ማስታዋሻ ቁጥር 12፡ ለአብይ አሕመድ ቡድን አጋዥ የሚሆን ከኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ ተደማሪ ኃይል ስለመመልመል

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

ለውጥ ጥቂት ንቁ የሆኑ የለውጥ አራማጆችን እና ከዳር ተቀምጠው የሚገኙ በርካታ ተመልካቾችን አይፈልግም፡፡ ለውጥ በጨዋታ ሜዳው ውስጥ ሁላችንም ገብተን እንድንጫወት የሚፈልግ እና የእራሳችንን ድርሻ እንድናበረክት የሚደረግበት ሂደት ነው፡፡ 

ለውጥ ተመልካቾች ከዳር ተቀምጠው የሚመለከቱት እና መልካም ውጤት ሲገኝ የሚጨበጨብለት፣ ውጤቱ ጥሩ ሳይሆን ሲቀር ደግሞ ትችት እና ወቀሳ የሚቀርብበት የጨዋታ ዓይነት አይደለም፡፡ (ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እ.ኤ.አ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ካደረጉት ንግግር ተወስዶ የተተረጎመ)

የመልካም ሀሳብ አላሚ እና የጽናት ሰው እንሁን፡፡ ማንዴላ የኢትዮጵያ ወጣቶች የተወደደውን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ለመፍጠር እና የመልካም ሀሳብ አላሚዎች እንድንሆን ያስተምሩናል፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ መልካም ቀኖች እየመጡ ነውና፡፡

እ.ኤ.አ ታህሳስ 13 ቀን 2013 ዓ.ም አቅርቤው በነበረው ትችቴ ለኢትዮጵያ ወጣቶች የሚል ምክር አቅርቤ ነበር፡፡

እንደመር! አንቀነስ! እንባዛ! አንከፋፍል! 

በነብይነት ባህል ለኢትዮጵያ ምሁራን መናገር [1]

የጸሀፊው ማስታዋሻ፡ በኢትዮጵያ ለአብይ አህመድ ቡድን አባዥዎች ምልመላ በድፍረት እራሴን የሾምኩ ዲያስፖራ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ቡድናቸው በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ አዎንታዊ ነገሮች እና የመጨረሻ ለውጥ እንዲመጣ ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ሆኖም ግን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ቡድናቸው ብቻውን ሀገሪቱ ከገጠማት የምጣኔ ሀብት ቀውስ ሊያድናት አይችልም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ከብዙ ዘመናት ጀምሮ ተጋርጠውብን የቆዩትን የውስጥ እና አህጉራዊ ችግሮች በመፍታት ድህነትን፣ ድንቁርናን እና ደካማ የጤና አገልግሎቶችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ማስወገድ አይችሉም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ቡድናቸው ዕገዛን ይፈልጋሉ! አሁኑኑ፡፡

ስለሆነም በይፋም ሆነ ይፋዊ ባልሆነ፣ ወይም ደግሞ በቀጥታም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ፣ ወይም መደበኛም ሆነ መደበኛ ባልሆነ መልኩ በእኔ በእራሴ ተነሳሽነት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ  መንግስት በዲያስፖራው ውስጥ ያለውን የምሁራን እና ባለሞያዎችን ኃይል እንዲደምር እና ኢትዮጵያን ከአምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሽግግር እንዲያደርግ፣ ከጎሳ ጭቆና ወደ ብሄራዊ አንድነት፣ ነጻነት እና ከጥፋት ለመዳን ከጎናቸው እንዲሰለፉ ለማድረግ በእራሴ ህሊና ወስኛለሁ፡፡

ለበርካታ ዓመታት የኢትዮጵያን ምሁራን ወገኖቼን በተለይም በዲያስፖራው የሚገኙትን በኢትዮጵያ ውስጥ ለሰብአዊ መብት መከበር እና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በንቃት እና በቀጥታ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ሳቀርብ ቆይቻለሁ፡፡

ሆኖም ግን ሳቀርባቸው የቆየኋቸው ተደጋጋሚ ጥሪዎች ጆሮ ዳባ ልበስ ተብለው የቆዩ መሆናቸውን ሳስብ ሀዘን ይሰማኛል፡፡

አሁን እያቀረብኩት ባለው በዚህ ማስታዋሻዬ ኢትዮጵያን ከጎሳ ዘረኛ አምባገነናዊ ስርዓት ወደ ብዙሀን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት፣ ከወሮበላ ዘራፊ መንግስት ወደ ተጠያቂነት እና ግልጽነት ወዳለው መንግስት ሽግግር ለማድረግ ሌት እና ቀን በመስራት ላይ የሚገኙትን ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ቡድናቸውን ለማገዝ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ምሁራን እና ባለሞያዎች ከጎናቸው እንድንሰለፍ እንደገና በድጋሜ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

በአሁኑ ጊዜ ለምናካሂደው ተግባራዊ ድርጊት እያቀረብኩ ያለሁት ጥሪ ግን የተለዬ ነው፡፡

የአሁኑ ጥሪዬ የኢትዮጵያ የነብስ አድን ጥሪ ነው፡፡

ነብሳችን ከአንድ የጭቆና አገዛዝ ቡድን ወደ ሌላ የጭቆና አገዛዝ ቡድን እንዳትሸጋገር ለማዳን የቀረበ ጥሪ ነው፡፡

የኢትዮጵያን ነብስ ለማዳን እና ነጻ ለማድረግ የቀረበ ጥሪ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በእራሷ ቀጥ ብላ እንድትቆም የቀረበ ጥሪ ነው፡፡

ኢትዮጵያ እንድትነሳ፣ እንድትራመድ እንድትቆም እና እንድትደመር የቀረበ ጥሪ ነው፡፡

በዲያስፖራው ማህበረሰብ ውስጥ ለሚገኙት የኢትዮጵያ ምርጥ እና የብሩህ አእምሮ ባለቤቶች በአሁኑ ጊዜ የአትዮጵያ የፍቅር ባቡር ለመንቀሳቀስ ዝግጅት ሲያደርግ በባቡሩ ጣቢያ ሆነን ዝም ብለን በመመልከት ላይ መሆናችንን ፍጹም ግልጽ ላደርግ እፈልጋለሁ፡፡ በባቡሩ ውስጥ ለመሳፈር ወይም በባቡር ጣቢያው ውስጥ በመሆን ሳንሳፈር ለመቅረት ለመወሰን በጣም ትንሽ ጊዜ ብቻ ቀርታናለች፡፡ የአብይ ቡድንን ለመቀላቀል እና አንድ ነገር በማድረግ ነጻነትን እና ክብርን አውጆ መኖር ወይም ደግሞ ቀሪውን ህይወታችንን ምን እየተደረገ እንደሆነ፣ ምን ማድረግ እንደሚቻል እና ምን መደረግ እንዳለበት እያሰላሰልን በማቃሰት የመኖር ምርጫ አለን፡፡

በአሁኑ ጊዜ በአንድ ላይ የመቆም እና የመደመር ጊዜ ነው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ለአንድ መቶ ሚሊዮን ሕዝቦች ሁነኛ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አሁን መጀመር አለብን!

