ማስታዋሻ ቁጥር 4፡ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሕያው መልዕክት ለዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ብሩህ ተስፋ፣

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም 

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

“… አሁን ከፊታችሁ ቆሜ ልገባላችሁ የምፈልገው ቃልኪዳን በአሜሪካ የብዙሀን መገናኛ ያላችሁ እና በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ለምትጥሩ፣ ድምጻችሁን ከፍ አድርጋችሁ ለምትጮሁ፣ የኃይል እርምጃ ለምትወስዱ እና ስለኢትዮጵያ ለምትጨነቁ ሁሉ አሁን በፊታችሁ ቆሜ ዋና ጽህፈት ቤታችሁን በአዲስ አበባ እንድታደርጉ ቃልኪዳን ልገባላችሁ እፈልጋለሁ፡፡ ወደዚህ በመምጣት በሀሳብ ሊሞግቱን ይችላሉ፡፡ አማራጭ ሀሳቦች ካሏቸው እና የተለየ አቅጣጫን [ለሀገሪቱ ] ለመከተል የሚፈልጉ ከሆነ እንደ ግለሰብ ወይም ደግሞ በድርጅት አማካይነት ማድረግ ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚበቃ ቦታ አላት፡፡ በሀሳብ ልዩነቶች ምክንያት በምዕራብ እና በምስራቅ እንዲሁም በደቡብ እና በሰሜን ተቀምጠን እንገኛለን፡፡ አንዳችን የሌላችንን ጉሮሮ የምናንቅ ዓይነት ሰዎች መሆን የለብንም፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ያለ ጥሪ አቅርበናል፡፡ ይህንንም ጥሪ አሁንም እንደገና እደግመዋለሁ፡፡ ማንም ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የሚፈልግ ሁሉ፣ ማንም የተለዬ አማራጭ ሀሳብ ያለው እና በሰላማዊ መንገድ ለአትዮጵያ ሽግግር የሚያቀርብ፣ ማንም እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ድርጅት አማራጭ ሀሳቡን ማቅረብ ይችላል፡፡ ሀገሪቱ እናንተን ትፈልጋችኋለች፡፡ ወደዚህ በመምጣት በትግሉ ተሳታፊ ሁኑ፡፡ ይህንን ቃልኪዳን አሁን ልገባላችሁ እፈልጋለሁ፡፡” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እ.ኤ.አ ሚያዝያ 27 ቀን 2018 ከተናገሩት የተወሰደ

ባለፉት ሳምንታት ባቀረብኳቸው ሶስት ትችቶቼ እንደገለጽኩት ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለአብይ አህመድ ጠንካራ ደጋፊ ነኝ፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ወደ ትውልድ ሀገራቸው እንዲመለሱ እና ሀገራቸውን ወደ ዴሞክራሲ ለማሸጋገር ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚጋብዙ፣ የሚለምኑ እና የሚማጸኑ ልዩ የሆኑ ወጣት መሪ አሏት፡፡ ለፉት አስራ ሶስት ዓመታት ገደማ ያህል ከኢትዮጵያ አቦሸማኔው ትውልድ (ወጣቱ ትውልድ) መካከል አንድ ኢትዮጵያ እና የማትከፋፈል ሀገር በማለት የሚያውጅ እንደዚህ ያለ መሪ እንዲወጣ እና እንዲህ የሚለው የማንዴላ ቃል ኪዳን በኢትዮጵያ እውን ሆኖ እንዳይ ጠንካራ የሆነ ፍላጎቴን ሳራምድ ቆይቻለሁ፡ ይህች ቆንጆ የሆነች ሀገር በፍጹም በፍጹም እንደገና አንዱ በሌላው የማትጨቆን እና የዓለም ሁሉ ውራጅ እንዳትሆን ጠንክረን መስራት አለብን፡፡”

ጽንፈኛ ዲያስፖራ እያሉ እና በቀሪዎቹ ላይ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት የጦርነት እቅድ ይወጣ የነበረባቸውን መልካም ያልሆኑ አሮጌ ቀናት አስታውሳለሁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በበዓለ ሹመታቸው ዕለት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በውጭ ሀገራት የሚገኙ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ወደ ትውልድ ሀገራቸው ቢመለሱ እጆቻቸውን ዘርግተው እንደሚቀበሏቸው አረጋግጠዋል፡፡ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን እውቀታቸውን፣ ሀብቶቻቸውን እና ልምዶቻቸውን በመያዝ ወደ ሀገር ቤት በመምጣት በሀገሪቱ ልማት እንዲሳተፉ ጋብዘዋል፡፡ በውጭ በሚገኙት ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን እና በሀገር ቤት ባሉት አትዮጵያውያን መካከል እውነተኛ እርቅ እንዲኖር በአጽንኦ ጠይቀዋል፡፡

በአራት ሳምንታት ወይም ከዚያ በላይ የቢሮ ስልጣናቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ሰላም፣ ብሄራዊ እርቅ ማውረድ እና በወደፊቱ የሀገሪቱ ዘለቄታዊ ግንባታ ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ በርካታ ግንኙነቶችን አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለብሄራዊ እርቅ እና አንድነት እያደረጉት ስላለው የማግባባት ስራ አደንቃቸዋለሁ ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ጎራዴዎቻችንን ወደ ማረሻ እና ጦሮቻችንን ወደ አበባ መቁረጫ የምንለውጥበት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያውያን ላይ ጎራዲያቸውን የማያነሱበት እንደዚሁም ሁሉ ምንም ዓይነት ጦርነት የማያደርጉበት ጊዜ መኖር የለበትም፡፡

አብዛኞቻችን በዲያስፖራው ያለን ማህበረሰቦች ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያደረጉት ላለው አዎንታዊ እርምጃ የሚመጥን ምላሽ እየሰጠን ባለመሆናችን አዝናለሁ፡፡ አብዛኞቹ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጥረቶች እና ፍላጎቶች ቅንነት የተሞላበት አድናቆታቸውን እያሳዩ ናቸው፡፡ በጥቂቶች ላይ ደግሞ የሰለጠነ ዝምታ ይታያል፡፡ ዋናዎቹ አክራሪ የተቃዋሚ ቡድን አባላት ደግሞ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በአሉታዊ መልኩ ይተቻሉ፡፡ ጥቂቶች ደግሞ ከጎናቸው በመቆም ሙሉ ድጋፍ ይሰጣሉ፡፡

በእርግጥ እኔ ለእርሳቸው ሙሉ ድጋፌን ለማሳየት ቀላል ነገር ነው፡፡ የፖለቲካ ፍላጎት የሌለኝ ሰው እንደመሆኔ መጠን አዕምሮዬ ያሰበውን በነጻነት እናገራለሁ፡፡ እናም በስልጣን ላይ ላሉትም ሆነ ለሌላ ለሚያዳምጥ ለማንኛውም ሰው ሁሉ እውነቱን እናገራለሁ፡፡

