ኢትዮጵያ አዲስ ህገ መንግስት ያስፈልጋታልን?
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
ጥያቄ ሆኖ መቅረብ ያለበት ጉዳይ ኢትዮጵያ አዲስ ሕገ መንግስት ትፈልጋለችን የሚለው አይደለም፡፡
መጠየቅ ያለበት ግን በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ሕገ መንግስት የሌላት ሀገር ስለሆነች ሕገ መንግስት ትፈልጋለችን? የሚለው ነው፡፡
“የ1995 የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት” እየተባለ የሚጠራው ሕገ መንግስት በዘ-ህወሀት ለዘ-ህወሀት የተዘጋጀ የዘ-ህወሀት ሕገ መንግስት ነው፡፡
ዘ-ህወሀት (የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ) በአሁኑ ጊዜ ስሙ በዓለም አቀፍ የአሸባሪዎች የመረጃ ቋት ስም ዝርዝር ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኝ የታወቀ የማፊያ አሸባሪ ድርጅት ነው፡፡
የዘ-ህወሀት ሀሳብ የለሽ፣ ጋጠወጥ እና ድፍረት የተሞላበት አውዳሚ የፖለቲካ ዓላማ ግልጽ በሆነ እና በማያሻማ መልኩ በሕገ መንግስት ተብዬው ሰነድ ውስጥ በዝርዝር ተጽፎ ይገኛል፡፡
የዘ-ህወሀት ሕገ መንግስት የፌዴራል እና ዴሞክራሲያዊ የመንግስት መዋቅር ለመመስረት ዓላማ ያደረገ ነው፡፡
ይኸ የፌዴራል እና ዴሞክራሲያዊ የመንግስት መዋቅር እየተባለ የሚጠራው መንግስታዊ መዋቅር አንድ እና አንድ ዓላማ ብቻ አለው፡፡ ይኸውም የፖለቲካ ስልጣኑን ማዕከላዊ በሆነ መልኩ ሙሉ በሙሉ ጠቅልሎ በመያዝ እና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙትን ሌሎችን የፖለቲካ ቡድኖች እና ድርጅቶችን አቅም የለሽ እና ምንም ነገር ለመስራት እንዳይችሉ ሽባ በማድረግ የፖለቲካ ስልጣኑን በብቸኝነት ዘ-ህወሀት ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጠር ማድረግ ነው፡፡
የዘ-ህወሀት የፌዴራል ሕገ መንግስት እ.ኤ.አ መጋቢት 1953 ከሞተው እና ደም ከተጠማው የሶቪየት ህብረት ንጹሀን ዜጎች ጨፍጫፊ ከነበረው ከጆሴፍ ስታሊን የጽሁፍ ዘዬ እና የርዕዮት ዓለም ግፊት በቀጥታ ተኮርጆ የተጻፈ ነው፡፡
እ.ኤ.አ በ1912 በቦልሸቪክ ፓርቲ ውስጥ በተፈጠረው ርዕዮተ ዓለማዊ እና ድርጅታዊ ቀውስ ምክንያት እርስ በእርሳቸው የሚሻኮቱ እና በጥላቻ የተሞሉ ተቀናቃኝ ቡድኖች ተፈጠሩ፡፡ በዚያን ወቅት በቦልሸቪክ ፓርቲ ውስጥ በጣም ወሳኝ የሆነው እና የርዕዮት ዓለም አለመስማማት ጉዳዮች ዋና መነሻ ሆኖ የቀረበው “የብሄር ጥያቄ” ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ1913 ስታሊን “ማርክሲዝም እና የብሄር ጥያቄ” በሚል ርዕስ አንድ ጽሁፍ ጻፈ፡፡ በዚያ ጽሁፍ ውስጥ ለብሄር ጥያቄ ጭቆና መፍትሄው ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች እያለ ለሚገልጻቸው ሁነቶች እውንነት እውቅና መስጠት እና ይህንን ጉዳይ በቦልሸቪክ ፓርቲ የፖለቲካ ፕሮግራም ውስጥ ማካተት ነው በማለት ሞገተ፡፡
ስታሊን እያራመደ የነበረውን የክርክር ጭብጥ ለመደገፍ በማሰብ ቁስ አካል/dialectical materialism የሚለውን የማርክስን ህልዮት በመውሰድ በስራ ላይ አዋለ፡፡ ስታሊን የብሄሮች እና የብሄር መንግስታት መነሳሳት እና የብሄራዊ ንቃተ ህሊና እውን መሆን ገበያዎችን ለማስፋፋት ሲባል በቡርዥዋው መደብ የሚመራ ልዩ የሆነ የካፒታሊስት ክስተት ነው በማለት የክርክር ጭብጡን አቀረበ፡፡
እ.ኤ.አ በ1914 ሌኒን “የእራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል” በሚል ርዕስ ጽሁፍ ካዘጋጀ በኋላ የስያሜውን ምክንያት እንዲህ በማለት አቀናበረው፡ “ቡርዥዋው የሀገር ውስጥን ገበያ መቆጣጠር አለበት፣ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ አንድ ዓይነት ቋንቋ መናገር የሚችሉ ህዝቦች እና የፖለቲካ መስተጋብርን የፈጠሩ ግዛቶች መኖር አለባቸው፡፡”
በቅድመ ካፒታሊስት (ፊውዳሊስት) ማህበረሰብ ውስጥ የጋራ የሆነ የጎሳ፣ የቋንቋ ወይም ደግሞ ባህልን መሰረት ያደረገ እውነተኛ ብሄራዊ የህብረተሰብ ንቃተ ህሊና አልነበረም፡፡ ቅድመ ካፒታሊስት ማህበረሰቦች የሚታወቁት በአጠቃላይ በፊውዳሉ የስልጣን ተዋረድ መሰረት የመንደሮች፣ የከተሞች እና የአካባቢዎች ባለስልጣኖች እና በይበልጥም ደግሞ በግዛቱ ውስጥ ያለውን መሬት በሙሉ ጠቅልሎ ለመያዝ ስልጣን ያለው ንጉሰ ነገስቱ ያሉበት ስርዓት የነበረ መሆኑ ነው፡፡
የካፒታሊስት ስርዓት ማቆጥቆጥ እና በቀጣይም የቡርዥዋው ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት መከሰት ለብሄር መንግስታት መመስረት እና የብሄራዊ ንቃተ ህሊና እና የማንነት ጥያቄ መዳበርን አስከተለ፡፡ እንደ ስታሊን አስተሳሰብ ጥቂት የምዕራብ አውሮፓ መንግስታት የብሄር ጥያቄን አስወገዱ ምክንያቱም በካፒታሊስቱ አብዮት ጊዜ የብሄር መንግስታትን አቋቁመው ነበርና ነው፡፡ በምስራቅ አውሮፓ ቀደም ሲል የነበሩ ግዛቶች ለምሳሌ ያህልም የአውስትሮ ሀንጋሪ ግዛት የጎሳ ቡድኖች በአንድ የብሄር መንግስት ውስጥ ከመምጣታቸው እና የብዙ ብሄሮች መንግስታት ችግር ከመፈጠሩ በፊት ተከስቶ ነበር፡፡
የብሄር ጥያቄን ትንታኔ ለመስጠት ስታሊን የእራሱን የብሄር ትርጉም ሰጠ፡፡ እንዲህ በማለት ሞገተ፣ “ብሄር ቋንቋን፣ ግዛትን፣ የኢኮኖሚ ህይወትን እና የስነልቦናዊ ዘይቤን በማካተት የጋራ ባህልን መሰረት በማድረግ ታሪካዊ በሆነ መንገድ የተመሰረተ፣ የተረጋጋ ማህበረሰብ ነው፡፡“ እንዲህ የሚል አጽንኦም ሰጥቷል፣ “እነዚህ ሁሉ ባህሪያት በአንድነት ሲኖሩ ብቻ ነው ብሄር የሚኖረን፡፡“
