የበቀለ ገርባ የፍትህ ሂደት በዘ-ህወሀት የዝንጀሮ (የይስሙላው) ፍርድ ቤት፣

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም    

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

Bekele 8በአሜሪካ የሕግ አፈ ታሪክ የስኮፐስ የዝንጀሮ (የይስሙላ) ፍርድ ቤት ነበር ፡፡

እ.ኤ.አ በ1925 ጆን ስኮፐስ ተብሎ የሚጠራ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር በቴኔሲ ግዛት ድንጋጌን በመጣስ በአንድ የሕዝብ ትምህርት ቤት ውስጥ ስለሰው ልጆች ዘገምተኛ ለውጥ/human evolution ሲያስተምር ተገኝቶ እንደወንጀለኛ ተቆጥሮ ለፍርድ ቤት ቀርቦ ነበር፡፡ የስኮፐስ የፍርድ ሂደት ጉዳይ ልጆቻቸው በዘመናዊ ትምህርት እንዲታነጹ በማይፈልጉ ምንም በማያውቁ ደንቆሮዎች እና ሌሎች ደግሞ ዘመናዊውን የአሜሪካ የሳይንስ ትምህርት እንዲገበዩላቸው በሚፈልጉ ሰዎች መካከል የሚደረግ ትግል ስለነበር የፍርድ ሂደቱ በመላው ዩኤስ አሜሪካ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሲታይ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 2016 የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ህወሀት) በበቀለ ገርባ እና በሌሎች በ21 ሰዎች ላይ የእራሱን የጸረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 በመጠቀም የሸፍጥ ክስ መስርቶባቸው የዉሸት ፍርድ ሂደቱ በመታየት ላይ ይገኛል፡፡

በቀለ ገርባም እንደዚሁ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ቋንቋ/እንግሊዝኛ የሚያስተምር ፕሮፌሰር መምህር ነው፡፡ ሆኖም ግን ያልተማሩትን ልጆች በማስተማሩ አይደለም ክስ የተመሰረተበት፡፡ የእርሱ ወንጀሎች የሚከተሉት ናቸው፡

1ኛ) ዘ-ህወሀት በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ እያደረሰ ያለውን አስደንጋጭ ሰይጣናዊ ወንጀሎች ለኢትዮጵያ ሕዝቦች በማስተማሩ እና በማሳወቁ፣

2ኛ) ዘ-ህወሀት በኦሮሚያ ክልል ሲፈጽም የነበረውን ገደብ የሌለው  የሰው ልጆች እልቂት በማጋለጡ፣ እና

3ኛ) በዘ-ህወሀት እየተደረገ ያለውን አይን ያወጣ የመሬት ቅርምት ሙስና፣ በሰው ልጆች ላይ ጭካኔ የተመላበት ግድያ እየፈጸመ መሆኑን እና ዘ-ህወሀት መቋጫ የሌለው ስልጣንን ከሕግ አግባብ ውጭ የመጠቀም አባዜውን በማጋጡ ምክንያት ነው፡፡

በዚህ ሸፍጥ በተመላበት የዘ-ህወሀት የአሸባሪነት ክስ ከበቀለ ጋር አብረው እንዲከላከሉ የሸፍጥ ክስ የተመሰረተባቸው የሚከተሉትን ወገኖቻችንን ያካትታል፡

1ኛ) ጉርሜሳ አያኖ ወይሳ፣

2ኛ) ደጀኔ ጣፋ ገለታ፣

3ኛ) አዲሱ ቡላላ አባዋልታ፣

4ኛ) አብደታ ነጋሳ ፈዬ፣

5ኛ) ገላና ነገራ ጅማ፣

6ኛ) ጭምሳ አብዲሳ ጃፋሮ፣

7ኛ) ጌቱ ግርማ ቶሎሳ፣

8ኛ) ፍራኦል ቶላ ዳዲ፣

9ኛ) ጌታቸው ደረጀ ቱጁባ፣

10ኛ) በየነ ሩዳ ደጁ፣

11ኛ) ተስፋዬ ሊበን ቶሎሳ፣

12ኛ) አሸብር ደሳለኝ በሪ፣

13ኛ) ደረጀ ነርጋ ደበሎ፣

14ኛ) ዩሰፍ አለማየሁ ሄረጋ፣

15ኛ) ሂካ ተክሉ ቁጡ፣

16ኛ) ገመቹ ሻንቆ ገዲ፣

17ኛ) መገርሳ አስፋው ፈይሳ፣

18ኛ) ለሚ ኢዴቶ ገረመው፣

19ኛ) አብዲ ታምራት ደሲሳ፣

20ኛ) አብዲሳ ኩምሳ ሂሳ፣ እና

21ኛ) ሀልኬኖ ቆንጨራ ጎሮ

ናቸው፡፡

ባለፈው ሳምንት በበቀለ እና በሌሎች ተከላካይ ጓደኞቹ ላይ የሸፍጥ ክስ በቀረበባቸው ጊዜ የዘ-ህወሀት የይስሙላው የዝንጀሮ ፍርድ ቤት በኢትዮጵያ የጋምቤላ ክልል የኗሪው ሕዝብ መሬት መብት ማስጠበቅ መሪ በነበሩት በኦኬሎ አክዋይ ኦቻላ ላይ ተመስርቶ በነበረው የአሸባሪነት የሸፍጥ ክስ የ9 ዓመታት እስራት ተበይኖባቸዋል፡፡ ኦኬሎ በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኘው የቀድሞ የጋምቤላ ክልል አስተዳዳሪ የነበሩ እና ዘ-ህወሀት በሰው ልጆች ላይ ሲፈጽማቸው በነበሩት ኢሰብአዊ ወንጆሎች ተማርረው እ.ኤ.አ በ2004 ወደ ኖርዌ ሀገር ተሰድደው ሲኖሩ የቆዩ ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ መጋቢት 2014 ዘ-ህወሀት ከደቡብ ሱዳን ወታደራዊ ቡድኖች ጋር በመመሳጠር ኦኬሎ ደቡብ ሱዳንን እየጎበኙ ባሉበት ወቅት ሕገወጥ በሆነ መልኩ ታፍነው ወደ ኢትዮጵያ እንዲወሰዱ አድርጓል፡፡ (በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ተዘጋጅቶ የቀረበውን የኦኬሎን የክስ መከላከያ ለማንበብ እዚህ ጋ ይጫኑ፡፡)

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2014 የሰብአዊ መብት ተሟጋች እና ግንቦት 7 የፍትሕ፣ የነጻነት እና የዴሞክራሲ ንቅናቄ እየተባለ የሚጠራው የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ቡድን ዋና ጸሐፊ የነበሩትን አንዳርጋቸው ጽጌን ከየመን መንግስት አባላት ጋር በመመሳጠር ሕገወጥ በሆነ መልኩ ጠልፎ ወደ ኢትዮጵያ ወስዷቸዋል፡፡

ህወሀት በበቀለ ገርባ እና በሌሎች 21 ሰዎች ላይ የመሰረተው የአሸባሪነት የሸፍጥ ክስ፣

Bekele 2በበቀለ እና በሌሎች 21 ሰዎች ላይ የተመሰረተው የሸፍጥ የውንጀላ ክስ የካፍካ የፍርድ ሂደት ቀጥታ ግልባጭ ነው፡፡ ያ ረዥም ታሪክ እንዲህ በሚለው ዓረፍተ ነገር ይጀምራል፡ “አንድ ሰው በጆሴፍ ኬ. ላይ ውሸት መናገር አለበት፣ እርሱ ምንም ዓይነት ስህተት እንዳልሰራ ያውቃል፣ ሆኖም ግን ከዕለታት አንድ ቀን ጠዋት በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡“

እንደዚሁም ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ በቀለ እና ሌሎች 21 ተከላካይ ሰዎች ምንም ዓይነት ስህተት እንዳልሰሩ እያወቁ በዘ-ህወሀት በቁጥጥር ስር ሲውሉ አንድ ሰው ውሸት መናገር አለበት፡፡

የዘ-ህወሀት “የጸረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001“ እየተባለ የሚጠራው ግራ የሚያጋባ እና የዘፈቀደ የአሸባሪነት የክስ ውንጀላ እንደሚከተለው ይጠቃለላል፡ “በቀለ ከማጎሪያው እስር ቤት መፈታቱን ተከትሎ እ.ኤ.አ ሀምሌ 2015 የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)/Oromo Federalist Congress ባለስልጣን በመሆን ወደ ዩኤስ አሜሪካ በመሄድ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)/Oromo Liberation Front መሪዎች ጋር ይገናኛል፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ እና የኦነግን አሸባሪ መልዕክት በማሰራጨት አመጽ እና ነውጥ ሊያስፋፋ ነው ተብሎ ተወነጀለ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ከሌሎች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ወደተለያዩ ከተሞች እና አካባቢዎች በመንቀሳቀስ የአሸባሪነት ድርጊት ለመፈጸም የሚያስችሉ ትዕዛዞችን ሰጥተዋል ተብለው ተወነጀሉ፡፡ በቀለ በኦነግ ስም የኦፌኮ አባላት የሽብር ድርጊት እንዲፈጽሙ እና የመንግስት ተቋማትን፣ መንገዶችን የማውደም እና በጸጥታ ኃይሎች ላይ የጥቃት እርምጃ እንዲወስዱ አስተባብሯል ተብሎ ተወነጀለ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቀለ ወደተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመሄድ እና የአመጽ ቅስቀሳ በማድረግ የበርካታ ሰው ህይወት እንዲጠፋ እና ንብረት እንዲወድም አድርጓል በማለት ተወንጅሏል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በሌሎች ተከላካዮች ላይ የቀረበው የውንጀላ መክተፊያ ቢላዋ በኦነግ ስም ሆነው የአሸባሪነት ድርጊት ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል የሚል አንድ ዓይነት መልዕክትን የሚደግም ነው፡፡“

