ኢትዮጵያ፤ ወደ ዴሞክራሲ የመጓዣው ጎዳና ካርታ ላይ
ባለፈው ሳምንት በሲያትል ከተማ የኢትዮጵያን ራዕይ በተመለከተ ሰፊ ሕዝባዊ ውይይት፤ ክርክር፤ ለማካሄድ በተመሰረተ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ፎረም ላይ (EPFS)ላይ ተጋብዤ ተገኝቼ ነበር:: በዚህምስብሰባ ላይ በቅርቡ ሳቀርባቸው በነበሩት የኢትዮጵያን ከፈላጭ ቆራጭ ግዛት ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ሽግግርን በተመለከተ ማብራሪያ እንድሰጥ ተጠይቄ ነበር፡፡ እኔ በኢትዮጵያ ከፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ሊካሄድ ስለሚገባው የሽግግር ሁኔታ የማቀርባቸው ሃሳቦች፤ በሃገራችን በመካሄድ ላይ ያለውን ጭካኔ የተመላበት አገዛዝ፤የሰብአዊ መብት ረገጣ፤የፍትሕ እጦት፤ እስራትና ወከባን በተመለከተ ካለኝ ወገናዊነት የተነሳ የተፈጠረብኝ የግል አመለካከቴ ነው፡፡