እንደ ስታሊን እና ሌኒን ያሉ ጽንፈኛ የቮልሸቪክ አመራሮች ባሉባት ሩሲያ የሩሲያ የብሄር ጥያቄ (በሩሲያ ግዛት የብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ጭቆና) አስቸጋሪ መሆኑ ተረጋገጠ፡፡
የሩሲያ ግዛት ሌኒን እንዳለው በርካታ ትናንሽ ብሄሮችን ወይም ደግሞ ህዝቦችን ማለትም ዩክሬኖችን፣ ፖሎችን፣ አርመኖችን፣ አዘርባጃኖችን፣ ፊኖችን፣ ጆርጃዎችን፣ ወዘተ አካትቷል፡፡ ሌኒን በሩሲያ ግዛት ውስጥ የብሄራዊ ነጻነት ንቅናቄዎችን በመደገፍ ብሄሮች ፍጹም አብዮታዊ በሆነ መልኩ የእራስን ዕድል በእራስ መወሰን እስከ መገንጠል ጥያቄ እንዲያራምዱ ይቀበላል፣ ይደግፋልም፡፡ ሌኒን እንዲህ በማለት ይሞግታል፣ “በእኛ የፖለቲካ ቅስቀሳ የመገንጠል ጥያቄ መብትን መፈክር ለማራመድ እና ለመወትወት የማንችል እና የምንወድቅ ከሆነ በእጆቻችን ለቡርዣዎች እያጨበጨብን ብቻ አይደለም ያለነው፡፡ ሆኖም ግን ይህንን እያደረግን ያለነው ለፊውዳሎች እና ፍጹም ጨቋኝ ለሆነው ብሄር ጭምር እንጂ፡፡“ ከዚህም በተጨማሪ ሌኒን በቡርዥዋ ብሄራዊነት ስር ያለውን የብሄሮችን እና ብሄረሰቦችን ጭቆና ለማጥፋት ከሌላ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከሚጠየቅ አካሄድ የተለየ መሆን እንዳለበት ያምናል፡፡ በኋላ ግን ስታሊን ስሌታዊ በሆነ መልኩ እንዲህ በማለት ብዙ ጽፏል፡፡ “የእራስን ዕድል በእራስ መወሰን እስከ መገንጠል መርህ ለሶሻሊዝም ስርዓት ግንባታ ለሚደረገው ትግል እንደ መሳሪያ ሆኖ ሊያገለግል እና ለሶሻሊዝም መርሆዎችም ተገዥ ሆኖ ሊያገልግል ይችላል“ ብሏል፡፡
ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ እና የማርክስ ህልዮት አቀንቃኝ የሆነችው ሮሳ ሉክስምበርግ የእራስን ዕድል በእራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚለው የሰራተኛው መደብ ትግል አስፈላጊ አይደለም በማለት ከሌኒን መርህ ጋር አትስማማም፡፡ ምክንያቱም ትላለች ምክንያቱም ያ አደሀሪ አካሄድ ነው፣ ይልቁንም የተጨቆኑ ብሄሮች ለባህል ነጻነት ዓላማ አድርገው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡ ሉክሰምበርግ ሶሻሊስቶች ለዓለም አቀፋዊ የሰራተኞች ትብብር እንጂ ለብሄራዊ ነጻነት መታገል የለባቸውም ትላለች፡፡
ስታሊን እና ሌኒን “የብሄር ጥያቄ” በእራሳቸው አብዮት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን እንደምታ ተገንዝበዋል፡፡ ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ሁለት አደገኛ ሁኔታዎችን አስተውለዋል፡፡ እነርሱም፡
1ኛ) አብዮትን ሊያጠፋ ይችላል፡፡ የሩሲያ ግዛት ፌዴራላዊ የአወቃቀር ዓይነት ያለው እንዲሆን እና የጥገናዊ ለውጥ አራማጅ በሆኑት በርካታ ብሄራዊ ፓርቲዎች የተደራጀ እና የሚመራ ስርዓትን ሊያቋቁሙ ይችላሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹ የበርካታ ፓርቲ ስርዓት የእራሱን አብዮታዊ ባህሪነት በማሳጣት የነበረውን የሩሲያን የጭቆና አገዛዝ እንደነበረው ሊያስቀጥል ይችላል፡፡
2ኛ) የአብዮታዊ ሶሻሊስት ጉጉትን ውስጣዊ ስሜት በጨቋኙ የሩሲያ ግዛት ተሞክሮዎች የመተካት ወይም ደግሞ አንድ ላይ የማቀላቀል እውነተኛ አደጋ ነበር፡፡
በመጨረሻም ስታሊን እና ሌኒን የቦልሸቪክን አብዮት ለማፋጠን እና ስልጣንን በአስተማማኝ ሁኔታ ተቆጣጥሮ ለመቆዬት እንዲቻል የሩሲያን ግዛት ማፈራረስ እና ሕዝቡንም በብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች መከፋፈል አስፈላጊ ነበር በማለት ደመደሙ፡፡
የብሄር ጥያቄን ለብሄራዊ የቡርዥዋ ጭቆና እና የባህል፣ የቋንቋ መብቶች ጭቆናን ከብዙ በጥቂቱ በማሳየት እንደ መደብ ትግል እንዲያገለግል ፈልገዋል፡፡
የዘ-ህወሀት ሕገ መንግስት አንቀጽ 39፣
የዘ-ህወሀት ሕገ መንግስት አንቀጽ 39 (1) (የብሄሮች ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች መብት) የሚከተለውን መብት ያጎናጽፋል፡
በኢትዮጵያ እያንዳንዱ ብሄር፣ ብሄረሰብ እና ሕዝብ የእራስን ዕድል በእራስ መወሰን እስከ መገንጠል መብት አለው ይላል፡፡
አንቀጽ 47 የፌዴራል ዴሞክራሲያዊ ሬፐብሊክ አባል መንግስታትን በሚከተለው ቅደምተከተል መሰረት አስቀምጧል፡
1ኛ) የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት
2ኛ) የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት
3ኛ) የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት
4ኛ) የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት
5ኛ) የሶማሊ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት
6ኛ) የቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት
7ኛ) የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት
8ኛ) የጋምቤላ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት
9ኛ) የሐረሪ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት
ከዚህም በተጨማሪ ድሬዳዋን እና አዲስ አበባን የፌዴራል ከተሞች በማለት ለየብቻ የከተማ አስተዳደር በማለት አዋቅሯቸዋል፡፡
አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ቦልሸቪኮች የሩሲያን የግዛት አንድነት እንዳፈራረሱት ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት በማፈራረስ ስልጣኑን ለማጠናከር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ከስታሊን እና ከሌኒን ጽሁፎች ስለብሄር ጥያቄ እና የእራስን ዕድል በእራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚሉ ጠቃሚ የሆኑ ትምህርትችን ወስዶ በተግባር አውሏል፡፡
ቦልሸቪክ በሩሲያ ግዛት “የመደብ ትግል” እያለ የሚጠራውን ሀሳብ አምባገነኑ መለስ እንዳለ በመኮረጅ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ለኢትዮጵያ ግዛት “የጎሳ ትግል” እንዲተከል እና ዜጎች እርስ በእርሳቸው በጥርጣሬ እንዲተያዩ፣ የጥላቻ መንፈስ እንዲዘራ፣ ሀገራዊ ስሜት ጠፍቶ መንደርተኝነት እና ጎጠኝነት እንዲንሰራፋ በማድረግ ሀገርን እንዲያፈራርስ እሾሁን ተክሎ እና መርዙን ረጭቶ ተሰናብቷል፡፡
እንደ መለስ/ዘ-ህወሀት የዘልማድ ሀሳብ ትረካ “የኢትዮጵያ ግዛት” በተቀናቃኝ ፊውዳል የአማራ ነገስታት፣ መሳፍንት እና መኳንንት መካከል ለስልጣን የበላይነት እርስ በእርስ በተደረገ ትግል በ19ኛው ክፍለ ዘመን እውን ሆኗል፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ አጼ ቴዎድሮስ በሰሜን ኢትዮጵያ የሀገሪቱ ክፍል እራሳቸውን ንጉሰ ነገስት (የንጉሶች ሁለ ንጉስ) ብለው በመሰየም በሰራዊታቸው እየታጀቡ አዳዲስ መሬቶችን እየተቆጣጠሩ ወደ ደቡብ በመዝመት ብሄር ብሄረሰቦች እና ሕዝቦችን አስገብረው ግዛታቸውን አስፋፍተዋል፡፡ የአጼ ቴዎድሮስን መሞት ተከትሎ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ስልጣን በመያዝ ጦራቸውን በመምራት በርካታ መሬቶችን የተቆጣጠሩ ሲሆን ብዙ ብሄሮች፣ ብሄሮች እና ህዝቦችን አስገብረዋል ይላል፡፡
እንደ ዘ-ህወሀት አፈ ታሪክ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ፍጹም የተለያዩ “ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች” በኃይል እና ጭካኔ በተመላበት ሁኔታ አንድ እንዲሆኑ የተደረገ ጥረት ውጤት ናት፡፡
እ.ኤ.አ በ1993 አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ እና የዘ-ህወሀት ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ፈላጭ ቆራጭ መሪ የነበረው መለስ ዜናዊ ቃለ መጠይቅ ላቀረበለት ጋዜጠኛ “ኢትዮጵያ የ100 ዓመት እድሜ ብቻ አላት:: ከዚህ ውጭ ሌላ ታሪክ የሚያራምዱ ካሉ እነርሱ እራሳቸውን ወደ አፈታረክ ጨምረዋል” ነበር ያለው፡፡
ስታሊን እና ሌኒን የብሄር ጥያቄን የቦልሸቪክ ፓርቲ ወደ ስልጣን እንዲወጣና የበላይነቱን እንዲያረጋግጥ እንደተጠቀሙበት ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ አምባገነኑ መለስ እና ዘ-ህወትም የብሄር ጥያቄን የተጨቆኑ ብሄረሰቦች በኃይል እና ጭካኔ በተመላበት መልኩ በኃይል አንድ እንዲሆኑ በማሳመን ስልጣናቸውን በማጠናከር እና የበላይነታቸውን በማረጋገጥ ላይ ይገኛሉ፡፡
የተጨቆኑ ብሄረሰቦችን ችግር ለመፍታት ዘ-ህወሀት እንደ መፍትሄ የተጠቀመበት የጎሳ ፌዴራሊዝምን ሕገ መንግስታዊ እንዲሆን በማድረግ እራሳቸውን ነጻ በማውጣት የፖለቲካ፣ የባህል፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ወዘተ ድልን በመቀዳጀት ነጻ እና የራሳቸውን መንግስት ይመሰርታሉ የሚል ነበር፡፡
ሆኖም ግን ዘ-ህወሀት የጎሳ ፌዴራሊዝምን በመሸጥ የተጨቆኑ ብሄረሰቦችን አታሏቸዋል፡፡ አምባገነኑ መለስ እና ዘ-ህወሀት ስለተጨቆኑ ብሄረሰቦች ደንታ አልነበራቸውም፡፡ ዘ-ህወሀት አንዱ እና ዋናው ፍላጎቱ ሆኖ የቆየው እና አሁንም ተጠናውቶት የሚገኘው የበላይ የመሆን አባዜ ነው፡፡
በእርግጥ ዘ-ህወሀት ስለ ብሄር ጥያቄ የሚያሰማው የከበሮ ጩኸት እውነተኛውን እና የተደበቀውን ነገር ሳይታወቅ ሰውሮ ለማቆየት ነው፡፡
የዘ-ህወሀት አጀንዳ ሶስት ዓላማዎችን ያካትታል፡፡ እነርሱም፡
1ኛ) ዓላማው ለዘለቄታው በስልጣን ላይ ለመቆየት እና የኢትዮጵያ ህዝብ ገዥዎች በመሆን እራሳቸውን መከላከልን ማረጋገጥ፣
2ኛ) ኢትዮጵያውያንን በጎሳ፣ በአካባቢያዊነት፣ በቋንቋ፣ በባህል እና በኃይማኖት መስመር በመከፋፈል የእነርሱን አገዛዝ የሚቃወሙትን ሁሉንም ተቃዋሚዎች የማዳከም እና ሽባ የማድረግ ዓላማ፣
3ኛ) “አማራዎች” ተመልሰው ወደ ስልጣን እንዳይመጡ እና አማራ ያልሆኑትን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦችን መልሰው ባሪያ እንዳያደርጓቸው ምናባዊ የሆነን የአማራን የጭራቅነት ሸፍጥ ፈጥሮ እና ፈብርኮ በማሳየት ለተጨቆኑ ብሄረሰቦች ተከላካይ ሆኖ የመቅረብ የአታላይነት ተውኔትን ማቅረብ ነው፡፡
ቀላል በሆነ መንገድ ለመግለጽ ዘ-ህወሀት የጎሳ ፌዴራሊዝምን እንደ ሽፋን በመጠቀም ሆኖም ግን በድብቅ የማዕከላዊ መንግስቱን በመቆጣጠር እና በማጦዝ በሚስጥር በመንግስት ላይ መንግስት (ማፊያ አላልኩም) ለማቋቋም የሚያስችል ሕገ መንግስት አረቀቀ፡፡
አጠቃላይ የብሄር ጥያቄ ለአምባገነኑ መለስ እና ለዘ-ህወሀት ለዘላለማዊ የፖለቲካ የበላይነት ሲባል የህዝብን ቀልብ ለማስቀየስ እየተጠቀሙበት ያለ ታማኝነት የሌለው ሸፍጥ እና ተራ የማጭበርበር ዘዴ ነው፡፡ እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ግን የዘ-ህወሀት ዋናው እና ቁልፉ ተልዕኮ ለሁልጊዜ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ማፈራረስ እና ማውደም ነው፡፡
