አስታዉሳለሁ መቼ እረሳለሁ! የመጋቢት 1960 እልቂት በደቡብ አፍሪካ ሻርፕቪል ከተማ
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
በየዓመቱ በአፍሪካ ውስጥ የተፈጸሙ ሁለት የሕዝብ እልቂቶችን አስታውሳለሁ፡፡
በወርሃ መጋቢት በደቡብ አፍሪካ የጥቂት ነጮች የበላይነት ዘረኛ አገዛዝ/apartheid በሻርፕቪሌ ከተማ እ.ኤ.አ መጋቢት 21/1960 የፈጸመውን ዘግናኝ እልቂት አስታውሳለሁ፡፡
እንደዚሁም ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን በህይወት በሌለው በአምባገነኑ መለስ ዜናዊ ልዩ ትዕዛዝ እ.ኤ.አ ሰኔ 8/2005 እና ከህዳር 1-10/2005 እንዲሁም ከ14-16 በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) የጥቂት ጥቁሮች የበላይነት የጎሳ አገዛዝ/apartheid የተፈጸመውን አሰቃቂ እልቂት አስታውሳለሁ፡፡
በዘር እና በጎሳ የጥቂት አፓርታይድ አናሳ ቡድኖች የበላይ አገዛዝ መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት የለም፡፡
በዘር መድልኦ እና በጎሳ መድልኦ መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት የለም፡፡
በጥቂት ነጮች የበላይ የዘር አገዛዝ “ባንቱስታንስ“ (መኖሪያ መንደሮች) እና በዘ-ህወሀት (የማጎሪያ በረት) “ክልሎች“ መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት የለም፡፡
“የተለያየ ህዝብ ራሱን በግሉ ማልማት” እየተባለ ይጠራ በነበረው የጠቅላይ ሚኒስትር ሄንድሪክ ቬርወርድ የጥቂት ነጮች የደቡብ አፍሪካ ዘረኛ የበላይ አገዛዝ ፖሊሲ እና በአምባገነኑ መለስ ዜናዊ የጥቂት ጥቁሮች “የጎሳ ፌዴራሊዝም” የበላይ አገዛዝ ፖሊሲ መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት የለም፡፡
አፓርታይድ የቆዳ ቀለም ዘር የለውም፣ ጎሳ የለውም፣ ኃይማኖት የለውም፣ ቋንቋ የለውም፣ እናም ምንም ዓይነት የብሄራዊነት ባህሪያት የሉትም፡፡ ሆኖም ግን በሰው ልጆች ላይ የተፈጸመ አሰቃቂ ስቃይ ነው፡፡
ከዛሬ 56 ዓመታት በፊት በመጋቢት ወር በሻርፕቪሌ (ከጁሀንስበርግ በስተደቡብ አቅጣጭ በትራንስቫል ግዛት በሚገኘው እና በአሁኑ ጊዜ ጓቴንግ እየተባለ በሚጠራው ከደቡብ አፍሪካ 9 ክልሎች መካከል አንዱ በሆነው ግዛት ውስጥ የምትገኘው) ተካሂዶ በነበረው በዚያ ጥላቻ በተመላበት ዕለት የጥቁር አፍሪካውያንን የአካል እንቅስቃሴ ለመገደብ ወጥቶ እና በጥቂት የነጮች የበላይ አገዛዝ ጸድቆ የነበረውን ሕግ (የአገር ዉስጥ ፓስፖርት ጥቁር አፍሪካውያኖችን አንቀሰቃሴ ለመገደብ) ለመቃወም ከፖሊስ ጣቢያው ፊት ለፊት 5 ሺ (የአፓርታይድ ፖሊስ የወሰደው የኃይል እርምጃ ትክክለኛ መሆኑን ለማሳየት አጋንኖ በማቅረብ ቁጥሩን እስከ 20 ሺ ያደርሰዋል) ተቃዋሚዎች ተሰባሰቡ፡፡
ምንም ዓይነት መሳሪያ ያልታጠቁት ሰላማዊ ሰልፈኞች የፖሊስ ቅጥር ግቢውን ሰብረው ለመግባት ሙከራ አደረጉ፡፡ ፖሊስ በመጀመሪያ በአስለቃሽ ጭስ እና በፖሊስ ቆመጥ በመጠቀም አመጹን ለማክሸፍ ምላሽ ሰጠ፡፡ ጥቂት ተቃዋሚዎች የፖሊስ ቅጥር ግቢ በሩን ሰብረው ለመግባት ሞከሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ፖሊስ በተቃዋሚ ስብስቡ ላይ በአውቶማቲክ እና ሌሎች መሳሪያዎች አማካይነት የእሩምታ ተኩስ ከፈተ፡፡
ይፋ በሆኑ መረጃዎች መሰረት ፖሊስ 705 ጥይቶችን በመተኮስ 69 ተቃዋሚዎችን 8 ሴቶችን እና 10 ልጆችን ጨምሮ ገድሏል፡፡ የቆሰሉት ሰዎች ቁጥር እና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች 31 ሴቶችን እና 19 ልጆችን ጨምሮ ከ180 ይዘላል፡፡
እ.ኤ.አ ግንቦት 1960 በተቃውሞ ሰልፉ የተሳተፉ እና ደጋፊዎች ናቸው ተብለው የተወነጀሉ 18,011 የሻርፕቪሌ ተቃዋሚዎች እየተያዙ ወደ እስር ቤት ታጎሩ፡፡ አብዛኞቹ የጥቃት ሰለባ የሆኑት ተቃዋሚዎች ከድርጊቱ ለማምለጥ ወደ ኋላ በመሸሽ ላይ እንዳሉ ከጀርባቸው በተተኮሱ ጥይቶች እየተመቱ የተገደሉ ነበሩ፡፡
በሻርፕቪል በተጨማሪነት የፖሊስ ኃይሉን ለማጠናከር የመጣው ፖሊስ ዋና አዛዥ የነበሩት ሌተና ኮሎኔል ፒናር ለጋርዲያን ቃለ መጠይቅ በሚያደርጉበት ጊዜ ደረታቸውን ነፍተው ምንም ነገር እንዳልተደረገ በሚመስል መልኩ እንዲህ ነበር ያሉት፣ “ይህ ሁሉ ድርጊት የተፈጸመው የተሰበሰበው የአካባቢው ህዝብ የፖሊስ ጣቢያውን መክበብ በጀመረበት ጊዜ ነበር፡፡ መኪናዬ በድንጋይ ተመትታ ነበር፡፡ እንደዚህ ያለ ድርጊት ከፈጸሙ ከባድ ነገር ሊገጥማቸው እንደሚችል መማር አለባቸው፡፡” የፖሊስ አዛዡ ሌላም ነገር በመጨመር እንዲህ ብለው ነበር፣ “የአካባቢው ተወላጅ ሰዎች አስተሳሰብ በሰላማዊ መንገድ ተሰብስበው ሀሳባቸውን ለመግለጽ ችሎታውም ሆነ ፍላጎቱ የላቸውም፡፡ ለእነርሱ መሰብሰብ ማለት ኃይል የተቀላቀለበት እርምጃ መውሰድ ማለት ነው፡፡“
