እጅ አዙር የስልጣን ዘዋሪዎች የለውጡን ሰዓት እጅ ወደኋላ ዝወራ ሙከራ በኢትዮጵያ !
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
ለ48 ዓመታት ከኢትዮጵያ ከተለየሁ በኋላ በአሁኑ ጊዜ ተመለስኩ፡፡
ኢትዮጵያ ለማሰብ ከምችለው በላይ ተለውጣለች፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ምንም ዓይነት አልተለወጠችም፡፡
አንድ የቀድሞ አባባል እንዲህ የሚል አንድ እውነታ አለው፡፡ “ነገሮች ሁሉ የበለጠ በተለወጡ ጊዜ የበለጠ እንደቀድሞው ሆነው ይቀራሉ፡፡” ወደፊት በምፅፋቸው ጦማሮቼ አእትዮያ ስላሳለፍኩት አስደናቂ ጊዜ አብራራለሁ።
ሆኖም ግን አንድ ፈፅሞ ያልተለወጠ ነገር አለ፡ የጨለማው ጎን ጦረኛ ኃይሎች በሰላማዊ ለውጣችን ላይ ጦርነት መክፈታቸው።
የጊዜ መሙያ እጀታውን ወደኋላ በመመለስ እንደገና በስልጣን ኮርቻ ላይ ፊጥ ለማለት እነዚህ ድሁር የጨለማው ጎን ኃሎች ያለ የሌለ ኃይላቸውን (በብልዮን የሰረቁትን ብር መሳርያ/ተገን አድረገው) በመፍጨርጨር ላይ ይገኛሉ፡፡
አሁንም ከጨለማው ምሽጋቸው ተደብቀው በርካታ የዜጎች እልቂቶችን በግንባር ቀደምትነት በማቀድ እና በማስፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡
አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያን በጎሳ፣ በኃይማኖት፣ በቋንቋ እና በክልል መከፋፈሉን ሌት እና ቀን አንደተራበ ጅብ ሲንከዋከዉ ይገኛሉ፡፡
የጨለማው ጎን ኃይሎች በመቀስቀስ እና በማነሳሳት የጎሳ በቀል፣ ብቀላ፣ የብቀላ ቅጣት ለመፈጸም እና የጦረኝነት ብቀላ ለማድረግ ማንኛውንም ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡
ማንዴላ መልካም ነገር እና ይቅርባይነት ብለው በሰየሙት እና አያቶቻችን እና ቅድመ አያቶቻችን ለዘመናት ሲጓዙበት በነበረው ጎዳና — መልካምነትና ይቅርታ — ላይ ኢትዮጵያ ዘለቄታዊ በሆነ መንገድ መጓዝ እንድትችል ሌት ከቀን እንሰራለን፡፡
የእኛ ቀደምቶች ኢትዮጵያ አንድነቷን ጠብቃ እንድትኖር የደም፣ የላብ እና የመከራ ህይወት መስዕዋትነትን ከፍለዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የጨለማው ጎን ኃይሎች በሰላማችን ላይ ጦርነትን እስካወጁብን ድረስ ተመሳሳይ መስዋዕትነትን ለመክፈል ዝግጁዎች ነን እየከፈልንም ነው ፡፡
እኛ የሰላም እጆቻችንን በምንዘረጋላቸው ጊዜ እነርሱ በገጀራ አንገቶቻችንን ለማስቀላት ለወሮበላ ቅጥር ነብሰ ገዳዮች ገንዘብ ይከፍላሉ፡፡
እነርሱን ለማቀፍ እጆቻችንን በምንዘረጋላቸው ጊዜ በልቦቻችን ውስጥ ጩቤ ለመሰካት ይሞክራሉ፡፡
ከእነርሱ ጋር እጅ ለእጅ በመያያዝ ደስታ በተመላበት ወንድማዊ መንፈስ እንድንጓዝ ጥሪ በምናቀርብበት ወቅት ከኋላ ሆነው ይወጉናል፡፡
የኢትዮጵያዊነት ሰውነት በሚባል በአንድ የነጠላ ክር ዕጣ ፈንታ የተሳሰርን ሕዝቦች ነን የሚል አመክንዮ በምናቀርብላቸው ወቅት እነርሱ በዱላ ይመቱናል፣ ጭንቅላታችንንም ይፈልጡናል፡፡
የጨለማው ጎን ኃይሎች ትዕግስተኛነታችንን እንደ አቅምየለሽነት፣ ለሰላማዊ ሽግግር ያለንን ቁርጠኝነት እንደ ፍርሀት፣ ለብሄራዊ ዕርቅ ያለንን አቋም እንደ መሸሽ እና እንደ ባርነት፣ በእራስ የመተማመን እና ለሰብአዊ መብት መከበር ያለንን መልካም አስተሳሰብ እንዲሁም ቆራጥ ልብ ያለን መሆናችንን እንደ ደካማነት እና ምንም ዓይነት ነገር የማናደርግ እርባናቢሶች እንደሆን ዓይነት አድርገው ቆጥረውታል፡፡
እንዲህ የሚለውን እና ጊዜ የማይሽረውን ዘላለማዊ እውነታ መገንዘብ ተስኗቸዋል፣ “ጥንካሬ ከአካላዊ ብቃት የሚመጣ ጉዳይ አይደለም፡፡ ጥንካሬ የሚመጣው ከማይበገረው የዓላማ ጽናት ነው፡፡“
ማንም ቢሆን በመግደል፣ አካለ ጎደሎ በማድረግ፣ ዕልቂትን በመፈጸም እና ሰላማዊ ሰዎችን በማረድ የሕዝቦችን ልብ እና አዕምሮ መቆጣጠር አይችልም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለበርካታ ጊዜ ደጋግመው እንደተናገሩት “ተሸናፊዎች ብቻ ናቸው ሰላማዊ ሰዎችን የሚገድሉት፡፡”
ሆኖም ግን የጨለማው ጎን ኃይሎች የማቀድ፣ ተንኮል የመሸረብ፣ ደባ የመስራት፣ ሰይጣናዊ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ በገንዘብ የመርዳት፣ የማስተባበር እና በሰላማዊ ዜጎች ላይ ሰብአዊ ወንጆሎች እንዲፈጸሙ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ እንዲሁም ተዕግስታችን ተሟጥጦ ወደ ኃይል እርምጃ እንድንገባ እና ከጨለማው ጎን ኃይሎች ጋር እንድንቀላቀል እና እንድንሰለፍ ያነሳሳሉ፡፡
በተስፋ መቁረጥ አስተሳሰብ በየጊዜው በሚፈጽሙት ሰብአዊ እልቂት ሕዝቡ ለበቀል እንዲነሳሳ እና በኢትዮጵያ ውስጥ የጎሳ እልቂት የምጽዓት ቀን እንዲመጣ ለማድረግ እያሞኙን ይገኛሉ፡፡
ሆኖም ግን የጎሳ የእልቂት የምጽዓት ቀን በኢትዮጵያ በምንም ዓይነት መልኩ አይከሰትም፡፡ ኢትዮጵያ ሊቀለበስ በማይችል መልኩ በሰላም፣ በይቅርባይነት እና በብህራዊ እርቅ ጎዳና ላይ በመንጎድ ላይ ትገኛለች፡፡
የጨለማው ጎን ኃይሎች በጨለማው ምሽጋቸው እራሳቸውን ደብቀው የማይታዩ ጉዶች እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ፡፡
ምንም ዓይነት ድብቅ ነገር የለም፣ እነርሱ በጉልህ እና በግልጽ ይታያሉ፡፡
በጅግጅጋ፣ በቡራዩ፣ በጎንደር፣ በሞያሌ፣ በሀዋሳ፣ በወላይታ ሶዶ፣ በወልቂጤ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በወልቃይት ጠገዴ፣ በራያ እና አዘቦ፣ በጋምቤላ እና በአፋር ክልሎች እና በሌሎች በርካታ ቦታዎች የእጅ አሻራቸውን፣ የእጅ መዳፍ አሻራቸውን፣ የጣት አሻራቸውን እና የእግር ኮቲያቸውን ማየት እንችላለን፡፡
የመስከረም 17ቱ ዕልቂት፣
እ.ኤ.አ መስከረም 17 ቀን 2018 ዓ.ም የጨለማው ጎን ኃይሎች የፍጅት እና የዕልቂት የተውኔት ትዕይንታቸውን በአዲስ አበባ ከተማ ዳርቻ አካባቢ ላይ እውን አድርገዋል፡፡
አበል በጨለማው ጎን ኃይሎች የመክፈያ ሰነድ/payroll ላይ የተመለከተው ወሮበላ ቅጥር ነብሰ ገዳዮች እና ዘራፊዎች ከአዲስ አበባ ከተማ በስተሰሜን ምዕራብ በ15 ኪ/ሜ ርቀት ላይ በሚገኙት በቡራዩ እና በአሸዋ ሜዳ ከተሞች በሚኖሩ ህዝቦች ላይ ጎሳን መሰረት ያደረገ ጥቃት በመክፈት 65 ሰላማዊ ዜጎችን ገድለዋል፡፡
የጎሳ ጥቃት ሰለባ የሆኑት ሰላማዊ ዜጎች በስለት ተወግተው፣ በዱላ ተደብድበው ወይም በድንጋይ ተወግረው የተገደሉ መሆናቸውን ዘገባዎች ይገልጻሉ፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል የጎሳ ግድያዎች ታስቦባቸው እና ታቅደው የተፈጸሙ እንደሆኑ እና በአንድ የዕዝ ሰንሰለት ትዕዛዝ ሰጭ አካል/command post አመራር ስር የሚያገኙ ናቸው ብለዋል፡፡
