ማስታዋሻ ቁጥር 2፡ ሕዝብን ለሚያዳምጡ መልካም መሪዎች እውነትን እንዴት መናገር እንደሚቻል፣
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
የጸሐፊው ማስታዋሻ፣ ላለፉት ጥቂት ሳምንታት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ላይ የተሰነዘሩ አሳማኝ ያልሆኑ እና ኃላፊነት የጎደላቸውን ትችቶች ሳነብ እና ስሰማ ቆይቻለሁ፡፡ አብዛኞቹ በእርሳቸው ላይ ትችት የሚያቀርቡት እ.ኤ.አ በ1970ቹ በወጣትነት ጊዚያቸው ተጣብቀውበት ከነበረው የበከተ የፖለቲካ አስተሳሰብ እና ምንም ዓይነት ዴሞክራሲያዊ የለውጥ አስተሳሰብ የሌላቸው የሻገተ አስተሳሰብ በማራመድ ተቸክለው የቀሩ እንደ እኔ ያሉ የጉማሬው (የቀድሞው ትውልድ) አባላት ናቸው፡፡
እነዚህ ከግጭቱ ተርፈው በመኖር ላይ ያሉት ጥቂቶች ጉማሬዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ደስታ በተቀላቀለበት መልኩ እየደገፍኩ መሆኔን እንድተው ይመክሩኛል፡፡ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን እየደገፍኩ መሆኔ እስከ አሁን ድረስ በአንባቢዎቸ ልብ ውስጥ ገንብቸው የነበረውን የታማኝነትን መንፈስ ላጣው እንደምችል ይናገራሉ፡፡
እነዚህ ውንጀላዎች የተለመዱ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የህወሀት ሰው እና አሻንጉሊት ነው ይላሉ፡፡ አገዛዙ በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ ለመቆየት እንዲችል የሚያደርግ የህወሀት ድብቅ መሳሪያ ነው ይላሉ፡፡ ህወሀት ጠንካራ እና አይበገሬ ሆኖ እንደገና እስኪመለስ ድረስ ጊዜ ለመሸመት እና ወንበር እያሟሟቀ የሚቆይ ሰው ነው ይላሉ፡፡ እንዲያውም አንድ ሰው ከዚህም ባለፈ መልኩ በእነዚህ ባለፉት አስርት ዓመታት ሰምቸው የማላውቀው ቃል “የውጭ ሰላይ” ነው በሚል ይገልጸዋል፡፡ ሰውን ማሳመን የሚችል አንደበተ ርትኡ እና አስመሳይ ነው ይላሉ፡፡
የእነዚህን አባባሎች እውነትነት በማስረጃ ለማስደገፍ እንዲቻል ጥያቄ በማቀርብበት ጊዜ ምንም ነገር የለም፡፡ ዝም ብለው በደፈናው “ወያኔዎች ምን ያህል አታላዮች እና ብልጦች እንደሆኑ አንተ አታውቅም፡፡ እነርሱ ሰይጣኖች ናቸው እያሉ ይነግሩኛል”፡፡
በህወሀት ላይ ያሉኝ አመለካከቶች በሚገባ የሚታወቁ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና በኦቦ ለማ መገርሳ አዎንታዊ እና አነሳሳሽ መልዕክቶች ምክንያት ሃሳቤን ቀይሪያለሁ፡፡ ስለህወሀትም ቢሆን፡፡ ሁላችንም መልካም ሰዎች እና ሰይጣኖች ነን፡፡ ዶ/ር ማርቲን ሉተር እንዲህ በሚል አሳስበዋል “በመጥፎዎቻችን መካከል ጥቂት መልካም ሰዎች ይኖራሉ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ መልካም በሆንን ሰዎች መካከል ጥቂት ሰይጣኖች ይኖራሉ“ ነበር ያሉት፡፡ ይህንን እውነታ በምንገነዘብበት ጊዜ ጠላቶቻችንን መጥላትን እንቀንሳለን፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኃጢያቶች ዝም ብሎ በደፈናው ጥፋተኛ ናቸው የሚል ነው፡፡ በአገዛዙ ውስጥ ሆነው በወታደራዊ እና በሲቪል የኃላፊነት የስራ መደቦች የማገልገላቸው እውነታ በፖለቲካ አገልግሎት ዘላለማዊ ኃጢያተኛ አድርጎ አስፈርጇቸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያዋቀሩት ካቢኔ የእርሳቸውን የውድቀት ዕጣ ፈንታ የሚያመላክት ምልክት ነው ይላሉ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳት አለባቸው ይላሉ፡፡ ሆኖም ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ቢያነሱት ደግሞ ውሸት ነው ይህ ለታዕይታ ነው ይላሉ፡፡ የሚቀጥለው ሀገር አቀፍ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሀዊ እና ተወዳዳሪነትን ያካተተ ይሆናል ብለው ሲናገሩ ደግሞ ለማታለል ነው በማለት ጨለምተኛ አስተሳሰባቸውን ያቀርባሉ፡፡ ገና በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት የስልጣን ዘመናቸው ስለወደፊቱ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ አስደማሚ በሆነ ሁኔታ ሲናገሩ በተግባር የማይገለጽ ባዶ ንግግር ነው ይላሉ፡፡
እርሳቸው ማሸነፍ እንዳይችሉ እና ለውድቀት እንዲዳረጉ ሆነው ነው በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ በስልጣን እንዲቀመጡ የተደረጉት፡፡ ቢሰሩም ይወገዛሉ ባይሰሩም ይወገዛሉ፡፡
ሆኖም ግን ለማንኛውም የስህተት ድርጊት የእርሳቸው የግል ጥፋት ምንድን ነው? ባገዛዙ ውስጥ ባላቸው ስልጣን ምንድን ስህተት ነው የሰሩት?
በአሁኑ ጊዜ በተቃዋሚዎች መካከል ከአገዛዙ ጋር እጅ እና ጓንት ሆነው የሚሰሩ በርካታዎች የሉምን? ወይም ደግሞ ካላቸው ቀረቤታ አንጻር ከአገዛዙ ጋር እየተሞዳሞዱ በሕዝብ ሀብት ላይ ተጠቃሚ የሆኑ አይደሉምን? እነዚህስ ብቃትየለሽ ተብለው መወገዝ የለባቸውም ወይ? እስኪ ለመሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ የመጀመሪያዋን ጠጠር ለመወርወር ዝግጁ የሆነ ማን ነው?
እውነታው ግልጥልጥ ብሎ ሲታይ ግን ፖለቲካ እንግዳ የሆነ የአልጋ ተጋሪነትን ይጠይቃል፡፡ ማንዴላ ዴሞክራሲን በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ከዴክለርክ ጋር ተቀራርበው መስራት ነበረባቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እያንዳንዱን ሰው እንደማያስደስቱ ወይም የእያንዳንዱን ሰው ፍላጎት እንደማያሟሉ አውቃለሁ፡፡ በእኔ አመለካከት እርሳቸው ድንግተኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው፡፡ በታሪካዊ ኃይሎች ለታሪካዊ ሚና የተገኙ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ባለብሩህ ተስፋ ወጣቶች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ እንደማንኛውም ሰው ያለምንም ጥርጥር ሊወድቁ ወይም ደግሞ ስኬታማ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ማንዴላ እንዲህ ብለው ነበር፣ “በህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ታላቁ ስኬት በፍጹም ያለመውደቅ አይደለም ሆኖም ግን ታላቁ ስኬት በእያንዳንዱ በወደቅንበት ጊዜ ሁሉ ፈጥነን የመነሳት ችሎታ ማዳበር ነው፡፡ ለማዘግየት ስኬታማዎች ልትሆኑ ትችሉ ይሆናል ሆኖም ግን ደቡብ አፍሪካን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሸጋገር የሚደረገውን ተልዕኮ በፍጹም ልታጨናግፉት አትችሉም“ ነበር ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለበርካታ ጊዜ ይወድቃሉ እናም በየጊዜው እንደገና እየተነሱ ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንደሚያሸጋግሯት አምናለሁ፡፡
ሆኖም ግን ከእርሳቸው ጋር እንዴት ነው ተቀናጅተን መስራት ያለብን?