የሽብርተኝነት የፍርድ ሂደት በዘህወሀት የዝንጀሮ/የጦጣ ፍርድ ቤት፣

የዘ-ህወሀት የፍትህ ዘርፍ እንደ ፍትህ ስርዓት ቅንነት በሌለው፣ በሙስና እና  በምዕናባዊ ስሜታዊነት ተግባራት ላይ የተመሰረተ የሸፍጥ የፍትህ ሂደት እንደሆነ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ስናገር ቆይቻለሁ፡፡

“የጦጣ የፍርድ ቤት ሂደት በዝንጀሮው ፍርድ ቤት”  በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ ታህሳስ 2007 አቅርቤው በነበረው ትችቴ የዘ-ህወሀት የፍትህ ስርዓት ነጻ የሆኑ ሰዎችን የጥቃት ሰለባ ለማድረግ የተዘጋጀ ኢፍትሀዊ ስርዓት እንደሆነ ከምንም ጥርጣሬ በላይ ለማመላከት ሞክሪያለሁ፡፡ የዘ-ህወሀትን የፍትህ ስርዓት የካንጋሩ/ጦጣ ፍርድ ቤት በማለት እየገለጽኩበት ያለው ሁኔታ ለጥቂት አንባቢዎቼ ግልጽ ላይሆንላቸው ይችላል፡፡

የካንጋሩ ፍርድ ቤቶች የሚለው ቃል በአውስትራሊያ ከሚገኙ ካንጋሮዎች ወይም ደግሞ የልጆቻቸው መሸከሚያ ከረጢት ካላቸው ማናቸውም አጥቢ እንስሳዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም፡፡ ሀረጉ የሕግን ወይም የፍትህን ፍትሀዊ መለኪያ ወደ ጎን አሽቀንጥሮ በመጣል ዝም ብሎ በጭፍንነት የሚደረገውን የፍትህ ሂደት ለማመላከት ሲባል ከጥቅም ላይ የዋለ ነው፡፡ የካንጋሩ ፍርድ ቤቶች፣

1ኛ)  የሕግ እና የስነ ምግባር ግዴታዎችን አሽቀንጥረው በመጣል ሆኖም ሕጋዊ በማስመሰል ሆን ብለው እውነታውን የሚዘሉ ወይም አላግባብ የሚተገብሩ እና የሕግ እና የስነምግባር ግዴታዎችን የሚያዛቡ ለታዕይታ ሲባል ብቻ የተቋቋሙ የይስሙላ ፍርድ ቤቶች ናቸው፡፡

2ኛ) በሕጋዊ መንገድ ሳይሆን ከሕግ አግባብ ውጭ ዜጎችን የፍትህ እጦት ሰለባ ለማድረግ ለማስመሰያነት የተቋቋሙ የውሸት ፍርድ ቤቶች ናቸው፡፡

በአፍሪካ በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ ለፖለቲካ ሸፍጠኝነት ጉዳዮች መጠቀሚያነት የሚውሉትን የተመሰረቱ የፍትህ ተቋማት “የዝንጀሮ /ጦጣ ፍርድ ቤት” የሚለውን ሀረግ ለመግለጽ እነዚህን ቃላት አጣምሪያለሁ፡፡ በጫካ በነበሩበት ጊዜ የዘ-ህወሀት መሪዎች በጫካው ፍርድ ቤታቸው የጫካ የፍትህ ስርዓትን ያራምዱ ነበር፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ እውቀት ወይም ማስረጃ ካላቸው ሰዎች እንደተገነዘብኩት በጫካ ህይወታቸው ጊዜ የዘ-ህወሀት ቁልፍ መሪዎች ስልታዊ በሆነ መንገድ ለወደፊት ተቀናቃኝ ጠላት ሊሆኑ የሚችሉትን፣ ሰላማዊ አመጸኞችን፣ ለምን የሚል ጥያቄ የሚያቀርቡትን ሞጋቾች፣ የወደፊት ጠላቶችን፣ ተቀናቃኞችን፣ ታማኝነት የላቸውም ተብለው በጥርጣሬ ዓይን የሚታዩትን ወይም ጠላት ናቸው ተብለው የተፈረጁትን ሚስጥራዊ እና ድብቅ በሆነ መልኩ ማጥፋት፣ ማግለል ወይም ደግሞ ሌሎች እቀባዎች እንዲደረጉባው ያደርጉ ነበር፡፡ (እ.ኤ.አ በ2009 “የህወሀት የፖለቲካ ታሪክ/A Political History of TPLF” በሚል ርዕስ የቀድሞው የህወሀት መስራች የነበሩት አረጋዊ በርሄ ባዘጋጁት መጽሐፍ ውስጥ ከገጽ 182-3 የቀረበውን የዘ-ህወሀትን የጫካ ፍርድ ቤት ሂደትን የሚገልጸውን ክፍል ይመልከቱ፡፡)

ዘ-ህወሀት እ.ኤ.አ በ1991 በኢትዮጵያ ስልጣንን ከተቆጣጠረ በኋላ ያደረገው ነገር ቢኖር በጫካ ውስጥ ሲተገብረው የቆየውን የጫካ የፍርድ ቤት ሂደት መጠኑን ከፍ የማድረግ እና አገር አቀፍ መልክ እንዲኖረው የማድረግ ስራ ነው፡፡ የዘ-ህወሀትን የጫካ ፍትህ ውርስ ነው አሁን የዝንጀሮ/ጦጣ ፍርድ ቤት ስርዓት እያልኩ የምጠራው፡፡

እ.ኤ.አ በ2012 የዩኤስ አሜሪካ የመንግስት መምሪያ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ዘገባ በኢትዮጵያ ላይ እንዲህ በማለት ደምድሟል፡ “ሕጉ ነጻ የዳኝነት ስርዓትን ይፈቅዳል፡፡ የሲቪል/የፍትሐብሄር ፍርድ ቤቶች ከፍተኛ የሆነ ነጻነትን ባካተተ መልኩ የሚሰሩ ቢሆንም ቅሉ የወንጀለኛ ፍርድ ቤቶቸ ግን ደካማ፣ ከፍተኛ ሸክም የተጫነባቸው እና ለፖለቲካዊ ተጽዕኖ የተጋለጡ ናቸው“ ብሏል፡፡ የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ደግሞ እንዲህ የሚል መግለጫ አውጥቷል፣ “በኢትዮጵያ ውስጥ የዳኝነት ነጻነት የለም እናም አሁን በቅርቡ እንደታዩት አንዳንድ በርካታ አጋጣሚዎች በሰላማዊ አመጸኞች ላይ ሸፍጥን የያዘ ኢፍትሀዊነት ድርጊት ለመፈጸም እና የኃይል እርምጃ ለመውሰድ በስራ ላይ እየዋሉ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሲቪል ማህበረሰብ በጎ አድራጎት ድርጅቶች እና የጸረ ሽብር አዋጁ የይስሙላ እና የዘፈቀደ አፈጻጸም እንዲኖራቸው የሚያጠናክር ህጎችን አውጥቷል“ ብሏል፡፡ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

ዘ-ህወሀት እየተገበረው ያለው የፍትህ ስርዓት የሕግ የበላይነትን ያሰፈነ ቅርጽ ያለው፣ ፍትሀዊ እና ትክክለኛ በማስመሰል ምናባዊነትን በመፍጠር በዘ-ህወሀት ጠላት ላይ የሚመሰረት ማንኛውም ክስ የተበላ እቁብ የመሆኑ እውነታ የታወቀ ቢሆንም ቅሉ የፍርድ ቤት ሂደቱን ለእራሱ ኢፍትሀዊነት ድርጊቱ መጠቀሚያ ለማስመሰያነት ይጠቀምበታል፡፡ የኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ጀግኒት የሆነችው እና የዘ-ህወሀት የሸፍጥ የአሸባሪነት ውንጀላ ክስ ሰለባ የነበረችው ርዕዮት ዓለሙ ውሸት ካልዋሸች እና በሀሰት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ስም የማጠልሸት ድርጊት ካልፈጸመች የሞት ቅጣት እንደሚበየንባት ከዚህም አነሰ ቢባል የእድሜ ልክ እስራት እንደሚበየንባት የዘ-ህወሀት አለቆች ሀሰን ሽፋ እና ለይኩ ገብረእግዚአብሄር ሲያስፈራሯት እንደነበር በግልጽ ዘግባዋለች፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ እንደ ሸቀጥ በገበያ በዘ-ህወሀት መሪዎች እና ግብር አበሮች እንዲሁም ደጋፊ በሆኑት ስምየለሾች፣ የማይታወቁ እና አቅም የለሽ ድሁሮች በስልጣን ማማ ላይ ተቀምጠው ከሕግ አግባብ ውጭ በስውር በሚሰሩ ሰዎች ጠቅላይነት የሚሸጥበት እና የሚገዛበት የውሸት የፍትህ ስርዓት ሆኗል፡፡ በዘ-ህወሀት የፍትህ ስርዓት ውስጥ ዓለም አቀፋዊ የሕግ መርሆዎች፣ ፍትህ እና የሕግ የበላይነት ወደ ጎን የተጣሉ፣ የተናቁ እና በሸፍጥ የተሞሉ ናቸው፡፡ ድሆች፣ የተገለሉ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ በተስፋ የተሞሉት ጋዜጠኞች፣ ሰላማዊ አማጺዎች፣ ተቃዋሚዎች እና የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች መሪዎች በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የድንጋይ ዓይነት ጸጥታዊ ዝምተኝነት ምክንያት በሕጋዊነት ስም ተገድለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ የዘ-ህወሀት አገዛዝ መሪዎች፣ ቤተሰቦቻቸው፣ ጓደኞቻቸው፣ እና ግብረ አበሮቻቸው ከሕግ በላይ የሆኑበት እና “ሕግ ማለት እኛ ነን” የሚሉበት ስርዓት ነው ያለው፡፡

ዩኤስ አሜሪካ የሚያሳስባትን ነገር ገለጸች፣

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 29/2016 የዩኡስ አሜሪካ የመንግስት መምሪያ ማድረግ ያለበትን እንዲህ የሚል የተሻለ ነገር አደረገ፣ “እ.ኤ.አ በ2015 መጨረሻ አካባቢ የኢትዮጵያ መንግስት በቁጥጥር ስር ባዋላቸው በኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር በሆኑት በበቀለ ገርባ እና በሌሎች በአሮሚያ ክልል ውስጥ ባሉት ሰዎች ላይ በቅርቡ የሽብርተኝነት ክስ ለመመስረት ያሳለፈው ውሳኔ በጥልቅ አሳስቦኛል“ ይላል፡፡

ወይ ጉድ ምን አይነት አነጋገር ነው ?   አሳስቦኛል! ድንቄ ም!