ለሕዝብ የተሻለ ነገር ለማድረግ እና አንድ ነገር ለማድረግም ዕድሉ እያለህ ያንን ነገር ማድረግ ካልቻልክ ጊዜህን በምድር ላይ በከንቱ አባክነሀል፡፡”

አሁን በቅርቡ ለመገናኛ ብዙሀን በሰጠሁት መግለጫ ለኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ ምሁራን እና ባለሞያዎች ስንጠብቀው የቆየነው ጊዜ የደረሰ (ወይም ለጥቂቶቻችን ደግሞ ለማስወገድ የምንሞክረው) መሆኑን አውጃለሁ፡፡

አንዳችን እና እያንዳንዳችን የኢትዮጵያ እውነተኛ ልጅ መሆናችን የሚታይበት ወይም ደግሞ ግድ የሌለን እና ከውጭ የቆምን የውጭ ተመልካች ሰዎች እና እንግዶች መሆናችን የሚጋለጥበት ቅጽበት ነው፡፡

በአብይ አህመድ የኢትዮጵያ የፍቅር ባቡር ለመሳፈር ወይም ደግሞ ባቡሩ ባቡር ጣቢያውን ለቆ ሲወጣ ለመመልከት ብቻ የተዘጋጀን መሆናችን እና በመጨረሻም ወደ ታሪክ ቆሻሻ የምንጣል ለመሆናችን የምንወስንበት ጊዜ አሁን ነው፡፡

የኢትዮጵያ የፍቅር ባቡራችን ወደ አንድ መዳረሻ ብቻ ሊመራ የሚችል አንድ ሀዲድ ብቻ ነው ያለው፡፡

የኢትዮጵያ የፍቅር ባቡር መዳረሻ “የተወደደች/ዉድቷ ኢትዮጵያ” እየተባለች የምትጠራ በተራራው ጫፍ ላይ እያንጸባረቀች የምትገኝ ከተማ ናት፡፡

ወደ ባቡሩ ምንም ዓይነት ጓዝ እና ጭነት ማምጣት አያስፈልግም፡፡ ነጻ ጉዞ ነው፡፡ ከስራ መሳሪያዎቻችሁ እና ከሙያዎቻቸሁ ጋር ብቻ መምጣት ነው፡፡

ሳይንቲስቶች፣ አጉሊ መነጽሮቻችሁን ማይክሮስኮፖቻችሁን እና የርቀት ማሳያ መሳሪያዎቻችሁን/ቴሌስኮፖቻችሁን አምጡ፡፡ ሐኪሞች እና የጤና ባለሞያዎች የልብ ማዳመጫ እና የሙቀት መለኪያ መሳሪያዎቻችሁን አምጡ፡፡ መሀንዲሶች እና የስነ ህንጻ መሀንዲሶች ፕሮትራክተሮቻችሁን አምጡ፡፡ የሕግ ባለሞያዎች የሕግ መጽሐፎቻችሁን አምጡ፡፡ መምህራን ጠመኔዎቻችሁን እና ወረቀቶቻችሁን አምጡ፡፡ የባንክ እና የቢዝነስ ባለሞያዎች የተሰመሩ ወረቀቶቻችሁን/spreadsheets አምጡ፡፡ ጸሐፊዎች እና ተመራማሪዎች ህትመቶቻችሁን አምጡ፡፡ አርቲስቶች የቀለም ቡርሾቻችሁን እና የሙዚቃ መሳሪያዎቻችሁን አምጡ፡፡ ሁላችሁም የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ምሁራን እና ባለሞያዎች የምትሰሩባቸውን መሳሪያዎች በሙሉ አምጡ፡፡ “የተወደደችዋን ኢትዮጵያን” በምንገነባበት ቦታ ሁላችሁንም እንፈልጋችኋለን፡፡

ኢትዮጵያ በልግስና ትታደላለች፡፡

በዲያስፖራ ወይም በሌላ የሚኖረው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በፈቃደኝነት ቦታ እና ሚና አለው፡፡

እነዚህን ነገሮች የምለው እንዲሁ በአላሚነት ህልመኛ ነው ልትሉ ትችላላችሁ፡፡

አዎ፣ ህልመኛ አላሚ ነኝ፡፡ ከቀድሞ ጀምሬ ሳልም የቆየሁ፡፡

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2012 ዓ.ም እንዲህ የሚል አንድ ህልም ብቻ እንዳለኝ ተናግሪያለሁ፡ “ኢትዮጵያ በሰላም ጎዳና“

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2012 ዓ.ም በተጨማሪ መልካም ነገር እና ይቅርባይነት በሚባሉ መንገዶች ላይ ጉዞ እንደምናደርግ ተናግሪያለሁ፡፡

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2018 ዓ.ም ህልሜ እውን ሆነ፡፡ በመጨረሻም በመልካም ነገር እና በይቅርባይነት መንገድ ላይ አብይ አህመድን አስከትለን በመጓዝ ላይ እንገኛለን፡፡

ስለሆነም ለሁሉም ዲያስፖራ የኢትዮጵያ ምሁራን እና ባለሞያ ወገኖቼ ከአብይ አህመድ ጋር በመቀላቀል እና በኢትዮጵያ የፍቅር ባቡር በመሳፈር እንዲህ የሚለውን የጆን ሌኖን መዝሙር እየዘመራችሁ እንድትጓዙ ሞቅ ያለ ግብዣዬን አቀርብላችኋለሁ፡

ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሰላም እንደሚኖሩ አስቡ፡፡

ህልመኛ ነህ ልትሉን ትችላላችሁ፡፡ ሆኖም ግን እኔ ብቻ አይደለሁም፡፡

ሆኖም ግን እንደ እኔ ያሉ ሌሎች አንድ መቶ ሚሊዮኖች አሉ፡፡

አንድ ቀን አሁን በቅርቡ ወደ እኛ ልትቀላቀሉ ትችላላችሁ፡፡ እናም ኢትዮጵያ አንድ ትሆናለች፡፡

.. ሀምሌ 12 ቀን 2012 . ለኢትዮጵያ ምሁራን እና ባለሞያዎች ያስተላለፍኩት ትንቢታዊ መልዕክት፣

እ.ኤ.አ ሀምሌ 12 ቀን 2012 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ምሁራን ካስተላለፍኩት መልዕክት ይልቅ አሁን እያስተላለፍኩት ያለው መልዕክት ለእውነታ የበለጠ እንደሚደውል አምናለሁ፡፡

እ.ኤ.አ ሀምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም ለኢትዮጵያውያን ምሁራን እና ባለሞያዎች እንዲህ የሚለውን አስቸኳይ ሁኔታ በመጥቀስ የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፊያለሁ፡

በአሁኑ ጊዜ በአንድ ላይ መቆም እና መደመር አለብን!

