እ.ኤ.አ በ2008 አቶ መለስ ዜናዊ ከሱዳን ጋር የተደረገውን “ስምምነት” አስመልክቶ በውሸት ባህር ውስጥ እየተንቦጫረቁ የጭቃ ጅራፋቸውን ማጮህ ጀመሩ፡፡ በዚያው ዓመት በግንቦት ወር ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ሙልጭ አድርጎ በመካድ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድም ጋት የሚሆን የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት የተደረገ ሰምምነት የለም የሚል መግለጫ ሰጠ፡፡ ያ መግለጫ በውጭ የሚገኙትን “የዜና አውታሮች” እና “ኃላፊነት የማይሰማቸው” በበሬ ወለደ የፈጠራ ወሬ የተሰማሩ ሽብር እና ፍርሀትን በህብረተሰቡ ዘንድ የሚነዙ አሸባሪዎች ናቸው በማለት ከሷቸው ነበር፡፡ የሱዳን ባለስልጣኖች ግን ያንን መግለጫ በሚጻረር መልኩ “ከኢትዮጵያ መሬት እንዳገኙ“ በይፋ በአደባባይ ተናግረዋል፡፡ በግንቦት አጋማሽ አቶ መለስ እና አጫፋሪዎቻቸው የመሬት ማደሉን ሚስጥር ደብቀው ማቆየት ባለመቻላቸው ወደ ቀድሞው ታሪካቸው ለመመለስ ተገደዋል፡፡ በድንበር ማካለሉ ወቅት አንዳንድ የቅድመ ስራ እንቅስቃሴዎች ብቻ እንደተከናወኑ፣ እናም የተጠናቀቀ ነገር የለም በማለት በግልጽ ተናግረዋል፡፡ በቀናት ጊዜ ውስጥ አቶ መለስ እና አጫፋሪዎቻቸው ሌላ አዲስ ቅጥፈትን ፈብርከው ብቅ አሉ፡፡ የሆነው “ቀደም ሲል በንጉሱ እና በደርግ ዘመን ከሱዳን ጋር የተደረጉ ስምምነቶችን ተግባራዊ አደረግን” ብለው ጭራ ቀረሽ ዉሸት ፈጠሩ፡፡