የዩኤስ አሜሪካ የመንግስት መምሪያ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ሁኔታ “አሳስቦኛል“ እያለ ሲያወጣው የቆየውን መግለጫ የምቆጥረው ቢሆን ኖሮ “በኢትዮጵያ የሚከሰተው የጸደይ አብዮት ቅሬታ ዩኤስ አሜሪካን ያሳስባታል“ በሚል ርዕስ መጽሐፍ ማሳተም እችል ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ግንቦት 2015 ተካሄደ የተባለውን የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ በማስመልከት ዘ-ህወሀት ምርጫውን መቶ በመቶ አሸንፊያለሁ በማለት እምቧከረዩ ካለ በኋላ ኋይት ሀውስ እንዲህ የሚል መግለጫ አውጥቶ ነበር፣ ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛዚዎች ምርጫው ዓለም አቀፍ መስፈርትን የማያሟላ መሆኑን ይፋ አድርገዋል፣ እናም ይኸ ጉዳይ ያሳስበናል“ ነበር ያለችው፡፡

እ.ኤ.አ በ2010 እና በ2015 ተደረጉ በተባሉት የይስሙላ የቅርጫ ምርጫዎች ዩኤስ አሜሪካ ያው እንደተለመደው አንድ ዓይነት በሆነ መልኩ ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛዚዎች ምርጫው ዓለም አቀፍ መስፈርትን የማያሟላ መሆኑን ይፋ፣ አድርገዋል፡፡ እናም ይኸ ጉዳይ ያሳስበናል“ ነበር ያሉት፡፡

እ.ኤ.አ ግንቦት 2014 የዩኤስ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ከዘ-ህወሀት ባለስልጣኖች ጋር በመገናኘት የኢትዮጵያ የዞን 9 ወጣት ጦማሪዎች በቁጥጥር ስር የመዋላቸው ጉዳይ ያሳሰበው መሆኑን ነበር የገለጸው፡፡

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2015 ባራክ ኦባማ የዘ-ህወሀት አገዛዝ ዴሞክራሲያዊ ነው ከማለቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሱሳን ራይስ በኢትዮጵያ የጋዜጠኞች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች አያያዝ ሁኔታ ዩኤስ አሜሪካን ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ያሳስባታል ነበር ያለችው፡፡

ዘ-ህወሀት ሁልጊዜ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣውን ወንጀል፣ የምርጫ ስርቆትን እና ዓለም አቀፍ ሕጎችን ሁሉ በጣሰ ቁጥር ዩኤስ አሜሪካ “አሳስቦኛል” የሚለውን አሰልቺ ቃል እንደ በቀቀን ትደጋግመዋለች፡፡

በየጊዜው ዘ-ህወሀት በሰው ልጆች ላይ ኢሰብአዊ ወንጀሎችን፣ በፈጸመ፣ ምርጫዎችን በሰረቀ እና ዓለም አቀፍ ሕጎችን በጣሰ ቁጥር ዩኤስ አሜሪካ “አስስቦኛል” በማለት መግለጫ ታወታለች፡፡

ድምጽን ከፍ አድርጎ በመጮህ “አሳስቦኛል” ማለት ምን ማለት ነው?

“አሳስቦኛል” ማለት “ከገዳይ ወሮበላ ዘራፊዎች ጋር አንድ አልጋ በመጋራታችን ሀፍረት ተሰምቶናል፣ ስለሆነም የዓለምን ማህበረሰብ ለማታለል እና ከገዳይ ወሮበላ ዘራፊዎች ጋር አንድ አልጋ ላለመጋራታችን የዓለም ሕዝብ እንዲያምነን እንፈልጋለን“ ለማለት የቀረበ የዴፕሎማሲ ቋንቋ ቃል ነውን?

ለእኔ ስለአንድ ነገር ያሳሰበው/ባት ሰው ስለዚያ ነገር ተገቢ የሆነ እርምጃ ይወስዳል/ትወስዳለች፡፡

ሰዎች የሌሎች ሰዎች ጤንነት እና ደህንነት ሲያሳስባቸው ዝም ብለው በቂጣቸው ተንዘርጥጠው አይቀመጡም ወይም ደግሞ “አሳስቦኛል” እያሉ ከንቱ የሆነ ዙረት አይዞሩም፡፡ ይልቁንም አንድ ነገር ያደርጋሉ፡፡

ዩኤስ አሜሪካ “አሳስቦኛል” ብትል ማን ጉዳዩ ነው? ዩኤስ አሜሪካ “አሳስቦኛል” ስትል ዘ-ህወሀት በሰው ልጆች ላይ እልቂት መፈጸምህን እና የሰብአዊ መብቶችን መደፍጠጥህን አቁም ማለቷ ነውን?

ዩኤስ አሜሪካ “አሳስቦኛል” የሚለውን ቃል ስትጠቀም  ቢያንስ ይህንን ቃል በመናገሯ አንድ ነገር እንዳደረገች እራሷን ለማሳመን ነውን?

እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ግን “አሳስቦኛል” ማለት ሌላ ምንም ዓይነት ነገር ሳይሆን አንድም ነገር አለማድረግ ማለት ነው፡፡

ዩኤስ አሜሪካ ዘ-ህወሀት በሰው ልጆች ላይ የሚፈጽመው ኢሰብአዊ ወንጀል ከልቧ በእርግጠኝነት “አሳስቦኛል” የምትል ከሆነ ስለሚያሳስባት ጉዳይ ተጨባጭ የሆነ አንድ ነገር ማድረግ ይኖርባታል፣ ለምሳሌ ያህልም የምትለግሰውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እርዳታ እና ዓመታዊ የእርዳታ ፕሮግራም ማቋረጥ ይኖርባታል፡፡

“አሳስቦኛል” የሚለው በሌላ በየትም ሳይሆን በአሜሪካ የሰብአዊ መብት ጥበቃ አያያዝ አስመሳይነት የዴፕሎማሲ መዝገበ ቃላት (ዲክሽነሪ) ውስጥ ብቻ የሚገኝ ቃል ነው፡፡

ለመሆኑ በቀለ ገርባ ማን ነው?

በቀለ ገርባ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ መሪ ነው፡፡

በቀለ ሰላማዊ በሆነ ነገር ላይ የሚያምን እና ኃይል መጠቀምን የማይፈልግ፣ እራሱን ክርሲቲያን አድርጎ የሚቆጥር ለአራት ዓመታት በእስር ቤት ሲያሳልፍም የማርቲን ሉተርን ኃይማኖታዊ ንግግሮች ሲናገር የቆየ እና እነዚህንም ኃይማኖታዊ ቃሎች ወደ ኦሮምኛ ቋንቋ በመተርጎም በቅርቡ በመጽሀፍ መልክ እንደሚወጣ ተስፋ አድርጎ ሲጠባበቅ የነበረ ሰላማዊ ሰው ነው፡፡

የመጽሐፉ ርዕሱም “ህልም ነበረኝ ” የሚል ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ2011 በቀለ ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል የሰብአዊ መብት መርማሪዎች ጋር ከተገናኘ በኋላ ዘ-ህወሀት በአሸባሪነት ክስ መሰረተበት፡፡

በቀለ እ.ኤ.አ ታህሳስ 2012 ብይን በተላለፈበት ጊዜ ለዘ-ህወሀት የይስሙላው የዝንጀሮ ፍርድ ቤት እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር፡

“በህይወቴ ዘመን ሁሉ ኢፍትሀዊነትን፣ አድልኦን፣ የዘር ልዩነትን እና ጭቆናን ስዋጋ ቆይቻለሁ፡፡  እኔው እራሴ ፈልጌው ሳይሆን በአምላክ ፈቃድ ለተፈጠርኩበት ለኦሮሞ ሕዝብ የዴሞክራሲ እና የሰብአዊ መብት ጥበቃ ሳካሂድ የቆየሁት ሰላማዊ ትግል እንደ ወንጀል ተቆጥሮ ያለአግባብ ክስ ቢመሰረትብኝም በሰላማዊ ትግሌ እኮራበታሁ፡፡ ይቅርታ እንድጠይቅ የሚፈቀድልኝ ቢሆን ኖሮ ይቅርታውን የምጠይቀው ባልሰራሁት ጥፋት ወንጀለኛ ካለኝ ከዚህ ፍርድ ቤት ሳይሆን አብረው በመኖራቸው ብቻ በከፍተኛ ደረጃ በመሰቃየት ላይ ላሉት ወገኖቼ ድምጼን ከፍ አድርጌ ባለመጮሄ ነበር…“

በቀለ ገርባ ማን እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ለአንባቢዎቼ መናገር አልፈልግም፡፡

ለመናገር ብፈልግም እንኳ አልችልም፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ እርሱን ለመግለጽ የሚያስችል አንደበት ወይም ደግሞ ምዕናባዊ የስነጽሁፍ ችሎታ የሌለኝ እና አንድ ልዩ የሆነ ድፍረት፣ ታማኝነት እና ስብዕናን የተላበሰ እንዲሁም ለእናንተ መናገር የሚያስችል የልህቅና ተመሳስሎ የማይገኝለት ሰው ማለት ነው በቀለ ገርባ፡፡

በቀለም ከ”ጽንፈኛ” ወይም ደግሞ ከ”አሸባሪነት” ውጭ ሁሉን ነገር ማለት ነው፡፡

በቀለ ገርባን አሸባሪ ማለት ዘ-ህወሀትን ዴሞክራሲያዊ ቡድን ነው ብሎ እንደመጥራት ያህል ነው፡፡ (ባራክ ኦባማ ምንድን ነበር ያለው?!)