በጊዜ ሂደት በለውጥ ላይ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ምሁራን በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ከዳር ቆመው መመልከት አይችሉም፡፡ ቶማስ ፔይን እንዳስቀመጡት የበጋ ወታደሮች፣ የጸሐይ ብርሀን ጀግኖች፣ የነጻነት፣ የዴሞክራሲ እና የሰብአዊ መብት አጠባበቅ የመልካም አየር አራጋቢ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ከጭቆና ጋር በንቃት አሁኑኑ ግብ ግብ መግጠም አለባቸው፡፡ እናም በኋላም ለአገዛዝ ስልጣን ከሚዘጋጁት ጋር መታገል አለባቸው፡፡ አሁን ከሕዝቡ ጋር መቆም አለባቸው፡፡ ከዳር በመቆም መመልከት የለባቸውም፡፡

የኢትዮጵያ ምሁራን ኢትዮጵያን ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሱ ለማሸጋገር የመረጃ እና የእውቀትን ክፍተት ለመሙላት እና ከአዲስ እና ፈጠራ ከታከለባቸው ሀሳቦች ጋር በመምጣት እራሳቸውን ማደራጀት አለባቸው፡፡

ኢትዮጵያን የሚያጠኑ ሁሉም ምሁራን በአሁኑ ጊዜ አስቸኳይ ሁኔታ ገጥሟቸዋል፡፡ እስከ አሁን ድረስ በእራሳቸው ላይ ነግሶ የቆየውን ዝምታ ወይም ደግሞ እራሳቸውን በሾሙ እና ለእራሳቸው ብቻ ትክክለኛ የሆነ ዴሞክራሲን አንግበው ሌላውን እየተቹ ባሉት ላይ ዝምታን በማስወገድ ኢትዮጵያ ከአምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ በምታደርገው ሽግግር እገዛ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ በመስቀለለኛ መንገድ ላይ ቆማለች፡፡ የለውጥ ምልክቶች በጉልህ ይታያሉ…

…የኢትዮጵያ አምባገነኖች የመንፈላሰሻ ጊዜዎች ተጠናቀዋል፡፡ እነዚህ እድለ ቢስ ቀኖች የተስፋ መቁረጥ እርምጃዎችን በመውሰድ የመጨረሻ ጨዋታቸውን በመጫወት ላይ ለሚገኙት እድለቢስ አምባገነኖች ቀኖች ናቸው፡፡

የኃይማኖት ጽንፈኝነት የእሳት ነበልባል ለማቀጣጠል ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ በሁሉም መንገዶች ላይ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብቶችን ለማዳፈን የሞት ሽረት ትግል በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ለመኖር ለመናገር የሚዘገንን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡

በመጨረሻም በአሁኑ ጊዜ እየተገነዘቡት ያለውን ሙዚቃቸውን እና እንዲህ የሚለውን የጋንዲን እውነተኛ መልዕክት በመጋፈጥ ላይ ይገኛሉ፡

ጨቋኝ አምባገነኖች እና ገዳዮች አሉ፡፡ ለጊዜው የማይበገሩ መስለው ይታያሉ፡፡ ሆኖም ግን በመጨረሻ ሁልጊዜ ይወድቃሉ፡፡ ይህንን ሁልጊዜ አስቡ፡፡“

ስለሆነም በመጨረሻው ጨዋታ ጨቋኞች እና ገዳዮች የዕቅድ መፍትሄ እና እንስሳዋ እንዳለችው የድሮ አባባል እንዲህ የሚለውን የመጨረሻ የጥሩምባ ካርዳቸውን ይመዛሉ፡ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል

ሆኖም ግን እነርሱ ያሰቡት የጎርፍ ማዕበል፣ የእሳት ቋያ እና የመሬት መንቀጥቀጥ ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይፈጥር በመንገድ ላይ ሁሉ ያገኘውን እነርሱን ጭምር ዶግ አመድ እንደሚያደርግ አልተገነዘቡትም፡፡

…ሆኖም ግን እነዚህ ቀኖች በተጨማሪ ለህዝቡ የተስፋ ቀኖች ናቸው፡፡ በመጨረሻ በጭቆና አገዛዝ ጉድጓድ ታነል ላይ የብርሀን ብልጭታ ሊመለከቱ ይችላሉ፡፡ ወደ ነጻነት፣ ዴሞክራሲ እና የሕግ የበላይነት የሚያመላክቱ ቀንዲሎችን መመልከት ይችላሉ፡፡

የጠረጴዛዎች የእይታ ድባብ በፍጹም ተቆይሯል፡፡ ህዝቡ ጨቋኞችን መፍራቱን አሽቀንጥሮ ጥሎታል፡፡ ጨቋኞች ግን ህዝቡን መፍራታቸውን በማሳየት ላይ ናቸው፡፡ ህዝቡ ምን ሊያደርግ እንደሚችል በፍርሀት ይጨነቃሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ህዝቡ እየተበሳጨ እና እየተራበ ነው፡፡ ንዴት ወደ ቁጣ፣ ጥላቻ እና የኃይል እርምጃ ይቀየራል፡፡ ረሀብ ሰውነትን ብቻ አይደለም የሚያጠፋው ሆኖም ግን ነብስን ጭምር እንጅ፡፡ የተራበ ሰው የተበሳጨ ሰውም ጭምር ነው፡፡ ለዚህም ነው በጨዋታው የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ጨቋኞች ፍርሀት እንደሚኖር የተጻፈው፡፡

የኢትዮጵያ ልሂቃን እና ምሁራን የሰውን ጨቋኝነት ብቻ ሳይሆን የርሀብን፣ የበሽታን፣ የድንቁርናን እና የድህነትን ጨቋኝነት ጭምር ለማጥፋት ሙያቸውን፣ ክህሎታቸውን እና እውቃታቸውን አንዱ ለሌላ ማካፈል አለባቸው፡፡ ጨቋኝነት በሁሉም አቅጣጫ መወጋት አለበት፡፡ የረሀብ እና የድርቅ ጨቋኝነትን ለመዋጋት ዕቅድ ለመንደፍ እና ድል ለመቀዳጀት የግብርና ባለሞያዎች ተግባር ነው፡፡ የኢትዮጵያ የትምህርት ባለሞያዎች በተስፋ እጦት የበሰበሰውን የትምህርት ጨቋኝነት ስርዓት ለመገዳደር መነሳት አለባቸው፡፡ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ሀኪሞች በሕዝቦቻችን ላይ ስቃይ ያነገሰውን የበሽታን ጨቋኝነት ለማጥፋት ኃይላቸውን ማሰባሰብ አለባቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በጭጋጎ በመስራት ላይ ያሉት ኢትዮጵያውያን ሀኪሞች ብዛት በመላ ኢትዮጵያ ተሰራጭተው ከሚገኙት ሀኪሞች የበለጡ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶች፣ መሀንዲሶች፣ ሳይንቲስቶች፣ የሕግ ባለሞያዎች፣ የታሪክ ምሁራን፣ አርቲስቶች፣ ተመራማሪዎች፣ ወዘተ. ወደ አንድ በመምጣት ህብረት መፍጠር እና ጨቋኝነት የሚገለጽባቸውን ሁሉንም ነገሮች መዋጋት አለባቸው፡፡

በእራስ የሙያ መስክ የእራስን ክህሎት መጻፍ እና መናገር የስራው የመጀመሪያ ምዕራፍ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የአካዳሚክ እና ምሁራን ማህበረሰብ አባላት ከዚህም በተጨማሪ የአደባባይ ምሁራን እንድትሆኑ እማጸናለሁ፡፡ ኢንተርኔት በዜጎች እና በኃይለኛ መንግስታት መካከል ትልቅ እኩልነትን ለማምጣት ብቻ የተቀመጠ መሳሪያ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን በምሁራን እና በደናቁርት  (አውቀው ደናቁርት በሆኑት እና በድንቁርና ለታወሩት) መካከልም ጭምር የሚሰራ እንጅ፡፡

