታደኑ ሲገደሉ እና በየቀጣሪዎቻቸው መኖሪያ ቤቶች እንደላውንድሪ ልብስ ሲሰቀሉ እና ሲሰጡ  እያዩ እና እየተመለከቱ ምላሳቸው ታሽጓል፣ አንደበታቸው ተሸብቧል፡፡ የአፍሪካ ህብረት በእነዚህ አሸባሪዎች ላይ እርምጃ  እንዲወስድ የመድረክ ላይ ትወና ያላደረጉት ወይም ደግሞ ቁጣቸውን ለመግለጽ ድፍረቱን ያጡት ለምንድን ነው? ለአድኃኖም፣ ለኃይለማርያም እና ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እ.ኤ.አ በ2013 በሳውዲ አረቢያ በዜጎቻችን ላይ እንደተፈጸመው፣ እ.ኤ.አ በ2005 በኢትዮጵያ የድሀረ ምርጫውን ውዝግብ ተከትሎ ተፈጥሮ እንደነበረው…ሁሉ ተመሳሳይ እንደሆነ አድርገው ነው የሚመለከቱት፡፡ ጉዳዩ ለአንድ ሳምንት ወይም ለሁለት ሳምንታት ያህል የሚያነጋግር ይሆን እና ከዚያ በኋላ እልም ሙልጭ ብሎ በመጥፋት ያው የተለመደው አካሄድ ይቀጥላል፡፡

በዚህ ባሳለፍነው የካቲት ወር ከ21 በላይ የግብጽ ጳጳሳት በጭራቃዊ አሸባሪ ቡድን አባላት በታረዱበት ጊዜም እንደዚሁ ምንም ነገር ሳይደረግ ነው የቀረው፡፡ በሊቢያ አንገታቸውን እንደተቀሉት ኢትዮጵያውያን ሁሉ የግብጽ ጳጳሳትም ብርቱካናማ ልብስ እንዲለብሱ ተደርገው እና እጃቸውን ወደ ጀርባቸው አድርገው በማሰር እልቂቱ እንዲፈጸምባቸው ተደርጓል፡፡ የግብጽ ወንዶች እንደ ኢትዮጵያ ወንዶች ሁሉ አንገታቸው ከመቀላቱ በፊት እንዲንበረከኩ ተደርገዋል፡፡

ፕሬዚዳንት አብደል ኤል ሲሲ የግብጽ ጳጳሳት አንገት መቀላቱን በሰሙ ጊዜ እንደ እብድ ሆነው ነበር፡፡ በቴሌቪዥን የዘለቀ ንግግር በማድረግ ለዚህ ዕኩይ ድርጊት ግብጽ ወዲያውኑ የአጻፋ እርምጃ እንዳትወስድ እና የመቆጠብ መብት እንዳላት አሳስበው ነበር፡፡ ጥልቅ የሆነ ሀዘናቸውን እንዲህ በማለት ገልጸው ነብር፣ “በሊቢያ የሞራል ስብዕና በጎደለው መልኩ ያለቁትን የግብጽ የጥቃት ሰለባዎች የዓለም ህዝብ እንዲገነዘበው እና በዚህ አሰቃቂ ዕልቂት የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እና የግብጽ ህዝብ የተጎዳውን ጉዳት ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡“ በሰዓታት ጊዜ ውስጥ ኤል ሲሲ በሊቢያ ከመከላከያ ምክር ቤታቸው ጋር በመምከር የአሸባሪዎች መቀመጫ ከተማ በሆነችው ዴርና ተብላ በምትጠራው የሊቢያ ከተማ ላይ የግብጽን ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ለማሰማራት ስምምነት አደረጉ፡፡ በአሰቃቂ ሁኔታ በግፍ ለተገደሉት 21 የግብጽክርስቲያኖች ሰማአታት ክብር ሲባል ግብጽ የሰባት ቀናት የሀዘን ቀናት አድርጋ አወጀች! በጣም የሚያበሳጨው እውነታ ደግሞ በሊቢያ የሚገኙት ቀሪዎቹ የኢትዮጵያ ስደተኞች እና በሊቢያ ከወያኔ አገዛዝ አምባሳደር የስልክ ቁጥር ተስጥቷቸው ግንኙነት እንዲያደርጉ ቢነገራቸውም ምንም ዓይነት የማቴሪያል እና የሞራል ድጋፍ ያለመደረጉ ጉዳይ ነው፡፡ እርዳታ ለማግኘት ሲያደርጓቸው የነበሩት ጥረቶች ሁሉ በግዴለሽነት ምክንያት ስኬታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ አሁን በቅርቡ ከአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ፕሮግራም ጋር ከኢትዮጵያ ስደተኞች ጋር ከተደረገ ቃለ መጠይቅ በተገኘ ዘገባ መሰረት ስደተኞቹ እርዳታ ከማግኘት ይልቅ ቸልተኝነትን እና ግድየለሽነትን አሳይተዋቸዋል፡፡ አንድ ቃለመጠይቅ አድራጊ እንዲህ የሚል ዘገባ አቅርቦ ነበር፡

“በግብጽ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር ለመገናኘት እና ድጋፍ ለማግኘት የኤምባሲውን ስልክ ቁጥር አግኘተን ነበር፡፡ ሆኖም ግን ከኢትዮጵያ መንግስት ምንም ዓይነት እርዳታ አላገኘንም፡፡ ይልቁንም በገዛናት ትንሽ የስልክ ጥሪ ካርድ በመጠቀም በግብጽ ካለው የኢትዮጵያ  ኤምባሲ ጋር ለመገናኘት የተቻለንን ያህል ጥረት በማድረግ ስንደውል ነበር፡፡ በምንደውልበት ጊዜ ስልኩን ያነሱ እና ያሾፉብን ነበር፡፡ ከእኛ ጋር ንግግር አያደርጉም ነበር፡፡ ስልኩን ያነሱ እና ከእኛ ጋር ባለመነጋገር ስልኩ የጥሪ ካርዱን ያለምንም ፋይዳ እንዲጨርስ ያደርጉብን ነበር፡፡ ከዚያም ሌላ ካርድ እንገዛ እና እንይዛለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ምንም ዓይነት ምላሽ አይሰጡም…”

ሌላ በአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ፕሮግራም ቃለ መጠይቅ የተደረገለት ሰው ደግሞ እንዲህ የሚል ተመሳሳይነት ተሞክሮ ያለው ዘገባ አቅርቧል፡

“በእርግጥ አድኃኖም፣ ኃይለማርያም እና ወያኔ ለእነርሱ ምን እንደሚናገሩ ሁላችንም እናውቃለን፡ ምንም ነገር አይተውም፡፡ እድሉን አግኝተው ነበር ነገር ግን አልተጠቀሙበትም፡፡ ስለዚህም ቀደም ሲል ነግረናቸዋ፡፡ ከዚያም ትምህርት ይቀስማሉ ብለን እናስባለን…ዘበት! ዘበት! ዘበት! …“

ግን የኢትዮጵያ ወጣቶች እግሮቻቸው ወደመሯቸው የሚሄዱት ለምንድን ነው?

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሀገራቸውን በመልቀቅ እንደዚህ ላለ አደገኛ የሆነ ችግር ውስጥ የሚገቡት ለምንድን ነው?

