ዘመነ መንደርተኛ ! (ክፍል ሁለት – 22-9-2018)
ብስራት ኢብሳ (ሆላንድ)
የጎሳ ፌደራሊዝም የመጨረሻው አስከፊ ገጽታ ላይ ደርሰናል!
መንግሥታዊ እውቅና ተሰጥቶት ሕዝብ እያጫረሰ ያለው የጎሳ ፌደራሊዝም፣ ከሕ-ገመንግሥቱ ባስቸኳይ እስካልተወገደና ወደፊትም ዘርንና ኃይማኖትን መሠርት አድርገው የሚደራጁ ፖለቲከኞችን ወደ ሥልጣን እንዳይወጡ የሚያግድ ደንብ ባስቸኳይ እስካልወጣ፣ በሀገራችን እየተጀመረ ያለውን አስከፊ እልቂት ማስወገድና እንደ ሀገር መቀጠል አንችልም!
ይህ ሕዝባዊ የመፈናቀል ቀውስ፣ በሩዋንዳ ወይም በሱዳን ሳይሆን በሀገራችን ከተጀመረ ቆይቶ እየባሰበት ነው!
በቅርቡ በአዲስ አበባና ባካባቢዋ የደረሰው እልቂትና ስደት፣ ላለፉት ዓመታት በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎችና ወገኖቻችን ላይ በተደጋጋሚ የደረሰ፣ በፍጥነት እያደገ፣ እየሰፋና ስር እየሰደደ ያለውን እውነታ፣ የአክራሪ ብሔረተኛ መሪዎች ሰሞኑን ሊያስተባብሉና ሊሸፋፍኑ እንደሚጥሩት መሆኑ ቀርቶ፣ እውነቱ እንኳን ተነግሮ መፍትሄ ለመፈለግ ያለን ጊዜ በጣም አጭር ነው፡፡ ይህ አይነቱ አስተያየት፣ በጎጥ ሃረጋቸው ስም ሥልጣን ላይ ተንጠላጥለው ለመቆየት የሚፈልጉትን ዘረኞች እንደማይመች፣ እነ ጆሃር መሃመድና መሰል ተከታዮቹ በተደጋጋሚና በግልጽ ነግረውናል፡፡
ሥልጣን ከእጃቸው ያመለጣቸው ወያኔዎቹም ሆኑ፣ በዘር ተደራጅተውና “ተራችን ነው” ብለው ሥልጣን ለመያዝ በጉጉት ላይ የነበሩት አክራሪ ብሔረተኞች፣ ሁለቱም ክፍሎች የአቢይን አስተዳደር ለማደናቀፍ በግልጽና በስውር ትብብር እያደረጉ ችግር እየፈጠሩ መሆኑን ያደባባይ ሃቅ ነው፡፡ ምናልባትም በሹክሹክታ እንደሚነገረው፣ በትብብር እስከ መንግሥት ግልበጣ ሄደው ሥልጣን ሊከፋፈሉ ይችላሉ፡፡
የትብብራቸው ዋና ዓላማ፣ ለየግል ለ እቅዳቸው ግንባር ፈጥረውና ተናበው፣ በነአቶ ለማና አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ፈር ቀዳጅነት የተጀመረውን በጎ እንቅስቃሴ፣ ወደ ሽብርና እልቂት (ሰሞኑን እንደታየው) ቀይረውት በሚፈጠረው ክፍተት፣ የየራሳቸውን የተደበቀ አጀንዳ በሕዝባችን ላይ ለመተግበር ነው፡፡
እነዚህ ጠባብና የአክራሪ ብሔርተኛ መሪዎ፣ በተለያየ የማስመስያ ሽፋን፣ ወጣንበት በሚሉት ማኅበረሰብ ስም እየማሉና እየተገዘቱ ዋና ፍላጎታቸውን ይደብቁን እንጂ፣ ካለፈው ታሪካቸውም ሆነ፣ አሁን በተግባር ከምናየው መረጃ፣ ተሻግረው መድረስ የሚፈልጉበት ዋናው የፖለቲካ ግባቸው፣ የአንድን አክራሪ ብሔርተኛ ድርጅት የበላይነትን በሀገራችን ለማስፈን ሲሆን፣ የተወሰኑት ደግሞ፣ ተጨቁኗል በሚሉት ማኅበረሰብ ሽፋን፣ አክራሪ ኃይማኖታቸውን በሀገራችን ምድር ለማስፋፋት ነው፡፡
(ስለኃይማኖት ሳነሳ፣ ለዘመናት ተከባብረውና ተጋግዘው ክፉና ደጉን ጊዜ አብረው ሲያሳልፉ ለኖሩትና ላሉት ባህላዊ የክርስትናንና እና የዕስልምናን ተከታይ ወገኖቻችንን አይመለከትም!)