በበርካታ መንገዶች ኢንተርኔት ሀሳብን በነጻ ለመግለጽ ሙሉ ነጻነት ይሰጣል፡፡ የተማሩ ምሁራን እና የአካዳሚክ ሰዎች በአንድ በኩል እና ለጥፋት የሚያነሳሱ ቃላትን የሚተፉ፣ ወደፊት ጥላቻ እና አለመቻቻልን የሚፈጥሩት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሕዝቦች ልቦች እና አእምሮዎች እኩል ተደራሽነት አላቸው፡፡ ሆኖም ግን ሁሉም በኢንተርኔት ከሚገኙ መረጃዎች እና ሀብቶች በጣም ውድ እና ጠቃሚ፣ ብርሀን ሰጭ እና በተግባር ለመፈጸም የሚችሉ ጥቂት ነገሮች ብቻ አሉ፡፡

እ.ኤ.አ ሀምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም “ኢትዮጵያ፡ ለመናገር እና ለመጻፍ ነጻ ያልሆነች ሀገር?” በሚል ርዕስ አዘጋጅቸው የነበረው ትችቴ እ.ኤ.አ ሀምሌ 2018 ዓ.ም የእውንነት ትርጉሙን አግኝተናል፡፡

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2018 ዓ.ም አብይ አህመድ ከእኛ ጋር ለመገናኘት፣ ለመነጋገር እና እኛን ለማፋጠጥ ይመጣሉ፡፡

ምንም ዓይነት ምላሽ ያላገኘው ጥያቄ ግን የአብይ አህመድን ማፋጠጥ ምላሽ በመስጠት ከቡድናቸው ጋር መቀላቀል እና ወደፊት በመጓዝ የታሪክ ምስክር መሆን ነው፡፡

ለመብቶቻችሁ ንቁ፣ ተነሱ እና የአብይ አህመድን ቡድን ተቀላቀሉ፣

በአካዳሚክ፣ በሳይንስ፣ በኢንጅነሪንግ እና ቴክኖሎጂ፣ በጤና አገልግሎቶች፣ በቢዝነስ እና በሌሎች መስኮች የምትገኙ የዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፡

በአሁኑ ጊዜ የሀገራችን ዕጣ ፈንታ እውነታው በውል ባልታወቀበት ሁኔታ ላይ ተንጠልጥሎ ይገኛል፡፡

በአስደናቂው እና በረዥሙ ታሪካችን ታይቶ በማያውቅ መልኩ በአዲስ ዘመን ውስጥ ገብተናል፡፡

ሀገራችን በነጻነት ብርሀን እና በረዥም የጭቆና አገዛዝ ጥላ፣ ለወዲፊት ባለ ተስፋ እና ባለፈው አስከፊ ስርዓት የፍርሀት ቆፈን፣ በከፍተኛ የፍቅር መንገድ፣ ይቅርባይነት እና በዕርቅ፣ በጥላቻ፣ በበቀል እና  በህዝባዊ አመጽ መንገድ መካከል ተንጠልጥላ ትገኛለች፡፡

የብርሀኑ ጎን ኃይሎች ኢትዮጵያን የነጻነት ዴሞክራሲ ጸሐይ ወደምትወጣበት አቅጣጫ በኃይል በመሳብ ላይ ይገኛሉ፡፡

ሆኖም ግን የጨለማው ጎን ኃይሎች ያለ የሌለ ኃይላቸው ሁሉ ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ወደ ጨለማው ምድራቸው እንደገና ወደኋላ በመጎተት ላይ ይገኛሉ፡፡

የጨለማው ምድር ኢትዮጵያ ማለት ያለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያ ናት፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት 27 ዓመታት በዓለም የተዋረደች፣ የጭቆና፣ የስቃይ፣ የሙስና፣ በሰው ልጆች ላይ ወንጀል የመፈጸሚያ፣ የሕግ የበላይነት ሙሉ በሙሉ የተደፈጠጠባት፣ የሕዝብ ድምጽ የተሰረቀባት እና የጎሳ አፓርታይድ የተንሰራፋባት ሀገር ሆና ቆይታለች፡፡

በአሁኑ ጊዜ በጭቆና አገዛዝ ለረዥም ጊዜ ያደረግነው ጉዞ የመጠናቀቂያ ጊዜ መድረሱን ምስክር ሆነን እንገኛለን፡፡

በአሁኑ ጊዜ 13 ወራት የጸሐይ ብርሀን በሚንጸባረቅባት ምድር ላይ የነጻነት እና የዴሞክራሲ ብርሀን ብልጭታ ማየት ጀምረናል፡፡

ከጨለማው ምድር 13 ወራት የጸሐይ ብርሀን ወደሚንጸባረቅባት ምድር ሙሉ ለሙሉ የምንሸጋገር ለመሆናችን ምንም ዓይነት ዋስትና የለንም፡፡

በጣም አጥብቆ ከያዘን ጨለማ ውስጥ በአንድ ጊዜ በቀላሉ መንጠቅ ብሎ ለመውጣት አይቻልም፡፡

በአሁኑ ጊዜ የጨለማው ጎን ኃይሎች ማንኛውንም ዋጋ በመክፈል እና ማንኛውንም አስፈላጊ መስሎ የታያቸውን ነገር ሁሉ በማድረግ ግዛታቸውን ለማስጠበቅ የሞት የሽረት ትግል በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

በየቀኑ ምን በማድረግ ስራ ላይ ተሰማርተው እንደሚውሉ እየተመለከትን ነው፡፡ በጨለማ ምን እያደረጉ እንዳሉ የምናውቀው ነገር የለም፡፡

በሰላማዊ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ መካከል ላይ በጠራራ ጸሐይ ቦምብ በማፈንዳት ሁለት ሰዎችን የመግደል እና ከ150 በላይ ሰላማዊ ሰዎችን ከማቁሰል ወደኋላ አላሉም፡፡

በጎሳዎች መካከል ግጭት እና የጥላቻ እሳት ለመለኮስ ወደ ጠረፍ አካባቢ የሀገሪቱ ክፍሎች ይጓዛሉ፡፡

የጎረቤት ሀገር ወታደሮች በማስመሰል እና የእነዚህኑ የውጭ ወታደሮችን መለያ ልብሶች/ዩኒፎርሞች በመልበስ በሀገሮች ወሰን ድንበሮች አካባቢ ግጭት ለመፍጠር በመሞከር ላይ ናቸው፡፡

ሀገራችን በእነርሱ ጉልበት ስር እንድትንበረከክ አውዳሚ የሆነ የኢኮኖሚ አሻጥሮችን በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡

የሀገራችንን መሰረተ ልማቶች ለማውደም እንዲያስችላቸው ያለ የሌለ ኃይላቸውን ሁሉ በመጠቀም ሁሉንም ነገር በመተግበር ላይ ይገኛሉ፡፡

የለውጥ ኃይሉን በማደናቀፍ ለማስቆም ሌት ቀን በመዋተት ላይ ይገኛሉ፡፡

የፍቅር፣ የይቅርባይነት እና የዕርቅ ባቡራችንን ጉዞ ለማደናቀፍ እና ለማስቆም ሌት ቀን በመታተር ላይ ይገኛሉ፡፡

ሆኖም ግን የጨለማው ጎን ኃይሎች በሰይጣናዊ ድርጊታቸው ይህን ያህል ሰይጣናዊ እና ዕኩይ የሆኑ ተግባሮችን እየፈጸሙ ባሉበት ሁኔታ የብርሀን ጎን ኃይሎች የት ላይ እና ምንስ በማድረግ ላይ ናቸው?

