የአፍሪካ ቀንድ ተስፋ ሊኖረው ይችላልን?
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2014 “ለአፍሪካ ተስፋ ሊኖረው ይችላልን?“ በሚል ርዕስ አንድ ትችት ጽፌ ነበር፡፡
ያንን ትችት የጻፍኩት ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ውስጥ ተንሰራፍቶ በሚገኘው እና ማቆሚያ በሌለው በአፍሪካ ሰው ሰራሽ ቀውስ ምክንያት ምንም ዓይነት ተስፋ የሌለኝ በመሆኑ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2014 የመካከለኛው አፍሪካ ሬፐብሊክ (መአሬ) አውዳሚ በሆነ የጎሳ-ኃይማኖት የዘር ማጥፋት ዘመቻ እልቂት ውስጥ ተዘፍቃ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2014 የአፍሪካ አዲስ ሀገር ሆና የተመዘገበችው ደቡብ ሱዳን የእራሷን የዘር ማጥፋት ወንጀል በመፈጸም ላይ ነበረች፡፡
እ.ኤ.አ በ2007 የተካሄደውን ሀገር አቀፍ የምርጫ ውዝግብ ተከትሎ አሁሩ ኬንያታ እና ተባባሪዎቹ የነብስ ገዳይ ተውኔት ፈጻሚ ቡድኖችን በማቋቋም ወደ ሁለት ሚሊዮን ገደማ የሚደርሱ ንፁሀን ኬንያውያንን በማስገደል ከ650 ሺ በላይ የሚሆኑት ዜጎችን ደግሞ ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ አድርገዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኬንያታ እና የእርሱ ምክትል የሆነው ዊሊያም ሩቶ በሰው ልጆች ላይ በፈጸሙት ሰብአዊ ወንጀል በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እ.ኤ.አ መጋቢት 2011 ክስ ተመስርቶባቸው ከችሎት አደባባይ ከሕግ ፊት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተላልፎባቸው ነበር፡፡ እነዚህ የሰብአዊ መብት ቀንደኛ ደፍጣጮች በመሰል ሰብአዊ መብት ረጋጭ ታላቅ ወንድሞቻቸው እገዛ አማካይነት ከጥቂት ጊዜ በፊት ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት መዳፍ ውስጥ እንዲያመልጡ ተደርገዋል፡፡
እ.ኤ.አ ታህሳስ 2005 ቻድ መጠነ ሰፊ በሆነ የእርስ በእርስ የጦርነት እሳት ውስጥ ተማግዳ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ ከሰኔ 2005 ጀምሮ እና በተከታታይ በነበሩት ወራት ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው አገዛዝ እና ስሙ በዓለም አቀፍ የአሸባሪዎች የመረጃ ቋት ስም ዝርዝር ውስጥ ተመዝግቦ በሚገኘው በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብብስ (ዘ-ህወሀት) ቅጥር ነብሰ ገዳዮች ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ያልታጠቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች በጠራራ ጸሐይ እንደ አውሬ እየታደኑ አሰቃቂ በሆነ መልኩ በጥይት እየተደበደቡ እንዲገደሉ ሲደረግ 30 ሺ የሚሆኑት ሰላማዊ ዜጎች ደግሞ በማጎሪያው እስር ቤት እየታጎሩ በመጥፎ የእስር ቤት አያያዝ እንዲሰቃዩ እና እንዲማቅቁ ተደርገዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ሂዩማን ራይትስ ዎች (ሂራዎ)/Human Rights Watch (HRW) የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ዘ-ህወሀት እያካሄደ ስላለው የሰላማዊ አማጺዎች አያያዝ ሁኔታን በማስመልከት “ጭካኔ የተመላበት እርምጃ፡ ለኢትዮጵያ ኦሮሞዎች ተቃውሞ የተሰጠ የግድያ እና እስራት ምላሽ“ በሚል ርዕስ ትልቅ ዘገባ አቅርቧል፡፡
እ.ኤ.አ የካቲት 2003 በሱዳን ዳርፉር ወደ ግማሽ ሚሊዮን ገዳማ ለሚሆኑ ዜጎች ህይወት እልቂት መነሻ የሆነው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተጀመረ፡፡
እ.ኤ.አ በ2003 ላይቤሪያ በወሮበላ ዘራፊ ጦረኞች የገሀነም እሳት ውስጥ ተማግዳ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ ከ1998 – 2000 ድረስ ተደርጎ በነበረው እና ኃላፊነት በማይሰማቸው የእብዶች ጦርነት ወደ 120 ሺ ገደማ የሚሆኑ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወታደሮች እና ሲቪሎች እልቂት ተፈጽሟል፡፡
እ.ኤ.አ ሚያዝያ 1994 በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት እልቂቱ በከፍተኛ ደረጃ ተጠናክሮ የቀጠለበት ሁኔታ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ1991 በሶማሊያ ጎሳን መሰረት ያደረጉ የታጠቁ ተቃዋሚ ቡድኖች ወታደራዊ አገዛዙን በኃይል ያስወገዱ ሲሆን ሶሚሊያ በአሁኑ ጊዜ የሽብርተኝነት ሰለባ እና በዓለም አቀፍ የፖለቲካ መድረክ ውስጥ የአሸባሪዎች መጠለያ ሆና ትገኛለች፡፡ አሁን ትላንት አሸባሪዎች በመኪና ላይ የተጠመደ ቦንብ በአንድ ሆቴል ላይ በማፈንዳት በርካታ ንጹህን ዜጎች ሙት እና ቁስለኛ እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡
በዴሞክራቲክ ሬፖብሊክ ኮንጎ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ በተካሄደው ጦርነት የስድስት ሚሊዮን ዜጎች ህይወት የቀጠፈ ሲሆን እልቂቱ አሁንም ድረስ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡
“ማንም ወደዚህ የሚገባ ሁሉ ተስፋውን ያጣ ነው“ የሚለው የጽሁፍ መግለጫ በዳንቴ የገሀነም በር ላይ ተጽፎ የሚገኝ ነው፡፡
የአፍሪካ ወሮበላ ዘራፊዎች እና አምባገነኖች አፍሪካን ለአፍሪካ ሕዝቦች ገሀነም አድርገዋታል፡፡
አፍሪካ በቀጣይነት ተስፋ የሚኖራት ወይም ደግሞ የማይኖራት የመሆኑ ጥያቄ በአፍሪካውያን፣ በአፍሪካውያን ወዳጆች እና በአፍሪካውያን ጠላቶች አእምሮ ውስጥ የሚመላለስ ጉዳይ ነው፡፡
አፍሪካ ተስፋ የሚኖራት ስለመሆኑ ለእኔ ጥያቄ ማቅረብ ማለት በጽኑ የታመመ ወይም በጣር ላይ ያለ በሽተኛ እርዳታ እየተደረገለት የመዳን እና ያለመዳን ሁኔታን የመመለስ ጥያቄ ዓይነት ነው፡፡ በጽኑ ታሞ ከፍተኛ በሆነ መልኩ የህይወት አድን ህክምና እየተደረገለት ያለ በሽተኛ ሊድንም ይችላል ወይም ደግሞ ላይድን ይችላል፡፡ እርግጠኛ ሆኖ የመናገሩ ሁኔታ ውኃ የሚቋጥር አይደለም፡፡ በሌላ አገላለጽ ያፍሪካ ተስፋ መኖር አስተማማኝ አይደለም፡፡
ይህንን ጥያቄ እ.ኤ.አ በ2014 አቅርቤው በነበረው ትችቴ በስሜታዊነት የተሞላ እና ሊሆን የማይችል ተስፋ ነው የሚል ምላሽ ሰጥቸ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ተስፋ እንዳለ አወጅኩ፣ ምክንያቱም አፍሪካ ማድረግ ለሚችሉ አፍራካውያን እንጅ ምንም ነገር ለማያደርጉ እና እጆቻቸውን አጣጥፈው ተቀምጠው ለሚመለከቱ ዜጎች አይደለችምና፡፡
በአፍሪካ ውስጥ አንድ ቀን የመንግስት ስህተቶች በሰብአዊ መብት ጥበቃ እንደሚተኩ እና የአፍሪካ መንግስታት ሕዝቦቻቸውን እንደሚፈሩ እንዲሁም ሕዝቡም ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እስከዘላለሙ ፍርኃቱን አሽቀንጥሮ የሚጥልበት ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል አመንኩ፡፡ እንደነዚህ ያሉ ተምኔታዊ ህልሞች የአንድ ኢትዮጵያዊ አፍሪካዊ ታምኔታዊ አላሚ የቀን ህልሞች ነበሩ፡፡
አሁን ግን እንዲህ የሚል ጥያቄ በማቅረብ ላይ እገኛለሁ፣ “የአፍሪካ ቀንድ ተስፋ ሊኖረው ይችላልን?“
ስለተስፋ ተስፋ በማድረግ ላይ እገኛለሁ ምክንያቱም ታዋቂው ገጣሚ አሌክሳንደር ፖፕ “ተስፋ በሰው ልጅ ከፍተኛ ስሜቶች ላይ ዘላለማዊ ይሆናል“ በሚል ተናግሯልና፡፡
በእርግጥ ይኸ አባባል እውነት ነውን?
