ለኢትዮጵያ አቦ ሸማኔዎች ትውልድ ልዩ መልዕክት፡ ነጻ ሆናችሁ እንደተወለዳችሁ ሁሉ ነጻ ሆናችሁ ኑሩ!

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም    

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

(የተመደበ፡ ለኢትየጵያ አቦ ሸማኔዎች ዓይን ብቻ)  

 2013 ወዲህ የመጀመሪያ መልዕክቴ፣

Cheetahs30ይህ በሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔ ትውልድ ማለትም ለኢትዮጵያ ወጣቶች ለሁለተኛ ጊዜ ያቀረብኩት ልዩ መልዕክት  ነው፡፡

እ.ኤ.አ ጥር 2013 ዓመቱ የኢትዮጵያ አቦ ሸማኔ ወጣት ትውልድ ዓመት እንደሚሆን የአዲስ ዓመት መልዕክቴን ጽፌ አስተላልፌ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ “ምርጦቹ እና የብሩህ አዕምሮ ባለቤት” የሆኑትን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁትን እና ባለሙያዎችን ብቻ ያካተተ ሳይሆን በነጻነት ለመተንፈስ ተጋድሎ እያደረጉ ያሉትን ሁሉንም በአንድነት የሚቆሙ የወጣቶች ስብስብን ያቀፈ  ነው በማለት ገልጨ ነበር፡፡

የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ህወሀት) አድሎአዊ አሰራር፣ የጓደኝነት ስራ፣ ሙስና እና የሰብአዊ መብቶች ረገጣ ሰለባ ለሆኑት ለሁሉም በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩት ወጣቶች የክርክር መድረክ እንዲፈጠር ጥሪ አቅርቤ ነበር፡፡

እንደዚሁም ሁሉ ለኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ትውልድ እና የዘ-ህወሀት የፖለቲካ እስረኞች ማለትም እስክንድር ነጋ፣ አንዷለም አራጌ፣ ውብሸት ታዬ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ በቀለ ገርባ፣ ኦልባና ሌሊሳ እና ሌሎችም እንደ እነርሱ ያሉት በርካታዎቹ የሞራል መሪዎች ከማጎሪያው እስር እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቤ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ በ2013 አቅርቤው በነበረው መልዕክቴ የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ ሀገሪቱን ከዘ-ህወሀት የጭካኔ እና አምባገነናዊ የግፍ አገዛዝ የብረት መዳፍ አደጋ ውስጥ ፈልቅቆ ሊያወጣት የሚችል ብቸኛው ትውልድ ነው በማለት አውጀ ነበር፡፡ ይህ ወጣት ትውልድ ኢትዮጵያን ከጨካኝ አምባገነኖች የእባብ መርዝ አደጋ ውስጥ ሽራ እንድትወጣ ማድረግ የሚችል ብቸኛው እና በቅጥፈት እና በሙስና ላይ የተገነባውን ይህንን የበሰበሰ እና በወታደር ኃይል የቆመ ምንም ዓይነት ኃላፊነት የማይሰማው የበከተ መንግስት አሽቀንጥሮ በመጣል ወደታሪከ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ የሚጥለው ይኸው ወጣት ትውልድ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ ይፋ ያልሆኑ የክርክር መድረኮችን በእራሳቸው መካከል ማካሄድ መጀመር እና የእራሳቸው ብሄራዊ ዕርቅ መወሰን እንዳለባቸው ጥሪ አቅርቤ ነበር፡፡

እንዲሁም ወጣቶች እራሳቸውን እንዲያጠናክሩ እና የእራሳቸውን የፖለቲካ ምህዳር እንዲፈጥሩ እና በጎሳ፣ በኃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በጾታ፣ በክልል እና በመደብ መስመሮች ላይ አንድ በአንድ እያነሱ እንዲነጋገሩባቸው ተማዕጽኖዬን አቅርቤ ነበር፡፡

