ኢትዮጵያ፡ ከጭፍን የፖለቲካ ጥላቻ ባሻገር፣

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም 

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ  

የእምነቴ መርሆዎች፡ በአሁኑ ጊዜ ጥላቻ በኢትዮጵያ ሕዝብ እና በነጻነት፣ በዴሞክራሲ እና በሰብአዊ መብት ጥበቃ የተፈረከሰከሰ ግድግዳ መካከል የቆመ ነገር ሆኖ ይገኛል፡፡

የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) ጥላቻን የፖለቲካ መጠቀሚያ መሳሪያ አድርጎት ይገኛል፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ በዘ-ህወሀት እየተቀነቀነ ያለው የጭቃ ግድግዳ ጥላቻ በሕዝባዊ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ አመጽ ዶግ አመድ እየሆነ በየቦታው ባስደማሚ ሁኔታ በራሱ በዘ-ህወሀት ላይ በመፈረካከስ ላይ ይገኛል፡፡ ክልሎች (የዘ-ህወሀት የአፓርታይድ ባንቱስታንስ አቻ) እንደበረዶ ሲሟሙ እንደ ቅቤ ሲቀልጡ በዓይናችን በብረቱ በመመልከት ላይ እንገኛለን፡፡ ዘ-ህወሀት ላለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን ያህል ስልጣንን ጠቅልሎ በስልጣን ማማ ላይ እንደመዥገር ተጣብቆ እንዲቆይ ያደረገው ዋና ምክንያት ጭፍን የጎሳ እና የኃይማኖት ጽንፈኝነት የፖለቲካ ጥላቻን ሲያራግብ በመቆየቱ ነው፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በየቦታው ከዘ-ህወሀት የክልል እስር ቤት በሮችን በሰላማዊ አመጽ እየሰበሩ በመውጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ ጀግኖቹ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በጥላቻ ጌቶች ላይ በአስደማሚ ሁኔታ በማመጽ ላይ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች በጽኑ የሰላማዊ የእምቢተኝነት የትግል መንፈስ እጆቻቸውን በማጣመር ምንም ዓይነት የዘ-ህወሀት ኃይል መንፈሳቸውን እንደማይሰብረው በማወጅ “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች” በሚል መሪ ቃል እየተመሩ ጉዟቸውን በማጠናከር ላይ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዘ-ህወሀት የጥላቻ ሰለባ ሆነው ለበርካታ ጊዜ ከመቆየታቸው አንጻር በስቃዮቻቸው እና መከራዎቻቸው ስፋት እና ጥልቀት እንደ አንድ ሆነው ተባብረዋል፡፡ የኦሮሞ ልጆች በሰላማዊ መንገድ መብቶቻቸውን በመጠየቃቸው ብቻ በግፈኛው አገዛዝ እልቂት በተፈጸመባቸው ጊዜ አማራ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ እና ሌሎች ወላጆች በሙሉ አልቅሰውላቸዋል ምክንያቱም እነዚህ ልጆች የእናት ኢትዮጵያ ልጆች ናቸውና፡፡ የአማራ፣ የትግሬ፣ የጉራጌ እና የሌሎች ወላጆች ልጆች ላይ ዘ-ህወሀት እልቂትን በፈጸመ ጊዜ የኦሮሞ ወላጆች ለእነዚህ ልጆች አንብተዋል ምክንያቱም ሁሉም ልጆች የእናት ኢትዮጵያ ልጆች ናቸውና፡፡

እነዚህ ጥላቻን ሲዘሩ የቆዩት በአሁኑ ጊዜ በህዝቦች ህብረት እና አንድ መሆን የዘሩትን ማጨድ ጀምረዋል፡፡ ዘ-ህወሀት ከረዥም ጊዜ ጀምሮ የእርሱ ዕድል እና ዕጣ ፈንታ ከትግራይ ሕዝብ ዕድል እና ዕጣ ፈንታ ጋር የተሳሰረ እና የተቆራኘ እንደሆነ አድርጎ በቅጥፈት ሲሰብክ ቆይቷል፡፡ እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ግን ዘ-ህወሀት ማንንም የኢትዮጵያ እውነተኛ ልጆች አይወክልም፣ ሊወከል የሚችለው ግን ከሁሉም የጎሳ ቡድኖች እና የእምነት ተቋማት ያሉ ሆድ አምላኩ እበላባይ አግበስባሾች እና ከእርሱ የበከተ የሙስና ማዕዱ ተቋዳሽ የሆኑትን አባሎቹን፣ ደጋፊዎቹን እና ግብረ አበር ታማኝ ሎሌዎቹን ብቻ ነው፡፡

 ፈይሳ ሌሊሳ በሪዮ ኦሊምፒክ ብር መዳልያ ተሸላሚ የኢትዮጵያ ወጣቶች እምቢተኝነት ምልክት ሲያሳይ

ፈይሳ ሌሊሳ በሪዮ ኦሊምፒክ ብር መዳልያ ተሸላሚ የኢትዮጵያ ወጣቶች እምቢተኝነት ምልክት ሲያሳይ

የሪዮ ማራቶን የነሐስ ማዳሊያ ያገኘው ፈይሳ ሌሊሳ ለኢትዮጵያ ወጣቶች ያለውን ታላቅ ክብር ድሉን ከተቀዳጀ በኋላ እጆቹን በማጣመር በዓለም አደባባይ አሳይቷል፡፡ 

የብልህነት የካርቱን  ገጸ ባህሪ ባለው እና በስም ፖጎ እየተባለ በሚጠራው እና በእኔ እድሜ በጣም አስቂኝ ቀልዶችን ያቀርብ በነበረው ቀልደኛ ትችቴን ልጀምር፡፡

በዚያ አስቂኝ በሆነው የእንስሳት የካርቱን ቀልድ ረግራጋማ በሆነ አካባቢ በሚኖር ማህበረሰብ ውስጥ የአሜሪካንን ብዙሀን ህዝብ በመወከል ከተመሳሳይ ጉዳዮች ጋር እየተፋጠጠ ይኖር ነበር፡፡ ያ ማህበረሰብ መፈረካከስ ጀመረ ምክንያቱም የአካባቢው ኗሪዎች በጣም ጠቃሚ እና አንገብጋቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አብረው በመግባባት መኖር አልቻሉም፡፡ በማይረቡ ጉዳዮች ላይ በመጨቃጨቅ እና መጥፎ ባህሪን በሚያንጸባርቅ መልኩ በመወዛገብ ጊዚያቸውን በከንቱ ያሳልፉ ነበር፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ፖጎ ይኖርበት የነበረው ረግራጋማ ቦታ በፍርስራሽ እና ቁርጥራጭ ቆሻሻ ነገሮች ተሞልቶ አየው፡፡ በዚህ ጊዜ ፖጎ በከፍተኛ ደረጃ በመተንፈስ እና ተስፋ በቆረጠ የስሜታዊነት መንፈስ እንዲህ አለ፣ “ከጠላታችን ጋር ተገናኘን፡፡ እርሱም እኛው ነን!“ ነበር ያለው፡፡

ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን ያህል ዘ-ህወሀት በኢትዮጵያ ውስጥ በፈጠረው እና ኮትኩቶም ባሳደገው የፖለቲካ ጥላቻ ስሜታዊነትን በተላበሰ እና ተስፋ በቆረጠ መልኩ የፖጎን አባባል በመዋስ እንዲህ በማለት አውጃለሁ፡

“በጥላቻ ከተሞሉት ጋር ተገናኘን፡፡ እነርሱም እራሳችን ነን!“ 

ባለፈው ሳምንት “አእምሯቸው የደነዘ አማሮች፣ የኦሮሞ ወንጀለኞች እና አሸባሪዎች በ2016 በኢትዮጵያ ምድር እየተነሱ ነውን?” በሚል ርዕስ አዘጋጅቸው በነበረው ትችት በርካታ የሆኑ መደበኛ እና ሌሎችን አንባቢዎቼን ቀልብ የሳበ ለመሆኑ ትምህርት ወስጀበታሁ፡፡ የዚህ ውሱን የሆነ ትችት በድረገጽ እና በማህበራዊ የግንኙነት መስመሮች በአንባቢዎች ላይ የነበረው ተደራሽነት ልዩ በሆነ መልኩ ከተለመደው በላይ  በእጅጉ ልቆ ታይቷል፡፡  ግን ለምን?

ተደራሽ ከሆኑት አንባቢዎች ለእኔ ትችት የተሰጡት ግብረ መልሶች የተለያዩ ሲሆኑ ጥቅል መንፈሳቸው እንደሚከተለው ተጨምቀው ቀርበዋል፡

1ኛ) የጥላቻ ንግግርን እና የጥላቻ አራጋቢዎችን ውስብስብ ጉዳይ በጣም ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ በሌላ መልኩ መቅረብ ሲኖርበት እንደዚህ ባለ “አስደንጋጭ” እና “ፊት ለፊት በሆነ መልኩ” በብዙሀን መገናኛ ዘዴዎች ማቅረብ እንዳልነበረብኝ ሀሳብ ቀርቦልኛል፡፡

2ኛ) ለበርካታ ጊዜ ውጉዝ ከማሪዮ በመሆን አይነኬ ሆኖ የቆየውን “የጎሳ ንቀት” እና “የጎሳ ጥላቻ” አንገብጋቢ ርዕሰ ጉዳይ ለሕዝብ መወያያ አድርጌ ማቅረብ እንደሌለብኝ ተነግሮኛል፡፡ ለዚህም ይላሉ ምክንያታቸውን ሲያቀርቡ እንደዚህ ያለውን ነገር ለሕዝብ ውይይት በይፋ ማቅረብ ልማዳችን አይደለም (“ነውር ነው”) የሚል ነው፡፡

3ኛ) ይህ ትችት መቅረብ አልነበረበትም ምክንያቱም የጎሳ ግንኙነቶችን ያሻክራል እናም በዚህ መልኩ በጎሳ ጥላቻው ላይ የበለጠ “ነዳጅ ያፈርከፈክፋል” የሚል ነው፡፡

4ኛ) በእኔ ትችት ላይ የቀረበውን እና ያንን ድምጹን ከፍ አድርጎ ኢምክንያታዊ በሆነ መልኩ በምስል እና በድምጽ በተደገፈ ሁኔታ የዘረኝነት ቅስቀሳ ሲያካሂድ የነበረውን ሰው ስም እና ማንነት በመጥቀስ ማሳፈር እንደነበረብኝ ይጠቅሳል፡፡ አቅራቢው ምክንያቱም ይላሉ ያ ሰው በኢትዮጵያ ዲያስፖራ የዘ-ህወሀት ዋና ጠርናፊ/አገልጋይ ሎሌ መሆኑ(ኗ)  ይታወቃልና ነው የሚሉት፡፡

5ኛ) እንደዚያ ያለውን “የወረደ ዝቅተኛ” በኢንተርኔት በዓለም አቀፍ ደረጃ እና በኢትዮጵያ ሬዲዮ ማሰራጫ ጣቢያ ድምጹን ከፍ አድርጎ የጥላቻን መርዝ ለሚተፋ እና ኢምክንያታዊ ለሆነ ሰው ትኩረት ማድረግ እንደሌለብኝ የሚያሳስብ ነው፡፡ እንደዚህ ያለ “የወረደ ዝቅተኛ” እና በደም ፍላት በንዴት በሚናገር ሰው ላይ ትችት በማቅረቤ ለእነርሱ እውቅና እና ሕጋዊነትን እንደመስጠት እንደሚቆጠር ያላቸውን አስተያየት ገልጸዋል፡፡

6ኛ) ሁሉም የጥላቻ አራጋቢዎች ጥላቻቸውን በተጠናከረ መልኩ እንዲተፉ የበለጠ የሚያደፋፍር እንዲሆን እንዳደርግሁ ጠቁመዋል፡፡ ምክንያቱም በወደፊቱ በእኔ ትችቶች የሕዝብን ቀልብ እንደሚያገኙ ይጠብቃሉና ብለዋል፡፡