እ.ኤ.አ ሰኔ 8/2005 በአዲስ አበባ ከተማ እና እ.ኤ.አ ከሕዳር 1-10 እና ከሕዳር 14-16/2005 ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ እና በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች የዘ–ህወሀት አፓርታይድ ኃይሎች መሳሪያ ባልታጠቁ ተቃዋሚ ስብስቦች ላይ የእሩምታ ተኩስ በመክፈት 193 ሰላማዊ ዜጎችን በመግደል 763 የሚሆኑትን ደግሞ ቁስለኛ አድርገዋል፡፡ ይህ መረጃ አሁን በህይወት በሌለው እና የዘ-ህወሀት ፈላጭ ቆራጭ መሪ በነበረው በአምባገነኑ መለስ ዜናዊ በተሾመው የምርመራ አጣሪ ኮሚሽን ይፋ የተደረገ ነው፡፡ የምርመራ አጣሪ ኮሚሽኑ እ.ኤ.አ በግንቦት 16 እና በታህሳስ 2005 መካከል የተፈጸሙትን በመቶዎች የሚቆጠሩ የሞት ሰለባ እና ቁስለኛ የሆኑትን የሌሎች ዜጎችን ዘገባ እንዲያቀርብ አልተፈቀደለትም፡፡ (የትዕዛዝ አዋጁን ለማንበብ እዚህ ጋ ይጫኑ ፡፡)
የአምባገነኑ መለስ ዜናዊ የእልቂት ምላሽ በሚያስገርም ሁኔታ ከኮሎኔል ፒናር ምላሽ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ አምባገነኑ መለስ እንዲህ የሚል ገላጻ አድርጎ ነበር፣ “ሰላማዊ የሆነ ሰልፍ አልነበረም እላለሁ፡፡ እየተካሄደ የነበረው አመጽ ነበር፣ እናም ህዝባዊ አመጹን አስተንፍሰነዋል፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ የሰው ህይወት ጠፍቷል፡፡ ሆኖም ግን በምንም ዓይነት መልኩ በፍጹም ሰላማዊ ሰልፍ አልነበረም፡፡“
እ.ኤ.አ በ2005 ተካሄደ የተባለውን የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ ተከትሎ ተፈጥሮ በነበረው ውዝግብ ጋር በተያዘ መልኩ 30 ሺ ሰላማዊ ዜጎች በዘ–ህወሀት በቁጥጥር ስር እየዋሉ ወደ ዘብጥያ በመወርወር ለእስር ተዳርገዋል፡፡
በደቡብ አፍሪካ ጥቂት የነጮች ዘረኛ አገዛዝ በአፓርታይድ በሰው ልጆች ላይ የፈጸማቸው ኢሰብአዊ ድርጊቶች በፊልም ተቀድተው ተቀምጠዋል፡፡ (አንዱን አሳዛኝ የቪዲዮ ምስል ለመመልከት እዚህ ጋ ይጫኑ ፡፡)
እ.ኤ.አ በ2005 በዘ–ህወሀት አናሳ የጎሳ አፓርታይድ አገዛዝ በሰው ልጆች ላይ የተፈጸመውን እልቂት የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል በይፋ የለም፡፡ ሆኖም ግን የአምባገነኑ መለስ የጥቃት ሰለባ የሆነ የእያንዳንዱ ሰው ስም ዝርዝር ይታወቃል፡፡ ጥቂት ፎቶግራፎች (በጣም አሰቃቂ ፎቶግራፎች ስለሆኑ ፣ ተመልካቾችን አናስተነቀቃለን :: የጥቃት ሰለባዎቹን ፎቶግራፍ የጥቃት ሰለባዎች ስም ዝርዝር ቀጥሎ ይገኛል አዚህ ይጫኑ ለማየት)፡፡
የሻርፕቪሌን እልቂት ማስታወስ ያለብን ለምንድን ነው?
እ.ኤ.አ በ1960 በሻርፕቪሌ የተፈጸመውን እልቂት በምናስታውስበት ጊዜ እንደዚሁም ሁሉ ከዚህም በላይ በመቶዎች የሚቆጠሩትን በአፍሪካ በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸሙ ያሉትን፣ ትላንት የተፈጸሙትን፣ ባለፈው ዓመት የተፈጸሙትን፣ ከ10 ዓመታት በፊት የተፈጸሙትን እና ከ100 ዓመታት በፊት የተፈጸሙትን እልቂቶች እናስታውሳለን፡፡
ባለፈው ዓመት ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እና ሌሎች የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በአብዛኞቹ የሰብ አፍሪካ ሀገሮች ውስጥ ከሕግ አግባብ ውጭ የተፈጸሙትን መጠነ ሰፊ ግድያዎች መዝግበው ይዘዋል፡፡
ባለፈው ወር ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እንዲህ የሚል ዘገባ አውጥቷል፣ “የኢትዮጵያ የደህንነት ኃይሎች እ.ኤ.አ በሕዳር 2015 በኦሮሚያ ክልል የተጀመረውን መጠነ ሰፊ ሰላማዊ ህዝባዊ ተቃውሞ ኃይልን በመጠቀም በመጨፍለቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ አዲሱ ዓመት እ.ኤ.አ 2016 ከባተ ጊዜ ጀምሮ ሂዩማን ራይትስ ዎች በየዕለቱ በሚባል መልኩ የዘፈቀደ ግድያዎችን እና እስራቶችን እየመዘገበ ይገኛል፡፡“ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)
እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ግን ወሮበላ ዘራፊዎች በምዕራቡ ዓለም እና በቻይና መልካም ፈቃድ እና ግዙፍ የገንዘብ ድጋፍ እየታገዙ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እልቂቶችን ከመፈጸማቸው በስተቀር “ሻርፕቪሌዎች” በአፍሪካ በየዕለቱ ይፈጸማሉ፡፡
