ኢትዮጵያውያኖች፣ ያገኘነዉን ታላቅ ሰጦታ አንዳናጣ አይናችንን ከፍተን መጠበቅ አለብን!
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም* እና ከአርቲስት/አክቲቪስት ታማኝ በየነ**
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
[ይህ ጽሁፍ በአማርኛ በአጭሩ እንዲተረጎም ተደርጎ በስፋት የሚሰራጭ ይሆናል፡፡]
Original post: http://almariam.com/2018/08/17/we-must-keep-our-eyes-on-the-prize-in-ethiopia/
በማህበራዊ መገናኛዎች/ሜዲያ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያውያን የዲያስፖራው ማህበረሰብ ውስጥ ጭምር በሚሰራጩት አሉባልታዎች፣ የውሸት ወሬዎች እና የማወናበጃ መሪጃዎች ላይ ነቄ ብለናል፡፡ ለማያውቁሽ ታጠኝ እንዲሉ!
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ደህንነት ዙሪያ እየተካሄዱ የሚገኙት የማስፈራራት መሰረተ ቢስ አሉባልታዎች እውነት መሆን እና አለመሆናቸውን ለማወቅ በርካታ ሰዎች እኛን እየተገናኙ በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
እየተናፈሱ ባሉት አሉባልታዎች ላይ በመንግስት በኩል ይፋ የሆነ የማስተባበያ መግለጫ ባለመሰጠቱ ምክንያት ለሚዥጎደጎደው አሉባልታ ጥቂት እውነታነት ሊኖረው ይችላል በማለት ሰዎች ይጠይቁናል፡፡
ለሚራገቡ ተራ ቅጥፈቶች እና የፈጠራ ወሬ አሉባልታዎች ይፋ የሆነ መንግስታዊ ምላሽ መስጠት የማይገባቸውን ትኩረት እንዲያገኙ በማድረግ በከፊልም ቢሆን ማመንን የሚያመላክት መስሎ ሊታይ ይችላል፡፡ እዚህ ላይ “ከዓሳማ ጋር ትግል አትግጥም፣ እርሱ ይወደዋል አንተ ግን በጭቃ ትበላሻለህ” የሚለውን የድሮ ብሂል ማስታወስ ተገቢ ይሆናል፡፡ በእርግጥ ለአንድ ተራ አሉባልታ ምላሽ መስጠት ከዚህም የበለጠ በርካታ ምላሾችን ለመስጠት በሩን እንደመክፈት ይቆጠራል፡፡
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በኢትዮጵያውያን መካከል አሉባልታዎችን፣ የውሸት ወሬዎችን እና የማወናበጃ መረጃዎችን በማሰራጨት ከበስተጀርባ ፍርሀት እና ጭንቀት በመፍጠር ላይ የሚገኙት እነዚያው የተለመዱት ተጠርጣሪዎች እንደሆኑ እናምናለን፡፡
የሚሰራጩት ውሸቶች እና አሉባልታዎች ብቻ ቢሆኑ ኖሮ ጉዳዩ ብዙም የሚያሳስበን እና የሚያሰጋን ነገር ባልሆነ ነበር፡፡
ሆኖም ግን እኛን የሚያሳስበን እና እያሰጋን ያለው ነገር ውሸቶች እና አሉባልታዎች በተወሰኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ውስጥ በሕዝቦች መካከል አለመረጋጋትን፣ የኃይል እርምጃ መውሰድን፣ ሞትን፣ እልቂትን እና መጠነ ሰፊ የንብረት እና የሀብት ውድመትን እንዲያስከትሉ ሆነው በጥቅም ላይ እየዋሉ የመገኘታቸው ሁኔታ ነው፡፡
