ኢትዮጵያ ወዴት ነው የምትሄደው እና የማትሄደው?

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም    

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

Quo vadis 4(እ.ኤ.አ መጋቢት 27/2016 በማሪዮት ጆርጅታዎን  ከተማ  (ዋሺንንግቶን ድሲ ) ቪዥን ኢትዮጵያ በተባለው ድርጅት አስተባባሪነት “ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ፡ ሽግግር፣ ዴሞክራሲ እና ብሄራዊ አንድነት ጉባኤ” በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛው ቅጅ ከቀረበው ንግግር የተወሰደ ነው፡፡)

“ስለወዲፊቷ ኢትዮጵያ፡ ሽግግር፣ ዴሞክራሲ እና ብሄራዊ አንድነት ጉባኤ” በሚል ርዕስ ስለተዘጋጀው ጉባኤ ቪዥን ኢትዮጵያን እና የጉባኤውን አስተባባሪዎች በሙሉ ለማመስገን እፈልጋለሁ፡፡

ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው ከወራት በፊት በዚህ ጉባኤ ላይ እንድገኝ እና እንድሳተፍ ጥሪ ባቀረበልኝ ጊዜ ኢትዮጵያን ገጥመዋት ባሉት መሰረተ ሰፊ የተሳትፎ መድረክ፣ ውይይት እና ክርክር ጉዳዮች ሀሳብ እጅግ በጣም ነበር የተደሰትኩት፡፡ የቪዥን ኢትዮጵያን አርዓያ በመከተል ሌሎችም እንደዘሁ በርካታ የውይይት መድረኮችን ያዘጋጃሉ የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

ፕሮፌሰር ጌታቸው እና የቪዥን ኢትዮጵያ አስተባባሪዎች በሙሉ ላደረጉት ከፍተኛ ጥረት እና ጉባኤው በስኬታማነት በመካሄዱ ያለኝን አድናቆት እና ምስጋና ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡ ስለኢትዮጵያ እና ስለኢትዮጵያ ሕዝብ ያገባናል በማለት ይህ ጉባኤ ስኬታማ እንዲሆን የየበኩላችሁን ጥረት ላደረጋችሁ ወገኖቼ ሁሉ ከፍተኛ የሆነ ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡ ያለጥረት ለውጥ አይመጣምና፡፡

እንደዚሁም ሁሉ ይህ ጉባኤ ለሕዝብ ተደራሽ እንዲሆን ሰፊ ሽፋን በመስጠት ሲዘግብ ለነበረው ለኢትዮጵያ ሳቴላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ከፍ ያለ ምስጋና ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) ከንቱ ፕሮፓጋንዳ ተዳክሞ በነበረበት በዚያ አስከፊ ወቅት ከስድስት ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ ግንቦት 2010 ኢሳት አማራጭ የዜና፣ የመረጃ፣ የትንታኔ እና የመዝናኛ ምንጭ በመሆን ለኢትዮጵያውያን ወገኖቹ አዲስ ክስተት በመፍጠር ከሕዋ በመብረቃዊ ኃይል አለሁላችሁ በማለት ከተፍ አለ፡፡

የኢሳት የአማካሪ ኮሚቴ የመጀመሪያው ሊቀመንበር ሆኘ አገልግያለሁ፡፡ የተለያዩ የሙያ ስብጥር ካላቸው ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን መስራት እጅግ በጣም የሚያስደስት ነገር ነበር፡፡

በጨለማው ጎን በኩል ያሉት እና ስልጣናቸውን በፍርሀት፣ በቁጣ፣ በጥላቻ፣ በበቀል እና የኃይል እርምጃን በመውሰድ ለማቆየት የሚፈልጉ ኃይሎች የኢሳትን ስርጭት ለማቋረጥ ያለ የሌለ ኃይላቸውን ቀጥለውበት እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ግን ኢሳት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ተጋርዶ የሚገኘውን የጨለማ መጋረጃ የብርሀን እጀታ ባለው ጎራዴው እየበጠሰ እና እየበጣጠሰ ብሩህ ብርሀን ማሳየቱን ቀጥሎበት ይገኛል፡፡

የአምባገነኖች ዋና የጥፋት መሳሪያቸው ሚስጥራዊነት ነው፡፡

አምባገነኖችን ለማጥፋት የተሻለው መሳሪያ ደግሞ ነጻ ሜዲያ ነው፡፡

ለአምባገነኖች የተሻለው የጦርነት ሜዳ ዕቅድ እስከ ጥርስ ድረስ የእውነታን ዝናር ታጥቆ  እራቁታቸውን በስልጣን እርካብ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው በሚገኙት ጨቋኞች የተጠያቂነት ጨለማ ላይ አንጸባራቂ ብርሀን ማብራት ነው፡፡

ምንም ዓይነት ራዕይ በሌላቸው ጨቋኞች ጨለማ ላይ አንጸባራቂ ብርሀናችሁን በማብራታችሁ ኢሳትን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ  መረጃ በማቅረብ እና ሰፊውን ሕዝብ በማስተማር እያደረጋችሁ ላላችሁት ከፍተኛ ጥረት ኢሳቶችን በጣም አመሰግናለሁ፡፡

በዚህ ጉባኤ ላይ በመገኘት ምሁራዊ ክህሎት የታከለበት እና ቀስቃሽ የሆነ ጽሑፍ ላቀረባችሁ ወገኖቼ በሙሉ ላቅ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ ካቀረባችኋቸው ምልከታዎች እና ዘርፈ ብዙ አመለካከቶች እና ሀሳቦች በርካታ ፍሬ ነገሮችን ተምሪያለሁ፡፡

በዚህ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በጉባኤው በመገኘት ተሳትፎ ያደረጋችሁትን ወገኖቼን በሙሉ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ላቀረባችኋቸው ጠንካራ ጥያቄዎች እና ልዩ ምልከታ ለተንጸባረቀባቸው አስተያየቶቻችሁ ከፍ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡ የእናንተ ተሳትፎ ይህንን ጉባኤ በእጅጉ ፍሪያማ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

አብዛኞቻችሁ እንደምታውቁት ሁሉ አሁን በህይወይት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ በ2005 ተካሄደ የተባለውን የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ ተከትሎ ተፈጥሮ በነበረው ውዝግብ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ባልታጠቁ ሰላማዊ አማጺዎች ላይ የእሩምታ ተኩስ እንዲከፈት በማዘዝ በወገኖቻችን ላይ ከፍተኛ እልቂት እንዲፈጠር ካደረገ በኋላ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ትግል ውስጥ ገብቻለሁ፡፡ በዚያ አሰቃቂ እልቂት ላይ 193 ንጹሀን ወንዶች፣ ሴቶች እና ልጆች በአነጣጣሪ አልሞ ተኳሽ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች በአደባባይ በየመንገዶች ላይ በግፍ የተገደሉ ሲሆን በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ከ30 ሺ በላይ የሚሆኑ ንጹሀን ዜጎች ደግሞ ወደ ማጎሪያው እስር ቤት ዘብጥያ እንዲወርዱ ተደርገዋል፡፡ እነዚህን መጠነ ሰፊ የተንሰራፉ የሰው እልቂት እና መብት ድፍጠጣ ኢሰብአዊ ወንጀሎችን የፈጸሙት 237 የፖሊስ ነፍሰ  ገዳዮች በአሁኑ ጊዜ ያለምንም ተጠያቂነት ደረታቸውን ገልብጠው በየአውራ መንገዶች በነጻነት በመንገዳወል ላይ ይገኛሉ፡፡