ኮሚሽነር ዘይኑ ብቸኛው ትዕዛዝ ሰጭው አካል የቅጥረኛ (mercenary) ወታደራዊ ትዕዛዝ ሰጭ አካል ነው አላሉም፡፡
የዚህ ግድያ ጥቃት ዓለም አቀፋዊ እና ፈጣን ውግዘት ደርሶበታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰውን ይህንን ጥቃት “የፈሪዎች ጥቃት” በማለት ያወገዙ ሲሆን ይህም ጥቃት በሕዝቦቻችን አንድነት እና አብሮነት ላይ ያነጣጠረ መልዕክት በመሆኑ ተገቢውን ምላሽ እንሰጣለን ብለዋል፡፡
እንደዚሁም ሁሉ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ የኦሮሞ አንድነት ለነጻነት፣ የኦሮሞ አንድነት ግንባር፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ ፓርቲዎች ጥቃቱን በአንድነት ሆነው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አውግዘዋል፡፡
በሌላም በኩል የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሀማት ድርጊቱን በማውገዝ እንዲህ የሚል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡ “ይህ የወንጀል ጥቃት የኢትዮጵያን አመራር እና ሕዝቡን በአንድነት እንዲቆሙ እና ጥንካሬ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፣ ለለውጥ ጉዞው በጽናት እንዲቆሙ እና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥም ያደርጋል“ ብለዋል፡፡
በሚያስገርም ሁኔታ የጨለማው ጎን ኃይሎች ስለዚህ ጥቃት ጉዳይ ከአፋቸው አንዲትም ቃል ትንፍሽ ሳይሉ ቀርተዋል፡፡ የእነርሱ የጥቃት ሰለባ የሆኑት ንጹሀን ዜጎች የግፍ ዕልቂት ተፈጽሞባቸው ወደ መቃብር ሲወርዱ እንደ መቃብር ጸጥ ረጭ በማለት አልፈውታል፡፡
ግፈኛ ገዳዮች የእጃቻቸውን እስኪያገኙ ድረስ በሕዝቡ ውስጥ ተደብቀው ወንጀሎችን ሲሰሩ ይቆያሉ ይባላል፡፡
የጨለማው ጎን ኃይሎች ግን የትም ቦታ አልታዩም፣ እንደዚሁም ደግሞ ድሞጾቻቸው በቡራዩ ወይም በአሸዋ ሜዳ ላይ አልተሰሙም፡፡ ሆኖም ግን እነርሱ እየከፈሉ ባስፈጸሙት እልቂት፣ ሞት እና ውድመት በጨለማው ምሽጋቸው ሆነው በመሳቅ አሳልፈውታል፡፡
ቡራዩ እና አሸዋ ሜዳ ለጨለማው ጎን ኃይሎች ፍጹም ለሆነ ማዕበል ፍጹም የሆነ መደበቂያ እና ፍጹም የሆነ ጊዜ ነበሩ፡፡
ይህንን ቆሻሻ እና እርኩስ ድርጊታቸውን እውን ለማድረግ የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ለበርካታ ዓመታት የትጥቅ ትግል ሲያካሄዱ የቆዩት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራሮች (ኦነግ) የኃይል ድርጊትን በማውገዝ ወደ ሰላማዊ ውይይት ወደ ሀገር ቤት የሚገባበትን አጋጣሚ በመጠቀም ነበር፡፡
በቡራዩ እና በአሸዋ ሜዳ ጥቃቱ ከመፈጸሙ ከጥቂት ቀናት በፊት የጨለማው ጎን ኃይሎች በከተማይቱ የተለያዩ አካባቢዎች ወሮበላ ዘራፊዎችን በገንዘብ በመደለል እየከፈሉ በማሰማራት የህዝቦች ስስ ብልት በሆነው የኢትዮጵያ ባንዲራ ጉዳይ ብጥብጥ እና ሁከት በማስነሳት ዕልቂት እና ውድመትን የመደገስ ሙከራ አድርገዋል፡፡
ያ እርኩስ ጥረት ከፍጻሜ ሳይደርስ መክኖ ቀርቷል፡፡
የጨለማው ጎን ኃይሎች ለዚህ እኩይ ድርጊት ኃላፊነቱን እንዲወስዱ በኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና በፖለቲካ ሂደቱ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል በቅርቡ ወደ ሀገር ቤት በተመለሰው በአርበኞች ግንቦት ሰባት እና ቄሮ በመባል በሚታወቀው በወጣቶች ንቅናቄ ለማላከክ አስበው ነበር፡፡
በመዲናዋ አቅራቢያ የዘር ማጥፋት እልቂትን በመፈጸም እና የዘር ማጥፋት የምጽአት ቀንን በማነሳሳት ፍጹም የሆነ ማዕበል መፍጠር እንደሚችሉ አስበው ነበር፡፡
አማራን እና ሌሎችን የጎሳ ቡድኖች በመቀስቀስ በኦሮሞዎች ላይ የብቀላ ግድያ እንዲፈጽሙ በማድረግ እና ማቆሚያ የሌለው የብቀላ፣ የቅጣት እና የጦርነት አዙሪት እንዲመሰረት በማድረግ በመጨረሻም ታምራዊ ስሌት እንዳገኙ አድርገው ያስባሉ፡፡
ሆኖም ግን ተንኮታኩተው ወድቀዋል፡፡
የምጽአት ቀንን እውን ለማድረግ የሚያልሙት የጨለማው ጎን ኃይሎች በአንድነት፣ በአብሮነት፣ በሰላም እና በጎሳዎች መካከል እና በኃይማኖት ተቋማት የጋራ የዓላማ ጽናት እነዚህን ወንጀለኞች ወደ ፍትህ አደባባይ በማቅረብ የሚጠናቀቅበት ጊዜ ይሆናል፡፡
ፖሊስ ከቡራዩ እና ከአሸዋ ሜዳ ግድያ ጋር በተያያዘ በርካታ ተጠርጣሪዎች በቀጥጥር ስር መዋላቸውን ዘግቧል፡፡ የቅድመ ምርመራ ውጤቶች ይፋ እንዳደረጉት ከሆነ እነዚህ ወሮበላ ቅጥር ነብሰ ገዳዮች እንደዚህ ያለውን ቆሻሻ ድርጊት እንዲፈጽሙ በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ እንደተከፈላቸው ግልጽ አድርጓል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል የሕዝቡን ሰላም ለማናጋት እና በጎሳዎች መካክል የተካሄደ ግጭት ለማስመሰል ሆን ብሎ ታስቦበት የገንዘብ ድጋፍ እየተሰጠ የተፈጸመ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የጨለማው ጎን ኃይሎች ሰለባ ለሆኑት ወገኖቻችን ቤተሰቦች እየተደረገ ያለው መጠነ ሰፊ እርዳታ ሊታመን የማይችል እና የኢትዮጵያን በጎ ስነምግባር አሳይቷል፡፡
የፖለቲካ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሰብአዊ መብት ወትዋቾች፣ አርቲስቶች እና ተራ ዜጎች ከእልቂቱ ለተረፉት ወገኖች የሞራል እና የቁስ ድጋፍ ለማድረግ ተሰልፈዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ የጥቃቱን ሰለባዎች ለመደገፍ እና እንዲያገግሙ ለማድረግ ሙሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በቁጥር ሲታይ 11,902 የሚሆኑ የጥቃቱ ሰለባዎች ወደ ቤቶቻቸው እንደተመለሱ ተዘግቧል፡፡ ለጥቃቱ ሰለባዎች በጊዚያዊነት ተዘጋጅተው ከነበሩት መጠለያዎች ውስጥ 17ቱ ተዘግተዋል፡፡ በዚህም መሰረት 1,514 የሚሆኑት የጥቃቱ ሰለባዎች በመጠለያ ውስጥ ቀርተዋል፡፡
“ከእኛ በኋላ የምጽአት ቀን ይምጣ!”
የኢትዮጵያ አህያ ተረት እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ይላል፡፡
ከዙፋናቸው የተፈነገሉት የጨለማው ጎን ኃይሎች በፍርሀት ግድያ እና ውድመታቸው ኢትዮጵያ የእነርሱ መጫወቻ ሜዳ እና ማላገጫ ካልሆነች በስተቀር ገሀነም መግባት ትችላለች በማለት አውጀዋል!