የጾታ ልዩነቱን በመዝጋት እና የወጣት ሴቶችን ተሳትፎ ከምንጊዜውም በላይ በማሳደግ በብሄራዊ ዕርቅ ንግግሩ ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስምሬበት ነበር፡፡ ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ወደ ስምምነት፣ እርቅ እና ግጭትን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ረገድ በእጅጉ ከወንዶች እንደሚልቁ በማህበራዊ ሳይንሳዊ መረጃዎች በተደገፈ መልኩ ለማቅረብ ሞክሬ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ውይይት እርስ በእርስ መነጋገርን ብቻ የሚያካትት አይደለም፣ ሆኖም ግን  እርስ በእርስ መደማመጥ አስፈላጊ እንደሆነ ምክሬን ለግሸ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ ብዝሀነታቸውን እንደ ጥንካሬ በመጠቀም እና በተጻራሪው ብዝሀነታቸውን ለከፋፍለህ ግዛ እና ለሽንፈት ለሚያበቃቸው እኩይ ምግባር በፍጹም ቀዳዳ እንዳይከፍቱ ተማዕጽኖ አቅርቤ ነበር፡፡

ለመሆኑ ባለፉት ሶስት ዓመታት ምን ተከናወነ?

የኢትዮጵያ አቦ ሸማኔ ወጣት ትውልድ ሙሉ በሙሉ የነቃ ለመሆኑ አምናለሁ፡፡ ጥቂት የአቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ በአሁኑ ጊዜ እንደምናየው በንዴት በመነሳት በአይበይገሬነት ዘ-ህወሀትን በመገዳደር እና ጉሮሮ ለጉሮሮ በመተናነቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በመንሾካሾክ እና በማጉተምተም ላይ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ ደስተኛ አይደሉም፡፡ ለዚህም ነው በመላ ሀገሪቱ ጅቦቹን በመጋፈጥ በማጉተምተም ላይ ያሉት፡፡

ለኢትዮጵያ አቦሸማኔ ወጣት ትውልድ የእኔ አዲሱ የመገዳደር መልዕክቴ፣

የኢትዮጵያ የጉማሬው ትውልድ (በእርግጠኝነት በምርጫም ባይሆን እኔም አባል የሆንኩበት) የጨነገፈው የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔ ትውልድ እንደሆነ አምናለሁ፡፡

ጆርጅ አይቴ የአፍሪካን የጉማሬ ትውልድ እንዲህ በማለት በትክክል ገልጸውታል፣ “በምሁራዊ ጨለምተኝነት የታጠሩ እና አመክንዮአዊነት በራቀው የቅኝ ገዥዎቻቸው የተለጣጠፈ የትምህርት ዘይቤ ላይ እንደ መዥገር የተጣበቁ“ በማለት ገልጸዋቸዋል፡፡ ነጮች በጥቁሮች ላይ የሚያደርጉትን የኢፍትሀዊነት ደባ በጭልፊት ዓይን ግልጽ በሆነ መልኩ ገና ከሩቅ ያዩታል፡፡ ሆኖም ግን እነርሱ በእራሳቸው ጥቁር ዜጎች ላይ ለሚያደርጉት የበለጠ ሰይጣናዊ ለሆነው ተስፋ በሌለው መልኩ እውር ይሆናሉ…”

እኛ ኢትዮጵያውያን የጉማሬው ትውልድ አባላት በጎሰኝነት፣ በኃይማኖት ጽንፈኝነት፣ በፍርሀት እና በጥላቻ በመታወር አመክንዮአዊ በጎደለው የትምህርት ዘይቤ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀን ህሊናን በሳተ መልኩ አውዳሚ የሆነውን የፖለተካ ጎማ በማሽከርከር ላይ እንገኛለን፡፡