ያ አሰቃቂ እልቂት በአሁኑ ጊዜም ቀጥሎ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ብዙሀኑን ሕዝብ በቁጥጥር ስር ማዋል እና በዜጎች ላይ ስቃዮችን መፈጸም በተጠናከረ መልኩ ቀጥሎ ይገኛል፡፡

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ብቻ በአምባገነኑ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) በኦሮሚያ ክልል በ270 ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ አሰቃቃ እልቂት ተፈጽሟል፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩት ወገኖቻችን ደግሞ በዘ-ህወሀት ድብቅ እና በሚታወቁ የማጎሪያ እስር ቤቶች ውስጥ ታስረው በመማቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ የተገደሉትን እና በእስር ቤት ውስጥ በመሰቃየት ላይ የሚገኙትን ወገኖቻችንን ሌላ ማንም ሳይሆን እራሱ ዘ-ህወሀት ብቻ የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ እነርሱ ግልፅነት የሚባል ነገርን በፍጹም አያውቁም፡፡ እነርሱ የሚያውቁት እና የተካኑበት ነገር ቢኖር መግደል እና በማጎሪያው እስር ቤት በጅምላ እና በተናጠል ዘብጥያ ማውረድን ነው፡፡

በኦሮሚያ ላይ እየተካሄደ ላለው የሕዝብ ቁጣ ዘ-ህወሀትን በመቃወም ከሕዝቡ ጎን አብሮ መሰለፍ ያለመቻል እና ተጨባጭነት ያለው ወገናዊ ድጋፍ ያለማሳየት አሳፋሪ እና በእራሱ የሞራል ስብዕና ኪሳራ ውጤት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ኦሮሞ ወገኖቻችን እየደሙ፣ ወደ እስር ቤት እየተጋዙ እና በስውር እየታፈኑ ደብዛቸው እንዲጠፋ እየተደረጉ ባሉበት ሁኔታ ሌሎቻችን በዝምታ የምንመለከተው ከቶ ለምንድን ነው? እኮ ለምን?

የእራሴን ምልከታ ከማቅረቤ በፊት እ.ኤ.አ በ2005 ተካሄደ በተባለው የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ በአምባገነኑ መለስ በግፍ ላለቁት 193 ወንዶች፣ ሴቶች እና ልጆች፣ ሌሎች ዘ-ህወሀት እልቂት ለፈጸመባቸው በሺዎች ለሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎች እና ምንም ዓይነት አጣሪ ኮሚሽን ሳይቋቋም ከይስሙላው የቅርጫ ምርጫ በፊት እና የማጣራት ስራ ከተሰራም በኋላ ምንም ዓይነት ፍትህ ሳያገኙ ደማቸው እንደ ውሻ ደም ተቆጥሮ ደመ ከልብ ሆኖ ለቀረው ወገኖቻችን፣ አሁን በቅርቡ ደግሞ በዘ-ህወሀት መጠነ ሰፊ የማን አለብኝነት የጭካኔ የኃይል እርምጃ በመውሰድ እልቂት ለፈጸሙባቸው 270 በመረጃ ተረጋግጦ ለተያዙ የእልቂት ሰለባዎች እና በዘ-ህወሀት የማጎሪያ እስር ቤት በመማቀቅ ላይ ለሚገኙት የፖለቲካ እስረኞች እያደረግሁት ላለው እልህ አስጨራሽ ትግል ከጎኔ ተሰልፋችሁ የበኩላችሁን ወገናዊ ግዳጃችሁን እንዲትወጡ እንድትቀላቀሉኝ በአጽንኦ እጠይቃለሁ፡፡

በአሁኑ ጊዜ ኢፍትሀዊነት በሆነ መልኩ በእብሪተኛው ዘ-ህወሀት ማን አለብኝነት በግፍ ታስረው በመማቀቅ ላይ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን ጀግኖችን ለአንድ አፍታ እንድናስታውሳቸው ለማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡ እነዚህም ብርቅየዬ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ጀግኖች በርካታ ናቸው፡፡ ሁሉንም ዘርዝሮ ለማቅረብ የሚቻል አይሆንም፡፡ ሆኖም ግን እስቲ ከብዙዎቹ ጥቂቶቹን እናስታውስ፡፡

እስክንድር ነጋን፣ አንዷለም አራጌን፣ በቀለ ገርባን፣ አህመድ ጀቤልን፣ አበበ ቀስቶን፣ እማዋይሽ ዓለሙን፣ ውብሸት ታዬን፣ ተመስገን ደሳለኝን እና በርካታዎቹን ሌሎችንም እናስታውስ፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ወዴት እየሄድች ነው/quo vadis ?

ይህንን ጥያቄ በጥያቄ ለመመለስ የበለጠ ግልጽ በሆነ መልኩ በጥያቄው በእራሱ ላይ ጥያቄ ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡

“ኢትዮጵያ ወዴት ነው የምትሄደው?” ማለት እራሱ ምን ማለት ነው?

ለብዙ ሰዎች ይህ ጥያቄ ቀጥተኛ እና መልሱም ቀጥተኛ መስሎ ሊታያቸው እንደሚችል እርግጠኛ ነኝ፡፡ ይህ ጥያቄ ለእኔ አእምሮን የሚበጠብጥ ውስብስብ ጥያቄ እና ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው መልሶች ያሉት ሆኖ ነው የሚታየኝ፡፡

በዘመናዊ ቋንቋ አጠቃቀም ኮአ ቫዲስ የሚለው ሀረግ ሮም ውስጥ በኔሮ ኬሳር በመስቀል መከንቸሩን በመፍራት በተሰደደበት ጊዜ ለደቀመዝሙር መላዕክ ቅዱስ ጴጥሮስ ወዴት እየሄድክ ነው የሚል ጥያቄ ተጠይቆ ነበር፡፡ ጴጥሮስም በሮም መውጫ አካባቢ እየሱስን አገኘው እና “ወዴት እየሄድክ ነው ብሎ ጠየቀው?” እየሱስም እንዲህ በማለት መለሰለት፣ “እንደገና በመስቀል ለመከንቸር ወደ ሮም እየሄድኩ ነው“