ዘ-ህወሀት “ዴሞክራት” ከሆነ በእርግጠኝነት በቀለ “አሸባሪ” ነው፡፡ አራት ነጥብ!

ይልቁንም ስለበቀለ ልዩ  የሆነው እውነታ ነገር ሌሎች በርካቶች እንደሚያደርጉት ሁሉ በቀለ በዘ-ህወሀት ላይ ጠንካራ የሆነ ትችት የሚያቀርብ ሰው አይደለም፡፡

የበቀለ ሀሳቦች ሚዛናዊነት፣ ምክንያታዊነት፣ በውል የታሰቡ እና በእውነታ ላይ ትክክለኛ በሆነ መንገድ ተዘጋጅተው የሚገለጹ ናቸው፡፡ በቀለ በዘ-ህወሀት የጭቆና አገዛዝ ማሽን የማይበሳጭ እና ስሜታዊ በሆነ መልኩ እና ያለማቋረጥ ጽሑፎችን በዘፈቀደ እያወጣ የሚያሰራጭ ሰው አይደለም፡፡

በቀለ መቁረጥ የሚያስችል መጥረቢያ የለውም፡፡ በምንም ዓይነት መንገድ ያልተቀባባውን እና እንደወረደ ያለውን ጥሬ ሐቅ እንዳለ ይናገራል፡፡

እ.ኤ.አ በ2010 በኢትዮጵያ ውስጥ ተደርጎ በነበረው የመሬት ቅርምት በቀለ ገርባ በእራሱ አንደበት የተናገረው ከዚህ በታች ቀርቧል፡፡

ቪዲዮ እየተናገረ ያለው (ከታች ተተርጉሞ የቀረበው) በእውነት ስለእውነት በሚገባ ታስቦበት በውል ተጢኖ የተደረገ፣ ብሩህ፣ ዘርፈ ብዙ እውቀት ያለው፣ የሚያስብ፣ ነገሮችን በፍጥነት የሚገነዘብ እና ለሰው ልጆች ጥልቅ የሆነ ፍቅር ያለው ሰው ከመሆን ውጭ ሌላ የሚታይበት ነገር ስለመኖሩ  አንባቢዎቼ ፍርዳቸውን እንዲሰጡ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡ (የቪዲዮ ምስሉን ለማየት እዚህ ጋ ይጫኑ፡፡ ትርጉሙንም ከዚህ በታች ይመልከቱ፡፡)

እ.ኤ.አ በ2010 በቀለ ምን ዓይነት ስብዕና ያለው ሰው መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ለዘ-ህወሀት እንዲህ በማለት አሳዬ፡

“…ኢህአዴግ [የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር እና በዘህወሀት የሚመራው የፖለቲካ ሸል ኮርፖሬሽን የብዙሀን የፖለቲካ ፓርቲ ህብረት] ምዕናብን በመመስረቱ ረገድ ምንም ያደረገው ነገር የለም አንልም፡፡ ያደረገው ነገር እንዳለ እምነታችን ነው ምክንያቱም ሀገሪቱ የመረጠችውን ነገር አድርጓል፡፡ ሀገርን መምራት እንዲህ ቀላል ነገር እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡  ሆኖም ግን ከዓመት ዓመት ኢህአዴግ የሕዝቡን ጥያቄ አይሰማም፣ ከእራሱ ተሞክሮ ለመሻሻል ወይም ደግሞ ለመማር አልሞከረም፣ እናም ህዝቡን እና ሀገሪቱን እንደሚጠበቀው ወደፊት ማስኬድ አልቻለም፡፡ ቀን በቀን ኢህአዴግ ወደኋላ እየሄደ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሀገሪቱን መምራት ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ሆኖም ግን ኢህአዴግ ለዚህች ሀገር ምንም ነገር አላደረገም ወይም ደግሞ አላበረከተም ለማለት በፍጹም አንችልም 

እያቀረብኩት ባለሁት በዚህ ጽሑፍ ላይ ስለመሬት ባለቤትነት፣ ስለትክክለኛ የመሬት አጠቃቀም እና ስለልማት ውጤቶች ትኩረት ለማድረግ እፈልጋለሁ፡፡የፌዴራል ሕገ መንግስቱ እና ገየዥው ፓርቲ [ኢህአዴግ] ሰነዶች ግልጽ እንደሚያደርጉት መሬት የሕዝብ እና የመንግስት ነው፡፡ ሆኖም ግን በእውነት እስቲ እንነጋገር እውን መሬት የሕዝብ ነው? በእርግጥ መሬት የመንግስት ነውን? ወይም ደግሞ መሬት በእርግጥ የሁለቱም ነውን?  (የመንግስት እና የሕዝብ ?) 

በእኛ ግምት መሬት የማንም አይደለም፡፡ ይልቁንም መሬት የገዥው ፓርቲ ባለስልጣኖች ብቸኛ ሀብት ነው፡፡ መሬት የሚሸጡት እና የሚለውጡት ንብረታቸው ነው፡፡ መሬት ጓደኞች የሚያበጁበት ለዘመዶቻቸው የሚያድሉት፣ ለፓርቲ አባሎቻቸው የሚሰጡት እና ሌላ አዲስ የፓርቲ አባላትን ለመመልመል በመሳሪያነት የሚጠቀሙበት ነገር ነው፡፡ 

መሬት የተማሩ ሰዎችንም እውር የሚያድርግ መሳሪያ ለመሆን በቅቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተወሰኑ ቦታዎች ያሉ የተማሩ ሰዎችን በምናይበት ጊዜ ስለፍትህ፣ ስለእኩልነት እና ስለመብት መናገር ከማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ ምክንያቱም መሬት እውሮች እንዲሆኑ አድርጓቸዋልና፡፡ 

በአሁኑ ጊዜ በከተሞች እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች የተማሩ ሰዎች መሬት ይሰጣቸዋል፣ እናም ምንም ዓይነት ነገር ላለመናገር አፋቸው ይለጎማል፡፡ ስለሆነም መሬት አፍን ለመሸበብ የሚያገልግል መሳሪያ ነው፡፡ መሬት በውጭ ሀገሮች ያሉትን ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ውስጥ ለመሳብ የሚያስችል ማግኔት ሆኗል፡፡ እነዚህን ሰዎች ዲያስፖራ እያሉ ይጠሯቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በአንድ ወቅት መሬት ለማግኘት ሲሉ እዚህ በመምጣት ወረውን ነበር፡፡ መሬት ካገኙ በኋላ ግን መሬቱን ሸጠው ወደመጡበት ሀገር ተመልሰው ሄዱ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ የእኛ ወገኖች በየመንገዱ ተበትነው ነበር እናም፣ አንዲት ሴንቲሜትር እንኳ የምትሆን መሬት አልነበራቸውም፡፡ 

ለዚህም ነው መሬትን ማግኔት ነው የምንለው፡፡ በአሁኑ ጊዜ መሬት ለጥቂቶቹ በብርሀን ፍጥነት ሀብትን ለማካበት የሚወነጨፍ ሮኬት ሆኖላቸዋል፡፡ ጥቂት ሀብታሞችን እንኳ ብንመለከት እና ታሪኬ ባጭሩ እየተባሉ እንደሚጠሩ ብንጠይቃቸው [ሀብታም በመሆናቸው] ይህንን ሁሉ ገንዘብ እንዴት አገኛችሁት ብለን ብንጠይቃቸው ይህንን ሀብት ጠንክረን በመስራት ነው ያገኘነው ብለው ለማስረዳት እንኳ አይችሉም፡፡ ይህንን ያህል ገንዘብ እንዴት ሊያጭቁ እንደቻሉ እንኳ አያውቁትም፡፡ 

በአሁኑ ጊዜ መሬት እንዴት እየጠቀመ እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡ እንግዲህ እራሳችንን ለማሻሻል የምናደርገው ጥረት ይኸ ነው፡፡ እያልን ያለነው በዜጎች መካከል ፍትሀዊ በሆነ መልኩ በእኩል መከፈል ያለበት ሀብት ነው፡፡ መሬት ወሳኝ ሀብት እንደሆነ እናውቃለን፡፡ 