ለዚህም ነው በሚችሉት ነገር ሁሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ጥላቻን፣ ግጭትን፣ ልዩነትን እና ቅራኔን በመፍጠር ላይ የሚገኙት፡፡
ኢትዮጵያን ወደ ዱሮው የድንጋይ ዘመን (የጫካው ዘመን) ለመመለስ የሰነዘሩትን ካራ ወደ ሰገባው እንዲገባ አልመለሱትም፡፡
እስከ አሁንም ድረስ ኃይል ከጠብመንጃ አፈሙዝ ይመጣል የሚለውን ያረጃ እና ያፈጀ አስተሳሰባቸውን ለማረጋገጥ በመሞከር ላይ ይገኛሉ፡፡
ሆኖም ግን የሚጠቀሙባቸው ጠብመንጃዎች እና ገጀራዎች በእጆቻቸው ላይ አይደሉም፡፡
የእነርሱ ዋና መሳሪያዎቻቸው ባለፉት 27 ዓመታት ከኢትዮጵያ ሕዝብ በግፍ የዘረፏቸው እና የሰረቋቸው ረብጣ ረብጣ ብሮች እና የተቆለሉ ብሮች ናቸው፡፡
በዘረፉት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እገዛ የበርካታ ንጹሀን ዜጎች ህይወት በገጀራ እንዲቀጠፍ እነዚህ ስውር እጆች እርኩስ ስራቸውን ይሰራሉ፡፡
የጨለማው ጎን ኃይሎች የ27 ዓመታትን መከራ እንደገና መልሶ ለማምጣት የሚጠቀሙት ስልት፣
የጨለማው ጎን ኃይሎች ባለስድስት ምላስ የማሸነፊያ ስልት በመጠቀም እንደገና ወደ ስልጣን ለመምጣት እንደሚችሉ ያምናሉ፡፡ ስልታዊ ዓላማቸው ቀላል እና እንዲህ የሚል ነው፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍርሀትን ለማሰራጨት እና ጥልቅ ጥላቻን በመፍጠር የጎሳ እልቂት ምጽአትን በመፍጠር ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ ሊያመጡ የሚችሉ የግድያ ክስተቶችን መፍጠር ነው፡፡
I. ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና አስተዳደራቸው ደካማ እና የማስተዳደር አቅም የሌለው ማስመሰል፣
የጨለማው ጎን ኃይሎች ተስፋ በቆረጠ መንፈስ ከአመክንዮ ውጭ በሆነ መልኩ ፖሊስ፣ ደህንነት እና ወታደራዊ ኃይል በዘፈቀደ እርምጃ እንዲወስድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጡ ይፈልጋሉ፡፡
ይኸ ስልት ሊወድቅ እንደማይችል ሁለት መንገዶች እንዳሉ ያምናሉ፡፡ እነርሱም፡
ሀ) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በስሜታዊነት ወዲያውኑ ምላሽ የሚሰጡ ከሆነ እርሳቸው አምባገነን ናቸው በማለት ስም የማጠልሸት ዘመቻቸውን ይከፍታሉ፡፡
ለ) ስሜታዊ ሳይሆኑ ወዲያውኑ እርምጃ የማይወስዱ ከሆኑ ደግሞ መወሰን የማይችል፣ ፈሪ፣ በእራስ የመተማመን ስሜት የሌለው እና ደካማ በማለት ለማሳየት ይሞክራሉ፡፡
በስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ነገሮች ሁሉ ልዩ እንደነበሩ አድርገው እራሳቸውን ከፍ ከፍ በማድረግ ይኮፍሳሉ፡፡ ሀገሪቱ የተረጋጋች ነበረች፣ ምንም ዓይነት ሰላማዊ ሰልፎች አልነበሩም፣ ምንም ዓይነት ቁስለኛ አልነበረም ይላሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አመራር ሁሉም ነገር ስርዓተ አልበኝነት እና የብጥብጥ ጊዜ እንደሆነ አድርገው ያራግባሉ፡፡
በመጨረሻም ዓላማዎቻቸው አራት ናቸው፡፡ እነርሱም፣
1ኛ) የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን አመራር ዋጋ በማሳጣት፣ በማዋረድ ሕዝቡ በእርሳቸው ላይ ጥርጣሬ ላይ እንዲወድቅ እና በእራስ የመተማመን ስሜት እንዳይኖረው ማድረግ፣
2ኛ) እነርሱ ባለፉት ሶስት ዓመታት ያህል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ በስልጣን ኮርቻ ተፈናጥጠው ለመቆየት እና በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ የሆነ መከራ ጭነውበት ሕዝባዊ አለመረጋጋት ተከስቶ እንደነበረው ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይንም በማስገደድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጁ ለማድረግ፣
3ኛ) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና አመራራቸው ፍጹም ሕዝባዊ ቅቡልና እንዳይኖራቸው እና ሕዝባዊ ድጋፍ እንዳይኖራቸው ለማድረግ፣
4ኛ) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ ውጭ ሀገር በሚሄዱበት ጊዜ የወንጀል ድርጊቶቻቸውን በመፈጸም የውጩ የዲፕሎማሲያዊ ኮሙኒቲ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ እምነት እንዳይኖረው ለማድረግ እና የጉዞ እቀባን እንዲያውጁ ለማስገደድ ነው፡፡
II. ተቃዋሚ ቡድኖችን እና መንግስትን ለመከፋፈል እና በመካከላቸው ቅራኔ ለመፍጠር፣
የጨለማው ጎን ኃይሎች በተቃዋሚ ቡድኖች ላይ ሁለት ስልቶች አሏቸው፡፡ በአንድ ድንጋይ በርካታ ወፎችን ለመግደል ዓላማ አድርገዋል፡፡
1ኛ) ከሕዝብ በዘረፉት በቢሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ ተቃዋሚዎችን ለመግዛት ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ እያንዳንዱ ሰው የመሸጫ ዋጋ እንዳለው አድርገው ያስባሉ፡፡ ጉዳዩ ምን ያህል የሚለው ብቻ ነው፡፡ ለተቃዋሚ መሪዎች ገንዘብ በመስጠት ከእጃቸው መዳፍ እንዲበሉ በማድረግ ለጥፋት ዓላማ እንዲሰማሩ ማድረግ፣
2ኛ) በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት እና በሀገሪቱ ውስጥ ባሉት ተቃዋሚ ቡድኖች በተለይም በአሁኑ ጊዜ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ ሀገር ውስጥ በገቡት በኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና በአርበኞች ግንቦት 7 በሁለቱ ተቃዋሚ ቡድኖች መካከል እርስ በእርስ ያለመተማመን፣ ፍርሀት፣ ክፍፍል እና የቅራኔ ዘር ለመዝራት ነው፡፡ የተቃዋሚ ቡድኖች እና መንግስት እርስ በእርሳቸው ጣት መቀሳሰር ከተጀመረ ኤኬ 47 ጠብመንጃቸውን በመያዝ ለመነጋገር ብዙ ጊዜ የሚወስድባቸው አይሆንም፡፡
3ኛ) ተቃዋሚ ቡድኖች ሕጋዊ እውቅና እንዳይኖራቸው፣ ስማቸውን ለማጠልሸት እና ስብዕና ለማሳጣት ነው፡፡ የጨለማው ጎን ኃይሎች በአንድ ወቅት አሸባሪዎች ናቸው ተብለው ተፈረጁት በአሁኑ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ችሮታ በመካከላችን ናቸው በማለት የሕዝብን ቀልብ ለመሳብ ነው፡፡
4ኛ) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለአሸባሪዎች መግባት የፈቀዱ እና ነጻ ያደረጓቸው መሆናቸውን ሕዝብ እንዲያምን ለማድረግ ነው፡፡
5ኛ) የጨለማው ጎን ኃይሎች በተቃዋሚ ቡድኖች እና በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት መካከል ቁጣ፣ ጥላቻ፣ ጥልቅ ጥላቻ እና መልካም ያልሆነ ስሜት እንዲፈጠር ዓላማ አድርገዋል፡፡
አንበሶች በታደኔ አውሬ ማን ይብላ ማን ይብላ ብለው ሲጣሉ ጅቦች በመሃል መንትፈው ዞር ይላሉ። አንበሶች ቁስላቸዉን አየላሱ ወደየመጡበት ይመላሳሉ።
መንግስትና ተቃዋሚዎች እርስ በእርሳቸው ጣት እየተቀሳሰሩ ሲካሰሱ የጨለማው ጎን ኃይሎች እየሳቁ ወደስልጣን ለመመለስ ይሞክራሉ።
III. እራሳቸውን እንደ ሰለባ እና የዘር ማጥፋት ዒላማ አድርገው መመልከት፣
የጨለማው ጎን ኃይሎች እራሳቸውን ወደ ስልጣን ለመመለስ እና ከተጠያቂነት ለማምለጥ ሁለት ስልቶች አሏቸው፡፡
የጨለማው ጎን ኃይሎች ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በስልጣን ኮርቻ ላይ ለመቀመጥ ፍላጎት እንዳላቸው ምንም ዓይነት ጥያቄ የለም፡፡
የመቶ ዓመታት የግዛት ዘመናቸው በ27 ዓመታት የመጠናቀቁ ጉዳይ ለማመን የማይቸሉት አስገራሚ ነገር ሆኖባቸው አይቻለሁ፡፡
ጥቂቶች ግራ በመጋባት የሚይዙት የሚጨብጡትን በማጣት ተስፋ የለሽ እና ስሜታዊ በመሆን ሁሉንም ነገር እንዳጡ በመንሾካሾክ በጭንቀት ላይ መሆናቸውን ተመልክቻለሁ፡፡