በተሰጠው መልስ በመደነቅ ጴጥሮስ ወደ ሮም ተመልሶ በመሄድ ስራውን ለመቀጠል እና በመስቀል ተዘቅዝቆ ለመሰቀል ወሰነ፡፡

በአሁኑ ጊዜ ያንን በዓል ለምታከብሩት ሁሉ መልካም የፋሲካ በዓል ይሁንላችሁ፡፡

እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ አዲስ አበባ በነበርኩበት ጊዜ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ያንን የላቲን ሀረግ (ኩአ ቫዲስ የሚለውን) ያወቅሁትና የተጠቀምኩበት ፡፡

ከአራት አስርት ዓመታት በፊት በአንድ በታወቀ በየወሩ በሚታተም የእንግሊዝኛ መጽሔት (?) እ.ኤ.አ በ1968-69 አዲስ አበባ ውስጥ አሁን ስሙን በማላስታውሰው እና ያለው ትውስታየ ትክክል ከሆነ “በእኔ እኩያ ያሉት ወጣቶች የዘመኑን የኑሮ ሁኔታ ያልተከተለ የአኗኗር ዘይቤ” በሚል ርዕስ እኔ የማምንበትን የላቲን ሀረግ ያለው ጥያቄ በመጠቀም አንድ ጽሑፍ አውጥቸ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት የነበረውን አስቀያሚ ሁኔታ በመገንዘብ ወጣቶች ወዴት እየሄዱ ነው የሚል ጥያቄ ጠይቄ ነበር፡፡

ከግማሽ ምዕተ ዓመት አካባቢ በኋላ እንደገና እንዲህ የሚል ተመሳሳይ ጥያቄ አቀርባለሁ፣ “ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች ነው/Quo vadis, Ethiopia?“ እንዲህ የሚል ሌላ ጥያቄም ለመጨመር እወዳለሁ፣ “ኢትዮጵያ ወዴት ነው የማትሄደው?“

አንዳንድ ጊዜ ሕይወት እንግዳ እና አስቂኝ ነገር ሊሆን ይችላል፡፡

ከብዙ ዓመታት በፊት በወቅቱ ከነበሩት ለእኔ ጓደኞች ያቀረብኩትን ጥያቄ አሁንም በተመሳሳይ መልኩ ያንኑ ጥያቄ አሁን ላሉት ወጣቶች ማቅረብ ለእኔ እንግዳ እና አስቂኝ ነገር ነው፡፡

ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እድሜው ከ35 ዓመት በታች ነው ይባላል፡፡

ስለሆነም ጥያቄውን የበለጠ ግልጽ በማድረግ የመጀመሪያ ጥያቄ “የኢትዮጵያ ወጣቶች ወዴት እየሄዱ ነው?” በሚል መልኩ ተቃኝቶ መቅረብ አለበት፡፡

ደረቁን እውነታ በመግለጽ የእኔን የጉማሬ ትውልድ ለማግለል ሙከራ እያደረግሁ አይደለም፡፡

ወጣቶች ወዴት እንደሚሄዱ እየጠየቅሁ ባለሁበት ጊዜ ለአቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ እንዲህ የሚለውን አንድ የአፍሪካ ስለጉዞ ብልህ  ማስጠንቀቂያ አባባል  በማስመልከት የሰጠውን በማስጠንቀቂያነት ለማቅረብ እገደዳለሁ፣ “ወዴት እንደምትሄድ የማታውቅ ከሆነ ማንኛውም መንገድ ወደዚያው ይወስድሀል፡፡“

ስለሆነም የኢትዮጵያ ወጣቶች ወደመረጡት መድረሻቸው ለመጓዝ ከፈለጉ የሚመሩበት ዋና ዕቅድ (የመንገድ ጉዞ  ካርታ) ያስፈለጋቸዋል፡፡

ሌሎች ደግሞ እንዲህ ይላሉ፣ “ሁሉም መንገዶች ወደ ሮም ያመራሉ፡፡“

የሮም ግዛት እጅግ በጣም ሰፊ እና የፖለቲካ ስልጣኑ ከሮም በመውጣት ወደ ሌሎች ንጉሳዊ አገዛዞች ሁሉ የተሰራጨ ነበር፡፡

(እግረ መንገዴን እንዲህ የሚለውን የሙሶሊኒን ቅዠት ገልጨ ማለፍ እፈልጋለሁ፣ “ቤኒቶ ሙሶሊኒ አዲሱን የሮማን ግዛት ለመጀመር እ.ኤ.አ በ1935 ወደ ኢትዮጵያ የሚወስደውን መንገድ ፈልጎ አገኘ፣ እናም እንዲህ ብሎ በማወጅ ወራሪ ጦሩን ወደዚያው ላከ፣ “መጣሁ፣ አየሁ፣ እናም ድል አደረግሁ፡፡“ የእርሱ ቀደምቶች እ.ኤ.አ በ1896 ተመሳሳይ ድርጊትን በኢትዮጵያ ለመፈጸም ሙከራ አድርገው ነበር፡፡

ኢትዮጵያውያንን ለሮም ወራሪዎች የሰጡት መልስ  አንዲህ ነበር ፣ “መጡ፣ አዩ፣ ከዚያም አይቀጡ ቅጣት ቀምሰው ጭራቸው ተቆርጦ በፍጥነት ወደ ሮም ተባረሩ ፡፡)

ሆኖም ግን ለኢትዮጵያ ወጣቶች የሚቀርበው ጥያቄ እንዲህ የሚል ነው፣ “ሁሉም መንገዶች ወደ ኢትዮጵያ ይወስዳሉን?“

“ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች ነው?” የሚለው ጥያቄ “ዘ-ህወሀት ወዴት እየሄደ ነው?” ከሚለው አባባል ጋር ተፈጥሯዊ ቁርኝት አለው፡፡

የዘ-ህወሀት የሙስና ግዛት መስራች ጌቶች ሙሶሊኒ እንዳደረገው ሁሉ አንድ ዓይነት አመለካከት አላቸው፡፡ ከጫካው ውስጥ እመር ብለው በመውጣት እንዲህ በማለት አወጁ፣ “መጣን፣ አየን፣ እናም ድል አደረግን፡፡“

ኢትዮጵያውያን ለዘ-ህወሀት እንዲህ የሚል ተመሳሳይ መልዕክት ማስተላለፍ ይኖርባቸዋል፣ “መጣችሁ፣ እልቂትን ፈጸማችሁ፣ ዘረፋችሁ፡፡ አሁን የንሳችሁን አይቀጡ ቅጣት ቀምሳችሁ ተመልሳችሁ ወደ ጫካችሁ የለደዳቺሁት ዱር ትሄዳላችሁ፡፡“ (ዱርዬዎች አልኩ አንዴ?)