እኛ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ከመሬት ሀብት ጋር ባለን ግንኙነት መሰረት በአራት ደረጃዎች እንደምንከፈል አምናለሁ፡፡ በስልጣን ላይ ያሉ እና መሬትን የሚሰጡ የመጀመሪያ ደረጃ ዜጎች የሚባሉት ናቸው፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ዜጎች ደግሞ መሬትን የሚቀበሉ ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ እያንዳንዱ ሰው መሬት አግኝቷል ማለት አይደለም፡፡ ሶስተኛ ደረጃ ዜጎች ደግሞ የመሬት ቅርምት ልውውጥ ተውኔቱን ከዳር ቆመው የሚመለከቱት የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ የሚመለከቱ ሰዎችም እንደሌሎች ሁሉ ይበላሉ፡፡ አራተኛ ደረጃ ዜጎች የሚባሉት ደግሞ ተወልደው ያደጉባቸውን እና እትብቶቻቸው የተቀበሩባቸውን መሬቶቻቸውን እየተነጠቁ የሚወሰዱባቸው ዜጎች ናቸው፡፡ እነዚህ ዜጎች ንብረት አልባ ተደርገው በመባረር መሬቶቻቸው ለሌሎች የሚሰጡባቸው ናቸው፡፡ የእንደዚህ ዓይነት ንብረትየለሽነት ሰለባ የሆኑ አርሶ አደሮች አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ነው እንግዲህ እየታገልን ያለነው፡፡ በኢትዮጵያ ገዥዎች የተከፋፈለው ብሄራዊ ሀብት እነርሱ የሀገራችንን ህዝብ በሚመድቡት የዜግነት ደረጃ መሰረት ስለሆነ እና ኢፍትሀዊነትን ያንሰራፋ በመሆኑ ምክንያት ብሄራዊ ሀብቱን የእኩልነት መርሆዎችን ባካተተ መልኩ ለህዝቡ የማከፋፈል ዓላማን ሰንቀን ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው፡፡ ለዚህ ነው በመታገል ላይ ያለነው፡፡ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል እንፈልጋለን እናም ይህንን ስርዓት በመለወጥ የመሪነቱን ሚና እንጫወታለን፡፡

 ተገቢ የመሬት አጠቃቃም ሌላው ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ እያንዳንዷ ቁራጭ መሬት፣ እያንዳንዷ ሜትር መሬት በአግባቡ በጥቅም ላይ መዋል እንዳለባት እናውቃለን፡፡ ሆኖም ግን ትላንት ጥሩ የሰብል ምርት የሰጠ መሬት በአሁኑ ጊዜ ምን ይመስላል? በአሁኑ ጊዜ ከዚያ መሬት ጥቂቱ የድንጋይ ክምር ማከማቻ ሆኗል፣ ግማሹ ደግሞ በአጥር ተከልሎ እሱን የሚጠብቅ ዘበኛ ተቀምጦለት ይታያል፡፡ ምናልባትም በአንድ ወቅት ዘበኛ፣ የእርሱ ዘመዶች ወይም ደግሞ ቤተሰቦች ባለቤት የነበሩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህ ዓይነት መልኩ ነው እንግዲህ ጉዳዩን የምንመለከተው፡፡ ስለሆነም አንዳንድ መሬት ተገቢ የሆነ አገልግሎት ይሰጣል፣ ጥቂቱ መሬት ደግሞ እንዲበላሽ ተደርጎ ይቀራል፡፡ ስለሆነም የማዕድን ሀብቶች ክምችት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የማዕድን ማውጣት ስራው ከተከናወነ በኋላ ለአካባቢው መሬት ምንም ዓይነት ክብካቤ ወይም መፍትሄ ሳይሰጥ እንዲሁ ይተዋ፡ል፡ ከዚህም የተነሳ መሬቱ ከጥቅም ላይ የማይውል ወይም ደግሞ የተጎዳ ሆኖ ይቀራል፡፡ 

ስለሆነም መሬቱ እንዲያገግም እና አስፈላጊ የሆነው መፍትሄ እንዲሰጠው ማድረግ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በበርካታ የማዕድን ማውጫ መሬቶች ላይ ምን ሊከሰት እንደሚችል የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ሆኖም ግን መሬቱን በአግባቡ ይዞ የመጠቀም መንገድ ወይም መፍትሄ ሊኖር ይገባል፡፡ 

ሌላው  ጉዳይ ደግሞ የአካባቢው ጤንነት ነውበሀገራችን የሚፈስሱ እና በብክለት የሞቱ ወንዞች አሉ፡፡ ብዙም ርቀት ሳይሄድ በብክለት ምክንያት ህይወት የሌላቸው እና የሞቱ ወንዞች አሉ፡፡ 

ከዚያም ከተበከሉ ወንዞች በቅርብ ሜትሮች ርቀት ላይ የሚኖሩ እና የተበከለውን ውኃ የሚጠጡ ወገኖቻችን አሉ፡፡ ከተበከሉ ወንዞች በጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ የሚገኙ እና የተበከለውን ውኃ የሚጠቀሙ እንስሶች አሉ፡፡ እንግዲህ እነዚህ ዜጎች እና የሀገር ሀብቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ልናስብ ይገባል፡፡ ታዲያ ለምንድን ነው አስፈላጊ ነገሮች የማይደረጉት እና ብክለትን መቆጣጠር የማይቻለው? ለምንድን ነው ከፋብሪካዎቻቸው ትርፍን የሚያጋብሱት ሰዎች ለዜጎቻችን፣ ለአርሶ አደሮቻችን ጤንነት የማያሳስባቸው? ለምንድን ነው መንግስት የአካባቢ ደህንነትን የማይጠይቀው? 

ሌላው ጥያቄ ደግሞ ስለማዳበሪያ ጉዳይ ነው፡፡ መንገስት ስለዚያ ጉዳይ አይናገርም፡፡ መንግስት በሀገር ውስጥ ማዳበሪያ ለማምረት የሚያስችል ዕቅድ ስለመጀመሩ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው? ይኸ ጉዳይ ውስብስብ ወይም ደግሞ ብዙ ገንዘብ የሚፈልግ ነገር ሆኖ አይደለም…“ [የተመደበው ጊዜ በማለቁ ምክንያት አወያዩ እየቀረበ ያለውን ትችት አስቆሙት፡፡]

በአዲስ ስታንዳርድ አማካይነት የቀረበውን ገላጭ እና መሳጭ የሆነውን የበቀለ ገርባን ቃለ መጠይቅ (እ.ኤ.አ ግንቦት 2015) ለማንበብ እዚህ ጋ ይጫኑ፡፡

የዓለም ባንክ እና የፍትህ የጦጣ ቢዝነስ በዘህወሀት የዝንጀሮ ፍርድ ቤት፣

“ዋና የፖሊስ አዛዦች፣ ዓቃብያን ሕጎች እና ዳኞች በፖሊስ መንግስት“ በሚል ርዕስ የዘ-ህወሀትን የጫካ ፍትህ ስርዓት የሚተቸው ባለ32 ገጽ የትችት ትንታኔየ ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ በ2006 ወጣ፡፡ “ረዥሙ ጉዙዬ ወደ ጨለማው የሰብአዊ መብት ረገጣ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ትችት በመዓመቱ መጀመሪያ ነበር የተጻፈው፡፡ ያ ትችት እ.ኤ.አ በ2005 ተካሄደ የተባለውን የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ ውዝግብ ተከትሎ የቃሊቲ ተከላካዮች እየተባሉ ይጠሩ በነበሩት ወደ 30 አካባቢ ወይም ከዚያ በላይ ለሚሆኑ ዋና የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች መሪዎች፣ ጋዜጠኞች እና በሌሎች ላይ የተደረገውን የፍርድ ቤት ሂደት በማስመልከት ሰፊ ትንታኔ በመስጠት ዓላማ ላይ ያነጣጠረ ነበር፡፡ ያ የፍርድ ሂደት የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማታለል የተዘጋጀ የመድረክ ላይ ተውኔት መሆኑን ለማሳየት ሞክሪያለሁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የማይሰራ እና በሙስና የተዘፈቀ የዳኝነት ስርዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የተቃዋሚ የፖለቲካ አባላትን እና ሰላማዊ አማጺዎችን ለማጥፋት እንደሆነ ለማሳየት ሞክሬ ነበር፡፡ የቃሊቲን ተከላካዮች የፍርድ ቤት ሂደት በእጅ ተመርጠው በተቀመጡ ዳኞች፣ በሸፍጥ ክስ፣ እውቀቱ በሌላቸው አቃብያን ሕጎች አማካይነት የሚካሄደው የፍርድ ቤት ሂደት ታላቅ ቅሌት እና የእዩልኝ እመኑኝ የታዕይታ አካሄድ መሆኑን በመግለጽ የፍትህ መጨንገፍ በማለት ድምዳሜ ሰጥቼ ነበር፡፡

የፍትህ ዘርፉ በዘ-ህወሀት የጨነገፈ ለመሆኑ በዓለም ባንክ ተዘጋጅቶ በቀረበው እና 448 ገጽ ባካተተው እና “በኢትዮጵያ ሙስናን መመርመር“ በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ሰነድ  በጥሩ ሁኔታ ቀርቧል፡፡ (በዓለም ባንክ የተመረመረው የኢትዮጵያ የፍትህ ዘርፍ ከበርካታዎቹ በጥቂቱ የፍርድ ቤቶችን፣ ፖሊሶችን፣ አቃብያን ሕጎችን፣ የአስተዳደር ስልጣን ያላቸው የሚመስሉትን አስተዳደራዊ ወኪሎችን፣ እና የመንግስት እና የግል ጠበቃዎችን፣ እስር ቤቶችን፣ እና ሕግ እና ደንቦችን በማውጣት ተፈጻሚነታቸውን የሚቆጣጠሩትን የሚሉትን ያካትታል፡፡)

