የአስመሳይ ባራክ ኦባማ ጉዞ በኩባ!

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም    

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

የአስመሳይነት የምስክር ወረቀት

ይህ የምስክር ወረቀት በስም ባራክ ሁሴን ኦባማ ለተባለ በአስመሳይነት በዓለም የመጀመሪያውን ደረጃ ለያዘ እና ለተናገረው አንድ ነገር ሌላ ተቃራኒውን ነገር ለሚተገብር አስመሳይ ሰው ምስክር ይሆን ይሆነው ዘንድ በማስረጃነት ተሰጥቷል፡፡

              እ.ኤ.አ መጋቢት 21/2016 በሃቫና ኩባ ተሰጠ

Obama Certificate20ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ኩባ እየጎበኘ ነው! ጉብኝቱ ተልዕኮ አለው፡፡ ኩባውያን ከኮሙኒስት የአእምሮ ባርነት ነጻ ይውጡ!

እል ል ል ል ! ኩባ ነጻ ወጣች!

እ.ኤ.አ ወደኋላ ወደ 1898 መለስ ብለን ስንመለከት ቴዲ ሩዝቬልት በህዋላ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሆኑትና ክጥል ስማቸው በመባል “ያልተገሩ ፈረሶች ጋላቢ”  እና ባልደርባዎቻቸው  ኩባውያንን ከስፓኝ አገዛዝ ነጻ የማውጣት ተልዕኮ በመያዝ ታምፓ ፍሎሪዳ ከምትባል የባህር ወደብ በጀልባ ተሳፈሩ፡፡

ያ አስደማሚ የነበረው የእስፓኝ-አሜሪካ ትንሹ ጦርነት ከሁለት ወራት በኋላ አካባቢ ተጠናቀቀ፡፡ የእስፓኝ ግዛትም ወደቀ፣ እናም አሜሪካ የእስፓኝ ይዞታ የነበሩትን በርካታ ትናንሽ ደሴቶችን  በሙሉ ነጠቀች፡፡

አዬ! እነዚያን የደሴት ግዛቶች የማስተዳደር ዕጣ ፈንታ ሸክም በአሜሪካ እጅ ወደቀ፡፡

ሆኖም ግን ኩባ በዚያ ትንሽ ጦርነት ማጠናቀቂያ ላይ ነጻ አልወጣችም፡፡ ለስ፣ኡ ግን ነፃ ነች ተባለ፡፡

እ.ኤ.አ በ1928 ፕሬዚዳንት ካልቪን ኩሊጅ በፓን አሜሪካ ጉባኤ ላይ በመገኘት እና እንደዚህ የሚለውን ንግግር ለማድረግ ወደ ኩባ ሄዱ፡ “በአሁኑ ጊዜ ኩባ የእራሷን ሉዓላዊነት ያረጋገጠች ሀገር ናት፡፡ ህዝቦቿ በማንም ዘንድ ጥገኛ ያልሆኑ፣ ነጻ፣ የበለጸጉ፣ ሰላማዊ እና እራስን በእራስ የሚያስተድድር መንግስትን በማጣጣም ላይ ናቸው፡፡“

ዩናይትድ ስቴትስ ለኩባ ነጻነቷን ሰጠች፡፡ ሆኖም ግን ኩባ ነጻነቷን ለማግኘት በምትኩ አሜሪካ በኩባ አስተዳደር ጣልቃ ገብነት ካስፈለገ እንዲኖራትና ደግሞም ለአሜሪካ ጉዳዮች ማስፈጸሚያ ያገለግል ዘንድ በጓንታናሞ ባህረ ሰላጤ (እ.ኤ.አ ከጥር 2001 ጀምሮ ከሕግ አግባብ ውጭ 800 እስረኞች ታስረውበት የሚገኘው እና ኦባማ እዘጋዋለሁ የሚል ቃል ገብቶለት የነበረው የእስር ቤት ካምፕ) ተከታታይነት ባለው ኪራይ ለአሜሪካ ባህር ኃይል እንድትሰጥ  የሚል ስምምነት ማድረግ ነበረባት፡፡

ያ ስምምነት እ.ኤ.አ በ1950ዎች መጀመሪያ አካባቢ ፊደል ካስትሮ እና ቡድናቸው ኩባን ከተደራጀ የአሜሪካ ወንጀል እና የኩባን ኢኮኖሚ ጠቅልለው ለመያዝ ከተደራጁ የአሜሪካ ኩባንያዎች ነጻ ለማውጣት የትጥቅ ትግል እስከ ጀመሩበት ጊዜ የቆዬ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ጥር 1959 ካስትሮ እና ቡድናቸው ድልን ተጎናጸፉ፡፡ ፊዴል ካስትሮ እንዲህ በማለት አወጀ፣ “እኔ አምባገነን አይደለሁም፣ ወደፊትም ለመሆን አላስብም፡፡ በጦር መሳሪያ ኃይል በመታገዝ ስልጣንን አልይዝም፡፡“

