ማስታዋሻ ቁጥር 10፡ አብይ አህመድ፣ የኢትዮጵያ  “ሕይወት አድን”ጠቅላይ ሚኒስትር

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከእስር ነጻ ካደረጓቸው ኢትዮጵያውያን ጋር

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ 

የጸሐፊው ማስታዋሻ፡ በዚህ ማስታዋሻ ውስጥ ሁለት ትችቶች አሉ፡፡

የመጀመሪያው እና “አጭሩ“ (ቢያንስ እንዲህ እያልኩ የምጠራው አስተያየት ከዚህ በታች ) የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ክልል ውስጥ በመስጠት ላይ ስላለው አመራር የቀረበ ትችት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኢትዮጵያውያንን ከበርካታ ሀገሮች ከእስራት እና ከእስር ቤቶች በማውጣት እያደረጉት ስላለው ህይወት አድን ልዩ ስራ አድናቆቴን የገለጽኩበት የተለመደው ማስታዋሻ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሚያዝያ መጀመሪያ ገና ስራቸውን ሲጀምሩ አዎንታዊ ድምጸቴን ከፍ አድርጌ በማሰማት ኢትዮጵያ ከጨለማው የጎሳ አፓርታይድ አዘቅት ውስጥ በመውጣት ረዥሙን ጉዞ በማድረግ አስራ ሶስት ወራት የጸሐይ ብርሀን የሚያንጸባርቅባት ምድር እንድትሆን ስማጸን ቆይቻለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስራቸውን ከጀመሩ ጀምሮ ለበርካታ ዓመታት ስተነብየው የቆየሁት ጉዳይ በስኬት የተጠናቀቀ መሆኑን በመገንዘብ ህወሀትን ሙሉ በሙሉ እርግፍ አድርጌ በመተው ወደ ታሪክ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫት ውስጥ ጥየዋለሁ፡፡

ከዚህ በታች በአጭሩ እንደተመለከተው ኢትዮጵያን የእነርሱ ብቻ ለማድረግ የማይችሉ ከሆነ ኢትዮጵያን የመበታተን እና ፍጹም የሆነ የማውደም ዕቅዳቸውን በመሞከር የመጨረሻውን የምጽአት ቀን እውን ለማድረግ ህወሀት የህጻንነት አይነት ባህሪ ያለው መሆኑን፣ አጭበርባሪ፣ በጥባጭ፣ እርባናቢስ ባህሪ ያለው እና ኢሞራላዊ የሆኑ ተግባራትን የሚፈጽም መሆኑን በመጥቀስ ጥቂት ያለፉ ምልከታዎችን ለማቅረብ ዓላማ አድርጊያለሁ፡፡ የእነርሱ የምጽአት ቀን ዕቅድ እንዲህ ባለችዋ እንስሳ የአማርኛ የቀድሞ አባባል ይገለጻል፣ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል“

=============  =============  ================

                                                          ልዩ የሆነ ጠቃሚ ትችት፣ 

ህወሀት ተጠንቀቅ በሰዎች ላይ እንዲፈጸም ስትመኘው የነበረው እርኩስ ተግባር በአንተው በእራስህ ላይ ይፈጸማል 

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 1 ቀን 2018 ዓም ባቀረብኩት ትችት እንዲህ በማለት ጽፌ ነበር፣ በአሁኑ ጊዜ ጂኒው ከጠርሙሱ ወጥቷል፡፡ የህወሀት ሰይጣናዊ የጂኒ ጠርሙስ ተሰብሯል፡፡ የህወሀት ጡብ ተሰብሯል፡፡ የኢትዮጵያ አቦሸማኔ (ወጣቱ) ትውልድ የቆሰለውን የህወሀት አውሬ በእራሱ የመጫወቻ ሜዳ ድል አድርጎታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ አቦሸማኔ ትውልድ የህወሀት አውሬ እግሮች ከሸክላ የተሰሩ መሆናቸውን በጠራራ ጸሐይ ማየት ይችላል፡፡“

ለእነዚህ የህጻናት ዓይነት ባህሪ ለሚያሳዩት የህወሓት መሪዎች እውነቱን ልንገራቸው ምክንያቱም ንጹሀን ዜጎችን  በመግደል፣ በማሰር እና በማሰቃየት ፍጎታቸውን ሊያሳኩ እንደማይችሉ እና በማጭበርበር የተገኘ ስልጣናቸውን ከሕግ አግባብ ውጭ ሊጠቀሙ እንደማይችሉ እንዲሁም በየቦታው ያሉ በእራሳቸው የማይተማመኑ ቦቅቧቃ ፈሪዎች ልብ ገዝተው ድምፃቸዉን ከፍ አድርገው ስለህውሃት ወንጀሎች እንዲናገሩ ልብ ለመስጠትም ነው።

የሚገርም ነገር ነው! የቆሰለ አውሬ ለበለጠ በቀል ተመልሶ ለመምጣት በመጨረሻው የጣዕረሞት ትግል በመወራጨት ላይ ይገኛል፡፡ ህወሀት ከስልጣን መወገዱን ያህል የሚያስደስት ነገር የለም!

የህወሀት የምጽአት ቀን ዕቅድ በከፍተኛ ደረጃ ተጠናክሮ ይገኛል፡፡

ህወሀት ለበርካታ አስርት ዓመታት ሲያራምደው የቆየውን ኢትዮጵያን ፍጹም በሆነ መልኩ ለማጥፋት እና የትግራይ ሪፐብሊክን ለመመስረት ሲያልም የቆየውን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የህጻንነት ባህሪውን ለዓለም በማሳት ላይ ይገኛል፡፡

ላፉት ጥቂት ዓመታት የህወሀት ዋና መሪዎች ኢትዮጵያን እንደ ብረት ቀጥቅጠው እንደ ሰም አቅልጠው መግዛት የማይሳካላቸው ከሆነ እና የጎሳ አፓርታይድ ስርዓታቸውን ለዘላለም ማስቀጠል የማይችሉ ከሆነ የትግራይ ሬፐብሊክ ምስረታ የምጽአት ቀን ዕቅዳቸውን ተግባራዊ ያደርጋሉ በማለት ፍንጭ እና ምልክት ሰጥተዋል፡፡ ዋናው መሮኋቸው “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቅል” ካለችው እንስሳ የቀድሞ አባባል ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡ በሌላ አባባል ከእኔ በኋላ ጎርፍ በመምጣት ሁሉንም ነገር ይጠራርገው እንደማለት ነው፡፡