በመጨረሻው የመብላት/መስረቅ ጊዜ መጨረሻ አንዳለው አላወቁም፡፡ የመበዝበዝ የመገዝገዝ ጊዜው ለዘላለሙ አክትሟል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ መደነቅ አይኖርባቸውም፡፡ የሂትለር የአንድ ሺ ዘመናት የምርጦች ዘር አገዛዝ ድንፋታ ግልብ ድስኩር የቆየው ለአስራ ሁለት ዓመታት፣ ከአራት ወራት እና ከስምንት ቀናት ብቻ ነው፡፡
የመቶ ዓመታት አገዛዝ የሚባል ቅዥት ለዘላለም ተሰናብቷል።
ምክንያቱም ማንዴላ እንዳሉት አዲስ ሀገር በመመስረት ላይ ነን፡፡ እናም “ይህች ቆንጆ ምድር በፍጹም በፍጹም በፍጹም አንዱ በሌላው የሚጨቆንባት አትሆንም”::
ከዚህም በተጨማሪ የጨለማው ጎን ኃይሎች ከተጠያቂነት ለማምለጥ ይፈልጋሉ፡፡ ይህንን ዓላማ ለማሳካት ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን የጎሳ የዘር ፍጅት ለመፈጸም ዕቅድ ነድፈዋል በማለት ፕሮፖጋንዳቸውን በመንዛት ላይ ይገኛሉ፡፡
የኦሮሞ-አማራ አንድነት በመጨረሻው የሩዋንዳ ዓይነት የዘር ፍጅትን ያስከትላል በማለት ሕዝብ እንዲያምን ለማድረግ ሙከራ ያደርጋሉ፡፡
በሕዝብ ዘንድ የፍርሀት ድባብን በመፍጠር ኃላፊነትን ለማስወገድ ያልማሉ፡፡
ሆኖም ግን የጨለማው ጎን ኃይሎች መሰረታዊ የሆኑ ድክመቶች አሉባቸው፡፡
የጨለማው ጎን ኃይሎች አንዱ እና ዋናው ድክመታቸው እራሳቸውን ያለማወቃቸው ነው፡፡
እነርሱ ብልጦች እና ጎበዞች እንደሆኑ ማንንም በብልጠት ማሸነፍ እንደሚችሉ፣ ከማንም እንደሚበልጡ፣ ከማንም የበለጠ እንደሚያስቡ፣ ከማንም በላይ ቀልብን መሳብ እንደሚችሉ፣ ከማንም በላይ ድል ማድረግ እንደሚችሉ እና ማንኛውንም ሰው መፐወዝ እንደሚችሉ በእርግጠኝነት ያምናሉ፡፡ እንግዲህ ላለፉት 27 ዓመታት እራሳቸውን ሲመለከቱት የቆዩት በዚህ ማዕቀፍ ስር አድርገው ነው፡፡
እነርሱ ጀግናዎች እና እጅግ በጣም ብልጦች እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ፡፡
ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ለምንም ነገር የማይረቡ ቂሎች እና ደደቦች እንደሆኑ አድርገው ያምናሉ፡፡
የጨለማው ጎን ኃይሎች ሁለተኛው እና ትልቁ ድክመታቸው በመግደል፣ በማሰር፣ በማሰቃየት እና ስልጣናቸውን ከሕግ አግባብ በላይ በመጠቀም ወደ ስልጣናቸው ለመመለስ የሚችሉ እና የፖለቲካ ችግሮችን ሊፈቱ እንደሚችሉ አድርገው ያምናሉ፡፡
ሶስተኛው እና ዋናው ድክመታቸው ጊዜው ምን እንደሆነ ምንም ዓይነት ሀሳብ የሌላቸው የመሆናቸው ጉዳይ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜም ቢሆን በጫካ ውስጥ የነበራቸውን አስተሳሰብ ይዘው ነው በመጓዝ ላይ ያሉት፡፡ እስካሁንም ድረስ የሚመሩት በጫካው ሕግ ነው፡፡
ሆኖም ግን እ.ኤ.አ ሰኔ 2007 ዓ.ም ጊዜው ምን እንደሆነ አስረግጨ ነግሪያቸዋለሁ፡፡
የታላቁን የአሜሪካ የሰብአዊ መብት ተሟጋች መሪ የነበሩትን የሀሪ ቤላፍንቴ ቃላት በመጠቀም ኢትዮጵያ እየተባለች በምትጠራዋ ምድር ላይ ባሉ ወንድሞች እና እህቶች መካከል ፍቅርን የመስበኪያ ጊዜው አሁን ነው በማለት ነግሪያቸው ነበር! (በግልፅ) ፡፡
ነጻ የሆነ ማህበረሰብ የመገንቢያ እና በጎሳ ጥላቻ እና ክፍፍል የቆሰለውን ቁስል የመፈወሻ ጊዜው አሁን ነው በማለት ነግሪያቸው ነበር! (በግልፅ)
የሕግ የበላይነትን በማክበር የሕዝብ ነጻነቶችን እና ሰብአዊ መብቶችን በማክበር አዲሲቷን ኢትዮጵያ የመገንቢያ ጊዜው አሁን ነው በማለት ነግሪያቸው ነበር፡፡ (በግልፅ)
እየተንቀለቀለ ካለው ሕዝባዊ ቁጣ እና ጥልቅ ጥላቻ በመላቀቅ የዴሞክራሲን መንፈስ የመለኮሻ ጊዜው አሁን ነው በማለት ነግሪያቸው ነበር፡፡ (በግልፅ)
ብሄራዊ ዕርቅ በመመስረት ጎራዴዎችን እና ገጀራዎችን የመቅበሪያ ጊዜው አሁን ነው በማለት ነግሪያቸው ነበር፡፡ (በግልፅ)
ለጋራ ጥቅም በጋራ በመስራት እና ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት በኢትዮጵያ የተቀደሰውን ሰብአዊ መብት እና ዴሞክራሲን ማስፈን ይቻላል በማለት ጊዜው አሁን ነው በማለት ነግሪያቸው ነበር፡፡ (በግልፅ)
ሕዝቡን ጠቃሚ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ገንቢ የሆኑ ውይይቶች እንዲያደርግ በማድረግ ጥቃቅን ልዩነቶች እንዲወገዱ የማድረጊያ ጊዜው አሁን ነው በማለት ነግሪያቸው ነበር፡፡ (በግልፅ)
ድልድዮችን በመግንባት ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ዘንድ የመድረሻ እና በተለያዩ ቡድኖች መካከል ሊያገናኙ የሚችሉ ድልድዮችን በመገንባት በትናንሾቹ መጠለያዎች ተነጣጥለን እንድንቀመጥ ያደረጉንን ግንቦች የምንንድበት ጊዜው አሁን ነው በማለት ነግሪያቸው ነበር፡፡ (በግልፅ)
የጎሳ ፖለቲካ በፍጹም አያስፈልግም፣ እናም የሰብአዊ መብት ጥበቃ እና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጊዜው አሁን ነው በማለት ነግሪያቸው ነበር፡፡ (በግልፅ)
ነግሪያቸው ነበር፡፡ ነግሪያቸዋለሁ! ነግሪያቸዋለሁ! ግን የሚሰማ ጆሮ፣ የሚያሰላስል አእምሮ እና የሚያገናዝብ ልቦና አልፈጠረባቸውም፡፡
ሆኖም ግን በምንም ዓይነት መንገድ አይሰሙም፡፡ ጆሮ እያለው የማይሰማ አይን አያለው የማያይ እንደሚባለው ነው።
አሁን ደግሞ የመደመር ጊዜ ነው በማለት እነግራቸዋለሁ፡፡
መቀነስን የሚመርጡ ይመስላል ። የማረጋግጥላቸው ግን የመደመር በራችን ሁል ጊዜ ክፍት ነው።
አንድ ነገር ሙሉ በሙሉ እርገጠኛ ነኝ! ከጭለማ ሆነው ብርሃንን ሲያዩ አየሮጡ ለመደመር ወደኛ እንደሚመጡ። ለዚህ ጊዜው ሩቅ አይደለም።
IV. በኢትዮጵያ ያሉ ሌሎቹ የጎሳ ቡድኖች በ”ኦሮሞ አገዛዝ” ላይ እንዲነሱ ቅስቀሳ ማድረግ፣
የጨለማው ጎን ኃይሎች በኦሮሞዎች ላይ የስነ ልቦና ጦርነት ዘመቻ ከፍተዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና በ”ኦሮሞ አገዛዝ” ላይ ሕዝቡ እንዲያምጽ እና ጠኝካራ ተቃውሞ እንዲያደርግ የሕዝብ ስሜትን በማጦዝ ላይ ይገኛሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “የኦሮሞ መሪ” እንደሆኑ በማድረግ ጥላሸት በመቀባት ላይ ይገኛሉ፡፡
ሕዝቡ በኦሮሞዎች ላይ በቁጣ እና በጥላቻ እንዲነሳ እና ሰብአዊ እልቂትን እንዲፈጽም ለመቀስቀስ ይፈልጋሉ፡፡
እየከፈሉ በሚያሰማሯቸው ቅጥር ነብሰ ገዳይ ወሮበሎች አማካይነት እልቂት እንዲፈጸም በማድረግ ሕዝቡ በቁጣ ገንፍሎ እንዲነሳ እና በሀገሪቱ ውስጥ የጎሳ ፍጅት እሳት እንዲቀጣጠል በማድረግ ሀገሪቱን የሚያወድም የምጽአት ቀን እንዲመጣ ይፈልጋሉ፡፡
በሕዝቦች መካከል ያለመተማመን፣ ተስፋ ቢስነት እና ፍርሀት እንዲነግስ እና ለወደፊቱም በጭንቀት ውስጥ እንዲኖር ለማድረግ ይፈልጋሉ፡፡
ስራ የሌላቸው ተስፋ የቆረጡ ወጣቶች የአሸባሪዎች ዕኩይ ድርጊቶች እንዲፈጽሙ በማቀድ እና በገንዘብ በመደገፍ እጅግ የገዘፈ እና መጠነ ሰፊ የጥፋት ውጤት እንዲመጣ በጽናት ይሰራሉ፡፡
የጨለማው ጎን ኃይሎች በኢትዮጵያ ሕዝቦች ውስጥ ፍርሀት እና ጭንቀት እንዲሰፍን ይፈልጋሉ፡፡
በሕዝባዊ ቁጣ አማካይነት እጅግ የገዘፉ የአጻፋ ምላሾችን ለመስጠት እንዲቻል የዘረፉትን የሀገሪቱን አንጡራ ሀብት ለመጠቀም ዓላማ አድርገዋል፡፡
V. የኦሮሞ ጥላቻ/Oromo phobia መፍጠር፣
የጨለማው ጎን ኃይሎች ኦሮሞዎችን ለማግለል ባለሁለት ጣት ስልት አላቸው፡፡
የመጀመሪያው በኦሮሞ ላይ ጥላቻን በማሰራጭት በጽናት ቆመዋል፡፡ ኦሮሞዎችን ለማጠልሸት፣ ስብዕናቸውን ለማሳጣት፣ ከሌላው ሕዝብ ነጥሎ ለማግለል እና አስደንጋጭ ድርጊት ለመፈጸም ወይም ባህሪ ለማሳየት ወደኋላ አይሉም፡፡
ሁለተኛ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አመራር እና የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ደካሞች፣ መወሰን የማይችሉ፣ ወላዋዮች እና እርገጠኝነት የሌላቸው አድርጎ የማሳየት ዓላማ አላቸው፡፡
ማስተዳደር አይችሉም ለማሰኘት የታቀደ ነው፡፡ ችሎታ ክህሎት የላቸውም ለማለትይወገዱ የሚል ዘመቻ ያካሂዳሉ።
አብይና ለማን የዛሬ 27 ዓመት ታድለን ብናገኝ ኖሮ ኢትዮጵአ ሳትሆን አፍሪካ ስንት ቦታ በደረሰች ነበር!