የካስትሮ ወንድሞች ፊደል፣ ራውል እና ራሞን (በቅርብ ጊዜ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየ) የጦር መሳሪያን በመጠቀም ጣታቸውን በጠመንጃ ምላጭ ላይ አርገው የኩባን ሕዝብ ለ56 ዓመታት እንደ ሰም አቅልጠው፣ እንደ ብረት ቀጥቅጠው በመግዛት ላይ ይገኛሉ፡፡

ዩኤስ አሜሪካ በኩባ ላይ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል የምጣኔ ሀብት ማዕቀብ ጥላ ቆይታለች፡፡

ባራክ ኦባማ በአሁኑ ጊዜ አሜሪካ ኩባን ከቀዝቃዛው (ከቀዝቃዛው ጦርነት አላልኩም) የዴፕሎማሲ እና የምጣኔ ሀብት ግንኙነት ለማውጣት ኩባ ውስጥ ይገኛል፡፡

ባራክ ኦባማ እ.ኤ.አ በ2016 የኩባን ግዛት ነጻ ለማውጣት አይደለም ኩባ ውስጥ የሚገኘው፣ ሆኖም ግን ኦባማ ኩባ ውስጥ የሚገኘው ኩባውያንን ከጨቋኝ አምባገነኖች እና ከሰብአዊ መብት ጭቆናዎች እና የድህነት እጦቶች ነጻ ለማውጣት ነው፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በመጋቢት ወር ሶስተኛው ሳምንት ላይ ኦባማ ካስትሮ በሰብአዊ መብት ላይ የሚያደርሰውን የመብት ረገጣ ለማስቆም ወደ ኩባ እንደሚሄድ ይፋ አድርጓል፡፡

ዩኤስ አሜሪካ የካስትሮን ወንድሞች ለማንበርከክ ለ50 ዓመታት ያህል ጥረት ስታደርግ የቆየች ቢሆንም የካስትሮ ወንድሞች ግን አይበገሬ ሆነው ቆይተውባቸዋል (ቀልድ ለመቀለድ አይደለም)፡፡

ኦባማ እንዲህ ብሏል፣ “እስከ አሁንም ድረስ ከኩባ መንግስት ጋር ልዩነቶች አሉን በማለት ጉዳዩን በቀጥታ አነሳዋለሁ፡፡ አሜሪካ በዓለም ላይ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ ሁልጊዜ በጽናት ትቆማለች፡፡“

ደህና! ደህና! እውን አሜሪካ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ ሁልጊዜ በጽናት ትቆማለች?

ባራክ ኦባማ እ.ኤ.አ ሀምሌ 2015 ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ እንዲህ ብሎ ነበር፣ እንደዚህ ያሉ ጉዳዮች በሚመጡበት ጊዜ ምላሴን አላጥፍም፡፡ መንግስትን በኃይል ለማስወገድ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን የኢትዮጵያን መንግስትም ጨምሮ ዓላማ ያደረገን ማንኛውንም ቡድን እንቃወማለን፡፡ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

ኦባማ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን እያለ የሚጠራው ሌላ ማንንም ሳይሆን በአሁኑ ጊዜ በአሸባሪነት የተፈረጀውን እና በዓለም አቀፍ የአሸባሪዎች መረጃ ቋት ስም ዝርዝር ውስጥ ስሙ ሰፍሮ የሚገኘውን የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን (ህወሀትን) ነው፡፡

ዘ-ህወሀት እ.ኤ.አ ግንቦት 2015 ተካሄደ የተባለውን የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ ለይስሙላው ፓርላሜንት ያሉትን መቀመጫዎች መቶ በመቶ አሸነፈ፡፡

እንደ ፍሪደም ሀውስ ዘገባ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በአስከፊ ሁኔታ በማሰር ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እንዳቀረበው ዘገባ ከሆነ “የኢትዮጵያ ባለስልጣኖች ሀሳብን በነጻ የመግለጽን፣ በነጻ የመደራጀትን እና በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብ መብቶችን በከፋ መልኩ በመገደብ እና ጨቋኝ የሆኑ ሕጎቹን በማውጣት የሲቪል ማህበረሰቡን እና ነጻውን ሜዲያ እንዲሁም ግለሰቦችን የፖለቲካ ዒላማ በማድረግ ወደይስሙላው የሕግ አካል በማቅረብ ጥቃቱን ቀጥሎበት ይገኛል፡፡“

ኦባማ ዘ-ህወሀትን ዴሞክራት ነው ቢለውም እውነታዎቹ ይህንን ቅጥፈት ዋጋ በማሳጣት ከጉዳይ አይቆጥሩትም፡፡

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2009 ወደ ጋና አክራ በመሄድ እንዲህ ብሎ ነበር፣ “በአሁኑ ጊዜ እንዳትሳሳቱ፡፡ ታሪክ ከእነዚህ ጀግኖች አፍሪካውያን ጎን ነው የተሰለፈው እንጅ መፈንቅለ መንግስት በማካሄድ ወይም ደግሞ ሕገ መንግስትን በማሻሻል ስልጣንን ከሚወስዱ ጎን አይደለም፡፡ አፍሪካ ጠንካራ ሰዎችን አትፈልግም፡፡ አፍሪካ የምትፈልገው ጠንካራ ተቋማትን ነው፡፡“

