“ደስታ ነገ ጠዋት አሸብርቆ ይመጣል!”፡ ለ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት መልዕክቴ
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
ያለ መራራ ትግል ምንም ዓይነት ዕድገት ሊኖር አይችልም!
እ.ኤ.አ መስከረም 11/2016 የኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት የ2009 ዓ.ም የመጀመሪያ ዕለት ነው (እንደ ኢትዮጵያውያን ዘመን አቆጣጠር መስከረም 1 ቀን)፡፡
“2009 መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልዎ“ የሚሉትን ቃላት መናገር ለእኔ በጣም የሚያም እና የሚቆጠቁጥ ነገር ነው፡፡
ወገኖቻችን በየቦታው በገዛ ሀገራቸው መብታቸው ተገፍፎ እንደ ፋሲካ ዶሮ እየታረዱ እና በየእስር ቤቶች እንደ ደመራ በእሳት እንዲቃጠሉ የሚደረጉበት አስከፊ ሁኔታ ላይ ያለንበት ጊዜ ስለሆነ እንደዚህ ያሉትን ቃላት ደፍረን እንዴት “መልካም አዲስ ዓመት” ልንል ይቻለናል?!
ወገኖቻችን እንደዚህ ባለ አስከፊ ሁኔታ በጅምላ እያለቁ ባለበት ሁኔታ ከኢትዮጵያውያን ባህል እና ልማድ ባፈነገጠ መልኩ በተጠሩባቸው መድረኮች ሁሉ በመገኘት መልካም አዲስ ዓመት በማለት ሲዘፍኑ የነበሩ አርቲስት ተብዬ አዝማሪዎች ዘፋኝ የዘፈነ ሳይሆን አለሌ አህያ እንዳክላላ ያህል ነው የምንቆጥራቸው፡፡
እናት በልጇ ሬሳ ላይ እንድትቀመጥ የምትገደድበት ድርጊት እየተፈጸመ ባለባት ሀገር ውስጥ ምን ዓይነት ደስታ ሆኖ ነው አዲስ ዓመት እያሉ በማለዘን ላይ የሚገኙት?! አሳፋሪ እና የወረደ ነገር ነው፡፡ ባለቁት ሰማዕታት ነብሶች ለህሊና መንበር ለፍርድ ይቀርባሉ፡፡
የተጠናቀቀው እና አሮጌው የ2008 የበጀት ዓመት የኢትዮጵያን ሕዝብ እጅግ ያሳዘነ እና ማቅ ያለበሰ አስከፊ ዓመት ነበር፡፡
የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) ከሩብ ክፍለ ዘመን በፊት ስልጣንን በሕዝብ ድምጽ ሳይሆን በጠብመንጃ ኃይል ከተቆጣጠረበት እ.ኤ.አ ከ1991 ጀምሮ በዜጎች ላይ ሲፈጽመው የቆየውን የሞት እልቂት አባዜ እ.ኢ.አ በ2008 ዓ.ም የበለጠ መጠኑን እና ስፋቱን አጠናክሮ ቀጥሎበት ይገኛል፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዎች (ሂራዎ) የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እ.ኤ.አ ሰኔ 2016 እንዲህ የሚል ዘገባ ይፋ አድርጓል፣ “በኢትዮጵያ የደህንነት ኃይሎች እ.ኤ.አ ከህዳር 2015 ጀምሮ በሀገሪቱ ትልቅ በሆነው በኦሮሚያ ክልል በአብዛኛው በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን በመግለጽ ላይ በነበሩት ዜጎች ላይ ከመጠን ያለፈ ኃይል መጠቀምን እና ጥልቅ ጥላቻን አሳይተዋል“ ብሏል፡፡
እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች (ሂራዎ) ዘገባ ከሆነ የዘ-ህወሀት የደህንነት ኃይሎች፡
“ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመግለጽ በተሰባሰቡ ሰዎች ላይ የእሩምታ ተኩስ በመክፈት ዜጎችን ገድለዋል፣ አሰቃይተዋል፣ እንዲሁም በእስር ዘብጥያ እንዲወርዱ አድርገዋል፡፡ ቀደም ሲል በመጀመሪያ የሰላማዊ ተቃውሞውን ያቀጣጠሉት በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በመሆናቸው ምክንያት በርካታዎቹ ከ18 ዓመት እድሜ በታች የሆኑት ልጆች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርገዋል ወይም ደግሞ ተገድለዋል፡፡ የደህንነት ኃይሎች የፌዴራል ፖሊሶችን እና ወታደሮችን ጨምሮ በጋራ ከሕግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ ተማሪዎችን፣ መምህራንን፣ ሙዚቀኞችን፣ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን፣ የጤና ባለሙያዎችን እና ሌሎችን እርዳታ የሰጡትን ወይም ደግሞ ለሸሹት ተማሪዎች መጠለያ የሰጡትን ሁሉ በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር አውለዋል“ የሚል ዘገባ ነበር ይፋ ያደረገው፡፡