የብርሀን ጎን ኃይሎች በከፍተኛ የደስታ ምድር ላይ ናቸው፡፡

በከፍተኛ ደስታ ውስጥ ተውጠው ይገኛሉ፡፡ እራሳቸውን በመደመር ላይ ናቸው፡፡

በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር ከመዋል፣ ከእስራት እና ከስቃይ ተላቀው፡ የነጻነት ደስታ ስሜትን ያሸታሉ፣ ይቀምሳሉ፡፡ ለመናገር እና ለመጻፍ ነጻ ናቸው፡፡ ለመደረጃት እና ትችት ለማቅረብ ነጻ ናቸው፡፡ ሰብአዊ መብታቸው እና ክብራቸው ተከብሮ ነጻ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት 90 ቀናት ውስጥ ወይም ከዚያ በላይ በተከናወኑት ተግባራት ያልተደሰተ አእምሮው ጤና የሆነ ሰው ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡

ሆኖም ግን የእኔ ደስታ በስጋት የታጀበ ነው፡፡

ከመጠን በላይ በእራሳችን የተማመን እና በደስታ ተውጠን የመገኘታችን ሁኔታ ያስፈራኛል፡፡

የጨለማው ኃይል ወታደሮች በጨለማ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ለማየት እችላለሁ፡፡

ከተቀዳጀነው ድል መንጋጋ ውስጥ ድልን ለመቀማት እና ወደ ጨለማው ምድር ለማስገባት  አሻጥር እና ደባ ሲሰሩ ለማየት እችላለሁ፡፡

በእራሳችን ላይ ከፍተኛ አደጋ በመደቀን ብቻ የጨለማው ጎን ኃይሎችን ዝቅ አድርገን ወይም አሳንሰን ለማየት እንችላለን፡፡

ከጨለማው ጎን ኃይሎች ነጻ ሆነን ለዘላለም ለመኖር እና ተባብረን ለመቆም ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆን ይኖርብናል፡፡

ከተባበርን እንቆማለን  ከተከፋፈልን እንወድቃለን፡፡ እናም ለቀን ጅቦች እራት እንሆናለን!

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለማለት እንደሚወዱት ስንደመር በአንድነት እንቆማለን፡፡

ለኢትዮጵያውያን ዲያስፖ ምሁራን እና ባለሞያዎች መደመር ማለት የኃይል ብዜቶች ማለት ነው፡፡ 

ወደፊት መጓዝ እንጅ ወደኋላ መመለስ የለም፡፡

የታሪክ ጉዞው ከጭቆና አገዛዝ ወደ ነጻነት፣ ከጭቆና ወደ ፍትህ ነው፡፡ ኔልሰን ማንዴላ መልካም ነገር እና ይቅርባይነት በማለት በሰየሟቸው ሁለት መንገዶች የምናደርገው ጉዞ በፍጹም አይቆምም፡፡

የአብይ አህመድ ቡድን ከረዥሙ የጎሳ አፓርታይድ የጨለማ ጉዞ በማውጣት ኢትዮጵያዊነት ወደሚባለው አስደናቂ የጸሐይ ብርሀን ወዳለበት እየመራን ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ምርጦች እና ባለብሩህ አእምሮ ባለቤቶች ለብዙ ዓመታት በአፓርታይድ የጨለማ ምርኮኝነት ስር ተቀፍድዶ የቆየውን ሕዝብ ነጻ በማውጣት አስደናቂ ወደሆነው የኢትዮጵያዊነት የጸሐይ ብርሀን ለመውሰድ ምን ማድረግ ይችላሉ?

ከዓመት በፊት ስታደርጉት እንደነበረው ጸጥ ማለት እና ጆሮ ዳባ ማለት አይሰራም፡፡

የእናንተ ጥርጣሬ እና እስቲ ለትንሽ ጊዜ ሁኔታውን እንየው የሚለው አካሄድ አይሰራም፡፡

ሌላ ሰው ይሰራዋል የሚለው አመለካከታችሁ ከእንግዲህ ወዲያ አይሰራም፡፡

እራሳችሁን ልትጠይቁት የሚገባ እና እንዲህ የሚል አንድ ጥያቄ ብቻ አለ፡፡

አሁን ስንት ሰዓት ነው?

ይህ ትክክለኛውን ትርጉም ይሰጣችኋል፡፡

አሁን ሁሉም በአንድነት የመቆሚያ ጊዜው ነው!

የመደመር ጊዜ ነው!

እኔ ካልሰራሁት ማን ሊሰራው ነው? በማለት ጥያቄ የሚቀርብበት ጊዜ ነው::

እንዲህ በማለት የሚታወጅበት ጊዜ ነው፣ አብይ አህመድ እና ቡድናቸው ለኢትዮጵያ ምንድን ይሰራሉ የሚል ሳይሆን እኔ ለኢትዮጵያ ምንድን ለመስራት እችላለሁ?“ የሚል መሆን አለበት፡፡

የአብይ አህመድን ቡድን የመቀላቀያ ጊዜው አሁን ነው!

ለኢትዮጵያ እና ለአብይ አህመድ ቡድን የኃይል ብዜት ተደማሪ የመሆን ጊዜው አሁን ነው! 

የኃይል አብዥዎች እነማን ናቸው?

የኃይል አባዥ ጽንሰ ሀሳብ ወይም ደግሞ የኃይል አባዥዎች በርካታ እንደምታዎች አሏቸው፡፡ መሰረታዊ የሆነው ጽንሰ ሀሳብ ጥቂት ሆኖም ግን በከፍተኛ ደረጃ የተደራጀ እና መፈጸም የሚችል ቡድን በአሁኑ ጊዜ ያለውን ኃይል አስገራሚ በሆነ መልኩ ኃይሉን ሊጨምረው ይችላል፡፡ በቀላል አገላለጽ በጥሩ ሁኔታ የተደራጀ፣ የሰለጠነ፣ ብቃት ያለው እና ለተግባር እራሱን መስዋዕት ያደረገ ጥቂት የግለሰቦች ኃይል በደንብ ያልተደራጀን የተበታተነን ኃይል አቅም  ከፍ ጎላ በማድረግ ውጤታማ ስኬትን ያስገኛል፡፡

ለዩኤስ መከላከያ መምሪያ የኃይል አባዥ ችሎታ ነው እናም ሲጨመር እና በተዋጊ ኃይል ሲታገዝ ለዚያ ኃይል እምቅ የመዋጋት ጉልበት ይጨምርለታል፡፡ በዚህም መሰረት የስኬታማ ተልዕኮ እና አፈጻጸም ዕድሉን ከፍ ያደርግለታል፡፡

ሆኖም ግን “ኃይል አባዥዎችን” በየዕለታዊ ሁኔታዎች፣ ማሽኖች እና መጠቀሚያ መሳሪያዎች እንመለከታለን፡፡ የቆሻሻ መግፊያ ጋሪ ከፍተኛ የሆነ ክብደት የተሸከመን ብዙ ኃይልን ሳይጠቀም እና በአንድ ሰው ኃይል ብቻ ቢሰራ ኖሮ ብዙ የሰው ኃይል የሚሸከመውን ክብደት አንድ ሰው ብቻ እየገፋ በቀላሉ ሊሰራው ይችላል፡፡