ወጣቶችን ተከተሉ፣

ኢትዮጵያ ወዴት እንደምትሄድ ፈልጎ ለማግኘት ወጣቶችን ተከተሉ እላለሁ፡፡

ስለሆነም ጥያቄው እንደገና ተሻሽሎ እንዲህ በማለት ቀርቧል፣ “የኢትዮጵያ ወጣቶች ኢትዮጵያን ፈልገው ለማግኘት እየተመለከቱ ነውን?“

አልበርት ኤንስታይን በአንድ ወቅት እንዲህ የሚል ምልከታ አድርገው ነበር፣ “አንድን ችግር ለመፍታት የአንድ ሰዓት ጊዜ የሚኖረኘ ከሆነ 55ቱን ደቂቃዎች በችግሩ ዙሪያ ላይ በማሰብ አጠፋዋለሁ፣ እናም አምስቷን ደቂቃ ደግሞ ለመፍትሄው አውላታለሁ፡፡“

ኤንስታይን ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ሀሳባዊነት ከእውቀት የበለጠ ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ እውቀት ለሁሉም ውሱን ከመሆኑ አንጻር በአሁኑ ጊዜ ሀሳባዊነት ዓለምን በሙሉ አቅፎ ይዟል፣ እናም ሁሉም ለማወቅ እና ለመገንዘብ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡“

ይህንን አባባል የበለጠ ግልጽ በማድረግ ጆርጅ በርናርድ ሻው እንዲህ ብለው ነበር፣ “ ነገሮችን ታያላችሁ እናም “ለምን” ትላላችሁ፡፡ እኔ ግን እንዲህ የሚሉትን እና ከዚህ በፊት ያልነበሩ ነገሮችን አልማለሁ፣ “    “ለምን አይሆንም?“ እላለሁ፡፡

እንግዲህ እኔ እየተናገርኩለት ያለው ስለዚያ ዓይነት ሀሳባዊነት ዓይነት ጉዳይ ነው፡፡

ሁሉንም የኢትዮጵያ ችግሮች ለመፍታት 20 ደቂቃዎችን ተሰጥቼ ነበር፡፡ ስለሆነም 17ቱን ደቂቃዎች ስለችግሮች ማሰቢያነት ከእናንተ ጋር እጠቀማለሁ ፡፡ ቀሪዎችን 3 ደቂቃዎች ስለመፍትሄዎች ጠቃሚነት የማውላቸው ይሆናል፡፡

የአፍሪካን አባባሎች፣ የኤንስታይንን የትኩረት ማሰብ እና የሀሳባዊ የፈጠራ እሳቤን መንታ ሀሳቦች እና ሁሉም መንገዶች ወደ ሮም ይወስዳሉ የሚሉትን አራቱን አባባሎች በአንድ ላይ በመቀመር አራት ድሮችን ማድራት እችላለሁ፡፡

ለጉባኤው ዋና አስተባባሪ ጥያቄ ሆኖ የሚቀርበው “ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች ነው?” የሚለው ነው፡፡

ይህ ጥያቄ በጣም ጠቃሚ ጥያቄ ነው ምክንያቱም በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አእምሮ ውስጥ ያለ ጉዳይ ነውና፡፡

ከጥያቄው ጋር ለተወሰነ ጊዜ ግብግብ/ልፊያ አድርጊያለሁ፡፡

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2011 በዋናው ካርታ ላይ ያለው የዴሞክራሲ ድልድይ በሚል ርዕስ ትችት ጽፌ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2012 ኢትዮጵያ፡ በሕገ መንግስታዊ የዴሞክራሲ ጎዳና ላይ በሚል ርዕስ ትችት ጽፌ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ጥር 2011 የአፍሪካ ወሮበላ ዘራፊ አምባገነኖች ከወደቁ በኋላ በሚል ርዕስ በሳምንታዊ አምድ ላይ ትችት ጽፌ ነበር፡፡

ከዚህም በላይ በዚህ ጥያቄ ላይ በርካታ ትችቶችን ያቀረብኩ ሲሆን አሁን በቅርቡ በዚህ ባሳለፍነው ታህሳስ ወር ውስጥ ደግሞ በኢትዮጵያ የዘህወሀት የፍጻሜ ታሪክ በሚል ርዕስ ትችት ጽፌ ነበር፡፡ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አእምሮ ለዚህ ጥያቄ ከፍት የሆነው ለምንድን ነው? ያንን ጥያቄ ለመጠየቅ በሺዎች የሚቆጠሩ በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡

ይህ ጥያቄ የተነሳበት ምክንያት የዘ-ህወሀት ውድቀት መጨረሻው ፍንትው ብሎ ሊታየን በመቻሉ ምክንያት ነውን?

ጥቂቶች ከኢትዮጵያ አድማስ ባሻገር ጥልቅ ጭቆና ያለ መሆኑን ስለሚያዩ እና ሌሎቹ ደግሞ ከዘ-ህወሀት አገዛዝ ዋሻ መጨረሻ የነጻነት ብርህን ፍንጣቂ እየታያቸው እና በኢትዮጵያ ውስጥ ነገሮች ሁሉ ፈጣን በሆነ መልኩ እየተለዋወጡ በመምጣታቸው ምክንያት ነው ሊሆን ይችላልን?

ለእኔ በጥያቄው ውስጥ ያሉት አራት ቃላት የተለያዩ ምላሾችን ይሰጡኛል፡፡

እነዚህን ቃላት በምሰማበት ጊዜ አንድ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ህልቆ መሳፍርት የሌላቸውን  እንዲህ የሚሉ ጥያቄዎችን እንዳነሳ ያደርጉኛል፡

1ኛ) ኢትዮጵያ ከዘ-ህወሀት ጋር ወዴት እየሄድሽ ነው? (ኢትዮጵያ ከዘ-ህወሀት ጋር ለመገላገል በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡)

2ኛ) ዘ-ህወሀት ከስልጣኑ ከተወገደ በኋላ ኢትዮጵያ ወዴት ታመሪያለሽ?

3ኛ) ኢትዮጵያ ዘ-ህወሀት ከስልጣኑ ከተወገደ በኋላ ስልጣኑን ተረክቦ የሚመራሽ ማን ነው?

4ኛ) ኢትዮጵያ ዘ-ህወሀት ከስልጣኑ ከተወገደ በኋላ ምንም ሳትታወቂ ድብቅ ሆነሽ ትቀጥያለሽን?

5ኛ) ኢትዮጵያ ላለፉት መቶ ዓመታት በጭቆና እና በፈላጭ ቆራጭነት አገዛዝ ስትገዢ እንደኖርሽው ሁሉ አሁንም ወደኋላ በመንሸራተት በዚያው ልትቀጥይ ትችያለሽን?

6ኛ) ኢትዮጵያ ላለፉት 25 ዓመታት ዘ-ህወሀት ሲገዛሽ በቆየበት መንገድ መገዛትሽን በመቀጠል አደገኛ ቅርቃር ውስጥ በመግባት ልትፈነጅ ትችያለሽን?

7ኛ) ኢትዮጵያ ወደ የእርስ በእርስ ጦርነት አዘቅት ውስጥ ልትዘፈቂ ትችያለሽን?