በሱዳን፣ በላይቤሪያ፣ በሴራሊዮን፣ በማዕከላዊ አፍሪካ ሬፐብሊክ፣ በማሊ፣ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፐብሊክ እና በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች በአፍሪካ ውስጥ በደህንነት ኃይሎች፣ በወታደር እና በፖሊስ ኃይሎች እየተፈጸሙ ያሉት የዘፈቀደ ግድያዎች ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ ተንሰራፍተው ይገኛሉ፡፡ ጥቂቶች አዲስ እልቂቶች ደግሞ እጅግ በጣም የሚዘገንኑ እና አስደንጋጭ እየሆኑ መጥተዋል፡፡
ቀላሉ እውነታ ሲታይ ግን ታላላቆቹ የምዕራብ ሃያላን ሀገሮች በአፍሪካ ውስጥ ስለሚፈጸም የሰው ልጆች ዕልቂት መስማት አይፈልጉም፡፡ ይልቁንም የመንግስት ስልጣንን በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሳይሆን የህዝቦችን ፍላጎት በኃይል በመጨፍለቅ በመንግስት ስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው የሚገኙትን ወሮበላ ዘራፊ ገዳይ መንግስታት ለመጠበቅ ሲሉ ጥርሳቸውን ነክሰው በመዋሸት ላይ ይገኛሉ፡፡
ባለፈው ዓመት የኬንያ ፕሬዚዳንት የሆነው ኡሁሩ ኬንያታ በሰው ልጆች ላይ በተፈጸመ ሰብአዊ ወንጀል አምስት የውንጀላ ክሶች ቀርበውበት ሄግ ውስጥ በሚገኘው በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ቀርቦ ጉዳዩ መታት እንዲችል ዝግጅት ተደርጎ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2007/08 ተደርጎ የነበረውን የኬንያ ድህረ ምርጫ ውዝግብ ተከትሎ ከ1,200 በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 600 ሺ ዜጎች ደግሞ ከመኖሪያ ቦታቸው ተፈናቅለው ነበር፡፡
ኬንያታ ሙንጉኪ እየተባለ የሚጠራ የማፊያ ዓይነት ወንጀለኛ ድርጅት በማሰማራት ከናይሮቢ በስተደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በሚገኘው እና ከአፍሪካ ታላላቅ የቆሻሻ ስፍራዎች መካከል አንዱ በሆነው እና ኪቤራ እየተባለ በሚጠራው ቦታ ጎሳን መሰረት ባደረገ መልኩ በስሜት በመነሳሳት ግድያ እና የአካል ጉዳት ማድረሱን የሚያመላክቱ በርካታ ማስረጃዎች ነበሩ፡፡ ሆኖም ግን የምዕራቡ ዓለም ኃያላን መንግስታት በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት/International Criminal Court (ICC) ዋና አቃቤ ሕግ ላይ ተጽዕኖ በማድረግ በኬንያታ ላይ የተያዘው የወንጀል ክስ እንዲቋረጥ አድርገዋል፡፡ (ከአመት በፊት አስቀድሜ ኬንያታ ሙሉ በሙሉ ከICC በነጻ ተሰናብቶ ደረቱን ገልብጦ እንደሚሄድ ስተነብይ ቆይቻለሁ፡፡)
እ.ኤ.አ ታህሳስ 2014 በICC ተይዞ በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረው ኬንያታ ተለቅቆ እንደ ወፍ በመብረር ከወጣ በኋላ ቅጥፈቱን በመንዛት ደረቱን ገልብጦ በመንገዳወል ላይ ይገኛል፡፡
ለአፍሪካ ወሮበላ ዘራፊዎች ደግ እና ትህትና የተመላበት መስተንግዶ ማድረግ በዚህ ላይ ብቻ የሚያቆም አይደለም፡፡
የነጻው ዓለም ታላቅ መሪ የተባለው ባራክ ኦባማ እ.ኤ.አ ሀምሌ 2015 ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ እንዲህ ብሎ ነበር፣ “እንደዚህ ያሉ ጉዳዮች በሚመጡበት ጊዜ ምላሴን አላጥፍም፡፡ መንግስትን በኃይል ለማስወገድ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን የኢትዮጵያን መንግስትም ጨምሮ ዓላማ ያደረገን ማነኛውንም ቡድን እንቃወማለን፡፡“
ኦባማ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን እያለ የሚጠራው ሌላ ማንንም ሳይሆን በአሁኑ ጊዜ በአሸባሪነት የተፈረጀውን እና በዓለም አቀፍ የአሸባሪዎች መረጃ ቋት ስም ዝርዝር ውስጥ ስሙ ሰፍሮ የሚገኘውን የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን (ዘ-ህወሀትን) ነው፡፡
ኦባማ በተግባር የማያውለውን ሆኖም ግን እራሱን ከፍ ከፍ እያደረገ ለአራት ዓመታት ያህል እንዲህ በማለት ሲቀጥፍ ቆይቷል፣ “አፍሪካ ጠንካራ ሰዎችን አትፈልግም፡፡ አፍሪካ የምትፈልገው ጠንካራ ተቋማትን ነው፡፡ የአፍሪካ ጠንካራ ሰዎች በተሳሳተው የታሪክ መንገድ ላይ የሚጓዙ ናቸው፡፡“
አዬ! ለምንድን ነው ኦባማ በመንታ ምላስ የሚናገረው!
የኦባማ መንታ ምላስ እንዲህ የሚሉትን የሸክስፒር ማክቤዝ ጥቂት ዓረፍተ ነገሮች አስታወሱኝ፡ “የአንተ እጆች፣ የአንተ ምላስ:: ልብ ብለህ ተመልከት ውብ አበቦች ይመስላሉ፡፡ ሆኖም ግን በመርዝ የተሞላ እባብ ማለት ናቸው፡፡“
ኢትዮጵያውያን እንደዚህ ባለ መንታ ምላስ ለተካነ ሰው እንዲህ የሚል የአባባል ተረት አላቸው፣ “አፉ ቅቤ ሆዱ (ልቡ) ጩቤ ከሆነ ሰው ተጠንቀቁ፡፡“
በኦባማ ምላስ ላይ ካለው ተለዋዋጭ መርዛማ እባብ ተጠንቀቁ!