ምናልባትም ይህ አባባል ትክክል መሆኑን ኢሚሊ ዲክሰን እንዲህ በሚሉ አባባሎቹ አረጋግጧል፡
ተስፋ በስሜታዊነት የተሞላ ነው፣
በቀዝቃዛዋ መሬት አዳምጨዋለሁ፣
በእንግዳው ባህርም አዳምጨዋለሁ፣
ሆኖም ግን በውኑ ዓለም የለም፣
የእራሴን ግን ጠይቆኛል፡፡
አሁን በቅርቡ በኬንያ ቴሌቪዥን ኔትዎርክ ዓለም አቀፍ/Kenya Television Network (KTN) – World View ቤዮኔ ኦክዋራ ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ አምባሳደሮች የቀረበላቸውን ቃለመጠይቅ ከተመለከትኩ በኋላ እጅግ በጣም እንቆቅልሽ የሆነብኝ ሲሆን በአፍሪካ ቀንድ የተስፋ ፍንጣቂ ይኖር ይሆን የሚል ጥያ ቄ ፈጠረብኝ ሆኖልኛል፡፡ ኦክዋራ የKTN ዋና አዘጋጅ እና የአፍሪካ ታዋቂ ወጣት ጋዜጠኛ ናት፡፡ (የኦክዋራ የጋዜጠኝነት ድፍረት ምንም ዓይነት ፍርሀት የሌለውን እና በርካታዎቹን የዓለም መሪዎች፣ አምባገነኖች እና ታዋቂነት ያላቸውን ሰዎች በቃለመጠይቅ ስልቱ በአንድ እግራቸው የምታቆመው ታዋቂ ዋ ጋዜጠኛ ኦሪና ፋላሲን አስታወሰኝ፡፡)
ሁለቱ “አምባሳደሮች” አሁን በቅርቡ ነጋሪት እየተጎሰመለት ስላለው ጦርነት (ወይም ደግሞ የጦርነት ጨዋታ እያልኩ ስለምጠራው) በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ስላለው ጦርነት ቃለመጠይቅ ተደርጎላቸው እንዲነጋገሩ ተደርጎ ነበር፡፡
ሁለቱ አምባሳደሮች በቃለመጠይቁ ሲሰጡት የነበረው ምላሽ ሀገሮቻቸውን እና መንግስቶቻቸውን በመወከል ነበር፡፡
ሆነም ግን የጨ ረባ ተስካር አስመሰለዉት ነበር። የሌባ ጣትን ከመቀሰር፣ (ሌቦች አላልኩም) ምላስን ከማሾል እና ምላስን በማውጣት በአንድ ሰው ላይ ከመቀለድ ያልተናነሰ በሚመስል መልኩ ሆያሆዬ ዓይነት ጨዋታ ቃለ መጠይቅ ከሆነ ነበር ማለት ይቻላል ፡፡
ሁለቱ አምባሳደሮች እንደ በጥባጭ የትምህርት ቤት ጎረምሳ ሲጨሁ እና እርስ በእርሳቸው ሲጠዛጠዙ የሚያሳየውን የቪዲዮ ምስል ተመልክቸዋለሁ፡፡
የተራቡ ጅቦች በወቀደ ጥንብ ላይ እኔ እወስድ እኔ እወስድ በማለት ሲረባረቡ እንደሚታየው ሁሉ እነዚህም ሁለቱ አምባሳደሮች እርስ በእርሳቸው ሲዋጉ የሚያሳየውን የቪዲዮ ምስል ተመልክቸዋሁ፡፡
ለማመን የሚያስቸግር ታምራዊ የሆነ ነገር ነበር፡፡ ሶስት ጊዜ አይቸው ነበር፡፡
ሁለቱ አምባሳደሮች እርስ በእርሳቸው ሲዘላለፉ መመልከት ታላቅ ስቃይ ነበር፡፡
ለእራሴ እንዲህ በማለት ነገርኩ ፣ “የማየውን ነገር አይታመንም ፡፡ የሚዋሹ ዓይኖቼ እና ጆሮዎቼ ለእኔ ውሸት እየዋሹ ነው፡፡“
በዚያ የቪዲዮ ምስል ላይ ያየሁት ነገር ሁለት ሰካራም ሰዎች በአፍሪካ የቢራ ቤት ወይም ደግሞ ቡና ቤት (ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ ጠጅ ቤት ወይም ጠላ ቤት እየተባለ በሚጠራው) ውስጥ ሆነው ከእነዚያ መጠጦች በብርሌ ወይም በጣሳ ላፍ ላፍ አድርገው ሞቅ ሲላቸው በጥላቻ መልክ እየተያዩ እርስ በእርሳቸው የሚያደርጉትን ጉንጭ አልፋ ክርክርና ንትርክ እየተመለከትኩ ያለሁ ነበር የመሰለኝ፡፡
በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በርዕሰ መምህሩ ቢሮ ውስጥ በመገኘት “እርሱ ነው የጀመረው! አይደለም እርሱ ነው የጀመረው!” እያሉ እርስ በእርሳቸው ጣታቸውን አንዳቸው በአንዳቸው ላይ እየቀሰሩ ሲካሰሱ ሁለት ደደብ ተማሪዎችን ተመልክቻለሁ፡፡ “አምባሳደሮቹም” በእርግጠኝነት እንደዚህ ብለዋል፡፡ “አንተ ነህ የጀመርከው፡፡ ስለእኛ ውስጣዊ ጉዳይ ተናግረሀል፡፡ አንተ በርቀት የምትጓዝ ከሆነ እኔም እንደዚሁ በርቀት እጓዛለሁ“ በማለት የኤርትራው አምባሳደር በዘ-ህወሀት አምባሳደር ላይ የእብሪት እና የንቀት ንግግር ሲያደርግ ነበር፡፡
ሁለት ጎረቤታሞች የሆኑ ልጆች እርስ በእርሳቸው “የእኔ አባት የአንተን አባት ያሸነፈዋል“ በማለት ሲነጋገሩ አየሁ፡፡
በዚያ የቪዲዮ ምስል ላይ ያየሁትን ካየሁ በኋላ ጥልቅ የሆነ ሀፍረት ተሰማኝ፡፡ ወይ ቅሌት !