7ኛ) በዚህ አሁን በሀገሪቱ ውስጥ በጣም አንገብጋቢ በሆነው ጊዜ ላይ ስለጥላቻ እና በጥላቻ ስለተሞሉ ሰዎች ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ መቅረብ አልነበረበትም፣ ምክንያቱም ጥቂት ሰዎችን እንዲበሳጩ እና በንዴት ደመነፍስ በሆነ መልኩ እርምጃ እንዲወስዱ ያደፋፍራልና በማለት አስተያየታቸውን ያቀርባሉ፡፡

8ኛ) ይህንን ትችት በማቅረብ በእርግጠኝነት በተወሰኑ ቡድኖች ላይ ጥላቻን የማራመድ ተልዕኮ እንደፈጸምኩ ትችት ቀርቧል፣ ምክንያቱም ይላሉ ትችት አቅራቢው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የጥላቻ አራጋቢዎችን ተልዕኮ እንዳራገብኩ ይተቻሉ፡፡

9ኛ) በአሁኑ ጊዜ ዘ-ህወሀት ለደጋፊዎቹ እና ለተከታዮቹ በእኛ ላይ እየተነሱብን ነው እናም ከእኛ ጎን በመሰለፍ እያንዳንዳችሁ እኛኑ እንድትቀላቀሉ የሚል ስብከት እንዲያካሂድ እንዳስቻልኩት አድርገው ጽፈዋል፡፡

10ኛ) እኔ እራሴ የጥላቻ አራጋቢ እንደሆንኩ እና የጥላቻ አራጋቢዎችን መልዕክት እራሴ በመድገም ላይ እንደምገኝ እና ከዚህም በተጨማሪ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ በዘ-ህወሀት ላይ  የማይናወጥ እና ጠንካራ ትችት አቅራቢ እና መንግስት ምንጊዜም ቢሆን መልካም ነገር ቢሰራም በምንም ዓይነት መንገድ ፈጽሞ ዕውቅና እንደማልሰጥ በማድረግ ትችታቸውን አቅርበዋል፡፡

11ኛ) እኔ ባቀረብኩት ትችት ላይ ሁሉንም የጥላቻ አራጋቢዎች ማቅረብ እንደነበረብኝ እና አንድን የጥላቻ አራጋቢ ቡድን ብቻ ነጥየ በማቅረብ ማስተናገድ መሞከሬ ፍትሀዊ እንዳልሆነ አድርገው ጽፈዋል፡፡

12ኛ) የጥላቻን ርዕሰ ጉዳይ በሕዝብ ፊት ለውይይት በአደባባይ ማውጣቴ ታላቅ ድፍረት መሆኑን ምክንያቱም ይህ ርዕሰ ጉዳይ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን በእርግጠኝነት በግል እንኳ ለመናገር የሚሸሹት እንደሆነ ትችታቸውን አቅርበዋል፡፡

13ኛ) ይህንን የዘረኝነት ቅስቀሳ ጉዳይ ለሕዝብ በአደባባይ ማቅረቤ ትክክለኛ ሰው መሆኔን ጠቅሰዋል ምክንያቱም ይላሉ አቅራቢው ከብዙ ጊዜ ጀምሮ እኔ የሞራል ስብዕና መሪ እንደሆንኩ በመግለጽ በዚህ እንድቀጥልበት ጠቁመዋል፡፡

14ኛ) ሌሎቹ ደግሞ እኔ ባቀረብኩት ትችት በጣም እንደተበረታቱ እና ሌሎችንም እንደዚህ ያሉ አይነኬ ጉዳዮችን/taboos እየፈለፈልኩ በማውጣት ለሕዝብ ለአደባባይ እንዳቀርብ ያላቸውን ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡

15ኛ) እንደዚሁም ሁሉ ብዙውን ጊዜ በተረሱ ጎጂ እና ባረጁ ልማዶች፣ ወዘተ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እንደዚህ ያለ ትችት ማቅረብ እንዳለብኝ ሀሳባቸውን ያቀረቡም አሉ፡፡

የእኔን ትችቶች የሚያነቡ ሰዎች ከእራሳቸው አጀንዳዎች፣ አመለካከቶች፣ ምርጫዎች  እና ሀሳቦች ጋር በማዛመድ እንደሚተረጉሟቸው ጥርጥር የለኝም፡፡ ያ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው፣ እናም በሕዝብ የአደባባይ የክርክር ጭብጦች እና ውይይቶች ላይ ሊቀርቡ እንደሚችሉ የሚጠበቅ ነው፡፡

ከላይ ለቀረቡት በርካታ ነጥቦች በሙሉ የእኔ አጭር መልስ የእኔ ትችት ስለጥላቻ እንጅ ጥላቻን ስለሚያራግቡ የጥላቻ አራማጆች ጉዳይ አይደለም የሚል ነው፡፡ የእኔ እምነት ሞሀንዳስ ጋንዲ እንዳሉት “ሀጢያትን እራሱን ጥላ እንጂ ሀጢያተኛውን እራሱን አይደለም“ በማለት ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡

ሰዎች በአጠቃላይ ስለጥላቻ የአስፈሪነት ኃይል ዕውቅና ለመስጠት መፍራቱን ማስወገድ ይኖርባቸዋል፡፡

ጥላቻ በዓለም ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉልበት ያለው አውዳሚ ኃይል እንደሆነ በሰው ልጆች ላይ ግንዛቤ የተወሰደበት ጉዳይ ነው፡፡

ሆኖም ግን ጥላቻ በሁላችንም ልቦች ውስጥ ይኖራል፡፡ ይህንን ልንክድ እንችላለን፣ ጥላቻ አንደሌለ ለመስመሰል አንሞክራለን፡፡ ሆኖም ግን በአልጋችን ላይ ስንጋደም በጨለማ የበቀል ቋንቋ ለበርካታ ጊዚያት በጆሯችን ላይ ያንሾካሹካል፡፡

ጥላቻን በሚመለከት ማንም ከጥርጣሬ በላይ አይደለም፡፡ ማንም ሰው ወይም ደግሞ ሕዝብ በጥላቻ ላይ የጠቅላይነት ይዞታ የለውም፡፡

የአማራ፣ ኦሮሞ፣ የጉራጌ…የአሜሪካ፣ የሩሲያ፣ የቻይና…የጥላቻ አራማጆች ይኖራሉ፡፡

ጥላቻ የሚጀምረው “በእራሳችን እና በእነርሱ አእምሮ” ውስጥ ነው፡፡

ጥላቻን እራሱን እጠላለሁ እንጅ የግዴታ የጥላቻ አራማጆችን እጠላለሁ ማለት አይደለም፡፡ ለጥላቻ አራጋቢዎች እውነታውን እስከ አፍንጫቸው ድረስ እናገራለሁ እንጅ በምንም ዓይነት መልኩ እነርሱን አልጠላም፡፡

የተሰበከው የዘር ጥላቻ በድምጽ እና በምስል ተደግፎ እውነተኛ የሆነ እና መቶ በመቶ ተጨባጭነት ያለውን የዘር ቅስቀሳ በዓለም ላይ ያሉ ወገኖቼ ሁሉ እንዲሰሙት እና የእራሳቸውን ትዝብት በመውሰድ ላለመሞት እና ከእልቂት እንዲተርፉ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳሰብሁ እንጅ ቃሪያ አምባቃሪያ፣ ጨው ጭረጨው ወይም ደግሞ አቁማዳ ቀልቀሎ አላልኩም፡፡

ታዲያ እውነቱ መነገሩ፣ አካፋው አካፋ እንጅ አዷማ መባል የለበትም መባሉ ነውርነቱ ከምን ላይ ነው? ደግሞስ እኛ በይሉኝታ እና በኋላቀር አድርባይ ጎታች ባህል ተጠፍንገን እውነትን ላለመናገር ተሸብበን የምንኖረው ለምን ያህል ጊዜ ነው? የተባለውን እንዳለ ማቅረብም የዘረኝነት ቅስቀሳ ሳይሆን የዘረኝነት ቅስቀሳ እያደረገ ያለውን ሰው ማንነት እና የአስተሳሰብ ዝቅጠት በሕዝብ አደባባይ ማጋለጥ እና እንደ ነፋስ እንዲቀል ማድረግ እንጅ ሌላ ሊሆን ከቶ አይችልም፡፡ ስለዚህ የዘር ቀስቃሹ “…ጎጃሜው (የአማራ ሕዝብ) they are called retards, retards (ደነዞች) ነው የሚባሉት፡፡ ጎንደሬው (ሌላው የአማራ ሕዝብ) ጠላት ነው ሊሸለሙ አይገባቸውም፣(ደነዞች) retards ናቸው በአስተሳሰብ፣ በጭንቅላት በጣም ዝቅ ያሉ ዝቅተኞች retards ናቸው…” እያለ በአደባባይ የዘር ቅስቀሳ ያደረገው ሳያፍር የተናገረውን እንደወረደ ሀቁን ማቅረብ የዘረኛውን ሰው ሀሳብ እንዳለ የመደገፍ አባዜ ካልተጠናወተ በስተቀር ነውርነቱ ከምን ላይ ነው?

ለዚህ ያዋሉትን ጊዜ እና ጉልበት ዘረኝነትን ለሚሰብከው ሰው በመገሰጽ ለነብሱ ንስሀ እንዲገባ ለተዘለፈው ለብዙሀኑ ሕዝብ ክብር ሲባል ደግሞ በአደባባ ይቅርታ እንዲጠይቅ ቢመክሩት ምንኛ የምሉዕ አስተሳሰብ ባለቤት በሆኑ! ነው ወይስ ደግሞ የዘር ቅስቀሳውን ማድረግ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ቀኖናዊ መርህ ይፈቅዳልና ተዋቸው እዳሻቸው ሕዝብን እየዘለፉ፣ ሀብቱን እየዘረፉ ይኑሩ ነው የሚሉት? አካፋ አሁንም አካፋ መባል እንጅ ማጭድ ወይም ሌላ መባል የለበትም፡፡ ይህ የእኔ መርህ ነው! የምንግባባ ይመስለኛል፡፡

“ሰው ለሰው ተኩላ ነው (Homo homini lupus est” የሚለውን የሰውን ልጅ ታሪክ አውቃለሁ፡፡ እኔ ግን ጥላቻ ነው የሰውን  ልጅ ተኩላ የሚያደርገው እላለሁ፡፡

ዶናልድ ትራምፕ በዕጩ ፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ቅስቀሳው በየመድረኩ ላይ በመሰየም በአሜሪካ ሀገር የጥላቻን ወንጌል በመስበክ ላይ ይገኛል፡፡

ሆኖም ግን እውነተኛው ወንጌል የሚያስተምረን እንዲህ የሚል ነው፣ “የሰው ልጅ ልቦች በበለጠ መልኩ በሰይጣናዊነቶች የተሞሉ ናቸው፣ እናም እየኖሩ ባሉ ሰዎች ልቦች ውስጥ  እብደት አለ፡፡“ 

በእኔ የኃይማኖት ልማድ ከሁሉም ሰይጣናዊነቶች በላይ የሆነ እና ማቋረጫ በሌለው መንገድ መልካም የሆነ አንድ ሰው ብቻ አለ፡፡

ሆኖም ግን “በሰው ልጆች ልቦች ውስጥ ተደብቆ የሚኖረውን ሰይጣናዊነት የሚያውቀው ማን ነው?” 

