የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መልዕክት ለኢትዮጵያ ወጣቶች፡ “በብልጽግና ፓርቲ ከድህነት ነጻ እንወጣለን!”
የፀሐፊው ማስታወሻ: ይህ ጽሁፍ በእንግሊዘኛ ጃኑዋሪ 6 2020 ወጥቶ ነበር:: እዚህ ይጫኑ:
PM Abiy Ahmed’s Message to Ethiopia’s Youth: Up From Poverty With Prosperity Party!
በፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረ ማርያም
ትርጉም ከኢንግሊዘኛ ነፃነት ለሀገሬ
ከጥቂት ቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የብልጽግና ፓርቲን ለማስተዋወቅ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም የስብሰባ አዳራሽ ለተሰበሰቡት ወጣቶች ያሰሙትን ንግግር ባዳመጥኩ ጊዜ በአእምሮየ ውስጥ ሁለት ዓይነት ስሜቶች ተንጸባርቀዋል፡፡
የመጀመሪያው ስሜት ወደር የሌለው ደስታ ነው፡፡
በእኔ የህይወት ዘመን ሰላምን ከፖለቲካ በላይ፣ ስብዕናን ከጎሳ በላይ፣ ትህትናን ከዜግነት በላይ፣ ፍቅርን ከጥላቻ በላይ እና ብልጽግናን ከድህነት በላይ ለወጣቱ የሚያስተምር ኢትዮጵያዊ መሪ በፍጹም ሰምቸ አላውቅም፡፡
የኢትዮጵያውያን መሪዎች በግዛታቸው ውስጥ ያሉ ህዝቦች በአገዛዛቸው እግር ስር እንዲንበረከኩ ለማድረግ ኃይልን ሲጠቀሙ ነው ሁልጊዜ የማውቀው፡፡ እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ አጋማሽ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣንን የተቆጣጠረው ወታደራዊው ኮሙኒስት ደርግ 60ዎቹን ከፍተኛ የንጉሰ ነገስቱን ባለስልጣኖች በጥይት በመደብደብ አሰቃቂ የሆነ እልቂትን ፈጽሟል፡፡ በኋላም በመደብ ትግል ሰበብ “የቀይ ሽብር ዘመቻን በማወጅ” ዜጎች የመከራ እና የስቃይ ህይወትን እንዲገፉ አድርጓል፡፡ በአብዛኛው ወጣቶች የሆኑ ወደ 500,000 ገደማ የሚሆኑ ዜጎች ተገድለዋል፡፡ እንዲሁም ከ10,000 በላይ የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ታፍነው እንዲሰወሩ ተደርገው የገቡበት ሳይታወቅ ቀርቷል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አገዛዝ በጎሳ “ፌዴራሊዝም ስም” “የጎሳ ትግል” ዘመቻ በማወጅ ቀደም ሲል እንደዘገብኩት ከደቡብ አፍሪካው የጥቂት ነጮች የበላይነት ዘረኛ አገዛዝ (አፓርታይድ) በከፋ መልኩ በ10,000ዎች ወጣቶች ላይ እልቂትን ፈጽሟል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ወጣቱን ትውልድ እንዲህ በማለት እያስተማሩ ያሉ ወጣት ኢትዮጵያዊ መሪ አግኝተናል፡፡
ለፖለቲከኞች ወይም ለፖለቲካ ስትሉ አትሙቱ ወይም አትግደሉ፡፡
ላመናችሁበት ስትሉ አትሙቱ ወይም አትግደሉ፣ ምክንያቱም ስህተት ስህተት ነውና፡፡
የምርጫ ድምጽ ለመስጠት የምርጫ ካርድን እንጅ ድንጋይ አትወርውሩ፡፡
እኔን ወይም ደግሞ ፓርቲየን ካልወደዳችሁ ድምጽ በመንፈግ ቅጡን እንጅ የመንገድ ላይ ነውጥን አትፈጽሙ፡፡
ፓርቲየ የሚሸነፍ ከሆነ በ24 ሰዓት ውስጥ ስልጣንን በማስረከብ ታማኝ ተፎካካሪ ሆኘ እቀጥላለሁ፡፡
ፓርቲያችሁ የሚሸነፍ ከሆነ የህዝቡን ዳኝነት መቀበል እና ለሌላ ጊዜ በሀሳብ ልዕልና ለመታገል መኖር እንጅ አትሙቱ፡፡
የእኛ ችግር የማንነት እና የጎሳ ፖለቲካ አይደለም፡፡ የእኛ ችግር ድህነት ነው፡፡ የእኛ ችግር የብልጽግና እጥረት ነው፡፡ የእኛ ችግር የሌሎችን ስሜት መገንዘብ ያለመቻል ነው፡፡