ድምጼን ከፍ አድርጌ በመጮህ እንግዲህ እነዚህ የአፍሪካ ዴፕሎማቶች ናቸው ወይም ደግሞ ጥርስ ለጥርስ በመያያዝ እርስ በእርሳቸው የሚቦጫጨቁ ባለጌ ወሮበሎች ናቸው! (አራዊቶች አላልኩም።)
እንዴት ሁለት የአፍሪካ ዴፕሎማቶች እርስ በእርሳቸው (እና በሂደቱ ሁሉም አፍሪካውያን) በኤሌክትሮኒክ መገናኛ ሊዘላለፉ እንክያ ሰላምትያ ሊሉ ይችላሉ?
አንድ ቦታ ላይ የኤርትራው አምባሳደር የዘ-ህወሀትን አምባሳደር እንደ ዴፕሎማት ስርዓት እንዲጠብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጠው እንዲህ በማለት ፣ “በመሸታ ቤት ውስጥ አይደለንም፡፡ ያለነው በህዝብ ፊት ነው፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ሕዝቦች ሁሉ ይመለከቱናል“ በማለት የኤርትራው አምባሳደር ተማጽዕኖውን አቀረበ፡፡
ሁለቱ አምባሳደሮች ቃለመጠይቁን እጅ በእጅ በመያያዝ ወደሚደረግ የቃላት ጦርነት ዕድል ቀየሩት፡፡
ሁለቱም አምባሳደሮች ወደ ቃለመጠይቁ በሚቀርቡበት ጊዜ ተጽፈው የተዘጋጀ የመነጋገሪያ ነጥቦችን እና እንደ ሮቦት ተሞልተው የተነገራቸውን እንዲያሰሙ የመጡ ነበሩ፡፡
የመነጋገሪያ ነጥቦቻቸው አንዱ ሌላኛውን ወገን ገና በመጀመሪያው ዙር በቡጢ ዘርሮ እንደሚጥል እና በድል አድራጊነት እተጎማለለ እንደሚሄድ የተቆጣ ቦክሰኛ ለመሆን ተሞልተው የመጡ ነበሩ፡፡
ሁለቱም አምባሳደሮች በአሁኑ ጊዜ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ጦርነት ለምን እንደተነሳ ግልጽ እና ጨዋነትን በተላበሰ መልኩ ለመግለጽ ፍላጎቱ አልነበራቸውም፡፡ የእራሳቸውን የግል አጀንዳ ብቻ ለመናገር ፈለጉ፡፡
ሁለቱም አምባሳደሮች እርስ በእራሳቸው የቃላት ቡጢዎችን እና ጎጂ የሆኑ ቃላትን ተወራወሩ፡፡
ከአንድ ውስብስብ ከሆነ እና ታላቅ ከበሬታ ካለው ዓለም አቀፍ የዴፕሎማት ሰው ከሚጠበቅ ጨዋ ንግግር ይልቅ ለመንገድ ወሮበላ ዱርዬዎች አፍ የሚስማማ፣ በጣም ባዕድ የሆነ እና ቆጥቋጭ የሆነ መግለጫ ሰጡ፡፡
አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ርካሽ ተኩስ በመክፈት አንዳቸው በአንዳቸው ላይ የበላይነትን የማረጋገጥ ጨዋታ ለመጫወት ሙከራ አደረጉ፡፡
የእነዚህ የሁለቱ አምባሳደሮች እርባና ቢስ ቃለመጠይቅ የዶናልድ ትሩምፕን ቃለመጠይቅ ከማየት የበለጠ አስከፊ ሆኖብኝ ነበር፡፡ (ሰዉረነ ከዚያ መዓት!)
ሁለቱ አምባሳደሮች እርስ በእርሳቸው በዴፕሎማሲያዊ ስድበ ጭቃ ጅራፍ ተማዘዙ ጠናክረው ተሰዳደቡ፡፡ የኤርትራው አምባሳደር በአንድ አጋጣሚ ላይ እንዲህ አለ፣ “አንተ እኔን እየተሳደብክ የእኔን አፍ ለማዘጋት ትፈልጋለህ?“ በማለት የዘ-ህወሀቱን አምባሳደር አቋረጠው፡፡
ሁለቱም አምባሳደሮች የዓይናቸውን ቅንድብ ወደ ላይ በመሸብሸብ፣ የንቀት ምላሽ በመስጠት፣ ድብቅ ቃላትን በመወርወር፣ አዋራጅ ቃላትን በመጠቀም እና ሌላውን አሳንሶ በማየት እርስ በእርሳቸው ተጠዛጠዙ፡፡
እርስ በእርሳቸው ጥላሸት ተቀባቡ፣ አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ሰይጣናዊ ድርጊትን ፈጸሙ፡፡
በሁኔታቸው ተስፋ የቆረጠችው ጋዜጠኛ እስከምታስቆማቸው ድረስ አምባሳደሮቹ እንደ በቀቀን የሚለፈልፉትን የቃላት ጦርነት አጠናክረው ቀጠሉ፡፡
“አምባሳደር ለሀገር ጥቅም ሲባል ለመዋሸት ወደ ውጭ ሀገር የሚላክ ታማኝ ሰው ነው“ ይባላል፡፡ እነዚህ ሁለት አምባሳደሮች አምባሳደር ለሀገሩ ሲል ለመዋሸት ወደ ውጭ ሀገር የሚላክ እና በሂደት በዴፕሎማሲያዊ እና ጨዋነትን በተላበሰ መልኩ ለሀገራቸው ከመስራት ይልቅ የዘለፋ ቃላትን የሚጠቀሙ እና እራሳቸውን በእራሳቸው የሚያሞኙ የሚ ያዋረዱ መሆናቸውን በተግባር አስመስክረዋል፡፡
ቃለመጠይቁ በሚጀመርበት ጊዜ የዘ-ህወሀት አምባሳደር በመጀመሪያው ቀን የመነጋገሪያ ነጥቦችን በማውጣት ዝርዝር መረጃዎችን አቀረበ፡፡ እንዲህ በማለትም አወጀ፣ “ኢትዮጵያ ያሏት ብቸኞቹ ጠላቶቿ ድህነት፣ ኋላቀርነት እና ድንቁርና ናቸው…በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ በፕላኔቷ ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ከሚያስመዘግቡ ሀገሮች መካከል አንዷ ናት፡፡፡“
ይኸ “የፈጣን ኢኮኖሚ ዕድገት“ እየተባለ ሁልጊዜ በቀጣይነት የሚቀርበው የማጭበርበሪያ ርዕሰ ጉዳይ እኔ በየጊዜው ቅሬታዬን ሳቀርብበት የቆየሁበት ጉዳይ ነው፡፡ የቪዲዮ ምስሉን በምመለከትበት ጊዜ “ሚስተር ‘አምባሳደር’ ውሸት እየዋሸህና ተራ ቅጥፈት የቁጥር ጨዋታ በመጫወት እየነገርከን ነው” በማለት ላቋርጠው ፈልጌ ነበር፡፡
በእርግጥ የዘ-ህወሀት አምባሳደር “ኢትዮጵያ እና የዓለም ባንክ የሚያደርጉትን ተራ ቅጥፈት እና የቁጥር ጨዋታ“ ለማስተባበል በማይቻልበት ደረጃ በማጋለጥ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እያቀረብኳቸው ያሉትን ግልጽ የሆኑ እና ወቅታዊ የሆኑ የትንታኔ ትችቶቼን አላነበበም፡፡
ባለፉት አስርት ዓመታት አስመዘገብኩት እያለ የሚመጻደቅበት የዘ-ህወሀት ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ከምንም ጥርጣሬ በላይ ፍጹም ውሸት፣ ተራ ቅጥፈት እና የቁጥር ጨዋታ መሆኑን በተጨባጭ ማስረጃ እያቀረብኩ ሳጋልጥ ቆይቻለሁ! ከዚህም በተጨማሪ ማንም ሰው ቢሆን ይህንን ተራ ቅጥፈት እንደ ዘ-ህወሀት በመቅጠፍ የሚደግም ቢኖር እርሱም የለየት ቀጣፊ ውሸታም ነው!