እ.ኤ.አ በ2014 የአፍሪካን ወሮባላ ዘራፊ አምባገነኖች ወደ ኋይት ሀውስ በመጋበዝ የቸበርቻቻ ሰርግ እና ምላሽ በማድረግ ከአምባገነኖቹ ጋር አብሮ እና ከእያንዳንዳቸው ጋር በግል ለብቻ ፎቶግራፎችን ተነስቷል፡፡

በኋይት ሀውስ በተደረገው የራት ግብዣ ላይ የተገኙ ተጋባዥ እንግዶች፣

1ኛ) በሰው ልጆች ላይ በፈጸመው የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት በበርካታ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶበት የነበረው የኬንያው ኡሁሩ ኬንያታ፣

2ኛ) ለአስርት ዓመታት ያህል የሰብአዊ መብቶችን በመደፍጠጥ መጥፎ ታሪክ ያለው የካሜሮኑ ፓውል ቢያ፣

3ኛ) እ.ኤ.አ ጥቅምት 2014 በሕዝባዊ ተቃውሞ ተገድዶ ስልጣኑን ከመልቀቁ በፊት በህዝቦች ላይ የተንሰራፋ የሰብአዊ መብት ረገጣ ፈጽሞ የነበረው የቡርኪና ፋሶው ብሌይስ ኮምፓዎሬ፣

4ኛ) በምስራቃዊ ኮንጎ አመጺያን ላይ መጠነ ሰፊ አጥቂ ሰራዊት በማሰማራት በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች የሞት ሰለባ እንዲሆኑ ያደረገው የሩዋንዳው ፖል ካጋሜ፣

5ኛ) በበርካታ ህዝቦች ላይ የረዥም ጊዜ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ መጥፎ ታሪክ ያለው እና ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለመጨረሻ ጊዜ የተካሄደውን የሕዝብ ምርጫ በመዝረፍ የሚታወቀው የኡጋንዳው ዮሪ ሙሴቬኒ፣

6ኛ) ለበርካታ አስርት ዓመታት 95 በመቶ የምርጫ ውጤት በማምጣት ድልን ተቀዳጀሁ እያለ የሕዝብን ድምጽ በመዝረፍ የቆየው የኢኳቶሪያል ጊኒው ቶዶር ኦቢያንግ ኔማሶጎ፣

7ኛ) የእራሱን መንግስት እንደ ቤተሰብ ንግድ በመቁጠር (እንደ ወንጀለኛ የንግድ ኩባንያ አድርጎ) ሲመራ የቆየው የአንጎላው ጆሴ ኤዱዋርዶ ዶስ አንቶስ፣

8ኛ) የፕሬዚዳንትነት ስልጣኑን ገና በ30 ዓመቱ ከአባቱ በመውረስ የሙስና ግዛትን ሲያስፋፋ የቆየው የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፐብሊኩ ጆሴፍ ካቢላ፣

9ኛ)  የይስሙላው ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነው እና እርባናቢስ የመቀለጃ ስብዕናን የተላበሰው የኢትዮጵያው ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ሌሎችም ናቸው…

በኦባማ የተዛነፈ ምልከታ ምክንያት የአፍሪካ ጠንካራ ሰዎች ከምንጊዜውም በላይ ጠንካራ ሆነው ወጥተዋል፡፡

የአፍሪካ ጠንካራ ሰዎች የበለጠ ጠንካራ በመሆን እና ያለምንም ሀፍረት ዓይናቸውን በጨው ታጥበው በድፍረት እና በኩራት ምርጫን መቶ በመቶ አሸንፊያለሁ (ኢትዮጵያ)፣ የእድሜ ልክ ፕሬዚዳንት ሆኛለሁ በሩዋንዳ፣ በኡጋንዳ ወይም ደግሞ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ ፓርቲ የእድሜ ልክ ገዥ ሆኖ ለመቀጠል እያደረጉት ያለው ሁኔታ የድርጊቱን ምንነት በይፋ ያመላክታል፡፡

እ.ኤ.አ በ2013 የባራክ ኦባማን የሰብአዊ መብት ዴፕሎማሲ በአስመሳይነት ለመግለጽ የአስመሳይነት ዴፕሎማሲ የሚል ሀረግን ተጠቅሚያለሁ፡፡

በዚያን ጊዜ እ.ኤ.አ በ2013 የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መምሪያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብት ዘገባን በማስመልከት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በጆን ኬሪ ላይ የነበረኝን ተቃውሞ አሰምቸ ነበር፡፡

ኬሪ እንዲህ የሚል ንግግር አደረጉ፣ “የሰብአዊ መብቶች ለአደጋ በተጋለጡበት በየትኛውም ቦታ ዩናይትድ ስቴትስ በኩራት፣ ያለማወላወል በጽናት በመቆም ለነጻነት፣ የበለጠ ለግልጸኝነት እና ለሁሉም ህዝቦች ዕድሎች ተጠቃሚነት ትግሏን አጠናክራ ትቀጥላለች፡፡“