ወተት እና ማር የሚፈስባትን እና ባለሁለት አሀዝ የምጣኔ ሀብት ዕድገት እያስመዘገበች ነው እየተባለ የሚደሰኮርላትን ሀገራቸውን እየለቀቁ ለመሰደድ የሚመርጡት በምን ምክንያት ነው?

ዕድለቢሶቹ ኢትዮጵያውያን አሰቃቂ የሆነውን የዕልቂት ዕጣ ፈንታ ለመገናኘት ወደ ሊቢያ የሚጓዙት ለምንድን ነው?

ለእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልሱ ቀላል እና አጭር ነው፡፡ እነዚህ ወጣቶች ኢትዮጵያን ጥለው የሚሄዱት በትምህርት እና በሥራ ዕድል በተንበሸበሸ ስርዓት ውስጥ ስለኖሩ ነው?  እነዚህ ወጣቶች ኢትዮጵያን ጥለው የሚሄዱት የምጣኔ ሀብት ነጻነትን ተጎናጽፈው ስለኖሩ ነው? እነዚህ ወጣቶች ኢትዮጵያን ኢትዮጵያን ጥለው የሚሄዱት በሰሜን አፍሪካ ባሉ በረሀዎች ላይ ጀብዶችን ለመስራት ስለሚፈልጉ ነው?  እነዚህ ወጣቶች ለሁሉም ነገር አደጋን ህይወታቸውን ጨምሮ የመጋፈጥ ድፍረቱ አላቸው ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚያገኙት የኑሮ ሁኔታ የበለጠ ወደ ውጭ በመሰደድ የተሻለ የኑሮ ሁኔታ ማግኘት ስለሚችሉ ነው፡፡ ህይወታቸውን ለማሻሻል ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖሩ ነበር፣ ሆኖም ግን በድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀው የሚገኙትን ደኃ ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ሲሉ በተቃጠለው የአፍሪካ በረሀ በመጓዝ የመሞት አደጋን ይጋፈጣሉ፣ ወይም ደግሞ በመካከለኛው ምስራቅ ለሚገኙ ጨካኝ ለሆነ ወይም ለሆነች የቤተሰብ ኃላፊ አገልጋዮች ይሆናሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ ወጣት ኢትዮጵያውያን በወያኔ አምባገነን ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ቁጥጥር ስር በድህነት እና በነጻነት እጦት ተዋርደው ከሚኖሩ ይልቅ እግራቸው ወደመራቸው በበረሀ እና በጫካ ውስጥ ሄደው ለመሞት ፈቃደኞች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ወደ ሊቢያ በመሄድ እንዲህ የሚለውን ታዋቂ የነጻነት መፈክር በማሰማት የሞት ጽዋቸውን ተጎንጭተዋል፡ “ሞቴን ስጠኝ ወይም ደግሞ ነጻነቴን ስጠኝ!“ እነዚህ ወጣቶች ከወሮበላ አምባገነኖች የግፍ አገዛዝ ነጻ ሆነው ለመኖር ሲሉ በሌሎች ወሮበሎች እጅ ወድቀው ህይወታቸውን አጥተዋል! ሆኖም ግን በነጻነት ለመኖር ሙከራ ሲያደርጉ በመስዋዕትነት አልፈዋል!

ኢትዮጵያውያን/ት ሀገራቸውን ከልብ ይወዳሉ፡፡ ሀገራቸው በዲኤንኤ ዘረመላቸው ውስጥ ተቀብሮ የሚኖር ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን የመጨረሻዎቹ ወንድ እና ሴት እስከሚቀሩ ድረስ የምጣኔ ሀብት ፍላጎታቸውን ለማሻሻል ሲሉ ብቻ ሀገራቸውን ትተው እና በከፍተኛ አደጋ ውስጥ ገብተው በፈቃደኝነትም ሆነ በሌላ መልክ ከሀገር በመውጣት ስደተኛ አይሆኑም ወይም ደግሞ በረሀውን እና ጫካውን እያቋረጡ የአውሬ እና የአሞራ እራት አይሆኑም፡፡ ወጣቶች ሀገራቸውን ባለመውደዳቸው ምክንያት አይደለም እየተሰደዱ ያሉት ሆኖም ግን የፍቅር እና የሰላም የነበረችው መሬት ወደ ጥላቻ መሬትነት በመሸጋገሯ ምክንያት ነው፡፡ የ13 ወራት የጸሐይ ብርሀን ባለቤት የሆነችው ሀገራቸው አስከፊ በሆነ የአምባገነንነት የጨለማ መጋረጃ ለሩብ ምዕተ ዓመት ያህል በመሸፈኗ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ትተው ከሚሰደዱ ይልቅ ለሀገራቸው ያላቸው ፍቅር የበለጠ ነው፡፡

እንደ ጣሴ አብይ ዘገባ የኢትዮጵያውያን/ት ወደ ውጭ ሀገር የሚደረግ ፍልሰት እንደማዕበል ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ የተካሄደው የመጀመሪያው ማዕበል በጣም ጥቂት በሆኑ ምሁራን እና በጊዚያዊነት ብቻ አብዛኛውን ጊዜ ወደ ምዕራቡ ዓለም በዋናነት በትምህርት እና በስልጠና ስም ከሀገር የሚወጡ እና ወደ እናት ሀገራቸው የመመለስ ዓላማን ያነገቡ ነበሩ፡፡ ያ አዝማሚያ እ.ኤ.አ ከ1974 – 1982 ባሉት ዓመታት ውስጥ የተከናወነው ሁለተኛው የስደት ማዕበል ነው፡፡ በዚህ ጊዜ አምባገነኑ እና አረመኔው የወታደራዊ መንግስት እ.ኤ.አ ከ1974 ጀምሮ ማንኛውም ዜጋ ሀገሩን ትቶ መሰደድ እንዳይችል ከፍተኛ የሆነ ችግር ፈጥሮበት ነበር፡፡ እናም በተለያየ ሁኔታ ከሀገር ሾልከው ለመኮብለል ሲሞክሩ የተገኙ ዜጎች ላይ አደገኛ የሆነ ቅጣት ይጣል ነበር፡፡ የደርግ ወታደራዊ ጭቆና የኢትዮጵያውያንን የስደተኞች የጎርፍ በር ብርግድ አድርጎ ከፈተው፡፡

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን/ት የኑሮ መሰረታቸውን በሰሜን አሜሪካ ለማድረግ ሀገራቸውን ትተው ይሰደዳሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ1965 የዩኤስ አሜሪካ የስደተኞች እና የዜግነት ድንጋጌ ሕግ ሀኖ ከወጣ በኋላ ኢትዮጵያውያን/ት ወደ ዩኤስ አሜሪካ ለመሰደድ ከአፍሪካ ሶስተኛ በመሆን ትልቅ ደረጃ ላይ ሆና ተገኝታለች፡፡

አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን/ት ወደ አሜሪካ የደረሱት ዩናይትድ ስቴትስ እ.ኤ.አ በ1980 በምክር ቤቱ ህግ ሆኖ ከወጣ በኋላ ሶማሌዎች እ.ኤ.አ በ1994 በመቅደም የመሪነቱን ቦታ እስከሚይዙት ድረስ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ታላቁ የስደተኞች ቡድን ሆና ቆይታለች፡፡