ፌስቡክ፣ ትዊተር እና ሌሎች ማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች የኃይል አባዥዎች ናቸው፡፡ አንድ ግለሰብ ወይም ደግሞ ትንሽ ቡድን ከዓለም አቀፍ የግንኙነት መረብ የመረጃ ምንጮችን በመውሰድ በሺዎች እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ኃይል እንዲያገኙ እና ወደተግባር እንዲገቡ ማድረግ ይችላል፡፡

የጋንዲ የተቀላቀለ እና አብዛኛውን ጊዜ ለመለየት ግልጽ ያልሆነ ቡድን ተከታዮች በባህር ጨው ላይ የነበረውን የእንግሊዞችን ሞኖፖሊ እ.ኤ.አ መጋቢት 1930 ዓ.ም በመቃወም አይበገሬነቱን በተግባር በማሳየት ለህንድ የነጻነት ንቅናቄ አባዥ ኃይል ነበር፡፡

እያንዳንዱ ሰው ሰላማዊ በሆነ የእምቢተኝነት እንቅስቃሴ በመሳተፍ ታላቅ ብዙሀን ድርጊትን በመፈጸም የእንቢተኝነት፣ የአይበገሬነት እና የመስዋዕትነት ተምሳሌት መሆን እንደሚችል ጋንዲ አምነዋል፡፡ ስኬታማ በሆነ ሕዝባዊ የእምቢተኝነት ድርጊቶች ላይ የቱንም ያህል የሰው ብዛት ቢኖርም ቅሉ ዋናው እና ወሳኙ በስራው ላይ የሚሳተፈው የሰው ኃይል ጥራት እና የመተግበር ብቃታቸው ዋነኛው መሳሪያቸው እንደሆነ ጋንዲ አስተምረዋል፡፡

የደቡብ አሜሪካ ክርስቲያን አመራር ጉባኤ/Southern Christian Leadership Conference (SCLC) ለአሜሪካ የሰብአዊ መብት ንቅናቄ ብቸኛው እና ጠንካራው የኃይል አባዥ ነበር፡፡ በ60 አፍሪካ አሜሪካውያን ቀሳውስት እና ፓስተሮች በአትላንታ እ.ኤ.አ ጥር 10 ቀን 1957 ዓ.ም የተቋቋመ እና ስራውን የጀመረ ድርጅት ነበር፡፡ ብቸኛ ዋና ዓላማው በሰላማዊ የትግል ስልት መስዋዕት በመሆን የአሜሪካን ነብስ ለማስተሰረይ ነበር፡፡ በዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ አመራር ሰጭነት SCLC ለአሜሪካ የህሊና እስረኞች እሳትን ለኮሰ፡፡

ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ለእራሱ ኃይል አባዥ በመሆን 100 ሚሊዮን የሚሆነውን የኢትዮጵያን ሕዝብ በአድሏዊነት፣ በጓደኝነት፣ በጎሰኝነት ማዕከልነት፣ በማይታረቅ ቅራኔ እና በጸረ ኢትዮጵያዊነት ለ27 ዓመታት ሲገዛ የቆየ መሆኑን መርሳት የለብንም፡፡

እንደዚሁም ሁሉ የአእምሮ ስነ ልቦናዊ ሁኔታ የኃይል አባዥ ነው፡፡ ተሸናፊዎች የአእምሮ ስነ ልቦናዊ ተሸናፊነት ውጤቶች ናቸው፡፡ ድል አድራጊዎች ደግሞ የአእምሮ ስነ ልቦናዊ ድል አድራጊነት ስነ ልቦናዊ ውጤቶች ናቸው፡፡ ምን ያህል ከፍታ መዝለል እንደምንችል የሚወሰነው ምን ያህል ከፍታ ለመዝለል ባሰብነው መጠን ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ታላቁ አባዥ ኃይል ናቸው፡፡ በየዕለቱ ለእርሳቸው ንዝረታዊ የፍቅር፣ የይቅርባይነት እና የዕርቀ ሰላም መልዕክቶቻቸው የመቶ ሚሊዮን ሕዝቦችን ልቦች እና አእምሮዎች እየለወጡ ለመሆናቸው ምስክሮች ነን፡፡

የኢትዮጵያ ምሁራን እና ባለሞያዎች በሁሉም የሰው ልጅ የጥረት መስኮች የአብይ አህመድ ቡድን ኃይል አባዥ እንዲሆኑ በምጠይቅበት ጊዜ የአብይ አህመድን ቡድን እንዲቀላቀሉ እና አስደናቂ በሆነ ሁኔታ የቡድኑን የመፈጸም ብቃት  እና ሀብቶችን በመጠቀም ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ የሚከተሉት ነገሮች ተግባራዊ እንዲሆኑ እጠይቃለሁ፡፡

1ኛ) የተጀመረው ሽግግር እንዲረጋገጥ እና ባለፉት 90 ቀናት በመፋጠን ላይ የቆየው የለውጥ እንቅስቃሴ መቀጠል እና ጭማሪው በከፍተኛ የጭማሪ ኃይል በመታጀብ መጓዝ አለበት፣

2ኛ) በአብይ አህመድ ቡድን የመጡትን እና የተገኙትን ድሎች እና ለውጦች ለመቀልበስ የሚደረጉ ማናቸውንም ጥረቶች መከላከል እና እየተከታተሉ ማምከን፣

3ኛ)  የቡድኑን ስራዎች ለማሳለጥ ፈቃደኝነትን መሰረት ባደረገ መልኩ የቴክኒክ ዕገዛዎችን መስጠት፣

4ኛ) በሁሉም መስኮች በፖሊሲ ቀረጻ እና ትግበራ ከፍተኛ እገዛ በማድረግ የእራስን ልምድ እና ክህሎት ማካፈል፣

5ኛ)  ኢትዮጵያን በአሁኑ ጊዜ ተጋርጠውባት ለሚገኙት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ተግዳሮቶች መፍትሄ ለመስጠት ሁሉንም ብልሀቶቻችንን፣ እውቀቶቻችንን እና ሀብቶቻችንን በስራ ላይ እንዲውሉ ማድረግ፡፡

ጨለማን ጨለማ አያስወግደውም፡፡ ይህንን ማድረግ የሚችለው ብርሀን ብቻ ነው፡፡

ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዲህ ብለው ነበር፣ ጨለማን ጨለማ አያስወግደውም፡፡ ይህንን ማድረግ የሚችለው ብርሀን ብቻ ነው፡፡“

በአሁኑ ጊዜ በአብይ አህመድ ቡድን እና በጨለማው ጎን ኃይል ወታደሮች መካከል የሞት ሽረት ትግል በመደረግ ላይ ነው፡፡

የአብይ አህመድ ቡድን ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሸጋገር እንዲቻል አዲስ መሰረተ ልማት፣ ተቋማት እና ሂደቶችን በመገንባት ላይ የሚገኝ ወጣት ኃይል ነው፡፡ ምን መሰራት እንዳለበት ሊያስፈጽም የሚችል በጣም ትንሽ ገንዘብ ብቻ ነው ያለው፡፡ የገንዘብ ካዝናዎች ባዶዎች እና በዕዳ መግለጫ ሰነዶች የተሞሉ ናቸው፡፡

