ኢትዮጵያ በእሳተገሞራ ጫፍ ላይ ተቀምጣ!
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
“በሰላማዊ መንገድ ለውጥ እንዳይመጣ የሚከላከሉ ሁሉ ሞገደኛውን እና የማይቀረውን የአብዮት ማዕበል እንዲያስተናግዱ ይገደዳሉ” ጆን ኤፍ. ኬኔዲ
እንዲፈጸምልህ በምትመኘው ነገር ላይ አስቀድምህ ተጠንቀቅ ምክንያቱም የሚሆነው አይታወቅም የተመኘኸውን ልታገኝ ትችላለህና…
በአሁኑ ጊዜ በህይወት የሌለው እና የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) ፈላጭ ቆራጭ መሪ የነበረው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ አፈር ይቅለለውና የእርሱን አገዛዝ የማይወዱ ተቃዋሚ ኃይሎች ካሉ ወደ ጫካ በመግባት ተዋግተው በማሸነፍ የእርሱ ወሮበላ የአማጺያን ቡድን እ.ኤ.አ በ1991 እንዳደረገው ሁሉ ስልጣን መያዝ ይችላሉ በማለት ሰላማዊ ዜጎችን ለኃይል በትምከት አመጽ ይገፋፋ ነበር፡፡
አንድ የዱሮ አባባል እንዲህ የሚል ትምህርት ያስተምረናል፣ “እንዲፈጸምልህ በምትመኘው ነገር ላይ አስቀድምህ ተጠንቀቅ ምክንያቱም የሚሆነው አይታወቅም የተመኘኸውን ልታገኝ ትችላለህና::”
ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ምድር ላይ የተፈጸሙት ክስተቶች ሁሉ ዘ-ህወሀት ሲመኘው የነበረውን እያገኘ ለመሆኑ ያለምንም ስህተት በተጨባጭ ሁኔታ የሚያመላክቱ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ በዘ-ህወሀት የጭቆና አገዛዝ ላይ መጠነ ሰፊ የሆኑ ሰላማዊ ሰልፎችን እና ተቃውሞዎችን፣ ህዝባዊ የእምቢተኝነት ድርጊቶችን እንዲሁም ሰላማዊ የአመጽ ድርጊቶችን እና ተጨባጭነት ያላቸው የትጥቅ ትግሎችን በማካሄድ የሞት ሽረት ተጋድሎ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በከተሞች እና በገጠር አካባቢዎች የዘ-ህወሀትን አምባገነናዊ የጭቆና አገዛዝ የመገዳደር ሁኔታዎች ግልጽ በሆነ መልኩ በመታየት ላይ ይገኛሉ፡፡ አሁን ትላንት እንኳ በዘ-ህወሀት የጭቆና አገዛዝ ላይ መጠነ ሰፊ የሆነ ህዝባዊ ተቃውሞ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በትላንትናው ዕለት በምስራቅ ኢትዮጵያ ሀረርጌ ውስጥ በአወዳይ ከተማ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን ባሰሙ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ዘ-ህወሀት እልቂት መፈጸሙን ይፋ የሆኑ ዘገባዎች ያስረዳሉ፡፡
በሰላማዊ መንገድ ለሚካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎች እና ህዝባዊ ተቃውሞዎች ዘ-ህወሀት የሚሰጠው አጠቃላይ የሆነው እና የተለመደው ምላሹ ያለምንም የሕግ ተጠያቂነት በንጹሀን ዜጎች ላይ የእሩምታ ተኩስ መክፈት እና ህዝባዊ እልቂትን መፈጸም ነው፡፡ እ.ኤ.አ ግንቦት 2005 ተካሄደ የተባለውን የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ ውዝግብ ተከትሎ ተፈጽሞ በነበረው ማህበራዊ ቀውስ የዘ-ህወሀት ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አድራጊ ፈጣሪ መሪ የነበረው እና አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ በእራሱ ትዕዛዝ ቅጥር ነብሰገዳዮችን በማሰማራት በመቶዎች በሚቆጠሩ ወገኖቻችን ላይ እልቂት እንዲፈጸም ማድረጉን ተከትሎ በዚህ ዘግናኝ ድርጊት በመበሳጨት ይህንን የመሰለውን የማንአለብኝነት የአምባገነኖች የእልቂት ድርጊት በመቃወም ለወገኖቼ ድምጽ ለመሆን እና እልቂት የተፈጸመባቸው የንጹሀን ዜጎች ደም ደመከልብ ሆኖ እንዳይቀር የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቀው እና ለፍትህ አደባባይ ለማብቃት ወደ ሰብአዊ መብት ጥበቃ ተሟግችነት ዘው በማለት ገባሁ፡፡
እ.ኤ.አ ሰኔ 15/2016 ሂዩማን ራይትስ ዎች (ሂራዎ) የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት “ጭካኔ የተሞላበት የኃይል እርምጃ፡ በኢትዮጵያ የኦሮሞ ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎች እና በቁጥጥር ስር በማዋል የተሰጡ ምላሾች“ በሚል ርዕስ ዘ-ህወሀት በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ ያለውን ሕገ ወጥ አያያዝ በማብራራት ታላቅ ዘገባ አውጥቷል፡፡ በመጨረሻም ዘገባው እንዲህ በማለት ደምድሟል፣“ከ400 በላይ የሚገመቱ ንጹሀን ዜጎች ተገድለዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩት ቁስለኛ ተደርገዋል፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩት ሰላማዊ ዜጎች ደግሞ ወደ እስር ቤት ዘብጥያ እንዲወርዱ ተደርገዋል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ መቶ እና ከዚያም በላይ ሊበልጡ የሚችሉ ንጹሀን ዜጎች ታፍነው ደብዛቸው እንዲጠፋ በማድረግ የጥቃት ሰለባ ሆነዋል፡፡“
ዘ-ህወሀት የመረጠው የግጭት አፈታት ዘዴ ሆኖ የቆየው እና አሁንም ሽንጡን በመገተር ቀጥሎበት የሚገኘው የህዝብ እልቂት፣ የጭካኔ ግድያ፣ መጠነሰፊ ውድመት እና የግድያ ወንጀሎችን መፈጸም ነው፡፡
ከብዙ ጊዜ ጀምሬ በተጨባጭ ስከራከር እንደቆየሁት ዘ-ህወሀት ግንዛቤ ወስዶ ልቦናውን ለሰላማዊ ለውጥ ክፍት እስካላደረገ እና የተገኙ ዕድሎችን በመጠቀም አስፈላጊውን የማሻሻያ የለውጥ እርምጃ እስካልወሰደ ድረስ በመጨረሻ የሚቀረው አንድ አማራጭ ብቻ ነው፡፡ ይኸውም 24/7/365 የሆነውን የግድያ ማሽኑን (ፋብሪካ) በዘላቂነት ተግባራዊ በማድረግ በስልጣን እርካብ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ መቆየት ነው፡፡
አንድ ትልቅ ጥያቄ ሆኖ የሚቀርበው ግን ዘ-ህወሀት የግድያ ማሽኑን በመጠቀም ስልጣኑን ጨምድዶ ይዞ የሚቆየው ለምን ያህል ጊዜ ይሆናል? የሚለው ነው፡፡
ዘ-ህወሀት ለዘላለሙ በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጥጦ ለመቆየት እንዲችል በእያንዳንዱ የሀገሪቱ ክፍል ላይ ነፍሰገዳይ የሆነውን የፌዴራል ፖሊሱን በማሰማራት እልቂትን በመፈጸም መዝለቅ ይችላልን?
በአሁኑ ጊዜ የዘ-ህወሀት አካባቢያዊ እና መንደርተኛ ሎሌዎች የዘ-ህወትን አስቀያሚ ቆሻሻ የግድያ እና የእልቂት እኩይ ምግባራትን ለመፈጸም ጠብመንጃዎቻቸውን ወደ ጓደኞቻቸው እና ዘመዶቻቸው ግንባሮች ላይ በማነጣጠር ግድያ ለመፈጸም የሚዘጋጁ ለመሆናቸው አጠራጣሪ ጉዳይ ነው፡፡
ጨቋኝ አምባገነኖችን ለመገዳደር የምናደርገው የትግል ታሪክ ጥቂት የማይበገሩ ትምህርቶችን ያስተምረናል፡፡
ዘ-ህወሀት የግድያ ማሽኑን በመጠቀም ለዘላለም በስልጣን ኮርቻ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ የመኖር ዕድሉ በሁለት እና ሁለት ሁኔታዎች ብቻ የሚወሰን ይሆናል፡፡ እነርሱም፡
1ኛ) የኢትዮጵያ ህዝብ የዘ-ህወሀትን የሰብአዊ ወንጀሎች፣ ሙስናዎች፣ ስልጣንን ከሕግ አግባብ ውጭ መጠቀምን፣ የምርጫ ድምጽ ዘረፋን፣ መጠነ ሰፊ የህዝብ ሰብአዊ መብት መደፍጠጥን እና የከፋፍለህ ግዛን ፖሊሲ አሜን ብሎ በመቀበል በታጋሽነት በላዩ ላይ እንደ መርግ የተጫኑትን እነዚህን እንዛዝላዎች በመሸከም አንገቱን ደፍቶ ምንም ነገር ሳያደርግ ዝም ብሎ የሚኖር ከሆነ፣
2ኛ) የኢትዮጵያ ህዝብ በዘ-ህወሀት ላይ ያለውን የፍርሀት ስፋት፣ ወርድ፣ ርዝመት፣ ቁመት እና መጠን ለማሸነፍ ያለው ቁርጠኝነት ናቸው፡፡
ታላቁ የአሜሪካ ሞገደኛ የለውጥ አራማጅ የነበሩት ቶማስ ፔይን በአንድ ወቅት እንዲህ የሚል ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር፡
“ኃይል ያለፍላጎት ምንም ዓይነት የማድረግ መብት ወይም አቅም የለውም፡፡ መቸውንም ሆኖ አያውቅም፣ ወደፊትም በፍጹም አይሆንም፡፡ እስኪ በሰዎች ላይ ስላሉት ነገሮች ለትንሽ ጊዜ አስቡ፣ እናም በላያቸው ላይ የተጫኑት የኢፍትሀዊነት ብዛት እና ትክክል ያልሆኑ ነገሮች መሆናቸውን ትደርሱበታላችሁ፡፡ እናም እነዚህ ነገሮች በቃላት ትግል ወይም በኃይል ወይም ደግሞ በሁለቱም እንዲወገዱ እስካልተደረጉ ድረስ በቀጣይነት ይኖራሉ፡፡ የጨቋኞች የመኖር ህልውና በተጨቋኞች የመሸከም ትዕግስት ላይ የሚወሰን ነው፡፡“
ሮበርት ሆልምስ “የሰላማዊ ትግል ስነምግባሮች” (2013 ገጽ 2260) በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፋቸው እንዲህ የሚል የክርክር ጭብጥ አቅርበዋል፡
“ህዝብ ፍርሀቱን ሲያስወግድ ኃይል የጉም ሽታ በመሆን ድምጥማጡ ይጠፋል፡፡ አንተን የማይፈሩህን ህዝቦች እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ መግደል ትችላለህ፣ ሆኖም ግን በምንም ዓይነት መንገድ ልትቆጣጠራቸው አትችልም፡፡ የሞቱ ሰዎችን ልትቆጣጠር አትችልም፡፡ ከፈለግህ የድምጽ ማጉያ በመያዝ በመቃብር ስፍራ መጓዝ ትችላለህ፡፡ ህዝቦች እንዲነሱ ትዕዛዝ ስጥ፣ መንገዶችን አጽዱ፣ ግብር ክፈሉ፣ ለወታደራዊ ግዳጅ ዘገባ አቅርቡ በል፣ እናም ምንም ሳያደርጉ ዝም ይሉሀል፡፡ የፖለቲካ ኃይል የኃይል መሳሪያዎችን በተቆጣጠሩት ሰዎች ዘንድ እምቢ የምትል ከሆነ ስቃይን በመፍራት ታዛዥነትን ይፈልጋል፡፡ ያ ኃይል ህዝቦች ፍርሀትን ሲያስወግዱ እንደ ጧት ጤዛ በኖ ይጠፋል…“ ነበር ያሉት፡፡