ዘ-ህወሀት እ.ኢ.አ በ2008 ዓ.ም መጠነ ሰፊ የሆነ የሕዝብ እልቂትን በመፈጸሙ ምክንያት ሌላው ቀርቶ የዘ-ህወሀት ቀንደኛ ጠባቂ፣ ዋና የስርዓቱ ተጠቃሚ እና ደጋፊ የሆነው የኦባማ አስተዳደር እንኳ ሳይቀር በተፈጠረው ዘግናኝ እልቂት እና ሕዝባዊ የደስታ እጦት ዴፕሎማሲያዊ በሆነ መልኩ ሳይወድ በግድ እንዲገልጽ ተገዷል፡፡
በተባበሩት መንግስታት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር የሆኑት ሳማንታ ፓወር በኢትዮጵያ ውስጥ በሰላማዊ አማረጺዎች ላይ እየተወሰደ ባለው ከመጠን ያለፈ የኃይል እርምጃ በጣም ያሳሰባቸው መሆኑን ባለፈው ሳምንት ገልጸዋል፡፡
ፓወር ዘ-ህወሀት እየወሰደው ያለው የኃይል እርምጃ እጅግ በጣም አስከፊ ስለሆነ ግልጽ በሆነ መልኩ እና ገለልተኛ በሆነ አካል እንዲመረመር ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ፓወር እንዲህ ብለዋል፣ “ሕዝቡ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞውን እንዲገልጽ ለማድረግ መንግስት እንዲፈቅድ ዩናይትድ ስቴትስ ጠይቃለች“፡፡
“ዘ-ህወሀት በሰው ልጆች ላይ መጠነ ሰፊ የሆነ እልቂት ፈጽሟል፡፡ እነዚህን እልቂት የፈጸሙትን ወንጀለኞች ለፍትህ አካል ማቅረብ እና ተማዕኒነት ያለው ዓለም አቀፍ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ነው:: ዘ-ህወሀት ሰላማዊ አማጺዎች ሰላማዊ ሰልፍ እንዲያደርጉ መፍቀድ አለበት” የሚሉት ሁሉ ለዴፕሎማሲያዊ ፍጆታ ሲባል ብቻ የተደረጉ እንቶ ፈንቶ ንግግሮች ናቸው፡፡
እ.ኤ.አ ነሀሴ 10/2016 የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ጥበቃ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር በርካታ በሆኑ መሳሪያ ባልታጠቁ አማጺዎች ላይ የዘ-ህወሀት ታጣቂ ኃይሎች እልቂት በፈጸሙባቸው አካባቢዎች እና ሕዝቡ መገዳደር ባደረገባቸው ቦታዎች ምርመራ ማድረግ የሚችሉ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች እንዲገቡ እንዲፈቅድ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ዘ-ህወሀት ከዋና ኮሚሽነሩ ለቀረበለት ጥያቄ አልፈቅድም በማለት አፍንጫውን ነፍቶ አኩሩፏል፡፡
እ.ኤ.አ ነሀሴ 21/2016 የዩኤስ አሜሪካ የዴሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብቶች እና የስራ ረዳት ዋና ጸሀፊ እና የኦባማ ዓለም አቀፍ የዴሞክራሲ እና የሰብአዊ መብቶች ዋና መልዕክተኛ የሆኑት ቶም ማሊኖውስኪ የዘ-ህወሀት አገዛዝ “በሀገሪቱ ውስጥ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች በአመጹ ዜጎች ላይ የተሰጠው ስልታዊ ምላሽ እራስን በእራስ ድል አድርጎ የማሸነፍ ያህል ነው“ በማለት አውጀዋል፡፡
ይህም ማለት “ዘ-ህወሀት በርካታ ሰላማዊ በሆኑ ዜጎች ላይ እልቂትን በፈጸመ ቁጥር እራሱን ለአስከፊ አደጋ እያጋለጠ እና ዕድሉን እያጨለመ ነው የሚሄደው፡፡ በጎራዴ ላይ ተንጠልጥለው
የሚኖሩ ሁሉ በጎራዴ ይጠፋሉ“ የሚል ዴፕሎማሲያዊ ንግግር ነበር ያደረጉት፡፡
እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ግን ዘ-ህወሀት መሮጥም ሆነ እራሱን መደበቅ አይችልም፡፡ ዘ-ህወሀት አልቆለታል። የዘህዋሃት ጉዳይ አክትሟል!