ኦባማም እ.ኤ.አ በ2016 ተመሳሳይ እንደምታ ያለው ንግግር አድርጓል፡፡ ካስትሮ የሰብአዊ መብቶችን የማክበር ግዴታ እንዳለበት እና አሜሪካ ሁልጊዜ ለሰብአዊ መብቶች መከበር በጽነት እንደምትቆም ተናግሯል፡፡

የኦባማን የሰብአዊ መብት አያያዝ ፖሊሲ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መልኩ በአሁኑ ጊዜ በዝርዝር ነቅሸ ለማውጣት አልችልም፡፡

ሆኖም ግን በቅርቡ እየታየ ባለው ጨዋታ ኦባማ አስመሳይ እንደሆነ ዝርዝር አድርጌ መናገር እችላለሁ፡፡ ነገር ግን እርሱ እንደሚለው ዓይነት አስመሳይነት አይደለም እኔ እየተናገርኩ ያለሁት፡፡

“እውነተኛ አስመሳይ እያታለለ መሆኑ እንዳይታወቅበት በታማኝነት መዋሸቱን እንዲቀጥል” የሚያደርግበት ሁኔታ አለ፡፡

ከዚያም ከውሸታም የከፋ አስመሳይ ይሆናል፣ ምክንያቱም እርሱ ቀጣፊ ውሸታም ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ አስመሳይ ነው፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንቶችን ትሩፋት በተለይም በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ያለውን ነገር እገነዘባለሁ፡፡

ሪቻርድ ኒክሰን ቻይናን ከፈቱ፡፡

ጌራልድ ፎርድ በቬትናም ያለውን ጦርነት አቆሙ፡፡

ሮናልድ ሬጋን የቀዝቃዛውን ጦርነት አሸነፉ፡፡

ጆርጅ ቡሽ አሜሪካንን በኢራቅ የጦርነት አዘቅት ውስጥ ለመዝፈቅ በህዝቡ ላይ የማታለያ መንገዶችን ተጠቀሙ፡፡

ባራክ ኦባማ ከኢራን ጋር ያውን የኒኩሌር ስምምነት ፈጸመ፣ እንደዚሁም የአየር ንብረት ለውጥን ስምምነት ከትራንስ ፓሲፊክ ትብብር (ከ12 የፓሲፊክ ሀገሮች ጋር የተደረገ የንግድ ስምምነት) ጋር አከናወነ፡፡ ለአሜሪካ ዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥሩትን ስምምነቶች ማለቴ አይደለም፡፡ እኔ እያልኩ ያለሁት ከበርኔ ሳንደርስ ጋር ስላለው ሁኔታ ነው፡፡

በርኔ እንዲህ በማለት ካስቀመጡት ጋር እኔም እስማማለሁ፣ “የትራንስ ፓሲፊክ አስከፊ የንግድ ስምምነት አጋርነት የሰራተኞችን፣ የደንበኞችን፣ የአካባቢን እና የአሜሪካ ዴሞክራሲ የተመሰረተባቸውን እሴቶች ከጉዳት ላይ በመጣል የታላላቆቹን ዘርፈ ብዙ ብሄራዊ ኮርፖሩሽኖች ጥቅም ለማስከበር የተደረገ ስምምነት ነው፡፡“

ኦባማ በአሜሪካ ህይወቶች እና ገንዘብ ላይ ተደጋጋሚ የሆነ ስጋትን ፈጥሮ የሚኖር የሚመስለውን በኢራን እና በአፍጋኒስታን መካከል ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት በማስቆሙ አክብሮት እሰጠዋለሁ፡፡

አቅምን ላገናዘበው የኦባማ የጤና ክብካቤ ድንጋጌ እና እ.ኤ.አ ከ2008 ቀውስ በኋላ ኢኮኖሚው በሁለት እግሮቹ እንዲቆም በማድረጉ ለኦባማ አክብሮት እሰጠዋለሁ፡፡

በፕሬዚዳንታዊ ዘመኑ መጨረሻ አካባቢ ኩባን ከቅቃዜዋ ለማውጣት እያደረገ ያለው ስራ መልካም ነገር ነው፡፡

ስለዩኤስ-ኩባ አዲስ ግንኙነት የማልስማማባቸው ጥቂት አስተያየቶች ነበሩኝ፣ ሌላ የምለው ምንም ነገር የለምኝ፡፡

ሆኖም ግን ኦባማ በመላው ዓለም በተለይም በአፍሪካ ውስጥ ላለው የሰብአዊ መብት መሻሻል ጉዳይ ምንም ዓይነት አክብሮት አልሰጠውም፡፡

ኦባማ ስለሰብአዊ መብት ለመነጋገር ወደ ኩባ እሄዳለሁ ብሏል፡፡ ሰብአዊ መብት 56 ዓመታትን ያህል በኩባ ላይ ማዕቀብ ለመጣሉ ዋናው ምክንያት ነውን?

የካስትሮ ወንድሞች በእነዚህ 56 ዓመታት ሁሉ ስለሰብአዊ መብት ምንም ነገር ካልተማሩ በአሁኑ ጊዜ አሮጌዎቹን ውሾች አዲስ የማጭበርበር ስልት ማስተማር ይቻላልን?