የዘ-ህወሀት አምባሳደርም ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2000 እና በ2009 ዓመተ ምህረቶች መካከል 11.7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ምክንያት ያጣችበትን እውነታ በንግግር አጀንዳው ውስጥ ሳይጠቅስ ሆን ብሎ በማጭበርበር አልፎታል፡፡
እ.ኤ.አ በ2011 ግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ/Global Financial Integrity የተባለው ድርጅት ከኢትዮጵያ በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ምክንያት ከሀገር ውስጥ የወጣው ገንዘብ እ.ኤ.አ 2009 በሁለት እጥፍ በላይ በመሆን 3.26 ቢሊዮን ዶላር ሆኗል፡፡
በሕገ ወጥ ወጥ የገንዘብ ዝውውር የወጣን ያንን ያህል ገንዘብ በውጭ ሀገር ባንኮች የሂሳብ አካውንት በመክፈት ማጨቅ የሚችል በኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ባለስልጣን ማን ነው? ለመሆኑ ኢትዮጵያን ደኃ፣ ኋላቀር እና ድንቁርና የተንሳራፋባት ሀገር እንድትሆን ያደረገ ማን ነው?
የዚህ ጥያቄ ምላሽም እንዲህ የሚል ይሆናል፡ የኢትዮጵያ አራተኛው ጠላቷ!
የዘ-ህወሀት አምባሳደር በቅርብ ጊዜ የተደረገውን የትጥቅ ግጭት የጀመረችው እና ላለፉት ዓመታት ሁሉ በቀጣናው ሌሎች ግጭቶችን ስትፈጥር የቆየች ኤርትራ ናት በማለት ከሷታል፡፡
የኤርትራው አምባሳደር እጅግ በጣም በመበሳጨት እና ንቀትን የተላበሰ በማያስመስል መልኩ ለመቅረብ ሞከረ፡፡ ሙሉ ትችቱን እንዲህ በማለት ጀመረ፣ “በአምባሳደሩ በጣም አዝናለሁ ምክንያቱም ይህንን ጥያቄ በመመለሱ ረገድ የተሰጠውን የስራ ኃላፊነት ገደብ ጥሷል፡፡“ ከብዙ ጊዚያት በፊት ኤርትራውያን እና ዘ-ህወሀት ጽኑ ወዳጆች እንደነበሩ ያለፈውን በመቃኘት እንዲህ በማለት ተናገረ፣ “ሁላችንም በአንድ ላይ የቆምን ወዳጆች ነበርን፡፡ በአንድ ላይ ሆነን የመንግስቱን አገዛዝ አስወገድን፡፡ እናም እ.ኤ.አ በ1998 እስከተከሰተው የኢትዮጵያ – ኤርትራ የጦርነት ጥቃት ድረስ በሰላማዊ መንገድ እንኖር ነበር፡፡” ባለፈው ሳምንት ባቀረብኩት ትችቴ ላይ እኔም ይህንኑ አንድ ዓይነት ነገር ነበር ያልኩት፡፡
የኤርትራ አምባሳደር የተሰጠውን መድረክ ለዘለፋ እና ለጭቅጭ መጠቀሙን በመተው የቀረበለትን ጥያቄ ብቻ እንዲመልስ በቃለመጠይቅ እድራጊ ጋዜጠኛዋ ተማጽዕኖ በቀረበለት ጊዜ ተቆጣ፡፡ ቃለመጠይቅ አድራጊዋ በተደጋጋሚ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ወደሚቀጥለው ርዕሰ ጉዳይ ለማለፍ ሙከራ በማድረግ ላይ ነበረች፡፡ በከፍተኛ ፍጥነት ያቋርጣት ነበር፡፡ ድምጹን ከፍ በማድረግ የዘ-ህወሀትን አምባሳደር እንዲህ በማለት ይተች ነበር፡
“ምናልባትም ዲና አያውቀውም ይሆናል፡፡ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ በአንድነት ሆነን የመንን ወግተናል…በሕግ ባለመገዛት የኤርትራን ግዛትነት ወደ ኋላ በመተው በኤርትራ ድንበር ላይ የሚገኙትን ሁለቱን ደሴቶቻችንን እየከበበች ያለች የመን መሆኗን የነገረችን ኢትዮጵያ ነበረች… በኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛውን ስልጣን የተቆጣጠረው እና አናሳ ቡድን የሆነው ህወሀት (ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ) ይህንን ጉዳይ በሚገባ ያውቀዋል፡፡ የመንን በመወጋንበት ጊዜ እገዛ አድርገውልናል፡፡“
የዘ-ህወሀት አምባሳደር በበኩሉ ግልጽ በሆነ መልኩ የኤርትራውን አምባሳደር አፍ ለማስያዝ በማሰብ “ሁለቱ ቡድኖች ጥሩ ወዳጆች ነበሩ፣ ሆኖም ግን አሁን በእጅ ላይ ያለው ጉዳይ የመንግስቱ ባህርይ ጉዳይ ነው [የኤርትራ አምባሳደር የሚወክለው]… አሁን ዋናው ጉዳይ የድንበር ስምምነቱን ተግባራዊ ማድረግ ነው… የጋራ የሆኑ ዕድሎች አሉን፡፡ እንደምታውቀው ወይ አብረን እንዋኛለን አለያም አብረን እንሰጥማለን” ነበር ያለው፡፡
ለእራሴ እንዲህ አልኩ፣ “ቢንጎ!” (ማለትም ጎሽ እርፍ በለዉ ! )
ባለፈው ሰኞ ባወጣሁት ትችት በኢትዮጵ-ኤርትራ መካከል እየተካሄደ ያለው የጦርነት ጨዋታ በሁለቱ ወንድማማቾች መካከል የሕዝቡን ስሜት ለማስቀየስ (ለማወናበድ) ነው በማለት የክርክር ጭብጤን አቅርቤ ነበር፡፡ የጦርነት ተጫዋቾች በስልጣን ላይ ለመቆየት አንድ ዓይነት የሆነ መንትዮች የአንዱ መኖር ለሌላው ህልውና በመሆኑ እና አንዱ ከሌለ ሌላው እንደማይኖር ስለሚያውቁ እነዚህ ሁለት ጽንፈኛ ቡድኖችም በተመሳሳይ መልኩ ለህልውናቸው አንዳቸው ለአንዳቸው ይፈላለጋሉ፡፡ ባተር መያዣ ከረጢት ውስጥ ያሉ የአተር ዘሮች ማለት ናቸው፡፡ እንዲህ በማለት ጥያቄ አቅርቤ ነበር፣ “በአንድ ሳንቲም ሁለት የተለያየዩ ገጽታዎች ላይ ባሉ ቡድኖች መካከል ጦርነት ሊካሄድ ይችላልን?”