እ.ኤ.አ መስከረም 6/2016 የአውሮፓ ህብረት (አህ) ለዘ-ህወሀት የሚሰጠውን የአስቸኳይ ጊዜ የገንዘብ እርዳታ በመቁረጥ እርምጃ ወስዷል፡፡ የአውሮፓ ህብረት እንዲህ የሚል መግለጫ ሰጥቷል፡ “ለአፍሪካ የሚሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ የገንዘብ እርዳታን በሚመለከት በተጠቃሚ ሀገሮች መንግስታት መዋቅሮች አማካይነት ምንም ዓይነት ገንዘብ በማዕከል እንደማይያዝ ወይም ደግሞ እንደማይለቀቅ መታወቅ ያለበት ጠቃሚ ነገር ነው“ ነበር ያለው፡፡ በሌላ አገላለጽ የአውሮፓ ህብረት የዘ-ህወሀትን አውሬዎችን በቀጣይነት ሊመግብ አይችልም፡፡
እ.ኤ.አ መስከረም 11 በአሜሪካ ታሪክ በመጥፎ ትውስታ ስትታወስ ትኖራለች፡፡
እ.ኤ.አ መስከረም 11/2001 የአልቃይዳ አሸባሪ ቡድን በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ አራት ዙር ጥቃቶችን በማቀናበር በ3,000 ንጹሀን ዜጎች ላይ እልቂትን የፈጸመ ሲሆን ለመናገር የሚያዳግት በቢሊዮኖች ዶላር ሊቆጠር የሚችል ንብረትን አውድሟል፡፡
አሜሪካውያን እና መላው ዓለም በአልቃይዳ ዕኩይ ድርጊት የተሰማውን ሀዘን እና ድንጋጤ ገልጿል፡፡
ሆኖም ግን ስሙ በዓለም አቀፉ የአሸባሪዎች የመረጃ ቋት ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው አሸባሪው ድርጅት ዘ-ህወሀት በጠራራ ጸሐይ ቀን በቀን መጠነ ሰፊ የሆነ እልቂትን ወንጀሎችን በንጹሀን ዜጎች ላይ እየፈጸመ ባለበት በአሁኑ ወቅት የኦባማ አስተዳደር አላየሁም፣ አልሰማሁም በማለት ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ይገኛል፡፡
ወቼ ጉድ! ይህ ሁኔታ በዓለም አቀፍ አሸባሪዎች ላይ የሚታይ ባለሁለት ምላስ አወናባጅ ፖሊሲ ነው፡፡
የኦባማ አስተዳደር አመለካከት እንዲህ የሚል ሆኖ ይገኛል፣ “ዘ-ህወሀት አሸባሪ ድርጅት ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን እነርሱ የእኛ አሸባሪዎች ስለሆኑ ተዋቸው አትንኳቸው“ ነው እያለ የሚገኘው፡፡
በተመሳሳይ መልኩ እንደ ፕሬዚዳንት ዲ. ሩዝቤልት አመለካከት ሁሉ የላቲን አሜሪካ አምባገነን የነበረው ሶሞዛ ጋርሻ የታወቀ በጥባጭ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም “ሶሞዛ ጋርሻን ተውት እርሱ የእኛ በጥባጭ ነው” እንዳሉት መሆኑ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን በመስከረም 2009 ዓ.ም የሚያከብሩት ምንም ዓይነት በዓልየለም፡፡
ለእነርሱ መስከረም እንደ ቶማስ ሁድ “ህዳር” ይቆጠራል፡፡