በዓለም ባንክ ጥናት መሰረት በኢትዮጵያ የፍትህ ዘርፍ ያለው ሙስና አንድ ወይም ሁለት ዓይነት ገጽታዎችን ይይዛል፡፡ እነርሱም፡ በፍርድ ቤቶች ነጻ እንቅስቃሴዎች ወይም በሌሎች ዘርፎች ላይ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት፣ ለጉቦ ገንዘብ መጠየቅ ወይም ውሳኔን ወይም ድርጊትን ማስቀየር፡፡ የዓለም ባንክ ጥናት በፍትህ ዘርፉ  ላይ ስለሙስና፣ ስልታዊ የሆኑ ፍትህ ተቋማት ውድቀት፣ ስለፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እና የፍትህ አካላቱን ሀብቶች በአግባቡ መያዝን እና ስለተቋማቱ ጽናት ወሳኝ የሆኑ ምልከታዎችን አቅርቧል፡፡

በዘኢትዮጵያ በዘ-ህወሀት የፍትህ ዘርፍ ውስጥ ያለው ግዙፍ ሙስና የፖለቲካ ባለስልጣኖች ከሕግ ባለስልጣኖች የበለጠ ሰፊ ስልጣን (ከሹመት እስከ የሕግ አስተዳደር ድረስ) ያላቸው ከመሆኑ እውነታ የሚነጭ እና የፖለቲካ ባለስልጣኖች ትንሽ ተጠያቂነት የፍትህ ዘርፉን ለማጠናከር ትንሽ ማበረታቻ ብቻ ስላላቸው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በፍትህ ስርዓቱ እና በፖለቲካ ሂደቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ለመቆጣጠር ጥቂት የሆኑ የቁጥጥር ስርዓቶች ብቻ ነው ያሉት፡፡ ቀደም ሲል የቁጥጥር ስርዓቶች ቢኖሩም እንኳ ለበርካታ ጊዚያት ተቋርጠው የቆዩ በመሆናቸው በአሁኑ ጊዜ ሕጎችን ለማስተዳደር፣ ተጠያቂነትን ለማምጣት እና ጠንካራ የዘገባ አቀራረብ ስርዓትን እና ግልጸኝነትን በማምጣት ጠንካራ አስተዳደረዊ ተሞክሮን ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ እንደዚህ ያለ ተቋማዊ መበስበስ በዘ-ህወሀት የፍትህ ዘርፍ ውስጥ የሙስና ባህል ማደግ እና የፍትህን በሰፊው መዳኘት ያለመቻል ሚና በፍትህ ዘርፉ ተቋማት ውስጥ ማዳከም መቀጠሉ ብቻ አይደለም፣ ሆኖም ግን በፍትህ ስርዓቱ በእራሱ ላይ የሕዝብ አመኔታ እንዲታጣ ሆኗል፡፡

ፍትህ በፖሊስ መንግስት፣

በፖለስ መንግስት ውስጥ ፍትህን መጠበቅ በሰሀራ በረሀ መካከል ውስጥ ትሮፒካል ገነትን እንደመጠበቅ ያህል ነው፡፡

ታላቁ ግራውጭሆ  ማርክስ “የወታደር ሙዚቃ ለሙዚቃ እንደሆነ ሁሉ የወታደር ፍትህም ለፍትህ ነው“ የሚል ዘገባ አቅርቦ ነበር ይባላል፡፡

እንደዚሁም ሁሉ የዘ-ህወሀት የጦጣ ፍርድ ቤት ፍትህ እንደ ወታደራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዓይነት ነው፡፡ ማንም ምክንያታዊ የሆነ ሰው የወታደራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ፍትህን ያሰፍናል ብሎ አያምንም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ማንም ምክንያታዊ የሆነ ሰው ፍጹማዊ ስልጣን ካለው ጭራቃዊ ሸፍጠኛ አምባገናነዊ ፍትህን አይጠብቅም፡፡

እ.ኤ.አ በ2015 ባራክ ኦባማ አዲስ አበባ በመሄድ ቀጥ ብሎ በመቆም ዘ-ህወሀት ዴሞክራሲያዊ መንግስት ነው ብሎ አወጀ፡፡

የእኔ ውድ!  በእውነት ለመናገር ባራክ ኦባማ ዘ-ህወሀት ዴሞክራት ነው ብሎ ቢናገር ደንታ የለኝም፡፡

ዘ-ህወሀት በኢትዮጵያ ውስጥ የፖሊስ መንግስትን በመምራት ላይ ይገኛል እላለሁ፡፡

እ.ኤ.አ በ2012 “የአፍሪካ የፖሊስ መንግስት አርዓያነት“ በሚል ርዕስ አዘጋጅቸው በነበረው ትችቴ እንደሞገትኩት ሁሉ ዘ-ህወሀት ዋናው ተልዕኮው መዝረፍ የሆነ የጫካ ወሮበላ የዘራፊዎች ስብስብ ነው ብዬ በግልጽ ተናግሬ ነበር፡፡ ለውበት በማለት ከንፍሩን የከንፈር ቀለም የተቀባ ዓሳማ ከቀኑ መጨረሻ ያው ዓሳማ ነው፡፡ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በውጭ ሀገር የባንክ ሂሳቡ ውስጥ አጭቆ የሚገኝ ዘራፊ ወሮበላ ከቀኑ መጨረሻ ያው ዘራፊ ወሮበላ ነው፡፡ ያው ዘራፊ!

ነዋሪነቱ በዋሺንገተን ዲሲ የሆነ የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ የነበረውን ጋዜጠኛ የዘ-ሀወሀት የፖሊስ ወሮበላ ዘራፊ እ.ኤ.አ የካቲት 2013 ዘጋቢው ጋዜጠኝ በስልክ ቃለመጠይቅ ለማድረግ ሙሉ ስሙን በመጠየቁ ብቻ ያስፈራራው መሆኑን በፍጹም አልረሳውም፡፡ ያ ወሮበላ ዘራፊ ፖሊስ የቪኦውን ዘጋቢ ጋዜጠኛ እንዲህ ነበር ያለው፣ “ዋሺንግተን ወይም ቤተሰማያት ብትኖር ደንታ የለኝም፣ ጉዳዬ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን በቁጥጥር ስር አድርጌ እወስድሀለሁ፡፡ ይህንን ማወቅ አለብህ!!“ አንግዲህ ከቤተሰማያት መንጥረው ከሚያመጡ ወሮበላ ዘራፊ ፖሊሶች ይሰውረን ከማለት ውጭ ሌላ ምን ሊባል ይችላል?

አንድ እርባናየለሽ የዘ-ህወሀት የፖሊስ ኃላፊ እንደዚህ ያለ ፍጹም የሆነ ስልጣንን በአንድ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ መንግስት ሰራተኛ ጋዜጠኛ ላይ ለመተግበር እንደዚህ ድፍረቱን የሚያገኝ ከሆነ በዘ-ህወሀት የምግብ ሰንሰለት ውስጥ ባሉ ዜጎች ላይ ምን ሊታሰብ ይችላል?

የዘ-ህወሀት አገዛዝ የሙስና መፈልፈያ እንደሆነ ህይወት የሚያስተምረን ሲሆን ስልጣን ሙስናን ሲፈጥር ፍጹም የሆነ ስልጣን ደግሞ ፍጹም የሆነ ሙስናን ያስከትላል፡፡

የዘህወሀት ህጋዊ ግድያ፡ የበቀለ ገርባ እና ተከላካይ ጓደኞቹ ዕጣፈንታ በዘህወሀት የጦጣ ፍርድ ቤት፣

በቀለ ገርባ እና ተከላካይ ጓደኞቹ በኢትዮጵያ ውስጥ በዘ-ህወሀት የጦጣ ፍርድ ቤት በተወነጀሉበት የሸፍጥ ክስ ፍትሀዊ የፍርድ ሂደት ያገኛሉ ብሎ የሚያምን አለ?

በኢትዮጵያ በዴፕሎማሲው ማህበረሰብ ውስጥ በቀለ ገርባ እና ተከላካይ ጓደኞቹ በዘ-ህወሀት የጦጣ ፍርድ ቤት በተወነጀሉበት የሸፍጥ ክስ ፍትሀዊ የፍርድ ሂደት ያገኛሉ ብሎ የሚያምን አለ?

በኢትዮጵያ በዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ወይም በዩናይትድ ስቴትስ የመንግስት መምሪያ ውስጥ በቀለ ገርባ እና ተከላካይ ጓደኞቹ በዘ-ህወሀት የጦጣ ፍርድ ቤት በተወነጀሉበት የሸፍጥ ክስ ፍትሀዊ የፍርድ ሂደት ያገኛሉ ብሎ የሚያምን አለ?

በአፍሪካ ህብረት ውስጥ በቀለ ገርባ እና ተከላካይ ጓደኞቹ በዘ-ህወሀት የጦጣ ፍርድ ቤት በተወነጀሉበት የሸፍጥ ክስ ፍትሀዊ የፍርድ ሂደት ያገኛሉ ብሎ የሚያምን አለ?

በኢትዮጵያ ዲያስፖራ ውስጥ በቀለ ገርባ እና ተከላካይ ጓደኞቹ በዘ-ህወሀት የጦጣ ፍርድ ቤት በተወነጀሉበት የሸፍጥ ክስ ፍትሀዊ የፍርድ ሂደት ያገኛሉ ብሎ የሚያምን አለ?

በዓለም አቀፈፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና በፕሬስ ጥበቃው ማህበረሰብ ውስጥ በቀለ ገርባ እና ተከላካይ ጓደኞቹ በዘ-ህወሀት የጦጣ ፍርድ ቤት በተወነጀሉበት የሸፍጥ ክስ ፍትሀዊ የፍርድ ሂደት ያገኛሉ ብሎ የሚያምን አለ?

