ወግ ከርዕዮት አይበገሬዋ ጋር፣

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም   

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

የጸሐፊው ማስታወሻ፡ በኢትየጵያ ውስጥ የፕሬስ ነጻነት እንዲከበር ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ላይ ካለችው ከአይበገሬዋ ርዕዮት ዓለሙ አስደናቂ ታሪክ ጋር በተያያዘ መልኩ ለማቀርበው ተከታታይ ውይይት ይህ የመጀመሪያው ክፍል ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዴሞክራሲ፣ በህግ የበላይነት፣ በሰብአዊ መብት ጥበቃ እና በተጠያቂነት ጠንካራ መሰረት ላይ ለምትገነባው በኢዲሲቷ ኢትዮጵያ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ልዩ የሆነ ጥረት በማድረግ ላይ ከሚገኙት በላስ ቬጋስ ከሚኖሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን ጋር የሚደረግ ውይይት የሚቀርብበት ነው፡፡

ርዕዮትን እንዴት እንዳገኘኋት፣

Reeyot Eskedar pix 30ርዕዮት አሁን በህይወት በሌለው እና የአለቆች ሁሉ አለቃ በነበረው በአምባገነኑ መለስ ዜናዊ የግል ትዕዛዝ እ.ኤ.አ ሰኔ 2011 በቁጥጥር ስር ከዋለች እና ወደ ማጎሪያው እስር ቤት እንድትወረወር በተደረገችበት ጊዜ አቅልን በሚያሳጣ መልኩ እጅግ በጣም ተበሳጭቼ ነበር፣ ሆኖም ግን የተለመደው የዘረኛው ቡድን ሸፍጥ ስለነበር በሁኔታው እምብዛም አልተደነቅሁም ነበር፡፡ ስለእርሷ ማንነት ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ሌላው ቀርቶ ስሟንም እንኳ በፍጹም ሰምቼ አላውቅም ነበር፡፡

እ.ኤ.አ በ2005 በኢትዮጵያ ተድርጎ የነበረውን የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ ተከትሎ ተከስቶ በነበረው ውዝግብ እርሱን እንደ መልዓክ የማያመልኩትን እና የማይኮፍሱትን እያንዳንዱን ጋዜጠኛ እንደ አበደ ውሻ እየሮጠ እና እየተክለፈለፈ መንከስ ጀመረ፡፡ የእኔ ግላዊ መርህ በአምባገነኑ መለስ ዜናዊ እና በእርሱ ዘ-ህወሀት ጥቃት የሚደርስበትን ማንኛውንም ጋዜጠኛ መከላከል ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ምክንያት ነው ርዕዮትን ለማግኘት የቻልኩት፡፡

አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ለይስሙላው ፓርላማ ተብየው ርዕዮት በዓለም የመጀመሪያ ደረጃን የያዘች እና ስሙ በማይታወቅ ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድን እና የኢትዮጵያ ጎረቤት በሆነችው በኤርትራ ድጋፍ አማካይነት መሰረተ ልማቶችን፣ የቴሌኮሙኒኬሽን እና የኃይል መስመሮችን ለማውደም ዕቅድ ነድፋ ስትንቀሳቀስ የነበረች አሸባሪ ናት በማለት የእዩልኝ እመኑልኝ ንግግሩን ካደረገ በኋላ የርዕዮት ቁጥር አንድ አድናቂ እና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሀሳብ ዳኝነት ፍርድ ቤት ፊት በመቆም ለእርሷ እራሴን ጠበቃ አድርጌ ቆምኩ፡፡ ዓይኑን በጨው አጥቦ በድርቅና እንዲህ አለ፣ “ርዕዮት የአሸባሪዎች ተላላኪ ናት“  ወዘተ፣ ወዘተ ወዘተ…

በአምባገነኑ መለስ ዜናዊ ውንጀላ ላይ ከት ብዬ ሳቅሁ፣ ምክንያቱም የእርሱ መሰረተቢስ ውንጀላዎች የሚያስቁ ብቻ አልነበሩም ሆኖም ግን ከምንም ጥርጣሬ በላይ ተራ ቅጥፈት እና ነጭ ውሸት ነበሩና፡፡

አምባገነኑ መለስ ውንጀላውን እየሰጠ በነበረበት ጊዜ የዘህወሀት (የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ) አገዛዝ የቴሌኮሙኒኬሽን ተቋማትን በእርግጠኝነት አውድሞ ነበር፡፡

አሌክሳንደር ግራህም ቤል በመሳሪያ የድምጽ ግንኙት መሳርያ ከፈጠሩ በኋላ ንጉስ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የቴሌፎን እና የቴሌግራፍ አገልግሎትን እ.ኤ.አ በ1889 በአፍሪካ አህጉር ያስተዋወቁ የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሪ መሆናቸው የታሪክ እውነታ ነው፡፡ በጭንቀት ላይ የነበሩት መኳንንቶቻቸውና ቀሳዉስት ይህ የሰይጣን ስራ ነው እናም መወገድ አለበት በማለት ለዳግማዊ አጼ ምኒልክ በነገሯቸው ጊዜ አጼ ምኒልክ ይህንን ለስልጣኔ ጸር የሆነውን አባባል ወደ ጎን በመጣል የኢትዮጵያን የቴሌኮሙኒኬሽን መሰረተ ልማት ግንባታ በቆራጥነት አስጀመሩ፡፡ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በስራ ላይ ማዋል በአውሮፓ ኃያላን ላይ እንደ ሀገር ጠንካራ ሆነን ለመኖር የሚያስችለን እና የተማሩ ሰዎችን ለማግኘት ያለንን ፍላጎት የሚያሳካልን ነው በማለት አጽንኦ ሰጥተው ተንቀሳቅሰዋል፡፡

ከ127 ዓመታት በኋላ እ.ኤ.አ በ2016 ኢትዮጵያ ከዓለም በአስከፊነቱ የመጀመሪያውን ደረጃ የያዘ የቴሌኮሙኒኬሽን መሰረተ ልማትን ይዛ ትገኛለች፡፡

ሁሉም ነገሮች በዚያው ይቀጥላሉ ብለን ብናስብ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ1889 የነበረችበት የቴሌኮሙኒኬሽን መሰረተ ልማት ግንባታ አሁን በ2016 ካለበት ሁኔታ የተሻለ ነበር ማለት አስደናቂ ሊሆን አይችልምን? ምን ዓይነት የወረደ እና አሳፋሪ ነገር ነው እባካችሁ! ይኸ ጉዳይ‘ወደ ታች ነው እንጅ ውኃ አወራረዱ ሽቅብ ሽቅብ አለኝ እኔንስ ለጉዱ’ ማለት አይደለምን?

