“እሾሆችን ከጽጌረዳው አበባዎች መለየት አለብን፡፡”
“እሾሆችን ከጽጌረዳው አበባዎች መለየት አለብን፡፡”
(ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ እ.ኤ.አ ሰኔ/2018 ዓ.ም ከተናገሩት የተወሰደ)
እንደመር! አንቀነስ! እንባዛ! አንከፈል!
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
“በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ እምነት ማጣት የለብንም፡፡ ኢትዮጵያ ውቅያኖስ ናት፡፡ ከውቅያኖሱ ቅንጣት የውኃ ጠብታ ቆሻሻ ቢሆን ውቅያኖሱ በሙሉ ቆሻሻ ሊሆን አይችልም፡፡” (የማህተመ ጋንዲን ፍልስፍና በኢትዮጵያ መተግበር)
“አንድ ፍቅር! አንድ ልብ! አንድ ኢትዮጵያ፡፡ በአንድ ላይ እንሁን እናም ትክክለኛነት ይሰማን፡፡ ምስጋናን አቅርቡ እናም ጌታን አሞግሱ፡፡ እናም ደስታ ይሰማናል፡፡ ደስተኞች እንሆናለን፡፡ ሁላችንም ትክክል እንሆናለን፡፡ በአንድ ፍቅር በአንድ ላይ እንሁን! በአንድ ልብ በአንድ ላይ እንሁን! በአንድ ኢትዮጵያ በአንድ ላይ እንሁን እናም ትክክለኛነት ይሰማን፡፡“ (የቦብ ማርሌይን ፍልስፍና በኢትዮጵያ መተግበር)
የጸሀፊው ማስታዋሻ፡ ይህ ጽሁፍ በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “በፍቅር፣ በይቅርታ እና ዕርቅ ቀን“ በኢትዮጵያ በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ እ.ኤ.አ ሰኔ 23 ቀን 2018 ዓ.ም በመገኘት ለድጋፍ ለወጣው ሕዝብ እና የቦምብ ፍንዳታ አደጋ መድረሱንም ተከትሎ ባደረጉት የአማርኛ ሙሉ ንግግር ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ ከዚያም ወደ አማርኛ በተመለሰው ንግግር ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡
እ.ኤ.አ ሰኔ 23 ቀን 2018 ዓ.ም ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፍቅሩን እና ድጋፉን ለማሳየት ከሶስት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ መውጣቱ ተዘግቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግራቸውን እንዳጠናቀቁ ከፍተኛ ባለስልጣኖች ካሉበት መድረክ በቅርብ ርቀት ላይ የእጅ ቦምብ ፍንዳታ ተሰማ፡፡ የፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሰ እና ማንነቱ ያልታወቀ አንድ ፖሊስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሌሎች ባለስልጣኖች ጋር ተቀምጠውበት ወደነበረው የመድረክ አቅጣጫ የእጅ ቦምብ ወረወረ ተብሏል፡፡ ኒዮርክ ታይምስ የኢትዮጵያን ጤና ጥበቃ ሚኒስትር በመጥቀስ አንድ ሰው መሞቱን፣ 154 ሰዎች ከእነዚህም ውስጥ አስሩ በጽኑ መቁሳለቸውን ዘግቧል፡፡
የሚወዷቸውን ቤተሰቦቻቸውን ላጡት ቤተሰቦች እና ለመላው ኢትዮጵያውያን ሁሉ በዚህ በፍርሀት ቆፈን በተወሸቀ እና በጥላቻ ጥቃት በናወዘው የእኩይ ምግባር ባለቤት በሆነው ኃይል ለደረሰው አሰቃቂ እልቂት የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እገልጻለሁ፡፡ ለዚህ አሰቃቂ እልቂት እግዚአብሄር ነብሳቸውን በገነት እንዲያኖርልን እጸልያለሁ፡፡
ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዲህ በማለት አስተምረውናል፣ “ጨለማን ጨለማ ሊያስወግደው አይችልም፡፡ ይህንን ለማድረግ የሚችለው ብርሀን ብቻ ነው፡፡ ጥላቻን ጥላቻ ሊያስወግደው አይችልም፡፡ ይህንን ማድረግ የሚችለው ፍቅር ብቻ ነው፡፡“
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ልዩ ችሎታ ባላቸው እና ዋና የለውጥ አቀንቃኝ በሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር በበሰለ አመራር ለሰው ልጆች ሁሉ ፍቅር፣ ዕርቅ እና ሰላም በመባል በሚታወቁት ጠንካራ መሳሪያዎች አማካይነት 13 ወራት የጽሐይ ብርሀን ካላት ምድር ጨለማን በሙሉ ለማስወገድ ከመቶ ሚልዮን ህዝባቸው ጋር ጉዞ ቀጥለዋል፡፡
ይፈጸም ዘንድ ጊዜው የደረሰን ሀሳብ ምንም ዓይነት የወታደር፣ መንግስት፣ አሸባሪ እና በሰው ልጆች ላይ ወንጀልን የሚሰራ ኃይል ሊያቆመው አይችልም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የእውነት፣ የሰላም፣ የዕርቅ እና ሰላም ጊዜ እየመጣ ነው፡፡ ኔልሰን ማንዴላ፡ መልካም ነገር እና ይቅርባይነት በማለት በሰየሙልን ሁለት መንገዶች ከመጓዝ ሊያግደን የሚችል ምንም ኃይል እና ሰው የለም፡፡
ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያለኝን ከፍተኛ አክብሮት እና አድናቆት አቀርባለሁ፡፡ የእሳት አደጋ ህይወት አድን ስብዕና የተላበሱ ሰው ናቸው፡፡ በእሳት ነበልባል ላይ ነበሩ፡፡ ሆኖም ግን በፍጹም አልተበገሩም ወይም ደግሞ ግንባራቸውን አላጠፉም፡፡ በአላቸው እውቀት በመታገዝ በተረጋጋ ስሜት በመጨረሻው ሰዓት መልካም ነገር በሰይጣናዊ ድርጊት ላይ ሁልጊዜ ድልን እንደሚቀዳጅ አሳምረው ያውቃሉ፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያውያን ወንድሞቼ እና እህቶቼ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ሙሉ በሙሉ እንዲደግፉ እማጸናለሁ፡፡ በተራራው ጫፍ ላይ ወደተገነባቸው ማለትም ፍቅር የገነባት እና ተወዳጇ ኢትዮጵያ እየተባለች ወደምትጠራው አንጸባራቂ ከተማ የሚወስዱን መሪያችን ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ የመንግስት ቋንቋ የሆነውን አማርኛን መናገርም ሆነ መተርጎም ለማይችሉ ሰዎች የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን መልዕክት ዋና ዳህራ እንዲገነዘቡት በሚል ቀጥታ የአማርኛውን ንግግር ወደ እንግሊዝኛውም በመተርጎም አዘጋጅቸዋለሁ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ንግግሮች መተርጎም ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ልዩ የሆኑ አንደበተ ርትኡ ናቸው፡፡ የአማርኛ ቋንቋ ችሎታቸው፣ ሀሳቦቻቸውን የመግለጽ ክህሎታቸው፣ የስነ አመክንዮ ትንታኒያቸው፣ የተመሳስሎ ንግግሮችን አጠቃቀማቸው፣ መረጃን መሰረት ያደረገው አሸናፊ የክርክር ጭብጣቸው እና ውስብስብ የሆኑ ነገሮችን አቅልለው የማቅረብ ክህሎታቸው እንደ እኔ ላለው ለመተርጎም ጀማሪ ለሆነው የእርሳቸውን ሙሉ መልዕክት እንዳለ ለማስተላለፍ በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ በእኔ የትርጉም