አሁን ለተወሰነ ጊዜ በፖለቲካ ኮማ (መንፈስ መደንዘዝ) ደረጃ ውስጥ በመግባት በድን ሆነን እንገኛለን፡፡ ያንኑ የዱሮውን ያፈጀውን እና ያረጀውን እንዲሁም ተደጋግሞ የሚነገረውን እና አሰልችውን አንድ ዓይነት መዝሙር በመዘመር ያለፉትን ሀሳቦች በመኮነን አንድ ዓይነት ነገርን በማነብነብ እናወጣለን፡፡ በማንኛውም ነገር ላይ አሳፋሪ በሆነ መልኩ ከዘ-ህወሀት አሻሻ ገዳሜ ዳንስ ጋር በመሰለፍ አብረን እንሾራለን፡፡ በአቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ ላይ የምናሳርፈው ተጽዕኖ ጎታች፣ ከአድራጊነት ስሜት የሚገታ፣ ራዕይ የለሽ የሚያድርግ እና ሙሉ በሙሉ ከፈጠራ ስራ የሚያኮላሽ ነው፡፡

እኛ የጉማሬው ትውልድ አባላት ለአቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ ያተረፍንለት ነገር ቢኖር የውድቀት ትሩፋት፣ ተጠራጣሪነት፣ ያለመተማመን፣ ህብረት የለሽነት፣ ጥላቻ፣ የደስታ እጦት፣ ወኔቢስነት፣ ፍላጎት የለሽነት፣ ተምኔታዊነት እና በእራስ አለመተማመንን ነው፡፡

እስቲ ትንሽ እናፍታታው!

ይኸ እየተሰጠ ያለው ማብራሪያ እያንዳንዱን የኢትዮጵያን የጉማሬ ትውልድ አባላት በመውቀስ በጅምላ እራሱን በእራሱ የሚከስ የጉማሬው ትውልድ አባል ይመስላል፡፡ በእርግጥ ይህ የአንድ የጉማሬው ትውልድ አባል ግላዊ እምነት ነው፡፡ የእኔን አመልካች ጣት በሌሎቹ ላይ በምቀስርበት ጊዜ ሶስቱ ጣቶቼ ወደ እራሴ እንደሚያነጣጥሩ እየመረረኝም ቢሆን እገነዘባለሁ፡፡

በተወሰኑ ልማዶች ጥፋትን ማመን ብዙውን ጊዜ ንስሀ የመግባት ድርጊትን ያስከትላል፡፡ ይህም ማለት በቀደሙ ጊዜ የተሰራን መጥፎ ድርጊት በመልካም ነገር ለመካስ ሲባል ስህተት መሆኑን በማመን ሀጢአትን መናዘዝ እና መልካም ነገርን ለመስራት ቃል ኪዳን መግባት ማለት ነው፡፡

እንግዲህ ይህ የእራሴን ኃጢአት በመናዘዝ በቀጥታ ከኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ ጋር በመቀላቀል ለለውጥ እንዲነሱ እና የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን እንዲወስኑ ማድረግ ነው፡፡ (ኃጢያቴን በመናዘዙ ረገድ የተጋነነ የሞራል ልዕልናን እንዳሳየሁ እና ስብከት መሳይ ነገርን ያደርግሁ እንደሚመስል አምናለሁ፡፡ ሆኖም ግን እራሴን በመሻሻል ላይ ያለሁ አድርጌ እቆጥራለሁ፡፡ በጊዜ ሂደት አሻሽላለሁ፡፡)

በዚህ ዓመት በማስተላልፈው መልዕክት የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔ ትውልድ አዕምሯቸውን ክፍት በማድረግ እና ለእራሳቸው በማሰብ፣ ትክክለኛ እና ጠጣር ጥያቄዎችን በመጠየቅ እንዲሁም እንደ ነጻ ወንዶች እና ሴቶች ሆነው ለህሊናዎቻቸው እንዲኖሩ ለማድረግ መገዳደር ነው፡፡

እነዚህን መገዳደሮች ለመቀመር አልበርት አነስታይን በአንድ ወቅት እንደተመለከቱት እና እንዲህ በሚለው በጣም እመሰጣለሁ፣ “አንድን ችግር ለመቅረፍ የአንድ ሰዓት ጊዜ የሚኖረኝ ከሆነ 55 ደቂቃውን ስለችግሩ በማሰብ አጠፋለሁ፡፡ በ5ቷ ደቂቃ ውስጥ ደግሞ ስለመፍትሄው አስባለሁ፡፡“ ብለዋል፡፡

