ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተጻፈ የግል ደብዳቤ (ትርጉም ከንግሊዘኛ)

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም 

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ 

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 8 ቀን 2018 ዓ.ም
ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ
ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት
አዲስ አበባ   ኢትዮጵያ  

“እንደማንኛውም ተራ ደቡብ አፍሪካዊ ዜጋ ዕለት በዕለት የምናከናውናቸው ተግባራት የሰው ልጆች በፍትህ ላይ ያላቸውን እምነት እና በእራስ የመተማመን መንፈስ በማጠናከር ለሁሉም ሕዝብ የተመቸ እና አንጸባራቂ ህይወት ለማስገኘት እንዲቻል ይህች ቆንጆ የሆነች ሀገር በፍጹም በፍጹም እንደገና አንዱ በሌላው የማትጨቆን እና የዓለም ሁሉ ውራጅ እንዳትሆን ጠንክረን መስራት አለብን፡፡” ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ እ.ኤ.አ በ1994 ካደረጉት የመክፈቻ ንግግር የተወሰደ

ውድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣

ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመሾምዎ ልባዊ የሆነ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክቴን ይቀበሉኝ፡፡ የኢትዮጵያ አዲስ ትውልድ አባል በኢትዮጵያ በጣም ከፍተኛውን የስልጣን እርካብ ተቆናጥጦ በማየቴ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡

በጋናዊው የኢኮኖሚ ጠበብት እና ጓደኛዬ በሆነው በፕሮፌሰር ጆርጅ አይቴይ ተመሳስሎ ታዋቂነት ያገኘውን አዲሱን ትውልድ ከኢትዮጵያ አዲሱ ትውልድ ጋር በማቆራኘት ቀደም ሲል ጀምሬ አቦሸማኔው ትውልድ እያልኩ ስጠራው ቆይቻለሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቄሮዎች፣ ፋኖዎች፣ ዘርማዎች እና ነብሮች በመባል ይታወቃሉ፡፡ የተለያዩ ስም ቢሰጣቸው ማነናታቸዉን አይቀይረዉም። ጽጌራዳ በሌላ በማንኛውም ስም ብትጠራም ያው የሚያውደውን ሽታዋን ጽጌረዳነቷን ይዛ ትቀጥላለች አንደሚባለው፡፡ የኢትዮጵያ አቦሸማኔ ትውልድ (ወጣቱ ትውልድ) አባላት በልቤ ጓዳ እና በህሊናዬ ውስጥ የተለዬ ቦታ አላቸው፡፡

ለድፍን አስራ ሶስት ዓመታት ያህል ለኢትዮጵያ ወጣቶች መብት መከበር በመከራከር ድምጼን ከፍ አድርጌ ስጮህ እና ስለሰብአዊ መብት መከበር ስሰብክ ቆይቻለሁ፡፡ እርስዎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመሾምዎ ገደብ የሌለው ግላዊ ደስታ እንደተሰማኝ ይገነዘባሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ እርስዎ በሀገሪቱ ውስጥ የመጨረሻ ከፍተኛ የተባለውን የስልጣን ርካብ በመቆናጠጥዎ ይኸ አንጸባራቂ ድል በቀጣይነት ምንም የሚያቆመው ነገር ሳይኖር ቅብብሎሹ ለኢትዮጵያ ወጣቶች ተምሳሌት ሆኖ አነሱም በሀገራቸው ከፍተኛ ቦታ ለመያዝ አንደሚጥሩ ሙሉ ተስፋ አለኝ። እስቲ ከማያ አንጌሎ ደራሲዋ ጥቂት ቃላትን በመዋስ የሁኔታውን አስደማሚነት ግልጽ ላድርገው። የኢትዮጵያ ወጣቶች   “እንደዚሁም ሁሉ ያቀረቀሩ ጭንቅላቶቻቸው ቀና ይላሉ፣ ያቀዘዙ ዓይኖቻቸው ጎላ ይላሉ፣ ትከሻዎቸው ከፍ ይላሉ“።

ለፕሬዚዳንቶች እና ለሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣኖች ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን፣ ዶናልድ ትራምፕን እና ሌሎች የዓለም መሪዎችን ጨምሮ እውነታውን መስበክ የመንገር ወይም የመጻፍ ባህል አለኝ፡፡ ላለፉት አስራ ሶስት ዓመታት ገደማ ያህል ሁልጊዜ ሰኞ ሳላቋርጥ ለኢትዮጵያ ባለስልጣኖች ስጽፍ ቆይቻለሁ፡፡ ሆኖም ግን በጥንቃቄ ቢያነቡኝም ሳይሰሙኝ ቆይተዋል፡፡

ለእራሴ መገለጫ ስል ነው ይህንን ደብዳቤ በመጻፍ ላይ ያለሁት፡፡ ሆኖም ግን ቃላቶቼ እና ሀሳቦቼ ለበርካታ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን እና ሳምንታዊ ትችቶቼን ላለፉት አስራ ሶስት ዓመታት ሲከታተሉ ለቆዩት ለኢትዮጵያ ወዳጆች እና ለሌሎች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሚሊዮኖች እኔን በሬዲዮ እና በሌሎች ብዙሃን የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ዘዴዎች ለሚያዳምጡኝ ብዙ ግንዛቤዎችን አስጨብጠዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

በአሁኑ ጊዜ ይህንን ደብዳቤ የጻፍኩት ለበርካታ ምክንያቶች ነው፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ ተስፋው የጨለመውን የኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ አንገት ቀና ለማድረግ በሚያደርጉት ጥረት በመርህ ላይ የተመሰረተ ድጋፌን ከጎንዎ ሆኘ ለማበርከት ያለኝን ጽኑ እምነት ለመግለጽ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ትንሳኤ በወጣት ልጆቿ እውን እንደሚሆን ሁልጊዜ አምናለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች በተደጋጋሚ ተስፋ ከማጣት እና የሚጠብቁትን ነገር ካለማግኘታቸው የተነሳ ተስፋ ቆርጠዋል፣ ልባቸው ተሰብሯል፣ እምቢተኛ ሆነዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በማመጽ ላይ ናቸው ምክንያቱም በአምባገነናዊ ስርዓት ለረዥም ጊዜ ተንሰራፍቶ የቆየውን የሰብአዊ መብት ረገጣ፣ ግዴለሽነት እና ደንታቢስነት ለማጥፋት በመወሰናቸው ነው፡፡ ከታሪክ መገንዘብ እንደሚቻለው እንደሌሎች ሀገሮች ወጣቶች ሁሉ እንደዚህ ያለውን ጨቋኝ እና አምባገነናዊ አገዛዝ በማስወገድ የወደፊት ደህንነታቸውን ሊጠብቅላቸው የሚችል አዲስ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ማቋቋም መብታቸው እና ተግባራቸው ሆኖ አግኝተውታል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ እርስዎን የኢትዮጵያ ወጣቶች መሪ አድርጌ እቆጥርዎታለሁ፡፡ እኔ ከእርሰዎ ጋር እና ከጎንዎ ነኝ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ በሹመትዎ ስነስርዓት ላይ አድርገውት በነበረው ንግግርዎ እና ባነሷቸው እና በዳሰሷቸው በርካታ ጉዳዮች ሁሉንም ባይሆን እንኳ በበርካታዎቹ ላይ አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት ስለምመኝ ነው፡፡ በዚያ ንግግርዎ በበርካታ ጉዳዮች ላይ የእኔን ቋንቋ ሲናገሩ እንደነበር ላረጋግጥልዎት እወዳለሁ፡፡ በበርካታ ነገሮች ላይ ስምምነት አለን፡፡

በሶስተኛ ደረጃ ለዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ያለዎትን አቋም በአዎንታዊ መልኩ እንደምመለከተው ላረጋግጥልዎ እፈልጋለሁ፡፡ እውቀታቸውን፣ ሀብታቸውን እና ልምዳቸውን በመያዝ ሀገራቸውን ለማበልጸግ እና ከሩቅ ሆነው ሀገራቸውን ለሚያግዙ ዜጎች እጅዎን ዘርግተው እንደሚቀበሏቸው ግልጽ አድርገዋል፡፡ ለሁሉም ጉድለቶች ሁሉ ያለዎትን በጎ አመለካከት በጣም አድርጌ አደንቃለሁ፡፡ ይህ ሁኔታ የጥሩ አመራር መገለጫ ነው፡፡

በአራተኛ ደረጃ ወደፊት በምንሄድበት ጊዜ እንደ ሀሳብ አፍላቂ የእራሴን አቋም ግልጽ ለማድረግ እመኛለሁ፡፡ የእኔ መልዕክት በወደፊቱ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ላረጋግጥልዎ እወዳለሁ፡፡ የታሪክ ቆሻሻ ማጠራቀሚያውን ቅርጫት ለብቻው አንተወዋለን፡፡

ስለዚህ ደብዳቤ ረዥምነት ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ እዚህ በማቀርባቸው በርካታ ጉዳዮች ሀሳቤን በቁልፍ ጉዳዮች እና ርዕሶች ላይ አድርጊያለሁ፡፡

እርስዎ ከዕጣ ፋንታ ዕድል ጋር የጊዜ ቀጠሮ ይዘዋል… እባክዎትን በማንዴላ ጫማ ይራመዱ!

በእኔ መልካም አስተያየት እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር አንድ እና አንድ ተልዕኮ ብቻ አለዎት፡፡ ኔልሰን ማንዴላ ለደቡብ አፍሪካ ሕዝቦች ፕሬሲደንት ሲሆኑ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር እርስዎም በበኩልዎ በኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ በማድረግ ማሳካት ነው ያለቦት። “ይህች ቆንጆ የሆነች ሀገር በፍጹም በፍጹም እንደገና አንዱ በሌላው የማትጨቆን እና የዓለም ሁሉ ውራጅ እንዳትሆን ጠንክረን መስራት አለብን::

እ.ኤ.አ በ1964 ዓ.ም በሪቮኒያ የዳኝነት ችሎት ላይ ኔልሰን ማንዴላ በዝንጀሮው የአፓርታይድ ፍርድ ቤት ፊት ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን መስጠት በመተው ከ30 ዓመታት በኋላ ደቡብ አፍሪካ ተጠብቃ እንድትቆይ ያደረገውን ንግግራቸውን በመምረጥ እንዲህ ብለው ነበር፣

“በህይወት ዘመኔ እራሴን ለአፍሪካ ሕዝቦች ትግል መስዋዕት አድርጊያለሁ፡፡ የነጮችን የበላይነት ተዋግቻለሁ፡፡ ሁሉም ህዝቦች በፍቅር እና በእኩልነት በአንድነት የሚኖሩበት ለዴሞክራሲያዊ እና ነጻ ሕዝብ ህልውና እውን መሆን ስታገል ቆያቻለሁ፡፡ የእኔ መኖር ዋና ዓላማ ለዚህ ዓላማ ስኬታማነት ነው፡፡ አስፈላጊ ሆኖም ሲገኝ እስከሞት ድረስ የምሄድበት መርሄ ነው“ ነበር ያሉት፡፡

ማንዴላ የእድሜ ልክ እስራት ተበይኖባቸው እነዚህን ቃላት በሚናገሩበት ጊዜ ከእርስዎ እድሜ በ5 ዓመታት ብቻ ይበልጡ ነበር፡፡

እነዚህን ቃላት ሁልጊዜ እንዲያነቧቸው እና በተግባር ላይ እንዲያውሏቸው እማጸንዎታለሁ፡፡ የአማራን፣ የትግሬን፣ የኦሮሞን … የበላይነት መዋጋት አለብዎት፡፡ ይህንን ነው ወጣቱ ትውልድ በትክክል ከእርስዎ የሚጠብቀው እና እንዲያደርጉለትም የሚፈልገው፡፡ ይህች ቆንጆ ሀገራቸው በፍጹም በፍጹም አንዱ በሌላው የማይጨቆንባት እንድትሆን ይፈልጋሉ፡፡

እባክዎትን ከታሪክ ጋር ያሎትን ቀጠሮ እንዳይዘነጉ!