ምናልባትም ቶማስ ሁድ ይህን ጉድ ቢያይ “ህዳር” በሚል ርዕስ ያዘጋጃቸውን እና እንዲህ የሚሉትን የግጥም ስንኞች “መስከረም 2009 ዓ.ም በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በመቀየር ይሰይማቸው ይሆናል፡
ምንም ጸሐይ የለች እንዲሁም ጨረቃ፣
ተፈርክሳ ይሆን ከመሬት ላይ ወድቃ፣
ወይስ ተሰውራ ዓለማትን ንቃ ከህዋው ርቃ፡፡
ጧት የሚባል የለም እንዲሁም ምሽት፣
የሚያበሳጭ እንጅ የሚያደብን ቆሽት፡፡
ንጋትም ኮብልሏል ጨለማም አክትሟል፣
ሁሉም በየፊናው ካለም ተሰውሯል፣
የሁል ጊዜ ግብሩን ኡደቱን አቁሟል ፡፡
ትክክል ያልሆነ የቀናት ጎደሎ፣
ውሸትን ተላበሶ እውነት አስመስሎ
ጊዜውን አዛብቶ ሰላማዊ ገድሎ፣
አምባገነኖችን ገዳዮችን አዝሎ፣
የታሪክ ቆሻሻ ጥንባት ዘባትሎ፡፡
ምንም ሙቀት የለም ደስታም ርቋል፣
ምንም ጤና የለም ጤንነት ተቃውሷል
ምቾትም አክትሟል በድን ግኡዝ ሆኗል፡፡
ምንም ጥላ የለም ነጸብራቅም ጠፍቷል፣
ቢራቢሮዎችም ካገር ኮብልለዋል፣
ትጉሀን ንቦችም አገር ቻው ብለዋል፡፡
ፍራፍሬ የለም አበቦች መክነዋል፣
አረንጓዴዎቹ ቅጠሎች ጠፍተዋል፣
ዘማሪ ወፎቹ ካይን ተሰውረዋል፡፡
ስለዚህ መስከረም ልምላሜው ቀርቶ፣
አዲስ ተስፋን ትቶ ሀዘንን አስፋፍቶ፣
አበቦችን ሳይሆን መከራን አፍክቶ፣
የወፎች ዝማሬ ቅላጼን አጥፍቶ፣
የጠራ ውኃውን በድፍርሱ ሞልቶ፣
ይኸው ብቅ አለልን ተጀባኖ ኮርቶ፡፡
ስለዚህ መስከረም የድሮም አይደለሽ የምንጠብቅሽ፣
የምንቦርቅብሽ የምንፈነጭብሽ፣ የምንዘልብሽ፣
የምናቅድበሽ፣ የምንመክርብሽ፣ ቃል የምንገባብሽ፣
የቶማስ ህዳር ነሽ ስቃይ ያጠላብሽ፣
ሰይጣን የሚነዳሽ ሲኦል የሚያዝዝሽ፡፡
ነጻነት፣ ዴሞክራሲ እና ሰብአዊ መብቶች በ2009 ዓ.ም በኢትዮጵያ እንደ ጸሐይ ያንጸባርቃሉ፡፡
ጨለማውን ሰማይ በኢትዮጵያ ሸፍኖ ይዞት ከሚገኘው ሰይጣናዊ ሰራዊት ጋር የሚደረገው ጦርነት በመጧጧፍ ላይ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ጊዜ እየተካሄደ ያለው የኢትዮጵያን ሕዝቦች ልብ እና አእምሮ ለማሸነፍ እና ለመቆጣጠር የሚደረግ የመጨረሻው ጦርነት ነው፡፡
ሆኖም ግን ጦርነቱ በጠብመንጃዎች፣ በሮኬቶች፣ በሚሳይሎች እና በታንኮች እየታገዘ የሚደረግ ጦርነት አይደለም፡፡
ይልቁንም ጦርነቱ በድፍረት፣ በተስፋ፣ በጀግንነት እና በዓላማ ጽናት እየታገዘ የሚካሄድ ትክክለኛ እና ፍትሀዊ የብዙሀኑ ሕዝብ ጦርነት ነው፡፡