የእነርሱ ዋናው መሪ ዕቅዳቸው በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊነትን ማጥፋት ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እምነት የሌለው ማንም ኢትዮጵያዊ በእራሱ መሬት ላይ መኖር ይችላል፡፡ ዘ-ህወሀት ሌት ቀን እንደበቀቀን እየደጋገመ ለሚለፈልፍለት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችን እና ሕዝቦችን ነጻ ለማውጣት ምንም ዓይነት ዕቅድ የለውም፡፡ ዘ-ህወሀት አንድ ጊዜ ስልጣን ከያዘ በኋላ የኢትዮጵያን ግዛት የተጨቆኑ ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦችን ነጻ በማውጣት አስተባብራለሁ በሚል ማታለያ ለስልቱ ተግባራዊነት እንዲረዳው የብሄር ጥያቄን በማንሳት በማራገብ ላይ ይገኛል፡፡ ዋናው ዓላማቸው ግን አዲስ ስርዓት በመፍጠር የዘ-ህወሀትን ግዛት መመስረት ነው፡፡ (በነገራችን ላይ ማንም ቁንጮ የዘ-ህወሀት ባለስልጣን አሁን በህይወት የሌለውን አምባገነኑን መለስ ዜናዊን ጨምሮ “እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ወይም ደግሞ ኢትዮጵያን እወዳለሁ” በማለት የተናገሩት ካለ መቸውንም ጊዜ ቢሆን በኦዲዮ ወይም በቪዲዮ የተቀረጸ ማስረጃ አቀርባለሁ የሚል ሰው ካለ ፊት ለፊት ለመሞገት ዝግጁ ነኝ፡፡)
የዘ-ህወሀት ሕገ መንግስት በታሪክ አንዱ እና ዋናው የማጭበርበሪያ እርባናየለሽ ሰነድ ነው፡፡
እንዲህ የሚለው የብሩክሊን ድልድይ (ማለትም ላም አለኝ በሰማይ) የማጭበርበር ሸፍጥ ሁለተኛ ሊሆን ይችላል፡
“ ሄሎ ጌታዬ! እዚህ ያለውን አስደሳች እና ቀልብን የሚገዛ ድልድይ ሊገዙት ይችላሉን? ለዛሬ ብቻ በሽያጭ ላይ ይቆያል፡፡ ድልድዩን ለማቋረጥ ስለሚከፈለው ገንዘብ እስቲ ያስቡ፡፡“ ግራ የተጋበው ሰውዬ እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጠ፣ “እርግጠኛ ነህ ይኸ ድልድይ ይሸጣል?“ ሰውየው እንደገና እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጠ፣ “ታዲያ ለምን ይመስልሃል ይሸጣል የሚል ማስታወቂያ የተለጠፈበት?” አለ፡፡ ዘ-ሀወሀትም በብሄር ጥያቄ ስም ያደረገው ይህንኑ ነው፡፡
ዘ-ህወሀት የጎሳ ፌዴራሊዝም የብሩክሊን ድልድይን ለተጨቆኑ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ሸጧል፡፡ ይኸ የሚገኘው ከዘ-ህወሀት ብቻ ነው ብሎ ነግሯቸዋል፡፡ በጎሳ ፌዴራሊዝም መኖር የምታገኙትን ነጻነት እስቲ አስቡት በማለት የዘ-ህወሀት ሸፍጠኛ አታሎች በማደናገር ላይ ይገኛሉ፡፡
ያለምንም ጥርጥር የዘ-ህወሀት ሕገ መንግስት በአፍሪካ ውስጥ ከተጻፉት ሕገ መንግስቶች ሁሉ ታላቅ ማጭበርበር እና ሸፍጥን ያካተተ መናኛ ዉዳቂ ሰነድ ነው፡፡
የዘ-ህወሀት ሸፍጠኛ አጭበርባሪዎች ላለፉት 25 ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ የተጨቆኑ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ማታለያ የሸፍጥ ስም የማይነጥፍ ያጋተ የላም ጡት ወተትን በመጥባት ላይ ይገኛሉ፡፡
ዘ-ህወሀት የሌኒንን አባባል በመዋስ የተጨቆኑ ህዝቦችን ከኢትዮጵያ ግዛት የብሄረሰቦች እስር ቤት ነጻ ለማውጣት ለ25 ዓመታት ያህል የሸፍጥ ህገ መንግስታቸውን በማሳየት ላይ ይገኛሉ፡፡
በማስመሰያው ህገ መንግስት ዘ-ህወሀት የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር እየተባለ የሚጠራ የማጭበርበሪያ እና የሸፍጥ ግንባር በመፍጠር የአማራ ጭቆና ሰለባ የሆኑትን ነጻ እናወጣለን በማለት በማደናገር፣ ልክ ስታሊን እና ሌሊን እንዳደረጉት ሁሉ ዘ-ህወሀትም በተመሳሳይ መልኩ የእራስን ዕድል በእራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚለውን መብት አረጋግጠዋል፡፡ ይህም ማለት ከኢትዮጵያ መንግስት ጥላ ስር በማንኛውም ጊዜ ሙሉ በሙሉ በመገንጠል የእራስን መንግስት ማቋቋም ይቻላል የሚል ሆኖ ይገኛል፡፡ እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ግን ዘ-ህወሀት የእራሱን የፖለቲካ የበላይነት ለማቀላጠፍ እና ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ እንድትበጣጠስ የማድረጉ እውነታ ነው፡፡
እንደ ስታሊን ሁሉ አሁን በህይወት የሌለው የዘ-ህወሀት ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ፈላጭ ቆራጭ መሪ የነበረው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ በየትኛውም መለኪያ የማይገናኙትን እና የማይዛመዱትን የጎሳ ቡድኖች በአንድ የጎሳ ግዛት ቅርጫት ውስጥ እንዲታጨቁ አደረገ፡፡ አምባገነኑ መለስ እና ዘ-ህወሀት የራሳቸውን የሸፍጥ የጎሳ ፌዴራሊዝም ለመፍጠር ያለምንም ሙያዊ ጥናት በዘፈቀደ የሸፍጥ የይስሙላ የድንበር ወሰኖችን ፈጥረዋል፡፡ ለምሳሌ ያህልም በንጉሱ የአገዛዝ ዘመን የትግራይ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ የነበሩት ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም አሁን በቅርቡ ለአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት በሰጡት ቃለ መጠይቅ በትግራይ እና በቤጌምድር መካከል የነበረው ታሪካዊ የወሰን ድንበር የተከዜ ወንዝ ነበር፡፡ እናም ወልቃይት ጠገዴ መቸውንም