ከአምስት አስርት ዓመታት በኋላ ከኩባ ጋር ያለውን ግንኙነት ወደነበረበት ለመመለስ መታሰቡ እንከን የለውም፡፡ ግንኙነቶችን እንደገና ለመመስረት፣ የበረራ አገልግሎቶችን ወደ ቀድሞው ለመመለስ፣ የጉዞ እገዳዎችን ለማንሳት እና ኩባውያን የዩኤስ የገንዘብ ተቋማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እንዲቻል የዴፕሎማሲ እና የሰብአዊነት ፋይዳ ያለው ይመስላል፡፡

ወንድም ኦባማ ለአፍሪካ ወንድሞች እያደረገ ያለው ማንኛውም ነገር (በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እርዳታ) እኔ በማይበት መንገድ ለካስትሮ ወንድሞችም ቢያንስ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የገንዘብ እርዳታ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

ዩኤስ አሜሪካ በህዝቦቻቸው ላይ ከፍተኛ የሆነ እልቂት ለሚፈጽሙት እና የዘር ማጥፋት ወንጀል ለሚያካሂዱት ለአፍሪካ ወሮበላ ዘራፊ አምባገነኖች በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በመስጠት ስልጣናቸውን እንዲያጠናክሩ ስታደርግ ኩባን በመነጠል በሰብአዊ መብት ረገጣ ታሪኳ ላይ በመመስረት ለመቅጣት መሞከር በእርግጠኝነት የዩኤስ አሜሪካንን አስመሳይነት ጣራ መንካት በውል ያመላክታል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በሁሉም ዜጎች የሰብአዊ መብት አጠባበቅ ዙሪያ በሚደረገው ልዩነት ላይ ችግር እንዳለብኝ አምናለሁ፡፡

ሆኖም ግን በካስትሮ ወንድሞች የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰት ኃጢያቶች በአፍሪካ ወንድሞች ከሚፈጸሙ ኃጢያቶች የበለጡ ኃጢያቶች ናቸውን? እኔ በእርግጠኝነት ይህንን እላለሁ፡፡

በኢትዮጵያ ላይ እንደ መዥገር በስልጣን እርካብ ላይ ተጣብቆ የሚገኘው የዘ-ህወሀት አገዛዝ ከኩባ አገዛዝ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ በእጅጉ የበለጠ እና የሰፋ እንደሆነ ምንም ዓይነት ጥያቄ የለውም፡፡ ሆኖም ግን ዩኤስ አሜሪካ ዘ-ህወትን የበለጠ ለማጠናከር በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን በማስታቀፍ ላይ ትገኛለች፡፡

ለሴቷ ዳክዬ መልካም የሆነው ነገር ሁሉ ለወንዱም ዳክዬ መልካም ነገር ነው፡፡

ሆኖም ግን የኦባማ የባለሁለት ምላስ የሰብአዊ መብቶች አስመሳይነት ይህን ይመስላል፡፡

የካስትሮ ወንድሞች  ላለፈው ግማሽ ምዕት ዓመት በላይ ያህል በዩኤስ ግንብ ዙሪያ አካባቢ ቆይተዋል፡፡

ምንድን እየተደረገ እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ ንግግሩን ማን እንደሚናገረው እና ማን እንደሚፈጽመው ያውቃሉ፡፡

የሰብአዊ መብትን ጉዳይ በሚመለከት ኦባማ ንግግር ብቻ ማድረግ እንዳለበት ያውቃሉ፡፡

የካስትሮ ወንድሞች የሚጠሉት ነገር ቢኖር የሰብአዊ መብት ምዝገባ ታሪካቸውን መተችት ብቻ ነው፡፡

ሆኖም ግን ኦባማ የዩኤስ-ኩባን ግንኙነት በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እና በኩባ የምጣኔ ሀብት ቁጥጥር ላይ የላላ ሁኔታ መፈጠር ያለበት ስለመሆኑ እንደሚፈልግ ይናገራል፡፡ በርካታ የንግድ ልውውጥ፣ ግንኙነት፣ ቱሪዝም፣ ማህበራዊ እና የባህል ልውውጦች በማድረግ ኩባ ወደ በለጠ የዴሞክራሲ ማህበረሰብ መሸጋገር የሚኖርባት እንደሆነ ያምናል፡፡ ይህ ሁኔታ እንግዲህ በሂደት ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡

ኦባማ ኩባን ሲጎበኝ የፖለቲካ እስረኞች እንዲለቀቁ ጥሪ የሚያቀርብ ከሆነ የሚገርመኝ ይሆናል፡፡ ከፖለቲካ እስረኞች እና ከአማጺዎች ቤተሰቦች ጋር እገናኛለሁ ብሏል፡፡

ካገኛቸው በኋላ ለእነዚህ ሰዎች ምን ይላቸው ይሆን?

የሀዘን ስሜት አልተሰማችሁምን/ነገሮች እየከፉ ሲሄዱ በእኔ ላይ እምነት አልጣላችሁምን?

ቀኖቹ እየቀረቡ ሲመጡ እና በወንዙ ላይ እያደረጋችሁት ባለው ጉዞ የመስጠም አደጋ ሲደርስባችሁ ምን ተሰማችሁ?