ስራ ውስጥ እንከኖች ተፈጥረው ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን በቅድሚያ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ንግግሮች ከእኔ በተሻለ መተርጎም ከሚችሉ ሰዎች ጋር በመሆን ለመተርጎም ሞክሪያለሁ፡፡ ሆኖም ግን ለሚከሰተው ማንኛውም ስህተት እና በትርጉም ሂደቱ በትክክል ከመገለጽ የጠፉ መልዕክቶች ካሉ ኃላፊነቱን ሙሉ በሙሉ እኔ እወስዳለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባደረጓቸው ንግግሮች ላይ የአድናቆትን ስሜቶች ለመግለጽ በሕዝቡ ሲደረጉ የነበሩትን የእጅ ጭብጨባዎች በሙሉ ዘልያቸዋለሁ፡፡ ሆኖም ግን በእርሳቸው ንግግሮች ወቅት የእርሳቸውን ንግግሮች ተከትሎ መጠነ ሰፊ የሆኑ ጭብጭባዎች ሲደረጉ እንደነበር መግለጽ ተገቢ ነው፡፡
እ.ኤ.አ ሰኔ 23 ቀን 2018 ዓ.ም አዲስ አበቤዎች የእኔን ጥያቄዎች በመቀበል ትክክለኛውን መልዕክት ያስተላለፉችሁልኝ ስለሆነ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ፡፡ በእናንተ ሁለገብ ምላሾች እጅግ በጣም እረክቻለሁ፡፡
አለማየሁ ገብረ ማርያም
====== ============== ================
“በፍቅር፣ በይቅርባይነት እና ዕርቅ ቀን” የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ንግግር ትርጉም፣
**ይህ የአማአርኛ ቋንቋ ትርጉም ቀደም ብሎ በንግሊዝኛ ከተሮምቁት ላይ የተወሰደ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡትን ንገግር ለመስማት አዚህ ይጫኑ ።
የእኔ ውድ እና የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ በዛሬው ዕለት ፍቅራችሁን፣ ይቅርባይነታችሁን እና አንድነታችሁን ለማሳየት በርካታ ኢትዮጵያውያንን በዚህ ቦታ ተገኝታችሁ በማየቴ ልዩ የሆነ ተስፋ ያደረብኝ ሲሆን በታላቅ ክብር እና ደስታ ተሞልቻለሁ፡፡
ንግግሮቼን ለማጠቃለል ሁልጊዜ እንደምጠቀመው ቃሎቼን በመክፈቻ ንግግሬ ላይ ለመጠቀም እንድችል እንድትፈቅዱልኝ እጠይቃለሁ፡፡
የማይሳነው ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ተቋማዊ አቅማችንን ያሳደግን ቢሆንም ቅሉ እና ለስድስት ወራትም ቢሆን ኃላፊነታችንን ለመወጣት እና ከፊታችን ተጋርጦብን የሚገኘውን የማይነቃነቅ የጨለማ ተራራ ለመናድ ከፊታችሁ ቆሜ እገኛለሁ፡፡
ጥላቻ አጎሳቁሎናል እናም እንድንዳከም አድርጎናል፡፡ ሆኖም ግን ፍቅር ትልቅ ዋጋ እንዳለው እና በተስፋ እንድንሞላ ነግራችሁናል፡፡ ለእኛ ድልድይ ይፈጥርልናል፡፡
ማንም በፍቅር እና በተስፋ ስራውን ጀምሮ ዓላማውን ሳያሳካ የወደቀ የለም፡፡ የዛሬው “የፍቅር እና የምስጋና ቀን” ጥንካሬ የተሞላባቸውን እርምጃዎቻችንን ወዴት እንደምንወስድ የሚያመላክትን ነው፡፡
በዛሬው ዕለት እዚህ ያልታዩትን ሰዎች ልናመሰግናቸው የሚገባ ነገር ነው፡፡
እነርሱ ሞተው እኛ እንድንኖር ያደረጉንን፣ እነርሱ አፍረው እና እኛ ክብር እና ሞገስ እንድንጎናጸፍ ያደረጉንን፣ እነርሱ ታስረው እኛ ነጻ እንድንሆን ያደረጉንን እና ውድ ህይወታቸውን ገብረው እኛ በነጻ እንድንኖር ያስቻሉንን ወገኖቻችንን ማመስገን አለብን፡፡ በዚህ በተከበረ ቦታ ላይ ሆነን ለእኛ ሲሉ ከፍተኛ የሆነውን የህይወት መስዋዕትነት ለከፈሉት ሰማዕታት ሁላችንም ማመስገን አለብን፡፡