ሆኖም ግን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን የምደግፋቸው እንዲሁ በጭፍንነት አይደለም፡፡ ባለፉት አስራ ሶስት ዓመታት ገደማ ያህል አብጠርጥሬ የምተች እና ጥልቅ ነቀፌታን ለማድረግ እንደምችል በግልጽ እንዳሳየሁ አምናለሁ፡፡ እኔ ሳቀርባቸው የነበሩትን ጠንካራ ትችቶች በመረጃ ላይ የተደገፉ ስለሆነ ብዙ ተከራካሪ በማስረጃ መከላከል አልቻለም፡፡

አብይ አህመድን እወዳቸዋለሁ ምክንያቱም እርሳቸው በእርግጠኝነት እስከ ዛሬ ድረስ ስጠብቀው የነበረውን የኢትዮጵያ አቦሸማኔ ናቸው፡፡ ፍጹም አይደሉም፡፡ ወጣት ናቸው፤ እናም ብዙ የሚማሯቸው ነገርች አሏቸው፡፡ በህሊና ሊታሰቡ ከማይችሉ ተግዳሮቶች እና ችግሮች ጋር ፊት ለፊት ገጥመዋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ሀገር ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ከባድ ስራ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህንን ከባድ ስራ ለመከወን አንድ ሰው ተገኝቷል፡፡ በእኔ አመለካከት በአሁኑ ጊዜ ይህንን ስራ ለመስራት ከአብይ የተሻለ ሌላ ማንም አይገኝም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና የጨለማው ጎን ኃይሎች፣

የጨለማው ጎን የማይታዩ/ስውር ኃይሎች ረዥም ቢላዋቸውን በመያዝ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ እየዘመቱ ነው፡፡ እነርሱም በፓርላማው ውስጥ ናቸው፡፡ በቢሮክራሲው ውስጥ ናቸው፡፡ በደህንነት ኃይል አገልግሎቱ ውስጥ ናቸው፡፡ በወታደራዊ ክፍሉ ውስጥ ናቸው፡፡ በንግዱ ማህበረሰብ ውስጥ ናቸው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በዲያስፖራው ማህበረሰብ በዓለም አቀፉ ድረ ገጽ ከኢንተርኔት ጀርባ ተደብቀው የሚገኙ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን አድፍጠው ለመጣል በየትም ቦታ ሆነው የሚጠባበቁ ናቸው፡፡

ሆኖም ግን እነዚህ የጨለማው ጎን ኃይሎች የብርሀኑን ጎን ኃይሎች በፍጹም ሊያሸንፉ አይችሉም፤ ይህ ኃይል እጅግ በጣም ኃያል ነውና፡፡

ለእኔ የፖለቲካ መሪ ባህሪ ከፖለቲካ ውስብስብነት ወይም ደግሞ ከጉብዝና እና ከሰራተነት የበለጠ ነው፡፡ ጆርጅ ኦርዌል እንዲህ ብለዋል፣ “በዚህች ማጭበርበር በተንሰራፋባት ዓለም እውነትን መናገር አብዮታዊ ድርጊት ነው፡፡“

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የእኔን ቋንቋ ይናገራሉ፡፡ እውነት የእኔ ቋንቋ ነው፡፡ እርሳቸው የሚናገሩትን የሚሉ ደግሞም የሚሉትን የሚናገሩ ዓይነት ሰው ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በፍጹም በጠብመንጃ ኃይል ወይም ደግሞ አንዱ የጎሳ ቡድን በሌላው የጎሳ ቡድን የበላይነት አትገዛም ይላሉ፡፡ እውነተኛው ስልጣን ከሕዝብ ፍላጎት ይመነጫል፣ እናም አመራሩ የተሰጠውን ስራ በተገቢው ሁኔታ ማከናወን ካልቻለ ሕዝቡ ይህንን አመራር ማባረር እና በምትኩ የተሻለ ለመስራት እና ሕዝብን ለማገልገል በሚችል ሰው መተካት አለበት ይላሉ፡፡ መንግስታቸው በሙስና ተዘፍቋል እናም ሲናገሩ ቀላል የሆነውን እና ሲሰሩት ከባዱን ሙስናን አስወግዳለሁ ይላሉ፡፡ ካንሰር በሰው አካል ላይ እንደሚሰለጥን ሁሉ ሙስና ደግሞ በሀገር ላይ ይንሰራፋል፡፡ ሙስናን መፈወስ ካንሰርን ከመፈወስ ጋር መሳ ለመሳ ነው፡፡ እስከ አሁን ድረስ ለካንሰር ወይም ለሙስና ፈውስ መድኃኒት ያገኘ ማንም ሰው የለም፡፡

ሕዝቡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ይወዳቸዋል፡፡ በከተሞች አዳራሾች በሚደረጉ ስብሰባዎች ሕዝቡ ከእርሳቸው ጋር እንደሚፈራ እና እንደ ትልቅ ባለስልጣን አይደለም የሚነጋገር፣ ሆኖም ግን እንደ ልጁ እያየ ነው፡፡ እንደማንኛውም ሰው ስህተት ሊሰሩ እንደሚችሉ ለሕዝቡ ይናገራሉ፣ እናም ስህተት በሚሰሩበት ጊዜ ከስህተታቸው እንዲመለሱ እና በትክክለኛው መንገድ እንዲጓዙ ትንሽ ቁንጥጫ በመስጠት እንዲመልሳቸው ይናገራሉ፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብይ ለእነርሱ መልካም ሰው ናቸው ካለ በእርግጠኝነት ለእኔም መልካም ሰው ናቸው፡፡

ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን በዓለም ላይ ተሰራጭተው ከሚገኙት እና ከሚፈበረክ የተቃርኖ ዘመቻ፣ የአሸናፊነት ርኩስ መንፈስ፣ ተጠራጣሪነት፣ ጨለምተኝነት፣ ግትርነት፣ ዘውገኝነት፣ ተጻራሪነት እና የተለየ ፍጡርነት ከሚያራምዱት የጨለማው ጎን ኃይሎች ግለሰባዊ አውዳሚ ፖለቲካ ለመከላከል በጽናት የቆምኩት፡፡

አሁን በቅርብ ጊዜ በአማርኛ ተዘጋጅቶ በነበረ ትችት ታማኙ እና መንፈሰ ጠንካራው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም እንዲህ በማለት ጽፈዋል፣ “እርሱን [ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን] ለመጣል በጨለማው ውስጥ አድፍጠው የቆሙ በርካታዎች ያሉ ይመስላል“ ብለዋል፡፡