ታሪካዊ ምሳሌዎችን በመጥቀስ እ.ኤ.አ መስከረም 2013 “በኢትዮጵያ የሰላማዊ ትግል የለውጥ ሽግግር ዴፕሎማሲ“ በሚል ርዕስ አቅርቤው በነበረው ትችቴ በሰላማዊ ትግል መገዳደር እና ፍርሀትን ከጨቋኞች እና ከአምባገነኖች ማስወገድ በሚሉት መካከል ያለውን የተዛምዶ ግንኙነት መርምሬ ነበር፡፡
ህዝቦች በጨቋኞቻቸው ላይ የነበራቸውን ፍርሀት ሲያስወግዱ እና ነባራዊ ሁኔታዎች ተሟልተው የጨቋኞቻቸውን ፍርሀት በልጠው ሲሄዱ ሰላማዊ የማህበራዊ እና የፖለቲካ ለውጥ ታሪክ ዕውን ይሆናል በማለት ለዓመታት ያለምንም ማቋረጥ የክርክር ጭብጤን ሳቀርብ ቆይቻለሁ፡፡ ቀላል በሆነ መንገድ ለመግለጽ ህዝቦች በጨቋኞቻቸው ላይ ያላቸውን ፍርሀት ማራመድ በሚተውበት ጊዜ ጨቋኞቻቸውን መፍራት ያቆማሉ፡፡ የህይወት መስዋዕትነት መክፈል፣ አካለ ጎደሎ መሆን ወይም ደግሞ የነጻነት ማጣት አደጋ ቢኖርም እንኳ ህዝቦች በአንድነት በመነሳት የጦርነት መዋጋት መዝሙራቸውን እንዲህ በማለት ማወጅ ከሚያስችላቸው ደረጃ ላይ ይደርሳሉ፡ “በቃ በቃ ነው! ከዚህ በላይ መቀጠል አንችልም! ከዚህ በኋላ ሽንጣችንን ገትረን እንዋጋለን!“
ዘ-ህወሀት ሲፈራው የነበረው በኢትዮጵያ የመጨረሻው ሰዓት የደረሰ መሆኑን አምናለሁ፡፡
በየትኛውም ቦታ የሚገኙት የኢትዮጵያ ህዝቦች በዘ-ህወሀት ላይ እንዲህ የሚል አዋጅ በማወጅ ላይ ይገኛሉ፣ “በቃ በቃ ነው! ከዚህ በላይ መቀጠል አንችልም! ከዚህ በኋላ ሽንጣችንን ገትረን እንዋጋለን!“
የተጨቆኑ ሕዝቦች እና እሳተገሞራ አንድ ዓይነት ባህሪ እንዳላቸው አምናለሁ፡፡
እሳተ ገሞራ ለበርካታ አስርት ዓመታት ያህል ምንም ዓይነት የእሳተ ገሞራ የፍንጣቂ ምልክቶችን ሳያሳይ በድን ሆኖ ይቆያል፡፡ በድን ሆኖ የቆየ እሳተገሞራ በመሬት ከርሰ ምድር ውስጥ በሚፈጠረው ኃይለኛ የሙቀት ግፊት እና በሚፈጠረው የቀለጠ አለት ሙቀት ምክንያት የመሬትን የሽፋን ገጽታ በድንገት ወደላይ በመግፋት ይፈነዳ እና እሳተገሞራ እውን ይሆናል፡፡ በሂደት በቂ የሆነ ጋስ ከጥልቁ መሬት ውስጥ በየጊዜው እንዲወጣ ቢደረግ ኖሮ በሙሉ አቅም የሚፈነዳው እሳተ ገሞራ የመከሰት እድሉ ይዘገይ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በከርሰ ምድር ውስጥ ያለው ግፊት እና የአለቱ የመቅለጥ ኃይሉ አይሎ እሳተ ገሞራው ለመፈንዳት ከወሳኝ ደረጃ ላይ በሚደርስበት ጊዜ ሙሉ የሆነ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ውጤት እውን ይሆናል፡፡
እንደዚሁም ሁሉ የተጨቆኑ ሕዝቦች ለበርካታ አስርት ዓመታት ምንም ዓይነት የኃይል፣ የሙቀት፣ የተስፋ እና ተደጋጋሚ የደስታ እጦት፣ የቁጣ፣ የበቀል እና የጥላቻ ምልክቶችን ሳያሳዩ በድን ሆነው ይቆያሉ፡፡ በጊዜ ሂደት እነዚህ ሁኔታዎች እየተብላሉ እና ጥልቀት እና ስፋትን እያገኙ በህብረተሰቡ ውስጥ በድንገት እንደ ሰደድ የቋያ እሳት ቦግ ይላሉ፡፡
እ.ኤ.አ በ1980 በዋሺንግተን ግዛት በሄለንስ ተራራ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው የእሳተገሞራ እንቅስቃሴ ፍጹም በሆነ መልኩ ያልተጠበቀ ነበር፡፡ ይህ እሳተገሞራ ለ123 ዓመታት ያህል ምንም የሌለ በድን ሆኖ የቆየ ነበር፡፡ የብሄራዊ ፓርክ መግለጫ ጽሁፎች የሄለንስ ተራራን በጣም ቆንጆ እና ሰላማዊ የሆነ፣ ቱሪስቶችን የመሳብ አቅም ያለው እያሉ ነበር የሚገልጹት፡፡ ሆኖም ግን እ.ኤ.አ በመጋቢት 1980 በክፍለ ዘመኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ትናንሽ የመንቀጥቀጥ ምልክቶች መታየት ጀመሩ፡፡ እ.ኤ.አ ግንቦት 18/1980 ምንም ዓይነት ምልክት ሳይታይ በሬክተም ስኬል 5.1 የተመዘገበለት የመሬት መንቀጥቀጥ በሌሎች ተከታታይነት ባላቸው ክስተቶች ታጅቦ በመሬት ላይ ከተመዘገቡ ታሪኮች ሁሉ በዓይነቱ ግዙፍ የሆነ የመሬት መንሸራተት ፍርስራሽን ጨምሮ በሚያስደንቅ ሁኔታ ተከሰተ፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በጣም ወሳኝ የሆነ ደረጃ ላይ የደረሰውን ሁኔታ ሊያመላክቱ የሚችሉ ምልክቶች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አልታዩም ነበር፡፡ ዘ-ህወሀት እንደተለመደው ምንም አይመጣብኝም በማለት ህዝቦችን ከመረቶቻቸው እያፈናቀለ ለአባሎቹ፣ ለሎሌዎቹ፣ ለደጋፊዎቹ እና ለጓደኞቹ በማደል ላይ ነበር፡፡ ዘ-ህወሀት ኢትዮጵያን እንደ ማፊያ መንግስት ወይም ደግሞ እንደወሮበላ ዘራፊ መንግስት በማድረግ ምስቅልቅሏን በማውጣት ላይ ይገኛል፡፡ ዘ-ህወሀት በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ ውስጥ እርሱን መገዳደር የሚችል መንፈሰ ጽኑ፣ ፍርሀትየለሽ እና በግልጽ የሚታይ ህዝባዊ እምቢተኝነት ይከሰታል ብሎ አልገመተም ነበር፡፡
ዘ-ህወሀት በትዕቢት እና በእብሪት ተወጥሮ እራሱን በምዕናባዊ የማን አህሎኝ አይበገሬነት ዘይቤ ሰይሞ በላዩ ላይ እየናኘበት ያለውን ድንቁርናውን ባለመገንዘቡ ምክንያት እርሱን ዶግ አመድ ማድረግ የሚችል ዘለቄታዊ የሆነ ህዝባዊ አመጽ እያደገ እና እየጎመራ መጣ፡፡
በአንድ ወቅት ከዘ-ህወሀት የውስጥ ሰው መካከል አንዱ የዘ-ህወሀት መሪዎች የዓለም እይታ (የኢትዮጵያ እይታ) በሁለት መሰረታዊ እሳቤዎች ላይ የተዋቀሩ ለመሆናቸው ዓይኑን በጨው ታጥቦ ባልሰለጠነው ግልድፍ እንደበቱ እንዲህ በማለት ተናግሮ እንደነበር የሰማ ሰው ነግሮኛል፡
“1ኛ) የዘ-ህወሀት ድርጅት፣ መሪዎቹ እና ደጋፊዎቹ ጀግኖች፣ አይበገሬዎች፣ ደፋሮች፣ ጀብደኞች እና ተባባሪዎች ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው በአጠቃላይ በህዝቡ ላይ የበላይነትን መቀዳጀት የቻሉት፡፡
2ኛ) የኢትዮጵያ ህዝቦች በአጠቃላይ ፈሪ ቦቅቧቃዎች፣ ጥንካሬ የሌላቸው ደካማዎች፣ ስግብግቦች፣ በቀላሉ የሚገዙ እና የሚሸጡ እንደዚሁም በተፈጥሯቸው መተባበር የማይችሉ ወይም ደግሞ በጋራ ሆነው ነገሮችን መፈጸም የማይችሉ አቅም የለሽ ስንኩላን ናቸው“ ብሏል፡፡
በሌላ አባባል የዘ-ህወሀት መሪዎች ኢትዮጵያውያን የተናገሩትን የማይፈጽሙ ፍጡሮች ናቸው የሚል አስተሳሰብን እንደሚያራምዱ ያምናሉ፡፡
የብሄራዊ ፓርክ አገልግሎት በሄለንስ ተራራ ላይ አስደማሚ የሆነው እና ባልተጠበቀ መልኩ የፈነዳው እሳተገሞራ ከመከሰቱ በፊት ይገልጹት እንደነበረው ገለጻ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ዘ-ህወሀት እና የድህነት አቃጣሪ ተባባሪዎቹ እንዲህ በማለት ላይ ይገኛሉ፣ “ኢትዮጵያ በዘ-ህወሀት አገዛዝ በዓለም ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ከሚያስመዘግቡት ሀገሮቸ መካከል በ4ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች…እናም ከምንም በላይ አስደናቂ የሆነው ነገር ደግሞ በአሁኑ ጊዜ እያስመዘገበችው ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገት በዚሁ መጠን የምታስቀጥል ከሆነ እ.ኤ.አ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ትሰለፋለች” በማለት ከተጨባጩ እውነታ 360 ዲግሪ በመራቅ እየቀላመዱ ነው ያሉት፡፡ (በእርግጥ እያንዳንዱ ሰው እንደሚያውቀው ሁሉ ዘ-ህወሀት እና የድህነት አቃጣሪ ተባባሪዎቹ እንደዚህ ያለውን ነጭ ውሸታቸውን እና ተራ የቅጥፈት አሀዛቸውን ከምንም ጥርጣሬ በላይ አስተማማኝ የሆነ መረጃ በማቅረብ ሳጋልጥ ቆይቻለሁ፡፡)
እ.ኤ.አ ግንቦት 2009 “የዘ-ህወሀት የአእምሮ በሽታ የስነልቦና ቀውስ“ በሚል ርዕስ አቅርቤው በነበረው ትችቴ ላይ ዘ-ህወሀት ባልጠበቀው ሁኔታ ከስልጣኑ ተሽቀንጥሮ እንደሚወድቅ አድርጌው የነበረው ትንበያ የሰጠሁት:: ይኸው በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ ሀምሌ 2016 ተፈጻሚነት እያገኘ የመሆኑን ምስክርነት በማየት ላይ እንገኛለን፡፡ በዚያን ወቅት እንዲህ የሚል ትንበያ ነበር የሰጠሁት፡
“[ዘ-ህወሀት] ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል የኢትዮጵያን ነብር (ወይም አንበሳ) በመጋለብ ላይ ይገኛል፡፡ ሆኖም ግን አንድ ቀን ከተፈናጠጡበት ነብር ላይ እንደሚወርዱ ያውቃሉ፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ
ዘ-ህዋሀት ጥርሶቻቸውን በማንገጫገጭ በመርበትበት የኢትዮጵያ አይን ያፈጠጡ ነብሮችን ያያሉ !“ ነበር ያልኩት፡፡
ላለፉት 25 ዓመታት ያህል በድን ሆኖ የቆየው እሳተገሞራ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር ላይ እየተንፈቀፈቀ፣ እያስገመገመ እና እያጉረመረመ ይገኛል፡፡ እናም ዘ-ህወሀት በእሳተገሞራው ላንቃ ጫፍ ላይ ተቀምጦ እንደሚገኝ እና በነበልባሉ ለመጋየት በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሆነ አሳምሮ ያውቃል፡፡ ዘ-ህወሀት ጭቆናውን፣ የግፍ እና የጭካኔ ድርጊቱን እያጠናከረ በመጣበት በአሁኑ ጊዜ ሙቀት እና ግፊቱ በኢትዮጵያ እሳተገሞራ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በመጨመር ላይ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የዘ-ህወሀት ዓይኖች የሚጉረጠረጡትን የነብር ዓይኖች እያዩ ከባድ መከራ ላይ ይገኛሉ፡፡ የነብሩን ዓይን ተጠንቀቁ! (ደስ የሚል ሁኔታ አይደለም እየታየ ያለው!)