የአሉባልታ መሳሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን እና የመንግስታቸውን ሕጋዊ ቅቡልነት ለማሳጣት እና ወገን እና ሀገር ወዳዱ መሪ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ሰላማዊ የለውጥ ሂደት አንጸባራቂ ኮከብ በመሆን የተጎናጸፉትን ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ አመኔታ ለመሸርሸር እና ለማጥፋት ሲባል ሆን ተብሎ ታስቦበት፣ በስሌት እና በታቀደ መልኩ እየተካሄደ ያለ መሰረተ ቢስ ዘመቻ እንደሆነ እናምናለን፡፡
“ሀገሪቱ ወደ ሕግ አልባነት ስርዓት ተቀይራለች፤ ሕገ መንግስቱ እየተጣሰ ነው” እያሉ በነጋ በጠባ ሽንጣቸውን ገትረው የቅጥፈት ስዕል ለመሳል የሚያደርጉትን ከንቱ መንፈራገጥ እና ባዶ ጩኸት በአርምሞ እና በቁጭት እየተመለከትነው እንገኛለን፡፡ ይህም በሕይወት እና በሞት መካከል የሚደረግ ከንቱ መንጠራወዝ ካልሆነ በስተቀር ከወደቁ በኋላ መንፈራገጥ ለመላላጥ ነው ከሚለው የአበው ብሂል የሚያልፍ አይሆንም፡፡
ወቼ ጉድ! ድንቄም ሕገ መንግስት! 27 ዓመታት ያህል በሕዝብ ላይ እልቂትን እየፈጸሙ፣ ዜጎችን እያፈኑ እያጠፉ፣ አካለ ጎደሉ እያደረጉ፣ በሕዝቦች መካከል ጥላቻን እንደ እህል እየዘሩ፣ የኃይማኖት መቃቃርን እየቀፈቀፉ፣ የጎሳ በረት እያጠሩ፣ አንዱን ብሐር ወርቅ ሌላውን ጨርቅ በማለት እየፈረጁ፣ የሀገርን ሉዓላዊነት እየደፈሩ እና እያስደፈሩ፣ የሀገርን ጥሪት እንደ ባዕድ ወራሪ ኃይል እየዘረፉ፣ አሁን ደግሞ የህዝብ ብሶት ሲያይል እና ጊዜ ፊቷን ስታዞርባቸው ስለሕግ እና ሕገ መንግስት ጠበቃ በመሆን ሊሰብኩን ይሞክራሉ፡፡ ሕገ መንግስት ማለት በሕዝቦች ላይ እንደዚህ ያለ መዓትን የሚያወርድ እና ሸፍጥን የሚያሰራ ከሆነ ገሀነም ይግባ፡፡
ከዚህ በስተጀርባ ያለው እና ያልተደበቀው መልዕክት የሕግ እና የስርዓት አስከባሪ ዋና ጠባቂ በመምሰል አንድ ዓይነት ወታደራዊ ኃይል በመጠቀም ስልጣንን እንደገና ቀምቶ በመያዝ የነበረውን የአፈና እና የጥልመት የጭቆና አገዛዛቸውን ለማስቀጠል ይመስላል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ጥቂት ግለሰቦች የተከፈተውን የፖለቲካ ምህዳር ለእራሳቸው የስልጣን መወጣጫ መጠቀሚያ መሳሪያ ለማድረግ እና እርካሽ ታዋቂነትን ለማግኘት ሲሉ የሚያደርጉት እኩይ ምግባር እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ስንዴውን ከእንክርዳዱ መለየት እንደሚችሉ እንተማመናለን፡፡
አሁን በቅርቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በተለይም በሶማሊ ክልል እየተፈጸመባቸው ያለውን ጥቃት ለማምለጥ ሲሉ ከመኖሪያ ቀያቸው በኃይል እየተፈናቀሉ ለመከራ ሲዳረጉ ከጀርባ ሆኖ ለስደት እየዳረጋቸው ያለው ሚስጥር ባለቤት ማን እንደሆነ በውል እንገነዘባለን፡፡ አብዛኞቹ ለዚህ እልቂት እና የመከራ ሕይወት የተዳረጉት ደግሞ ሴቶች፣ አረጋውያን እና ህጻናት ናቸው፡፡ ይህንን አስከፊ ድርጊት ከበስተጀርባ ሆነው የሚያቅዱ፣ አመራር የሚሰጡ እና ከሕዝብ የዘረፉትን መጠነ ሰፊ ገንዘብ ለቅጥር ነብሰገዳዮች እና የጥፋት ኃይሎች በመርጨት የሚያስፈጽሙት ወንጀለኞች እነማን እንደሆኑ ደግሞ ከእጆቻቸው አሻራዎች እና ከእግሮቻቸው ኮቴዎች አንጻር በኢትዮጵያውያን ሕዝቦች ዘንድ በውል ይታወቃሉ፡፡ ይህም ሀገር ያወቀው እና ጸሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡
በዜጎች ላይ የኃይል ጥቃት የሚሰነዝሩትን ግለሰቦች እና ቡድኖች እንዲሁም ይህንን ዕኩይ የኃይል ድርጊት በመላ ኢትዮጵያ የሚመሩትን እና በገንዘብ የሚደግፉትን በሙሉ እናወግዛለን፡፡
የሕዝቦችን ደህንነት ለማረጋገጥ እና እንደ አስፈላጊነቱም የፌዴራል መንግስት ባለስልጣኖችን እገዛ በመጠየቅ የክልል ባለስልጣኖች የወገኖቻችሁን ህይወት እና ህልውና ለመታደግ ስትሉ ስልጣኖቻችሁን ሁሉ አሟጣችሁ እንድትጠቀሙ በአጽንኦ እንጠይቃለን፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በረዥሙ ታሪኳ አይታው የማታውቀውን ሰላማዊ የለውጥ ሂደት በማካሄድ ላይ ትገኛለች፡፡
ከ27 ዓመታት አምባገነናዊ አገዛዝ በኋላ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ ብሩህ ቀን እየመጣላቸው ስለመሆኑ እንደገና ተስፋ እያደረጉ እና ለወደፊቱም በእራሳቸው ላይ የመተማመን ስሜት በማሳየት ላይ ይገኛሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች በመፍታታቸው፣ የፕሬስ ነጻነትን በመስጠታቸው፣ በኢትዮጵያውያን አንድነት እና በኢትዮጵያዊነት ላይ እምነት እንዲገነባ በማድረጋቸው እና ከጎረቤቶቻችን ጋር በተለይም ከኤርትራ ጋር በሰላም እንድንኖር በማድረጋቸው ከፍ ያለ ምስጋና እናቀርባላቸዋለን፡፡
አዎንታዊ ለውጦች እንዲቀጥሉ እንፈልጋለን፡፡ ሆኖም ግን የጨለማው ጎን ኃይሎች እኛን ወዳለፉት 27 ዓመታት የአፈና እና የጽልመት አገዛዝ ቅዠት ለመመለስ ሌት ከቀን በመስራት ላይ እንዳሉ እናውቃለን፡፡
የመረጡት የውጊያ መሳሪያ ደግሞ የብዙህን ትኩረትን በማስቀየስ ስንት መስዋዕትነት በመክፈል ድል ያደረግነውን የምርኮ መርከብ መልሰን እንድናጣው ማድረግ ነው፡፡
በማህበረሳባችን ውስጥ በማህበራዊ መገናኛዎች የሚሰራጩት ሁሉም አሉባልታዎች፣ ቅጥፈቶች እና ውሸት ወሬዎች ዓይኖቻችንን ለማንሸዋረር፣ ጆሮዎቻችንን ለማደንቆር እና ተያያዥነት የሌላቸውን እንቶ ፈንቶ ነገሮች እርስ በእርሳችን በማውራት ጊዚያችንን በከንቱ እንድናባክን የታሰበ እና የታቀደ ነው፡፡
እኛ ክብ እየሰራን የእነርሱን አሉባልታዎች እና የውሸት ወሬዎች ስንሰልቅ እነርሱ የማረክናቸውን መርከቦቻችንን በድብቅ ለመስረቅ መሰረታቸውን ይጥላሉ፡፡
እኛ በርካታ ስጦታዎች አግኝተናል፡፡
በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ወይም ደግሞ በአማጽያን ቡድኖች ወታደራዊ ኃይል ሳንጠቀም ስኬታማ የሆነ ሰላማዊ የለውጥ ሂደት ተግባራዊ ለማድረግ መልካም አጋጣሚ አግኝተናል፡፡
በሀገራችን የግለሰቦች እና የፕሬስ ነጻነት ድሎችን ለማጠናከር መልካም አጋጣሚ አግኝተናል፡፡
የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እና የሕዝባዊ ተጠያቂነትን ለመመስረት እና ተቋማዊ ለማድረግ መልካም አጋጣሚ አግኝተናል፡፡