እ.ኤ.አ በ2013 ፍሪደም ሀውስ/Freedom House የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት እንዲህ የሚል ዘገባ አቅርቦ ነበር፣ “እጅግ በጣም አናሳ የሆነ የመሰረተ ልማትን በመያዝ፣ መንግስት የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፉን በብቸኝነት ጠቅልሎ በያዘበት ሁኔታ እና ችግር ፈጣሪ የቴሌኮም ፖሊሲዎች እየተነደፉ በስራ ላይ እየዋሉ ባለበት ሁኔታ ኢትዮጵያ በኢንተርኔት እና በተንቀሳቃሽ ስልክ አጠቃቀም መጣኔ መስፈርት ከዓለም በመጨረሻው ደረጃ ላይ ከሚገኙ ሀገሮች አንደኛዋ ሆና ትገኛለች…“

እ.ኤ.አ በ2014 ዎል ስትሬት ጆርናል/Wall Street Journal የተባለው መጽሄት የኢትዮጵያ ገበሬዎች የተንቀሳቃሽ ስልኮች ያሏቸው ቢሆንም ትልቁ ችግር የተሻለ የግንኙነት መስመር ለማግኘት በርካታ ኪሎ ማይሎችን መጓዝ ይኖርባቸዋል በማለት ዘግቧል፡፡ ኢትዮጵያ በኢንተርኔት አጠቃቀም አስከፊነት ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ እንደ ፍሪደም ሀውስ ዘገባ ከሆነ ከአዲስ አበባ በስተደቡብ በኩል በ450 ማይሎች ርቀት ላይ የምትገኘው ኬንያ በኢንተርኔት አጠቃቀም ፍጥነት እ.ኤ.አ በ2012 ከጋና ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች በማለት ዘግቧል፡፡ እ.ኤ.አ በ2016 የኬንያ የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ እድገት “ምንም ዓይነት የቴክኖሎጂ እድገት ያልተጓደለበት ምሉዕ“ እየተባለ ይጠቀሳል፡፡

እንግዲህ እንደዚህ ያለውን እና በአፍሪካ በአስከፊነቱ የሚታወቀውን የቴሌኮሙኒኬሽን ስርዓትን ነው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ርዕዮት ልታወድመው ዕቅድ ነድፋ ተነስታለች በማለት ውንጀላ ያቀረበው! አዬ ጉድ! መለስ “ባለራዕይው መሪ”!

ያም ሆነ ይህ የርዕዮትን በቁጥጥር ስር መዋል ተከትሎ በአምባገነኑ መለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት (አንዳንድ ጊዜ ቃሊቲ የማጎሪያ እስር ቤት እየተባለ በሚጠቀሰው) ስለእርሷ ሁኔታ የተሟላ መረጃ ይደርሰኝ እንደነበር በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡

በዚህ ተከታታይነት ባለው ውይይት ላይ የርዕዮትን ወይም ደግሞ የእርሷን ልዩ ወላጆች (ርዕዮትን እና እህቷን እስከዳርን የሰጡንን ወላጆች ልዑል አምላክ ይባርካቸውና) ታሪክ ለመዘገብ አይደለም ዋናው ትኩረቴ፡፡ ሆኖም ግን የርዕዮት ጽናት ያለው እውነታ፣ ድፍረት፣ አርበኝነት፣ መስዋዕትነት፣ ክብረ ሞገስ፣ ታማኝነት፣ የሞራል ልዕልና እና ሰብአዊነት ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ለነጻነት የሚያነቃቃ እና ለእምነታቸው በጽናት እንዲቆሙ የሚያደርግ በፍቅር የተሞላ ተስፋ ፍንትው እና ወለል ብሎ ስለሚታየኝ ነው፡፡ በእርግጠኝነት እርሷ እኔን የበለጠ እንድነሳሳ አድርጋኛለች፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ውይይቴን ከርዕዮት ታሪክ ጋር እቀጥላለሁ፣ ስለሆነም በእርሷ ላይ የተፈጸመውን ሰብአዊ ወንጀል እና በሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ሰብአዊ ወንጀል የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በእርሷ መነጽር ለማየት እንዲችል በማሰብ ነው፡፡ በርዕዮት ላይ የተፈጸመው ሰብአዊ ወንጀል ሁሉ በእያንዳንዱ የፖለቲካ እስረኛ ኢትዮጵያዊ ላይ ይፈጸማል፡፡ ርዕዮት እራሷን በዘ-ህወሀት ሰብአዊ ወንጀል የተፈጸመባት አንድ ልዩ የጥቃት ሰለባ አድርጋ አትቆጥርም፡፡ ይልቁንም በዘ-ህወሀት የማጎሪያ እስር ቤት ውስጥ ዘብጥያ ተጥለው ከሚገኙ በብዙ ሺዎች ከሚቆጠሩ ከታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች መካከል እራሷን አንዷ አድርጋ ታቀርባለች፡፡ የእርሷ ትግል ለእርሷ ነጻነት አይደለም፣ የእርሷ ትግል ይልቁንም ከጎሳ፣ ከኃይማኖት፣ ከቋንቋ፣ ከክልላዊነት እና መንደርተኝነት፣ ከጾታ፣ ወዘተ የጸዳ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ነጻነት ማቀዳጀት ነው፡፡

ርዕዮትን መግለጽ እንዲህ ቀላል ነገር አይደለም፡፡

ርዕዮት በበርካታ መንገድ ከህይወት ተምሳሌት በላይ ናት፡፡ ገና የ31 ዓመት እድሜ እንደነበራት አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ወደ ማጎሪያው እስር ቤት ወረወራት፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት በግንባር በአካል ባገኘኋት ጊዜ ሳስበው ከነበረው እና ከምንም ነገር በላይ ሆና ነው ያገኘኋት፡፡

አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ስለእርሷ ጉዳይ ለይስሙላው ፓርላማ እዩልኝ እመኑልኝ የውንጀላ ዲስኩር ባቀረበበት ጊዜ አንድ አስፈሪ የሆነ ሰው፣ እሳት የሚተነፍስ፣ አስፈሪ እና የፍሀት ማዕበልን የሚረጭ ነገር እንደገጠመው ነበር የጠበቅሁት፡፡ አስፈሪውን ተምሳሌት እንደሚጋፈጥ ነበር የጠበቅሁት፡፡ (ምናልባትም አስፈሪ የሚለውን ቃል በዚህ ጽሁፍ ማቅረብ ስህተት ሊሆን ይችላል)፡፡

ርዕዮት ባለ ትንሽጠርዝ ወጣት ሴት ናት፡፡

ገና በመጀመሪያ ዓይን ለዓይን በተገናኘንበት ጊዜ ለእርሷ ያቀረብኳቸው ቃላት እንዲህ የሚሉ ነበሩ፣ “አንች ርዕዮት ነሽን?! ምንም አታስፈሪም!“ በሳቅ ፈነዳች፡፡