ሁለቱ ገጽታዎች አንዱ በአንዱ ላይ ጦርነት ለማወጅ አቅሙ የላቸውም ምክንያቱም ያንን ካደረጉ ሁለቱም አብረው ይሰጥማሉና፡፡
የኤርትራ አምባሳደር በእራሱ ተቀናቃኝ ላይ ጮኸበት፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በአንድነት ሆነው የመንግስቱን ወታደራዊ አገዛዝ ወግተዋል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ሁለቱም ወገኖች በአንድነት ሆነው የመናውያንን ወግተዋል፡፡
ያለ ኤርትራውያን እገዛ ዘ-ህወሀት የሀገሪቱ መናገሻ ከሆነችው አዲስ አበባ አይደርስም ነበር፡፡
በሁለተኛው የቃለመጠይቅ ክፍል ሁሉም ገሀነም ክፍት ነበር፡፡ ለሁሉም ነጻ የጭካ ጅራፍ ዘመቻ ተከፈተ ፡፡
ሁለቱ አምባሳደሮች ቃለመጠይቅ አድራጊዋ ጥያቄ እንድታቀርብላቸው አልፈቀዱም ነበር፡፡ አፍ አፏን አሏት ። (ስያሳፍሩ!)
አንዳቸው ሌላኛውን መከተል ጀመረ ፡፡ እንዲያውም እንደ ድመት እና የውሻ ጦርነት ነበር ማለት ይቻላል፡፡
የዘ-ህወሀት አምባሳደር እንዲህ በማለት አወጀ፣ “ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ልዩ የሆኑ ስምምነቶች አሉን…የኤርትራው አምባሳደር እያደረገ ያለው ንግግር በተጨባጭ በመሬት ላይ የሌለ ነው…በማናቸውም ሀገሮች ጉዳይ ጣልቃ አንገባም…“
ይህ በእንዲህ እንዳለ “የተሰጠህን ጥያቄ ብቻ ምላሽ ስጥ” በማለት የኤርትራው አምባሳደር በኃይል አቋረጠው፡፡
የዘ-ህወሀት አምባሳደር በበኩሉ እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጠ፣ “አምባሳደር አንተ አትመራኝም፣ እኔ የእራሴን ህሊና ብቻ ነው የምናገረው… እስቲ እንደ ዴፕሎማት እንስራ፣ እባክህ፣ እባክህ… አንተ ጨዋ ሰው ነህ፣ ትልቅ ሰው ነህ“ በማለት የዘ-ህወሀት አምባሳደር የትችት ናዳውን አወረደ፡፡
የዘ-ህወሀት አምባሳደር እንዲህ በማለት ትችቱን ቀጠለ፣ “አምባሳደሩ ኢትዮጵያ ምን እየጠየቀች እና እያለች እንዳለ ምንም ዓይነት መረጃ የለውም… (ደንቆሮ ማለቱ ይሆን?) እኔ ከእርሱ እንደዚህ ያለ ነገር በፍጹም አልጠብቅም ነበር ምክንያቱም ዝም ብሎ ምዕናባዊነትን ፈጥሮ የማይነገር የተከበረ ሰው፣ የተከበረ አምባሳደር ይመስለኝ ነበር…“
“አንተ እየተሳደብክ የእኔን አፍ ማዘጋት ትፈልጋለህ?” በማለት የኤርትራው አምባሳደር አቋረጠው፡፡
የዘ-ህወሀት አምባሳደር የኤርትራ አገዛዝ አምባገነን ተብሎ እንደሚጠራና ቀጣናውን የሚያተራምስ ነው በማለት ከሰሰው፡፡ የእራሱን ክስ ግልጽ ለማድረግ “የዘ-ህወሀት አምባሳደር የኤርትራ አገዛዝ በሶማሊያ ከአልሸባብ [የሶማሊያ አሸባሪ ቡድን] ጋር ይተኛ ነበር” ብሏል፡፡
የዘ-ህወሀት አምባሳደር በእርሱ ተቀናቃኝ ቆዳውን በስቶ የሚገባ ትችት አቅርቦበታል፡፡
የጩኸቱ ውድድር አምባሳደሮቹ አንዳቸው ሌላኛውን እያቋረጡ በሚጠዛጠዙበት ጊዜ ክርክሩ ወደተሟላ ደረጃ የደረሰ ሲሆን ለዚህ የአጻፋ ምላሽ የኤርትራው አምባሳደር እንዲህ የሚል ትችት አቀረበ፡
“እስከ አሁን ድረስ በጨለማ ውስጥ ነው ያለ ስል በጣም አዝናለሁ… ኤርትራ ለአልሻባብ ምንም ዓይነት እርዳታ አልሰጠችም እያለ መርማሪ ቡድኑ በየጊዜው ዘገባ ሲያወጣ ቆይቷል“ በማለት የኤርትራው አምባሳደር ካደ፡፡ የዘ-ህወሀቱ አምባሳደር ጨዋነትን ባልተላበሰ መልኩ የኤርትራውን አምባሳደር በሚያቋርጥበት ጊዜ የኤርትራው አምባሳደር በጣም ተበሳጨ እና “እባክህ! እባክህ ልናገርበት! በመሸታ ቤት ውስጥ አይደለም ያለነው፡፡ ያለነው በሕዝብ ፊት ነው፡፡ ሕዝቡ እኛን እየተመለከተ ነው“ በማለት የኤርትራው አምባሳደር ተማጽዕኖውን አቅርቧል፡፡
የአልሻባብ ውንጀላ ለኤርትራው አምባሳደር የመጨረሻው የተወረወረ ገለባ መሆን ነበረበት፡፡ ሆኖም ግን የኤርትራው አምባሳደር እንደገና ሙሉ መተማመንን በተላበሰ መልኩ መተቸቱን እንዲህ በማለት ቀጠለ፣ “እነርሱ [ዘ-ህወሀት] በኢትዮጵያ ውስጥ 400 አማጺ ኦሮሞዎችን ገድለዋል፡፡ የዘ-ህወሀት አገዛዝ ከእራሱ ሕዝብ ጋር በሰላማዊ ሁኔታ አይደለም ያለው፡፡ በሁሉም አቅጣጫዎች በመተኮስ ላይ ነው የቆየው፡፡“ የዘ-ህወሀት አምባሳደር እጆቹን ወደ ኤርትራው አምባሳደር አቅጣጫ ማወናጨፉን እንዲያቆም እንዲህ በማለት ትዕዛዝ ሰጠው፡፡ “እጆችህን እንደ እኔ ሁሉ እዚያው በእራስህ ምህዋር ጠብቅ [የእራሱን እጆች በወንበሩ መደገፊያ ላይ እንዴት አድርጎ እንዳስቀመጠ እያመላከተ]“ እጅግ በጣም አስገራሚ ነገር ነበር!