ጊዜ ቢሆን በትግራይ አስተዳደር ውስጥ ገብቶ አያውቅም በማለት ቃለ መጠይቅ ሰጥተው ነበር፡፡ ሆኖም ግን በዘ-ህወሀት ህገ መንግስታዊ የቋንቋ፣ የታሪክ፣ የግዛት ምቹነት፣ የባህል፣ ወዘተ መስፈርት እንኳ ቢሆን ወልቃይት ጠገዴ በአማራ ክልል ውስጥ ሊካለል ይገባል፡፡ (እንዲያው ለታሪክ ያህል፡ በኢትዮጵያውያን ላይ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ወዘተ እየተባለ የመለያ ባጅ በመለጠፉ ዕኩይ ተግባር ላይ እምነቱ በፍጹም የለኝም፣ ከዚህ ቀደምም የለኝም ወደፊትም አይኖረኝም፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመረጠው ቦታ የመኖር፣ ስራ የመስራት እና ቤተሰብ የመመስረት ፍጹም የሆነ መብት እንዳለው ሙሉ በሙሉ አምናለሁ፣ ለዚህም ተግባራዊነት በጽናት እታገላለሁ፡፡)
ላለፉት 25 ዓመታት ዘ-ህወሀት የብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች መፈክርን በማራገብ ውጤታማ በሆነ መልኩ ጥቂት ሰዎችን ለብዙ ጊዜ፣ አብዛኛውን ህዝብ ደግሞ ለጥቂት ጊዜ ለማታለል ተጠቅሞበታል፡፡ ሆኖም ግን ሁሉንም ህዝብ ለሁልጊዜ ሊያታልል አልቻም፡፡
እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ግን የተጨቆኑ ብሄሮች እና የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች እየተባለ ሌት ቀን እንደሚደሰኮረው ሳይሆን መቸውንም ጊዜ ከጭቆና ነጻ ሆነው አያውቁም፡፡ ዘ-ህወሀት በጎሳ ፌዴራሊዝም ስም ዝም ብሎ በተግባር የማይገለጽ የይስሙላ ነጻነት ፈቅዷል፡፡
እንደስታሊን ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ አምባገነኑ መለስ እና ዘ-ህወሀት የእነርሱን አገዛዝ የሚቃወመውን እና የእራስን ዕድል በእራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚለውን የይስሙላ መብት ለመጠቀም የሚሞክረውን ቡድን ወይም ግለሰብ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ይጨቁናሉ፡፡
ሚሊዮኖችን እንዳጋዘው እንደ ስታሊን ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ አምባገነኑ መለስ ዜናዊ እና ዘ-ህወሀትም የአማራ ሰፋሪዎችን ህገ ወጥ ሰፋሪዎች በማለት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙትን በሺዎች የሚቆጠሩ አማራዎች እንዲጋዙ አድርገዋል፡፡
ዘ-ህወሀት የጋምቤላን እና የሌሎች አካባቢዎችን ህዝቦች በመንደር ማሰባሰብ በሚል ፈሊጥ ከቀያቸው በገፍ በማፈናቀል ከቀደምት አባቶቻቸው ጀምረው ሲጠቀሙበት የነበረውን መሬታቸውን እየነጠቁ ዓለም አቀፍ ለሆኑ አየር በአየር ነጋዴዎች የመሬት ቅርምት ሸፍጠኞች እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ ሲቸበችቡት ቆይተዋል፡፡
ዘ-ህወሀት ከአማራ አስፈሪ ጭራቅ ለመጠበቅ የእራስን ዕድል በእራስ መወሰን እስከ መገንጠል ለሚለው ዕኩይ መርሆው እራሱን መልዓክ አድርጎ በማቅረብ ለመከላከል ይሞክራል፡፡ ዘ-ህወሀት የእራስን ዕድል በእራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚለውን ዕኩይ መርሆውን አማራን ለማሸማቀቅ እና አማራው በሀገር አንድነት እና ነጻነት ላይ ያለውን ቀናኢነት ለማዳከም በማስፈራሪያነት እየተጠቀመ የኢትዮጵያን ብሄሮች እና ብሄረሰቦች በመጨቆን የግዛት ዕድሜውን ለማራዘም ይሞክራል፡፡
የዘ-ህወሀት ምዕናባዊ ጭራቅ ኢትዮጵያን በማሳደድ ላይ ነው፡፡ በኮሙኒስት ማኒፌስቶው ላይ የተቀመጠውን የማርክስን አባባል በመዋስ “ ይህንን እርኩስ መንፈስ ለማርከስ እና ፈውስን ለማምጣት ሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረግ አለባቸው፡፡“
በአሁኑ ጊዜ ዘ-ህወሀት የኢትዮጵያን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች በማዕከል በእራሱ ቁጥጥር ስር በማዋል ስልጣን አልባ አድርጎ በመግዛት ላይ ይገኛል፡፡
ዘ-ህወሀት በማንኛውም ረገድ የፌደራል ስርዓት መዋቅሩን በበላይነት ተቆጣጥሮ ይገኛል፡፡ ዘ-ህወሀት በኢትዮጵያ ምድር ላይ መቶ በመቶ ተቆጣጥሮ ይገኛል፡፡
ዘ-ህወሀት በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ወታደራዊ ኃይል፣ የደህንነቱን እና የፖሊስ መዋቅሩን መቶ በመቶ ተቆጣጥሮ ይገኛል፡፡
ዘ-ህወሀት ኢኮኖሚውን መቶ በመቶ በመቆጣጠር በደጋፊዎቹ እየታገዘ በመመዝበር የእራሱን የክሮንይ (crony) ካፒታሊዝም ስርዓት ፈጥሮ ይገኛል፡፡
ዘ-ህወሀት ቢሮክራሲውን እና የፍትህ ስርዓቱን መቶ በመቶ በእራሱ ቁጥጥር ስር አድርጓል፡፡
በኢትዮጵያ የውሸት ግዛት የሚበሳጩ ኢትዮጵያውን እውነተኛው እና ድብቁ የዘ-ህወሀት ግዛት መሆኑን ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ባምባገነኑ መለስ ዜናዊ እና ወሮበላ የደናቁርት ስብስብ ጓዶቹ የጥላቻ አእምሮ የተፈጠረው የኢትዮጵያ ግዛት በፍጹም ህልውና የለውም፡፡
ያለምንም መደበቅ እውነተኛው ግዛት ግን የጥላቻ ግዛት፣ የኢፍትሀዊነት ግዛት፣ እኩልነት ያለመሆን ግዛት፣ የሙስና ግዛት እና ስልጣንን ከህግ አግባብ ውጭ የመጠቀም የዘ-ህወሀት ግዛት ነው፡፡
የጎሳ ፌዴራሊዝም እና ዴሞክራቲክ ሬፐብሊክ እያለ ቢጮህም ዘ-ህወሀት በምዕናባዊዋ ኢትዮጵያ እውነተኛ እና ህልውና ያለው የዘ-ህወሀት ግዛትን በፈጠረው ሕገ መንግስት ለማቋቋም በቅቷል፡፡
እውነት ኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ትፈልጋለችን?