(እንዲሁም የራሳቸውን ተጽእኖ ለማሳደር የሚፈልጉ የውጪ ሀገር መንግሥታት፣ ለራሳቸው ዘለቄታዊ ጥቅም ብለው በተለያየ መንገድ በማተራመሱና ቀጣይ መሪዎቻችንን በማማረጡ ሚና የሚያመቻቹትን እቅድ፣ የዲፕሎማሲ፣ የመሳርያ፣ የገንዘብ ድጋፍና ውስጥ ለውስጥ ከሕዝብ ጀርባ የሚያካሂዱት ሎቢ ሳይዘነጋ፡፡)
እነዚህ የጋራ ዓላማ ያላቸው የለውጥ እንቅፋቶች፣ እስካሁን ትግላችንን ባዳከመው “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” አካሄድ ለጊዜው ይስማሙ እንጂ፣ ቦኋላ አንድ ወንዝ ሳይሻገሩ እንደሚጣሉ ግልጽ ነው፡፡ እስከዛው ድረስ ግን ብዙ ነገር ያበላሻሉ፡፡ ይህ በመርኅ ላይ ያልተመሠረተ “ኅብረት” ዘለቄታው ግብ የሌለው ያጭር ጊዜ ድራማዊ ትብብር፣ የተለያየ ማኅበረ-ሰብን እንወክላለን በሚሉ ምሁራኖች በተደጋጋሚ በተግባር እንደ ፖሊሲ ይዘውት ሲጠቀሙበት ታይቷል፡፡ የእንደዚህ አይነት ሰይጣናዊ ኅብረት ውጤት ብዙ ጊዜ አጠቃላዩን የሕዝብ ትግልን ከማዳከምና ከመጎተት ያለፈ እርባና እርባና ኖሮት አያውቅም፡፡ የፈለጉበት ቦታ ሳይደርሱ ብዙ ጊዜ መንገድ ላይ ተጠላልፈው ይወድቃሉ፡፡
የሕዝብ ፍላጎትና የጠባብ ዘረኛ ምሁራን ዓላማ የተለያየ ቢሆንም፣ እነዚህ አክራሪ ብሔርተኞች፣ ሁኔታው እስከሚመቻችላቸው የሕዝብን ጥያቄ የደገፉ እየመሰሉ በሚነሳው ማንኛውም ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እራሳቸውን በመቀላቀል፣ የትግሉን የጉዞ አቅጣጫ ወደሚፈልጉት መንገድ ለማስቀየር አድፍጠውና ተግተው ይሰራሉ፡፡ ብዙ ጊዜ አቋማቸውን እንደ እስስት እየቀያየሩ፣ ሁኔታዎች የተመቻቸ ሲመስላቸው፣ በቅርቡ እንዳየናቸው እንደ ጆሃር መሃመድ፣ ጸጋዬ አራርሳ የመሳሰሉት ሃላፊነት የጎደለው ቅስቀሳ ሲያሰራጩ አዳምጠናል፡፡ እንደ እነ በቀለ ገርባ አይነቶቹም ለመላው ሕዝባችን የቆሙ መስሎን፣ ሲታሰር ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ሕዝብ እንደዛ እንዳልታገለለትና እንዳልዘመረለት፣ ለተደበቀ ዓላማው የተመቻቸ ሁኔታ የቀረበ ሲመስለው፣ እንዴት ወደ አንድ ጥንፍ ተገልብጦ የታገለለትን ሕዝብ ውለታ ክዶ፣ ያስተላለፋቸው መልእክት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለቀውሱ ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህም ለደረሰው ጥፋትና ላስከተለው ጠባሳ፣ ምንም አይነት የመግለጫ ጋጋታ ለማስተባበል ቢደረደር ሁኔታውን ወደነበረበት አይመልሰውም፡፡
ባጠቃላይ አክራሪ ብሔረተኛነት እከሌ ከከሌ ሳይባል ከየትኛም ማኅበረሰብ ቢጀመር አግላይ እና ጸረ ዲሞክራሲ መሆኑ እየታወቀ፣ የተወሰነ ዘር ብቻውን ተደራጅቶ ሥልጣን ቢይዝ፣ ከራሱ ውጪ ያሉትን ሁሉ አቅፎ ብዙሃኑን ወደ ዲሞክራሲ ያሸጋግራል የሚል ቅዠት መስማት እየተለመደ ሄድዋል፡፡ ምሁሩ ወደ ስልጣን ለመውጣት ስለሚረዳው፣ መጣሁበት በሚለው ማኅበረ-ሰቡ ላይ ተንጠላጥሎ የሚያስጠብቀው ጥቅም ምናልባት “የኔ” ወይም “የኛ” ለሚለውን እንጂ ስለሌላው ግድ አይኖረውም፡፡ ለሕዝብ የቆሙ ያስመስሉ እንጂ ዋናው ፍላጎታቸው ሥልጣንና ጥቅም ነው፡፡