እኔ እንደማስበው ከሆነ በእኔ ላይ የቀረቡት በርካታዎቹ የትችት ግብረ መልሶች እና ስሜቶች አስበውበትም ይሁን ሳያስቡት ሁሉም አንድ ነገር ይጋራሉ፡ የጽሁፍ ምርመራ/ሳንሱር (censorship)፡፡

ለእኔ እንደሚመስለኝ የግብረ መልሶቹ ዋና ዳህራ ስለጥላቻ እና የጥላቻ አራጋቢዎች ርዕሰ ጉዳይ መጻፍ እንዳልነበረብኝ ነው አጽንኦ በመስጠት የቀረቡት፡፡ በሌላኛው አማራጭ የህብረተሰቡን ይፋዊ ያልሆነ የዝምታ የድባብ አባዜ (የኢትዮጵያ የማፊያ ወንጀለኞች ዝምታ) የመከተል እና የጥላቻ ንግግር የለም ቢኖርም እንኳ ሊኖር የሚችለው በጋነም ውስጥ ብቻ በዝቅተኞቹ ውስጥ እንጅ በነባራዊ ዓለም ውስጥ በፍጹም የለም እያልኩ የማስመሰል እርባና ቢስ ንግግር እንዳቀርብ ነው የተፈለገው፡፡

በሌላ አባባል እራሴን በእራሴ ላይ የጽሁፍ ምርመራ ገደብ/ሳንሱር  (censorship) እንዳስቀምጥ እና ትችት በዚህ መልክ መጻፍ እንደሌለብኝ፣ ወይም ደግሞ ዓለም አቀፍ ጦማሪዎች የሚገናኙበት ድረገጽ እና ማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች በገፍ የሚያሰራጩትን የእኔን ትችቶች ማረም/ ሳንሱር (censor) ማድረግ እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ ነው፡፡

የጥላቻ ንግግር ሊወገድ ወይም ደግሞ ሊጠፋ አይችልም፣ በዝምታ፣ ወይም ደግሞ በንቀት እና በምንግዴለሽነት፡፡ የጥላቻ ንግግር እንደ እንጉዳይ በጨለማ ውስጥ ይፈላል፡፡ ሆኖም ግን በብርሀን ወሳኝ ትንታኔ እና እውቀት ህልውና እርባና ቢስነቱ ይታያል፡፡

የጽሁፍ ምርመራ/ሳንሱር ለእኔ ጥልቅ ተቃውሞ የማሳይበት እውነታ ነው፡፡

ጥንታዊ የግሪክ ምክር ቤት አባላትን በሚመለከት ጆን ሚልተን በጣም ህይወትን በሚያነሳሳ መልኩ አቅርቦት በነበረው የመናገር ነጻነት እና ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት የፍልስፍና መርሆዎች ላይ ተጥሎ የነበረው የጽሁፍ ምርመራ/ሳንሱር ንግግር ለኔ አስተሳሰብ መሰረታዊ ነው፡፡

የጥላቻ አራጋቢዎች ጥላቻቸውን መግለጽ እንዲችሉ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ እና በሕዝባዊ ውይይቶች ሁሉ የመከላከል የእራሴ ድርሻየን ባለፉት አመታት ተዋጥቼአለሁ፡፡

የዩኤስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍትህ አካላት በወጣት አፍሪካ አሜሪካውያን ላይ ለሚያሰራጯቸው የጥላቻ መልዕክቶች፣ ዕጩ ፕሬዚዳንቶች በምርጫ ዘመቻቸው በግትራዊነት አቋም አንድ የተለየ እምነት ያለው ህብረተሰብ ወደ እነርሱ ሀገር እንዳይገባ እገዳ ለሚጥሉት ወይም ደግሞ ተኩሰው ለሚገድሉ እና በኋላ ጥያቄ ለሚያቀርቡ (ምክንያቱም የጥቁሮች ህይወት ጉዳያቸው ስላልሆነ) ታማኝ ላልሆኑ የፖሊስ ኃላፊዎችም ቢሆን እውነታውን እስከ አፍንጫቸው ድረስ እናገራለሁ፡፡

የእምነት ተቋማት ምክር ቤት እየተበላ በሚጠራው እና በኢትዮጵያ ውስጥ የኃይማኖት ጽንፈኝነት ጥላቻን ለመዋጋት ለተመሰረተው ድርጀት በተለያዩ አጋጣሚዎች የእራሴን ሀሳብ ሳቀርብ ቆይቻለሁ፡፡

አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ በ2010 በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በመገኘት የመናገር መብት እንዳለው ሽንጤን ገትሬ እና ፍቅርን በተላበሰ መልኩ ስከራከርለት እንደነበር በርካታዎቹ አንባቢዎቼ እንግዶች አይደሉም፡፡ (“ሚስተር ዜናዊ ኮሌጅ ሄደ!” የሚለውን ትችቴን መመልከት ይችላሉ፡፡

አምባገነኑ መለስ በኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች የስልታዊ ጥላቻ አራጋቢ ዋና መሀንዲስ በመባል ይታወቃል፡፡ የእራሱን ስልጣን ለማጠናከር በሚል እኩይ ዓላማ የጎሳ ክፍፍል እና ጥላቻን በመፍጠሩ ምክንያት ከግብረ አበሮቹ፣ ከመሰሎቹ እና ከታማኝ ሎሌዎቹ ችሮታ ተሰጥቶታል፡፡

በኮሎምቢያ የዓለም መሪዎች መድረክ/World Leaders Forum ላይ አምባገነኑ መለስ አቅርቦት በነበረው ንግግር ላይ ዲያስፖራ ኢትዮ-አሜሪካውያን ምንም ዓይነት ልዩነት የሌለው በሚመስል መልኩ ሁሉም ተቃውሞ አቅርበውበት ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ታዋቂ የሆኑ ጋዜጠኞችም ግፊት ነበረበት፡፡

የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ለሆኑት ለሊ ቦሊንገር መለስ ለጉባኤው መጋበዝ እንደሌለበት የሚጠይቅ ጠንካራ እና አነቃቂ የሆነ ደብዳቤ ጽፈው ለነበሩት የእኔ ጀግና እስክንድር ነጋ እና ሰርካለም ፋሲል ለእኔ ልብን የሚነካ የሀሳብ መለያየት የነበረበት ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ አንድ ሰው ከሚወዳቸው እና ከሚያደንቃቸው አጠቃላይ ከሆኑ ጀግኖች እና ጅግኒቶች ይልቅ መርህን ከሰዎች በላይ አድርጎ ማስቀመጥ መቻል በጣም ቆጥቋጭ እና ከመግለጽ በላይ አስቸጋሪና መንፈስ የምበጠብጥ  ነገር ነው፡፡

እዚህ ላይ እንዲህ የሚሉትን የፕሮፌሰር ቾምስኪን ምክሮች መጥቀስ አስፈላጊ ነው፣ “የምንንቃቸው ሕዝቦች ሀሳቦቻቸውን በነጻነት በመግለጽ መብቶቻቸው ላይ የማናምን ከሆነ በነጻነት በእራሱ ላይ እምነት የለንም፡፡“ ስልታዊ የጥላቻ አራጋቢ መሀንዲሱ አምባገነኑ መለስ እንኳ ሀሳቡን የመግለጽ መብት አለው ነበር ያልኩት፡፡

እንደ ተማሪ እና እንደ የአሜሪካ የሕገ መንግስት ባለሙያ በጽሁፍ ምርመራ ላይ ያሉኝ ሀሳቦች እንዲህ በሚሉት በዩኤስ ተባባሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ በፖተር ስቴዋርት በሚገባ ተቀምረው ተቀምጠዋል፡

የጽህፍ ምርመራ/ ሳንሱር ህብረተሰቡ በእራሱ ላይ ምንም ዓይነት እምነት የሌለው መሆኑን ያንጸባርቃል፡፡ የጸሁፍ ምርመራ የኃይል አገዛዝን የሚጠቀም አገዛዝ መለያ ዋና ባህሪ ነው፡፡ ከብዙ ገዜ በፊት የእኛን የመጀመሪያውን ማሻሻያ/First Amendment የጻፉት ሰዎች የተለየ ነገር ግልጽ አድርገዋል፡፡ አንድ ማህበረሰብ ጠንካራ ለመሆን የሚችለው እውነተኛ ነጻነት ሲኖረው ብቻ ነው በማለት አምነዋል፡፡ በዚህ ዓይነት የገለጻ አድማሳቸው ብሩህ ሆኖ በሚታያቸው የማህበረሰብ ምርጫ ላይ ከፖሊስ መጥፎ ጣልቃገብነት ወይም ደግሞ ከዳኛ ጠንካራ እጅ ነጻ መሆን  ላይ እምነታቸውን ለተሻለ ወይም ደግሞ ለመጥፎ ነገር አስቀምጠዋል፡፡ ስለሆነም የሚጎረብጠውን፣ ለስላሳ እና ብልግና ያለበትን መግለጫ በማረቅ ከምንም በላይ በታማኝነት የሚከላከለው ሕገ መንግስት ነው፡፡ ለእኔ ምንም ዓይነት ዋጋ የሌለው ነው በማለት የገመትኩት መጽሀፍ ለጎረቤቴ ዋጋ ያለው አንድ ነገር ማስተላለፍ ይችላል፡፡ እራሳቸችንን የሰዋንለት ሕገ መንግስት ነጻ ማህበረሰብ እያንዳንዱ ለእራሱ [ለእራሷ] ለመምረጥ የሚያስችል ሰነድ ነው  (በጊዘንበርግ ቪ. ዩናይትድ ስቴትስ፣ 383 U.S 463 (1966)፣ አጽንኦ ተጨምሯል፡፡

ባለፉት አስር ዓመታት መደበኛ አንባቢዎቼ “በስልጣን ላይ ላሉት” እንዲሁም ለስልጣን ረሀብተኞች፣ ለስልጣን ጥመኞች፣ ስልጣናቸውን ከሕግ አግባብ ውጭ ስልጣን ለሚጠቀሙ፣ ስልጣናቸውን በተሳሳተ መንገድ ለሚጠቀሙ እና ምንም ዓይነት ስልጣን ለሌላቸው ስልጣን የለሾች እውነት መናገር የሚለውን ዓላማዬን ለእራሴ የመረጥኩ መሆኔን ያውቃሉ፡፡

በስልጣን ላይ ላሉት እውነቱን እናገራለሁ ምክንያቱም እንዲህ በሚለው የመጽሀፍ ቅዱስ ቃል አምናለሁና፣ “እውነት ነጻ ያወጣሀል፡፡“

እውነት በመናገር ተልዕኮዬ ተነሳሽነቱን የወሰድኩት ከፕሮፌሰር ኤድዋርድ ሰይድ እና ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ከሁለቱም አቻ ከሌላቸው አንጋፋ ልሂቃን ነው፡፡

ፕሮፌሰር ሰይድ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሕዝቦችን ነጻነት እና እውቀትን በማራመድ ምሁራን እንዲህ የሚለውን ተልዕኳቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፣ “በስልጣን ላይ ላሉት እውነቱን በመናገር፣ በአምባገነኖች እብሪተኝነት በሚደርሰው ስቃይ እና መከራ ለሕዝቡ ምስክር ሆነው በመቅረብ እና ከባለስልጣኖች ጋር በሚኖር ግጭት የሰላማዊ አማጺያንን ድምጽ ሆነው መቅረብ ይኖርባቸዋል“ ብለዋል፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ካለፈው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ጀምረው እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ላሉት አምባገነኖች ሁሉ እውነቱን በመናገር ላይ ይገኛሉ፡፡ (እ.ኤ.አ ሕዳር 2015 በፕሮፌሰር መስፍን “አዳፍኔ”: “ኢትዮጵያውያንን ከኢትዮጵያውያን መጠበቅ” በሚል ርዕስ ያቀረብኩትን ትችት ይመልከቱ፡፡)

እ.ኤ.አ በ2007 ተካሄደ የተባለውን የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ ተከትሎ ተፈጥሮ በነበረው ውዝግብ የተካሄደውን የወገኖቻችንን እልቂት በመመልከት ወደ ሰብአዊ መብት ጥበቃ ዘው ብዬ በመግባት በግፈኛው እና በአምባገነኑ መለስ የግል ትዕዛዝ በቅጥር ነብሰ ገዳዮች ያለቁትን ባለብሩህ ተስፋ ወገኖቻችንን እልቂት፣ አካለጎደሎነትን እና እስራትን ይፋ በማድረግ እና በማውገዝ ምስክርነት በመስጠት የሰብአዊ መብት ጥበቃ ተልዕኮዬን ማራመድ ጀመርኩ፡፡

በዚያን ወቅት ገና በመጀመሪያው ጊዜ አሁን በህይወት የሌለው አረመኔው እና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ የእርሱን የደህንነት እና ወታደራዊ ኃይሎች በማሰማራት ምንም ዓይነት መሳሪያ ያልታጠቁትን እና የምርጫውን መዘርፍ እና መጭበርበር ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ለኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ለማሳወቅ ሰልፍ በመውጣታቸው ብቻ በአምባገነኑ የግል ትእዛዝ በጅምላ እንዲጨፈጨፉ በማድረግ እራሱን የማይነካ ጠንካራ እንደሆነ አድርጎ በማቅረብ እርሱም ሆነ ተንቀሳቃሽ ዕቃ ገዳይ ሎሌዎቹ በሕግ ሳይጠየቁ የመቀመጣቸው ሁኔታ የእግር እሳት ሆኖ ያበሳጨኝ እና ያንገበግበኝ ነበር፡፡ ንዴቴ ትንሽ በረድ ካለልኝ በኋላ እንዲህ የሚል ጥያቄ ማንሳት ጀመርኩ፡ ምን ዓይነት ሰብአዊ ፍጡር ነው ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ባልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች ላይ እንዲህ ዓይነት ዕልቂት እንዲፈጸም ያዘዘው?

