እንደማንኛቸውም የአፍሪካ ግፈኛ ገዢዎች በቅርቡ ያለፈው መለስ ዜናዊም፤ እራሱን ከሕይወት ባሻገር አድርጎ በማግዘፍ አስቀምጦ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መዳኛ (መድሃኔ ዓለም) ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም ጭምር ነኝ እያለ ያስፎከር ነበር፡፡ እራሱን ‹‹ሕልመኛ መሪ፤ የአፍሪካ መኩሪያ አፈ ጉባኤ፤ እና የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ከፍተኛው ተግባሪ›› አድርጎ አስቀምጦም ነበር፡፡ ባለፈው በጋ ወቅት ህልፈቱን ተከትሎ መነዛት የጀመረው ቅጥፈተ ፕሮፓጋንዳ፤ ጥንታዊነትን፤ ውዳሴን፤ አይረሳነትን፤ ተመላኪነት፤ የዘበት ተውኔት (የቀልድ ትያትር) ሆኖ አየታየ ነው፡፡ በመለስ ዜናዊ ፍቃድና ምርጫ የተሰየመው፤ የይስሙላው ጠቅላይ ሚኒስቴር ሃይለማርያም ደሳለኝ፤ ታማኞች በተሰገሰጉበት ፓርላማ ባደረገው ንግግር መለስን ከክርስቶስ በታች ብቸኛ በማድረግ ምርቃቱንና የራሱንም ታማኝነት መግለጫ መካቢያ ንግግሩን ሲያደርግ: ‹‹ዘልዓለማዊ ክብር ለታላቁ መሪያችን›› በማለት ነበር፡፡ ዋነኛው ታላቁ መሪ የሚባለው የሰሜን ኮርያው ኪም ኢልሱንግ እንኳ፤ ‹‹የሕዝብ ልጅ›› ከመባል ያለፈ ከበሬታ አልተቸረውም ነበር፡፡ ሃይለማርያም የተጣለበትን የፍጥምጥሞሽ መለኮታዊ ውክልና ተልእኮ እንደሃይማኖት ሰባኪ ለመወጣት ከፍተኛ ጉጉት እንዳለው በንግግሩ ቃለ መሃላ ሰጥቷል፡፡ ‹‹ አሁን ያለብኝ ሃላፊነት፤ ……. የማይረሳውን ታላቁን መሪያችንን ዓላማ፤ ምኞት፤ በተሳካ ሁኔታ መፈጸም ነው፡፡……….የታላቁ መሪያችን የእግር ኮቴ በመከተል፤ በአህጉር፤በዓለም አቀፍ ደረጃ ያን ተደማጭነት ያለውን ድምጽ ቀጣይ ማድረግ ነው፡፡ ታላቁ መሪያችን ተደናቂ የሃሳብ አፍላቂያችን ሞተር ብቻ ሳይሆን እራሱን በመሰዋት አርአያነትን ያስተማረም መሪ ነበር…….››