ማስታዋሻ ቁጥር 8፡ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፡ እባክዎትን፣ እባክዎትን በዩናይትድ ስቴትስ የእኛ እንግዳ ይሁኑ!
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
(የግልጽ ደብዳቤ ቅጅ)
ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ
C/o የኢትዮጵያ ኤምባሲ
3506 International Dr., NW
ዋሺንግተን ዲሲ. 20008
ውድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፡
ሠላም ለእርስዎ ይሁን!
ቀደም ሲል ተይዞ በነበረው ፕሮግራም መሰረት በሀምሌ መጀመሪያ አካባቢ ዩናይትድ ስቴትስን እንደማይጎበኙ ተገንዝቢያለሁ፡፡
የሚቻል ከሆነ በሀምሌ ውስጥ ተይዞ በነበረው የጉብኝት ፕሮግራም መምጣት በዩናይትድ ስቴትስ ካሉ በርካታ ደጋፊዎችዎ እና መልካም አሳቢዎችዎ ጋር በቀጥታ እንዲገናኙ እርስዎን በማክበር ለመጠየቅ እና ለመማጸን ነው ይህንን ደብዳቤ እየጻፍኩ ያለሁት፡፡
ጋንዲ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ “በስብዕና ላይ እምነት ማጣት የለብህም፡፡ ስብዕና ውቅያኖስ ነው፤ ጥቂት የውቅያኖሱ ነጠብጣቦች ቆሻሻ ከሆኑ ውቅያኖሱ ውስጥ ያለው ሁሉም ዉሀ ቆሻሻ ነው ማለት አይደለም፡፡“
በአሜሪካ ዲያስፖራ ላይ ያለዎትን እምነት ማጣት የለብዎትም ምክንያቱም እኛ እራሳችንም ውቅያኖስ ነንና፡፡ በእርግጥ የአሜሪካ ምድር ከሁሉም አቅጣጫዎች የመጡ ስደተኞች መኖሪያ ውቅያኖስ ናት:: ለዘርፈ ብዙ ባህሎቻችን ብቻ አይደለም ትልቅ ዋጋ የምንሰጠው፤ ሆኖም ግን ሀሳቦቻችንን ያለምንም ተጠያቂነት የምንገልጽበትን መብታችንን ጭምር እንጅ፡፡ ይኸ ሁኔታ በዩናይትድ ስቴትስ “ከበርካታዎቹ አንዱ” የሚለውን እና ምንም ዓይነት የሕግ ማዕቀብ ሳይጣል የሚተገበረውን የብዝሐነት ምክንያታዊነትን ዓላማ ለማመን ይመስላል፡፡ ይህም ማለት “ከበርካታዎቹ ብሄር ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች አንድ ኢትዮጵያ“ ከሚለው ኢትዮጵያዊነት መርህ ጋር አንድ እና አንድ ዓይነት ነው፡፡
እ.ኤ.አ በሚያዝያ 2018 ዓ.ም የቢሮ ስራዎን በይፋ ከጀመሩ ጀምሮ በተግባር እንዳሳዩት እኛን አንድ አድርጎ ስለያዘን ስለጋራ ስብዕናችን እና ስለኢትዮጵያዊነት መስበክዎን መቀጠል አለብዎት፡፡ የማንዴላን ትሩፋት ለዘለቄታው በመያዝ በኢትዮጵያ የብሄራዊ ዕርቅ እና ጠቅላይነት መንገድን መርጠዋል፡፡
የሰው ልጆችን ልብ እና አእምሮ ተቆጣጥረው በያዙት በፍርሀት እና በመጥፎ ሀሳቦች በተከፋፈለች ዓለም ውስጥ እንኖራለን፡፡ እርስዎ የቢሮ ስራዎን ከያዙ ጀምሮ የፍቅር፣ የመግባባት፣ የጓዳዊነት፣ የእውነት እና የእርቅ መልዕክቶችን ከፍ አድርገው በመያዝ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ልብ እና አእምሮ ለማሸነፍ ድፍረት፣ አይበገሬነት እና ጥንካሬ የተቀላቀለባቸውን እርምጃዎች ወስደዋል፡፡
እውነት ለመናገር በስልጣን ላይ ላሉት እውነትን መናገር እና እውነትን መስበክ ሁልጊዜ እውነትን ለመቀበል በማይፈልጉት ላይ ዛቻ እንደማድረግ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ጎቴ እንዲህ ብለው ነበር፣ “በዚህ ዓለም ላይ ከድንቁርና የበለጠ የሚያስፈራ ነገር የለም፡፡“ ከእውነት ኃይል የበለጠ መልካም ነገር እንደሌለ አምናለሁ፡፡
እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ትግል ስገባ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረግሁት ንግግር በኢትዮጵያ ዘለቄታዊ ለውጥ እንዴት እንደሚመጣ እንዲህ በማለት ተንብዬ ነበር፡፡ “ለውጥ የሚመጣው በጦር ሜዳ ውስጥ በደም በመነከር እና በሬሳ ክምር እንዳልሆነ ያረጋገጥን መሆኑን አምናለሁ፡፡ ሆኖም ግን ለውጥ የሚመጣው በልቦቻቸው እና በአእምሯቸው መልካም ሀሳብ ባላቸው ወንዶች እና ሴቶች ነው፡፡”
እርስዎም ያለማንም አጋዥ እና እርዳታ ብቻዎን በሀገሪቱ ውስጥ የሚኖሩትን እና በዲያስፖራው ያሉትን መልካም ሀሳቦች ያሏቸውን ሰዎች ልቦች እና አእምሮዎች በማሸነፍ ኢትዮጵያን ከደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት እና የጎሳ ጥላቻ አደጋ ጎትተው አውጥተዋታል፡፡ እኔ ለእርስዎ የተለየ ምስጋና እና ውዳሴ ለማቅረብ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን እኔ እያደርገሁ ያለሁት እውነታውን ብቻ እየተናገርሁ ነው!