የትግራይ ሬፐብሊክን የመመስረት የህወሀት የምጸአት ቀን ዕቅድ ለበርካታ ዓመታት ታውቋል፡፡

እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም የቀድሞው የህወሀት ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩት ገብረ መድህን አርዓያ የህወሀት ርዕይ እና ተልኮ ሁልጊዜ ትግራይን ከአማራ የቅኝ አገዛዝ ነጻ ማውጣት እና የትግራይ ሬፐብሊክን መመስረት እንደሆነ ግልጽ አድርገዋል፡፡ [የህወሀትን ዋናውን እና የመጀመሪያውን የእጅ ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ጋ ይጫኑ፣ ለግንኙነት መስመር ደግሞ እዚህ ጋ ይጫኑ፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በማስረጃ በማስደገፍ እንዳቀረብኩት “የህወሀት መልዕክት ኢትዮጵያን ለዘላለም እንደ ብረት ቀጥቅጦ እንደ ሰም አቅልጦ መግዛት አለያም ደግሞ በቁንጮ ባለስልጣናቱ አማካይነት ሁልጊዜ በተደጋጋሚ ድፍረት የተቀላቀለበት ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት፣ ንግግሮችን ማድረግ እና ቅጥ አምባሩ የጠፋበት የጽሁፍ ትችቶችን ማቅረብ ነው”፡፡

እ.ኤ.አ መስከረም 2016 ዓ.ም የህወሀት ዋና አለቃ በኢትዮጵያ ከሩዋንዳ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሀሳባዊ የሆነ የዘር እልቂት እንደሚመጣ አወጀ፡፡ ዋና መልዕክቱም እንዲህ የሚል ነበር፣ የሩዋንዳው ዓይነት በኢትዮጵያ እንዳይደገም የትግራይ ሬፐብሊክን መመስረት ነው፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት ህወሀት በኢትዮጵያ ውስጥ የእርሱን የቅጥረኛ ኮማንድ ፖስት በማዋቀር እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ በኢትዮጵያ ውስጥ የሽብር አገዛዙን በማስፋት የሞት የሽረት ትግል በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

መልዕክቱም እንዲህ የሚል ነው፣ ህወሀት የሽብር አገዛዙን በህዝብ ጫንቃ ላይ ካልጫነ እና የጎሳ አፓርታይድ ስርዓቱን ማስቀጠል ካልቻለ የትግራይ ሬፐብሊክን ይመሰርታል፡፡“

እ.ኤ.አ የካቲት 2018 ዓ.ም የህወሀት ዋና አለቃ ስዩም መስፍን የትግራይ ህዝብ የጦር ትጥቅ እንዲታጠቅ እንዲህ በማለት ጥሪ አቀረበ፣ ጓዶች በአሁኑ ወቅት ተጋፍጠነው የሚገኘው የአፈጠጠው አደጋ እጅግ በጣም የሚያስፈራ፣ እጅግ በጣም የሚያስፈራ ነው፡፡ መሮጥ ካልቻልን እና ፈጥነን ካልሮጥን እና ጸሐይ ከመጥለቋ በፊት አደጋውን መከላከል ካልቻልን በህይወት የመቆየታችን ጉዳይ አጠራጣሪ ነው“ ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን መንግስትን ማቆሸሽ እና በትግራይ ህዝብ ላይ የስነ ልቦና ጦርነት መክፈት በማለት ከሷቸዋል፡፡ መልዕክቱም እንዲህ የሚል ነው፣ ከዘር አጥፊዎች ጥቃት ለማምለጥ በፍጥነት መሮጥ እና ንጹኋን የትግራይ ሬፐብሊክን መመስረት፡፡

እ.ኤ.አ የካቲት 2018 ዓ.ም የህወሀት ጄኔራል ጻድቃን ገብረ ኪዳን የህወሀትን ህልውና ለማረጋገጥ “ነጻ ኮሚሽን” እንዲቋቋም በማለት ድፍረት የተቀላቀለበት የተስፋ ድምጹን ከፍ አድርጎ በመናገር የህወሀትን የጎሳ አፓርታይድ ስርዓት ለማስቀጠል እና በአትዮጵያ ውስጥ የእርሱን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ቡድን የበላይነት ዘላለማዊ ለማድረግ የሸፍጥ ዕቅዱን አቅርቧል፡፡

መልዕክቱም እንዲህ የሚል ነው፣ ህወሀትን በስልጣን ላይ ለማቆየት የሚያስችል ነጻ ኮሚሽን ካልተቋቋመ ነጻ የትግራይ ሬፐብሊክን መስርት፡፡“

በአሁኑ ጊዜ ህወሀት ለማሸበር እና ለማስፈራራት እንዲህ በማለት ወኪሎቹን ይጠቀማል፡፡ የትግራይ ህዝብ የመዋጋት እና ድል የማድረግ ብቃት አለው፡፡ ጊዜ እና ታሪክ ምስክራችን ነው!“ መልዕክቱም እንዲህ የሚል ነው፣ ህወሀት የትግራይ ሬፐብሊክን ለመመስረት እራሱን ለወታደርነት እያዘጋጀ ነው፡፡“

በአሁኑ ጊዜ ህወሀት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን መንግስት ለማዳከም በተወሰኑ የሀገሪቱ ክፍሎች የጎሳ ጥቃት እና የጥላቻ ችግር በመፍጠር ላይ ነው፡፡ መልዕክቱም እንዲህ የሚል ነው፣ ህወሀት እንደፈለገው ሊያደርጋት የሚችለውን ኢትዮጵያን በሴተኛ አዳሪነት መያዝ ካልቻለ በጎሳ ጥላቻ እና በመበታተን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መጥፋት አለባት፡፡“

 

በአሁኑ ጊዜ ህወሀት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ አሳሪውን የድንበር ኮሚሽን የስምምነት ውሳኔን ለይስሙላ በመቀበል (ከሟቹ ባለራእዩ መሪያቸው ከመለስ ዜናዊ በስተቀር ማንም ለመቀበል ያልተስማማበትን) ችግር ለመፍጠር በትግራይ ውስጥ ወጥነት የሌላቸው እና ከተለመደው ዓይነት ስርዓት ያፈነገጡ በሁለት ወይም በሶስት ቦታዎች ላይ ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን በማደራጀት ላይ ይገኛል፡፡ መልዕክቱም እንዲህ የሚል ነው፣ ህወሀት የትግራይ ሬፐብሊክን ለመመስረት እና ወሰኖችን ለመከላከል የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ እንደ ሰበብ ይጠቀምበታል፡፡“ (ባለፉት 27 ዓመታት በትግራይ ወስጥ መንግስትን የሚቃወም አንድም ዓይነት ህዝባዊ ተቃውሞን ሊያስተናግድ የሚችል ሰላማዊ ሰልፍ በፍጹም ተደርጎ አያውቅም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የትግራይ ህዝቦች በነጻነት ለመናገር እና ሀሳቦቻቸውን ለመግለጽ ዕድል አይሰጣቸውም ነበር፡፡ ህወሀት ላደራጃቸው ጥቂት ሰላማዊ ሰልፍ አድራጊዎች ስለሰላማዊ ሰልፍ ከተለመደው ወጣ ያለ እና ልዩ የሆነ የሰላማዊ ሰልፍ ስልጠና ሰጥቷቸዋልን?)