8ኛ) ኢትዮጵያ በመጨረሻው እልህ አስጨራሽ ትግልሽ ኔልሰን ማንዴላ እንዳሉት ወደ ነጻነት ወደሚያመራው ጉዞሽ ልትራመጅ ትችለሽን?

9ኛ) ኢትዮጵያ ወደ እውነት እና እርቀ ሰላም ጉዞ ልትራመጅ ትችያለሽን?

10ኛ) ኢትዮጵያ በእራስሽ ላይ ክልል እየተባለ ከሚጠራው የታጠረ የብረት (የበርት አልኩ አንዴ?) አጥር ሰብረሽ በመውጣት ከጎሳ ፖለቲካ፣ ከኃይማኖት ጽንፈኝነት እና ከወሮበላ የዘራፊ አገዛዝ እግረ ሙቅ ሰንሰለት በመፈታት ነጻ መሬት ሆነሽ ልትቀጥይ ትችያለሽን?

እነዚህን ጥያቄዎች ማንም ቢሆን ለመመለስ ወይም ደግሞ ለመመለስ ሙከራ ማድረግ እንደማይፈልግ አውቃለሁ፡፡

እኔ እራሴ በእርግጠኝነት እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ አልፈልግም፡፡

እነዚህ ጥያቄዎች በጣም አስቸጋሪዎች ናቸው፡፡ አስፈሪ ጥያቄዎቸ ናቸው፡፡ ውስብስብ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ አእምሮን የሚበጠብጡ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች አስቸጋሪ እና ምንም ዓይነት መፍትሄ ሊገኝላቸው የማይመስሉ የሚታዩ ናቸው፡፡ እጅግ በጣም ብሩህነት በሚታያቸው እና መልካም ሀሳብን በሚያስቡ ኢትዮጵያውያን ላይ ጨለምተኝነትን የሚያላብሱ ጥያቄዎች ናቸው፡፡

እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ እጅግ ልዩ የሆነ የፈጠራ ክህሎትን፣ ልዩ የሆነ ሀሳባዊነትን እና ልዩ የሆነ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል፡፡

ዘ-ህወሀት እነዚህን ጥያቄዎች እንዴት አድርጎ እንደሚመልስ አውቃለሁ፡፡

ዘ-ህወሀት ከእነርሱ መመሪያ አውጭነት እና አመራር ሰጭነት ውጭ ኢትዮጵያ እንደ ሶሪያ እና ሊቢያ ዓይነት በሆነ መንገድ ላይ ትጓዛለች እያሉ ይነግሩናል፡፡ (ይኸ የእነርሱ የደስታ ምኞት ነው፡፡ ለእነርሱ ቁማር መጫወቻነት ኢትዮጵያን ማግኘት የማይችሉ ከሆነ እስከመጨረሻው ትጥፋ ብለው ያስባሉ፡፡ (ከእኛ በኋላ የጥፋት ውኃ)፣ ወይም ደግሞ ኢትዮጵያውያን እንደሚሉት “አህያ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንዳለችው መሆኑ ነው፡፡ (አህዮች አላኩም ::)

አሁን በህይወት የሌለው እና የዘ-ህወሀት ጭንቅላት እየተባለ የሚጠራው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ እርሱ እንደሚመራት ካልሄደች እንደ ዩጎዝላቪያ ትበታተናለች እያለ ሟርት ያወራ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ለሰባት ሀገር ተበጣጥሳለች፡፡ አምባገነኑ መለስ ለኢትዮጵያ የነበረው ራዕይ ይኸ ነበር፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በአሁኑ ጊዜ የዘ-ህወሀት ራዕይ ይኸው ነው፡፡ እነርሱ ከሄዱ በኋላ ኢትዮጵያ በ 7 ወይም በ 9 መንገዶች ትግዋዛለች ይላሉ ፡፡

አምባገነኑ መለስ ለኢትዮጵያ ያሟረተው እጣ ፈንታ ለርሱ ደረሰው ፡፡ ኢትዮጵያ ግን በሕያው አለች ለዘላለመም ትኖራለች።

ዘ-ህወሀትም የመሪ ዉን እጣ  ፈንታ ካገኘ በህዋላ ኢትዮጵያ እንደዚሁ ትቀጥላለች፡፡

መንገዱ ከእነርሱ ውጭ እንደማይኖር በእብሪት ተወጥረው የሚናገሩት ሌላ ማንም ሳይሆን እራሳቸውን መላዕከት አድርገው የሰየሙት የዕኩይ ምግባር ስብስቦች ብቻ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ የክልል የበረት አጥር ከዘ-ህወሀት ፍጻሜ ጋር አብሮ እንደሚወገድ ምንም ዓይነት ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ አይደለም፡፡

በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የጥቂት ነጮች የበላይነት አገዛዝ ሲያከትም አፓርታይድም አብሮ አላከተመምን?

የጎሳ ፌዴራሊዝም (የጎሳ አፓርታይድ) ዘ-ህወሀት ተረግዞ የተወለደበት የማህጸን ውስጥ ፈሳሽ ነው፡፡

ክልላዊነት ዘ-ህወሀት በስልጣን ላይ ጠንካራ ሆኖ እንዲኖር የተወለደ ጉድ ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከአፓርታይድ ውጭ የጥቂት ነጮች የበላይነት አገዛዝ እና ባንቱስታንስ መኖር እንደማይችሉ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ከጎሳ ፌዴራሊዝም እና ክልላዊነት ውጭ በኢትዮጵያ ውስጥ ዘ-ህወሀት የሚባል ሰይጣን መኖር አይችልም፡፡

ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች ነው/Quo vadis የሚለውን ጥያቄ ጥልቅ ሀሳብን በተላበሰ መልኩ ለማሻሻል መርጫለሁ፡፡

በዚህም መሰረት ጥያቄው እንዲህ የሚል ይሆናል፣ “ዘ-ህወሀት ከተወገደ በኋላ ኢትዮጵያ ወዴት ትሄዳለች?“

ይኸ ጥያቄ ለእኔ አንድ በካንሰር በሽታ ተይዞ ሲሰቃይ የቆየ ሰው በድንገት ከካንሰር በሽታው ነጻ ቢሆን ምን ሊሆን ይችላል ከሚለው ጥያቄ ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡

ለምሳሌ እንበል እና ለበርካታ አስርት ዓመታት ፍትሀዊ ባልሆነ መልኩ ከሕግ አግባብ ውጭ በእስር ቤት ታስሮ የቆየ ሰው ነጻ ቢሆን ያ ሰው ምን ስሜት ሊሰማው ይችላል?

እንደዚሁም ሁሉ ለአስርት ዓመታት በባርነት ቀንበር ውስጥ ተይዞ አሳር መከራውን ሲያይ የቆየ አንድ ህዝብ አንድ ቦታ ላይ ነጻ ነህ ቢባል ምን ሊሰማው ይችላል?