እ.ኤ.አ መጋቢት 2015 አቅርቤው በነበረው ትችቴ ለበርካታ ዓመታት ስለው የነበረውን እንዲህ በማለት በድጋሜ ተናግሬ ነበር፡
“የዘ-ህወሀት መሪዎች በእርሳስ በተሞላ ፈንጅ ላይ የተቀመጡ መሆናቸውን ፍጹም በሆነ መልኩ ማወቅ እንዳለባቸው አምናለሁ፡፡ ቀደም ሲል ሳቀርበው እንደነበረው ሁሉ ዘ-ህወሀት ቤተመንግስቱን በአሸዋ ላይ ገንብቷል፡፡ ብቸኛ ጥያቄ ሆኖ የሚቀርበው በአሸዋው ላይ የተገነባው ቤተመንግስት የሚደረመሰው ጥልቅ በሆነው እና ደስታ በራቀው በህዝባዊ ማዕበል ነው ወይስ ደግሞ የህዝብ ቁጣን በተላበሰው አስገምጋሚ እና አውዳሚ አውሎነፋስ ነው የሚለው ነው፡፡ በየትኛውም ይሁን በየት ዘ-ህወሀት አፈር ድሜ በመብላት ወደ ታሪክ ቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ የሚጣል ይሆናል“ በማለት በማስትንቀቅ ተናግሬ ነበር፡፡
ዘ-ህወሀቶች እስከ አሁን ድረስ የማያውቁት ከሆነ ማወቅ የሚገባቸው እና እንደብረት የጠነከረ የማይሞት የታሪክ ሕግ አለ፡፡ እንዲህ የሚለውን ይህንን ሕግ የቀመሩት ማህተመ ጋንዲ ናቸው፣ “ጨቋኞች እና ገዳዮች ለጊዜው የማይበገሩ መስለው ይታያሉ፣ ሆኖም በመጨረሻ ሁልጊዜ ተንኮታኩተው ይወድቃሉ፡፡ ይህ የማይለወጥ እውንታ ነው” ነበር ያሉት፡፡
የዘ-ህወሀትን የመጨረሻ ፍጻሜ መተንበይ የለብኝም የለኝም፡፡ ዘ-ህወሀት እራሱ የእራሱን ዕጣ ፈንታ ከእኔ ትንበያ በፊት ተንብዮታልና፡፡
እ.ኤ.አ የ2005 የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ ከተካሄዱ ከአንድ ወር በኋላ እ.ኤ.አ ሰኔ 2005 በአንድ ወቅት የዘ-ህወሀት የኮሙኒኬሽን ሚኒስትር የነበረው እና እንደናዚ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንደ ናዚው ጎቤል በመዋሸት እና በቅጥፈት ከፍተኛውን ደረጃ የያዘው በረከት ስምዖን በዚያን ዓመት ተከስቶ በነበረው የምርጫ ቀውስ ሳቢያ ተቃውሟቸውን ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሰማት ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ወጥተው የነበሩ መሳሪያ ያልታጠቁ ዜጎችን የወሮበላው የዘራፊ ቡድን ስብስብ ቅጥር ነብሰገዳዮች በጥይት ግንባር ግንባራቸውን እና ደረታቸውን እየተመቱ ስለተጨፈጨፉት ወገኖቻችን የማስተባበያ መልስ ለመስጠት ሲያደርግ በነበረው የቅጥፈት አንደበቱ ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ይሏታል እንዲሉ ተቃዋሚዎች የጎሳ ግጭን ያስከትላሉ በማለት እንዲህ የሚል ትንበያ ሰጥቶ ነበር፡ “በተለያዩ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች መካከል የሚደረገው የህጻንነት ዓይነት ጨዋታ የሚመስል የጎሳ ጥላቻ እንደ ርዋንዳ ዓይነት የዘር ማጥፋት ፍጅት ሊያስከትል ይችላል“ በማለት ነበር ያሟረተው፡፡ ቀጣፊው በረከት በዚህም አላበቃም፡፡ እምቦቃቅላ የትምህርት ቤት ልጆችን እና ሰላማዊ ሴት እና አዛውንቶችን በጥይት እያስቆላ የመንግስትን ባንክ ሲዘርፉ ነው የተገደሉት በማለት እንደ ሀምሌ ሰማይ ተቀደደ፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 በሚስጥር በተቀረጸ ንግግር እና “በኢትዮጵያ የዘ-ህወሀት የፍጻሜ ታረክ?“ በሚል ርዕስ አዘጋጅቸው በነበረው ትንታኔየ ላይ ግልጽ አድርጌ ነበር፡፡ በረከት ስምዖን እና የእርሱ ግብረ አበር ጓደኛው የሆነው የዚያን ጊዜው “ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር” አዲሱ ለገሰ ግልጽ በሆነ መልኩ የዘ-ህወሀት ጊዜ እያለቀ መሆኑን እና የመጨረሻ ቀን እየመጣ መሆኑን ለዘ-ህወሀት ቡድን አባላት እና ለደጋፊዎቹ ተናግረው ነበር፡፡ አዲሱ እንዲህ በማለት በግልጽ ተናግሮ ነበር፡
“ከእኛ አንጻር ሁኔታውን ስንገመግመው ሁሉም ነገር ከእጃችን ወጥቷል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ምንም ዓይነት ጥያቄ አያስነሳም፡፡ የመምህራን ማህበር ምን እየሰራ እንደሆነ በግልጽ ማስተዋል እንችላለን፡፡ ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት መምህራን የእኛ አባሎች (የፓርቲያችን) ሲሆኑ እኛን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ የታሪኩ መጨረሻ ነው፡፡ አረና ፓርቲ ብቻ አይመስለኝም ግንቦት ሰባትም አለ ብዬ አስባለሁ፡፡ በባህርዳር ጸረ ጸረ ህወሀት የሆኑ በራሪ ወረቀቶች ተበትነዋል፡፡ ከተበተኑት ውስጥ ምንም ዓይነት በራሪ ወረቀት አላገኛችሁም? ሌሎች በስብሰባው ላይ የነበሩት በማቋረጥ ምላሻቸውን ሰጡ፡፡ በባህርዳር ውስጥ ወረቀቶች ተበትነዋል፡፡ እኛ ያንን ነገር አናውቅም ምን ለማለት እንደፈለግሁ ካወቅህ፡፡ በራሪ ወረቀቶች ተበትነዋል፣ እናም በተጨባጭ ታይተዋል፡፡ ስለሆነም እስከ ሴል ድረስ በመዝለቅ በየቦታው ተደራጅተዋል ብየ አስባለሁ፡፡ እራሱን ያደራጀ አንድ ኃይል እንዳለ አስባለሁ፡፡ ስለዚህ ከግንቦት ሰባት አካባቢ የመጣ እንደሆነ አድርጌ አስባለሁ፡፡“ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)
ህልሜዬ ሰላሟ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ማየት ነው፣
ይህንን ትችት የምጽፈው የዘ-ህወሀትን የግፍ ወንጀሎች፣ የዘፈቀደ ሰብአዊ እልቂቶች፣ ጭራቃዊ ባህሪያት፣ ሰይጣናዊነት እና በሙስና የመዘፈቅ እና የመጨማለቅ ድርጊቶችን ለመጥቀስ እና ለመኮነን አይደለም፡፡ የዘ-ህወሀትን ስርዓት ውዳቂነት በተጨባጭ የመዘገበ፣ ያጋለጠ፣ ሚስጥሩን ይፋ ያደረገ እና ያለምንም እረፍት የዘ-ህወሀትን ወንጀለኛነት ከእኔ የበለጠ የተቃወመ የለም ብዬ አምናለሁ፡፡
ይህንን ትችት የምጽፈው ለተለዬ ተግባር ነው፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ሊመለስ ከማይቻልበት ከወንዙ ጫፍ ላይ (ወይም በመካከል ላይ) የምትገኝ ሲሆን ከዚያ መስመር ውጭ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሁሉ ምንም ዓይነት ደህንነት የሌለበት እና ሰላማዊ ያልሆነ ነገር እንደሆነ ይታየኛል፡፡
ማንም ለመናገር የሚፈራውን ነገር እኔ ደፍሬ እናገራለሁ ምክንያቱም በስልጣን ላይ ተኮፍሰው በህዝብ ላይ ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ ለሚተገብሩ፣ የስልጣን ረሀብ እና ጥም ለተጣባቸው እና ለተጠናወታቸው እንዲሁም ምንም ዓይነት ኃይል ለሌላቸው ወገኖቻችን እውነታውን በመናገር ስራ ላያ ረጅም አመታት አሳልፈአለሁና፡፡
በኢትዮጵያ አድማስ ላይ እያንዣበበ ያለ የእርስ በእርስ ጦርነት ይታየኛል፡፡
ልድገመው! በኢትዮጵያ አድማስ ላይ እያንዣበበ ያለ የእርስ በእርስ ጦርነት ይታየኛል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ለአስር ዓመታት ያህል ቀን በቀን ስኳትንለት የቆየሁት የሰላማዕ ለውጥ ብትዮጵያ ግላዊ ተልዕኮ እንደ ጧት ጤዛ ከዓይኔ ላይ ብን ብሎ ከመጥፋቱ በፊት ሰላማዊ የሆነ የለውጥ ሽግግር አንድከሰት የምችለዉን ሁሉ ማድረግ ግዴታያኤ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የእርስ በእርስጥ ጥላቻ በምንም ዓይነት መለኪያ እና ደረጃ ላለፉት አስር ዓመታት ሳደርገው ለቆየሁት ለእያንዳንዷ ድርጊት ፍጹም በሆነ እና በአጠቃላይ መሸነፍ ስለሆነ ይህ ነገር እንዳይከሰት ሽንጤን ገትሬ እዋጋለሁ እንጅ በምንም ዓይነት መንገድ አልፈቅድም፡፡
በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ተሟጋችነች ለመታገል ገና በመጀመሪያ በወሰንኩ ጊዜ የኢትዮጵያን ቤት እያነደደ ያለውን የቋያ እሳት የተቻለኝን ሁሉ በማድረግ የማዳፈኛ ውኃ በማመላለስ እሳቱን ለማጥፋት እራሴን እንደ ትንሿ ዘማሪ ወፍ እንደሆንኩ አድርጌ አውጀ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ መጋቢት 2007 “ትንሿ ዘማሪ ወፍ እና የጫካው እሳት“ በሚል ርዕስ አንድ የተመሳስሎ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡
ያ ታሪክ በነበልባል እና በቋያ እሳት ተያይዞ በመንቦግቦግ ላይ የነበረውን የጫካ ሰደድ እሳት ለማጥፋት አንዲት ትንሽ ዘማሪ ወፍ በኩምቢዋ ውኃ እየያዘች ከወንዝ በማመላለስ ያንን የማይበገር የሚመስለውን የጫካ እሳት ቀስ በቀስ በማዳከም በመጨረሻም እንዲጠፋ ስላደረገችው ጀግና እና መንፈሰ ጠንካራ ትንሽ ዘማሪ ወፍ የሚያትት ትረካ ነው፡፡ (አንዲት ትንሽ ዘማሪ ወፍ እንደዚያ ያለውን ግዙፍ የጫካ ሰደድ እሳት ለማጥፋት እንዴት መሞከር ትችላለች የሚለው እውነታ በእራሱ አጠራጣሪና አስገራሚ አይደለምን?!)