በመጀመሪያ ጊዜ አዘጋጅቸው በነበረው መግለጫዬ እንዲህ የሚል ጥያቄም ጠይቄ ነበር፣ “ለሁላችንም አስደሳች እና ትልቅ ጥያቄ፡ እኛ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን በአሜሪካ ውስጥ እየኖርን፣ እየሰራን እና እየታገልን በሀገራችን ውስጥ ለውጥ ለማምጣት እንችላለን? አዎ እንችላለን በማለት እከራከራለሁ፤ በእርግጥ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ለውጥ ለማምጣት እንችላለን“ ነበር ያልኩት፡፡
ባለፉት በርካታ ሳምንታት በተለያዩ በርካታ አጋጣሚዎች ከአስራ ሁለት ዓመታት በፊት አንስቸው የነበረውን ጥያቄ በአዎንታዊ መልኩ እርስዎ መልሰውታል፡፡
እርስዎ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው በመመለስ እና ሀገራቸውን በማገዝ ወይም ደግሞ ከየትም ቦታ ሆነው በያሉበት ሀገራቸውን እንዱረዱ በማለት በማያጠራጥር መልኩ አውጀዋል፡፡
ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው በመመለስ በፖለቲካ ሂደቱ በሰላም ለመፎካከር ነጻ ናቸው ብለዋል፡፡
በዲያስፖራው ማህበረሰብ ውስጥ የሚገኙት የመገናኛ ብዙሀን ወደ ሀገራቸው በመመለስ ጽ/ቤታቸውን ከፍተው በነጻ መሳተፍ እንዲችሉ ጋብዘዋል፡፡
በዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን እና በኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖሩት ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው መካከል ዕርቀ ሰላም እንዲወርድ ከልብዎ ተማጽነዋል፡፡
ከምንም ጥርጣሬ በላይ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን መካተት እንዳለባቸው ጠንካራ ተነሳሽነትዎን አስመስክረዋል፡፡ በዚህም መሰረት በሂደቱ ለእኛም ታላቅ ክብር ሰጥተውናል፡፡
እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፣ “ምንም ዓይነት ራዕይ ከሌለ ሕዝቦች ይጠፋሉ፡፡“ በቁጥር 4 ማስታዋሻዬ እንዲህ በማለት ጽፊያለሁ፣ “እኛ በዲያስፖራው የምንገኝ ማህበረሰቦች ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጎን ነን፡፡ ማንኛውንም ነገር ባለበት ሁኔታ ሊነግሩን ይገባል፡፡ የእርሳቸውን ተስፋዎች እና ስጋቶች ሊነግሩን ይገባል፡፡ እርሳቸው ሊያደርጓቸው የሚችሉትን እና ማድረግ የማይችሏቸውን ነገሮች ሊነግሩን ይገባል፡፡ እርሳቸው ስኬታማ እንዲሆኑ እርሳቸውን እንዴት ማገዝ እንደምንችል እና ቢወቀድቁ ምን ሊከሰት እንደሚችል ሊነግሩን ይገባል“ ብዬ ነበር፡፡
ላሉበዎት ተግዳሮቶች ምላሽ በመስጠት ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ላለፉት 27 ዓመታት ጥላሸት የተቀባውን የኢትዮጵያን ገጽታ ለመመለስ ተልዕኮ አለን፡፡ እርስዎም ተመሳሳዩን ነገር ማድረግ አለብዎት ምክንያቱም “በአሁኑ ጊዜ እርስዎ እራስዎም የኢትዮጵያ ገጽታ ነዎት፡፡ ብሩህ ተስፋዎን ለመተንበይ እና ኢትዮጵያ ተስፋ ያላት እና ስኬታማ ሆና በዓለም ላይ መልካም ገጽታ እንዲኖራት የእራስዎን ጥረቶች አጠናክረው መቀጠል አለብዎት፡፡”
አሁን በሀምሌ የመጀመሪያው ሳምንት ወደ እኛ በመምጣት አክብሮትዎን በአካል ማሳየት አለብዎት፡፡ ስለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ያለዎትን ራዕይ ይንገሩን:: እናም በሂደት አደጋውን ቶሎ ቀልብሶ አዲስ ስዕል ይዛ እንድትነሳ ማድረግ ነው፡፡ አጋጣሚዎች ባይመቹ እና ወደ አሜሪካ ባይመጡም እንኳ በርካታዎቹ የእርስዎ ደጋፊዎች ለእርስዎ ያላቸውን አክብሮት ለአፍታም ቢሆን የማያቆሙ መሆናቸውን እንዲገነዘቡ ነው፡፡
የአሜሪካ የልብወለድ ጸሀፊ ኬን ኬሰይ በእኔ ወጣትነት ዘመን እንዲህ ብሎ ነበር፣ “ሕዝብን ወደ አንድ ቦታ እንዲሄድ በማመላከት እና በመንገር ልትመራ አትችልም፡፡ እዚያ ቦታ በመሄድ እና ጉዳዩን በመያዝ ምራ፡፡“
ባለፉት ሁለት ወራት ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ታች ሲሉ የሕዝቡን ድምጽ ለመስማት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ለዚህ ጥንካሬዎ እጅግ በጣም አደንቃለሁ ምክንያቱም የሕዝቡ ድምጽ የአምላክ ድምጽ ማለት ነው፡፡ በእነዚህ ጉብኝትዎ መልካም ሀሳቦችዎን አቅርበዋል ፡፡ እንዲሁም ሀገሪቱን በማረጋጋት እና ለወፊቷ ኢትዮጵያ ተስፋን በማጫር የእርስዎ ልዩ የአመራር ክህሎት ይመሰረታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እስረኞችን ለማስፈታት እና ለአህጉራዊ ሰላም፣ መረጋጋት እና ትብብር እንዲጠናከር ወደ ጎረቤት ሀገሮች ተጉዘዋል፡፡ በጥረቶችዎ ሁሉ እጅግ በጣም ስኬታማ ሆነዋል፡፡
ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ወደ አንድ በማምጣት ሀገራቸውን እና ሕዝቦቻቸውን ለመርዳት ዓላማ በማድረግ ወደ አሜሪካ በመምጣት ኢትዮጵያውያንን እና ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያንን እንዲጎበኙ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡
ወደ አሜሪካ የመምጣትዎ ዋና ዓላማ የብሄራዊ ዕርቀ ሰላም እና ስለሀገር አንድነት እኛን በማንቀሳቀስ በሀገር ቤት ከሚገኙት ከወንድሞቻችን እና ከእህቶቻችን ጋር ግንባር በመፍጠር ዶ/ር ማርቲን ሉተር በሄዱበት መንገድ የተወደደውን የኢትዮጵያን ማህበረሰብ ለመገንባት እንዲቻል መልዕክት ለማስተላለፍ ነው፡፡ ወደዚህ በመምጣት ስለኢትዮጵያ ያሉዎትን ተስፋዎች፣ ህልሞች እና ርዕዮች እንዲያካፍሉን ይፈለጋሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ስለሀገራችን ያሉንን የእኛን ጭንቀቶች፣ ስጋቶች እና ተስፋዎች እንደሚያዳምጡ አምናለሁ፡፡
በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የሚገኙት በርካታዎቹ የእርስዎ ደጋፊዎች እርስዎን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጥልዎታለሁ፡፡ እርስዎን በመካከላችን አድርገን ስለብሄራዊ እርቅ፣ ብሄራዊ አንድነት እና ውዱን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ እንዴት መገንባት እንደምንችል ሲናገሩ መስማት እንፈልጋለን፡፡ ስለዘመናት የተሳሳተ አገዛዝ እና መጥፎ አስተዳደር ስለሀገራዊ ምጽአት እርስዎ እያቀረቡት ላለው ተማጽዕኖ ምላሽ ለመስጠት እና ለመዘጋጀት የምናባክነው ጊዜ አይኖርም፡፡
የእርስዎ የአመራር አርዓያነት ምልክት የሆኑት ማንዴላ በአንድ ወቅት አንዲህ ብለው ነበር፣ “ከጠላትህ ጋር ሰላም ለማውረድ ከፈለግህ ከጠላትህ ጋር አብረህ መስራት አለብህ፡፡ ከዚያ በኋላ ጠላትህ ጓደኛህ ይሆናል፡፡“
እርስዎ በፖለቲካ መስተጋብር ውስጥ እያገለገለ ያለውን “ጠላት” የሚለውን ቃል እንደማይወዱት አውቃለሁ:: ይልቁንም “ተፎካካሪ” ማለትን ይመርጣሉ፡፡