ሁሉም የህወሀት የተፈበረኩ የማታለያ ዘዴዎች የዘላለም ህልማቸው የሆነውን የትግራይ ሬፐብሊክን ለመመስረት ከሆነ ጫካውን አትደብድቡ እላችኋለሁ (እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ እና 80ዎቹ ስታደርጉት እንደነበረው):: እስቲ ተነሱ እና በጭንቅላታችሁ ውስጥ ያለዉን ፍርጥርጥ አርጋችሁ ተናገሩ ። ማወናበዳችሁን አቁሙ፡፡

ሆኖም ግን ከ1994ቱ ትምህርት ውሰዱ፡፡ እንደፈለጋችሁ ለመፐወዝ ለምትሞክሩት እና ፍጹም የማይፈልገውን ምርጫ እንዲቀበል ለምታስገድዱት የትግራይ ህዝብ ታማኝ ሁኑ፡፡ እንዲህ የሚለውን አንድ እና አንድ ጥያቄ በማንሳት እራሳችሁን ጠይቁ፣ .. 1994 . ከኢትዮጵያ የተገነጠሉት ወገኖች በአሁኑ ጊዜ 1994 በፊት ከነበሩበት የተሻለ ህይወት ይኖራሉን?“

የትግራይ ህዝብ ከቀሩት ኢትዮጵያውያን ወንደሞቹ እና እህቶቹ ጋር በሰላም እና በፍቅር መኖር ይፈልጋል፡፡ ከኢትዮጵያ መለየት/መገንጠል አይፈልጉም ምክንያቱም ትግራይ የኢትዮጵያ የመሰረት ድንጋይ ናት፡፡ በእኔ አመለካከት የትግራይ ህዝብ በአርበኝነት ተጋድሏቸው ወይም ደግሞ በኢትዮጵያዊነት ባላቸው ኩራት ከማንም በላይ ናቸው፡፡ ለዚህ አባባሌ ታሪክ ለማስተባበል የማይችለው ምስክር ነው!

እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ግን የትግራይ ህዝቦች ከማንም በላይ ያውቃሉ፡፡ ህወሀት በእነርሱ ስም እየነገደ እና የፍርኃት ጥላቻን እየቀፈቀፈ እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ የትግራይ ህዝቦች ህወሀት ስልጣን ላይ ተጠብቆ ለመኖር መጠቀሚያ እንደሆኑ አሳምረው ያውቃሉ፡፡ የትግራይ ህዝቦች እስቲ ነጻ ሆነው መብቶቻቸው ይጠበቁ እና የምርጫ ድምጾቻቸውን በትክክል ለህወሀት ድጋፍ መስጠት አለመስጠታቸውን ውጤቶቻቸውን እንይ፡፡

ያም ሆነ ይህ የትግራይ ህዝቦች ባለፉት 27 ዓመታት ከሕግ አግባብ ውጫ ተስተናግደው ከሆነ እና መብቶቻቸው ተደፍጥጠው ከሆነ ይህንን የመብት ድፍጠጣ እና ከሕግ አግባብ ውጭ ማስተናገድን የፈጠረውን መንግስት እየተቆጣጠረ ያለው ማን ነው?

የህወሀት አመራሮች ያዘጋጃችሁት የምጽአት ቀን ሌላ በማንም ላይ ሳይሆን ዕቅዱ በእራሳችሁ ላይ እንደሚፈጸም እወቁ፡፡

የአንቀጽ 39 መርዝ ኢትዮጵያን አይገድላትም፡፡ ሆኖም ግን ኢትዮጵያን ይገድላል በማለት አስበው የዋጡትን ይገድላል፡፡

የህወሀት አለቆች የቀብር ደወሉ ለኢትዮጵያ ህዝቦች እየተደወለ ነው ብለው ያስባሉ፡፡

ስማ፣ ስማ፣ ህወሀት! “ደወሉ ለማን እንደተደወለ አላወቅኸውም፤የተደወለው ለአንተው ለእራሰህ ነው፡፡“

ህወሀት የተሻለ መንገድ አለ፡፡ ቀሪዎቹን ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችሁን እና አህቶቻችሁን ተቀላቀሉ እና እጅ ለእጅ በመያያዝ የአፍሪካን አህጉር የሚያቋርጡትን እና በኔልሰን ማንዴላ መልካም ነገር እና ይቅርባይነት እየተባሉ የሚጠሩትን ሁለቱን አውራ መንገዶች በማቋረጥ ተራመዱ፡፡

ተለዋጩ መንገድ ግን ወደ ሲኦል የሚወስደው መንገድ ነው፡፡

ለዚህም ነው እንግዲህ በሰዎች ላይ እንዲሆን ለምትመኙት ነገር ሁሉ ጥንቃቄ ማድረግ ያለባችሁ ምክንያቱም ለሌሎች የተመኛችሁት በእራሳችሁ ላይ ሊፈጸም ይችላልና፡፡ እናም ወደ መልካም ነገር የሚያስሄደውን አንዱን መንገድ ያዙ፤ የሲኦል መንገድ መመለሻ የለውምና፡፡

============  ==================  ==================

አብይ አህመድ ህይወት አድኑ ጠቅላይ ሚኒስትር

 በኢትዮጵያ ውስጥ አእምሮ ከሚያስበው በላይ በበለጠ መልኩ ፈጣን የሆነ ለውጥ በማምጣት ላይ በመሆናቸው የዓለም ፈጣን የሩጫ ርቀት ሪከርድ ባለቤት በሆነው እና በስም ዩሰይን ቦልት እየተባለ በሚጠራው አትሌት ስም በአሁኑ ጊዜ አብይ አህመድን “ጠቅላይ ሚኒስትር ቦልት“ እያሉ የሚጠሩ አሉ፡፡

“ከጠቅላይ ሚኒስትር ቦልት” ጋር ምንም ዓይነት ችግሮች የሉብኝም፡፡ ለእኔ “የኢትዮጵያ ህይወት አድኑ” ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው፡፡

ይኸ ጉዳይ እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ አጋማሽ የአሜሪካ የፊልም አስቂኝ ተዋንያን ከሆነው እና እንዲህ ከሚለው ከጎስትቡስተርስ የሙዚቃ ቅላጼ የጥሪ ምላሽ ጋር ይመሳሰላል፡ በጎረቤትህ አንድ የተለየ አዲስ ነገር ካለ ማንን ትጠራለህ? (እርኩስ መንፈስ አስወጋጅን ) አንድ ያልተለመደ ነገረ ካለ እና ጥሩ መስሎ የማይታይ ከሆነ ማንን ትጠራለህ ? (እርኩስ መንፈስ አስወጋጅን )።

እንገዲህ! ደህና በግብጽ ሀገር ህገወጥ በሆነ መልኩ የታሰሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ካሉ እና እጅግ በጣም ኢሰብአዊ በሆነ መልኩ የሚሰቃዩ ከሆነ ማንን ትጠራለህ? አብይ አህመድን!