ያለምንም ጥርጥር አዎ ትፈልጋለች! ያስፈለጋታለም!
ኢትዮጵያውያን በህዝብ የተዘጋጀ ለህዝብ የሆነ ሕገ መንግስት ያስፈልጋቸዋል፡፡
ኢትዮጵ እንዲህ በሚሉ ቃላት የሚጀምር ሕገ መንግስት ትፈልጋለች፡ “እኛ የኢትዮጵያ ህዝቦች ፍጹም የሆነ አንድነትን ለመፍጠር…“
ኢትዮጵያ ህዝቧን አንድ የሚያደርግ እና በህዝቦች መካከል ፍጹም የሆነ ፍቅር እና አንድነት እንዲፈጠር ትፈልጋለች፡፡
ለመሆኑ ፍጹም የሆነ አንድነት ማለት ምን ማለት ነው?
ለእኔ ፍጹም የሆነ አንድነት ማለት ስለግዛት አንድነት ጉዳይ አይደለም፡፡
ይልቁንም “ፍጹም የሆነ አንድነት” ማለት የኢትዮጵያ ህዝቦች የልብ እና አእምሮ አንድነት ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵውያን በ40 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የአውሮፓን ኃይል ወታደራዊ ወራሪ ሰራዊት ሁለት ጊዜ በማሸነፍ ከቅኝ ገዥዎች የበላይነት እራሳቸውን ነጻ አድርገዋል፡፡ ምክንያቱም በልብ እና በአእምሯቸው አንድ ነበሩና ነው፡፡
በቅኝ ግዛት ሲሰቃዩ ለነበሩ ህዝቦች ሁሉ ኢትዮጵያውያን ለመላው የአፍሪካ ህዝብ የነጻነት ቀንዲል ተምሳሌት ለመሆን በቅተዋል፡፡ ምክንያቱም በአንድ አእምሮ እና ልብ አንድ ሆነው ተነስተው ነበርና፡፡
ኢትዮጵያውያን በዘረኝነት እና በአድልኦ በመሰቃየት ላይ ላሉት ለአፍሪካ አሜሪካውያን ቤዛ ሆነዋል፡፡ ምክንያቱም ህዝብ እንደ አንድ ሆኖ ከተባበረ በምንም ዓይነት መንገድ ሊሸነፍ እንደማይችል በተግባር አረጋግጠዋልና፡፡
ኢትዮጵያውያን የነጻነት ቀንዲል መሆናቸው በጥቂት ታላላቅ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ገጣሚዎች ተወድሰዋል፡፡ ምክንያቱም እንደ አንድ ህዝብ ሆነው በመቆም በደም፣ በአጥንት፣ በላብ እና በእንባ መስዋዕትነት የሀገራቸውን ነጻነት ጠብቀዋልና፡፡
ለመሆኑ በኢትዮጵያ ህዝቦች አእምሮ እና ልብ ውስጥ እንዴት አድርግን ነው ፍጹም የሆነ አንድነት ለመፍጠር የምንችለው?
ጉዳዩ ቀላል ነው!
በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ፍጹም የሆነ አንድነት ለመፍጠር እኛ ህዝቦች (እያንዳንዳችን) ያለምንም መታከት ጠንክረን በመስራት የሕግ የበላይነትን፣ የኢትዮጵያን ህዝቦች ሰብአዊ መብት አጠባበቅ (የመናገር ነጻነት፣ የፕሬስ ነጻነት፣ የኃይማኖት ነጻነት፣ ቅሬታን የመግለጽ መብት፣ የመሰብሰብ መብት፣ ወዘተ) መጠበቃቸው እና መከበራቸውን ማረጋገጥ አለብን፡፡
በስልጣን እና በኃላፊነት ቦታ ላይ ባሉ ባለስልጣኖች ላይ ፍጹም የሆነ የሕግ ተጠያቂነት መኖሩን፣ ነጻ እና ፍትሀዊ ምርጫ መኖሩን፣ የንብረት ባለቤትነት መብት በተለይም የመሬት ባለቤትነት መብት መጠበቁን እና መንግስት በንብረት የባለቤትነት መብት ላይ ጣልቃ እንዳይገባ በሕገ መንግስቱ መታገዱን እንዲሁም ጠንካራ እና ነጻ የሆነ የፍትህ ስርዓት መኖሩን ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡
በኤሜሪካ በሲቪል መብቶች የትግል ምዕራፍ ወቅት መሪዎች የአንድነትን ጠቃሚነት እስከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ድረስ ለማስረዳት አምስቱን ጣቶቻቸውን በተመሳስሎ ይጠቀሙ ነበር፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ኢትዮጵያውን ፍጹም የሆነ አንድነት ለመፍጠር በሚሰሩበት ጊዜ ከእነዚህ ተመሳስሎዎች በርካታ ቁምነገሮችን ሊማሩ ይገባል፡፡
በእያንዳንዱ እጅ ላይ አምስት ጣቶች አሉ፡፡ በሁለቱም እጆች ያሉት አስሩም ጣቶች በተናጠል ለየብቻቸው ሲዘረጉ ምንም ዓይነት ኃይል ሊፈጥሩ አይችሉም፡፡
አስሩም ጣቶች ታጥፈው በአንድነት ቡጢን ከፈጠሩ ግን ለጠላት የማይበገሩ መሳሪያዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ከእያንዳንዱ እጅ አንድ ጣት የሚነሳ ከሆነ በቡጢው ውስጥ ያለው አብዛኛው ኃይል ይቀንሳል፡፡
ሁለተኛው ጣት ከእያንዳንዱ እጅ ላይ የሚነሳ ከሆነ በቡጢው ላይ ያለው ሁሉም ኃይል ሙሉ በሙሉ ይጠፋል፡፡
ላለፉት 25 ዓመታት ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአምባገነኑ እና በእብሪተኛው ዘ-ህወሀት በመጥረቢያ የመከተፍ፣ የመበጣጠስ፣ የባንቱስታናዊነት እና ክልላዊነት እኩይ ምግባሮች ሁሉ ተፈጽመውባቸዋል፡፡
