ዘ-ህወሀት በኢትየጵያ የታክሲ ሾፌሮች ላይ የከፈተው ጦርነት!

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም  

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

Taxi drivers pixበአሜሪካ “ባለሶስት-ጥፋት ሕግ“ እያሉ ይጠሩታል፡፡ ወንጀለኞች ሶስት ከባድ ወይም ደግሞ አስከፊ ወንጀሎችን የሰሩ ከሆነ ከ25 ዓመት እስከ እድሜ ልክ እስራት የሚያደርስ ቅጣት ይበየንባቸዋል፡፡

ዘ-ህወሀት በኢትዮጵያ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች ላይ ጦርነት አውጇል!

በኢትዮጵያ የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ህወሀት) ለሶስት ወር ተራዝሟል የሚል ሽንገላ ያስቀመጠለትን እና አንድ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌር ሶስት ተከታታይ ጥፋቶችን ከፈጸመ ከታክሲ ማሽከርከር ስራው የመንጃ ፈቃዱን ተነጥቆ ይሰናበታል በማለት ከእጅ ወደ አፍ በሆነች ገቢ ኑሯቸውን በመግፋት ትግል እያደረጉ ባሉት አሽከርካሪዎቸ ላይ የሚተገበር “ሕግ” አውጥቷል፡፡ የትራፊክ ሕግ ደንብን በመጣስ 20 ወይም ከዚያ በላይ ነጥብ የተያዘባቸው የታክሲ አሽከርካሪ ሾፈሮች ለዘላለሙ ከታክሲ አሽከርካሪነት ሙያው ይሰናበታሉ፡፡

እንደ አዲስ ስታንዳርድ ድረ ገጽ ዘገባ ከሆነ “የዘ-ህወሀት አዲሱ የትራፊክ ቁጥጥር ደንብ ስድስት የቅጣት ደረጃዎችን አካትቶ የያዘ ሲሆን የትራፊክ መብራት ጥፋትን ጨምሮ ሁለት ነጥብ በመቀነስ ይጀምር እና ተሽከርካሪን አለአግባብ ማቆም እና ከታክሲው የመጫን አቅም በላይ ተሳፋሪን ጭኖ የመገኘት በመሳሰሉት ጥፋቶች ላይ የቅጣት ዝርዝሩን አቅርቧል፡፡ ደንቡ ቀደም ሲል ከ14 – 16 የጥፋት ነጥቦች  የተያዘባቸውን አሽከርካሪዎች የመንጃ ፈቃድ በመንጠቅ ለስድስት ወራት ከስራ ገበታ ውጭ እንዲሆኑ የሚያደርግ እንደሆነ ይጠበቃል፡፡ ከ17 – 19 ነጥብ የተያዘበት/ባት አሽከርካሪ መንጃ ፈቃዱ/ዷ ለአንድ ዓመት ያህል እንዲነጠቅ ይደረጋል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ማንኛውም አሽከርካሪ 20 እና ከዚያ በላይ ነጥብ የተያዘበት ከሆነ መንጃ ፈቃዱ ለዘላለሙ ይነጠቅ እና ውሳኔው ከተሰጠበት ከሁለት ዓመታት በኋላ እንደ አዲስ እንደገና መንጃ ፈቃድ ለማግኘት ሊያመለክት ይችላል” ይላል፡፡

ዘ-ህወሀት 500 ወይም ከዚያ በላይ ብዛት ላላቸው የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች ስለአዲሱ የትራፊክ ቁጥጥር ደንብ ገለጻ ካደረገ በኋላ ያንን ሕግ “ወይም ሌላ” እንዲከተሉ እና ተግባራዊ እንደሚያደርግ ይፋ አድርጓል!

“ወይም ሌላ” የሚለው ተቀጽላ ቃል የቀረበው አሽከርካሪዎቹ ወደዱም ጠሉ አዲሱ ሕግ በዘ-ህወሀት ጉሮሯቸውን ተይዘው በግድ ተግባራዊ እንደሚደረግ ለተሰባሰቡ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች ሲናገር እና ሲያስፈራራ በነበረው በስም አሰፋ መዝገቡ በተባለ የዘ-ህወሀት ታዛዥ ሎሌ ነው፡፡ ዛቻዉን ሲጥል አሰፋ መዝገቡ  ዓይኑንም አላሸም!

በታክሲ አሽከርካሪዎች ላይ የተደረገው የመዝገቡ የጦርነት እወጃ ቅጽበታዊ የሆነ ግጭትን አስከትሏል፡፡ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች እጅግ በጣም ተቆጥተው ነበር፡፡ እ.ኤ.አ የካቲት 22/2016 የስራ ማቆም አድማ መቱ፡፡ የከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ሽባ ሆኖ ውሏል፡፡ በዕለቱ የአዲስ አበባ ኗሪዎች በየቦታው በእግር ሲቋትኑ/በእግር ጉዞ ሲውተረተሩ ተስተውለዋል፡፡ ዘ-ህወሀት አዲሱ ሕግ ለ90 ቀናት ያህል ተግባራዊ ሳይደረግ እንደሚቆይ አሳውቋል፡፡ በሚቀጥለው ዕለት የታክሲ አሽከርካሪዎች ወደ መደበኛ ስራቸው ተመለሱ፡፡

እንደ አንድ ዘገባ ከሆነ አዲስ አበባ በ7,500 ሰማያዊ እና ነጭ ቅብ ባላቸው ሚኒባስ ታክሲዎች፣ በዘ-ህወሀት ቁጥጥር ስር ባለው እና በአንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ስር በሚተዳደሩ በ800 አውቶብሶች፣ በ500 ሀይገር መካከለኛ አውቶብሶች፣ በአሊያንስ የትራንስፖርት አገልግሎት ኩባንያ ባለአክሲዮኖች የግል ንብረትነት በሚተዳደሩ በ25 አውቶብሶች፣ በ4,000 ነጭ ሚኒ ባሶች እና በ400 ሀገር አቋራጭ አውቶቶብሶች እየታገዘ የሚካሄድ አገልግሎት አላት፡፡

እጅግ በጣም የተቆጣ  አንድ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌር እንዲህ የሚል ቃለመጠይቅ ሰጥቷል፡

“የስራ ማቆም አድማው ቅጽበታዊ መነሻ ምክንያቱ አዲሱ የትራፊክ ሕግ ቢሆንም ቅሉ ዋናው እና ቁጥር አንድ የሆነው ምክንያት ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ በተለያዩ አጋጣሚዎች የመንግስት ባለስልጣኖች ስልጣናቸውን ከሕግ አግባብ ውጭ በመጠቀም የተሳሳቱ ሕጎችን እየተገበሩ የታክሲ ሾፌሮችን የተጎጅነት ሰለባ እንዲሆኑ እያደረጉ በመምጣታቸው ምክንያት ነው፡፡ ለዚህም ነው ህብረተሰቡ የእኛን የስራ ማቆም አድማ ደግፎ የወጣው፡፡ ህብረተሰቡ በሀገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ችግር እንዳለ ያውቃል፡፡ የፍትህ እጦት ተንሰራፍቷል፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት ችግር ህዝቡን እጅ ከወርች ጠፍንጎ ይዟል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ማንኛውም የህወሀት አባል የፈለገውን ነገር ማድረግ ይችላል፣ አንድን የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌር በቁጥጥር ስር ማዋል እና ማሰር ይችላል፡፡ የታክሲ ሾፌሩን ወደየትም ወደሚፈልገው ቦታ እንዲያሽከረክር ሊያዝዘው ይችላል፡፡ ይህ የስራ ማቆም አድማ እንቅስቃሴ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች መብታቸውን ለመጠየቅ ያደረጉት ሙከራ ነው፡፡ ህወሀት እና ኢህአዴግ (እውነተኛውን የህወሀትን ማንነት ለመደበቅ ሲባል ለህወሀት መጠቀሚያ ሲባል የተቋቋመ ግንባር) የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮችን በማስፈራራት የስራ ማቆም አድማውን ለማጨናገፍ ጥረት አድርገዋል፡፡ በአዲሱ ሕግ አንድ ጥፋት 7 ነጥቦችን ያስይዛል፣ እናም አንድ ሾፌር 20 ነጥቦች ከተቆጠሩበት ሙሉ በሙሉ ህልውናውን እንዲያጣ በማድረግ ከስራው ይታገዳል፡፡ እነርሱ [ህወሀቶች] የአሽከርካሪ ሾፌሮችን መንጃ ፈቃዶች መንጠቅ እንደሚችሉ፣ የታክሲዎቻቸውን ሰሌዳዎች በመፍታት እና ከዚህም አልፎ ተሸከርካሪዎችን ለመቀማት እንደሚችሉ ለማስፈራራት ሙከራ አድርገዋል፡፡ ሆኖም ግን የፈለገውን ያህል ለማስፈራራት ጥረት ቢያድርጉም 99.9 በመቶ የሚሆኑት የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች ያለምንም ፍርሀት የስራ ማቆም አድማውን ተቀላቅለዋል…“ ብሏል፡፡