ከምላሴ ጸጉር ይነጭ አንድም አይኖርም! አንድም!

ጥቂቶቻችን ለምንድን ነው በቀለ ገርባን እና ሌሎች 21 ተከላካይ ጓደኞቹን የሚዳኝ የፍትህ አካል ሂደት አለ በማለት እራሳችንን የምናታልል?

ስለበቀለ ገርባ የወጡትን መግለጫዎች እና ትችቶች እንዲሁም የሸፍጥ ክሶችን በግንኙነት መስመር ላይ ባነበብኩበት ጊዜ እራሴን ነቀነቅሁ፡፡ ስለዘ-ህወሀት የፖለቲካ የይስሙላ ፍርድ ቤቶች የምትናገሩ ሰዎች ዘ-ህወሀት የፍርድ ቤት ስርዓትን እያራመደ ነው የሚያሰኝ ሕጋዊነትን ትሰጡታላችሁ፡፡ አካፋን አካፋ ማለት አለብን፡፡ ህወሀት ምንም ዓይነት የፍርድ ቤት ስርዓት እያራመደ አይደለም፣ ይልቁንም በተጻራሪው የጦጣ የፍርድ ቤት ሂደትን በማራመድ ላይ ይገኛል፡፡

ዘ-ህወሀት ተቃዋሚቹን እና ተቺዎቹን መግደል ተሸክሞት የቆየው የብዙ ጊዜ ተልዕኮ አለው፡፡ የዘ-ህወሀት የፍርድ ሂደት ከእውነታው ያፈነገጠ ነው፡፡ ነጻ የሆኑ ሰዎችን (የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አንቀጽ 20 (3) በግልጽ ተጥሷል፡፡ አሁን በህይወት የሌለው የዘ-ህወሀት መሪ አምባገነኑ መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ በ2011 በኖርዌ በመገኘት ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ጥፋተኛ የሆኑት ፍሪላንስ የሰዊድን ጋዜጠኞች ጆሀን ፔርሰን እና ማርቲን ሽብዬ በአሸባሪነት የክስ ሂደታቸው በመታየት ላይ ነው ብሎ አውጆ ነበር፡፡

አምባገነኑ መለስ እርግጠኛ በሚመስል መልኩ እነዚህ ሁለቱ ጋዜጠኞች ቢያንስ የአሸባሪዎች ተላላኪዎች ናቸው ብሎ ነበር፡፡ ፔርሰን እና ሽብዬ የብዙ ዓመታት እስራት ተበይኖባቸው ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ነሐሴ በ2005 የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል የሆኑት ክርስቶፈር ስሚዝ (የኒው ጀርሲ ሬፐብኪካን) አሁን በህይወት ከሌለው አምባገነኑ መለስ ጋር ተገኛኙ፡፡ እ.ኤ.አ ጥቅምት 22/2007 ስሚዝ (የኒው ጀርሲ ሬፐብሊካን) በዚያ ጊዜ ከአምባገነኑ መለስ ጋር ያደረጉትን ውይይት እንዲህ በማለት እንደሚከተለው አጠቃለው አቀረቡት፡

“…ከዚህም በተጨማሪ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በጣም ረዥም የሆነ ስብሰባ አለኝ፡፡ የዴሞክራሲ አቀንቃኝ የነበሩት እና የተገደሉት ሰላማዊ አማጺዎች ሁኔታ እንዲመረመር እና ጥፋተኞቹም በሕገ ፊት ቀርበው በኃላፊነት እንዲጠየቁ እንዲሁም ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንደፈቱ እና እንደለቀቁ ተማጽኘው ነበር

 በመጨረሻ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከተቃዋሚዎች ጋር አብሮ እንዲሰራ እና የተለያዩ ሀሳቦች ካሏቸው ቡድኖች ጋር ተከባብራችሁ እና ተቻችላችሁ ኢትዮጵያ ያሉባትን ተግዳሮቶች ለማስወገድ ስሩ የሚል ጥያቄ ባቀረብኩለት ጊዜ እንዲህ ነበር ያለው፣ ሁሉም የሀገር ክህደት ወንጀለል ፈጻሚዎች ለመሆናቸው መረጃው በእጀ አለ ነበር ያለኝ 

ሁሉን ነገር አውቃለሁ በሚለው ድምጸቱ ተገርሜ ነበር፡፡ ጥፋተኛ! መለስ በማለቱ ምክንያት ብቻ  ሁሉም ጥፋተኛ ናቸው ማለት ነውን? ምንም ዓይነት የፍርድ ሂደት የለም ማለት ነውን? የዝንጀሮ ፍርድ ቤት የፍርድ ሂደት እንኳ?… 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያንን ዓይነት መንገድ እንዳይከተል ተማጽኘው ነበር፡፡ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

እንግዲህ አምባገነኑ መለስ እና ጓደኞቹ ጫካ በነበሩበት ጊዜ በዚህ መልክ ነበር የሚሰሩት፡፡ በተቀናቃኞቻቸው ላይ ፋይሎችን ይይዛሉ እናም የጫካ ፍትህን ያጎናጽፏቸዋል፡፡ የዝንጀሮ ፍርድ ቤት እንኳ አልነበረም!

እ.ኤ.አ በ2008 አምባገነኑ መለስ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዋ የሴት የፖለቲካ ፓርቲ መሪ የነበረችው ብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳዩአ በፍርድ ሂደት መታየት ይቅርና ምንም ዓይነት ጥያቄ ሳይቅርብላት በፍጥነት እንድትከሰስ አደረገ፡፡ የጦጣው ፍርድ ቤት የፍርድ ሂደት ይደረግ እንኳ አላለም ነበር! ብርቱካን በቀጥታ ከመንገድ ተይዛ ለብቻዋ እንድትታሰር በማለት አምባገነኑ መለስ እራሱ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ በኋላም እንዲህ በማለት አወጀ፣ “ብርቱካንን ለመፍታት ከማንም ጋር ምንም ዓይነት ድርድር በፍጹም አይኖርም፡፡ በፍጹም፡፡ አራት ነጥብ፡፡ ያ የሞተ ጉዳይ ነው፡፡“ አሁን በህይወት የሌለው የዘ-ህወሀት መሪ የነበረው አምባገነኑ መለስ ይህንን የመሰለ መግለጫ በሚሰጥበት ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ሕግ ማለት እርሱ  እንደሆነ እና የፍትህ የመጨረሻው ምንጭም እርሱ ብቻ እንደሆነ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማወጁን አልተገነዘበም ነበር፡፡ የእርሱ ቃላት የሀገሪቱን ሕገመንግስት ይንዳሉ!

እ.ኤ.አ በ2009 ከአገዛዙ ቁንጮ መሪዎች የሆነው አንዱ 40 የሚሆኑ ተከላካዮችን ከፍተኛ የሆኑ የመንግስት ባለስልጣኖችን ለመግደል እና የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎትን እና የኤሌክትሪክ መጠቀሚያዎችን ለማውደም እና በሀገሪቱ ውስጥ መጠነ ሰፊ የሆነ የትርምስ ሁኔታን ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል በማለት ዋነኛ ወንጀለኞች አድርጎ አቀረባቸው፡፡ በሁለም ላይ ክስ እንዲመሰረት ተደርጎ የረዥም ዓመታት የእስር ብይን ተበየነባቸው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያላቸው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ርዕዮት ዓለሙ፣ ውብሸት ታዬ እና ሌሎች በርካታዎቹ ለወራት ያህል የሕግ አማካሪ እንዳይዙ በመከልከል የዘ-ህወሀትን ሕገ መንግስት አንቀጽ 20 (2) በመጣስ በእስራት እንዲቆዩ ተደርጓል፡፡

የኃይማኖት ጣልቃገብነት እንዲቆም የኢትዮጵያ ሙስሊም ወትዋቾች ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት ተይዘው ወደ ማጎሪያው እስር ቤት ተጥለዋል፣ እንደዚሁም ደግሞ የሕግ አማካሪ እንዳይዙ ተከልክለዋል፡፡ በማጎሪያው እስር ቤት ከሕግ አግባብ ውጭ በመያዝ እንዲስተናገዱ ተደርገዋል፡፡ በርካታ ጋዜጠኞች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እና ወትዋቾች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርገው ጉዳያቸው በይስሙላው ፍርድ ቤት እንዲታይ እና የጸረ ሽብር አዋጅ እየተባለ በሚጠራው የሸፍጥ አዋጅ ተከሰው እንዲሰቃዩ ተደርገዋል፣ እንዲሁም የሕግ አማካሪ እንዳያገኙ ተደርገው በማጎሪያው እስር ቤት እንዲማቅቁ ተደርገዋል፡፡ በዘ-ህወሀት ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ምንም ዓይነት የሕግ አማካሪ ሳይኖራቸው ለጥያቄ እንዲቀርቡ እየተደረጉ የግዴታ የእምነት ቃል እንዲሰጡ ይደረጋሉ፡፡ ሆኖም ግን የዘ-ህወሀት ሕገ መንግስት አንቀጽ 19 (5) ማንም ቢሆን ተገድዶ ቃሉን የመስጠት ግዴታ የለበትም፣ በግዳጅ የተሰጠ ማስረጃ ሁሉ ተቀባይነት የለውም የሚል መብትን ያጎናጽፋል፡፡

የዞን 9 ጦማርያን የፍርድ ሂደት ሸፍጥን በያዘ መልኩ 34 ጊዜ እንዲቋረጥ እየተደረገ በሕገ ወጥ መልክ የፍርድ ሂደታቸው ሳይታይ ለረዥም ጊዜ በእስራት እንዲማቅቁ ተደርገዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ሀምሌ 2015 ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኝ በመጠበቅ ዘ-ህወሀት 2 ጦማሪዎችን እና 3 ጋዜጠኞችን ከማጎሪያው እስር ቤት ለቋል፡፡ መንግስት እነዚህን አምስቱን ጸሐፊዎች በድንገት ፈትቶ የክስ ጉዳያቸውም እንዲቋረጥ እና ነጻ ተብለው እንዲሄዱ ሲደረግ ፍርድ ቤቱ ስለጉዳዩ ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረውም፡፡

አዎ ዳኞች ስለጉዳዩ ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም!!!

