በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከአቢይ ጎን መቆም ምርጫ ብቻ ሳይሆን ሁኔታውም ያስገድዳል!
(ከብስራት ኢብሳ፣ ሆላንድ)
አላሰልቻችሁና በተደጋጋሚ እንደተባለው፣ ወቅቱ ከኮረና የወረርሺኝ በሽታ በተጨማሪ የውጭ እና የውስጥ የሀገራችን ጠላቶች ባደባባይ ግንባር ፈጥረው፣ በእቅድ ሕዝባችንን ገለው የተረፈውን እያፈናቀሉ ሽብር በመፍጠር የየራሳቸውን፣ የተለያየ ዓላማን ለማስፈጸም የመጨረሻ ሙከራ ላይ ናቸው፡፡
ወደ 30 ለሚጠጉ ዓመታት በወያኔ ተጀምሮ ሀገሩን የበከለው የከረረ ብሔረተኝነት፣ ሌሎች ተገደውም ሆነ ፈቅደው ፈለጉን ተከተሉት፡፡ ብዙ ምሁራን፣ “ቆመንለታል” ለሚሉት ማኅበረሰብ በተለይ ለወጣቱ የሱን ቋንቋ የማይናገሩትንና በሱ አካባቢ ያልተወለዱትን እንዲጠላ መርዝ ሲግቱና አእምሮዋቸውን ሲመርዙ እንደነበር፣ አሁን ወደ አውሬነት እንዴት እንደ ቀየሯቸው ውጤቱ በገሃድ እየታየ ነው፡፡ ይህ እየተካሄደ ያለው የመጀመርያው መንደርደርያ እንጂ፣ ለባሰው እልቂት እየተቀረቀበልንና እየተሰነቀልን ነው፡፡ የችግሩ ግዝፈት እንኳን ለየብቻ ቆመን በጋራም ቀላል አይሆንም፡፡
ዛሬም “ለየብቻ ሆኖ በብሔር ወይም በአንድ የፖለቲካ ቡድን ዙርያ በመደራጀት፣ እየተካሄደ ያለውን ማኅበራዊ ምስቅልቅል በማስወገድ፣ ሰላም ለሁሉም ሕዝባችን ማምጣት ይቻላል” እያሉን ሕዝባችን አብሮ አደጋውን እንዳይከላከል ተጨማሪ እንቅፋት መሆንን የቀጠሉ አሉ፡፡
በእርግጥ ከነዚህም ውስጥ ሀገራዊ ሃላፊነት የተሰማቸው የተቃዋሚ ድርጅቶች፣ ኢትዮጵያ በዙርያዋ የገጠማትን አሳሳቢ አደጋ አጢነው፣ ከችግር ፈጣሪዎችና አክራሪዎች እራሳቸውን ከማራቅ ጀምሮ እስከ የመፍትሄው አካል እስከመሆን እያሳዩ ያለው ብስለት ማመስገን ሳንዘነጋ፡፡
አንዳንድ የዞረባቸው “የተቃዋሚ ድርጅቶችም ሆኑ ታዋቂ ግለሰቦች”፣ አደጋው እነሱን ጭምር ጠራርጎ ሊሄድ እንደሚችል ያልገባቸው የሚመስሉ፣ ከዚህ ቀውስ የሚያተርፉ እየመሰላቸው፣ እራሳቸውን ጭምር የሚያቃጥል ቤንዚን ላቃጣዮቻቸው ሲያቀብሉ ይታያሉ፡፡
ሌሎችም በተለይ በውጭው አለም ዘና ብለው የግል ሕይወታቸውን እያጣጣሙና በተግባር የማይታይ “የኅብረት ትግል ጥሪ” እያሰሙ፣ መንግሥት አንድ ስህተት እስከሚያደርግ አድብተው ይጠብቁና፣ “ይሄው እኛም ብለን ነበር”፣ “እንደዚህ እንደሚሆን ቀድሞ ውቃቢያችን ነግሮናል…..” እያሉ እየተነፈሱ መኖራቸውን ብቻ ለማስመከር ሁኔታውን ያልገናዘበ ምኞታዊ መግለጫ በየወቅት ከማውጣት ውጪ ምንም ያሳዩን አቅጣጫ የለም፡፡
በስልጣን ላይ ያለው መንግስትም፣ ዘርንና ቋንቋን መሠረት ያደረገ ፌደራላዊ አስተዳደር አሁን የምናየውን አደጋ እንደሚያስከትልና ሀገራችንን ሊበትነን እንደሚችል ለረዥም ጊዜ ከተለያየ አቅጣጫ ሲነገረውና ሲመከር አልሰማ ብሎ ከርሞ፣ አሁን ጀንበሯ ከመጥለቋ በፊት ችግሩ ስር ከሰደደ በኋላ ባኖ የነቃ ይመስላል፡፡