የተለመዱት እና ማህበረሰቡ የሚቀበላቸው መልሶች ለእኔ አርኪ ሆነው አልተገኙም፡፡ በእርግጥ አምባገነኖች በስልጣን እርካብ ላይ እንደ መዥገር ተቆናጥጠው ለዘላለም ለመኖር በቁጥጥራቸው ስር ያለውን ማንኛውንም ነገር ይጠቀማሉ፡፡ አምባገነኖች በስልጣናቸው ላይ ተጣብቀው ለመቆየት ሲሉ ሰላማዊ ዜጎችን ይገድላሉ፣ ይዘርፋሉ፣ ያጭበረብራሉ፣ ይደበድባሉ፡፡

በመለስ እና በዘ-ህወሀት የቀረበው የተለመደው የአምባገነኖች ምላሽ እውነት ሆኖ ሰውን ሊያሳምን የሚችል አልነበረም፡፡

ወደ ህወሀት ነገረ ታሪክ ጠለቅ ብዬ ስገባ የፕሮግራም ሰነዳቸውን/ማኒፌስቷቸውን በማጥናት እና የህወሀት የቀድሞ አባላት የህወሀትን ሚስጥር ሲያጋልጡ የኦዲዮ ቪዲዮ ምስል በመመልከት እና በማዳመጥ እንዲሁም በህወሀት የቀድሞ መሪዎች የሚቀርበውን ምሁራዊ ትንታኔ ሳነብ  መለስ እና የእርሱ ድርጅት ለፖለቲካ ስልጣን ሲሉ በጥላቻ የሚመሩ የሰይጣን ፈረሶች መሆናቸው ፍንትው ብሎ ታየኝ፡፡

ገና ከመጀመሪያው ጀምሮ አምባገነኑ መለስ እና ዘ-ህወሀት እነርሱ ከሚለው ይልቅ እኛ በሚል  ቡድናዊ የከባቢ አየር ምህዳር ውስጥ ተዘፍቀው መታየታቸው ግልጽ እየሆነ መጣ፡፡ ጥላቻ በአምባገነኑ መለስ እና በግብረ አበር ጓደኞቹ የደም ስር ውስጥ ተዋህዶ ይገኛል፡፡

መለስ እና ዘ-ህወሀት የጥላቻን ኃይል ተገንዝበውታል፣ እናም የበለጠ የፖለቲካ ስልጣንን ለመቆጣጠር በዘዴነት ተጠቅመውበታል፡፡

ቀላል በሆነ የተመሳስሎ አገላለጽ ጥላቻ ከበሰበሰ ስጋ የትል መንጋ እንደሚገነፍል ሁሉ በተመሳሳዬ መልኩ ጥላቻም ከመለስ አፍ ይገነፍላል፡፡

በአንድ ወቅት አምባገነኑ መለስ ታላቅ ከበሬታ የነበራቸውን እና ታዋቂ የሆኑ ኢትዮጵያዊ ስሜት ያራምዱ የነበሩትን እና አሁን በህይወት የሌሉትን ለእኔ ምርጥ ጓደኛ ለፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር፡ “ትግራውያን አክሱም አላቸው፣ ያ ግን ለጉራጌዎች ምናቸው ነው? አገዎች ላሊበላ አላቸው፣ ያ ግን ለኦሮሞዎች ምናቸው ነው? ለጎንደሬዎች ቤተመንግስት አላቸው፣ ያ ግን ለወላይታዎች ምናቸው ነው?“ ለመሆኑ እንደዚህ ያሉ ጥያቄዎች ትርጉም እና አባባል ምን ማለት ነው?

አምባገነኑ መለስ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ “ቁራጭ ጨርቅ” ከመሆን የዘለለ ነገር የለውም እንዲሁም “ኢትዮጵያ የ100 ዓመታት ታሪክ ብቻ ያላት ሀገር ናት፣ ከዚህ ውጭ ሌላ ሀሳብ የሚያራምዱ ካሉ እራሳቸውን በታሪክ ሳይሆን በትረካ ላይ የዶሉ ናቸው” ብሎ ነበር፡፡

አምባገነኑ መለስ ቀደም ሲል ያምን እንደነበረው እና በአሁኑ ጊዜም የእርሱ ተከታይ ግብረአበሮቹ እንደሚያምነት ኢትዮጵያ የሚባል ነገር የለም፡፡ ያለው በአንድ ሀሳባዊ በሆነ ምድር ላይ የተመሰረቱ የብሄሮች ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች ስብስብ ብቻ ነው በማለት ምንም ዓይነት አመክንዮ ከሌለው እና ከአስፈሪው ከስታሊን ጽሁፍ ቀምተው ያቀርባሉ፡፡ (እ.ኤ.አ ግንቦት 2016 “ኢትዮጵያ አዲስ ሕገ መንግስት ትፈልጋለችን?” በሚል ርዕስ አቅርቤው የነበረውን ትችት ይመልከቱ፡፡)

መለስ እና ዘ-ህወሀት በውል መገንዘብ ያልቻሉት ነገር ቢኖር ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያ የምትባል እውነተኛ ሀገር መኖሯን ወደ ኋላ መለስ ብለው ታሪክን ያለማወቃቸው ጉዳይ ነው፡፡ (እ.ኤ.አ ሕዳር 2014 “ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ማጥፋት” በሚል ርዕስ አቅርቤው የነበረውን ትችት ይመልከቱ፡፡)

ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአክሱም፣ በላሊበላ፣ በሉሲ (ድነቅነሽ)፣ በሐረር ጀጎል፣ (በዩኔስኮ 4ኛው የእስልምና ቅዱስ ከተማ ተብሎ የተሰየመው)፣ በገዳ እና በጉሚ አስተዳደር ስርዓት እና በሌሎቸ በርካታ ነገሮች ላይ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሞራል እና ሕጋዊ መብቶች እንዳሏቸው መጠየቅ ይችላሉ፡፡

ዘ-ህወሀት ከሚያራምደው ጥላቻ እና የወንጀል ድርጊቶች እራሱን ነጻ ለማድረግ በሌሎች ሕዝቦች ጥላቻ የተፈጠሩ ድርጊቶች አስመስሎ በሀሰት በተቀነባበረ በእራሱ የሸፍጥ ስራ ነገር ይለኩስ እና እራሱ ያለበትን ወቅታዊ ትኩሳት ሁልጊዜ ወደ ሌላ አቅጣጫ የማስቀየስ የማጭበርበር ርኩስ ስነምግበር አለው፡፡ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጽሟቸውን ወንጀሎች ለመደበቅ ሲሉ ታሪክን አዛብተው እና አወናብደው ለመጻፍ ሙከራ ያደርጋሉ፡፡ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የሴቶች ጡቶች የሚቆርጡ ጨካኝ ንጉስ እንደነበሩ ለማስመሰል እና በኦሮሞዎች እና በአማራዎች መካከል ዘላለማዊ የሆነ ጥላቻ እንዲኖር ሚሊዮኖችን ብር የፈጀ ሀውልት አቁመዋል፡፡

የጭካኔ ጉዳይ በሚነሳበት ጊዜ ከአረመኔው መለስ ዜናዊ እና ከእርሱ ዘ-ህወሀት የበለጠ ጨካኝ እና አረመኔ በምድር ላይ ይኖራልን?

እ.ኤ.አ በ2005 ተካሄደ የተባለውን የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ ውዝግብ ተክትሎ ወያኔ ፈጽሞት በነበረው እልቂት መነሻነት በመለስ በእራሱ በተቋቋመው የምርመራ ኮሚሽን የማጣራት የዘገባ ውጤት መሰረት ሆን ተብሎ ታስቦበት እና ተመክሮበት ቢያንስ 193 ምንም ዓይነት መሳሪያ ያልታጠቁ ንጹሀን አማጺዎች እንደተገደሉ፣ ሌሎች 763 ዜጎች ደግሞ የከባድ ቁስለኛ ጉዳት ሰለባ እንደሆኑ በመግለጽ ሙሉ ጥፋቱን በዘ-ህወሀት ላይ ደፍድፏል፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እ.ኤ.አ ሰኔ 2016 ባወጣው ዘገባው በኦሮሚያ ምንም ዓይነት መሳሪያ ባልታጠቁ 400 ንጹሀን ዜጎች ላይ ለተፈጸመው እልቂት ኃላፊነቱን ሙሉ በሙሉ በአገዛዙ ላይ ደፍድፏል፡፡ እንደዚህ ባለው ጭካኔ በተሞላበት የኃይል ጥቃት አረመኔው መለስ እ.ኤ.አ በ2004 በኢትዮጵያ በጋምቤላ በ400 ምንም ዓይነት መሳሪያ ባልታጠቁ ሰላማዊ የሲቪል ዜጎች ላይ የጅምላ እልቂት እንዲፈጸም አድርጓል፡፡

ጨካኙ መለስ በግል ባቀናበረው ትዕዛዙ የኦጋዴን መንደሮች በቦምብ እንዲጋዩ አድርጓል፡፡ በተባበሩት መንግስታት የሂዩማን ራይትስ ዎች አድቮኬሲ ዳይሬክተር የሆኑት ስቴቭ ክራውሻው በአረመኔው መለስ እና በዘ-ህወሀት አማካይነት በኦጋዴን የተፈጸሙት ሰብአዊ የእልቂት ወንጀሎች እንደ “ትንሹ ዳርፉር” ሆኖ ሊቆጠር ይችላል በማለት ገልጸውት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

በእርግጥ የዘ-ህወሀት የጎሳ ጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ሙሉ በሙሉ በሸፍጥ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

አንድ እና አንድ ዓይነት ብቻ የጎሳ ዝርያ ብቻ ነው ያለው በማለት ሀሳብ የሚያቀርቡ ኢትዮጵያውያን/ት ካሉ ከእነርሱ ጋር ፊት ለፊት ለመሞገት ዝግጁ ነኝ፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የዲኤንኤ የዘረ መል ምርመራ እንዲያደርግ የናሙና ጥናት ቢደረግ በኢትዮጵያ ውስጥ ከእያንዳንዱ የጎሳ ቡድን የዘረ መል አመላካቾችን ብቻ አይደለም የሚያገኙት ሆኖም ግን በሚያስደንቅ ሁኔታ በዓለም ላይ በየትም ቦታ ቢሆን የዘር አመላካች ሊገኝ ይችላል፡፡

በአሁኑ ጊዜ አንድ ሰው እውነታውን ለመረዳት ዝግጁ ከሆነ በትንሽ እና በ99 ዶላር ክፍያ ብቻ የአንድን ሰው የዘር ታሪክ አመጣጥ ለማወቅ ይችላል፡፡

“ንጹህ” ከየትም ያልተቀላቀለ የሆነ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትገሬ፣ ወዘተ የሚባል ነገር በፍጹም ሊኖር አይችልም፡፡ የለም!