ዘ-ህወሀት የግል የትርንስፖርት ዘርፉን ለማሽመድመድ ሲያደርገው የቆየው ይህ የመጀመሪያ ጊዜው አይደለም፡፡

እ.ኤ.አ ነሐሴ 2014 መኪና ወደ ሀገር ውስጥ በሚያስገቡት እና በሚያከፋፍሉት ሰዎች ላይ (በእርግጥ የዘህወሀት አጫፋሪዎች ከግብር ጫናው ነጻ ናቸው) ከፍተኛ የሆነ ግብር ቆለሉባቸው፡፡

አንድ መኪና አከፋፋይ የሆነ ነጋዴ በድንገት በወጣው የጉምሩክ ሕግ መሰረት ልክ በድንገት ቅጽበታዊ በሆነ መልኩ እንደወጣው የትራፊክ ደንብ ሁሉ ቀደም ሲል በተከታታይ በ5 ዓመታት ውስጥ በአንድ መኪና ላይ ይጣል የነበረው ሁሉም ግብሮች/sundry tax 134,000 ብር የነበረ ሲሆን እ.ኤ.አ በ2014 ለተመሳሳይ ግብይት በ183.6 በመቶ በማሳደግ ብቻ ሳይሆን በመቆለል ብር 380,000 እንዲከፍል ዱብ ዕዳ ሆኖ ተጣለበት፡፡ መኪና አከፋፋዩ 35 በመቶ የጉምሩክ ግብርን ጨምሮ፣ 10 በመቶ የሱር ታክስ ግብር፣ 100 በመቶ የኤክሳይስ ታክስ ግብር፣ 15 በመቶ የተጨማሪ እሴት ታክስ ግብር እና 3 በመቶ ዊዝሆልዲንግ ታክስ ግብር በመክፈል እንደዚህ ያሉትን በርካታ የግብር ዓይነቶች እንዲከፍል በመዳረጉ ቅሬታውን ለዘ-ህወሀት አቀረበ፡፡

ዘ-ህወሀት በሕገወጥ መልክ የሚሰበስበውን እና ግብር እያለ በሚጠራው በዜጎች ሊከፈል በማይገባው ሕግን ያልተከተለ የገንዘብ ዘረፋ ላይ እጅግ ከመጠን በዘለለ መልኩ ደስታ እና ሀሴትን ተጎናጽፎ ይገኛል፡፡

የዘህወሀት የባለሶስት ጥፋት እና ከታከሲ ማሽከርከር ስራ ላይ የማባረር ሕግ በእርግጠኝነት ዓላማው ስለምንድን ጉዳይ ነው?  

የዘ-ህወሀት የባለሶስት ጥፋት እና የታክሲ ስራህን በማቆም ከንግድ ዘርፉ ዘወር በል ቻው በማለት ዘ-ህወሀት በአሁኑ ጊዜ እየፈጸመ ያለው ሕገ ወጥ ድርጊት ዘ-ህወሀት ቀደም ሲል ጀምሮ በህዝቦች ላይ ሲሰራ የቆየው የረቀቀ ሸፍጥ እና ደባ አንዱ ተቀጽላ አካል እንደሆነ እገነዘባለሁ፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ዘ-ህወሀት የሕክምና ቱሪዝም/Medical tourism የሚል የወሲብ ቱሪዝምን የሚያስፋፋ አስፈላጊ ያልሆነ ውሳኔ ለማስተላለፍ ሞክሯል፡፡

አዎ፣ ዘ-ህወሀት በመካከለኛው ምስራቅ ከሚገኙ እና የወሲብ ስራ ሀራራ ከሚያናውዛቸው በዘ-ህወሀት አጠራር አልሚ ተብየ አጥፊዎች ከካታር ጋር በኢትዮጵያ ውስጥ ግዙፍ የሆነ የዝሙት ማሳደጃ ማዕከል እና እንደዚሁም ደግሞ የሕክምና ቱሪዝም/Medical tourism ገንቢዎች እያለ ከሚጠራቸው ጋር የውል ስምምነት አድርጓል፡፡

የዘ-ህወሀት ወሮበላ ዘራፊዎች እኛን ሊያታልሉ እንደሚችሉ አድርገው ያስባሉ፣ ሆኖም ግን ሳይሳካላቸው ቀርቶ ሙሉ በሙሉ ከስረዋል፡፡ እኛ ነቂቶ ካልን ቆይተናል፣ እናም ከንቱ ድካም እና የተበላ እቁብ ነው፡፡

የዘ-ህወሀትን ሸፍጠኛ የቡድን መንግስታዊ ማሽንን የሚያንቀሳቅሱት በጣም ጥቂት ስብስቦች ቡድንን ያካተተ እጅግ በጣም አታላዮች፣ ድብቆች፣ አጭበርባሪዎች፣ ተደጋጋሚ ሸፍጥ ሰሪ መሰሪዎች፣ ሰይጣናዊ ድርጊት ሰሪዎች፣ ጨካኝ እና አረመኔዎች፣ አውዳሚዎች፣ አደገኞች፣ ጽልመተኞች እና የማኪቬሌያንን የፖለቲካ ፍልስፍና የሚያራምዱ በዓለም ላይ በሁሉም ቦታ የሚገኙ ሰው መሰል ሰይጣኖች ያሉበት መሆኑን ሁልጊዜ ስናገር ቆይቻለሁ፡፡ በሁሉም አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ጡንቻማ ሸፍጠኞች ናቸው፡፡

የዘ-ህወሀት ሸፍጠኞች እንደገና ለማታለል፣ የበለጠ ለማጭበርበር፣ ለማሞኘት፣ ለማጦዝ፣ የበለጠ ለማታለል እና ተቃዋሚዎቻቸውን ለማጥፋት ብቅ ያሉ ለመሆናቸው አምናለሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን የጥፋት በትራቸውን ለማሳረፍ እየታገሉ ያሉት በታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች ላይ ነው!

ለመናገር የምጠላው ነገር ቢሆንም በእርግጥ ለእኔ አብዛኞቹ የስራ ማቆም አድማ የመቱት የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች በጫካው ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን ዛፍ ለመመልከት አይችሉም፡፡

ትልቁን ስዕል እያዩት አይደለም፡፡

በዘ-ህወሀት “አዲሱ የትራፊክ ደንብ”  እየተባለ በሚጠራው የድብብቆሽ ጨዋታ ሀሳባቸው እንዲቀለበስ ተደርጓል፡፡

የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች በዘ-ህወሀት የውሸት የማስመሰያ ወጥመድ ውስጥ ወድቀዋል፡፡

የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች ተታለዋል፣ እናም ተጭበርብረዋል፣ ሆኖም ግን ነገር በግልጽ አይታያቸውም፡፡ ምን ዓይነት አሳዛኝ ድርጊት ነው እባካችሁ!!!

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን እያሉ የሚጠሩትን እንዛዝላ በአዲስ አበባ ዙሪያ አካባቢ በሚገኙ አርሶ አደሮች ላይ በመጫን ለማታለል ሙከራ አድርገዋል፡፡

አሁን በቅርቡ ባዘጋጀሁት ትችቴ በግልጽ ለማመላከት እንደሞከርኩት የአዲስ አበባ ሳይሆን የዘህወሀት ማስተር ፕላን ነበር፡፡ የዘ-ህወሀት ሆዳሞች እና የመሬት ዘረፋን በማካሄድ የማይረካ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሌት ቀን የሚቋምጡት ወሮበላ ዘራፊዎች ለዕኩይ ዓላማቸው ስኬታማነት በድብቅ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን እያሉ በሚጠሩት ስም ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ዘ-ህወሀት በከተማዋ ዙሪያ ያለውን እያንዳንዷን ስንዘር መሬት ከወሰደ በኋላ በቀጣይነት ደግሞ ከከተማዋ በመውጣት የተለመደ እና ተመሳሳይ ዘረፋውን ይቀጥላል፡፡

ሆኖም ግን በደፋር ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት እና ተጋድሎ የዘ-ህወሀት ቀልደኛ/ኮሚኮች ገሀነም እንዲገቡ እና በዚያው እንዲቆዩ በማድረግ ታግደዋል፡፡ የዘ-ህወሀት ቦቅቧቆች እንደዚህ ያለ ዕቅድ አልነበረም፣ እንዲያው ስለዚያ ነገር የሚብላላ ሀሳብ ብቻ ነበር ያለው በማለት ዓይኔን ላፈር በማለት ቅጥፍናቸውን ለቀውታል፡፡ ወቼ ጉድ፣ ወይ ነዶ!