በኢትዮጵያ ባለው ጭቆና ላይ የዴሞክራሲ፣ የነጻነት እና የሰብአዊ መብቶችን ለማረጋገጥ የሚደረግ ጦርነት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ልብን እና አእምሮን ለማሸነፍ እና ለመቆጣጠር የሚጠቀሙባቸው መሳሪያዎች በሰው ልጆች ዘንድ በጣም ታዋቂነት ያላቸው እና ከሀይድሮጅን ቦምብም እንኳ የበለጡ ናቸው፡፡ አምባገነኖች እንደሚያስቡት እና መርሃቸው አድርገው እንደሚተገብሩት ሳይሆን እነዚህ መሳሪያዎች ግን ኃይል አልባ መሳሪያዎች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያውያን መጠነ ሰፊ በሆነ ሰላማዊ እምቢተኝነት፣ በህዝባዊ መገዳደር፣ ለጠላት ተባባሪ ባለመሆን፣ በሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፎች፣ በአመጾች፣ በሕዝባዊ ተቃውሞዎች፣ በጸሎቶች፣ በዓለም አቀፍ የእስፖርት እንቅስቃሴዎች የእምቢተኝነት እና ያለመታዘዝ ድርጊቶች ምልቶችን በማሳየት፣ የንግዱ ማህበረሰብ የንግድ ድርጅቶችን በመዝጋት እና ስራን በማዳከም፣ የኢኮኖሚ እቀባን በማድረግ እና የገዥው ፓርቲ አባላት ዋና የገንዘብ ማግበስበሻ የሆኑ የልማት ድርጅቶችን ምርቶች እና አገልግሎቶችን ባለመጠቀም ማሽመድመድ እና ከገበያ ውጭ ማድረግ፣ የተወሰኑ የጀግንነት ስራዎችን በመስራት፣ መንገዶችን በመዝጋት፣ የማህበራዊ እና የሙዚቃ በዓላት ኮንሰርቶችን በመዝጋት እና በማጨናገፍ፣ በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማን ተግባራዊ በማድረግ፣ በይፋ እና በስውር ለአምባገነኑ ገዥ አካል ባለመታዘዝ፣ በወታደራዊ ባለስልጣኖች ላይ በማመጽ እና ሌሎች በርካታ መንገዶችን በመጠቀም የሕዝብ አሸናፊነትን ማረጋገጥ እና ነጻነትን ከአምባገነኖች መዳፍ በመንጠቅ ሕዝባዊ ባለቤትነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል ኢትዮጵያውያን በተግባር የተረጋገጡ የኃይል አልባ የትግል ተሞክሮዎች አሏቸው፡፡
የኃይል አልባ ትግል የመንፈስ አንድነት ሳይኖር፣ የጋራ ዓላማ ሳይሰነቅ እና የጋራ የድርጊት ተሞክሮ ከሌለ አይሰራም፡፡
በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ለነጻነት፣ ለዴሞክራሲ እና ለሰብአዊ መብቶቸ መከበር ለሚደረገው ጥረት ከምንጊዜውም በላይ ህብረታቸውን እና አንድነታቸውን በማሳየት ላይ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ለጋራ ዕድሎቻቸው ህብረታቸውን በማሳየት ላይ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ጭቆናን ለመዋጋት እና በድል አድራጊነት ለመደምደም ህብረታቸውን በማሳየት ላይ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ለወደፊት ልጆቻቸው እና ለአቦሸማኔው ወጣት ትውልድ መጻኢ ዕድል ሲሉ ህብረታቸውን በማሳየት ላይ ይገኛሉ፡፡
ህብረት ካለ እና በጋራ የመስራት ባህል ከተለመደ ሁልጊዜም ቢሆን ድልን መቀዳጀት ይቻላል፡፡ ሁልጊዜ!