በእርግጠኝነት የጨለማው ጎን ኃይሎች በዓለም ድረ ገጽ የኢንተርኔት መረብ ማንነታቸውን በመደበቅ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ የቃላት ጦርነታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ስለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚሉት ምንም ዓይነት አዎንታዊ ነገር የላቸውም፡፡ ያንኑ ያረጀውን እና መሰረተቢስ የሆነውን ሀሜት እና ውንጀላቸውን በማሰራጨት እንዲህ በማለት ላይ ይገኛሉ፣ “አብይ የወያኔ አሻንጉሊት ነው፡፡ ወያኔ ያሳደገው ነው፡፡ እነርሱ ተቆጣጥረውታል፡፡ የእነርሱን ቆሻሻ ስራ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ወያኔ በጣም አጭበርባሪ እና ጎበዝ ነው፡፡ የማንቹሪያውን እጩ የኢትዮጵያ አምሳያውን አእምሮውን በማጠብ ጠፍጥፈው ሰርተውታል፡፡ የወያኔ ወኪል ነው፡፡ እርሱ ንግግር ማድረግ እንጅ ተግባር የሚባል ነገር አያውቅም፡፡ በርካታ ጉዞዎችን ያደርጋል፡፡ መቼ ነው ስራ ሊሰራ የሚችለው?  አሰልች  አሰልች…..“

እነዚህ እራሳቸውን ትክክለኛ አድርገው የሰየሙ የጨለማው ጎን ኃሎች በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ የሚያቀርቧቸውን ውንጀላዎች ሊደግፉ የሚችሉ ማንኛውንም ዓይነት ማስረጃ በቃላት ወይም በድርጊት የሚያቀርቡ ከሆነ እኔ እራሴ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ አመልካች ጣቴን በመቀሰር የእነርሱን ውንጀላዎች እደግፍ ነበር ፡፡ ሆኖም ግን ክሶቻቸውን ሊደግፉ የሚችሉ ቅንጣት ያህል ማስረጃ የላቸውም፡፡

ለእነዚህ የጨለማው ጎን ኃይሎች የእኔ ምላሽ እንዲህ የሚል ነው፣ “በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ የምታራምዱበትን ውንጀላ ማስረጃ አቅርቡ አለዚያም ዝም በሉ፡፡“ ግለሰብን ጥላሸት የመቀባት ፖለቲካችሁን አቁሙ!

እስቲ እራሴን ግልጽ ላድርግ፡፡ ሰሜታዊነት ቅሬታ፣ ሆድ ቁርጠት፣ ጥርስ መቆርጠም ፣ ማጠልሸት፣ መወንጀል፣ ማቃሰት እና መጮህ ማስረጃ አይደለም፡፡

ተደጋጋሚ መሰረተቢስ ክሶችን እና ውንጀላዎችን የሚያቀርቡትን መሃይም የጨለማው ጎን ኃይሎችን ብዙ ጊዜ አይቶ አንዳላየ አልፈዋለሁ፡፡ ሆኖም ግን አሁን አልችልም ምክንያቱም እንዲህ የሚለውን የጎቴን ምክር አስባለሁና፣ “በዚህ ዓለም ላይ ድንቁርናን በተግባር ከማየት በላይ የሚያስፈራ ምንም ዓይነት ነገር የለም፡፡“

የእውቀትን ኃያልነት በፍጹም አልፈራም፣ ሆኖም ግን የድንቁርናን ኃያልነት በከፍተኛ ደረጃ ነው የምፈራው፡፡

ማይማን ደናቁርት ቻይና ሀገር በመጠለያ ውስጥ እንዳለ ኮርማ ወይፈን ናቸው፡፡ በአካባቢያቸው የሚያገኙትን ማንኛውንም መልካም ነገር ሁሉ ያወድማሉ፡፡

ድንቁርና በእውቀት ሊሞላ እስከሚችል ድረስ ባዶ ሆኖ የሚጠብቅ ጭንቅላት አይደለም፡፡ የደንቆሮ አእምሮ በጥላቻ፣ በጥርጣሬ፣ በእራስ አለመተማመን፣ በበቀል፣ በተጻራሪነት እና በምቀኝነት የተሞላ ነው፡፡ በደንቆሮ አእምሮ ውስጥ ለእውነት እና ለማስረጃ ቦታ የለም፡፡

ደንቆሮ ሰዎችን አደገኛ የሚያደርጋቸው አነሱ ከሚያውቁት በላይ የሚታወቅ ነገር የለም ብለው ያምናሉ ፡፡ ጥያቄዎችን አይጠይቁም፡፡ ማስረጃዎችን አይሰበስቡም፡፡ በጥልቀት አያስቡም፡፡

ድንቁርና ተላላፊ በሽታ ነው፡፡ እንደ እንፍሉዌንዛ  ከአንድ ሰው ወደ ሌላው የሚተላለፍ ቫይረስ ነው፡፡ ድንቁርና በአደጋ የተጋለጡ፣ ግራ የተጋቡ፣ ተስፋ የቆረጡ፣ ኃይል የለሾችን እና የተገለሉትን አእምሮ ያጠምዳል፡፡ ምንም ነገር አያውቁም፡፡ እናም በነሲብ ይገምታሉ፡፡ ያለምንም እውነታ እና ማስረጃ በሚገምቱበት ጊዜ የማያስብ እንስሳነት ባህሪን ያመለክታል፡፡

ለእኔ አስቂኙ ነገር የጨለማው ጎን ኃይሎች ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሻማ ሊይዙ የመሞከራቸው ጉዳይ ነው፡፡ እነርሱ ለእርሳቸው በምንም ዓይነት መልኩ ሻማ ሊይዙ ሊወዳደሩ አይችሉም፡፡ ከጥቃቅን ወቀሳዎች እና ባዶ ትችቶች በስተቀር እነዚህ የጨለማው ጎን ኃይሎች አንዳንድ ጊዜ በመረጃ ያልተደገፈ ሙግታቸውን ለማቅረብ ባልተጠበቀ ጊዜ ብቅ ከማለት በስተቀር በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ በትክክለኛ ማስረጃ ላይ ተመስርተው በሀሳብ ለማሸነፍ ፊት ለፊት ሲቆሙ አይቻቸው አላውቅም፡፡ በሚያቀርቧቸው ትችቶች ትክክለኛነት ላይ እርግጠኛ  ከሆኑ እና የተሻለ ስራ የሚሰሩ ከሆነ በኢትዮጵያ ላይ የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት፣ የሕገ መንግስት ማሻሻያዎቻቸውን፣ ሀገሪቱ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ቀውስ ውስጥ ገብታ እየዳከረች ባለችበት ሁኔታ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞቻቸውን እና የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት እየቀነሰ መምጣቱን መፍትሄ ለመስጠት የሚያቀርቧቸውን አጠቃላይ ጠቋሚ ዕቅዶቻቸውን ለምን አያሳዩንም?