እነዚህን ጥያቄዎች በሌሎች ጥያቄዎች መመለስ እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡

በደቡብ አፍሪካ የጥቂት ነጮች የበላይነት አፓርታይድ አገዛዝ ሲወድቅ እና እ.ኤ.አ በ1994 በብዙህን አገዛዝ ሲተካ አብዛኞቹ ደቡብ አፍሪካውያን ምን ዓይነት ስሜት ነበር የተሰማቸው?

ኔልሰን ማንዴላ እና በሺዎች የሚቆጠሩት ጸረ-አፓርታይድ መረዎች እና የፖለቲካ እስረኞች እ.ኤ.አ በ1991 ከእስር ቤት ሲለቀቁ አብዛኞቹ ደቡብ አፍሪካውያን ምን ዓይነት ስሜት ነበር የተሰማቸው?

በህይወታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ያለምንም ምርጫ ማጭበርበር በነጻነት እና ፍትሀዊ በሆነ ምርጫ፣ እንደዚሁም የጥቂት ነጮች የአፓርታይድ አገዛዝ ምርጫውን መቶ በመቶ ማሸነፉ ቀርቶ የእራሳቸውን መንግስት ለመምረጥ የምርጫ ካርዶቻቸውን በመጠቀም ለሰዓታት ሰልፍ በመያዝ ቆመው መቆየታቸውን ሲመለከቱ አብዛኞቹ ደቡብ አፍሪካውያን ምን ዓይነት ስሜት ነበር የተሰማቸው?

አንግዲህ አፍጣጭ ጥያቄው ዘ-ህወሀት ተጠራርጎ ወደታሪክ ቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ከተወረወረ በህዋላ ምን ይመጣል ነው ?

የዘ-ህወሀት አምባገነናዊ የጭቃ ግንብ ከተደረመሰ እና የዘ-ህወሀት የመስታወት የቅዠት የመስታወት ግንብ በህዝባዊ ማዕበል ከተሰባበረ ወይም እየተንፏቀቀ በሚሄድ ተቃውሞ እየተናጠ ከሄደ በኋላ ኢትዮጵያ ወዴት ትሄዳለች?

ኢትዮጵያ እንደ አስቀያሚው ጋላቢ ከወደቀች እና ከፉኛ ከተጎዳች በኋላ እንደገና በንጉሱ ፈረሶች እና በሁሉም የንጉሱ ሰዎች አማካይነት ተነስታ መጓዝ ትችላለችን?

ወይም ደግሞ ኢትዮጵያ ከወደቀችበት የዘ-ህወሀት አመድ ላይ በመነሳት ታርጋለች ?

ዘ-ህወሀት ባንድ እግሩ አየተንገዳገደ የስልጣኑን ጊዜ በብድር ገዝቶ ተቀምጧል፡፡ የዘ-ህወሀት  ጠቅላይ ሚኒስትር በቅርቡ ዘ-ህወሀት በህዝቦች ጀርባ ላይ ታዝሎ ሊቆይ አይችልም በማለት ተናግሯል፡፡ እንደ ኃይለማርያም አባባል ዘ-ህወሀት ቀኖቹ አልቀዋል፡፡

ዘ-ህወሀት ወደ ታሪክ ቆሻሻ ማጠራቀሚያነት እየተጓዘ ነው!

በአሁኑ ጊዜ ዘ-ህወሀት በኢትዮጵያ ውስጥ ወደየትም በማያስኬድ መንገድ ላይ እንደ ጅብራ ተገትሮ ይገኛል፡፡

ስለሆነም መመለስ ያለባቸው ሁለት ጥያቄዎች እነሆ፡

1ኛ) ዘ-ህወሀት ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫት እስከሚጣል ድረስ እያደረሰ ባለው ሰብአዊ እና የማቴሪል ጉዳት ኪሳራ ምን መደረግ ይኖርበታል?

2ኛ) ዘ-ህወሀት ተጠራርጎ ወደ ታሪክ ማጠራቀሚያ ቆሻሻ ውስጥ እስከሚጣል እና ዘ-ህወሀትን የሚተካ ታሪክ እስከሚተካ ድረስ ምን መደረግ ይኖርበታል?

መፍትሄለረዥሙ የነጻነት ጎዳና ዋና ዕቅድ፣

እንዲህ ወደሚለው የአፍሪካውያን አባባል እንደገና እመለሳለሁ፣ “የት እንደምትሄድ የማታውቅ ከሆነ ሁሉም መንገዶች ከቦታው ያደርሱሀል፡፡“

ዋናው ዕቅድ ላድሲቷ የኢትዮጵያ አዲስ ሕገመንግስት ማዘጋጀት ነው፡፡

የዘ-ህወሀትን ሕገ መንግስት አጥንቸዋለሁ፡፡ የዘ-ህወሀት ሕገ መንግስት ልክ ከተለያዩ ሀገሮች የሽብርተኝነት ሕጎች እየተቆረጠ እና እየተለጠፈ እንደተዘጋጀው የጸረ- ሽብር ሕግ እየተባለ እንደሚጠራው የሸፍጥ ሕግ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ባልተቃኘ መልኩ ከሌሎች ሀገሮች ሕገ መንግስቶች የተውሶ ቋንቋ እየተቆረጠ እና እየተቀጠለ የተደረተ ድሪቶ ነው፡፡ (የተኮረጀ ነው አልኩ?)

ከዘ-ህወሀት ሕገ መንግስት ለመሰብሰብ ያቻልኩትን ያህል በሁሉም በሚባል መልኩ ባየሁት ሁኔታ “ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች” የሚል እንጅ ኢትዮጵያ እየተባለች በምትጠራው ግዙፍ ምድር ላይ  ኢትዮጵያ የሚል አንድም ቃል አላገኘሁም፡፡

ምናልባትም እራሴን ማረም ይኖርብኛል ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ በዕርቅ ሰበብ በሰሜናዊው ክፍል ለአንድ ወራሪ ኃይል የተሰጠው መሬት ተቀንሶ እና እንዲሁም 700 እና ከዚያ በላይ ኪ/ሜ ርዝመት ያለው የሀገሪቱ ሉዓላዊ ግዛት ተቆርሶ በድብቅ ለሱዳን ተሰጥቶ ባለበት ሁኔታ ኢትዮጵያ የሚባል ግዙፍ ምድር በእራሱ ለመኖሩ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነውና፡፡

በዘ-ህወሀት ሕገ መንግስት መንደርደሪያ መግቢያው ላይ እንዲህ የሚል ጽሁፍ ተጽፎ ይገኛል፣ “እኛ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች…“

በሕገ መንግስቱ ውስጥ ብሄሮች እና ብሄረሰቦች እንጅ እንደ ሀገር ኢትዮጵያ የሚል ምንም ዓይነት ነገር የለም፡፡

ምን ለማለት እንደፈለግሁ ግልጽ ለማድረግ መንደርደሪያውን ወደ የዩናይትድ ስቴትስ ሕገመንግስት በመመለስ እንዲህ የሚለውን ይሰጠናል፡ “እኛ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ሕዝቦች…“ የሚለውን ይፋ ያደርጋል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ከሁሉም የዓለም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች የመጡ የስደተኞች ሀገር ብትሆንም እንኳ በዩናይትድ ስቴትስ አንድ ሕዝብ ብቻ (እኛ ሕዝቦች…) በማለት ነው በግልጽ የተቀመጠው፡፡

