ማስታዋሻ ቁጥር 3፡ አብይ አህመድ ለኢትዮጵያ መስራት ስለሚችሉት ነገር አትጠይቅ፣ ይልቁንም አንተ ለኢትዮጵያ መስራት ስለምትችለው ነገር ጠይቅ!
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
“… ይኸ ሁሉ ነገር በመጀመሪያዎቹ መቶ ቀናት ውስጥ ሊጠናቀቅ አይችልም፡፡ ወይም ደግሞ በመጀመሪያዎቹ አንድ ሺ ቀናት ወይም በዚህ የአስተዳደር ዘመን ወይም በእኛ የእድሜ ዘመን ውስጥ ሊጠናቀቅ አይችልም፡፡ ሆኖም ግን እስቲ እንጀምረው፡፡“ ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ በፕሬዚዳንትነት የሹመት በዓላቸው ዕለት እ.ኤ.አ ጥር 1961 ዓ.ም ካደረጉት የመክፈቻ ንግግር የተወሰደ
የጸሐፊው ማስታወሻ፡ ይህ የማስታወሻ መልዕክት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እና ለኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከጸሐይ በታች ሁሉንም ነገር ሁሉ ከሰላሳ ቀናት ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንዲያጠናቅቁት በስሜት የሚጠይቁ ሰዎች አሉ፡፡
እርሳቸው ማከናወን የሚችሉት ነገር በመቶ ቀናት ውስጥ ወይም ደግሞ በአንድ ሺ ቀናት ውስጥ ወይም አሁን በህይወት ባለ በአንድ ኢትዮጵያዊ የህይወት ዘመን ወይም በዚህች ምድር በማንኛውም ጊዜ ላይከናወን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ታላቅ ጅማሮ አድርገዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አይነኬ መሳይ ጉደኞች እንደ መዥገር ተጣብቀውበት ከነበረው ስልጣናቸው ባልተጠበቀ እና በድንገተኛ ሁኔታ ቀስ በቀስ በገፍ እየወጡ የቀድሞውን የልቃቂት ተረቶቻቸውን እየፈተሉ እና እየገመዱ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማምከን በጨለምተኛ አስተሳሰቦቻቸው ውስጥ ተዘፍቀው ይገኛሉ፡፡ ኦ በእርግጠኝነት ይወድቃል ይላሉ፡፡ እርሳቸው ስራቸውን እንዲሰሩ አይፈቅዱላቸውም፡፡ በጥብቅ የቁጥጥር ሰንሰለት ውስጥ ያስቀምጧቸዋል፡፡ በካቢኒያቸው ውስጥ የወያኔ አለቆቻቸዉን በማስቀመጥ ተከበው ምንም ማድረግ አይችሉም፡፡ እናም እርሱ ጥሩ ጥሩ ዲስኩሮችን ያደርጋል ሆኖም ግን ምንም ነገር ማድረግ አይችልም ይላሉ፡፡ ሌላም በርካታ እርባና ቢስ እና አሰልች ነገሮችን ያደርጋሉ…
ላለፉት አስራ ሶስት ዓመታት ገደማ ያህል በእያንዳንዷ ዕለት እና በእያንዳንዷ ሳምንት መለስ ዜናዊ እና ህወሀትን ሰሞግት፣ ስሰብክ እና ሳስተምር በአሁኑ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ዙሪያ ጥምጥም ከበው በመጨቅጨቅ እና በመነዝነዝ ላይ ካሉት የተኩላ መንጋ ስብስቦች (የሚያሽካኩ ጅቦች ማለቱ የተሻለ ተመሳስሎ ሳይሆን ይቀራል?) መካከል ከእኔ ጎን በመቆም ለፍትህ እና ለርትዕ መከበር ሲል ድምጹን ከፍ አድርጎ በመጮህ ለህወሀት እውነትን የተናገረ አንድም ሰው አልነበረም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ባልተጠበቀ መልኩ በፍጥነት ብቅ ይሉ እና ማንነታቸውን በመደበቅ በብዕር ስም ይጽፉ እና በኢንተርኔት ይለቁ ነበር ምክንያቱም እነርሱ እንዲህ ፊት ለፊት በመጋፈጥ ለመሟገት አቅሙም ሆነ ድፍረቱ ስለሌላቸው ነው፡፡ አሁን ግን ከተደበቁበት ዋሻ እየወጡ የጨለምተኛ እና የተቃርኖ ወንጌላቸውን በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ በመስበክ ይገኛሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜ የተኩላው መንጋ ስብስብ ከመታጎሪያ የእስር ሰንሰለታቸው በመውጣት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከሰላሳ ቀናት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በውኃ ላይ እንዲራመዱ ብቻ ሳይሆን ያለክንፍ በሰማይ ላይ እንዲበሩ የውሸት ሸፍጣቸውን እውነት በማስመሰል ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ የቅጥፈት ጩኸታቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜ የድል አጥቢያ አርበኞች ፍልስፍናቸው ኢትዮጵያዊ በሆኑ እና ሰላምን፣ እውነትን እና ብሄራዊ ዕርቅን በሚሰብኩ በአንድ ወጣት ስር በመሆን በመዶለት ላይ ይገኛሉ፡፡
ስለእነርሱ ጉዳይ በቅርቡ እ.ኤ.አ ሀምሌ 2017 ዓ.ም ጽፊያለሁ፡፡ እጆቻቸውን በኪሶቻቸው አስቀምጠው ምን ማድረግ እንደሚችሉ አያውቁም እናም ምንም ዓይነት ነገር ማድረግ አንችልም ይላሉ፡፡ እነርሱ ዝም ብለው በመቀመጥ ጭራቃዊውን ስርዓት ሌሎቹ መፍትሄ እንዲሰጡት ይጠብቃሉ፡፡ ከልብ በመነጨ ሁኔታ እና ውጤት ሊያመጣ በሚችል መልኩ ምንም ነገር አይሰሩም፡፡ ለእነርሱ ሲባል ሌሎቹ መስዋዕትነትን እንዲከፍሉላቸው ይፈልጋሉ፡፡ ድል እንደሚገኝ እርግጠኛ በሚሆኑበት ጊዜ አብዛኞቹ ባልተጠበቀ እና በድንገተኛ ሁኔታ ብቅ በማለት የድል አጥቢያ አርበኛና ጀግኖች መሆን ይፈለጋሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ድል በምንም ዓይነት ሁኔታ አልተረጋገጠም፤ እነርሱ ግን አሁን እንደተረጋገጠ አድርገው ያምናሉ፡፡
በተሳሳተ መንገድ እንድትገነዘቡኝ አልፈልግም፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ለተቆለሉት ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት ሲባል ባወጡት እቅድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ቢተቿቸው ደስ ይለኛል፡፡ እንዲያውም ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አጠቃላይ የሆነ ዝርዝር የኢኮኖሚ ዕቅድ ቢነድፉላቸው ወይም ደግሞ የሕገ መንግስት ማሻሻያ ቢያደርጉ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለማስወገድ ሲባል የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስን እንደዚሁም በአሁኑ ጊዜ በመላ ሀገሪቱ ውስጥ ስር ሰዶ የሚገኘውን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ ጥረት ቢያደርጉ… እነርሱን በማድነቅ ከጎናቸው እሰለፋለሁ፡፡
አሰልች እና አታላይ አነብናቢ ተናጋሪዎች ሀሳቦቻቸውን በወረቀት ላይ የማስቀመጥ ችሎታ አንክዋን የላቸውም፡፡ ሆኖም ግን በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በተዘጋጁ በማናቸውም የፕሮጅክት ሀሳቦች ላይ እራሳቸውን ከፍ ከፍ እያደረጉ በመኮፈስ ባዶ መግለጫዎችን ለመስጠት ወይም ደግሞ ቃል ኪዳኖችን ለመግባት ከነፋሰ የፈጠኑ ይሆናሉ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር የስልጣን ዘመን የሁለት ጊዜ ብቻ ምርጫ ይሆናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነርሱ ደግሞ ኦ ይኸ የሰውን ቀልብ ለመሳብ የሚደረግ ጥረት ነው ይላሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የፈለገውን ያህል መልካም ነገር ይስሩ አይስሩ እነርሱ ግን ማዋረዳቸውን እና ሕጋዊነትን የማሳጣት ስራቸውን ይቀጥላሉ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አይነኬ መሳይ ጉደኞች ከሚፈጽሟቸው ድርጊቶች መካከል ሁለት ቀላል የሆኑ እውነታዎች ግልጽ የሚሆኑ ይመስላል፡፡ እነርሱም፤
1ኛ) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም፣ ብሄራዊ እርቅ እና ተስፋ የሚያመጡ እርምጃዎችን በመውሰድ ስኬታማ ከሆኑ እነዚህ ጉደኞች የሞት ያህል ይፈራሉ፡፡
2ኛ) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስኬታማ ከሆኑ የእነርሱ እጣ ፈንታ ይወድቃል፡፡ ለስልጣን፣ ለዝና፣ እና የበላይነትን እንደያዙ ለመቀጠል ያላቸው ጉጉት ፍጹም በሆነ መልኩ ይወድቃል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ አስቸኳይ ውድቀት ያመጣሉ ተብለው በሚሰጡት ትችቶች ላይ ትኩረት በማድረግ የሚከተሉትን የመከራከሪያ ጭብጦች አቀርባለሁ፣
1ኛ) በርካታዎቹን እርሳቸውን ከበው የሚጠብቁትን አሮጌዎቹን የካቢኔ አባላት በአጠገባቸው አስቀምጠዋል፡፡ እርሳቸው ሊወድቁ ይችላሉ ምክንያቱም እያደረጉት ያለው ነገር ወጡ እንዲጣፍጥ በሚል ተስፋ ወጡን ከአንዱ ምድጃ ወደ ሌላ ምድጃ በማዘዋወር እየጣዱት ይገኛሉ ነው እያሉ ያሉት፡፡
2ኛ) ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ንግግር ማድረግ እንጅ በተግባር የሚገለጽ ነገር በተጨባጭ አይታይም፡፡ የሚናገሩትን ነገር በተግባር እያዋሉት አይደለም ይላሉ፡፡
እንዴት ነው ጎበዝ! እንዲህ ከሰላሳ ቀናት ባነሰ ጊዜ ውስጥ?! ሱሪህን በአንገትህ አውጣ ዓይነት ነገር ለማንም አይጠቅምም!