እነርሱ ካለእኛ መኖር ይችሉ ነበር ፡፡ እኛ ግን ካለእነርሱ መኖር አንችልም፡፡ ይህች ምድር- የአምላክ ረቂቅ ጥበብ የተገለጸባት ኢትዮጵያ፣ የ80 ቆንጆ ብሄረሰቦች መኖሪያ ምድር፣ ይህች ቆንጆ ኢትዮጵያ፣ የሰው ልጅ መገኛ የሆነችው ምድር ኢትዮጵያ፣ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት እና የነጻነት ተምሳሌት- ለሁለት ወራት የሰራ መሪ አትፈልግም፡፡ ይልቁንም ሁሉንም ችግሮች ከመሰረታቸው ነቅሎ መጣል የሚችል መሪ ትፈልጋለች፡፡
ለሕዝቦቹ ፍቅር የሌለው መሪ እንግዳ ነው፡፡ የሕዝቦቹ አንድነት የሌለው መሪ ባዶ ነው፡፡ አዎ በሕዝቦቹ ዘንድ ደህንነት የሌለው መሪ ምንም ዓይነት ውጤት የለውም፡፡ ስለሆነም እስከ አሁን ድረስ ለሰጣችሁን ፍቅር እና ደህንነት ለማመስገን በዛሬው ዕለት ከፊታችሁ መጥቻለሁ፡፡
አዎ ገና በመጀመሪያው ቀን ይህ ኃላፊነት ከተሰጠን ጀምሮ ለሰጣችሁን ድጋፍ ለማመስገን በዛሬው ዕለት እዚህ መጥቻለሁ፡፡ ትልቅ ጸጋ እና ሀብት ያደላትን ሆኖም ግን በፍቅር ስለተራበችው ሀገራችን ፊት ለፊት በመገናኘት ልነግራችሁ በዛሬው ዕለት እዚህ ቦታ እገኛለሁ፡፡
ያሉንን ነገሮች በማጣት እና የሌሉንን ነገሮች በመፈለግ በርካታ ጊዚያትን ያባከንን መሆናችንን ለእናንተ ለመንገር ከዚህ ቦታ እገኛለሁ፡፡ እስከ አሁን ድረስ አስሮ እና ቀፍድዶ ይዞን የቆየው ጥላቻ እና የበቀል ስሜት ነው፡፡ ጥላቻን እና የበቀል ስሜትን በፍቅር በጣጥሰን መጣል እንደምንችል ልነግራችሁ ከዚህ ቦታ መጥቻለሁ፡፡
ስለሆነም ባልተጠበቀ መልኩ እርስ በእርሳችሁ እንድትዋደዱ የሚያደርገው ቀን በሚመጣ ጊዜ እኔን እና ከእኔ ጋር ሌት ከቀን የሚሰሩ ሰዎችን ታመሰግናላችሁ፡፡
ያ ቀን በሚመጣ ጊዜ “ምንም ዓይነት ሌብነት እና ሙስና የለም”፤ ያ ቀን እኔን በግል የምታመሰግኑበት ቀን ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡
ያ ቀን በሚመጣበት ጊዜ ይህ ክልል የእኔ ነው፣ ይኸ ወሰን የእኔ ነው፣ ከዚህ አካባቢ ውጡ ምክንያቱም የእኔ ነው የምትሉበት ጊዜ አይኖርም፡፡ እናም ለሀገራችን በፍቅር ከልብ የምትሰሩበት ቀን ለእኔ እና ከእኔ ጋር ከፍተኛ ስራ የሚሰሩትን የምታመሰግኑበት ቀን ነው፡፡
የእያንዳንዳችንን ጥንካሬ በፍቅር የምንደምርበት እና ከምስራቅ ጫፍ እስከ ምዕራብ ጫፍ እና ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ጫፍ የሀገራችን ክፍል እና ቤተመንግስቱ እና ፓርላማው ለሕዝብ እይታ ክፍት እንዲሆን የሚያደርገውን ቀን እንጠብቃለን፡፡
ለልጆቻችሁ ስለፊደሎች እንደምታስተምሩት ሁሉ ስለሀገር ፍቅር እና የኢትዮጵዊነት ካባ እንዲከናነቡም አስተምሩ፡፡ ይህንንም በማድረጋችሁ የእናንተን የምስጋና ፍሬ እንቀበላለን፡፡
ለእናቶቻችን እና ለእህቶቻችን እውቅና እና ክብር ስትሰጡ እንዲሁም ሁሉንም ሴቶች በእኩልነት ስታስተናግዱ የእናንተን ምስጋና ዓለም ያስተውላል፡፡ ለሀገራችሁ እና ለአካባቢያችሁ ልማት ጥልቅ ፍቅር የሚሰማችሁ ከሆነ እና በዚሁ መሰረት ነገሮችን መስራት ከጀመራችሁ የእናንተ ምስጋና ልባዊ ይሆናል፡፡
ግባችን ሩቅ ነው፣ ዓላማችን ደግሞ እጅግ በጣም ሰፊ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ታላቅነቷ መመለሷ ቅንጣት ያህል የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ለታላቅነት እና ለብልጽግና ድልድይ ዕርቅ፣ ፍቅር እና መደመር መሆናቸውን ላስታውሳችሁ እፈልጋለሁ፡፡