እነርሱ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚጠብቋቸውን ከ30 ቀናት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የኢኮኖሚ ብልጽግናን ለማምጣት፣ የሰብአዊ መብቶች መጠበቃቸውን ለማረጋገጥ፣ የዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለመመስረት እና የምርጫ ማሻሻያ ለማድረግ  ዕቅዱ ካላቸው በደቂቃ ውስጥ ከእነርሱ ጎን እቆማለሁ፡፡

አሁን እየታየ ያለው የጨለማው ጎን ኃይሎች ያዙኝ ልቀቁኝ እምቧ ከረዩ ድርጊት እውነተኛው ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በያዙት አካሄዳቸው ስኬታማ ይሆናሉ ብለው ስለሚፈሩ ብቻ ነው፡፡ እኒህ ጠቅላይ ሚኒስትር ከምንም ተነስተው እንደዚህ ያለ የሕዝብን አክብሮት፣ እምነት እና አድናቆት የሚጎናጸፉ ከሆነ በመልካም አስተዳደር፣ በጸረ ሙስና ትግል ጥረታቸው እና በሰላም እና እርቅ ተጋድሏቸው ስኬታማ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስኬታማ የሚሆኑ ከሆነ ደግሞ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የሚገኙት የጨለማው ጎን ኃይሎች ይወድቃሉ፡፡ ለስልጣን ያሏቸው ህልሞቻቸው እና ፍላጎቶቻቸው ከስርዓት ውጭ በመሆን ይንኮታኮታሉ፣ እንደ ጉም ይበናሉ፣ ዶግ አመድ ሆነው እስከመጨረሻው ይሞታሉ፡፡ ከዚያ በኋላ በምንም ዓይነት መልኩ ከፋፍለው መግዛት አይችሉም፡፡ ጎሰኝነትን እና ኃይማኖትን የጭቆና መጠቀሚያ መሳሪያ በማድረግ ለመጠቀም አይችሉም፡፡ ለእነርሱ ጨዋታው ተጠናቆባቸዋል፡፡

ስለሆነም የጨለማው ጎን ኃይሎች በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ እያራመዷቸው ያሉት ተቃውሞዎች የተመሰረቱት በይሆናል ግምት ላይ ተመስርተው ነው፡፡ እውነት አስመስለው ለመናገር የይሆናል መላ ግምትን በመሳሪያነት ይጠቀማሉ፡፡

ለዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ተገቢ መልዕክት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስፈላጊነት፣

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንን ስጋት እና ጉዳዮችን በጥሞና በማዳመጥ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡ በስልጣን ላይ በቆዩባቸው በእነዚህ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ከዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ጋር በመድረስ አመርቂ የሆነ ስራ ሰርተዋል፡፡ ሆኖም ግን በዲያስፖራው ማህበረሰብ ውስጥ እስከ አሁንም ድረስ በጨለማው ጎን ኃይሎች ግራ የተጋቡ፣ የተታለሉ እና የተጭበረበሩ በርካታ ዜጎች አሉ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሀሳቦች እና ዓላማዎች ላይ ጥርጣሬ ለመፍጠር እና ህሊናቸውን እንዲጠራጠሩ ለማድረግ በየቀኑ የቅጥፈት እና አሳሳች መረጃዎችን ያዥጎደጉዳሉ፡፡

አንድ የቅርብ ጊዜ ምሳሌን እንውሰድ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የዲያስፖራው ማህበረሰብ ወደ ትውልድ ሀገሩ በመመለስ በሀገር ግንባታው የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ በማለት ያደረጉትን የጥሪ ግብዣ የወያኔ ወጥመድ ነው ይላሉ፡፡ ይህ ጥሪ ያልጠረጠሩትን እና የዋህ የሆኑ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ወደ ሀገር ቤት እንዲሄዱ እና እንደደረሱም የወጥመዱን በር በመዝጋት የጥፋት ሰለባ ለማድረግ የታቀደ ደባ ነው ይላሉ፡፡ ለደህንነታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሰጠው ዋስትና የለም ይላሉ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በስራ ላይ እስካለ ድረስ ወደ ሀገር ቤት መመለሱ ትርጉም የለውም ይላሉ፡፡ ምክንያቱም በቀላሉ ኮማንድ ፖስት እየተባለ ለሚጠራው አካል ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ ይላሉ፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በእርግጠኝነት ሁለት መንግስታት እንዳሉ ይነግሩኛል፡፡ እነርሱም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚመራው የሲቪሉ መንግስት እና በሌሎች ቁጥጥር ስር ያለው የኮማንድ ፖስቱ ወታደራዊ መንግስት ናቸው፡፡ የኮማንድ ፖስቱ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ዋና እና የማሻሻያ ፕሮግራማቸውን ሊያደናቅፉባቸው የሚችሉ ነገሮችን በማስወገድ ለውጤታማነት እንዲሰሩ አይፈቅዱላቸውም ይላሉ፡፡ የኮማንድ ፖስቱ ዜጎችን በሚስጥር ያስራል፣ እንዲያውም ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እውቅና ውጭ፡፡ ኮማንድ ፖስቱ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን የእነርሱ ግንባር ቀደም ሰው በማድረግ ረዘም ያለ ጊዜ ለመግዛት ይፈልጋል፡፡ የጸረ ሽብር ሕጉ በስራ ላይ እስከዋለ ድረስ የእነርሱ (ወደ ሀገር ቤት የሚመለሰው ዲያስፖራ) ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ አይገኝም ይላሉ፡፡

እኔ ለእነዚህ ሁሉ ስጋቶች መልስ የለኝም፡፡ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ወደፊት ጥሩ ግንዛቤ እንደሚኖር እርግጠና ነኝ፡፡

የእኔ ስሜት የጨለማው ጎን ኃይሎች ይህንን ሁኔታ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዲያስፖራው ዓይን ውስጥ ቅራኔ ውስጥ እንዲገቡ ለማድረግ፣ ለማሳነስ እና ሕጋዊ እንዳይሆኑ ለማድረግ የሚሸረብ ደባ ነው፡፡

ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን የሚያስተላልፏቸውን መልዕክቶች በተገቢው ሁኔታ ማስተላለፍ ጠቃሚ ነው ብየ የማምነው፡፡ የሚቻል ከሆነ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ወይም ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ጋር በቀጥታ ስርጭት መገናኘት አለባቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የዲያስፖራ ጨለምተኞችን፣ ተጠራጣሪዎችን፣ የአሸናፊነት መንፈስ አራማጆችን… በብሩህ የቀጥታ ስርጭት መልዕክቶች፣ በደስታ መንፈስ፣ በአብሮ መኖር ስብከት እና በሀሳባዊነት መሳሪያዎች በመጠቀም መታገል፣