በኢትዮጵያዊነት ላይ፣

ኢትዮጵያዊነት ለልቤ ቅርብ እና ውድ ነገር ብቻ አይደለም፡፡

ይልቁንም ኢትዮጵያዊነት ለእኔ ልቤ፣ አዕምሮዬ እና ህሊናዬ ነው፡፡

በንግግርዎ ላይ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ብዙ ጊዜ ደጋግመው አንስተዋል፡፡ እናም መቁጠሬን አቋርጨ ነበር ምክንያቱም ስለደከምኩ አልነበረም ሆኖም ግን ከደስታዬ የተነሳ ነው፡፡ እስከ አሁን ድረስ በኢትዮጵያ በሀገር መሪ ደረጃ ላይ እንደዚህ ዓይነት ንግግር ማንም ሰው ሲያደርግ አይቸም ሰምቸም አላውቅም፡፡ እንዲያውም እስከአሁንም ድረስ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል የሚያሳፍር ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ግን እርስዎ የኩራት እና የዝና ቃል አድርገውታል፡፡

በሹመት በዓል ንግግርዎ ላይ ስለዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ጉዳዮች በሚናገሩበት ጊዜ በደስታ ተውጨ ፈገግ ብየ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያንን ከኢትዮጵያ ውስጥ መውሰድ ይቻላል፣ ሆኖም ግን ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ አውጥቶ መውሰድ ፍጹም አይቻልም፡፡

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2 ቀን 2006 ዓ.ም በኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ሰብአዊ መብት ጥበቃ ትግል ስገባ ያደረግሁትን እና እንዲህ የሚለውን የእኔን የመጀመሪያ ንግግር፣ የመጀመሪያ ፕሮግራሜን አስታወሰኝ፣ “በእርግጠኝነት ላረጋግጥላችሁ ኢትዮጵያን ለቅቄ ብሄድም ሆኖም ግን ኢትዮጵያ በፍጹም ለቃኝ አልተወችኝም፡፡ የእኔ ጉዳይ ቀላል ነገር ነው፡፡ እንዲህ የሚለውን የቆዬ አባባል እስቲ እናስታውስ ‘የኢትዮጵያን ልጆች ከኢትዮጵያ መውሰድ ይቻላል ሆኖም ግን ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያ ልጆች ልብ ውስጥ መውሰድ አይቻልም! “እኔ በእርግጠኝነት እንደዚህ ነው የማስበው፡፡“

ላለፉት አስራ ስስት ዓመታት ገደማ ያህል ይህንን የተመጠነ እና ዒላማውን መሰረት ያደረገ ትችት ለበርካታ ጊዜ ሳቀርብ ቆይቻለሁ፡፡ ያ ሁኔታ እንዴት ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ እንዳደረገኝ ማሰብ ይችላሉ፡፡

በየሳምንቱ በማቀርባቸው ትችቶቼ ምክንያት ከጥቂት ወራት በፊት ጥቂት ሰዎች ስለእኔ ኢትዮጵያዊነት ጥርጣሬ እንዳላቸው ግልጽ አድርገዋል፡፡ ለጥርጣሪያቸው መሰረት የሆነ ምንም ዓይነት ማስረጃ አንድ ቃል እንኳ ማቅረብ አልቻሉም፡፡ የአምባገነናዊ አገዛዛቸውን እኩይ ምግባር ማቋረጫ በሌለው መንገድ በመቃወሜ ብቻ ኢትዮጵያዊነት ይጎድለዋል የሚል የተሳሳተ መንገድ ወስደዋል፡፡ ሆኖም ግን ለእነርሱ ያለኝ የእኔ ምልሽ እንዲህ የሚል ጠቃሚ ነጥብን ይዟል፣ “ልጁን ከኢትዮጵያ ልትወስዱት ትችላላችሁ ሆኖም ግን ኢትዮጵያዊነትን ከልጁ ልብ ውስጥ ልትወስዱ አትችሉም“ የሚል ነበር፡፡

እንደው መደጋገም አይሁንብኝና ስለኔ ኢትዮጵያዊነት ጥርጣሬ ያላቸው በቂ ማስረጃ አንድያቀርቡ አለዚያም ደግሞ ለወገኖቼ መብት መከበር በመታገሌ ብቻ ይህንን የመሰለ አሉባልታ የሚያራምዱት ሰዎች ይቅርታ ሊጠይቁኝ ይገባል፡፡ እስከ አሁን ድረስ ከእነዚህ ከሁለቱ ነገሮች አንዱንም በተግባር አላየሁም፡፡ እውነት ለመናገር መሳሳትን እምኖ ይቅርታ መጠየቅ የሰውን ልጅ ተስፋ ለዘላለም ያለመልማል፡፡

ለእኔ ስለኢትዮጵያ እና ስለኢትዮጵያ ሕዝቦች መናገር እና መጻፍ በምትሀታዊ ኃይል የታደልኩበት የተቀደሰ እና የጸና አቋሜ ነው፡፡ እኔ የምጽፈው አሁን ላለው ትውልድ ብቻ አይደለም፣ ለሚመጣው ትውልድም ጭምር ነው፡፡ ከብዙ ጊዜ ጀምሬ እንደምመለከተው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚሰቃይበት እና መከራውን በሚያይበት ጊዜ እነዚህ ብሶቱን የሚያጋልጡትን እና የሚያወጡትን ጽሁፎች እያዘጋጀሁ ማውጣቴ ለእኔ መጽሀፍ ቅዱሶቼ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን የእኔ ወንድሞች ለማ መገርሳ እና ቴዎድሮስ (ቴዲ አፍሮ) ካሳሁን፣ ገዱ አንዳርጋቸው፣ እርስዎ እራስዎ እና ሌሎቹ በርካታዎቹ ወጣቶች በአሁኑ የ”ሰላም ፌስቲቫል” ላይ የሚሳተፉትን ጨምሮ እኔ እስከ አሁን ድረስ ላድርገው ከምችለው በላይ በተሻለ ሁኔታ ስለኢትዮጵያዊነት ሰብካችኋል፡፡

ለማ እንዲህ ብሎ ነበር፣ “ኢትዮጵያዊነት ጥልቅ ሱስ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ እና አእምሮ ውስጥ ያለ ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን ልብ እና አእምሮ ተከፍቶ የሚታይ ቢሆን ሊገኝ የሚችለው የተባበረው ኢትዮጵያዊነታችን ነው“ ነበር ያለው፡፡ በተጨማሪም እንዲህ ብሏል፣ “ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ የተሰባሰቡ፣ በአንድ ላይ የሚፈጩ እና በአንድነት የሚበሉ እና እንደ ሰርገኛ ጤፍ ሊለዩ የማይችሉ ናቸው፡፡“

ገዱ አንዳርጋቸው እንዲህ ነበር ያለው፣ “ኢትዮጵያዊነት አንድነት ነው፣ ኢትዮጵያዊነት አብሮነት ነው፣ ኢትዮጵያዊነት እርስ በእርስ ተከባብሮ በአንድነት መኖር ነው፡፡“

ቴዲ አፍሮ ስለኢትዮጵያዊነት እንዲህ በማለት አቀንቅኗል፣ “ኢትዮጵያ ስሟ ሲነሳ የማይጮህ ማን አለ! ኢትዮጵያ ሀገሬ በአንች አይደለም ተከብሬ ያለሁት?“ ነበር ያለው፡፡

ከዚህም በላይ ትናንሽ ልጆች እንኳ ስለኢትዮጵያዊነት ይዘምራሉ፡፡ እንዲህ በማለት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ይጮሀሉ፣ “ኢትዮጵያ ትናንት ነበረች፣ አትዮጵያ ነገም ከነገ ወዲያም ትኖራለች፣ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች፡፡“ እነዚህን የ7 ወይም የ8 ዓመት ህጻናት ለኢትዮጵያ ሰላም እያሉ በቤተክርስቲያን ውስጥ ሲዘምሩ ስመለከት ዓይኔ በእንባ ይሞላል፡፡ ሰላም ለሀገራችን፡፡ የማይሳነው አምላክ ሰላምን ይላክልን፡፡

ለእኔ ኢትዮጵያዊነት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሰው የመሆን ጉዳይ ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም የመጀመሪያ የሆነውን ንግግሬን ባቀረብኩ ጊዜ ኢትዮጵያዊነት በእግዚአብሄር የተሰጠን ጸጋ መሆኑን እንዲህ በማለት ገልጨው ነበር፣ “እኛ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያውያን ነን፣ በኃያሉ አምላክ በአንድ የተገመድን በዓለም ላይ የምንገኝ የብሄረሰቦች ሙዚየም ነን፡፡ ይህንን ነገር በመጽሀፍ ቅዱስ ተመልከቱ፡፡ ይህንን ጉዳይ በቁራን ተመልከቱ፡፡ በመጽሀፍ ቅዱስ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ሰላሳ ሶስት ጊዜ የተጠቀሱ መሆናቸውን ይነግሩናል፡፡ በቅዱሱ ቁራንም ከዚያ ላላነሰ ጊዜ የተጠቀሱ መሆናቸውን ይነግሩናል፡፡“

በበዓለ ሹመትዎ ጊዜ ንግግርዎን በመቀጠል እንዲህ ብለው ነበር፣ “በውጭ የሚኖሩ እና እዚህ በሀገር ቤት ውስጥ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል ከልባችን በመነጨ ሁኔታ እርስ በእርሳችን ይቅር እንባባል፡፡“

የእርስዎን ምክር እቀበላለሁ፡፡ በእኔ ኢትዮጵያዊነት ላይ ጥርጣሬ ባላቸው ሰዎች ላይ ጥላቻ ሳልይዝ የእኔን ኢትዮጵያዊ ያለመሆን ሕጋዊ ለማድረግ ሲጥሩ ለቆዩት ሰዎች በሆዴ ምንም ዓይነት ቂም ሳልይዝ የማያቋርጠውን የሰብአዊነት መብት መከበር ትግሌን ሳላቋርጥ እቀጥላለሁ፡፡ የእኔን ኢትዮጵያዊነት በመጠራጠራቸው ከልብ በመነጨ ሁኔታ ከውስጤ ይቅርታ አደርግላቸዋለሁ፡፡

የተባበሩ የኢትዮጵያ ወጣቶች አይሸነፉም! 