ለውጥ ጥቂት ተጫዋቾችን እና ከዳር ሆነው የሚመለከቱ በርካታ ተመልካቾችን ብቻ የሚፈልግ አይደለም፡፡ ለውጥ ሁላችንም በመጫወቻ ሜዳው ውስጥ በመግባት የእራሳችንን ድርሻ እንድናበረክት የሚፈልግ ሂደት ነው፡፡ ለውጥ ተመልካቾች የሚመለከቱት እና መልካም ውጤት ሲታይ የሚጨበጨብለት እና ውጤቱ መልካም ሳይሆን ሲቀር ደግሞ የሚተችበት እና ቅሬታ የሚቀርብበት የጨዋታ ዓይነት አይደለም፡፡
ልዩነቱ እንዴት አድርገን በሙሉ ልብ፣ በኃላፊነት፣ በችሎታ መጫወት እና ምን ያህል ለማበርከት እንደምንችል ከማወቁ ላይ ነው፡፡ ልሂቃን መልካም ሀሳቦችን ያመጣሉ፡፡ ባለሞያዎች ነገሮችን በአዲስ መንገድ የመስራት ዘዴን ያሳዩናል፡፡ የእምነት አባቶች መጥፎ ሀሳብን እና ሙስናን ያስወግዳሉ፡፡ እናም ተነሱ እና እንዲህ በሉ፣ “ደኃ ተበደለ፣ ፍትህ ተጓደለ፡፡“
በመላው ዓለም የምትኖሩ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ለእናት ሀገራችሁ ሀብታችሁን እና እውቀታችሁን ለማምጣት አስቡ፡፡
የፖለቲካ ተፎካካሪዎች እና ፓርቲዎች ትላንት ስለተደረገው ነገር እርሱት፡፡ ከልባችሁ ለእርቅ እና ለመልካም ነገር አራማጅ ኃይል ሁኑ፡፡
ወጣቶች ቀበቶዎቻችሁን ጠበቅ በማድረግ ሀገራችሁን ለማልማት ለስራ ተሰለፉ፡፡
አባቶች ልጆቻችሁን ምከሩ፡፡ እናቶች ልጆቻችሁን አደፋፍሩ፡፡
ወጣቶች ምሩ፡፡ መምህራን የዕውቀት ዘሮችን ዝሩ፡፡ ተማሪዎች ጠንክራችሁ አጥኑ እናም ለጥንካሬ እና ለተስፋ ወደፊት ስሩ፡፡
ሀገራችንን የምንወድ ከሆነ ግዴታዎቻችንን መወጣት አለብን፡፡ መብቶቻችንን መጠየቅ አለብን፡፡
ሀገራችንን የምንወድ ከሆነ ስልጣን ኃላፊነት እንጅ የእኛን የዘፈቀደ አገዛዝ በሌሎች ጫንቃ ላይ ለመጫን የተሰጠ ፈቃድ አለመሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡
በስልጣን ወንበር ላይ መቀመጥ ማለት ሕዝብን ማገልገል እንጅ ሕዝብ እኛን እራሳችንን እንዲያገለግለን ማድረግ ማለት አይደለም፡፡
ከሕዝብ መስረቅ የቅሌት ምልክት እንጅ የኩራት ምንጭ አይደለም፡፡
ሀገራችንን የምንወድ ከሆነ እንደ ኢትዮጵያዊ ለተፈናቀለው እና አላግባብ ለተስተናገደው ለእንዳንዱ ሰው እና ዜጋ ዘብ እንቁም፡፡
ሀገራችንን የምንወድ ከሆነ ለእያንዳንዷ ለምትባክነው ሳንቲም ተቆርቋሪ እንሁን፣ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ናትና፡፡
ሀገራችንን የምንወድ ከሆነ ለእያንዳንዱ ለምናጠፋው የኢትዮጵያን የስራ ሰዓት እንዳጠፋን በመቁጠር ጥልቅ ስጋት ይኑረን፡፡
ሀገራችንን የምንወድ ከሆነ እና የሚባክነውን ንብረት የምንመለከት ከሆነ እንዲህ በማለት መጮህ አለብን፣ “ይህ የባከነው ንብረት የእናቴ የኢትዮጵያ ነው፡፡“
ሀገራችንን የምንወድ ከሆነ በማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የማንኛውም ዜጋ ሰብአዊ መብት ሲደፈጠጥ በምናይበት ጊዜ ለእርሱ/ሷ በአንድነት በመቆም የእርሱ/ሷ ጎሳ፣ ኃይማኖት ወይም ሌሎች ንገሮች ምንም ይሁኑ ምን እርሱ/ሷ መብቱ/ቷ ሊጠበቅለት/ላት የሚገባ/ት ዜጋ ነው/ናት ማለት አለብን፡፡
እንዲህ በማለት በአንድነት እንቁም፣ “ኢትዮጵያ ተጎዳች፡፡ የአንድ ሰው ፍትህ ማጣት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ፍትህ ማጣት ነው፡፡ ኢትዮጵያን በጋራ እንገንባት፡፡ ኢትዮጵያ ሁላችንንም ትፈልጋለች፡፡