ላለፉት አስር ዓመታት በየሳምንቱ በማዘጋጃቸው የሰኞ ትችቶቼ በኢትዮጵያ በዘ-ህወሀት እብሪተኛ እና የማንአህሎኝነት ርኩስ ባህሪ አማካይነት እየተቀጣጠለ የመጣውን እና የተቆለለውን የጎሳ ጥላቻ እና የኃይማኖት ጽንፈኝነት የፖለቲካ ቀውስና እና የኢኮኖሚ ውድመት በማምጣት ሀገሪቱን ይዞ ይዞ እንዳይሞት የተቀጣጠለውን እሳት ለማጥፋት ስሞክር ቆይቻለሁ፡፡ ከዚህ አንጻር በዚህ ተግባር ላይ በትንሹ ኩምቢዋ ውኃ ከወንዝ በመቅዳት እያመላለሰች አስገራሚ የነበረውን የጫካ ሰደድ እሳት ለማጥፋት እንደሞከረችው እና በስኬታማነት እንደፈጸመችው እንደ ትንሿ ዘማሪ ወፍ ውጤታማ ሆኛለሁ ብየ አስባለሁ፡፡
እ.ኤ.አ በ2007 የተናገርኩለት ያ የጫካ እሳት በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያን ቤት ለማቃጠል ባለ አምስት ማስጠንቀቂያ የእሳተገሞራ ደወል በመያዝ ወደ ኢትዮጵያ በመገስገስ ላይ ይገኛል፡፡
መልካም እና ጀግና የሆኑ ኢትዮጵያውያን ወንዶች እና ሴቶች ውድ ሀገራቸውን ከዚህ ከጥፋት ማዕበል ለማውጣት በአንድነት ሆነው መድረስ ካልቻሉ ምንም ዓይነት የኢትዮጵያ ቤት የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ ሊኖር የሚችለው አመድ እና አቧራ ብቻ ነው፡፡
እንደዚህ ያለ ውጤት ቢመጣ ዘ-ህወሀቶች ሲመኙት የነበረ እና አሁን ደግሞ ወደ እውነታነት እየተቃረበ በመሆኑ የሚያጡት ምንም ነገር የለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የወታደራዊ ኃይል ጌቶች በመሆናቸው የኢትዮጵያ ቤት የመቃጠል የወዲፊት ዕጣ ፈንታ ለእነርሱ ግዙፍ የሌሊት የህልም ቅዠት ይሆናል፡፡ ከዚያ ያለፈ የሚያሳስባቸው ነገር አይኖርም፡፡
በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ መካከል የሚኖረው የፖለቲካ ጥላቻ እጅግ በጣም የሚያሳስበኝ ይሆናል፡፡
እኔ እንደዚህ ያለውን ወራዳ የጥላቻ ነገር አልወደውም! አልወደውም! በፍጹም አልወደውም!
ዘ-ህወሀት ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ የጎሳ ጥላቻ እና የኃማኖት ጽንፈኝነት የድር ገመዱን አጠናክሮ ሲገምድ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን በቀቢጸ ተስፋነት ከአስርት ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲዘራው የቆየውን የጥላቻ አዝመራ ለማጨድ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡
ዘ-ህወሀት በአሁኑ ጊዜ በእራሱ የጥላቻ እና ጥልቅ የጥላቻ መረብ ውስጥ እራሱን ተብትቦ እንደሚገኝ ምንም ዓይነት ጥያቄ የለውም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ዘ-ሀወሀት እራሱን በጥላቻ እና በኃይል አዘቀቅት ውስጥ ቁልቁል ወደ መቀመቅ እየወረደ መሆኑን በመመልከት ላይ ይገኛል፡፡
ደ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዳሉት “ጥላቻ ጥላቻን ይወልዳል፣ ኃይል ኃልን ይወልዳል፣ የበለጠ ኃይል ሌላ የበለጠ ጠንካራ ኃይልን ይወልዳል…የመጨረሻው የኃይለኝነት ድክመት የሚያጠፋውን በመውለድ እየተጠማዘዘ ቁልቁል ወደ መሬት ውስጥ መውረድ ነው፣ ሰይጣናዊነትን ከማጥፋት ይልቅ የበለጠ እያባዛው ይሄዳል፡፡“
የዘ-ህወሀት ጥላቻ የበለጠ ጥላቻን ይወልዳል፣ የዘ-ህወሀት ኃይል የበለጠ ኃይልን ይወልዳል፣ እናም የዘ-ህወሀት ጠንካራ መሆን የኢትዮጵያ ህዝብ የበለጠ እንደ አረብ ብረት የጠነከረ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
በአራተኛ ደረጃ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በፍርሀት ጭንቀት ውስጥ እገኛለሁ፡፡ የዘ-ህወሀት አገዛዝ በድንገት ከመቅጽበት ቢደረመስ ነገሮች ሁሉ መልካም እንደሚሆኑ ተነግሮኛል፡፡ ተቃዋሚ ኃይሎች ሁሉ ወደ አንድ በመምጣት ስልጣንን በመቆጣጠር ነገሮችን ሁሉ ጥሩ ያደርጋሉ፡፡ እርግጠኛ አይደለሁም! ሁሉን ነገር እንደሚያውቅ የፖለተካ ሰው ሳይሆን እንደ ተጠራጣሪ ደህና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነው የምነጋገረው፡፡ የእኔ ዋናው ጭንቀት በኢትዮጵያ ውስጥ ህይወት እንዳይጠፋ መከላከል ነው፡፡ እውነት ለመናገር በብሉይ ኪዳን አስቴር እንደ ፐርሻ የአይሁድ ንግስት ህዝቧን ከእልቂት ለማትረፍ አንዳለችው “ለስንት ጊዜ ነው ምፃት ወገኖቼ ላይ ሲወድቅ ማየት የምቸለው? እንዴት አድርጌ ነው የወገኖቼን እና የመሰሎቼን እልቂት ለማየት ጽናቱ የሚኖረኝ?“ በማለት እጠይቃለሁ፡፡
ምናልባትም ጥቂቶች ተኩላ በሌለበት እንደተኩላ እንደምጮህ አድርገው ሊናገሩ ይችላሉ፡፡ ምናልባትም ቀበሮን በተኩላ አሳስቸ ተናግሬ ይሆናል ልሉም ይቺላሉ ፡፡
ሆኖም ግን በእርግጠኝነት ተኩላ አለ፡፡ ተኩላን በጎሳ ጥላቻ ጋቢ ውስጥ ተከናንቦ እየተመለከትኩት ነው፡፡ የጽንፈኝነትን ልብስ ለብሶ እያየሁት ነው፡፡ በበቀል፣ ተኩላ በከፍተኛ ቁጣ የተዥጎረጎረ ልብስ ለብሶ የጥቃት ጥፋቱን ለመጀመር እና ሰላማዊ ደኃ ህዝቦችን ለመጨረስ በማቆብቆብ ላይ እንደሚገኝ በማስተዋል ላይ እገኛለሁ፡፡
አዎ፣ ተኩላው ከበሩ ጋ ቆሟል፣ እናም እግሩን በኢትዮጵያ ቤት ላይ እንዳያቆም እና እንዳያጋይ ውኃ በመርጨት እንድ ትንሿ ዘማሪ ወፍ የምችለውን ማንኛውንም ነገር ሁሉ በጽናት አደርጋለሁ፡፡
ሆኖም ግን ሁልጊዜም በተስፋ የተሞላሁ ነኝ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የዘ-ህወሀት ጨለማ እንደ መርግ ተጋርዶ የሚገኝ ቢሆንም በመጨረሻው ሰዓት ጨለማው ከኢትዮጵያ ሲገፈፍ እንደ ገና በብርሀን ያሸበረቀ ጧት እንደሚመጣ ሁልጊዜ አምናለሁ፡፡
እ.ኤ.አ ሀምሌ 2012 “ሰላሟ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ማለም” በሚል ርዕስ ረዘም ያለ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡
ያ ትችት የእኔ ጀግና ለሆኑት ለኔልሰን ማንዴል የ94ኛ ዓመት የልደት በዓልን በማስመልከት ጀግናውን የሰላም ፖለቲከኛ ለማሞካሸት ያዘጋጀሁት ጽሁፍ ነበር፡፡ በዚያም ትችቴ ላይ እንዲህ የሚል ጽሁፍ አቅርቤ ነበር፡
“ኢትዮጵያን እንደገና ወደነበረችበት መልካም ሁኔታ ለመመለስ በፖለቲካ ኃይሉ አዳራሾች፣ በቢሮክራሲው በሮች እና በወታደራዊ ካምፖች አካባቢ ብቻ የታጠረ ሳይሆን በሀገሪቱ በሩቅ አካባቢ በሚገኙ መንደሮች፣ በቤተክርስቲያኖች እና መስጊዶች አዳራሾች እና በሌሎች የእምነት ቦታዎች፣ በትምህርት ቤቶች እና በኮሌጆች፣ በጎረቤት ማህበራት እና ካፊቴሪያዎች፣ በየመንገዶች እና በየገበያዎች እንዲሁም ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ጭምር ብሄራዊ ውይይት ማድረግ አለብን፡፡ ምንም ዓይነት ምርጫ የለንም ሆኖም ግን በመልካም መንፈስ እና በሙሉ እምነት መነጋገር መጀመር አለብን“ ብዬ ነበር፡፡
ባለፉት ዓመታት ውስጥ ስለእውነት እና ዕርቀሰላም በርካታ ትችቶችን ጽፌ አቅርቢያለሁ፡፡
እ.ኤ.አ መስከረም 2013 “የሰላማዊ የለውጥ ሽግግር ዴፕሎማሲ በኢትዮጵያ“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት ሰላማዊ የለውጥ ሽግግር እና ዕርቀሰላምን ለመጎናጸፍ እንዲቻል በዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግን ትምህርቶች ላይ ገለጻ አድርጊያለሁ፡፡
በዚህ ትችቴ ላይ ለማስተላለፍ የፈለግሁት ዋናው ዓላማ በአሁኑ ጊዜ በአስቸኳይ ሁኔታ ተቀራርቦ እርስ በእርስ በጥሩ መንፈስ እና በጽኑ እምነት ላይ በመመስረት መነጋገር እንዲጀመር ምች ሁኔታ እንዲፈጠር ለማድረግ ነው፡፡
በእርግጥ እንደ አንድ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ስልጣን ፍላጎት እንደሌለው እና እንደ አንድ እረፍትየለሽ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሰው እራሴን ለመግለጽ ወይም ደግሞ ሁልጊዜ ለማለት እንደምፈልገው በስልጣን ላይ ላሉት እና ከሕግ አግባብ ውጭ ለሚሰሩት፣ የስልጣን ረሀብ ላለባቸው፣ ምንም ኃይነት ኃይል ለሌላቸው እና እኔ የማስተምረውን ትምህርት ለመስማት ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ለማስተማር እና ለመናገር ምሁራዊ ነጻነት አለኝ፡፡