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በጨለማው ጎን ላሉት ኃይሎች የሚሉት ወይም ደግሞ የሚያደርጉት ምንም ዓይነት ነገር የለም፡፡

ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉትን ዲያስፖራ ኢትዮጵያውን የጨለማው ወገን ኃይል አሳንሰው እንዳይመለከቷቸው በጥብቅ ለማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን እንዳሉት “እርሳቸውን ለመጣል አድፍጠው ተቀምጠዋል፡፡”

ወራት በሄዱ ቁጥር ጸረ አብይ ኃይል ለመመስረት እንደሚያስተባብሩ አውቃለሁ (ግምት እየሰጠሁ አይደለም)፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዲህ የሚለውን የሰንትዙን ስልታዊ ምክር ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው፣ “ጠላቶቹን በማቅለል በንቀት የሚያይ በመጨረሻ የእነርሱ ምርኮኛ እንደሚሆን እርግጠኛ መሆን አለበት፡፡“

ምን ዓይነት የስነ ልቦና መሸርሸር ጦርነት የማድረግ ጨዋታ እንዳቀዱ ስመለከት እደነቃለሁ፡፡

እንዲህ የሚል አባባል አለ፣ “ከመጥፎ ወሬዎች በስተቀር ከብርሀን ፍጥነት የሚቀድም ምንም ዓይነት ነገር የለም

የጨለማው ጎን ኃይሎች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ለማሳነስ፣ ዝቅ አድርጎ ለማየት እና ተቀባይነት እንዳያገኙ ለማድረግ መጥፎ ወሬዎችን ቀስ በቀስ የማሰራጨት ስልታቸውን ለመጠቀም ተስፋ አድርገዋል፡፡ ስራው ተግባራዊ እንዲሆንላቸው በውድቀት ዕጣ ፈንታ፣ የቡድን ሀሳብ፣ በበርካታ ኢትዮጵያውያን በተለይም በዲያስፖራው ማህበረሰብ መካከል የእንስሳነት አስተሳሰብ እንዲኖር እኩይ ምግባሮቻቸውን በማራመድ ዘዴዎች ላይ ይመካሉ፡፡

የሰብአዊ መብት ተሟጋች እና ስብከት አራማጅ ከመሆኔ አንጻር ከሁሉም የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋራ በተለያዩ መንገዶች እገናኛለሁ፡፡ የጨለማው ጎን ኃይሎች በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ አሉታዊ ዘገባ በማሰራጨት የሀሳብ ወይም ደግሞ የአመለካከት ግጭቶች ለመፍጠር ጠንክረው ይሰራሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሚያሳዩት ጥብቅ ታማኝነት እና ቅንነት የተመሰጡ መሆናቸውን ያዩአቸው እና የሰሟቸው በርካታ ሰዎች ይነግሩኛል፡፡ ስለአንድነት እና ኢትዮጵያዊነት ይናገራሉ፡፡ እንደ ፖለቲከኛ አይደለም የሚናገሩት ሆኖም ግን እንደ አንድ መብቱ እንደተደፈጠጠ ዜጋ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ድባብ ውስጥ በፍጹም ተሰምቶ የማያውቅ ቋንቋን በመጠቀም ይናገራሉ፡፡

“ስለዚህ ያለው ችግር ምንድን ነው” በማለት እጠይቃለሁ፡፡

አንተ አታውቀውም በማለት ይነግሩኛል፡፡ ልታምነው አትችልም፡፡ ወያኔዎች አሳድገው ያሰለጠኑት ነው፡፡ የእነርሱ የትሮጃን ፈረስ ነው፡፡ ወያኔ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሊጠቀምበት ያስቀመጠው ሰው ነው፡፡ እንዲያውም አንዱ ማንነታቸውን ለመግለጽ እንዲህ የሚለውን የቆየ የኢትዮጵያውያን አባባል ተጠቅሟል፣ “አፉ ቅቤ ልቡ ጩቤ“፡፡ በልቡ ጩቤ በመያዝ ተናግሮ የሚያሳምን አንደበተ ርትኡ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ እንዲህ ብሏል፣ “ያልጠረጠረ ተመነጠረ፡፡“

እንደዚህ ያሉትን ያልተለመዱ ምላሾች ልገነነዘባቸው አልችልም፡፡ እውነት ለመናገር በመሬት ላይ ሳይሆኑ የትኛው ፕላኔት ላይ ነው አብዛኛውን ጊዚያቸውን ያሳለፉት በማለት ሁልጊዜ እደነቃለሁ፡፡

እንደ ፖለቲካ ሳይንቲስት አሉታዊ የሆኑ የፖለቲካ ቅስቀሳዎች የሚያስከትሏቸውን ውጤቶች የማጥናት እድሉ አለኝ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እየተሰራጩ የሚገኙት አሉባልታዎች እና መጥፎ ወሬዎች በጨለማው ጎን ኃይሎች የሚሰራጩ አሉታዊ የፖለቲካ ቅስቀሳ ስራዎች እንደሆኑ አድርጌ እቆጥራቸዋለሁ፡፡

የፖለቲካ ስነ ልቦና ባለሞያዎች የአሉታዊ ፖለቲካ ቅስቀሳዎችን ይመለከታሉ፡፡ ህልውናችን በአጥቂዎች ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ለአደጋ በተጋለጠ ጊዜ ከሰው ልጆች ዝግመተ ታሪክ ከሚመነጨው ከአሉታዊ አጧዡ ጋ እንደሚጣበቁ ጥቂት ሰዎች ሀሳቦቻቸውን ይሰነዝራሉ፡፡ አብዛኞቹ ሰዎች ከአዎንታዊ ነገሮች ይልቅ ብዙ ትኩረት የሚሰጡት ለኡታዊ ወይም ለመጥፎ ወሬ እና ልምድ እንደሆነ የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ አለ፡፡

የእኔ የሁለተኛ መረጃ ምንጭ ምልከታ እንደሚያሳየኝ የምገናኛቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን በዕጣ ፈንታ (ነገሮች አስቀድመው ምን እንደሚሆኑ የተወሰኑ ናቸው፡፡ እናም የሰው ልጆች ለለውጥ ደካሞች ናቸው ብለው የሚያምኑ) ላይ የሚያምኑ ናቸው፡፡ ስለወደፊቱ አስቀድመው እጅ የመስጠት እና የማይቀረው እና ወደፊት የሚመጣው ነገር መጥፎ እንደሆነ አድርገው የማሰብ ዝንባሌን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ምንም ዓይነት ኃይል እንደሌላቸው ይሰማቸዋል፣ እናም እርምጃ ለመውሰድ ሽባ ይሆናሉ፡፡ ሁሉንም ነገር አምላክ እንዲሰራላቸው ለእርሱ ይተውታል፡፡