“ቸር ሆነን” ከቀረ የዘገየ ይሻላል እንበላቸውና፣ መንግስት አሁን በመጨረሻ በጀመረው አካሄድ “ችግሩ ጋብ ብሏል” ወይም ቀድሞ እንዳሳየው አካሄድ “ብቻዬን እወጣዋለሁ” የሚል የበላይነት ሳይሰማው፣ ከሌሎች ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንድትቀጥልና ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ተቆርቋሪነትና ሃላፊነት ከሚሰማቸው የተለያዩ ተቃዋሚ “ተፎካካሪ” ድርጅቶች፣ የሐይማኖት፣ ሲቪክ ….ወዘተ ተቋማትና ባለሞያዎች ጋር እየተመካከረ፣ ስህተቱ ሲነገረውም አዳምጦ እየተቀበለ በጋራ ችግሩን እንድንሻገር የሀገራቸው ጉዳይ የሚያሳስባቸው ሚሊዮኖች እንደሚፈልጉና እንደሚጠብቁም መታወቅ አለበት፡፡
በተረፈ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ስትቀጥል ብቻ ነው፣ ምርጫ፣ ዲሞክራሲ፣ መፎካከር፣ ጭቅጭቅ፣ ጸቡም ሆነ እርቅ የሚኖረው፡፡ ሀገር ከፈረሰ ምንም ነገር የለም አጨብጭቦ በዜሮ ድምር በባዶ መቅለጥ ነው፡፡ ሀገራችን አንዴ በውጭና በውስጥ ጥንፍ በረገጡ አክራሪ ብሔረተኞች ቅርጫ ውስጥ ገብታ ከተበታተነች ቦኋላ፣ እንደገና እንደነበረ መመለስ አስቸጋሪ እንደሚሆን መዘርዘር ለቀባሪው ማርዳት ይሆንብኛል፡፡
ዛሬ ካለሃጢያታቸው በየቦታው መጤ እየተባሉ በተላይ በአማራው፣ ጉራጌው፣ ወላይታው፣ ሶማሌው….ወዘተ፣ ቅልቅልና ከሌላ አካባቢ መጣ የሚሉትን ኦሮሞውን ጭምር፣ (ያንዱ ከሌላው ቢከፋም)፣ እጅግ ብዙ ወገኖቻችን ላይ ጥንፍ በረገጡ የኦሮሞ ብሔረኞችና “የትግራይ ነፃ አውጭዎች” ወያኔ፣ ግብጽን ጨምሮ በእጅ አዙር (ፕሮክሲ) ትብብርና ድጋፍ በጭካኔ እየተገደሉና ንብረታቸው እየተዘረፈ፣ እየተቃጠለና እየወደመ፣ የተረፉት በየጫካው ተሰደው የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ነው፡፡ ይህን ሽብር ስር ወደ ሰደደ የዘርና ሃይማኖት ቅርጽ እንዲይዝ በረዥሙ ተሰርቶበታል፡፡ አሁንም “አክቲቪስቶቻቸው” ቀንና ማታ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የማይቆፍሩት ጉድጓድ የለም፡፡
ቀድሞ ወያኔ ሀገር ውስጥ እንደተቃወሙት በማስመሰል አጀግኖና በተቃዋሚ ሽፋን ሸክፎ ወደ ውጭ ሀገር ቀብድ ተከፍሏቸው የተላኩት ቅጥረኛ “አክቲቪስቶች” ጭምር፣ የጌቶቻቸውን እቅድ ለማሳካት ከፋፋይ ጽሁፎችንና ውይይቶችን በየፌስቡኩና ድኅረ ገፆች ሕዝብን ለማጫረስ ሲክለፈለፉ ባለፉት ሳምንታት በስፋት ታይቷል፡፡
ከነዚህ ውስጥ ጥቂቶቹ እውነተኛ የዘር ፖለቲካ ተቃዋሚ መስለውን ብዙዎቻችንን ቀርበውንና አምነናቸው አስጠግተን እኛ ስናስተናግዳቸው እነሱ እየሰለሉን ቆይተው፣ ጌቶቻቸው ጭንቀት በገጠማቸው ሰአት፣ እራሳቸውን ግልጽ አድርገው በይፋ የመጨረሻውን ፍልሚያ እንዲቀላቀሉ፣ አሊያ ከቀብዱ ሌላ ዋናውን ክፍያ እንደማያገኙ ማስጠንቀቂያ የደረሳቸው ይመስል፣ ቆዳቸውን ገልብጠውና ጭንብላቸውን አውልቀው በአደባባይ ከጸረ ኢትዮጵያ ሃይሎች ጋር የተሰለፉ በመምሰል ሀገራችንን በማድማት ላይ ይገኛሉ፡፡ የተሰለፉ በመምሰል ያልኩበት ምክንያት፣ ማንም በገንዘብ ከገዛቸው ጎን አስመስለው ያገለግላሉ እንጂ፣ የእውነት እራሳቸው የሚያምኑበት የፖለቲካ አቋም ስለሌላቸው ነው፡፡ ዛሬ እዚህ ነገ እዚያ ናቸውና፡፡
