ኢትዮጵያ፡- ከረጂም ርቀት ሯጮቻችን የምንማረው
ኢትዮጵያ በመልካም ስሟም፤በአስከፊ ገጽታዋም ትታወቃለች:: ኢትዮጵያ በመልካም እንግዳ ተቀባይነቷና አስተናጋጅነቷ፤በሕዝቦቿ መልካም ባሕሪ፤ በመልክአ ምድሯ ውበት፤እና በግሩሙ ቡናዋና በማይደፈሩት ጅጋኖች ረጂም ርቀት ሯጮቿ ትታወቃለች፡፡ ተወዳዳሪ በሌለው የሰብአዊ መብት ጥሰት፤የፕሬስ ማፈኛ ተቋሟም፤በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፖለቲካ እስረኞች የሚገኙባት ሃገርም ሆና ኢትዮጵያ ትታወቃለች፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ችጋር (ኤክስፐርቶቹ እንደሚሉት፤ “ሥር የሰደደ የማይነቀል የምግብ እጥረት”) ከውቢቷ ኢትዮጵያ ጋር ከተሳሰረ ዘመናት አልፈዋል፡፡ የሆነው ሆኖ አትዮጵያ ከጭቆና የፈላጭ ቆራጭ አስተዳደር ወደ ዴሞክራሲ ጉዞዋን ጀምረለች፤ ወይስ ኢትዮጵያዊያኖች ከአምባገነኖች አገዛዝ ወደ ነጻነት እየሮጡ ነው ብል ይሻላል?