“እኛ ሕዝቦች…” የሚለው በሁለት ምዕተ ዓመታት ውስጥ ዕንከኖች የሉበትም ባይባልም ቅሉ ለዩናይትድ ስቴትስ ህልውና እና ብልጽግና ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡  (እንደ ዶናልድ ትሩምፓውያን በጥላቻ የተሞላ ፉዞ ቢኖሩበትም አላልኩም፡፡)

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ለሚዘጋጀው አዲስ ሕገ መንግስት የመንደርደሪያው ክፍል/Preamble እኛ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ …“ በማለት እንደሚጀምር አምናለሁ፡፡

ሁለተኛ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አዲስ ሕገ መንግስት ከሚከተሉት አስተሳሰቦች ላይ ሊመሰረት ይገባል፡ “በሕገ መንግስቱ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ መንግስት ያልተሰጡ ወይም ደግሞ ለአካባቢ ግዛቶች ያልተከለከሉ ስልጣኖች እንደየአግባባቸው ለመንግስታት እና ለሕዝቡ የተተው ናቸው፡፡“  በሌላ አገላለጽ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አዲሱ ሕገ መንግስት ብሄራዊው ሕገ መንግስት ስልጣን ሲሰጠው ብቻ ነው ተፈጻሚነት የሚኖረው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ከ10ኛው ማሻሻያ ያሜሪካ ህገ መንግስት ጀምሮ ለረዥም ጊዜ እስከቆየው ጽናት የተሞላው ሕገ መንግስት ድረስ ተመሳሳይ ቋንቋዎችን በጥቅም ላይ ሲውል ተመልክታችኋል፡፡

ሶስተኛ እና ቀጥተኘ በሆነ መልኩ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አዲስ ሕገ መንግስት እንዲህ የሚለውን የጋናን ሕገ መንግስት አንቀጽ 55 (4) ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ አለበት፣ “ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ ብሄራዊ ባህሪ ያለው መሆን አለበት፣ እናም አባልነት በጎሳ፣ በኃይማኖት፣ በክልላዊነት ወይም ደግሞ በሌሎች ከፋፋይ ነገሮች ላይ ተመስርቶ መከናወናን የለበትም፡፡“

እነዚህ ሶስት ሕገ መንግስታዊ ዓላማዎች እውን የሚሆኑ ከሆነ የሚቀረው ነገር የማንዴላ ረዥሙ ጉዞ ለነጻነት የሚለው ነው፡፡

በማንዴላ መንገድ የሚደረገውን የነጻነት ግልቢያ እናስብ፡፡

የማንዴላ መንገድ ምንድን ነው?

የማንዴላ መንገድ ከአእምሮ እስረኝነት እና ከዘር፣ ከጎሳ እና ኃይማኖት የጽንፈኝነት ጥላቻ ነጻ ማውጣት ነው፡፡

ማንዴላ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ለመውጣት ወደ ዋናው የእስር ቤት በር እየተጠጋሁ በሄድኩ ጊዜ ያ ወደ ሙሉ ነጻነት እንደሚወስደኝ የማውቅ ሲሆን ያንን አስከፊውን ጥላቻ እዚያው እስር ቤቱ ውስጥ ጥየው ካልወጣሁ አሁንም ቢሆን እዚያው እስር ቤቱ ውስጥ እንዳለሁ እቆጥረዋለሁ፡፡”

ያድሲቷ የኢትዮጵያ አዲሱ ሕገ መንግስት ዕቅድ ሁሉንም ኢትዮጵያውን ከረዥም ጊዜ የአእምሮ እስረኝነት፣ ከጎሳ ጥላቻ እና በመልክዓ ምድራዊ ወሰን ታጥረው ከተቀመጡት እና ክልል እየተባሉ ከሚጠሩት የማጎሪያ በረቶች በማውጣት እውነት እና ብሄራዊ ዕርቀ ሰላም ወደሰፈነባት አዲሲቷ ኢትዮጵያ እንደሚወስድ አምናለሁ፡፡

የማንዴላ የእውነት እና የዕርቅ መንገድ፣

በርካታ ሀገሮች ሩዋንዳን፣ አርጀንቲናን፣ ሴራሊዮንን፣ ሲሪላንካን፣ ኬንያን፣ ጋናን እና ሌሎችን ጨምሮ የእውነት እና የዕርቅ ሂደትን አከናውነዋል፡፡

ለእውነት እና ዕርቅ ተግባራዊነት በርካታ አቀራረቦች አሉ፡፡ መሰረታዊ ዓላማው ሀገሪቱ በአንድ በተወሰነ ጊዜ የሰብአዊ መብቶችን አጠባበቅ በመርገጥ ደርሶባት ከነበረው የፖለቲካ እና ማህበራዊ ምስቅልቅል ሁኔታ ቁስሉ እንዲሽር ለማድረግ ነው፡፡ መሰረታዊ ዓላማው በቀልን እና “ዓይን ላጠፋ ዓይን” በሚል የእብሪት አካሄድ በመነሳሳት ሌላ አዲስ ሀገር መገንባት እንደማይቻል ለማሳየት ነው፡፡ ይህንን መርህ በመጣስ የሚካሄድ ነገር ሁሉ ወደ ጨለማ ሀገር ህዝቦች የሚወስድ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የህጻናት መብት ድፍጠጣ ምስል የሚታይባት ሀገር ናት፡፡ ስለሆነም የድህረ ዘ-ህወሀት መወገድን ተከትሎ ኢትዮጵያ የእውነት እርቅ ሂደት እንዲከናወን ማድረግ ዋናው አስፈላጊ ነገር ነው፡፡

የተሳካ ብሄራዊ የእውነት እና የዕርቅ ሂደት መካሄድ ለእውነተኛ የብዙሀን ፓርቲ ዴሞክራሲ መንገድ ይከፍታል፡፡

ስለብዙሀን ፓርቲ ዴሞክራሲ በመናገር ላያ ያለሁት የሕግ ልዕልና የበላይነትን፣ የሰብአዊ መብት አጠባበቅን፣ መልካም አስተዳደርን፣ ተጠያቂነትን እና ግልጽኝነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ነው፡፡