ለሁለት ወራት ገደማ ያህል በቢሮ ስራዎ በዘመናዊ የአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማያውቅ የአመራር ክህሎትን አሳይተዋል፡፡ ይህንን የምለው እውነታውን ተመርኩዠ እንጅ እንዲሁ በስሜት ተገፋፍቸ አይደለም፡፡
የእርስዎን ተፎካካሪዎች ያደናገረ እና እንቆቅልሽ ያደረገ የአመራር ባህሪያት እና ልዩ ተሰጥኦ አሳይተዋል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ደጋፊዎችዎን አበርትተዋል፣ ድንቅ አሰኝተዋል፣ እናም በሙሉ ልብ አንቀሳቅሰዋል፡፡ የጨለማውን ጎን ኃይሎች ሽባ አድርገዋል፣ እናም መቅናቸውን አጥተው እንደ ጅብራ ተገትረው እንዲቀሩ አድርገዋል፡፡
ጄኔራል ዶግላስ ማርተር እንዲህ በማለት እንደተናገሩት የአመራር ብቃትዎን አስመስክረዋል፣ “እውነተኛ መሪ ብቻውን የመቆም፣ ጠንካራ ውሳኔዎችን የመስጠት እና የሌሎችን ሰዎች ፍላጎቶች የማዳመጥ በእራስ የመተማመን ችሎታ አለው፡፡ መሪ ለመሆን ብሎ እቅድ አያዘጋጅም፣ ሆኖም ግን በሚተገብራቸው ፍትሀዊ ስራዎቹ እና ፍላጎቱን ለማሳካት በሚያሳየው ታማዕኒነት እውነተኛ መሪነቱን በስም ሳይሆን በተግባር ያስመሰክራል“ ብለዋል፡፡
በእኔ እውቀት (እውነታውን ለማወቅ በማደርገው የምርምር ደረጃ) እርስዎ የአገር መሪ ለመሆን ብለው የተዘጋጁበት ነገር ፍጹም የለም፡፡ ሆኖም ግን በፍትሀዊ ስራዎ እና በታማኝነትዎ የብሄራዊ እርቅ እና የመልካም አስተዳደር ስርዓት በኢትዮጵያ ለማምጣት ካለዎት ዓላማ አንጻር እውነተኛ መሪ ለመሆን በቅተዋል፡፡
እንደ ባቢሎሎናውያን አባባል ለድፍን 27 ዓመታት በአረመኔ ጨቋኝ ገዝዎች እጅ ከወርች ተጠፍሮ የቆየውን ሕዝብዎን ከባርነት ነጻ ለማውጣ ከፈጣሪ ተልከው የመጡ መልዓክ እንደሆኑ ሲነገር ሁልጊዜ እሰማለሁ፡፡
ከጨለማው ጎን ኃይሎች ፊት በሚቆሙበት ጊዜ አፍጥጠው ሲመለከቷቸው፣ ከዓላማዎም ፍንክች እንደማይሉ ሲያሳውቋቸው፣ ሊመለሱ እና ሊቀለበሱ እንደማይችሉ ሲያስገነዝቧቸው እና የእራስዎን መሰረት ሲይዙ ታላቅ ድፍረት እና ኩራት እንደሚሰማዎ አምናለሁ! ከፍተኛ ብርሀን እንደተለቀቀበት፣ በጊዜ እና በቦታ ተወስኖ እንደቀዘቀዘ እና ፈጣን የጭነት ባቡር እየቀረበው እንዳለ የባህር አጋዘን ዕድለቢስ ሆነው ይታያሉ፡፡
ጥላቻ፣ በቀል፣ ቅጣት እና ማጥቃት እየተባሉ በሚጠሩ የኋላ የመኪና መስታወት እየተመለከቱ እየሾፈሩ መጓዝ ኢትዮጵያን በፍጹም ወደፊት የማያስኬዳት መሆኑን ሲያውጁ ታላቅ በእራስ የመተማመን ችሎታ ያለዎ መሆንዎን አሳይተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ በየእስር ቤቱ ሲማቅቁ የቆዩትን የፖለቲካ እስረኞች ሲፈቱ እና ከዚህም በማለፍ በሱዳን እና በሳውዲ አረቢያ ታስረው የሚገኙት በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወንድሞች እና እህቶች ከእስር ቤት እንዲፈቱ ስምምነት ሲያደርጉ ታላቅ በእራስ የመተማመን ችሎታ ያለዎ መሆንዎን አሳይተዋል፡፡
በሳውዲ አረቢያ ጉብኝት እያደረጉ ባሉበት ጊዜ አግባብነት ያለው ሕክምና ሳይሰጥ ቀርቶ ጉዳት ደርሶበት በነበረ አንድ የ16 ዓመት ኢትዮጵያዊ ልጅ በማዘን የሳውዲ አረቢያን መንግስት በማሳመን የ22 ሚሊዮን ብር ካሳ ጉዳት ለደረሰበት ልጅ እንዲከፍል ማድረግዎ ለወገንዎ ልዩ የሆነ ፍቅር ያለዎ መሆንዎን አሳይተዋል፡፡ እ.ኤ.አ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ማንም የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣን የሆነ ሰው በኮማ ውስጥ (እራሱን በማያውቅበት ሁኔታ ላይ ያለ) ወጣቱን ልጅ ጎብኝቶት አያውቅም!
የእርስዎ ቀደምት አገዛዝ ከሕግ አግባብ ውጭ ስልጣናቸውን በመጠቀም ዜጎችን ሲያሰቃይ የቆዬ እና እርስዎ የወረሱት መንግስት በሌቦች፣ በክፉዎች እና በሸፍጠኞች የተሞላ እና የሀገሪቱን የገንዘብ ግምጃ ቤት ወደራሳቸው የግል አካውንት ቀይረውት የቆዬ መሆኑን በመገንዘብ በይፋ ይቅርታ መጠየቅዎ የእርስዎን ታላቅ ታማዕኒነት ያሳያል፡፡ የማርቲን ሉተርኪንግን አባባል በመዋስ ከወሮበላ የዘራፊነት ተራራ ጫፍ ላይ የዴሞክራሲ ድንጋይ መወርወር ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ በሚገልጹበት ጊዜ ቃላት አልነበረዎትም፡፡
በአሁኑ ጊዜ ወደ ዩኤስ አሜሪካ በመምጣት እኛን ለመጎብኘት በማቀድዎ የተቀደሰ ዓላማን አሳይተዋል፡፡
እረኛ ለመንጋዎቹ እንደሚጨነቅ ሁሉ የእረኛን ተግባራት በማሰብ እና በመገንዘብ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ምክንያቱም መንጋዎቹን ለመጠበቅ ፈቃደኛ ነዎት፣ እናም ላለመሆን አይደለም ሆኖም ግን መንጋዎቹን ለማገልገል ጉጉ ስለሆኑ ነው፡፡
አሁን ሁሉንም ነገር እንደወረደ መናገር አለብኝ፡፡
በሀምሌ ውስጥ እርስዎ እኛን ለመጎብኘት ፈቃደኛ መሆንዎ እጅግ በጣም ጠቃሚ ነገር ነበር፡፡ ሆኖም ግን የእርስዎ ዕቅድ ጨለማ ይሁን እንዲሁም እንደሌሊት ጨለማ የማያሳልፍ ይሁን፣ እናም በሚሄዱ ጊዜ ያንን ሁሉ ጨለማ በመግፈፍ እንደ መብረቅ ይውረዱ፡፡
እኛን ለመጎብኘት በሚያቅዱ ጊዜ እንደ መብረቅ ደርሰው ከተፍ ይበሉ፡፡ በምንም ዓይነት ሁኔታ የማይገመት እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ትጥቅ የሚያስፈታ ፈጠራ የታከለበት እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ልዩ የሆነ ጥበባዊ የታከለበት ስልት ነበር፡፡
ማናችንም ብንሆን እንደዚህ ያለ ድፍረት የተቀላቀለበት፣ ክስተቱን የመያዝ እና በእንደዚህ ያለ ቀላል ክብር የተሞላበት ድርጊት የዲያስፖራውን የፖለቲካ ምህዳር ስልታዊ በሆነ መልክ ለመቆጣጠር እርምጃ ይወስዳሉ ብለን አልጠረጠርንም ነበር፡፡
የእርስዎ የጉብኝት ቃል መግባት ተስፋ እዚህ ለመምጣት እና እራስዎን ለጓደኞችዎ እና ለጠላቶችዎ በግልጽ መድረክ ላይ በመግለጽ ከሞራለቢስ ዲያስፖራ ወንጭፎች እና ቀስቶች እንዲሁም ትችት እና የዘለፋ ቋንቋ ድፍረት የሚያንሰዎ እንደሆኑ አድርገው የሚያስቡትን ጥቂት ሰዎች እንደሚያስደነግጧቸው ላረጋግጥልዎች እችላለሁ፡፡
የእርስዎ እዚህ መገኘት ጥቂቶቻችንን ግራ ያጋባል፡፡ ምንድን ለማድረግ እንደሆነ አናውቅም፡፡ የእርስዎን ቀደምት የመንግስት ባለስልጣኖች በአሜሪካ እና በሌሎች ሀገሮች ከየስብሰባ አዳራሾች ማባረር ነበር ልምድ አድርገን ይዘን የቆየነው፡፡ አሁን የእራሳችንን ጠረጴዛ በእራሳችን ላይ ቀየሩ፡፡ አሁን በእኛ በእራሳችን ግዛት በመምጣት በሰለጠነ ንግግር ለማባረር ይፈልጋሉ፡፡ ይህም ታላቅ በእራስ የመተማመን ችሎታ ነው!
ብዙዎቻችን አደጋ ይደርስብናል ብለን አናስብም ነበር፡፡ እኔ እራሴ እንደዚያ ነበርኩ፡፡
በቀላሉ ጥያቄውን በመቀበል ከሚመቸን ዞናችን በመምታት ያስወጡን፡፡ ገንዘባችንን አፋችን ባለበት ቦታ ላይ እንድናስቀምጥ አስገደዱን፡፡ በአደገኛ ሁኔታ ላይ አስቀመጡን፡ በመድረክዎ ላይ ያስቀምጡኝ እናም ሰላሜ ወይም ደግሞ ዝም በል፣ ስለማላደርገው ነገር ቅሬታችሁን አታቅርቡልኝ!