በአሁኑ ጊዜ ደግሞ መልኩን በመቀየር የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮችን የጥቃት ሰለባ ለማድረግ ተመሳሳይ ሸፍጡን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ሆኖም ግን ደፋር በሆኑ ኢትዮጵያውያን የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች አማካይነት የዘ-ህወሀት ፈጣጣ ኮሚኮችን ገሀነም ግቡ ብለዋቸዋል፡፡ ዘ-ህወሀት የአዲሱን የትራፊክ ደንብ ተግባራዊነት ለ90 ቀናት አራዝሜዋለሁ ብሏል፡፡ ሆኖም ግን ሾፌሮች እንዳትሞኙ አንዳተኙ ፡፡ ህወሀት ለጊዜው ጸጥ ያለ መስሎ ይቆይ እና እንደ ቀሳፊው የድርቅ አደጋ ተመልሶ ዘው ብሎ ይመጣል፡፡

እኔ ባለኝ መረጃ መሰረት እና እንደማስበው ከሆነ ዘ-ህወሀት አዲሱ የትራፊክ ደንብ እያለ የሚጠራው ደንብ የትራፊክ ሁኔታውን ለማሻሻል አስቦ አይደለም፡፡

መጨናነቅን ለመቀነስ ታስቦ አይደለም፡፡

እንደዚሁም ደግሞ የትራንስፖርት ዘርፉን ቅልጥፍና ለማሻሻል ታስቦም አይደለም፡፡

TPLF 30በተጫባጭ ማስረጃ እና በመረጃ ላይ ተደግፎ የቀረበው የእኔ ትንታኔ አዲሱ ሕግ የትሮጃን ፈረስ ነው፡፡ በጥንት ዘመን ግሪኮች እጅግ ግዙፍ የሆነ የእንጨት ፈረስ ሰሩ እና በውስጡ ወታደሮች እንዲደበቁ በማድረግ የሚዞር ለማስመሰል ሞከሩ፡፡ ያልጠረጠሩት ትሮጃዎች ፈረሱን ወደከተማው በማምጣት በጨለማው ተታለው እንደነበር ተገነዘቡ፡፡ የግሪክ ወታደሮች ከፈረሱ ሆድ ውስጥ ወጡ እና ውጊያ በመክፈት ከውጭ ያሉ ወታደሮች እንዲገቡ አደረጉ፡፡ ትሮይ ወደቀች ፡፡ ስለዚህ ገለጻው እንዲህ ይላል፣ “የግረክ መሳይ ስጦታዎችን ተጠንቀቁ“፡፡

ዘ-ህወሀት አዲሱን የትራፊክ ደንብ ለአዲስ አበባ ከተማ እና ለሌሎች ከተሞች በስጦታነት አቅርቧል፡፡ በአዲሱ ሕግ ውስጥ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮችን የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እውንነትን እና የፖለቲካ አጋርነትን በማጥፋት የከተማውን ኗሪ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የተዘጋጁ፣ ፈቃደኛ የሆኑ እና የሰለጠኑ ወታደሮች አሉ፡፡

የዘህወሀት አዲሱ የትራፊክ ሕግ””  አራት ዓላማዎች አሉት የሚል እምነት አለኝ፡፡ እነርሱም፣

አንደኛ፡  “አዲሱ የትራፊክ ሕግ” በዘ-ህወሀት እጅ ዘንድ ያለ ጠንካራ የሆነ የፖለቲካ መሳሪያ ነው፡፡ የሕጉ ዋናው ዓላማ የኢትዮጵያ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች በቀጣይነት የዘ-ህወሀት የኢኮኖሚና የፖለቲካ የስጋት አደጋዎች እንዳይሆኑበት አስቀድሞ በሕግ ሽፋን ሽባ ለማድረግ እና ስለዕለት በዕለት ኑሮ ላይ ብቻ ተጠምደው በፍርሀት እና በቆፈን ተጠፍንገው ለአገዛዙ እያጎበደዱ እና እየሰገዱ እንዲኖሩ ለማድረግ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ለታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች ግልጽ ሆኖ ላይታያቸው ይችላል፡፡

የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች እንደ አንድ የኢኮኖሚ ስብስብ ቡድን ትስስር ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ኃይል እንደሚኖራቸው ዘ-ህወሀት አሳምሮ ያውቃል፡፡ በየዕለቱ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡት ባለው በሚሊዮን በሚቆጠር ህብረተሰብ የደም ስር ላይ ጣቶቻቸውን አስቀምጠዋል፡፡ እምቅ የሆነ የፖለቲካ ኃይል አላቸው፡፡ ይኸ እውነታ ለበርካታ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች ሊታያቻው የሚችል አይሆንም፡፡ እምቅ የፖለቲካ ኃይል ስል በመቶ ሜትሮች ርቀት ላይ በሚገኝ ዒላማ ላይ በማነጣጠር በደጋኑ ውስጥ የተጠራቀመውን ኃይል በመጠቀም ዒላማውን ለመምታት እንደሚቻል ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮችም በታመቀው የፖለቲካ ኃይል ዒላማውን መምታት ይችላል ለማለት ነው፡፡

ዘ-ህወሀት የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮችን እምቅ የፖለቲካ ኃይል በህልዮት፣ በተግባር እና በታሪክ አሳምረው ያውቃሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ1973 የነዳጅ ዋጋ በኢትዮጵያ በአራት እጥፍ በጨመረ እና አውዳሚ ረኃብ በተከሰተበት ጊዜ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች የነዳጅ ዋጋ ጭማሪውን በመቃወም በንጉሳዊው አገዛዝ ላይ የስራ ማቆም አድማ በመምታት ህዝባዊ አመጹ እንዲቀጣጠል ወሳኝ ሚና ተጫውተው ነበር፡፡ እንደዚሁም እነርሱ ለሌላው አርዓያ በመሆን መምህራን፣ የባቡር ሰራተኞች እና ጫኝ እና አውራጅ ሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ በማንሳት የስራ ማቆም አድማ እንዲመቱ ምሳሌ ሆነዋል፡፡ ተማሪዎች የተከሰተውን ረኃብ በመቃወም ህዝባዊ እንቅስቃሴ ያደረጉ ቢሆንም ወታደሮች ህዝባዊ አመጹን በመንጠቅ አምባገነናዊ ወታደራዊ መንግስት አቋቋሙ፡፡

ሆኖም ግን የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች እ.ኤ.አ በ1973 የተከሰተውን ህዝባዊ አመጽ የስራ ማቆም አድማ በማድረግ ያቀጣጠሉት ለመሆናቸው የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይደለም፡፡

እ.ኤ.አ የካቲት 22/2016 የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች የስራ ማቆም አድማውን ውጤታማ በሆነ መልኩ የሚተገብሩት ከሆነ ድባቅ ለመምታት የሚያስችል ኃይል እንዳላቸው ለዘ-ህወሀት በግልጽ አሳይተዋል፡፡

የዘ-ህወሀት ስልት ነዳፊዎች የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች ከፍተኛ የሆነ እምቅ የፖለቲካ ኃይል እንዳላቸው እና በእነርሱ ላይ ለሚደረግ ህዝባዊ አመጽ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ አሳምረው ያውቃሉ፡፡ ስለሆነም የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮችን ስልታዊ በሆነ መልኩ ማዳከም እና የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ስብስብ ትስስራቸው እንዲበጠስ እና እንዲበታተን ለማድረግ አጥንክሮ መስራት የዘህወሀት አዲሱ የትራፊክ ሕግ ዋና መርህ ነው፡፡

ዘ-ህወሀት የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች የኢትዮጵያ የከተማ ኢኮኖሚ እና የትራንስፖርት ስርዓቱን ኦክሲጂን ተሸካሚ ቀይ የደም ሕዋሳት/hemoglobin መሆናቸውን አሳምሮ ያውቃል፡፡

የታክሲ አሽከከርካሪ ሾፌሮች የኢኮኖሚ እና ትራንስፖርት ስርዓቱን ትስስር አጠናክረው በመያዝ ዘ-ህወሀትን ከጉልበታቸው ስር የማንበርከክ ኃይል አላቸው፡፡ እ.ኤ.አ የካቲት 22/2016 የተደረገውም ይኸው ነው፡፡

ዘ-ህወሀት ሁሉንም የፖለቲካ ተቃናቃኞቹን እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን አጥፍቷል፡፡ ይፋ በሆነ መልኩ 79 የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አንድ ፓርቲ ብቻ (የህወሀትን ማንነት ለመደበቅ ሲባል የበግ ለምድ ለብሶ ለማስመሰያ የተቀመጠው ኢህአዴግ) በይስሙላው የዝንጀሮ ፓርላማ ስር ያሉትን መቀመጫዎች መቶ በመቶ ተቆጣጥሮ ይገኛል፡፡

የዘ-ህወሀት አዲሱ የትራፊክ ሕግ ለወደፊቱ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ አደጋ ስጋት ይሆኑብኛል ብሎ የሚያስባቸውን የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች ህልውና ለማሳጣት ሲባል ዓላማ አድርጎ የተዘጋጀ ለመሆኑ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለኝም፡፡

ሁለተኛ፡  ዘ-ህወሀት የእራሱን የፖለቲካ ዓላማ ለማሳካት በማሰብ ስልታዊ በሆነ መንገድ አሁን በሾፌርነት ደረጃ እያገለገሉ ያሉትን የታክሲ ሾፌሮች ከታክሲ ገበያው በማስወገድ የዘ-ህወሀት፣ ታዛዥ ሎሌዎች፣ ደጋፊዎች፣ ጓደኞች፣ አገልጋዮች እና ሌሎች ታማኞች የታክሲውን ገበያ በብቸኝነት ጠቅልለው እንዲይዙ ለማስቻል እንደሆነ አምናለሁ፡፡