በእርግጠኝነት አይዟችሁ እየመጣሁላችሁ ነው/እየመጣሁላችሁ ነው፡፡

ይኸ ምስቅልቅል ያለ ሁኔታ ነው፡፡

ስለፖለቲካ እስረኞች መነጋገር ከተነሳ ዘንድ የካስትሮ ወንድሞች በጓንታናሞ ታስረው ስለሚገኙት የፖለቲካ እስረኞች የሰብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታ በድንገት ማንሳታቸው እና መናጋገራቸው አይቀርም፡፡

ፊደል ካስትሮ እንዲህ በማለት ያስገነዝባል፣ “እኔ ማርክሲስት ሌኒኒስት ነኝ፣ እናም የሕይወቴ መጨረሻ የምትሆነዋ ዕለት እስከምትመጣ ድረስ ማርክሲስት ሊኒኒስት እንደሆንኩ እቀጥላለሁ፡፡“

ፊደል ካስትሮ ማርክሲስት-ሌኒኒስት፣ ፍጹማዊ የሆነ ስልጣን ያለው ገዥ፣ አምባገነን እና ወዘተ የመሳሰሉትን ባህሪያት አካትቶ የያዘ ሰው ነው፡፡

ሆኖም ግን ፊደል ካስትሮ አስመሳይ አይደለም፡፡ ፊደል ካስትሮ በመንታ ምላስ አይናገርም፡፡ ፊደል ካስትሮ ማለት የፈለገውን ይናገራል፣ እናም የሚናገረውን ያደርጋል፡፡

በፕሬስ እና በግለሰብ ነጻነቶች፣ በንብረት መብቶች፣ በሕግ የበላይነት እና በመሳሰሉት ላይ ከፊደል ካስትሮ ጋር እስማማለሁ፡፡ ሆኖም ግን ባካሄደው የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ እና በበርካታዎቹ የጤና እና የትምህርት መሻሻል ጉዳዮች ላይ ታላቅ አክብሮት እሰጠዋለሁ፡፡

ሆኖም ግን ለፊደል ካስትሮ አክብሮት እሰጣለሁ፣ ምክንያቱም አስመሳይ አይደለም፡፡

ባራክ ኦባማ በሀቫና በመገኘት ምን ዓይነት ንግግር ያደርግ ይሆን?

በሚከተሉት ዙሪያዎች ላይ ንግግር ያድርጋል ብዬ አስባለሁ፡

“እያንዳንዳችሁ እንደምን ዋላችሁ፡ በሀቫና በእናንተ መካከል በመገኘቴ ታላቅ ክብር ይሰማኛል…ለተደረገልኝ አቀባበል ከፍተኛ የሆነ ምስጋናዬን አቀርባለሁ…

የኩባ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በኩባውያን እጅ ላይ የተንጠለጠለ ነው ከሚለው መነሻ ሀሳብ ላይ መጀመር አለብኝ፡፡ ይህንን የምለው በዚህ የካሪቢያን ክፍል በሆነው አካባቢ ባለፈው ጊዜ አጥልቶ የቆየውን አስፈሪ ሁኔታ እያወቅሁ ነው ይህንን የምናገረው፡፡

ይኸ እንግዲህ በህዝቦች መካከል ባሉት የግንኙነት ወሰኖቻችን ላይ ችግር አጥልቶ በነበረበት ጊዜ የሆነውን ቀላል እውነታ የሚያመላክት ነው፡፡ የእናንተ ብልጽግና የአሜሪካንን ብልጽግና ያሳድጋል፡፡ የእናንተ ጤና እና ደህንነት ለዓለም ህዝብ ጤንነት እና ደህንነት የእራሱን ድርሻ ሊያበረክት ይችላል፡፡ የእናንተ የዴሞክራሲ መጠንከር እና አንድ ጊዜ ማጣጣም ከጀመራችሁ በየትም ቦታ ላሉ ህዝቦች የሰብአዊ መብት መከበር እገዛ ሊያደርግ ይችላል፡፡

የኩባ እና የአሜሪካንን ህዝብ እንደተለያየ የዓለም ህዝብ አድርጌ አልቆጥርም፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ ኩባ ከእኛ በ90 ማይሎች ርቀት ላይ የምትገኝ ሀገር ናት!

ኩባን በብዙ መልኩ እንደተሳሰረው ዋና የግዛት ክፍላችን አድርጌ እቆጥራታለሁ – (የድጋፍ ጭብጨባው ይቀልጣል) ወደፊት ሁላችንም ለልጆቻችን በጋራ ከአሜሪካ ጋር በአጋርነት የምትሰራ ሀገር ሆና ትታየኛለች፡፡ ያ አጋርነት ደግሞ በጋራ ኃላፊነቶች እና በጋራ መከባበር  ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት፡፡ እናም ዛሬ በእናንተ መካከል ተገኝቼ መናገር የምፈልገው ነገር ይኸው ነው፡፡

አሁን ያንን ቃልኪዳን ወደተግባር ለማሸጋገር ኩባ ከቀሪው የዓለም ህዝብ ጋር በኢኮኖሚ ልማት አብራ ለመራመድ እንድትችል መሰረታዊ የሆነውን እውነታ መገንዘብ አለብን፡፡