እኛ የወንድሞቻችን እና የእህቶቻችን ጠባቂዎች ነን እንጅ አሳሪዎች፣ ገራፊዎች እና አሰቃዮች አይደለንም፡፡
የጎሳ እና የኃይማኖት ጽንፈኝነትን በመጠቀም ስልጣንን በኃይል በመንጠቅ ህዝብን ከፋፍሎ የመግዛት አባዜ ጊዜው አልፎበታል፡፡
ብልጽግና የአእምሮ ውጤት ሲሆን ድህነት ደግሞ የጉልበት እና የእብሪት ውጤት ነው፡፡
ያሰባችሁትን ነው የምትሆኑት፡፡
ምንጊዜም እራሳችሁን በድህነት ውስጥ የምትኖሩ አድርጋችሁ ከቆጠራችሁ ብልጽግናን በፍጹም ልትጎናጸፉ አትችሉም፡፡
ጥላቻን የምታስቡ ከሆነ ጥላቻን ቀፍቃፊ ጠይዎች ትሆናላችሁ፡፡
ፍቅርን የምታስቡ ከሆነ አፍቃሪዎች ትሆናላችሁ፡፡
አሉታዊ ሀሳቦች አሉታዊ ድርጊቶችን ይወልዳሉ፡፡ አዎንታዊ ሀሳቦች አዎንታዊ ድርጊቶችን ይወልዳሉ፡፡
አሉታዊ ኃይል አቅመቢስ ያደርጋል፡፡ አዎንታዊ ኃይል አቅምን ያጎለብታል፡፡
ፍርሀት ድርጊት አልባ እና አለመለወጥን ይወልዳል፡፡ ድፍረት ድርጊትን እና ለውጥን ይወልዳል፡፡
በመጨረሻም ሁላችንም የምናስበውን እንሆናለን፡፡
ለመፍትሄዎች አስቡ፡፡ መፍትሄዎችን አሰላስሉ፡፡ በችግሮች ውስጥ አትዋኙ፡፡
ብልጽግናን ለመጎናጸፍ ጠንክራችሁ ስሩ፡፡ ብልጽግናን ተመኙ፡፡ ብልጽግናን አልሙ፡፡ ለብልጽግና ተስፋ አድርጉ፡፡
ከድህነት ጋር ጓደኛ አትሁኑ ወደ ቁልቁለት ይወስዳችኋል፣ እናም በቁልቁለት መንገድ እንድትዘልቁ ያደርጋችኋል፡፡
የአእምሮ ድህነት አለ፡፡ ጥላቻን የሚያራግቡ እና ኃይልን የሚጠቀሙ የአእምሮ በሽተኞች ናቸው፡፡
የመንፈስ ድህነትን አስወግዱ፡፡ እምነት የሌላቸው ሰዎች እምነታቸውን ወደ ገሀነም ይመራሉ፡፡
በማንነታችሁ፣በጎሳችሁ ወይም በዜግነታችሁ ምክንያት ለአስርት ዓመታት የምርኮኝነት አስተሳሰብ ስሜት እንዲሰማችሁ ስትማሩ ቆይታችኋል፡፡ እናንተ አሸናፊዎች እንጅ ምርኮኞች አይደላችሁም፡፡ እናንተ ድል አድራጊዎች የእጣ ፋንታችሁ መሪ መርከበኞች ናችሁ፡፡
የተሸናፊነትን ስሜት እያራመዳችሁ አሸናፊዎች ልትሆኑ አትችሉም፡፡ ሁልጊዜ ሁሉም ነገር ይቻላል የሚል አመለካከትን ያዙ፡፡ በጠንካራው የመደመር መሳሪያ በመታገዝ የጋራ ጠላት የሆነውን ድህነትን ተዋጉ፡፡
እጅግ በጣም የሚያስገርም ነገር ነው፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በኢትዮጵያ ውስጥ ስርነቀል የአመራር ጥበብ ተመዘገበ በማለት መናገር እችላለሁ፡፡
በፖለቲካ ስርነቀል ለውጥ አንድ ሰው እንዳሰበው ሊያደርግ ይችላል፣ ፖለቲካም እንደዚሁ ነው፡፡
ሙሉ በሙሉ ልገልጸው በማልችለው መልኩ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የወጣቱን ልቦች እና አእምሮዎች በመለወጥ ላይ ናቸው፡፡
የቀድሞው (የጉማሬው) ትውልድ አባል እንደመሆኔ መጠን እኔ እስከማውቀው ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአቦሸማኔው (ለወጣቱ) ትውልድ ያላቸው አቀራረብ እንዲህ የሚል ቀጥተኛ መልዕክትን የሚያስተላልፍ ይመስለኛል፡ “ወጣቱ ትውልድ ያለምንም ማቋረጥ ሌት ከቀን እንዲሰራ እና ዓላማውን ለማሳካት እንዲችል ማሳመን ከቻልክ ብቻ ኢትዮጵያን ታላቅ እና የበለጸገች ሀገር ልታደርጋት ትችላለህ፡፡”
ወጣቱን ለማሳመን በመጀመሪያ ደረጃ ልቦቻቸውን እና አእምሯቸውን መማረክ አለብህ፡፡ ይህንን ለማሳካት ደግሞ ወጣቶችን ማነሳሳት፣ መንፈሳቸውን መቀስቀስ፣ ነብሶቻቸውን መዳሰስ እና ለኢትዮጵያ ብልጽግና ያላቸውን ፈጠራ ሙሉ በሙሉ መጠቀም አለብህ፡፡
በአጭሩ ለማስቀመጥ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የምርጫ ድምጽን ለማሸነፍ ሳይሆን የወጣቶችን ልቦች እና አእምሮዎች ለማሸነፍ ዘመቻ በማካሄድ ላይ ናቸው!