የወጣቶች ተስፋዎች፣ ምኞቶች እና ህልሞች በእርሶ እጅ ነው፡፡ ካሉበት ችግር አንድያድኗቸው በአንክሮ ይጠባበቃሉ፡፡

ሁልጊዜ ስለኢትዮጵያ ወጣቶች መከራ እና ስቃይ በመጨነቅ ድምጼን ከፍ አድርጌ ስጮህ በመቆየቴ ኩራት የሚሰማኝ መሆኔን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

ላለፉት አስራ ሶስት ዓመታት ገደማ ያህል በኢትዮጵያ ወጣቶች ላይ ያለኝን ፍጹም የሆነ እምነት ሳውጅ ቆይቻለሁ፡፡ እ.ኤ.አ መስከረም 17 ቀን 2016 ዓ.ም ከርዕዮት ዓለሙ ጋር አድርጌው በነበረው ቃለ መጠይቅ (ለ14 ደቂቃዎች የሚቆየውን ክሊፕ ይመልከቱ) ያለኝን አቋም በማያወላውል መልኩ ገልጫለሁ፡፡

እኔ ሁልጊዜ እራሴን በጉማሬው (የቀድሞው) እና በአቦሸማኔው (በአዲሱ) ትውልድ መካከል ያለ አድርጌ እቆጥራለሁ፡፡

እ.ኤ.አ ሰኔ 2010 የኢትዮጵያን ወጣቶች ሁኔታ የገለጽኩበት መንገድ እንዲህ የሚል ነበር፣“የኢትዮጵያ ወጣቶች ያሉበት ደስታ የራቀው ሁኔታ ባልተጠበቀ መልኩ ሊፈነዳ የሚችል በሰዓት የተሞላ እና የተቀበረ የጊዜ ቦምብ ማለት ነው፡፡ የወጣቶች ተስፋ የመቁረጥ፣ የደስታ እጦት፣ እምነት የማጣት እና ለብዙ ጊዜ ተንሰራፍቶ በሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ዕድሎች እጦት እና መቃወም በማይቻልበት በፖለቲካ ጭቆና ተዘፍቀው ያሉበት ሁኔታ ነው፡፡ ወጣቶች ለነጻነታቸው እና ለመሰረታዊ ለውጥ እያደረጉት ያለው ጥረት ለዚህ ሁኔታ ተጨባጭነት ያለው ማስረጃ ነው፡፡ ብቸኛ ጥያቄ ሆኖ ሊቀርብ የሚችለው የሀገሪቱ ወጣቶች ለውጡን ሊያመጡ የሚችሉት በኃይል እና በአመጽ ነው ወይስ ደግሞ በልላ በሰላማዊ መንገድ የሚለው ነው፡፡“

እ.ኤ.አ በ2018 የኢትዮጵያ ወጣቶች ኃይል ያልተቀላቀለበትን እና ሰላማዊ የሆነ የትግል መንገድን በመምረጣቸው እፎይታን አግኝቻለሁ፡፡

እ.ኤ.አ የካቲት 2011 አቅርቤው በነበረው ትችቴ የአፍሪካ ወጣቶች ተባበሩ በፍጹም እንዳትሸነፉ በማለት አውጀ ነበር፡፡ ጋንዲ እንዲህ ብለው ነበር “ኃይል ከአካላዊ ብቃት ወይም ደግሞ ከጠብመንጃ፣ ከታንኮች እና ከጦር አውሮፕላኞች ጋጋታ የሚመጣ አይደለም፡፡ ኃይል የሚመጣው ከማይበገረው የዓላማ ጽናት ብቻ ነው“ ነበር ያሉት፡፡

እ.ኤ.አ በ2013 የእኔ መፈክር ለሁልጊዜ የሚሆነው እና ሆኖም የሚቆየው ‘የኢትዮጵያ ወጣቶች ተባበሩ በፍጹም እንዳትሸነፉ! ኃይል ለኢትዮጵያ ወጣቶች!‘ የሚል ነው በማለት አውጀ ነበር፡፡ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለኝም የኢትዮጵያ ወጣቶች ተባብረዋል በፍጹም ሊሸነፉ አይችሉም፡፡

እ.ኤ.አ 2013ን የኢትዮጵያ አቦሸማኔው ትውልድ አባላት ዓመት ነው በማለት አውጀ ነበር፡፡ እናም የኢትዮጵያ ወጣቶች የሰላማዊ ለውጥ እና የእርቅ ጉባኤን እንዲመሩ ተማጥኘ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ በ2014 አቅርቤው በነበረው ትችቴ “በእኔ አመለካከት የ21ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ አንገብጋቢው ችግር የኢትዮጵያ ወጣቶች ችግር ነው” በማለት ጽፌ ነበር፡፡

በተለያዩ በርካታ አጋጣሚዎች የኢትዮጵያ ወጣቶች በሰላማዊ መንገድ ሀገራቸውን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በማሸጋገር የእራሳቸውን ዕድል መወሰን አለባቸው የሚለውን የማይናወጽ እምንቴን ስገልጽ ቆይቻለሁ፡፡

እጅግ ከብዙ ሺ ኪሎ ሜትሮች ውቅያኖሶችን በማቋረጥ ለኢትዮጵያ የአቦሸማኔው ትውልድ በጠርሙስ ውስጥ እንዲህ የሚል ልዩ መልዕክት ልኪያለሁ፣ “ነጻ ሆናችሁ ተፈጥራችኋል! ነጻ ሆናችሁ መኖር አለባችሁ! ነጻ ሆናችሁ እንዳትኖሩ ግን ተፈርጃችኋል!“

ኢትዮጵያን ከህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) የጭቆና አገዛዝ እና አምባገናዊ የብረት መዳፍ ውስጥ ፈልቅቆ ሊያወጣ የሚችል ኃይል የኢትዮጵያ የአቦሸማኔው ትውልድ ብቻ እንደሆነ አውጃለሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የአቦሸማኔው ትውልድ እየተደረገ ያለው ሁኔታ ይህንን እውነታ በጉልህ እያሳየ መሆኑን አምናለሁ፡፡

ኔልሰን ማንዴላ እንዲህ የሚል ምልከታ አድርገው ነበር፣ “የእኛ ልጆች ትልቁ ሀብቶቻችን ናቸው፡፡ የእኛ የወደፊት አለኝታዎች ናቸው፡፡ በእነርሱ ላይ የጭቆና ተግባራትን የሚፈጽም የማህበረሰባችንን ክር በመበጠስ ሀገራችንን የሚያዳክም ኃይል ነው” ነበር ያሉት፡፡ የኢትዮጵያ ታላቅ ሀብቶች ፍጹም በሆነ መልኩ ተረስተው፣ መብቶቻቸው ተጨፍልቀው፣ ባክነው እና ከጥቅም ውጭ ተደርገው ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች የኢትዮጵያ ታላቅ ሀብቶች መሆናቸውን ሁልጊዜ አምናለሁ፣ ሆኖም ግን ለሀገሪቱ የወደፊት አለኝታ የሆኑት ወጣቶች ለአደገኛ ሁኔታ ተጋልጠው ይገኛሉ፡፡

ይህንን ሁሉ ካልኩ በኋላ ያለውን የፖለቲካ እና የማህበራዊ ጉዳይ እውነታ ከተመለከትኩ በኋላ በኢትዮጵያ የወደፊት ዕታ ፈንታ ላይ ተስፋ የቆረጥኩ መሆኔን አምኛለሁ፡፡ ከኮሌጅ እየተመረቁ የሚወጡትን ሥራ ያጡ ወጣቶችን ወይም ደግሞ ቴክኒካዊ ስልጠና ወስደው ያጠናቀቁ ወጣቶች የኮብል ስቶን ድንጋይን እንዲደረድሩ መደረጋቸውን ከሚወጡት ሪፖርቶች እየሰማሁ እና እያነበብኩ እጅጉን በጣም አዘንኩ፡፡ እንደነዚህ ያሉ ወጣቶች ለሁሉም ዓይነት ምስቅልቅል ችግሮች፣ ለአደንዛዥ እጽ እና ለሌሎች የሞራል ዝቅጠት ቅጥ አምባር ድርጊቶች ተዳርገው ማየት እና መስማት የሚያም ነገር ነው፡፡ በዚህ ጭጋጋማ ሁኔታ ላይ እንደ ለማ መገርሳ፣ አብይ አህመድ፣ እስክንድር ነጋ፣ አንዷለም አራጌ፣ እማዋይሽ ዓለሙ ርዕዮት ዓለሙ እና ሌሎች በርካታዎች ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች እየፈነጠቁት ያለውን ብርሀን ማየት በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡

በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ብሩህ ቀኖች እየመጡ ስለሆነ ከምንጊዜውም በላይ የበለጠ ደስተኛ ነኝ፡፡ እንደዚህ ዓይነቱን አባባል ከዚህ ቀደም ከትክክለኛው እውናዊነት ነባራዊ ሁኔታ ይልቅ በተመሳስሎ መልክ ብዙ ጊዜ ተናግሬዋለሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ብሩህ ቀኖች በመዳፎቻችን ውስጥ ናቸው፡፡ እንደ እርስዎ እና ከላይ እንደጠቀስኳቸው ያሉ ፈቃደኛ የሆኑ፣ ችሎታ ያላቸው እና ከመቅጽበት ወደ ተግባር የሚለውጡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት መሪዎች አሉን፡፡

ከእኔ ብርቅዬ አቦሸማኔ ትውልድ አባላት ጋር እንደሆኑ፣ እንዲቆዩ እማጸንዎታለሁ፣ እለምንዎታለሁ፡፡

ስለሰላማዊ ለውጥ፣

ከላይ እንደጠቀስኩት በበርካታ ጉዳዮች ላይ አንድ ዓይነት ሀሳቦችን እናስባለን፡፡ ሰላማዊ ትግል በእርግጠኝነት አንዱ እና ዋናው ነው፡፡