ቋንቋንና ዘርን መሠረት ያደረገ ፌደራሊዝም፣ በዘር መከፋፈል፣ ብሔራዊ የአንድነት መንፈስ መዳከም፣ በሕዝብ መሃከል የተገነባውን አንድነት የሚያላላ፣ የግለሰብ መብትን የሚያሳንስና ለቡድን ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ሀገርን የመገንጠል ሁኔታ የሚያመቻች፣ እንድንቃቃር፣ እንድጨካከን፣ እንዳንተማመን፣ ግላዊነት፣ ስግብግበትና በጎ ለማይመኙልን የአካባቢው ጠላቶቻችን መመቻቸት፣……ወዘተ ብሎ ብዙ ምክንያቶች መጨመር ይቻላል፡፡ ለሃያ ሰባት ዓመታት በጎሳ ፌደራሊዝም ስም ወደ ሥልጣን የወጡት፣ የጥቅም ተጋሪ ቡድን ፈጥረው ሕዝብን በማታለልና፣ እርስ በእርሱ አጋጭቶ በማራራቅ፣ እራሳቸው ቱጃር ሆነው ሥልጣናቸውን አራዘሙበት እንጂ፣ ለሀገራችንም ሆነ ለጠቅላላው ሕዝባችን አልጠቀመንም፡፡
ይህ የጎጥ ፌደራሊዝም ባለፉት ዓመታት አንድነታችንን አናግቶና ኅብረታችንን አላልቶ አክራሪዎች ሥልጣን ላይ እንዲቆዩ የረዳው፣ አንዱን ማህበረ-ሰብ በሌላው ላይ በማነሳሳት፣ ኦሮሞውን በሶማሌ፣ አማራውን በቤኒሸንጎል፣ ሲዳማውን በኦሮሞ፣ ትግሬውን በአማራው …ወዘተ ላይ እያዘመቱ ነበር፡፡ ያስከተለው የሕዝብ እልቂት፣ የንብረት መውደምና መፈናቀል ውጤት፣ ከ 3.6 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ እንደተሰደደ፣ የሀገርና ዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አረጋግጠዋል፡፡ በዚህ የእርስ በርስ ግጭት በተፈጠረ መፈናቀል የተገኘው አሃዝ፣ በቅርቡ ከዓለም የአንደኛ ደረጃ ላይ አስቀምጦናል፡፡ ይህን ያህል የሕዝብ እልቂት፣ የንብረት መውደምና ተፈናቅሎ የተሰደደው ወገን ብዛት በታሪካች ሰምተነውና አይተነው የማናውቀው ዘርን መሠረት ባደረገ ፌደራሊዝም ምክንያት ነው፡፡
ይህንን እውነታ፣ “ተራችን ነው” ብለው በወያኔ ጫማ ውስጥ ተተክተው፣ በተመሳሳይ መንገድ ሕዝባችንን እያጋጩ የመቀጠል ህልም ያላቸው ጆሃርና መሰል ተከታዮቹ ይቀበላሉ ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም ሰሞኑን በተደጋጋሚ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ወያኔ ካርቀቀላቸው ሕገ-መንግሥት አንድም ቃል እንዳይቀየር በማለት አንዴ ሲፎክሩ ሌላ ጊዜ ሲማጸኑ ተሰምተዋል፡፡ ወያኔን በራሳቸው መተካት እንጂ የሥርዓት ለውጥ ካደረጉ፣ እነሱን ወደ ሥልጣን የሚያወጣ መሰላል ስለሚሰበርና በሰፊው ሕዝባችን መሃል ተወዳድረው ለማሸነፍ ዕድሉን ስለሚያጠብባቸው፣ የወያኔን መንገድ በመከተል፣ ተሰርቶ የተቀመጠን መዋቅር ተረክቦ ምንም ሳይቀየሩ መቀጠሉ ያዋጣናል ብለው ያምናሉ፡፡