ሰብአዊ መብቶች ዋጋ የሚያገኙበት እና የሚከበሩበት ባህልን ለመመስረት መልካም አጋጣሚ አግኝተናል፡፡
ሁሉንም ነገር እንደ ዋስትና መውሰድ አንችልም፡፡ ነጻነትን ለማግኘት ከባድ ነገር ነው፡፡ ሆኖም ግን ነጻነትን ለማጣት ቀላል ነገር ነው፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያውያን ዓይኖቻቸውን ካገኘነው ስጦታ ላይ እንዲያተኩሩ እንጠይቃለን፡፡
እነዚህን ስጦታዎች ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ከፍለንባቸው ያገኘናቸው ናቸው፡፡
በርካታ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ጊዜ ተጎናጽፈነው የሚገኘው የነጻነት ጎህ ይቀድ ዘንድ የመጨረሻ የሆነውን ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ መልካም ነገር በሰይጣናዊነት ላይ ድልን ተቀዳጅቶ ያገኘነው ሁሉም ኢትዮጵያውያን የደም፣ የላብ እና የእንባ መስዋትነትን ከፍለው ነው፡፡
ስለእራሳችን ጉዳይ ማንም ሲነግረን የነበረውን በፍጹም አንረሳም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ወደፊትም ማንም እንዲነግረን አንፈቅድም፡፡
ሆኖም ግን እውነትን እንደወረደ እንነግራቸዋለን!
ሁላችንም በአንድነት ታስረን እንደነበርን እንነግራቸዋለን፡፡ ሁላችንም በአንድነት እንገረፍ ነበር፡፡
ሁላችንም በአንድነት እንሰቃይ ነበር፡፡ ሁላችንም በአንድነት ደማችንን አፍስሰናል፡፡
በመጨረሻም በአንድነት ሆነን በመዋጋት በአንድነት ድልን ተቀዳጅተናል፡፡
ለእኛ ሲሉ መስዋዕትነት የከፈሉትን ወገኖቻችንን የምናስታውሳቸው ኢትዮጵያ በፍጹም ለጨቋኝ አምባገነኖች አገዛዝ እንዳትንበረከክ በማድረግ እና ለነጻነት እና ለዴሞክራሲ የሚደረገውን ረዥሙን ጎዳና ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥምም እንኳ ያለምንም ማወላወል ከዳር ለመድረስ ጉዟችንን በመቀጠል በድል አድራጊነት ስናጠናቅቀው ብቻ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ተጋርጠውብን የሚገኙት ችግሮች ባለፉት ስድስት ወራት የተጀመሩ አይደሉም፡፡
ላለፉት 27 ዓመታት ያህል ከእኛ ጋር የቆዩ ናቸው፡፡ እነዚህ ችግሮች የኢትዮጵያን ሕዝቦች በጎሳ፣ በኃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በባህል እና በክልል የበረት መስመሮች ለመለያየት ሲባል ታቅደው የተሰሉ ፖሊሲዎች ቀጥተኛ ውጤቶች ናቸው፡፡
የጨለማው ጎን ኃይሎች በስልጣን ኮርቻ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ለመኖር የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲን ሲጠቀሙ ቆይተዋልል፡፡
የጭቆና እና የአፈና አገዛዛቸውን በኃይል ለማስቀጠል ሲሉ ወታደራዊ ኃይልን እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተጠቅመዋል፡፡