አምባገነንነትን እና ጭቆናን በሰላማዊ መንገድ ታግሎ ለማስወገድ በተጨባጭ ተግባር እና በህልዮት ሁልጊዜ አምናለሁ፡፡

“ታላቁን ማንቃት፡ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በእናት ሀገራቸው ለውጥ ለማምጣት ይችላሉን?“ በሚል ርዕስ ለመጀመሪያ ጊዜ አድርጌው በነበረው ንግግር በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት መከበር ለማደርገው ትግል ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን እንዲሰጡኝ እና ከጎኔ እንዲሰለፉ ተማጽዕኖ አቅርቤ ነበር፡፡ “በኢትዮጵያ ውስጥ በሚደረገው የሰብአዊ መብት ትግል ውስጥ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት በጦር ሜዳ ተሰማርቶ በደም ጨቅይቶ እና የሬሳ ክምርን ከምሮ ሳይሆን በኢትዮጵያውያን ወንዶች እና ሴቶች ልቦች እና በሚያስቡ አእምሮዎች መልካም ፈቃደኝነት ብቻ ነው” ብዬ ተናግሬም ነበር፡፡

ለአስራ ሶስት ዓመታት ገደማ ያህል የኢትዮጵያውያንን እና መልካም ፈቃድ ያላቸውን በዓለም ላይ የሚገኙ ሕዝቦችን ልቦች እና አአምሮዎች ለማሸነፍ በየሳምንቱ ሰኞ በማወጣው ትችቴ አንዳንዶቹ ቅዱስ ጽሁፎች እያሉ የሚጠሯቸውን እያዘጋጀሁ ስታገል ቆይቻለሁ፡፡ ሁልጊዜ ሰላማዊ ትግልን መሳሪያ በማድረግ ትግላችንን የምናራምድ ሰዎች በተለይም ሁሉንም ቀንበር የተሸከሙት፣ የሚሞቱት እና በእስራት የሚማቅቁት የኢትዮጵያ ወጣቶች በአሁኑ ጊዜ ያለምንም ደም መፋሰስ ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መለወጥ እንደሚቻል እርግጠኞች ሆነናል፡፡

በመጀመሪያ ጊዜ አድርጌው በነበረው ንግግሬ እኔ የክርስቶስን አስተምህሮ ከልብ እና በሙሉ ስሜት ያደንቁ የነበሩት የሁለት መሪዎች የማህተመ ጋንዲ እና የማርቲን ሉተር ኪንግ ደጋፊ እንደሆንኩ ገልጨ ነበር፡፡ በሰላማዊ ትግል፣ በእውነት እና በፍቅር መንገዶች ድል መቀዳጀትን አምናለሁ፡፡ ከዚህም በላይ እነዚህ መርሆዎችን ማወጅ በእራሱ በቂ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ጋንዲ እና ኪንግ ለሰው ልጅ ከፍተኛ መገለጫ የሆነውን የፍትህ ፍቅር፣ ለከፍተኛው ክብር ለእውነት መቆምን እና ከፍተኛ እሴት ላለው ለወንድ እና ለሴት ጓደኞቻችን ፍቅር ማሳየትን አስተምረውናል፡፡ ፍትህ ቀጥ ብሎ በመቆመበት ጊዜ ኃይለኝነት ቦታ የለውም፡፡ የሕግ የበላይነት በሰፈነ ጊዜ ለጭቆና መንገድ ቦታ የለውም፡፡

ስለአመራር ሰጭነት፣

ማንዴላ “ረዥሙ ጉዞ ለነጻነት” በሚለው በግለ የህይወት ታሪክ መጽሐፋቸው እንዲህ የሚል ጽሁፍ አስፍረው ይገኛል፣ “እውነተኛ መሪ ከመንጋዎቹ ኋላ ይከተላል፡፡ ፈጣን እና ንቁ የሆኑት ወደፊት በመሄድ እንዲመሩ፣ ሌሎች ደግሞ እንዲከተሉ፣ በአጠቃላይ ግን ከኋላ እየተመሩ እንዳሉ በማይታወቅ መልኩ አመራር መስጠትን ይፈቅዳል“ ይላል፡፡

የእርስዎ ፈጣኖች እና ንቁ አቦሸማኔዎች ወደፊት እንዲሄዱ ይፍቀዱ እናም ቀሪዎቹን እኛን የጉማሬዎችን ትውልድ አባላት (የቀድሞ ትውልድ) ከጎን ሆነን እንድንመለከት ያድርጉ፡፡

በመጀመሪያ ጊዜ አድርጌው በነበረው ንግግሬ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አቅርቤ ነበር፣

ለሰው ልጆች መልካም ነገርን ለማድረግ ሲሉ የግል ፍላጎታቸውን በማመቅ የሚታትሩ መሪዎችን ማፍራት እንችላለን? መሪነት የርዕይ ሌላው ገፅታ ነው፡፡ የግል ፍላጎትን ለማሳካት ወይም ደግሞ ገብጋባ ፍላጎትን ለማርካት የማይፈልጉ እና መልካም ነገርን ብቻ ለመስራት ፍላጎቱ ያላቸውን መሪዎች ማፍራት እንፈልጋለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንደዚህ ያሉ ባህሪያትን የተላበሱ በርካታ መሪዎች በመካከላችን አሉ ሆኖም ግን ወደፊት በመምጣት የእኛን ጉዞ በመቀላቀል ጉዞውን መከተል ይኖርባቸዋል!

ኢትዮጵያ በጣም ሩቅ በማይባል ጊዜ እራሳቸውን በማሳመን ብቻቸውን መፈጸም የሚችሉ እና ህልማቸውን በእራሳቸው ጭንቅላት ውስጥ ብቻ አድርገው ለሕዝቡ ግን ቅዠት የሆነ ነገር የሚያስቡ ሩቅ አላሚዎች ነበሯት፡፡ ለግል ዝና እና ስኬት ብቻ ሲሉ የአመራር መንገድን የሚቀይሱ እና ታላቁ ባለራዕይ መሪ እየተባሉ እንዲመለኩ የሚደረጉ መሪዎች ነበሩ፡፡

የአመራር ጽሁፍ ዳሰሳዬ እንደሚያመላክተኝ በመልካም መሪ እና በታላቅ መሪ መካከል ያሉ ጥቂት ልየነቶች አሉ፡፡ ታዋቂው ጅም ኮሊንስ አመራር ሰጭነት በሚል አምስት የመሪነት ደረጃዎችን ማለትም ኃይለኛ፣ አዋራጅነት ቅልቅል እና አይበገሬ ፈላጭ ቆራጭነት ያላቸው መሆናቸውን ግልጽ አድርጓል፡፡ ሊታመን በማይችል መልኩ የስልጣን ጉጉት አላቸው፡፡ ሆኖም ግን ይህ የስልጣን ጉጉታቸው ከሁሉም በላይ ለድርጅቱ እና ለስራው እንጅ ለእራሳቸው ጥቅም ሲሉ አይደለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኮሊንስ የቡድን ስራ አስፈላጊ ነው ይላሉ ምክንያቱም በአውቶብሱ ውስጥ ትክክለኛዎቹን ሰዎች ማግኘት ይቻላልና፡፡ የበሰበሰ እንጨትን በጀርባ ላይ ተሸክሞ ብዙ ርቀት መጓዝ አይቻልም፡፡

ብቻዎን ልሰሩት የሚቻል ነገር አይደለም፣ ሆኖም ግን ስራውን ሊሰሩት እንድቺሉ እገዛ የሚለግሱህ ሌሎች በጣም ተፈላጊ ሰዎች ይኖራሉ እና እነርሱን ፈልገው ማግኘት ስኬታማ ያደርጋል፡፡ በአርሶ ላይ ውድቀት እንዳይደርስ ሊያደርጉ የሚችሉ የተለየ እውቀት ያላቸው ሰዎች አሉ፡፡ በአርሶ ላይ ስለተደቀኑት ችግሮች ጥልቅ እውቀት አላቸው እናም እነዚያን ችግሮች ለማስወገድ መፍትሄ ያመጣሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች መልካም መሪ እንድሆኑ በማገዝ በስልጣንህ እንድያድጉ ያደርጋሉ፡፡

እርግጥ ጥቂት የመሪነት እና የቡድን ጉዳዮች ያጋጥምዎታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ያለጥርጥር የበሰበሰ እንጨት በአመራር ቦታዎች ላይ ያሉት በስብዕና ተፈላጊነታቸው እና ችሎታቸው መሰረት ሳይሆን በሙስናና በጓደኝነት የተሰየሙ “መሪዎች” አሉ። አነዚህ ባለስልጣናት ያገኙት ቦታ የታማኝነት ፈተናውን ያለፉ እና በሉ የተባሉትን ተቀብለው እንደገደል ማሚቶ የሚያስተጋቡ ናቸው፡፡

በሌላ ደግሞ አመራርነትን የሚፈልጉ ይኖራሉ ምክንያቱም ለርሶ መልካም ያስባሉ እናም በኩራት የተቻላቸዉን እገዛ ማድረግ ይፈለጋሉ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አጠራጣሪው የቶማስ ተጠራጣሪነት፣ ተችነት፣ እና ሌሎች ከጎን ሆነው ይመለከታሉ ምክንያቱም ድፍረት፣ መተማመን እና የፈጠራ ችሎታን በመጨመር ትክክለኛ አመራር ሰጭነት ስለሚጎድላቸው፡፡

ሌሎች ደግሞ አርሶ እንዲወድቁ ሌት ቀን የሚሰሩ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ በፊቶ ሲገኙ ፈገግታን ያሳያሉ ሆኖም ግን ከጀርባ ሆነው ይዶልታሉ፡፡

ስለሆነም የእራስህን የአመራር ቡድን ለማቋቋም ከፍተኛ ችግር ያጋጥሞታል፡፡

እንዲህ የሚለው የማንዴላን የአመራር ዘይቤ በመከተል ታላቅ መሪ ለመሆን ይቻላል፡

“ታማኝነት፣ ቅንነት፣ ግልጽነት፣ ለጋስነት፣ ኩራት አልባነት ሌሎችን ለማገልገል ዝግጁ መሆን፣ በእያንዳንዱ ሰው መንፈስ ውስጥ ያሉ እሴቶች የመንፈሳዊ ህይወት መሰረቶች ናቸው፡፡

የእኛ የሰዎች ፍቅር በምቀኝነት ሳይሆን ወይም ደግሞ በዘመድ አዝማድነት ሳይሆን አንዳችን ከአንዳችን ጋር እንድንተሳሰር አድርገው ይይዙናል፡፡ ሆኖም ግን እንደ ሰብአዊ ፍጡር የሚጋረጡብንን ችግሮቻችንን በማስወገድ በወደፊቱ ተስፋ መቀየር እንችላለን፡፡