የጎሳ ፌደራሊዝምን የሚቃወሙ በሙሉ አሃዳዊ መንግሥትን ብቻ እንደሚፈልጉ አድርገው ተከታዮቻቸውን እያታለሉና እያስፈራሩ፣ ሌሎች የተለያዩና ምናልባትም ዘርንና ቋንቋን መሠረት ያላደረጉ ብዙ የተሻሉ፣ ሕዝባችን ከሚኖርበት መልካዓምድራዊ አሰፋፈርና ታሪክ ጋር ሊስማሙ የሚችሉ አማራጮች እንዳሉ ወይም እንዲጠኑ አይፈልጉም፡፡ አብዲ ኢሌ፣ በዶክክተር አቢይ አመራር እየተሞከረ ባለው በመቻቻል ወደ ዲሞክራሲ በሚወስደው ባቡር ውስጥ ተደምሬ ገብቻለሁ ባለ ጥቂት ጊዜያት ውስጥ፣ የሰራው ወንጀልና የዘረፈው ገንዘብ ተደርሶበት ሲጠየቅ፣ “የሶማሌን ክልል ለመገንጠል ሕገ-መንግሥቱ ይፈቅድልኛል” ብሎ፣ በመሪዎቻችን ብልህነት፣ ክልሉም እንዳይገነጠል፣ እሱም ከፍርድ እንዳያመልጥ ችግሩን በዘዴ ፈተውታል፡፡ ይህ አይነት ችግር ነገ ሌላው የፌደራል መንግሥት ውስጥ አይከሰትም ብሎ ማመን አውቆ መካድ ካልሆነ? የዋኅነት ነው፡፡ በቅርቡም ባንዳንድ የትግራይ ኢሊቶች አስተያየት፣ እነሱ በሚፈልጉት መንገድ ነገሮች ካልሄዱ፣ ትግራይን ለመገንጠል ያስፈራሩ የነበሩና አሁንም ያሉ ሳይዘነጋ፡፡
ሰሞኑን እንደ ጃሃር ያሉ በተቃዋሚ ጎራ ተሰልፈው የነበሩ አክራሪ ብሄርተኞች፣ ሕገ-መንግሥቱን “ሕገ አራዊት”፤ “የወያኔ የጫካ ሕገ-መንግሥት” መሻሻል አለበት፣ መቀየር አለበት…..ወዘተ እያሉ ይቀሰቅሱ እንዳልነበሩ፣ ወደ የሥልጣን ወንበሩ የቀረቡ ስለመሰላቸው፣ “ሕገ መንግሥቱ አይቀየርም፣ አይሻሻልም”፣ እያሉ ካሁኑ መፎከር ጀምረዋል፡፡ እውነታቸውን ነው! ሕዝብ እየከፋፈለ የሚያጫርስ! ሕዝብ ተስማምቶ አብሮ ቆሞ እንዳይቃወማቸው የሚረዳ! እንደ አብዲ ኢሌ ተጠያቂነት ሲመጣ ለመገንጠል በር የሚከፍት! የፌደራል መንግሥቶችን በየተራ ኮርቻ እየቀያየሩ ተቃውሞ በሚያነሳ ላይ በቀላቸውን የሚወጡበት፣ እንደ አለንጋቸው ተጠቅመው ሌላውን የፌደራል መንግሥት የሚቀጡ በት፣ (አብዲ ኢሌን እንዴት የኦሮሞ ወገኖቻችንን ታዞ እንዳስጨረሰና እንዳፈናቀለ…..ወዘተ) አይነት የአሽከር ጓደኛ የሚያስገኝ ፌደራል መንግሥት ለምን አይኑር? አብሮ የሚኖርን ሕዝብ፣ ንብረት፣ ቁሳዊ፣ ኅሊናዊ፣ ታሪካዊ፣ ሞራላዊ…..ወዘተ፣ በራሱ ጥረትም ይሁን በሂደት ጊዜ ያጎናጸፈውን ባለቤትነት ፣ በክልል፣ በቋንቋ፣ በፌደራል፣ በደም ትስስር…ወዘተ ሽፋን ከማንም ተዘርፎና ህልውናቸውን ክዶ፣ በአንድ ምሽት ሕግ በማውጣት፣ የበፊቱን የሚደመሰስ ሕገ መንግሥት? ወይስ ሕገ አንባገነን? ወያኔ ድሮ የኦሮሞ ምሪዎች ማፈንገጥ ሲጀምሩና ሊቀጧቸው ሲፈልጉ ናዝሬት፣ ሌላ ጊዜ የአንድነት ክፍሉ (ቅንጅት) ሳይመቻቸው ሲቀርና ሊበቀሏቸው ሲፈልጉ አዲስ አበባ የኦሮሞ ዋና ከተማ ናት እያሉ እያላገጡ የሚያወጡት ሕገ መንግሥት፣ እውነትም ለምን የነጆሃር ተራ ሲደርስ ይቀየር?፡፡