እ.ኤ.አ አሁን የፊታችን ግንቦት 2020 የሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ የመንግስቱን አመራር የሚይዙት መሪዎች የሚመረጡበት ምርጫ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወሰንበት የነጻነት ምርጫ እንደሚሆን አምናለሁ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች፡፡ የቀጣዩ ትውልድ ህልውና ሀገሪቱ በምትከተለው የጉዞ መንገድ የሚወሰን ይሆናል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ያገኘችው ዕድል የቅዱስ አምላክ ታምራዊ ቡራኬ ነው ብየ አምናለሁ፡፡
በዓለም ላይ እጅግ ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ያላት ሀገር ፕሬዚዳንት ለመሆን ከበቃው ስግብግብ ህጻን መማር፣
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከእውነተኛ የህይወት ገጠመኝ ምሳሌዎች እና ተመሳስሎዎች በማጣቀስ ለወጣቱ ትውልድ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡
ስለቻይና ፕሬዚዳንት ጂንፒንግ ከመጽሀፍ ያነበቡትን ታሪክ በማጣቀስ ለወጣቶቹ አካፍለዋል፡፡
ጂንፒንግ ህጻን በነበረበት ጊዜ በጣም ስግብግብ/ገብጋባ ልጅ ነበር፡፡ እርሱ ጉዳዩ አድርጎ የሚያየው ስለሚፈልገው ነገር እንጅ ለሌሎች ደንታ አልነበረውም፡፡ የእርሱ ጓደኞች እርሱን ለምን እንደማይወዱት ከማማት በስተቀር እርሱ ጥሩ ጓደኛ የመሆን ዝንባሌ ስለሌለው ጓደኞች ማፍራት አልቻለም ነበር፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን የጂንፒንግ አባት ልጃቸው ጂንፒንግ ጓደኛ እንዴት ማፍራት እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆን እንደሚችል ትምህርት ሊያስተምሩት ፈለጉ፡፡ ለዚህም እንዲመች በጂንፒንግ የልደት በዓል ዕለት በሁለት ጎድጓዳ ሳህን የተዘጋጀ ፓስታ አቀረቡ፡፡ በአንደኛው ሳህን ፓስታ ላይ አንድ እንቁላል አስቀመጡ፡፡ ሌላኛው ሳህን ፓስታ ላይ የሚታይ እንቁላል የለም፡፡ በመቀጠል አባቱ ጂንፒንግን ከሀለቱ ሳህን ፓስታ አንዱን በመምረጥ መብላት እንዲጀምር ነገሩት፡፡ ጂንፒንግ ወዲያውኑ በብረሀን ፍጥነት ከላይ እንቁላል ያለበትን ፓስታ መረጠ፡፡ የጂንፒንግ አባት ከሌላኛው በፓስታ ከተሸፈነው ፓስታ መብላት ጀመሩ፡፡ ሆኖም ግን በዚህ ሳህን ካለው ፓስታ ስር ሁለት እንቁላሎች ነበሩ፡፡
ጂንፒንግ ይህንን በተመለከተ ጊዜ አጅግ በጣም አዘነ፡፡ አባቱም ይህንን ተመለከቱና እንዲህ የሚል ምክር ሰጡት፣ “ልጄ ዓይኖችህ የሚያዩት ነገር ሁሉ ሁልጊዜ እውነት አይደለም፡፡ ስግብግብ በመሆን የሌሎችን ሁሉ ለመውሰድ በምታደርገው ጥረት በመጨረሻ እራስህ ታጣለህ፣ ትከስራለህ፡፡”