በሳውዲ አረቢያ ሀገር ህገወጥ በሆነ መልኩ የታሰሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ካሉ እና እጅግ በጣም ኢሰብአዊ በሆነ መልኩ የሚሰቃዩ ከሆነ ማንን ትጠራለህ? አብይ አህመድን!

በሱዳን ሀገር ህገወጥ በሆነ መልኩ የታሰሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ካሉ እና እጅግ በጣም ኢሰብአዊ በሆነ መልኩ የሚሰቃዩ ከሆነ ማንን ትጠራለህ? አብይ አህመድን!

በኬንያ ሀገር ህገወጥ በሆነ መልኩ የታሰሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ካሉ እና እጅግ በጣም ኢሰብአዊ በሆነ መልኩ የሚሰቃዩ ከሆነ ማንን ትጠራለህ? አብይ አህመድን!

እ.ኤ.አ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በሆስፒታል ውስጥ እራሱን ለማወቅ በማይችልበት ሁኔታ/ኮማ ተኝቶ በሚገኝ ኢትዮጵያዊ ህጻን እና የሀገሩ መንግስት የተረሳ ካለ ማንን ትጠራለህ? አብይ አህመድን!

ኢትዮጵያውያን በእራሳቸው ሀገር ህገወጥ በሆነ መልኩ ከህግ አግባብ ውጭ ታስረው፣ ከህግ አግባብ ውጭ መብቶቻቸው ተደፍጥጠው እና ስቃይ የሚፈጸምባቸው ከሆነ ማንን ትጠራለህ? አብይ አህመድን!

ወደ ግብጽ ሄደህ ህዝቦቼን አስለቅቅ!

እ.ኤ.አ ሰኔ 11 ቀን 2018 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በጣም ኢሰብአዊ በሆነ ሁኔታ በግብጽ ውስጥ ታስረው የቆዩትን በደርዘን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ይዘው በድል አድራጊነት ተመልሰዋል፡፡ (ቪዲዮውን እና የተተረጎመውን የቃለ መጠይቅ መግለጫ ከዚህ በታች ይመልከቱ)።

ከዚህም በተጨማሪ በእራሳቸው ጀት አውሮፕላን ወደ ሀገር ቤት አምጥተዋቸዋል፡፡ ከግብጽ ባርነት ነጻ በመሆናቸው ሁሉም ከመጠን ያለፈ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፣ እንደገና እንደተወለድኩ ያህል እቆጥረዋለሁ፡፡“ በግብጽ የባርነት ምርኮኛነት አደጋ ተጋልጠው በቆዩት ኢትዮጵያውያን ምስክርነት ልቡ ያላዘነ ካለ ድንጋይ ልበ ድፍን ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በግብጽ ውስጥ ተጋርጦባቸው ከነበረው አደጋ ማዳናቸው እ.ኤ.አ ሀምሌ 2015 ዓ.ም ለፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የጻፍኩትን ደብዳቤ አስታወሰኝ፡፡ በዚያ ደብዳቤ ባራክ ኦባማ ለህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ እንዲህ የምትል አንድ ዓረፍተ ነገር እንዲያስተላልፉ ጠይቂያለሁ፣ ሕዝቤን ልቀቅ

በምወደው እና በታላቁ መንፈሳዊ የጥቁር አሜሪካኖች መዝሙር “ሙሴ ውረድ” ወደ ግብፅ ህዝቤን  አስፈታ በሚለው መዝሙር በመገፋፋት ያቀረብኩት ልዩ ጥያቄ ነበር፡፡ ከህወሀት ምርኮኝነት እና ባርነት ነጻ ቢያወጣን ኖሮ ኦባማን ኢትዮጵያዊው ሙሴ መሆን ይችል ነበር ብየ አስባለሁ፡፡

በህይወቴ ውስጥ ከፍተኛ ስህተት ከምላቸው አንዱ ይህኛው የኦባማ ነገር ነው፡

ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ ውረድ ወደ ኢትዮጵያ ምድር ሂድ፣

ለህወሀት አሮጌ ፈርኦኖች ህዝቤን ልቀቅ በማለት ተናገር፣

መከራን ተሸክመው መቆም አይችሉምና፣

ህዝቤን ልቀቅ በልልኝ ፡፡

ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ ውረድ ወደ ኢትዮጵያ ምድር ሂድ፣

ለህወሀት አሮጌ ፈርኦኖች ህዝቤን ልቀቅ በማለት ተናገር፣

ስለሆነም ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ ምድር ወረደ፣

እናም አሮጌዎቹ የህወሀት ፈርኦኖች “ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የተመረጡ ናቸው” በማለት ለዓለም ተናገረ፡፡

ኦባማ ለ25 ዓመታት በባርነት ሲሰቃዩ ለቆዩት የኢትዮጵያ ህዝቦች ምንም ዓይነት የተስፋ እና የሀጢያት ስርየት መልዕክት አላስተላለፈም፡፡ ይልቁንም የግንዛቤ ደረጃቸውን የሚፈታተን፣ ክብራቸውን የሚያዋርድ እና ሞገሳቸውን ዝቅ የሚያደርግ ይፋ የስድብ መልዕክት ነበር ያስተላለፈው፡፡

ኦባማ እ.ኤ.አ በ2015 ዓ.ም መቶ በመቶ የፓርላማ ወንበሮችን ለተቆጣጠሩት እና እ.ኤ.አ በ2010 ዓ.ም ደግሞ 99.6 በመቶ በማሸነፍ አሮጌዎቹ የህወሀት ፈርኦኖች በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመልካም ሁኔታ መመረጣቸውን እንዲህ በማለት ተናግሯል፡

እነዚህ ጉዳዮች ሲነሱ ምላሴን አላጥፍም፡፡ መንግስትን በኃይል ለማስወገድ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን የኢትዮጵያን መንግስት ጨምሮ የሚሞክርን ማንኛውንም ቡድን እንቃወማለን፡፡ ሕገ መንግስቱ ከጸደቀ ቅርብ ጊዜ ቢሆንም የተደረገው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መንግስት የተመረጠበት ነው“ ነበር ያለው አፉን ሞልቶ፡፡