ይህም ሆኖ የአብይ ቡድን ለኢትዮጵያ ህይወት አድን እና በድል አድራጊነት ለመውጣት ማንኛውንም ዓይነት ችግሮች ሁሉ በመቋቋም በመታገል ላይ ይገኛል፡፡

የአብይ አህመድ ቡድን ከኃይለኛው የጨለማው ወታደሮች ጋር ተፋጥጦ ይገኛል፡፡ እነርሱ ለቁጥር የሚያዳግት ገንዘብ ይዘዋል፣ ምክንያቱም ባንኮችን ባዶ አድርገዋቸዋል፡፡ ስለወታደራዊ ኃይላቸው እራሳቸውን ከፍ ከፍ በማድረግ በመደስኮር ላይ ይገኛሉ፡፡ በማስፈራራት እና በማሸማቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ግን የቱንም ያህል ገንዘብ እና ወታደራዊ ኃይል ቢኖራቸውም የጨለማው ኃይል ወታደሮች ዕጣ ፈንታ ሽንፈት ነው፡፡ ምክንያቱም የጥላቻ፣ የክፍፍል እና የበቀል መሳሪያዎቻቸው እኛ ካሉን የፍቅር፣ የይቅርባይነት እና የዕርቅ መሳሪያዎች ዓይነት እና መጠን ጋር አይመጣጠኑም፡፡

እኛ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ምሁራን እና ባለሞያዎች ለአብይ አህመድ ቀስት ጫፍ በመሆን የጨለማውን ኃይል ወታደሮች መጋፈጥ ይኖርብናል፡፡

አሮጌ ችግሮችን በአዲስ ሀሳብ ለመፍታት፣ በአዲስ ስልቶች የቀድሞዎቹን የወደቁትን ለመተካት እና ለወደፊቱ በአዲሶቹ ለመተካት በመጀመሪያው ረድፍ ላይ መገኘት ይኖርብናል፡፡ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ረቂቅ ፍኖተ ካርታ ፈቃደኞች እና የመሪነት ቦታውን በመያዝ መሳተፍ ይኖርብናል፡፡ እያንዳንዱ ሰው አሸናፊ ሊሆንበት በሚችለው አካታች አዲስ የጨዋታ ዕቅድ ላይ ግንባር ቀደም መሆን አለብን፡፡

እንግዲህ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ነው ኃይል አባዥ ለመሆን የምንችለው፡፡ ፈቃደኛ ኃይል አባዥ ለኢትዮጵያ (ፈኃአኢ)፡፡

በሚገባ የሰለጠነ፣ የመፈጸም ብቃት ያለው እና ብሩህ አእምሮ ያለው ፈቃደኛ ኃይል የዘመናት ጠላቶቻችን የሆኑትን ድህነትን፣ በሽታን እና ድንቁርናን ጨምሮ የጨለማው ኃይል ላይ ድልን በመቀዳጀት ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡

የእኛ ጦርነት በፖሊሲ መስኮች ብቻ አይደለም፣ ሆኖም ግን የሰዎችን ልቦች እና አእምሮዎች መያዝ እንደሆነ ሁሉም ፈኃአኢ እንዲገነዘቡት እፈልጋለሁ፡፡

የጨለማው ጎን ኃይሎች ከአንድ በላይ በበርካታ መንገዶች ማሸነፍ እንደሚችሉ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡

የሕዝቦችን ሞራል በመስበር ማሸነፍ ይችላሉ፡፡ የተለመደውን የተዛባ መረጃ የማሰራጨት፣ የማታልል እና የውሸት ዘመቻቸውን በማካሄድ፣ ማሸነፍ ይችላሉ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና በለውጥ ጥረቶች ላይ ያለንን መተማመን በመሸርሸር ማሸነፍ ይችላሉ፡፡

የሕዝብን ስሜቶች በማስቀየስ እና ውድመትን በመፍጠር ማሸነፍ ይችላሉ፡፡

ብቻችንን ሳይሆን በመደመር ለመፋለም መዘጋጀት አለብን፡፡ በእያንዳንዱ ወንድ፣ ሴት እና ልጅ ልብ፣ አእምሮ እና ህሊና ልንወጋቸው ይገባል፡፡ የእነርሱን የጎሰኝነት የዘር ፍልስፍና ርዕዮት ዓለም እና ጥላቻ በእያንዳንዱ ጎጥ፣ መንደር፣ የገጠር ከተማ፣ ከተማ፣ ጎረቤት እና መንገድ በፍቅር፣ በይቅር ባይነት እና በዕርቅ ለማሸነፍ መዋጋት አለብን፡፡

የማሸነፍ ቀመር፡ መደመር እና ኃይል ማባዛት፣

ካርል ማርክስ ፊዩርባች በሚለው መጽሀፋቸው እንዲህ በማለት ጽፈዋል፣ ፈላስፋዎች ብቻ ናቸው ዓለምን በተለያዩ መንገዶች መተንተን የቻሉት፡፡ ዋናው ነጥብ ግን እርሷን ከመለወጡ ላይ ነው፡፡“ ምሁራንን እና ባለሞያዎችን በፈላስፋዎች መተካት እንችላለን፡፡

በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ምሁራን እና ባለሞያዎች ሚና እራስን ከፍ ከፍ በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለምን አንድ ነገር አልሰሩም በማለት ከዳር በመቆም ማጉረምረም እና ማቃሰት  የለባቸውም፡፡ ለእነርሱ አሁን ጊዜው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ቡድን ጋር መቀላቀል እና ለሁሉም ነገር ትኩረት በመስጠት ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ነገር ለማድረግ እና የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

እ.ኤ.አ ሰኔ 23 ቀን 2018 ዓ.ም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ በሀገሪቱ ዋና ከተማ በመስቀል አደባባይ በመውጣት የአብይ አህመድን ቡድን እንደሚደግፍ አረጋግጧል፡፡

እ.ኤ.አ ከሀምሌ 28 – 29/2018 በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተመሳሳይ መልኩ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የድጋፍ ሰልፍ ያደርጋሉ፡፡

በቅርብ ጊዜ ባደረጉት ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዲህ ብለው ነበር፣ ለውጥ ጥቂት  ተጫዋቾችን እና በርካቶች ደግሞ ከዳር ተቀምጠው ተመልካች የሚሆኑበትን ሁኔታ አይፈልግም፡፡ ለውጥ ሁላችንም በሜዳው ውስጥ ገብተን በመጫወት የየድርሻችንን እንድናበረክት የሚደረግበት ሂደት ነው፡፡ ለውጥ ተመልካቾች ተቀምጠው የሚመለከቱበት እና ጥሩ ውጤት ሲገኝ ደስታቸውን የሚገልጹበት፣ ጥሩ ውጤት ሳይገኝ ሲቀር ደግሞ ወቀሳቸውን የሚያቀርቡበት የጨዋታ ዓይነት አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ጥቂት ቀልጣፋ ተጫዋቾችን ብቻ በማሰማራት በፍጹም መሰረታዊ ለውጥ ልናመጣ እንደማንችል እውነት ነው፡፡ ሁላችንንም በመቀላቀል እኛ ልንሰራ የምንችለውን ስራ መስራት አለብን፡፡

የአብይ ቡድን ከልፋት፣ ጠንክሮ ከመስራት፣ ከእንባ እና ከላብ በስተቀር ሌላ የሚሰጠው ምንም ዓይነት ነገር የለም እላለሁ፡፡

የአብይ ቡድን የተወደደችዋን ኢትዮጵያን ለመገንባት ብዙ ወራት እና ዓመታት የሚወስደውን ትግል በመምራት ላይ ነው እላችኋለሁ፡፡

ከአብይ አህመድ ቡድን ጋር መቆም እና መደመር አለብን፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተነስተዋል፣ እናም ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ድምጽ የእግዚአብሄር ድምጽ ነው፡፡ እጅግ በጣም በርካታዎቹ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአብይ አህመድን ቡድን ይደግፋሉ፡፡

የአብይ አህመድ ቡድን ፖሊሲ ምንድን ነው?