አቋም መያዝ መብት እንደሆነ ብቀበልም፣ ጥቂቶቹን በቅርበት እንዳጠናኋቸው፣ ፖለቲካው ሽፋን እንጂ ዋናው ፍላጎታቸው ገንዘብ ነው፡፡ የተሻለ ጥቅም ሲያገኙና “ማርሽ ሲቀይሩ” በፖለቲካ ክህደታቸውን ይሸፍኑበታል እንጂ፣ ሕዝብ፣ ሀገር፣ ትግል የሚባለውን ለሽፋን እንጂ አያምኑበትም፡፡ በጥቅም ሰው በድለው ፖለቲካዊ ሽፋን ለመስጠት ይሞክራሉ፡፡ ቡድን እየቀያየሩ መደበቂያና ነውራቸውን መሸፈኛ መከላከያ አዲስ ምሽግና አጋዥ አግኝተው እዛም እስከሚነቁባቸው ወይም የተሻለ $$ እስከሚያገኙ ቀን ይገፉበታል፡፡
በተረፈ መንግስት እየወሰደ ካለው እርምጃ ውጪ እስካሁን ከዚህ ቀውስ ለመውጣት የሚያስችል አማራጭ አልቀረበም፡፡ ምናልባት አንዳንድ እየተሰሙ ያሉት እንደ የአዘቦቱ ትግል “መፍትሄዎች”፣ ምናልባት ለስሜታችን ይረዳ እንደሆን እንጂ ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስቸግር፣ መንግስትንና ችግር ፈጣሪዎቹን በአንድ ጊዜ አብሮ ደርቦ ታግሎ ወይም አስወግዶ ውጤት ለማምጣት የሚሉት፣ የትግል ቅደም ተከተል የሌለው፣ ጊዜ የማይሰጠውን አጣዳፊውንና መለስተኛውን ችግር ያላገናዘቡ ምኞቶች …ወዘተ ናቸው፡፡
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በአቢይ የሚመራው የመንግስት አስተዳደር ቢገረሰስ፣ በዚህም ማን ሊጠቀምና ማን ሊጎዳ እንደሚችል በግልጽ እየታወቀ፣ እራሳቸው በሚፈልጉት መንገድ ካልሄደ፣ “እኔ ካልበላሁት ጭሬ እበትነዋለሁ”እንደተባለው የዶሮዋ መንገድ እንዳይሆን እሰጋለሁ፡፡ ሕዝብ እና ሀገር ከመጥፋቱ በፊት እንጂ ከዚያ ቦኋላ መፈራገጥ ዋጋ የለውም፡፡ በየግል ወይም ትናንሽ ቡድን ይዘን እቤታችን ምንም ሳንሞክር በመቀመጥ፣ ችግሩን ብቻ እያነሳን ስልኩ እስከሚሞቅ ከንፈራችንን እየመጠጥን የደረሰውን አደጋ እያነሳን ብንቆዝም ዋጋ የለውም፡፡
ብዙ ነገሮች እንዳመለጡን ሁሉ፣ ሀገራችንም አንዴ ከተበታተነ በኋላ መልሰን እንደገና ስለማናገኘው፣ የሀገራችን ጠላቶች እንደሚፈልጉት፣ በዘርና በእምነት ሳንከፋፈል፣ ከቡድናዊ አስተሳሰብ፣ ከእልህ፣ በዘልማድ ለመቃወም ከመቃወም፣ ካላስፈላጊ ፉክክርና እሰጥ እገባ፣…ወዘተ ወጥተን፣ ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ ሌላ ሌላውን ለይደር አቆይተን፣ ቢያንስ በተሻለ የተደራጀና፣ በጠላቶቻችን ዒላማ ውስጥ ከገባው መንግስት ጎን በኅብረት ቆመን አደጋውን እንከላከል፡፡ እንደ ቀደምት አርቀው አሳቢ ወላጆቻቻን፣ አደጋውን አማትረን አጣዳፊ እና የባሰውን ከመለስተኛ ችግሮቻችን እንለይ እላለሁ፡፡ የተሻለ አማራጭ ካለ ለመማር ዝግጁ ነኝ፡፡
ለሞቱት ወገኖቻችን ነብሳቸውን እግዚአብሔር ይማርልን፣ ለቤተሰቦቻቸውም ጽናቱን ይስጥልን፡፡
ለተሰደዱትና ለተቸገሩ ወገኖቻችን እንድረስላቸው፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅ! እኛም አንተባበረው!