ሆኖም ግን እነዚያ ቀኖች በአሁኑ ጊዜ አልፈዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ችግሮቻችንን በውይይት፣ በስምምነት እና በመግባባት እንፈታለን፡፡
ችግሮችን እያጎሉ በመናገር ሳይሆን በመፍትሄዎች ላይ ማተኮር ይኖርብናል፡፡
ጣት መቀስር እና ጥላሻት የመቀባባት ፖለቲካን ማቆም አለብን፡፡
በየዕለቱ ለዜጎቻችን ምን ያህል እንደምንጠነቀቅ በማሳየት የፍቅር ፖለቲካን መተግበር አለብን፡፡
በህብረተሰብ ውስጥ ዘለቄታዊ ሰላምን ለማምጣት ጥይትን ሳይሆን የምርጫ ካርድን መጠቀም እንዳለብን ታላቁ አፍሪካዊ መሪ አስተምረውናል፡፡ አዲስ የወደፊት እኩልነት እና ለሁሉም ሕዝቦች ፍትህ ለማምጣት የሚቻለው በእውነት እና በብሄራዊ እርቅ ብቻ ነው፡፡
ሁላችንም መናገር እና መፍትሄዎችን መስጠት አለብን፡፡
ከሁሉም የበለጠ ደግሞ ኢትዮጵያ ከአምባገነናዊ ስርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንድትሸጋገር ለማገዝ የእራሳችንን ሚና መጫወት አለብን፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሁሉም ዓይነት መልሶች አሏቸው ብለን አናምንም፡፡
የኢትዮጵያን ችግሮች ሁሉ መፍታት የሚችሉት ብቸኛው ሰው እርሳቸው ናቸው ብለን አናምንም፡፡
የሀገራችንን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት አንድ ሰው ወይም ቡድን ሁሉም ዓይነት መልሶች አሏቸው ብለን አናምንም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ችግሮችን ሁሉ አልፈጠሩም፡፡ እናም ለሁሉም መፍትሄዎች ምንጭ እርሳቸው ናቸው በማለት አንጠብቅ፡፡
የመፍትሄ አካል በመሆን የእራሳችንን ሚና መጫወት አለብን፡፡
የእራሳችንን ሚና መጫወት ማለት በፌስ ቡክ የሚወዱትን የኮምፒውተር ቁልፍ መጫን ወይም ደግሞ በማህበራዊ መገናኛዎች የጥላቻ ጭቃ መቀባባት ማለት አይደለም፡፡
የእራሳችንን ሚና መጫወት ስንል በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን፣ የሰብአዊ መብት ጥበቃን እና የሕግ የበላይነትን ማደራጀት እና በተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በመሳተፍ በማገዝ ኢትዮጵያ በሰላማዊ የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን ማረጋገጥ ነው፡፡
ለመፍትሄዎቹ መንግስት ብቻ ሳይሆን ወደ ሕዝቦችም ማየት ይኖርብናል፡፡
ባለፉት 27 ዓመታት በመንግስት በተፈጠሩት ችግሮች ምክንያት በአሁኑ ጊዜ ባለንበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡
ለችግሮቻችን መፍትሄዎች በእጆቻችን በእያንዳንዳችን እጆች ላይ እንጅ በፖለቲከኞች እና በመንግስት ባለስልጣኖች እጆች ላይ አይደሉም፡፡
ስልጣናቸውን ያጡ ስልጣናቸውን እንደገና ለማግኘት ሲሉ በእራሳቸው ኃይል ማንኛውንም ነገር ሁሉ እንደሚያደርጉ እናውቃለን፡፡ ይህንን ማድረግ ካልቻሉ ደግሞ ሀገሪቱን ማጥፋት የሚችል ማንኛውንም ነገር ይፈጽማሉ፡፡
ሆኖም ግን ይኸ ጉዳይ ሊሳካላቸው አይችልም ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አዲስ ቀን ነው፡፡
አሮጌው የጥላቻ ፖለቲካ፣ ክፍፍል እና ግጭት በአዲሱ የፍቅር፣ የመግባባት፣ የእርቅ እና የሰላም ፖለቲካ በመቀየር ላይ ነው፡፡
እውነት በእራሱ ይናገራል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ኢትጵያውያንን እንደገና በመከፋፈል ለመግዛት በመሞከር ላይ የሚገኙት የጨለማው ጎን ኃይሎች እራሳቸውን ተከፋፍለው፣ ስርዓት አጥተው፣ ተበታትነው፣ በተሳሳተ ሀሳብ ላይ ወድቀው፣ ተስፋ ቢስ እና ስሜታዊ ሆነው አገኙት፡፡
በአንድነት፣ በወንድማማችነት፣ በእህትማማችነት እና በኢትዮጵያዊነት መንፈስ እንዲህ በሙሉ እና በቅርበት ሆነን የመታየታችን ሁኔታ እንዴት እጅግ እንደሚያስደስተን እና አነርሱ ደግሞ በተስፋየለሽነት እና በአግራሞት ሁኔታ ላይ ወድቀው የሚገኙ መሆናቸውን መመልከት በጣም ስሜትን የሚቀሰቅስ ሁኔታ ነው፡፡
ምንም እንኳ እንደ ገና ዳቦ ብንቆራረስ እና ብንከፋፈልም ሁላችንም በአንድ ዕጣ ፈንታ ስር ያለን አንድ ኢትዮጵያውያን ሕዝቦች ነን፡፡
በመጨረሻም ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዳሉት እንዲህ የሚል አንድ እና አንድ ምርጫ ብቻ አለን፣ “ሁላችንም እንደ ወንድማማች እና እህትማማች በአንድ ላይ መኖር አለብን፡፡ ወይም ደግሞ እንደሞኞች በመሆን በአንድነት እንጠፋለን፡፡“
የጋራ ዓይኖቻችንን በትላልቆቹ ስጦታችን ላይ ሰክተን የተቀዳጀናቸውን ድሎች በንቃት እንደ ዓይን ብሌኖቻችን መጠበቅ እንጅ በስሜታዊነት ቅጥፈቶች፣ በውሸት ወሬዎች እና በማወናበጃ መረጃዎች ስሜታችንን ማስቀየስ እንደሌለብን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን እንጠይቃለን፡፡
========================
*እ.ኤ.አ ነሀሴ 2007 ዓ.ም የቅንጅት አመራሮች ከእስር ቤት መፈታታቸውን ተከትሎ ታማኝ በየነ እና እኔ እራሴ ያለንበት ሶስት አባላት ያሉት ቡድን በማቋቋም በሰሜን አሜሪካ እና በአውሮፓ የሚያደርጉትን ጉዞ ስናስተባብር ነበር፡፡ በርካታ ችግሮች የነበሩ ቢሆንም ቅሉ የቅንጅት መሪዎች ልኡክ በሰሜን አሜሪካ ሲያደርገው የነበረውን ጉዞ ስኬታማ በሆነ መልኩ ለማስተባበር ችለናል፡፡ በዚያ የቤት ስራ ላይ ከታማኝ በየነ ጋር መስራት ለእኔ ታላቅ እና ልዩ ክብር ነበር፡፡ ምክንያቱም የእርሱ ኃይል፣ ወሰንየለሽ ብሩህ ተስፋው እና መሰረታዊ የሞራል ስብዕናው አስቸጋሪ የነበረውን ጊዜ ስኬታማ በሆነ መልኩ እንድናልፈው አግዞናል፡፡
እንደዚሁም ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ለቅንጅት አመራሮች ስንሰራ ከቆየንበት አስራ አንድ ድፍን ዓመታት ካለፉ በኋላ በዚያው ተመሳሳይ ወር ውስጥ እ.ኤ.አ ነሀሴ 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ እንዲስፋፋ፣ ሰብአዊ መብት እንዲከበር፣ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን እና ሀገሪቱ በሰላማዊ የለውጥ ሂደት እና በዴሞክራሲያዊ የሽግግር ጎዳና መጓዟን እንድትቀጥል ለማገዝ እንደገና በወሳኝ የትግል መድረክ ላይ በመገናኘታችን ታላቅ ክብር እና ሞገስ ይሰማኛል፡፡