ከጥቂት ቀናት በኋላ የጂንፒንግ አባት እንደቀድሞው በሁለት ሳህን ፓስታ አዘጋጁና ከሁለቱ አንዱን መርጦ እንዲበላ ጠየቁት፡፡ ጂንፒንግ ከቀድሞው ልምዱ በመማር ከላዩ ላይ እንቁላል የሌለበትን ሳህን ፓስታ መረጠ፡፡ ሆኖም ግን ጂንፒንግ ፓስታውን ከስር ፈንቅሎ እንላሎች ለማግኘት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቶ ምንም ዓይነት እንቁላል ሳያገኝ ቀረ፡፡
ጂንፒንግ አልፎ አልፎ በሚዘጋጀው ምግብ እንቁላሉን ባለማግኘቱ እጅግ በጣም አዘነ፡፡ ይህንን እንዳስተዋሉ አባቱ ሌላ እንዲህ የሚል ምክር ሰጡት፣ “ልጄ በቀድሞው ልምድ እና ተሞክሮ እጅግ በጣም አትተማመን፣ ምክንያቱም ህይወት ሊተነበይ የማይችል የማይጠበቅ ሊሆን ይችላልና፡፡”
እንደገና ከጥቂት ቀናት በኋላ የጂንፒንግ አባት ተመሳሳይ ነገር አደረጉና ልጃቸው እንዲመርጥ ጠየቁት፡፡ ሆኖም ግን በዚህ ጊዜ ጂንፒንግ ትምህርት በመውሰድ ለአባቱ እንዲህ አለ፣ “አባቴ ለቤተቦቻችን ስትል ታላቅ መስዋዕትነት ከፍለሀልና የመጀመርያውን ምርጫ አንተ እንድታደረግ ይሁን፡፡ እባክህን አንት ምረጥ” አለ፡፡ አባቱም ከፓስታው በላይ አንድ እንቁላል ያለበትን ፓስታ የያዘውን ሳህን መረጡ፡፡ ከዚያም አባት ለልጃቸው እንዲህ የሚል ምክር ሰጡ፣ “ልጄ ሁልጊዜ አስብ፣ ለሌሎች በምታስብበት ጊዜ መልካም ዕድልን ትጎናጸፋለህ” አሉት ይባላል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህንን ከላይ የቀረበውን ምክር እንዲህ በማለት አጠናከሩት፣ “ለሌሎች በምታስቡበት ጊዜ ፈጣሪ ይረዳችኋል፡፡”
በአሁኑ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለኢትዮጵያ ወጣቶች ካቀረቡት ጥልቅ ምክር እኔም በወጣትነት ዘመኔ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ካቀረቡት ትምህርት እና እንዲህ ከሚለው ጋር የሚመሳሰል የጠለቀ ምክርን አግኝቸበታለሁ፣
“ማንኛውም ወንድ [እና ሴት] በብርሀን እና በእውነት ወይም ደግሞ በተቃራኒው አውዳሚ በሆነው በስግብግብነት መንገድ እየሄዱ ስለመሆናቸው እና አለመሆናቸው መወሰን አለባቸው፡፡ ይህ የእራስ ብይን ነው፡፡ የህይወት ቀጣይ እና አንገብጋቢ ጥያቄ ለሌሎች ሰዎች ምን እያደረግህ ነው?” የሚል ነው፡፡
ዶ/ር ኪንግ እ.ኤ.አ በ1957 ባደረጉት ንግግር የእራስን ስግብግብነት ማሸነፍ እንዴት እንደምንቸል አስተምረውናል፡፡ በዚያ ወቅት እንዲህ ብለዋል፣ የዚህን ዓይነት የእራስ ስግብግብነት ችግር ለማሸነፍ የተሻለው ዘዴ አንድ ምክንያት እና አንድ ዓላማ በመፍጠር ከእራስ ቁጥጥር ውጭ የሆነ ታማኝነትን በማንገስ እራስን ለዚያ ነገር አሳልፎ በመስጠት እውን ለማድረግ ጥረት ማድረግ ነው፡፡
ይህ እውነት ነው!