በአሁኑ ጊዜ እውነት የምንናገርበት ጊዜ ነው፡፡ እውነቱን እናገራለሁ፡፡
እኔ እንደማየው ከሆነ መመለስ ያለበት እንዲህ የሚል አንድ እና አንድ ጥያቄ ብቻ አሌ፡፡ እርሱም እንዲህ የሚል ነው፡ “በአሁኑ ጊዜ እራሳችን ከቆፈርነው ጉድግዋድ ማጥ ውስጥ በድል አድራጊነት ለመውጣት ምን ማድረግ አለብን?“ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሊሆን የሚችል እና እንዲህ የሚል አንድ እና አንድ ብቻ መልስ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ሰጥተውናል፡ “እንደ ወንድማማች እና እህትማማች በአንድነት መኖር አለብን ወይም ደግሞ አብረን እንጠፋለን“ ነበር ያሉት፡፡
እኔ በበኩሌ በአንድነት ከመጥፋት ይልቅ ወንድማማች እና እህትማማች በመሆን በአንድነት መኖርን እመርጣለሁ፡፡
አሁን በቅርቡ በቀድሞው የዘ-ህወሀት ጄኔራል በጻድቃን ገብረትንሳኤ በአማርኛ የተጻፈ ትችት ስለዘ-ህወሀት አገዛዝ ሰፊ ትንታኔ ከሰጠ በኋላ የመፍትሄ ሀሳብ በሚል ርዕስ ኢትዮጵያን ከእርስ በእርስ የጦርነት አዘቅት ውስጥ (በእርግጥ ይህንን ሀረግ በትክክል ደፍሮ ባይጠቀምበትም) ማውጣት በሚል ማሳረጊያ ሀሳቡን ደምድሟል፡፡
ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ ሲንጸባረቅ የነበረውን፣ የመልካም አስተዳደር እጦትን፤ የፍትህ እጦትን፣ ሙስናን፣ ስልጣንን ከህግ አግባብ ውጭ መጠቀምን፣ የሰብአዊ መብቶችን መደፍጠጥን፣ የሕግ የበላይነት ያለመስፈንን፣ በአገዛዙ ላይ የሚታየውን የህዝባዊ ደስታ እጦትን፣ በዘ-ህወሀት ውስጥ ውስጣዊ ስምምነት ያለመኖርን፣ በስልጣን ላይ ለመቆየት ወታዳራዊ ኃይል መጠቀምን፣ እና የዘ-ህወሀት ወታደራዊ የእንዱስትሪ ኮምፕሌክስን ማጠናከርን ወዘተ – ጨምሮ እውነታዊ የዘ-ህወሀትን ባህሪ እና ተሞክሮ በሚገባ ከገለጸ በኋላ ጻድቃን በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ ውስጥ የሚታየውን ፖለተካዊ ሁኔታ ከግንዛቤ በማስገባት በተለያዩ ደረጃዎች በሀገሪቱ ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ሶስት ቢሆኖችን/Scenarios በመዘርዘር አቅርቧል፡፡
በመጀመሪያው የቢሆን ክስተት/scenario ጻድቃን በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ ውስጥ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ሁኔታ ከውጭ ኃይሎች ከሚደረገው ቅስቀሳ ጋር ህብረት በመፍጠር የዘ-ህወሀት አገዛዝ መፍረስ እና መጥፋት ሊፈጠር ይችላል በማለት ትንበያ ሰጥቷል፡፡ ይኸ የቢሆን ክስተት የመፈጸም ዕድሉ በጣም ጠባብ የሆነ እና የመፈጸም ዕድሉ ግን ዜሮ እንዳልሆነ እንደሚያምን ግልጽ አድርጓል፡፡ በቅርቡ በአሮሚያ ውስጥ ተከስቶ የነበረውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ዘ-ህወሀት በፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች ያስቆመው መሆኑን እና በክልሉ አቅም ግን የማይቻልበት ሁኔታ ተከስቶ እንደነበር ጠቁሟል፡፡
በሁለተኛው የቢሆን ክስተት/scenario ጻድቃን ዘ-ህወሀት የተወሰኑ የማሻሻያ ለውጦችን በማድረግ ጊዜ ለመግዛት እና አገዛዙን ለተወሰነ ጊዜ ለማራዘም ይቻል ይሆናል የሚል ትንበያ ሰጥቷል፡፡ ይኸ ስልት ሁኔታውን ለማዘግየት እንጅ አደጋውን እንደማያስቀረው እና ከመውደቅ ሊድን እንደማይችል ጻድቃን እንደሚያምን ግልጽ አድርጓል፡፡ በእርግጥ ይህ የቢሆን ክስተት አደገኛ የሆነ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ስር በመስደድ ሰላማዊ ለውጥ እንዳይመጣ በመከልከል ለስሌት የከበደ ምስቅልቅለል ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል ያምናል፡፡
የጻድቃን ሶስተኛው የቢሆን ክስተት/scenario ያቀረባቸው የሁሉም ቢሆኖች ዋና ምሰሶ እንደሆነ አድርጎ አስቀምጦታል፡፡ በአሁኑ ጊዚ ያለውን መጥፎ ሁኔታ ለማስወገድ ያለው የተሻለው አማራጭ በቅንነት ከልብ ለለውጥ እና ስርዓት መገዛት ነው የሚል የክርክር ጭብጥ አቅርቧል፡፡ ይህም ማለት በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ውስጥ ያለው ፖለቲካ በቀውስ ውስጥ መሆኑን በማመን ይህንን ቀውስ ለመፍታት የሕገ መንግስቱን ሂደት በመከተል መንገድ መፈለግ አለብን ይላል፡፡
ጻድቃን እንደመፍትሄ በማለት ጥቂት የመፍትሄ ሀሳቦችን አቅርቧል፡፡ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ማስፋት አስፈላጊ ነው ይላል፡፡ የግል እና የቡድን የፖለቲካ መብቶች ሙሉ በሙሉ መመከበር ይኖርባቸዋል የሚል ሀሳብ አቅርቧል፡፡ ዜጎች ሀሳቦቻቸውን የመግለጽ፣ የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ እንዲችሉ እና ቅሬታዎቻቸውን ሊገልጹበቸው የሚገቡ መንገዶች ሊኖሩ እንደሚገቡ ጠቁሟል፡፡ እንደዚህ ያሉት እንቅስቃሴዎች ወደ ነጻ እና ፍትሀዊ ምርጫ ይመራሉ ብሏል፡፡ በእዚህ አካባቢዎች ክህሎቶች ያላቸው ዜጎች እነዚህን መንገዶች የማመቻቸት ስራ መስራት ይኖርባቸዋል የሚል ሀሳብ አቅርቧል፡፡
በእነዚህ መልካም በሆኑ ሀሳቦች ላይ ምንም ዓይነት ተቃውሞ የለኝም፡፡ ከሁሉም በላይ በእነዚህ ሀሳቦች ላይ ላለፉት አስር ዓመታት ሳምንት በሳምንት አንድም ሳምንት ሳላሳልፍ አጽንኦ በመስጠት ስላቸው እና ስታገልላቸው የቆየሁባቸው ናቸው፡፡
እ.ኤ.አ መጋቢት 2012 “ኢትዮጵያ፡ ከአምባገናነዊነት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት“ በሚል ርእስ ባቀረብኩት ትችትና እንደዚሁም ደግሞ እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2012 “የሕግ የበላይነት በኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት“ በሚል ርዕስ እና ሌሎችን በርካታዎችን ትችቶቸም በየጊዜው በማቅረብ ስገልጽ እና ስማጸን ቆይቻለሁ፡፡
በኢትዮጵያ የዲያስፖራ ማህበረሰብ ሁኔታ ላይ ጻድቃን የተደበላለቀ ስሜትን አንጸባርቋል፡፡
በርካታ አስተያየት ሰጭዎች እርሱን በግል ስብዕናው እንደዚሁም ባቀረባቸው ሃሳቦች ላይ በመመስረት ጥልቅ የሆኑ ትችቶችን አቅርበዋል፡፡ ጥልቅ ከሆኑ ትችቶች መካከል ለናሙና ያህል የሚከተሉትን በመጭመቅ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
ጻድቃን በእርሱ ትንታኔ ላይ ባቀረባቸው ሀሳቦች አማካይነት የህዝቡን ምላሽ ለመገምገም እና የአየር የሙቀት ግለት ሁኔታውን ለመለካት ሲል ዘ-ህወሀት የላከው የፊኛ ከረጢት የተልዕኮ መልዕክተኛ ነው፡፡
ዘ-ህወሀት የተቃውሞ እና የመገዳደር ችግር እጅ ከወርች ቀስፎ ይዞት በማዕበል ውስጥ ለመስመጥ እያተጣጣረ ባለበት ሁኔታ ለዘ-ህወሀት የህይወት አድን የመዋኛ ፊኛ ለመወርወር ሙከራ በማድረግ ላይ የሚገኝ ነው፡፡
ለዘ-ህወሀት የአገዛዝ እድሜ መራዘም እና የበለጠ ጊዜ ለመስጠት እና ለመሸመት ጸሐይ ከጠለቀች በኋላ የመፍትሄ ሀሳብ ለማቅረብ የመጣ መልዕክተኛ ነው፡፡
ዘ-ህወሀት ሁልጊዜ በሚጥሰው እና በሚደፈጥጠው የእዩልኝ እምኑልኝ የይስሙላ ሕገ መንግስት በመመራት በሀገሪቱ ውስጥ ሰላማዊ እና ስርዓት ያለው ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያቀረበው ሀሳብ ታማኝነት እና ቅንነት የጎደለው ህዝብን የማጭበርበር ዕኩይ አካሄድ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አጠቃላይ ውድቀት የይስሙላውን ሕገ መንግስት ካለመተግበር ነው ብሎ ማመን የተሳሳተ እና ምዕናባዊ ሀሳብ ነው፡፡
የአገዛዙ አካል እና ዋና አባልም የነበረ ሰው አሁን የሚያደርገው ትችት በተቃዋሚዎች እና በሕዝቡ ዘንድ ተማዕኒነትን ለማትረፍ ሲባል ለማስመሰል ሲል የሚያደርገው የይስሙላ እና የውሸት ትችት ነው፡፡