ማንም ሰው ቢሆን የአዲሱን የትራፊክ ሕግ የቅጣት ደረጃዎች በጥሞና በማገናዘብ ይህንን ስልት በግልጽ ማየት ይችላል፡፡ ባለ 20 ነጥብ የነጥብ አሰጣጥ ስርዓት ዋና ዓላማ ተደርጎ የወጣው በአሁኑ ጊዜ በታከሲ ሙያ ላይ ተሰማርተው የሚገኙትን የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች በተቻለ መጠን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከታክሲ ገበያው ስራ ውስጥ ለማስወጣት የታቀደ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌር በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ 7 ነጥብ የሚያሰጥ ቅጣት ሊሰጠው ይችላል፡፡ ለምሳሌም የእንዝህላልነት አነዳድ፣ የመሳሪያ ያለመኖር፣ በቂ ያልሆነ የትራፊክ ቁጥጥር መሳሪያዎች ያለመኖር፣ አደጋዎች፣ ህዝብ የሚበዛባቸው ሰዓቶች ላይ የሚፈጸም ጥፋት፣ ወዘተ፡፡ በቀናት ወይም ደግሞ በሳምንታት ውስጥ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌር 20 ወይም ከዚያ በላይ ነጥቦችን በመስጠት ከታክሲ ገበያው ለዘላለሙ ማባረር ይችላል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ያሉት የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች በነጥብ አሰጣጥ ስርዓት ከሙያቸው በግዳጅ እንዲለቁ በማድረግ ዘ-ህወሀት ሕግን የጣሱ ናቸው በማለት የነጠቃቸውን ጥቂት የመንጃ ፈቃዶች ለእርሱ ታዛዥ ሎሌዎች፣ ደጋፊዎች፣ ጓደኞች እና አገልጋዮች እንደሽልማት (ለዋና ደጋፊዎቻቸው ነጻ ስጦታ) በማድረግ በደስታ ያድላሉ፡፡ ዘ-ህወሀት በከፍተኛ  የተረፈዉን ፈቃዶች በከፍተኛ ዋጋ ይሸጠዋል ፡፡ ቀስ በቀስም የዘህወሀት ደጋፊዎች፣ ታዛዥ ሎሌዎች እና ጫማ ላሾች የታክሲ ገበያውን በበላይነት በመቆጣጠር የዘህወሀትን ፍላጎት ለማሳካት ጥረት ያደርጋሉ፡፡

ከዚህም አልፎ የፓርቲ ሰላዮች በመሆን የህዝቡን መንፈስና እና አስተሳሰብ ቀን በቀን እየሰለሉ እና እየለኩ ዘገባ በማቅረብ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡

የዘህወሀት አዲሱ ሕግ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ 80 – 85 በመቶ የሚሆኑት የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች ከታክሲ ማሽከርከር ገበያው ውስጥ እንዲወጡ በማድረግ በዘህወሀት ደጋፊዎች፣ እና ታዛዥ ሎሌዎች እንዲተኩ ይደረጋሉ፡፡

እድለኛ የመሆን አጋጣሚ ካገኙ ደግሞ ጥቂቶች የኢህአዴግ አባል በመሆን የመንጃ ፈቃዳቸው ሊመለስላቸው ይችላል፡፡ ከዚያ ውጭ ያሉት ደግሞ ሌላ ስራ መፈለግ ይኖርባቸዋል ወይም ደግሞ መምገድ ላይ ለመለመን ይገደዱ ይሆናል፡፡ (ወደ እውነታነት የሚመጡ ነገሮችን በመተንበይ ረገድ በጣም ጥሩ የሆነ ምዝገባ እንዳለኝ አምናለሁ፡፡)

እንግዲህ የኢትዮጵያ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች ይህንን መራር እውነታ መጋፈጥ አለባቸው፡፡

የዘ-ህወሀት የተበላሸና ወንጀለኛ የፈቃድ አሰጣጥ፣ የመንግስት ኮንትራት ስምምነቶች፣ የግብር እዳ ቅነሳ ሙስና እና የህግ ውጤቶች በየጊዜው የመቀያየር ሁኔታን በማስመልከት የዓለም ባንክ እ.ኤ.አ በ2012 በኢትዮጵያ ላይ ባደረገው መጠነ ሰፊ የሙስና ጥናት ላይ ይፋ ተደርጎ ተመዝግቦ ተቀምጧል፡፡

ዘ-ህወሀት አዲሱን የትራፊክ ሕግ በመጠቀም ጠቅላላ የከተማውን ኢኮኖሚ በቀጥጥሩ ስር በማድረግ ለእራሱ አጎብዳጅ ሁኔታን ለመፍጠር እያደረገ ካለው እውነታ ጋር በተያያዘ መልኩ ያለው ምላሽ ከሚከተሉት ጥያቄዎች ከሚገኙ ምላሾች የሚገኝ ይሆናል፡

1ኛ) በአሁኑ ጊዜ ማንም ኢትዮጵያዊ የዘ-ህወሓት (ኢህአዴግ የማችበርበሪያ የማጭበርበሪያ ሰሙ) አባል ሳይሆን በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ በእርግጠኝነት ስራ ፈልጎ መቀጠር ይችላልን?

2ኛ) ማንም ሰው ቢሆን ለዘ-ህወሓት ታማኝነትን ሳይሳይ እና አጎብዳጅ ታዛዥ ሎሌ ሳይሆን በያዘው የመንግስት ስራ ላይ በነጻነት ያለምንም ችግር ሊቀጥል ይችላልን?

3ኛ) በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ የዘ-ህወሓት  አባል ሳይሆን በተሻሉ የከፍተኛ የትህምህርት ተቋማት በመመዝገብ ትምህርቱን መከታተል ይችላልን? ወይም ደግሞ ዓለም አቀፍ የምግብ እርዳታ ማግኘት ይችላልን?

ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት “ልማት ካለነጻነት፡ እርዳታ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት ለመጨቆኛ መሳሪያ እየዋለ እንደሆነ“ በሚል ርእስ ያዘጋጀውን እና ዘ- ህወሀት በለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ የሚያገኘውን ሀብት እና እርዳታ እንዴት አድርጎ ስልጣኑን ለማጠናከር እየተጠቀመበት እንደሆነ ይፋ የሆነውን ባለ105 ገጽ ዘገባ መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡

4ኛ) ዘ-ህወሀት የተራቡ አርሶ አደሮችን ከጉልበቱ ስር እንዲንበረከኩ የሚያደርግ ከሆነ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮችን አጥንታቸው እስኪታይ ቢግጣቸው የሚያስገርም ነገር ሊሆን ይችላልን?

እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ የዘ-ህወሀት የቁጥጥር አባዜ ደህንነት እንዲሰማው ከተፈለገ ሁሉንም ነገር መቆጣጠር አለበት፡፡

የታክሲ አሽከርካሪዎች ዘ-ህወሀቶችን ገሀነም እንዲገቡ እና ደህንነት እንዳይሰማቸው አድርገዋል፡፡ ዘ-ህወሀት በማንኛውም መንገድ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮችን መቆጣጠር በሺታ አለበት፡፡

ሦስተኛ፡ የዘህወሀት አዲሱ የትራፊክ ሕግ በሸፍጥ ወረቀት የተጠቀለለ ድብቅ የታክሲ ግብር ልመናን አቅርቧል፡፡ ገንዘቡን ተከተል፡፡

ዘ-ህወሀት ተስፋቢስ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ዘ-ህወሀት እንደ ደም መጣጭ ሰይጣን ደምን ለመጠጣት ተስፋቢስ ሆኗል፡፡

ዘ-ህወሀት ገንዘብን ለማግኘት ሲል ያለ የሌለ አቅሙን ሁሉ በማድረግ ጥረት ያደርጋል፡ መሬትን በመቀራመት ይሸጣል፣ ከሀገሪቱ ጥንታዊ ቤተመጽሐፍት ታሪካዊ መጽሐፍትን በማውጣት ይሸጣል፣ የስነ አጽም ቅሪቶችን እና ሌሎችንም በዓይን የሚታዩ ነገሮችን ይሸጣል፡፡

ከዚህም ባለፈ መልኩ ዘ-ህወሀት የወሲቡን ቱሪዝም  የህክምና ቱሪዝም እያለ በሚጠራው ማደናገሪያው የሴት እህቶቻችንን ገላ በመሸጥ ገንዘብ ለማግኘት በመቋመጥ ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት አገልግሎት በአብዛኛው በትክክለኛው አካሄድ ስለማይመራ የውጭ ምንዛሬ ጥቁር ገበያዎች (ኮንትሮባንድ) እንደ አሸን እንዲፈሉ አድርጓል፡፡

ዘ-ህወሀት ወደ ውጭ ሀገር በመዞር ዶላርን እና ኢውሮን በመለመን ወደ ግል ባንካቸው ለማጨቅ ይቋምጣሉ፡፡

ባለፈው ወር በአፍሪካ ህብረት እና በቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት በታቦ ኢምቤኪ ሊቀመንበርነት የተመራ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን በተካሄድ ጥናት መሰረት ኢትዮጵያ ከአፍረካ በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር በአብዛኛውም ወደ አደጉ ሀገሮች በሚወጣ ገንዘብ ቀዳሚ ሆና ተገኝታለች፡፡

ግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት እ.ኤ.አ በ2011 እንዲህ የሚል ዘገባ አውጥቷል፣ “የኢትዮጵያ ህዝቦች አጥንታቸው እስኪታይ ድረስ ተግጠዋል፡፡ ከአስከፊ እጦት እና ድህነት ማጥ ውስጥ ለመውጣት የቱንም ያህል ጊዜ ጥረት ቢያደርጉም እንኳ በአሁኑ ጊዜ ባለው ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ምክንያት በወንዙ ወደ ላይ አቅጣጫ በመዋኘት ላይ ይገኛሉ“ ብሏል፡፡ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

የዘህወሀት አዲሱ የትራፊክ ሕግ የኢትዮጵን የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች አጥነታቸው እስኪታይ ለመጋጥ የተሰላ ስሌት ነው፡፡ የታክሲ ማሽከርከር ሙያ እስከ አሁን ድረስ በአንጻራዊ መልኩም ቢሆን ነጻ ነው እየተባለ የሚጠራ እና በዘ-ህወሀት ብቸኛ ቁጥጥር ስር ያልዋለ የንግድ ስራ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በዘ-ህወሀት ያልተያዘ፣ በቁጥጥር ስር ያልዋለ፣ የማይተዳደር ወይም ደግሞ ከዘ-ህወሀት መዳፍ ውስጥ ያመለጠ ገቢ የሚያስገኝ ስራ ከቶውንም የለም፡፡ በፍጹም!

ዘ-ህወሀት የማያነፈንፈው አትራፊ እና አዳጊ የሚመስል ቢዝነስ እንደሌለ የሚክድ ሰው አለን? ምንም ዓይነት ቢዝነስ! እነርሱ የማይወስዱት ቢዝነስ ከሆነ በአንድ ምሽት ሊያጠፉት አይችሉምን?

ዘ-ህወሀት ኢኮኖሚውን፣ ወታደራዊ ኃይሉን፣ ፖለቲካውን፣ የሲቪል ተቋማትን፣ ወዘተ አይቆጣጠርምን? ዘ-ህወሀት የመጨረሻውን የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ በስንት መቶኛ ነው ያሸነፈው? በዚህ ጉዳይ ላይ ማንም ምንም ዓይነት ሀሳብ ሊኖረው ይችላልን?

የዘ-ህወሀት አዲሱ የትራፊክ ሕግ ከፍተኛ የማጭበርበር ሸፍጥን በተላበሰ መልኩ ተዘጋጅቶ የቀረበ የተደበቀ ግዙፍ ህገወጥ ግብር የተቆለለበት የሸፍጥ አሰራር ዕቅድ ነው፡፡

እ.ኤ.አ የካቲት 22/2016 እራሱን “ለሁሉ” እያለ የሚጠራ የንግድ ተቋም እንዲህ የሚል መግለጫ አወጣ፡

“በዛሬው ዕለት (ሰኞ የካቲት 22/2016) የትራፊክ ደንቡን የሚጥሱ በአዲስ አበባ የሚገኙ ሁሉም ሾፌሮች ቅጣታቸውን “በለሁሉ” በመቅረብ መክፈል ይኖርባቸዋል፡፡ ለሁሉ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኝ የትራፊክ ቅጣት ክፍያን ለመሰብሰብ የተቋቋመ ብቸኛ ድርጅት ነው፡፡“

እኔ እስከማውቀው ድረስ የትራፊክ ቅጣትን በአንድ የግል ኩባንያ እስከፋይነት ገቢ እንዲደረግ የሚለው መሰረተ ሀሳብ ከፍተኛ ደረጃ የሙስና ግማት ሽታን ይጋብዛል፡፡

በዘ-ህወሀት የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች የልመና ሸፍጥ ውስጥ ያለው “ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ” እየተባለ የሚጠራው እና ለሁሉ እየተባለ በሚጠራው የክፍያ አሰራር ስርዓት ውስጥ የዘ-ህወሀትን ቦርሳ የተሸከመ ጽልመታዊ ተቋም አለ፡፡

ይገማል! ይጠረናል! የዘህዋሃትና ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ መሞዳሞድ ፡፡

በለሁሉ ውስጥ ከዘ-ህወሀት ጋር ስምምነት የምታደርግ ግዙፍ፣ ወፍራም እና ዓይኗ የፈጠጠ አይተ ሞገጥ አሸታለሁ፡፡

ያች የሙስና አይጥ ገና ከ10 ሺ ሜትሮች ርቀት ላይ ትሸተኛለች፡፡ (ቅርናት!  ቅርናት! …ኡፍ፤ ኤዲያ እቴ…)

ግንክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂምንድን ነው?  “ለሁሉምንድ ነው?

**** ”ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ“ የሚለውን አየመረመርን ሳለን የእርሱ ድረ ገጽ በአስቸክዋይ ተዘጋ : እንዲህ የሚል ጽሁፍ አስቀምጧል፡፡ **** አስፈላጊ የሆነው ድረ ገጽ ጫን በሚደረግበት ጊዜ መልዕክቱ እንዲህ ይላል፣ “ይኸ ድረ ገፅ አይገኝም፡፡“

ለጉግል መዛግብት ምስጋና ይግባና ማስረጃው እስከ አሁንም ድረስ አለ፡፡ (1) እዚህ፣ (2) እዚህ (3) እዚህ የሚሉትን የግንኙነት መስመሮች ተመልከት፡፡

እንደ newbusinessethiopia.com “ለሁሉ“ በኮሙኒኬሽን እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና በክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መካከል እና በፌዴራል የትራንስፖርት ባለስልጣን እና በአዲስ አበባ የመንገዶች ባለስልጣን ተባባሪነት የተደረገ የግል እና የመንግስት ስምምነት ነው፡፡

ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ እንዲህ የሚል ራዕይ አስቀምጧል፣ “ራዕይው ግብይቶችን ቀላል በማድረግ፣ አቅምን ያገናዘበ እና ሊደረስበት የሚችል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የህዝቦችን ህይወት በማሻሻል የእራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ“ ይላል፡፡ ተልዕኮው ደግሞ እንዲህ ይላል፣ “ቀጣይነት ያላቸውን ቴክኖሎጂዎች እና የማሰራጫ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ፋይናንስ ነክ ለሆኑት እና ላልሆኑት ተደራሽነትን በመፍጠር የተቀናጀ እና ሊያድግ የሚችል አገልግሎትን ማቅረብ ነው፡፡“

ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ አጋሮች የኮሙኒኬሽን እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ኢትዮ-ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን እና የአዲስ አበባ ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ባለስልጣንን  ያካትታል፡፡

ሆኖም ግን ከዘ-ህወሀት ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ጋር አጋሮች (እውነተኛ ስሞች) እነማን ናቸው?

ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂን በባለቤትነት የያዘው ማን ነው?

ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ጀርባ ማን አለ? ስላቅ ያበዛ የነበረው እና አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ ጠቅላይ ሚኒስትር በአንድ ወቅት በስሩ ያለውን አጎብዳጅ ድርጅት በስም ኦህዴድ በሚባለው ድርጅት ላይ ተቆጣ እና አሁን ልባችሁ እንደፈጣን ሎተሪ ቢፋቅ ኦነግ ሆናችሁ ትገኛላችሁ እንዳለው ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ አሁንም የክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ልብ እንደ ፈጣን ሎተሪ ቢፋቅ ማን ሊሆን ይችላል? ውስጡን ለቄስ ነው፣ ሆድ ይፍጀው!

በእራሱ ድረ ገጽ ላይ ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ እንዲህ ይላል፣ ኩባንያው የተመሰረተው .. 2010 ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ልምድ ባለው ድርጅት መስራችነት ነው፡፡“ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ድረ ገጽ ወይም ደግሞ በሌሎች የመንግስት ምንጮች ላይ ስለባለቤቶቹ ማንነት የትም ቦታ መረጃ ስለመኖር አለመኖሩ፣ ስለጋራ ባለቤትነት፣ ስለአጋርነት ወይም በኩባንያው ውስጥ ስላሉት ባለድርሻ አካላት ሁኔታ የሚገልጽ ምንም ነገር የለም፡፡

ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ባለቤቶች ማንነት ሆን ተብሎ እና ፍጹም በሆነ መልኩ በሚስጥር እንዲያዝ እና እንዳይታወቅ ተደርጓል፡፡

እኮ ለምን?

ከኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጋር እውቅና ያላቸውን ግለሰቦች በግል እና በመንግስት ዘርፎች ስለ ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ቢጠየቅ ማንም የሚያውቅ ሰው የለም ፡፡

በኢትዮጵያ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጁው ዘርፍ ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ እነማን ባለቤቶች፣ ባለድርሻ አካሎች፣ አጋሮች፣ ወዘተ እንደሆኑ አይታወቅም፡፡ በክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ውስጥ እነማን ታቅፈው እንደሚገኙ ለይቶ ለማወቅ ያለመቻሉ ጉዳይ ግልጽ አይደለም!

ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ በእራሱ ድረ ገጽ በደርዘን ስለሚቆጠሩት “ለሁሉ ማዕከሎች” ከፍ ከፍ እያደረገ ይናገራል፣ ሆኖም ግን ዋና መስሪያ ቤት እንደሌለው መዝግቧል፡፡

ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ድረ ገጽ የግንኙነት መስመር ክፍያ ለዋና መስሪያ ቤቶች የመዘገበው አድራሻ የለም፡፡ ይህም በርካታ ደንበኞች አሉኝ እያለ ለሚናገር ድርጅት እና ከመንግስት ጋር ስላለው አጋርነት ጉራ እየቸረቸረ ላለ ድርጅት እንግዳ የሆነ ነገር ነው፡፡ እንደመገናኛ ነጥብ የፖስታ አድርሻ እና የኢሜይል አድራሻውን ብቻ መዝግቧል፡፡ (አንዴ ሙስና ሙስና ይገማል ይጠረናል!)

በአጠቃላይ 1.92 ቢሊዮን ብር ገቢ የሚያስገኝ ኩባንያ info@email አድራሻ ብቻ የሚገናኝ መሆኑ ሲታሰብ ጭንቅላትን የሚበጠብጥ ነገር ነው፡፡

ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ በእያንዳንዱ ወር 2..1 ሚሊዮን ግብይቶችን ከ1.1 ሚሊዮን ከፋይ ደንበኞች ጋር እንደሚያካሂድ ግልጽ አድርጓል፡፡ እንደዚሁም 450 እና ከዚያ በላይ ሰራተኞችን እንደሚቀጥር እና በ31 ለሁሉ ማዕከሎች በቅርቡም 26 እንደሚጨመሩ ዕቅድ በመያዝ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ኩባንያው በፕሮጀከቱ ማጠናቀቂያ 1.92 ቢሊዮን ብር እንደሚያስገኝ ይጠብቃል፡፡

ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በድረ ገጹ ላይ የእርሱ ባለቤቶች የአስር ዓመታት ልምድን ያካባቱ IT ባለሙያዎች እንደሆኑ ጉራ አሰምቷል፡፡

እንደዚህ ባለ ሁኔታ ጉራ እየተቸረቸረባቸው ያሉ የክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች እነማን ናቸው? ለመሆኑ ስም አላቸው? ምናልባትም ቅጽል ስም? ተቀጥላ ስሞችስ? ሌላም ነገር? በእውን ህልውና አላቸውን?

የአስርት ዓመታት ልምድ አላቸው እየተባለ ስለሚነገርላቸው የIT ባለሙያ ባለቤቶች ምንም የሚታወቅ ነገር የለም! በድረ ገጾቻቸው ላይ ስለእነርሱ ማንነት ድበቅ ስራ የሚሰሩ ከሆነ ሊደብቁት የሚፈልጉት አንድ ነገር አለ ማለት ነውን?

በግልጽ ለመነጋገር ባለፉት ቀናት የክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂን ባለቤቶች ማንነት ለማወቅ ከፍተኛ የሆነ ምርመራ የተደረገ ቢሆንም ለማረጋገጥ አልተቻለም ወይም ደግሞ ከኩባንያው በስተጀርባ ያሉትን መስራች ባለቤቶች ወይም ግለሰቦች ማወቅ አልተቻለም፡፡ ለማወቅ ዕድሉ ያላቸው እንኳ ስለክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ባለቤቶች፣ አጋሮች እና ባለድርሻ አካላት የሚያውቁት ምንም ዓይነት ነገር የለም፡፡

እዚህ አንድ አፍታ ቆም በሉ! ምን እንዳሰባችሁ አውቃለሁ!

ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ በባለቤትነቶች፣ በአጋርነቶች እና በባለድርሻ አካላት ማንነት ላይ ጭጋጋማ ሚስጥራዊነት እና ጠቅላላ የሆነ ድብቅነት የሚታይበት ሁኔታ የመኖሩ ምክንያት ሊባል ይቻል ይሆናል፣ እኔ ግን የሸፍጥ የይስሙላ የዝንጀሮ የቢዝነስ ማችበርበር ስራ አለ ብዬ አላልኩም !

እባካችሁ በኮምፒውተር መክፈቻ ቁልፎቼ ላይ ቃላትን አታስቀምጡልኝ!

ይህንን ጉዳይ ግልጽ ላድርገው!

ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በዘ-ህወሀት አባላት፣ ደጋፊዎች እና በታማኝ ግብረ አበር ሎሌዎች የተያዘ፣ የሚንቀሳቀስ እና የሚመራ ነው እያልኩ አይደለም፡፡

የዘ-ህወሀት አለቆች ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂን በእርግጠኝነት በባለቤትነት በመያዝ ኩባንያውን ልክ የኢህአዴግን ፓርቲ ለዘ-ህህወሀት ጭንብልነት እንደሚጠቀሙበት ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ይህንን ኩባንያም በጭንብልነት እየተጠቀሙበት ነው እያልኩ አይደለም፡፡

የዘ-ህወሀት አለቆች ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂን በአጋርነት በድብቅ በመያዝ እየተጠቀሙበት ነው እያልኩ አይደለም፡፡

ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ኩባንያ ባለቤቶች (ማንም ይሁኑ ማን) ከትርፋማው ስምምነት ትርፍን በመዛቅ ወይም ደግሞ እንደዚህ ያለውን የማትነጥፍ ላም ስምምነት ከዘ-ህወሀት ጋር በመፈጸም ወይም ደግሞ ከታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች እና ከሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ገንዘብን እያለቡ ለዘ-ህወሀት ክፍያ ይፈጽማሉ እያልኩ አይደለም፡፡

በክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ባለቤቶች፣ በአጋሮች እና በባለድርሻ አካላት ዙሪያ ያለው ሚስጥራዊነት እና ድብቅነት ማለት ማንም ማየት የሚችል ዓይን ያለው ሰው ሁሉ ህወሀት በክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ላይ ያለውን የእጅ አሻራ እና የእግር ኮቴውን በግልጽ ይመለከታል እያልኩ አይደለም፡፡

ዘ-ህወሀት ሁሉንም ዓይነት የንግድ እንቅስቃሴዎች እና የሸፍጥ ስራዎች ለማካሄድ ቀደም ሲል እንደ ማረት/EFFORT የመሳሰሉ ግንባር ድርጅቶችን ይጠቀም እንደነበር እና አሁን ደግሞ ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂን በተለመደው መንገድ እተጠቀመበት ነው እያልኩ አይደለም፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ሁሉ ናቸው እያልኩ አይደለም፡፡ ስለሆነም ቃላትን በአፌ ላይ ወይም ደግሞ የበለጠ ግልጽ ለማድረግ በኮምፒውተር መክፈቻ ቁልፎቼ ላይ አታስቀምጡልኝ፡፡

እኔ እንደዚህ አላልኩም፡ ለልበ  እርግ ብ ነኝ!

በአጠቃላይ እያልኩ ያለሁት እንዲህ የሚል ቀላል ነገር ነው፡ “ብዙ ውጣ ውረድ ሳይደረግበት በቀላሉ ህገወጥ ገንዘብ እንደ አሸዋ የሚዛቅበትን ግዙፍ የፋይናንስ ተቋም እና 1.2 ቢሊዮን ብር የማመንጨት አቅም ያለውን ድርጅት ባለቤቶች፣ አጋሮች እና ባለድርሻ አካሎችን ማንነት መሰወር እና መደበቅ ለእኔ ሊታመን እና ሊታሰብ የማይችል አስደናቂ ነገር ነው፡፡“

ለኢትዮጵያ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች መናገር የምፈልገው እንዲህ የሚል አንድ ነገር ብቻ ነው፡ ገንዘቡን ተከተሉ! የክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ባለቤቶች ማን መሆናቸዉን ስታውቁ ለዘህዋሃት የሚታለቡ ላሞች እና ለዘ-ህወሀት የወርቅ እንቁላል የሚጥሉትን ዳክየዎች አንዴት አንደሆናችሁ ታውቃላቸሁ፡፡

በክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ   ውስጥ የዘ-ህወሀትን ሚስጥራዊ የባለቤትነት ይዞታ ለማወቅ በዘ-ህወሀት የይስሙላው የዝንጀሮ ፍርድ ቤት ቀርባችሁ ትግል አድርጉ፡፡

ፍትሕን እንደማታገኙ እርግጠኞች ብትሆኑም ዝንጀሮዎችን በዝንጀሮው ፍርድ ቤት በመገኘት ላብ በላብ አድርጓቸው፡፡

አራተኛ፡ የዘ-ህወሀት አዲሱ የትራፊክ ሕግ  ለዘ-ህወሀት የትራፊክ ፖሊሶች ነፋስ አመጣሽ ከሰማይ የወረደ መና ነው፡፡

አዲሱ የትራፊክ ሕግ በሙስና ስለተዘፈቁት የዘ-ህወሀት የትራፊክ ፖሊሶች ሾፌሮችን በማስፈራራት ስለሚዘርፉት ጉቦ ምንም ያለው ነገር የለም፡፡ የዘ-ህወሀት የትራፊክ ፖሊሶች በሕጉ መውጣት ምክንያት ለሀጫቸውን እያዝረበረቡ እና የእጆቻቸውን መዳፎች እያፋተጉ እንደሚሽከመከሙ ጅቦች በመፈንደቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮችን ለማጥቃት የመቆየት እንኳ ትዕግስቱ የላቸውም፡፡ አዲሱ የትራፊክ ሕግ የታክሲ ሾፌሮች በትራፊክ ፖሊሶች አንደ ዱር አራዊት የሚታደኑበትን መድረክ ይከፍታል፡፡

የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ውስጥ በዘ-ህወሀት የፖሊስ ሙስና ዝቅጠት ላይ ስላወጣው መረጃ እስቲ እንመልከት፡፡

የዓለም ባንክ እ.ኤ.አ በ2012 “በኢትዮጵያ ሙስናን መመርመር“ በሚል ርዕስ ካወጣው የሙስና ጥናት ዘገባ ውስጥ ከገጽ 214 – 215 በግልጽ እንደተመለከተው የዘ-ህወሀት ፖሊሶች እየፈጸሟቸው ያሉትን የሙስና ልምዶች በዝርዝር አስቀምጧል፡፡

የጥናት ሰነድ ዘገባው የዘ-ህወሀት ፖሊሶች የተዘፈቁባቸውን የሙስና ልምዶች ዝርዝር መዝግቦ ይፋ አድርጓል፡፡

በዓለም ባንክ የጥናት ሰነድ ዘገባ ውስጥ ከቀረቡት በደርዘን ከሚቆጠሩት የሙስና ልምዶች መካከል የሚከተሉት ይካተቱበታል፡

  • በትራፊክ ፖሊሶች የሚወሰድ ጉቦ፣
  • ስልጣንን ከሕግ አግባብ ውጭ መጠቀም ወይም ደግሞ ከመጠን ያለፈ ኃይልን መጠቀም- አብዛኛውን ጊዜ ሙስና ነው ባይባልም አንዳንድ ጊዜ በማስፈራራት በሀሰት በቁጥጥር ስር ማዋል ወይም ደግሞ የሀሰት ማስረጃ ማቅረብ፣
  • ማስረጃዎችን ለማስቀየር ጉቦ መስጠት፣
  • ምስክሮች እንዳይመሰክሩ ማስፈራራት እና ጉቦ መስጠት ወይም ደግሞ ከሕጋዊ እርምጃ አንጻር የፖሊስ የስራ ጓደኝነትን ለመርዳት ጥረት ማድረግ፣
  • ዋጋ ያለው ሆኖ ሲገኝ ማስረጃን መስረቅ፣
  • ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስራ ላለማቆየት ወይም ደግሞ በቁጥጥር ስር አድርጎ ለማቆየት ጉቦ መቀበል- አንዳንድ ተጠርጣሪዎች እስከ ሰኞ ድረስ በቁጥጥር ስር ሆነው እንዲቆዩ የመጠየቅ ሁኔታ እና ሳምንቱን ሙሉ በእስር ቤት እንዳይቆዩ ወይም ደግሞ ዋስትና በማስያዝ ሙሉ በሙሉ እንዲለቀቁ የማድረግ.
  • ጉቦ በመቀበል፣

ሀ) ተከላካዩ በክስ መስሚያው ዕለት እንዳይገኝ/ትገኝ ማድረግ ወይም ደግሞ

ለ) በምስክርነት መስሚያው ዕለት ምስክሮች እንዳይቀርቡ ማድረግ ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

የዘ-ህወሀት ፖሊሶች የማፊያ ዓይነት ስራዎችንም ይሰራሉ፡፡ በማፊያ ቤተሰብ ውስጥ ካለ “ወታደር” ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡ (አስገዳጆች፣ ጡንቸኞች፣ የዘ-ህወሀትን ቆሻሻ ስራ የሚሰሩ እና በሙያው ጥልቅ እውቀት የሌላቸው ግልቦች ናቸው)፡፡

ግልጽ በሆነ መልኩ የልመና ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ የኢትዮጵያ ሞተረኞች ለዘ-ህወሀት የትራፊክ ፖሊሶች ጉቦ የሰጡበት ግላዊ የሆነ የስልክ ቪዲዮዎች በዓይኔ አይቻለሁ፡፡ በማንኛውም አጋጣሚ ሁሉ የዘ-ህወሀት ፖሊስ ጉቦ የሚጠይቅበት በደርዘን የሚቆጠሩ ማስረጃዎች አሉኝ፡፡ በአንድ ልዩ አጋጣሚ አዲስ አበባን በመጎብኘት ላይ የነበረ ሞተረኛ የአውሮፕላን በረራ ዕድሉን ላለማጣት ሲል 500 ብር ጎቦ ከፍሏል፡፡ ያ ሞተረኛ በኋላ በጓደኞቹ መሳቂያ እና መሳለቂያ ሆኗል፣ ምክንያቱም ሞተረኛው ሙሉ በሙሉ ተታሏል፡፡ 50 ብር ብቻ በመስጠት ከችግሩ መገላገል ይችል ነበር፡፡ በጉቦ ተቀባዩ ዓይን አውጣ ጉቦኛ ፖሊስ በደረሰበት ውርደት ምክንያት ሞተረኛው ኢትዮጵያን ዞር ብሎ ላለማየት እና ላለመመለስ ምሎ ተገዝቷል፡፡ የትራፊክ ፖሊሱ 500ውን ብር ከገሸለጠች  በኋላ የዋቱሲን ዳንስ እንደምታስነካው  እርግጠኛ ነኝ፡፡ ከማይጠረጠረው ሞተረኛ፡፡ (ትራፊክ ፖሊሷ ፋስካዋ ነበር )

ግሎባል ኢንቴግሪቲ እንደሚባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ዘገባ “የኢትዮጵያ መንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን ትክክል ያልሆነ የአሽከርካሪዎች መንጃ ፈቃድን በመስጠት እና ዓመታዊ የተሸከርካሪዎችን ምርመራ ከማድረግ ጋር በተያያዘ መልኩ በሀገሪቱ ውስጥ ካሉት በሙስና ከተዘፈቁ መንግስታዊ ተቋማት መካከል አንዱ ነው፡፡ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣንም (ፌትባ) እንደዚሁ በርካታ ለሙስና በር የሚከፍቱ አሰራሮችን በመተግበር ለሙስና የተጋለጠ ድርጅት ነው“ ብሏል፡፡

የውጭ ሀገር ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያፈስሱትን መዋዕለ ንዋይ እ.ኤ.አ ጥር 2014 በተደረገው ጥናት መሰረት የዘ-ህወሀት ትራፊክ ፖሊሶች ከሌሎች መስሪያ ቤቶች ሰራተኞች የበለጠ ጉቦ በመጠየቅ የቀዳሚነቱን ስፍራ እንደሚይዙ ይፋ አድርጓል፡፡

አዲሱ የትራፊክ ደንብ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮችን ሙልጭ አድርጎ ለመጋጥ የተሸረበ የሸፍጥ ዕቅድ ነው፡፡ የትራፊክ ሕግ በሚል ማታለያ የታክሲ ሾፌሮች ላይ ለመቆለል የታሰበ የግብር እዳ ነው፡፡

ክፈል እና እንጫወት ዓይነት ሸፍጥ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች ከዘ-ህወሀት የታክሲ ማሽከርከር ጨዋታ ጋር ለመጫወት ከፈለጉ ላለቆቻቸው በሚያስተላልፉ የትራፊክ ፖሊሶች አማካይነት ለዘ-ህወሀት ህገ ወጥ ገንዘብ መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡

የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች ለመክፈል እና ለመጫወት የማይፈልጉ ከሆነ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይወድቃሉ፡፡

የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች የታክሲ ማሽከርከር ጨዋታውን ለመጫወት መክፈል ይኖርባቸዋል፡፡

ይኸ ሁሉ ነገር ለታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች ምን ማለት ነው?

የዘ-ህወሀት የትራፊክ ፖሊስ በኢትዮጵያ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች ላይ የሞት እና የሽረት ያህል ኃይል እና ስልጣን አለው፡፡

አንድ በሙስና የበከተ የዘ-ህወሀት የትራፊክ ፖሊስ ማንኛውንም የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌር አቅም ለማሽመድመድ ሲፈልግ ከእርሱ የሙስና ተባባሪ አጋሮቹ እና አለቆቹ ጋር በማበር በጥቂት ቀናት ውስጥ የማባረሪያ የሸፍጥ ሰነዶችን በማዘጋት ከታክሲ አሽከርካሪነት ሙያው ለዘላለሙ ለማሰናበት ይችላል፡፡ እንግዲህ አዲሱ የትራፊክ ሕግ (ካልተሻረ በስተቀር) ሊሰራው የሚችለው ነገር ይህንን ነው፡፡

የዘ-ህወሀት አዲሱ የትራፊክ ሕግ ከጅ አፍ በሚታገሉ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች ላይ የትራፊክ ፖሊሶችን ትንሹ አምላክ የሚያደርግ ነው፡፡

ይኸ ሊካድ የማይችል ሀቅ ነው!

የፌዴራል ትራንስፖርት ቢሮ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች የስራ ማቆም አድማ በመቱበት ዕለት የአዲሱ ደንብ ተግባራዊነት በሶስት ወራት ተራዝሟል የሚል መግለጫ ሰጠ፡፡ ወቼ ጉድ፣ እንዴት ተቀለደ!