እነዚህን የቀረቡትን ሁለቱንም የመከራከሪያ ጭብጦች ታሪካዊ ዳህራን የሳቱ በማለት እቀበላቸዋለሁ፡፡
እስቲ የኔልሰን ማንዴላን ካቢኔት እናስብ፡፡ የደቡብ አፍሪካ የጥቂት ነጮች ዘረኛ አገዛዘዝ አፓርታይድ ፕሬዚዳንት የነበሩት ኤፍ.ደብልዩ ዴክለርክ የማንዴላ ምክትል ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ስርዓት ውስጥ በርካታ የነጮች የፖለቲካ እና የንግድ ድርጅቶች መሪዎች በማንዴላ ካቢኔ ውስጥ በጣም ጠቃሚ የሚባሉ የስልጣን ቦታዎችን ተቆጣጥረው ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በማንዴላ የአስተዳደር ዘመን ጊዜ ነጮች የዳኝነት ስርዓቱን፣ የመገናኛ ብዙሃንን፣ የመንግስት ስራ (ሲቪል ሰርቪስ) አገልግሎቱን እና ኢኮኖሚውን በበላይነት ተቆጣጥረውት ነበር፡፡ የአፍሪካን ብሄራዊ ኮንግረስ በከፍተኛ ደረጃ ይቃወም የነበረው ማንጎሱዙ ቡቴሌዚ ከፍተኛውን የሚኒስቴር የስራ ኃላፊነት ቦታ ተቆጣጥሮ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ማንዴላ በመጨረሻው ሰዓት የደቡብ አፍሪካን ሰላማዊ የሕገ መንግስት ሽግግር እውን አድርገውታል፡፡
ማንዴላ በፈጸሙት ድርጊት የወድድቀት ዕጣ ፈንታን ተከናንበው ነበርን? ማንዴላ ለእውነት እና ለብሄራዊ ዕርቅ ሲሉ ያደርጉት የነበረው ንግግር በደቡበ አፍሪካ ውስጥ ትርጉም ያለው ፋይዳ ያላመጣ እንዲሁ ለታዕታ የሚደረግ ንግግር ነበርን? ማንዴላ ወድቀው የቀሩ መሪ ነበሩን?
እስቲ ሌላውን ደግሞ እንመልከት፣ የሚካኤል ጎረባቾቭስ ጉዳይ እንዴት ነበር?
የጎርባቾቭ ዋና ቅርብ እና ቁልፍ ባለስልጣኖች አስር የፕሬዚዳንታዊ ምክር ቤት አባላት እና የመጥፎ ዕድል ሟርተኞች የነበሩት የኬጅቢ ዋና ኃላፊ ቭላድሚር ክሪዩችኮቭ፣ ጽንፈኛ ብሄረተኛ የነበረው ቫለንቲን ጊ. ራስፑቲን፣ ጽንፈኛ የሰራተኛ ማህበር መሪ የነበረው ቬኒያሚን ኤ. ያሪን እና ምንም ዓይነት ለውጥ የማይቀበለው ግትሩ እና የጦር ፈረሰኛው የመከላከያ ሚኒስትር የነበረው ዲሚትሪ ቲ. ያዞቭ የተካተቱበት ነበር፡፡ ጎርቫቾቭ በመጨረሻም በግልጽነት (glasnost) እና በመልሶ ማዋቀር (perestroika) ፖሊሲያቸው የሶቪየት ህብረትን ሽግግር በሰላም አከናውነዋል፡፡
ታዲያ ጎርባቾቭ ሶቪየት ህብረትን በሰላም አላሸጋገሯትምን? የግልጽነት እና የማዋቀር (glasnost and perestroika) ፖሊሲዎቻቸውን በማራመዳቸው ውድቀት ደረሰባቸውን?
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከሰላሳ ቀናት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ምን ለማድረግ ይችላሉ?
ታማኙ እና መንፈሰ ጠንካራው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ተከራካሪ የሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ይህንን ጉዳይ በማስመልከት ባቀረቡት የአማርኛ ትችት እንዲህ በማለት ደህና አድርገው ገልጸውታል፣
“አብይ አሁን ገና መጀመሩ ነው፡፡ እራሱ እንዳለው የመጀመሪያ ተግባሩን ለማከናወን እየጀመረ ነው፡፡ ገና የመጀመሪያ እርምጃውን በመውሰድ ላይ ነው፡፡ መሮጡ ይቅር እና ቀስ እያለ እንኳ መራመድ አይችልም፡፡ በርካታዎቹ በጨለማው ውስጥ በመሆን አድፍጠው እርሱን ለመጣል የተዘጋጁ አሉ፡፡ ሕዝባችንን ከመጥፎ ሸፍጥ በመጠበቅ ሀገራችንን ወደ ተሻለ ስርዓት ያሸጋግራታል ብዬ አምናለሁ፡፡
በእኔ ግምት በእርሱ ላይ የመረረ ተቃውሟቸውን ሲገልጹ የቆዩ ሰዎች የእርሱ ደጋፊዎች ወደ መሆን ይሸጋገራሉ፡፡ እኔ እንደምገነዘበው በአጠቃላይ አብይ የሰራው ነገር ቢኖር የወያኔን የስልጣን መዋቅር በተለይም የወልቃይትን የአማራ ሕዝብ ቁስል መንካቱ ነው፡፡ እኛ በእርሰ ጉዳዩ ላይ ብንሆንም የወልቃይት ጠገዴ ውዝግብ የመጀመሪያውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ በቱርኮች እና በግሪኮች መካከል ተከስቶ የነበረው እና እስከ አሁንም ድረስ ምንም ዓይነት መፍትሄ ካላገኘው የሸፍጥ ውዝግብ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
የጎሳ ፖለቲካን እና የዘር ማንነትን አልፈን የምንጓዝ ከሆነ ሁለቱም በሽታዎች ፈውስን ያገኛሉ“ ነበር ያሉት፡፡
ሮም በአንድ ቀን ውስጥ አልተገነባችም፣ ኢትዮጵያም ብትሆን እንደዚሁ፣
አንድ የቀድሞ አባባል ሮም በአንድ ቀን ውስጥ አልተገነባችም ይላል፡፡ ሆኖም ግን ንጉስ ኔሮ በከተማዋ እሳት ለኮሰ ተብሎ በተወነጀለው መሰረት በአንድ ቀን ውስጥ እንድትወድም በማድረግ በምንም ዓይነት ሁኔታ ለምክር ቤቱ/ሴኔቱ ሳያማክር እና ጣልቃ ሳያስገባ እርሱ በሚፈልገው መልኩ እንደገና ሊገነባት ፈለጎ ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅት እኔ እያየሁት እና እየሰማሁት ያለው ኢትዮጵያን ለማቃጠል እራሳቸውን በሰየሙ የዘመኑ ንጉስ ኔሮዎች እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንደ ዋና የእሳት አደጋ አጥፊ ኃላፊ ሆነው ከእርሳቸው በኋላ ደግሞ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣት እሳት አጥፊዎች ሀገሪቱን ከመከራ ለማውጣት እና ወደ ሰላማዊ ህይወት ለማሸጋገር የተሰማሩበት የትግል መስክ ነው፡፡ አንደኛውን እሳት ሲያጠፉ ነገሮችን በእሳት ለማቃጠል ፍላጎቱ ያላቸው ሌላ እሳት ይለኩሳሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜ እያየሁት ያለው ነገር ከ11 ዓመታት በፊት “ትንሽዬዋ ዘማሪ ወፍ እና የጫካው እሳት፡ የዲያስፖራው የሞራል ትረካ” በሚል ርዕስ አቅርቤው ከነበረው ትችት ጋር አንድ ዓይነት ነው የሚል ትንበያ አድርጊያለሁ፡፡
ያ ትረካ አንድ ትንሽዬ ዘማሪ ወፍ በኩምቢዋ ውኃ እየቀዳች በእሳት ተያይዞ በመንቀልቀል ላይ የነበረውን የጫካውን እሳት ለማጥፋት ታደርገው የነበረውን ጥረት የሚተርክ ነው፡፡ ትላልቆቹ የጫካው እንስሳት የጫካውን እሳት እንዴት ለማጥፋት እንደሚችሉ አስቸጋሪ ሆኖባቸው በከባድ ሲተነፍሱ እና ምላሳቸውን እያወጡ ሲያለከልኩ ትንሽዬዋ ዘማሪ ወፍ በኩምባዋ ውኃ ከወንዝ እያመላለሰች እሳቱን ለማጥፋት ቆርጣ ተነሳች፡፡ በዚህ የውኃ ነጠብጣብ በእርሷ ኩምቢ እየተመላለሰ ያንን ያህል የጫካ እሳት ለማጥፋት መሞከሯ በግዙፎቹ የጫካው እንስሳት መሳቂያ እና መሳለቂያ ሆና ነበር፡፡ ትንሽዬዋ ዘማሪ ወፍ ግን “ማድረግ የምችለውን ብቻ አደርጋለሁ” የሚል ምላሽ ትሰጥ ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሌሎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሌሎች ትንሽዬ ዘማሪ ወፎች የታጀቡ ትንሽዬ ዘማሪ ወፍ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን ከእርስ በእርስ የጎሳ የጦርነት እሳት ለማዳን የቻሉትን ማንኛውንም ነገር ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ ከዳር ተቀምጠው የሚመለከቱ ትችት አቅራቢዎች ደግሞ ባዶ የሆነ ትችታቸውን ያጎርፋሉ፡፡ ቀኑን ሙሉ በከባድ ሁኔታ ሲተነፍሱ እና ሲያለከልኩ ሊውሉ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን ዋናው እሳት አጥፊ አብይ አህመድ እሳቱን ያጠፉታል ምክንያቱም የአምላክን ኃያልነት እና የአቦ ሸማኔውን ሰራዊት ከጎናቸው አሰልፈዋልና!