በእርግጥ እየቀለድኩ አይደለም፡፡ በእርግጥ ቃላትን በስሜታዊነት እየወረወርኩ ነው፡፡

የእርሷ ቀለል ሆኖ የመቅረብ ሁኔታ ርዕዮትን ለመግለጽ ከባድ አድርጎታል፡፡

ርዕዮት ልክ እንደ አልማዝ ናት፡፡ ፊለፊት ሲመለከቷት ታንጸባርቃለች፣ እናም የብርሀን ፍንጣቂ ትረጫለች፡፡

ከእርሷ ጋር ለጥቂት ደቂቃዎች መነጋገር መቻል ማለት ሌላውን የአልማዝነቷን ጥራት መመልከት ማለት ነው፡፡ የአረብ ብረት ነርቭ የተጎናጸፈች፣ አንጸባራቂ የብረት የማድረግ ኃይል ያላት እና የሲልቨር ብረት ጽናትን የተላበሰች አይበገሬ ጀግኒት ናት፡፡

ርዕዮት ግልጽ የሆነ እና ወገናዊ ፍቅርን የተላበሰ ስብዕና ያላት ጀግኒት ናት፡፡ እንዲህ የሚለውን የህይወቷን ተልዕኮ ሚስጥር አድርጋ አትይዘውም፣ “እኔ በኢትዮጵያ ለነጻነት እና ለዴሞክራሲ ካልቆምኩ ሌላ ማን ሊያደርገው ይችላል?“

እኔ ለእራሴ እንዲህ በማለት አጉረመረምኩ፣ “ወይ ጉድ!!! አምላኬ! መለስ ዜናዊ እና የእርሱ ወሮበላ የዘራፊዎች ስብስብ ምንድን አይነት ሰው የፈጠሩት!?“

(ወደ ኋላ መለስ ብዬ ስመለከት በእያንዳንዷ ቀን ለአስር ዓመታት ያህል ለመሳሳይ ጥያቄ በጽናት በመቆም ስታገል ቆይቻለሁ በማለት መናገር እችላለሁ፡፡ ስለሆነም የርዕዮትን የህይወት ተልዕኮ ለመገንዘብ ችግር አይኖርብኝም፡፡ በእርግጥ የእኔን ትንሽ ጥረቶች ከርዕዮት መስዋዕትነት ወይም ከእርሷ ወሰን ከሌለው ድፍረቷ ጋር ላነጻጽረው አልችልም፡፡)

አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ርዕዮትን ወደ ማጎሪያው እስር ቤት ከመወርወሩ በፊት አንድ ተራ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት፣ ጋዜጠኛ እና በየሳምንቱ እየታተመ የሚወጣው የፍትህ ጋዜጣ ዓምድ ጸሀፊ ነበረች፡፡ (የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው አይበገሬው ተመስገን ደሳለኝ በአሁኑ ጊዜ በዘ-ህወሀት የማጎሪያ እስር ቤት ታስሮ ይገኛል፡፡)

አምባገነኑ መለስ ዜናዊ አንዷን ተራ መምህርት እና ጋዜጠኛ አምባገነናዊ እና ጨቋኝ ስርዓትን ወደምትገዳደር እና ወደምትፋለም ደፋር ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነጻነት ታጋይነት አሸጋገራት፡፡

አውነት እላችህዋለሁ፡ አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ርዕዮት እንድትፈጠር ስላደረገ አመሰግነዋለሁ፣ ምክንያቱም እንደ አረብ ብረት በጠነከረው ጽናታቸው፣ በአይበገሬው ድፍረታቸው እና በመርህ ላይ በተመሰረተው ትግላቸው የኢትዮጵያ ወጣቶች አስከፊው የጭቆና አገዛዝ ከጉልበታቸው ስር ወድቆ እንዲማጸን የሚያስችላቸው ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡

ሆኖም ግን ስለአምባገነኑ መለስ ዜናዊ በአእምሮዬ ጭንቅላት ውስጥ እየተብላላ ያለ አንድ ጥያቄ አለ፡፡ እርሱም፣ “በእርግጥ አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ርዕዮት አሸባሪ ሆና እስከ አፍንጫዋ ቦምብ ታጥቃ የቴሌኮሙኒኬሽን መሰረተ ልማትን ዒላማ በማድረግ ለማውደም ከወዲያ ወዲህ በማለት ስትቅበዘበዝ ነበር ብሎ በእርግጠኝነት ያምናልን?“ ያንን የሚያምን ከሆነ የምስክር ወረቀት የተሰጠው የአዕምሮ በሽተኛ ነው ወይም ደግሞ የለየለት ቦቅቧቃ ፈሪ አለያም ሁለቱን ነው፡፡

ስለበርካታ ጉዳዮች ለሰዓታት ተነጋገርን፡፡ ውይይቶቻችን ሙሉ በሙሉ ነጻነትን የተላበሱ ነበሩ፡፡ የወጣት አፈታሪኮች እንደሚሉት “በጥሩ ሁኔታ አወጋን፡“

ስለዘ-ህወሀት ዕንጭጫዊ አጭበርባሪነት፣ ስለድድብናቸው እና ባዶነታቸው፣ ስለድንቁርናቸው እና እብሪታቸው፣ ስለአቅመቢስነታቸው እና ስለጨካኝነታቸው፣ ስለጥላቻቸው እና ጥልቅ ጥላቻቸው፣ ስለአውሬነታቸው እና ኢሰብአዊነታቸው፣ ስለዘራፈ ወሮበላነታቸው እና እርባናቢስ ባህሪያቸው፣ ስለቅጥፈታቸው፣ ስለአታላይነታቸው እና ስለመረጃ አፋላሽነታቸው፣ ስለሙሰኛነታቸው፣ ስለአድሏዊ እና ወገንተኝነታቸው በስፋት እያነሳን በቆየንባቸው ጊዚያት በሙሉ ሳቅን፡፡ ሳቅን፣ እናም እንደገና ሳቅን…

ሪዮትን ለማግኘት ሲሄድ ሃሳቤ በአምባገነኑ መለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት ውስጥ ሆና ሲደርስባት የነበረውን ኢሰብአዊ ወንጀል ለማስተዛዘን ነበር::  ስለእርሷ እስራት እና ስለሌላውም ነገር ሁሉ የሆድ ቁርጠት እና የእራስ ምታት ይሆንበኝ እንደነበር ልነግራት እንደምፈልግ ነገርኳት፡፡

በመለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት ውስጥ ሆና እንዴት እንዳሳለፈችው እንድትነግረኝ እየተዘጋጀሁ ባለሁበት ሁኔታ ከመቅጽበት ሳቋን ለቀቀችው፡፡ ተደናገርኩ፡፡

ይልቁንም ለአራት ዓመታት በእስር ቤት ውስጥ በማማቀቅ መንፈሳዊ ጥንካሬዋን ለመስበር ሲያደርጉት በነበረው ያልተሳካ ሙከራ የሆድ ቁርጠት እና የእራስ ምታት የሆነባቸው የእራሱ የዘ-ህወሀት ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አባላት ናቸው፡፡ ምናልባትም ለእነርሱ ላዝንላቸው እችላለሁን?

