በካምፕ ዴቪድ የአፍሪካ የችጋር ትርኢት
ባለፈው ሳምንት የሁዋይት ሀውስ ቤተ መንግስት ቃል አቀባይ ጄይ ካርኒ ፕሬዜዳንት ኦባማ የጋናን፤ የታንዛንያን፤የበኒን ፕሬዜዳንቶችንና መለስ ዜናዊን የስምንቱን የኤኮኖሚ ሃያላን ሃገሮች (G8) ስብሰባ ላይ በካምፕ ዴቪድ ሜሪላንድ በሜይ 19 ስለ ምግብ ዋስትና በሚካሄደው ውይይት ላይ እንዲገኙ መጋበዛቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ የአሜሪካን መንግሥት ለዘመናት ለአፍሪካ አህጉር የምግብ እርዳት ሲያደርግ መክረሙ ይታወቃል፡፡ አሁንም በድጋሚ አፍሪካን ‹‹የመረረ የችጋር ወቅት›› ገጥሟታል ይላሉ ፕሬዜዳንት ኦባማ፡፡ ኦክስፋም በበኩሉ ከአሁኑ አስፈላጊው ሁሉ ካልተደረገ በስተቀር በመታየት ላይ ያሉ ጠቋሚ ምልክቶች ሁሉ እጅጉን ዘግናኝ የሆነ መአት እንደሚከተል ያሳያሉ ይላል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ድርጅት በበኩሉ ባስተላለፈው የድረሱ ጥሪው፤ በሳሄል ምእራብ አፍሪካ ለ800,000 በችጋሩ ለተጎዱት ረሃብተኞች መርጃ የሚሆን 70 ሚለዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልግ፤አስቀድሞ ማስጠንቀቂያው መተንበዩን መሰረት አድርጎ ኢትዮጵያና ሶማልያ በጉዳቱ ወደ አዘቀዘቀው ደረጃ እንደሚወርዱም ይፋ አድርጓል፡፡ የዝናቡ አናሳ መሆንም አስፈላጊውን ምርት ስለማያስገኝ የግጦሽ መሬትንም መልሶ ስለማያለማው፤በአጠቃላዩ አካባቢም የውሃ እጦት ሌላው ችግር በመሆኑ የደቡብ ኢትዮጵያውን ክፍል በእጅጉ የሚጎዳና ሕዝቡንም ለመረረ ችጋር ከብቱንም ለእልቂት የሚዳርግ ክፉ ቀን እንደሚመጣ ይተመናል:: ይህ ደሞ በገሃድ እየታየ ያለ በመሆኑ አደጋው ከአደጋዎች ሁሉ የባሰ በሆነ መልኩ ነው፡፡ አንባቢዎቼ እንደሚያስታዉሱት ሁሉ ባለፉት ሁለታ ዓመታትና ከዚያም ባለፈ በኢትዮጵያ ስለሚከሰተው ችጋር በርካታ አስተያየቶችን አስመልክቼ ጽፌ ነበር፡፡