የአፍሪካ ህይወቶች ለኦባማ ጉዳዮቹ ናቸውን? (ይኸ አወዛጋቢ ጥያቄ ነው አትመለስ ገና፡፡)
ኦባማ እና የምዕራቡ ዓለም በአፍሪካ በስልጣን ላይ ተፈናጥጠው ላሉት ወሮበላ ዘራፊዎች መንታ ምላስን በመጠቀም ላይ ይገኛሉ፡፡
የምዕራቡ ዓለም ኃያላን መንግስታት ወሮበላ ዘራፊዎቹ ከእስር ቤት በነጻ እንዲወጡ ማድረግ ብቻ አይደለም እየፈጸሙ ያሉት፣ ሆኖም ግን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠረውን የእራሳቸውን ግብር ከፋይ ህዝቦች ዶላሮችን እና ዩሮዎችን በመሰብሰብ በባንክ ሂሳባቸው ውስጥ ያጭቁላቸዋል፡፡
እንግዲህ ኦባማ ለዘ-ህወሀት በትክክል ያደረገው ይህንን ነው፡፡ ዴሞክራት በማለት የይለፍ ወረቀት ይሰጣቸዋል፡፡ አባማ በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉት ጨካኝ እና ሙሰኛ ወሮበላ ዘራፊዎች በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የአሜሪካ ግብር ከፋይ ህዝብ ዶላሮችን ያስታቅፋቸዋል፡፡
እ.ኤ.አ ነሀሴ 2012 የደቡብ አፍሪካ ጥቁር ፖሊስ ኃላፊዎች በሰሜናዊ ምዕራብ ደቡብ አፍሪካ በምትገኘው በማራኪና የማዕድን ቁፋሮ አመጽ ያካሄዱ ሰራተኞች ላይ የእሩምታ ተኩስ በመክፈት 44 ዜጎችን ሲገድሉ 78ቱ ደግሞ ቁስለኞች እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡ (መሳሪያ ባልታጠቁ አማጺዎች ላይ የተፈጸመውን እና ለማመን የሚያስቸግረውን እና ልብ የሚያደማውን የጥይት ድብደባ ትክክለኛውን የቪዲዮ ምስሉን እዚህ ጋ በመጫን ይመልከቱ [ዝርዝር ምስሉን]፡፡
በዚያን ጊዜ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ እንዲህ ብሎ ነበር፣ “በዚህ ትርጉም የለሽ ጥቃት ደንግጠናል፣ አዝነናልም፡፡“ “ትርጉም የለሽ ጥቃት” የሚለው ማንም ሰው በለማዳ እንስሳት ላይ የሚፈጸም ትቃትን ለመግለጽ የሚጠቀምባቸው ቃላት ናቸው፡፡
ዙማ እ.ኤ.አ በ1960 የተፈጸመውን የሻርፕቪሌ እልቂት ለመግለጽ እንደዚህ ያሉትን የተለሳለሱ እና ፍጹም በሆነ መልኩ ኢሰብአዊ የሆኑትን የቢሮክራሲ ቋንቋዎች ለመጠቀም ባይመርጥ ኖሮ የሚገርመኝ ይሆን ነበር፡፡
ኦባማ ስለማራኪና እልቂት ምንም ትንፍሽ ያለው ነገር የለም፡፡ ኦባማ እ.ኤ.አ ከ2009 ጀምሮ በሀገር ውስጥ እና በውጭ አሸባሪዎች ሲፈጸሙ በቆዩት የህዝብ እልቂቶች ላይ የተሰማውን ሀዘን ሲገልጽ ቆይቶ ነበር፡፡ ሆኖም ግን የአፍሪካ ወሮበላ ዘራፊ አገዛዞች በአፍሪካ ህዝቦች ላይ ሲፈጽሙት በቆዩት እልቂት ላይ አንዲትም ቃል ትንፍሽ ሳይል ቆይቷል!
አሁን እንዲህ የሚለውን ጥያቄ መመለስ ትችላላችሁ፣ “የአፍሪካ ህዝቦች ህይወት ለኦባማ ጉዳዩ ነውን?“
የማራኪና እልቂት ተፈጽሟል ምክንያቱም የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ኮንግራስ አመራር ለፈጸማቸው የወንጀል ድርጊቶች እና ጉድለቶች በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ቀርቦ ተጠያቂ ሊሆን እንደማይችል አስቀድሞ ያውቅ ነበርና ነው፡፡
በቁስል ላይ እንጨት ስደድ እንዲሉ የማራኪናን እልቂት የማጣራት ስራ ከተጀመረ ከሶስት ዓመታት በኋላ ህዝባዊ ነጻ የሆነ የፖሊስ ምርመራ ሲያካሂዱ የቆዩት መርማሪዎች ለእንዲዚያ ዓይነቱ የህዝብ ፍጅት አንድንም የፖሊስ አባል እስከ አሁንም ድረስ ተጠያቂ ማድረግ ሳይችል ቆይቷል፡፡ በማራኪና በግፍ 44 ንጹሀን ዜጎችን በጥይት እየደበደቡ የገደሉ እና 78 የሚሆኑትን ዜጎች ያቆሰሉት አንዳቸውም የፖሊስ ኃላፊዎች እስከ አሁን ድረስ ወደ ፍትህ አካል ፍጹም አልቀረቡም!!!
በተመሳሳይ ሁኔታ 193 መሳሪያ ያልታጠቁ ሰላማዊ ተቃዋሚ ዜጎችን በጥይት በመደብደብ የገደሉት የአምባገነኑ መለስ የፖሊስ እና የደህንነት ኃይሎች እስከ አሁን ድረስ ለፍትህ አካል ሳይቀርቡ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ግን በፖሊስ እና በደህንነት መምሪያዎች ሰላማዊ ዜጋ መስለው የሚኖሩ ሆኖም ግን እጃቸው በንጹሀን ደም ተጨማልቆ የሚገኘው የ237 የፖሊስ እና የደህንነት ወሮበላ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች ስም ዝርዝር ተይዞ ይገኛል፡፡
የማራኪና እልቂት እ.ኤ.አ በ2012 በደቡብ አፍሪካ መፈጸም የሚችል ከሆነ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት በሻርፕቪል መሬት ላይ የተፈጸመው እልቂት እና በተመሳሳይ መልኩ በኢትዮጵያ ወይም በአፍሪካ በተለያዩ ቦታዎች ውስጥ እ.ኤ.አ በ2016 ተመሳሳይ እልቂቶች ቢፈጸሙ የሚያስደንቀን ነገር ሊሆን ይችላልን?
ወሰን የማይገድበው ሰይጣናዊነት፣
በአፍሪካ ውስጥ ሁሉም እልቂቶች በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጥጠው በሚገኙት ወሮበላ ዘራፊዎች እና አንዳንድ ጊዜም ለወደፊት ስልጣን ለማግኘት ሲሉ ስልጣን በሌላቸው ዘራፊዎች በውል ታስቦባቸው የተቀነባበሩ ስሌቶች ናቸው፡፡
በአፍሪካ ውስጥ የሚፈጸሙ እልቂቶች ህዝባዊ ፍጅትን ለማድረግ የሚያገለግሉ መሳሪያዎች ናቸው፡፡
በሻርፕቪል በጥቂት ነጮች የበላይ ዘረኛ የአፓራታይድ አገዛዝ በተፈጸመው ኢሰብአዊ ወንጀል እና እ.ኤ.አ በአምባገነኑ መለስ ዜናዊ በተፈጸመው እልቂት ወይም ደግም በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ላይ በተደረገው የዘር ማጥፋት ወንጀል መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት የለም፡፡ ምንም!