እነዚህ ሰዎች ገና የሥልጣን ቁሌቱ ሲሸታቸው፣ “ኦሮሞ ፎቢያ”፣ የቀድሞ ሥልጣን ናፋቂዎች፣ ዱርዬዎች፣ ወሮበሎች፣ ኦሮሞ በቁጥር ብዙ ስለሆነ ምርጫ የሚፈሩት…..ወዘተ እያሉ የተለየ አስተሳሰብ ያለውን ካሁኑ መግጨት ከጀመሩ፣ ነገ በወገኔ ኦሮሞ ሕዝብ ስም ስልጣን ላይ ቢወጡ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ፣ መገመት እንደ ዶክተር ኅዝቅኤል የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር መሆን የሚያስፈልገው አይመስለኝም፡፡
ለያሃ ሰባት ዓመታት ሀገራችንን ለመበታተን በዘር ፖለቲካ የተገዘገዝነው ሳያንሰን፣ ይባስ ብሎ አዲስ አበባንም፣ ወጣቱ እንዳይተባበር በዘር ተከፋፍሎ አንዲደራጅ በመገፋፋት ተግተው መሥራት የጀመሩ እንዳሉ እየተሰማ ነው፡፡ ይቺን ብቸኛ የተረፈችንን የሁላችንም ከተማ፣ በጎጥ ሊያተራምሱ የተነሳሱትንም ወጣቱ ተደራጅቶ ሊያሳፍሯቸው ይገባል፡፡ አዲስ አበባ ሁሉም አይነት ዘርና ዕምነት ተከባብሮ፣ በክፉም ሆነ በደግ ለረዥም ዘመናት ተደጋግፈው የሚኖሩባት፣ የሀገራችን ዋና ከተማ፣ የአፍሪካ ማኅበር የተመሰረተባት መዲና፣ ብዙ ዓለም አቀፋዊ ተቋሞች የሚስተናገዱባት ማዕከል፣ የመላው ኢትዮጵያ እንጂ፣ የአንድ የተወሰነ ማኅበረ-ሰብ ወይም ቡድን ንብረት ልትሆን አትችልም፡፡
የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም ሆኑ በዙርያዋ ያሉት ህዝቦች፣ ለዓመታት ቤታቸው በግሬደር እላያቸው ላይ ሲፈርስ፣ ንብረታቸው ሲዘረፍና ከኖሩበት ስፍራ በልማትና በክክል ስም ካለፈቃዳቸው በአገዛዙና የጥቅም ተካፋይ ወኪሎቻቸው ጭምር ንብረታቸው በጠራራ ፀሐይ ሲቀሙ ማንም የተከራከረላቸውና ችግራቸውን ያሰማ የፖቲካ ቡድንም ሆነ የመንግሥት አካል ስላልነበር የጥቃት ዓላማ ሲሆኑ ኖረዋል፡፡ አሁን ደግሞ ከዛ በባሰ ህልውናቸውንም በሚፈታተን መልኩ፣ አዲስ አበባ ከመላ ሀገሪቱ ተነጥቃ ለአንድ ማኅበረ-ሰብ ንብረት እንድትሆን እያመቻቿት ነው፡፡
በትንሹ ከስድስት ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝብ የሚኖርባት ታላቋ የአፍሪካ ከተማችን አዲስ አበባ፣ ለሁሉም ወይም ከሁሉም ጋር እንደኖረችው ትቀጥላለች እንጂ፣ እንደ የጭሰኛና የባላባት ዘመን፣ “ልዩ ጥቅም” “ሲሶ” “ድርቦ” የሚሉ ኋላ ቀር የይገባናል አስተሳሰብ ያላቸው የአክራሪ የኦሮሞ ብሔረተኛ መሪዎች ፍላጎት ማሟያ መሆን አይገባትም፡፡ አዲስ አበባ ላዲስ አበቤዎች ሆና ፣ እንደማንኛውም ትላልቅ የዓለም ዋና ዋና ከተሞች፣ ነዋሪዎቹ የራሳቸውን አስተዳዳሪዎች የመምረጥ መብት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብም ቢሆን መላው ኢትዮጵያ ሀገሩ እንደሆነ እየታወቀና፣ ለሌላውም ኢትዮጵያዊ፣ የኦሮሞ ሀገርም ጭምር የጋራ መሆኑ እየታወቀ፣ አዲስ አበባን መርቆ ለኦሮሞ መስጠትና ጥገኛ ማድረግ ለምን አስፈለገ?