አነስታይን ያስተላለፉት ዋናው መልዕክት አንድ ሰው ችግሩን ለመገንዘብ በርካታ ጊዜ የሚያጠፋ ከሆነ ለችግሩ በጣም ውጤታማ የሆነ መፍትሄን እና ውሳኔን የማምጣት ዕድሉ ከፍተኛ ይሆናል ለማለት እንደሆነ አስባለሁ፡፡ አብዛኞቻችን (ከእራሴ ጀምሮ) አምባገነኖችን ከማስወገድ እና ድህነትን ከስሩ መንግሎ በመጣል ሁሉንም የኢትዮጵያን ችግሮች ለማጥፋት መፍትሄዎች እንዳሉን የእራሴ ምልከታ አለኝ፡፡ አብዛኞቹ መፍትሄዎቻችን በግማሽ የተጋገሩ፣ ቅርብ ዕይታን የያዙ፣ የመከኑ እና በድክመት የታሰቡ ናቸው ማለት እችላለሁ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አነስታይን እንዲህ የሚል ምልከታን አድርገዋል፣ “ማሰብ ከእውቀት የበለጠ ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ እውቀት ለሁሉም ውሱን እንደመሆኑ መጠን አሁን ልናውቅ እንችላለን እናም ልንገነዘብ እንችላለን፡፡ ማሰብ ግን ዓለምን በሙሉ ያቅፋል፣ እናም ሁሉም ነገር ለማወቅ እና ለመገንዘብ ይሆናል፡፡“ ጆርጅ በርናርድ ሻው የበለጠ ውበትን በተላበሰ መልኩ እንዲህ ብለዋል፣ “ነገሮችን ታያለህ፣ እናም እንዲህ ትላለህ፣ ‘ለምን?‘ ሆኖም ግን ስላልነበሩ ነገሮች አልማለሁ፣ እናም እንዲህ እላለሁ፣ ‘ለምን አይሆንም?’“ እንግዲህ እየተናገርኩ ያለሁት ስለእንደዚህ ዓይነቱ ማሰብ ነው፡፡

አነስታይን ማለት ፈልገው የነበረው የሰው የወደፊት አቅም እና ዕድል በእርግጠኝነት በምናውቀው ነገር የሚወሰን አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ከዚህም በተጨማሪ ልናስበው በምንችለው ነገር ነው የሚወሰነው፡፡ እንዲህ የሚለውን ታላቅ ቆንጆ የማሰብ ጥያቄን ጠይቀው የነበሩት አነስታይን ናቸው፣ “በህዋ ላይ በብርሀን ፍንጣቂ እየጋለብኩ ብሄድ ምን ይፈጠራል?“ ይህንን ነገር እስቲ አስቡ!!!

የኢትዮጵያን የአቦ ሸማኔ ወጣት ትውልድ በህዋ ላይ አቋርጦ በሚሄድ የብርሀን ፍንጣቂ እንዲጋልቡ አልማጸንም፡፡

በእርግጠኝነት እንዲበሩ ነው የምፈልገው፡፡ በባርነት ውስጥ ከሚዘፍቅ የጎሳ ፖለቲካ በርረው እንዲያመልጡ ነው የምፈልገው፡፡ ከአምባገነንነት በነጻነት ብረሩ፡፡ ከሙስና እና ከሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ነጻ ሁኑ፡፡

ብዙም ሳይርቅ ዘ ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሔት ለበርካታ ዓመታት በአዕምሮየ ውስጥ ሲብላላ የቆየውን ጥያቄ ጠየቀ፡፡ እንዲህ የሚለው ያ ጥያቄ እንደ መብረቅ መታኝ፣ “ኢትዮጵያውያን በእርግጠኝነት ነጻ ቢሆኑ ኖሮ ምንድን ይሆን ነበር?