የኤርትራው አምባሳደር ከመቅጽበት ቱግ ብሎ ተቆጣ እና እንዲህ አለ፣ “በርቀት የምትጓዝ ከሆነ እኔም በርቀት እሄዳለሁ፡፡ እርሱ [የዘ-ህወሀት አምባሳደር] ከትግራይ ወገን ውስጥ አይደለም፡፡ የእርሱ ህዝቦች ተገድለዋል፡፡ እርሱ ኦሮሞ ነው፡፡ በርቀት የምትጓዝ ከሆነ እኔም በርቀት እሄዳለሁ“ አለው፡፡
የዘ-ህወሀት አምባሳደር እንደገና እንዲህ በማለት ተኮሰ፣ “ለኦሮሞዎች አንተ ልትናገርላቸው አትችልም“ አለው፡፡
የኤርትራው አምባሳደር ብልጠትን ባዘለ፣ ፈጣን በሆነ እና ጨዋነትን ባልተላበሰ መልኩ “ለኦሮሞዎች መናገር እችላለሁ“ አለው፡፡
የኤርትራው አምባሳደር እንዲህ በማለት ክሱን አጠናከረ፣ “አንተው ጀመርከው፡፡ ስለእኛ ውስጣዊ ጉዳይ ብዙ አወራህ፡፡“
የዘ-ህወሀት አምባሳደር በተኩስ የዒላማ ጨዋታ ጥይት መደብደብ ስላልፈለገ የነገሩን ዳህራ ወደ ሌላ አቅጣቻ በማዞር እንዲህ አለ፣ “እኛ ፖሊሲ አለን…ኤርትራ ጥቃት የምትሰነዝርብን ከሆነ ለጥቃቱ ተመጣጣኝ የሆኑ እርምጃዎችን እንወስዳለን፡፡ እነርሱ በተዋጊ አውሮፕላን የሚደበድቡን ከሆነ እኛም በተመሳሳይ መልኩ በአውሮፕላን የአጻፋ ምላሽ እንሰጣለን፡፡ በመሬት ላይ ጥቃት የሚፈጽሙብን ከሆነ እኛም በመሬት ላይ ተመጣጣኝ ጥቃት እንፈጽማለን“ ነበር ያለው፡፡
የኤርትራው አምባሳደር እራሱን በማረጋጋት እንዲህ በማለት ጸጥ ለማለት ሞከረ፡
“ጸጥታ በነገሰበት ሁኔታ መናገር እችላለሁን?” እባክሽንእርሱን [የዘ-ህወሀትን አምባሳደር] ጸጥ እንዲል ልታደርጊው ትችያለሽን?... ለድንበር ውዝግቡ ቀላል የሆነ መፍትሄ አለ… በሰላም መኖር እንፈልግ ነበር… አሁን በህይወት የሌለው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እየደጋገመ በኤርትራ ውስጥ የአገዛዝ ለውጥ መደረግ አለበት እያለ በየጊዜው ሲናገር ቢቆይም ከአገዛዝ ለውጥ በኋላ በወሰኑ አካባቢ ምን ሊመጣ እንደሚችል እንኳ አያውቀውም በማለት ስናገር ሀዘን ይሰማኛል ምክንያቱም አንድ ጊዜ አፉ ላይ ካስቀመጡለት እርሱም እራሱ የአገዛዝ ለውጥ መደረግ አለበት ወዘተ፣ ወዘተ፣ ወዘተ በማለት ይናገራል፡፡ እርሱ [ደሳለኝ] እራሱ የአብዮቱ እና የአገዛዙ አካል አልነበረም፡፡ ሆኖም ግን እንዲሁ በእጅ ብድግ በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ስለሆነም በድንበር ውዝግቡ ላይ የተሰጠውን ፍርድ በመቀበል የእራሱን ኃይሎች ከአካባቢው ለማንቀሳቀስ በኢትዮጵያ መንግስት፣ በህወሀት መንግስት እና በአናሳው መንግስት የሚወሰን ይሆናል፡፡ እኛ ግን የዴፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን ጀምረናል…”
ቃለመጠይቅ አድራጊዋ ጋዜጠኛ ስለ ሰብአዊ መበቶች አያያዝ ጉዳዮች እና ዜጎች በኤርትራ ውስጥ ታፍነው ስለሚሰወሩበት ሁኔታ ጥያቄ ባቀረበችለት ጊዜ የኤርትራው አምባሳደር የጭቃ ጅራፉን ማጮህ ጀመረ፡፡ እንዲህ በማለት ገለጻ አደረገ፣ “ከዚህ አካባቢ የተሰደዱት ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ናቸው“ ጠበቅ ተደርጎ ሲያዝ እንዲህ በማለት ጋዜጠኛዋን መክሰስ ጀመረ፣ “ትልቁ ችግር እናንተ ኃላፊነት የሚሰማችሁ ጋዜጠኞች አይደላችሁም፡፡ ምንም ዓይነት የእራሳችሁን ምርመራ አታደርጉም፡፡ ታውቃላችሁ ችግሩ ያለው በኢትዮጵያ ላይ እንደሆነ ማወቅ ነበረባችሁ፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ናቸው የእራሳቸውን ሕዝቦች በመግደል ላይ ያሉት፡፡ ኤርትራ የእራሷን ዜጎች ገትድላለች የሚል አንድም ዓይነት ዘገባ ማቅረብ አትችሉም፡፡ በዚህ ላይ የእራሳችሁንም ምርምር በማድረግ መምጣት አለባችሁ፡፡ እኛ በየጊዜው የምናወጣቸውን ጋዜጣዊ መግለጫዎች እና ማንኛውንም ነገር አንብባችሁ መምጣት አለባችሁ…“
በቃለመጠይቁ የመጨረሻ ደቂቃ ላይ ከሰል ድስቱን ጥቁር ብሎ የመጥራት ያህል በሆነ መልኩ የተጠናቀቀ ነበር፡፡
የኤርትራ አምባሳደር እንዲህ የሚል አንድ የመጨረሻ ቃል ነበረው፣ “ይህ አናሳ መንግስት ወደ ህሊናው መመለስ እንዳለበት ተስፋ አደርጋለሁ“ የሚል ነበር፡፡
ቃለመጠይቅ አድራጊዋ ቃለመጠይቁ ተጠናቅቋል በማለት ካወጀች በኋላ የዘ-ህወሀት አምባሳደር እንደገና ተመልሶ የመጨረሻ መለስ ለመስጠት እንዲህ ብሎ ነበር፣ “ይህ መንግስት [የኤርትራ] ለበርካታ ዓመታት ምርጫ የሚባል ነገር አያውቅም፡፡ ለብዙ ዓመታት ምርጫ የሚባል ነገር በፍጹም አያውቅም፡፡ ይልቁንም ይኸ መንግስት ነው ሕዝቡን ለበርካታ ዓመታት በመግደል ላይ ያለው“ ነበር ያለው፡፡
አቤቱ ፈጣሪያችን!