አብይ አህመድ ለኢትዮጵያ ምን ለመስራት እንደሚችሉ አትጠይቁ ይልቁንም እናንተ ለእናንተይቱ ኢትዮጵያ ምን እንደምትሰሩ ጠይቁ፣
1ኛ) ከዘመናት ትውልድ ጀምሮ ሲጠራቀሙ እና ሲቆለሉ የቆዩትን የኢትዮጵያ ችግሮች በሙሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሰላሳ ቀናት ባነሰ ጊዜ ውስጥ መፍትሄ ለመስጠት የሚችሉ ብቸኛው ሰው እና ኃላፊ እርሳቸው ናቸውን?
2ኛ) ለችግሮች ሁሉ ሁሉም መልሶች ያሏቸው ብቸኛው ሰው እርሳቸው ብቻ ናቸውን?
3ኛ) ኢትዮጵያን ከምጽዓት ቀን ለማዳዳን የተላኩ ብቸኛው መሲህ እርሳቸው ብቻ ናቸውን?
4ኛ) ለእነዚህ ከላይ ለቀረቡት ሶስት ጥያቄዎች መልሱ ባዶ እና የለም የሚል ነው!
እነዚህን ጥያቄዎች በማስብበት ጊዜ ከልጅነት ዘመኔ ጀምሮ እስከ ዛሬም ድረስ በህይወት ዘመኔ ሁሉ የሚያስደንቀኝን እና እ.ኤ.አ በ1961 ዓ.ም ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ. ኬኔዲ በፕሬዚዳንትንት የሹመት በዓላቸው ዕለት ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስታውሳለሁ፡፡
ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ፕሬዚዳንት ኬኔዲ “ነጻነትን እና ለውጥን እያከበሩ” ነበር፡፡
የሰው ልጅ ሁሉንም ዓይነት ድህነት እና ሁሉንም ዓይነት የሰው ልጅ ህይወት ለማጥፋት የሚያስችል ስልጣን ባለው እና በሚሞተው እጁ ውስጥ ስላለችው “ልዩ ስለሆነችው ዓለም” ተናግረዋል፡፡
እንደዚሁም ሁሉ አንድ ዓይነት አብዮታዊ እምነት ሆኖ ስለሚገኘው እና በዓለም ዙሪያ ያሉ ቀደምቶቻችን ሲዋጉለት ለቆዩት እና አሁንም ቢሆን ጉዳያችን ሆኖ የሚገኘው የሰው ልጆች መብት የሚገኘው ከመንግስት ሩህሩህነት አይደለም፤ ሆኖም ግን መብታችን የሚገኘው ከአምላክ እጅ ነው በማለት ተናግረዋል፡፡
እንዲህ በማለት አውጀዋል፣ “ከዚህ ጊዜ እና ቦታ ጀምሮ ለጓደኞቻችን እና ለጠላቶቻችን የሚመላለስ ቃል እንዲህ በማለት እንዲተላለፍ እንፍቀድ፣ ይህች ሀገር ሁልጊዜ ለምትተጋለት እና እኛም በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን እና በዓለም ዙሪያ ሁሉ እየታገልንለት ላለነው ሰብአዊ መብት እንዲደፈር ለማይፈቅዱ ወይም ደግሞ አፈጻጸሙ ዘገምተኛ እንዲሆን ለማይተጉ ለአዲሱ አሜሪካውያን ትውልድ ጧፉ ተላልፏል“ ነበር ያሉት፡፡
ለአፍሪካውያን እና ለሌሎች በቅኝ ግዛት ጭቆና ከሰብአዊነት ውጭ ተደርገው ለዘመናት ሲሰቃዩ ለቆዩት እንዲህ የሚል ዘመን የማይሽረው መልዕክት ነው፣ “ነጻ መንግስታት እንድትሆኑ እኛ ያገዝናችሁ አዲሶቹ መንግስታት ሁሉ መራራው የቅኝ ግዛት የቁጥጥር አስተዳደር በጣም በበለጠ እና በጨቋኝ አገዛዝ መተካት የለበትም፡፡ እኛ ሁልጊዜ የእራሳችንን ሀሳቦች በመደገፍ እንድትቀመጡ ብቻ አንጠብቅም፡፡ ሆኖም ግን ሁልጊዜ የእራሳቸውን ነጻነት ለመጠበቅ ኃይለኞች እንዲሆኑ ጠንካራ ድጋፈችንን እንሰጣለን፡፡ እናም ቀደም ሲል በቂልነት ስልጣናቸውን ለማጠናከር በማሰብ በነብሩ ጀርባ ላይ ሆነው ሲጋልቡ የነበሩ ሁሉ በመጨረሻ ጊዜ ከነብሩ ጀርባ ወርደው በሆዱ እንደሚገለበጡ ሊያስታውሱ ይገባል፡፡“
ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ በማለት ተማዕጽኗቸውን አቅርበዋል፣ “በመሬት ላይ ያለን ሕዝቦች ሁሉ አንድ እንሁን፡፡ የነብዩ ኢሳያስን ትዕዛዝ በማክበር፣ “በሰዎች ላይ ከባድ ሸክምን አንጫን፣ የተበደሉት ነጻ እንዲወጡ እንፍቀድ፡፡“ በአንተ አማካይነት ጓደኞቼ የመጨረሻውን ስኬት ይጎናጸፋሉ ወይም ደግሞ በመንገዳችን አብረን እንወድቃለን“ በማለት ተንብዮአል፡፡
ከዚያ በኋላም ጊዜ የማይሽራቸው እና የማይሞቱ ሁለት እንዲህ የሚሉ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፣
1ኛ) እናም አሜሪካውያን ወገኖቼ፣ ሀገራችሁ ለእናንተ ምን እንዳደረገችላችሁ አትጠይቁ፣ ይልቁንም እናንተ ለሀገራችሁ ምን ለማድረግ እንደምትችሉ ጠይቁ፣
2ኛ) በዓለም ላይ ያላችሁ ወገኖቼ ሁሉ፣ አሜሪካ ለእናንተ ምን ለመስራት እንደምትችል አትጠይቁ፣ ሆኖም ግን ለሰው ልጆች ነጻነት ሁሉ ሁላችንም በአንድነት ሆነን ምን ለመስራት እንደምንችል ጠይቁ (አህጽሮት ተጨምሯል) ነበር ያሉት፡፡
በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲህ የሚሉ ጥያቄዎችን አቀርባለሁ፣
አብይ አህመድ ለኢትዮጵያ ምን ለመስራት እንደሚችሉ አትጠይቁ፣ ይልቁንም እናንተ ለኢትዮጵያ ምን እንደምትሰሩ ጠይቁ፣
ለአስራ ሶስት ዓመታት ገደማ ያህል በኢትዮጵያ ውስጥ ለሰብአዊ መብት መከበር፣ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መስፈን እና ለሕግ ልዕልና መከበር ሳደርገው በነበረው አልህ አስጨራሽ ትግል በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብት ሲደፈጠጥ ምስክር ለማይሆኑ እና ለማይፈቅዱ ለኢዮጵያውያን አዲሱ ትውልድ ጧፉ ተሸጋግሯል፡፡ ይህም ትውልድ የእኔ የጉማሬው (የቀድሞው ትውልድ) ሳይሆን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የአቦ ሸማኔው (አዲሱ ትውልድ) ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ በእነርሱ ስኬታማነት እና ውድቀት ላይ ተንጠልጥሎ ይገኛል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ትውልድ ስኬታማ እንዲሆን የምችለውን ማንኛውንም ነገር ሁሉ አደርጋለሁ ምክንያቱም የመንግስት ውድቀት፣ የፖለቲካ ውድቀት፣ የኢኮኖሚ ውድቀት እና የማህበራዊ ውድቀት ለኢትዮጵያ ምርጫዎች አይደሉምና!
ለእራሴ እውነት በመናገር ሊታለፍ የማይገባውን እና እንዲህ ሚለውን ጥያቄ በመጠየቅ መልሱን እራሴ እሰጣለሁ፣ “ለእኔይቱ ኢትዮጵያ ምን ለማድረግ እችላለሁ?”