ለእያንዳንዷ ለሚሰሯት ስህተት ሁሉ ውግዘት እና ትችትን ማጉረፍ ወይስ ደግሞ እርሳቸውን በመልካም ሁኔታ በመገንዘብ ወንድማዊ ፍቅርን እና ጓዳዊ ትብብርን በመስጠት ወደ ታለመው ግብ መገስገስ?
ለእያንዳንዱ ሰይጣናዊ ድርጊት ሁሉ እርሳቸውን ተጠያቂ ማድረግ ይኖርብናልን? ወይስ ደግሞ እርሳቸው የሚፈልጓቸውን ሁሉንም ዕድሎች ሁሉ ለእርሳቸው በመስጠት ስኬታማ እንዲሆኑ እና በድል አድራጊነት እንዲወጡት ማገዝ ይኖርብናል?
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መጠነሰፊ የሆነ ሕዝባዊ ድጋፍ በተለይም ደግሞ ሰባ አምስት በመቶ የሚሆነውን የህብረተሰብ ክፍል በሚወክለው በወጣቱ ትውልድ እንዳላቸው የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በየከተሞች እየተገኙ ከሕዝብ ጋር የሚያደርጓቸው ውይይቶች ስኬታማነታቸውን በማረጋገጥ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ለማ መገርሳ በዘረመል የትውልድ ህዋሶቻችን ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን ያነቃቁ እና ወንድማዊ ፍቅርን ለማስፈን የሚታትሩ የማይናወጥ ጽኑ እምነት ባለቤቶች ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ለማ አብረን እንቆማለን ወይም ደግሞ አብረን እንወድቃለን ይላሉ፡፡ ዕጣ ፈንታችን በአንድነት የተገመደ ነው፡፡ ማንም ብቻውን አይቆምም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ማለት እንግዲህ እንደዚህ ነው ይሉናል፡፡
በዚህ አሁን እየጻፍኩት ባለው ማስታዋሻየ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ እያራመዷቸው ያሉትን የተጠናከረ ተጠራጣሪነታቸውን፣ ጨለምተኛነታቸውን የአሸናፊነት መንፈሳቸውን እና አሉታዊ አስተሳሰቦቻቸውን እርግፍ አድርገው በመተው ጨለምተኛና የተቃርኖ አመለካከቶቻቸውን ወደ አዎንታዊ አመለካከቶች፣ የብቸኝነት እና የእራስ ወዳድነት ስሜትን ወደ ጋርዮሽ እና አብሮነት፣ ውስጣዊ ጥላቻዎቻቸውን ወደ ፍቅር እና ብሄራዊነት አስተሳሰቦች፣ ቀኖናዊ ግትርነታቸውን፣ ስሜታዊነታቸውን እና አድሏዊነታቸውን ወደ ምሁራዊነት፣ ተራማጅ እና መርህን መሰረት ያደረጉ አስተሳሰቦች፣ የቡድናዊ እና ጎሳዊ አስተሳሰቦችን ወደ ኢትዮጵያዊነት፣ ሰብአዊነት፣ ሀሳባዊነት እና ትክክለኛነት እንዲቀይሩ ለእኔ ጓደኞች የጉማሬው ትውልዶች (አሮጌው ትውልድ) ተማጽዕኖዬን አቀርባለሁ፡፡
አሁን በእጃችን ያለው አንገብጋቢው ተግባር ኢትዮጵያን ወደፊት እንዴት ማስኬድ እንደምንችል እና ይህንንም መልካም አስተሳሰብ እንዴት ማቆየት እንደምንችል ትኩረት ማድረግ ላይ ነው፡፡ ለአንድ የጋራ ዓላማ ወደ ነጻነት፣ ዴሞክራሲ እና የሰብአዊ መብት መከበር አንድ አቅጣጫ መጓዝ አለብን፡፡
በተዛባ መልኩ እንዳትገነዘቡኝ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኢትዮጵያ አዳኝ ወይም ደግሞ መለኮታዊ ኃይል ናቸው ብየ አላስብም፡፡ እርሳቸው ወጣት ሰው ናቸው፡፡ አብዛኞቻችን በእርሳቸው የእድሜ ክልል ያሉ ልጆች አሉን፡፡ እንደማንኛውም ወጣት ሰው እርሳቸውም ብዙ የሚማሯቸው ነገሮች አሏቸው፡፡ አብዛኞቻችን በወርቃማው የእድሜ ክልላችን ልንማራቸው የሚገቡን በተለይም ስለእውነት እና እርቅ በርካታ ቁምነገሮች አሉን በማለት ደፍሬ ለመናገር እችላለሁ፡፡
ግልጽ የሆነው ነገር ፍጹም በሆነች ዓለም ውስጥ አንኖርም፡፡ ለዚህም ነው ምጡቅ አስተሳሰብ ማሰብ ያለብን እና ትችን ማውገዝ ያለብን፡፡ ይህንንም በማድረግ አስደማሚ የሆኑ መፍትሄዎችን ይዘን በቅ እንላለን፡፡
በአሁኑ ጊዜ ቅድመ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩን በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አመራርነት ኢትዮጵያ በቀጥተኛው መንገድ እና በትክክለኛው መስመር ላይ ወደፊት በመጓዝ ላይ ትገኛለች፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋራ በመሰለፍ ኢትዮጵያ በትክክለኛው መስመር ላይ እንድትቆይ እና በፈጣን ሁኔታ እንድትራመድ የበኩላችንን ማድረግ አለብን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሩህሩህ፣ መልካም አሳቢ ፍቅርን የተላበሱ እና የኢትዮጵያን ወጣቶች እና ሀገሪቱን በሰላም፣ በአንድነት እና በእርቀ ሰላም ወደፊት እንድትጓዝ ማድረግ የሚችል ችሎታ ያላቸው ወጣት መሪ ሆነው ይታዩኛል፡፡
ለእኔ አሮጌ የጉማሬ ትውልድ እህት እና ወንድሞቸ የነጻነት ባቡሩ መነሻ ጣቢያውን ለቅቋል ተነስቷል በማለት ልነግራቸው እፈልጋለሁ፡፡ ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን ለመሳፈር የሚፈልጉ ከሆነ ባቡሩን በቀጣዩ ጣቢያ ለመያዝ ይችላሉ፡፡
በወጣትነት ዘመኔ በጣም የምወደው መዝሙር ነበር፡፡ ይህም መዝሙር “እልም አለ ባቡሩ ወጣት ይዞ በሙሉ“ ይባል ነበር፡፡
የአቦሸማኔው ትውልድ አባላት በባቡሩ ተሳፈሩ:: አብይ አህመድ ባቡሩን በመሾፈር ላይ ናቸው፡፡
ወደ ዋናው ርዕሴ ከመግባቴ በፊት ባለፈው ሳምንት በሰማኋቸው አንዳንድ ዜናዎች ላይ አስተያየቴን መስጠት እፈልጋለሁ፡፡
“ይቅርታ እጠይቃለሁ…” የሚለው ቃል የመፈወስ ኃይል ያለው እና ለወጣቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ለእኛ ታላቅ ትምህርት ትቶ ያለፈ ክስተት ነው፡፡
በውይይቱ ወቅት ቀርቦ ለነበረ ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ላይ ጥቂት ኢትዮጵያውያንን ጨለምተኛ እንዲሆኑ ያደረገ ስለነበር እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በተሳሳተ መንገድ ግንዛቤ በመወሰዱ ይቅርታ እጠይቃለሁ በማለታቸው እኔ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ ያለኝ ክብር እጅግ በጣም አየጨመረ መጥቷል፡፡
ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለብዙ ጊዜ አወዛጋቢ ሆኖ የቆየውን የወልቃይት ጉዳይ እንደ ቀላል ነገር በመውሰድ የወልቃይት ጉዳይ የልማት ችግር ነው፣ የመሰረተ ልማት እና የማህበራዊ አገልግሎቶች ያለመሟላት ችግር ነው በማለት የንቀት ንግግር አድርገዋል በሚል የማህበራዊ ሜዲያዎች ውንጀላዎችን አቅርበው ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የዘመናት የኢትዮጵያ መሪዎችን መጥፎ ባህል በሚያስደንቅ እና ባልተጠበቀ ሁኔታ አሽቀንጥረው በመጣል ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ አስደናቂው ነገር ይቅርታ መጠየቃቸው ብቻ ሳይሆን የእርሳቸውን ሀሳብ ሌሎች ሰዎች እንዴት እንደተገነዘቡ የሰጡበት ምላሽም ጭምር ነበር፡፡ ከዚያም በመቀጠል ከወልቃይት የአማራ ማንነት ኮሚቴ አመራር አባላት እና ከሌሎች በደርዘን ከሚቆጠሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተገናኝተዋል፡፡ ስለሁኔታውም ተገቢውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ሩህሩህነትን በሚያሳይ መልኩ ሰከን ብለው ስለጉዳዩ ጥልቅ ስሜት እንደተሰማቸው እና ከዚህም ተገቢ የሆነ ልምድ ወስደዋል፡፡
በከተማው ተደርጎ በነበረው ሀዘን የተንጸባረቀበት ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስለወልቃይት ጉዳይ ተናግረውት በነበረው ንግግር ምክንያት ሕዝቡ ቅር በመሰኘቱ ወደ ጎንደር እንዳይሄዱ ተነግሯቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ግን ይህንን ነገር ወደ ጎን በመተው ወደ ጎንደር ለመሄድ ወሰኑ ምክንያቱም እርሳቸው ስህተት ሰርተው ከሆነ የጎንደር ሕዝብ ትንሽ ቁንጥጫ እንደሚሰጣቸው እና እንደሚያስተምራቸው ተናግረዋል፡፡ በሌላ አባባል እርሳቸው ማለት የፈለጉት እርሳቸው ወጣት ስለሆኑ ስህተት መስራት እንደሚችሉ ወይም ደግሞ በተሳሳተ መንገድ ግንዛቤ ሊወሰድባቸው እንደሚችል ግልጽ ማድረጋቸው ነው፡፡ ሆኖም ግን እርሳቸው የጎንደር ሕዝብ ልጅ ናቸው፡፡ ስህተት ከሰሩ ወይም ከተናገሩ ሕዝቡ እንደ ልጆቻቸው በማየት አርሞ ያስተካክላቸዋል፡፡
እንደዚህ ያለ ጨዋ እና ሩህሩህነትን የተላበሰ የሀገር መሪ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ተሰምቶ አያውቅም፡፡ ለሚሰራቸው ስራዎች እራሱ ኃላፊነትን የሚወስድ መሪ ሙገሳ እንጅ ውግዘት አይፈልግም፡፡ ለዚህም ነው ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ገንቢ እና አዎንታዊ የሆኑ ትችቶችን መስጠት አለብን የምለው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተያየትን ይቀበላሉ፣ ከዚህም ትምህርት ይወስዳሉ እናም በሂደት ልምድ እየወሰዱ የበለጠ ጠንካራ እና ውጤታማ መሪ ይሆናሉ፡፡
የኢትዮጵያ መሪ የሆነ እና ላደረገው እና ለተናገረው ስህተት ድርጊት ይቅርታ በመጠየቅ ከሕዝብ ጋር ሆኖ በመስራት ቅሬታዎችን ለማስወገድ እና መፍትሄዎችን ለማምጣት የሞከረ በየትኛውም ጊዜ አላውቅም ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሹመት በዓል ንግግራቸው ዕለት ባሰሙት ንግግር በሰላማዊ አማጺዎች ላይ በወታደር እና ደህንነት ኃይሎች ለተፈጸሙ ግድያዎች እና ለደረሱ ጉዳቶች ይቅርታ የጠየቁ ብርቅየ እና ልዩ ሰው መሆናቸውን አውቃለሁ፡፡ ለእኔ ያ ማለት ብዙ ነገር ነው ምክንያቱም ከሕግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ በንጹሀን ኢትዮጵያውያን ላይ ግድያ መፈጸም ነው እኔን በመጀመሪያ ደረጃ ወደ ሰብአዊ መብት ተሟጓችነት ትግሉ ዘው ብየ እንድገባ ያደረገኝ፡፡
ይቅርታ ለመጠየቅ ድፍረቱ እና ስብዕናው ያለው መሪ ሩህሩህ፣ አእምሮው ግልጽነትን የተላበሰ፣ ልቡ ክፍት የሆነ እና በእራስ የመተማመን ስሜት ያለው መሪ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ መሪ ለእኛ ለኢትዮጵያውን ስልጣን ለሕዝብ አገልግሎት ብቻ መዋል እንዳለበት ያረጋግጥልናል፡፡ እንዲህ በማለት ይነግረናል፣ “እኔ ሰው ነኝ እንደማንኛውም ሰው ስህተት ልሰራ እችላለሁ፡፡ እኔ የሕዝብ አገልጋይ የመሆንን ከባድ ኃላፊነት ከመሸከም የዘለለ ሌላ ልዩ ነገር የለም“ ይላሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከሕዝብ ጋር ንስሀ የመግባት እና ዕርቀ ሰላም የማውረድን ዋጋ ምሳሌ በመሆን ያስተምሩናል፡፡
እ.ኤ.አ ሰኔ 2010 አቅርቤው በነበረው ትችቴ መሪዎችን ከሕዝብ ጋር ለማቆራኘት ንስሀ መግባት አስፈላጊ እንደሆነ ጽፌ ነበር፡፡ አሁን በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጥጠው ያሉ እና ተቃዋሚዎች ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲህ ማለት አለባቸው፣ “አምታተናችኋል፣ ግራ አጋብተናችኋል፡፡ ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ ወደፊት ከስህተቶቻችን እንማራለን ለሁለተኛ ጊዜ አንደግመውም፡፡“ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ብዙዎቻችን ከስህተት ላይ እንወድቃለን እናም ስህተት ትክክል ነው እያልን ለብዙ ጊዜ ይህንኑ ስናራምድ እንቆያለን፡፡
ይቅርታ የመጠየቅ ኃይል ምህረትን እና ይቅርታን የመጠየቅ ኃይል ነው፡፡ ቅንነት ያለው ይቅርታ ብልህነት ነው፡፡ ንዴትን እና ጥላቻን ያስወግዳል፡፡ ፍቅርን፣ መግባባትን እና ዕርቅን ያጠናክራል፡፡
ጋንዲ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ደካሞች በፍጹም ምህረት ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ ምህረት የጠንካሮች እሴት ነው“ ብለዋል፡፡
እኔ ደግሞ እንዲህ የሚል እጨምራሁ፣ “ደካሞች በፍጹም ይቅርታ ሊጠይቁ አይችሉም፡፡ ይቅርታ የጠንካሮች እሴት ነው“ እላለሁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ታላቅ ትምህርትን አስተምረውኛል ምክንያቱም እራሴ ታላቅ ይቅርታ የማድረግ ጉድለት አለብኝ፡፡ ሆኖም በዚህ ላይ እራሴን ለማሻሻል እየሰራሁ ነው፡፡
ከወጣቱ ትውልድ ለመማር ጊዜው እሩቅ አይደለም፡፡ እኔ ለእራሴ እውነትን እናገራለሁ!