በእኛነታችን ላይ ያለ የመልካም እና የመጥፎ ተኩላ ተመሳስሎ፣
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በእያንዳንዱ ሰው ልብ እና አእምሮ ውስጥ ሁልጊዜ በመዋጋት ላይ የሚገኙ የሁለት ተኩላዎችን ተመሳስሎ ተጠቅመዋል፡፡ ይህንንም በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፣
በእያንዳንዱ ሰው ህልውና ውስጥ የሚኖሩ ሁለት አስፈሪ ተኩላዎች አሉ፡፡ አንደኛው ለሌሎች ሰዎች ጥረት እና ስራ ዋጋ የማይሰጥና የሚያጠለሽ በጥላቻ፣ በአድሏዊነት እና በመሳሰሉት እኩይ ምግባሮች የተሞላ መጥፎ ተኩላ ነው፡፡ ሰነፍ ነው፣ ሌሎች ጠንክረው የሚሰሩትን ሰዎች ስም ያጠፋል፣ ያጠለሻል፡፡ ይዋሻል፣ ይሰርቃል፣ ያጭበረብራል፡፡ እጅግ በጣም ስግብግብ እና እራስ ወዳድ ነው፡፡
ሌላኛው ተኩላ ደግሞ እውነት የሚናገር፣ ጠንክሮ የሚሰራ እና ጎረቤቱን የሚወድ እንዲሁም ለሌሎችም ይቅርታን ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነ ፍጡር ነው፡፡ ታሪክን በሚገባ የተገነዘበ እና መደመርን በመተግበር ብልጽግናን ለማምጣት ጥረት የሚያደርግ መልካም ተኩላ ነው፡፡
ከሁለቱ ተኩላዎች የትኛው ያሸንፋል ብላችሁ ብትጠይቁ መልሱ በገፍ እና በብዛት የተቀለበው ቅልብ ተኩላ የሚል ይሆናል፡፡
ለመጥፎው ተኩላ ምቀኝነትን፣ ሌብነትን እና ጥላቻን የምትቀልቡት ከሆነ እጅግ በጣም እያደገ ይሄድ እና መልካሙን ተኩላ ይውጠዋል፣ ይሰለቅጠዋል፡፡
ሆኖም ግን ለመልካሙ ተኩላ እውነትን፣ ታማኝነትን፣ መልካም አመለካከትን እና ለጋስነትን የምትመግቡት ከሆነ አጅግ በጣም እየገዘፈ ይሄድ እና መጥፎውን ተኩላ ይውጠዋል፣ ይሰለቅጠዋል፡፡
ስለሆነም ምርጫው የእናንተው ነው፡፡
መልካምም ይሁን መጥፎ በእራሳችሁ ላይ የሚያድገውን እና በእናንተ ላይ ብቻ ተወስኖ የማይቀረውን ተኩላ ተጠንቀቁ፡፡ መጥፎው ተኩላ እናንተን እና በእናንተ ዙሪያ ያሉትን ሁሉ ይበላል፡፡ መልካሙ ተኩላ የሚያሸንፍ ከሆነ ደግሞ በዙሪያችሁ ፍቅርን፣ መልካምነትን እና ይቅርባይነትን ያስፋፋል፡፡
ስለሆነም ወጣቶች የእውቀት ኃይላችሁን በመጠቀም መልካም ነገርን ለመስራት እንድትችሉ ፈጣሪ ልቦቻችሁን እና አእምሯችሁን ያብራላችሁ፡፡
ለኢትዮጵያ ወጣቶች ያለኝ ይቅርታ፡ በመጥፎ ተኩላ ተጠልፎ ለነበረው የእኔ ትውልድ ያለኝ ጸጸት!
በአሁኑ ጊዜ ላለው ትውልድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እያስተማሩት እንዳለው ሁሉ የእኔንም ትውልድ የሚያስተምር መሪ አለመኖሩ ከልብ ያሳዝነኛል፡፡
ሙሉ በሙሉ በጸጸት ላይ ነኝ፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የመጥፎውን ተኩላ የጎሳ ጥላቻን፣ የሀገር መነጣጠልን፣ የጎሰኝነትን እና የኃይማኖት ጽንፈኝነትን ኢምክንያታዊ ጥሬ ስጋ ስትመገቡ ለቆያችሁ ላሁኑ ትውልድ ወጣቶች በእኔ ትውልድ ስም ሆኘ ታላቅ ይቅርታን እጠይቃለሁ፡፡
የመጥፎ ተኩላን ከፍተኛ የጥላቻ፣ የቁጣ፣ የክፍፍል እና የጎሳ የበላይነት ምግብን እየመገብን ያሳደግናችሁ ትውልድ አባላት ጸጸቴን ለመግለጽ እወዳለሁ፣ ይቅርታንም እጠይቃሁ፡፡
በወጣት ኢትዮጵያውያን ልቦች እና አእምሮዎች ውስጥ የነበረውን መልካም ተኩላ ሲገርፍ፣ ሲሰባብር፣ በኃይል በማንበርከክ እና በመደፍጠጥ እያሳደገ እና እያጠናከረ በቆየው የመጥፎ ተኩላ ድርጊት የእኔ ትውልድ ስም በመጸጸት ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡
ለዘመናት የኢትዮጵያን ወጣቶች “ሰው ለሰው ተኩላ ነው” እያሉ ሲያስተምሩ የቆዩትን እና የጎሰኝነት፣ የስግብግብነት እና የጽነፈኝነት መርዛቸውን በፖለቲካ ድባቡ ላይ ለመርጨት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ምክንያት ስለሆኑት ስለእኔ ትውልድ አባላት በትውልዱ ስም ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡
ለኢትዮጵያ ወጣቶች ያሉኝ ተስፋዎች እና ህልሞች፡ የወደፊት ሰላም፣ ብልጽግና፣ እድገት እና ነጻነት
የኢትዮጵያ ወጣቶች በፍጹም ወደኋላ ዞራችሁ እንዳትመለከቱ እላለሁ፡፡ ወደኋላ ዞራችሁ የምትመለከቱበት ጊዜ ምን ያህል ርቀት እንደተጓዛችሁ ለማወቅ ብቻ መሆን አለበት፡፡
አስራ ሶስት ወራት የጸሐይ ብርሀን ጸጋ የማይለያትን ሀገር በአንድ ወቅት ያ እከካም አሮጌ ተኩላ ወሯት እርሱ በሚፈልገው መልኩ ለመምራት ሲዳክር በመቆየቱ ብዙም አትጨነቁ፡፡ አሁን ሄዷል፣ ለዘላለም ሄዷል፡፡ በምንም ዓይነት መንገድ ተመልሶ አይመጣም፣ በፍጹም!
