ሀገሬ፣ ህዝቤ፣ ክብሬ…
እጅግ በጣም የተለዬ ችሎታ ያላት ወጣት ኢትዮጵያዊት የኪነ ጥበብ ባለሙያ የሆነችው ሜሮን ጌትነት ባለፈው ሳምንት “ሀገሬ፣ ህዝቤ፣ ክብሬ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጠንካራ የሆነ የአማርኛ ግጥም በዩቱቢ ድረ ገጽ በመልቀቅ እንዲነበብ አድርጋለች፡፡ ሜሮንን ለመጨረሻ ጊዜ “ያየኋት” በዚህ አሁን በያዝነው ዓመት መስከረም ወር በአንዲት ኢትዮጵያዊት ልጃገረድ ላይ በተደረገው የጠለፋ ጋብቻ ወንጀል ላይ ተመስርቶ የተሰራውን ተውኔት (ፊልም) በማስታወቂያነት እንዲያገለግል በቪዲዮ ተቀርጾ የቀረበውን ምስል ባየሁበት ጊዜ ነበር፡፡ በሀገሪቱ በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ የሚገኘው ገዥ አካል ለዚህ ጉዳይ ጆሮ ዳባ ልበስ ስላለ ያ አስቀያሚ የጠለፋ ጋብቻ ወንጀል ድርጊት አሁንም ቢሆን እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ ድፍረት በሚለው ተውኔት ላይ ሜሮን የማትበገር የህግ ባለሙያ ገጸ ባህሪን በመላበስ ወሳኝ ሚናን በመጫወት የጥቃቱ ሰለባ ለሆነችው ልጃገረድ ነጻነት ብቻ ሳይሆን እርሷ እንደሴትነቷ የራሷን እና የሌሎችን ሴቶች ክብር ለማስጠበቅ ስኬታማ የሆነ ተውኔት ሰርታለች፡፡