ኢትዮጵያ ለሁላችንም አስፈላጊያችን ናት፡፡ የእኛን ኢትዮጵያ ሊተካ የሚችል ምንም ዓይነት ነገር ሊሰጠን አይገባም፡፡ የኢትዮጵያ ልጆች መተባበር ከቻሉ ስንፍናን በማስወገድ ሌት እና ቀን በመስራት ተራራውን በመውጣት ኢትዮጵያን ያከናነባትን የድህነት ብርድ ልብስ መግፈፍ እና ማስወገድ እንችላለን፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የሰላም ማዕክል ሆና መዝለቅ የምትችል መሆኗን ለማረጋገጥ ከጎረቤቶቻችን ጋር ያሉንን ግንኙነቶች ማጠናከር እና ግንኙነቶቻችንም በፍቅር፣ በጋራ ጉዳይ፣ ጥቅም እና ምሁራዊ እድገት መርሆዎች ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ታላቅ እና ድንቅ ናት፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ የ2000 ዓመታት የድንጋይ እና የወረቀት ላይ ጽሁፍ ያላት ናት፡፡ ኢትዮጵያ የእራሷን መዝሙር መዘመር የምትችል፣ በእራሷ መንገድ መጓዝ የምትችል፣ የእራሷን ክብር መጠበቅ የምትችል እና ምንጊዜም እራሷን መጠበቅ የምትችል ሀገር ናት፡፡
ሆኖም ግን ሕዝቡ ነጻነት፣ ፍትህ፣ ዴሞክራሲ እና የኢኮኖሚ ብልጽግና ከሌለው የዚህ ድንቅ ታሪክ እና ሀብት ዋጋ ምንድን ነው፡፡ እናም ባዶ ኩራት እና በጠረጴዛ ላይ ያልተቀመጠ ምግብ ማለት ነው፡፡
ነጻ ሀገርን እና ነጻ ሕዝብን በመገንባት ረገድ ልዩነት አለ፡፡ በነጻ ሀገር ነጻ ሕዝብ ከሌለ የነጻነት ትርጉሙ ምንድን ነው?
የክልል ወሰኖች የድንበር መስመሮች ከሆኑ እና እኛን በሚያስተሳስረው ድልድይ ላይ እኛን የሚከፋፍል የግንብ አጥር የምናስቀምጥ ከሆነ የሺህ ዘመናት ታሪክ ዋጋ እና ትርጉም ምንድን ነው?
ለመናገር የምንፈራ ከሆነ፣ ለመጻፍ የምንፈራ ከሆነ እና የምንደበቅ እና እራሳችንን ለማስተባበር የምንፈራ ከሆነ የሺህ ዘመናት ታሪክ ዋጋ እና ትርጉም ምንድን ነው?
አንዱ የጎሳ ቡድን ሌላውን የጎሳ ቡድን “ወደ እኔ አካባቢ አትምጣ፤ ከእኔ አካባቢ ውጣ፤ ይህ የኢትዮጵያ ክፍል የእኔ ነው እናም የአንተ አይደለም የሚል ከሆነ ቅኝ ገዥዎችስ ከዚህ በላይ ምን አድረጉን?“
በመጨረሻም በእምሯችሁ እንዲቀመጥ የምፈልገው አንድ ነገር እንዲህ የሚል ነው፣ “ግለሰቦችን ከጎሳ ቡድኖች እንለይ፡፡ እሾሆችን ከጽጌረዳ አበቦች እንለይ፡፡ ምክንያቱም ነገሩ አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ ነውና፡፡ ምክንያቱም አንድ ጠማማ እንጨት ቢኖር ደኑን ሁሉ አናጠፋም፡፡“
የጥላቻ ኃይልን ለማሸነፍ ይቅርባይነት መልካም መሳሪያ መሆኑን በየዕለቱ እናስታውስ፡፡
በዚህ አጋጣሚ በዚህ ክስተት ለእኔ እና ከእኔ ጋር ሌት እና ቀን ለሚሰሩት ለሁሉም ጓደኞቼ የተሰጠን ድፍረትን የተላበሰ ፍቅር እንደማዘናጊያ እና በእራስ መተማመን ላይ ተንጠልጥሎ እንዲቀር ብቻ ሳይሆን የእናንተን ፍቅር በመቀበል የበለጠ ጠንክረን እንድንሰራ ትልቅ አቅም እና ስንቅ ይሆነናል፡፡
በእያንዳንዷ ደቂቃ እና ሰዓት ከሁሉም ዓይነት ሙስና እና ጥላቻ በመራቅ እናንተን በታማኝነት፣ በፍቅር፣ በመልካም እምነት፣ በንጹህ ልብ ወደ ፍትህ እና የዴሞክራሲ አቅጣጫ ለመምራት እንደምናገለግላችሁ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡
የማጠቃለያ ሀሳቤን ከመሰንዘሬ በፊት የተወደዳችሁ እህቶቼ እና ወንድሞቼ እንድትጠነቀቁ ልጠይቃችሁ የምፈልገው ነገር ላለፉት አንድ መቶ ዓመታት ጥላቻ አታሎናል፣ ጥላቻ ነግሶብናል፡፡ ለእኔ የማለት ስግብግብነት፣ እራስ ወዳድነት እና ግለሰባዊነት እራሳችንን ጎድቶናል፡፡
የተወደዳችሁ እና የተከበራችሁ ወገኖቼ ከፍትሀዊነት እና ከመከራ ጋር በመታገል በአሸናፊነት ከወጣን በኋላ የትግል ታሪካችን በድልድዩ ተሻግረን ከተወደደችዋ ኢትዮጵያ ለመድረስ የሚያስችሉን መንገዶች ይቅርባይነት እና ፍቅር ብቻ ናቸው፡፡
በቀልተኝነት የደካሞች ብቻ ነው፡፡ እና ኢትዮጵያውያን ደካሞች አይደለንም፡፡ ስለሆነም በቀልን አንፈጽምም፡፡
በፍቅር እናሸንፋለን፡፡
እያንዳንዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ “በዚህች በፍቅር እና ይቅርባይነት ቀን” ባጠገባችሁ ከሚገኙት ወገኖች ጋር በመተቃቀፍ እንድትወዷቸው እና ይቅርታ እንድታደርጉላቸው እጠይቃለሁ፡፡ ይህንን ነገር በፍቅር እንድታደርጉት እጠይቃለሁ፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥንካሬ ታፍራ እና ተከብራ ለዘላለም ትኑር፡፡ የማይሳነው ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ!
አመሰግናለሁ፡፡“
========== ================ ================
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እ.ኤ.አ ሰኔ 23 ቀን 2018 ዓ.ም የቦምብ ፍንዳታውን ተከትሎ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሰጡት መግለጫ፣
… በተባበረው ክንዳችሁ ሰይጣናዊ ድረርጊትን በማሸናፋችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ፡፡
ይህ ቀን ኢትዮጵያውያን በፍቅር እና በይቅርባይነት እጅ ለእጅ ተያይዘው ፍቅር ከሰማይ የዘነበበት ዕለት ነው፡፡
እንደዚህ ዓይነት መልካም ነገሮችን ለማየት የማይወዱት ኃይሎች በጥንቃቄ አቅደው፣ ስልት ነድፈው እና ሞያዊ በሆነ መንገድ ሰርተው የሰዎችን ህይወት በመቅጠፍ ይህንን አንጸባራቂ የሆነውን ቀን በደም አጨቅይተውታል፡፡
አጠቃላይ ዕቅዳቸው ከሽፏል፡፡ ዓላማቸው ተጨናግፏል፡፡ ዓላማቸው የከሰረ ነው እናም በሙሉ የወደቀ ነው፡፡
በርካታ ሰዎች ተጎድተዋል፡፡ ጥቂት ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፣ ሌሎቹ ደግሞ በጽኑ ቆስለዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ለዚህች ቀን ዓላማ፣ ለኢትዮጵያ ፍቅር እና ዕርቅ ሲሉ ህይወታቸውን ላጡት እና ለተጎዱት ወንድሞቼ እና እህቶቼ ቤተሰቦች የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
የዛሬዎቹን ሰማዕታት ለኢትዮጵያውያን ፍቅር፣ ለኢትዮጵያውያን ሰላም፣ ለኢትዮጵያውያን አንድነት እና ዕርቅ ሁልጊዜ በየዓመቱ እናስታውሳቸዋለን፣ እንዘክራቸዋለን፡፡
ይህንን የተከበረ ቀን በታላቅ መስዋዕትነት አግኝተነዋል፡፡
የበርካታ ወገኖቻችንን ህይወት መስዋዕት በማድረግ ያገኘነው ቀን ነው፡፡ እንደገና በመስዋዕትነት የተገኘ ድል እና ያለ መስዋዕትነት ድል ሊገኝ እንደማይችል የተማርንበት ቀን ነው፡፡
ያም ሆነ ይህ ለኢትዮጵያውያን ወንደሞቼ እና አህቶቼ ለማሳሰብ የምፈልገው ነገር ፍቅር ሁሉንም የሚያሸነፍ መሆኑን ነው፡፡