ግን የሃያ ሰባት ዓመት እርግማን በስድስት ወር በረከት ድግም እጥፍ ተከፍለናል።
ሶስተኛ በአማራ እና በኦሮሞ ሕዝቦች መካከል የጎሳ ጥላች እሳትን ለመፍጠር ዓላማ በማድረግ ተነስተዋል፡፡
ላለፉት 27 ዓመታት የጎሳ ውጥረትን ለመፍጠር እና ለማቆየት ጥረት አድርገዋል፡፡ እንዲሁም በአማሮች እና በኦሮሞዎች መካከል ጽንፈኝነት እና ክፍፍልን ፈጥረዋል፡፡
አማሮች እና ኦሮሞዎች ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ጠላቶች ናቸው በማለት አውጀዋል፡፡ “እናም ሁለቱ የሚተባበሩ እና አንድ የሚሆኑ ከሆነ የቤት ስራችንን አልሰራንም ማለት ነው”፡፡
አማሮች እና ኦሮሞዎች ዘይት እና ውኃ ናቸው፣ መቀላቀል አይችሉም ብለዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ “አማራ እና ኦሮሞ ጭድ (የኢትዮጵያ የተለመደ የምግብ እህል የጤፍ ገለባ) እና እሳት (የእሳት ተመጣጣኝ እና በጣም የሚነድ ሳር) ናቸው ብለዋል፡፡ ሁለቱ በፍጽም ወደ አንድ እንዲመጡ ሊፈቀድላቸው አይገባም“፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለእነርሱ የሚሆን መልዕክት አላቸው፡፡ በኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ 9ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዲህ ብለዋል፡ (የጸሀፊው ትርጉም)
“አማራን እና ኦሮሞዎችን መከፋፈል አይቻልም፡፡ አማራን እና ኦሮሞዎችን ለመከፋፈል ጥረት የሚያደርጉ የኢትዮጵያን ታሪክ አያውቁም፡፡ የጎሳ ግጭቶችን ለመፍጠር የሚሸረበው ደባ አይሰራም፡፡ ኦሮሞዎችን እና አማሮችን፣ ሲደማ እና ወላይታን፣ ኦሮሞ እና ሶማሊን እና ሌሎችን ለመከፋፈል የሚደረገው ጥረት የሚሳካ አይደለም፡፡ ሰላማዊ ጉዟችን በመንገዱ አባጣ ጎረባጣነት የሚደናቀፍ አይሆንም፡፡ ገንዘባቸውን እና ጊዚያቸውን በእንደዚህ ያሉ ዕኩይ ድርጊቶች የሚያባክኑ ከእንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች መታቀብ አለባቸው“ ብለዋል፡፡
VI. ኢትዮጵያ ወደፊት የምትወድቅ የተከፋፈለች ሀገር ናት የሚል የማወናበጃ መረጃ በዓለም ዙርያ ማሰራጨት፣
የጨለማው ጎን ኃይሎች ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የአፍሪካ የሰላም ንቅናቄ መሪ ናት በማለት የኢትዮጵያን ገጽታ ለማጠልሸት ይፈልጋሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ማጥፋት ድርጊት በመፈጸም ላይ ነው የሚል ሀሳብ እንዲፈጠር ይፈልጋሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ስርዓተ አልበኝነት ተንሰራፍቷል፡፡ እናም ሀገሪቱ ለመበታተን በቋፍ ላይ ናት እንዲባል ይፈልጋሉ፡፡
በትላንትናው ዕለት የላይቤሪያ የሰላም የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ሎሬት ሌይማህ ቦዊ የ2018 የዓለም የሰላም ቀን ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ የተበረከተ ነው በማለት እንዲህ ብለዋል፡፡ “የዓለም የሰላም ቀንን በምናከብርበት ዕለት ዓለም ለዓለም አቀፍ ሰላም አንድ እርምጃ ወደፊት እንድትራመድ ጸሎቴ ነው፡፡ ይህ ቀን የፖለቲካ ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው ሰላም እንደገና በመካከላቸው እንዲሰፍን ላደረጉት ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ የሚበረከት ነው”፡፡
የጨለማው ጎን ኃይሎች የኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ገጽታ የግጭት፣ የጥላቻ እና የጎሳ ጽንፈኝነት እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡
የውጭ ኤማባሲዎች የጉዞ እቀባ መግለጫ እንዲያወጡ፣ በዚህም መሰረት ዲፕሎማቶች የቢዝነስ ሰዎች እና ሀገር ጎብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት እንዲፈሩ ይፈልጋሉ፡፡
ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለመበታተን በቋፍ ላይ ያለች እና በእርስ በእርስ ጦርነት የምትታመስ መስላ እንድትታይ ይፈልጋሉ፡፡
ሆኖም ግን አይሳካላቸውም!
የጨለማው ጎን ኃይሎች በእነዚህ እኩይ ድርጊቶቻቸው ይቀጥላሉ:: እናም ለእነርሱ ፋታ ልንሰጣቸው አይገባም፡፡
ሁላችንም የሚቆጠቁጡ ጥቂት እውነታዎችን መጋፈጥ አለብን፡፡
የጨለማው ጎን ኃይሎች ኢትዮጵያ ወደ ብጥብጥ እድትዘፈቅ የሚያደርጓቸውን ዕኩይ ድርጊቶች ከመፈጸም አያቆሙም!
ኢትዮጵያን የጎሳ እልቂት የምጽአት ቀን የመግደያ ቀጣና የማድረግ ሙከራቸውን አያቆሙም!
ተስፋ የቆረጡ ስራ አጥ ወጣቶች ቆሻሻ ስራቸውን እንዲሰሩ ለማድረግ ገንዘብ እየረጩ መመልመላቸውን አያቆሙም!
የሰዓት የጊዜ መሙያ እጀታውን ወዳለፉት 27 ዓመታት ለመመለስ ሙከራ ከማድረግ አያቁሙም!
ምን ማድረግ እንችላለን?