የኦሮሞን ሕዝብ ከቀረው ወገኑ “አዲስ አበባን ከነፎቆቹ ወስደን ባለ እርስት ልናረግህ ነበር፣ ነፍጠኞቹ እንቢ አሉ፣ በርትተህ ታገላቸው…..ወዘተ” ብላችሁ ምስኪኑ ወገናችንን ያልሆነ ተስፋ በመስጠት በዙርያው ጠላት እንዲበዛበት ለማድረግና፣ ለጊዜያዊ ማታገያ መፈክርነት ለመጠቀም ካልሆነ በስተቀር፣ መፈክሩም፣ ሕልሙም፣ ቅዠቱ፣ ምኞቱም ለተከበረው ኦሮሞ ወገናችን ሳይሆን በስሙ ለመነግድ ስለሆነ የሚጠቅመው፣ ከአዲስ አበባ ላይ እጃሁን አንሱ!
ይሄ አዕምሮዋችሁን የከለለው “የጎሳ ክልል” በ21ኛው ክፍለ ዘመን፣ ቴክኒዮሎጂው ዓለምን በሰከንድ እየገናኘ፣ ድንበሮች እየፈረሱ ወደ አንድ ጠንካራ የኤኮኖሚና የፖለቲካ ማዕከል እየተቀራረቡ ሲዋሃዱ እያያችሁ፣ ትላንት ዶክተር አቢይ፣ ከኛ አልፈው የአፍሪካን ቀንድ ሀገሮች ለማስተባበር ራዕያቸውን ነግረውን ምነው እናነተ ባላችሁበት ቆማችሁ ቀራችሁ?
የአዲስ አበባ ወጣቶችም ሆኑ ነዋሪዎቹ፣ ይህንን በመሳሰሉ ጉዳዮችና በቅርብ እንደተከሰተው አይነት አሳዛኝና አሳፋሪ እልቂት በአካባቢውና በከተማው ውስጥ ዳግም እንደማይከሰት ዋስትና ስለሌላቸው፣ ካለፈው ችግር ተምረው፣ የእራሳቸውንና የከተማቸውን ደህንነት፣ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ተደራጅተው መብታቸውን ለማስከበር መንቀሳቀስ መጀመር መብታቸው ብቻ ሳይሆን አጣዳፊ ተግባርም ነው፡፡
በየሰፈሩ ያለው ታዳጊው ወጣት በየግሉ ከሚከተለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ባሻገር፣ እንደ ወጣት በእስፖርት፣ በባሕል፣ በአንዳንድ የልማትና የበጎ ሥራ ተግባራትም ጭምር ለማከናወን እንደ ኅብረ-ብሔራዊነታቸው በኢትዮጵያዊነት መንፈስ በየአካባቢያቸው ቢደራጁና አንድ ማዕከል ቢፈጥሩ፣ ለብሔራዊ አንድነታችን ተጨማሪ እገዛ እንደሚያደርግ አምናለሁ፡፡
ለዚህም ዓይነት በጎ እንቅስቃሴ፣ ማንኛውም ሀገሩን የሚወድ ዜጋም ሆነ፣ በመላው ዓለም የሚገኙ የከተማዋ ቀደምት ነዋሪዎች ከጎናቸው ቆመው እንደሚተባበሩ ግልጽ ነው፡፡ ይህ አይነት አደረጃጀት ኅብረ ብሔራዊ በሆኑ ትላልቅ ሌሎች ከተማዎችም ቢስፋፋና፣ በቅርቡ እስንደምንሰማው ከሌላ አካባቢ ካሉ ወጣቶች ጋር የሚያገናኛቸው ድልድይ ዘርግተው በጣና ሐይቅ (እንቦጭ) እንደታየው ትብብር፣ በችግር ጊዜ ለመረዳዳትም ሆነ፣ ይበልጥ በሕዝብ መሃከል ያለውን ኅብረት፣ ተቀራርቦ መረጃ እየተቀያየሩ ልምድ ለማዳበር ይጠቅማል፡፡
በተረፈ ነፃነትም ይሁን ዴሞክራሲ ከሃላፊነት ጋር የተቀናጀ ሲሆን እንጂ፣ ሰሞኑን እንደታየው፣ የባንዲራ ውድድር፣ የደጋፊን ብዛት የማስመስከር ፉክክር “ትርዒት”፣ በሥርዓትና በጥንቃቄ በሁሉም ወገን ታስቦበት፣ ቀውስ ቢፈጠር ሊያስከትል ከሚችለው አዳጋ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የፖሊስና የጸጥታ አካላት በበቂ ባልተዘጋጀበት ሁኔታ የተካሄዱት ሰልፎችና አላስፈላጊ ፉክክሮች ምክንያት የደረሰው፣ ሞት፣ ዝርፊያና መሰደድን ነው፡፡ አዲስ አበባችንም የተጋለጠችው ለሀገር ወዳድና ለነፃነት ናፋቂዎች ብቻ ሳይሆን፣ ህብረ-ብሄራዊ መስለው በማናቸውም ዓይነት ወደ ሥልጣን ለመውጣት የሚያስቡ ድርጅቶች፣ ለጽንፈኞችና ለጠባብ ቡድኖችም ጭምር መፈንጫም ሆና ነበር፡፡