ከፊት ለፊት ሆነው ይምሩ ግን መሰረቶን (ወጣቱን) ከኋላ አይተዉት፡፡

“ከኋላ ሆነው ይምሩ ሌሎች ከፊት እንዳሉ እምነት እንዲኖርባቸው ያድርጉ“ ይላሉ ማንዴላ፡፡

ስለግላዊ የፖለቲካ ውድመት፣

ይህ መናገር የማልፈልግለት ሆኖም ሊነገርለት የሚገባ ርዕስ ነው፡፡

እስከ አሁን ከሰበሰብኳቸው መረጃዎች እንደምገነዘበው እርስዎ በአሁኑ ጊዜ በጫጉላ ሽርሽር ውስጥ አይደሉም፡፡

ምናልባትም ሁለት ሳምንታት ገደማ በቢሮ ስራዎ ላይ ከቆዩ በኋላ የረዥሙን ቢላዋቸውን ሰገባ በማውለቅ እና የጥላሸት መቀባት ዘመቻቸውን በመጀመር ግላዊ ስብእናን በሚያጠፋ መልኩ አስቀያሚ የሆነ የስብዕና ጥላሸት መቀባት ትግባራትን ይፈጽማሉ፡፡ ሲተቹም አንዲህ ይላሉ– ችግሮች ሁሉ በእርስዎ ላይ ይቆልላሉ፡፡ እርስዎ ለስልጣን በጣም ልጅ ብቃት የሎትም፡፡ የፖለቲካ አናሳ ልምድ አሎት፡፡ ለሰጡት ወታደራዊ አገልግሎት ጥላሸት ይቀባሉ፡፡ እርስዎ ሌላኛው አሻንጉሊት ኖት ይላሉ፡፡ የእርስዎን አንደበተ ርትኡ መሳጭ ንግግር ባዶ ንግግር እና በተግባር የማይገለጽ ዲስኩር ነው ይላሉ፡፡

እንዲያውም አንዳንዶቹ እንዲህ ይላሉ፣ ስልጣኑን እርስዎ ያገኙት ሌሎች ስለማይፈልጉት ነው፡፡ በሚፈልጉት ጊዜ ስልጣኑን ከእርስዎ ሊያባርሩ እንደሚችሉ ይናገራሉ፡፡ ዛሬ፣ ነገ፣ ባለፈው ሳምንት፣ ባለፈው ወር፣ ባለፈው ዓመት… መስራት ያለብዎትን ያልሰሩትን ነገሮች ዝርዝር ያወጣሉ ምንም አንድ ሳመንት በማይበልጥ ጊዜ ስራ ላይ ቢገኙም፡፡ ከዚያም አልፎ በውኃ ላይ መራመድ አይችልም ወይም ደግሞ እንደጭልፊት አይበርም ይላሉ፡፡ እራስዎትን በተግባር እንዲያረጋግጡ ዕድሉን አይሰጡዎትም፡፡ ለ27 ዓመታት የጠነባ እና የበሰበሰውን ስርዓት እርስዎ በ7 ቀናት ውስጥ እንዲያስተካክሉት ይፈልጋሉ፡፡

ለመሆኑ እነርሱ እነማን ናቸው?

እነርሱ አሉባልታን የሚያሰራጩ አሉታዊ አስተሳሰብ ያላቸው ተስፋ የሌላቸው የአእምሮ ጤንነት ጉድለት ያለባቸው እና የታሪክ ሀሳባዊ ህመም ያለባቸው ሰዎች ናቸው፡፡

ዓላማቸው ሀሳብን ለማስቀየስ፣ ጥላሸት ለመቀባት፣ ስም ለማጥፋት፣ ስብዕናን ለማጥፋት አሉባልታ ለማሰራጨት እና በኢትዮጵያ ወጣቶች ላይ ብሩህ ተስፋ የሚያደርጉትን ኢትዮጵያውያን ሀሳብ ለማጨለም እና በተስፋየለሽ የፖለቲካ አዘቅት ውስጥ ገብተው አንዲዳክሩ ለማድረግ የሚሞክሩት ናቸው፡፡

በመጀመሪያ ጊዜ አድርጌው በነበረው ንግግሬ ላይ እነዚህን አሉባልታን የሚያሰራጩትን ሰዎች እንዲህ በማለት አስጠንቅቄ ነበር፣ “ምንም ዓይነት በቂ ማስረጃ ሳይኖረን አመራርነት ለመስጠት የተዘጋጁትን እና ድርጅት ለመመስረት የሚያስቡትን ግለሰቦች በስድብ በመተቸት እና ያልተጣሩ አሉባልታዎችን በማሰራጨት ስብዕናቸውን እናጠፋለን፡፡

እነዚህን ስም የሚያጠፉትን አሉባልተኞች እና አሉታዊ አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች ዝም ብለን አንመልከታቸው፣ እንቅልፍም አንተኛላቸው፡፡”

በኋላ መስታወት እያዩ ወደፊት እንዲነዱ እና ተከስክሰው እንዲሞቱ ነው እነርሱ የሚፈልጉት፡፡ ይህ በፍጹም አይፈጸምም ምክንያቱም የእርስዎ ደጋፊዎች በርካታ ናቸው፡፡ በአስር ሚሊኒዮኖች የሚቆጠሩ የአቦሸማኔዎች ትውልድ አባላት ከጀርባዎ፣ ከፊት እና ከጎንዎ ናቸው፡፡

ለእነዚህ አሉባልታ አመላላሽ ሸውከኞች የእርስዎ ምላሽ “ይቅርታ የ75 ሚሊዮን ወጣት ሕዝቦችን ጉዳይ በመከታተል ላይ ነኝ“ የሚል ይሆናል፡፡

የ75 ሚሊዮን አቦሸማኔ ወጣት ትውልድ አባላትን ኃይል አይናቁ፡፡ ይህ ኃይል ዓለምን ይለውጣል!

በእርግጥ እርስዎ ከትችት እና ከሀሜት ነጻ ይሆናሉ የሚል ሀሳብ የለኝም፡፡ ማንም በሕዝብ የስልጣን መንበር ላይ የተቀመጠ ሰው ያለምንም ጥረት ምንም ነገር ሊያገኝ አይችልም፡፡ ሆኖም ግን ለሚሰሩት ነገር፣ ላልሰሩት ነገር እንዲሁም ዝም ብለው ለመስራትም ላለመስራትም ሲሉ ለሚያዩት ነገር ሁሉ ለመተቸት ፍትሀዊነትን ይጠይቃል፡፡

እርግጠኛ ለመሆን እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም ኃይለማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆን ሲጠቆም እኔ ለእርሱ መልካም አመለካከት ነበረኝ፡፡ ሌሎች በርካታዎቹ በእርሱ ላይ እንዳደረጉት ሁሉ እኔ እርባናቢስ አድርጌ አላቀርብኩትም፡፡ ረጋ ብየ ነው የተመለከትኩት፡፡ የሚሰጠውን ጥርጣሬ ሁሉ ለማጣራት ሙሉ ጊዜ ሰጥቸ ነው ያየሁት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ እንዳይወድቅ እና ስኬታማ እንዲሆን እፈልግ ነበር፡፡

እውነት ለመናገር በመጀመሪያው ሳምንት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣንዎ ትልቅ አድናቆት ሊሰጥዎ ይገባል፡፡ በተለምዶ ማዕከላዊ እየተባለ የሚጠራው የዜጎች የማጎሪያ እና የማሰቃያ እስር ቤት ተዘጋ የሚል ሪፖርት አይተናል፡፡ የኢንተርኔት አገልግሎት በመላ ሀገሪቱ ክፍት ሆኖ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ቀደም ሲል ታስረው የቆዩት የፖለቲካ እስረኞች ከፈተፈቱ በኋላ እንደገና ታስረው ስለነበር አሁን ደግሞ እንደደገና ለመፈታት በቅተዋል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ከሶማሊ ክልል አመራሮች ጋር ተደርጎ የነበረው ስብሰባ በጥሩ ሁኔታ ተከናውኗል፡፡ ይደልዎ! ብያለሁ

እርግጥ ጥቂቶች ናቸው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከእኔ በበለጠ ጥብቅ አነጋገር አስተያየት የሚሰጡ። ሆኖም ግን ፍትሀዊ በሆነ ትችት እና ፍትሀዊ ባልሆነ ትችት መካከል ልዩነት መደረግ እንዳለበት አምናለሁ፡፡ ለአስራ ሶስት ዓመታት ገደማ ያህል ያለምንም ማቋረጥ ሳቀርብ በነበረው ጠንካራ ሳምንታዊ ትችት በአሁኑ ጊዜ እንዲያውም ከአንድ ሺ በላይ ይሆናል አንድም ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጥጦ የሚገኘው አገዛዝ ስለምናገረው ወይም ደግሞ ስለምጽፈው ነገር ጠቃሚነት ምላሽ ሰጥቶኝ አያውቅም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ሁልጊዜ አስቸጋሪ በሆነ ጊዜ ሁሉ ያለምንም መጠራጠር እውነትን እና እውነትን ብቻ በመያዝ ስለምናገር እና ስለምጽፍ ነው፡፡ በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች መራራውን እውነት መያዝ እንደማይሆንላቸው ተምሪያለሁ፡፡ ሆኖም ግን እኔ ሁልጊዜ በየሳምንቱ ለእነሱ መራራውን እውነት ከመጋት የታቀብኩበት ጊዜ የለም፡፡

እኔን የሚሳዝነኝ ነገር ቢኖር እነዚህ አሉባልታ አራጋቢ ቡድኖች ለእርስዎ ምስጋና መስጠትም ሆነ እራስዎን በተግባር እስከሚያስመሰክሩ ድረስ እንኳን ጊዜ ሲሰጡ የማላይ እና የማልሰማ መሆኑ ነው፡፡

እነዚህን አሉባልታ አራጋቢ ቡድኖች አባላት ከፍተኛ የሞራል ስብእና ምሳሌ ሆኖ ከማሳየት በስተቀር እነርሱን ለማሳመን ሌላ የሚጠቀሙበት ነገር ይኖራል ብየ አላስብም፡፡