1ኛ) የጨለማው ጎን ኃይሎች በየጊዜው የሰው እልቂትን በሚፈጽሙበት ጊዜ መደንገጥ እና ስሜታዊ የሆኑ እርምጃዎችን መውሰድ የለብንም፡፡ እንደሌሎቹ አሸባሪዎች ሁሉ የጨለማው ጎን ኃይሎች በሕዝቡ ውስጥ ድንጋጤ፣ ማስፈራራት፣ ግራ መጋባት፣ ፍርሀት እና ያለመረጋጋት ስሜታዊነትን ለማንገስ ዓላማ ያደርጋሉ፡፡ በየጊዜው የሕዝብ እልቂትን በሚፈጽሙበት ጊዜ ሕዝቡ የሚደናገጥ እና ወዲያውኑ ስሜታዊ የሆኑ እርምጃዎችን የሚወስድ ከሆነ ይህ ሁኔታ ለእነርሱ ብርታትን የሚሰጥ እና የበለጠ የህዝብ እልቂትን እንዲፈጽሙ የሚያደርጋቸው ነገር ይሆናል፡፡
ለዚህም ነው በጨለማው ጎን ኃይሎች በሚፈጸሙ የሽብር ድርጊቶች በምንሰጠው ምላሽ መለካት መቆጠብ ያለብን፡፡
2ኛ) ሕዝቡን በመቀስቀስ የጎሳ ብቀላ እንዲያደርግ የጎሳ ዕልቂት የምጽአት ቀን እሳት እንዲለኮስ ይፈልጋሉ፡፡ የእነርሱን ዓለማ በመቀበል ወደ ጎሳ ብቀላ ድርጊቶች፣ ወደ ኃይል የመጠቀም ብቀላ እና ወደ አጻፋ ቅጣት መግባት የለብንም፡፡
3ኛ) ስንዴውን ከገለባ መለየት አለብን፡፡ የጨለማው ጎን ኃይሎች በሚገባ ይታወቃሉ፡፡ ማንንም የጎሳ ቡድን አይወክሉም፡፡ እነርሱ የሚወክሉት የእራሳቸውን ስግብግብ ፍላጎቶች ብቻ ነው፡፡ እንዲህ የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ምክር መቀበል አለብን፣ “እሾሆችን ከጽጌረዳ አበባዎች መለየት አለብን፡፡ በአንድ መጥፎ ዛፍ ምክንያት ሁሉንም ደን ማውደም የለብንም፡፡“
4ኛ) የማይናወጥ እና ጽናት ያለው ምልከታ ማድረግ አለብን፡፡ ዋጋ ሳይከፈል ነጻነትም ሆነ ሰላም አይገኝም፡፡ ኢትዮጵያውያን ወዳለፉት 27 የመከራ እና የስቃይ ዓመታት ለመመለስ ፍላጎት የማያሳዩ ከሆነ በቅርቡ በደማቸው በላባቸው እና በስቃይ ያገኟቸውን ነጻነት እና ሰላም መጠበቅ አለባቸው፡፡ በጨለማ ውስጥ ተቀምጠው በድብቅ ሽረባ የሚሰሩትን ነቅተን መጠበቅ አለብን፡፡
5ኛ) በጨለማው ጎን ኃይሎች ሰይጣናዊ ድርጊቶች መደናገጥ የለብንም፡፡ ከመጀመሪያቸው ጀምሮ በጫካው ሕግ ነው ሲመሩ የቆዩት፡፡ ስልጣን የያዙት በመግደል፣ ንጸሀንን ሽባ በማድረግ እና ስቃይ በመፈጸም ነው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ለ27 ዓመታት በስልጣን ኮርቻ እንደ መዥገር ተጣብቀው የቆዩት በመግደል፣ ሽባ በማድረግ እና ስቃይ በመፈጸም ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከስልጣን መንበራቸው የተወገዱ ቢሆኑም እንደገና ወደ ስልጣናቸው ለመመለስ ሲሉ መግደል፣ ሽባ ማድረግ እና ስቃይ መፈጸምን ይቀጥላሉ፡፡
6ኛ) የሕዝቡ ሰላም የመንግስት ኃላፊነት ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ነቅቶ በመጠበቅ እና ሁሉንም ነገር በጥንቃቄ በመመልከት ከመደበኛው እንቅስቃሴ የተለየ ነገር ሲታይ እርስ በእርስ መጠበቅ እና ለሕግ አስፈጻሚው አካል ማቅረብ የሁሉም ዜጎች ኃላፊነት ነው፡፡ በጨለማው ጎን ኃይሎች የሚፈጸሙትን ሁሉንም ጥቃቶች ለመመከት የመንግስት ኃላፊነት ብቻ አድርጎ መውሰድ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ሁሉንም የአሸባሪዎችን ድርጊቶች ከሰው ስህተት ነጻ በሆነ መልኩ መከላከል የሚያስችል መሳሪያ የለም፡፡ ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ሕዝቦች በንቃት እና እያንዳንዱን ነገር በትኩረት የሚመለከቱ ከሆነ የሽብር ጥቃቶችን አፈጻጸም በእጅጉ መቀነስ ይቻላል፡፡
7ኛ) “የማይመስል ነገር ስታዩ ከመተቆም አታመንቱ” በሚል ርዕስ ዘመቻ ለመጀመር ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ለእምነት ተቋማት፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች እና ማህበራት፣ ለሀገር በቀል እና ባህላዊ ድርጅቶች በሙሉ ጥሪየን አቀርባለሁ፡፡ እንደዚህ ያለ ዘመቻ በአሜሪካ ውስጥ ስኬታማ ስለሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ስኬታማ የማይሆንበት ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም፡፡
ኢትዮጵያ ተነስታለች!
ለኢትዮጵያ ሰላም ከአምላክ ተሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ መበታተን እና ውድመት ከፍተኛ በሆነ መልኩ እየተጋነነ ይነገራል፡፡
ኢትዮጵያን ወዳለፉት 27 ዓመታት ወደነበረችበት መስመር ለመመለስ የሚችል ምንም ዓይነት ምድራዊ ኃይል የለም፡፡ ምንም!
እ.ኤ.አ በ2013 ዓ.ም የጨለማው ጎን ኃይሎች ኢትዮጵያን ጥልቅ በሆነ መልኩ ለማሰቃየት እያደረጉት ባለው ጥረት ጉምን ይዘግናሉ በማለት ትንበያ ሰጥቸ ነበር!
በአሁኑ ጊዜ የጨለማው ጎን ኃይሎች ጉምን በመዝገን ላይ ናቸው አይባልምን?
እ.ኤ.አ በ2016 ዓ.ም የጨለማው ጎን ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ የቱንም ያህል ነገር ቢያደርጉ ኢትዮጵያ ነገ ምንም አትሆንም! ጸሐይም በፀሃይቷ ኢትዮጵያ ላይ መውጧትን ትቀጥላለች በማለት ትንበያ ሰጥቸ ነበር፡፡
ከአስርት ዓመታት በፊት የጨለማው ጎን ኃይሎች ኢትዮጵያን በጎሳ ጥላቻ እና የኃይማኖት ጽንፈኞች ግጭት በመፍጠር ኢትዮጵን ለመቅበር ዕቅድ አወጡ፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከአናሳ ጎሳ አገዛዝ እና ጭቆና መቃብር ውስጥ በመነሳት ላይ ናት፡፡
በተነሳችዋ ኢትዮጵያ አንደኛ ደረጃ እና ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ የሚባል ነገር የለም፡፡
በተነሳችዋ ኢትዮጵያ ጎሳ፣ ኃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ክልል ወይም ጾታ ከአንድ ሰው የዓይኖች ቀለም በላይ ዋጋ ያለው አይሆንም፡፡
በተነሳችዋ ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ለሁሉም ዜጎች ዋስትና ያገኛል፡፡
ከብዙ ጊዜ በፊት የጋና የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት የነበሩት ክዋሜ ንክሩማህ “ኢትዮጵያ ትነሳለች“ በማለት ተንብየዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2013 ዓ.ም ለአንባቢዎቼ መልካም የነክሩማን ትንቢት አውጃለሁ፡፡
እ.ኤ.አ መስከረም 2018 በተነሳችዋ ኢትዮጵያ እግሬን በማሳረፌ ዕድለኛ ሆኛለሁ፡፡
ንክሩማህ ስለተናገሩላት ኢትዮጵያ መነሳት እንዲህ በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን ይሆናል ብዬ በፍጹም አስቤው አላውቅም፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ፣ ነጻነት እና ሰብአዊ መብት ጥበቃ እየተጓዘችበት ያለው ሁኔታ ለእኔ ህልም እና ቅዠት ነበር፡፡
ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ልዩ ምስጋና አለኝ፡፡
በሀምሌ መጨረሻ አካባቢ ዩኤስ አሜሪካንን በጎበኙበት ጊዜ ለሁሉም ዲያስፖራ ኢትዮጵያውን እንዲህ በማለት ተግዳሮቶችን አስቀምጠዋል፣ “ሀገራችሁን አታውቁም፡፡ ሕዝቦቻችሁን አታውቁም፡፡ በርካታ ወገኖቻችሁ እንስሶች ከሚጠጡበት አንድ ወንዝ ላይ በጋራ ይጠጣሉ፡፡ እራሳችሁ በመምጣት እውነታውን ተመልከቱ፡፡“
ከ48 ዓመታት ቆይታ በኋላ (እ.ኤ.አ በ1974 ዓ.ም ለሶስት ወይም ከዚያ በላይ ካልሆ በስተቀር) ተመልሸ መሄዴ ለእኔ ከንቱ እና እርባና የለሽ ነው የሚል ሙግት ከራሴ ጋር ገጥሜ ነገር።
ሆኖም ግን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ቃላት በልዩ ሁኔታ ሞረዱኝ እና ሄጀ እንድጎበኝ አደረጉኝ፡፡
ስለዚሁ ጉዳይ የበለጠ ባሰብኩ ቁጥር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ትክክል በመሆናቸው ላይ እራሴን አሳመንኩ፡፡
እራሴን ከሀገሬ ጋር እና ከወገኖቼ ጋር አስተዋውቃለሁ ብዬ ተነሳሁ፡፡
ከወንዝ ከእንስሶቻቸው ጋር ውኃ ይጠጣሉ ወዳሏቸው ወገኖቻችን በመሄድ ከእነርሱ ጋር መነጋገር አለብኝ ብዬ ወሰንኩ፡፡
በአዲስ አበባ ውስጥ ጥቂት ቀናትን አሳልፊያለሁ፡፡ አብዛኛውን ጊዜየን ገጠር ውስጥ አሳልፊያለሁ፡፡