ከብዙ ጊዜ ጀምሬ የእኛ እናት ሀገር የሆነች ኢትዮጵያ እየተባለች የምትጠራ ጥንታዊ ሀገር እንዳለች ስሰብክ ኖሪያለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ክልል/ማጎሪያ በረት እየተባለች እንደ ገና ዳቦ ልትቆራረስ፣ በጎሳ ፌዴራሊዝም ከአለት ላይ እንደወደቀ ብርጭቆ ልትበታተን አትችልም፣ ወይም ደግሞ ለአየር ባየር ጭልፊት ኢንቨስተሮች ልትሸጥ ወይም ደግሞ በድብቅ በሚደረግ የወሰን “ስምምነት” ለሌላ ለባዕድ ሀገር ዜጎች ተላልፋ የምትሰጥ ሀገር አይደለችም፡፡

ዘ-ህወሀት ከእነርሱ ይልቅ ለእኛ የማለት አባዜ ድብቅ የሆነው ስልታቸው ነው፡፡

እኛ የሚለው ማለትም የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ መሪዎች፣ አባላት እና ግብረ አበሮች እንዲሁም በወታደራዊ ብቃት አለን በሚል የአጠራር ቃል እራሳቸውን በእራሳቸው የሚያሞካሹት ሰዎች እራሳቸውን “እኛ” ብለው ይጠራሉ፡፡

በሙስና ባህር ውስጥ በመዋኘት ላይ የሚገኙ፣ በሰው ልጆች ላይ ሰብአዊ ወንጀልን የፈጸሙ እና ስልጣናቸውን ከሕግ አግባብ ውጭ የሚጠቀሙ የዘ-ህወሀት ግፈኞች “እኛ” አሉ፡፡

የትግራይ ተራ የሆኑ ዜጎች እና ሌሎችን ተራ ኢትዮጵያውያንን የሚመስሉት ደግሞ ደም በተጠሙት የህወሀት አማጺ ቡድን ወሮበላ ዘራፊዎች በትግል ላይ በነበሩበት ጊዜ ከጊዜ ወደ ጊዜ ስቃያቸውን እና መከራቸውን ያዩ ነበር፡፡

ዘ-ህወሀት የትግራይን ሕዝብ እንደ መጠለያ ምሽግ አድርጎ ይጠቀምበት ነበር፡፡

ሆኖም ግን ተራው የትግራይ ሕዝብ ዘ-ህወሀት ለእራሱ የወንጀል ድርጊቶች በስማቸው ይጠቀም ነበር የሚል ሀሳብ ሊኖራቸው ይችላልን? የትግራይ ተራ ሕዝቦች በነጻ፣ በፈቃደኝነት እና ያለምንም ጫና በእራሳቸው ፍላጎት ዘ-ህወሀትን ይደግፋሉን?

እነዚህን ጥየቄዎች ለመመለስ ማስረጃ መመርመር አለብን፡፡

ያ ማስረጃ ከሌላ ከየትም ሳይሆን የዘ-ህወሀት ነባር መስራች እና የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ከነበረው ከስዬ አብረሃ ይመጣል፡፡

እ.ኤ.አ በ2010 ተደርጎ በነበረው የፓርላማ የማሟያ ምርጫ ተብዬ ወቅት (ስዬ በትግራይ በተወዳደረበት ጊዜ) ስዬ የዘ-ህወሀት የፖሊስ መንስት እያንዳንዱን የትግራይን ተራ ሕዝብ የህይወት እንቅስቃሴ ሳይቀር ሁሉንም ነገር ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ አጋልጦ ነበር፡፡ የትግራይ ሕዝብ ዘ-ህወሀትን እንዲደግፍ ያደርግበት የነበረውን ስቃይ እና መከራ በማስረጃ አስደግፎ አቅርቦ ነበር፡፡

ስዬ ዘ-ህወሀት እንዴት አድርጎ የመንግስትን ሀብት፣ ተቋማትን፣ ጓዳዊ አሰራርን፣ የአድልኦ አሰራርን፣ ጉቦ መስጠትን እና በሙስና መዘፈቅን በመጠቀም ተራውን የትግራይ ሕዝብ በኃይል በማስገደድ ደጋፊ እንዲሆን በማድረግ እና ዘ-ህወሀት የእርሱን የፓርቲ መስመር የማይከተሉትን ወይም ደግሞ በግልጽ የሚቃወሙትን እንዴት አድርጎ እንደሚቀጣ በግልጽ አሳይቶ ነበር፡፡

ስዬ እንዲህ የሚል የክርክር ጭብጥ አቅርቦ ነበር፣ “ለዘ-ህወሀት [በትግራይ ውስጥ]  በፓርቲ የፖለቲካ ሥራ እና በመንግስት ሰራተኛ አገልግሎት መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት የለም፡፡ የፓርቲው ስራ በመንግስት ቢሮ ፋሲሊቲዎች፣ ትራንስፖርት፣ የውሎ አበል፣ ወዘተ አማካይነት ከመንግስት ስራ ጋር ጎን ለጎን አብሮ ይሰራል“ በማለት ሞግቶ ነበር፡፡

ስዬ እንዲህ በማለት ገለጻውን ይፋ አድርጎ ነበር፡

በትግራይ ክልል ዘ-ህወሀት በገጠር አካባቢዎች በጸጥታ ኃይሉ እና በፖለቲካው መዋቅር ላይ ጥብቅ በሆነ መልኩ የተሳሰረ መረብ እንዲኖር በመንደር ደረጃ ሊያገለግሉ የሚችሉ ዋና መሰረቶችን በመጣል ሁለት መዋቅሮችን ፈጥሯል፡ ዋሂኦ እና የልማት ጉጂሌ/Wahio and Development Gujille (DG):: በህወሀት መዋቅራዊ ሰንሰለት ዝቅተኛው ክፍል/unit ዋሂኦ በመባል ይጠራል፡፡ እናም ይህ ክፍል/unit እስከ 20 የሚደርሱ የህወሀትን አባላት ይይዛል፡፡ በአንድ መንድር ውስጥ እንደ መጠኑ ብዛት እስከ 20 ዋሂኦዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በአንድ መንድር ውስጥ ያሉ ዋሂኦዎች ሊቀመንበሮች በተራቸው ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ ቡድን በመሆን ይደራጁ እና የመጀመሪያ ዊዳቤ/Primary Widdabe (PW) በመባል ይጠራሉ፡፡ የእራሳቸውን ሊቀመንበሮች እራሳቸው ይመርጡ እና በመንደር ደረጃ የሚካሄዱትን ሁሉንም የመንግስት እና የፓርቲ እንቅስቃሴዎች ይቆጣጠራሉ፡፡ 

ህወሀት በእያንዳንዱ መንደር በእያንዳንዱ ሰው ላይ እኔን ከመሳሰሉት ሰዎች አካሄድ ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎ በሚጠራጠራቸው ሰዎች ላይ ጥናት ያደርጋል፡፡ ከደርግ አገዛዝ ጋር በትጥቅ ትግሉ ተሳትፎ የነበራቸው በርካታ ነባር የህወሀት ታጋይ አባላት አሉ፡፡ ሆኖም ግን ፓርቲው በተሰነጠቀበት ወቅት ከእኔ እና ከሌሎች ከእኔ መሰል ሰዎች ጋር ወገንተኝነት ይኖራቸዋል በሚል ምክንያት ከጥርጣሬ ውስጥ የሚገቡትን ሰዎች ከፓርቲው አባልነት ያስወግዷቸዋል፡፡ ከዚህም በላይ በትጥቅ ትግሉ እና አንድ ብቻ ሳይሆን ሁለት ወይም ሶስት ልጆች የተሰውባቸው ቤተሰቦች ምንም ዓይነት እረዳት የሌላቸው በርካታ ቤተሰቦች አሉ፡፡ የዘ-ህወሀት ካድሬዎች የድምጽ መስጫ የሚስጥር ካርድ የምርጫ ሂደቱን እንዴት አድርገው እንደሚያጭበረብሩበት መረጃዎችን ተቀብያለሁ፡፡ መራጮች/ድምጽ ሰጭዎች ለህወሀት ማን ድምጽ እንደሰጠ እና ማን እንዳልሰጠ የሚያሳዩ ካሜራዎችን ሚስጥራዊ በሆኑ ቦታዎች ላይ አስቀምጧል በማለት በህወሀት ይነገራቸዋል፡፡“ 

ስዬ እንዲህ በማለት ዘገባውን ደምድሟል፡

እ.ኤ.አ በ2010 ተካሂዶ የነበረው የማሟያ ምርጫ በህወሀት ለህወሀት ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ የተደራጀ እና የተያዘ የውሸት ዴሞክራሲያዊ የማታለያ ምርጫ ነበር፡፡ የምርጫ ቦርዱ ገለልተኛ ሆኖ እንዲታይ ለማስመሰል በማሰብ በህወሀት የቀበሌ እና የወረዳ አስተዳዳሪዎች ከፍተኛ የሆነ ቁጥጥር እና ግምገማ ሲደረግ ይታይ ነበር፡፡ በገጠሩ አካባቢ በሚገኙት ቀበሌዎች እና መንደሮች የሚኖሩት በርካታዎቹ አርሶ አደሮች የህወሀት አባላት እንዲሆኑ ይገደዳሉ፡፡ ማንም ሰው የትም ቢሄድ የሚያገኘው የህወሀትን አባላት ነው፡፡ በተጫባጭ ሁኔታ ሲታይ የህወሀት ጥቅሞች የተባሉ ነገሮች ሁሉ የህወሀት አባል ላልሆነ ለማንም ሰው ሁሉ ዝግ ናቸው፡፡ አባል ያልሆኑ ሰዎች እንደጠላት ይፈረጃሉ፣ እናም ህይወታቸው ወደገሀነምነት ይለወጣል፡፡ ህዝቦችን የሚያስተሳስሯቸው ሰንሰለቶች ሴፍቲ ኔት እና የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ፕሮግራሞች/Safety Net and Emeregency Programs የሚባሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ፕሮግራሞች ሕዝቡ ሙሉ በሙሉ ለገዥው ፓርቲ አጎብዳጅ እንዲሆን በመስራት እና በማጦዝ ተግባራት ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ“ በማለት ነበር ሀሳቡን የደመደመው፡፡ 

በእርግጥ ዘ-ህወሀት የትግራይን ሕዝብ ይወክላልን?

የትግራይ ሕዝብ ነጻ በሆነ መልኩ እና በእራሳቸው ፈቃደኝነት ላይ በመመስረት ብቻ ዘ-ህወሀትን ይደግፋሉን? የትግራይ ሕዝብ የዘ-ህወሀት መደበቂያ ምሽግ ነውን?

ወይም ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ምንም ዓይነት እረዳት እንደሌቸው የዘ-ህወሀት ሰለባ ሆነው እንደሚሰቃዩት እንደ የኦሮሚያ፣ ወይም ደግሞ እንደ አማራ ክልል እና እንደሌሎች ክልሎች ሁሉ ምንም ዓይነት እረዳት የሌለው ነውን?