አናሳው የደቡብ አፍሪካ የጥቂት ነጮች የበላይነት አገዛዝ የነበረው እና አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ በስልጣን እርካብ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ የሚገኘው ዘ-ህወሀት በስልጣኖቻቸው ላይ የሚመጡባቸውን ማናቸውንም ነገሮች ቢሆን መግደል እና ማጥፋት እንደሚችሉ ለህዝቡ በማሳያነት በማቅረብ እልቂቶችን እና የኃይል ጥቃቶችን ይጠቀማሉ፡፡
የሻርፕቪል እልቂት የጥቂት ነጮች ዘረኛ የበላይ አገዛዝ ቃፊር [በደቡብ አፍሪካ ነጮች የተናቁ ጎሳዎች] እያሉ ለሚጠሯቸው የደቡብ አፍሪካ ጎሳዎች ሊረሱት በማይችሉት መልኩ ዘላለማዊ ትምህርት ለመስጠት ታስቦ የተፈጸመ እልቂት ነበር፡፡
መልዕክታቸውም ቀላል እና እንዲህ የሚል ነበር፣ “የአናሳዎቹን የነጮች የበላይ አገዛዝ መገዳደር እርባናየለሽ ሙከራ ነው፡፡“
የአምባገነኑ የመለስ እልቂት እና በአሁኑ ጊዜ በዘ-ህወሀት ቀጥለው የሚገኙት እልቂቶች ለብዙሀኑ ህዝብ እንዲህ የሚለውን አንድ ዓይነት መልዕክት ለማስተላለፍ ዓላማ በማድረግ እየተሰራበት ይገኛል፣ “የአናሳውን የዘ-ህወሀትን የበላይ አገዛዝ መገዳደር እርባናየለሽ ሙከራ ነው፡፡“
ልዩ በሆነ መልኩ የሚፈጸም የኃይል ጥቃት እና እልቂት የሰይጣናዊነት ትሩፋት ውርስ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደቡብ አፍሪካ ጥልቀት ባለው ሁኔታ ተከፋፍላለች፣ እናም ብዙሀኑ ህዝብ በመበሳጨት ላይ የሚገኝ ሲሆን ደቡብ አፍሪካ በሰዓት የተሞላን የጊዜ ቦምብ በመጠባበቅ ላይ እንደሆነች በቂ መረጃ ያላቸው ተመልካቾች ያምናሉ፡፡
በዘ–ህወሀት አገዛዝ ስር ባለችው ኢትዮጵያም ተመሳሳይ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ባቀረብኳቸው ሶስት ተከታታይ ትችቶቼ እንደ ደቡብ አፍሪካ ሁሉ በኢትዮጵያ ውስጥም በባሩድ በተሞላ ሳጥን ውስጥ የተቀመጠ ቦምብ እንዳለ እና የማቀጣጠያ ፊዩዟ ከተሳበች ሊፈነዳ እንደሚችል ለማሳየት ሞክሪያለሁ፡፡ ጥያቄ ሆኖ የሚቀርበው ግን መቼ ነው ይኸ በሰዓት የተሞላ ቦምብ የሚፈነዳው የሚለው ነው እንጅ በባሩድ ሳጥኑ ላይ ያለው የማቀጣጠያ ፊዩዝ ቦምቡን ሊያፈነዳው ይችላል ወይ የሚለው ጥያቄ አይደለም፡፡
“ሰይጣናዊነት ድልን ሊቀዳጅ የሚችልበት ዋናው አስፈላጊ ነገር ጥሩ ወንዶች እና ሴቶች ምንም ነገር ማድረግ ሳይችሉ ሲቀሩ ብቻ ነው…“
ሰይጣናዊነት ድልን ሊቀዳጅ የሚችለው እያንዳንዱ ሰው ምንም ዓይነት ሰይጣናዊነት አልሰማሁም፣ ምንም ዓይነት ሰይጣናዊነት አላየሁም እና ምንም ዓይነት ሰይጣናዊነት አልተባለም የሚሉ በውል የተጠኑ ውሳኔዎችን ማስተላለፍ በሚችልበት ጊዜ ነው፡፡ ለእውነት በመቆም የትኛው ጥሩ እና ትክክለኛ ነው የሚለው የሁሉም ሰዎች ጠንካራ ምርጫ ነው ምክንያቱም ይኸ ጉዳይ የሞራል ግልጽነትን እና ለህሊና የማደር ድፍረትን ይጠይቃል፡፡
ከሰይጣናዊነት እጅግ በጣም የከፋው ሰይጣናዊነት ደግሞ እንዲህ የሚሉ ቀላል ምርጫዎችን የሚሰጡን ናቸው፡ ጸጥ ማለት፣ የምንግዴለሽነት ባህሪ ማሳየት፣ ተበድሎም ቢሆን ይቅርታ ጠያቂዎች ሆኖ መቅረብ እና የሰይጣናዊነትን ድርጊቶች መፈጸም ናቸው፡፡
እኛ ብቻ እንደ ግለሰብ በሞራል ልዕልና ድፍረት እና በሰይጣናዊነት ድርጊቶች መካከል ያሉትን ምርጫዎች በመለየት መተግበር መቻል ይኖርብናል፡፡
ሮበርት ኬኔዲ የሰይጣናዊነት ድርጊት እንቆቅልሽ ባጋጠመን ጊዜ ማድረግ የሚገባንን የሞራል ልዕልና እንዲህ በማለት አቅርበውልናል፡
“በእያንዳንዷ ጊዜ ወንድ [ሴት] ላመነበት ሀሳብ ሲቆም፣ ወይም ደግሞ የሌሎችን የበርካታዎችን ህይወት ለማሻሻል ሲሰራ፣ ወይም በኢፍትሀዊነት ላይ ሲያምጽ፣ የተስፋ ፍንጣቂዎችን ያሰራጫል፣ እናም እነዚህ የተስፋ ፍንጣቂዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የተለያዩ የኃይል እና የድፍረት ማዕከሎችን ሲያቋርጡ የጭቆና እና የተግዳሮት ዋና ኃይል የሆነውን ኃይለኛውን ግንብ ሊደረምስ የሚችል የፍንጣቂ ኃይል ይገነባል፡፡“
በአፍሪካ ውስጥ የሚፈጸሙትን እልቂቶች ማስታወስ ያለብን ለምንድን ነው?