ሆኖም ግን ኢትዮጵያውያን የተባበሩትን የጣቶች ቡጢ ኃይል በማድነቅ ታሪካቸውን እንደገና መለስ ብለው ማየት ይኖርባቸዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ጣቶቻቸውን ሲያጥፉ እና ቡጢን በመፍጠር አንድ በሚሆኑበት ጊዜ ኃይለኛ የተባሉትን ጠላቶቻቸውን ድል ያደርጋሉ፡
ታሪክ እንዲህ በማለት ያረጋግጥ፡
ኦሮሞዎች ሀገራቸውን የወረረውን አንዱን ኃያል የአውሮፓ (ጣልያን) ወራሪ ኃይል ብቻቸውን ድል አላደረጉትም፡፡
አማራዎች ሀገራቸውን የወረረውን አንዱን ኃያል የአውሮፓ (ጣልያን) ወራሪ ኃይል ብቻቸውን ድል አላደረጉትም፡፡
ትግራውያን ሀገራቸውን የወረረውን አንዱን ኃያል የአውሮፓ (ጣልያን) ወራሪ ኃይል ብቻቸውን ድል አላደረጉትም፡፡
ጉራጌዎች ሀገራቸውን የወረረውን አንዱን ኃያል የአውሮፓ (ጣልያን) ወራሪ ኃይል ብቻቸውን ድል አላደረጉትም፡፡
አፋሮች ሀገራቸውን የወረረውን አንዱን ኃያል የአውሮፓ (ጣልያን) ወራሪ ኃይል ብቻቸውን ድል አላደረጉትም፡፡
ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን የወረረውን አንዱን ኃያል የአውሮፓ (ጣልያን) ወራሪ ኃይል ብቻቸውን ድል አላደረጉትም፡፡
ኦሮሞዎች፣ አማራዎች፣ ትግራውያን፣ ጉራጌዎች፣ አፋሮች፣ ኦጋዴናውያን፣ ሀረሪዎች፣ ጋምቤላውያን እና ሌሎች ሁሉም በደቡብ፣ በሰሜን፣ በምስራቅ እና በምዕራብ ኢትዮጵያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንደ አንድ ህዝብ ሆነው ሀገራቸውን የወረረውን ታላቅ የአውሮፓ ወራሪ ኃይል (ጣልያን) ድል ለማድረግ በቁ፡፡
እንደዚሁም ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ እያንዳንዳቸው በተናጠል በመዋጋት ዘ-ህወሀትን ድል ሊያደርጉ አይችሉም፡፡
እንደ አስሩ ጣቶቸ ሁሉ በየስራ መስኩ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ወደ አንድ በመምጣት ቡጢያቸውን በማጠናከር ኃያል የተባለውን የአውሮፓ ወራሪ ኃይል ድባቅ ለመምታት በቅተዋል፡፡
ዘ-ህወሀት በኢትዮጵያ ላይ የጫናቸው 9ኙ ጣቶች (ክልሎች) በአሁኑ ጊዜ ወደ አንድ ቡጢ በመምጣት ለዘ-ህወሀት ትምህርት ሊሰጥ የሚችል ምት መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ሕገ መንግስታዊ ወሮበላ እና ዘራፊነትን አይፈልጉም፡፡
ኢትዮጵያውያን የሰው ልጆችን ዘር አጥፊ እና የአእምሮ በሽተኛ በሆነው በጆሴፍ ስታሊን አእምሮ ውስጥ የበቀለ ሕገ መንግስትን አይፈልጉም፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለቄታው አንድነትን የሚያጠፋ፣ ጥላቻን የሚዘራ፣ ልዩነትን የሚፈጥር እና የሚበታትን መሪ ዕቅድ እና ሰነድ የያዘ ሕገ መንግስት አትፈልግም፡፡
ኢትዮጵያ የፖለቲካ መከፋፈልን፣ የስልጣን ማዕከላዊነትን፣ የህብረተሰብ ክፍፍን እና ህዝቦች በመልክዓ ምድር እና በግዛት እየተሸነሸኑ ለጨቋኝ አገዛዝ በሚመች መልኩ የሚበጣጠሱበትን መንገድ አትፈልግም፡፡
ኢትዮጵያ እኩልነትን፣ ወንድማማችነትን/እህትማማችነትን እና ነጻነትን መሰረት ያደረገ የኢትዮጵያን ህዝብ እንደ አንድ ብሄር፣ እንደ አንደ ብሄረሰብ እና እንደ አንድ ህዝብ የሚያስተሳስር ሕገ መንግስት ትፈልጋለች፡፡
ኢትዮጵያን ለማዳን የሚደረግ ትግል፡
ለእያንዳንዱ የኢትዮጵያ የጎሳ ቡድን እውቅና የሚሰጥ ሕገ መንግስት ሳይሆን የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ሰው የመሆን መብት የሚያረጋግጠው ሕገ መንግስት በኢትዮጵያ እውን እንዲሆን አልማለሁ፡፡
ኢትዮጵያውያን የብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች አባል ከመሆናቸው በፊት በእግዚአብሄር አምሳል ነጻ ሆነው የተፈጠሩ ህዝቦች እንደሆኑ አምናለሁ፡፡ የኢትዮጵያውያን ሰው የመሆን ክስተት ከኢትዮጵያዊነት፣ ብሄራዊነት እና አፍሪካዊነት በፊት ቀድሞ የመጣ ነው፡፡
ነጻ ሆኖ እንደተፈጠረ ሰው የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ክብር እና ሞገስ መጠበቅ እንዳለበት አምናለሁ፡፡ በቡድን መብቶች አላምንም፡፡ እርሱ ወይም እርሷ የአንድ ቡድን አባል ባለመሆኑ/ኗ እና ከዚያ ቡድን ጋርም ምንም ዓይነት ግንኙነት ስለሌው/ላት በምንም ዓይነት መንገድ ቢሆን የሕግ ጥበቃ የመከልከል፣ የህግ የበላይነትን እና እኩል ዕድልን የማጣት ድርጊት ሊፈጸምበት/ባት አይገባም፡፡ አራት ነጥብ!