ልማት የሚወሰነው በመልካም አስተዳደር ነው፡፡ ይኸ እርሾ ነው አንግዲህ በኩባ ላይ ለረዥም ጊዜ ጠፍቶ የቆዬው፡፡ ያ ለውጥ ነው እንግዲህ የኩባን የወደፊት በር ሊከፍት የሚችለው፡፡ ያ ኃላፊነትም በኩባውያን ብቻ ሊሟላ የሚችል ጉዳይ ነው፡፡

ይህ የጋራ ኃላፊነት የአጋርነታችን ዋና መሰረት ነው፡፡ እናም በአሁኑ ጊዜ ለወደፊት ለኩባ እና ለካሪቢያን በጣም ወሳኝ በሆኑ በአራት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አደርጋለሁ፡፡ እነርሱም፡ ዴሞክራሲ፣ ልዩ ዕድል፣ ጤና እና ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚሉት ናቸው፡፡

በመጀመሪያ ጠንካራ እና ቀጣይነት ያለው ዴሞክራሲ የሚያራምዱ ሀገሮችን መርዳት አለብን፡፡

ካይሮ፣ አንካራ እና አክራ ላይ እንደተናገርኩት ሁሉ እያንዳንዱ ሀገር በእራሱ መንገድ እና በእራሱ ባህል መሰረት ለዴሞክራሲ ማበብ ህይወት ሊዘራ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ታሪክ እንዲህ በማለት የእራሱን ፍርድ ይሰጣል፡ በጭቆና ሳይሆን በስምምነት በማስተዳደር የሕዝቦቻቸውን ፍላጎት የሚያከብሩ መንግስታት የእራሳቸውን ዜጎች ከማያከብሩ መንግስታት የበለጡ ባለጸጋዎች፣ የበለጠ የተረጋጉ እና የበለጠ ስኬታማ የሆኑ ናቸው፡፡

ዴሞክራሲ በእርግጠኝነት ምርጫ ከማካሄድ በላይ ነው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ምርጫዎች በሚካሄዱበት ጊዜ ምን ሁኔታ እንደተደረገ እንዳለ ያለውን ሂደት የሚያመላክት ነው፡፡ ጭቆና በርካታ የሆኑ መገለጫዎችን ይይዛል፣ እናም በርካታ ሀገሮች ምርጫ የሚያካሂዱትም ቢሆኑ ህዝቦቻቸውን ወደ ድህነት አዘቅት ውስጥ በሚጨምር አደጋ እየተመቱ ውግዘት ይደርስባቸዋል፡፡

የሕግ ልዕልና የበላይነት ለጨካኝነት እና ለሙስና የበላይነት ቦታውን እንዲለቅቅ የሚፈልግ ማንም ሰው የለም፡፡ (ምንም ዓይነት ጭብጨባ የለም፡፡)

በ21ኛው ክፍለ ዘመን ብቃት ያለው፣ አስተማማኝ እና ግልጽነትን የተላበሱ ተቋማት ለስኬት ቁልፍ ነገሮች ናቸው፡፡ እናም ጠንካራ ፓርላማዎች፣ ታማኝነት ያለው የፖሊስ ኃይል እና ነጻ ዳኞች አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ (ምንም ዓይነት ጭብጨባ የለም፡፡) እነዚህ ነገሮች ናቸው እንግዲህ ለዴሞክራሲ ህይወት የሚሰጡት፣ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች በሰዎች የዕለት ከዕለት ህይወት ላይ የሚንጸባረቁ ናቸውና፡፡

አሜሪካ በሌላ በማናቸውም መንግስት ላይ ምንም ዓይነት የመንግስት ስርዓት ለመጫን አትፈልግም፡፡ የዴሞክራሲ ዋና አስፈላጊው እውነታ እያንዳንዱ ሀገር የእራሱን ዕድል እራሱ ከመወሰኑ ላይ ነው፡፡ ሆኖም ግን አሜሪካ መስራት ያለባት ነገር መልካም አስተዳደርን መርዳት፣ የሕግ ልዕልና የበላይነት እንዲከበር እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማገዝ ነው፡፡

ኩባ በተሻለ የመንግስት አስተዳደር የመሰረተ ሰፊ ባለጸጋነት የመጨረሻውን ደረጃ እንደያዘች ጥርጥር የለኝም፡፡ የኩባ ልዩ የሆነ ስኬት የእኔ ሀገር አሜሪካ ምስክርነቷን ትሰጣለች፡፡ በጣም ጥሩ ነገር ነው የሰሩት፡፡

አሜሪካ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት የበለጠ መስራት ትችላለች፡፡ የእኔ አስተዳደር ዋናው ቁርጠኝነቱ ይኸ ጉዳይ ነው፡፡ እናም መልካም አስተዳደር ካለ በመንግስት-የግል አጋርነት፣ በአቅም ግንባታ እና በገንዘብ አገልግሎት ብልጽግናን ማስፋፋት እንችላለን፡፡