በአምባገነኖች የሚፈጸሙ እልቂቶች አብዛኛውን ጊዜ የአምባገነኖቹ ደካማነት፣ ለአደጋ ተጋላጭነት እና የህዝባዊ አመጽን የመፍራት መገለጫዎች ናቸው፡፡
ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን የጥቂት ነጮች የበላይ የዘር አገዛዝ ያወጣውን ዘረኛ ሕግ በመጣስ ለተፈጸሚነቱ አንገዛም በማለት የሻርፕቪልን የፖሊስ ጣቢያ ጥሰው ባለፉ ጊዜ እነዚህ ህዝቦች ምንም ዓይነት ፍርሀት እንደሌለባቸው እና ማንኛውንም ዓይነት መስዋዕትነት የሚያስከፍል ሁኔታ ቢመጣም እንኳ አንገታቸውን እንደማያጥፉ ለጥቂት ነጮች የበላይ ዘረኛ አፓርታይድ አገዛዝ ግልጽ የሆነ መልዕክት ያስተላለፉ መሆናቸውን ያመላክታል፡፡
የጥቂት ነጮች የበላይ ዘረኛ የአፓርታይድ አገዛዝ የሻርፕቪሌ አመጾች በመላ ሀገሪቱ ውስጥ ይስፋፋሉ ብሎ በፍርሀት ቆፈን ውስጥ በመወሸቅ አመጸኞቹ ከጉልበታቸው ስር ያንበረክኩኛል በሚል ስጋት ውስጥ ወድቆ ነበር፡፡
የጥቂት ነጮች የበላይ ዘረኛ የአፓርታይድ አገዛዝ ጥቁር አፍሪካውያን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወታደራዊ የበላይነትን ሊቀዳጁ ይችላሉ ብሎ አልነበረም ይፈራ የነበረው፡፡ የእነርሱ ታላቁ ፍርሀት የነበረው ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ከኃይል ነጻ የሆኑ ሰላማዊ ትግሎችን፣ የሰራተኞች የስራ ማቆም አድማዎችን፣ ሙሉ የስራ አቅምን አለመጠቀምን እና ምርት መቀነስን፣ ኃይል ያልተቀላቀለባቸው መገዳደሮችን መፈጸምን፣ የመንገድ ላይ አመጾች እና ጉዞዎችን ማድረግን፣ ከህንጻዎች ውጭ የተቃውሞ አመጾችን ማካሄድን፣ ተጠቃሚዎች የሚመረቱ ምርቶችን አለመጠቀም እና የመሳሉትን ነገሮች ነበር፡፡
ዘ-ህወሀትም የጥቂት ነጮች የበላይ ዘረኛ የአፓርታይድ አገዛዝ እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ እና በ1980ዎቹ ሲያደርግ እንደነበረው ሁሉ እርሱም በተመሳሳይ ድርጊት ላይ ተጠምዶ ይገኛል፡፡
ሆኖም ግን የዘ-ህወሀት መሪዎች የጥቂት ነጮች የበላይ ዘረኛ የአፓርታይድ አገዛዝ መሪዎች ለብዙሀኑ በመገዛት ስምምነት በማድረግ ቀልጣፎች በመሆን የተደላደለውን ኑሯቸውን በሰላማዊ መንገድ ሲገፉ እንደነበሩት ሊሆኑ ስለማይችሉ በዘ-ህወሀት መጨረሻ ላይ ስጋት አለኝ፡፡
እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ ለዘ-ህወሀት ከባድ እና እሾሀማ ይሆናል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ውስጥ ለሚፈጸሙ እልቂቶች ተጠያቂ ያለመሆን ጉዳይ መቆም አለበት!
የሻርፕቪልን እና የአምባገነኑን መለስ እልቂቶች እና ሌሎችን በርካታዎችን የሀገር ክዳት ወንጀሎች ማስታወስ ዋናው እና የመጀመሪያው ጉዳይ በአፍሪካ በሰው ልጆች ላይ ወንጀሎችን በሚፈጽሙ ወሮበላ ዘራፊዎች ላይ ከእንግዲህ ወዲያ የወንጀል ተጠያቂነት መኖር እንዳለበት ለማረጋገጥ እንዲቻል ነው፡፡ ይህም ሲባል እስከ አሁን ድረስ በሰው ልጆች ላይ በተፈጸሙት ወንጀሎች ላይ ተጠያቂነት አይኖርም ለማለትም አይደለም፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡
እ.ኤ.አ በ1994 የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል በተፈጸመ ጊዜ አብዛኛው የዓለም ህዝብ ጸጥ ብሎ ይመለከት ነበር፡፡ ያ አስከፊ የሆነ የዘር ፍጅት ከተፈጸመ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ፕሬዚዳንት ክሊንተን እንዲህ ብለው ነበር፣ “በወቅቱ አስቸኳይ የሆነ እርምጃ ብንወስድ ኖሮ ቢያንስ ያለቀውን ህዝብ አንድ ሶስተኛ ያህል ህወይወት ማትረፍ እንችል ነበር… እንዲህ ዓይነቱ ነገር ተፈጻሚነት ቢኖረው ኖሮ ለእኔ ጽናት ያለው ፋይዳ ሊያመጣ እንደሚችል ይሰማኛለል፡፡“
የሩዋንዳን የዘር ማጥፋት ፍጅት ለመከላከል ምንም ዓይነት እርምጃ ባለመወሰዱ ምክንያት እ.ኤ.አ በ2003 በሱዳን በዳርፉር ተመሳሳይ ዓይነት የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጸመ፡፡ የኦማር አልባሽር አገዛዝ አረባዊ ደም በሌላቸው እና በዳርፉር በሚኖሩ የሱዳን ዜጎች ላይ መጠነ ሰፊ የሆነ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመፈጸም ቢያንስ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ንጹሀን ዜጎች እንዲገደሉ አድርጓል፡፡
የዓለም ህዝብ ለአልባሽር እልቂት ነጻ የይለፍ ካርድ በመስጠቱ ምክንያት አምባገነኑ መለስ ዜናዊ እና ዘ-ህወሀት እ.ኤ.አ በ2005 ተካሄደ የተባለውን የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ ተከትሎ ተፈጥሮ በነበረው ውዝግብ በመቶዎች በሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎች ላይ እልቂት ፈጽመዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ዘ-ህወሀት ያንን ገዳይ የሆነ ባህሉን በበለጠ ደረጃ ቀጥሎበት ይገኛል፡፡
የዓለም ህዝብ ለአምባገነኑ መለስ ዜናዊ እልቂት የይለፍ ካርድ በመስጠቱ ምክንያት እ.ኤ.አ በ2007 ኡሁሩ ኬንያታ እና ግብረ አበሮቹ ወንጀለኛ የማፊያ ድርጅትን በመጠቀም ከ2007 ምርጫ በኋላ በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት/ICC ዋና አቃቤ ሕግ ክስ የተመሰረተበት ኬንያታ በንጹሀን ህዝቦች ላይ እልቂትን ፈጽሟል፡፡ በኬንያታ ላይ ICC የመሰረተበት የወንወጀል ክስ እንዲቋረጥ ተደርጎ እጁ በደም የተጨማለቀው ወንጀለኛ ደረቱን ነፍቶ በመንገዳወል ላይ ይገኛል፡፡