እኔ ለእርስዎ ያልተጠየቁ ሁሉት ቀላል ምክሮች አሉኝ፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ በዚያ በአስደማሚው ንግግርዎ እንዳደረጉት ሁሉ ነገሮችን ሁሉ ለሀሳብ ፍጭት ወደ ከፍተኛ ደረጃ በአደባባይ ያውጡት፡፡ በአሉታዊ አመላካከት ጦር ሰብቀው የሚመጡትን በሰለጠነ እና ዙሪያ መለስ በሆነ ዘመቻ ምላሽ ይስጧቸው፡፡ እንዲህ የሚለውን የዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግን ሕጎች ይከተሉ፣ ጨለማን በፍጹም ጨለማ አያስወግደውም፡፡ ይልቁንም ጨለማን ሊያስወግደው የሚችል ብርሀን ብቻ ነው፡፡ ጥላቻ ጥላቻን ሊያስወግደው አይችልም፡፡ ጥላቻን ሊያስወግደው የሚችለው ፍቅር ብቻ ነው፡፡ በሌላ አባባል ተስፋቢስነትን በተስፋ በመተካት ያስወግዱ፡፡ በጨለምተኝነት ደረቅ በረሀ ውስጥ የብሩህ ተስፋ ተክልን ትከሉ፡፡ መጥፎ ሀሳቦችን በማስወገድ በመልካሞች ተኳቸው እናም መልካም ነገር በሰይጣናዊ ድርጊት እና አስተሳሰብ ላይ ድል እንዲቀዳጅ እንጣር፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ከነገሮች ሁሉ የበለጠ አእምሮን የሀሳብ የበላይነትን እንመን፡፡ ችላ ካሉት አያሳስብም፡፡ እንደ ጥንታዊው የአፍሪካ አባባል “ውሾቹ ይጮሀሉ፣ ግመሎቹ ግን ጉዟቸውን ይቀጥላሉ“ አንደሚባለው ነው። ረዥሙን የነጻነት ጉዙ ከኋላ ሆኖ በመምራት ጉዞውን ቀጥሉ፡፡

ለምን እንደማደርግ እና ምን እንደማደርግ፣

በቅርቡ አንድ ጓደኛዬ እየቀለደ እንዲህ በማለት ጠየቀኝ፣ “አንዱን የአንተን የአቦሸማኔ ትውልድ አባል በቦታው አድርገሀል፡፡ ስለዚህ ተልዕኮየን አሳክቻለሁ ብለህ ታስባለህ?“

ሆኖም ግን ይህ ጥያቄ ካለፉት አስርት ዓመታት ጀምሮ በቤተሰብ አባላት ሳይቀር ስጠየቅ ቆያቻለሁ፡፡ “መቸ ነው ተልዕኮህ የሚሳካው እና ወደ መደበኛው የህይወት ጉዞህ የምትመለሰው?“ የሚሉ ጥያቄዎችን በተደጋጋሚ ስጠየቅ ቆይቻለሁ፡፡

ሆኖም ግን አንድ ቀጥተኛ የሆነ መልስ በፍጹም ልሰጣቸው አልችልም፡፡ አንድያው በራሴ ማሰላስለው የሮበርት በርንስን የግጥም ስንኞች ነው፣ “ጫካዎቹ ጠቁረዋል ቃላቱ ቆንጆዎች ናቸው፣ ሆኖም ግን እነርሱን ለመጠበቅ ቃል ኪደን አለብኝ፡፡ ከመተኛቴ በፊት ብዙ ኪሎ ሜትሮችን እጓዛለሁ።“

አዎ የኢትዮጵያ አቦሸማኔዎችን ነጻነት ለማስመለስ ከመተኛቴ በፊት ብዙ ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍነውን ረዥም መንገድ መጓዝ አለብኝ፡፡

ላለፉት አስራ ሶስት ዓመታት ገደማ ያህል በርካታ ሰዎች ለምን እንደማደርግ እና ምን እንደማደርግ ይደነቁ ነበር፡፡

እያደረግሁ ያለሁት ሌላ ምንም ነገር ሳይሆን በስልጣን ላይ ተፈናጥጠው ለሚገኙት እውነትን እስከ አፍንጫቸው ድረስ መንገር ነው፡፡

በስልጣን ላይ ተፈናጥጠው ላሉት እውነትን እስከ አፍንጫቸው ድረስ እነግራቸዋለሁ ምክንያቱም ቅዱሱ መጽሀፍ “እውነት ነጻ ታወጣሀለች ይላልና”፡፡ የእኔን የእውነት ተናጋሪነት የጉጉት ተልዕኮ የወሰድኩት አቻ ከማይገኝላቸው አንጋፋ ልሂቃን ከፕሮፌሰር ኤድዋርደ ሰይድ እና ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ነው፡፡

ፕሮፌሰር ሰይድ “እውነትን በስልጣን ላይ ላሉት በመናገር እና ለሚገደሉት እና ለሚሰቃዩት ህዝቦች ምስክር በመሆን እንዲሁም በስልጣን ላይ ያሉት በህዝብ ላይ ለሚያድርሱት በደል የተቃውሞ ድምጽን በማሰማት“ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ያሉ ምሁራን የሰው ልጆችን ነጻነት እና እውቀትን ተልዕኮ ያራምዳሉ ነበር ያሉት፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከሁለተኛው አጋማሽ ማጠናቀቂያ ላይ ጀምረው እውነትን በስልጣን ላይ ላሉት ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡

እንደዚሁም ሁሉ እኔም በተመሳሳይ መልኩ እንደነርሱ በስልጣን ላይ ላሉት የመናገር እኩል እድል አለኝ፡፡ እውነትን የምናገረው በስልጣን ላይ ላሉት እና ስልጣናቸውን ከሕግ አግባብ ውጭ ለሚጠቀሙት ብቻ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን እኔ የምናገረው ለስልጣን ረሀብተኞች ለስልጣን ጥመኞች፣ ስልጣናቸውን ከሕግ አግባብ ውጭ ለሚጠቀሙ እና ምንም ዓይነት ስልጣን ለሌላቸው ወገኖች ሁሉ ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ2005 ተካሄደ የተባለው የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ መጠናቀቅን ተከትሎ ተፈጥሮ በነበረው እልቂት ምክንያት የሰብአዊ መብት ተሟጋችነት ትግሌን የጀመርኩት በጠራራ ጸሐይ አምባገነኑ መለስ የምርጫ ኮረጆን በመዝረፉ ምክንያት ተቃውሟቸውን ባሰሙት የብሩህ ተስፋ ባለቤት ወጣቶች ላይ የግፍ ጭፍጨፋውን በማካሄዱ ለእነዚያ ደመከልብ ሆነው ለቀሩት እምቦቃቅላ ወጣቶች ምስክር ለመሆን ነው፡፡

በርካታ ሰዎች የእኔን የማያቋርጥ የሰብአዊ መብት ተሟጋችነት ከሚገባው በላይ እየተደረገ ያለ ትልቅ ነገር እንደሆነ አድርገው ያቀርባሉ፡፡

እንደዚሁም ሁሉ ሌሎች እኔ ዝም ብዬ ጊዜየን የማባክን አድርገው ይቆጥራሉ ምክንያቱም በተጨባጭ ለዚህ ትግሌ የማሳየው ምንም ነገር እንደሌለ አድርገው ስለሚቆጥሩ ነው፡፡ ጥቂቶቹ ደግሞ የእኔን መራራ ተቃውሞ በመውሰድ የህወሀት የዘር ጥላቻ ስላለው ነው የሚሉ አሉ፡፡

ያም ሆነ ይህ ሁሉም እንደየሀሳባቸው ይመደባሉ፡፡

እኔ የፖለቲካ ፍላጎት በፍጹም እንደሌለኝ በተለያዩ አጋጣሚዎች አውጃለሁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስልጣንን አላግባብ ለሚጠቀሙ፣ ለስልጣን ረሀብተኞች እና ጥመኞች ንቀት እንጅ ሌላ ምንም ነገር እንደሌለኝ ለበርካታ ጊዚያት ስናገር ቆይቻለሁ፡፡ ከስልጣን ፍቅር በላይ ለተጨቆኑት ህዝቦች፣ በችግር ላይ ለወደቁት እና ለሚሰቃዩት ህዝቦች ደንታ የሌላቸው፣ ለድምጽ አልባዎች እና ተከላካይ ለሌላቸው ምንም ዓይነት የፍቅር ስሜት የማያሳዩ በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች የአስመሳይነት እኩይነትን የሚያመላክት ነው፡፡ በስልጣን ላይ እንደመዥገር ተጣብቀው ላሉት እውነታን በመናገር ረጅም አመታት የሰራ ሰው የስልጣን ፍላጎት ካስዬ ያስጠይቀዋል ስራችንን፡፡

የፕሮቴስታንት ኃይማኖት አባት እና የኃይማኖት ሰው የሆኑት ማርቲን ሉተር እንዲህ ብለው ነበር፣ “ዓለምን ለመቀየር ከፈለግህ ብእርህን አንሳና ጻፍ፡፡“ እኔ ፕሮቴስታንት አይደለሁም ሆኖም ግን ከአስራ ሶስት ዓመታት በፊት ብእሬን አንስቻለሁ እናም እስከ አሁን ድረስ ጠንካራ ሆኘ ቀጥያለሁ፡፡

በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውን የቱፓክ ሻኩርን አባባል በመጥቀስ “ኢትዮጵያን ለመለወጥ በቂ እርምጃዎችን ተራምጃለሁ ማለት አልችልም ሆኖም ግን ከመጀመሪያው ጀምሮ ዋስትና አድርጌ የያዝኩት ኢትዮጵያን መለወጥ ለሚችሉ አእምሮዎች ብልጭታን ፈንጥቂያለሁ ብዬ አምናለሁ“ እንግዲህ ይህንን ለማድረግ የተወሰነ ስኬታማ ስራን ሰርቻለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡

ያለምንም ጥርጥር ያለፉት አስር ዓመታት ለእኔ በህይወቴ መልካም ዓመቶች ናቸው ብዬ መናገር እችላለሁ፡፡ ለሰብአዊ መብት መከበር፣ ለዴሞክራሲ፣ ለሕግ የበላይነት እና ለነጻነት በኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያ ውጭ ሌላ ምንም ሳልይዝ በብእሬ ብቻ በመጠቀም በእያንዳንዷ ሳምንት የመታገል ዕድሉን አግኝቻለሁ፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ፍቅር የነገሰበትን ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት እንዲህ በቀላሉ የሚጠናቀቅ ተግባር አይደለም፡፡ ያለምንም ረፍት ተጠናከሮ መቀጠል አለበት፡፡

ዶ/ር ማርቲን ሉተር “ለነጻነት የሚደረግ ረዥሙ ጉዞ“ በሚለው መጽሀፋቸው እንዲህ በማለት ጽፈው ነበር፣ “የሰው ልጆች እድገት የአንድ ጊዜ እመርታ ወይም ደግሞ የማይቀር ነገር አይደለም፡፡ ወደ ፍትህ ግብ የሚደረግ እያንዳንዱ ርምጃ መስዋዕትነትን፣ ስቃይን እና ትግልን እንደዚሁም ለዚሁ ተግባር ህይወታቸውን የሰጡ የማይሰለቹ እና በሕዝብ ፍቅር የነደዱ ግለሰቦችን ይፈልጋል…“