ኦባማ አሮጌዎቹ የህወሀት ፈርኦኖች ዘላለማዊ ምርጥ ወዳጅ መሆኑን አስመስክሯል፡፡

የባራክ ኦባማ አሳዛኝ እና አሳፋሪ ውሸቶች ህሊናየን በጠበጡት እናም እምነቴን ተፈታተነ፡፡ ሆኖም ግን ተስፋ አልቆረጥኩም፡፡ የኦባማ ውሸቶች የበለጠ እንድጠነክር እና የአረብ ብረት በመሆን ለአሮጌ የህወሀት ፈርኦኖች አንድም ሳምንት ሳላሳልፍ በእያንዳንዱ ሳምንት “ህዝቤን ልቀቁ!” የሚል መልዕክት በማስተላለፍ እውነታውን እንድናገር የበለጠ አደፋፈረኝ፡፡

በእኔ ልዩ አስተሳሰብ መልዕክቴን ለአሮጌው የህወሀት ፈርኦን ሊያደርስልኝ የሚችል ሰው ይመጣል የሚል ሀሳብ በፍጹም አልነበረኝም ሆኖም ግን ለአሮጌው ፈርኦን መንገዱን በማሳየት እንዲህ ብለውታል፣ “ህወሀት መንገዱን ይዘህ ተጓዝ፡፡ ከዚህ በኋላ ተመልሰህ አትመጣም በፍጹም በፍጹም … “

አብይ አህመድ በአሁኑ ጊዜ ህዝባቸውን ከህወሀት የጎሳ አፓርታይድ የባርነት በረሀ በድል አድራጊነት ነጻ በማውጣት ወደ ሰላም እና እርቅ የለመለመ ሸለቆ በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡

ሆኖም ግን አብይ አህመድ በተጨማሪ ህዝባቸውን ከያሉበት የእስራት ባርነት ነጻ በማውጣት ንቁ የሆኑ ዓለም አቀፋዊ ህይወት አድን ሆነዋል፡፡

አብይ አህመድ ወደ ሳውዲ አረቢያ በመውረድ “ህዝቤን ልቀቁ” በማለት ለሳውዲ አረቢያ ፈርኦኖች ነግረዋቸዋል፡፡ እናም በሳውዲ አረቢያ ውስጥ በባርነት ተይዘው የነበሩትን ከአንድ ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ነጻ አድርገዋል፡፡

አብይ አህመድ ወደ ተባበሩት የዓረብ ኤምሬቶች በመውረድ “ህዝቤን ልቀቁ” በማለት ለተባበሩት የዓረብ ኤምሬቶች ፈርኦኖች ነግረዋቸዋል፡፡ እናም በተባበሩት የዓረብ ኤምሬቶች ውስጥ በባርነት ተይዘው የነበሩትን ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ነጻ አድርገዋል፡፡

አብይ አህመድ ወደ ሱዳን በመውረድ “ህዝቤን ልቀቁ” በማለት ለሱዳን ፈርኦኖች ነግረዋቸዋል፡፡ እናም በሱዳን ውስጥ በባርነት ተይዘው የነበሩትን 1400 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ነጻ አድርገዋል፡፡

አብይ አህመድ ወደ ኬንያ በመውረድ “ህዝቤን ልቀቁ” በማለት ለኬንያ ፈርኦኖች ነግረዋቸዋል፡፡ እናም በኬንያ ውስጥ የእስረኞች የመፈታት ልውውጥ ለማድረግ ስምምነት አድርገው ተመልሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በግብጽ ጉብኝታቸው ወቅትም ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በዓባይ ወንዝ ላይ እየተሰራ ወዳለው የኢትዮጵያ ግድብ የሚፈሰውን ውኃ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ በመቆጣጠር የግብጽን ህዝብ ትጎዳለች ከሚለው የፍርኃት ባርነት፣ ጥላቻ እና ስጋት ነጻ አድርገዋል፡፡

የፕሬዚዳንት ሲሲን “ኢትዮጵያ ግብጽን አትጎዳም ለሚለው ለአምላክ ቃል እንዲገቡ” ያላቸውን ውስጣዊ ተማጽዕኖን በመቀበል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዲህ በማለት አውጀዋል፣ መንግስቴ እና ህዝቤ የግብጽን ህዝብ እና መንግስት የመጉዳት ዓላማ የላቸውም፡፡ በማንኛውም መንገድ ከግብጽ ህዝብ ጋር በጋራ እንሰራለን፡፡“

መልሷቸው፣ ወደ ኢትዮጵያ ምድር መልሳችሁ ምሯቸው፣ አብይ አህመድ!

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኢትዮጵያውያንን በአሮጌው የህወሀት ፈርኦን ጨካኞች አገዛዝ ምክንያት ስደተኞች ለመሆን ተገደው እስረኛ እና ምርኮኛ ወጣት ኢትዮጵያውያንን በማዳናቸው የእኛ ሙሴ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ሀገራቸውን ለቀው በመሰደድ በመካከለኛው ምስራቅ ባሪያ ሆነው ለቆዩት በመቶዎች እና በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የእነርሱ ሙሴ ናቸው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለም!

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከግብጽ ባርነት ነጻ ያወጧቸው ጥቂት ኢትዮጵያውን መግለጫዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

ሴት ቁጥር 1 በእኛ ላይ በርካታ ነገሮች ተፈጽመውብናል፡፡ በጋለ የኤሌክትሪክ ሽቦ እንድንቀመጥ በማድረግ አቃጥለውናል፡፡ ተደብድባናል፡፡ በቴሌቪዥነ መስኮት ላይ እንድንቀርብ በማድረግ አስቸጋሪ እና ዘፋኞች እንደሆን አድርገን በሀሰት እንድንናገር አድርገዋል፡፡

በድንገት መጡ እና እንድንዘጋጅ ነገሩን፡፡ የት እንደምንሄድ ምንም ዓይነት ሀሳብ አልነበረንም፡፡ ወደ ሌላ እስር ቤት ሊያዛውሩን ነው የሚል ነገር ነበር ያሰብነው፡፡ የነገሩን እንደዚያ በማለት ነበር፡፡ እዚያ ከደረስን በኋላ እንዲህ በማለት ነገሩን፣ መንግስታችሁ እዚህ መጥቷል [ግብጽ]  እናም እናንተን ነጻ ለማድረግ ተዘጋጅቷል፡፡“ ከመጠን ያለፈ ደስታ አደረግን፡፡ በእውነት በጣም ተሰቃይተናል፡፡ እንደገና እንደተወለድኩ አድርጌ እቆጥረዋለሁ፡፡ እግዚአብሄር ያክብራቸው [ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን] ፣ ረዥም እድሜ  ይስጣቸው፡፡ በጣም ተደስቻለሁ፡፡ ሆኖም ግን የእኛ ወገኖች እዚህ እየተሰቃዩ ናቸው፡፡ እግዚአብሄር ይስጣቸው፡፡ ከዚህ በላይ ምንም የምለው ነገር የለም፡፡