የአብይ አህመድ ቡድን ፖሊሲ በሰው ልጆች ላይ ሲፈጸም ከቆየ አስቀያሚ አምባገነናዊ የጭቆና አገዛዝ የስርዓት ውርስ ሀገሪቱን መንጥቆ በማውጣት ሰላም እና ዕርቅ ወደሰፈነባት ሀገር ሽግግር ማድረግ ነው፡፡

የአብይ አህመድ ቡድን ዓላማ ምንድን ነው?

ድል መቀዳጀት ነው፡፡ ማንኛውም ዋጋ ተከፍሎ የተገኘ የሰላም እና የዕርቅ ድል፡፡

ማንኛውም ዓይነት የሽብር ድርጊት እየተፈጸመ ያለ እና ኢትዮጵያዊነታችንን ለማጥፋት እና እንደ አንድ ሕዝብ በጽናት በአንድነት እንዳንቆም አንድነታችንን ለማናጋት ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም አይሳካም፡፡

ለሰላም እና ለዕርቅ የሚደረገው ጉዞ ረዥም እና እልህ አስጨራሽ ቢሆንም ድል ከማድረግ በስተቀር ኢትዮጵያ እንደ አንድ ሀገር የመቆየት ህልውና የላትም፡፡

የአብይ አህመድ ቡድን በኢትዮጵያ በእያንዳንዱ ጎረቤት፣ ጎጥ፣ መንደር፣ የገጠር ከተማ፣ ከተማ እና ክልል ሰላም እና ዕርቅን ለማምጣት በዘርፉ ያሉ ባለሞያዎችን እና የዕውቀት ሰዎችን ይፈልጋሉ፡፡ ባለን ኃይል እና እግዚአብሄር በሰጠን የጥንካሬ ኃይል ሁሉ በመጠቀም እውነታው ይነገር፡፡ እውነት፣ ይቅርባይነት እና ዕርቅ ከሌለ በስተቀር የኢትዮጵያ ህልውና አይኖርም፣ ኢትዮጵያ እንደሀገር ልትኖር አትችልም፣ ምንም ዓይነት ህልውና አይኖርም፣ የዘመናት ጥረት ዓላማዎች ሁሉ አይኖሩም፡፡

ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ ባለሞያዎች እና ሁሉም ኢትዮጵያውያን ወንድሞቼ እና እህቶቼ ኑ፣ የአብይ አህመድን ቡድን እንቀላቀል፡፡ እናም በተባበረው ኃይላችን በአንድነት ወደፊት እንጓዝ፡፡“

እንደመር፡፡

በአንድ ላይ እንቀላቀል እና ፈቃደኛ የኢትዮጵያ አባዥ ኃይል እንሁን፡፡

ህይወታቸውን መስዋዕት በማድረግ እና ተወዳጇን ኢትዮጵያን ለመገንባት ዕድሉን ያስገኙልንን በርካታዎቹን በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በፍጹም አንርሳቸው፡፡

የኢትዮጵያ ፈቃደኛ የኃይል አባዥዎች በመሆን ለከፈሏቸው መስዋዕትነቶች እና ትሩፋት ክብር እንስጥ፡፡

ለአብይ አህመድ ቡድን አባልነት ማረጋገጫ አዋጅ፣

በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት እኔ እና ጓደኞቼ ሁሉም የኢትዮጵያ ምሁራን እና ባለሞያዎች እንዲፈርሙ እና የአብይ አህመድን ቡድን እንዲቀላቀሉ በይፋ ጥሪ እናደርጋለን፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የአብይ አህመድን ቡድን እንዲቀላቀሉ በይፋ በማወጅ ተግባራዊ እንዲሆን እናደርጋለን፡፡

ለዚህ አዋጅ ፊርማን ማስቀመጥ ልዩ ዕድል ይሆናል፡፡

ለአዋጁ ተፈጻሚነት ፊርማውን የሚያስቀምጥ እያንዳንዱ ሰው በስም እና በሞያ ዝርዝር ውስጥ እንዲሰፍር ተደርጎ ለመላው ዓለም ዕይታ ይፋ የሚደረግ ይሆናል፡፡

በመፈረሚያ ዝርዝር ውስጥ የአዋጁን ጥሪ በመቀበል ለመፈረም ፈቃደኛ የሆነ እያንዳንዱ ሰው ሁሉ የተወደደችዋን ኢትዮጵያን ለመገንባት በፈቃደኝነት የአብይ አህመድን ቡድን ለመቀላቀል በይፋ ለዓለም ያውጃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዩናይትድ ስቴትስን ለመጎብኘት በሚመጡበት ጊዜ የታተመውን የአዋጅ ፊርማ የያዘውን ሰነድ አስረክባቸዋለሁ፡፡

ይኸ የስም እና የፊርማ ዝርዝር እንግዲህ ከእርሳቸው ቡድን ጎን ማን እንደቆመ ለቡድን መሪው ሙሉ ስዕል ይሰጣል!

ኑ፣ የአብይ አህመድን ቡድን እንቀላቀል፡፡ እናም በተባበረው ኃይላችን በአንድነት ወደፊት በቆራጥነት እንጓዝ፡፡“ 

እንደመር! አንቀነስ! እንባዛ! አንከፋፈል!

ኢትዮጵያዊነት ዛሬ፡፡

ኢትዮጵያዊነት ነገ፡፡

ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም! 

በኢትዮጵያ የፍቅር ባቡር ለተሳፈራችሁ በሙሉ!

[1] ነብያዊ በሆነ መንገድ ለመናገር የወደፊቱን ወይም ደግሞ ስለኃይማኖት እምነት የመተንበይ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይልቁንም ይህ ማለት የሞራል እምነት ጽናት ወይም ደግሞ ስለአምልኮት ተነሳሽነት ወይም ደግሞ ስለሁለቱም ጉዳይ በስልጣን ላይ ላሉት እውነትን ስለመናገር ጉዳይ ነው፡፡ ቀደም ሲል ጀምሮ ተንሰራፍቶ ስለቆየው እና በማህበረስብ ውስጥ ተንሰራፍቶ ስለሚገኘው ስለኢፍትሀዊነት፣ ስለአድሏዊነት እና ስለሙስና ጥቂት ቆራጦች እና ምክንያታዊ ሰዎች ወደኋላ መለስ በማለት ስለመናገር ባህል ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ በዋናነት ስለመንግስት፣ ማህበረሰባዊ ስህተቶች፣ ስለሰብአዊ መብቶች እና ስለግለሰብ ነጻነቶች ጉዳይ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!     

ሀምሌ 5 ቀን 2010   .

Original post in English:

https://goo.gl/LnRK5X

 

 

Similar Posts