እራሱን ለዚህ ተግባር እንዳዋለ ሰው እራሴን እንዲህ በማለት እጠይቃለሁ፣ “እኔ የማልሰራው ከሆነ ማን ሊሰራው ነው?“ እላለሁ፡፡

የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብት መከበር ትግል ከፍ ወዳለ እና ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ በደስታ ቀጥየበት እገኛለሁ፡፡ ይኸ መታደል ነው፡፡

እኔ ውስብስብ ሰው አይደለሁም፡፡ እኔ ንግግሬ ፊትለፊት ነው። መደበቅ መዘባረቅ ማወናበድ ማጭበርበር ንግግር አልወድም። ከኔ ጋር የምታዩት እና የምትሰሙት የምታገኙት ነገር ግልፅ ነገር ብቻ ነው፡፡ የምለውን እናገራለሁ፣ የምናገረውን አደርጋለሁ፡፡ ለቀልድ ካልሆነ በስተቀር ሰም እና ወርቅ አልናገርም፡፡

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2006 ቃልኪዳን ያልገባሁትን ባለፉት አስራ ሶስት ዓመታት ውስጥ አላልኩም አላደረግሁም፡፡ ምንም ነገር፡፡ እንደ እ.ኤ.አ በ2006 የትግል ጉዞዬን ጀመርኩ፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ነጻ ለማውጣት ረዥሙ ጉዞ ወደ ነጻነት እየተደረገ ነው፡፡ አሁን በሚሊዮን በሚቆጠሩ የአቦሸማኔው ትውልድ አባላት መካከል ስለሆንኩ ወሰን በሌለው መልኩ ተመችቶኛል፡፡

እኔን ጥላቻ እንዳለብኝ የሚናገሩ እና በስልጣን ላይ የሚገኙት በጎሳ ዘራቸው ምክንያት እኔን የዲያስፖራው አክራሪ አድርገው ይፈርጁኛል፡፡

በእርግጥ ይህንን ፍረጃ በኩራት እቀበለዋለሁ፡፡ ይህንን እንደ እውነት ወስጀ እንዲህ በማለት እገልጸዋለሁ፣ “ነጻነትን ለመጎናጸፍ የሚደረግ አክራሪነት ምንም ዓይነት ወንጀል የለበትም፡፡ ፍትህን ለመጎናጸፍ የሚደረግ ትግል በቀላ የሚያዝ አይደለም፡፡“

ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ነጻነት ለመከራከር ስል ያደረጉትን ጽኑ ተጋድሎ፣ ለድርድር የማይቀርብ ተግባር፣ ጠንካራ ሆኖ መቆየት፣ ስህተት ከሆነ ስህተቴን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ፍትህ በወሰን ተለክቶ መሰጠት እንደሌለበት አምናለሁ፡፡ ይህ ማለት ፍትህ በምህረት ሊታይ አይችልም ማለት አይደለም፡፡

የንግግሬ ድምጸት እና ጽሁፍ ብዙውን ጊዜ ያቃቤ ሕግ ክስ ይመስላል የሚሉ አሉ፡፡ የአሜሪካ የሕግ ትምህርት አንዱ ገፅታ ጥብቅ ክርክር ማካሄድ ነው፡፡

በእኔ የሰብአዊ መብት ትግል ላይ ጥቂቶች የሕዝቡን የሀሳብ ዳኝነት እንደ መደበኛው የዳኝነት ስርዓት እንደምመለከተው አድርገው ይናገራሉ፡፡ በፍርድ አደባባይ ላይ ስለፍትህ ያለኝን ክርክር ዕድል አግቼ እስከሰራ ድረስ ለማደርገው ጥብቅ ክርክር ኃላፊነት አወስዳለሁ፡፡

የእኔ ተቃውሞ ስለህወሀት ስብዕና በፍጹም አይደለም። ተቃውሞየ በሚያራምዱት ጥላቻ እና በተንሰራፋው የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ድርጊታቸው ነው፡፡

የጎሳ ዘረኝነትን የሚያሳይ ነገር አልተናገርኩም ወይም ደግሞ አላሳየሁም፡፡ ለአስራ ሶስት ዓመታት ገደማ ያህል ሳቀርበው በቆየሁት ትችት እና ንግግር ማንም ቢሆን የዘረኝነት መንፈስን ለማራመዴ ማስረጃ ሊሆን የሚችል የሚያቀርብ ሰው ሊኖር አይችልም፡፡ እኔ የምታገለው ስለሰው ልጆች ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ፣ አንድነት እና ስነምግባር እንጅ ስለዘረኝነት አይደለም፡፡ ስለእነርሱ ግላዊ የሆነ ጥላቻ የለኝም ምክንያቱም አላውቃቸውም፡፡ ሆኖም ግን በሰብአዊ መብት ላይ የሰሩትን ወንጀል አውቃለሁ፡፡ በእርግጥ አምባገነኑ መለስ እ.ኤ.አ በ2006 በሰው ልጆች ላይ በፈጸመው እልቂት ምክንያት ነው ወደ ሰበአዊ መብት ተሟጋችነት የገባሁት እናም በትግሉ ውስጥ እገፋለሁ ምክንያቱም እያደረሷቸው ያሉት ወንጀሎች መቋጫ የላቸውም፡፡

በእርስዎ የስልጣን ርክክብ የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የጸጥታ ኃይሎች በንጹሀን ዜጎች ላይ ስለሚፈጽሙት የዘፈቀደ ግድያ ይቅርታ መጠየቅዎ እጅግ በጣም ደስ አሰኝቶኛል፡፡ ሆኖም ግን ሌሎች የአዞ እንባቸውን ያነባሉ፡፡

ለሕግ የበላይነት መስፈን ማረጋገጫ የሚሰጡኝ ከሆነ እነርሱን ለማገዝ ደስተኛ መሆኔን በየጊዜው ስገልጽ ቆይቻለሁ፡፡ እ.ኤ.አ ጥቅምት 2017 መጀመሪያ አካባቢ እንዲህ ብየ ነበር፣ “እኔ ከዘ-ህወሀት ወይም ከማንኛቸውም መሪዎች ወይም አባላት ጋር በግሌ ምንም ዓይነት ግንኙነት ወይም ጥላቻ የለኝም፡፡ እነርሱ የሕግ የበላይነትን ቢያረጋግጡልኝ፣ መልካም አስተዳደርን ቢያሰፍኑ እና የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ሰብአዊ መብቶችን ቢያከብሩ ቁጥር አንድ አድናቂያቸው ነበርኩ፡፡ ያ አቋሜ እስከ አሁንም ድረስ እንደጸና ነው“ ብየ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ በ2010 መለስ ዜናዊ በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ መናገር እንዲችል መብቱ እንዲከበርለት ሽንጤን ገትሬ ስከራከር ይህ አቋሜ በሰፊው ተወግዞ ነበር፡፡ መሳተፍ እንዳይችል ለኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ለከሊ ቦሊንገር ደብዳቤ ከጻፉት ከእኔ የግል ጀግናዎች ከእስክንድር ነጋ እና ከሰርካለም ፋሲል ጋር በሀሳብ ተለያይተን ነበር፡፡ መርህን ከሰዎች በላይ እንዲውል ለማድረግ አንድ ሰው ከሚወደው እና ከሚወዳት የትግል አጋሮቹ በላይ ለማድረግ ምን ያህል እንደሚቆጠቁጥ እና እንደሚያም መገንዘብ ይቻላል፡፡ ሆኖም ግን በነጻነት የመናገር መብትን በምንጠላቸው ሰዎች ላይ የምንገድብ ከሆነ በእራሱ በእምነት ላይ በእርግጥም አናምንበትም ማለት ነው፡፡

ለሁሉም ጊዜ አለው…

ቅዱሱ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፣ “ለሁሉም ጊዜ አለው፣ ከሰማይ በታች ለሁሉም ድርጊት ተፈጻሚነት ወቅት አለው“፣ “ለመግደል ጊዜ፣ ለማዳንም ጊዜ” ያስፈልጋል፡፡ “ለማፍረስም ጊዜ፣ ለመገንባትም ጊዜ ያስፈልጋል”፣ ኢትዮጵያን የመገንባቱ እና ክልሎች እየተባሉ የሚጠሩትን ባንቱስታንት ማጎሪያ በረቶች የማፍረሻ ጊዜው አሁን ነው፡፡ ለማልቀስ እና ለማዘን ጊዜ፣ ለመሳቅ እና ለመደነስም ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ እርስ በእርስ ተቃቅፎ መሳቅ እና ሌሊቱን ሙሉ መደነስ ጊዜው አሁን ነው፡፡ ለመቅደድ ጊዜ፣ ለመጠገንም ጊዜ አለው፡፡ በዘረኝነት፣ በኃይማኖት በቋንቋ ተበጣጥሰን እንገኛለን፡፡ አሁን በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ቁስላችንን የምንጠግንበት እና የምንፈውስበት ጊዜ ነው፡፡ ለማፍቀር ጊዜ፣ ለመጥላትም ጊዜ አለው፡፡ የመጥላት ጊዜ ተጠናቋል፡፡ አሁን ጊዜው የፍቅር ነው፡፡

ወደፊት እየተራመድንበት ባለበት በአሁኑ ጊዜ የእኔ መልዕክት አብሮነት፣ ወንድማማችነት፣ እህትማማችነት ነው፡፡ ሌላ ጥላቻ እና በቀል የለም፡፡ ጣት መቀሳሰር፣ ጥርስ መንከስ እና የሆድ ቁርጠት የለም፡፡

ሌሎች ስለጦርነት ሲነጋገሩ እኛ ስለሰላም እናወራለን፡፡ ለኢትዮጵያ አቦሸማኔ ትውልድ ምስጋና ይግባው፡፡ የፈውስ፣ የአንድነት እና የኢትዮጵያ ወርቃማ ጊዚያት አሁን እየመጡ መሆኑ መልዕክቱ ሊነገራቸው ይገባል፡፡

ጋንዲ እንዲህ በማለት አስተምረዋል፣ “እምነቶቻችሁ የእናንተ ሀሳቦች ይሆናሉ፡፡ ሀሳቦቻችሁ ቃሎች ይሆናሉ፡፡ ቃሎቻችሁ ደግሞ ድርጊቶች ይሆናሉ፡፡ ድርጊቶቻችሁ ልማዶች ይሆናሉ፡፡ ልማዶቻችሁም እሴቶቻችሁ ይሆናሉ፡፡ እሴቶቻችሁ ደግሞ ዕጣ ፈንታችሁ ይሆናሉ“ ብለዋል፡፡