ልንገራችሁ ርዕዮት በጣም ቧልት ታውቃለች ፡፡

ያም ሆነ ይህ ዘ-ህወሀት በእርሷ ላይ ምን እንደሰራ እንድትነግረኝ ጠይቂያት ስለዘ-ህወሀት ያለውን ሁሉ ኢሰብአዊ ወንጀል አንድ በአንድ ልቅም አድርጋ ከነገረችኝ በኋላ ሆድን በሚያፈርስ ሳቅ ከት ብላ ስቃ ደመደመችው፡፡ እነዚህ ሰዎች ዉነት የሚአሰብ አምሮ አላቸው ብዬ ራሴን ጠየኩ::

አንደዚያ ዘህዋሃት ላይ ስንስቅ ርዕዮት የመለስ ዜናዊ እስር ቤት ተደላደላ ትኖር ነበር ማለቴ አይደለም:: ርዕዮት የመለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት ሰለባ የነበረች ስለሆነ ጠንካራ የሆነ ስሜታዊነት አይንጸባረቅባትም እያልኩ አይደለም፡፡ ርዕዮት እኔ በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ በአምባገነኑ መለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት ውስጥ ተሰቃይታለች፡፡

እጅግ በጣም አስፈሪ የሆኑ ገጠመኞችን አሳልፋለች፡፡

ለምሳሌ በስም ሀሳን ሽፋ  የሚባል አፈ ጤቀኛ ወሮበላ ዘራፊ የፖሊስ ኮሚሽነር ተብዬው ለመናገር የሚዘገንን፣ አስፈሪ እና እንደተራራ የተቆለለ የስድብ ናዳ ያወረደባትን ስታስብ በጥልቅ ታዝናለች፡፡

ያን ስሰማ እንዲህ በማለት ልነግራት ፈለግሁ፣ “ወሮበላ ዘራፊዎችን ከጫካ በማስወጣት እርካሽ ልብስ በማልበስ የባለስልጣን ስም መስጠት ይቻላል፣ ሆኖም ግን ጫካውን ከወሮበሎች ውስጥ ነጥሎ ማውጣት በፍፁም አይቻልም፡፡ ወሮበላ ዘራፊ ምንጊዜም ዘራፊ ነውና፡፡“ ይህንን በሚገባ ታውቀዋለች፣ መድገም ለምን አስፈለገ!

ርዕዮት በዘ-ህወሀት የማጎሪያ እስር ቤት በወሮበሎች በየዕለቱ ይደርስባት በነበረው ማሸማቀቅ እና ዘለፋ ሁልጊዜ ትበሳጭ ነበር፡፡

ርዕዮት በዘ-ህወሀት የማጎሪያ እስር ቤት በመታሰሯ ምክንያት በእናቷ፣ በአባቷ እና በእህቷ ይደርስ በነበረው ሊነገር በማይችለው ስቃይ እጅግ በጣም ታዝን ነበር፡፡

ርዕዮት እህቷ እስከዳር በዘ-ህወሀት ወሮበሎች ኃላፊነት በጎደለው መልኩ በተደበደበችበት እና በእራስ ቅሏ ላይ በደረሰው ስብራት ምንክንያት ለአንድ ሳምንት ጊዜ ሆስፒታል ስትታከም መቆየቷን ባወቅች ጊዜ ከቁጥጥሯ ውጭ በሆነ መልኩ አልቅሳለች፡፡

ርዕዮት በአምባገነኑ መለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት በምትሰቃይበት ወቅት ቤተቦቿ በሙሉ መለስ ዜናዊ በፈጠረው እና በኢትዮጵያ ክፍት የሆነ እስር ቤት እየተባለ በሚጠራው እስር ቤት ውስጥ ይሰቃዩ እንደነበር የምታውቀው ጉዳይ ነው፡፡

ርዕዮት ለዘ-ህወሀት ተባባሪ እንድትሆን እና ሌሎችንም በመወንጀል ተባባሪ እንድትሆን ተጠይቃ ፈቃደኛ ባለመሆኗ ምክንያት የጡት ካንሰር ኦፕሬሽን ክትትሉን እንዳታደርግ ተከልክላ በነበረበት ወቅት ተስፋ ቆርጣ ነበር፡፡ ህይወትን በሚፈታተን አደገኛ ቁስል ትጨነቅ ነበር፡፡

ርዕዮት በአምባገነኑ የመለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት ውስጥ የስነ ልቦና ዶክተር ነኝ የሚለው ደደብ በስም ዶ/ር ዓለሙ የሚባል የእርሷ ችግር የጡት ካንሰር ሳይሆን የስነ ልቦና ችግር ነው በማለት ሲነግራት ጆሮዋን አላመነችውም ነበር፡፡ ዓለሙ ከጡት ጋር በተያያዘ መልኩ ለሚመጡ በሽታዎች ባለሙያ ነኝ በማለት ከነገራት በኋላ የህክምና ስነምግባሩ ከሚፈቅደው ውጭ ጡቷን ይነካካ ይጫን ነበር፡፡ የዓለሙ የህክምና ውጤት እንዲህ የሚል ነበር፡ ርዕዮት እየተሰቃየች ያለችው በመንፈስ ጭንቀት ነው፡፡ ያ እርባናቢስ የሆነው ዶ/ር ተብዬው ዓለሙ የእርሷ ችግር ያለው ከጭንቅላቷ ነው በማለት ነገራት፡፡ ምንም ዓይነት የጡት ካንሰር የለባትም! አለ፡፡ ባለሙያ አሰዳቢ !

ርዕዮት ሀሰን ሽፋ እና ሌላው በስም ለይኩ ገብረ እግዚአብሔር በሚባል ወሮበላ ዘራፊ የዓቃቤ ሕግ ኃላፊ በሁለት በተለያዩ አጋጣሚዎች በኤሊያስ ክፍሌ ላይ የሀሰት ምስክርነት እንድትሰጥ ያለዚያ ከሞት ቅጣት እንደማታመልጥ ሲዝትባት በነበረው ሰው መሳይ ሰይጣን ላይ በጥልቅ አዝና ነበር፡፡