ይቅርባይነት ሁሉን ነገር የሸንፋል፡፡ መግደል ሽንፈት ነው፡፡ መግደል ሀፍረት ነው፡፡
ማንም የሀገርን ደስታ ለማጨናገፍ እና ለማውደም የሚሰራ የታናሽነት ምልክት ነው፡፡ ሆኖም ግን እኛ ኢትዮጵያውያን ትንሾች አይደለንም፡፡ ይልቁንም ታላቅ ሕዝቦች ነን፡፡
እራሳችንን ጠባብ አእምሮ እንዳላቸው እንደታናናሾች ወደታች በማውረድ ታናሾች አንሆንም፡፡ እነርሱ ወደታች ሲወርዱ እኛ ወደ ላይ ከፍ እንላለን፡፡
በደስታችን ላይ ጨለማን ለማንገስ፣ በፍቅራችን ላይ ጨለማን ለመትከል በሞከሩት ኃይሎች እና አንድነታችንን የተፈታተናችሁ ሁሉ ዕቅዳችሁ አልተሳካም፡፡
አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ለፍቅር፣ ለይቅርባይነት እና ለአንድነት የዘረጋቻቸው እጆቿ አይታጠፉም፡፡
በኢትዮጵያ ላይ እየዘነበ ያለው የፍቅር እና የሰላም ዝናብ መዝነቡን ይቀጥላል፡፡
እንደዚህ ያለ እኩይ ሰይጣናዊ ድርጊት የምትፈጽሙ ኃይሎች ሁሉ ትላንት ዕቅዳችሁ አልተሳካም፡፡ ዛሬም አይሳካም፡፡ ነገም አይሳካም፡፡
ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ እንደዚህ ያለውን ክፉ ስራችሁን እንድታቆሙ እመክራችኋለሁ፡፡ ስለሆነም ሕዝብ እና መንግስታቸው በተሳሳተ አቅጣጫ አይሄዱም፡፡ ጥንቃቄ ማድረግ እና ስህተቶችን ማረም ይኖርባችኋል ብዬ አስባለሁ፡፡
የኢትዮጵያን ሕዝብ በተመለከተ ልቦቻችንን ክፍት በማድረግ፣ አንድነታችንን በማጠናከር እና በመደመር እንቀጥላለን፡፡
ወደኋላ በፍጹም አንመለስም፡፡
አንድነታችን በማይረቡ ነገሮች አይናጋም፣ እናም እንደዚህ ያለ የወረደ ሰይጣናዊ ድርጊት ለፈጸሙት ሰዎች እናዝንላቸዋለን፡፡ በዛሬው ዕለት መስዋዕት ለሆኑት ሰዎች አምላክ ነብሳቸውን በገነት ያኑርልን፡፡ የቆሰሉ ሰዎችም ተገቢውን ህክምና ያገኛሉ፡፡
የሚወዷቸውን ፍቅረኞቻቸውን ላጡት ቤተሰቦች መጽናናትን እንመኛለን፡፡ በዛሬው ዕለት መስዋዕት የሆኑት እና የእነርሱ ቤተሰቦች የኢትዮጵያ ሕዝቦች አካል ናቸው፡፡
የእኔ ወንድሞች ናቸው፡፡ እንደዚሁም የሁሉም ወንድሞች ናቸው፡፡
የደም ወንድሞች እና እህቶች ባይሆኑም እንኳ በእርግጥ የሁላችንም ቤተሰቦች አባላት ናቸው፡፡ ለፍቅር ያደረጉት የእነርሱ መስዋዕትነት የድል የመጨረሻው ይሆናል፡፡
ፖሊስ በጣም ዝርዝር የሆነ ምርመራ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ምርመራው እንደተጠናቀቀ ወዲያውኑ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ አደጋው በተከሰተበት እና በአካባቢያችሁ የምታዩትን እና የምትሰሙትን ነገር ሁሉ ወዲያውኑ ለፖሊስ እንድታሳውቁ አሳስባችኋለሁ፡፡
በአንድ ላይ በመሆን በህብረት በመስራት በጥላቻ እና ሰይጣናዊ ድርጊት ላይ ድልን እንቀዳጃለን፡፡
ኢትዮጵያ በፍቅር እና በዕርቅ ጎዳና ላይ ከመሄድ የሚያቆማት ምንም ዓይነት ኃምድራዊ ኃይል የለም፡፡ ኃይልን መጠቀም የወደቀ እና የተሸነፈ ሀሳብ ነው፡፡ በወደቁ እና በተሸነፉ ኃይሎች እንደማንገዛ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡
አመሰግናለሁ፡፡
============= ============= ==============
አንድ ፍቅር!
አንድ ልብ!
አንድ ኢትዮጵያ! ደስተኞች እንሆናለን!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ሰኔ 21 ቀን 2010 ዓ.ም