በአሁኑ ጊዜ ያ አሮጌ ተኩላ የኢትዮጵያን ቤት ለማፍረስ ሌት ቀን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
በፍጹም አትፍሩ፡፡ የኢትዮጵያ ቤት የተሰራው ከጠንካራ ድንጋይ እና ጡብ ቢሆንም መጥፎው ግዙፍ ተኩላ ሌትና ቀን መሸ ነጋ ሳይል የሞት ሽረት ትግል በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ቤት ካለበት ንቅንቅ አይልም፡፡ ይልቁንም ቤቱ ከተራራው ጫፍ ላይ በግርማ ሞገስ ተቀምጦ ይዘልቃል፡፡
ስለዚህ አሮጌው ተኩላ እንደሚፈረካከስ፣ ግራ እንደሚጋባ፣ ልቡን እንደሚያጣ እና መብቱን እንደሚያጣ ማወቅ ይገባል፡፡
በእርግጥ ትልቁ መጥፎ አሮጌ ተኩላ ጉምን ይዘግናል፣ ከጉሙ ጋርም ብን ብሎ ይጠፋል!
ትልቁ መጥፎ ተኩላ ከመጣበት ቋጥኝ ስር በውርደት ተቀብሮ ማየት እንዴት ደስ ይላል!
አሁን ትልቁ አሮጌ ተኩላ ላይመለስ ሄዷል፣ አሁን መልካሙን ተኩላ ተንከባክቦ ማሳደግ የእናንተ ኃለፊነት ነው!
የኢትዮጵያ ወጣቶች ሆይ!
የእናንተን ልቦች እና አእምሮዎች እንዲገዛ አሉታዊ አሰተሳሰብ እና ጥላቻ የሚናኝበትን መጥፎ ተኩላ የምትፈቅዱለት ከሆነ የአእምሯችሁን እና የመንፈሳዊ ኃይላችሁን ታጣላችሁ፡፡ ብስጩ፣ በጥላቻ የተሞላ፣ ጨካኝ እና ጠብ ጫሪዎች ትሆናላችሁ፡፡
መልካሙን ተኩላ ፍቅር፣ እርቅ፣ ይቅረባይነት፣ መቻቻል፣ ደግነት እና ጨዋነትን እንዲመገብ የምትፈቅዱለት ከሆነ ኃይለኞች እና አይበገሬዎች ትሆናላችሁ፡፡ ይህንንም በማድረግ በተራራው ጫፍ ላይ ታላቅ ማህበረሰብ እና የምታንጸባርቅ ከተማን ትገነባላችሁ፡፡
እርግጠኛ ነኝ ጠንካራ፣ ፍርሀት የለሽ እና መንፈሰ ጽኑ ስብዕናን ለመላበስ ፍላጎቱ እና ጽናቱ እንዳላችሁ ከሚገባው በላይ እተማመናለሁ፡፡
አሸናፊነቱን የሚወስነው የተኩላው የሰውነት መጠን መገዘፍ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን የትግሉ መጠን እና ስልት ነው በተኩላው ላይ ድልን መቀዳጀት የሚያስችለው፡፡
ወጣቱ መልካም የብልጽግና ተኩላ የመጥፎውን የድህነት፣ የድንቁርና፣ የበሽታ፣ የጥላቻ እና የጥልቅ ጥላቻ ተኩላ ድል ያደርገዋል፡፡
አሁን እየተንከባከባችሁት ያለው ወጣቱ መልካም ተኩላ በርካታ ስሞች አሉት፡፡ እነርሱም፤ ሰላም፣ ፍቅር፣ ይቅርባይነት፣ እርቅ፣ ብልጽግና እና መቻቻል ይባላሉ፡፡
ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በጋብቻ፣ በእህትማማችነት፣ በወንድማማችነት፣ በጓደኝነት፣ በጎረቤትነት እና በአብሮነት ኖረዋል፡፡
ሁልጊዜ “ሰው ለሰው ሰው” እንጅ “ሰው ለሰው ተኩላ ነው” ብለን አናስብም፡፡
በመከራ ጊዜም በጓዳዊነት እና ፈጣሪን በማምለክ የዕየለት ኑሯችንን ስንገፋ ኖረናል፡፡
እምነት አለን፡፡ የመልካሙ ተኩላ ድል በተዓምር የተሰጠ ነው፡፡
ለኢትዮጵያ ወጣቶች ያለኝ ማስጠንቀቂያ… የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ በእጃችሁ እና በእጃችሁ ብቻ ነው!