እንደ ጣሴ ዘገባ እ.ኤ.አ በ1991 የኮሎኔል መንግስቱ አገዛዝ ከወደቀ በኋላ አራተኛው የስደተኛ የጎርፍ ማዕበል አብዛኛውን ጊዜ የጎሳ ግጭትን ለማምለጥ እና የፖለቲካ ጭቆናን ለማስወገድ ሲባል የጎሳ ባለሙያዎች በገፍ ከሀገር መሰደድ ጀመሩ፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር  በጣም አስቸጋሪ የሆነበት እና ሀገርን ጥሎ ለመሰደድ የተቻለበት ጊዜ አምስተኛው ማዕበል እየተባለ የሚጠራው የስደተኞች ጊዜ ነው፡፡ “ከዓለም አቀፍ የባሪያ ንግድ ወደ ዓለም አቀፍ የቤት ሰራተኛ ንግድ“ በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ ጥር 2012 ባቀረብኩት ትችት መሰረት ወደ ውጭ ለሚደረግ ስደት ዋናው ምክንያት የኢትዮጵያ ውስጣዊ የፖለቲካ ሁኔታ ነው፡፡

በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አገዛዝ ዘመናዊ የባሪያ በንግድ አስፈጻሚዎች ትስስር እና ፈቃድ አውጥተው እየሰሩ ያሉ የግል ቀጣሪ ኤጀንሲዎች በመካከለኛው ምስራቅ በኢትዮጵያውያን ሴቶች ላይ ታላቅ ችግርን ፈጥሯል፡፡ እነዚህ የሰው ንግድ የሚያካሂዱ ድርጅቶች የኮንትራት ባርነትን በመፍጠር በድብቅ በባለስልጣኖች የሚሰጥ ድጋፍ እና ምንም ዓይነት የክትትል ስራ ሳይሰራ የሰራተኞችን ደህንነት እና የኑሮ ሁኔታ በሄዱበት ሀገር የሚረጋገጥ ይሆናል፡፡

በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የኢትዮጵያ የቤት ሰራተኞች በቢና ፌርናንድዝ ጥናት በ7ኛው ምዕራፍ ላይ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ በ2009 በየመን አድርገው ወደ ሳውዲ አረቢያ ለመሸጋገር 74 ሺህ ህዝብ በአደጋ ውስጥ ወድቆ የነበረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 42 ሺህ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን/ት ናቸው፡፡ በመንግስት መረጃ መሰረት በመካከለኛው ምስራቅ ከሚገኙት ኢትዮጵያዊ የቤት ሰራተኞች ውስጥ 91 በመቶ የሚሆኑት ብቻቸውን ያሉ ሴቶች ሲሆኑ 83 በመቶ የሚሆኑት ከ20- 30 ባሉት የእድሜ ጣሪያ ውስጥ የሚገኙት ናቸው፡፡ ወደ 63 በመቶ የሚሆኑት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያላቸው ሲሆኑ 26 በመቶ የሚሆኑት ምንም ዓይነት ማንበብ እና መጻፍ የማይችሉ ማይሞች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 71 በመቶ የሚሆኑት ሙስሊሞች ሲሆኑ 93 በመቶ የሚሆኑት በየወሩ ከ100 – 150 ዶላር የኪስ ግንዘብ ይሰጣል፡፡ እነዚህ ጥቂት ሴቶች ከመንግስት ጋር በስደተኛ ሰራተኝነት በመንግስት ምዝገባ ያደርጋል፡፡ ሌሎቹ ህገወጥ ደላላዎች እና ላባቸውን ያላፈሰሱበትን መውሰድ የሚፈልጉ በዝባዦች ደግሞ የሴቶችን ገንዘብ ቀምተው ይወስዱ እና ሶማሌ እንኳ ሳይደርሱ በበረሀ ላይ ጥለዋቸው ይሄዳሉ፡፡

ህወሀት እና ህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣

እ.ኤ.አ ከ1998 ጀምሮ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በአዋጅ ቁጥር 104/1998 የግል ስራ ቀጣሪ ኤጀንሲን በማቋቋም ለግል ስራ ቀጣሪ ኤጀንሲዎች እና ህገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎችን እና ደላላዎችን በህግ ሊያስጠይቅ የሚችል አዋጅ አወጣ፡፡ እ.ኤ.አ በ2009 ይኸ አዋጅ ተሻረ እና “የስራ አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 632/2009“ በሚል ሌላ አዋጅ ተተካ፡፡ ይህ አዲሱ አዋጅ የግል የስራ ቀጣሪ ኤጀንሲዎች እድሚያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎችን መቅጠር እንደማይቻል፣ ከተቀጣሪው ሰው ጋር በጽሁፍ ስምምነት እስካልተደረሰ በስተቀር ማንንም ሰራተኛ ተነስቶ ከስራው ማባረር እንደማይቻል፣ ስራ ለመቀጠር እና አዲስ ስምምነት ለመፈራረም ወይም የቆዬ ስምምነትን ለማደስ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ወይም ቆንስላ ጽ/ቤት ፈቃድ ማግኘት እንደሚያስፈልግ፣ ወደ ውጭ ሀገር የሄደ ስራ ፈላጊ በ15 ቀናት ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ወይም ቆንስላ ጽ/ቤት ቀርቦ መመዝገብ እንዳለበት በግልጽ አስቀምጧል፡፡  

ስራ ፈላጊዎችን ወደ ውጭ ሀገር የሚልክ የግል ስራ ቀጣሪ ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ዜጎች ለስራ ፍለጋ የሄዱበት ሀገር የስራ ሁኔታ የሌሎች ሀገሮች ስራ ፈላጊዎች ሄደው ከሚሰሩት የስራ ሁኔታ እና ያነሰ ጥቀም እንዳይኖረው የማረጋገጥ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ የውጭ ሀገር ቀጣሪ ሰራተኛው ለተንቀሳቀሰበት ሀገር የቪዛ ክፍያ፣ የደርሶ መልስ ቲኬት፣ የኗሪነት፣ የስራ ፈቃድ እና የኢንሹራንስ ክፍያዎችን ለሰራተኛው እንዲከፍል ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህም በላይ ስራ ፈላጊዎችን ወደ ውጭ ሀገር ልኮ ስራ ለማስቀጠር ፈቃድ የተሰጠው ማንኛውም የግል ስራ ቀጣሪ ኤጅንሲ የሰራተኛውን መብት ለማስጠበቅ እና በመብቱ ሊያገኛቸው የሚፈለጉትን ጥቅሞች ተግባራዊ ለማስደረግ እስከ 500 ለሚሆኑ ሰራተኞች ቢያንስ 30,000 ዶላር በባንክ ሂሳብ ማስቀመጥ ወይም ደግሞ ቦንድ መግዛት እንዳለበት ግዴታ ተጥሎበታል፡፡