አሁን ጊዜው እምነቶቻችንን እና ሀሳቦቻችንን በመለወጥ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሀገራቸውን እንዲለውጡ እና የእራሳቸውን ዕድል እንዲወስኑ ማገዝ ነው፡፡

እጅዎን ለዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን መዘርጋት፣

በስልጣን ርክክብ የመክፈቻ ንግግርዎ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንን እጅዎን ዘርግተው እንደሚቀበሏቸው እና እውቀታቸውን፣ ሀብቶቻቸውን እና ልምዶቻቸውን ይዘው በመምጣት ሀገራቸውን በመገንባቱ ሂደት ላይ የእራሳችውን ሚና እንዲጫወቱ እንደሚያደርጉ እና ሌሎችም ከሩቅ በመምጣት ለማገዝ የሚችሉ ሁሉ እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ይህ መልዕክት ለሰላም እና ከዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ጋር ለብሄራዊ እርቅ ለማድረግ እጅግ ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ በጣም አደንቃለሁ፡፡ ከዲያስፖራ አክራሪዎች ጋር የጦርነት ዕቅድ ሲዘጋጅ እና በሌሎቹ ላይ ደግሞ የፕሮፓጋንዳ ስራ ሲሰራበት የነበረውን እና የቆየውን ቀደምት ጊዜ አስታውሳለሁ፡፡

ሁሉንም ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ወክየ ለመናገር አልችልም ሆኖም ግን ላለፉት አስር ዓመታት ድምጻቸው ሆኘ እንዳገለግላቸው ለምመለከቱኝ ለመናገር እችላለሁ፡፡

በዲያስፖራው ማህበረሰብ ውስጥ በግላዊ እና በፕሮፌሽናል ባለሙያነት ህይወታችን አማካይነት ከመቀበል ይልቅ መስጠት የምንችል በርካታዎች አለን፡፡ ከመካከላችን ብዙ መስጠት የምንችል እና ብዙ የሚጠበቅብን አለን፡፡ ወጣቶቻችን የተሻለ የወደፊት ህይወት እንዲኖራቸው ለእርካታችን ስንል ብዙ ነገር እንሰጣለን፡፡

ለማ መገርሳ እንዲህ ብሎ ነበር፣ “መማር እና እና ሀገርን ማገልገል የአካዳሚክ ምርምር ወረቀት ማቅረብን አይጠይቅም፡፡ ይህም ማለት ሀገርን መንከባከብ፣ ሀገራችንን ለመጠበቅ የሚያስቸሉ መንገዶችን መከተል እና ፈጠራ ያላቸውን ሀሳቦች ይዞ መምጣት እና እንደዚህ ያሉ ሀሳቦችን ማሰራጨት ነው፡፡ ይህ ከማንም በላይ የበለጠ ከምሁራን የሚጠበቅ ነው፡፡ እኔ የማስበው እንደዚህ ነው፡፡“

ለማ ምስማሩን ከጭንቅለቱ ላይ አጥብቆ መቶታል፡፡ ለለማ ታለቅ ክብር እና አድናቆት አለኝ፡፡

ለማ የኢትዮጵያውያን ምሁራን እራስን እያስደሰቱ የአካዳሚክ ህትመቶችን እያሳተሙ ከመቀመጥ ይልቅ ትግሉን እንዲቀላቀሉ እና የእራሳቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ልዩ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

በእርግጥ እኔ ወዲያውኑ ለስራው ራሴን አቅርቤ ነበር፡፡ በርካታዎቹ አላደረጉም ብየ እሰጋለሁ፡፡ ታላቅ ተግዳሮት ነው፡፡ አንገዲህ ኳሷ በዲያስፖራው ሜዳ ላይ ናት፡፡ የተናገርነውን ወደ ተግባር ለመለወጥ እንገደዳለን፡፡

ውድቀት ለእናንተ አማራጭ አይደለም፡ የኢትዮጵያ አቦሸማኔ ሰዓት ነው አሁን፣

የምጽአት ቀን ነብዮች የዕጣ ፈንታ አድልህ ወድቋል በማለት አወጁ፡፡ ጥገናዊ ለውጥ ከማካሄድ በስተቀር ምንም ነገር እንዳትሰራ በቁጥጥር ስር እናስቀምጥሀለን በማለት ይናገራሉ፡፡ ለእኔ እንደመስለኝ ባሮጌው ጨለማ መነጽር ነው የሚመለከቱት፡፡

በቅርብ ጊዜ የሚታዩትን እድገቶች በምመለከትበት ጊዜ በብሩህ ተስፋ እሞላለሁ፡፡ ሆኖም ግን ፍጹም ከአደጋ ውጭ ስለመሆናችንን እጠይቃለሁ፡፡ የቅልበሳ መንፈራገጥ አደጋ ሊከሰት ይችላል፡፡

ጣቶቻቸውን በህዝቡ የልብ ትርታ ውስጥ የሚያስቀምጡ እና እውቀቱ ላላቸው ለባህላዊ የሀገር ሽማግሌዎች ከብዙ ጊዜ ጀምሬ ሳዳምጥ እና ስማር ቆይቻለሁ፡፡

በቅርቡ አስደናቂ የሆኑት አባገዳ በየነ ሰንበቶ ስለውድቀት ኪሳራ እንዲህ በማለት እውነትን ሰብከዋል፣

“አንድ ነገር ልንገራችሁ፡፡ አሁን በቅርብ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ስለመምረጥ ጉዳይ ነበር፡፡ እውነታውን ልናገር፣ ሁሉም በሀገር ውስጥ ያለው ይስማ፡፡ ይህች ሀገር በአጠቃላይ ከትልቅ አደጋ ውስጥ ትወድቅ ነበር፡፡ እግዚአብሄር ምስክሬ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው የሰላ ቢላዋውን ይዞ በዝግጅት ላይ ነበር፡፡ ሁሉም እንዲህ ይሉ ነበር፣ ‘ምን እንደሚደረግ እናያለን‘ ሆኖም ግን እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይጠብቃታል፡፡ እናም የመንግስት አካላት ትክክለኛው ነገር ሰሩ፣ እናም ከጥልቅ ጭንቀት ተጠበቁ፡፡ ያ ሳይሆን ቢቀር ኖሮ ሺ ኮማንድ ፖስት ወታደሮች አንድ መቶ ሚሊዮን የሚሆንን ሕዝብ ማመቅ ይችሉ ነበርን? በፍጹም ሊያድርጉት አይችሉም…“ነበር ያሉት፡፡

አባገዳ በየነ ትክክል ናቸው፡፡ እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይጠብቃል፡፡

ለዚህ ነው ውድቀት ለእናንተ አማራጭ የማይሆነው፡፡

ለዚህም ነው ውድቀት ለሁላችንም አማራጭ የማይሆነው፡፡

ሁላችንም በስኬትዎ ላይ ጥረት አድርገናል ምክንያቱም እርስዎ ቢያጡ እኛ ህይወታችንን፣ ነጻነታችንን እና ህብረታችንን ነው የምናጣው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ትክክል ሆኖ ነው የምናገኘው!

በአሜሪካ የአቶሚክ ሳይንቲስቶች ሳይንስ እና የደህንነት ቦርድ መጽሄት የምጽአት ቀን እየተባለ የሚጠራውን እና በሰው ሰራሽ ዓለም አቀፋዊ እልቂት በተለይም ከዓለም አቀፍ የኒኩሊየር ጦርነት ሊመጣ እንደሚችል ዘግቧል፡፡ ሰዓቱ ግምታዊ ዓለም አቀፋዊ እልቂት በእኩል ሌሊት እና ዓለም ለዓለም አቀፍ እልቂት በእኩል ሌሊት እንደሚሆን ተንብዮአል፡፡

የእኔን ሀሳባዊ የኢትዮጵያ አቦሸማኔዎች የምጽአትን ቀን ሰዓት ሞልቻለሁ፡፡ ሰዓቱ 11ኛ ሰዓት ላይ ነው፡፡ ሰዓቱን ወደ 12 ሰዓት ወደ ህዋላ እንመልሰው፡፡

አውቃለሁ አትወድቁም ምክንያቱም ከ70 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ወጣት ህዝብ (71 በመቶ የሚሆነው ህዝብ እ.ኤ.አ በ2014 እድሚያቸው ከ30 ዓመት በታች) የሆኑት ከጀርባዎ ናቸው፡፡

ማዕበሉን ማጥፋት፣

የአሜሪካ ታላቁ ጸሐፊ እና ቀልደኛ ማርክ ትዋይን እንዲህ ብሎ ነበር፣ “በጦርነቱ ውስጥ የውሻው ግዙፍነት አይደለም ዋናው ጉዳይ፣ ይልቁንም ዋናው ጉዳይ የጦርነቱ ግዙፍነት በዉሻው ልብ መታሰብ ያለበት፡፡“ ለዚህም ነው ዳዊት ጎልያድን ሊያሸንፍ የቻለው፡፡ እርስዎም እንደዚሁ አሸናፊ ይሆናሉ፡፡

ስለሰይጣናዊነት እና ስለማዕበል እንዲህ የሚል አንድ የቀድሞ አባባል ጥቅስ አለ፣ እናንተ ማዕበሉን ለማጥፋት ጠንካራ አይደላችሁም የሚሉትን ሰዎች እንዲህ በማለት ልነግራችሁ እወዳለሁ። ማበሉን አይችሉትም ለሚሉ ሁሉ ይህን መልስ ይስጡ: “እኔ ነኝ ማዕበሉ“፡፡ ማዕበል መሆኖን ለማያምኑ “በማዕበል ዓይን ያለሁ ሰላም ነኝ”። ይህንን ለማያምኑ ሰዎች እንዲህ በማለት ንገሯቸው፣ “ቆዩ እና ተመልከቱ አቦሸማኔዎቹ በእናንተ ላይ ይዘንባሉ፡፡“

ውድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከታሪክ ጋር ቀጠሮ አሎት፡፡ ወደ ቀጠሮዎ ሲሄዱ የማንዴላን የኮቴ እርምጃ ይከተሉ፡፡

እስከሚቀጥለው ጊዜ መልካሙን እመኝልዎታለሁ፡፡

ዓለማየሁ

ኢትዮጵያ ዛሬ፣ ኢትዮጵያ ነገ፣ ኢትዮጵያ ለዘላለም…

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!   

ሚያዝያ 4 ቀን 2010 ዓ.ም

በንግሊዘኛ ፅሁፍ ይህን ይጫኑ

http://almariam.com/2018/04/08/my-personal-letter-to-prime-minister-abiy-ahmed-of-ethiopia/