የልጁን፣ የወፏን እና የብልሁን ሽማግሌ የተሞክሮ ተመሳስሎ ለኢትዮጵያ ወጣቶች ለማካፈል እወዳለሁ፡፡
በአንዲት ትንሽ መንደር ውስጥ እያንዳንዱ ሰው ለአመራር እና ለምክር የሚጠይቃቸው አንድ ብልህ ሽማግሌ ይኖሩ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ብልሁ ሽማግሌ በትክክል ለመመለስ የማይችሉትን ጥያቄ ወጣቱ ልጅ በመጠየቅ አታልልና አዋርዳቸዋለሁ በማለት ወሰነ፡፡
ወጣቱ ልጅ አንዲት ትንሽ ወፍ መፈለግ እና ወፊቱን ከእጆቹ መዳፎቹ ውስጥ በማስገባት ከእይታ በመከለል ላላ በማድረግ መያዝ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ብልሁ ሽማግሌ ቀረብ በማለት በእጆቹ መዳፍ ውስጥ ያለችው ወፍ በህይወት አለች ወይስ ሞታለች እስቲ ይገምቱ ይላቸዋል፡፡ ሽማግሌው በምላሻቸው ወፏ ሞታለች የሚል መልስ ከሰጡ ወጣቱ ልጅ ወፏን እጆቹን ከፍቶ በመልቀቅ እንድትበር በማድረግ ብልሁ ሽማግሌ ህዝቡ እንደሚያምነው ብልህ አይደሉም በማለት ብልሁን ሽማግሌ ለማሳፈር ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ብልሁ ሽማግሌ ወፏ በህይወት አለች በማለት ምላሽ የሚሰጡ ከሆነ ወጣቱ ልጅ በእጆቹ መዳፎች ስር ያለችውን ወፍ በመደፍጠጥ ይኸው ሞታለች በማለት ብልሁ ሽማግሌ የማያውቁ መሆናቸውን ማጋለጥ ነበር፡፡
በዚህም መሰረት ወጣቱ ልጅ ብልሁን ሽማግሌ በዚህ መልኩ ከቀረበ በኋላ እንዲህ በማለት ጠየቃቸው፣ “ብልሁ ሽማግሌ በእጆቼ ምን እንዳለ ሊነግሩኝ ይችላሉ?“ ብልሁ ሽማግሌ “በእርግጥ እችላለሁ” በማለት መለሱ፡፡ “በእጆችህ ጣቶች መካከል ወጥተው ከማያቸው ላባዎች አንጻር በእጆችህ ውስጥ ትንሽ ወፍ ያለች መሆኑን ልነግርህ እችላለሁ” በማለት መለሱለት፡፡
“የተናገሩት እውነት ነው!” ሆኖም ግን “እንደ ብልህ ሽማግሌ በመዳፎቼ ውስጥ ያለችው ወፍ ሞታለች ወይስ በህይወት አለች?” በማለት ወጣቱ ልጅ ጠየቃቸው፡፡
ብልሁ ሽማግሌ ለጥቂት ጊዜ ዝም በማለት ልጁን በአንክሮ ከተመለከቱ በኋላ የሚከተለውን ምላሽ ሰጡ፣ “የወፏ በህይወት መኖርም ሆነ መሞት በእጆችህ ላይ ነው፡፡ ምርጫው የአንተው ነው” አሉት ይባላል ፡፡
እንደዚሁም ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮጵያም በኢትዮጵያውያን ወጣቶች እጅ ናት፡፡ ኢትዮጵያ የሰላም፣ የብልጽግና፣ የእድገት እና የነጻነት ምድር ሆና እንድትኖር ወይም እንዳትኖር ምርጫው ያለው በኢትዮጵያውያን ወጣቶች እጅ ነው፡፡ እናም ኢትዮጵያ በእናንተ እጅ ብቻ ላይ ናት!