አዋጅ ቁጥር 632ን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም የግል ስራ ቀጣሪ ኤጀንሲ ስራው ለተወሰነ ጊዜ እዲቋረጥ፣ ህገወጥ ስለሆነ ወደ ተግባር መሸጋገር እንደማይችል ወይም ደግሞ የስራ ፈቃዱ እንደሚሰረዝ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ በዚያ አዋጅ በአንቀጽ 40 ስር በርካታ የሆኑ አሳሪ የወንጀለኛነት ቅጣቶች ተዘርዝረው የተቀመጡ ቢሆንም ቅሉ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር አስፈጻሚዎችን ወደ ህግ ሊያቀርብ የሚያስችል ተግባራዊ እንቅስቃሴ ግን በጣም አናሳ መሆኑን ሊያስረዱ የሚችሉ ማስረጃዎች አሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 የወጣው የዩኤስ የመንግስት መምሪያ ዘገባ ከሆነ እ.ኤ.አ በመጋቢት እና ጥቅምት 2009 መካከል የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት 11ኛ የወንጀል ችሎት ስለድንበር ተሻጋሪ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር የተያያዙ 15 ጉዳዮች ቀርበውለት ከእነዚህ ውስጥ 5ቱ የጥፋተኝነት ብይን የተሰጠባቸው፣ 9ኙ ጥፋተኝነት የሌለባቸው እና አንዱ ደግሞ ምስክር ባለመገኘቱ ምክንያት እንዲቋረጥ የተደረገ ሆኗል፡፡ 5ቱ የጥፋተኝነት ብይን ከተሰጠባቸው መካከል 3ቱ ተከላካዮች የ5 ዓመት እስራት በመጣል ስራቸውም እንዲቆም ሲደረግ፣ ሁለቱ ተከላካዮች ደግሞ በገንዘብ እንዲቀጡ የተደረገ ሲሆን አንዱ ተከላካይ ደግሞ የ5 ዓመት እስራት ተበይኖበታል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን/United Nations Higher Commission for Refugees (UNHCR) እ.ኤ.አ በ2011 እንዲህ የሚል ዘገባ አውጥቷል፣ “የኢትዮጵያ መንግስት የእራሱ ዜጎች ለስራ ጉዳይ ከሚሄዱባቸው ሀገሮች መንግስታት ጋር የኢትዮጵያ ሰራተኞችን የስራ ሁኔታ ለማሻሻል እና የጥቃት ሰለባ የሚሆኑትን ዜጎቹን ደህንነት ለመጠበቅ ሲል ብዙ ርቀት ያልተጓዘ እና ገና በጅምር ላይ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ፈቃድ ያላቸው የሰራተኛ ቀጣሪ ኤጀንሲዎች የሰራተኞች የውል/ኮንትራት ስምምነት ቢቋረጥ ለመያዣነት በሚል ከሰራተኞች እየተቆረጠ ገንዘብ በባንክ እንዲቀመጥ የሚደረግ ቢሆንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህንን የተከማቸውን ገንዘብ የጥቃት ሰለባ ሆነው ወደ ሀገራቸው ወደ ኢትዮጵያ በሚመለሱበት ጊዜ ለእነዚህ የጥቃት ሰለባ ለሆኑት ሰራተኞች ምንም ዓይነት የትራንስፖርት መጓጓዣ አይከፍልም፡፡“

ሆኖም ግን የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ሌሎች የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎችን ከአደጋ ለመከላከል ሲታትር ይታያል፡፡ ለምሳሌ ያህልም እንዲህ የሚለውን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽንን ዘገባ ማየቱ ለዚህ ታላቅ ማስረጃ ነው፣ “እ.ኤ.አ በ2010 ኢትዮጵያ በሲናይ በረሀ በራሻዳ የኮንትሮባንድ ህገወጦች የሚዘረፉትን፣ የሚሰቃዩትን፣ በግዴታ በግንባታ ስራ ላይ እየተመደቡ ጉልበታቸውን የሚበዘበዙትን እንደዚሁም ደግሞ ከብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ፕሮግራም ጋር በተያያዘ መልኩ ከኤርትራ እየኮበለሉ ወደ ጎረቤት ሀገር የሚሰደዱትን የኤርትራ ዜጎች እና ከግብጽ ለተጋዙት 1,383 የኤርትራ ስደተኞች ጥገኝነት ሰጥታለች፡፡“ እንደዚህ ዓይነቱ ከህገወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ መልኩ የጥቃት ሰለባ ለሚሆኑት እና የሰብአዊ መብታቸውን ተነፍገው ለሚሰቃዩት ዜጎች ከለላ መሆን እና መጠለያ መስጠት ከመልካም ስራ እና ከሞራል ስብዕና አንጻር በጎ ምግባር ቢሆንም ቅሉ ደግነት ከቤት መጀመር እንዳለበትም እውነት ነው፡፡

ለችግሩ መፍትሄ ለመፈለግ ቃል የተገባው .. 2013 ነበር፡፡

እ.ኤ.አ. ጥቅምት 2013 የኢትዮጵያ የቤት ሰራተኞች እና ጥገኝነት የጠየቁ ወገኖች በሳውዲ አረቢያ ስቃይ እና መከራን እየተቀበሉ በነበረበት ወቅት አድኃኖም እንዲህ ብሎ ነበር፡ “በእርግጥ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ችግር ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ እና መፍትሄ ለመስጠት የአጭር እና የረዥም ጊዜ ዕቅድ በመንደፍ ያላሰለሰ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ እናም እንደምታውቁት ሁሉ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ መሻሻል እያሳየች እና ባለሁለት አሀዝ ዕድገት (ይህንን ባለሁለት አሀዝ የምጣኔ ሀብት ዕድገት እየተባለ በየዕለቱ የሚደሰኮርለትን ተራ ፕሮፓጋንዳ ተጨባጭ መረጃ በማቅረብ በማጋለጥ ከምንም ጥርጣሬ በላይ ቅጥፈት፣ ነጭ ውሸት እና የቁጥር ጨዋታ ነው በማለት ቀደም ሲል ማስተባበሌን ልብ ይሏል) እያስመዘገበች ነው፡፡ ከዋሻው መጨረሻ ብርሀን ይታያል፣ እናም ማድረግ እንደምንችል እናውቃለን፡፡ ድህነትን ማጥፋት እንደምንችል እናውቃለን፡፡ ጉዟችን በትክክለኛው ጎዳና ላይ ነው፡፡ ሆኖም ግን እስከ አሁንም ድረስ በዓለም አቀፋዊ ትብብር ማመን አለብን፡፡ ቢሆንም ግን እንደዚህ ያለ ሁኔታ ይፈጸማል ብለን አልጠረጠርንም፡፡“ አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

አድኃኖም ከተናገራቸው ንግግሮች ውስጥ በኢትዮጵያ ስደተኞች ላይ በሳውዲ አረቢያ “እንደዚህ ያለ ሁኔታ ይፈጸማል ብለን አልጠረጠርንም ነበር” ወይም ደግሞ ለእርሱ ሁሉም ነገር “ፍጹም አስገራሚ ነበር“ በሚሉት አባባሎች ላይ ለማመን እስከ አሁንም ድረስ ይከብደኛል፡፡ በእርግጥ በዚያን ወቅት አዘጋጅቸው በነበረው ትችቴ ላይ በግልጽ እንዳስቀመጥኩት ሁሉም ነገር “ፍጹም አስገራሚ ነበር“ የሚለው አባባል ለሁሉም አስገራሚ ሊሆን እንደማይችል አስገንዝቤ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ጥቅምት 2013 ኢትዮጵያውያን በሳውዲ አረቢያ እንደዚያ ያለ የሰብአዊ ቀውስ አደጋ ይድረስባቸዋል በማለት አድኃኖም የወደፊቱን በትክክል ይተነብያል ለማለት የሚያስደፍር ምንም ዓይነት ተጨባጭ ሁኔታ የለም፡፡

ያም ሆነ ይህ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን እየተው በገፍ ወደ ሌሎች ሀገሮች የሚጎርፉበትን ጉዳይ እና እንደ ጥገኝነት ጠያቂነታቻው በሄዱባቸው ሀገሮች ሁሉ መብቶቻቸው ተጠብቀው እና የሰራተኞች የውል/ኮንትራት ስምምነትም በተለይም ደግሞ በመካከለኛው ምስራቅ በሚደረጉት ላይ መፍትሄ ለማምጣት አድኃኖም “ለብዙ ጊዜ ስንሰራው የቆየነው የአጭር እና የረዥም ጊዜ ዕቅድ መፍትሄ” እያለ የሚጠራው ምን እንደሆነ ለማወቅ በመጠባበቅ ላይ ነኝ፡፡

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2015 ሆነን የተባለውን እና ቃል የተገባለትን ነገር ሁሉ ስንቃኘው ምንም የተለወጠ ነገር የለም፡፡ ወጣት ኢትዮጵያውያን/ት ወንዶች እና ሴቶች እግሮቻቸው ወደመሯቸው በመጓዝ ላይ ናቸው (በእጆቻቸው ሊመሩ ባለመቻላቸው፡፡) በመካከለኛው ምስራቅ ለመናገር በሚያዳግት ሁኔታ የጥቃት ሰለባ የመሆናቸው ጉዳይ ቀጥሎ ይገኛል፡፡ እነዚህ ወገኖቻችን ድብደባ ይፈጸምባቸዋል፣ ይሰቃያሉ፣ በረሀብ እንዲጠቁ ይደረጋሉ፣ ይሰቀላሉ፣ አሁን ደግሞ አንገታቸውን ይቀላሉ፡፡

እነዚህ ወንጀሎች አድኃኖም “ለብዙ ጊዜ ስንሰራው የቆየነው የአጭር እና የረዥም ጊዜ ዕቅድ መፍትሄ” በአገዛዙ በኩል በመደረግ ላይ ነው ብሎ በድፍረት ከተናገረ ከሁለት ድፍን ዓመታት በኋላም ሁኔታዎች ሁሉ ይዘታቸውን፣ የመፈጸም የጊዜ ፍጥነታቸውን እና መጠናቸውን በመጨመር በተጠናከረ መልኩ በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም የአድኃኖምን እና የኃይለማርያምን ተወዳጅ ሀረጎች በመዋስ በመካከለኛው ምስራቅ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያውያን/ት ላይ “የዘር አደን/race hunted” እና “የኃይማኖት አደን/religious hunted” ይፈጸማል ልበል ይሆን! እነዚህን ወገኖቻችንን ለመርዳት እና ለመናገር ከሚዘገንኑ ወንጀሎች ለመጠበቅ እስከ አሁን ድረስ ምንም ዓይነት ነገር አልተሰራም!

እንደ አካደሚክ፣ የህግ እና የሰብአዊ መብት ጥበቃ ወትዋች ባለሙያ ኢትዮጵያውያን/ት በአሸባሪዎች፣ በወሮበሎች፣ በዘራፊዎች እና ሰብአዊ መብታቸውን በሚደፈጥጡ የሰራተኛ ቀጣሪዎች የጥቃት ሰለባ መሆናቸው ብቻ ላይ አይደለም ብዙ መሰራት ያለበት፡፡ ሆኖም ግን በህግ ጥላ ከለላ ስም ህጉን እየጣሱ እና እየደረመሱ ከህግ ውጭ እየተራመዱ በወገኖቻችን መብቶች እና ህይወት ላይ ቁማር በሚጫወቱ ኃላፊ ተብዬዎች ላይ ነው ብዙ ነገር መሰራት ያለበት፡፡ ለምንድን ነው በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያውያን/ት ጥገኝነት ጠያቂዎች እና በሀገር ውስጥ መብታቸውን ለሚያጡ ሰራተኞች መፍትሄ ሊፈልግ የሚችል ቋሚ እና ልዩ ግብረ ኃይል የማይቋቋመው? ለምንድን ነው የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች ዜጎች ወደ ውጭ እንዳይሰደዱ የማይከላከሉት እና ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚመለሱት ስደተኛ እና ጥገኝነት ጠያቂ ወገኖቻችን በሀገራቸው ላይ ስራ አግኝተው በሰላም እንዲኖሩ የማያግዙት? ለመሆኑ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ስለኢትዮጵያውያን/ት ጥገኝነት ጠያቂዎች፣ የኮንትራት ሰራተኞች እና ሌሎች ምንም ዓይነት ጥሩ አያያዝ ለማይደረግላቸው፣ ሰብአዊ መብቶቻቸው ለሚደፈጠጡባቸው እና ለሚሰቃዩት ወገኖቻችን ደንታ አለውን? እንዴት ሆኖ! (በእርግጥ ይኸ የድስኩር እንጅ የተግባር ጥያቄ አይደለም፡፡)

ኢትዮጵያውያንን/ትን በሳውዲ አረቢያው እንደደረሰው ያለ ቀውስ በሚያጋጥምበት ጊዜ ለዜጎቹ የሚያስብ ማንም አገዛዝ ቢሆን የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ ኃይል በማቋቋም በተቀነባበረ መልኩ እገዛ እያደረገ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን እየቀረበ እርዳታ እና ድጋፍ ማሰባሰብ ይኖርበታል፡፡ (ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን እየቀረበ ስል ከእነርሱ ገንዘብን እየለመነ ወደ ኪሱ ያጭቅ ማለቴ እንዳልሆነ ልብ ይባልልኝ፡፡) አድኃኖም እና አገዛዙ በመካከለኛው ምስራቅ እና በሌሎች ሀገሮች በኢትዮጵያውያን/ት የቤት ሰራተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ የደረሰው የአደጋ ሁኔታ ሲያልፍ የትርፍ ስሌታቸውን በመስራት እንደተለመደው የንግድ ጥባ ጥቤ የቁማር ጨዋታቸውን ይቀጥላሉ፡፡

ስለሆነም እነዚህን ሊመለሱ የማይችሉ ጥያቄዎችን ለእራሴ በመጠየቅ እንዲህ የሚሉትን የብቸኝነት የግጥም ስንኞችን እነሆ… 

ምንድን ነው ነገሩ? 

ምንድን ነው ነገሩ እስቲ ተናገሩ፣

ከቶ ምንድን ይሆን ይህ ሁሉ እሽሩሩ፣

ዕልቂት ዕጣ ፈንታ የሆነ ተግባሩ፣

ሰው መኖር አይችልም በገዛ ሀገሩ?

 

የኢትዮጵያውያን ነብስ እንዴት ረከሰ፣

በሊቢያ በሳውዲ ደም እየታፈሰ፣

በሲናይ በረሀ አሸዋ እየላሰ፣

ባሸባሪ ቡድን ሰው እየታመሰ፣

ደሙ ተግተልትሎ እንባውም ፈሰሰ፡፡

በሰይጣን ምግባራት ወገን ተላቀሰ፡፡

 

ጉልበቴን መንዝሬ ልኑር ልስራ ባለ፣

ለሌላው ሰው ድሎት ጉልበቱን ባዋለ፣

ከሀገር ተሰዶ በተንቀዋለለ ነብሱን ባቃጠለ፣

ከሰማይ ጠቀስ ፎቅ ተገፍቶ ተጣለ?

በጥይት እሩምታ በግፍ ተገደለ?

 

ስራ ልስራ ብሎ ካገር በነጎደ፣

ለህይወት መሻሻል ሀሳብ ባራመደ፣

እንደ ፋሲካ በግ በካራ ታረደ?

 

ለመስራት አቅዶ ከሄደ በኋላ፣

ለደኃ ወገኑ ሊሆን ጋሻ ባላ፣

ችጋርን በማጥፋት በጥረት በመላ፣

ሊመለስ ላገሩ ነገሩ ሲብላላ፣

እንደ ሀገር ጠላት በጥይት ተቆላ?

 

ሀገር እንደሌለው እንደ ባዕዳ ሰው፣

ከሀገር ተገፍቶ ሀገር እያለው፣

መኖር አልችል ያለ መብት የሌለው፣

በበረሀ ቀልጦ ጫካ የቀረው፣

የአራዊት መፈንጫ ነብሱ የሆነው፣

በባዕድ ሀገር ባከኖ ውኃ የበላው፣

እሱን ማን ልበለው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡

 

አንች የሀገር ቆንጆ ተስፋው የራቀሽ፣

በሀገርሽ መኖር ፍጹም ተስኖሽ፣

በባዕድ ሀገር ሆነሽ ኑሮን የቀመስሽ፣

ከስብዕና በታች ሆኖ ህይወትሽ፣

ያልፍልኛል ብለሽ ውጥንቅጥ ኑሮሽ፣

ዘመድ ወገኖችሽ እንደናፈቁሽ፣

በሰው ሀገር ሄደሽ ባክነሽ የቀረሽ፣

ሀዘናችን ከፍቷል እስቲ ተመለሽ፡፡

 

አዕምሮ የሰጠን ለማመዛዘን ነው፣

ደግ እና ክፉውን ለማነጻጸር ነው፣

ግና ምን ያደርጋል ሁሉ አይተገብረው፣

ወያኔ ያዋለው ተንኮል ለማድራት ነው፣

ህዝብን ከህዝብ ጋር ለማተራመስ ነው፡፡

 

የኢትዮጵያውያን ደም ቢፈስ ቢንዠቀዠቅ፣

በጥይት ቢቆላ በገመድ ቢታነቅ፣

ቢጣል በውቅያኖስ በወንዝ እና በሐይቅ፣

ወያኔ ከጥቅሙ መች ይል እና ንቅንቅ፡፡

 

ምንድን ነው ነገሩ እስቲ ተናገሩ?

ማንንም ሳትፈሩ ሳትደናገሩ፣

አንድም ነገር የለ በባህር ባየሩ፣

በየብስ በጫካው ባፈሩ በዱሩ፣

የኢትዮጵያ ደም ነው ዶፉ ውሽንፍሩ ፡፡

 

ምንም የሚያሳስብ የለም አንድ ነገር፣

በባህር በወንዙ ባየሩም በምድር፣

በሰማይ በጫካ በሐይቁ በባህር፡፡

 

በመሬት ቢዞሩ ባየር ላይ ቢበሩ፣

የማያሳስበው ምንድን ነው ነገሩ?

የኢትዮጵያ ደም ነው ጎርፉ ስንክሳሩ?

የወጣቶቸ  ደም ነው ዘዋሪው አኪሩ?

 

ያሳስባል እንጅ በውንም በህልምም፣

በግፈኞች ድርጊት ህይወት ስትጨልም፣

ራዕይ ሲኮላሽ ሃሳቦች ሲመክኑም፣

ጭራቃዊ ድርጊት ባለም ሲለመልም፡፡

 

ምንድን ያሳስባል በዚህች ምድር ላይ?

ደኃውን ሀብታሙን ሁሉንም ስናይ፣

ሀቀኛ ሲያዳምጥ ሲናገር አባይ፣

ዓለም ስትናውዝ በሌት በጸሐይ፡፡

 

የኢትየጵያውያን ህይወት ያሳስባል፣

ሁሉም የሰው ልጆች ህይወት ያሳስባል!

 

እውነት ተናገሩ ምንድን ነው ነገሩ?

እስቲማ ንገሩኝ ምንድን ነው ነገሩ?

ወገኖቼ አኩርፈው ጠፍተዋል ካገሩ፣

የእውነትን መድኃኒት ሄደው ሊቀምሩ፣

ተመልሰው መጥተው ሀገርን ሊያኮሩ፡፡

 

ወያኔ ጨካኝ ነው የሞራል ኪሳራ፣

እሱ በመደንገጥ ህዝብን የሚያስፈራ፣

ቀኙን ያዘው ሲሉት የሚመርጥ ግራ፣

ብዕርን ሲያሳዩት የሚመዝ ካራ፣

ጣፋጩን ሲያሳዩት የሚመኝ መራራ፣

የጽድቅ በር ትቶ ጋነም የሚያጓራ፡፡

 

አሸባሪ አውሬነት ስብዕና የሌለው፣

ኃላፊነት የለሽ ምግባር የጎደለው፣

የደቡብ አፍሪካው ወሮበላው ሌባው፣

የሊቢያው አጋንንት በደም ላይ የዋኘው

የሳውዲው መናጢ ውቃቢ የራቀው፣

እንዴት ሆኖ ይሆን ከህሊና እሚያድረው?

 

የዲያስፖራው አቅምየለሽነት፣

በኢትዮጵያዊነት ትብበር እጦት፣

በሰው ልጆች ጭራቅነት፣

በሰው ልጆች ኢሰብአዊነት፣

ይንጸባረቃል በዋናነት፣

ሁሌም ያሳስባል የኢትዮጵያዊ ህይወት፡፡

 

ወያኔ ወገኑን ኬሬዳሽ ብሎታል፣

ቢፈለጥ ቢቆረጥ ዓይኑን ሸፍኖታል፣

ቢሰደድ ቢሰቀል አላይም ብሎታል፣

የኢትዮጵያውያን ህይወት አልሰምር ብሎታል፡፡

 

ለምንወዳት ሀገራችን ለኢትዮጵያችን እጮሃለሁ፣ ሆኖም ግን ከዋሻው መጨረሻ ብርሀን አለ

የኢትዮጵያ የቤት ሰራተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች በሳውዲ አረቢያ ስቃይ እና መከራ እየደረሰባቸው በነበረበት ጊዜ አድኃኖም እንዲህ ብሎ ነበር፣ “ከዋሻው መጨረሻ ብርሀን አለ፣ እናም ድህነትን ማጥፋት እንደምንችል እንደምናጠፋ እናውቃለን፡፡“

እኔም እንደዚሁ በኢትዮጵያ በስልጣን እርካብ ላይ ከህዝብ ፈቃድ ውጭ ተፈናጥጠው ከሚገኙት ጨካኞች እና አምባገነኖች መጨረሻ ብርሀን አለ እላለሁ፡፡ ከአድማሱ ባሻገር አዲስ ቀን አለ፡፡ አንድ መሆን አለብን፣ ክርስቲያን እና ሙስሊም ሳንል ሁላችንም በሀገሪቱ ውስጥ ያለን ሁላችንም ኢትዮጵያውያን/ት ሁሉ እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድነት መጓዝ አለብን፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዘን በዋሻው ውስጥ በቀጥታ በመጓዝ ለሁለት አስርት ዓመታት እና ከዚያ በላይ በጭቆና እና መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶችን ተነጥቀን ከቆየንበት ዋሻ ውስጥ በጥሰን እና በጣጥሰን በድል አድራጊነት ብርሀን ከሚታይበት ጫፍ ብቅ ማለት አለብን፡፡