በዘ-ህወሀት መንግስት የቀድሞ ፕሬዚዳንት በነበሩት  በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የቀረቡትን ማስረጃዎች ደግሞ እስቲ እንመርምራቸው፡፡

ዶ/ር ነጋሶ እ.ኤ.አ መስከረም 2009 በኦሮሚያ ክልል በቀለም ወለጋ ዞን በዶምቢዶሎ ሲካሄድ የነበረውን ልዩ ሁኔታ በመለየት ይገልጻሉ፡፡ ዘ-ህወሀት የመለስን መሪ ዕቅድ የጨዋታ መጽሀፍ በኦሮሚያ እና በትግራይ ውስጥ በአንድ ዓይነት ሁኔታ የተገበረው ለመሆኑ ከዚህ በታች የቀረበው የዶ/ር ነጋሶ ገለጻ ይፋ አድርጓል፡

ፖሊስ፣ የጸጥታ ኃይሉ ቢሮዎች ሰራተኞች በተለያዩ መንገዶች ስለአንድ አባወራ የተለያዩ መረጃዎችን ይሰበስባሉ፡፡ ከእነዚህ መንገዶች አንዱ “ሻኔ” በአሮሞኛ “አምስት” እየተባሉ የሚጠሩትን ድርጅቶች እና መዋቅሮች ያካትታል፡፡ አምስት አባዎራች በአንድ ላይ ሆነው በአምስቱ አባወራዎች ላይ መረጃዎችን በሚሰበስብ በአንድ መሪ ተጠርንፈው/ተጠፍንገው (በአንድ ላይ ተደርገው) ይዋቀራሉ… የደህንነቱ ኃላፊ የሰበሰበውን መረጃ በቀበሌ በከፍተኛ አስተዳደራዊ ደረጃ ላይ ላለው ለእርሱ የበላይ አለቃ ያስተላልፋል፡፡ የቀበሌው አለቃ ደግሞ በተራው ለወረዳው ፖሊስ እና የደህንነት ቢሮ ያሳውቃል፡፡ እያንዳንዱ አባወራ ወደ እራሱ የመጡ እንግዶች እና ጎብኝዎች ካሉ ወዲያውኑ የመጡበትን ምክንያት፣ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆዩ፣ ምን እንዳሉ እና በምን እንቅስቃሴዎች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ዘገባ እንዲያቀርብ ይጠበቃል… ኦህዴድ/ኢህአዴግ የሚመራቸው ማህበራት (የሴቶች፣ የወጣቶች እና የአነስተኛ እና ጥቃቅን የብድር ቡድኖች) እና የፓርቲ ሴሎችን (“እናቶች”፣ “አባቶች” እና “ወጣቶች”) ይመራል፡፡ በትምህርት ቤቶች፣ በጤና፣ እና በኃይማኖት ተቋማት ውስጥ ያሉት የፓርቲ ሴሎችም እንደዚሁ ተመሳሳይ ተግባራትን ያካሂዳሉ…“ ነበር ያሉት፡፡

የአሮሚያ ሕዝብ ነጻ በሆነ መልኩ እና በእራሳቸው ፈቃደኝነት ላይ በመመስረት ብቻ ዘ-ህወሀትን ይደግፋሉን?

ዘ-ህወሀት የመለስን የጨዋታ መጽሀፍ የሆነውን የምርጫ ዘረፋ መሪ ዕቅድ በመጠቀም ህዝቡ በግድ እንዲመርጠው ያስገድዳል ወይስ ደግሞ ሌላ መንገድ ይጠቀማል?

እነዚህን እውነታዎች አጉልተው ሊያሳዩ የሚችሉ ሌሎች ሁለተኛ ደረጃ መረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ጥቂቶች እንሚያቀርቡት የክርክር ጭብጥ ከሆነ አንዳንድ የትግራይ ሕዝቦች ከሌሎች የትግራይ ሕዝቦች በተለየ መልኩ ዘ-ህወሀት በመሰረተ ልማት ፕሮግራሞች፣ በመዋዕለ ንዋይ ፍሰቶች/ኢንቨስትመንቶ እና ከዓለም አቀፍ እርዳታ ከሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ልግስና ተመጣጣኝነት በሌለው ሁኔታ ከሌሎች በተለየ መልኩ ተጠቃሚዎች ናቸው የሚል የክርክር ጭብጥ ይቀርባል፡፡

ይህንን አባባል በመረጃ ለማስደገፍ ምን ተጨባጭነት ያለው ማስረጃ አለ?

እ.ኤ.አ በ2016 በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ተከስተው ከነበሩት ድርቆች ሁሉ በበለጠ ደረጃ በአስከፊ ሁኔታ ከተጠቁት ክልሎች መካከል የትግራይ እና የአፋር ክልሎች ይገኙበታል፡፡

እ.ኤ.አ መጋቢት 2016 እንደቀረበው እንደ ውጭ ጉዳይ ዘገባ “በኢትዮጵያ የሰብል ምርት በሰሜን ትግራይ እና በአፋር ክልሎች ከ50 እከከ 90 በመቶ ባለው መካከል እንደቀነሰ ይፋ ተደርጓል፡፡“

ዘ-ህወሀት የትግራይን እና የአፋርን ክልሎች ለማገዝ ምን ያደረገው ጥረት አለ? የመለመኛ ሳፋዎቹን ይዞ ወደ ዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪ ለልመና ነው የተፈተለከው/ሸመጠጠው፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ያለው ተጨባጭ እውነታ!

በእርግጥ አምባገነኑ መለስ ስልጣንን ከተቆጣጠረ በኋላ እ.ኤ.አ በ1991 ለመጀመሪያ ጊዜ ለቀረበለት ቃለመጠይቅ እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጥቶ ነበር፣ “ኢትዮጵያውያን በቀን ሶስት ጊዜ መመገብ ከቻሉ የእኔ መንግስት ስኬቱ የሚለካው በዚህ ነው“ ነበር ያለው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አምባገነኑ መለስ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2015 የማንንም እርዳታ ሳትጠይቅ በምግብ እህል እራሷን ትችላለች ብሎ ነበር፡፡ የመለስ ቅጥፈት ስንቱ ተዘርዝሮ ያልቃል ዘርፈብዙ ነው!

እ.ኤ.አ በ2008 የትግራይ ዘላቂ የግብርና እና የአካባቢ ተሀድሶ በትግራይ/Sustainable Agriculture and Environmental Rehabilitation እን Tigray (SAERT) በሚል ስያሜ  አነስተኛ ግድቦችን እና የመስኖ ስራዎች ዘዴዎችን ተግባራዊ በማድረግ ትግራይ በምግብ እህል እራሷን ትችላለች በማለት ዘ-ህወሀት እየተኮፈሰ ዲስኩሩን ሲያሰማለት የቆየው ባዶ ዕቅድ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ግን ሁኔታዎች በዚህ ደረጃ ላይ እንዳሉ ዘ-ህወሀት እ.ኤ.አ በ2016 ለትግራይ ሕዝብ የምግብ እህል እርዳታ ለማቅረብ የልመና ሳፋውን ይዞ ብቅ አላለምን? ከዚህ በላይ ውሸት እና ሕዝብን ማደናገር ከቶ ከየት ይገኛል?

እ.ኤ.አ በ2014 በማዕካለዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ እና የዓለም የምግብ ፕሮግራም በቀረበው ዘገባ መሰረት ከፍተኛ የሆነ የምግብ ኃይል እጥረት ያላቸው አባወራዎች የሚገኙት በአዲስ አበባ (50%)፣ በአማራ (49%)፣ በድሬዳዋ (42%) እና በትግራይ  (42%) ሆኖ እንደተመዘገበ ይፋ አድርገዋል፡፡ ከምግብ ድህነት አኳያ ደግሞ ከፍተኛ ተጠቂ ክልሎች ሆነው የተገኙት አማራ (35%) እና ትግራይ (30%) ናቸው፡፡ ዘ-ህወሀት ሕዝቡን በረሀብ አለንጋ፣ በኑሮ ውድነት እና በችጋር እያሰቃየ የሚኮፈስበት አንዳችም ነገር የለውም፣ ምንም! ይኸው ነው በቃ!

እንደ ትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የፕላን እና ገንዘብ ቢሮ ዘገባ ከሆነ በትግራይ ክልል ውስጥ 75 በመቶ የሆነው የገጠሩ ሕዝብ እና 61 በመቶ የሚሆነው የከተማ ኗሪው ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች ኑሮውን በመግፋት ላይ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ዘ-ህወሀት የሚኮፈስበት አንዳችም ነገር የለውም፣ ምንም!

ያለምንም ተጨባጭ ነገር ትግራይ በኢትዮጵያ ውስጥ የእንዱስትሪ ኃይል ማዕከል ትሆናለች እየተባለ ይደሰኮራል፡፡

እንደ አንድ ዘገባ ከሆነ “በኢትዮጵያ ውስጥ በትግራይ ጎሳ አባላት የሚንቀሳቀሱ እና 20 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 66 ኩባንያዎችን በመምራት ላይ ይገኛሉ” ተብሏል፡፡ የ20 ሚሊዮን ብር ጉዳይ ጥያቄ ሆኖ የሚቀርበው “ስንቶቹ ናቸው በትግራይ ክልል ውስጥ ያሉት?” የሚለው ነው፡፡

እ.ኤ.አ ሕዳር 2015 የዩናይትድ ስቴትስ የግብርና ቢሮ መምሪያ የውጭ የግብርና አገልግሎት/United States Department of Agriculture Office Foreign Agricultural Service ዘገባ “ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የሸንኮራ አገዳ ከሚያመርቱ 10 ዋና ሀገሮች መካከል ለመሆን ታልማለች” የሚል ዘገባ አሰራጭቷል፡፡

በመላ ሀገሪቱ ውስጥ በግንባታ ላይ ባሉት የስኳር ፋብሪካዎች እና ግምታዊ በሆነው የማምረት አቅማቸው ላይ ያለው መረጃ ዘ-ህወሀት ፍትሀዊ በሆነ መልኩ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት በማፍሰስ ትግራይን የእንዱስትሪ ኃይል ማዕከል አደርጋለሁ እያለ የሚያራመደውን ፕሮፓጋንዳ የሚደግፍ ሆኖ አልተገኘም፡፡ እንዲየውም በተጻራሪው ሆኖ ይገኛል!

በትግራይ ውስጥ ያለው የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት መረጃ ምንድን ነው?

እንደ ትግራይ የኢንቨስትመንት የስራ ሂደት ዋና ባለቤት እንደ ጎይቶም ገብረ ኪዳን መረጃ ከሆነ እ.ኤ.አ በ2015 የትግራይ ክልላዊ መንግስት የከተማ ልማት እና የኮንስትራክሽን እንዱስትሪ ጽ/ቤት ከ800 በላይ ለሚሆኑ እና 10.5 ቢሊዮን ብር በጀት ለተያዘላቸው ፕሮጀክቶች ፈቃድ መስጠቱን ግልጽ አድርጓል፡፡ ገብረ ኪዳን እንዲህ ብሏል፣ “ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ 829 እንዱስትሪዎች በግብርና፣ በአግልግሎት፣ በባህል እና ቱሪዝም ዘርፎች ላይ ኢንቬስት በማድረግ ተመዝግበው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡“

(ጉድ እኮ ነው 800ዎቹ ፕሮጀክቶች የአውሮፓው የገና ሺማግሌ ሳንታ ከሎስ የበረዶ ጋሪዉን በሰማይ አየጋለበ ሲሄድ ጂፒኤሱ (የመንገድ መምሪያ መሳርያ) ተሰብሮ በአስቸኳይ በገብረ ኪዳን ደጅ ላይ ያረፈ ጊዜ ነበር ፡፡)

እ.ኤ.አ በ2009 የሚሊኒየም ከተሞች ተነሳሽነት እና የቬል ኮሎምቢያ ማዕከል/Millennium Cities Initiative and Vale Columbia Center “የኢንቨስትመንት ዕድሎች በመቀሌ በትግራይ መንግስት በኢትዮጵያ“ በሚል ርዕስ ባቀረበው ባለ 80 ገጽ ዘገባ እ.ኤ.አ በ2016 የኢንቨስትመንቶች ሁኔታ ዲስኩር ምን ይመስላል?