በእኛ ፍላጎት እንደሚንጸባረቀው ህዝቦች ከድህነት አዘቅት ውስጥ የሚወጡ ከሆነ እና በኩባ ውስጥ ሀብት የሚፈጠር ከሆነ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ትችላላችሁ? እኛ ለምናመርታቸው የምርት ሸቆጦች ገበያዎችን ይፈጥራሉ፡፡ ስለሆነም ለሁለታችንም መልካም ነገር ነው፡፡

ሞስኮ ውስጥ ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት እንዲከበር እና የሰዎችን መብቶች የሚደፈጥጡትን መቃወም እንደሚያስፈልግ ተናግሬ ነበር፡፡ እናም ያ ቁርጠኝነት ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት የሚያደርጉትን፣ ማዕቀብ የሚጥሉትን እና ሌሎችን የማያድርጉትን እንዲሁም በችግር ላይ የሚሰቃዩትን ሁሉ የሚጨምር ነው፡፡

እንደ ኩባ ባለች ሀገር ወጣቱ ኃይል የሕዝቡን ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የህብረተሰብ ከፍል ይሸፍናል፡፡

እናም ወጣት ኩባውያን ማወቅ ያለባቸው ይህንን ነው፡ ዓለም የሰራሀትን ነው የምትሆነው፡፡ መሪዎቻችሁን ተጠያቂዎች የማድረግ እና ተቋሞቻችሁን ለህዝቡ በመገንባት ህዝቡን እንዲያገለግሉ የማድረግ ኃይል አላችሁ፡፡ ህብረተሰባችሁን ማገልገል እና ኃላፊነታችሁን እና ትምህርቱን አዲስ ሀብት እንዲፈጥር በማድረግ ከዓለም ጋር የሚኖራችሀን የግንኙነት ትስስር ለማጠናከር ይረዳችኋል፡፡ በሽታን በመዋጋት ግጭቶችን ማስወገድ እና ለውጥን ከታች ወደ ላይ ማምጣት ትችላላችሁ፡፡ ይህንን ማድረግ ትችላላችሁ፡፡ አዎ ትችላላችሁ፣ (ጭብጨባ ቀጠለ) ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ታሪክ በመገስገስ ላይ ነው፡፡

ሆኖም ግን እነዚህ ሁሉ ነገሮች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉት ለወደፊቱ ሁላችሁም ኃላፊነትን ለመውሰድ ስትችሉ ብቻ ነው፡፡ እናም ቀላል ነገር ሊሆን አይችልም፡፡ ጊዜ እና ጉልበትን ይጠይቃል፡፡ መሰቃየት እና በችግር የመጠመድ ሁኔታ ይኖራል፡፡ ሆኖም ግን ይህንን ቃል እገባላችኋለሁ፡ በእያንዳንዱ መንገድ አሜሪካ እንደ አጋርነት እና እንደ ወዳጅ ከእናንተ ጎን ትሰለፋለች፡፡ (ጭብጨባው ቀጠለ፡፡)

ኩባ ነጻነት የዘር ውርሳችሁ ነው፡፡ (አዬ ጉድ! የኩባ ነጻነት!) አሁን የነጻነትን መሰረት ለመገንባት የእናንተ ኃላፊነት ነው፡፡ እናም ይህንን ካደረጋችሁ እንደ ሀቫና ያሉትን ቦታዎች ወደ ኋላ መለስ ብለን በማየት ቃልኪዳኑ የተሳካበት ጊዜ ይኸ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ብልጽግና የተገኘበት አጋጣሚ፣ ስቃይ ድል የተደረገበት ሁኔታ እና አዲስ የእድገት ጎዳና የተጀመረበት ይኸ ነበር ማለት እንችላለን፡፡ (ጭብጨባው ቀጠለ፡፡)

በመጨረሻም ምንም ዓይነት ስህተት እንዳትሰሩ፡ ታሪክ ከጀግኖች ኩባውያን ጎን እንጅ ለ56 ዓመታት በስልጣን እርካብ ላይ ከተቆናጠጡት ኃይሎች ጎን አይደለም፡፡ (ምንም ዓይነት ጭብጨባ የለም፡፡)

ኩባ ጠንካራ ሰዎችን አትፈልግም፡፡ ጠንካራ ተቋማትን ነው የምትፈልገው፡፡ (ምንም ዓይነት ጭብጨባ የለም፡፡)

በጣም አመሰግናለሁ፡፡

ኦባማ እ.ኤ.አ ሀምሌ 2009 በጋና አክራ ላይ ያደረገዉን ንግግር አይመስልም?  

አንዴት አደናባሪ ነገር ነው!

እ.ኤ.አ መጋቢት 20/2016 ኩባውያን በኩባ ሰማይ ላይ ምን ለማየት እንደሚችሉ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ወፍ ነው! ክንፍ ያለው የትሮጃን ፈረስ ነው፡፡ ኦ፣ አይደለም የኦባማ አይሮፕላን ነው!

የኩባ ሕዝብ፡ አስመሳይ ባራክ ኦባማን ባድናቆት ተቀበሉ! 

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!  

መጋቢት 13 ቀን 2008 .

 

 

Similar Posts