ሀሰን ሽፋ እና ለይኩ ገብረእግዚአብሔር ሁለቱም የሞት ቅጣት ባይፈጸምባትም እንኳ ያለምንም ጥርጥር የእድሜ ልክ እስራት ይበየንባት እንደነበር ያስፈራሯት ነበር፡፡ እድሜዋ ስንት እንደሆነ እና ከእስር ቤት ስትወጣ ስንት ሊሆናት እንደሚችል የቁጥር ስሌት ሲሰሩ ነበር፡፡ ከእስር ቤት የምትወጣበት ጊዜ 20 ወይም 25 ዓመታት እንደሚሆኑ ነግረዋት ነበር፡፡ ከዚያ ጊዜም በኋላ ጋብቻ ልትፈጽም እንደማትችል፣ ልጆች እንደማይኖሯት እና ምንም ዓይነት ሙያ እንደማይኖራት ነግረዋት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ እርሷ ምንም ነገር እንዳልሆነች ዋጋ እንደሌላት አድርገው ነግረዋት ነበር፡፡

ርዕዮት እራሷን በማረጋጋት ቆየች፡፡ የዘ-ህወሀት ፕሬዚዳንት የሞት ቅጣትን መፈረም እንደማይወድ የሰማች መሆኗን ነገረችው፡፡ ሆኖም ግን የሞት ቅጣቱን የሚፈርመው ከሆነ ርዕዮት ለወሮበላ ዘራፊው እንዲህ በማለት ነገረችው፡ “ያ ምንም ዓይነት ችግር የለውም፡፡“

እንዴ? ምን አይነት አነጋገር ነው!?  (ችግር የለም? በጣም ችግር አለ አንጂ ብዬ ከራሴ ተሟገትኩ::)

አዎ፣ ርዕዮት በዘ-ህወሀት ወሮበላ ዘራፊ ፊት በመቅረብ የሞት ቅጣቱ ለእርሷ ምንም ዓይነት ችግር የሌለው መሆኑን ነግራዋለች!

ወይ ርዕዮት! የእኔ! የእኔ፣ የእኔ ርዕዮት!!!

ለዚህም ነው እርሷን አይበገሬዋ (የማትንበረከከዋ ርዕዮት) ርዕዮት እያልኩ የምጠራት፡፡

የዘ-ህወሀትን ሰይጣን ዓይኖች ተመለከተች እና እንዲህ በማለት ነገረችው፣ “አሁን ልትገለኝ ተችላለሀ፣ ሆኖም ግን ገሀነም አስድጄ አስገባሃለሁ!“

ወሮበላ ዘራፊው ጭንቅላቱን ተመታ፡፡ እንደተቆጣ ግመር ዝንጀሮ የሚይዝ የሚጨብጠውን አጣ፡፡ ሆኖም ግን ርዕዮት ከዓላማዋ ስንዝር ያህል ፍንክች አላለችም፡፡ ስለዚሁ ጉዳይ እንድታስብበት የሶስት ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ሰጣት፡፡ ከዚያ በኋላ ተመልሳ በመሄድ ለዘ-ህወሀት ወሮበላ ዘራፊዎች ሁሉ ምላሽ ለማግኘት ሲጠባበቁ እንዲህ አለቻቸው፡ መልሴን  ለማግኘት ቀጥታ ገሀነም ሂዱ አለቻቸው ፡፡

ስለርዕዮት በርካታ አስደማሚ የሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ እናም በአምባገነኑ መለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት ውስጥ ሲፈጸሙ የቆዩትን ተሞክሮዎች በተከታታይ በማቀርባቸው ጽሁፎች የሚዳሰሱ ይሆናል፡፡ የዘ-ህወሀት ወሮበላ ዘራፊዎች ምን ያህል ጨካኞች እና ኢሰብአዊ ፍጡር እንደሆኑ ለመናገር ከማሰብ አድማሳችን ውጭ ነው፡፡ እንዴት የሰው ዘር የሆኑ ሰዎች ሰይጣንን ይሆናሉ? (በዘ-ህወሀት ባንዲራ መካከል ላይ ያለውን የኮከብ ምስል (የጨለማውን ልዑል የሚከተሉትን ዓለም አቀፍ ምስሎች) ናቸው አላልኩም፡፡)

ዘ-ህወሀት ርዕዮትን በብቻ እስር ቤት ውስጥ ለማጎር የተለየ መሰረት የሌለው ትንሽ የቆርቆሮ እስር ቤት ገነባ፡፡ ርዕዮት የምትናገረውን እና የምታደርገውን ሁሉ በየዕለቱ ዘገባ የሚያቀርቡ በዚያ መሰረት በሌለው እስር ቤት ውስጥ ከሶስት ሰላዮች ጋር እንድትቀመጥ አደረጉ፡፡

ለምንድነው ከላይ እስከታች ያሉት የዘ-ህወሀት ወሮበላ ዘራፊዎች፣ ሲቪሎች፣ ወታደሮች፣ ፖሊስ ሁሉም በርዕዮት ፍርሀት ያደረባቸው?

ሆኖም ግን አንድ ነገር አለ፣ አንድ ነገር እንደ መብረቅ የሚመታኝ፡፡ ርዕዮትን እንዲህ ልዩ እንድትሆን የሚያደርጋት አንድ ነገር አለ፡፡

ለበርካታ ሰዓት ተቀምጠን ውይይት ባደረግንበት ጊዜ በዘ-ህወሀት ወሮበላ ዘራፊዎች ላይ ምንም ዓይነት የጥላቻ፣ የፍርሀት እና የጥልቅ ጥላቻ ምልክት አላሳየችም፡፡

ፈፅሞ ሊገባኝ አልቻለም ፡፡ እንደዚያ ያለ ኢሰብአዊነት ድርጊት የተፈጸመበት፣ የተዋረደ ከህግ አግባብ ውጭ የተያዘ እና በአምባገነኑ መለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት ውስጥ የተዋረደ ሰው እንዴት እንደዚህ ያለ ጨዋ እና የመርህ ሰው ለመሆን የመቻል ነገር የሚያስደንቅ ነገር ነው፡፡

ዘ-ህወሀት ርዕዮትን በቁጥጥር ስር ባዋላት ጊዜ ምን ዓይነት ሰውን እያስተናገዱ እንደነበር ምንም ዓይነት ሀሳብ አልነበራቸውም፡፡ ርዕዮት የእርሷ ሙያ የሆነው ጋዜጠኝነት ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊ ዉጤት በሚገባ ተገንዝባ የገባችበት ነበር፡፡ አንድ ቀን በቁጥጥር ስር ውላ ወደማጎሪያው እስር ቤት እንደምትጣል ለአዕምሮዋ ምንም ዓይነት ጥያቄ እንደሌለው ታውቅ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ሰኔ 21/2012 የሆነው ታላቁ አስደናቂ የሆነባት ነገር ያ አንድ ቀን እየተባለ ይታሰብ የነበረው በጣም በተፋጠነ መልኩ የመድረሱ ሁኔታ ነው፡፡