ምናልባትም ለዚህ ጥያቄ መልስ ከትግራይ ክልላዊ መንግስት እንዱስትሪ እና ንግድ ቢሮ ጽ/ቤት የሚገኝ ይሆናል፡፡

የእኔ ዓላማ ዘ-ህወሀት እያደረገው ስላለው ስለእያንዳንዱ ፕሮፓጋንዳ እና ስለትግራይ ሕዝብ ምን ተግባራትን እንደሰራ ለመቃወም አይደለም፡፡ ያ ውይይት ለሌላ ጊዜ የሚቆይ ይሆናል፡፡

የእኔ ዋናው ነጥብ ዘ-ህወሀት ለትግራይ ሕዝብ ሰራሁት እያለ የሚያሰራጨው ፕሮፓጋንዳ በጥንቃቄ መታየት ያለበት ጉዳይ መሆኑን ለማስገንዘብ ነው፡፡

ቀላል እውነታ ለመናገር ያህል የዘ-ህወሀት የኃይል መዋቅር ማንንም አይወክልም ሆኖም ግን እራሱን ፣ ደጋፊዎቹን፣ ግብረ አበሮቹን እና ጓደኞቹን ብቻ ነው ሊወክል የሚችለው፡፡

ዘ-ህወሀት በሰው ልጆች ላይ የሚፈጽማቸው ሰብአዊ ወንጀሎች እንደተራራ እየተቆለሉ በመጡ ቁጥር ከብቸኛ የወንጀል ተጠያቂነት እራሱን ለመደበቅ ሲል የትግራይን ሕዝብ በመጠለያነት እና በመደበቂያነት ይጠቀማል፡፡

ከዚህ ትምህርት አድርገን ልንወስደው የሚገባን ነገር ተራ የሆነውን የትግራይን ሕዝብ ከዘ-ህወሀት ጋር በመቀላቀል ለዘ-ህወሀት እርዳታ የሚያደርግ እና ደጋፊ ነው ብሎ መውሰድ የሞራል ስብዕና ዝቅጠት እና የእውነታነት ስህተት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

ይህም ሲባል የብዙ ሚሊዮኖች ብሮች ካፒታል ያላቸው በርካታ የቢዝነስ ሰዎች እና የንግድ ድርጅቶች በጥቅም ከዘ-ህወሀት ጋር በጥብቅ የተሳሰሩ እና ህብረትን የፈጠሩ የትግራይ ጎሳ አባላት የሉም ማለት አይደለም፡፡

ይህም ማለት ዘ-ህወሀት በቤተሰባዊነት፣ በፖለቲካ ትስስር እና የሙስና ስርዓት በመዘርጋት ለትግራይ ጎሳ ደጋፊዎቹ እና ግብረአበሮቹ ልዩ የሆነ ጥቅም አልሰጠም ማለት በፍጹም አይደለም፡፡

የወንጀል ድርጊትን በመፈጸም የሚታወቀው እና ማህበረ ረድኤት ትግራይ (ማረት) እየተባለ የሚጠራው ድርጅት በተለይ የትግራይ ጎሳ የሆኑትን የዘ-ህወሀትን መሪዎች፣ ካድሬዎች፣ ግብረ አበሮች እና ደጋፊዎችን ለመጥቀም ሲባል የተቋቋመ ድርጅት አይደለም የሚል ሀሳብ ለመሰንዘርም አይደለም፡፡

ይህም ሲባል ዘ-ህወሀት የትግራይ ጎሳ ለሆኑት አባላቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር  ለመንግስት የኮንትራት ስራዎች እና ከሀገሪቱ የህዝብ ባንኮች ሊከፈል የማይችል ብድር በልዩ ትዕዛዝ እየወጣ እንዲሰጣቸው አላደረገም የሚል ሀሳብ ለመሰንዘር አይደለም፡፡

ይህም ሲባል የትግራይ ጎሳ አባላት ከሌላው ጎሳ አባላት በተለየ መልኩ የመንግስት ስራ በመስጠት፣ በከፍተኛ ትምህርት ገብተው እንዲማሩ በማድረግ፣ ሕዝባዊ አገልግሎቶችን፣ ወዘተ እንዲያገኙ አላደረገም የሚል ሀሳብ ለመሰንዘር አይደለም፡፡

የትግራይ ጎሳ አባላት የሆኑ የዘ-ህወት አባላት፣ ካድሬዎች፣ ግብረ አበሮች እና ደጋፊዎች ግብር አይከፍሉም፣ ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገባ ዕቃ በጣም ዝቅተኛ የሆነ የቀረጥ ክፍያ ብቻ ወይም እንዲያውም አይከፍሉም የሚል ሀሳብ ለመስንዘር አይለደም፡፡

ዋናው ነጥብ ማንም ከማንኛውም የጎሳ ቡድን ቢሆን ህይወቱን እና ስብዕናውን ለዘ-ህወሀት ሰይጣን የሚሸጥ እስከሆነ ድረስ ተመሳሳይ ጥቅም ሊያገኝ ይችላል፡፡

ዘ-ህወሀት ከማንም ጋር፣ በማንኛውም ጊዜ፣ በማንኛውም ቦታ የፋውስትን የአስመሳይነት የሸፍጥ ስምምነት ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነ፣ ችሎታ ያለው እና ዝግጁ የማፊያ ድርጅት ነው!

የጎቴ ዶ/ር ፋውስት ለሀብት፣ ለስኬት፣ ለዓለም አስደሳች ነገሮች ሲል ከሰይጣን ጋር ስምምነትን ይፈጽማል፡፡

ዘ-ህወሀት እኩል የሆነ የሰይጣን ዕድል ሰጭ ነው፡፡

ዘ-ህወሀት ለእርሱ ነብሱን ለመሸጥ ለሚዘጋጅለት ለማንኛውም ሰው ሁሉ የጎሳ ማንነት፣ ብሄር፣ ኃይማኖት፣ ወዘተ ሳይል ሀብት፣ ስኬት ዓለም አቀፋዊ አስደሳች የሆኑ ነገሮች እና ስልጣንን ይሰጣል፡፡

ዘ-ህወሀት በመጨረሻው ሰዓት የአንተን ነብስ እስካገኘ ድረስ አንተ ማን እንደሆንክ እና በማንኛውም መልኩ ከማንኛውም ሰው ጋር ስምምነት ብትፈጽም ጉዳዩ አይደለም፡፡

አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ሁልጊዜ ማለት ይወደው እንደነበረው ለዘ-ህወሀት ታማኝነት መሆን ከጎሳ፣ ከኃማኖት፣ ከትምህርት፣ ከስራ ልምድ ወይም ደግሞ ከማንኛውም ነገር የበለጠ ጠቃሚ ነው፡፡

ለዘ-ህወሀት ታማኝነት ዋናዉና የመጨረሻው ፈተናን ማለፍ ማለት ነው፡፡

የእራሳቸውን ነብሶች በመሸጥ ለዘ-ህውሀት ታማኝ ሎሌዎች የሆኑ እና ህሊናቸወውን ለገንዘብ ያስገዙ በርካታ አማሮች፣ አሮሞዎች፣ ጉራጌዎች እና ሌሎች ሰዎች አሉ፡፡ ይህንን እውነታ የሚክድ ሊኖር ይችላልን?

አጽንኦ በመስጠት ላቀርበው የምፈልገው ዋናው እውነታ በዘ-ህወሀት ሀጢያቶች እና ወንጀሎች ምክንያት የጎሳ ህብረትን በመፍጠር በተራው የትግራይ ሕዝብ ላይ ጥፋተኝነትን ለመፈለግ ባለመቻኮል ፍትሀዊ መሆን እና ከማንኛውም መጥፎ ድርጊት መቆጠብ እንዳለብን ላስገነዝብ እፈልጋለሁ፡፡

ተራው የትግራይ ሕዝብ እንደሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ሁሉ እተሰቃየ እና መከራውን እያየ ያለ ምስኪን ሕዝብ ነው፡፡ እንደሚነዛው አሉባልታ ሳይሆን ሐቁ ይህ ነው፡፡

ህብረት በመፍጠር እና በመደራጀት የሚፈጸም ጥፋት ኢሞራላዊ እና አሳፋሪ ድርጊት ነው ምክንያቱም ስነአመክንዮያዊ ያልሆነ እና ውጤቱም የደጋፊዎቹ የጋራ የቅጣት መፈክር ነው፡፡

የዘ-ህወሀት ሰይጣኖች ሕግን እና የስነምግባር መርሆዎችን በመደፍጠጥ በሰሯቸው ሀጢያቶች እና ሰብአዊ ወንጀሎች ተራውን የትግይ ሕዝብ ማውገዝ ፍትሀዊ አይደለም፡፡

የዘ-ህወሀት መሪዎች ሁልጊዜ በእነርሱ በእራሳቸው ላይ ስለሚደርሰው አደጋ እና ማስፈራራት ምንም ሳይጨነቁ በትግራይ ሕዝብ ህይወት እና ህልውና አደጋ ላይ እንደሚወድቅ አድርገው ሌት ቀን የሀሰት ቅጥፈታቸውን ይሰብካሉ፡፡ ዘ-ህወሀት የእራሱን ዕጣ ፈንታ ከትግራይ ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ጋር በማቆራኘት ወደ ፊት የሚመጣውን ማሰቃየት እና ከዚህም አልፎ የሚከሰተውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ሁሉ ከተራው ሕዝብ ጋር ለማያያዝ ይሞክራሉ፡፡

ተራውን የትግራይ ሕዝብ በሙስና እስከ አንገታቸው ድረስ ተዘፍቀው ከሚገኙት ከዘራፊ ወሮበላ የዘ-ህወሀት አባላት መለየት መቻል አለብን፡፡ ለኃጢያን የተባለው ለጻድቃን ይተርፋል ተረት ተግባራዊ እንዳይሆን አበርትቶ መስራትን ይጠይቃል፡፡

የዘ-ህወሀት መሪዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 25 ዓመታት የፈጸሟቸው ወንጀሎች የናዚ መሪ የነበረው ኸርማን ጎሪ በአንድ ወቅት በኑረምበርግ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የፍርድ ችሎት ላይ ቀርቦ ከሰጠው እና እንዲህ ከሚለው አባባል ጋር የቅርብ ትስስር አላቸው፡

በእርገጥ ሕዝቡ ጦርነትን አይፈልግም፡፡ ሆኖም ግን ከሁሉም በላይ የሀገሪቱ መሪዎች  ናቸው ፖሊሲውን የሚወስኑት፡፡ እናም ሁልጊዜ ወደ ዴሞክራሲ፣ ፋሽስት አምባገናነዊነት ወይም ደግሞ ወደ ፓርላሜንታዊ አገዛዝ ወደ ኮሙኒስት አምባገነንነት ሕዝቡን የሚስቡት እነርሱ ናቸው፡፡ ሕዝቡ ድምጽ ኖረው አልኖረው ምንጊዜም ቢሆን ጉዳዩ የሚያልቀው በመሪዎቹ ነው፡፡ ያ ቀላል ነገር ነው፡፡ ሁሉም ልታደርጉ የምችሉት ነገር ቢኖር በሌላ ኃይል ሕዝቦች እንደሚወጉ ንገሯቸው፡፡ እናም በሰላማዊ መንገድ ግጭቶችን ለመፍታት የሚሞክሩትን ጀግንነት የሌላቸው እና በሀገሪቱ ላይ አደጋን ለማምጣት የሚፈልጉ ናቸው በማለት በማውገዝ አጋልጧቸው“ ነበር ያለው፡፡ 

ዘ-ህወሀት የጥላቻ እና የጥልቅ ጥላቻ ከበሮውን በመደለቅ የትግራይ ሕዝብ እየተወጋ ነው፣ እናም የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝብ በአንድነት ህብረት በመፍጠር ትግሬዎቹን ሊያጠቁ ነው በማለት መቀስቀስ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ይህ የሞኝ ብልጣብልጥነት ያለቀበት ያረጀ እና ያፈጀ ነው።

በፍጹም አይሰራም፡፡

ዘ-ህወሀት በዚህ ጊዜ አይሰራም!