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የቆሰሉትን ለመፈወስ ሲሉ በሚያሰሟቸው ቃላት እና ለሚያሳዩት መልካም ባህሪ፣ ደግነት፣ ሩህሩህነት እና ፍቅር አመሰግናቸዋለሁ፡፡ ቃላት ለመፈወስና ለማውደም ኃይል አላቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ልቦቻቸው በተናገሯቸው ቃላት ተሰብረው የቆዩትን በርካታዎቹን ኢትዮጵያውያን በተሳሳተ መንገድ ስለተገነዘባችሁኝ ነው ይቅርታ በማለት ቃሎቻቸውን ለፈውስ አገልግሎት እንዲውሉ አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያዊ ጀግና እስክንድር ነጋን በከፋፋይ ፖለቲካ ለማጥቃት መሞከር፣
ቅዱሱ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፣ “ሰይጣናዊ ድርጊትን ካልሰሩ ስለማያርፉ ሰውን ለማጥቃት ሲሉ እንቅልፋቸውን አጥተዋል“ ይላል፡፡ በሌላ አባባል ሰይጣኖች በፍጹም አይተኙም፡፡
ከጥቂት ቀናት በፊት ኢትዮጵያዊው አርበኛ እና ጀግና እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ እውቅናን የተጎናጸፈው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የአምነስቲ ኢንተርናሽናልን የወርቅ ኢዮ ቤልዩ በዓል ለማክበር ተጋብዞ ወደ ኔዘርላንድ እንዳይበር ክልከላ ተደርጎበት ነበር፡፡ ፓስፖርቱን በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የኢሜግሬሽን የመቆጣጠሪ ጣቢያ ከተነጠቀ በኋላ ወደ ውጭ መጓዝ እንዳይችል የጉዞ ማዕቀብ የተጠለበት መሆኑን ተነግሮታል፡፡
ፓስፖርቱን እንደነጠቁት እስክንድር ለኢሚግሬሽን ባለስልጣኖች ጉዳዩን ለከፍተኛ ባለስልጣኖች በማቅረብ ይረጋገጥ ምክንያቱም አላስፈላጊ የሆነ ትችትን በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር ላይ መስጠትን አልፈለገም፡፡ ፓስፖርቱን እንዲነጠቅ ትዕዛዙ የመጣው ከከፍተኛው ባለስልጣን እንደሆነ ተነግሮት ነበር፡፡ እንዳጋጣሚ በሰዓታት ጊዜ ውስጥ ለመሄድ ነጻ መሆኑ ተዘግቦ ነበር፡፡
እስክንድር እ.ኤ.አ የካቲት 2018 ነበር ከእስር የተፈታው እናም እንደገና ባለፈው ወር መጀመሪያ አካባቢ በአንድ የግለሰብ ቤት ውስጥ ሲደረግ በነበረ ዝግጅት ላይ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሰንደቅ ዓላማ አሳይተሀል በማለት ከሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ጋር እንደገና ወደ እስር ቤት እንዲገባ ተደርጎ ነበር፡፡
“ከፍተኛ የሆኑ ባለስልጣኖች” እገዳውን በማድረግ ወደ ውጭ አገር እንዳይወጣ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል የሚለውን እስክንድር ነጋ የሰብአዊ መብት ክብረ በዓልን ለማክበር ከሀገር ወደ ውጭ እንዳይወጣ የከለከሉት ለምንድን ነው?“ የሚል ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ከሁለት ሳምንታት በፊት ገደማ ከእስር ቤት ለቀውታል፡፡
አንድ ሀሳብ በአእምሮዬ ላይ ውልብ አለብኝ፡፡ ኢትዮጵያ እስክንድር ነጋን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የወርቅ ኢዮ ቤልዩ በዓል ላይ የክብር እንግዳ ሆኖ እንዳይገኝ እንደገና በመከልከል “የዓለም ውራጅ” መሆን ይኖርባታልን?
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከእስክንድር ነጋ ጋር ጠብ የላቸውም፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በፊት የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትር እስክንድር ነጋ እና ሌሎች በርካታዎቹ በእርግጥ “የፖለቲካ እስረኞች” ናቸው ብሏል፡፡
በእርግጥ ለእኔ ይህንን ሁኔታ ለማወቅ ጊዜ አልወሰደብኝም፡፡
ምን ዓይነት ጨዋታ እየተጫወቱ እንዳለ እና ይህን ጨዋታ የሚጫወተው ማን እንደሆነ በእርግጠኝነት አውቃለሁ፡፡ ቀደም ሲል ሲጫወቱት አይቻለሁ፡፡
እ.ኤ.አ ግንቦት 2016 በዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች ላይ ተመሳሳይ ሸፍጥን ሰርተዋል፡፡ የዘላለም ክብረትን እና የሌሎችን አምስት ጦማሪዎችን ፓስፖርት በአውሮፕላን ማረፊያው ቅጥር ግቢ ውስጥ ወስደዋል፡፡ ዘላለም እ.ኤ.አ በሰኔ 2016 የኦባማን ወጣት የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤን እንዲካፈል ይጠበቅ ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ የመንግስት ከሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ እንዲህ በማለት ገልጾ ነበር፣ “ድርጊቱ የተፈጸመው ከስልጣናቸው ገደብ በላይ አልፈው በዳኞች እና በኢሚግሬሽን ባለስልጣኖች ነበር፡፡ ለማስተካከል ወራትን ወይም ዓመታትን የሚፈጅ ስህተት ሊሰሩ ይችላሉ“ ነበር ያለው፡፡
በእስክንድር ላይ የተፈጸመውም እንዲዚያ ዓይነት ነገር ነውን? በዳኞች እና በእረፍት የለሽ የኢሚግሬሽን ባለስልጣኖች ነውን?
ያንን ጨዋታ እናውቀዋለን፡፡ በስልጣን ላይ ያሉ እና እስክንድርን ለማዋረድ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ለማበሳጨት የሚፈልጉ አንዳንድ አድሀሪ ግለሰቦች እንደዚህ ያለ ድብቅ አጀንዳ አላቸው፡፡
እስክንድርን የመውጫ ቪዛ በመከልከል የሚከተሉትን ዓላማ ለማሳካት ጥረት አድርገዋል፡
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ተቀባይነት እና ክብር ለማዋረድ እና ለማበሳጨት፣
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና በዲያስፖራው ማህበረሰብ መካከል አጥር ለማጠር፣
ዝናው አየናኘ በመጣበት ወቅት ታላቁን እስክንድር ነጋን ለማዋረድ፣
እስከ አሁንም ድረስ በስልጣን ላይ ናቸው እናም የፈለጉትን ነገር ሁሉ ማድረግ ይችላሉ የሚል መልዕከት ለማስተላለፍ፣
ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን እንደገና ወደ ክስ እንዲገቡ እና ሀሳቦቻቸውን ለማስቀየስ፣
ወደ ጨለማው ክፍል ሊመልሱን ስለሚፈልጉ ነው፡፡
ሆኖም ግን እኛ ከእንግዲህ ወዲያ ወደ ጨለማው አንሄድም ምክንያቱም ኃይሉ ያለው ከእኛ ጋር ነው!