እኛ ወደ ሀገር ቤት ስንመለስ እጆቻችንን ዘርግተን እንቀበላችኋለን ባሉ ጊዜ ይኸ ጥሩ ሁኔታ ነው በማለት አስቤ ነበር፡፡ “እርስዎን በምናይበት ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ እናይዎታለን” የሚል ስሜት ተሰምቶኛል፡፡ ምንም የሚያስቸኩል ነገር የለም፡፡
ሆኖም ግን እርስዎን መጥተን እስክናይ ድረስ አይጠብቁንም፡፡ ስለሆነም በሀምሌ ወደ ራሳችን በር በመምጣት ለማየት ወስነዋል፡፡
ምናልባት በእርስዎ መገኘት ያልተገነዘቡት እውነታ ቢኖር ጥቂቶቻችንን በአስቸጋሪ እንቆቅልሽ ውስጥ የሚያስቀምጡን መሆኑን ነው፡፡ እርሳቸው ንግግር ብቻ እንጅ ተግባር አያውቁም ለምንል ሰዎች ህይወትን አስቸጋሪ ያደርጉብናል፡፡ ጥቂቶቻችን ስለእርቀ ሰላም፣ ሰላም፣ ይቅርባይነት እና ስለዴሞክራሲ ማውራት እንጅ በተግባር የለም እንላለን፡፡ አሁን እግሮችዎ ባሉበት ላይ እንዲጋበዙ ሆነው ብሄራዊ እርቅን፣ ሰላምን፣ ይቅርባይነትን እና ዴሞክራሲን እንዴት እንደሚያመጡ ያሳዩናል፡፡
የፖለቲካ ጠላቶቻችንን ግማሽ መንገድ በመጓዝ እንቀበላቸዋለን በማለት መናገር እንወዳለን፡፡ እርስዎ ደግሞ እኛን በግማሽ መንገድ ለመቀበል እንደማይፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ይልቁንም በሁሉም መንገድ አሜሪካ ያገኙናል፡፡
በሁሉም መንገድ እንዲያገኙን የሚቀበሉ ከሆነ ከፍተኛውን የሞራል ስብዕና በክብር ይላበሳሉ፡፡ የእራስዎን የክርክር ጭብጥ ድፍረት ያሳያሉ፣ እናም የእኛን አስመሳይ ፈሪዎች እንድናይ ያስገድዳሉ፡፡ በቀላሉ ከእኛ ጋር ለመነጋገር በመጠየቅ ወደ ዳር ያስወጡናል፡፡ እስከ አሁን ድረስ ማንም የኢትዮጵያ መሪ ያላደረገውን እርስዎ አድርገዋል፡፡ ከተልዕኮ ወይም ከቢሮ ጥሪ በዘለለ መልኩ ከእኛጋር ደርሰዋል፡፡
ጥቂቶቻችን ለማፈር ምክንያት እንዳለን ሁሉ እርስዎም ሊኮሩ የሚችሉባቸው በርካታ ነገሮች አሉ፡፡
ማስታዋሻ ቁጥር 4ን ለማስታወስ እንደሚችሉት ከዲያስፖራ ኢትዮጵያውን ጋር የሚያደርጉትን ግንኙነት በማስተባበር በኩል የኤሌክትሮኒክ ስራውን ማናቸውንም ነገር ሁሉ እኔ ለማስተባበር ዝግጁ ነኝ፡፡ በእንደዚህ ያለ ሁኔታ የማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች የበለጠ ተስማሚ እና ጥሩ የመገናኛ መድረኮች ናቸው፡፡
በዚህ ሀሳብ እርስዎ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ የማስተባበሪያ አስተዳደር ጽ/ቤቱን ለመርሳት ይወስኑ እናም ከበራችን ድረስ በመምጣት ያሳዩን፡፡ በዩኤስ አሜሪካ እንደሚገኙ በመወሰን እና ከእኛ ጋር በቀጥታ በመገናኘት የኢትዮጵያ አቦ ሸማኔ ለኢትዮጵያው ጉማሬ በማንኛውም ሳምንት በመገኘት ተፎካካሪውን በመሞገት ማሸነፍ እንደሚቻል ያረጋግጡልኛል፡፡ ይህንን ነገር በጣም እወደዋለሁ!
የእርስዎ ለጉብኝት እዚህ መገኘት ጥቂቶቻችንን ያስፈራናል ምክንያቱም እርስዎን እንፈራዎታለን፡፡ የበለጠ በተለይም ደግሞ የማይበገሩት የእርስዎ ሀሳቦች ኃይል ያስፈሯቸዋል፡፡ ጥቂቶቻችን እርስዎን እንፈራለን ምክንያቱም በሕዝብ የክርክር መድረክ ላይ ሻማ ይዘን ለመቆም አንችልምና፡፡ በእርግጠኝነት ስለእርስዎ ኢትዮጵያዊነት፣ ስለኢትዮጵያ አንድነት፣ ስለሕግ የበላይነት፣ ስለመንግስት ተጠያቂነት እና ስለግልጽነት የክርክር ጭብጥ በመከራከር ልናሸነፍ አንችልም፡፡ እውነት ለመናገር ወደ አሜሪካ እንዲመጡ እና እንዲያሳፍሩን አንፈልግም፡፡
ስለሆነም ለምን ወደ አሜሪካ መምጣት እንደማይችሉ አስቂኝ የሆነ የማታለያ ዘዴ ለመፈብረክ እና የሸፍጥ ይቅርታዎችን ለማቅረብ አስገድደውናል ለማለት እወዳለሁ፡፡ (መምጣት አይችሉም ምክንያቱም እዚያ ብዙ የሚሰሩ ነገሮች አሉ፡፡ ወደ አሜሪካ የሚመጡት ለታዕይታ ነው፡፡ ስለደህንነትዎ ዋስትና የለንም (የደህንነት አገልግሎቱ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንዳልሆነ ሁሉ)፣ ወዘተ፣ ወዘተ …
ወደ ዋናው ነጥቤ ልመለስ፡፡
ወደዚህ የሚመጡ ከሆነ የሕዝቡን ቀልብ ይስባሉ እናም አድናቆትን ያገኛሉ በሚል እንፈራለን፡፡ ታማኝ እና በጣም ጠቃሚ ሰው ይሆናሉ! ስለዚህ ጉዳይ ምንም ዓይነት ጥያቄ የለም! በርካታ ታዳሚዎችን ያስቃሉ የድጋፍ ጭብጨባም ያደርጋሉ፡፡ እናም ሰዎች ይንጫጫሉ ያላቸውን አድናቆትም ይገልጻሉ፡፡ እርስዎም መድረኩን ይቆጣጠራሉ፡፡ በወጣት ኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደ ሮክ ስታር በአሮጌው ትውልድ ደግሞ ከፈጣሪ እንደተላከ መልዓክ ይቆራሉ፡፡
ሰን ትዙ እንዲህ በማለት መክረዋል፣ “ትልቁ ድል ምንም ዓይነት ጦርነት የማይፈልግ ሲሆን ነው“ ብለዋል፡፡ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ቢመጡ ኖሮ በድል አድራጊነት እንዲህ በማለት ሊያውጁ ይችሉ እንደነበር ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለኝም፣ “መጣሁ፣ አየሁ እናም በአሜሪካ ያሉትን ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያንን ልቦች እና አእምሮዎች ማርኪያለሁ፡፡“
ሰን ትዙ ጠላት ባለመምጣቱ ላይ እንድንመካ አይደለም የሚያስተምሩን፡፡ ሆኖም ግን እሱን ለመቀበል ያለን ዝግጁነት እንጅ፡፡ ጥቃት ባለመሰንዘሩ እድል ላይ አይደለም መመካት ያለብን፡፡ ሆኖም ግን እራሳችን ምንም ዓይነት የጠላትነት አቋም ባለመያዛችን ላይ ነው፡፡ እርስዎ መጡም አልመጡም የእርስዎን የጠላትነት የማስወገድን የሞራል ስብዕና አቋም በማጠናከር የኢትዮጵያውያንን ልቦች እና አእምሮዎች ለማሸነፍ እርግጠኛ መሆን እና ልዩ የሆኑ የፖለቲካ እና የሞራል ስብዕና መሪ እንደሆኑ ማረጋገጥ መቻል ነው፡፡
እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ እኛን አሸንፈውናል፡፡ ለእርስዎ እንዴት አድርገን ምላሽ እንደምንሰጥ አናውቅም ምክንያቱም ምንም ነገር እናድርግ ወይም አናድርግ ያሸንፋሉ፡፡ የእርስዎን መገኘት ከተቀበልን ይመጣሉ እናም መልካም የሚሉትን ነገር ያደርጋሉ፡፡ የእርስዎን ዲያስፖራ ወንድሞች እና እህቶች ልቦች እና አእምሮዎች ያሸንፉ፡፡ የእርስዎን መገኘት የማንቀበል ከሆነ ከፍተኛውን የሞራል መሰረት ይጥላሉ ምክንያቱም የእርስዎን መልካም የጉብኝት እምነት ቀልብሰናልና፡፡
በተፈጥሮ በተሻለ ሁኔታ የምንሰራውን አድርገናል፡ መልካም አጋጣሚን ላለማጣት መልካም አጋጣሚን በፍጹም አትጡ፡፡
ሆኖም ግን የአንዱ ማጣት የሌላው መልካም ዕድል ነው፡፡
በአሜሪካ የሚገኙ የእርስዎ በርካታ ደጋፊዎች በሀምሌ፣ ነሐሴ፣ መስከረም፣ ወይም ደግሞ በመረጡት በሌላ በማንኛውም ጊዜ በመምጣት እንዲጎበኙን ዝግጁ፣ ፈቃደኛ እና ችሎታ ያለ መሆኑን ይወቁ፡፡
ወደ ሀገር ቤት የምንመለስ ከሆነ እጅዎን ዘርግተው እንደሚቀበሉ በተለያዩ በርካታ አጋጣሚዎች ተናግረዋል፡፡ ደህና፣ በዩናይትድ ስቴትሰ አሜሪካ የሚገኙት የእርስዎ በርካታ ደጋፊዎች በአጻፋው እጆቻቸውን ዘርግተው እርስዎን ለመቀበል ፈቃደኛ፣ ችሎታው ያላቸው እና ዝግጁ ናቸው፡፡ በአሜሪካ ውስጥ የዘንባባ ዝንጣፊን ለማበርከት በርካታ ሺ ኪሎ ሜትሮችን የሚጓዙ ከሆነ ከምንም በላይ ተዘጋጅተን እንጠብቅዎታለን፡፡
አሁን በህይወት የሌለው የእርስዎ ቀደምት ንግግር ለማድረግ ወደ ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የመጣበትን እ.ኤ.አ መስከረም 2010 ዓ.ምን አስታውሳለሁ፡፡ በዚያ ጉባኤ ላይ በርካታ ንቀት፣ ዘለፋ እና ተቃውሞ ተደርጎበታል፡፡ እኛን ጽንፈኛ እና የዲያስፖራ ጽንፈኛ አሸባሪዎች እና የመሳሰሉት በማለት ይጠራን ነበር፡፡ ደጋፊ አባላትን ማብዛት በሚል ስም በዲያስፖራው ማህበረሰብ የሚገኙትን ተቃዋሚዎች ለማጥፋት የማጥቂያ ዕቅድ አዘጋጅቷል፡፡ ለእኛ በምንም ዓይነት መልኩ መልካም ነገርን አያሳይም ነበር፡፡ ከእኛ ጋር ለመነጋገር በፍጹም አይፈልግም ነበር፡፡ ሁልጊዜ እኛን በማዋረድ፣ በመናቅ እና አሳንሶ በማቅረብ በእብሪት ይናገር ነበር፡፡
ሆኖም ግን እርሱ በዩኒቨርስቲው ተገኝቶ በሰላም መናገር እንዲችል ተከራክሬለታለሁ ምክንያቱም እርሱ በሀገር ቤት ለበርካታ ዜጎች የነፈገውን ነጻነት እርሱ እንዲያጣጥም ፈልጌ ስለነበር ነው፡፡
በግለሰብ ደረጃ የእርስዎ ቀደምት አገዛዝ እኔን በስም ለይቶ በማውጣት “የእኔን ኢትዮጵያዊነት” እንደሚጠራጠር ለዓለም ሕዝብ ይፋ አደረገ፡፡ እኔ ግን በዚህ ስሜቴ አልተጎዳም፡፡ ይልቁንም በተጻራሪው በእነርሱ ላይ ታላቅ እንድሆን አደረገኝ፡፡ አዲስ መድረክ እና ሊለካ ከሚችል በላይ ኃይል በመስጠት የእኔን የኢትዮጵያዊነት ዘመቻ የሰብአዊ መብት ትግል በተጠናከረ መልኩ ቀጥየበታለሁ፡፡
እ.ኤ.አ ሀምሌ 2018 ዓ.ም ወደ እኛ ወደ አሜሪካ ለመምጣት ይፈልጋሉ፡፡ እናም የነጻነትን፣ የዴሞክራሲያዊ ለውጥ፣ ብሄራዊ አንድነት እና እርቀ ሰላም መልካም ዜናዎችን ማካፈል ብቻ አይደለም የሚያደርጉት፡፡ ሆኖም ግን ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያ ጉዳዮች ናቸው በግንባር ሊያረጋግጡልን ይገባል፡፡ እንደ ዲያስፖራ ህንዳውያን፣ አይሁዶች እና ሌሎች ሁሉ ሀገራቸውን እንደገነቡ እኛ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንም መገንባት እንደምንችል እውቅና ሰጥተውናል፡፡
በዩናይትድ ስቴትስ የምንኖር ጥቂት ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ልዩ ዝርያዎች በማለት ማሰብ አለብዎት፡፡ እ.ኢ.አ በ2010 ዓ.ም ምንም ዓይነት የጥላቻ መልዕክተኛ እና ክፍፍል አንፈልግም፡፡ እ.ኤ.አ በ2018 ዓ.ም የፍቅር እና የእርቀ ሰላም መልዕክተኛ እንፈልጋለን፡፡
ሆኖም ግን እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ እርስዎ ወደ አሜሪካ እንዲመጡ እና ምን እንደምንል እንዲያዳምጡን የምንፈልግ በርካታ ዜጎች አለን፡፡ ወደ እኛ በመምጣት ያለዎትን መልካም ዜና እንዲያካፍሉን እንፈልጋለን፡፡ ወደ እኛ በመምጣት የነጻነት ጎዳና ምን ያህል ረዥም እንደሆነ ሊነግሩን እንፈልጋለን፡፡ ምን እንዳሰብን፣ እርስዎን በምን ዓይነት ሁኔታ እንደምናግዝዎ፣ እንድንነግርዎ እና ኢትዮጵያ በትክክለኛው ጎዳና ላይ ሆና እንድትቀጥል መስራት ያለብዎትን እንድንነግርዎ እንፈልጋለን፡፡
እንደግለሰብ ወደ አሜሪካ እንዲመጡ እንፈልጋለን፡፡ እናም እ.ኤ.አ በጥር 2018 ዓ.ም አቅርቢያቸው የነበሩትን እና እንዲህ ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጡ እጠይቃለሁ፡
የቆሰለ ፍትህ፣ በገጠር በቆሻሻ መንገዶች ተዘርግተው የሚገኙት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ከፍ የሚሉት እና የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልቦች እና አእምሮዎች የሚፈወሱት እስከ መቼ ነው?
እስከ መቼ ነው እውነታው በኢትዮጵያ ውስጥ ፍርጥርጥ ብሎ የሚወጣው?
እስከ መቼ ነው የጭቆና ጨለማ ደመና ከኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የሚገፈፈው እና የነጻነት ጸሐይ 13 ወራት የጸሐይ ብርሀን የሚመለሰው?
እስከ መቼ ነው ፍትህ በኢትዮጵያ ውስጥ ተሰቅላ የምትቆየው እና እውነት ተደብቆ የሚቆየው?
እስከ መቼ ነው ኢትዮጵያ ከጎሳ አፓርታይድ ቀንበር ነጻ ሳትወጣ የምትቆየው?
እርግጠኛ ነኝ እነዚህን ጥያቄዎች እንደሚመልሱ አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ግን ከእርስዎ መስማት እፈልጋለሁ፡፡
እስከ መቼ አብይ?