 ወንድ ቁጥር 1 በእስር ቤት ውስጥ በምን ዓይነት አስቀያሚ ሁኔታ እንስተናገድ እንደነበር ለመግለጽ ቃላት የለኝም፡፡ ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ እና የማሰቃየት ድርጊት የሚፈጸምብን ጊዜ ነበር… ኢትዮጵያውያን በሀገራችን በመስራት እራሳችንን መለወጥ እንችላለን፡፡ በተለይም እኛ ወጣቶች በተለያዩ ስሜታዊ ግፊቶች በእርግጥ በበርካታ ማክንያቶች ከሀገራችን በመውጣት ስደተኛ እንሆናለን፡፡ ሆኖም ግን በሀገራችን በመስራት መለወጥ እንችላለን፡፡ ጉልበቱ የወደፊት ተስፋው አለን…

ሴት ቁጥር 2፡ በመጀመሪያ ወደ እስር ቤት በገባን ጊዜ በጋለ የኤሌክትሪክ ሽቦ አቃጥለውናል፡፡ በቀን 24 ሰዓት ሙሉ ይደበድቡን ነበር፡፡ ውኃ፣ ምግብ እንኳ አይሰጡንም ነበር፡፡ ወደ መጸዳጃ ቤትም እንድንሄድ አይፈቅዱልንም ነበር፡፡ ምንም ዓይነት ነገር አይሰጡንም ነበር፡፡

ወንድ ቁጥር 2፡ በጣም በጣም እናመሰግናለን፡፡ እናት ልጆቿን እንደምትሰበስብ እና እንደምታቅፍ እርሳቸው [ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ] መጥተው አዳኑን ወደ ሀገራችንም ወሰዱን፡፡ በጣም አመሰግናለሁ፡፡

ወንድ ቁጥር 3፡ ተኝተን ነበር፡፡ እናም በጧት በመምጣት በራችንን በኃይል አንኳኩት፡፡ እንዲህ በማለትም ጮኹ፣ ውጡ! ውጡ!“ በእስር ቤቱ ውስጥ ሁልጊዜ ምርመራ ስለሚያደርጉ ያ ይሆናል በማለት በማሰብ ቀስ በማለት ወጣን፡፡ እቃዎቻችንን ይዘን እንድንወጣ ነገሩን፡፡ በጣም ድንገተኛ በመሆኑ ምንም አላመንንም ነበር፡፡ ሀገራችንን ለቀን ሄደናል ምክንያቱም የተሰደድነው ለመለወጥ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ያ ነገር ለእኛ አልሰራም፡፡ እናም በቁጥጥር ስር በመዋል ወደ እስር ቤት ተወረወርን፡፡

ሴት ቁጥር 3፡ እኔ የምፈልገው ነገር ወደ ሀገሬ በመመለስ በሰላም ሴት ልጀን ማሳደግ ነው፡፡ የምፈልገው ይህንን ነው፡፡ ከእንግዲህ በኋላ ምንም ዓይነት ስደት አላስብም፡፡

የኢትዮጵያውያን ህይወት ከቁብ ያልገባበት ጊዜ፣

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሰሩት ስራ ትልቅ ነገር አይደለም ብለው ለሚያስቡ ወገኖች ጥቂት ዓመታትን ወደኋላ መለስ ብለው እንዲያስቡ እፈልጋለሁ፡፡

በአረመኔ አሸባሪ ቡድኖች እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2015 ዓ.ም በሊቢያ 30 ወጣት ኢትዮጵያውያን አንገታቸውን ሲቀሉ የህወሀት አገዛዝ በመጀመሪያ በአሸባሪዎች አንገታቸውን የተቀሉት ነጻ በሆነ አካል ባለመረጋገጡ ምክንያት በሚል ሰበብ ኢትዮጵያውያን ስለመሆናቸው እውቅና ለመስጠት ተቃወመ፡፡ ሬውተር፣ ኤጄንስ ፍራንስ፣ ቢቢሲ፣ ቪኦኤ፣ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ዋሺንግተን ፖስት ሁሉም የዜና አውታሮች የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ኢትዮጵያውያን ናቸው በማለት እየዘገቡም አንኳ የህወሀት አገዛዝ በክህደቱ እንደቀጠለበት ቆየ፡፡

እ.ኤ.አ ህዳር 2013 ዓ.ም የህወሀት ቁንጮ መሪ ቴወድሮስ አድሀኖም ሳውዲ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን እና የቤት ሰራተኞችን መብቶች በመደፍጠጧ የሳውዲ አረቢያን መንግስት ይቅርታ ጠየቀ፡፡ ኢትዮጵያውያንን በሳውዲ አረቢያ ማጋዝ እና መገደል ለተወሰነ ጊዜ አስቆጥቶኛል በማለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ፡፡ ለሳውዲው አምባሳደር እንዲህ በማለት ነገረው፣ የሳውዲ ባለስልጣኖችን እና ህገወጥ ስደተኞችን የሚያግዘውን/ግዞት የሚያስገባውን ፖሊሲ ለማመስገን እውዳለሁ፡፡“

በተሳሳተ የሕክምና አሰጣጥ ምክንያት እ.ኤ.አ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያዊ ህጻን ተገቢ ሕክምና ባለማጋኘቱ ምክንያት የችግር ሰለባ ሆኖ እራሱን ማወቅ በማይችልበት/ኮማ ሁኔታ ሲኖር እና የልጁ ወላጆች እርዳታ እንዲደረግለት ልተቋረጠ ተማጽዕኖ ሲያቀርቡ ቢቆዩም ማንም የህወሀት አገዛዝ ባለስልጣን ልጁን አልጎበኘውም ወይም ምላሽ አልሰጠም፡፡ በግንቦት አብይ አህመድ ወደ ሳውዲ አረቢያ በሄዱ ጊዜ የመጀመሪያ ነገር አድርገው የያዙት ልጁን መጎብኘት እና ወዲያውኑ ለሳውዲ መንግስት የገንዘብ ካሳ የመስጠት ስምምነት እንዲደረግ እና ልጁን ወደ ሀገሩ እንዲመለስ አድርገዋል!

በአብይ አህመድ አመራር በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ህይወቶች ከቁብ ይገባሉ/በደንታቢስነት እና በኬሬዳሽ አይታለፉም!