እውነታውን መናገር አለብኝ፡፡ በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ተስፋ እቆርጣለሁ፣ እናም ለምንወዳት ኢትዮጵያችን አለቅሳለሁ፡፡ ይህንን በጽናት አደርጋለሁ፡፡ ምን ያህል እንደማደርግ ብታውቁልኝ? እ.ኤ.አ. በ1948 በዚያው ዓመት አፓርታይድ በደቡብ አፍሪካ እራሱ ህግ መሆኑን በማስመልከት አላን ፓቶን እንዲህ በማለት ጻፉ፣ “ለውዲቷ ሀገራችን እንጩህ“ በማለት በደቡብ አፍሪካ ዕጣ ፈንታ ላይ ጥልቅ የሆነ የተስፋ ማጣት ስሜታቸውን ገልጸው ነበር፡፡ የእኔ የግሌ በኢትዮጵያ ላይ ተስፋ የማጣት ስሜቴ ከፓቶን ስሜት ጋር ጎን ለጎን በመሄድ እንዲህ በማለት ያስተጋባል፡

…የኮሶ መታሪ እንደገባው የኮሶ ትል ስለተበጣጠሰው የጎሳ ክፍፍል፣ መቅኖውን ስላጣው የህግ ስርዓት እና እንደ አሮጌ ቁና ወደ ጎን ስለተሽቀነጠረው ብርቅዬ ባህላችን እና ልማዳችን እጮሀለሁ፡፡ አዎ፣ ስለሞተው ወንድ፣ ስለሞተችዋ ሴት እና በሞት ስለተነጠቁት ልጆች እጮሀለሁ፡፡ ስለውዲቱ ሀገሬ እጮሃለሁ፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ በመጨረሻው የውድቀት ምዕራፍ ላይ አይደሉም፡፡ ጸሐይ ሁሉም ሰው ተደስቶ ሊኖርባት ባልቻለባት በመሬት ላይ መሀለቋን ላይ ትጥላለች፡፡ ሰው የሚያውቀው የልቡን ፍርሀት ብቻ ነው፡፡

እኔም እንደ ፓቶን ሁሉ በኢትዮጵያ የጎሳ ክልል እየተባሉ ተበጣጥሰው ላሉት ጎሳዎች እጮሀለሁ፡፡

ለዚህ መቅኖውን አጥቶ ለበከተው እና ለተዋረደው የፍትህ ስርዓት እና እንደ አሮጌ ቁና ለተሽቀነጠረው አኩሪ ባህላችን እና ልማዳችን ድምጼን ከፍ አድርጌ እጮሀለሁ፡፡ ጨርቅ ነው እያሉ በአደባባይ ላዋረዱት ለኢትዮጵያ ባንዲራ ድምጼን ከፍ አድርጌ እጮሀለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ የመቶ ዓመት እድሜ ብቻ ነው በማለት በድንቁርናቸው ለገደቡት እና በህዝብ በተሳለቁት ደምጼን ጮክ አድርጌ እጮሀለሁ፡፡ ኢትዮጵያ የ100 ዓመት ገደማ ያህል ህልውና ያላት ሀገር ናት ብለው ለተዘባበቱት ድምጼን ከፍ አድርጌ እጮሀላሁ፡፡

ለወንዞች እና ድምጻቸው ለተገደበው ድምጽ የለሾች ድምጼን ከፍ በማድረግ እጮሀለሁ፡፡ ለተራሮች፣ ለሸለቆዎች እና ለበረሀዎች ድምጼን ከፍ በማድረግ እጮሀለሁ፡፡ ወርቋን እና የከርሰ ምድር ማዕድኗን ተነጥቃ ለምትደማው ሀገሬ ድምጼን ከፍ በማድረግ እጮሀለሁ፡፡

በጭራቃዊ አሸባሪ ቡድን አንገታቸውን እየተቀሉ በግፍ እንዲያልቁ ለተደረጉት ለ30 የኢትዮጵያ ወጣት ክርስቲያን ወንዶች ወገኖቼ ድምጼን ከፍ በማድረግ እጮሀለሁ፡፡ ለእነዚህ ወጣቶች አባቶች እናቶች፣ ለእህቶቻቸው እና ለወንድሞቻቸው ለአጎቶቻቸው እና ለአክስቶቻቸው እንዲሁም ለአያቶቻቸው ድምጼን ከፍ በማድረግ እጮሀለሁ፡፡ ለጓደኞቻቸው እና ለጎረቤቶቻቸው፣ ለከተሞቻቸው እና ለመናገሻ መዲናቸው ድምጼን ከፍ በማድረግ እጨሀለሁ፡፡ ለውዲቱ ሀገራቸው እና ለኢትዮጵያ አለቅሳለሁ፡፡ እነዚህ ነገሮች እስከመጨረሻው ለመውደም በመጨረሻው እረድፍ ላይ አይደሉም፡፡ ጸሐይ በአሁኑ ጊዜ በጣም ጥቂቶች ብቻ እየተደሰቱ በሚኖሩባት መሬት ላይ ለ13 ወራት ያህል የሚዘልቀውን መሀለቋን በኢትዮጵያ ምድር ላይ ትጥላለች፡፡ ፍርሀታቸውን በልባቸው ውስጥ ብቻ ለሚያውቁት ወገኖቼ ድምጼን ከፍ በማድረግ እጮሀለሁ፡፡ የወገኖቼን ስቃይ እና መከራ እንዲሁም የሚደርስባቸውን መንገላታት እና መሪር ሀዘን ሁሉ እጋራለሁ፡፡

እንደ በግ ጠቦት ጸጥ ያሉትን እና በሊቢያ አረመኔ ጨካኝ እና ገዳይ ወሮበሎች ለታረዱት ወጣት ወንድሞቼ ድምጼን ከፍ በማድረግ እጮሀለሁ፡፡ ከእግዚአብሔር በቀር ምንም ዓይነት ሊረዳቸው የሚችል ኃይል በሌለበት በሊቢያ ምድር ላይ በወጥመድ ውስጥ ተይዘው በመቁለጭለጭ ላይ ላሉት ወገኖቼ ድምጼን ከፍ በማድረግ እጮሀለሁ፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ አስገድዶ መድፈር በሚፈጸምባቸው፣ በሚደበደቡት እና ከታላቅ ህንጻ ላይ በመስኮት እየተወረወሩ ለሚሞቱት፣ ከጣራ እና ከዛፍ ላይ ለሚሰቀሉት፣ የፈላ ውኃ በላያቸው ላይ ለሚደፋባቸው ወጣት እህቶቻችን ድምጻችንን ከፍ አድርገን እንጮሀለን፡፡ ተወልደው ያደጉበትን እና እትብታቸው የተቀበረበትን ሀገራቸውን በግዳጅ እንዲለቁ እና ለስደት በመዳረግ ነጻነት እንዳይሰማቸው፣ መብት ያላቸው ለመሆናቸው ምንም ዓይነት ስሜት እንዳይኖራቸው በገዛ ሀገራቸው ምንም ዓይነት የሰብአዊ ፍጡር ስሜትነት እንዳይሰማቸው በማድረግ ለከፍተኛ አደጋ እንዲጋለጡ ለሚደረጉ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች ድምጼን ከፍ በማድረግ እጮሀለሁ፡፡ በገዛ ሀገራቸው 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ዜግነት እንዳለ ያውቃሉ፡፡ ኑሯቸውን እና ህይወታቸውን ለማሻሻል በማሰብ የየመንን፣ የሊቢያን እና የሳውዲ አረቢያን በረሀዎች ሲያቋርጡ በሞት ለተነጠቁት እና አሁንም በመሞት ላይ ለሚገኙት ኢትዮጵያውያን/ት ወገኖች ድምጻችንን ከፍ በማድረግ እንጮሀለን፡፡ እ.ኤ.አ የ2005 ሀገር አቀፍ ምርጫ ከተጠናቀቀ በኋላ በመለስ ዜናዊ እና በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ጭካኔ እና አረመኒያዊነትን በተላበሰ መልኩ   በአዲስ አበባ መንገዶች በጠራራ ጸሐይ በአደባባይ ህይወታቸውን ላጡ ወጣት ወንዶች፣ ወጣት ሴቶች፣ አባቶች እና አባቶች ድምጼን ከፍ በማድረግ እጮሀለሁ፡፡