ይህንን ጥያቄ በእራሴ ቃላት ልመልሰው፡፡
አሁን በቅርቡ ከኢትዮጵያ የንግዱ ማህበረሰብ ጋር በተደረገ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ግልጽ የሆኑ እና በእኔ ላይ በጥልቀት ያሚያቃጭሉ በርካታ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡ ለንግዱ ማህበረሰብ ዋና ቁንጮዎች እውነትን ተናግረዋል፡፡
ስለውጭ ምንዛሬ እጥረት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዲህ ብለዋል፣
“…የውጭ ምንዛሬ ለማመንጨት ትልቅ ችግር አለብን፡፡ ዱባይ ውስጥ አጭቃችሁት የሚገኘውን ገንዘብ (ዶላር፣ ኢውሮ) አሁን እንድትመልሱት ተማጽዕኖዬን ለማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ከሆነ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግሮች ጋር ተፋጥጠን እንገኛለን፡፡ ችግሩ ያለብን እንደ መንግስት ሳይሆን እንደ ሀገር ነው፡፡ እናንተ አሁን እንድታግዙን እንፈልጋለን፡፡ ለምን ብላችሁ ብትጠይቁኝ ይህንን ለእናንተ ለመግለጽ እስቲ አንድ ተመሳስሎ ልጠቀም፡፡ እናታችሁ ብትታመም እና ልጆቿ ከህመሟ መፈወስ እንድትችል የማያግዟት ከሆነ በመቃብሯ ላይ መገኘት ምንም ዓይነት ትርጉም የለውም፡፡ ሀገራችን በታላቅ ችግር በተለይም በውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግር ውስጥ ናት፡፡ መንግስት የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል ሆኖም ግን ከሀገሪቱ በሕገ ወጥ መልክ ወደ ውጭ ሀገር የወጣውን ገንዘብ ወደ ሀገር እንድትመልሱት ለእናንተ ተማዕጽኖዬን አቀርባለሁ፡፡ ከጓደኞችም ይሁን ከዘመዶቻቸሁ ወይም ደግሞ ከየትም ይሁን ካስቀመጣችሁበት የምትመልሱት ቢሆን ችግር የለውም፡፡ ገንዘቡን ወደ ሀገር መልሱት ስል ምን ማለቴ እንደሆነ በእርግጠኝነት ይገባችኋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህንን የማታደርጉ ከሆነ ችገሩ በቀላሉ የሚፈታ አይሆንም፡፡ ለዚህም ነው ወደ እናንተ የመጣነው እና በትልቅ ችግር ውስጥ ነን እርዱን እያልን ያለነው፡፡ ገንዘብ ስጡን አላልንም፡፡ እኛ እያልን ያለነው ከሀገሪቱ ያወጣችሁትን ገንዘብ መልሱት እና የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት ሕዝቡን እርዱት ነው፡፡ አሁን የምትረዱን ከሆነ በሌላ ጊዜ እርዱን እናንተ በችግር ላይ በነበራችሁበት ጊዜ እረድተናችኋል በማለት በችግሮቻችሁ ጊዜ እንድንደርስላችሁ ልትጠይቁን ትችላላችሁ፡፡ በእርግጠኝነት በአሁኑ ጊዜ ልትረዱን ይገባል፡፡ በእጃችን የሌለውን የውጭ ምንዛሬ እንድንሰጣችሁ መጠየቁ ዋጋ የሌለው ነገር ነው፡፡ ልትመልሱት ይገባል…
በዱባይ እና በቻይና ብዙ ገነዝብ አጭቀው የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ መጠነ ሰፊ የሆነ ሀብት፡፡ ገንዘቡን ወደ ሀገር እንዲመልሱት እየጠየቅናቸው ነው፡፡ በነገራችን ላይ ቻይናዎች ዜጎቻቸው ከሀገራቸው ውጭ ገንዘብ ሲያስቀምጡ ያላቸውን ስልጣን ሁሉ በመጠቀም ወደ እነዚያ ሀገሮች በመሄድ ገንዘቡን ወደ ቻይና እንዲመልሱ ያደርጋሉ፡፡ እዚያ ደረጃ ላይ አልደረስንም ሆኖም ግን ወደዚያ መድረሳችን አይቀርም፡፡ ከሀገር እያሸሻችሁ በውጭ ሀገር ሀብት የምታከማቹ እዚያ የመሄዳችን ነገር የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ትክክለኛ መፍትሄ የመገኘቱ ሁኔታ የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው… ገንዘቡ የሚመለስ ከሆነ በርካታ ችግሮችን ያስወግዳል…“ ነበር ያሉት››
መዋዕለ ንዋን ስለማፍሰስ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዲህ ብለዋል፣
“…ኢትዮጵያ የውጭ መዋዕለ ንዋይ ትፈልጋለች፤ በተለይም በአሁኑ ጊዜ፡፡ የውጭ ካፒታልን መሳብ ካልቻልን የአዘጋጀናቸውን የልማት ዕቅዶች ተግባራዊ ማድረግ አንችልም፡፡ ቀጥተኛ የውጭ መዋዕለ ንዋይ ጠቀሜታ የሁሉም ሀገሮች ልምድ እንደሚያሳየው ነው፡፡ ሁሉም እራሳቸውን በማልማት ስኬታማ የሆኑ ሀገሮች የውጭ ካፒታልን ይስባሉ እናም የእራሳቸው የልማት ዕቅድ አካል አድርገው ይይዛሉ፡፡ የውጭ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች በርካታ ጥቅሞችን ይሰጣሉ፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ዓለም አቀፋዊ የገበያ ተደራሽነት እንዲኖረን አስፈላጊዎች ናቸው እናም ይህ ተደራሽነት አስቸጋሪ እንደሆነ ሁላችሁም የምታውቁት ነገር ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ለቴክኖሎጅ ሽግግር እንፈልጋቸዋለን፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ስንቶቻችን ነን ከፍተኛ የሆነ ቴክኖሎጅ ውጤቶች የሆኑ ውድ ተሸከርካሪዎች ያሉን እናም ብልሽት በሚያጋጥማቸው ጊዜ ዝም ብለው ያቆሟቸዋል ወይም ደግሞ ወደ ዱባይ በመርከብ ይጭኗቸዋል ምክንያቱም እንደዚህ ያሉትን ተሽከርካሪዎች በሀገር ውስጥ ለመጠገን ችሎታው የለንም፡፡ የውጭ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ይዘዋቸው ከሚመጡት ቴክኖሎጂዎች ልጆቻችን ዘመናዊ ከፍተኛ የሆነ ቴክኒክ እና ልምድ ይቀስማሉ፡፡ በሶስተኛ ደረጃ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች የተለዬ የስራ ባህል ይዘው ይመጣሉ፡፡ እንዴት ባለ ባህላዊ አሰራር እንደምንሰራ እና እነሱ እንዴት እንደሚሰሩ ሁላችሁም ታውቃላችሁ፡፡ ከእነርሱ ስርዓት ካለው የስራ ባህል ጥሩ የስራ ባህል እንማራለን፡፡ በአራተኛ ደረጃ በጣም የሚፈለገውን የውጭ ምንዛሬ እንድናገኝ ይረዱናል፡፡ ስለሆነም እነርሱን ወደ ሀገር ቤት እንዲመጡ መጋበዝ እና ከእነርሱ ጋር ህብረት በመፍጠር መስራት ነው…“ ብለዋል፡፡
ከውጭ ስለሚላክ ገንዘብ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዲህ ብለዋል፣
“….ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር በተመሳሳይ መልኩ የህዋላ ገንዘብ እጥረትም ይታያል፡፡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶችም ሆኑ ተራ የሆኑ ስራዎችን የሚሰሩ ሰራተኞች የህዋላ ገንዘብ ወደ ሀገራቸው የሚልኩት ገንዘብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ዜጎቻቸው በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ጥቂት የአፍሪካ ሀገሮች መካከል አንዷ ናት፡፡ በርካታ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በዓለም ዙሪያ ሁሉ ተበትነው ይገኛሉ፡፡ ወደ ሀገራችን የሚገባው የህዋላ ገንዘብ በጣም ትንሽ ነው፡፡ እኛ በህዋላ ወደ ሀገር ውስጥ ከሚላከው ገንዘብ የበለጠ ናይጀሪያ በ500% እና ግብጽ በ300% ከእኛ የበለጠ ገንዘብ ያገኛሉ፡፡ ይህንን ጉዳይ አነሳዋለሁ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ የእኛን ውይይት ሊያዳምጡ ስለሚችሉ ስለሁኔታው እንዲያስቡ ለማድረግ ነው፡፡ ገንዘብ ወደ ሀገር ውስጥ ለመላክ መወሰን ወይም ደግሞ የህዋላ ገንዘብ እንዳይመጣ መከልከል መንግስትን ይጎዳዋል ማለት አይደለም፡፡ መንግስት እናንተን የማያስደስት ስራ ሲሰራ የህዋላ ገንዘብ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይላክ ማድረግ ተገቢ የሆነ ቅጣት አይደለም፡፡ አንድ ህጻን አንድ ስህተት የሆነ ነገር ሲሰራ ህጻኑን ለመቅጣት እራት መከልከል ተገቢ ቅጣት አይደለም፡፡ እራት እንሰጣቸዋለን እናም እንደ አሮጌው ባህል አርጭሜ ወይም ደግሞ እንደ አዲሱ አካሄድ ለትንሽ ጊዜ ጸጥ በማለት እንቀጣቸዋለን፡፡ እራት በመከልከል የምንቀጣቸው ከሆነ የሚያስከትለውን መዘዝ ታውቁታላችሁ፡፡
የዲያስፖራው ማህበረሰብ ገንዘብ ወደ ሀገር ውስጥ ባለመላክ መንግስትን እንቀጣለን በሚሉበት ጊዜ ማን ነው ሊጎዳ የሚችለው? የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማመንጨት የማይችሉት ትናንሾቹ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ናቸው ሊጎዱ የሚችሉት፡፡ ሆኖም ግን እንደ እናንተ ያለው በደህና ደረጃ ላይ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ከፍተኛ የምንዛሬ ለውጥ በመክፈልም ቢሆን ከጥቁር ገበያ ታገኛላችሁ፡፡ ድሆች ያንን ለመክፈል አቅም የላቸውም፡፡ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውን በጽሁፍ ትችት፣ በሰላማዊ ተቃውሞ እና የክርክር መድረክ በመክፈት መንግስትን ማስፈራራት ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን ወደ ሀገር ውስጥ በህዋላ የሚላከውን ገንዘብ መከልከል በአጠቃላይ ሀገሪቱን ይጎዳል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ልናስብ ይገባል፡፡ የህዋላ ገንዘብ እንዲጨምር ለማድረግ በአንድ ላይ ሆነን መስራት አለብን፡፡ ወደ ሀገር ውስጥ የሚላከው ገንዘብ እያደገ ሲሄድ በተወሰነ ደራጃም ቢሆን የውጭ ምንዛሬ ችግርን ሊቀርፍ ይችላል“ ብለዋል፡፡
ስለኢትዮጵያ የውጭ ገጽታ ግንባታ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዲህ ብለዋል፣
“ኢትዮጵያ በበርካታ ሀገሮች ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደሮች አሏት፡፡ እነዚህ አምባሳደሮች ብዙ ለመስራት አይችሉም ወይም ደግሞ ብዙ ነገር አልሰሩም፡፡ የዲፕሎማሲ ስራ እየተሰራ ያለው በኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ እና እንደ እናንተ ባሉት የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ነው፡፡ በሄዳችሁበት ሁሉ ግልጽ የሆነ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ኮሚሽን ባይኖራችሁም ቅሉ በተቻለ መጠን የኢትዮጵያን ገጽታ ለማሻሻል የተቻላችሁን ሁሉ ጥረት ማድረግ አለባችሁ፡፡ በንግግሮቻችሁ እና በምትሰሩት ስራ ሁሉ የሀገራችንን በጎነት ማሳየት አለባችሁ፡፡ በይፋ በተመደቡት አምባሳደሮቻችን ብቻ ቱሪስቶችን እና መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾችን መሳብ አንችልም፡፡ ጥቂት የአፍሪካ ሀገሮች ገጽታን የሚገነቡ ቢሮዎችን በአውሮፓ በመክፈት በሚያገኟቸው መልካም መረጃዎች በመጠቀም የቱሪዝምን እና መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾችን ቁጥር ለመጨመር ችለዋል…
ስለሀገራችን መጥፎ ነገሮች ከተነገሩ ሌሎች ህዝቦች እዚህ አይቆዩም እናም አይሳተፉም፡፡
በተቻለ መጠን ማድረግ ያለባችሁ ዋናው ነገር በዓለም ዙሪያ ሁሉ የኢትዮጵያን ገጽታ አሻሽሉ፡፡ ስለእኛ መንግስት ገጽታ አይደለም እየተናገርኩ ያለሁት፡፡ እተናገርኩ ያለሁት ስለኢትዮጵያ ገጽታ እና ያንን ገጽታ እንዴት አድርገን በአንድነት እንደምናሻሽለው ነው፡፡
መንግስትን ለመጉዳት በሚል ምክንያት የኢትዮጵን ገጽታ ጥላሸት መቀባት እና አሳንሶ ማየት የተሳሳተ አካሄድ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ገጽታ ለማሻሻል እስከ አሁን ድረስ ስታደርጉት ከነበረው የበለጠ ጥረት ማድረግ ያለባችሁ መሆኑን መገንዘብ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ ስለሆነም በተቻለ መጠን የኢትዮጵያን ገጽታ በመላው ዓለም ለማሻሻል ለሚደረገው ጥረት ብታግዙን ትልቅ ነገር ነው” ብለዋል፡፡
ቅንነት በተላበሰው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ንግግር እጅግ በጣም ተገርሚያለሁ ማለት እችላለሁ፡፡
እውነት ለመናገር በእውነታ ላይ የተመሰረተው ቅን ንግግራቸው የሀሳባቸው ምርኮኛ አድርጎኛል፡፡ እርሳቸው የሚያደርገውን የሚናገር እና የተናገረውን የሚያደርግ ዓይነት ሰው ናቸው፡፡ ምንም ዓይነት የማስመሰል ንግግር አላደረጉም፡፡ ነገሮችን ሁሉ እንዳለ እንደወረደ ነው የሚናገሩት፡፡ ምንም ዓይነት ነገር አልደበቁም፡፡ ከተሟላ ማክበር ጋር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንደ እኔ ሁሉ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ ሳያሳዩ መጥፎውን ነገር ሳይደብቁ በስልጣን ላይ ላሉት (ለእራሳቸው አስተዳደር)፣ የኢኮኖሚ ኃይል ላላቸው፣ ለዲያስፖራው ማህበረሰብ፣ ለድሆች እና አቅም ለሌላቸው እውነታውን ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ግን እኔ ያንን ለማድረግ እችላለሁ ምክንያቱም ምንም ዓይነት የፖለቲካ ተልዕኮ ሳይኖረኝ እና ለአንድ ተልዕኮ ብቻ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነኝ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አነጋገር ይገርማል!