ዘ ኢኮኖሚስት እራሱ የጠየቀውን ጥያቄ እራሱ እንዲህ በማለት መለሰው፡ “መንግስት የኢትዮጵያን ህዝብ በነጻነት እንዲተነፍስ ቢያደርግ ኖሮ ይበሩ ነበር፡፡“

የኢትዮጵያን ህዝቦች በነጻነት ለመተንፈስ ያለመቻል ችግር ለ55 ደቂቃዎች ያህል አሰብኩ፡፡ ከዚያም ስለመፍትሄው በማሰብ 5 ደቂቃዎችን አጠፋሁ፡፡

“ብረሪ ኢትዮጵያ፣ ብረሪ…የአቦ ሸማኔ ወጣት ትውልድ ብረሩ፣ ወደ ሰማይ ከፍ ብላችሁ ብረሩ…“ በሚለው ትችቴ ላይ የሀሳብ በረራን አከናውኛለሁ፡፡

ኢትዮጵያውያን መብረር የሚችሉ ቢሆን ኖሮ ለመሞት ወደ ባህር አቅዋርጠው አይሄዱም ነበር እላለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሴቶች ባሮች ለመሆን ወደ መካከለኛው የአረብ ሀገሮች አይሄዱም ነበር፡፡ ደም ለጠማቸው አሸባሪዎች ሰለባ ለመሆን በረሀዎችን አቋርጠው አይሄዱም ነበር፡፡ ወደ ስደት ሀገር አይሄዱም ነበር፡፡ የሚበሩ ቢሆን ኖሮ እንደ አፍሪካ ተሙለጭላጭ አሳ እንደ ባህር ወፍ አይገለባበጡም ነበር፡፡ ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ከፍ አድርገው ወደ ሰማይ ከፍ አድርገው ያነሳሉ፣ እናም ይበራሉ፡፡ እንደ ዘማሪዎቹ ትንሽየ ወፎች ክንፎቻቸውን በፍጥነት ያርገፈግፋሉ፡፡

ለዚህም ነው በዚህ ዓመት ከኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ትውልድ ጋር ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመቀላቀል እና አብሮ ለመጓዝ ዓላማ አድርጌ የተነሳሁት፡፡

በክንፎቻቸው ወደ ላይ ወደ ሰማይ ከፍ ብለው እንዲበሩ እፈልጋለሁ፡፡ ሁሉንም ትክክለኛ እና ጠንካራ ጥያቄዎችን ኢትዮጵያን ስለገጠሟት ህልቆ መሳፍርት ለሌላቸው ችግሮች ከብዙ አቅጣጫ ጥያቄዎችን እንደጠይቁ እፈልጋለሁ፡፡ በሀሳቦቻቸው በረራ እንዲያደርጉ እፈልጋለሁ፡፡ ከጎሳ ፖለተካ፣ ከኃይማኖት ጽንፈኝነት እና ከጥላቻ ነጻ የሆነች አዲሲቷን የእራሳቸው ፍጡር ኢትዮጵያን እንዲያስቡ ግፊት አደርጋለሁ፡፡ የእራሷ እና የጎረቤቶቿ ሰላም የተጠበቀ ኢትዮጵያን እንዲያስቡ እፈልጋለሁ፡፡ ከጭቆና እና ከወሮበላ ዘራፊነት ነጻ የሆነች ኢትዮጵያን እፈልጋለሁ፡፡ ተምኔታዊት ኢትዮጵያን እንዲያስቡ እፈልጋለሁ፡፡

እያንዳንዱ የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ትውልድ “የኢትዮጵያ ጥልቅ አሳቢ” –መሀንዲስ፣ ዕቅድ ነዳፊ፣ ፈጣሪ፣ ለኪ መሀንዲስ፣ ህንጻ ገንቢ እና ዜጎቿ ስለጎሳ ማንነታቸው ሳይሆን ስለእያንዳንዳቸው ሰው የመሆን እውነታነት፣ ዕኩል ዕድል ስላለባት ኢትዮጵያ፣ ከሙስና፣ ከጭቆና እና ከወሮበላ ዘራፊነት ነጻ ስለሆነች ኢትዮጵያ እንዲሟገቱ ጥረት እንዲያደርጉ እፈልጋለሁ፡፡