ባለፉት 25 ዓመታት በአምባገነናዊ አገዛዙ ለተፈጸሙት ለቁጥር የሚያዳግቱ ወንጀሎች እና ጥፋቶች ምንም ዓይነት የተጠያቂነት ሀሳብ ሳያቀርብ እንዲሁ በደፈናው ምንም ዓይነት አመክንዮ ሳያስቀምጥ ያለፈው አልፏል እናም ከዚህ በኋላ በአዲስ መልክ እንጀምር የሚል የተማጽዕኖ ሀሳብ ማቅረብ በየጊዜው በጠፉው የወገኖቻቸን ህይወት እና በወደመው የሀገራችን ሀብት እንዲሁም ክህደት በተፈጸመባት እና ሉዓላዊነቷ እንዲደፈር በተደረገችው ሀገራችን ላይ የመቀለድ እና የመሳለቅ አባዜ ነው፡፡
ዘ-ህወሀት የፈጠረውን እና ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ ቀስ በቀስ እንዲያድግ ያደረገውን አውዳሚ የሆነውን የጎሳ ፖለቲካ ያገጠጠ እና ያፈጠጠ እውነታነት ከልብ የተቀበለው አይደለም፡፡
ዘ-ህወሀት የፈጠረውን የጎሳ እና የከፋፍለህ ግዛ መደብ እና በዚያ ውስጥ ሆኖ እየዋሸ ያለ የመሆኑን እውነታ የተቀበለው አይደለም፡፡
ለእርሱ ትንታኔ አድናቆት የሚሰጡ እና ያቀረባቸው ሀሳቦች ጥሩ መሆናቸውን የሚመሰክሩ ጥቂት ሰዎች አሉ፡፡
ያቀረባቸው ሀሳቦች ጥሩ ሀሳቦች ናቸው ብለው የሚያምኑት ሰዎች በኢትዮጵያ ውስጥ በድብቅ ላሉት በርካታ እና አደገኛ ችግሮች ቅንነት የተሞላባቸው መፍትሄዎች ናቸው በማለት አድናቆት ይሰጡታል፡፡ ሌሎች ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ጻድቃን የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ የዳሰሰ እና ልዩ የሆነ ነው የሚል ሀሳብ ያቀርባሉ፡፡
በጻድቃን የቀረቡት ጥልቅ የግምገማ ትንታኔዎች እና ሃሳቦች በአመክንዮ ላይ የተመሰረቱ፣ ሕጋዊ እና ተስማሚ መሆናቸውን አምናለሁ፡፡
ጻድቃን ባቀረበው አጠቃላይ ጥልቅ ትችት ላይ የእራሴን አዲስ ሀሳብ ለመጨመር የሚያስችል ሁኔታ ይታየኛል፡፡
ሆኖም ለታሪክ ምዝገባ ሲባል ጻድቃን ባቀረበው ዋና ሀሳብ እና በዋና አቋሙ ላይ በስም የኢትዮጵያ ችግሮች በዘ-ህወሀት ሕገ መንግስት ማዕቀፍ ስር መፍትሄ ያገኛሉ የሚለው አስተሳሰቡ እና አቋሙ ዋና መቃወሚያ ሆኖ እንዲመዘግብልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ይህ ቧልትና ቀልድ ነው ።
ከዚህ በታች እንደምገልጸው እውነተኛው የችግር መፍትሄ በቀላል በአንድ ፊርማ ድርጊት የሚጀመር ይሆናል፡፡
በእርግጥ በዘ-ህወሀት ላይ ያሉኝ አመለካከቶች በሚገባ ይታወቃሉ፡፡
አሁን በቅርቡ እ.ኤ.አ ግንቦት 22/2016 “ኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ያስፈልጋታልን?“ በሚል ርዕስ አዘጋጅቸው ነበበረው ትችት እራሴን በመጥቀስ “የዘ-ህወሀት ሕገ መንግስት በታሪክ ቅንነት የጎደለው እና በሸፍጥ ከታጀቡት ሕገ መንግስቶች መካከል አንዱ ነው“ ከዚህ በላይ ሌላ መጨመር ያስፈልገኛልን?
ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ በግልጽ እንደሚታየው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ እጅግ የሚያሳስብ ነው ከሚለው ሀሳቡ ጋር ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ፡፡ በቁጥር ስሌት ሊተመን የማይችል የጥፋት አደጋ ከመድረሱ በፊት በሰለጠነ መልኩ በአንድ ላይ በመሆን በመወያየት ችግሮችን እንፍታ፡፡ ከዱሮ ወይም ደግሞ በአሁኑ ጊዜ የዘ-ህወሀት አባላት በአንድ ላይ በመቀመጥ በሰለጠነ መልኩ ችግሮችን እንፍታ የሚል የተማጽዕኖ ቃል መስማት ልክ አንድ ያልሰለጠነ ጋጠወጥ በጥባጭ የሕግ የበላይነት ይከበር የሚል የተማጽእኖ ቃል እንደሚያሰማው ደስ የማይል ዓይነት ስሜት እንደሚሰማኝ ማመን አለብኝ፡፡ በቃ ይኸው ነው እወቅና ሰጥቻለሁ!
ሆኖም ግን ከተቃዋሚዎቼ ጋር ግለጽ የሆነ ክርክር እና ውይይት በማድረግ ተግባር ላይ አምናለሁ፡፡ ሁሉም ሀሳቦች የተቃዋሚዎቼ ሀሳቦች ጭምር በነጻ ያለምንም አፈናና ገደብ መገለጽ እንዲችሉ አምናለሁ፡፡
አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ መስከረም 2010 በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በመገኘት የእራሱን ሀሳብ መግለጽ እንዲችል ጥልቅ ጥላቻ ያደረባቸው የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት እንዴት ለመለስ መብት መጠበቅ ትቆማለህ በማለት ውግዘት ቢያደርሱብኝም ለመለስ ሀሳቡን የመግለጽ መብት መከበር ሽንጤን ገትሬ በመቆም ስከራከር እንደነበር በርካታዎቹ አንባቢዎቼ የሚያስታውሱት ጉዳይ ነው፡፡
አሁን በህይወት የሌለው ወሮበላ ዘራፊ የነበረው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ግን በህይወት ሳለ እንዲህ ይል ነበር፣ “ከተቃዋሚዎች ጋር መነጋገር ፈጽሞ አይቻልም፡፡“
መለስ ይህንን ሲናገር ፍጹም ስህተት ነበር፡፡ እውነተኛው ነገር ግን ከዘ-ህወሀት ጋር በጠብመንጃ አፈሙዝ ካልሆነ ተቀራርቦ መነጋገር አይቻልም የሚለው ነው፡፡
አምባገነኑ መለስ በህይወት በነበረበት ጊዜ እና ዘ-ህወወሀት የተቃዋሚ መሪዎች፣ ሰላማዊ አመጸኞች እና ተቃዋሚዎች በሙሉ የእነርሱ ምሁራዊ የበታቾች እንደሆኑ ያምኑ እንደነበር ሁልጊዜ የማምንበት ጉዳይ ነው፡፡ እነርሱ፣ እንደሚልቁ፣ እንደሚበልጡ፣ እንደሚማርኩ፣ በብልጠት እንደሚያሸንፉ እና በማንኛውም የሳምንቱ ጊዜ ሁሉን ነገር ማድረግ እንደሚችሉ ያምናሉ፡፡ ተቃዋሚዎች ተስፋ በቆረጠ ሁኔታ የተከፋፈሉ፣ መስራት የማይችሉ ተነሳሽነት የሌላቸው እና ምንም ዓይነት ጥቅም የሌላቸው እና የእርሱን ስልጣን በመገዳደር ችግር መፍጠር በፍጹም የማይችሉ እርባናየለሾች ናቸው የሚል እምነት ነበረው፡፡
እንደዚህ ዓይነት እብሪተኞች ለእራሳቸው ሌላ ምንም ሳይሆን ንቀት እና ጥላቻን ነበር የሚያሳዩ፡፡ ተቃዋሚዎችን ታማኝ እንዳልሆኑ እና ቁጥጥር በማይደረግባቸው ልጆች ላይ ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲገቡ በየጊዜው ክትትል፣ የስነስርዓት እርምጃ እና ቅጣት እንደሚያስፈለጋቸው ልጆች አድርገው ነበር የሚቆጥሯቸው፡፡ እንደ ልጆች ሁሉ ለጥቂቶቹ ከረሜላ፣ ስራ፣ ቤት እና እነርሱን ጸጥ የሚያደርግ ማንኛውንም ነገር ይሰጧቸው ነበር፡፡ እንደነዚህ ጸጥ የማይሉ ተቃዋሚዎች ካሉ ማስፈራሪያ ይደርሳቸዋል፣ ተከታታይነት ባለው ክትትል ውስጥ እንዲቀመጡ እና እንዲሰቃዩ ይደረጋሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ተቃዋሚዎችን ለማሞኘት እና ለማታለል ይሞክራሉ፡፡
ስለሆነም ከቀድሞም ሆነ በአሁኑ ጊዜ ካሉት የዘ-ህወሀት አመራሮች ጋር በመቀመጥ ውይይት የማድረግ ዘዴ ወይም ደግሞ በታማኝነት፣ በቅንነት፣ በመከባበር እና ከልብ በመነጨ መልኩ ተወያይቶ ለቁም ነገር ይደረሳል የሚል ቅዠት በፍጹም የለኝም፡፡
ሆኖም ግን በሰላማዊ መንገድ ለሚደረግ ለውጥ እንደሚያምን ጠንካራ ሰው ያለው ማንም ሰው በይፋ፣ ግልጽ በሆነ እና እና ግልጽነት ባለው ሁኔታ ከተቃዋሚው ጋር መወያየት አለበት በሚለው ፍልስፍና ላይ እራሴን አስገዛለሁ፡፡
በመጀመሪያ ጥቂት ማስገንዘቢያዎች፣
ጻድቃን ገብረትንሳኤን አላውቀውም፡፡
ስለእርሱ ጥቂት የማውቀው ነገር ቢኖር ተቃዋሚዎች የዳሰሳ የምርምር ጥናት አድርገው ያገኘሁት የመጀመሪያ ደረጃ መረጃ ነው፡፡
የተቃዋሚዎች ምርምር ጻድቃን የዘ-ህወሀት ጀኔራል በመሆን የጦርነት ወንጀሎችን የፈጸመ እና ከዘ-ህወሀት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ የህዝብ ሀብት የዘረፈ መሆኑን ነው፡፡ በሕብር ስኳር አክሲዮን ማህበር ኩባንያ ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ ያለው እና ሌሎች ትርፋማ የሆኑ ሀብቶችን ሁሉ ተቆጣጥሮ የሚገኝ ሰው ስለመሆኑ ነው፡፡
በግንኙነት መስመር ድረ ገጽ በተለቀቀ ወረቀት በራስጌው ላይ ዓለም አቀፍ የቼክ ሬፐብሊክ የንግድ ማሕበር/International Chamber of Commerce የሚል ሎጎ ያለበት በባላርማ ወረቀት ላይ የተለቀቀውን የጻድቃንን ቀን የሌለውን ሲቪ/CV (የስራ ልምድ ዝርዝር) ገምግሚያለሁ፡፡
በሲቪው ላይ ጻድቃን የራያ ቢራ አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሊቀመንበር፣ ደቡብ ሱዳን የሚል ተመዝግቦ ይታያል፡፡