የእርሷ አመለካከት ኢትዮጵያ በጥላቻ ነጻ ልትሆን አትችልም የሚል ነው፡፡ በጥላቻ ምንም ዓይነት የወደፊት ህይወት ሊኖር አይችልም፡፡ ሰይጣናዊውን ድርጊት ጥሉ እንጅ ሰውን አትጥሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ አመለካከት በአብዛኛው በተራው ህዝብ ዘንድ ሊተገበር የማይችል እና ጥላቻን ኃይማኖታቸው ባደረጉ የሚፈጸም አስቸጋሪ የሆነ ነገር ነው፡፡

ኔልሰን ማንዴላ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ “ጥላቻ ማለት መርዝን እንደመጠጣት እና ጠላቶቼን ይገድልልኛል ብሎ ተስፋ እንደማድረግ ያህል ነው፡፡“

በመካከለኛ አድሜዬ ላይ የበለጠ ተጠራጣሪ ሆኛለሁ፡፡ “ለወያኔ ወሮበላ ዘራፊዎች አዝናለሁ፡፡ ወሮበላ ዘራፊዎች ሁልጊዜ ያው ወሮበላ ዘራፊዎች ናቸው፡፡ ዥንጉርጉር የሆነው ጅብ የቆዳ ቀለሙን ሊቀይር ይችላልን?“ይህ ነው ዘህውሃት ማለት ::

በሲኦል ገሀነም ውስጥ ቆይታ የወጣችው ርዕዮት ዓለሙ በሰይጣኖቹ ላይ ጥላቻ ሳይኖርባት በሰይጣዊ ድርጊቱ ላይ ብቻ መዝመት እንደሚያስፈልግ በጽናት እቆማለሁ በማለቷ ኩራት ይሰማኛል፡፡ ሆኖም አስተሳሰቧ ይደንቀኛል::

እንግዲህ ለሰዓታት ያወጋህዋት ርዕዮት ማለት ይህች ናት፡፡ በፈገግታ የተሞላች እና አዲሲቷን ኢትዮጵያ የምታልም ህልመኛ፡፡

ከርዕዮት ጋር ከተነጋገርን በኋላ ከምንጊዜውም በላይ ኢትዮጵያ ተስፋ ያላት  ሀገር እንደሆነች እና የተሻለ ጊዜ እየመጣ እንደሆነ እንዲሁም የኢትዮጵያ ወጣቶች ለዓላማው ስኬታማነት በጽናት መታገል እንዳለባቸው ግንዛቤ ወስጃለሁ!

በዘህወሀት ገሀነም ውስጥ ተጋድሎ በማድረግ በድል አድራጊነት የወጣች ወጣት ሴት፣

በገሀነም ውስጥ ገብተው ሳይጎዱ፣ ሳይቃጠሉ ሳይነዱ ሳይፈርሙ፣ ምንም ዓይነት ችግር ሳያጋጥማቸው የሚወጡ በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው!

በገሀነም ውስጥ ገብተው ሰይጣኑ ላይ ተፍተው ከዚያም ወጥተው ታሪካቸውን የሚናገሩ በጣም ጥቂት ሰዎቸ ብቻ ናቸው፡፡

ከሁሉም በላይ ታላቁ ኔልሰን ማንዴላ አንዱ ሰው ነበሩ፡፡

ማንዴላ ለ27 ዓመታት ያህል የአፓርታይድን ሰይጣን ፊት ለፊት በመጋፈጥ በእያንዳንዷ ዕለት ወደ ገሀነም እንዲሄዱ ይነግሯቸው ነበር፡፡

ማንዴላ ከቨረስቴር እስር ቤት የገሀነም በር ሲደርሱ እና የመጨረሻዎቹን 14 ወራት የእስራት ዘመናቸውን አጠናቅቀው እ.ኤ.አ የካቲት 11/1990 ሲደርሱ ፈገግታ ይነበብባቸው ነበር፡፡

በኋላ ላይ ማንዴላ እንዲህ ነበር ያሉት፣ “ነጻነቴን ወደሚያስገኘው ወደ ዋናው የመውጫ በር እየተጠጋሁ በሄድኩ ጊዜ ቀደም ሲል የነበረኝን ምሬት እና ጥላቻ እዚያው ውስጥ ጥየው የማልወጣ ከሆነ እዚያው እስር ቤቱ ውስጥ መቆየት እንዳለብኝ አውቃለሁ፡፡

ማንዴላ በመሬት ላይ ለ27 ዓመታት በገሀነም ውስጥ አስገብተው ስቃይ ሲያሳዩአቸው ለቆዩት ጠላቶቻቸው ይቅርታ ማድረጋቸው ታላቅ ሰው መሆን አለባቸው ብለው ለነገሯቸው ሰዎች ቀስ ብለው በመሳቅ እንዲህ ነበር ያሉት፣ “እኔ መልዓክ አይደለሁም፣ መልዓክ እንደሆንኩ አድርጋችሁ የምታስቡኝ እስካልሆነ ድረስ ደግሜ ደጋግሜ በመሞከር ላይ ያለሁ ኃጢያተኛ ሰው ነኝ፡፡“

ማንዴላ በእራሳቸው ጨዋታ የአፓርታይድን ሰይጣን በድል አድራጊነት ተወጡት! ለመውደድ ተማር፣ ለጥላቻ አትማር በሚሉት በማንዴላ መርሆዎች፣ “በቆዳ ቀለሙ ልዩነት፣ ወይም ደግሞ በታሪካዊ አመጣጡ ወይም ደግሞ በሚከተለው ኃይማት ምክንያት ማንም ሰው ቢሆን ሌላውን ሰው ለመጥላት አልተወለደም፡፡ ህዝቦች ለመጥላት መማር አለባቸው፣ እናም ለመጥላት የሚማሩ ከሆነ ፍቅርንም መማር ይችላሉ፣ ፍቅር በተፈጥሮ በሰው ልጆች ልብ ውስጥ ከተቃቀራኒው ይልቅ ቀድሞ ይመጣልና፡፡“

ወጣቷ ኢትዮጵያዊት የፕሬስ ነጻነት ቀንዲል ርዕዮት ዓለሙ የዘመናዊውን የጥቁር ህዝቦች የዘ-ህወሀት ቀንዳም አፓርቲድ  ሰይጣን ለ1500 ቀናት እና ሌሊቶች ያህል ፊት ለፊት ተጋፍጣ ከቆየች በኋላ እርሱ እራሱ ወደ ገሀነም፣ ገሀነም፣ ገሀነም እንዲገባ በግልጽ ነገረችው!!!