የብዙህን ፓርቲ ዴሞክራሲ ስል ጎሰኝነትን፣ ኃይማኖትን፣ ቋንቋን፣ ክልልን፣ ወዘተ መሰረት ባደረገ መልኩ ማለቴ አይደለም፡፡

መልካም አስተዳደር ሀሳቦቻቸውን በመግለጽ እና በፖለቲካ ሂደቱ ላይ በችሎታቸው ለመወዳደር በሚችሉት ግለሰቦች እና ቡድኖች ችሎታ ላይ መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ጠንካራ የብዙህን የፖለቲካ ፓርቲ ስርዓት ዜጎች በጉዳዮች ላይ እንዲሰባሰቡ እና ሀሳቦችን፣ ፖሊሲዎችን እና ፕሮግራሞችን ለመልካም አስተዳደር ማስተባበር እንዲችሉ ለማድረግ ነው፡፡ ጠንካራ የብዙሀን የፖለቲካ ፓርቲ ስርዓት ተመሳሳይነት ያላቸውን አስተያየቶች እና ሀሳቦችን በሚካፈሉ ሰዎች መካከል መተባበር እንዲችሉ እና በመንግስት ላይ ጫና ማድረግ እንዲችሉ ያረጋግጣል፡፡ በውድድር ላይ የተመሰረተ የነጻ የብዙሀን ፓርቲ ስርዓት ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት፣ የሲቪክ ማህበራት ቅሬታዎቻቸውን በግልጽ ለመግለጽ እና በገንቢ የፖሊሲ ክርክሮች እና በሰላማዊ መንገድ ለውጥ እንዲኖር ያስችላሉ፡፡ የብዙሀን መብለ ፓርቲ ስርዓት መኖር ከማህበረሰቡ ውስጥ የተገለሉ ቡድኖች በተለይም ወጣቶች እና ሴቶች እንዲካተቱ ያደርጋል፡፡

ስለሆነም ጥያቄውን አንድ ጊዜ እንደገና እንዲህ በማለት አነሳዋለሁ፣ ”ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች ነው?“

ኢትዮጵያ ከዘ-ህወሀት ክልላዊነት የአፈና አገዛዝ በመውጣት የሕግ የበላይነት ወደተረጋገጠበት እና ሰብአዊ መብቶች ወደሚጠበቁበት ሕገ መንግስት እየገባች ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከማስመሰል እና ተፈጥሯዊ ካልሆነው ክልላዊ አገዛዝ እየወጣች ወደ አንድ ብሄራዊት ኢትዮጵያ መኖሪያነት እየገባች ነው፡፡

እንዲህ የሚለውን የአፍሪካውያንን አባባል እስቲ አንድ ጊዜ ልድገመው፣ “ወዴት እንደምትሄድ የማታውቅ ከሆነ ሁሉም መንገዶች ወደዚያው ይወስዱሀል፡፡“

አሁን ግን ወዴት ለመሄድ እንደምንፈልግ እና የትኛው መንገድም ወደዚያ እንደሚያደርሰን በሚገባ እናውቃለን፡፡

የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ በሁሉም ኢትዮጵያውያን እጆች እና እግሮች ውስጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ለማንሳት ወይም ደግሞ ወደ ታች በመወርወር እንደብርጭቆ አንኮታኩቶ የመስበር ኃይል አላቸው፡፡ ወደ ነጻነት በሚወስደው ረዥሙ መንገድ አብረዋት መጓዝ ወይም ደግሞ ዘ-ህወሀት በገነባው በሚገፋ ተሸከርካሪ ወንበር ላይ ኢትዮጵያን ማስቀመጥ ይችላሉ፡፡

ኢትዮጵያ ወዴት እንደምትሄድ ሌላ የማንም ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ነው፡፡

እንደገና አንድ ጊዜ ወደ ኤንስታይን እና ሻው ልመለስ፡፡

ኤንስታይን እንዲህ ብለው ነበር፣ “ሀሳባዊነት ከእውቀት የበለጠ ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ እውቀት ለሁሉም ውሱን በመሆኑ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ የምናውቀው እና የምንገነዘበው ጥቂት ነገሮችን ብቻ ሲሆን ሀሳባዊነት ግን ሁሉንም ዓለም ያካትታል፣ እናም ምንጊዜም ቢሆን ማወቅ እና መገንዘብ ይኖራል፡፡“

ኤንስታይን ማለት የፈለጉት የሰው ልጆች ዕጣ ፈንታ በምናውቀው ብቻ የሚወሰን አይደለም ሆኖም ግን ከዚህም ባለፈ መልኩ ጥልቅ በሆነ መንገድ በምናስበውም ጭምር ነው፡፡

እንዲህ የሚለውን እጅግ በጣም አስደናቂ የሆነውን ሀሳባዊ ጥያቄ የጠየቁት ኤንስታይን ነበሩ፣ “አንዲትን የጨረር ፍንጣቂ በህዋ ላይ መጋለብ ብችልስ?”

በኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ የበላይነትን መሰረት ያደረገ እውነተኛ የመድብለ/ብዙሀን ፓርቲ ዴሞክራሲ ስርዓትን ለመመስረት ብናስብስ ?”

በኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣንን በብሄራዊ እና በአካባቢ ግዛቶች መካከል መሰረት ያደረገ የፌዴራል መንግስት ስርዓት ለመመስረት ብናስብስ ?

ጎሳን፣ ኃይማኖትን፣ ክልልን፣ ቋንቋን፣ ወዘተ መሰረት ባላደረገ መልኩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማቋቋም ብናስብስ ?

የኢትዮጵያ ህዝብ ሰውነት ከዘ-ህወሀት ካንሰር ነጻ እንዲሆን ብናስብስ ?

የእኔ ሀሳብ በነጻ እና በጉጉት እንዲንሸራሽር እፈልጋለሁ፡፡ እንደ ሻው ሁሉ እንዲህ የሚል ጥያቄ አቀርባለሁ፣ “ነገሮችን ታያለህ፣ እናም እንዲህ ትላለህ፣ ለምን? ሆኖም ግን ቀደም ሲል ሆነው የማያውቁ ነገሮችን አልማለሁ፣ እናም ለምን አይሆንም?“ እላለሁ፡፡

ጥቂቶች በብርሀን ፍንጣቂ ለመጋለብ ሲያስቡና ሲመኙ እኛ ለምን ረዥሙን የነጻነት መንገድ ጉዞ መጀመር ማሰብ ይሳነናል?

በመጨረሻም ኢትዮጵያ ወዴት እንደምትሄድ የተነሳው ጥያቄ በኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች እና ወንዶች አቦ ሸማኔ ትውልድ መሪነት በጉማሬው ትውልድ ድጋፍ ሰጭነት ተገቢውን ምላሽ ያገኛል፡፡ ለእኛ ነጻነት ሲሉ በኢትዮጵያ ውስጥ በማጎሪያው እስር ቤት ውስጥ ታጉረው በግፈኛው ስርዓት እየተሰቃዩ መስዋዕትነት እየከፈሉ ባሉ የፖለቲካ እስረኞች ተገቢውን ምላሽ ያገኛል፡፡

ሁሉም መንገዶች ወደ አዲሲቷ ኢትየጵያ ያመራሉ!!!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!  

መጋቢት 20 ቀን 2008 .

 

Similar Posts