በሲቪው ላይ የተገለጹት ፕሮፌሽናል ሙያዎች በዋናነት ወታደራዊ ግዳጆች ቢሆኑም በብሄራዊ ደህንነት ላይ የኤች አይቪ እንደምታ/Impact of HIV/AIDS on National Security በሚል ርዕስ አጠናሁት ያለው የምርምር ስራ ዋቢዎች ናቸው የተባሉ ሰዎች እንዳሉ እና በኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኤችአይቪን ስርጭት የመከላከል ፕሮግራምን/Program to Combat HIV/AIDS in the Ethiopian National Defense Forces በመተግበር ስራ ላይ ተሳትፎ ያለው መሆኑን ያመላክታል፡፡
ጻድቃን የሰራቸው የፖለቲካ የጽሁፍ ስራዎች ወይም ትንታኔዎች ካሉ በሚል እሳቤ በድረ ገጽ የግንኙነት መስመር ለማየት የሞከርኩ ቢሆንም ባለማግኘቴ ስኬታማ ሳልሆን ቀርቻለሁ፡፡
በዚህ በአሁኑ ጊዜ ውስጥ የእርሱን የቅርብ ጊዜ ጽሁፍ በማግኘቴ በመጠኑም ቢሆን ተገርሚያለሁ፡፡ ለእራሴ እንዲህ በማለት አስቢያለሁ፣ “ይህንን ትነታኔ እና የመፍትሄ ሀሳብ ይዞ ለመውጣት እንደዚህ ያለ ረዥም ጉዞና ጊዜ የፈጀበት ለምንድን ነው ? ለመሆኑ ላለፉት በርካታ ዓመታት ሁሉ ጻድቃን የት ነበር? ምንስ ሲያደርግ ነበር?“
ጻድቃን በሰጠው ትንታኔ እና ባቀረበው የመፍትሄ ሀሳብ እንደ ግል ሰው እራሱን ወክሎ ስመናገር አለመናገሩ፣ የዘ-ህወሀትን ስሜት እያስተጋባ ስለመሆን አለመሆኑ ወይም ደግሞ የሙከራ ባሉን ፊኛውን ወደ አየር ለሙከራ እንዲለቅ ታዝዞ ይሁን አይሁን የማውቀው ነገር የለም፡፡
በተገለጹት ሀሳቦች ላይ ግልጽ በሆነ መልኩ በቀጥታ ወይም ግልጽ ባልሆነ መልኩ በተዘዋዋሪ መንገድ በዘ-ህወሀት ይወከል አይወከል የማውቀው ነገር የለም፡፡
እስከ አሁን ድረስ እርሱ ያቀረበውን ትንታኔ እና የመፍትሄ ሀሳብ ይፋ በሆነ መልኩ የተቼ ወይም ደግሞ ትክክለኛ መሆኑን በመደገፍ አስተያየት የሰጠ ከዘ-ህወሀት ምንጭ በእርግጠኝነት አላነበብኩም፡፡
ጻድቃን የእርሱን የመፍትሄ ሀሳቦች በእራሱ እምነት የሰጠ ስለመሆን አለመሆኑ ወይም ደግሞ የእጅ ጽሁፎችን በትላልቅ/ካፒታል ፊደሎች ተጽፈው ከግድግዳ ላይ አንብቦ ያጠናቀረው ስለመሆን አለመሆኑ የማውቀው ነገር የለም፡፡
በዘ-ህወሀት አገዛዝ ላይ የተደረገው የጻድቃን ጥልቀት ያለው የትንታኔ ግምገማ ከቅን ልቦና የመነጨ ስለመሆን አለመሆኑ ወይም ደግሞ የአዞ እንባውን ለማንባት ከማሰብ የቀረበ ስለመሆን አለመሆኑ የማውቀው ነገር የለም፡፡
ጻድቃን በመጨረሻዋ ሰዓት ሙከራው ይህንን የመሰለ ትንታኔ እና የመፍትሄ ሀሳብ ያቀረበው የእራሱን፣ የዘ-ህወሀትን አባላት እና የደጋፊዎችን ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ለመጠበቅ ሲባል ያዘጋጀው ጽሁፍ ስለመሆን አለመሆኑ የማውቀው ነገር የለኝም፡፡
ጻድቃን ጥልቀት ያለው የንግግር አንደበትን በመላበስ እራሱን ዝግጁ ለማድረግ ያስብ ወይም አያስብ ወይም ደግሞ የአእምሮ ጨዋታ ለመስራት ያዘጋጀው ስለመሆን አለመሆኑ የማውቀው ነገር የለም፡፡
እኔ ለዘ-ህወሀት የዜሮ ድምር ጨዋታዎች አዲስ አለመሆኔን ብቻ ነው የማውቀው፡፡
ከተሟላ አክብሮት ጋር ጻድቃን ይህንን ጽሁፍ እራሱ የጻፈው ስለመሆን አለመሆኑ ወይም ደግሞ በኮሚቴ በተጻፈ ጽሁፍ ላይ የእራሱ ስም ሰለመለጠፍ አለመለጠፉ የማውቀው ነገር የለም እላለሁ፡፡ (የእያንዳንዱን ሰነድ ሕጋዊ ባለቤትነት የመመርመር ሙያ ለሕግ ባለሙያ የተሰጠ ነው፡፡)
ለማለት የምፈልገው ነገር ቢኖር ጻድቃን በትንታኔው እና በቀረበው ሀሳብ ላይ የአጨዋችነት መንፈስን ለመጫወት ሞክሮ ከሆነ ጊዜውን እና ቀለሙን በከንቱ አባክኗል፡፡
እ.ኤ.አ ግንቦት 2011 “ኢትዮጵያ፡ የወይራ ዝንጣፌን ከያዙ ሰዎች ተጠንቀቁ!“ በሚል ርዕስ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡ ያ ትችት እ.ኤ.አ በ2010 ተደርጎ በነበረው የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ አምባገነኑ መለስ ዜናዊ 99.6 በመቶ የምርጫ ድምጽ ድልን ተቀዳጀሁ በማለት ዓይን ባወጣ ቅጥፈት በመመራት ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋር እንደራደራለን እያለ ያፌዝ ስለነበረው የቀልድ ጨዋታ የጻፍኩት ነበር፡፡ ወቼ ጉድ ድንቄም መደራደር፡፡ መደራደር ሳይሆን ምናልባትም ተቃዋሚዎችን እና ህዝቡን መገዳደር ሊሆን ይችላል፡፡
የጻድቃን የመፍትሄ ሀሳቦች ሌላኛው የአምባገነኑ የመለስ የወይራ ዝንጣፊ ዓይነት አካሄድ ከሆነ ልለው የምችለው መልካም ነው የሞክረው፡፡ ግን ፋይዳ ቢስ ነው ! የሚል ነው፡፡
የሕገ መንግስት ባለሞያ የሆነን የሕግ ሰው አንዲህ በቀላሉ ማታለል ምናልባትም ይሆናል ብየ አምናለሁ፡፡
ስለጻድቃን ያለኝን እንዲያው ዋናውን ብቻ በመውሰድ ያለኝን አጠራጣሪ ዓላማ እና ሀሳብ ከገለጽኩ በኋላ አሁን ደግሞ ውይይት ማድረግ እንዲቻል የእራሴን ቀላል የሆኑ ሀሳቦችን አቀርባለሁ፡፡
ጻድቃን ወይም ደግሞ ዘ-ህወሀቶች ቅንነነትን የተላበሰ ውይይትን በማድረግ ኢትዮጵያን ከአደገኛ ጥፋት ለማዳን ከፈለጉ (ጥቂቶች ኢትዮጵያን ከዘ-ህወሀት ለማዳን ይላሉ) የመጀመሪያው ነጥብ ብዙ በመነጋገር ምንም አለማድረግ አይደለም፡፡ (ወሬ ፍሬ ከርስኪ ነው)።
ሆኖም ግን ከአንድ ነጠላ ፊርማ በላይ የማይጠይቅ ቀላል ነገር ማድረግ ነው፡፡ ሰዎች “አንድ ግራም ተግባር በበርካታ ቶኖች ከሚቆጠሩ ሰበካዎች የበለጠ ነገር ነው” ይላሉ፡፡ የሚሰማ ጆሮ ይስማ!
ጻድቃን እና ዘ-ህወሀት ለመነጋገር ከፈለጉ መነጋገር የሚጀመሩት ቃላትን በመወርወር ብቻ አይደለም፣ ተጨባጭ ተግባርን በማሳየት ነው፡፡ ድርጊት ከቃት ይበልጣል ይባላልና፡፡
የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታት ወሳኝ በሆነ እና በማይቀለበስ መልኩ ልዩ የሆነ ዓላማን በመሰነቅ በአንድ ላይ በመሰባሰብ በአስቸኳይ መሰራት ያለበት አንድ እና አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ይኸውም፡ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች መፍታት፣ አሁኑኑ! መሳሪያ ያልታጠቁ የሰላማዊ ተቃዋሚዎችን እልቂት ማቆም፡፡ ሰላማዊ ሰዎችን በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር ማወልን፤ ስልጣንን ከሕግ አግባብ ውጭ መጠቀምን፣ ሰላማዊ አማጺዎችን፣ ጋዜጠኞችን እና የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን እና አባላትን ማሸማቀቁን ማቆም፡፡
ምንም ዓይነት ትንሽ መተማመን ባልተመሰረተበት ሁኔታ ምንም ዓይነት ውይይት ወይም ደግሞ ግንኙነት ሊኖር አይችልም፡፡ በተቀናቃኝ ወገኖች መካከል ለጋራ ደህንነታችን ምንም ዓይነት መተማመን እስከሌለ ድረስ የፈለገውን ያህል አንደበተ ርትኡ ትንታኔ እና ውይይት ቢደረግ ዋጋ አይኖረውም፡፡
ጻድቃን፣ ዘ-ህወሀት ሌላ ምንም ቢሆን ኢትዮጵያን ለማዳን ከፈለጋችሁ፣ እራሳችሁን ለማዳን ከፈለጋችሁ በብዕር ጫፍ የሚሰራ አንዲት ቀላል የሆነ ነገር አድርጉ፡ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች አሁኑኑ ፍቱ፡፡
እኔም ለሀገሬ ሀሳብ አለኝ በማለታቸው እና የገዥውን ፓርቲ ፕሮግራም ባለመቀበላቸው ምክንያት ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች በየማጎሪያ እስር ቤቶች ታስረው ባሉበት እና በቁጥጥር ስር ተደርገው ለተለያዩ የጥቃት ሰለባዎች እየሆኑ በሚገኙበት የፖለቲካ ድባብ ውስጥ ምንም ዓይነት ንግግር፣ ውይይት ወይም ደግሞ ስምምነት ወይም እንደዚህ ያለ ጥያቄ የማቅረብ መብት ሊኖር ከቶ አይችልም፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ በእስር ቤት በመማቀቅ ላይ የሚገኙትን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት የስምምነቱን ሂደት እንጀምረው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ መተማመንን ለመገንባት ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች እንደመፍታት ያለ ቀላል ነገር የለም፡፡
ጻድቃን የሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች መፈታታ ማመቻቸት የሚችል ከሆነ ሁሉም ትክክለኛው ጨዋታ ተጀመረ እላለሁ!