በአብይ አህመድ ለምን እንደምኮራ እና ሁላችንም እርሳቸውን ለምን መደገፍ እንዳለብን፣

 ለግማሽ ምዕተ ዓመት በዘለቀው በጎልማሳነት ዘመኔ በማንኛውም የኢትዮጵያ መሪ ላይ በፍጹም በፍጹም ኮርቼ አላውቅም፡፡

ይልቁንም በተጻራሪ መልኩ በእነዚህ እራሳቸውን በስልጣን ማማ ላይ በኮፈሱት፣ ምንም ዓይነት ተጠያቂነት በሌላቸው፣ ምንም ነገር በማያውቁት፣ ለምንም ነገር በማይበጁ ወንጀለኞች፣ ሌቦች እና ገዳይ አስመሳይ የኢትዮጵያ መሪ ተብዬዎች ላይ ሁልጊዜ አዝናለሁ እተክዛለሁ፡፡

እስከ አሁንም ድረስ! ለዘመናት ኢትዮጵያን አጥንቷ እስኪቀር ሲግጧት ከቆዩት አረመኔ ገዥዎች እጅ በአሁኑ ጊዜ የመሪነት ዋንጫው በኩራት እና በደስታ ህዝቦችን ለሚመሩት ለወጣቱ እና ለጠንካራው የለውጥ አቀንቃኝ ለአብኝ አህመድ ተላልፏል፡፡

ለመሆኑ አብይ አህመድ ማን ናቸው?

የእርሳቸው ማንነት በምትጠይቄት ሰው አንደበት ይወሰናል፡፡ አብይ አህመድ ኢትዮጵያን ከጨለማው ዘመን በማውጣት መልካም ነገር እና ይቅርባይነት እየተባሉ በሚጠሩ ሁለት መንገዶች በመውሰድ በተራራው ጫፍ ላይ በምትገኘው ከተማ እና አዲሲቷ ኢትዮጵያ እየተባለች ወደምትጠራው ሀገር ሊያሸጋግሯት ከአምላክ የተላኩ መልዓክ ናቸው የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡

ሌሎች ደግሞ ስለእርሳቸው ምንም አዲስ ልዩ የሆነ ነገር የለም ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያን ከጎሳ አፓርታይድ መቃብር በማንሳት በአፍሪካ አህጉር አንጸባራቂዋ ኮከብ እንድትሆን ማድረግ በሚችሉ ሚሊዮን አብይ አህመዶች የተሞላች ናት ይላሉ፡፡

እንደዚሁም ደግሞ አብይ አህመድ ተልዕኮ ያላቸው ሰው ናቸው የሚሉ በርካታዎች አሉ፡፡ እርሳቸው የጭነት ባቡር ናቸው፡፡ ከመንገዳቸው ዉጡ እንዳትዳጡ በትዕግስት ተመልከቷቸው የማይቻለውን እንዲቻል ማድረግ የሚችሉ ሰው ናቸው፡፡

ለእኔ አብይ አህመድ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዳሉት ከስምምነት ለመድረስ ምርምር የማያደርጉ እራሳቸው የስምምነት ጡብ ቅን መሪ ናቸው::”

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በኢትዮጵያ አሮጌውን የጥላቻ፣ የመከፋፈል፣ የጦርነት እና የበቀል ጡብ በመስበር በአሁኑ ጊዜ አዲስ የአመራር ጡብ በማውጣት በፍጥነት እና በቆራጥነት በመስራት ሊደመሰስ የማይችል ሰላም፣ እርቅ እና ፍቅር የሰፈነባት አዲሲቷን ኢትዮጵያ በመገንባት ላይ ናቸው፡፡

ላለፉት አስር ሳምንታት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሌት እና ቀን በመስራት ፍቅርን ለማስፈን እና ሀገራችንን ከጥላቻ በማውጣት ወንድማማችነት የሰፈነባት ሀገር ለማድረግ ጥረት እደረጉ ይገኛሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስምምነት ያጡ ድምጾችን ወደ ስምምነት በማምጣት እና ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ፖለተካዊ መፍትሄዎችን በመፈለግ ሙሉ ኃይላቸውን በስራ ላይ በማዋል ላይ ይገኛሉ፡፡ ሁሉንም ነገር እርሳቸው ብቻቸውን ሊሰሩት እንደማይችሉ ያውቃሉ፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ እንዲሳተፍ እና በፈቃደኝነት እንዲያግዝ ጋብዘዋል፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ኢትዮጵያ ሁሉንም ልጆቿን ለማስተናገድ እና የምትበቃ ሰፊ ሀገር ናት በማለት ይናገራሉ፡፡ በውጭ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው በመመለስ መዋዕለ ንዋያቸውን በነጻነት እንዲያፈሱ እና በፖለቲካው ነጻ ሆነው እንዲሳተፉ እና ሀሳባቸውንም በነጻነት እንዲገልጹ ጋብዘዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የጋራ ግብ በሆኑት እኩልነት፣ ፍትህ እና በኢትዮጵያዊነት ነጻነት ላይ ስምምነት በመገንባት ላይ ናቸው፡፡ ይህ ነው የአብይ አህመድ የስምምነት አልፋ ኦሜጋ፡፡ የእርሳቸው የኦሜጋ አጀንዳ በተራራው ጫፍ ላይ አንጸባራቂ እና “የተወደደችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ” በመባል የምትጠራ ከተማ መገንባት ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስልት ቀላል እና ግልጽ ነው፡፡ የተወደደችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ከሁሉም ኢትዮጵያውን መልካም ፈቃድ እና መልካም እምነት ተሳትፎ ውጭ ልትገነባ አትችልም፡፡ ሁልጊዜ አንዱ ወገን የሚያሸንፍበትን እና ሌላው ወገን ደግሞ ሁልጊዜ የሚሸነፍበትን የዜሮ ድምር የፖለቲካ ጨዋታ ሰርዘውታል፡፡ የአብይ የጨዋታ ዕቅድ በኢትዮጵያ የሰብአዊነት ጠላቶች የሆኑትን ጥላቻ፣ መከፋፈል፣ ስግብግብነት፣ ሙስና፣ ድህነት፣ በሽታ እና ማይምነት በማሸነፍ እያንዳንዱ ሰው አሸናፊ የሚሆንበትን ነው፡፡ ስለሆነም የእርሳቸው ተልዕኮ እንደ አሸናፊ (ተሸናፊ አይደለም) እና እንደ ድል አድራጊ (ምርኮኛ አይደለም) በመሆን ማሰብ እና ያሰበውንም በተግባር ላይ ማዋል አለበት፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰውነት እምቅ ኃይል ዘርተውበታል፡፡ በአንድ ላይ እጅ በእጅ በመያያዝ አብረን በመዋኘ በተራራው ጫፍ ላይ ወደምትገኘው ደህንነቷ ወደተጠበቀችው ከተማ እና አዲሲቷ ኢትዮጵያ እየተባለች ወደምትጠራው ሀገር እንደምንደርስ ወይም ደግሞ በእርስ በእርስ ጦርነት እና ተስፋቢስነት አብረን እንደምንሰጥም ቀን በቀን ግልጽ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

“ኢትዮጵያን ለማዳን የአብይ አህመድ ዋና ዕቅድ ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ በሰዎች ሳልጠየቅ ያለፍኩበት ዕለት የለም፡፡ “ለኢትዮጵያ ህዝቦች ያላቸው ጠቃሚ መልዕክት ምንድን ነው? ለዘመናት የተቆለሉትን የኢትዮጵያን ችግሮች እንዴት መፍታት ይችላሉ ምክንያቱም ጊዜ የለንም?”