ኢትዮጵያውያን ለማንኛውም የቡድን መብቶች ጠቃሚ የሆኑ ግላዊ መብቶች አሏቸው፡፡
እያንዳንዱ ኢትዮጵዊ የእራሱን መንግስት እና የመንግስት መሪዎችን የመምረጥ መብት አለው፡፡
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በጫካ ወሮበላ ዘራፊዎች ባርነት እንዳይፈጸምበት መብት አለው፡፡
ከበርካታ ወጣቶች ጋር በመነጋገር እንደምገነዘበው ከሆነ ኢትዮጵያን የማዳን ትግሉ ከወሳኙ ምዕራፍ ላይ የደረሰ መሆኑን አምኛለሁ፡፡
በኢትዮጵያ “ቡጢ ለነጻነት” በማለት ለሁሉም ጀግኖች ኢትዮጵያውያን የተማጽዕኖ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
ሆኖም ግን ኢትዮጵያውያን ቡጢያቸውን እንዲያስተባብሩ እኔ ከማቀርበው የነጻነት የተማጽዕኖ ጥሪ የበለጠ ሌሎች የማይቀሩ ነገሮች አሉ፡፡
ታላቁ አፍሪካ አሜሪካዊ የህዝብ ገጣሚ ላንግስተን ሁጌ እ.ኤ.አ መስከረም 1935 የጣሊያን ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያን በወረረበት እና የጥቃት ዘመቻውን በጀመረበት ጊዜ ኢትዮጵያውያን ለነጻነት ቡጢያቸውን እንዲጠነክሩ እና ሁሉንም አፍሪካውያንን ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር ነጻ እንዲያወጡ ለኢትዮጵያውያን ወገኖቹ አንዲህ የሚል የትግል ጥሪ አቅርቦ ነበር፡
ለኢትዮጵያ የቀረበ የትግል ጥሪ፣
የጀግና አገር ውድ ኢትዮጵያ፣
የነጻነት ቀንዲል እሳት ቋያ፣
የሳባውያን ዝርያ አቢሲኒያ፣
ትጉኋ ንብ ውብ ባለሙያ፣
የአፍሪካ እናት ውድ ኢትዮጵያ፡፡
ጨለማውን ጥሰሽ፣
በነፍጥ ተዋግተሸ፣
ለአፍሪካውን ተሰውተሸ፣
ባርነትን አስወግደሽ፣
ነጻነትን ተቀዳጅተሽ፣
ሰንደቅሽን ታውለብልቢያለሽ፡፡
በአስደማሚ ሳቢ ደኖች፣
የተዋብሽው በተራሮች፣
የጀግኖችሽ ቤት ንብረቶች፣
መጠለያ ለፋኖዎች፣
ላርበኞችሽ አለኝታዎች፣
የሚሰው ለብዙዎች፡፡
እብሪተኞችን አዋርደሽ፣
አይቀጡ ቅጣት ቀጥተሽ፣
ዘላለማዊ ትምህርት ሰጥተሸ፣
ድልን ብድል ላይ ተረማምደሽ፣
ነጻነትሽን ትቀዳጃለሽ፣
አፍሪካውያንን ታኮሪያለሽ
እናም ለነጻነትሽ ተነሽ፡፡
ሁሉም አፍሪካውያን ተነሱ
እናንተ ጀግኖች ደፋር ህዝቦች፣
ዓይነ ጉርጥርጥ ደመ ፍሎች፣
የንግስተ ሳባ ቅዱስ ዘሮች፣
የነጻነት ቀንዲል ተዋጊ ፋኖዎች፣
የአፍሪካ ኩራት ታጋይ አርበኞች፡፡
ኢትዮጵያ ነጻ ሁኝ!
እንደ እኔ ነጻ ሁኝ፣
ሰላም ምቾትን እድታገኝ፡፡
ሁሉም አፍሪካውያን፣
በአራቱም ማዕዘን፣
እጅ ለእጅ ተያያዙና፣
አንድነትን ፍጠሩና፣
ነጻ ሁኑ ተነሱና፡፡
እናንተ ጥቁር ህዝቦች ሁሉ፣
ከጫፍ እስከጫፍ በሙሉ፣
ወንድ ሴት ልጅ ሳትሉ፣
ለነጻነት ተጋደሉ፡፡
አሽከር በሪያ ሳትሆኑ፣
ለዘር መድልኦ ሳትወግኑ፣
ሰውን በቀለም ሳትኮንኑ፣
ታገሉና ነጻ ሁኑ! ነጻ ሁኑ፡፡
የጋና የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት እና ታላቁ የአፍሪካ ፓን አፍሪካኒስት የነበሩት ክዋሜ ንክሩማህ ሁሉም አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን በመጀመሪያ ኢትዮጵያ እንድተነሳ እንዲህ ሲሉ የግጥም ስንኝ ቋጥረው ነበር፡
ኢትዮጵያ ለነጻነት ቡጢዋን ታነሳለች፣
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዕንቁ፣
ታሪክ ያላት በደማቁ፣
በልምላሜ የተሸፈነች፣
የሰውን ቀልብ የሳበች፣
በጀግንነት የታወቀች፡፡
የዓባይ ውኃ መፍለቂያ፣
ጥንታዊ ሀገር አቢሲኒያ፣
የብልሆች ሀገር ኢትዮጵያ፣
ለም የትምህርት መፍለቂያ፡፡
የጥንት ታሪክ መገኛ፣
የአፍሪካ ኩራት ሁነኛ፣
የአምባገነኖች መጋኛ፣
የኩራት ሀገር የእኛ፡፡
የአፍሪካ ባህል ቅርሳችን፣
የእኛነታችን የአንድነታችን፣
የማንነት አሻራ የስብዕናችን፡፡
ሀገረ ምድር የፈላስፋ፣
የአፍሪካውያን ተስፋ፣
ትነሳለች በይፋ፣
አቧራዋን አራግፋ፡፡
ከወደቀችበት ትነሳለች፣
ከእኛ ጋር ትታደሳለች፣
በስልጣኔ ትጓዛለች፡፡
የአፍሪካ ተስፋ ቀንዲል፣
ባለታሪክ የአፍሪካ ዕድል፡፡
ኢትዮጵያ ከዘ-ህወሀት የጭቆና አገዛዝ እና የበላይነት በድል አድራጊነት ትነሳለች!
ሁሉም ኢትዮጵያውያን የእራሳቸውን ዕድል በእራሳቸው በመወሰን ከዘ-ህወሀት የጭቆና አገዛዝ ነጻ እንዲወጡ ሁላችሁም በያላችሁበት እገዛ አድርጉ!
ኢትዮጵያውያን ወንደሞቼ እና እህቶቼ፡ አንድ ሀገር፣ አንድ ብሄር፣ አንድ ሕዝብ ነን!
“ገዥዎች ሽብርን በህዝብ ላይ የሚዘሩ እንደሆኑ አድርገን ልናስብ እንችላለን፡፡ ሆኖም ግን በተጻራሪው እነርሱ እራሳቸው በፍርሀት ሽብር ውስጥ ተዘፍቀው ይገኛሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ሽብር የእራሳቸውን ደህንነት ለማረጋገጥ ሲሉ እርባናቢስ በሆኑ ቦቅቧቃ ፈሪዎች የሚሸረብ የሸፍጥ ድርጊት ነው፡፡“ እ.ኤ.አ በ1870 በፓሪስ ኮሚዩን ማርክስ ለኤንግልስ የጻፈው
ይቀጥላል…
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ሰኔ 3 ቀን 2008 ዓ.ም