ርዕዮት እ.ኤ.አ ሀምሌ 9/2015 ከአምባገነኑ የመለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት በምትወጣበት ጊዜ እንደማንዴላ ሁሉ የጥላቻ መንፈስን አላሳየችም፡፡

ለዘ-ህወሀት አፓርታይድ ሰይጣን እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት እንዲህ በማለት ነበር የተናገረችው፣ “በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እና ፍትህ ሰፍነው ለህዝቦች ጥሩ መኖሪያ እስከምትሆን ድረስ ባለኝ አቅም ሁሉ ሙሉ በሙሉ ትግሌን እቀጥላለሁ፡፡  እንደዚህ ዓይነት ኢትዮጵያውያንን እስከማይበት ድረስ ትግሌን እቀጥላለሁ፡፡“

ርዕዮት እንደማንዴላ ሁሉ በዘ-ህወሀት ጨዋታ ላይ እርሷ ሙሉ በሙሉ ድልን እንደምትቀዳጅ ግልጽ አድርጋለች፡፡ የርዕዮት መርህ፡ ትግሉ ይቀጥላል! የሚል ነው፡፡

ማንዴላ እ.ኤ.አ በ1962 የአፓርታይድ የጥቂት ነጮች የበላይ አገዛዝ የእድሜ ልክ እስራት በበየነባቸው ጊዜ የ44 ዓመት ጎልማሳ ነበሩ፡፡

ርዕዮት ዓለሙ በኢትዮጵያ የስልጣን ኮርቻ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ በሚገኘው በዘ-ህወሀት አፓርታይድ አገዛዝ በቁጥጥር ስር ስትውል የ31 ዓመት ወጣት ነበረች፡፡

ርዕዮት በመጀመሪያ በዘ-ህወሀት የይስሙላ የዝንጀሮ ፍርድ ቤት የ14 ዓመት እስራት ተበየነባት፡፡ ብይኑ በተሰጠበት ዕለት በሌሎች ንጹሀን ዜጎች ላይ የሀሰት ምስክርነት የምትሰጥ ከሆነ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወዲያውኑ እንደሚፈታት ግልጽ አደረገ፡፡ ሆኖም ግን ዘ-ህወሀትን ወደ… እንዲሄድ ነገረችው፡፡

የዘ-ህወሀት የይስሙላ የዝንጀሮ ፍርድ ቤት ብይኑን ወደ አምስት ዓመታት ዝቅ አደረገው፡፡ ይሀ በእንዲህ እንዳለ ከዕለታት በአንዱ ቀን ከማጎሪያው እስር ቤት “ውጭ” ብሎ ነገራት፡፡ ምንም ዓይነት ስነስርዓት አልነበረም፡፡ ምንም ዓይነት ማብራሪያ እና ገለጻ አልነበረም፡፡ ምንም ነገር አልነበረም፡፡ ብቻ “ውጭ” የሚል ነበር!

የርዕዮት የፍርድ ሂደት እና መከራ በዘህወሀት አውሬዎች ሆድ ውስጥ፣

አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ በእራሱ ትዕዛዝ ርዕዮት በቀጥጥር ስር እንድትውል ማድረጉ እውነት ነው፡፡

ሆኖም ግን የዘ-ህወሀት ወሮበላ ዘራፊዎች ርዕዮትን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሄዱበት አካሄድ አስቂኝ ነበር፡፡ ይህ ክስተት በፖሊስ አካዳሚ ወይም ደግሞ በኪስቶን ወታደራዊ ፊልም የሚባለው ሲንማን  ያስታዉሰኛል፡፡ ርዕዮት በቁጥጥር ስር በዋለችበት ጊዜ የፌዴራል ፖሊስ እና የጸረ ሽብር ግብረ ኃይል እየተባሉ የሚጠሩ የጨካኞች፣ የመገንዘብ ብቃት የሌላቸው እና ብቃት የለሽ የወታደር ስብስቦች በዓለም ላይ የመጀመሪያ ደረጃ አሸባሪ እያሉ የሚጠሯትን ርእዮት ዓለሙን የመያዝ ዕቅድ ነድፈው አወጡ፡፡

እ.ኤ.አ ሰኔ 21/2011 ከሰዓት በፊት በቁጥጥር ስር ከማዋላቸው በፊት በእርሷ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ቅጥረ ግቢ ውስጥ የመምህራን ስብሰባ ላይ ከርዕሰ መምህሩ ጋር አብራ ትካፈል ነበር፡፡ በትምህርት ቤት ግቢው ውስጥ ተማሪዎች አልነበሩም፡፡ መምህራን የመጨረሻ ወሰነ ትምህርት ውጤት ማጠናቀር ስራ ላይ ነበሩ፡፡

ስብሰባው ከተጀመረ ከ20 ደቂቃ አካባቢ በኋላ የትምህርት ቤቱ ድረክቶር ያለመረጋገት እና ጭንቀት ይታይበት ነበር፡፡ ተንቀሳቃሽ ስልኩ መጮህ ጀመረ፡፡ በእያንዳንዱ የድወላ ጊዜ ይወጣ እና ጥቂት ደቂቃዎችን ከቆየ በኋላ እንደገና ወደ ስብሰባው ይገባ ነበር፡፡ ርዕሰ መምህሩ ከርዕዮት ጋር መቀለድ ጀመረ፡፡ “ለምንድ ነው ከጀርባ የተቀመጥሽው?“ በማለት እራሷን ለመደበቅ የተቀመጠች በማስመሰል መልኩ መቀለድ ሞከረ፡፡

ከስብሰባው ለበርካታ ጊዚያት ሲወጣ እና ሲገባ ከቆየ በኋላ ርዕሰ ድረክቶሩ ከውጭ ዘመድ እንደሚፈልጋት ነገራት፡፡ እርሷም እውነት መስሏት መንጠቅ ብላ ስትወጣ የሲቪል ልብስ የለበሱ አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ሁለት ሰዎች ሰላምታ አቀረቡላት፡፡ እንዲህ በማለት ነገሯት፣ “ኦ፣ ዘመድ ይፈልግሻል፡፡“

ርዕዮት ግራ ተጋባች፣ ሆኖም ግን ልዩ የሆነ ጥርጣሬ አላደረባትም፡፡ ምናልባትም በቤተሰብ ላይ የደረሰ አደጋ ነገር ሊኖር ይችላል የሚል ሀሳብ አሰበች፡፡

ሁለቱ ግለሰቦች እንደህ በማለት አረጋገጡላት፣ “ኦ፣ አሁን ከዚህ በምትወጭበት ጊዜ ዘመድሽን ታያለሽ፣ አይዞሽ አትጨነቂ…ምስጢሩን ታያለሽ ፡፡“

ርዕዮት ወደ ትምህርት ቤቱ በር ለመሄድ በደረጃዎች ላይ አብራ ወረደች፡፡

ወደ ትምህርት ቤቱ በር ስትቃረብ ርዕዮት እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ እና 4 የፖሊስ ተሽከርካሪዎችን የያዙ የፌዴራል ፖሊሶችን ስብስብ ተመለከተች (በግምት ወደ 9 የሚሆኑ ዩኒፎርም የለበሱ ፖሊሶች እንደሆኑ ትገምታለች፡፡)