ሆኖም ግን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እያደረጉት ያለው ነገር እውነተኛ እና ያልተጠበቀ የክስተቶች እድገት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ሚና በሚናገሩበት ጊዜ እውነታውን ለእኔ እና ከኢትዮጵያ ውጭ ለምንኖረው ለሁላችንም ነው እየተናገሩ ያሉት፡፡
እውነት ለመናገር ለእኔ እና ለቀሪዎቻችን ትህትና በተቀላቀለበት መልኩ እኛ ስንሰጥ የነበረዉን መድሃኒት መለሰው ሰጥተዉናል፡፡
ላለፉት አስራ ሶስት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ በስልጣን ላይ ላሉት እውነትን ስናገር ቆይቻለሁ፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ በአደጋ ላይ ያለ መሆኑን ወደ ኋላ መለስ በማለት ጥሬ እውነቱን የሚነግሩን ወጣት መሪ አግኝተናል፡፡ እያንዳንዱን የምትናገሩትን አድርጉ ወይም መናገራችሁን አቁሙ እያሉ ይነግሩናል፡፡
ስለሆነም እንዲህ የሚሉ ሁለት ጥያቄዎች ብቻ አሉ፣ በዲያስፖራ ያለውን እውነታ በአግባቡ ለመያዝ እንችላለን? የምንለውን እናደርጋለን ወይስ ዝም እንላለን?
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተግዳሮቶች ላይ በመነሳት እና በማስወገድ ወደፊት መጓዝ እንችላለን?
ለኢትዮጵያ ምን ለማድረግ እችላለሁ?
ስለውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የካፒታል ፍልሰት፣
በኢትዮጵያ የካፒታል ወደ ውጭ ፍልሰት ለእኔ አዲስ የሆነ ነገር አይደለም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ ታህሳስ 2011 “ኢትዮጵያ፡ የሀገርን ሀብት በሙሉ መዝረፍ“ በሚል ርዕስ ትችት ጽፌ ነበር፡፡ የካፒታል ፍልሰቱ ሁኔታ አውዳሚ ነው፡፡ ግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ እ.ኤ.አ በ2009 ዓ.ም እንዲህ የሚል ዘገባ አውጥቶ ነበር፣ “የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሀብቶቻቸውን በመዘረፍ ላይ ናቸው፡፡ ከፍጹም እጦት እና ከድህነት ለመውጣት የቱንም ያህል ትግል ቢያደርጉም እንኳ በህገ ወጥ የገንዘብ ፍልሰት ማዕበል ውስጥ ከታች ወደ ላይ በመዋኘት ላይ ይገኛሉ” ነበር ያለው፡፡
እ.ኤ.አ ከ2000 እስከ 2009 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ውስጥ በህገ ወጥ የካፒታል ፍልሰት ኢትዮጵያ 11.7 ቢሊዮን ዶላር አጥታለች፡፡ እ.ኤ.አ በ2009 ለኢትዮጵያ የተጣራ የልማት እርዳታ በጠቅላላው 3.8 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡
ከኢትዮጵያ በህገ ወጥ መልኩ ቀደም ከነበረው ዓመት እጥፍ በመሆን እ.ኤ.አ በ2009 ዓ.ም 3.26 ቢሊዮን ዶላር በሙስና፣ በእጅ መንሻ እና በጉቦ አማካይነት ባክኗል፡፡
እ.ኤ.አ ከ2008 እስከ 2012 ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ ዓመታዊ አማካይ የካፒታል ፍልሰት 3.55 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በዚሁ ተመሳሳይ ጊዜ በኢትዮጵያ በህገ ወጥ መልክ የወጣው ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወደ ሀገር ውስጥ ከገባው ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 1,355% ያህሉን ይዞ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ2016 የተደረገ ጥናት እ.ኤ.አ በ2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቀደም ሲል የወጣውን እና ከወለድ የሚገኘውን ጨምሮ ከውጭ የብድር ክምችት በላይ በ7 ቢሊዮን ዶላር በመብለጥ 29.9 ቢሊዮን ዶላር የካፒታል ፍልሰት እንደነበር ያሳያል፡፡
ከካፒታል ፍልሰት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ መልኩ መረጃው ያለን ሰዎች ዱባይ እና ቻይና ብቻ አይደሉም ዋና መዳረሻዎች እና ሀገሪቱን በመዝረፍ ባዶ ያስቀሯት፡፡ ዩናይትድ ስቴትስም ሌላዋ መዳረሻ ናት፡፡
ስለካፒታል ፍልሰቱ በተለይም በዋናናነት ስለችግሩ ተጠያቂዎች ስለሆኑት በመናገር ጊዜ እና ብዕሬን ማባከን አልፈልግም፡፡ እኔ እና እኔን መሰሎች ሌሎች በአንድ ላይ ህብረት ፈጥረን ቢያንስ በዩናይትድ ስቴትስ ሀብት ለማስመለስ የሚደረግ ጥረት አለ፡፡
በዩናይትድ ስቴትስ የፍትህ መምሪያ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና የሀብት አስመላሽ ክፍል መምሪያ ከሀብት ብክነት እና ከጸረ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ማስገደጃ ጥረቶች ጋር በተያዘ የጋራ ስምምነት አለ፡፡ ዓለም አቀፉ የሕገ ወጥ ገንዘብ እና ሀብት አስመላሽ እረዳት ቡድን በዩናይትድ ስቴትስ በህገ ወጥ መንገድ የሚገኝን ህገ ወጥ ሀብት የውጭ መንግስታትን ፍርድ ቤቶች እገዛ እያደረጉላቸው ሀብቶቻቸውን ማስመለስ እንደሚችሉ እገዛ ያደርጋል፡፡
ከዚሁም በተጨማሪ አጭበርባሪ ተጽዕኖ ፈጣሪ እና ሙሰኛ ድርጅቶች ድንጋጌ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የተዘዋወሩ ሕገ ወጥ ሀብቶችን ማስመለስ የሚያስችሉ ሌሎች አማራጮች አሉ፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብት ለማሻሻል እገዛ የሚያደርውን የማግኒቲስኪ ድንጋጌ የሚጠቀሙበት የዩናይትድ ስቴትስ የሕዝብ ተወካዮች አባላት አሉ፡፡ ሀብት በማስመለስ ጥረት ላይ ያ ማለት ባለሁለት በኩል ሰይፍ ጎራዴ በመሆን ሊያገልግል ይችላል፡፡
እ.ኤ.አ በታህሳስ 2012 “ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ከጀግኖች አፍሪካውያን ጎን ትቆማለችን?” በሚል ርዕስ አቅርቤው በነበረው ትችቴ ፕሬዚዳንት ኦባማ ከማግኒቲስኪ ድንጋጌ ጋር እኩል የሆነ እና በቅድመ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር የነበሩትን የተወሰኑ አባላት ተጠያቂ እንዲሆኑ ተማጽዕኖ አቅርቤ ነበር፡፡ ኦባማ የእኔን ጥያቄ ወደ ጎን ገፋው፡፡
እ.ኤ.አ ጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ለፕሬዚዳንት ትራምፕ በጻፍኩት ደብዳቤ በማግኒቲስትኪ ድንጋጌ የቅድመ አብይ አስተዳደር በነበሩ የተወሰኑ አባላት ላይ ኢላማ ያደረገ ማዕቀብ እንዲጣል ጥይቂያለሁ፡፡ እ.ኤ.አ ታህሳስ 21 ቀን 2017 ፕሬዚዳንት ትራምፕ ድንጋጌው በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ሀገሮች ላይ ተግባራዊ እንዲሆን የማስፈጸሚያ ትዕዛዝ ፈረሙ፡፡ (ይህ ነገር እውን እንዲሆን ላደረጉ ሁሉ ይፋ ምስጋና የሚቀርብበት ጊዜ ይመጣል)
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሂደት እንደ ቻይና ሁሉ ኢትዮጵያም በሕገ ወጥ መልኩ ወደ ዓለም ሁሉ የተዛወረውን ገንዘብ ለማስመለስ ጠንካራ እርምጃ የምትወስድበት ጊዜ ይመጣል ብለዋል፡፡ ፈቃደኞች የሆኑ የህግ ባለሞያዎች ይህንን ጥረት ለማገዝ ሊደራጁ ይችላሉ፡፡
በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የኢትዮጵያን የተዘረፈ ሀብት በማስመለስ ጥረት ውስጥ የማግኒትስኪ ድንጋጌን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ተግባራዊ የሚሆኑ ጥቂት ሀሳቦች አሉኝ፡፡
ዩኤስ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን እርዳታ በሚመለከት ከብዙ ጊዜ ጀምሬ በጥብቅ ስቃወም ቆይቻለሁ፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ቅድመ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የነበረው አስተዳደር የአሜሪካንን ግብር ከፋይ ሕዝብ ዶላር ያለምንም ግልጽነት እና ተጠያቀኒት በሙስና ይጠቀሙበት ስለነበር ነው፡፡ ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ የሚሰጠው እርዳታ በእጅጉ እንዲቀንስ ጠንካራ የሆነ የመከራከሪያ ጭብጤን ሳቀርብ ቆይቻለሁ፡፡ የዩኤስኤአይዲ ዳይሬክተር የነበረችው ጋይሌ ኢ. ስሚዝ ከቅድመ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከነበረው አስተዳደር ጥቂት ግለሰቦች ጋር የቀድሞ ግንኙነት የነበራት መሆኑን በመግለጽ የድርጅቱ ዳይሬክተር እንዳትሆን ፊት ለፊት በቀጥታ ተቃውሜ ነበር፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የበለጠ ግልጽነት እና ተጠያቂነት ዋስትና እና በሙስና ላይ በሚወስዱት ቀጥተኛ እርምጃ እኔ እንደ ግለሰብ እና ከሌሎች ጋር አብሬ በመሆን ማንኛውንም የምችለውን ሁሉ በማድረግ ትክክለኛ የሰብአዊ፣ የአስቸኳይ እና የልማት እርዳታዎች እንዲተገበሩ ጥረት አደርጋለሁ፡፡ ሆኖም ግን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የዩኤስን እርዳታ ከሙስና፣ ከብክነት እና ከማጭበርበር ለመጠበቅ የሚያስችል የክትትል እና ግምገማ መሳሪያ በስራ ላይ ማዋል አለባቸው፡፡
ስለሚላክ የህዋላ ገንዘብ፣
በኢትዮጵያ ስለህዋላ ገንዘብ ጉዳዮች ጥቂት የማውቃቸው ነገሮች አሉኝ፡፡ እ.ኤ.አ ጥቅምት 2008 ዓ.ም “በኢትዮጵያ የህዋላ ፖለቲካል ኢኮኖሚ“ በሚል ርዕስ አቅርቤው በነበረው ትችቴ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር አድርገውት በነበረው ስብሰባ ያነሷቸውን በርካታ ጉዳዮች ዳስሸ ነበር፡፡ “የእኛ የህዋላ ዶላር ህዝቦቻችንን ያግዛል ወይስ ይጎዳል?” የሚል ጥያቄ አቅርቤ ነበር፡፡ በጊዜው የእኔ ስጋት ትኩረት ያደረገው በህዋላ የምንልከው ገንዘብ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘውን የአንድ ፓርቲ፣ የአንድ አምባ ገነን ፈላጭ ቆራጭ ሰው የኢኮኖሚ ጥንካሬ፣ ሀብታም ማድረግ እና እድሜውን ማራዘም ነው በሚል ነበር፡፡
በዚያ ትችቴ የቀረበውን ዳታ፣ ትንትና እና የክርክር ጭብጦች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዲመለከቱት እጋብዛለሁ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ እንደነበሩት ሁሉ አሁንም ጠቃሚዎች ናቸው ብዬ ስለማምን ነው፡፡
እ.ኤ.አ በ2016 ወደ ኢትዮጵያ በግለሰቦች የተላከው ህዋላ የሀገር ውስጥ ምርትን (ጂዲፒን) 1% ነበር፡፡
እ.ኤ.አ የካቲት 2018 አቅርቤው በነበረው ትችቴ ወደ ኢትዮጵያ ይላክ የነበረው ህዋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲቀንስ የተላለፈውን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ደግፊያለሁ፡፡ እናም ጸረ ህዋላ ለሆኑ ጥቂት ቡድኖች በቅድመ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በነበረው አስተዳደር ላይ የሕዝባዊ እምቢተኝነት እንዲተገበር እገዛዬን አድርጊያለሁ፡፡
እ.ኤ.አ በ1956 ዓ.ም ከሞንትጎሜሪ አውቶብስ ክልከላ ጀምሮ ለጨቋኝ አገዛዝ ሕዝባዊ እምቢተኝነት የሚያሽመደምድ ጠንካራ መሳሪያ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ቃላት በመዋስ የቀድሞውን አስተዳደር ለመቅጣት ክልከላን እደግፋለሁ፡፡
በእርግጥ ወደ ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጥበቃ ተሟጋችነት ተሳትፎዬን ከጀመርኩባት እ.ኤ.አ ሀምሌ 3 ቀን 2006 ዓ.ም በፊት በኢትዮጵያ ስለ ሕዝባዊ እምቢተኝነት እና ስለሰላማዊ ትግል እና ስለነጻነት ትግሉ፣ ስለዴሞክራሲው እና ስለሰብአዊ መብት መከበር ስላለው ጠቀሜታ 3 ክፍል ያለው ትችት ጽፌ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ መጋቢት 2006 የተግባር ሊግ የአዲስ አበባ አመራር ኮሚቴ ሰላማዊ የሆኑ ድርጊቶችን እንደ ዋና ዋና መንገዶችን መዝጋት፣ ስራ ማጓተትን፣ ት/ቤቶችን መዝጋትን እና በኢህአዴግ በአጋር ድርጅቶቹ አማካይነት የሚመረቱትን እና የሚሸጡትን ምርቶች ያለመጠቀም መግለጫ ከመስጠቱ በፊት ያንን ጥረት ማድረግ ጀመርኩ፡፡
እ.ኤ.አ በ2014 ዓ.ም የኮካኮላ ኩባንያ በኢትዮጵያ ጀግና በቴዲ አፍሮ ካሳሁን ላይ የንቀት እና አዋራጅ አያያዝ በማሳየቱ የምርት መጠቀም እገዳ እንዲደረግ ከሚለው ቡድን ጋር ተቀላቀልሁ፡፡ እ.ኤ.አ ሰኔ 2014 አቅርቤው በነበረው ትችቴ “ኮካኮላን ለምን እንደማልጠቀም” በሚል ርዕስ አንባቢዎቼ ሁሉ የኮካኮላን ምርት እንዳይጠቀሙ ጥሪ አቀረብኩ፡፡ የኮካኮላን ምርት እንዳልነካ ለእራሴ ቃል ገባሁ፡፡ ያም ቃል ኪዳን እስከ አሁን ድረስ እንደተጠበቀ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ነገሮች ሁሉ እንደተለወጡ እምናለሁ እናም የእኔን ሀሳቦችም መለወጥ አለብኝ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን አስተዳደር የምቀጣበት ምንም ዓይነት ምክንያት አይታየኝም፡፡ የህዋላ ገንዘብ እንዳይላክ መከልከል ተራ የሆነውን የሚታገለውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ሊለካ በማይችል መልኩ ይጎዳል እንጅ ጥቂት ሸፍጠኛ ወፍራም ድመቶችን አይጎዳም፡፡ እነዚህማ ከየትም የት ብለው የውጭ ምንዛሪያቸውን ያገኛሉ፡፡
ጉዳዩን ለዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ለማቅረብ እና የህዋላ ገንዘብ መላክ ክልከላ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲተው ለመጠየቅ ዝግጅቴን አጠናቅቂያለሁ፡፡ ነጥባችንን ከፍ እንዲል እና ግልጽ እንደሆን ማድረግ አለብን፡፡ የቀድሞ አባባል እንደሚለው ገንዘብ ይናገራል እናም የእኛ የህዋላ ገንዘብ ክልከላም ተናግሯል፡፡ እናም ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ በመስማት ላይ ናቸው፡፡
የእኔ ዋናው ስጋቴ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያን ህጻናት ከመታጠቢያው ውኃ ጋር እንዲወረውሯቸው አልፈልግም፡፡ ሕዝባችን ተጎድቷል እናም የህዋለው ገንዘብ ሁኔታውን ሊያሻሽለው ይችላል፡፡ እኔ ከእነርሱ ጎን በመቆም የህዋለውን ገንዘብ እቅባት እንዲነሳ መወትወትወቴን አላቆምም፡፡ ላለፉት 13 ዓመታት ያህል ሳደርገው እንደቆየሁት የሞራል ትግል ዓይነት ማለት ነው፡፡
ትንሽ ጥልቅ ትንፋሽ በመውሰድ የህዋላን ገንዘብ ማገዱን ወደኋላ እንድናደርገው ሁላችንንም የዲያስፖራ አባላት እጠይቃለሁ!
የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት እና የዩኤስ እርዳታ፣
እንደዚሁም ሁሉ በኢትዮጵያ ስለውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት እና ስለውጭ ጥቂት ነገሮችን አውቃለሁ፡፡
የቅድመ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደርን የኢንቨስትምነት ፖሊሲ እና እንዴት እየተተገበረ እንደሆነ የማጥናት ዕድሉ ነበረኝ፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ እና ስለሕጋዊ ማዕቀፍ ለማወቅ ይፈልጉ በነበሩ ኢትዮጵያውያን ምክር እንድሰጥ እጠየቅ ነበር ምክንያቱም በመጥፎ ሁኔታ ይስተናገዱ እንደነበር እና መዋዕለ ንዋያቸውንም ይዘረፉ እንደነበር ይሰማቸው ስለነበር ነው፡፡
ወደፊት በመሄድ በኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን የሚያሱ የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች በወደፊት የተወሰኑ የሕግ ጉዳቶች ላይ ምክር እንድሰጥ እጠየቅ ነበር፡፡
ወደፊት ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ መዋዕለ ንዋያቸውን ለሚያፈሱ የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ አላደፋፍራቸውም ነበር፡፡ ምክንያቱም የቅድመ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር በውጭ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ላይ በርካታ የሆኑ ሸፍጦችን ይሰራ ነበር፡፡
በማወጣቸው የሕዝብ ትችቶቼ ሁልጊዜ እንዲህ የሚል እመለከታለሁ፣ “የዜሮ ድምር ከሚጫወት ሰይጣን ጋር በምትጨወት ጊዜ አንተ ሁልጊዜ ታጣለህ እናም እርሱ ህይወትህን እና ነፍስህን ይወስዳል!“
እንግዲህ ያንን ነው በትክክለኛው መንገድ ሳይ ካራቱሪ እ.ኤ.አ በ2010 መዋዕለ ንዋዩን ለማፍሰስ ከመወሰኑ በፊት እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም የመከርኩት፡፡ እንዲህ በማለትም አስጠንቅቄው ነበር፣ “ነጻ ገጸ በረከት ከሚሰጡት ተጠንቀቅ“
በመጨረሻም ተስፋ የቆረጠው ካሩቱሪ በኢትዮጵያ ያለውን መብት ለማስከበር የህንድን ሃያልነት እንደሚጠቀም የማስፈራሪያ ዛቻ አቅርቦ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ መስከረም 2017 ዓ.ም “ሳይ ካሩቱሪ ነግሬህ ነበር ሆኖም ግን አልሰማኸኝም!“ በሚል ርዕስ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡ ከእርሱ ጋር ያደረግሁት ምክር ምን ያህል ትክክለኛ እንደሆነ አብራርቻለሁ፡፡ የካሩቱሪ ጉዳይ ለሌሎች የእኔን ምክር ለሚፈልጉ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ትምህርት ይሆናል፡፡
የእኔ ሀሳብ የቅድመ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ወጥመዶች አንድ ኢንቨስተር ባልጠበቀው መንገድ አንድ ቦታ ሄዶ መዋዕለ ንዋይ እንዲያፈስ መጋበዝ፣ ከመጠን በላይ ለሚስገበገቡት ኢንቨስተሮች ህገ ወጥ የጥቅም ግንኙነት ስምምነት መፈጸም እና የተጠየቁትን ያለምንም ተቃውሞ መስጠት፣ ነጻ ገጸ በረከት፣ ነጻ ገንዘብ ወይም በጣም ዝቅተኛ በሆነ የወለድ መጣኔ ብድር መስጠት፣ ግብር እንዳይከፍሉ ማድረግ እና ምንም ችግር የለም በማለት በጠራራ ጸሐይ መዝረፍ ነበር ዋና ዓላማቸው፡፡ ለእኔ ግልጽ በሆኑልኝ እውነተኛ መረጃዎች መሰረት በካሩቱሪ እና በሌሎች የውጭ እና የዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ላይ የተፈጸመው ይኸው ነበር፡፡
በቅድመ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አስተዳደር ከዚህ በከፋ መልኩ የተፈጸሙ ሌሎች የውጭ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ጉዳዮች አሉ፡፡ እ.ኤ.አ መስከረም 2018 ዓ.ም የእስራኤል ኬሚካል ኩባንያ ወደ 200 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ለሚሆን ገንዘብ ሄግ ለሚገኘው ፍርድ ቤት በኢትዮጵያ ላይ ክስ መሰረተ፡፡ ኩባንያው ሊያመርት ላቀደው የፖታሽ ማዕድን ማውጣት ፕሮጅክት አስፈላጊ የሆነው የመሰረተ ልማት አውታር እና የቁጥጥር ማዕቀፍ አልተፈጸመልኝም የሚል ውንጀላ ነው ያቀረበው፡፡
ዓለም ባንክ እ.ኤ..አ በ2018 “ቢዝነስ መስራት 2018“ በሚል ርዕስ ባዘጋጀው ዘገባ ኢትዮጵያ ቢዝነስ ለመስራት እ.ኤ.አ ከ2004 ዓ.ም ጀምራ ከ2900 በላይ የሚሆኑ የቁጥጥር ማዕቀፎችን አዘጋጅታለች ብሏል፡፡ የቁጥጥር ማዕቀፎቹ መዘጋጀታቸው ባልከፋ ሆኖም ግን በእርግጠኝነት በቅን ልቦና ተግባራዊ ሊደረጉ ይችላሉን? እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ታላቅ ጥርጣሬ አለኝ፤ ሆኖም ግን ስለዚህ ጉዳይ በሌላ ጊዜ ለውይይት የሚተው ይሆናል፡፡
የእኔ ሀሳብ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኢንቨስትመንት የቢሮክራሲ ውጣውረዱን ሊቆርጡት፣ ከውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ ማፈሰስ ዘርፍ ጋር በተያያዘ መልኩ የሚፈጸመውን ሙስናን መቀነስ፣ ለመዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች የባለሀብትነት መብት ጥበቃ እንዲረጋገጥ ማድረግ፣ ለእነርሱም የዕንባ ጠባቂ ተቋም ጽ/ቤት ማቋቋም እና ያለምንም የመንግስት ጣልቃገብነት ቢዝነሳቸውን እንዲሰሩ መፍቀድ ተገቢ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ተግባራዊ የሚደረጉ ከሆነ ወደፊት የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ ቢዝነስ ትንሽ ሊጨምር ይችላል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ አስተማማኝ የሆነ የአሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እና ነጻ የኢንተርኔት አገልግሎት ተደራሽነት እንዲኖር ማድረግ አለባቸው፡፡ እነዚህ ሁለት ነገሮች ወደፊት ለሚመጡ እና ከእኔ ጋር ምክክር ያደረጉት መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች እንደሰጡኝ መረጃ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገቡ አውቃለሁ፡፡
ስለኢትዮጵያ ገጽታ ግንባታ፣
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኢትዮጵያ በውጭው ዓለም ላይ መልካም ገጽታ እንዲኖራት እና በመንግስት እና በሀገር መካከል ያለውን ልዩነት መለየት ጠቃሚ ነገር ነው ብለዋል፡፡
ጠንካራ ድምጽ እንዳለው ዲያስፖራ ኢትዮጵዊ እና በርካታ የብዙሀን መገናኛ ተደራሽነት፣ እንዲሁም ካሉኝ በርካታ አንባቢዎቼ በመጠኑም ቢሆን የኢትዮጵያ ገጽታ ግንባታ መልካም ቅርጽ እንዲይዝ የእራሴን እገዛ አድሪጊያለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡
በቅድመ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር ላይ የማቀርበው ማቋረጫ የሌለው ተቃውሞ በኢትዮጵያ የገጽታ ግንባታ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አድርጓልን?
ይህንን ጥያቄ በትክክል ልመልሰው አልችልም፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ያለኝ ጠንካራ የሰብአዊ መብት ጥበቃን አቋም በአዎንታዊ መልኩ የሚመለከቱት ሰዎች እንዳሉ አምናለሁ፡፡ ሌሎች ደግሞ ከአገዛዙ ጋር የማደርገው ተቃውሞ ከሀገሪቱ መልካም ገጽታ ጋር ይቀላቀላል ወይም ይጋጫል የሚሉ አሉ፡፡
ሁለቱም ወገኖች ትክክል ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ጠንካራ የሰብአዊ መብት ውትወታ ስራ በአሜሪካ የሰለጠነ የሕግ ባለሙያ እና የሰብአዊ መብት ጥበቃ ዋና ሞያ ነው፡፡ እንደ ሕግ ባለሞያ በአሜሪካ ትክክል የሆነውን አንድ ወገን ብቻ እንድደግፍ ሆኘ ነው የሰለጠንኩት፡፡ በማናቸውም ግብረገባዊ ዘዴ በክርክር ለአንደኛው ወገን ስለማሸነፍ ጉዳይ ነው፡፡ በእኔ ሞያ ላይ ያሉ አንዳንድ ጊዜ ከሁለቱም ወገን ጋር ባልሆኑ ላይ ጉዳትን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዓለም ላይ የኢትዮጵያን ገጽታ ቅዱስነት እውነታ በሚናገሩበት ጊዜ እንደዚህ ያለ ሰፊ የብዙሀን መገናኛ ተደራሽነት እንዳለው ሰው የእኔ ሚና እና ኃላፊነት በኢትዮጵያ ላይ አሉታዊ ገጽታ እንዳይፈጠር የበኩሌን ድርሻ እንዳበረክት የሚያሳስበኝ ጉዳይ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ማለት የምችለው በኢትዮጵያ ላይ አሉታዊ ገጽታ እንዳይፈጠር በምችለው ሁሉ ጥረት ማድረግ አለብኝ፡፡
እውነት ለመናገር ስህተት ከሰራሁ ስህተቶቼን በህዝብ ፊት በአደባባይ የምቀበል እና ወዲያውኑ የማስተካክል ሰው ነኝ፡፡ ስህተቴን ያሳዩኝ እናም ከመቅጽበት አስተካክላለሁ፡፡ እኔ የስግብግብነት ባህሪ በፍጹም የለኝም!