የኢትዮጵያውያን ድል በእጅ ነው ምክንያቱም ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለችና፡፡
አሁን ከያዝነው ወር ወደ 159 ዓመታት ገደማ ወደ ኋላ መለስ በማለት የነበረውን ሁኔታ ስናስታውስ ታላቁ አፍሪካ-አሜሪካዊ የጸረ ባርነት ታጋይ ፍሬዴሪክ ዳጉላስ አድርገውት የነበረው ንግግር ኢትዮጵያውያን ባለፈው ሩብ ዘመን ያህል በወሮበላ ዘራፊ ጨቋኝ ገዥዎች ቁም ስቅል እያዩ ሲገደሉ እና የግፍ ጭቆና ሲፈጸምባቸው የቆየውን ባርነት የሚገልጽ ወቅታዊ፣ አስገዳጅ እና ውጤታማ የሆነ መልዕክት ያስተላልፋል ብየ አምናለሁ፡፡
ዳጉላስ ካደረጉት ንግግር በአሁኑ ጊዜ አጽንኦ በመስጠት ሊታወስ የሚገባው አንድ መስመር እንዲህ የሚል ሆኖ ይገኛል፡ “መራራ ትግል ከሌለ ምንም ዓይነት ዕድገት አይኖርም“ ነበር ያሉት፡፡
የዳጉላስን ጊዜ አይሽሬ መልዕክቶች እንደ እራሴ መልዕክቶች በማድረግ እና በመጋራት የእራሴንም ጨምሬ ከዚህ በታች አዘጋጅቼ ለኢትዮጵያውያን ወገኖቼ በሙሉ በአዲሱ ዓመት እንዲያጤኑት እና እንተገብሩት እንደሚከተለው ጀባ እላለሁ፡
“የሰው ልጅ አጠቃላይ ባህሪ ሲታይ የሰው ልጅ ማድረግ የሚያስችል አጋጣሚን እስካገኘ ድረስ እና ለእራሱ ነጻነት ሲል መዋጋት ካልቻለ በሌሎች ሲወጋም ምንም ማድረግ የማይችል ዋጋ የሌለው ፍጡር ነው፣ እናም ይኸ ውስጣዊ ባህሪ እና አመላካከትም ትክክለኛ ነው፡፡ ለእራሱ ነጻነት ዋጋ የማይሰጥ ሰው ለሌሎች ሰዎች ነጻነት በፍጹም ዋጋ ይሰጣል ተብሎ አይታሰብም፣ ወይም ደግሞ ለሌሎች ነጻነት ሲል እራሱን በማይመች በማንኛውም ነገር ላይ አያስቀምጥም፡፡ እንደዚህ ያለ ሰው ይላል ዓለም የሚነሳሳ ስሜት እስከሚኖረው ድረስ ያለምንም ኮሽታ ለጥ ብሎ ይተኛል፡፡
እንደዚያ ዓይነቱ ሰው ለእርሱ በሚሰጠው በማንኛውም ግዴታ ቢሆን በዓለም ላይ በፍጹም ሊተኛ አይገባም፡፡ ሆኖም ግን በሞራል ስብዕና የዘቀጠ በመሆን የታሪክን ጎማ ወደ ኋላ የሚያሽከረክር ይሆናል፡፡ እና በተለይ ዘርነት የሚለይ ከሆነ በእራሱ እና በእራሱ ዝርያ ላይ ምንም ዓይነት ክብር የሌለው እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ የምንኖርባት ዓለም ለሁሉም ዓይነት ሕዝቦች በጣም የምትስማማ ናት፡፡ ህዝቦች በሚወስዷቸው እርምጃዎች ሁሉ ዓለም ከእነርሱ ጋር ትተባበራለች፡፡ እራሳቸውን በጽናት ለሚረዱ ሰዎች እርዳታዋን ትዘረጋለች፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ለእራሳቸው እንቅፋት ለሚሆኑ ሰዎች እርሷም እራሷ እንቅፋት ትሆናለች፡፡ እራሳቸው ለሚሰሯቸው ስህተቶች ስሜት አልባ ለሆኑ እና የእራሳቸውን መብቶች ለማስከበር ደንታ ለሌላቸው ሰዎች ተፈጥሮም እራሷ የምታግዛቸው እና የምታዝንላቸው አይሆኑም፡፡ እራሳቸውን ነጻ ለማድረግ ጠንካራውን ምት መምታት አለባቸው በማለት ገጣሚው የተናገረው የግጥም ስንኝ እውነትም ትክክል ነው፡፡