ከእንግዲህ ወዲያ በኢትዮጵያ ውስጥ እና በዲያስፖራው ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን እንደዚያ ያለውን ያረጀ እና ያፈጀ ጨዋታ አይጫወቱም፡፡
ለዓመታት በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያሉ ባለስልጣናት ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንን በደመ ነብስ፣ በስሜታዊነት እና በብስጭት ምላሽ እንዲሰጡ በማድረግ ሲጫወቷቸው የነበሩባቸውን አጋጣሚዎች ሁሉ እያስጠነቀቅሁ ስጽፍባቸው ቆይቻለሁ፡፡ ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት የማይጠቅም እርባና ቢስ የሆኑ ነገሮችን ሲሰሩ እናያለን፡፡ ሆን ብለው አስበውበት የዲያስፖራውን ማህበረሰብ ሀሳብ ለማስቀየስ አሳፋሪ የሆነ ነገር ይናገራሉ፡፡ ከዚያም የዲያስፖራው ማህበረሰብ ለዚያ ምላሽ ለመስጠት ቆላ ከደጋ በማለት በመዋተት ሌላ ሀሳብን የሚያስቀይስ ነገር እስኪመጣ ድረስ እና እንደገና በአዲስ እስኪጀመር ድረስ ጊዜውን ያባክናል፡፡
አሁን ዳንሱ ያለቀ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ጨዋታው ተጠናቅቋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ፍቅር፣ እውነት እና ዕርቅ የሰፈነባትን ኢትዮጵያ ለመገንባት በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን፡፡
ለእነርሱ እንዲህ የሚል ቀላል መልዕክት አለኝ፣
“እንደዚህ ዓይነት ሰይጣናዊ ድርጊት ስትፈጽሙ የቆያችሁ ሁሉ አሁን ጊዚያችሁ ያለፈ መሆኑን እወቁ፡፡ የጨለማ ዘመን ተጠናቅቋል፡፡ አሁን የጨዋነት፣ የመግባባት እና የእርቅ ዘመን ነው፡፡ በመጨረሻው ሰዓት የእናንተ ጨዋታ በጫካ ውስጥ በመሆን በአንድ እጅ ማጨብጨብ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በሕዝቦች መካከል ግጭት እና ጥላቻን ለመፍጠር እንቅልፍ የለሽ ምሽቶችን ማሳለፍ ትችላላችሁ፡፡ ሆኖም ግን እኛ ወደፊት ተንቀሳቅሰናል፡፡ ለእናንተ ቫይረስ ጸር የሆነውን እና ኢትዮጵያዊነት እየተባለ የሚጠራውን መድሀኒት በመርፌ ተወግተናል፡፡ እንደፈለጋችሁ ሞክሩ ሆኖም ግን በመከፋፈል ለመግዛት የምታደርጉት ጥረት ስኬታማ አይሆንም፡፡ ከዚህ በኋላ በፍጹም!“
ስለወንድሜ ስለእስክንድርና… እስቲ ልናገር…
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሹመት በዓል የመክፈቻ ንግግራቸው እንዲህ ብለው ነበር፣ “በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና በሀገር ውስጥ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል ከልብ በመነጨ ሁኔታ ይቅር ልንባባል ይገባል፡፡ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን እውቀታቸውን፣ ሀብቶቻቸውን እና ልምዶቻቸውን በመያዝ ሀገራቸውን በመገንባቱ ጥረት የእራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡ እጆቻችንን ዘርግተን እንቀበላቸዋለን“ ነበር ያሉት፡፡
የእርሳቸውን የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግሮች በሙሉ ልቤ አደንቃቸዋለሁ፡፡
የእኔ ህልም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እጆቻቸውን በመዘርጋት ዲያስፖራ ኢትየጵያውያንን ከመቀበላቸው በፊት የኢትዮጵያን የሀገር ውስጥ ጀግኖች ወንዶች እና ሴቶች ልጆች ለመልካም ነገር እና ለዴሞክራሲ ማበብ፣ ለሰብአዊ መብት መከበር እና ለሕግ ልዕልና ሲታገሉ የቆዩትን እና ምንም ዓይነት ወንጀል እንዳልሰሩ ፊት ለፊት በመናገር እቅፍ አድርገው ይሳሟቸው፡፡
ይንገሯቸዉም “እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተቀራርበን ልብ ለልብ ይቅር እንድንባባል እንፈልጋለን፡፡”
በግድግዳ ላይ ያለ ዝንብ በመሆን የእስክንድር ነጋን፣ የአንዷለም አራጌን፣ የፕሮፌሰር በቀለ ገርባን፣ የውብሸት ታዬን፣ የፕሮፌሰር መረራ ጉዲናን፣ የአበበ ቀስቶን፣ የኦልባና ሌሊሳን፣ የእማዋይሽ ዓለሙን፣ የዘላለም ወርቅ አገኘሁን፣ የማህሌት ፋንታሁንን፣ የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎችን፣ የአህመዲን ጀበሊን፣ የንግስት ይርጋን፣ የአቡ በካር አህመድን፣ የኦኬሎ ኦኳይ ኦቻላን፣ የኮ/ል ደመቀ ዘውዱን፣ የዶ/ር ፍቅሩ ማሩን፣ የናትናኤል መኮንንን፣ የማሙሸት አማረን…እንዲህ የሚሉትን ቃላት ሲሰሙ ማየት እወዳለሁ፣ “በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ከውስጥ ልባችን በመነጨ መልኩ እርስ በእርሳችን ይቅር መባባል ያስፈልገናል፡፡“
ምን ዓይነት ወርቃማ አጋጣሚ ይሆን!