ለእህቴ ለርዕዮት ዓለሙ፣ ለወንድሞቼ ለእስክንድር ነጋ፣ ለአንዷለም አራጌ፣ ለውብሸት ታዬ፣ ለበቀለ ገርባ፣ ለአቡባከር አህመድ እና ለሌሎችም በሺዎች ለሚቆጠሩት ለኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች ሁሉ ድምጼን ከፍ በማድረግ እጮሀለሁ፡፡ ለኢትዮጵያውያን እና ለኢትዮጵያ ድምጼን ከፍ በማድረግ እጮለሁ፡፡

ተስፋ በማጣት በማሰማው ጩኸት እንዲህ የሚሉትን የሸክስፒርን የግጥም ስንኞች አረፍ በማለት አንጸባርቃለሁ፡

ዕድል እጣ ፈንታ በጨለመ ጊዜ፣

አላንቀሳቅስ ሲል የያዘን አባዜ፣

ከወንዶች ዓይን ላይ በተነነ ጊዜ፣

ሁሉም አይሳካም አይኖርም ኑዛዜ፡፡

 

በተተፋው መንግስት ሁልጊዜ እጮሀለሁ፣

ግራ ተጋብቼ ቀኙን አጥቻለሁ፣

ወደላይ ከመሄድ ቁልቁል እወርዳለሁ፣

አንድነቱን ትቼ ነጠላ ሆኛለሁ፣

ፍቅርን በመተው ጥላቻን ይዣለሁ፣

በህይወት ከመኖር ሞትን መርጫለሁ፣

በሀገር ከመኖር ባድን አምልኪያለሁ፣

ዘረኛን ከማጥፋት ሀሜት ለምጃለሁ፣

በዚሁ ከቀጠልኩ ጋነም እገባለሁ፡፡

 

የጻዲቁን መንገድ ተረተሩን ስቼ፣

እውነትን በመፍራት ለሀሰት ሞግቼ፣

ቀረሁ ባደባባይ ለፍቼ ለፍቼ፣

ባልተሳካው ጩኸት ከጋነም ገብቼ፡፡

 

ጆሮው በማይሰማ በዲያብሎሱ ቤት፣

በጠራራ ጸሐይ ስመላለስበት፣

እዩኝ ተመልከቱኝ ለዚህ ብኩንነት፣

ወገን አንድ በሉ ወገን ላለቀበት፡፡

 

ቃል ኪዳን ግቡልኝ ለመልካም ዕድል፣

ፈዋሽ አቅርቡልኝ አምጡልኝ ጸበል፣

አማልዱኝ ካምላኬ ከኃያሉ ገድል፣

ተስፋዬ ለምልሞ እንድኖር በድል…

አዎ፣ ደግሜ ደጋግሜ በመጮህ ይህንን የማይሰማ መንግስተ ሰማያት ስኬታማ ባልሆኑት ጩኸቶቼ መግቢያ ቀዳዳ በማሳጣት አስቸግረዋለሁ፡፡ አዎ፣ በእኔ ተስፋ መቁረጥ አንድ ተጨማሪ ተስፋ እቋጥራለሁ፡፡ ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከወሮበሎች አገዛዝ ነጻ ትሆናለች፡፡ ህዝቧ የእነዚህን የአጭበርባሪዎች እና ሸፍጠኞችን ተንኮል በመገንዘብ በአንድ ላይ እጅ ለእጅ በመያያዝ አንድ ላይ ሆኖ በመቻቻል፣ በስምምነት እና በፍቅር ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን እንደሚገነባ ሙሉ ተስፋ አለኝ፡፡ ተስፋ አደርጋለሁ ምክንያቱም ተስፋየለሽነትን አስወግጃለሁ፡፡

ለውዲቷ ሀገራችን እጮሃለሁ፡፡ በደስታ እና በተስፋ እጮሀለሁ፡፡ ጩኸታችን ይሰማል የሚል ቃል ኪዳን እገባለሁ፡፡ ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ የጭካኔ አምባገነናዊ የዘረኝነት አገዛዝ ዋሻ ውስጥ አልወጣችምን? ማንዴላ እንዲህ ሲሉ አንድ ሌላ ተጨማሪ ተስፋን አልሰነቁምን?፡ “በፍጹም በፍጹም ከእንግዲህ ወዲያ በዚህ ቆንጆ መሬት አንዱ በአንዱ ላይ የሚጨቆንበት እና የሚሰቃይበት የተዋረደች ዓለም አትኖርም፡፡“

በፍጹም አትጠራጠሩ፡፡ እኔ የበለጠ በተስፋ የተሞላሁ፣ ከምንጊዜውም በላይ በደስታ የፈነጠዝሁ እንደሆንኩ እዘልቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያውያን/ት በቅርብ ጊዜ ውስጥ የነበራቸውን ክብር እና ሞገስ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ እንደገና እንደሚቀዳጁ ምንም ዓይነት ጥርጥር የለኝም፡፡

ኢትዮጵያውያን/ት በክልል አገዛዝ እንደ ደቡብ አፍሪካውያን የአፓርታይድ የዘረኝነት አገዛዝ የዓለም የውርደት ቋት ውስጥ በፍጹም አትገባም፣ እናም ይህንን ከልብ በሆነ መልኩ አምናለሁ፡፡ ኢትዮጵያ እጆቿን በቅርብ ጊዜ ውሰጥ ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች፣ እናም በደስታ ምንም ዓይነት ጩኸት እና ጫጫታ ሳይኖር በደስታ እና በፈንጠዝያ እንኖራለን የሚል እምነት አለኝ!

የማየሳነው እና ዘላለማዊው አምላክ እግዚአብሔር በሊቢያ የወደቁትን የወንድሞቻችንን እና የልጆቻችንን ነብስ ይማርልን፣ በገነት ያኑርልን!

አላህ ምህረት ሰጭው እና መልካም አድራጊው ለእኛ ወንድሞች እና ልጆች ምንም ዓይነት ምህረት ላላደረጉት ወገኖች ምህረቱን እና ጽናቱን ስጣቸው!

ተከብረሽ የኖርሽው ባባቶቻችን ደም
እናት ኢትዮጵያያ ያስደፈረሽ ይውደም!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ሚያዝያ 26 ቀን 2007 .