እንደዚህ ዓይነት ዕጣ ፈንታዎች ለአሉታዊነት እና ለተጠራጣሪነት አስተዋጽኦ በማድረግ ውጤትን ያቀጭጫሉ፡፡ ጥርጣሬ እና ያለመተማመን የጨለማው ጎን ኃይሎች በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ የጥላቻ እና የተቃርኖ ዘሮችን ለመዝራት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ፡፡

ድንቁርና የጥርጣሬ ምንጭ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ የማናውቀውን ነገር እንፈራን፣ እናም ሁሉም ነገር በመጥፎ ሁኔታ ይጠናቀቃል በማለት እንጠረጥራለን፡፡

የቀድሞው የዩኤስ የመከላከያ ሚኒስትር በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ “የሚታወቁ ታዋቂዎች አሉ፡፡ የምናውቃቸው ታዋቂዎች አሉ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ የምናውቃቸው የማናውቃቸው ተዋቂዎች አሉ፡፡ ይህም ማለት የምናውቃቸው ጥቂት የማናውቃቸው ነገሮች አሉ ማለት ነው፡፡ ሆኖም ግን የማናውቃቸው የማይታወቁ አሉ እኛ የማናውቃቸው፡፡“

በዕጣ ፈንታ ስሜቶቻቸው የሚጎዱ በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚታወቅ ነገር እንዳለ ያውቃሉ ፍርሀትም አይኖራቸውም፡፡ ነገር ግን የማይታወቅ ነገር ካለ ይህ ይፈራል ምክንያቱም የማይታወቅ ማለት ሁልጊዜም የማይታወቅ አደጋ ማለት ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መልዕክት እንዲህ የሚለውን ጥያቄ መመለስ አለበት፡ የኢትዮጵያ ብርጭቆ ግማሽ ሙሉ ግማሽ ጎደሎ ነውን?

እውነትን መናገር አለብኝ፡፡ በዲያስፖራው እንደምመለከተው ዕጣ ፈንታ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የኑሮ ስልት ነው፡፡ በርካታዎቹ የኢትዮጵያ ብርጭቆ ግማሹ ሙሉ እንደሆነ አድርገው ይመለከታሉ፡፡

እኔ የምናገራቸው ብዙዎቹ ትረካዎች የማሰብ፣ የስሜት እና የመሆን አጠቃላይ ዝንባሌ አላቸው፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ነገሮች ሁሉ ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ የማዘንበል ባህሪ አላቸው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስልጣን መያዝ ወደፊት ሊገኙ የሚችሉ መልካም አጋጣሚዎች እንደሚኖሩ አይታያቸውም፡፡ እርሳቸው ከሚያደርጉት ወይም ለማድረግ ከሚያቅዱት እነርሱ የሚመለከቱት አደጋውን እና ውድቀትን ብቻ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ትንሽ ተስፋ ብቻ አላቸው፡፡

ለዘመናት ሲጨቁን እና የመልካም አሰተዳደር እጦት ሲያሰቃየው የኖረ ከመሆኑ አንጻር እንደዚህ ያለ ግንዛቤ ቢኖረው ለጊዜውም ቢሆን የሚያስደንቅ ነገር አሆንም፡፡ ሆኖም ግን እንደዚህ ያለው አመለካከት እውነተኛው መልካም አስተዳደር እና የለውጥ ዕድል በሚመጣበት ጊዜም በእራሱ ችግር ይሆናል፡፡ ቀድም ሲል እንደተመለከትኩት መልካም አጋጣሚን ላለማጣት መልካም አጋጣሚን በፍጹም አያጡም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለወደፊት በኢትዮጵያ ላይ ብሩህ ተስፋ እንዲኖር ከፍተኛ የሆነ ስራ ሰርተዋል፡፡ በእራስ የመተማመን ተስፋ እንዲኖር እና ሌሎች ደግሞ በኢትዮጵያ እና በእራሳቸው የወደፊት ተስፋ እንዲኖራቸው ስሜትን ቀስቅሰዋል፡፡ በጣም ከልክ ያለፈ ደስታ እንዳያደርጉ እና የማይፈጽሟቸውን ነገሮች ቃል እንዳይገቡ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በእርግጥ በተለያዩ አጋጣሚዎች ምን ማድረግ እንደሚችሉ እና ምንስ ማድረግ እንደማይችሉ እንዲሁም የእራሳቸውን ውስንነት በግልጽ ተናግረዋል፡፡ በሕዝቡ ውስጥ የይቻላል መንፈስን ለማስረጽ እና ወጣቱ በጎ ፈቃደኝነትን እና የስራ ዲሲፕሊን መንፈስን እንዲያከብር ጥረት አድርገዋል፡፡

ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ በኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ተስፋ እንዲኖረው በጣም ጠንካራ ሆነው መስራት አለባቸው፡፡

የጨለማው ጎን ኃይሎች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በስልጣን ላይ የሚቆዩ ከሆኑ ግማሽ ሙሉ የሆነችዋን ኢትዮጵያን ፍጹም ባዶ እንደሚያደርጓት የቅስቀሳ ዘመቻቸውን በማካሄድ ዘመቻ ላይ ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ የሁልጊዜ ጨለምተኞች የሆኑትን ምንም ዓይነት አዎንታዊ ነገሮች ቢደረጉ ሁልጊዜ ስህተት በማነፍነፍ የሚዋትቱትን እንዲሁም ከመቅጽበት አሉታዊ ምላሻቸውን የሚሰጡትን ወገኖች ወደ ቀና መንፈስ በመመለስ አዎንታዊ አስተሳሰብ እንዲሰርጽባቸው ማድረግ መቻል አለባቸው፡፡

ጨለምተኝነት እና ዕጣ ፈንታ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ አውዳሚ አመለካከት ነው፡፡ ሰዎችን ለማድረግ የሰነፉ ዘፈቀደዎች እና ኃይል የለሾች ያደርጋቸዋል፡፡ ሽባ ያደርጋቸዋል፡፡ ሰዎች ነገሮችን ለማሻሻል የሚያደርጉትን ጥረት ይከለክላቸዋል፡፡ ጨለምተኝነት ሁልጊዜ የሚጠናቀቀው በአሸናፊነት መንፈስ እና ነገሮች ምን ያህል መጥፎ ቢሆኑም ባሉበት መቀበል ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዲህ የሚለውን የዶ/ር ማርቲን ሉተርን ምክር መቀበል አለባቸው፣ “ጨለማ ጨለማን አያስወግደውም፡፡ ጨለማን ሊያስወግደው የሚችለው ብርሀን ብቻ ነው፡፡ ጥላቻ ጥላቻን አያስወግደውም፡፡ ጥላቻን ሊያስወግደው የሚችለው ፍቅር ብቻ ነው፡፡