በሀገር ውስጥ ሆነው አምባገነኑን አገዛዝ ሲፋለሙ ለቆዩት ወጣት ኢትዮጵያውያን ምን ያህል ክብር እና አድናቆት እንዳለኝ አንባቢዎቸ ትገነዘባላችሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ እንግሊዝ በናዚ ላይ መልሶ የማጥቃት እርምጃ ከመውሰዷ ከአንድ ወር በፊት ዊንስተን ቸርችል ጥቂት ለታጠቁት የአውሮፕላን አብራሪዎቻቸው እንዲህ የሚል የሙገሳ ንግግር አሰምተው ነበር፣ “እነዚህ ጥቂት ጀግኖች ያደረጉት መስተዋፆ ጠቅላላው ህዝባችን ዉለታዉን መመለስ አይችልም” ነበር ያሉት፡፡
እንደዚሁም ሁሉ በኢትዮጵያ ታሪክ በተደረገው የሰብአዊ መብት ትግል ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ የነዚህን ጥቂት ወጣቶች ዉለታና መስዋእትነት መከፈል ያዳግተዋል፡፡
ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ፣ ለነጻነት እና ለሰብአዊ መብት መከበር ብዙ ከተሰቃዩት ከእነዚህ ጀግኖች ጋር የሚደረገው ዕርቀ ሰላም በኢትዮጵያ ውስጥ ለእውነት እና እርቀ ሰላም መስፈን እውነተኛ ማረጋገጫ ነው፡፡
አልጠራጠርም ይህ ድርጊት ይፈጸማል፡፡ የጊዜ ሁኔታ ብቻ ነው፡፡
ሕዝባቸውን ለሚያዳምጡ መልካም መሪዎች እውነትን መናገር፣
እኔ በስልጣን ላይ ላሉት እውነትን የምናገር በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል፡፡ ይህም መፈክር በድረ ገጼ መግቢያ ላይ እንዲህ በሚል ተጽፎ ይገኛል፣ “ሰብአዊ መብት ይከበር፡፡ በስልጣን ላይ ላሉት እውነትን መናገር፡፡“
ወደ ኋላ መለስ በማለት እ.ኤ.አ በ2006 ስለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት መጠበቅ ገና በመጀመሪያ ጊዜ መስበክ በጀመርኩበት ጊዜ ዓላማዬን ለማሳካት እንዲህ የሚሉትን የጋንዲን ቃላት ተውሻለሁ፣ “መጀመሪያ ይተውሀል፣ ከዚያም ይስቁብሀል፣ ከዚያም በመቀጠል ይታገሉሀል፣ ከዚያ በኋላም አሸናፊ ትሆናለህ“፡፡
ላለፉት አስራ ሶስት ዓመታት ጆሯቸውን ለዘጉብኝ፣ ዓይናቸውን ለጨፈኑብኝ እና ለተሳለቁብኝ በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ለሚገኙት እውነቱን ስናገር ቆይቻለሁ፡፡
በእርግጥ በስልጣን ላይ ላሉት እውነትን በመናገር ሳቀርባቸው የቆየሁት ሳምንታዊ ሰበካዎቸ በጋንዲ የትግል ስልት አጠራር መሰረት በግለሰቦች የሚደረጉ ሕዝባዊ እምቢተኝነቶች ናቸው፡፡
በአምባገነኖች ላይ ሰላማዊ ትግል፣ ሕዝባዊ እምቢተኝነት፣ ከጨቋኞች ጋር ያለመተባበር እና በመንግስት ላይ የብዙሀን ተቃውሞ በማድረግ መታገል “እውነተኛ ኃይል” መሆናቸውን ጋንዲ አስተምረዋል፡፡ የጋንዲ የእውነት ኃይሎች አስተምሮ በጨቋኞች ልብ እና አእምሮ ውስጥ ያለ ጥላቻ እንደሚያጠፋቸው እና ብቸኛው ጽድቅ እራስን፣ ማህበረሰቡን እና ሀገሪቱን መውደድ እንደሚሆን ያሳምናቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ከመጀመሪያ ጊዜ ጀምሮ ቀስ በቀስ በስልጣን ላይ ላሉት እውነትን በመናገር ቆይቻለሁ በማለት መናገር እችላለሁ፡፡ ሆኖም ግን እ.ኤ.አ እስከ 2006 ዓ.ም ድረስ ሰላሜን ይዠ ቆይቻለሁ፡፡
እ.ኤ.አ ሰኔ 10 ቀን 1991 ዓ.ም በጊዜው በኢትዮጵያ ቀደምት መጽሄት በነበረው በኢትዮጵያን ሪቪው የደርግ ዘመን ፍጻሜ እና በኢትዮጵያ ሁሉም ወገኖች አዲስ የሰላም እና የብልጽግና ምዕራፍ እንዲከፍቱ እና ይህን መልካም ዕድል እንድንጠቀምበት ወይም ደግሞ ይህችን ዕድለ ቢስ ሀገር በተሳሳቱ ምርጫዎች እና ስሌቶች ወደ ስቃይ እና መከራ እንዳትገባ የሚል ትንታኔ እና ነብያዊ ትንበያ ሰጥቸ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ ሀምሌ 1 ቀን 1991 ዓ.ም አቅርቤው በነበረው የግል አስተያየት ጽሁፍ ኢሀአዴግ ስልጣንን ከያዘ ወዲህ ተደቅነውበት በሚገኙት ተግዳሮቶች ላይ ትንታኔ በመስጠት አሳታፊነት፣ ቅንነነት እና አንድነት እንዲኖር ተማጽእኖ አቅርቤ ነበር፡፡ ከእውነተኛ ዴሞክራሲ ውጭ ምርጫው ወደ መጥፎ ነገር የሚሄድ እና ኢትዮጵያ ደህና ሰንብች ይሆናል በማለት አስጠንቅቄ ነበር፡፡
እነዚያ ቃላት ነብያዊ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ እናም እ.ኤ.አ በሚያዝያ 2018 እውነትን በስልጣን ላይ ላሉት በአደባባይ በመናገር አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ እንዲህ በማለት እውነታውን ፍርጥርጥ አድርገው ተናግረዋል፣
“አንድ ነገር ልንገራችሁ፡፡ አሁን በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመምረጥ እንደዚህ ያለ ነገር ነበር፡፡ ሰላማዊ የጠቅላይ ሚኒስትር ሽግግር አልተካሄደም ነበር፡፡ እውነታውን ልናገር፣ ሁሉም የሀገሪቱ ሕዝቦች ይስሙት፡፡ ሀገሪቱ በከፍተኛ አደጋ ውስጥ ነበረች፡፡ እግዚአብሄር ምስክሬ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ቢላዋውን በመሳል ተዘጋጅቶ ይጠብቅ ነበር፡፡ ምን እንደሚደረግ እናያለን እያሉ ነበር፡፡ ሆኖም እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይጠብቃታል፡፡ እናም የመንግስት አካላት ትክክለኛውን ነገር አደረጉ፡፡ እናም ከጭንቅ ገላገሉ፡፡ ያ ሳይሆን ቢቀር ኖሮ አንድ ሺ የኮማንድ ፖስት ወታደሮች አንድ ሚሊዮን የሚሆነውን ሕዝብ አምቀው ለመያዝ አይችሉም ነበር፣ በፍጹም አይችሉም…“ ነው ያሉት፡፡
አባገዳ በየነ ትክክል ናቸው፡፡ እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይጠብቃታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ጥይቱን እና ቢላዋውን አስወግደናል፡፡
ከስምንት ዓመታት ገደማ በፊት በሁፊንግተን ፖስት “በስልጣን ላይ ላሉት እውነትን መናገር …“ በሚል ርዕስ ተከታታይ ጽሁፎችን ጽፌ ነበር፡፡ በእነዚህ ተከታታይ ጽሁፎች ለእንግዳዎች (ለዓለም አቀፍ ለጋሽ እና አበዳሪ ድርጅቶች) እውነቱን መናገር፣ እንደዚሁም ደግሞ ለእውነት ፈላጊዎች (ለኢትዮጵያ ልሂቃን) እና በኢትዮጵያ ወጣቶች እና ሴቶች በኩል በመሆን ጽፌ ነበር፡፡ እርባና ቢስ የሆነ ንግግር ለሚያደርጉት ሁሉ እውነትን ተናግሪያለሁ፡፡ ምንም ኃይል ለሌላቸው ሁሉ ድምጽ በመሆን ተናግሬላቸዋለሁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን እንሞግት፡ የዲያስፖራ ኢትዮጵያውየንን አጀንዳ (ዎች) እንስጣቸው፣
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሹመት በዓል የመክፍቻ ንግግራቸው እንዲህ ብለዋል፣ “በውጭ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እውቀታችሁን፣ ሀብቶቻችሁን እና ልምዶቻችሁን በመያዝ ወደ ሀገራችሁ ብትመጡ እና በሀገር ግንባታው የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ለማድረግ ብትዘጋጁ እጆቻችንን ዘርግተን እንቀበላችኋለን“ ነበር ያሉት፡፡
በተመሳሳይ መልኩ እ.ኤ.አ ህዳር 2017 ለማ መገርሳ እንዲህ በማለት አጽንኦ ሰጥተዋል፣ “መማር እና ሀገርን ማገልገል የአካደሚክ የምርምር ወረቀት ማዘጋጀትን አይጠይቅም፡፡ ይህም ማለት ሀገርህን ለመጠበቅ፣ የተለያዩ መንገዶችን መፈለግ፣ ገንቢ የሆኑ ሀሳቦችን ይዞ መምጣት እና እንደነዚህ ያሉ ሀሳቦችን ማሰራጨት ነው፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ከምንም በላይ ከእኛ ምሁራን የሚጠበቀው፡፡ እኔ እንደዚህ ነው የማስበው“ ነበር ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ለማ ሁላችንንም እየሞገቱን ነው፡፡
እኔ በግሌ የእነርሱን መልዕክት ወስጃለሁ፡፡ ለእኔ እንደዚህ የሚል መልዕክት ነው የሰጡኝ፣ “የተናገርከውን አድርግ አለዚያም መናገርህን አቁም፡፡“
ለዚህም ነው በህዳር እና አሁን የቀረበውን መገዳደር ወዲያውኑ የተቀበልኩት፡፡ አደርጋለሁ!