በአንድ በኩል እነ ዶክተር አቢይ የዲሞክራሲ ነጻነትን ለተጠማ ሕዝብ ለማቋደስ የሚያደርገውን ሙከራ የሚያስመሰግነው ሆኖ፣ በሌላ በኩል ይህንን በጎ ጅምር ለማደናቀፍ ምክንያት የሚፈልልጉ፣ ተደራጅተው በቂ ጉልበትና ገንዘብ ያላቸው ክፍሎች አሰፍስፈው በሚጠብቁበት ወቅት፣ ሁኔታውን ያላገናዘበ ዝግጅት አለማደርግ ሃላፊነት ይጎለዋል፡፡ የዲሞክራሲ ባህልን በቅጡ ገና ባላጣጣምንበት ደረጃ፣ ለብዙ ዓመታት ከሠላማዊ ኑሮ፣ “በነፃ አውጪነትና” ለነጻነት ብለው፣ ለተለያየ ዓለማ ጽንፍ ቆመውና በብዙ መንገድ ተሸሻክረውና ተራርቀው የነበሩ ወገኖችን፣ በዚህ አይነት የፉክክር ሜዳ ውስጥ ካለ የጨዋታ ሕግ፣ ዳኛና አራጋቢ ማስጀመር አደጋው ከዚህም የከፋ አለመሆኑ ፈጣሪ ይመስገን ማለቱ ይበጃል፡፡
በምርጫ የዲሞክራሲያዊ ሥራዓትን መለማመድ ይቻላል እንጂ ዲሞክራሲን በሃይል ከላይ ገፍቶ ማስፈን አይቻልም፡፡ ወይም በዲሞክራሲ የተመረጠ ሁሉ ዲሞክራሲን ያሰፍናል ማለት አይደለም፡፡ በዚህ የዲሞክራሲ ሥርዓት ሂደት፣ ባህሉንም ጭምር እየተለማመድን መሠረቶቹን በመጣል ዲሞክራሲ የሚሰራበት ማኅበረሰብ ደረጃ እንደርሳለን፡፡ በውጪ ሀገር ጭምር እየኖርን፣ ስለ ዲሞክራሲ ግንዛቤና የአመለካከት ጥራት ችግር ጭምር እንድዳለብን እየታወቀ፣ ከውጭ ስለሄድን መፍትሄም ጭምር በቦርሳ ይዘን ሀገር ውስጥ እንደገባን ማስመሰል የለብንም፡፡ ሥልጣ ለመያዝ ያቆበቆቡ፣ ከጠባብ ድርጅታዊ የፖለቲካ ዓላማቸው ባሻገር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ደህንነትና የወል ጥቅም ግድ የሌላቸው ህብረ-ብሄራዊ ነን የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶችም ጭምር፣ በችግር ውስጥ የሚኖርን ወጣት እነሱ በሚያደርጉት ፉክክር ውስጥከማስገባት ራሣቸውን ቢገድቡ ይመረጣል፡፡
ለማጠቃለል አክራሪ ብሔረተኛነት፣ ቅጥ ያጣ ወገንተኛነት፣ ለራሱ ከሚገባው በላይ የሚጠይቅና የሌላውን መብት ማየት የማይችል፣ ሁሌ ወደኋላ እንጂ ወደፊት ማተኮር የሚሳነው ጨለምተኛ አካሄድ ነው፡፡ አንዳንዶቹም ትላንት ያስቀመጡትን “የኮሎኒና የታላቋ ኢምፓየር” የተሳሳተ አመለካከት ዛሬ ድረስ ከድኅረ ገጻቸው ላይ እንኳን አልቀየሩም፡፡ እንዳውም አዲስ ገቢዎች ሁሉ ተጨምረውበት ወደፊት በኦሮሞውና በአማራው ወጋናችን መሃል ጦርነት ሊያስቀሰቅስና የእርስ በርስ ግጭት ፈጥሮ ሀገራችንን ወደ መበታተን የሚወስደን መንገድ እየተከፈተ ይታያል፡፡