የጨለማው ጎን ኃይሎች በጨለማ አይወገዱም፡፡ ሊወገዱ የሚችሉት በብርሀን ጎን ኃይሎች ወይም ደግሞ ባጭሩ በፍቅር ኃይል ብቻ ነው፡፡

ይህ ኃይል ሰባ አምስት ሚሊዮን የሚሆነውን ወጣቱን ኃይል አቅፏል፡፡ ፍትህ እና እኩልነትን የተነፈገው ሕዝብ ከፊቱ ተሰልፏል፡፡ ኃይሉ ከእርሱ ዙሪያ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳተፍ አለባቸው፡፡ ይህ ኃይል ከእርሳቸው ጀርባ ነው፡፡ ወጣቱ ማህበረሰብ 75 ሚሊዮኑ ከእርሳቸው ጀርባ ነው፡፡ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከእርሳቸው ጀርባ ነው፡፡ የቀድሞው የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር በደረ ገጻቸው እንዲህ የሚል መልዕክት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተላልፈዋል፣ “የዴሞክራሲያዊ አሰራርን ለማሻሻል ድፍረት የተሞላባቸውን እርምጃዎች ከመውሰድ እንዳያቅማሙ፡፡ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከጀርባዎ ነው፡፡“

እኛ ዲያስፖራዎች ከጀርባቸው ነን፡፡ እያንዳንዱን ነገር እንደወረደ በትክክል ይንገሩን፡፡ የእርሳቸውን ተስፋዎች እና ስጋቶች ይንገሩን፡፡ ምን ለማድረግ እንደሚችሉ እና ምንስ ለማድረግ እንደማይችሉ ይንገሩን፡፡ እርሳቸው ስኬታማ እንዲሆኑ እንዴት መርዳት እንደምንችል እና እርሳቸው ስኬታማ ባይሆኑ እና ቢወድቁ ምን ሊከሰት እንደሚችል ይንገሩን፡፡

ወደ ነጻነት የሚደረገው ጉዞ ረዥም እና ከባድ ነው፡፡ ታላቁን ተራራ ስንወጣ ሌላ በርካታ ትናንሽ ተራራዎች ይመጣሉ በማለት ማንዴላ ለደቡብ አፍሪካ ሕዝቦች እንደተናገሩት ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ እርሳቸውም ይህንን ለኢትዮጵያ ሕዝቦች መናገር አለባቸው፡፡

ስለሆነም የአትዮጵያን የችግሮች ተራሮች እና ትናንሽ ተራሮች ለመውጣት የእርሳቸው መልዕክት ምን መሆን አለበት? ዶ/ር ኪንግ እንዲህ በማለት የመከሩንን መድገም አለባቸው፣   “መብረር ካልቻልክ ሩጥ፣ መሮጥ ካለቻልክ ተራመድ፣ መራመድ ካልቻልክ ተንፏቀቅ፡፡ ሆኖም ግን ምንም አደረግህ ምን ምንጊዜም ወደፊት መንቀሳቀስ አለብህ፡፡“

ወደፊት መንቀሳቀሳችንን መቀጠል አለብን ምክንያቱም ወደኋላ ወደ ጨቋኝ አምባገነኖች መሄድ ምርጫ አይደለም፡፡ ለነጻነት፣ ለዴሞክራሲ እና ለሰብአዊ መብት መጠበቅ ወደፊት፡፡

ታላቁን እና ትናንሾቹን ተራራዎች ለመውጣት ወደፊት መንቀሳቀሳችንን መቀጠል አለብን፡፡

የብሩህ ተስፋ ኃያልነት-ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እራስዎትን ወደ ጨለማው ሳይሆን ወደ ጸሐይ ቀጥ አድርገው ይቁሙ፣

ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ባደረጉት ባንድ የከተማ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የንግዱ ማህበረሰብ እና ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ማንኛውንም የሚችሉትን ነገር ሁሉ በማድረግ የኢትዮጵያን ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲገነቡ ጠይቀዋል፡፡

በእርግጥ በአሁኑ ጊዜ እርሳቸው እራሳቸው የኢትዮጵያ መልካም ገጽታ ናቸው፡፡ ስለሆነም የብሩህ ተስፋ ገጽታን፣ የተስፋ እና የስኬት ገጽታን  ለመላው ዓለም ለማሳወቅ ጥረታቸውን ከምንጊዜውም በላይ አጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡

ስለብሩህ ተስፋ ካነሳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከማንዴላ እንዲህ የሚለውን ምክር መማር ይችላሉ፣ “እኔ በመሰረቱ የብሩህ ተስፋ ናፋቂ ነኝ፡፡ ያ ከተፈጥሮም ይምጣ ከጥረት ምንም ማለት አልችልም፡፡ በከፊል የብሩህ ተስፋ ባለቤት መሆን በእግር እየተጓዙ የአንድን ሰው እራስ ወደ ጸሐይ ማድረግ ነው፡፡ ስለሰብአዊነት ያለኝ እምነት በጽኑ ሲፈተን በርካታ ጨለማ ክስተቶች ነበሩ፡፡ ሆኖም ግን እራሴን ለተስፋየለሽነት አልሰጥም ልሰጥም አልችልም፡፡ የመስጠት መንገድ ከመጣ ያ ሽንፈት እና ሞት ነው“ ነበር ያሉት፡፡

ከዚህም በተጨማረ ማንዴላ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ከጠላትህ ጋር ሰላም ለማውረድ ከፈለግህ ከጠላትህ ጋር አብረህ መስራት አለብህ፡፡ ከዚያ በኋላ የአንተ ጓደኛ ይሆናል፡፡“

ፕሮፌሰር መስፍን በቅርቡ በአማርኛ በጻፉት፣ “በእኔ ግምት አሁን በእርሱ ላይ ጠንካራ የሆነ ተቃውሟቸውን የሚገልጹ ሰዎች በኋላ ወደ እርሱ ደጋፊነት ይሸጋገራሉ“ በሚለው ትችት ውስጥ ማንዴላ በአእምሯቸው ውስጥ መኖራቸውን ያሳያል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንደ ማንዴላ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ መሰረታዊ የሆነ የብሩህ ተስፋ ባለቤት መሆን አለባቸው፡፡

ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ከመንግስት ባለስልጣኖች ጋር በቴሌቨዥን ወይም በኢንተርኔት መወያየት ይችላሉን?