የፌዴራል የፈለገውን ማንም ተብሎ ቢጠራ የአዲስ አበባን ማስተር ፕላንን ጨምሮ ሞቷል፡፡ በእርግጥ መቸውንም ቢሆን ሊኖር አይቸልም፡፡ ሆኖም ግን መቸውንም ቢሆን የሚኖር ባይሆንም ሞቷል፡፡ ቀጣፊዎች!

እንግዲህ ከዘ-ህወሀት ጋር ያለው ችግር ይኸ ነው፡፡ እነዚህ ወሮበላ ዘራፊ ሸፍጠኞች እነርሱ በጣም ብልጦች እና ሌላው ምንም የማያውቅ ደደብ እንደሆነ አድርገው በመቁጠር ልያታለሉ ይሞክራሉ፡፡

ዘ-ህወሀት ከ90፣ ከ180 ቀናት ወይም ከሁለት ዓመታት በኋላ (እስከዚያ እድሜውን የሚሰጣቸው ከሆነ) በአዲሱ አሮጌ የታክሲ አሽከርካሪ ሕግ እንደገና ብቅ ይላሉ፡፡

ዘ-ህወሀት ከ90፣ ከ180 ቀናት ወይም ከሁለት ዓመታት በኋላ (እስከዚያ እድሜውን የሚሰጣቸው ከሆነ) በአዲሱ አሮጌ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን እንደገና ብቅ ይላሉ፡፡

የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች ማድረግ ያለባቸው ምንድን ነው?

ዘ-ህወሀት የስልጣን ህልውናውን ለማቆየት ሲል በመንገዱ ላይ የሚያገኘውን ማንኛውንም ነገር ሁሉ የሚጨፈልቅ ደም የሚመጥ  ኃይል ነው፡፡

የታክሲ ማሽከርከር ሙያ በኢትዮጵያ ውስጥ በተነጻጻሪ መልኩም ቢሆን ትንንሽ የንግድ ቡድኖች በኢኮኖሚ ተደራጅተው የሚሰሩበት ብቸኛ ነጻነት ያለበት የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ እንደምንመለከተው ዘ-ህወሀት የታክሲ ማሽከርከር ሙያውን ለማውደም ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አይልም፡፡

የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮችን የመብት ማስከበር ትግል ለማኮላሸት በአሁኑ ጊዜ ዘ-ህወሀት የትግሉን መሪዎች እና የአደራጆችን ስም ዝርዝር በመልቀም ጥቃት ለማድረስ እና የበቀል እርምጃ ለመውሰድ እየመረመረው እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ፡፡

ዘ-ህወሀት በታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች ላይ የከፋፍልህ ግዛን መርህ ለመተግበር ጥረት በማድረግ ሙከራ ላይ ሊሆን ይችላል፡፡ የስራ ማቆም አድማውን መሪዎች በገንዘብ ለመግዛት ሙከራ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ የስራ ማቆም አድማውን መሪዎች እና እያንዳንዱን የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌር ያስፈራራሉ፡፡ በታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች መካከል ስምምነት እንዳይኖር እና ክፍፍል እንዲፈጠር አጠንክረው ይሰራሉ፡፡ በጎሳ እና በኃይማኖት እንዲከፋፈሉ ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ የሽብር ተጠርጣሪዎች በማለት ወደ ማጎሪያው እስር ቤት እንዲገቡ ያደርጋሉ፡፡ አሸባሪዎች ብለው በመፈረጅ ጉዳያቸው ወደ ይስሙላው የዝንጀሮ ፍርድ ቤት ቀርቦ ማለቂያ በሌለው የቅጥፈት የተንዛዛ የጊዜ ቀጠሮ በማጉላላት ሊበቀሏቸው እንደሚችሉ ያስፈራራሉ፡፡ በጓደኞቻቻው ላይ ሰላይ እና መረጃ አነፍናፊዎች ሆነው ለእነርሱ ቆሻሻ ዓላማ እንዲያገለግሉ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮችን የማድረግ ብቃት፣ ጽናት እና የትግል መንፈስ ለመግደል ማንኛውንም ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡

ያም ሆነ ይህ እንዲህ በማለት ትንበያ እሰጣለሁ፣ ዘ-ህወሀት ይወድቃል፣ ይወድቃል፣ ይወድቃል…

ሆኖም ግን የኢትዮጵያ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች እራስን በማተለል ደህነነት ከዋናው ዓላማቸው ለአፍታም ቢሆን ጸጥ ማለት የለባቸውም፡፡ አዲሱ የትራፊክ ሕግ 90 ቀናት ተራዝሟል ለሚለው ማታለያ እና ማደናገሪያ ጆሮ ሊሰጡ አይገባም፡፡ በምንም ዓይነት መልኩ ለዘህወሀት ቃል ፍጹም፣ ፍጹም፣ ፍጹም እምነት መስጠት የለባቸውም፡፡ TPLF በሚለው ቃል ውስጥ LF የሚሉት ፊደሎች የውሸት ፋብሪካ/Lie factory የሚለውን ይወክላሉ፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ የታክሲ አሽከርካሪዎች የኢኮኖሚ ህልውናቸው መረጋገጥ ለዘላለማዊ ህይወታቸው ዋስትና መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡

ዘ-ህወሀት ሌላ የትራፊክ ሕግ በማውጣት ጥሩ ስም ይሰጥ እና ወደ ሾፌሮቹ እንደገና ይመለሳል፣ አስፈላጊ ሆኖ ባገኘው ጊዜ ሁሉ እንደገና ለበርካታ ጊዚያት ይመላለሳል፡፡ ይኸ ነገር ጸሐይ ነገ ትወጣለች የማለትን ያህል እርግጠኛ  ነገር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች ዘ-ህወሀት ደም መጣጭ አጋንንት ድርጅት መሆኑን ማወቅ እና እምነት ሊያድርባቸው ይገባል፡፡

በስልጣን ለመቆየት ስልዘህ ዋሃት በአካባቢው ያለውን ማንኛውንም ኢኮኖሚያዊ ደም ሁሉ ይመጥጣል፣ የታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮችን የትግል ደም ጭምር፡፡

ማረት (ኤፎርት)  የዘ-ህወሀት ደም መጣጭ የኢኮኖሚ አገዛዝ ልብ እና መንፈስ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች እ.ኤ.አ በ1776 የአሜሪካንን ነጻነት የሚያውጀውን አዋጅ ከመፈረማቸው በፊት የአንድ አሜሪካውያንን መስራች የተናገሩትን ቃል ማስታወስ ይኖርባቸዋል፡፡ ቤንጃሚን ፍራንክሊን በዚያን ጊዜ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ሁላችንም እጅ ለእጅ መያያዝ አለብን፣ አለዚያም በተናጠል እየተያዝን እንሰቀላለን፡፡“

ከዓመት በኋላ በፓሪስ ፍራንክሊን እንዲሀ በማለት ጻፋ፣ “የእኛ ትግል ለሰው ልጆች ሁሉ በሰላም መኖር መረጋገጥ ትግል እንደሆነ የተለመደ እይታ ነው፣ እናም የእራሳችንን እየተካለከልን ለእነርሱ ነጻነት መዋጋት አለብን፡፡“

የኢትዮጵያ ታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች እጅ ለእጅ ተያይዘው በመጓዝ ሊበጠስ የማይችል ሰንሰለት መስራት እና ልብ፣ አእምሮ እና መንፈስ የጋራ ጥቅሞችን ከጨቋኝ አምባገነን ወሮበላ ዘራፊዎች ለማስከበር በጋራ በጽናት አንድ ሆነው መቆም አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ጨቋኞች እና ወሮበላ ዘራፊዎች እያንዳንዱን ሾፌር እየነጠሉ ይሰቅሉታል፡፡

የኢትዮጵያ ታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች የእነርሱ ጉዳይ የእነርሱ ብቻ አይደለም፣ ጉዳዩ የኢትዮጵያውያን በሙሉ ጭምር እንደሆነ መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ለነጻነታቸው በሚዋጉበት ጊዜ ለኢትዮጵያውያን ነጻነቶች ሁሉ እየተዋጉ መሆኑ ሊጤን ይገባል!

የኢትዮጵያ ታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች ጠንካሮች እና ህብረት የሌላቸው ከሆኑ ትልቁ መጥፎ አስቀያሚ ተኩላ አውሬ ዘ-ህወሀት እየተባለ የሚጠራው በእያንዳንዷ መንገድ ማዕዘን ላይ በመቆም እያንዳንዳቸውን ተራ በተራ ለመዋጥ ለሀጩን እያዝረበረበ በመቋመጥ ይጠብቃችኋል፡፡

የኢትዮጵያ ታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች፡ አንድነት ኃይል ነው፡፡ አንድነት በተፈጠረ ቁጥር ሁልጊዜ ድልን መቀዳጀት አለ

የኢትዮጵያ ታክሲ አሽከርካሪ ሾፌሮች ከተባበሩ ፍጹም ሊሸነፉ አይችልም! በርቱ እንዳትሸነፉ! ሌሊቱ እየነጋ ነው !  

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

የካቲት 29 ቀን 2008 .

Similar Posts