የግል ማስታወሻ…
ምርጫ 2020 ምርጫ ብቻ ሳይሆን የወደፊቷን ኢትዮጵያ ነጻነት መወሰኛ እንደሆነ አምናለሁ፡፡
የእኔን ትውልድ እንደማስበው የጎሳን፣ የጽንፈኝነትን፣ የሶሻሊዝምን፣ የኮሙኒዝምን፣ የማርክሲዝምን፣ የኃይማኖት ጽንፈኝነትን እና ሌሎችንም ኢዝሞች መጥፎ ተኩላ ስራዎች እንደመሳሪያ በመጠቀም ለስልጣን፣ ተጽዕኖ ለመፍጠር እና ለገንዘብ ሲሉ ያደርጉት ስለነበረው የተሳሳተ አካሄድ በትውልዴ ስም ይቅርታ እጠይቃሁ፡፡
ከልክ ያለፈውን ስግብግብ ፍላጎታችንን ለማሟላት በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን ደኃ ኢትዮጵያውያን ለተራበ ተኩላ ስንመግብ ቆይተናል፡፡
እንደ ዕድል ሆኖ እኛ የመጨረሻው ዳቦ ነን፡፡
ወጣቱ መልካም ተኩላ ለጋራ ጥቅማቸው የሚታገሉትን ኢትዮጵያውያን ልቦችን እና አእምሯቸውን ለመማረክ እና ለማሸነፍ በግስጋሴ ላይ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሙሉ በሙሉ ጊዚያቸውን እና ኃይላቸውን ሰውተው በብልጽግና ፓርቲያቸው አማካይነት ኢትዮጵያን ከድህነት አዘቅት ውስጥ መንጥቀው በማውጣት ወደ ከፍታ ቦታ አንደሚያሸጋግሯት ክልቤ እና ከአእምሮየ ያለምንም ጥርጥር ሙሉ በሙሉ አምናለሁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለወደፊቷ ኢትዮጵያ አለኝታ ለሆኑት ወጣቶች ህልውና ዘመቻ በማካሄድ ላይ ለመሆናቸው አምናለሁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለመጭው ትውልድ ሸክም የሆነውን ኃላፊነት እንደተሸከሙ አምናለሁ፡፡ ኢትዮጵያን ወደፊት ለማራመድ በኋላ መስታወት አይመለከቱም፡፡
ጥቂት ሀገሮች “የጀግኖች ምድር እና የነጻዎች ቤት” (land of the fee and home of the brave) በማለት እራሳቸውን በኩራት መንበር ላይ ያስቀምጣሉ፡፡
እኔ በግሌ ደግሞ ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት “የሰላም፣ የብልጽግና እና የነጻነት ምድር” በመባል በዓለም እንደምትታወቅ ነገ ጸሐይ ትወጣለች የማለትን ያህል እርግጠኛ ሆኘ መናገር እንደምችል አውቃለሁ፡፡
በጊዜ ሂደት ቀስቃሽ የሆነ የተወሰ ስነ ግጥም አስባለሁ፡፡
“ያልተጓዝንበት መንገድ” በሚል ርዕስ ከሮበርት ፍሮስት የግጥም ስንኞች በመዋስ ለኢትዮጵያ ወጣቶች ይጠቅማል በሚል እሳቤ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡
እውነቱን ተናገር አውጥተህ ከልብህ፣
ከዘመን ዘመናት ለተቆለለብህ፣
ግፍና መከራ ቤቱን ለሰራብህ፡፡
ሁለት መንገዶች የተመሳቀሉ፣
ኢትዮጵያን ለመውሰድ ደፋ ቀና ሲሉ፣
ረዥሙ መንገድ ጣጣ የበዛበት፣
እሾህ አሜከላ የተንሰራፋበት፣
አቋራጩ መንገድ ለጉዞ ተስማሚ፣
ሰላም ብልጽግናን ዕድገትን ፈላሚ፣
ነጻነትን ሳቢ ስህተትን አራሚ፣
ለቀጣዩ ትውልድ እድገትን አላሚ፣
ተመራጭ ይሆናል ለኢትዮጵያ ህላዊ፡፡
ሁላችን ባንድነት እጅ ለእጅ በመያያዝ፣
ለእድገት ብልጽግና ለሰላም እንጓዝ፣
ፍትህ እኩልነት ነጻነት ይታወጅ፣
እድገት ብልጽግና ፍቅር እንዲደረጅ፣
የጀግኖችን ሀገር ኢትዮጵያን እንዲዋጅ፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም