ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ዲፕሎማሲ ስራዎን ለመጀመር እንኳን በደህና መጡ!

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

በዩናይትድ ስቴትስ መልካም ነገርን የሚያስቡ እና በጎ ነገርን ለማድረግ የሚያምኑ ሁሉንም ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንን በመወከል የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንኳን በሰላም መጡ እላለሁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እ.ኤ.አ ሀምሌ 28 ቀን 2018 ዓ.ም በዋሺንግተን ዲሲ፣ ሀምሌ 29 ቀን በሎስ አንጀለስ እና ሀምሌ 30 ቀን በሚኒያፖሊስ በመገኘት ወደ ሀገር ቤት ከመመለሳቸው በፊት ፈጣን የሆነውን የዲያስፖራ ዲፕሎማሲ ጉብኝታቸውን ይጀምራሉ፡፡

እ.ኤ.አ ሰኔ 3 ቀን 2018 ዓ.ም አቅርቤው በነበረው ትችቴ “እባክዎትን እባክዎትን በዩናይትድ ስቴትስ የእኛ እንግዳ ይሁኑ” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ጠይቂያቸው ነበር፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቀልብ ለመሳብ ደብዳቤየን በድረገጼ ላይ በጫንኩ ጊዜ በርካታ የሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ደጋፊዎች ድምጾች አነሳስቸ ነበር፡፡

እኛ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የምንኖር የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ደጋፊዎች  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድምጾቻችንን በመስማታቸው እና ግብዣችንን በመቀበላቸው እጅግ በጣም ደስ ብሎናል፡፡ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጥሪያችንን ከመስማታቸው በስተቀር ላለፉት 27 ዓመታት ድምጽ አልባዎች ሆነን ቆይተናል፡፡ “የሕዝብ ድምጽ የእግዚአብሄር ድምጽ ነው” የሚለው የድሮ አባባል እውነትም ትክክል ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የጎሳ፣ የኃይማኖት እና የቋንቋ መስመር ያልገደበው መሰረተ ብዙ የዲያስፖራ የድጋፍ መሰረት አላቸው፡፡ የእርሳቸው ደጋፊዎች ከፍተኛ የሆነ የደስታ ስሜት አድሮባቸዋል፡፡ እናም ለመሄድ ዝግጁ ሆነዋል፡፡ እርሳቸውን እንዴት እንደሚደግፏቸው እና እንደሚወዷቸው ለማሳየት እርሳቸውን ለማየት፣ ለመስማት እና ለማናገር  በጉጉት ይጠብቃሉ ፡፡

በሚያስደስት ሁኔታ የእርሳቸው ደጋፊዎች እርሳቸውን እንደ “ጠቅላይ ሚኒስትር” አይመለከቷቸውም፡፡

የእርሳቸው ታላላቆቹ ደጋፊ ትውልዶች እርሳቸውን እንደ ልጃቸው ነው የሚመለከቷቸው፡፡ በእርሳቸው የትውልድ ዘመን ላይ የሚገኙት ደግሞ እንደ ወንድማቸው አድርገው ነው የሚያዩአቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአብዛኛው በሀገር ውስጥ በሚገኙት ኢትዮጵያውያን እና በዲያስፖራው ማህበረሰብ ዘንድ እንደዚህ ያለ እውነተኛ ፍቅር እና ከበሬታን ለማግኘት የቻሉበት እውነታ ሊታመን የማይችል በጣም አስገራሚ ነገር ነው፡፡ እስከ አሁን ድረስ ከኔልሰን ማንዴላ በስተቀር እንደዚህ ያለ ሕዝብን የሚያነሳሳ እውነተኛ ፍቅር እና እምነት በሕዝብ ላይ ያሳደረ አፍሪካዊ መሪ ታይቶ አያውቅም፡፡

እውነት ለመናገር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ዩኤስ አሜሪካ እንዲመጡ እና እንዲጎበኙን ያቀረብነው ጥያቄ እንዲህ ባለ ሁኔታ ይፈጸማል ብለን አላሰብንም ነበር፡፡ ለዚህም እንደምክንያት የምንወስደው፣

አንደኛ ሊታሰቡ የማይችሉ የአካል እና የአእምሮ ፈተናዎችን እንዲተገብሩ ነበር የጠየቅናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ ወደ ዩኤስ አሜሪካ የ14 ሰዓት የአውሮፕላን በረራ ማድረግ እና ያለምንም ማቋረጥ ወዲያውኑ በግዛቶቹ መካከል ከወሰን እስከ ወሰን ጫፍ በመጓዝ የሚያደርጓቸው ንግግሮች እና የከተማ ስብሰባዎች እንዲሁም ምንም ሳይዘገዩ ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ የወጣውን መርሀ ግብር መመልከት ምን ያህል ከባድ ፈተና እንደሆነ ማንም ማሰብ ይችላል፡፡

ሁለተኛ ከዚህ ቀደም በዲፕሎማሲያዊ ስምምነት ወይም ፕሮቶኮል ታይቶ በማያውቅ መልኩ እንዲህ የሚል ነገር እንዲሰሩልን ነበር የጠየቅናቸው፡ “የተለመደውን ምንም ዓይነት ይፋ የመንግስታዊ ዲፕሎማሲ ጉብኝት በሁለቱ መንግስታት መካከል ከማድረግዎ በፊት የዲያስፖራን ዲፕሎማሲ ጉብኝት ያድርጉ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ለመቀበል በደስታ ዝግጅት እያደረግን ቢሆንም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ ከሚጠበቀው በላይ ሄደን እንዲፈጽሙልን ጥያቄ በማቅረባችን ከልብ ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡

ሆኖም ግን ከሚጠበቀው በላይ ሄደን እንዲፈጽሙልን ጥያቄ ለማቅረባችን በቂ ምክንያቶች ነበሩን፡፡

ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን የቀድሞው አገዛዝ ወደ ትውልድ ሀገራችን እንዳንገባ በተለይም ከዩኤስ አሜሪካ እንዳንሄድ ክልከላ በማድረግ ሀገራችን በድርቅ፣ በእልቂት፣ በሰብአዊ መብት ረገጣ፣ በሙስና፣ ስልጣንን ከሕግ አግባብ ውጭ መጠቀም፣ በምርጫ ድምጽ ዘረፋ እና በጎሳ ክፍፍል በዓለም ላይ እንድትታወቅ በማድረግ በሀፍረት እንድንሸማቀቅ እና ልቦቻችን እንዲሰበሩ በማድረግ አንገታችንን እንድንደፋ አድርጎን ቆይቷል፡፡

አንድ ነገር በማድረግ ለውጥ ለማምጣት እና የኢትዮጵያን ህዝቦች ህይወት ለማሻሻል የነበረው ዕድል እጅግ በጣም የመነመነ ነበር፡፡

ሆኖም ግን አንድ ቀን ልንኮራበት የምንችል ኢትዮጵያዊ መሪ ወደ አሜሪካ እንደሚመጣ እና በኩራት እንድንሞላ ሊያደርገን እንደሚችል ሁልጊዜ እናልም ነበር!

ደህና፣ ይኸው አብይ አህመድ መጥተዋል፡፡ እናም በእርሳቸው ከምንም በላይ እንኮራለን!

በተቻለ መጠን እርሳቸውን በአሜሪካ እንድናገኛቸው ከፍተኛ የሆነ ጭንቀት፣ ጉጉት፣ እና እረፍትየለሽ የመሆን ሁኔታ እንዳለ ግንዛቤ መወሰድ እንዳለበት ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ከእኛ አመለካከት አንጻር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዲያስፖራ ዲፕሎማሲያቸው የሚሰሩት  ከተለመደው ዲፕሎማሲያዊ አሰራር በላይ ነው፡፡ ከታሪክ በላይ ነው፡፡ ይህ ክስተት ለኢትዮጵያ ጠቃሚ የታሪክ መጀመሪያ ነው፡፡ በኢትዮጵያ (ወይም በአፍሪካ) ውስጥ በታሪክ የእራሱን ህዝብ ዲስፖራውን ለማነጋገር ዓላማ አድርጎ ጉዞ ያደረገ መሪ እኛ እስከምናውቀው ድረስ የለም፡፡ ይህ በታሪክ የመጀመሪያው ነው!

ሆኖም ግን በዲያስፖራ/ የመንግስት ዲፕሎማሲ አንድ ዓይነት የሆነ አመለካከት አናይም፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር የዲያስፖራ ዲፕሎማሲ ጉብኝት በዩኤስ አሜሪካ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የመንግስት ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት እንደሚያሳልጠው እና እንደሚያጠናክረው እናምናለን፡፡ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ግልጽ የሆነ ድጋፍ የሚያሳይ ከሆነ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ባለስልጣኖች ከእርሳቸው ጋር በራስ መተማመን ስሜት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ማድረግ ይችላሉ፡፡

በዩኤስ አሜሪካ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ከሆንኩባቸው ዓመታት ጀምሮ አንዱ የተማርኩት ታላቅ ትምህርት ቢኖር በሕግ አውጭው እና በአስፈጻሚው መካከል ተጻራሪ ፍላጎቶች ያሉ መሆናቸውን ነው፡፡ የዩኤስ አሜሪካ ባለስልጣኖች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በኢትዮጵያ ዲያስፖራ መጠነ ሰፊ እና የተባበረ ጠንካራ ድጋፍ እንዳላቸው የተገነዘቡ ስለሆነ እርሳቸውን በተለያዩ የፖሊሲ አማራጮች በተለይም በጣም  አወዛጋቢ ሆኖ በቆየው የሰብአዊ መብት ጥበቃ እና በጋራ የጥቅም ጉዳዮች ላይ ወደፊት በጋራ መስራት እንደሚችሉ ይህ ማረጋገጫ ይሰጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በልማት የሚደረጉ ጥረቶችን ለማገዝ የዲያስፖራ ባለሞያዎችን እና የቴክኒክ ፈቃደኞችን ዝግጁ ሆነው ያገኟቸዋል፡፡

እንደዚሁም ሁሉ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ዲያስፖራ ዲፕሎማሲ በአሁኑ ጊዜ በሀገር ቤት የኢትዮጵያውያን ድምጽ ሆኖ በመስራት ላይ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በተመሳሳይ መልኩም በአሜሪካ ውስጥ ላለው የመንግስት ለመንግስት ዲፕሎማሲም እንዲጠናከር እና የተሳለጠ እንዲሆን ያግዘዋል፡፡

በዩኤስ አሜሪካ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ በተራ ቁጥር አንድ ላይ መቀመጥ የሚኖርበት አጀንዳ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ጉዳይ እንደሆነ ለማረጋገጥ እወዳለሁ፡፡

ባለፈው ሚያዝያ ስልጣን ከያዙ ጀምረው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት እና የነጻ ፕሬሱን በመክፈት የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ላይ ላቅ ያሉ መሻሻሎችን እያስመዘገቡ ለመሆናቸው ከበርካታዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኃላፊ ሁኔታዎችን በማመቻቸት መስራት እንዲችሉ በሩን ከፍተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የደህንነት እና ሌሎች የሕግ አስፈጻሚ ባለስልጣኖች መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸማቸውን በይፋ በማመን ከፍተኛ የእስር ቤት አስተዳዳሪዎችን ከስልጣናቸው አባረዋቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሕግ የበላይነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲከበር ቃል ኪዳን ገብተዋል፡፡

እ.ኤ.አ ሀምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ኢትዮጵያ እና ዩኤስ አሜሪካ በሰብአዊ መብቶች፣ በዴሞክራሲ እና በመልካም አስተዳደር ላይ ያተኮረውን 8ኛውን የሁለትዮሽ የመንግስት የጋራ ምክክር አድርገዋል፡፡ ያ የምክክር መድረክ እንዳለፉት እንደሌሎቹ ዓይነት አካሄዶች አይደለም፡፡

የምርጫ እና የፍትሕ ስርዓቱን ለማጠናከር፣ የመገናኛ ብዙሀን እና የሲቪል ማህበረሱ ሚና እና አቅም ከፍ እንዲል፣ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የሕግ አስፈጻሚው ሞያዊ እንዲሆን እና ለሰብአዊ መብቶች መጣስ ተጠያቂነት እንዲኖር ለማድረግ እንዲቻል ሁለቱም ሀገሮች ተቀራርበው ለመስራት ስምምነት አድርገዋል፡፡

ላፉት 13 ዓመታት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማህበረሰብ ላይ የሰብአዊ መብት ጥበቃ እንዲደረግ ለማስቻል እና የተጠያቂነት ሕጉ በዩኤስ ኮንግረስ እና በአስፈጻሚው አካል እንዲያልፍ ብዙዎቻችን ሌት ከቀን ስንሰራ ቆይተናል፡፡

ኤች አር 128 (እ.ኤ.አ የካቲት 2018 ዓ.ም የቀረበው) እንዲጸድቅ የቀረበውን ሰነድ በኃላፊነት የያዙት የሬፐብሊካኑ ክሪስ ስሚዝ (የኒው ጀርሲ ሬፐብሊካን)፣ ማይክ ኮፍማን (የኮሎራዶው ሬፐብሊካን)፣ ካረን ባስ (የካሊፎርኒያው ዴሞክራት) እና ሌሎች አሁን በቅርቡ ረቂቁ እንዲያልፍ ውሳኔ ያሳለፉት የሕዝብ ተወካዮች 114 አባላት በ8ኛው የሁለትዮሽ የመንግስት የጋራ ምክክር ከተደረገው ጋር አንድ ዓይነት ስምምነት ነው፡፡

በ9ኛው የሁለትዮሽ የመንግስት የጋራ ምክክር የዲያስፖራ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና የሰብአዊ መብት ወትዋቾች በጋራ ምክክሩ ላይ እንዲሳተፉ እና የየእራሳቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ዕድሉ እንደሚሰጠን ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለኝም፡፡

በጋራ ምክክሩ ላይ መቀመጫ ወንበር ሊሰጠን እንደሚገባ አምናለሁ፤ ምክንያቱም ይህንን መድረክ ያስገኘነው በደማችን፣ በላባችን እና በእንባችን ዋጅተን ነው!

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የዲያስፖራ ዲፕሎማሲ በዩኤስ አሜሪካ የሰብአዊ መብት አጠባበቅ የሚደረገውን መንግስታዊ ዲፕሎማሲያቸውን በእጅጉ እንደሚያጠናክረው አምናለሁ፡፡

የአብይ አህመድ ታዕምር፣

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከአሜሪካ የዲፕሎማሲ ተልዕኮ ጉብኝታቸው በፊት ወደ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውን ዲፕሎማሲ ተልዕኮ ቅድሚያ በመስጠት ሊጎበኙን በመምጣታቸው የእኛን የጋራ ጥልቅ ፍቅር እና ለእርሳቸው ያለንን ክብር የበለጠ ከፍተኛ እንዳደረገው እኔ በግለሰብ ደረጃ ጥልቅ የሆነ ስሜት ተሰምቶኛል፡፡

በዩኤስ አሜሪካ ለምትገኙ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ደጋፊዎች በሙሉ፣ የእርሳቸው ጉብኝት ለእኛ ለኢትዮጵያ ማህበረሰቦች ከፍተኛ ዋጋ እንደሰጡን እና እኛም ችሎታችንን እና አቅማችንን በመጠቀም ለሀገራችን ጠቃሚ የሆነ ድርሻ እንድናበረክት የሚያደርግ ለመሆኑ ምንም ዓይነት የማያወላዳ ማስረጃ ነው፡፡

በማንኛውም ጊዜ ለመንግስታዊ ጉብኝት ወደ ዩኤስ አሜሪካ ለመምጣት እንደሚችሉ እናውቃለን፡፡ ሆኖም ግን እኛን አሁን መጎብኘት አለባቸው! ምክንያቶቼን እ.ኤ.አ ሰኔ 2018 ዓ.ም አዘጋጅቸው በነበረው ግልጽ ደብዳቤዬ ላይ ገልጨዋለሁ፡፡

በአቀባበል ንግግራቸው እና ከዚያም በኋላ በተደጋጋሚ በሚያደርጓቸው ጉብኝቶች የዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ጥልቅ ስሜት አስደናቂ ነገር ነው፡፡ በማንኛውም ምክንያት ይሁን ከሀገሩ የተሰደደ በአልታሰበ መንገድ ወደ ሀገሩ ተመልሶ በማንኛውም መስክ በፖለቲካ፣ ያለምንም ፍርሀት፣ መሸማቀቅ ወይም ደግሞ መሰቃየት መሳተፍ እንዲችል ወደ ሀገሩ እንዲመለስ የሚፈቅድ ጠቅላይ ሚኒስትር ይኖራል ብሎ የሚጠብቅ ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡ ይኸ ለሁላችንም የሚያስደንቅ ነገር ነው፡፡

ላለፉት 27 ዓመታት ስንሰማው የቆየነው መልዕክት “ጽንፈኛ ዲያስፖራዎች”፣ “ጸረ ሰላም ኃይሎች”፣ “አሸባሪዎች” እና እንደዚህ የመሳሰሉትን ነገሮች ነበር፡፡ በቀላሉ ለመናገር ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን የመንግስት ጠላቶች ናቸው እየተባልን ሲነገረን ነበር!

ከአራት ወራት በፊት አብይ አህመድ ከምንም ነገር በመውጣት እንዲህ በማለት መስበክ ጀመሩ፣ “አሁን ጊዜው የይቅርታ፣ የዕርቅ፣ የሰላም  እና የኢትዮጵያዊነት ነው፡፡“

ለዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን የሚያጠናክር እንዲህ የሚል መልዕክት አመጡ፡፡  “እናንተ ጠላቶቻችን አይደላችሁም፡፡ እናንተን ጠላቶች ናቸው የሚል እራሱ እውነተኛ ጠላት ነው፡፡ ድምጽ የለሾች አይደላችሁም፡፡ አሁን ድምጽ አላችሁ፡፡ በኢትዮጵያዊነት ጽኑ መሰረት ላይ በመመስረት ከጎሳ ጥላሸት በመውጣት ኢትዮጵያን ለመገንባት እንድታግዙን እንፈልጋችኋለን፡፡ እጆቻችንን በመዘርጋት በደስታ እንቀበላችኋለን፡፡ ወደ ሀገራችሁ ተመለሱ እና እንንጋገር፡፡!“ ነበር ያሉት፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን መልዕክት በምንቀበልበት ጊዜ እና ተግባራዊ ማድረግ በምንጀምርበት ጊዜ ከአራት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ይህን ሁሉ ታዕምር በመስራታቸው ለመዋጋት፣ ለመጨቃጨቅ እና እርስ በእርስ ለመጣላት የሚሆኑንን ምክንያቶች ሁሉ እርግፍ አድርገን ተውናቸው፡፡

የአብይ አህመድ ታዕምር ማለት እንግዲህ ሌላ ምንም ነገር ሳይሆነ ይኸ ነው፡፡

እንግዲህ አብይ አህመድ የኢትዮጵያን ዲያስፖራ ቀልብ የሳቡት እና ያሸነፉት በዚህ ዓይነት መንገድ ነው፡፡ የድሮውን የጥላቻ፣ በቀልተኝነት እና ተጻራሪነት መሳሪያ በማስወገድ በአዲስ የፍቅር፣ የይቅርባይነት እና የዕርቅ መሳሪያ ተኳቸው፡፡

ሆኖም ግን ስለአብይ አህመድ ሁኔታ አእምሮዬን የሚኮረኩሩ ሁለት ነገሮች አሉ! እነርሱም፣

የመጀመሪያው ሁላችንም ይቅርባይነትን፣ ዕርቅን እና ሌሎችንም ነገሮች ለበርካታ አስርት ዓመታት ስንሰብክ ቆይተናል፡፡ ሆኖም ግን ጥረቶቻችን ሁሉ ምንም ዓይነት የተግባር ልዩነትን ሳያሳዩ እና ፍሬ ሳያፈሩ ቆይተዋል፡፡

ከስድስት ወራት በፊት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ያውቋቸው የነበሩት አብይ አህመድ ስለይቅርባይነት፣ ዕርቅ፣ ሰላም እና ኢትዮጵያዊነት መስበክ ጀመሩ፡፡ እናም እያንዳንዱ ሰው ጮቤ በመርገጥ እየዘለለ እና የእርሳቸውን ሙዚቃ እያዳመጠ አስደማሚውን እንቅስቃሴ ማከናወን ጀመረ፡፡ ይህንን ሁሉ ነገር እየሰሩ ያሉት ከ100 ቀናት ባነሰ ጊዜ ነው፡፡ እንዴት ነው ይህንን ሊሰሩ የቻሉት? እኔ እስከ አሁን ዘዴውን አላገኘሁትም!!

ሁለተኛው ደግሞ በምንም ዓይነት መልኩ የበለጠ ሊታመን የማይቻል ነገር ነው፡፡ በእኔ አዲስ እሳቤ ከማንኛውም የኢትዮጵያ መንግስት ወኪል፣ ባለስልጣን ተወካይ ጋር በመተባበር ለመስራት ይቻላል የሚለውን በአእምሮዬ ውስጥ አስቤው አላውቅም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት በእርግጥ በእኔ መግለጫዎች ወይም ደግሞ በትችቶቼ ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሉ ሀረጎችን አስገብቸ አላውቅም፡፡ ይህንን አድርጌ ከሆነ የብዕር ስህተት ነው፡፡

የነበረውን የጥላቻ መንፈስ፣ በቀልተኝነት እና ጥልቅ ጥላቻ እርግፍ አድርጌ በመተው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ጉብኝት ለማስተባበር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከኤምባሲ እና ከቆንስላ ባለስልጣኖች ጋር ስሰራ የመገኘቴ ሁኔታ ለእራሴ አስገራሚ ሆኖብኛል፡፡ እንደዚህ ያለ ሁኔታ ይመጣል ብዬ በፍጹም አስቤው አላውቅም፡፡ ይኸ ነገር ለእኔ የማንዴላ መርህ ማረጋገጫ ነው፡፡ እስከሚፈጸም ድረስ የሚሆን ነገር መስሎ አይታይም፡፡ አሁንም እራሴን በማወዛወዝ እንዲህ በማለት እራሴን እጠይቃለሁ፣ “ያ ነገር እንዴት ሊሆን ቻለ?“

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአሜሪካ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንን የመጎብኘታቸው ዓላማ ተጻራሪ የሆኑትን፣ ጥልቅ ጥላቻ እና በዲያስፖራው እና በኢትዮጵያ ባለስልጣኖች መካከል የቆየውን ጥላቻ በማስወገድ ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋገረው፡፡ የእርሳቸው ጉብኝት በዲያስፖራው እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ለበርካታ አስርት ዓመታት ተንሰራፍቶ የቆየውን አሉታዊ የጥላቻ አካሄድ ፍጻሜ በመስጠት ለኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ ማህበረሰብ በሀገሩ ጉዳይ የበለጠ ተሳትፎ እንዲያደርግ  የሚያስችሉ መልካም አጋጣሚዎችን እንደሚፈጥር አምናለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በጉብኝታቸው ወቅት ለወደፊቱ የዲያስፖራ ግንኙነቶች እና አብሮ የመስራት ሁኔታ አዲስ ድምጽት እንደሚፈጥሩ አምናለሁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተሟላ ዲያስፖራ ጉብኝት እንዲያደርጉ በጠየቅናቸው ጊዜ የጥያቂያችንን ያልተጠበቀ ባህሪያትን ተገንዝበን ነበር፡፡

እኛ እስከምናውቀው ድረስ አንድ የመንግስት መሪ የሚመጣበትን ሀገር ይፋ ጉብኝት ከማድረጉ በፊት ዲያስፖራ ማህበረሰቡን ሊጎበኝ ሲመጣ በዲፕሎማሲ ታሪክ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ የማይሆነውን ነገር እንዲያደርጉ ስንጠይቃቸው እንደነበር እናውቃለን፡፡ ጥያቂያችንን ከወራት በፊት በምናቀርብበት ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የማይቻለውን ለመስራት የሚያስችል ልዩ ባህሪ ያላቸው ስለመሆናቸው አናውቅም ነበር፡፡

ግብዣችንን እንኳ ስለመቀበላቸው በእርግጠኝነት የምናውቀው ነገር አልነበረም፤ ምክንያቱም ካላቸው የጊዜ ውጥረት የተነሳ እና በሀገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ካለው ፈጣን ለውጥ አንጻር ጥርጣሬው ነበረን፡፡

እንደዚሁም ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ባልተጠበቀ መልኩ ብቻ አልነበረም የጠየቅናቸው ሆኖም ግን ጥያቄው የተሳሳተም ሊሆን ይችል ነበር፡፡ የሚመጡባትን ሀገር በይፋ ከመጎብኘታቸው በፊት ዲያስፖራን ብቻ በመለየት በዚያ ላይ በማነጣጠር እንዲጎበኙን ነበር ጥያቄ ያቀረብነው፡፡

በሌሎች ሀገሮችም የተለመደ ባለመሆኑ ምክንያት ጥቂቶቻችን ግብዣዎቻችንን በፍጹም አይቀበሉም በማለት ተከራክረን ነበር፡፡ ጥቂቶቻችን ደግሞ ለመንግስታዊ ጉብኝት ቅድሚያ በመስጠት ለእኛ የተወሰነች ትንሽ ጊዜ ሊሰጡን ይችላሉ በማለት አስበን ነበር፡፡

እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ግን ወይም የሚል ሁኔታን ያካተተ አልነበረም፡፡ ድል አድራጊነትን የሚያሳጣ ሁኔታም አልነበረም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስታዊ ጉብኝታቸውን በፈለጉት ጊዜ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን ዲያስፖራ ደጋፊዎቻቸውን አሁን መጎብኘት አለባቸው፡፡

ለምን?

በአሜሪካ በሚኖረው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ ውስጥ በሀገሪቱ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር አሁኑኑ እንዲደረግ እራሳቸውን ያዘጋጁ እና በለውጡ ሂደት ለመሳተፍ ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ የሚጮሁ እና ገና ያልተነካ ጉልበት ያላቸው ዲያስፖራዎች እንዳሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዲያውቁት እንፈልጋለን፡፡

እኔ በግሌ ዘግይቶ ሳይሆን አሁኑኑ በሁሉም የሙያ ዘርፎች ፈቃደኛ የሆኑ፣ ብቃቱ ያላቸው እና ሀገራቸውን ለማገዝ የተዘጋጁ በርካታ ዲያስፖራ ባለሞያዎች ያሉበት ሁኔታ እንዳለ እውነታውን በመግለጽ ምስክርነቴን ለመስጠት እፈልጋለሁ!

አሁን የመጎብኘታቸው ሁኔታ አንገብጋቢ መሆኑን እንዲያውቁት እንፈልጋለን ምክንያቱም በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ በርካታዎቹ የእርሳቸው ደጋፊዎች ለበርካታ አስርት ዓመታት ከትውልድ ሀገራቸው እንደተገለሉ ሆኖ ይሰማቸዋል፡፡

በእርሳቸው አመራር የሚታየው ለውጥ አስደማሚ እና አእምሮን አጠቃሎ የሚስብ እንደሆነ አድርገው ያደንቃሉ፡፡

በአሜሪካ ውስጥ የምንገኝ እኛ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን አድናቂ መሪዎች ብቻ ሆነን እንድንታይ ወይም ደግሞ ከዳር በመቆም የምናይ ተመልካች አይደለንም፡፡ ሸክማችንን አብረን እንድንሸከም እና የእኛን ድርሻ ለማበርከት እንፈልጋለን፡፡ ኢትዮጵያ ሰላማዊ ሽግግር እንድታደርግ የከበረ ሞያችንን እና አገልግሎታችንን ከመስጠት የበለጠ ምንም ነገር ስለሌን እኛ ዲያስፖራዎች በአሁኑ ጊዜ ዝግጁ፣ ፈቃደኛ እና ማድረግ የምንችል ብቃቱ ያለን መሆናችንን ለማሳየት እንፈልጋለን፡፡ በሽግግሩ እኛም ተሳትፎ እንድናደርግ እና ከገንቢ ቡድኑ ጋር አብረን እንድንቆም እና ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ በመቆም ከባዱን ሸክም አብረን እንድንሸከም እንፈልጋለን፡፡

(በአሮጌው ትውልድ ያለን ሰዎች ከባዱን ሸክም ለሚሰሩት ውኃ በማቀበል ከጎናቸው በመቆም ልናግዛቸው እንፈልጋለን፡፡)

በአሜሪካ ወይም በሌላ በየትም የሚኖረውን ዲያስፖራ ኢትዮጵያዊ በዩ ትዩብ፣ በፌስ ቡክ እና በሌላ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መምራት አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡

እርሳቸው ስለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ያላቸውን ርዕይ እንዲያጋሩን እና እኛ ደግሞ ያንን ርዕይ እንዴት በማድረግ እውን ለማድረግ እንደምንችል የየእራሳችንን ድርሻ ለማበርከት መቻላችን ጠቃሚ እንደሆነ እናምናለን፡፡

አብይ አህመድን አሁኑኑ በመካከላችን እንድናገኛቸው እንፈልጋለን!

ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ምንድን ለመስማት እንደምንፈልግ፡ ሁላችንም ጆሮዎች ነን!

ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስለኢትዮጵያ ዴሞክራሲዊ ሽግግር ለመስማት እንፈልጋለን፡፡

የእርሳቸውን የፍቅር፣ የይቅርባይነት እና የዕርቅ መልዕክት ደግመን ደጋግመን ለመስማት እንፈልጋለን፡፡

ከእርሳቸው ስለሀገሪቱ ያልተበረዙ እና ያልተከለሱ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና ማህበራዊ ችግሮችን እውነታ ለመስማት እንፈልጋለን፡፡ ምን ያህል አስቸጋሪ እና አሰቃቂ ቢሆንም እውነትን እንይዛለን፡፡ ምክንያቱም እኛ የረዥም ጊዜ የችግሩ መፍትሄ አካል ለመሆን ዝግጅት አድርገናል፡፡

በአጭር እና በመካከለኛ የጊዜ ማዕቀፍ ምን ልናደርግ እንደምንችል ከእርሳቸው ለመስማት እንፈልጋለን፡፡ ስለእርሳቸው “የዲያስፖራ የአደራ ገንዘብ/Trust Fund” ማሰባሰብ ስራ በአንድ ላይ ተሳፍረናል፡፡ ሆኖም ግን ገንዘቡ በምን ዓይነት ሁኔታ በስራ ላይ እንደሚውል እና የተጠያቂነት እና ግልጸኝነት መዋቅር ዝርዝር ተግባራትን ያካተቱ መረጃዎችን ሊሰጡን ይችላሉን?

ወደ ሀገር ቤት የምንልካቸው የህዋላ ገንዘቦቻችን/remittances በተለይም በትናንሽ ኢንቨስትመንቶች ላይ የሚደረጉት የካፒታል ፍሰቶችን እንዴት ማሳደግ እንደምንችል ለማወቅ እንፈልጋለን፡፡

ለዲያስፖራ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች የቢሮክራሲያዊ እና አስተዳደራዊ ማነቆዎችን በማስወገድ የአንድ መስኮት አገልግሎት ለመፍጠር ዕቅድ ያለ መሆኑን ለማወቅ እንፈልጋለን፡፡

የቴክኖሎጂ እና የክህሎት ሽግግርን ለማሳለጥ በሁሉም የስራ መስኮች በከፍተኛ ደረጃ በቴክኒክ የሰለጠኑ እና በቂ ልምድ ያላቸው በጎ ፈቃደኞች ስላሉ ይህንን እንዴት ሊያፋጥኑልን እንደሚችሉ ለማወቅ እንፈልጋለን፡፡

ለመዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች የታክስ ማበረታቻ ዕቅዶች ስለመኖራቸው ለማወቅ እንፈልጋለን፡፡

እ.ኤ.አ በ2020 ዓ.ም የሚካሄደው ሀገር አቀፋዊ ምርጫ ነጻ እና ፍትሀዊ ስለመሆኑ ያላቸውን ዕቅዶች ማወቅ እንፈልጋለን፡፡

በይበልጥም ደግሞ በአሜሪካ የሚገኘውን መሰረተ ሰፊውን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ብዝሀ ድምጽ እንዲሰሙ እንፈልጋለን፡፡ ሁላችንም በርካታ ድምጾች ያሉን አንድ ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ በሀገራችን ነጻነት እና ዴሞክራሲ እስከሚሰፍኑ ድረስ ማንኛውንም ከባድ ሸክም ሁሉ ለመሸከም እንደምንችል እናምናለን፡፡

እኛ የኢትዮጵያ የእራሷ ትንሿ አካል ነን፡፡ ሁሉንም እሴቶች ለመወከል የሚችሉ የተለያዩ ሀሳቦች እና አመለካከቶች አሉን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስለእኛ የወደፊት ጉዳዮች፣ ስጋቶች እና ሀሳቦች እንዲያውቁ እንፈልጋለን፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስለእነዚህ ጥያቄዎች መልሶች ክብርን በጠበቀ መልኩ በመወያየት እንዲሰጡን እንፈልጋለን፡፡

በድጋሜ እንደገና ፍላጎቶቻችን እንዴት ምክንያታዊ እንዳልሆኑ በጽኑ እገነዘባለሁ፡፡ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዓቶችን በአየር ላይ በማዋል እነዚህን እና ሌሎችን በርካታ ጥያቄዎችን እንዲመልሱልን እንጠብቃለን፡፡ ሆኖም ግን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እኛን ለማስደሰት ሲሉ ከሚጠበቀው በላይ የሆነ መከራ ለመሸከም ፈቃደኝ በመሆናቸው እናመሰግናቸዋለን፡፡

በእርግጥ ለሁሉም ጥያቄዎች መልሶች እንደማይኖሯቸው እናውቃለን፡፡

ጥቂቶቻችን በሰብአዊ ኃይል ሳይሆን በአምላካዊ ኃይል ብቻ ሊመለሱ የሚችሉ ጥያቄዎችን እንደምንጠይቅ እናውቃለን፡፡

የኢትዮጵያን የዘመናት አሮጌ ችግሮች ሁሉ በአንድ ምሽት ይህም ካልሆነ ከመቶ ቀናት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው የሚያስቡ ሰዎች አሉ፡፡

የእርሳቸው፣ ሰላም እና ዕርቅ የሚለው ሀሳብ የተሳሳተ መንገድ ነው የሚሉ ጥቂት ሰዎች አሉ፡፡

በአሜሪካ የሚገኙ አብዛኞቹ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ከእርሳቸው ጎን የተሰለፉ እንደሆኑ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መቶ በመቶ ልናረጋግጥላቸው እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያዊነት፣ ፍቅር፣ ይቅርባይነት፣ እርቅ እና ሰላም የሚሉትን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ሀሳቦች በሙሉ ገዝተዋቸዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ እርሳቸውን ይወዷቸዋል! ከዚህ በላይ ምን ሊባል ይችላል?

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንኳን በሰላም ወደ አሜሪካ መጡ! የእኔ የግል የእንኳን ደህና መጡ ምኞት መግለጫ፣

ወደ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ እንኳን በደህና መጡ በማለት መልካም ምኞቴን እገልጽልዎታለሁ!

የእርስዎን ጉብኝት እንደ ታሪክ ሂደት ሳይሆን እንደ ታሪክ መጀመሪያ አስደማሚ ጊዜ አድርጌ እቆጥረዋለሁ፡፡

የዲያስፖራ ሕዝቦች ለየሀገሮቻቸው እጅግ በጣም አስፈላጊዎች መሆናቸውን በአፍሪካ ታሪክ የአፍሪካ መሪዎች ወደ ዲያስፖራ ህዝቦቻቸው በመሄድ እና በመጎብኘት ለአፍሪካ መሪዎች ትምህርት የሚሆን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍተዋል፡፡

ዘመናትን ያስቆጠረውን የልመናን ባህል ከኢትዮጵያ ምድር ጠራርጎ ለማስወገድ የተጀመረውን እና ሁሉንም የሚላከውን ገንዘብ የኢትዮጵያ የአደራ ገንዘብ/Ethiopian Diaspora Trust Fund እየተባለ በሚጠራ በአንድ ትልቅ ቋት ውስጥ የሚያስቀምጠውን የእርስዎን ሀሳብ እወደዋለሁ፡፡

አንድ ብልህ ሰው በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር፣ የሰው ፍጡራን ሁሉ ባዶውን ነገር ወደ አንድ ነገር የመቀየር የተለዬ ችሎታ አላቸው፡፡ አረሞችን ወደ አዝመራነት፣ ሳንቲሞችን ወደ ሀብትነት የመቀየር፡፡“  በተመሳሳይ መልኩ እኔም ከዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን የምጠብቀው በአደራ ገንዘቡ እንደዚህ ዓይነት ስራ እንዲሰራ ነው፡፡ የልመና ባህላችንን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ሳንቲሞቻችንን ወደ ሀብት ልንቀይራቸው እንችላለን፡፡

በዩኤስ አሜሪካ የምትገኙ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን “ሀብት ከተበታተነ ሕዝብ” (ሀከሕ) /Wealth from Mass Dispersion የሚለውን እንድታስቡ እፈልጋለሁ፡፡ በአንድ ቀን ከማኪያቶ ወጪያችን አንድ ዶላር በመቀነስ እና ከሌላ ገንዘባችን በማሰባሰብ ሀገራችንን ለማገዝ ዝግጁ፣ ብቃቱ ያለን እና ፈቃደንነቱ ያለን ሰዎች ነን፡፡

እንደዚሁም ሁሉ በዩናይትድ ስቴትስ የምንገኝ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ሀገራችንን ለማገዝ እንድንችል የቴክኒክ ድጋፍ ቡድን (ቴድቡ) ለመሆን እንደምናስብ እንድታስቡ እፈልጋለሁ፡፡ በሁሉም የስራ መስክ የሚገኙ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ምሁራን እና ባለሞያዎች በአንድነት በመነሳት በፈቃደኝነት “የአብይ አህመድ-ኢትዮጵያ ቡድን” በማለት ፈርመው ተቀላቅለዋል፡፡ በየስራ መስኩ የምትገኙ ሁላችሁም ባለሞያዎች “የአብይ አህመድ-ኢትዮጵያ ቡድንን ለመቀላቀል እንኳን በደህና መጣችሁ፡፡ ተደመሩ፡፡

የፍቅር፣ የይቅርባይነት እና የእርቅ መንገድ መልካሙ መንገድ መሆኑን አብዛኞቻችሁ የዲያስፖራ አባላት ያመናችሁ መሆናችሁን ላረጋግጥላችሁ እችላለሁ፡፡ በሰለጠነ መንገድ፡፡ ወደ ዘላቂ ሰላም የሚወስደው መንገድ፡፡ ወደ ኢኮኖሚ ልማት፣ ብልጽግና እና ክብር የሚወስደው ጎዳና፡፡

መልካሙ መንገድ ድልድዮችን በመገንባት እና ግንቦችን በማፍረስ መደመር መሆኑን አብዛኞቻችሁ የዲያስፖራ አባላት ያመናችሁ መሆናችሁን ላረጋግጥላችሁ እችላለሁ፡፡

በበርካታ የጎሳ ቡድኖች እናንተ ፍጹም የሆናችሁ ድልድዮች መሆናችሁን የተገነዘባችሁ እንደሆናችሁ እርግጠኛ ነኝ፡፡

ግንቦችን እጠላለሁ፡፡ ድልድዮችን እወዳለሁ፡፡

እ.ኤ.አ ነሀሴ 2016 ዓ.ም እንዲህ በማለት ጽፌ ነበር፣ “ጥላቻ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ነጻነት፣ ዴሞክራሲ እና ሰብአዊ መብቶች መካከል አንድ የሚደረመስ ግንብ ሆኖ ቆሟል፡፡ የቅድመ አብይ አገዛዝ ጥላቻን በመሳሪያነት እና በፖለቲካ መጠቀሚያነት ተጠቅሞበታል፡፡ ሆኖም ግን የቆሙት የጭቃ ግንቦች በአሁኑ ጊዜ በሕዝባዊ አመጽ የእሳተ ገሞራ የኃይል ግፊት አማካይነት በገነቧቸው ሰዎች በእራሳቸው ላይ እየፈረሱባቸው ነው፡፡“

ሕዝቦች ጥሩንባቸውን በከተማው አካባቢ ከነፉ በኋላ የእያሪኮ ግንብ ተደረመሰ፡፡ በምድሪቱ ላይ አዲስ ዓይነት የሰላም ዘመን ነገሰ፡፡

እ.ኤ.አ ሰኔ 1987 ዓ.ም የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬጋን ምዕራብ በርሊን በመሄድ እንዲህ በማለት ጮኸው ነበር፣ “ይህንን ግንብ አፍርሱ!“ ያ ግንብ ፈረሰ፡፡

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2018 ዓ.ም ሁሉም ኢትዮጵያውያን እንዲህ በማለት በመጮህ ላይ ይገኛሉ፣ “እንዳንገናኝ ክልሎን የሚገኘውን ይህንን የክልል (አፓርታይድ ዓይነት ባንቱስታነስ) ግንብ በማፍረስ ህዝቦች ወደ አንድ እንዲመጡ ድልድዮችን በመስራት እንረባረብ፡፡“

የክልሉ ግንብ ተደርምሶ ይንኮታኮታል!

በመከፋፈል ወይም የግንብ አጥር በመገንባት ማንም ታላቅ የሆነ ሀገር የለም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮጵያም የክልል ግንቦች በመከፋፈል በፍጹም ታላቅ ልትሆን አትችልም፡፡

ሆኖም ግን ሁሉም ታላላቅ ሀገሮች ታላቅ የሆኑት በአንድ ላይ በመሆን ወይም ደግሞ በዘመነኛው አባባል በመደመር ነው፡፡

የመደመር መልካም ምሳሌ የሚሆን ከዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ በላይ በዓለም ላይ ምንም ዓይነት ሀገር የለም፡፡

በየትኛውም የዓለም ክፍል የሌለ በአሜሪካ በርካታ አመለካከቶች እና ሀሳቦችን የበለጠ ለመግለጽ እንችላለን፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ በበርካታ ብዝሀነቷ እና እንደ አንድ ሕዝብ በመሆን አንድነት ያላት በመሆኗ ምንክንያት ታላቅ ሀገር ናት፡፡

የአሜሪካ ሬፐብሊክ መስራች አባቶች የ”መደመር” ሀሳብዎን በሕገ መንግስቱ መግቢያ ላይ በመንደርደሪያነት አስገብተውታል፡፡ የበለጠ ፍጹም የሆነ ግንኙነት ለመፍጠር ለተነሳሽነት ተጠቅመውበታል፡፡ የዩኤስ ሕገ መንግስትን የማርቀቅ ዋናው ዓላማ የአሜሪካ የነጻነት አብዮት ከተካሄደ በኋላ የተበታተኑትን ግዛቶች ወደ አንድ ለማምጣት እና ህዝቡን አንድ በማድረግ “እኛ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ሕዝቦች“ እውነተኛ ሉዓላዊነታችን የተከበረ እና ከሁሉም በላይ ዋናው ተግባሩ “የበለጠ ፍጹም የሆነ ግንኙነት ለመፍጠር” ወይም “መደመር” ከበርካታዎቹ አንዱ እንደሆነ አስቀምጠውታል፡፡

የአሜሪካ ሬፐብሊክ መስራች ከሆኑት መካከል አንዱ የሆኑት ቶማስ ጀፈርሰን እንዲህ ብለው ነበር፣ “መንግስት ሕዝብን መፍራት ሲጀምር ነጻነት አለ፡፡ ሕዝብ መንግስትን መፍራት ሲጀምር ግን የጭቆና አገዛዝ አለ፡፡“ ከዚህም በተጨማሪ ጀፈርሰን ጋዜጦች ሳይኖሩ ከሚኖር መንግስት እና መንግስት ሳይኖር ከሚኖሩ ጋዜጦች መካከል እንድመርጥ ዕድሉ ቢሰጣቸው የመጨረሻውን እንደሚመርጡ ተናግረዋል፡፡

ስለሕግ የበላይነት፣ ስለመንግስት ተጠያቂነት እና ግልጸኘነት እርስዎ እየሰበኩ ያሉት በእኔ አመለካከት የጀፈርሰንን ምርጥ ስራ ነው፡፡ ፕሬሱ በሙስና፣ በአጭበርባሪነት፣ በብክነት እና ስልጣንን ከሕግ አግባብ ውጭ መጠቀምን በማስመልከት እያጋለጠ ስራውን በሚገባ እንዲሰራ እና የሕዝብ ጠባቂ እንዲሆን የሚሰብኩ ከሆነ ይህ የጀፈርሰን ምርጥ ስራ ነው፡፡

ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዲመጡ በኩራት እንደምመኝላቸው ያለ መሪ ኢትዮጵያ ታገኛለች ብዬ በፍጹም አስቤውም አላውቅም፡፡ ይህ ማለት ግን አልሜ አላውቅም ማለት አይደለም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአሁኑ ጊዜ የማልመው አንድ ነገር አለ፡፡ እርሰዎን ከ27 ዓመታት በፊት ብታገኝዎ ኖሮ ኢትዮጵያ ምን ያህል ኃያል ሀገር ትሆን ነበር?

ወቼ ጉድ! ወቼ ጉድ!

ደህና፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ነጻዋ እና ወደ ጀግኖቹ ምድር በኩራት እንኳን በደህና መጡ እላለሁ!

እንደመር! አንቀነስ! እንባዛ! አንከፋፈል!

ኢትዮጵያዊነት ዛሬ፡፡

ኢትዮጵያዊነት ነገ፡፡

ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም! 

 

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ሀምሌ 18 ቀን 2010 ዓ.ም     

Similar Posts