እንዴት ያለ የሚያስገርም ነገር ነው እባካችሁ?
የዘ-ህወሀት አምባሳደር ዘ-ህወሀት እ.ኤ.አ ግንቦት 2015 ምርጫውን መቶ በመቶ በማሸነፍ ድል ተጎናጽፊያለሁ በማለት ያውጀውን እውነታ የተገነዘበው አይመስለኝም፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 ዘ-ህወሀት 99.6 በመቶ አሸነፍኩ በማለት እምቧ ከረዩ ሲል የነበረውን የሚያውቀው አይመስለኝም፡፡
ማወቅማ ያውቀዋል ግን አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም ነው ነገሩ!
ጉድ እኮ ነው ጎበዝ የዘ-ህወሀቱ አምባሳደር ኤርትራ ለበርካታ ዓመታት ምርጫ አታውቅም በማለት ለኤርትራው አምባሳደር የባዶ ዲስኩሩን ገለጻ ሲያቀርብ አጃይብ ከማለት በስተቀር ሌላ ምን ሊባል ይችላል! (የዘ-ህወሀት አምባሳደር በመሬት ላይ አምባሳደር ሆኖ ሳያገለግል በየትኛው ፕላኔት ላይ አምባሳደር ሆኖ ነው ጊዜዉን የምያሳለፈው ጃል!?)
የዘ-ህወሀት አምባሳደር በመስታወት ቤት ውስጥ የሚኖር ሰው ድንጋይ አይወረውርም የሚለውን የቆየ የኢትዮጵያውያን አባባል የሰማ ያለመሆኑን እገምታለሁ፡፡
ወይም ደግሞ የእውነት መንፈስ በአባዩ ህሊናህ ውስጥ እንዲያድር በቅዱሱ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈውን እና እንዲህ የሚለውን መስመር አላነበበም፡ “አንተ አስመሳይ በመጀመሪያ ደረጃ በአንተ ዓይንህ ውስጥ ያለውን ጉድፍ አውጣ፡፡ ከዚያም በኋላ በወንድሞችህ ዓይን ውስጥ ተጋርጦ የሚገኘውን ጉድፍ ጥርት ባለ ሁኔታ ትመለከታለህ፡፡“
በእነዚህ አምባሳደሮች መካከል በተደረገው የቃላት የተኩስ ልውውጥ ውስጥ ማን አሸናፊ ሆኖ ወጣ?
ሁሉም አፍሪካውያን ተሸነፉ፡፡
ጥያቄዬን እንዲህ በማለት እንደገና አቀርበዋለሁ፣ የአፍሪካ ቀንድ ተስፋ ሊኖረው ይችላልን?
ወገኖቼ ዓላማ አለን የሚሉ ሁለት የጎረቤት ሀገሮች በሰለጠነ መልክ፣ በተገራ አንደበት፣ ክብርን ባጎናጸፈ ሁኔታ፣ በመከባበር እና አርቆ አሳቢነትን ባከተተ መልኩ መነጋገር ካልቻሉ ተስፋ ይኖራል ብላችሁ ታስባላችሁ?
ዓላማ አለን የሚሉ የሁለት የጎረቤት ሀገሮች ዴፕሎማቶች ዘለፋን የሚገበዩ ከሆነ እና ለእርባናቢስ የፖለቲካ አጀንዳቸው ሲሉ አንደኛው በሌላኛው ላይ ሲቀልድ፣ ጉራውን ሲቸረችር፣ ሲበጠብጥ፣ ሲጮህ እና ሸፍጥ ሲሰራ ተስፋ ይኖራል ብላችሁ ታስባላችሁ?
ዓላማ አለን የሚሉ ሁለት የጎረቤት ሀገሮች ዴፕሎማቶች በንዴት እየጦፉ በመመጻደቅ በማሞኘት፣ በመናቅ፣ በጥላቻ፣ አሳንሶ በማየት እና በማጭበርበር የዓይናቸውን ቅንድብ ወደ ላይ በመሸብሸብ በንዴት የሚጦፉ ከሆነ ተስፋ ይኖራል ብላችሁ ታስባላችሁ?
ለሁለቱ አምባሳደሮች አስተማሪ የሆነች አጋጣሚ፣
የአስተማሪዎች ችግር ማስተማር የመውደዳቸው ጉዳይ ነው፡፡ እዚህ ጋ ለሁለቱ አምባሳደሮች እና ለሚወክሏቸው አገዛዞች ትምህርታዊ ዕድል እንዳለ አድርጌ አስባለሁ፡፡
እነዚህ አምባሳደሮች ከእነርሱ ታላቅ መሪዎች የተዋጊነት፣ በቅራኔ የተሞላ፣ ጀብደኛ፣ በቀላሉ የሚገነፍሉ እና ጠብየለሽ በዳቦ ከሆኑት ፍጡሮች የተማሯቸው ነገሮች ስለመኖራቸው እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ሆኖም ግን ከዚያ የተማሩት ነገር ይኖራል ብዬ እገምታሁ!
ያም ሆነ ይህ ባለፉት አስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከዘ-ህወሀት ጋር መነጋገር ማለት በጥቁር ባልጩት ድንጋይ ላይ ውኃ ከማፍሰስ ጋር መሳ ለመሳ እንደሆነ ግንዛቤ ወስጃለሁ፡፡ ፍጹም በሆነ መልኩ እርባናቢስ ሙከራ ነው፡፡
አንድ ምሳሌ እነሆ፡፡ ከሶስት ዓመታት በፊት በዩናይትድ ስቴትሰ አሜሪካ ውስጥ ያልተመዘገበ ቦንድ መሸጥ ወንጀል ነው በማለት ነግሪያቸው ነበር፡፡ ሊጥሱት የፈለጉትን የዩናይትድ ስቴትስን ሕግ አንቀጽ እና ምዕራፍ ሰጠኋቸው፡፡
ሆኖም ግን ሁልጊዜ ስለድክመታቸው እና ከሕግ አግባብ ውጭ ስለሚያከናውኑት መጥፎ ተግባራቸው በተደጋጋሚ ጠንካራ ትችት የሚያቀርብባቸው ሰው በመሆኑ ምክንያት ሊሆን ይችላል ጉዳዩን ከምንም ሳይቆጥሩት ቀሩ፡፡ ሆኖም ግን እውነተኛውን ነገር ፊት ለፊት በመናገር ከወንጀል ድርጊቶቻቸው እንዲቆጠቡ በግልጽ ነግሪያቸው ነበር፡፡
በዚህም መሰረት የእኔን ምክር ከምንም ባለመቁጠር እና ባለመቀባለቸው በአሁኑ ጊዜ ላታለሉት እና ለዘረፉት የዲያስፖራ ማህበረሰብ 6.5 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ ተገደዋል፡፡
ማናቸውም ቢሆኑ የእኔን ምክር ይቀበላሉ የሚል እምነት የለኝም ሆኖም ግን ከመናገር ወደኋላ አላፈገፍግም፡፡
ለእነዚህ ደንቆሮ አምባሳደሮች ልሰጣቸው የምፈልገው ምክረ ሀሳብ ቢኖር እነርሱ እና ተባባሪዎቻቸው በዲጂታል ዴፕሎማሲ ዘመን የእራሳቸውን የስራ ድርሻ አበጥረው ማወቅ እንደሚኖርባቸው ማስገንዘብ እፈልጋለሁ፡፡
የእነርሱ የዓለም አማጺያን እና የጫካ ዴፕሎማሲ ጊዜው አልፏል፡፡