ከዚህም በተጨማሪ የሲቪል ልብስ የለበሱ ሌሎች ሰዎች እና መለያ የሌላቸው መኪኖች በአካባቢው ቆመዋል፡፡ እንግዲህ ከእርሷ እይታ አንጻር በአካባቢው ሄሊኮፕተሮች እና ወታደሮችን የያዙ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች አልነበሩም፡፡ ርዕዮት እያሽካኩ ባሉ እና ለሀጫቸውን እያዝረበረቡ በሚቋምጡ የጅብ መንጋዎች መካከል እንዳለ አጋዘን እና (ወይም ደግሞ እንደ አነር ነብር) ዓይነት ስሜት ተሰማት፡፡

ወደ በሩ እየቀረበች በመጣች ጊዜ ተመልሳ ወደ ት/ቤቱ ለመሄድ ሞከረች፡፡ ሆኖም ግን እርሷን አጅበው ያመጧት ሁለቱ ሲቪል የለበሱ ሰዎች አልፈቀዱም፡፡ በዚህ ጊዜ ርዕዮት ተመልሳ የተማሪዎችን ውጤት መሙላቱን ለማጠናቀቅ ተመልሳ መሄድ እንዳለባት ለመንገር ሙከራ አደረገች፡፡ ወደ በሩ አጅቧት የመጣው ሰው ምንም ነገር ማድረግ አትችይም አላት፡፡

ከትምህርት ቤቱ በር መውጣት እንደማትችል ለመገዳደር ሞከረች፡፡ በዚያን ጊዜ በርካታ የፌዴራል ፖሊሶች በድንገት ተረባረቡቧት፡፡ እርሷን ለመያዝ ሁሉም ነገር ነጻ ነበር፡፡ ከመካከላቸው አንዱ በእጇ ላይ የብረት ካቴና አስገባ፣ ሌላው እጇን ይዞ ጎተታት፣ ሌሎቹ ደግሞ ሌሎችን የአካል ክፍሎቿን ሁሉ ያዙ፡፡ የጅብ መንጋዎች አጋዘንን በሁሉም አቅጣጫ በመውረር እንደሚያጠቁት እንደሚቀራመቱት አድርጋችሁ አስቡ፡፡

እርሷ ግን እንዲህ በማለት ተቃወመች፣ “ለምንድን ነው በቁጥጥር ስር የምውለው?” እርሷን ከስብሰባው ቦታ ጀምሮ አጅቧት የመጣው ሰው እንዲህ በማለት አምባረቃባት፣ “በሽብርተኝነት ስለተጠረጠርሽ ትፈለጊያለሽ“ ብሎ ተቆታት ፡፡ እርሷን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያስችል የማዘዣ ደብዳቤ አልነበረም፣ ወይም ደግሞ ለእርሷ በቁጥጥር ስር መዋል ሊያስረዳ የሚችል ምንም ዓይነት ህጋዊ ሰነድ አልነበረም፡፡

በእጇ ላይ ካቴና ካስገቡ በኋላ እርሷን አጅቧት የመጣው የሲቪል ልብስ የለበሰ ሰው ጎትቶ በመሳብ እንደ ቁራጭ ቡትቶ ወደ ፖሊስ መኪና ውስጥ ወረወራት፡፡

ርዕዮትን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተላኩት ፖሊሶች አንዲትን ሰላማዊ ወጣት መምህርት እና ጋዜጠኛ ሴት ለመያዝ የመጡ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ የሽብር ጥቃት አቀናባሪ እና ዋና መሪ የነበረውን ኦሳማ ቢን ላደንን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተላኩ ኮማንዶዎች ይመስሉ ነበር፡፡ (እርሷን በቁጥጥር ስር ለማድረግ የተላኩት ወሮበላ ዘራፊዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትፈለገውን ርዕዮት ዓለምን በቁጥጥር ስር በማዋላቸው ምክንያት በደስታ ተውጠው በእጅ መዳፎቻቸው በኃይል እየተመታቱ የደስታ ስሜቶቻቸውን ለመግለጻቸው ግልጽ የሆነ ነገር የለም፡፡)

በእርግጥ የዘ-ህወሀት ወሮበላ ዘራፊዎች ርዕዮት በመንገድ ላይ ስትሄድ ወይም ደግሞ በመኗሪያ ቤቷ ማታ በሯን ስትዘጋ በቀላሉ በመያዝ በኃይል ሊወስዷት ይችሉ ነበር፡፡ እንዲህ ያለውን ድርጊት ሁልጊዜ የሚፈጽሙት ድርጊት ነው፡፡ ሰላማዊ ዜጎችን ያፍኑ እና የደረሱበት እንዳይታወቅ በመሰወር ደብዛቸውን ያጠፋሉ፡፡

ስለዚህ ያ ሁሉ የትምህርት ቤት ተውኔት እንዲተወን የተፈለገው ለምንድን ነው?

እኔ የማውቀው ነገር የለም፣ ሆኖም ግን የዘ-ህወሀት የጸረ ሽብር ግብረ ኃይል እንደ ኪስቶን ወታደሮች የተንከባለለው በዚህ ዓይነት መልኩ ነው፡፡

ዘ-ህወሀት ርዕዮትን በቁጥጥር ስር ለማዋል ያደረገው የትምህርት ቤት ተውኔት የዘ-ህወሀት ወሮበላ ዘራፊዎች እንደ ኪስቶን ወታደሮች እ.ኤ.አ በ1914 በወሮበሎች መዳፍ ስር እንደዋለው ክስተት አድርጌ እቆጥረዋለሁ፡፡

የዘ-ህወሀት ወሮበሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ቁጥር አንድ የሆነችውን አሸባሪ ርዕዮት ዓለሙን በቁጥጥር ስር በማድረግ በመማረካቸው እና ወደ ማዕከላዊ የፖሊስ ምርመራ እንዲሁም የስቃይ ማዕከል ወደሚባለው የሰቆቃ ቦታ በመውሰድ እንኳን ደስ ያለህ በማለት እርስ በእርስ ሲጨባበጡ ነበር፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እ.ኤ.አ በ2013: “የእምነት ቃል እንዲሰጡ መፈለግ፡ በኢትዮጵያ ማዕከላዊ የፖሊስ ምርመራ ጣቢያ ማሰቃየት እና ደካማ የሰብአዊ መብት አያያዝ“ በሚል ርዕስ በማዕከላዊ ምርመራ በርካታ የሆኑ ማሰቃየቶች የተፈጸሙ መሆናቸውን በዘገባው አካትቷል፡፡

እንግዲህ ዘ-ህወሀት ርዕዮትን ያንን ያልታቀደ ጉብኝት እንድትጎበኘው ነው ወደ ማዕከላዊ ፖሊስ ምርመራ የወሰዳት፡፡

(ይቀጥላል አንቺ ርዕዮት ዓለሙ ነሽን? ብሎ ሀሰን ሽፋ በንቀት ደነፋባት) 

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!  

የካቲት 22 ቀን 2008 .

 

 

Similar Posts