“ሩቅ አይሆንም! ቀኑ ደርሷል!“
የማንዴላን ቃል ኪዳን እና እንዲህ የሚለውን ወደ አሜሪካ በሚመጡበት ጊዜ ሲናገሩ ለመስማት እፈልጋለሁ፣ “በፍጹም በፍጹም ይሀች ቆንጆ የሆነች ሀገር አንዱ በአንዱ የማትጨቆን እና የዓለም ውራጅ አትሆንም፡፡“
እራሴን የዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ሰብአዊ መብት አስከባሪ አድርጌ እንደመሾሜ መጠን ለኢትዮጵያውያን እና ለኢትዮጵያውን አሜሪካውያን የልብ ትርታ ስሜት አለኝ፡፡ እርስዎ በየዕለቱ ስኬታማ እንዲሆኑ የሚጸልዩልዎት በርካታዎቹ አሉ፡፡ እርስዎን በድረ ገጽ የሚመለከቱ እና ለእያንዳንዱ ቃልዎ እንዲሰራጭ የሚያደርጉ በርካታዎች አሉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እርስዎን የሚጠራጠሩ በርካታዎች አሉ፡፡ ሆኖም ግን በሂደት ቀስ በቀስ አእምሯቸውን በመቀየር የእርስዎ ደጋፊዎች ይሆናሉ፡፡ እርስዎ ከአምላክ የተላኩ አድርገው የሚያምኑ በርካታዎች አሉ፡፡
ከዚያም ከተቃርኖ፣ ከተሸናፊነት፣ ከእምነተቢስነት እና ከጨለምተኝነት ኃይማኖትን የሚፈጥሩ እና ከእርስዎ ፊት የማይቆሙ ጥቂቶች አሉ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በማስታዋሻ ቁጥር 4 ላይ ጽፊያለሁ፡፡
በመጨረሻም ሁሉንም የምርመራ ዘዴ በመጠቀም የእኔን ጥልቅ ኢትዮጵያዊነት በመያዝ በአሜሪካ ከእርስዎ በርካታ ደጋፊዎች ጋር በመገኘት ተማጽእኖዬን አቀርባለሁ፡፡
አሁኑኑ ወደ እኛ በመምጣት እንዲጎበኙን ያስፈለገበትን አስገዳጅ 7 ምክንያቶች ከዚህ በታች አቀርባሁ፡፡
ምክንያት ቁጥር 1፡ እንወድዎታለን፡፡ ልዑሉ ከመፈቀር ይልቅ ቢፈራ ይሻላል በማለት ሚኪያቬሊ ጽፏል፡፡ አሁን በህይወት የሌለው የእርስዎ ቀደምት በዚያ መርህ ያምን ነበር፣ እናም ወድቋል፡፡ አሁን በህይወት የሌለው የእርስዎ ቀደምት ጥላቻን መሳሪያ ያደርግ ነበር፡፡ እርስዎ ደግሞ ፍቅርን እና እርቅን መሳሪያ አድርገዋል፡፡ ሁሉንም ነገር አጥቷል፡፡ ፍቅር ሁሉን ያሸንፋል የሚለውን በየዕለቱ ለዓለም ያረጋግጣሉ፡፡ በየዕለቱ ልቦችን እና አእምሮዎችን ያሸንፋሉ፡፡ ደህና፣ እንግዲህ ወደ አሜሪካ ይምጡ እና ጥቂት ፍቅር እናሳይዎት፡፡
ምክንያት ቁጥር 2፡ እንደ ፖለቲካ መሪነት አርአያነት እና ተሳትፎ እርስዎን እናከብራለን፣ እናደንቃለን፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን ወደ አሜሪካ በመምጣት ከኢትዮጵያውያን እና ከኢትዮጵያውን አሜሪካውያን እንዲሁም ከተቃዋሚው ማህበረሰብ የፖለቲካ ወትዋቾች ጋር ያለምንም ጥላቻ ውይይት ያደረገበት አጋጣሚ እንደነበር አላምንም፡፡ ሁሉም በጀምላ ጥላሸት ሲቀቡ፣ ሲዋረዱ እና ወደ ጎን ሲገፉ ነው የቆዩት፡፡ ከዚህ ታሪካዊ ዳህራ በመነሳት እርስዎ ወደ አሜሪካ በአካል በመምጣት ከእርስዎ ጋር በማይስማሙት እና ወንጭፍ በሚወረውሩት እና ቀስት በሚደግኑት ላይ ድልን በመቀዳጀት በእራስዎ የሚተማመኑ ታላቅ መሆንዎን ማስመስከር ይኖርብዎታል፡፡
እንደሰብአዊ ፍጡር እና እንደ መሪ በግለሰብ ደረጃ እኔ ለእርስዎ ከፍተኛ የሆነ ክብር እና አድናቆት አለኝ፡፡ እንደሚያውቁት ሁሉ ከእርስዎ ቀደምት ከነበረው አገዛዝ ጋር ፍቅር አልነበረኝም፡፡ በእርግጥ እነርሱን ለመግለጽ ቢያንስ በደርዘን የሚቆጠሩ እና የማይመቹ አዲስ የእንግሊዝኛ ቃላትን አጣምሪያለሁ፡፡ አንድ ወይም ሁለት ቃላትን የምሰነዝርበት በርካታ አጋጣሚዎች ቢኖሩም እንኳ እርስዎ ካለዎት የሞራል ስልጣን አመራር አንጻር እርስዎ ስልጣን ከያዙ ጀምሮ ምንም ዓይነት አሉታዊ ማጣቀሻዎችን በአገዛዙ እና በአባላቱ ላይ ላለመሰንዘር ፍጹም በሆነ መንገድ እቆማለሁ፡፡ ጥላሸት በመቀባባት፣ በማውገዝ እና በመተቸት ኢትዮጵያን ወደፊት ልናራምዳት አንችልም የሚለውን ምክር መስጠትዎን ተከትሎ በእነርሱ ላይ ትችት ማቅረቤን አቁሚያለሁ፡፡ ወደ እኛ ይምጡ እና በእርስዎ ላይ ያለንን ክብር እና አድናቆት እናሳይዎ፡፡
ምክንያት ቁጥር 3፡ በእርስዎ እጅግ በጣም እንኮራለን፡፡ በአፍሪካ ወጣት መሪ እንደመሆንዎ እኛን እንድንኮራ አድርገውናል፡፡ በአፍሪካ ታሪክ ቀደምቷ ሀገር ወጣት መሪ አላት የሚለው አስገራሚ ነገር አይደለምን? በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ባሳዩት የማይቀለበስ እና ድፍረት የተሞላበት አቋምዎ በጣም ኮርተንብዎታል፡፡ በሕግ የበላይነት ላይ ምንም ዓይነት ድርድር የለዎትም፡፡ በዴሞክራሲ፣ በሰብአዊ መብት አጠባበቅ፣ በሰላም እና በእርቀ ሰላም ላይም እንደዚሁ፡፡
ከጥቂት ቀናት በፊት “ለጀኔራሎቹ” እውነታውን ተናግረዋል፡፡ እንዲህም ብለዋል፣ “በነጻ ሀገር ያለ የፖሊስ መኮንን በደሀ ሀገራ ካለ ጄኔራል የበለጠ ክብር አለው፡፡“ ይህንን በማድረግዎ እንዲህ የሚለውን የኢትዮጵያን ሕገ መንግስት አንቀጽ 74 ንኡስ አንቀጽ 1 ትክክለኛ ትርጉሙን አሳይተዋል፣ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስቱ መሪ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ነው፡፡“ ለጀኔራሎቹ ሞያዊ ውትድርና ምን ማለት እንደሆነ አስተምረዋል፡፡ የጦር ኃይሉ ከፓርቲ ወገናዊነት እና ከፖለቲካ ተቋማት ጋር ያልወገነ እና ለአዛዡ ክብር በመስጠት ትዕዛዝም ከጦር ኃይሎች አዛዥ መቀበል አለበት፡፡ ሞያዊ ወታደር ግማሽ ነጻነት ያለው ሞያዊ ወታደር ዓይነት ያልሆነ ቡድን እና ለጥቂት ለተመረጡ ከፍተኛ የፓርቲ አባላት ልዩ ታዛዥ መሆን የለበትም፡፡ ወይም ደግሞ በጦር አበጋዞች የእነርሱን ፍላጎቶች ለማስጠበቅ የተቀጠረ የግል ወታደር እስኪመስል ድረስ ቅጥረኛ ቡድን መሆን ፍጹም የለበትም፡፡ ይምጡ እና መላ አሜሪካንን ይጎብኙ እና እንዴት ያለ የሚያኮራ ነገር እንደሆነ እናሳይዎ፡፡
ምክንያት ቁጥር 4፡ የእኛ ወጣት ኢትዮጵያውን እና ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን እርስዎን ማየት፣ መስማት እና እርስዎ ደግሞ በተራዎ እነርሱን እንዲያዳምጡ ይፈልጋሉ፡፡ በአሜሪካ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በርካታ ቁጥር ያላቸው አትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውን አሜሪካውያን ተማሪዎች በቅድመ ምረቃ እና በድህረ ምረቃ ፕሮግራም ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንዳሉ የሚያውቁ መሆንዎን እርግጠኛ ነኝ፡፡ ይህንን አውቃለሁ ምክንያቱም ሁልጊዜ ከእነርሱ ጋር ግንኙነት አለኝ፡፡