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ብቻ ናቸው እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ የሚችሉት፡፡

ሆኖም ግን የእርሳቸውን ንግግሮች እና ህዝባዊ መግለጫዎች ለእራሴ እንደምመረምራቸው እንዲህ ሲሉ እሰማለሁ፣ ለዘመናት ለተቆለሉት የኢትዮጵያ ችግሮች ልዩ መፍትሄ የለኝም፡፡ ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ትክክል ለማድረግ ታምራዊ ኃይል የለኝም፡፡ ማንኛውም ለኢትዮጵያ የሚደረግ አስፈላጊ ነገር ቢኖር በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ወንድ፣ ሴት እና ልጅ እገዛ ብቻ እፈጽመዋለሁ፡፡ የእናንተን እርዳታ እፈልጋለሁ፡፡ የእናንተን እገዛ እጠይቃለሁ፡፡ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በአንድ  ኢትዮጵያ በምትባል ጀልባ ውስጥ ነን፡፡ አብረን እንዋኛለን ወይም ደግሞ አብረን እንሰጥማለን፡፡ ምንም ዓይነት ፍርሀት እና ጥርጣሬ አይደርባችሁ፡ መልካም ነገር እና ይቅርባይነት በሚል በተሰየሙ ሁለት መንገዶች በመጓዝ በተራራው ጫፍ ላይ ወደምትገኘው እና አዲሲቷ ኢትዮጵያ እየተባለች ወደምትጠራው ሀገር እንደርሳለን፡፡

እ.ኤ.አ ሰኔ 2018 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያስተላለፉት ሰፊ መልዕክት በእኔ አስተያየት ዊንስተን ቸርችል እ.ኤ.አ በ1940 እንግሊዝ የጨለማ ሰዓቶች በነበረችበት ጊዜ የተናገሩትን በመዋስ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን አባባል እንደሚከተለው አቀርበዋለሁ፡

ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲህ እላለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ የምሰጠው ምንም ዓይነት ነገር የለኝም፡፡ ሆኖም ግን ልሰጥ የምችለው ደም፣ ጥንካሬ የተሞላበት ስራ፣ እንባ እና ላብ ነው፡፡ ከፊታችን በጣም አስቸጋሪ የሆነ መንፈስ ይገጥመናል፡፡ ከፊታችን በጣም በርካታ በጣም በርካታ ትግሎች እና መከራዎች ይገጥሙናል፡፡

 ፖሲያችን ምንድን ነው? በማለት ትጠይቃላችሁ፡፡ በእያንዳንዱ ጎረቤት፣ ጎጥ፣ መንደር፣ የገጠር ከተማ፣ ከተማ እና በኢትዮጵያ ክልል ሰላም እና እርቅ ማስፈን እላችኋለሁ፡፡ ባለን ኃይል እና እግዚአብሄር አምላክ በሰጠን ኃይል ሰላም እና እርቅ እናሰፍናለን፡፡ በአስፈሪው አምባገነናዊ አገዛዝ በጨለማው እና በመጥፎው የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ አንቀደምም፡፡ ይልቁንም በእርሱ ከርሰ መቃብር ላይ ሰላም እና እርቅን እናሰፍናለን፡፡ የእኛ ፐሊሲ ይኸ ነው፡፡

ዓላማችሁ ምንድን ነው? በማለት ትጠይቃላችሁ፡፡ በአንድ ቃል ለመመለስ እችላለሁ፡፡ ድል ነው፡፡ የቱንም ያህል ዋጋ ተከፍሎ  ለሰላም እና እርቅ ድል፡፡ የእኛን ኢትዮጵያዊነት ለማጥፋት ሽብሮች እና እንደ አንድ ህዝብ አንድነታችንን ለማናጋት የሚደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም እንኳ ምን ጊዜም ድል በሰላምና እርቅ ፡፡ ድል ምንጊዜም ረዥም እና ወደ ሰላም እና እርቅ የሚወስደው መንገድ አስቸጋሪ ቢሆንም ከድል ውጭ ኢትዮጵያ እንደ አንድ ሀገር የመኖር ህልውናዋ አይኖርም፡፡

 ይህ እንዲታወቅ እናድርግ፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና አይኖርም፡፡ ኢትዮጵያውያን የቆሙለት ሁሉ አይኖርም፡፡ ፋላጎት አይኖርም፡፡ ኢትዮጵያን በሰላም እና በእርቅ ወደፊት ወዳላማው ለማስኬድ የሚያስችሉ የስሜት ዓመታት አይኖሩም፡፡ የእራሴን ስራ በደስታ እና በተስፋ ይዣለሁ፡፡ የእኛ ዓላማ በወንዶች እና በሴቶች ታጋድሎ እንደማይወድቅ የእርግጠኝነት ስሜት ይሰማኛል፡፡ በዚህ ወቅት በዚህ ጊዜ ደህና ስሜት ይሰማኛል፣ የሁሉንም እርዳታ እና ሁሉም የእኔ ወንደሞች እና እህቶች  እና በአንድነት ሆነን በተባበረው ኃይላችን አብረን እንጓዝ፡፡

ጠቅላይ ሚነስትር አብይን ከሙሉ ልብ በመደገፍ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እንዲህ እላለሁ፣

እናም በአንድነት በመሆን በተባበረው ኃይላችን ወደፊት እንጓዝ፡፡ እጅ ለእጅ እንያዝ እና ማንዴላ ለእኛ መልካም ነገር እና ይቅርባይነት በማለት በሰየሙልን ሁለት መንገዶች እንጓዝ፡፡ ወደፊት እንጓዝ እና ከመልካም ነገር እና ይቅርባይነት መንገዶች መገናኛ ላይ አዲሲቷ ኢትዮጵያ እየተባለች ምትጠራውን ከተማ ከታራራው ጭፍ ላይ እንገንባ፡፡“  

ኑ እናም ኢትዮጵያውያን በተባበረው ኃይላችን በአንድነት እንሁን እና ወደፊት እንጓዝ፡፡ 

ኢትዮጵያዊነት ዛሬ!

ኢትዮጵያዊነት ነገ!

ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!      

ሰኔ 12 ቀን 2010 ዓ.ም