የመንግስታት ውስጣዊ ሚስጥሮች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይፋ በሚሆኑበት እና በኮምፒውተር ቁልፍ መክፈቻ እና በኢንተርኔት መረብ ግንኙነት ለእያንዳንዱ ሰው መረጃ በሚቀርብበት በአሁኑ በዲጂታል ዴፕሎማሲ ዘመን እየኖርን እንገኛለን፡፡ የዊኪሊክስ /የመግቢያ ገመዶች አማካይነት መንግስታት ውሸቶቻቸውን፣ መጥፎ ድርጊቶቻቸውን እና ሙስናቸውን ለመደበቅ አሰቸጋሪ ሁኔታ ላይ ወድቀው ይገኛሉ፡፡
ሁለቱም አምባሳደሮች ሲደረግላቸው ከነበረው ቃለመጥይቅ አፈጻጸማቸውን እንደገና መለስ ብለው መገምገም እና ከዚያም ትምህርት መውሰድ እንዳለባቸው ተማጽዕኖዬን አቀርባለሁ፡፡ በዴፕሎማሲ አመራር ላይ አንድ ወይም ሁለት ኮርሶች መውሰድ እንዳለባቸው ማሰብ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም ማለት ዴፕሎማቶች እርስ በእርሳቸው ለመግባባት መናናቅ እና መዘላለፍ የለባቸውም፡፡
በዴፕሎማቶች የሚነገሩ ልዩ የሆኑ ቋንቋዎችን መማር እና መጥፎ ዴፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን እና ንግግሮችን በሚገባ ማወቅ እና መካን ይኖርባቸዋል፡፡ (መካን አለባቸው በምልበት ጊዜ የአስመሳይነት ዴፕሎማሲን ማለቴ አይደለም፡፡)
የለየለት ወሮበላ ዘራፊ ልዩ መለያ ልብስ ለብሰው ከመታየት ቢያንስ የህዝብ ዴፕሎማቶችን መምሰል አለባቸው፡፡
ቃለመጠይቅ የንግግር ስረ መሰረትን ለማሳት በመድረክ ላይ የሚደረግ ንግግር እንዳልሆነ መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ዴፕሎማሲ በማንኛውም ረገድ የቃላት ጦርነት ወይም ደግሞ የጦርነት ዴፕሎማሲ ጦርነት ማለት አይደለም፡፡
ዴፕሎማቶች ለእነርሱ የተዘጋጁላቸውን ጥያቄዎች መመለስ እንጅ እዚህም እዚያም በመርገጥ አግባብነት ከሌላቸው ጉዳዮች ጋር በማገናኘት የህዝብን ስሜት ለማስቀየስ ጥረት ማድረግ የለባቸውም፡፡
አንድ ቃለመጠይቅ የሚደረግለት ዴፕሎማት ከሌላው በተቃራኒ በኩል ቃለመጠይቅ ከሚደረግለት ሰው ጋር በሚጋጭበት ጊዜ ቃለመጠይቅ አድራጊውን ጋዜጠኛ መዘለፍ አግባብነት የለውም፡፡ ፕሮፌሽናል ባለሙያ የሆነችውን ጋዜጠኛ ኦክዋራን ቃለመጠይቅ ከማድረግሽ በፊት ምርምር ሳታደርጊ ቃለመጠይቅ የምታደርጊ ኃላፊነት የጎደለሽ ጋዜጠኛ ነሽ ብሎ መክሰስ ይቅርታ ሊደረግለት እና ማስተባበል ሊደረግበት የማይችል ጉዳይ ነው፡፡
ሁለቱ አምባሳደሮች እርስ በእርሳቸው ይቅር እና ለጋዜጠኛውም ቢሆን ክብር ማሳየት ይኖርባቸዋል፡፡
ሁለቱ አምባሳደሮች ዓለም አቀፍ ለሆኑ ጉዳዮች ልዩ ትኩረት በመስጠት መልካም የሆነ የጋዜጠኝነት ክብር መስጠት እንጅ እንደ አፍሪካ የቢራ ወይም መሸታ ቤቶች ውስጥ እንደሚደረገው ጭቅጭቅ፣ የዘፈቀደ አካሄድ፣ እርባና የለሽ ባህሪ ማሳየት እና የሞኝነት አካሄድ ማንጸባረቅ በፍጹም የለባቸውም፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ታላላቅ ዴፕሎማቶች ታላቅ አድማጮች ናቸው፡፡ የጩኸት ዴፕሎማሲ ታላቅ ዴፕሎማሲን አይፈጥርም፣ ይልቁንም ታላቅ የወሮበላ የዘራፊ ዴፕሎማሲን ብቻ ነው ሊያስገኝ የሚችለው፡፡
ተጠቃሚ መሆን አለባቸው፡፡
ተስፋየለሽነትን ሳይሆን የዴፕሎማሲ ተስፋን ለመተንበይ መሞከር ይኖርባቸዋል፡፡ የአፍሪካ አምባሳደር መሆን ይኖርባቸዋል እንጅ ተስፋቢስ የአፍሪካ አምባሳደሮች መሆን የለባቸውም፡፡
የአፍሪካ ቀንድ ተስፋ ሊኖረው ይችላልን?
እ.ኤ.አ ጥቅምት 2014 “የህወሀት ወሮበላ የዘራፊ ዴፕሎማሲ” በሚል ርዕስ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡ ያቀረብኩት ትችት በዋሺንግተን ዲ.ሲ. የኢትዮጵ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ውስጥ ተቃዋሚዎች ለመግባት በመሞከራቸው ምክንያት የዘ-ህወሀት ዴፕሎማት የጥይት ተኩስ በመክፈት ከተማውን ሲያተራምስ የነበረበትን አስደንጋጭ እና አሳፋሪ ድርጊት ያጋለጠ ነበር፡፡ ከጫካ ጀምሮ የለመደውን በተቃዋሚዎች ላይ ተኩስ በመክፈት ትርምስ ሲፈጥር ለነበረበት ሁኔታ የዴፕሎማሲ ከለላ እንዲለምድ ለመደረጉ ከታውስታ የማይጠፋ በመሆን የሚደንቀኝ ይሆናል፡፡ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከፍተኛ ተልዕኮ ያለው የውጭ ሀገር ዴፕሎማት መሆኑን እረስቶታልን?
የሁለቱን አምባሳደሮች ቃለመጠይቅ በማይበት ጊዜ ተመሳሳይ ስሜት ተሰምቶኛል፡፡ ብቸኛው ልዩነት የኤምባሲው ዴፕሎማት ሽጉት የያዘ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡
የአፍሪካ ቀንድ ተስፋ ሊኖረው ይችላልን?
ደህና…
ተስፋ በስሜታዊነት የተሞላ ነው፣
በቀዝቃዛዋ መሬት አዳምጨዋለሁ፣
በእንግዳው ባህርም አዳምጨዋለሁ፣
ሆኖም ግን በውኑ ዓለም የለም፣
የእራሴን ግን ጠይቆኛል፡፡
ለአፍሪካ ቀንድ ትንሽ የተስፋ ፍርፋሪ የሚሰጠኝ ባገኝ አንዴት ደስ ባለኝ!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ሰኔ 21 ቀን 2008 ዓ.ም