በባሌ ዞን አብዱል ጃባር በሚል ስም ከሚጠሩት አባ ገዳ (ባህላዊ መሪ) ጋር ሶፍ ኦማር (ሸክ ሶፍ ኦማር አህመድ በተባሉ ቅዱስ ስም በተሰየመው እና በዓለም ላይ በጣም አስደናቂ በሆነው እና ታላቅ የምድር ውስጥ ዋሻ) በሆነው ዋሻ ውስጥ ተገናኝቻለሁ፡፡
በሶፍ ኦማር አስደማሚ ውበት ስር አባ ገዳው ኢትዮጵውያን ከወይብ ወንዝ ጭቃ ያለበትን ውኃ እየጠጡ ያሉበትን አስቀያሚ እውነታ በምስክርነት እንድመለከተው ጋበዙኝ፡፡
ይህ ነገር ለእኔ እጅግ በጣም አስደንጋጭ ነገር ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከተናገሩለት እውነታ ጋር ለመጋፈጥ ከ10 ሺህ ኪ/ሜ በላይ ጉዞ አደርግሁ እንደ ብዬ ራሴን ጠየቁ፡፡ ልቤ ተሰብሮ ነበር፡፡ ለማልቀስ ፈልጌ ነበር ሆኖም ግን በሁኔታው በዚያ ሰው ሁሉ ፊት ሀፍረት ተሰማኝ፡፡
ባለፈው ሳምንት የማብሰያ ቤቱን ውጫዊ የውኃ መክፈቻ ለመክፈት ሳዞር፣ ሻወር ስወስድ እና በተለይም በጓሮዬ ባሉት ሳሮች ላይ ንጹህ ውኃ እየገነፈለ ሲወጣ ስመለከት የአባ ገዳ አብዱል ጃባር ገጽታ በህሊናዬ ውስጥ ውልብ አለ፡፡ እናም የእርሳቸው ጣት ወደ እኔ ተቀስሮ ተመለከትኩ፡፡
ምናልባትም ከዚህ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሸ በመሄድ እንደዚህ ያለውን የሚያም ሁኔታ ለመመልከት አልችልም ይሆን? ምናልባትም በዋና ከተማዋ በጎብኝዎች የመቆያ ማዕከሎች መቆየትይ አይሻልም? በአሁኑ ጊዜ እንደዚህ ያለውን ከባድ የአእምሮ ሸክም ለመሸከም ከመጠን በላይ ከባድ ነው።
ብዙ ለተሰጠው ብዙ ይጠበቅበታል። ከእንስሶቻቸው ጋር ውኃ ለሚጠጡ ወገኖቻችን የምችለውን ሁሉ ነገር በማድረግ ንጹህ ውኃ የመጠጣት መብታቸው እንዲከበር ጥረት አደርጋለሁ፡፡ ንጹህ የሚጠጣ ውኃ፡፡
እነዚህን ቃላት በምጽፍበት ጊዜ ጥልቅ በሆነ ስሜታዊነት ላይ ወድቂያለሁ፡፡
በዓለም ላይ በርካታ ቆንጆ ሀገሮች አሉ፡፡ ጥቂቶቹን ለማየት በመቻሌ ፍጹም ዕድለኛ ሆኛለሁ፡፡
አድሏዊ በመሆኔ ይቅርታ አድርጉልኝ፣ በሁሉም ዓይነት መንገዶች ሲታሰብ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ እጅግ በጣም ቆንጆ ሀገር ናት፡፡
ስለኢትዮጵያ ሌሎች እንግዶች እንደሚሉት ብዙ ነገር አልናገርም፡፡
ራፍ ጋይድስ የተባለው እና የታወቀው የእንግሊዝ የጉዞ መመሪያ መጽሐፍ እና የማጣቀሻ አሳታሚ መፈክሩ፣ “ብዙውን ጊዜህን በመሬት ላይ አሳልፍ“ የሚለው እ.ኤ.አ ሰኔ 2018 ኢትዮጵያን በዓለም ላይ እጅግ በጣም ጥሩ በሆነ መልኩ የምታስተናግድ በማለት የአንደኛነት ደረጃን ሰጥቷል፡፡ ስለኢትዮጵያውያን በርካታ ውብ ነገሮችን ማለት ይቻላል፡፡
በመሬት ላይ ጊዜን ከሚያሳልፉባቸው ቦታዎች ውስጥ አንዷ ስለመሆኗ በሙሉ ልብ በመመስከር እስማማለሁ፡፡
በሀገሪቱ ውስጥ በጣም በውብ መልኩ የሚያስተናግደው ህዝብ በጎሳ ግጭት እርስ በእርስ መገዳደል አይፈልግም።
እባካችሁ የፌሰቡክና ሶሻል ሚድያ ጀብደኞች ደሃው ሕዝባችንን አትበጥብጡት፡፡ በሰላም ኑሮዉን ይኑርበት።
መበጥበጥ ግዴታችሁ ከሆነ ቢያንስ ቢያንስ ገጠር ሂዱና ጥቂት ቀን ዉሃ ከከብት ጋር ከሚጠጣው ህዝባቺን ጋር አሳለፉ።
ያንን ጭካ ዉሃ ብትቀምሱት አንዴት ደስ ባለኝ!!
እመኑኝ ደሃው ህዝባችን ሰላም መኖርን ይፈልጋል፡፡
ጥላቻን አይፈልግም፡፡ ፍቅርን ይፈልጋል፡፡
ወንድሞቻቸውን እና እህቶቻቸውን መግደል አይፈልጉም፡፡ ቁስሎቻቸውን መፈወስ ይፈልጋሉ፡፡
አንድ ነገር ልለምናችሁ! በደሃው ህዝባችን ጫማ አንድ ኪሎሜትር ሂዱና ከዚያ በህዋላ ለፍፉ።
ከ48 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን ስጎበኝ የተሰማኝ ስሜት የሸክስፒር ሮሚዮ በመጀመሪያ ጊዜ ጁልየትን ሲያያት ልቡን እንደሰረቀቸው አይነት ስሜት ነበር። ሮሚዮ ሲናገር ስለ ጁልየት “በኢትዮጵ ላይ እንዳለ እንደ ሀብታም የጆሮ ጌጥ ሁሉ ቆንጆነትሺም በምድር ላይ አለ“ እንደሚለው ያህል ተሰማኝ፡፡
ሮሚዮ በጁሊየት የያዘው ድንገተኛ ፍቂር ተስፋ ቢስ ነበር። ምክንያቱም ከሁሉም ሴቶች በላይ ጁሌይ ማራኪ ስለነበርች፡፡
እኔም አንዴ ሮምዮ በኢትዮጵያ ፍቂር ተስፋ ቢስ ሆኛለሁ። የኢትዮጵ እና ኢትዮጵያውያን ሕዝቦች ውበትና ፍቂር ተማራቂ በመሆኔ!
ሆኖም ግን ማንም ሰው የእኔን ቃል መውሰድ የለቤትም፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያውያን በግሉ ሄዶ ማረጋገጥ ይችላል፡፡
የማስተነቀቀው ግን ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ፍቅር ማምለጥ አይቻልም! በምንም አይነት!
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ቃላት እንደ እራሴ አድርጌ ለዲያስፖራው ማቅረቤ እንግዳ ድግግሞሽ ይሆንብኛል፡፡
አብዛኛው ብዙሀኑ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን እና ወገኖቻቸውን አያውቁም፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያውያን በገጠር ይኖራል፡፡ እዚያ በመሄድ ነው ለመገናኘት፣ ሰላምታ ለመስጠት እና ለመነጋገር የሚቻለው፡፡ ስለህይወታቸው፣ ስለመከራቸው፣ ስለልጆቻቸው፣ ስለጎረቤቶቻቸው እና ስለሀገራቸው መጠየቅና መረዳት የሚቻለው፡፡
በሀገሪቱ መናገሻ ከተማ እና በከተማ አካቢዎች ለጥቂት ጊዜ ተንጠልጥሎ መቆየት የሚያስከፋ አይደለም። ሆኖም ግን ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ለማወቅ ሕዝቦቹ ወደሚኖሩበት እና ኑሯቸውን ለመምራት ወደሚታገሉበት መሄድ ጠቃሚ ነገር ነው፡፡
የፌስ ቡክና ሶሻል መድያ ጀብደኛነት በየሳምንቱ በብሎግ የጦርነት ቃላትን መወርወር ቀላል ነገር ነው፡፡
ከህዝብ ጋር አንድ ቀን መዋል ከሁሉም ይበልጣል!
መደመር ብቸኛው ከችግር የመውጫ መንገዳችን ነው!
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከ27 ዓመታት ባርነት በማውጣት ሰላም፣ ዕርቅ እና ይቅርባይነት ወዳለባት ወደ ተስፋይቱ ምድር አሸጋግረውናል፡፡
ይህ የመደመር መንገድ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን እንዲህ የሚል አንድ የዱሮ አባባል አላቸው፣ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር“ በሺዎች የሚቆጠሩ ሸረሪቶች ለአንድ ዓላማ ወደ አንድ ቢመጡ (ቢደመሩ) እና በአንድነት ቢሰሩ ያንን የጫካውን ንጉስ አንበሳውን ማንበርከክ ይችላሉ፡፡
አንድ መቶ ሚሊዮን የሚሆኑት የኢትዮጵያ ሕዝቦች እርስ በእርስ በመተባበር ቢደመሩ እና በአንድነት ቢሰሩ ሀገራቸውን ከተዘፈቀችበት ማጥ ውስጥ ማውጣት ብቻ ሳይሆን ዓለምንም ይለውጣሉ፡፡
“መደመር” ማለት እርስ በእርስ መረዳዳት ማለት ነው፡፡
መርዳት ማለት እጅን መስጠት ማለት እንጅ ምጽዋት መስጠት ማለት አይደለም፡፡
መደመር የአፍሪካዊ ልዩ መገለጫ እንደሆነ አምናለሁ፡፡
ባለፈው ጊዜ የኮሙኒዝም እና የካፒታሊዝምን ርዕዮተ ዓለሞች ሞክረናቸዋል፡፡
ኮሙኒዝም የተጨቆኑት እና የጨቋኞች ሰለባ የሆኑትን ሰዎች ባለድል ማድረግ ነው፡፡
ካፒታሊዝም ደግሞ በአትራፊዎች እና በከሳሪዎች መካከል ያለን ማህበረሰብ የሚያጠናክር ነው፡፡ ደኃ ከሆንክ የከሰርክ ነህ፡፡
መደመር በመሰረታዊ ዓላማው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ጭምር ፍትህ የሰፈነበት እና ሁላችንም አሸናፊዎች የምንሆንበትን ስርዓት የሚያመጣ ነው፡፡
የመደመር አሸናፊዎች እራሳቸውን በሌላው ሰው የችግር ጫማ ይሄዳሉ። ቅንነት ባለበት ውይይት ላይ ይሳተፋሉ፡፡ አእምሯቸው ክፍት ነው እናም ልዩነት ካላቸው ሀሳቦች እና ከተቃዋሚዎች ጋር የውይይት መድረክ ይቀበላሉ፡፡
የጋራ ፍላጎቶችን ለማሳካት ሲሉ ከግትርነት አልፈው ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ያደርጋሉ፡፡
ስልታዊ የጥቅም አሳዳጅነትን ወይም ተጫዋችነትን ያስወግዳሉ፡፡ ምክንያቱም የህይወት ጨዋታ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ ነውና፡፡
ላለፉት 13 ዓመታት የእኔን ትችቶች ሲከታተሉ ለቆዩ አንባቢዎቸ አንዱ ሁልጊዜ አሸናፊ የሚሆንበትን ሌላው እያንዳንዱ ደግሞ ሁልጊዜ ተሸናፊ የሚሆንበትን የዜሮ ድምር ጨዋታን እንዴት እንደምጠላ ያውቃሉ፡፡
ለመደመር ወደ ኢትዮጵያ ሄጃለሁ! ተደምረም መጥቻለሁ!