አንድ የአየርላንድ አርበኛ ለአየርላንድ ትክክለኛ መብቶች እና ነጻነቶች የሰው ልጆች ጥልቅ ፍቅር ሁሉ ከእርሱ ጋር ነበር እናም የእርሱ ጠላቶች እንኳ የእርሱን የጀግንነት አርበኝነት እንዲያከብሩ ተገደዋል፡፡ አንድ የሀንጋሪ አርበኛ ሀንጋሪ በጎራዴ ከወደቀች በኋላ ለሀንጋሪ ህዝቦች በብዕሩ ለረዥም ጊዜ ባደረገው ተጋድሎ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ የሊበራሉን ዓለም ፍቅር እና ድጋፍ ተጎናጽፏል፡፡
ቱርኮች ለእራሳቸው ነጻነት በጀግንነት በሚዋጉበት ጊዜ እና የሩሲያን ከፍተኛ ወታደሮች አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ከሀገራቸው ሲያባርሯቸው የሰውን ልጅ አድናቆት ሁሉ ነበር የተጎናጸፉት፡፡ ከእብሪተኛ እና ኃይለኛ ጠላት ፊት ለእራሳቸው መብቶች መከበር ሲሉ በጽናት ነበር የቆሙት፡፡
በአሁኑ ጊዜ የወገኖቻችንን ነጻነት ለማሳደግ እና ህዝቦቻችንን ከፍ ወዳለ ደረጃ ላይ ለማድረስ እየተካሄደ ባለው ትልቅ ጦርነት ሙሉ ኃይላችንን አሟጥጠን በመጠቀም በስራ ላያ ማዋል ይኖርብናል፡፡ አቅማችን እስከፈቀደልን ድረስ እንድ ሰውም ሆነ ወይም በርካታ ሰዎች በብዛት በመሆን ለእራሳችን አስፈላጊ የሆኑትን እርምጃዎች በመውሰድ ለነጻነታችን የሞት ሽረት ትግል ማድረግ ይኖርብናል፡፡
ስለለውጥ ፍልስፍና እስቲ ልንገራችሁ፡፡ የሰው ልጆች የነጻነት ዕድገት ታሪክ ሁሉም ክብሮች እና መብቶች ከጽኑ ትግል እንደሚወለዱ ያመላክታል፡፡
እየተካሄደ ያለው ግጭት ያለውን ደስታ፣ ቅስቀሳ ሁሉንም በመውሰድ ለጊዜውም ቢሆን ያለውን ጫጫታ እና ትርምስ ሊያስቆመው ይችላል፡፡ ይህንን ማድረግ አለበት ወይም ደግሞ ምንም ነገር ላያደርግ ይችላል፡፡ ምንም ዓይነት ትግል ከሌለ ምንም ዓይነት ዕድገት አይኖርም፡፡ ነጻነትን ለመጎናጸፍ የሚመኙ እና ቅስቀሳን የሚያወግዙ ሰዎች በምንም ዓይነት መንገድ መሬትን ሳያርሱ አዝመራ ማፈስን፣ መብረቅ እና ብልጭታ ሳይኖር ዝናብን ብቻ የሚጠብቁ ናቸው፡፡ አስቀያሚ የሆነውን የበርካታ ውኃዎችን ጩኸት እና ማዕበል ሳይሰሙ ብቻ ሰላማዊ የሆነውን ውቅያኖሱን ለማግኘት የሚፈልጉ ናቸው፡፡
ይኸ ትግል የሞራል ወይም ደግሞ የጉልበት አለያም የሁለቱም የሞራል እና የጉልበት ጥያቄ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ምንም ይሁን ምን ትግል መሆን አለበት፡፡ ኃይል ብቻውን ያለፍላጎት ምንም አይደለም፡፡ በፍጹም ምንም ሆኖ አያውቅም ወደፊትም በፍጹም ምንም ሊሆን አይችልም፡፡ ሰዎች ጸጥ በማለት ማንም እንዳደረጋቸው ለመሆን ሁሉንም ነገር ዝም ብለው የሚቀበሉ ከሆነ በላያቸው ላይ የሚጫኑትን ኢፍትሀዊነት እና ትክክል ያልሆኑ ነገሮችን ምንም ሳይገዳደሩ እንዳሉ በመቀበል በቃላት ወይም በኃይል ወይም ደግሞ በቃላት እና በኃይል ሁለቱንም ተጠቅመው የማያስወግዷቸው ከሆነ እንዳሉ እንዲቀጥሉ የሚፈቅዱ ይሆናል ማለት ነው፡፡ የጨቋኞች የጭቆና ወሰን እነርሱ እየጨቆኗቸው ባሉት ህዝቦች የታጋሽነት ገደብ የሚወሰን ይሆናል፡፡