የጨለማው ጎን ኃይሎች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ አሜሪካ እየመጡ ነው በማለት ቧልት በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህንን አሉባልታ ሊደግፍ የሚችል ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ ውስጥ እያሉ ውቅያኖስን አቋርጠው ዲያስፖራውን ለማግኘት የሚያደርጉት ጉዞ በጣም አጠራጣሪ ጉዳይ ነው፡፡

ሆኖም ግን ለትክኖሎጂ ምስጋና ይግባው እና እርሳቸው በሚፈልጉበት ጊዜ በኢንተርኔት የቪዲዮ ጉባኤ ግንኙነት ማድረግ ይችላሉ፡፡ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንን በቀጥታ እንዲሳተፉ ለማድረግ የተለያዩ አማራጮች እና ቴክኖሎጂዎች አሉ፡፡ የርቀት የስልክ ጥሪዎችን ከማድረግ በላይ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ሲያደርጉት እንደቆዩት ሁሉ ከዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንም ጋር መወያየት ይችላሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት እና በዲያስፖራው መካከል ተቋርጦ የቆየውን ሁኔታ መጠገን ይችላሉ፡፡ በጥርጣሬ ምክንያት ከተሳትፎ ታግተን የቆየነውን ሰዎች ችግር ማስወገድ ይችላሉ፡፡ ትርጉም ባለው ሁኔታ እንዲሳተፉ እና ወደ ትውልድ ሀገራቸው በመመለስ በሀገሪቱ የፖለቲካ ህይወት ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ማድረግ ይችላሉ ወይም ደግሞ ካለንበት ከየትም ሀገር ሆነን መሳተፍ እንችላለን፡፡ የእኛን ስጋቶች ማዳመጥ አለባቸው፡፡ የእኛን ጥያቄዎች መመለስ እና የእርሳቸውን ስጋቶች እና ጉዳዮች ከእኛ ጋር በመወያየት ማካፈል አለባቸው፡፡ የሰጥቶ መቀበል ሂደት ነው፡፡

በቅድሚያ የውይይት አጀንዳ መዘጋጀት ይችላል፡፡ ወይይቱ በሁለት ክፍሎች እንዲሆን ሀሳብ አቀርባለሁ፡፡ እነዚህም ስጋቶችን እና ጉዳዮችን በሚመከት ሀሳብ መለዋወጥ እና ለእነዚህ መፍትሄዎችን መፈለግ፡፡

በቴሌቪዥን እና በኢንተርኔት የሚደረገው ውይይት ጣት ለማስቀሰር፣ ጥርስ ለመንከስ፣ የሆድ ቁርጠት ለማስያዝ ወይም ደግሞ ጥላሸት የመቀባቢያ መድረክ አይደለም፡፡ ገንቢ ለሆኑ ውይይቶች እና መፍትሄ ፈላጊ መድረኮች ይሆናሉ፡፡ በጥሩ ሁኔታ የታቀደ እንደዚህ ያለ የቴሌቪዥን እና የኢንተርኔት ውይይት በጥንቃቄ የተዘጋጀ የድርገት መርሀ ግብር፣ የፖሊሲ ወረቀቶች እና የመፍትሄ ሀሳቦች የሚካተቱበት ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን እኔ ቀድሜ ሄጃለሁ…

ስለዚህ በመጨረሻ ባዘጋጀሁት ትችት መንፈስ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ምን ሊያደርግላቸው እንደሚችል እና እርሳቸው ደግሞ ለዲያስፖራው ምን ለማድረግ እንደሚችሉ እጠይቃቸዋለሁ፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቴሌቪዥን እና በኢንተርኔት የመወያየቱን ጉዳይ እኔ ኃላፊነቱን በመውሰድ ላስተባብር እችላለሁ፡፡ እንዲያውም እኔ የውይይቱ አሳላጭ መሆን እችላለሁ፡፡ ሆኖም ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውይይት አሳላጭነት የሚመርጡት ቆንጆ ይሆናል፡፡ ስራው እስከተሰራ ድረስ የቴሌቪዥን እና የኢንተርኔት ግንኙነት ውይይቱን ማንም ያዘጋጀው ም ንም  ችግር አይኖረውም፡፡

በአሜሪካ ሀገር እንደምንለው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን “እስቲ እንተግብረው” እላቸዋለሁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “ኢትዮጵያዊውን ከኢትዮጵያ ልታስወጡት ትችላላችሁ፣ ሆኖም ግን ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያዊው ልብ ውስጥ ልታወጧት አትችሉም“ የሚለውን ቃልዎን እና እኔም በሙሉ ልቤ የምደግፈውን እንዲያከብሩ አሳስበዎታለሁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሁላችንም የዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ማህበረሰቦች ሬይ ቻርለስ ጆርጂያ በአእምሯቸው ውስጥ እንዳለች ሁሉ እኛም በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮጵያ በአእምሯችን ውስጥ አለች፡፡

የሬይን ቃላት በመዋስ፡ ሌሎች እጆች ለእኔ ይደርሱልኛል፣ /ሌሎች ዓይኖች በደስታ ፈገግ ይላሉ፡፡ አሁንም በሰላማዊ ህልም እመለከታለሁ፣ /መንገዱ ወደአንቺ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ፣ ኦ ኢትዮጵያ እላለሁ/

(ቴዲ “አፍሮ” ካሳሁን አመሰግንሀለሁ!)

እኔ እራሴን የብሩህ ተስፋ ናፋቂ ነህ ወይስ ደግሞ ጨለምተኛ የሚል ጥያቄ ብጠየቅ በቀላሉ እንዲህ እላለሁ፣ በኢትዮጵያ ከአስራ ሶስት ዓመታት ገደማ ያህል እልህ አስጨራሽ የሰብአዊ መብት ትግል በኋላ ከመቸውም ጊዜ በላይ ጠንካራ እየሆነ የሚሄድ ጨለምተኛ ካለ እስቲ ሞክረው የሚል ይሆናል!

የኢትዮጵያ ሲኒ ግማሽ ሙሉ ወይም ግማሽ ጎደሉ መሆኑን ታምናለህ ወይ ተብየ ብጠየቅ መልሴ እንዲህ የሚል ቀላል ነው፣ “የእኔ የኢትዮጵያ ሲኒ ሞልቶ እየፈሰሰ ነው ” እላለሁ

ኃይል ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ለኢትዮጵያ መልካሙን ሁሉ ከምንመኝ ከሁላችንም ጋር ታላቁ ሃያል ይሁን!

ኢትዮጵያዊነት ዛሬ፡፡

ኢትዮጵያዊነት ነገ፡፡

ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም፡፡

 ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!    

ግንቦት 1 ቀን 2010 ዓ.ም