የሻርፕቪልን እና የአምባገነኑን መለስ እልቂቶች እና ሌሎችን በርካታዎችን የሀገር ክዳት ወንጀሎች ማስታወስ ሁለተኛው ዋና ጉዳይ “የአፍሪካ እልቂት መርሳት” እና “የኢትዮጵያ እልቂት መርሳት” እያልኩ የምጠራውን የቡድን እልቂት መርሳትን ለመዋጋት ነው፡፡ ለእኔ በአጠቃላይ አፍሪካውያን በእራሳቸው ላይ የተፈጸሙትን ሰብአዊ ወንጀሎችን የማስታወስ ዝንባሌ እያስወገዱ ያሉበት ሁኔታ መስሎ ይታየኛል፡፡ በእርግጥ ማስታወሱ እጅግ በጣም የሚያም ጉዳይ ነው፡፡
በአንድ ወቅት ስለአምባገነኑ መለስ እልቂት ሁልጊዜ ለምን እንደምናገር የእራሴ መልካም ጓደኛ ጠይቆኝ ነበር፡፡ ስለሞተው መለስ ለምን ትናገራለህ? ጓደኛዬ ይኸ ጉዳይ “ልቆጣጠረው የማልችለው እና በአእምሮየ ውስጥ ያለ ሀሳብ” እንደሆ አድርጎ ቆጠረኝ፡፡ ይኸ አንዴ የተደረገ ያለፈ ጉዳይ ነው፡፡ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ስለዚያ ነገር መርሳት እንዳለብኝ፣ ቢያንስ ሁልጊዜ ማስታወስ እንደሌለብኝ እና ወደ ሌላ ነገር መሄድ እንዳለብኝ ይነግረኝ ነበር፡፡ ይህንን ዓይነት አመለካከት ሊጋሩ የሚችሉ ሌሎችም ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ እርግጠኛ ነኝ፡፡
እንዲህ የሚለውን የሸክስፒርን ብልህ ምክር ለጓደኛየ ላካፍለው እችላለሁን? “ሰይጣናዊትን የሰሩ ሰዎች ከሞቱ በኋላም ቢሆን ሰይጣዊው ድርጊታቸው ይኖራል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ መልካሙ ነገር ከአጥንታቸው ውስጥ አብሯቸው ይቀበራል፡፡“
አምባገነኑ መለስ ዜናዊ በህይወት ባይኖርም ቅሉ ሰይጣናዊ ድርጊቱ ግን አሁንም አብሮን በመኖር ላይ ይገኛል፡፡ ያ ሰይጣናዊነት ድርጊት ህይወት ዘርቶ መልካም ነገር ባይሆንም እንደ ኮሶ ትል የዘ-ህወሀትን ስብዕና ተጣብቶ አብሮ በመኖር ላይ ይገኛል፡፡
አምባገነኑ መለስ ዜናዊ በእርሱ አሻንጉሊት ፍጡር በሆነው በኃይለማርያም ደሳለኝ እምነት መሰረት አልሞተም በህይወት ነው ያለው፡፡
ኃይለማርያም ደግሞ እና ደጋግሞ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይደረግበት የአምባገነኑን የመለስ ዜናዊን ትሩፋት ለማስቀጠል እያለ እንደ በቀቀን ሁልጊዜ እንደ መዝሙረ ዳዊት ይደግመዋል፡፡ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይደረግ ያ ትክክለኛ እንደሆነ አድርጎ ይለፈልፋል፡፡
በኃይለማርያም ደሳለኝ ቁሳዊ አካል እና መንፈስ ውስጥ የዘ-ህወሀት ትንሹ አምላክ አምባገነኑ መለስ ህያው ሆኖ ይኖራል፡፡
አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ለዘ-ህወሀት እና ለእርሱ ያልተቀደሱ ፍጡሮች ሁሉ እንደ ክርስቶስ ለሁለተኛ ጊዚ ተመልሶ ይመጣል፡፡
ዘ-ህወሀት በህይወት እስከኖረ ድረስ አምባገነኑ መለስ ዜናዊም በህይወት መኖሩን ይቀጥላል፡፡
በመቶዎች እና በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች ማጎሪያ የሆነው እስር ቤት እስካለ ድረስ አምባገነኑ መለስ ዜናዊም በህይወት መኖሩን ይቀጥላል፡፡
ዘ-ህወሀት ኢትዮጵያን የግሉ መዝናኛ ሆቴል (ወሲባዊ ቱሪዝም አላልኩም) እና የመጫወቻ ማድረጉን እስካላቆመ ድረስ አምባገነኑ መለስ ዜናዊም በህይወት መኖሩን ይቀጥላል፡፡
የአምባገነኑ መለስ ዜናዊ የጥቃት ሰለባዎች የሆኑት የእኔ ጓደኞች እናት፣ አባት፣ እህት፣ ወንድም፣ ዘመዶች እና ጓደኞች መሆናቸውን ጓደኛዬ ቢሆኑ ኖሮዝም በል ይለኝ ነበር ፡፡ አንዲህስ ለማለት ይችላል- “ስማኝ የእኔ ቤተሰቦች በአምባገነኑ መለስ እና በእርሱ ዘ-ህወሀት ተጨፍጭፈዋል ምን ይደረግ ያለፍ ነገር ነው ተዋቸው እርሳው ሁሉንም ነገር፡፡
የእኔ መልስ እንዲህ የሚል ቀላል ጥያቄ ነው፡ በአምባገነኑ መለስ ዜናዊ እና በዘ–ህወሀት እልቂቶች የጥቃት ሰለባ ለሆኑ ወገኖቼ እኔ ካልተናገርኩ ከቶ ማን ሊናገርላቸው ነው? እኮ ማ? ንገረኛ ምስኪኑ ጓደኛዬ!
ለነገሩ ግን ማናቸዉም ሰው የእራሱን ውክልና እራሱ በመያዝ በግፍ ስለተገደሉት ወገኖች መናገር ቢጀምር እኔ ራሴ ዝም እላለሁ፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ሁልጊዜ ሰኞ ሰኞ የአምባገነኑ መለስ የጥቃት ሰለባዎች ድምጽ ሆኘ መዝለቁን አጠናክሬ እቀጥልበታለሁ፡፡
ሆኖም ግን እኔ እየተከራከርኩለት ያለው መሰረታዊ መርህ ምንም ዓይነት ማስታወስ ሳይኖር ወንጀሎችን በፈጸሙት ወንጀለኞች ላይ ምንም ዓይነት ተጠያቂነት አይኖርም የሚል ነው፡፡ ተጠያቂነት ሳይኖር አንድ ዓይነት ሰብአዊ ወንጀሎች በየጊዜው ደግመው እና ደጋግመው ይፈጸማሉ፡፡
እንግዲህ በአፍሪካ ውስጥ የሚፈጸሙ እልቂቶች እና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ታሪክ ይህንን ይመስላል፡፡ ምንም ዓይነት ተጠያቂነት የማይኖር ከሆነ በየዕለቱ እልቂቶች ይፈጸማሉ፡፡
ሁሉም አፍሪካውያን የወሮበላ ዘራፊ አምባገነን አገዛዞች ሰለባ በሚሆኑበት ጊዜ ለወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው በግዴለሽነት ዝም ብለው መመልከት ሳይሆን ስለእነርሱ ሆነው የመናገር እና የማስታወስ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በአፍሪካ እልቂቶች ዘወትር ይፈጸማሉ፣ እናም ስለእነዚህ እልቂቶች ደጋግሞ ማንሳቱ ቂልነት ነው ብለው እራሳቸውን የሚያታልሉ ሰዎች አሉ፡፡ ደንታቢሶች!