ሌሎችም ይጋሩታል ብየ የማስበው የእኔ የዲያስፖራ አጀንዳ፣
የማይለወጥ እና አንድ ዓይነት ስብስብ አይደለም፡፡ በአንድ ከበሮ መች ስር የሚሰባሰብ አይደለም፡፡ በብዙ መልኩ ብዝሀነት የሚታይበት ስብስብ ነው፡፡ የተለያዩ ጉዳዮችን እና ፍላጎቶችን ያካተተ አጀንዳ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሊቀርባለቸው ይገባል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
የእኔ የወጣቶች እና የሰብአዊ መብቶች አጀንዳ ጉዳይ በየሳምንቱ ሁልጊዜ የምሰብከው ስለሆነ በደህና ሁኔታ የሚታወቅ ነው፡፡
የ21ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ በጣም አንገብጋቢው ችግር የኢትዮጵያ ወጣቶች ችግር እንደሆነ ከብዙ ጊዜ ጀምሬ አምናለሁ፡፡ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተለየ ትኩረት በመስጠት በስፋት ስጽፍበት ቆይቻለሁ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብቶች እንዲሻሻሉ በተለያዩ መድረኮች ተከራክሪያለሁ እንዲሁም ሰፊ ስብከት አድርጊያለሁ፡፡
ስለወጣቶች እና ስለሰብአዊ መብቶች መከበር ጉዳይ የሚጋሩኝ በርካታ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት እንዳሉ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ስለሆነም አንዱ ክፍል የሆነውን “የወጣቶች እና የሰብአዊ መብቶች አጀንዳ” በአንድ ላይ ሆነን ረቂቅ እናዘጋጅ እና ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንላክላቸው፡፡
በወጣቶቻችን ላይ ያለው ሁኔታ የሚያስፈራ ነው፡፡
እንደ ዩኤስ የሕዝብ ቆጠራ ቢሮ ዘገባ በሶስት አስርት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከሶስት ጊዜ በላይ እጥፍ በማደግ 278 ሚሊዮን በመሆን ሀገሪቱን ከ10 ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ከሚኖራቸው ሀገሮች መካከል አንዷ ያደርጋታል፡፡
የኢትዮጵያ የሕዝብ ብዛት ለበርካታ አስርት ዓመታት በከፍተኛ ሁኔታ ወደላይ እያደገ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1967 ዓ.ም የሕዝቡ ብዛት 23.5 ሚሊዮን ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1990 ወደ 51 ሚሊዮን እና በ2003 ዓ.ም ወደ 68 ሚሊዮን አደገ፡፡ እ.ኤ.አ በ2008 ዓ.ም ቁጥሩ ወደ 80 ሚሊዮን አደገ፡፡ እ.ኤ.አ በ2013 የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ከ94 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወደ 70 በመቶ (66 ሚሊዮን) የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እድሜው ከ35 ዓመት በታች ነው፡፡ እ.ኤ.አ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ዓመታዊ ዓማካይ የሕዝብ እድገት መጣኔው ከ3 በመቶ በላይ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
እ.ኤ.አ በ2014 ዓ.ም 45 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እድሜው ከ15 ዓመት በታች ሲሆን 71 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ደግሞ እድሜው ከ30 ዓመት በታች ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2018 የዚህ ዓይነት የሕዝብ ኮሆርት ግምት ከ75 በመቶ እንደሚበልጥ ጥርጥር የለውም፡፡
ስኢትዮጵያ ወጣቶች ችግሮች በርካታ ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም በዩኤስኤአይዲ በተደረገ ጥናት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የከተማ ስራ አጥነት የተንሰራፋባት እና እስከ 50 በመቶ ስራ አጥ እንደሆነ እና 85 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚኖርበት በገጠሩ ደግሞ ስውር የሆነ ስራ አጥነት ተንሰራፍቶ እንደሚገኝ ይፋ አድርጓል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ እ.ኤ.አ በ2012 በዓለም አቀፍ የእድገት ማዕከል (International Growth Centre) በተባለ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት በወጣቶች ስራ አጥነት ላይ በተደረገ ሌላ ጥናት እ.ኤ.አ ከ2010 – 2015 የሚተገበረው የዕድገት እና ትራንስፎርሽን ዕቅድ የወጣቶችን ስራ አጥነት በቀጥታ አያካትትም፡፡
እ.ኤ.አ በ2012 ኢትዮጵያ ከዓለም ከትምህርት ገበታ ውጭ ከሆኑ ሀገሮች ሕዝቦች መካከል በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
ከኢትዮጵያ ወጣቶች ውስጥ ስራ አጥ የመሆናቸው ችግር ብቻ ሳይሆን ስራውም ቢገኝ ተቀጥረው ለመስራት የሚያስችል በቂ የሆነ መሰረታዊ የእውቀት ክህሎት የላቸውም፡፡ ወጣቶች በመንግስት ስራዎች ላይ ተወዳድረው ስራ ለማግኘት በስልጠና እና በክህሎት በብቃት እና በፍትሀዊ ውድድር ላይ በመመስረት ብቻ አይደለም የሚገቡት፡፡ ሆኖም ግን ከዚህም ባሻገር የፖለቲካ እና የማህበራዊ ግንኙነት ትስስር እና የፓርቲ አባልነት እንደ መስፈርት ይወሰዳል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ማንኛውም ወጣት በስራ እና በትክክለኛው መንገድ ከሚያገኘው ዲግሪ እና ዲፕሎማ ይልቅ የገዥው ፓርቲ አባል መሆን የበለጠ ጠቃሚ ነው፡፡ ከዚህም በላይ የገጠር ወጣቶች መሬት አልባነት መሆን ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን ፍልሰት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንዲሄድ እና ብጥብጥ፣ ስራ አጥነት እና ተስፋየለሽነት እየተንሰራፋ ያለበት ሁኔታን አስከትሏል፡፡