እነዚህ ሁለት ጽንፍ የቆሙ አክራሪ ብሔረተኞች፣ አንድ ትልቅ ሀገርና ሕዝብ፣ ለብዙ ዘመናት በበጎም ሆነ በከፉ አብረው እየወደቁና እየተነሱ ተዋህደው በጋራ የሚኖሩባትን ሀገር እየሸሹ “የእኛ” ብለው እራሳቸውን ወደ አሳመኑት መልካዓ ምድር ተሸምቅቀው፣ እያነሱ ያሉት ፍጹም ሗላ ቀር የሆነ የመሬት ይገባኛል ጥያቄ፣ አንዱ በሌላው ላይ የሚደራረብ ከርታ እየሰሩ፣ ለነገው ግጭት እያመቻቹልን እንዳሉ የሚወራው እሳት ዳር ብቻ ነው፡፡ ይህንን እየሰሙና እያዩ እንዳላወቀ ለመሆን፣ ንቆ ለመርሳት መሞከርና ችግሩ እንደሌለ መሸፋፈን ፣ አደጋውን እንደ ቆላ ቁስል ውስጥ ለውስጥ ከማመርቀዙም በላይ፣ እንድንበታተን ለሚፈልጉ የውስጥም ሆነ የውጭ ጠላቶቻችን እንዲጠቀሙበት ዕድልና ጊዜ መስጠት ይመስለኛ፡፡
እዚህ አሳዛኝ ውሳኔ ላይ ለመድረስ፣ ምናልባት ከፍርሃትና ጥርጣሬ የመነጨና፣ “የሚፈሩት ማኅበረ-ሰብ ችግር ቢፈጥር ቅድመ ዝግጅት ለማደረግ ነው” እንኳን ብለን በበጎ ለማየት ብንሞክር፣ እራሱ እንደዚህ አይነት የመጠራጠርና የአለመተማመን ስሜት የፈጠረው፣ ከላይ የጠቀስኩት ቋንቋንና ዘርን መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም ሥራ ላይ መዋል ከጀመረ እንጂ ድሮ እንደዚህ አይነት ስሜቱም ሆነ ፍላጎቱም አይታሰብም ነበር፡፡ ሀገራችን በተጀመረው አዲስ መንገድ ሳትሰናከል ወደ ተሻለ ደረጃ እንድትደርስ፣ በማንኛውም ክፍል የሚኖር ሕዝባችን ሃላፊነትም ጭምር ስላለበት እንደነዚህ አይነት አደገኛ አካሄዶች ሲጀመሩ፣ ሁሉንም እኩል መውቀስና ለሀገር የሚጠቅም የተሻለ አቅጣጫ መሳየት ይበጃል እንጂ፣ ችግሩ እንደሌለ ወደ ጎን መግፋት፣ ካርታውን በተዘዋዋሪ ተቀብለን እየለመድነው መሄድ ነው፡፡
ምናልባት ይህንን ተከፋፍሎ የመገነጣጠል አደጋ ለማስወገድ፣ ይህንን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ደግፈው እየተናበቡና እየመሩን ያሉት የገዱና የለማ ቲም፣ አድማሳቸውን በማስፋት፣ እንደ እነሱ ያሉ ለውጥ ፈላጊዎችን ከየማኅበረሰቡ አሰባስበው፣ በውስጣቸው የሚያከሩትን እሺ ካሉ አሳምነውና ደምረው፣ እንቢ ካሉም ቀንሰውና እራሳቸውንም ከነዚህ አክራሪ ብሔርተኞች አርቀው፣ አንድ ጠንካራ ኅብረ-ብሔራዊ ፓርቲ ቢመሰርቱ? ሀገራችንን ከአደጋ ያድናሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህንን ካደረጉ የሀገራቸው ኅልውና እንዲቀጥልና ሕዝባቸው እንዳይለያይ የሚፈልጉ ሚሊዮኖች ከጎናቸው ይሰለፋሉ፡፡ ምናልባት አሁን የሥልጣን መሠረታቸውን ላለማጣት ውስጣቸው እውነቱን እያወቀ ይህን ሃቅ ቢያቅማሙ፣ ወደፊት ሀገር ሳይኖር ሕዝብ ስለሚበተን፣ አምርረው ሊያስቡበት ይገባል ብዬ ምኞቴን አስተላልፋለሁ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ! እኛም እንተባበረው!
ብስራት ኢብሳ (ሆላንድ) tebaber@gmail.com
የመጀመርያውን ዘመነ መንደርተኛ ላላገኛችሁና ማንበብ ለምትፈልጉ ከዚህ በታች ይጫኑ
http://almariam.com/wp-content/uploads/2016/11/Zemene-Mederegnanet-Bisrat-Ibssa.pdf