እልቂቶች የአጋጣሚ ድርጊቶች እና ክስተቶች ናቸው በማለት አቅልሎ መናገር ይቻላል፡፡
ለተከታታይ ስቃዮች የሚዳረጉ ሰዎች፣ በተከታታይ ሰብአዊ መብቶቻቸው የሚደፈጠጡባቸው ሰዎች ያለፈውን ከማስታወስ ይልቅ እንደሚረሱ እገነዘባለሁ፡፡ ማስታወስ እጅግ በጣም የሚያም ነገር ነው፡፡ የእልቂት ክስተቶችን መርሳት ወይም ደግሞ ለመፈጸማቸው መጠራጠር የበለጠ ቀላል ነገር ነው፡፡
የብዙሀን አፍሪካውንን እልቂቶች የመርሳት እና የኢትዮጵያውንን እልቂቶች የመርሳት ባህል እንዲኖር መፍቀድ በወጣቱ ትውልድ እና ወደፊትም በሚመጣው አዲሱ ትውልድ ላይ ወንጀልን መስራት ማለት ነው፡፡
የአፍሪካ ወጣት ሰዎች ክብረ ቢስ የሆነውን “ታላቅ ኃይል እውነታን ያመጣል“ የሚለውን የብሂል ባህል ማውገዝ አለባቸው፡፡ እውነት ብቻ፣ የፍትህ የበላይነት እና ፍትሀዊ ሕጎች ብቻ እውነትን ያስገኛሉ፡፡
የሕግ ባህልን ለማጎልበት የአፍሪካ ወጣቶች የአፍሪካ ወሮበላ የዘራፊ አገዛዝ ወንጀሎች አሁኑኑ እንዲቆሙ ማድረግ እና ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ማስታወስ እና እንዲታወሱ ማድረግ አለባቸው!
ባለፉት ጊዚያት በአፍሪካ ውስጥ በወሮበላ ዘራፊ አገዛዞች የተፈጸሙ እልቂቶች ጠንካራ በሆነ ታሪካዊ ትንታኔ እየታገዙ መመርመር እና ለመጭው ትውልድ ትምህርት እንዲሆን እና ለሁለተኛ ጊዜም እንዳይደገሙ ማረጋገጫ መሰጠት አለበት፡፡
ለዚህም ነው ወጣት አፍሪካውያን በአፍሪካ አህጉር ውስጥ እየተፈጸሙ ስለነበሩት ስለሻርፕቪል እልቂት፣ ስለኪቤራ እና ስለአምባገነኑ መለስ እና ስለሌሎችም እልቂቶች ማስታወስ እና መማር ያለባቸው፡፡
እነዚህን የተንሰራፉ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣዎች ዋና መንስዔዎች መገንዘብ እና የጥቃት ሰለባዎችን ትውስታ ማስቀጠል የወደፊቱ ትውልድ እልቂቶችን መከላከል እንዲችል ለማገዝ ጠንካራ መሳሪያ ነው፡፡
አልበርት ኤንስታይን በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ “ዓለም ለመኖሪያነት እጅግ በጣም አደገኛ ቦታ ናት፣ ይህም የሆነው ሰይጣናዊነት ስራን በሚሰሩ ሰዎች ምክንያት ብቻ አይደለም፣ ሆኖም ግን ስለእነዚህ ሰይጣናዊ ድርጊቶች ምንም ሳያደርጉ እጆቻቸውን አጣጥፈው በመቀመጥ በሚመለከቱ ሰዎች ጭምር እንጅ፡፡“
ከዚህ ጋር አንድ ዓይነት በሆነ መልኩ አፍሪካ በተንሰራፉ ሰብአዊ ወንጀሎች፣ በዘር ማጥፋት ወንጀሎች እና በጦር ወንጀሎች ለመኖሪያነት እጅግ በጣም አደገኛ የሆነች አህጉር ናት፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ሰይጣናዊ በሆኑ ወሮበላ ዘራፊ አምባገነኖች ምክንያት ብቻ አይደለም፣ ሆኖም ግን በዋናነት በቂ የሆኑ በጎ ነገር አሳቢ የአፍሪካ ሰዎች በተለይም ወጣቶች (እና የአፍሪካ ጓደኞች) በአንድ ላይ በጽናት በመቆም መናገር በማይችሉ እና በአህጉሩ ውስጥ ስለጅምላ የሰብአዊ መብት ረገጣው ምንም ዓይነት ድርጊት በማይፈጽሙ ሰዎች ጭምር እንጅ፡፡
በደቡብ አፍሪካ ውስጥ እ.ኤ.አ መጋቢት 21/1960 በሻርፕቪሌ የተፈጸመውን እልቂት አስታውሳለሁ፡፡
በደቡብ አፍሪካ ውስጥ እ.ኤ.አ ነሀሴ 16/2012 በማራኪና የተፈጸመውን እልቂት አስታውሳለሁ፡፡
በኬንያ ውስጥ እ.ኤ.አ ታህሳስ 2007 እና ጥር 2008 በኪቤራ የተፈጸሙትን እልቂቶች አስታውሳለሁ፡፡
በሩዋንዳ እና በሱዳን ዳርፉር ውስጥ የተፈጸሙትን የዘር ማጥፋት እልቂቶች አስታውሳለሁ፡፡
በአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች በአፍሪካ ውስጥ በአፍሪካውያን ላይ የተፈጸሙትን እልቂቶች አስታውሳለሁ፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ እ.ኤ.አ ሰኔ 8/2005 እና ከሕዳር 1-10 እና ከ14-16 በአምባገነኑ መለስ የተፈጸሙትን እልቂቶች አስታውሳለሁ፡፡
እነዚህን እልቂቶች በማስታወሱ ረገድ ከእኔ ጋር ልትቀላቀሉ አትችሉምን?
የአፍሪካውያን ህይወቶች ጉዳዮቼ ናቸው! የአፍሪካውያን ህይወቶች ጉዳዮቼ ናቸው! የአፍሪካውያን ህይወቶች ጉዳዮቼ ናቸው!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
መጋቢት 6 ቀን 2008 ዓ.ም