በእኔ አመለካከት ከእኛ ከበርካታዎቹ ከአቦ ሸማኔው (የቀድሞው) ትውልድ አባላት የበለጠ ኢትዮጵያን ይወዷታል፡፡ ወደዚህ በመምጣት ከእነርሱ ጋር መነጋገር እና በፈለጉት ጊዜ ወደ ትውልድ ሀገራቸው በመመለስ ወገኖቻቸውን እንዲረዱ ማሳመን ይኖርብዎታል፡፡ ለረዥም ጊዜ እነዚህ በአሜሪካ የሚኖሩት የተሻሉት እና ምርጦቹ ወጣት ኢትዮጵያውያን በሀገሪቱ ባለው የፖለቲካ ሁኔታ ፊታቸውን አዙረዋል፡፡ ነገሮች ባሉበት ሁኔታ ሀገራቸውን በመሄድ ይጎበኛሉ እንጅ በፍጹም ሊኖሩባት አይችሉም፡፡ እናም እርስዎ በአካል በመምጣት ከእነርሱ ጋር በመነጋገር ሁኔታውን መመለስ ይችላሉ፡፡ እንደነርሱ ሁሉ እርስዎም ወጣት ነዎት፡፡ እርስዎን ይሰሙዎታል ምክንያቱም እርስዎ የእነርሱን ቋንቋ ይናገራሉ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ የእነርሱን ቴክኖሎጂ፣ ሳይንስ፣ ፈጠራ እና የስራ ፈጣሪነት ባህል ይገነዘባሉ፡፡ እነዚህን ወጣት ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያ የፈጠራ መፈልፈያ ማሽኖች እና ስራ ፈጣሪዎች እንደሆኑ አድርገው ያስቡ፡፡ ይምጡ እና ከእነርሱ ጋር ይገናኙ እናም ኢትዮጵያ ስኬታማ ስትሆን እነርሱም በግል ስኬታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያሳምኗቸው፡፡
የሂድ ማርጋሬት ሚድ ምክር እንዲህ ይላል፣ “ሀሳብ ያላቸው ጥቂት ቡድኖች እና ስለዓለም ግድ የሚሉ ዜጎች ዓለምን ሊለውጡ እንደሚችሉ በፍጹም አትጠራጠሩ፡፡ በእርግጥ እስከ አሁንም ድረስ እየሆነ ያለው ይኸው ብቻ ነው፡፡“ በወጣት ኢትዮጵያውን አሜሪካውያን ኢትዮጵያን መለወጥ ብቻ ሳይሆን ዓለምን መለወጥ የሚችል የተጠራቀመ የኃይል ምንጭ አለ፡፡ ይምጡ እና ከእነርሱ ጋር ይነጋገሩ እናም ልቦቻቸውን እና አእምሯቸውን ያሸንፉ!
ምክንያት ቁጥር 5፡ የቢሮ ስልጣንዎን ከያዙ ጀምሮ የእርስዎን ሚና እንደገመገምኩት እርስዎ የመርህ ሰው እንደሆኑ እና የመርሆዎችን ትክክለኛ ትርጉም ለመተርጎም እንደሚኖሩ ደምድሚያለሁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንደ ፖለቲካ መሪ መምህር እንደሆኑ ደምድሚያለሁ፡፡ እንዲህ የሚል የድሮ አባባል አለ፣ “አመራር ብዙ መሪዎችን ለማፍራት እንጅ በርካታ ተከታዮችን ለማፍራት አይደለም፡፡“ እርስዎ ይህንን እደረጉ እንዳሉ እመለከታለሁ፡፡ እርስዎ በርካታ መሪዎችን እና ጥቂት ተከታዮችን ለማፍራት ይፈልጋሉ፡፡
በይፋ መግለጫዎችዎ እና በንግግሮችዎ መልካም አስተዳደር ምን ማለት አንደሆነ ለሕዝቦችዎ ሳያስተምሩ ያለፉበት ጊዜ የለም፡፡ የመልካም አስተዳደር መሰረቱ እውነት እና እርቅ ነው፡፡ እንዲህ የሚለውን የማርቲን ሉተር ኪንግን የለውጥ መርህ ድምጽዎን ከፍ በማድረግ ይጮሀሉ፣ “ዓይን ላወጣ ዓይን መገበር እያንዳንዱን ሰው ዓይነ ስውር ያደርጋል፡፡ ጊዜ ሁልጊዜ ትክክለኛ ነገር ለሚሰራበት ትክክለኛ ነው፡፡ ሰላማዊ የማህበረሰብ ለውጥ እርቅ ነው፡፡ የመጨረሻ ዓላማው በቀልተኝነትን ማስወገድ ነው፡፡ የመጨረሻ ዓላማው የተወደደ የኢትዮጵያ ማህበረሰብን ለመፍጠር ነው፡፡ ይህ ዓይነት መንፈስ እና ይህ ዓይነት ፍቅር ነው ተቃዋሚዎችን ወደ ጓደኝነት ለማሸጋገር የሚችለው፡፡“ እንዲህ የሚለውን የጋንዲን የለውጥ መንፈስ ድምጽዎን ከፍ በማድረግ ያቀነቅናሉ፣ “ዓለምን ከመለወጣችን በፊት እራሳችንን መለወጥ አለብን፡፡ በዓለም ላይ ሆኖ ለማየት የምትፈልገውን ለውጥ መሆን አለብህ፡፡ ደካማው በፍጹም ይቅርታ ሊያደርግ አይችልም፡፡ ይቅርታ የማድረግ ባህሪ የጠንካራው ነው፡፡“ ታንዛኒያ ውስጥ ካለህ “ምዋሊሙ” በማለት ይጠሩሀል፡፡
በአሜሪካ የሚገኙ የእርስዎ ደጋፊዎች ያደንቃሉ እናም የእርስዎን ለኢትዮጵዊነት፣ ብሄራዊ እርቅ እና አንድነት፣ ለሕግ የበላይነት መከበር፣ የማይናወጥ የሕዝቦች ሉዓላዊነት እና በሰብአዊ መብት የእራስን ዜጋ ከመንግስት ስህተት መጠበቅ ተነሳሽነትን በእርስዎ አምሳል መተግበር ይፈልጋሉ፡፡ እባክዎትን ይምጡ እና አንድ ወይም ሁለት ትምህርት ይስጡ፡፡
እንግሊዝ መቋጫ በሌለው የናዚ አየር ኃይል ጥቃት በሚደርስባት ጊዜ እና የናዚን የጦር መሳሪያዎች መከላከል በማትችልበት እና የጥቃት ሰለባ በሆነችበት ጊዜ ዓለም እንግሊዝ አበቃላት፣ ተደመሰሰች እና ጠፋች ብሎ ጽፎ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ቸርችል ለትምህርት ቤት ተማሪዎች እንዲህ በማለት የመልሶ ማጥቃት ዘመቻቸውን ተያያዙት፣ “በፍጹም እጅ እንዳትሰጡ፣ በፍጹም፣ በፍጹም፣ ትልቅም ይሁን ትንሽ፣ ግዙፍ ወይም አናሳ፡፡ በፍጹም ለክብራችን እና ለመልካም ነገር ስትሉ እጅ እንዳትሰጡ፡፡ ለኃይል በፍጹም እንዳትንበረከኩ፣ እጅግ ለጠነከረው ጠላታችን በፍጹም እጅ እንዳትሰጡ“ ነበር ያሉት፡፡
ከሁለት ወራት በፊት ወደ የእርስ በእርስ የጎሳ ጦርነት መአት ውስጥ ገባች እናም አበቃላት ብሎ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሂሳብ ተዘግቷል እናም አለቀላት ብለው ነበር፡፡ የእኛ ወጣቶች በፍጹም በፍጹም ሕዝባዊ እምቢተኝነት እና ሰላማዊ ትግሉ ቀጥሎ በድል አድራጊው ትግል አብይ አህመድን ወለደ፡፡
ወደ አሜሪካ ይምጡ እና የተነሳሽነት መርህን ያስተምሩ እላለሁ፡፡ ሀገሮች የሚመሰረቱት በመርሆዎች ነው፡፡ ምን ያህል ይቆያሉ ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ አሜሪካ ሁሉም ወንዶች እና ሴቶች እኩል ሆነው ተፈጥረዋል በሚል መርህ በእውነት ላይ የተመሰረተች ሀገር ናት፡፡ እናም ከፈጣሪያቸው ሊገሰሱ የማይችሉ መብቶችን ተጎናጽፈዋል፡፡ መንግስት የሚቋቋመው እነዚህን መብቶች ለመጠበቅ እና በሕዝቡ ፈቃደኝነት ፍትህን እንዲያስከብር ከተገዥው ሕዝብ ተቆርሶ የሚሰጥ ስልጣን ነው፡፡
ወደ አሜሪካ ይምጡ እና አዲሲቷ ኢትዮጵያ በምን ዓይነት መርህ መተዳደር እንዳለበት ይንገሩን፡፡ በእውነት እና በእርቀ ሰላም ላይ የምትመሰረት ነች…?