የዘ-ህወሀት የፍርድ ሂደት ስርዓት ተጠርጣሪዎችን ወንጀል ሰርተዋል የሚላቸውን በቁጥጥር ስር በማዋል ለሁለት ዓመታት ያህል አስሮ ከመረመረ በኋላ የፍርድ ሂደት ሌላ ተጨማሪ ማስረጃ ያስፈልጋል በማለት ማለቂያ የሌለው የተንዛዛ የጊዜ ቀጠሮ በመስጠት እና በማሰቃየት ከዓለም ብቸኛው ነው፡፡

የዘህወሀት የጦጣ ፍርድ ቤቶች ቅንጣት ፍትህ

በኢትዮጵ የፍትህ ዘርፍ ውስጥ ስለሙስና መናገር ማለት ከኦርዌል 1984 የእውነት ሚኒስቴር ጋር መነጋገር ማለት ነው፡፡ (ቅንጣት እውነት)

በኦርዌል 1984 የቅንጣት እውነት ዋና ዓላማው ፓርቲው ፍጹማዊ ነው፣ ሁሉም አዋቂዎች ናቸው፣ ሁሉም ኃይለኞች እና አይበገሬዎች ናቸው የሚልን ምዕናብ የሚይዝ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የፍትህ ሚኒስቴር ዋና ዓላማ ዘ-ህወወሀት ፍጹማዊ ነው፣ ሁሉንም ነገር ያውቃል፣ ሁሉም ኃይለኞች እና የማይበገሩ ናቸው የሚል ነው፡፡

የሕግ የበላይነት ፍጹም በሆነ መልኩ በሌለበት፣ ነጻ እና ከአድሎ የጸዳ ፍርድ ቤት በሌለበት የዳኝነት ስርዓት ፍትህ ሊኖር አይችልም፡፡

አሁን በቅርቡ በጦጣው ፍርድ ቤት ክስ በሚሰማበት ጊዜ በቀለ ለዘ-ህወሀት የጦጣ ፍርድ ቤት በማዕከላዊ እስር ቤት (በአዲስ አበባ ማዕከል የሚገኝ እስረኞች በማሰቃየት የሚታወቅ የፖሊስ ጣቢያ) ከምታሰር ሞትን እመርጣለሁ አለ ተብሎ ተዘግቧል፡፡

ወንድሜ በቀለ! አይዞህ! እጅህን እንዳትሰጥ፡፡ ቅዱሳን ጽሁፎች እንዲህ በማለት ያስተምሩናል፣ “ሰይጣናዊ ሰዎች በእርግጠኝነት በሰሩት ኃጢአት ይቀጣሉ፡፡ ሆኖም የእግዚአብሄር ልጆች በነጻ ይሄዳል፡፡“

በቀለ ገርባ፣ እስክንድር ነጋ እና ሌሎችም የፖለቲካ እስረኞች ሁሉ በነጻ ይለቀቃሉ፡፡ ስለዚያ ጉዳይ ምንም ዓይነት ጥያቄ የለውም!

እኔ ባለኝ መረጃ መሰረት የዘ-ሀውሀት አመራር በአብዛኛው የደናቁርትን ስብስብ ያካተተ ነው፡፡

አባባሌን ለማጠናከር የመደምደሚያ መረጃ ለማቅረብ ደስተኛ ነኝ፡፡

ከላይ በቀረበው ስዕል መሰረት በበቀለ ገርባ እና በ21ዱ ሌሎች ተከላካዮች ላይ ከቀረበው የሽብር ውንጀላ ኮሚሽን የክስ ሰነዱ ላይ በማውጣት የዘ-ህወሀት ፌዴራል ረዳት አቃቤ ሕግ ፈቃዱ ጸጋ እንደ ሕጋዊ ፊርማ እንዲያገለግል የአውራ ጣቱን የአሻራ ፊርማ በክስ ሰነዱ ላይ አሳረፈበት፡፡

አዎ የአውራ ጣት አሻራ!

Gerba 8በኢትዮጵያ እና በአብዛኛው በአፍሪካ ውስጥ ማነበብ እና መጻፍ የማይችል ሰው ነው የጣቱን አሻራ እንደፊርማ ሊጠቀም የሚችለው፡፡

በዘ-ህወሀት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ማይም የፌዴራል ዓቃቢ ሕግ በመንግስት ላይ ወንጀል ሰሩ በተባሉት ሰዎች ላይ ክስ መመስረት ተፈቅዶለታል፡፡

ማንበብ የማይችል ዓቃቢ ሕግ እንዴት ክስ መመስረት ይችላል?

ወንጀለኛውን የደርግ አገዛዝ አንደማወግዘው ያህል በመላው ሀገሪቱ ውስጥ የተሰጠው የግዳጅ የመሰረተ ትምህርት ፕሮግራም እያንዳንዱ ዜጋ ስሙን በአማርኛ ጥሁፍ መፈረም እንዲችል እንጂ በምንም ዓይነት መልኩ የአውራ ጣት የአሻራ ፊርማውን እንዳይጠቀም ሰጥቶት ለነበረው ዋስትና ታላቅ ክብር እሰጣለሁ፡፡

በአሁኑ ጊዜ ማይምነት የዘ-ህወሀት ዓቃብያነ ሕጎች የወንጀለኛ ክስ ሰነዶችን በአውራጣት አሻራቸው ይፈርማሉ፡፡

የጦጣው ፍርድ ቤት ብቻ የወንጀለኛ ክስ ሰነዶች በመሀይም ዓቃቢ ሕግ ሕጋዊነታቸው ይረጋገጣል፡፡

የምናገርበት አንደበት የለኝም!!! ድምጼን ከፍ አድርጌ በመጮህ ምን ማለት እችላለሁ!?

ሆኖም ግን ልንገረም አይገባም፡፡ አብዛኞቹ የዘ-ህወሀት ማይም መሪዎች ምንም ዓይነት መሻሻል አላሳዩም፡፡ የዘ-ህወሀት መሪዎች የተማሩ ለመምሰል የተጭበረበሩ ዲግሪዎችን ከግንኙነት መስመር የዲፕሎማ መቀፍቀፊያ ወፍጮዎች የገዙ ለመሆናቸው በርካታ ማስረጃዎች አሉ፡፡

እ.ኤ.አ ግንቦት 2015 በቀለ ገርባ እንዲህ ብሎ ነበር፡

ከፍተኛ የሆነ ትግዳሮት አለ፡፡ ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን ተስፋ እንዳለ አስባለሁ፡፡ ነገሮች ሁሉ ቀስ በቀስ መለወጥ እንደሚችሉ ሁልጊዜ አምናለሁ፡፡ ለመቶ ዓመታት ወይም ለሺዎች ዓመታት በነበሩን ባህሎች መሰረት መንግስትን ለመለወጥ ኃይልን መጠቀም ወይም ደግሞ የትጥቅ ትግል ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ አድርገን እናምን ነበር፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ ያለፈበት ነገር ሆኗል፣ በአሁኑ ጊዜ አገዛዞችን በሰላማዊ ትግል ፊት ለፊት በመጋፈጥ መለወጥ ይቻላል፡፡ ሰዎች ለሰላማዊ ትግል ቁርጠኝነቸታውን ካረጋገጡ ነገሮች ሁሉ ይለወጣሉ ብየ አስባለሁ፣ እናም መንግስት ይህንን ሁኔታ አሟጦ መጠቀም መቻል አለበትማለትም እንደተቃዋሚ ብዙ እገዛ እያደረግን ነው፣ በርካታ ነገሮችን አበርክተናል፡፡

እ.ኤ.አ ነሐሴ 2015 በቀለ እንዲህ ብሎ ነበር፣ በማንኛውም ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ምን ሊከሰት እንደሚችል ማንም በእርግጠኝነት ሊያውቅ አይችልም፡፡ በማንኛውም ጊዜ ሰዎች በቁጥጥር ስር ይውላሉ፣ እንዲሸማቀቁ ይደረጋሉ ወይም ደግሞ ይገደላሉ ወይም ታፍነው ይሰወራሉ፡፡“ በቀለ ገርባ በአሁኑ ጊዜ በእስር ቤት ውስጥ ነው ምክንያቱም በኢትዮጵያ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ለውጥ እንዲመጣ ይቀሰቅስ ነበርና!

በአሁኑ ጊዜ በቀለ ገርባ በእስር ቤት ውስጥ ነው ምክንያቱም ስለፍትህ፣ እኩልነት እና ፍትሀዊነት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይሰብክ ነበርና!

የፍትህ ጎራዴ በኢፍትሀዊነት መዶሻ ስትቀጠቀጥ ያንን ዕኩይ ታላቅ ተግባር የማጋለጡ ተግባር የተራው ሕዝብ ነው!

በቀለ ገርባ እና ሌሎች 21 ተከላካይ ጓደኞቹ በአስቸኳይ ይፈቱ!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!  

ሚያዝያ 25 ቀን 2008 .

 

 

 

Similar Posts