የእኛ ጠላት ጥላቻ ነው፣

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2008 “ከጠላቶቻችን ጋር ተገናኘን” በሚል ርዕስ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡ ሌላ ማንም ሳይሆን እኛው እራሳችን ነን፡፡ “ጠላት” በሚል ቃል የተደረገ ጥናት ነበር፡፡

እ.ኤ.አ በ2016 “ከጥላቻ አራጋቢዎች ጋር ተገናኘን፣ እናም እነርሱ እራሳችን ነን” በሚል ርዕስ ትችት አቀረብኩ፡፡

ነገሩ በቀላል መንገድ ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ጥላቻ የነብስ በሽታ ነው፡፡ ጥላቻ ሌላው የኃይለኝነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ነው፡፡ የፈላስፋውን እና የሰላም አባቱን የዳይሳቁ ኢቀዳን አባባል በመዋስ ስለጥላቻ የሚከተለውን እላለሁ፡

“ጥላቻ ከቆሰለ መንፈስ ይወለዳል፡ ጥላቻ በግትራዊነት እሳት ከተቃጠለ መንፈስ እና ካበጠ ቁስል፣ ኃይልየለሽ ከመሆን እና ከተስፋ ማጣት ከሚመነጭ ከተበጣጠሰ እና ከተቆጣ  መንፈስ፣ ለህይወት ትርጉም ከማይሰጥ ደረቅ እና እርካታ ከማይሰጥ መንፈስ፣ በዝቅተኝነት ስሜት ከኮሰመነ እና ከተዳከመ መንፈስ ይመነጫል፡፡ ለራስ ክብር ከመስጠት ከሚመነጭ ቁጣ እና ከውርደት ኃይል ይወለዳል፡፡ ሌሎችን በመደምሰስ እና በመደብደብ የግፍ ሰለባ በማድረግ ደሰታን ለማግኘት ከሚደረግ ጥረት፣ በሕዝብ መገናኛ ዘዴዊች በህብረተሰቡ ውስጥ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት የጥላቻ እና የኃይል ባህል እውን ይሆናል…ከተፈወሰ፣ ከሰላማዊ ልብ ጨዋነት ይወለዳል፣ ከጨዋነት ደግሞ ሌሎችን የማዳመጥ ፈቃደኝነት ይወለዳል፣ ሌሎችን ከማዳመጥ ፈቃደኝነት ደግሞ የጋራ መግባባት ይወለዳል፣ ከጋራ መግባባት ደግሞ ሰላማዊ ማህበረሰብ ይወለዳል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በጥላቻ ከተሞሉት እና የጥላቻ ፖለቲካን ከሚያራምዱት ከጠላቶቿ ባሻገር ወደፊት በመመልከት በመስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች፡፡

እኛ በአሁኑ ጊዜ ለልጆቻችን፣ ለእራሳችን እና ለቀጣዩ ትውልድ ቅርጽ መስጠት፣ መልክ ማስያዝ፣ መፍጠር እና መገንባት ያለብን ለወደፊቱ ነው፡፡

የወደፊቱ ጊዜ ከፍርኃት፣ ከኃይል፣ ከጥላቻ፣ ከኃይማኖት እና ከጎሳ ያለመቻቻልነት ነጻ መሆን አለበት፡፡

የወደፊቱ ጊዜ በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ በጥብቅ የተመሰረተ አንድነት፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት እና ጠንካራ የዴሞክራሲያዊ ተቋማት የሚመሰረቱበት መሆን ይኖርበታል፡፡

የወደፊቱ የኢትዮጵያ ሁኔታ ኔልሰን ማንዴላ ለደቡብ አፍሪካ ሕዝብ ሲያልሙት እንደነበረው እና እንዲህ እንደሚለው መሆን ይኖርበታል፡ “በፍጹም፣ በፍጹም እናም በፍጹም ይህች ቆንጆ የተዋበች ምድር ሰዎች እንደገና አንዱ በአንዱ የሚጨቆኑባት እና ሕዝቦች የሚናቁባት እና የሚዋረዱባት ዓለም አትሆንም፡፡“

ወደፊት መንግስት የዜጎችን መብት የሚያከብርበት እና የእያንዳንዱን ዜጋ ነጻነት የሚጠብቅበት እንዲሁም መሪዎች ለሕዝቦቻቸው እና በሀገሪቱ ሕጎች ተጠያቂዎች የሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡

የወደፊቱ ጊዜ ወጣቱ የመንግስቱን እና የሕዝቡን ስልጣን የሚይዙበት ነው፡፡

የጥላቻ አራጋቢዎች በኢትዮጵያ ቦታ የላቸውም፡፡

በእርግጥ የጥላቻ አራጋቢዎች ዘር የላቸውም፣ ሀገር የላቸውም፣ ብሄር የላቸውም፣ ጎሳ የላቸውም፣ ኃይማኖት እና ጾታ የላቸውም፡፡

የጥላቻ አራጋቢዎች የእራሳቸው የሆነ እና በአንድ አካባቢ የተቀነበበ የጥላቻ ፕላኔት ነው ያላቸው፡፡

“የጥላቻ አራጋቢዎች ወደ ጥላቻ ይሄዳሉ፡፡” የእኛ ስራ መሆን ያለበት እነዚህ የጥላቻ አራጋቢዎች በራሳቸው የብቸኝነት የግዛት ክልል ፕላኔት ውስጥ ብቻ ተወስነው እና ተቀፍድደው እንዲቆዩ ማድረግ ነው፡፡

የማንዴላን አባባል በመዋስ “ጥላቻን ማራገብ  መርዝ በመጠጣት ሌላው ሰው ይሞትልኛል ብሎ እንደመጠበቅ ነው፡፡“

እዚህ ላይ መርዙን የጠጣው የጥላቻ አራጋቢ አስቀድሞ እንደሚሞት ልብ ይሏል፡፡

ወደ አንድነት ከሚያመጡን ነገሮች ይልቅ ከፍተኛ የሆነ ጊዜ በመውሰድ ስለሚለያዩን ነገሮች በከንቱ ጊዜ አናጠፋለን፡፡

የእኛ ችግር የፍትህ እጦት ነው፣ የእኛ ችግር የሰብአዊ መብት አለመከበር ችግር ነው፣ የእኛ ችግር የነጻነት እጦት ችግር ነው፣ የእኛ ችግር እራሳችንን በእራሳችን ማስተዳደር እንዳንችል የድምጻችን የመዘረፍ ችግር ነው፡፡

ስለእራሳችን መናገር አለብን፣ ስለእነርሱ መናገር አለብን፣ እኛ ሁላችንም የተባበረች ኢትዮጵያ በመባል እንታወቃለን፡፡

እኛው እራሳችን ማን እንደሆን እና ማን እንዳልሆን፣ ለማን እንደቆምን፣ በምን እንደምናምን፣ እርስ በእርሳችን እንዴት እንደምንረዳዳ እና እራሳችንን ከሚጎዱ ነገሮች መወገድ እንዳለብን፣ ሌሎችን የተሻለ ዕድል የሌላቸውን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ለመርዳት መተባበር እንዳለብን መነጋገር አለብን፡፡

ሁላችንም ኢትዮጵያውን ነን – የወሮበላ ዘራፊዎች ወንድማማቾች የግፍ ሰለባ የሆንን የአንዲት ሀገር ወንድማማቾች እና እህትማማቾች ነን ፡፡

ነጻነትን፣ ዴሞክራሲን እና የሰብአዊ መብትን ለማስከበር በምናደርገው ትግል በጠላትነት ሳይሆን በትብብር እና በመከባበር መንፈስ ነው ድልን መቀዳጀት የምንችለው፡፡

ለነጻነት፣ ለዴሞክራሲ እና ለሰብአዊ መብት መከበር የምናደርገው ትግል ለድል የሚበቃው የጥላቻ ፖለቲካን ከላያችን ላይ አሽቀንጥረን ስንጥል እና የአንድነትን እና የብዝሀነትን ፖለቲካ እቅፍ አድርገን ስንይዝ ብቻ ነው፡፡

ስለወንድማማችነት እና እህትማማችነት ተቀራርበን መነጋገር አለብን እናም ረዥሙን ጉዞ እንዴት አድርገን እንደምናጠናቅቀው እና በመጨረሻ አረንጓዴ፣ ብጫ እና ቀይ ቀለም ወደያዘው ቀስተደመና እንዴት መድረስ እንዳለብን ደጋግመን መወያየት አለብን፡፡

ከዚያ ቀስተደመና  በኋላ ስለሚገኘው እና ዋጋ ሊተመንለት ስለማይችለው ውድ እንቁ፡ የሰብአዊ መብት በሕግ ይጠበቃል፣ በሕዝቦች መፈቃቀድ የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ለዘለቄታው ይጠናከራሉ፣ የመንግስት ተጠያቂነት በሀገሪቱ የሕግ የበላይነት እውን ይሆናል፡፡

ሆኖም ግን እርስ በእርሳችን ጥላቻን በማራገብ የማይረቡ ፍሬከርስኪ ንግግሮችን እያደረግን በተመሳሳዩ እና በአሮጌው መንገድ እየተገዟን፣ እርስ በእርሳችን እየተካሰስን፣ ጥላሸት እየተቀባባን እና አየተዘላለፍን ወደ ጉዟችን መዳረሻ ልንደርስ ከቶውንም አንችልም፡፡ ወይም ደግሞ በጥላቻ ክንፍ እና በጠባባዊ የአእምሮ አስተሳሰብ ከቀስተደመናው ጫፍ ላይ በፍጹም ልንደርስ አንችልም፡፡

ብዙ ርቀት በማያስሄድ እና ቅርብ በሆነ መንገድ መጓዝ አለብን፡፡ የሮበርት ፍሮስት የግጥም ስንኞች በመዋስ አንዲህ በማለት ጉዳዩን ግልጽ አናርገው፡

  …

  ድምጼን ከፍ አድርጌ መናገር አለብኝ፣
የትም የትም ቦታ እግሬ በወሰደኝ፣
ለሰው ልጆች ፍትህ የሰላሙ ዘብ ነኝ፣
የሕግ ልዕልና ዲሞክራት ታማኝ፡፡

  ሁለት መንገዶች በእንጨት ተከልለው፣
አንዱ ቅርብ ሲሆን ሌላው ግን ሩቅ ነው፣
እኔ የመረጥኩት አጭር አቋራጭ ነው፣
ከጫፍ የሚያደርሰኝ ከቀስተደመናው፣
ከቀይ ቀለሙ ከብጫ አረንጓዴው፡፡

  እናም አቋራጩ አጭሩ መንገድ፣
የለውጥ ራስ ሆነ ሰላም የሚወድ፣
ሕዝብን የሚያገኛኝ በብረት ገመድ።

በአሁኑ ጊዜ ከጥላቻ አራጋቢዎች ጋር ተገናኝተናል፡፡ በወንድማማችነት እጅ ለእጅ እንያያዝ እና ለወደፊቱ ጉዟችን በጣም ርቀት የማያስኬደውን አቋራጭ መንገድ እንምረጥ፡፡

ይህ መንገድ እንደ ሰብአዊ ፍጡር የተለየ መልካም ዉጤት ያመጣል!

ለእኛ እንደ ሕዝብ እና እንደ ሀገር የተለየ መልካም ዉጤት ያመጣል!

ጆርጅ በርናንድ ሻው ብልህነትን በተላበሰ መልኩ እንዲህ የሚል ምልከታ አድርገው ነበር፣ “ያለለውጥ እድገት የማይቻል ነገር ነው፣ እናም አእምሯቸውን የማይለውጡ ሰዎች ምንም ዓይነት ነገር ሊለውጡ አይችሉም፡፡“ 

እራሳችንን ከፖለቲካ ጥላቻ በማጽዳት ወደ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት የፍቅር ፖለቲከ እንለውጥ፣ እናም “በዓለም ላይ እውን ሆኖ ለማየት ለምንመኘው እራሳችን ለውጥ እንሁን፡፡”

ጥላቻ ጥላቻን ይወልዳል፡፡ ፍቅር ሁሉን ያሸንፋል!  

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!  

ነሐሴ 17 ቀን 2008 ዓ.ም