**ታማኝ በየነ በዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ግንባርቀደም የሰብአዊ መብት ወትዋች/አክቲቪስት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተከበረ የሙዚቃ እና የጥበብ ባለሞያ ነው፡፡
ታማኝ እ.ኤ.አ ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ እኩልነት እንዲረጋገጥ፣ ብሄራዊ አንድነት እንዲጎለብት፣ ፍትህ እንዲሰፍን፣ ዴሞክራሲ እንዲመሰረት እና ሰብአዊ መብት እንዲከበር ያለምንም ማቋረጥ ሲታገል ቆይቷል፡፡ ታማኝ ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ባሉ እና በዲያስፖራው በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ዘንድ ታላቅ ክብርን እና ሞገስን ተጎናጽፏል፡፡ በአማርኛ “ታማኝ” ማለት “ሁልጊዜም እምነት የሚጣልበት” ማለት ነው፡፡ በዩኤስ አሜሪካ የባሕር ኃይል ዋና ዓላማ በሕዝቡ ዘንድ ሁልጊዜም እምነት የሚጣልበት ሆኖ መገኘት ነው፡፡ በእኔ መልካም አስተያየት በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ከታማኝ በየነ የበለጠ እምነት የሚጣልበት ሰው የለም፡፡
ታማኝ በየነ እና እኔ በስልጣን ላይ ላሉት በተለይም ለበርካታ አስርት ዓመታት ስልጣናቸውን ከሕግ አግባብ ውጭ ሲጠቀሙ ለቆዩት እና በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የተነጠቁትን ስልጣን በማንኛውም አስፈላጊ መስሎ በታያቸው መንገድ ሁሉ በመጠቀም ለማስመለስ እና የቀድሞውን የአፈና፣ የጽልመት እና የጭቆና አገዛዛቸውን ለማስቀጠል በጽናት በመቆም ሌት ከቀን በመስራት ላይ ለሚገኙት እውነታውን ለመናገር በምናደርገው ጥረት እንድተቀላቀሉን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የሰብአዊ መብት ወትዋቾች/አክቲቪስቶች፣ ምሁራን እና ፕሮፌሽናል ባለሞያዎች ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን በዚህ እንዲቀላቀሉን የተማጽዕኖ ጥያቄ በማቅረብ እያደረግነው ባለው ጥረት ላይ እንዲህ የሚለውን የዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግን መልዕክት አጽንኦ እንዲሰጡት እናስታውሳቸዋለን፣“በመጨረሻም የጠላቶቻችንን ቃላት ብቻ አይደለም የምናስታውሰው ሆኖም ግን ጸጥ ብለው የቆዩትን የጓደኞቻችንን ድምጾች ጭምር እንጅ፡፡“
እንደመር፣ አንቀነስ፣ እንባዛ፣ አንከፋፈል!
ኢትዮጵያዊነት ዛሬ!
ኢትዮጵያዊነት ነገ!
ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ነሀሴ 13 ቀን 2010 ዓ.ም