መደመርን በሚተገብሩ ሰዎች መካከል ተሸናፊዎች የሉም፡፡ የሚኖሩት አሸናፊዎች ብቻ ናቸው፡፡
የጨለማው ጎን ኃይሎች አንድ እና አንድ ብቻ ምርጫ አላቸው፡፡ ይህም መደመር ወይም ደግሞ ወደ ታሪክ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫት ውስጥ መጣል!
በአብይ አህመድ ልዩ አመራር አለን፣
ዓለም አቀፍ የመገኛኛ ዘዴዎች ስለአብይ ብዙ መልካም ነገሮችን ይላሉ፡፡
ፋይናንሻል ታይምስ እንዲህ በማለት ጽፏል፣ “አብይ አህመድ በአፍሪካ በጣም ታዋቂ ይሆናሉ፡፡“ እናም “የኢትዮጵያ ማንዴላ” ሲል ጠርቷቸዋል፡፡
ሲኤንኤን እንዲህ በማለት ለመግለጽ ሞክሯል፣ “ኢትዮጵያውያን አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትራቸውን ለምን ነብይ እያሉ በመጥራት ላይ እንደሚያምኑ“
ዘ ኢኮኖሚስት እንዲህ በማለት ለመግለጽ ሞክሯል፣ “ኢትዮጵያውያን በአብይ አህመድ ላይ ለምን በደስታ ይቦርቃሉ?“
አልጃዚራ እንዲህ በማለት አድናቆቱን ገልጿል፣ “ኢትዮጵያውያን በአብይ ፍቅር አብደዋልን?“
ኒዮርክ ታይምስ ስለአብይ አህመድ እንዲህ ብሏል፣ “በታልቅ አንክሮ የሚመለከቷቸው በአፍሪካ የሚገኙ መሪ“
ብላክ ስታር ኒውስ እንዲህ በማለት አውጇል፣ “ዶ/ር አብይ አህመድ ሕጋዊ እውቅና ያላቸው የሰላም የኖቤል ተሸላሚ ዕጩ ናቸው፡፡“
የቀድሞው የዩኤስ አሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊ ሄርማን ኮሆን በትዊተር ገጻቸው እንዲህ ብለዋል፣ “በእኔ ፕሮፌሽናል ህይወት ለመጀመሪያ ጊዜ አንድን ሰው ለኖቤል ሽልማት አሸናፊነት እጠቁማለሁ፡ እርሳቸውም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚያመጡ ከሆነ ጠቅላላ የአፍሪካ ቀንድ ወደተሻሻለ ሁኔታ ይሸጋገራል፡፡“
ይኸ ሁሉ ሲታይ አንድ ሰው ከሚያስበው በላይ ለማመን የሚያስቸግር አስገራሚ ሁኔታ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ይህ ጽሁፍ እስከሚጻፍበት ጊዜ ድረስ ለ175 ቀናት ብቻ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል!
ለሁሉም ወቅቶች የሚሆኑ ሰው አብይ አህመድን አግኝተናል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ለአብይ አህመድ ጫፋቸውየሚደርስ መሪ የለም ስል ይቅርታ የምጠይቅበት አይደለም፡፡
እርሳቸው ከሌሎች የመንጋ የአፍሪካ መሪዎች የሚለዩ ልዩ የሆነ ጥበብ ያላቸው መሪ ናቸው፡፡
ጠንቃቃ እና ስልታዊ አሳቢ ናቸው፡፡
የግል አብይ አሕመድ እና የሕዝብ አብይ አሕመድ የሚባል ነገር የለም፡፡ የምትመለከቱት የምታገኙት አብይ አህመድ ነው፡፡
አብይ አህመድ የሚያደርጉትን ይናገራሉ፣ የሚናገሩትን የሚያደርጉ ሰው ናቸው፡፡ ሁሉንም ነገር እንደወረደ ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ነው ሕዝቡ ከመጠን በላይ የወደዳቸው፡፡
ለዚህም ነው ኢትዮጵያ በታሪኳ ታላቅ ክብር እና ሞገስ ያላቸውን ታላቅ የፖለቲካ መሪ አፈራች በማለት የማምነው፡፡
እውነት ለመናገር የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች እ.ኤ.አ በ2020 ዓ.ም ከእርሳቸው ጋር ለምርጫ ፉክክር ሲሰለፉ ማየት አፍራለሁ፡፡
በእኔ ትውልድ ያሉትን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች እንዲህ የሚል ምክር እሰጣቸዋለሁ፡
በክብር ከመድረክ በመውረድ ወደ ቤታችሁ ሂዱ፡፡ የእናንተ ጊዜ አልፏል፡፡ ከወጣቱ አመራር ጋር በመሰለፍ እራሳችሁን አታዋርዱ፡፡ አሁን የእነርሱ ጊዜ ነው፡፡ የእነርሱ ቀን ነው፡፡ ኢትዮጵያ የወጣቶች ሀገር ናት፡፡ ስለእነርሱ ለመናገርም ሆን ምን እንደሚፈልጉ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ የእኛን አመራርነት እንደማይፈልጉት ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡ የእራሳቸውን ነው የሚፈልጉት!!!
ስለሆነም ሁላችሁንም እንዲህ በማለት እማጸናችኋለሁ፡ ሁላችንም ከፖለቲካ መድረኩ በክብር እና ሞገስ እንልቀቅ፡፡ ይልቁንም የእኛን አብይ አህመዶች፣ ለማ መገርሳዎች፣ እስክንድር ነጋዎች፣ አንዷለም አራጌዎች፣ ንግስት ይርጋዎች፣ ሙፈሪያት ካሚሎች፣ እማዋይሽ ዓለሙዎች፣ አቡባካር አህመዲዎች፣ ኦኮሌ አክዋይ ኦቻሊዎች፣ ደመቀ ዘውዱዎች እና ሌሎችም በርካታዎችን እናጅብ፡፡
አሁን የእነርሱ ጊዜ ነው!
ለዲያስፖራ እና ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ያለኝ መልዕክት፡ “እየተነሳን ነው፣ እያደግን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ላይ የሰላማዊ ለውጥ ነፋስ በመንፈስ ላይ ይገኛል፡፡”
ሰላማዊ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚጥሩ ሁሉ ጉምን ይዘግናሉ፡፡
ስለነገ ማሰብን አታቁሙ፡፡
በእኔ የወጣትነት ዘመን (48 ዓመታት በአሜረካ ውስጥ በመኖር) እንዲህ የሚል ልዩ መዝሙር መዘመር አለብን፡
ስለነገ ማሰብ አታቁሙ/ በቅርቡ ደህና እንደሚሆን እወቁ/
ከቀድሞው የበለጠ እዚህ ጥሩ ይሆናል/ትላንት አልፏል፣ ትላንት አልፏል/
ስለነገ ማሰብ አታቁሙ/በቅርቡ ደህና እንደሚሆን እወቁ /…
ሆኖም ግን የአፍሪካ ዘሮቼ ከደቡብ አፍሪካ የማርጋሬት ሲንጋናን እንዲህ የሚለውን መመዝሙር እንድዘምር አስገደዱኝ፡ “እያደግን ነው (ሙሉ ቅላጼውን እዚህ ጋ በመጫን ይጠቀሙ)፡፡ እየተነሳን ነው፡፡ ኢትዮጵያ እየተነሳች ናት! ወደ ከፍታ እና ከፍታ… …“
እኛ ኢትዮጵያውን እያደግን ነው [እየተነሳን] ነው፡፡
እያደግን ነው [እየተነሳን] ነው፡፡ ወደ ከፍታ እና ከፍታ
እያደግን ነው [እየተነሳን] ነው
ልጆቻችን እንስማ፣ ልጆቻችን እንስማ፡፡
ከእኛ ጋር ይነጋገራሉ፡፡
ሰላማዊውን [የሰላም] አዳምጡ፣ ሰላማዊውን [የሰላም] አዳምጡ፣
የኢትዮጵያ ምርጥ ቀኖች እየመጡ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር እንድትነሳ እና እንደፀሐይ እንድታንጸባርቅ እናድርግ!
በኢትዮጵያ ውስጥ እየነፈሰ ያለውን የሰላም ነፋስ እናዳምጥ! እንመገብ!
ልጆቻችሁ ከእናንተ ጋር ሲነጋገሩ አዳምጡ…
እንደመር፣ አንቀነስ፣ እንባዛ፣ አንከፋፈል!
ኢትዮጵያዊነት ዛሬ!
ኢትዮጵያዊነት ነገ!
ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
መስከረም 16 ቀን 2011 ዓ.ም