ምክንያት ቁጥር 6፡ ወደ አሜሪካ ይምጡ እና “ከጠላትዎችዎ” ጋር ይገናኙ፡፡
እ.ኤ.አ ሀምሌ 2008 ዓ.ም አቅርቤው በነበረው ትችቴ አሁን እንዲጎበኙ ከሚጋበዙበት ጉዳይ ጋር የሚያያዝ እና በአሜሪካ ጋዜጦች በየዕለቱ ይወጣ የነበረ “ፖጎ” እየተባለ የሚጠራ አስቂኝ ቀልድ ትዝ አለኝ፡፡ በፖጎ አስቂኙ ቀልድ እንስሳት ገጸ ባህሪያት መሰረት የአሜሪካንን ማህበረሰብ ብዝሀነት ለማመላከት ማህበረሰቡ በረግረጋማ ቦታ ይኖር እና ከጉዳዮች ጋር ይገዳደር ነበር፡፡ ያ ማህበረሰብ መፈረካከስ ጀመረ ምክንያቱም በማህበረሰቡ ውስጥ የሚኖረው እያንዳንዱ ሰው የገጠመውን አንገብጋቢ ችግር እና ጉዳይ ለመፈጸም እንዲችል ለሚደረገው ጥረት እርስ በእርሱ መግባባት አይችልም ነበር፡፡ ወርቃማ ጊዚያቸውን ጠቃሚ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ አባከኑ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ፖጎ የሚኖሩበት ረግረጋማው ቦታ በፍረስራሽ እና በቆሻሻ ተሞልቶ አየው፡፡ በስሜት ከፍ ያለ ድምጹን በማሰማት እንዲህ አለ፣ “ከጠላታችን ጋር ተገናኝን፡፡ እርሱም እኛው እራሳችን ነን!“ አለ ይበላል፡፡
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ንቅናቄ አራማጆች አባላት እንደመሆናችን መጠን ስለእራሳችን በመስታወት በመመልከት እንዲህ የሚሉትን መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ አልቻልንም፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ እና የሰብአዊ መብት ጥበቃ ውትወታ ለማካሄድ እንደ ዓለም አቀፍ ኃይል በመሆን ለመተባበር ያልቻልነው ለምንድን ነው? በጎሳ መስመሮች መካከል ጠንካራ የሆነ ድልድይ ለመገንባት እና የሰብአዊ መብት ቋንቋዎችን በመጠቀም እርስ በእርሳችን ለመግባባት ያልቻልነው ለምንድን ነው? የመልካም ሀሳብ ባለቤት እና የተመሰከረለት ችሎታ እና ብቃት ያለውን መሪ የማንደግፈው ለምንድን ነው? በቅርጫት ውስጥ እንዳለ ቅማል እና ከቅርጫቱ ውስጥ በመውጣት ለመምራት ጥረት የማናደርገው ለምንድን ነው? እጅ ለእጅ ተያይዘን ህብረት በመፍጠር የሰላ ወፍጮ በመሆን ወገኖቻችንን ከመከራ ለመታደግ የማንችለው ለምንድን ነው?
እርስ በእርስ በመካሰስ፣ ጥላሸት በመቀባባት፣ በመወጋገዝ እና በመተቻቸት አሮጌ መንገድ ላይ በመጓዝ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ከመዳረሻው ቦታ ልናደርሳት ከቶውንም አንችልም፡፡ ወይም ደግሞ በመጠላላት፣ በጠባባዊነት፣ በማታለል እና በሸፍጠኝነት ክንፍ በመብረር የትም አንደርስም፡፡
እርስዎ ስለሚናገሩለት ለእውነት እና ለብሄራዊ እርቅ ብዙ ርቀት የማያስኬድ ሆኖም ግን ቶሎ ለመድረስ የሚያስችል የተለየ መንገድ መያዝ አለብን፡፡ ይህንን እውነታ እንዲህ በሚሉት በሮበርት ፍሮስት የግጥም ስንኞች እንደምድም፡
…ትንፋሼን ከፍ በማድረግ እናገራለሁ፣
የትም የት ይሁን በምድር ላይ ሳለሁ፡፡
በጫካው ውስጥ ካሉ ሁለት መንገዶች፣
ሩቅ ጠመዝማዛ ለጉዞ እማይመች፣
ቅርብ ርቀት ሆኖ ምቹ ለተጓዦች፣
እኔ ግን መረጥኩት አጭሩን ለሰዎች፣
ልዩነት ስላለው ለተገፉ ሕዝቦች፡፡
ወደ አሜሪካ ይምጡ እና “”ከጠላትዎ ጋር ይገናኙ፡፡ ይምጡ እና ከጠላቶችዎ ጋር እጅ ለእጅ በመያያዝ ጓደኝነት በመፍጠር ቅርብ በሆነው መንገድ ወደፊት ይምሩን፡፡ ወደ እውነት እና እርቅ በሚወስደው መንገድ ላይ ይምሩን፡፡ እንደሰብአዊ ፍጡርነታችን ይኸ መንገድ በህይወታችን ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል! ይኸ መንገድ ለሺህ ዘመናት እንደኖረ ሕዝብ፣ እንደ ሀገር ትልቅ የለውጥ ልዩነት ያመጣል!
ማንዴላ ጥሩ መሪ ሕዝቦቹን እንደሚከተል ያምናሉ፡፡ እርስዎም ወደ አሜሪካ ይምጡ እና እኛ ወደ ሀገራችን ስንጓዝ ከኋላችን ይከተሉን እላለሁ፡፡
ለመምራት ወይም ለመከተል ፍላጎቱ የሌላችሁ ወገኖች “ወደ አውነት እና እርቅ ከሚወስደው መንገድ እራሳችሁን አስወግዱ፡፡”
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ቢያነሱ ታላቅ ክብር እና ሞገስ ያገኙበታል፡፡ ይህንን ተግባር እውን እንደሚያደርጉት ምንም ዓይነት ጥርጣሬ በአእምሮዬ ውስጥ የለም፡፡ ኢትዮጵያ በውጭ ወራሪ ስትደፈር እና በተፈጥሮ አደጋ ስትወድቅ ብቻ ነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማታነሳው!
እንግዲህ እንዲህ በማለት ቁጥር 8 የማስታዋሻ ጽሁፌን ልቋጨው፣ “በመጀመሪያ ይንቁሀል፣ ከዚያም ይስቁብሀል፣ ከዚያም ይወጉሀል፡፡ በመጨረሻም አሸናፊ ትሆናለህ፡፡“ጋንዲ
ኢትዮጵያዊነት ዛሬ!
ኢትዮጵያዊነት ነገ!
ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ግንቦት 29 ቀን 2010 ዓ.ም