ሆኖም ግን በአብዛኛው የኢትዮጵያ የገጽታ ግንባታ ችግር ጉዳይ ከቅድመ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ይመስላል፡፡
እ.ኤ.አ በ2016-17 የዩናይትድ ስቴትስ እና የእንግሊዝ መንግስታት ቢያንስ 5 የጉዞ ማስጠንቀቂያ እና ማስታወቂያዎችን አውጥተዋል፡፡ ጊዜው የቱሪስት ስብስብ 13 ወራት የጸሐይ ብርሀን ወደ ሚንጸባረቅባት እና የድንቅ ምድር ኢትዮጵያ የሚጓዙበት ነበር፡፡
አሁን በህይወት የሌለው እና የታላቁ አቀንቃኝ ሬጌ ኪንግ ማርሌይ ልጅ ዚጊ ማርሌይ ስለዚሁ ጉዳይ እንዲህ የሚል ሙዚቃ ጽፏል፣
13 ወራት የጸሐይ ብርሀን ወደምናገኝባት ወደዚያች ምድር ውሰዱን፣ ውሰዱን፣ ውሰዱን፡፡
በተራራዎቿ ላይ የሚወጣ እና በተቀደሰችዋ ቦታ የሚቆም ማን ነው፡፡ እራሶቻችሁን ቀና አድርጉ/
ኦ ጥንታዊ በሮች/13 ወራት የጸሐይ ብርሀን የተጎናጸፈች ናት፡፡ ወደ እርሷ ሂዱ፣ ወደ እርሷ ሂዱ፣ ወደ ዚያች ምድር ሂዱ/ ውኃ በነጻ ወደሚጎርፍባት/ ለመሆን እንፈልጋለን…
ቱሪዝም በኢትዮጵያ እየጨመረ ነው የመጣው፡፡
በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ2006 እስከ 2015 ያለው የ10 ዓመታት የቱሪስት ፍሰት ብዛት በሚከተለው ሰንጠረዥ ላይ ተመልክቷል
ተ.ቁ | ዓ.ም | የቱሪስት ብዛት | ተ.ቁ | ዓ.ም | የቱሪስት ብዛት |
1 | 2006 | 330,000 | 6 | 2011 | 358,000 |
2 | 2007 | 383,000 | 7 | 2012 | 427,000 |
3 | 2008 | 468,000 | 8 | 2013 | 523,000 |
4 | 2009 | 597,000 | 9 | 2014 | 681,000 |
5 | 2010 | 770,000 | 10 | 2015 | 864,000 |
እ.ኤ.አ ከጥቅምት 2016 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላ በኢትዮጵያ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እየቀነሰ መጣ፡፡
የቅድመ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር እ.ኤ.አ በ2016 ኢትዮጵያ 800,000 ቱሪስቶችን ተቀብላ በማስተናገድ ከ5.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማግኘቷን አስታውቋል፡፡
እ.ኤ.አ ጥቅምት 2016 ዓ.ም የቱሪዝም አንቅስቃሴው በ100,000 ዝቅ አለ፡፡ እንደዚህም ሆኖ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር እ.ኤ.አ በ2017 ዓ.ም የቱሪስቶችን ብዛት ወደ አንድ ሚሊዮን ከዚህ የሚገኘው ገቢ ደግሞ ከ29.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሆን ተስፋ አድርጎ ነበር፡፡
ሆኖም ግን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዳሰቡት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ በጣም ተፈላጊ ነው፡፡ ያ ሁሉ የጉዞ ማስጠንቀቂያ ተደርጎ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ እና ሌሎችም ችግሮች እያሉ ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳራሻ ምርጫ የመሆኗ ጉዳይ የሚሳካ አይሆንም፡፡
የነጠፈ እና የደረቀ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በአካባቢው ባለው የኢኮኖሚ አገልግሎት ላይ ከባድ ተጽዕኖን የሚያስከትል አውዳሚ ክስተት ነው፡፡
በአዲስ ስታንዳርድ እ.ኤ.አ መጋቢት 2017 በወጣ ታሪክ የቱሪዝም የንግድ ድርጅቶች ቱሪስት በሚመጣበት በከፍተኛው ወቅት ላይ 95% የነበረው የተመዘገበው ተጠቃሚ ቱሪስት የተሰረዘ መሆኑን ዘግቧል፡፡
የቅድመ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር በሎስ አንጀለስ፣ በኒዮርክ፣ በቶሮንቶ እና በሌሎች ከተሞች የቱሪዝም በዓላት፣ ኤግዚቢዥኖችን እና ወርክሾፖችን በማዘጋጀት እንዲሳተፉ ለማድረግ እና ቱሪዝምን ለማስፋፋት ይፈልግ ነበር፡፡ ‘የሰው ዘር መገኛ’ እና የጥቁር ዓባይ መነሻ በሚል መጠሪያ የቱሪዝም ድረ ገጽ ከፍተው የማስተዋወቅ ስራ ሲሰሩ ነበር፡፡ የትኛውም ዓይነት የሕዝብ ግንኙነት ስራ ውጤት አላመጣም፡፡ ቱሪስቶች ርቀው ቆይተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንደጠቆሙት የቱሪዝም ዘርፉ እየተዳከመ መምጣት በውጭ ምንዛሬ ግኝቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ ከውጭ የምናስገባቸውን ሸቀጦች እና አገልግሎቶች ለማሟላት የውጭ ምንዛሬ ጠቃሚ ነገር ነው፡፡
የቱሪዝም መዳከምን እንደገና ወደ ነበረበት መመለስ ይቻላልን?
በእርግጠኝነት!
መሰራት ያለበት የመጀመሪያው እና ዋናው ነገር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳት ነው፡፡
እንደዚሁም ሁሉ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ በኢሚግሬሽን ባለስልጣኖች ችግሮች እንዳሉ እና እንዲያውም በማስፈራራት ገንዘብ እንደሚቀበሉ በርካታ ተጨባጭነት ያላቸው ማስረጃዎች አሉኝ፡፡
ከዩኤስ አሜሪካ የጥናት ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት “ትምህርታዊ ቱሪዝምን” ማስፋፋት እንደሚቻል አምናለሁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ውስጥ የአካዳሚክ፣ የስኮላር እና ሳይንሳዊ ጉኤዎችን ማደራጀት ይቻላል፡፡ በአሜሪካ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የምንገኝ የቱሪዝሙን ጉድለት ለመሙላት በከፍተኛ ሁኔታ እገዛ ልናደርግ እንችላለን፡፡
ሁለት ዓይነት ኢትዮጵያውያን፡ የእኔን እውነታ ልናገር!
በአሁኑ ጊዜ ሁለት ዓይነት ኢትዮጵያውያን እንዳሉ አምናለሁ፡፡
የሮበርት ኬኔዲን ቃላት በመዋስ ነገሮችን ባሉበት ሁኔታ መመልከት የሚችሉ ኢትዮጵያውያን እና ለምን ይሆናል? ብለው የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከዚህ ቀደም ታይተው የማያውቁ ነገሮችን የሚያልሙ እና ለምን አይሆንም? በማለት የሚጠይቁ ናቸው፡፡ እኔ በሁለተኛው ቡድን ውስጥ እመደባለሁ፡፡
ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ለእኔ ጥያቄ ሆኖ ሊቀርብ የሚችለው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን መርዳት ወይም ደግሞ አንዳንድ ሰዎች እንደሚጠብቁት ሁሉንም ችግሮች በአንድ ጀንበር እንዲያስወግዷቸው እና በውኃ ላይ መራመድ ይችላሉ ብሎ ዝም ብሎ ማየት የሚለው ነው፡፡
ጥያቄ ሆኖ የሚቀርበው በሀገር ውስጥ ያሉት ኢትዮጵያውያን ወይም ደግሞ በውጭ ያለው የዲያስፖራ ማህበረሰብ ነገሮች በአሉበት ሁኔታ እንዲቀጥሉ እና ለምን ይሆናል በሚል ወይም ደግሞ ሌላው ቡድን ከዚህ ቀደም ታይተው የማያውቁ ነገሮችን ማየት እና ለምን አይሆንም የሚል ጥያቄን በሚያስተናግዱ ቡድኖች መካከል ከየትኛው ቡድን ይሆናሉ የሚለው ነው፡፡
ነገሮችን ባሉበት የሚያዩ እና ለምን በማለት ለሚጠይቁ ከዛሬ 50 ዓመታት በፊት እ.ኤአ. ሚያዝያ 5 ቀን 1968 ዓ.ም በዛሬው ወር የተለዩትን የሮበርት ኬኔዲን ቃላት በመዋስ፡
ብዙውን ጊዜ እብሪተኞችን እና ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ የሚጮሁትን እብሪተኞች እንደዚሁም ከትክክለኛው መንገድ የሚርቁትን እናከብራለን፡፡ ብዙውን ጊዜ በሌሎች የተሰበሩ ህልሞች ላይ የእራሳቸውን ህይወት የሚገነቡትን ሰዎች ይቅርታ እናደርጋለን፡፡ በውጭ ያሉ እና ሰላማዊ ትግልን የሚሰብኩ ጥቂት አሜሪካውያን እዚህ በሀገር ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ላይ ግን ይወድቃሉ፡፡ ጥቂቶች ሌሎችን ብጥብጥ በማነሳሳት በማለት የሚከሱ በራሳቸው ባህርይ ብጥብጡን እንዲፈጽሙ ይጋብዟቸዋል፡፡ ጥቂቶች የእነርሱን ጥፋት በኃላፊነት ሌሎች እንዲወስዱላቸው ይፈልጋሉ፣ ሌሎች ደግሞ መዶለትን ይፈልጋሉ፣ ሆኖም ግን ሁኔታው እንደዚህ ግልጽ ነው፡ ኃይል ኃይልን ይወልዳል፣ ጭቆና በቀልተኝነትን ያመጣል፣ እናም በመላ ሕዝቦቻችን ይህንን በሽታ ከመንፈሳችን በማስወገድ ማህበረሰባችንን ማጽዳት እንችላለን፡፡
እንዲህ የሚሉትን የሮበርት ኬኔዲ ቃላት በመዋስ ሀሳቤን እደመድማለሁ፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ዜጋም ሆናችሁ ወይም የዓለም ዜጋ ሆናችሁ እናንተን በጠየቅናችሁ ከፍታ እና የጥንካሬ መለኪያ እና በከፈልነው መስዋዕት ደረጃ ጠይቁን፡፡ በመልካም ህሊና ብቸኛው የእኛ እርግጠኛ ሽልማት ለሰራናቸው ስራዎች ዳኝነቱን የሚሰጠን ታሪክ ነው፣ 13 ወራት ሙሉ የጸሐይ ብርህን የሚያንጸባርቅባትን ምድር በፍቅር በመምራት የአምላክን ቅድስና እና እርዳታ እየጠየቅን ወደፊት መገስገስ ነው፡፡ ሆኖም ግን በዚህች በምድር ላይ የእግዚአብሄር ስራ በእውነተኝነት የእኛ መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዲህ ብለዋል፡ “የተናገርከውን አድርግ ወይም ደግሞ ዝም በል!”
እኔ ደግሞ “ለማገለግል ዝግጁ ሁን!” እላለሁ
ኢትዮጵያዊነት ዛሬ
ኢትዮጵያዊነት ነገ
ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ሚያዝያ 24 ቀን 2010 ዓ.ም