ዘ-ህወሀት ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች የሚፈታ ከሆነ እርሱም እራሱ በህዝባዊ ውይይቱ ላይ ለመቀመጥ እና ኢትዮጵያን እና እራሱን ከአውዳሚ ጥፋት ለማዳን ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋር መደራደር ይችላል፡፡ የእስር ቤት ካምፖችን የሚራምዱ አካሎች የእራሳቸውን እስረኞች እየተመለከቱ ሌላው ቀርቶ እራቸው አሳሪዎቹ ነጻ ሊሆኑ ከቶውንም አይችሉም፡፡ የእስር ቤት የጥበቃ አባሎች እራሳቸው ነጻነቶቻቸው እንደተወሰዱባቸው እስረኞች ሁሉ ነጻ አይደሉም፡፡
በእርግጥ አሁን እንደዚህ ያለውን አቋም በመያዝ ለእራሴ እና ለማህበራዊ ለውጥ ምክንያት ይሆናል ብየ ለማስበው ጉዳይ በእርግጠኝነት ላይ ሆኘ በመናገር ላይ እገኛለሁ፡፡
እኔ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ዜጋ እና ለዚያ ትግል እራሴን በጽናት ያቆምኩ እና የወሰንኩ ሰው ነኝ፡፡ እኔ ማለት የምፈልገውን በነጻነት መናገር፣ ህሊናዬ የፈቀደልኝን በነጻነት የምናገር እና እውነት ብቻ እያዘዘኝ የምኖር ሰው እንጅ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ስልጣን የመያዝ ጉጉት እና ፍላጎት የለኝም፡፡
ከእኔ ጋር የማይስማሙ ጥቂት ሰዎች እንደሚኖሩ እርግጠኛ ነኝ፡፡ እ.ኤ.አ መስከረም 2010 በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ የአምባገነኑን የመለስ ዜናዊን የመናገር መብት ለመጠበቅ ሳደርገው በነበረው ጥረት የህይወት ትግሌን እንደከዳሁ አድርገው የቆጠሩ ሰዎች የነበሩ መሆናቸውን ወደ ኋላ መለስ በማለት አስታውሳለሁ፡፡ ትችቶች ምንም ዓይነት ፍላጎት ይኑራቸው አይኑራቸው ለማሰብ ነጻ ናቸው፡፡
እኔ እንደ ግለሰብ ለኢትያውጵያውያን ወንድሞቸ እና እህቶቼ ያለኝ ፍቅር በእኔ ላይ እንደ ግለሰብ ከሚሰነዘሩብኝ ትችቶች በላይ መጨረሻ የለውም፡፡
በአሁኑ ጊዜ የፐርሻዋ የአይሁድ ንግስት በአንድ እግሯ በመቆም ስታደርገው እንደነበረው ተማጽዕኖ “በህዝቦቸ ላይ የመጣውን ሰይጣናዊ ድርጊት እንዴት አድርጌ በጽናት በመቆም ላስወግደው እችላለሁ? ወይም ደግሞ የምወዳቸው ህዝቦቸ በአደጋ ተጋልጠው ለአውዳሚ ጥፋት ሲዘጋጁ እንዴት አድርጌ ነው በትዕግስት የምመለከተው?“ የሚል ነው፡፡
ለእራሴ ለህሊናዬ ለመናገር እና በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ የሽግግር ለውጥ እንዲመጣ ለጻድቃን እና ለዘ-ህወሀት መሪዎች እንዲህ እላቸዋለሁ፣ “እራሳችሁን እና ኢትዮጵያን ለማዳን ከፈለጋችሁ በአሁኑ ጊዜ ይህንን የተቀደሰ ዓላማ ከመጀመር የተሻለ ጊዜ የለም፡፡ ይህንን ስራ ልትሰሩ ትችላላችሁ! ማድረግም አለባችሁ! ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች አሁኑኑ ፍቱ እናም ሀገራችንን ከእርስ በእርስ ጦርነት እንድትመለስ አድርጉ፡፡ እባካችሁ ከጨለማው የእርስ በእርስ ጦርነት ታደጓት፡፡ የእኔ የመፍትሄ ሀሳብ ይኸው ነው፡፡“
እንግዲህ ሌላው አማራጭ የእርስ በእርስ ጦርነት ነው፣ አዎ የእርስ በእርስ ጦርነት፡፡ ያ ጉዳይ የሞት እና የሽረት ጉዳይ ነው!
የአንግዲህ ይህን ያህል ካልኩ በትንሿ ወፍ የሞራል ትረካ ሀሰቤን ልቋጨው፡፡ (የወፎችን ትረካ እወዳለሁ በተለይም የዘማሪ ወፎችን ትረካ፡፡)
በአሜሪካ ሀገር ከሚገኙት ታታላቅ የፍርድ ቤት ዳኞች መካከል አንዱ የሆኑት ጌሪ ስፔንስ በአንድ ወቅት በአንድ የወንጀል ጉዳይ የመዝጊያ ንግግር ላይ በመገኘት ኢትዮጵያውያን እንደተለመደው ያገኙትን መልካም አጋጣሚ ደግመው የሚያጡ ከሆኑ ምን ሊከተል ይችላል በማለት የተናገሩት ሙሉ ስሜቴን እና ቀልቤን የሚስብ ነበር፡፡
ስፔንስ እንዲህ በማለት ነበር የክርክር ጭብጣቸውን ያቀረቡት (እኔ አሁን ለመላ ኢትዮጵያውያን እንደማደርገው)፡
“ክቡራት እና ክቡራን፡ ከመሄዴ በፊት ስለአንድ ብልህ ሽማግሌ እና አፈ ጮሌ ልጅ ትረካ ልነግራችሁ እፈልጋለሁ፡፡
አፈጮሌው ልጅ ሽማግሌውን ለማሞኘት የሚያስችለውን ዕቅድ ነደፈ፡፡ አፈጮሌው ልጅ ከጫካው ውስጥ ወፍ ያዘ፡፡ ወፏን በእጆቹ መዳፍ ውስጥ ላላ አድርጎ በመያዝ ጅራቷ ወጣ ብሎ ይታይ ነበር፡፡ በእጆቹ መዳፍ ውስጥ ያለችው ወፍ በህይወት ነበረች፡፡
ልጁ የነደፈው ዕቅድ እንዲህ የሚል ነበር፡ ወደ ሽማግሌው ሰው በመሄድ እንዲህ ይላል፣ “ሽማግሌው በእጀቸ መዳፍ ውስጥ ምንድን ይዣለሁ?“ ሽማግሌው እንዲህ ይላሉ፣ “ልጄ ወፍ ይዘሀል፡፡“ በመቀጠልም ልጁ እንዲህ ይላል፣ “ሽማግሌው ይህች ወፍ በህይወት አለች ወይስ ደግሞ ሞታለች?“
ሽማግሌው ወፏ ሞታለች የሚሉ ከሆነ ልጁ የእጆቹን መዳፎች ከፈት ያደርግ እና ወፏ በነጻነት ወደ ዛፍች እንድትበር ያደርጋል፣ እናም በህይወት አለች ስለዚህ አሞኘኋቸው ለማለት ያስችለዋል፡፡
ሆኖም ግን ሽማግሌው ወፏ በህይወት አለች የሚል ምላሽ የሚሰጡ ከሆኑ ኮሚኩ ልጅ በእጆቹ መዳፎች ውስጥ ያለችውን ወፍ በመዳፎቹ በመደፍጠጥ እንድትሞት ያደርግና “ሽማግሌው ይመልከቱ ወፏ ሞታለች“ በማለት ያታለላቸው መሆኑን ለማረጋገጥ ያስችለዋል፡፡
ስለሆነም ኮሚኩ ልጅ ይህንን ሁሉ የማጭበርበሪያ ስሌት ቀምሮ ከጨረሰ በኋላ ወደ ሽማግሌው በመሄድ እንዲህ አለ፣ “ሽማግሌው በእጆቼ ላይ ምንድን ይዣለሁ?“ ሽማግሌው እንዲህ የሚል መልስ ሰጡ፣ “ልጄ በእጅህ ላይ ያለችው ወፍ ናት፡፡“ አሁንም ኮሚኩ ልጅ እንዲህ አለ፣ “በእጄ ላይ ያለችው ወፍ በህይወት አለች ወይስ ደግሞ ሞታለች?“ ሽማግሌው ምናቸው ሞኝ እንዲህ የሚል የሚያስገርም መልስ ሰጡ፣ “ልጄ ወፏ በእጆችህ ላይ ናት፡፡“ በማለት ልትገድላትም ልታድናትም ስለምትችል እጆችህ እንዳደረጓት ነው የእርሷ ህልውና የሚረጋገጠው የሚል ቅኒያዊ ንግግርን አራምደዋል፡፡
ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እና ለዘ-ህወሀት መሪዎች ኢትዮጵያ በእጃችሁ ላይ ናት እላችኋለሁ፡፡
እርሷ በህይወት ስለመኖሯ ወይም ደግሞ ስለመሞቷ ወይም ደግሞ ወደፊት በህይወት መኖር ስለመቻሏ ወይም መሞት ስለመቻሏ እናንተው ናችሁ የምታውቁት፡፡
ለዘላለም በህይወት ስለመኖሯ ሌላ ማንም ሳይሆን እናንተው ናችሁ የምታረጋግጡት!
እኔ ግን ዘማሪዋ ትንሿ ወፍ ብቻ ነኝ፡፡
ለአስር ዓመታት ያህል አንድም ሳምንት ሳላሳልፍ ቃል የገባሁለትን ተግባር በየእያንዳንዱ ሳምንት ማከናወኑን እቀጥላለሁ፡፡ ባለችኝ ትንሽ ኩምቢ ከወንዝ ውኃ በመቅዳት እና በማመላለስ በእሳት ተቀጣጥሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ቤት ላይ በመጨመር እሳቱ እንዲጠፋ አደርጋለሁ፡፡
አንድ መቶ ሚሊዮን የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ወንድሞቼ እና እህቶቼ ሳይቀላቀሉኝ ላደርግ የምችለው ነገር ይኸው ብቻ ነው፡፡
ምንም ዓይነት ቅሬታ አላሰማም፡፡ ያለመደሰቴን ወይም ደግሞ ተከታታይነት ያለው ቅሬታን አላቀርብም፡፡ ምንም ዓይነት ነገር፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ትንሿ ወፍ ነጻ እና ሰላሟ የተጠበቀ ሆና እስከማይ ድረስ የተሸከምኩትን እና የመረጥኩትን መስቀል አላስቀምጥም፡፡
ዘ-ህዋሃት አስተውሉ! ለፃድቃን የመጣ ለሃጣን ይተርፋል !
እንደ ሽማግሌው ሁላችንም ብልህ መሆን የለብንም? ስለዚህ ጉዳይ አስቡ፡ እንዲህ የሚል አንድ ምርጫ ብቻ አይደለም ያለን፡ “እንደ እህትና እንደ ወንድም በአንድነት መኖር አለብን ወይም ደግሞ በአንድነት እንጠፋለን፡፡“ ማርቲን ሉተር ኪንግ
በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ አስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አሁኑኑ ይፈቱ፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ሀምሌ 27 ቀን 2008 ዓ.ም