እ.ኤ.አ ጥቅምት 2017 ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ወጣት ኢንተርፕሪነሮችን ለማፍራት እና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመንባት የ400 ሚሊዮን ተዘዋዋሪ ፈንድ ኢንቨስትመንት በማድረግ በየዓመቱ በመቶዎች እና በሺዎች ለሚቆጠሩ አዲስ ተመራቂ ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጠር እና የወጣቱን ስራ የማግኘት እድል ለማሳለጥ ለግል ዘርፉ እገዛ ይደረጋል“ የሚል ንግግር አድርገው ነበር፡፡
በተጨባጭ በመሬት ላይ የሚታየው ግን ኢንቨስትመንቱም አልተተገበረም ወጣቶችም በሕዝባዊ እምቢተኝነት አምጸዋል፡፡ እናም አሁን ያለው ሁኔታ በተጨባጭ ይህን ይመስላል፡፡
እ.ኤ.አ በ2004 በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አገዛዝ “ብሄራዊ የወጣቶች ፖሊሲ” የሚል ፖሊሲ በማውጣት ከ44 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍጹማዊ ድህነት ወለል በታች እንደሆነ ግልጽ አድርጓል፡፡ የዚህ ዓይነት ድህነት በተንሰራፋበት ሁኔታ ወጣቱ በከፍተኛ ሁኔታ የችግሩ ሰለባ የሚሆን የህብረተሰቡ ክፍል ነው፡፡ ከዚህም በላይ ያ ፖሊሲ ወጣቶች ስራ ለማግኘት የአገዛዙ እና የገዥው ፓርቲ ደጋፊዎች እንዲሆኑ በማስገደድ ባዶ ሰነድ ሆኖ ሸረሪት አድርቶበት እና አቧራ ተኝቶበት ቀርቷል፡፡
እ.ኤ.አ ከ2006 ጀምሮ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያዎችን በማሰባሰብ ስኬታማ ባይሆንም የሕግ ጥበቃ ፈንድ ለማቋቋም ጥረት አድርጊያለሁ፡፡
እ.ኤ.አ በ2011 ይፋ ያልሆነ የፐብሊክ ፖሊሲ (ህዝብ መምሪያ) የምሁራን ቡድን ለማቋቋም እንዲያግዝ ለበጎ ፈቃደኞች ጥሪ አቅርቢያለሁ፡፡
ለዚህ ጥረት ስኬታማነት ለበርካታ ዓመታት ብዙ ጥያቄዎችን በማቅረብ ጥረት አድርጊያለሁ፡፡ ይህንን ሀሳብ ለተቃዋሚ ቡድኖች ሳይቀር አቅርቤው ነበር ምላሹ ጆሮ ዳባ ቢሆንም፡፡
ሌሎች የተለያዩ ትብብራዊ ጥረቶችን ሞክሪያለሁ ሆኖም ግን ጉዳዩን በውል በመያዝ ስራዬ ብለው አልወሰዱትም፡፡ የእኔ ጥረቶች ለምን እንደወደቁ በርካታ የሆኑ ምክንያቶችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ የረዥም ጊዜ ስራ እና የሰብአዊ መብት ትግሉን የእራስ ህይወት አድርጎ መውሰድ ለእያንዳንዱ ሰው ሊከብደው ይችላል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥበቃን ለማሻሻል ሊሰሩ የሚችሉ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ አጠቃላይ የሆነ የዲያስፖራ ሰብአዊ መብት ጥበቃ አጀንዳ ምንም ዓይነት የተለየ ከባድ ችግርን የሚያስከትል አይደለም፡፡
ወደፊት ለመጓዝ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር የሚደረጉ ትብብሮች ምን መሆን አለባቸው?
ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር ወደፊት እንዴት መራመድ ይችላሉ? እርሳቸው ከእኛ ጋር በምን ዓይነት ስምምነት ነው መስራት የሚችሉት?
እ.ኤ.አ በ2010 አሁን ላለንበት ሁኔታ ጠቃሚ የሆኑ የተወሰኑ አብሮ የመስራት የስምምነት ሃሳቦችን አቅርቤ ነበር፡፡
በተወሰኑ ጥቂት መሰረታዊ በሆኑ አብሮ የመስራት ሃሳቦች ስምምነት ካደረግን ውጤታማ የሆነ እና የመከባበር ግንኙነት ማድረግ እንደምንችል አምናለሁ፡፡
መረጃን መሰረት ያደረገ እሳቤን እናዳብር፣ ግምትን አሉ ባሌ መሰረት ያደረገን እሳቤ እናስወግድ፣
በእኔ አመላካከት በርካታ ነገሮችን የሚያነሱ እና በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ አሉታዊ የሆነ አመላከከት ያላቸው ሰዎች ግምትን አሉ ባሌን መሰረት ባደረገ መረጃ ላይ ይመሰረታሉ፡፡ ያለምንም ማስረጃ ትችት ያቀርባሉ፡፡ በተጨባጭ መረጃ ላይ በመመስረት እና ስልታዊ የሆነ ጥናት ሳያደርጉ መሰረት በሌላቸው እና በተደጋጋሚ በሚደረጉ ታሳቢዎች እና ግምቶች ላይ በመመስረት ይተነብያሉ፡፡ ታሳቢዎቻቸውን እንደገና ለመመርመር ፈቃደኞች አይደሉም እንዲሁም አዲስ መረጃዎችን ለመጠቀም ከእራሳቸው እሳቤዎች ጋር ቅራኔ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ፎርሙላ የመሰለ እሳቤን የመውደድ ዝንባሌ ያሳያሉ፡፡ እናም ነገሮችን ሁሉ ለመስራት አንድ ዓይነት መንገድ ብቻ አለ ወደሚል ዝንባሌ ያመራሉ፡፡
አንድ የቀድሞ አባባል እንዲህ ይላል፣ “እያንዳንዱ ሰው ለእራሱ ሀሳብ ብቻ ነው የሚገዛው ነገር ግን ለእራሱ እውነታዎች ተገዥ አይደለም፡፡“
የእራሳችንን አመለካከቶች እና ሀሳቦች ከተለያዩ ምንጮች ከተሰባሰቡ መረጃዎች በአንክሮ በመገምገም መሰረት አድርጎ መወሰን አለብን፡፡ አድሏዊነታችንን ማስወገድ አለብን፡፡ ክፍት የሆነ አእምሮን ለመያዝ ፈቃደኛ መሆን እና ለረዥም ጊዜ በቆዩ እና ወጥነት በሌላቸው አመለካከቶች እና ታሳቢዎች ላይ ሳንመሰረት ትክክለኛውን መንገድ ተከትለን መጓዝ አለብን፡፡
በዓለም ላይ ለማየት የምንፈልገውን ለውጥ እንሁን፣
የቀድሞ አባባል እንደሚለው አመልካች ጣታችንን በአንድ ሰው ላይ በምንቀስርበት ጊዜ ሶስቱ ጣቶቻችን ወደ እኛው ያመለክታሉ፡፡
ሆኖም ግን ለውጥ በሰው ላይ ይጀምራል፡፡ ጆርጅ በርናርድ ሻው እንዲህ ብለው ነበር፣ “ያለለውጥ መሻሻል አይቻልም፡፡ እናም አስተሳሰባቸውን የማይለውጡ ምንም ዓይነት ነገር ሊለውጡ አይችሉም፡፡“
ብዙዎቻችን እራሳችንን ሳይሆን ዓለምን ለመለወጥ እንፈልጋለን፡፡ በአሳዛኝ ሁኔታ በውስጣችን ያለውን ተቃርኖ አናስተውለውም፡፡
ዓለምን ለመለወጥ ከመቻላችን በፊት የምንለውጥበትን የአስተሳሰብ መንገድ መለወጥ አለብን፡፡
ጋንዲ እንዲህ በማለት አስተምረውናል፣ “በዓለም ላይ ሆኖ ለማየት የምትፈልገውን ለውጥ ሁን፡፡ ያ ለውጥ የሚመጣው ከአእምሮ እና ከልብ ነው፡፡ በመቀጠልም እንዲህ አሉ “እምነቶችህ ሀሳቦችህ ይሆናሉ፣ ሀሳቦችህ ቃላቶችህ ይሆናሉ፣ ቃላቶችህ ተግባሮችህ ይሆናሉ፣ ተግባሮችህ ደግሞ ልማዶችህ ይሆናሉ፡፡ ልማዶችህም እሴቶችህ ይሆናሉ፣ እሴቶችህ ዕጣ ፈንታዎችህ ይሆናሉ“ ነበር ያሉት፡፡
ወኔ ያለው ተናጋሪ ለመሆን ብዬ የመስበክ ወይም የማስመሰል ዓላማ የለኝም፡፡ ሆኖም ግን አብዛኞቻችን ግልጹን ነገር እንረሳዋለን፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ሚያዝያ 17 ቀን 2010 ዓ.ም