በዚህች ዓለም ሰዎች ለከፈሉት ሁሉ ዋጋውን ላያገኙ ይችላሉ፣ ሆኖም ግን ላገኙት ሁሉ ዋጋ መክፈል አለባቸው፡፡ በላያችን ላይ ከተቆለሉት ጭቆናዎች እና ትክክል ያልሆኑ ኢፍትሀዊ ነገሮች ነጻ ለመሆን እና ለማስወገድ ዋጋ መክፈል አለብን፡፡ ይህንን ድርጊት በጉልበት፣ በመሰቃየት፣ በመስዋዕትነት እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም የእራሳችንን እና የሌሎችን ሕይወት በመገበር ተግባራዊ ማድረግ አለብን፡፡
እንደገናም የባሮቹ የነጻነት ንቅናቄዎች በበርካታዎቹ ሀሳባዊ እና ወደተግባር የማይቀየሩ ሆነው እንዲቀሩ ጥረት ይደረጉ እንደነበር እገነዘባለሁ፡፡ እንደዚህ ያሉ ንቅናቄዎች በአሁኑ ጊዜ በደቡብ እየተደረጉ ነው፡፡ ጀኔራል ተርነር በሳውዝአምፕቶን ወደብ የንቅናቄ እሳቱን ባይጀምር ኖሮ የነጻ ማውጣቱ ተግባር በምዕራብ ኤንዲስ እና በቪርጂኒያ በአጠገባቸው አይደርስም ነበር፡፡“(አህጽኖ ተጨምሯል፡፡)
ለቅሶ እስከ ዛሬ ምሽት ከዚህም አልፎ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ደስታ በ2009 ዓም በጧት ከተፍ ይላል!
በ2009 ዓ.ም ለእያንዳንዱ ሰው እንዲህ የሚል አንድ ነገር እመኛለሁ፡ “አሮጌው ከነኮተቱ ይውጣ፣ አዲሱ ከነጠቃሚ ነገሮቹ ይግባ!“ በባህላዊ የአዲስ ዓመት ትውፊታችንም “የጎመን ምንቸት ይውጣ፣ የገንፎ ምንቸት ይግባ” እንል የለ!
2009 ዓ.ም ብሄራዊ የድብብቆሽ ጨዋታው እና የዘረኝነት አባዜው ከነጉግ ማንጉጉ ተጠራርጎ ወደ ታሪክ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫት የሚጣልበት ዓመት ይሆናል፡፡
እ.ኢ.አ መስከረም 1/2009 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ ነጻነት፣ ዴሞክራሲ እና የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታወሱበት ዕለት ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝቦች በንቅናቄ ላይ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔ ወጣቶች በቀንደኛ ጠላታቸው ላይ እመር በማለት ከጭንቅላቱ ላይ ለመውጣት ድምጾቻቸውን ከፍ በማድረግ በማጉረምረም ላይ ናቸው፡፡
ለ25 ዓመታት የዘለቀው የዘ-ህወሀት መቅሰፍት በ2009 ዓ.ም ከነጉግማንጉጉ ተጠራርጎ ግብአተ መሬቱ ይፈጸማል፡፡ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፡፡
ለቅሶ እስከ ዛሬ ምሽት ከዚህም አልፎ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ደስታ በ2009 ዓም በጧት ከተፍ ይላል!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
መስከረም 2 ቀን 2009 ዓ.ም