“በጠርሙስ ውስጥ ያለ መልዕክት” የሚለውን ተመሳስሎ በመጠቀም የእኔን መልዕክት (ትችቴን) በጠርሙስ ውስጥ ከትቸ ኢንተርኔት እየተባለ በሚጠራው ባህር ውስጥ እንዲለቀቅ በማድረግ ሁሉም የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ በአጋጣሚ እንዲያገኘው እና የጠርሙሱን ክዳን በመክፈት እንዲያነበው አደርጋለሁ፡፡

የእኔን መልዕክት ለማንበብ ስንቶቹ እንደሚያገኙት አላውቅም፡፡ በርካታዎቹ እንደሚያነቡት ግን ተስፋ አለኝ፡፡ እርግጠኛ ነኝ ጥቂቶች ከእኔ ጋር ይስማማሉ፣ ሌሎች ግን አይስማሙም፡፡ ስምምነት ወይም ደግሞ አለመስማማትን አልፈልግም፡፡ የእኔ መልዕክት ዋናው ዓላማው የኢትዮጵያ ወጣቶች ትክክለኛ ጥያቄዎችን እንዲጠይቁ፣ እውነታውን (የእራሳቸውን እውነታ) ለማወቅ እንዲደፍሩ እና አዲስ ሀገር እንዲያስቡ የኢትዮጵያን ወጣቶች ማደፋፈር ነው፡፡

የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔ ወጣት ትውልድ፡ ነጻ ሆናችሁ ተወልዳችኋል፣ ሆኖም ግን ነጻ ሆኖ ለመኖር ከጎሳ ፌዴራሊዝም እግረ ሙቆች አዕምሯችሁን ነጻ ማድረግ አለባችሁ፡፡ 

ጥያቄው፡ የጎሳ ፌዴራሊዝም ምንድን ነው?

የዘ-ህወሀት ህገ መንግስት መግቢያው እንዲህ የሚል ለዚህ የተዘጋጀ መልስ አለው፡ “እኛ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና የኢትዮጵያ ህዝቦች…“ የሚከተሉትን ለመፈጸም ህገመንግስቱን አርቅቀን ጽፈናል፡

1ኛ) ብሄር ብሄረሰቦች የእራሳቸውን መብት መወሰን እስከ መገንጠል ለማስከበር፣

2ኛ) የብሄር ብሄረሰቦችን የግዛት ልዩነት ለማረጋገጥ፣ ስለሆነም ከእራሳችን ከበለጸገ እና የሚያኮራ የባህል ውርስ ጋር አብረው ለመኖር፣

3ኛ) ለዘመናት ፍትሀዊ ያልሆነ ግንኙነቶችን ለማስተካከል፣ እና

4ኛ) እንደ አንደ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለማሳለጥ፡፡ (ከዚህም በተጨማሪ አንቀጽ 39ን ይመልከቱ፡፡)

የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ የዘ-ህወሀትን የጎሳ ፌዴራሊዝም ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ስላለበት ሁኔታ ተጨባጭ መረጃ እና አባባሌን ሊደግፍ የሚችል ማስረጃ በማቅረብ የክርክር ጭብጤን አቀርባለሁ፡፡

የክርክር ጭብጤ ፍሬ ነገር ማጠቃለያ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡ “የጎሳ ፌዴራሊዝም የኋህ እና አስመሳይ የሚመስል ስያሜን በመያዝ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አፍሪካ አዲስ እና የተሻሻለ የጥቂት የነጮች የበላይነት የተንጸበረቀበት የአፓርታይድ ቅጅ ነው፡፡ የዘ-ህወሀት ክልል በዘር ላይ ለተመሰረተው የአፓርታይድ ባንቱስታን ዘመናዊ ትርጉም ነው፡፡ የጥቂት የነጮች የአፓርታይድ መንግስት በደቡብ አፍሪካ ባንቱስታንስን የፈጠረ ሲሆን ዋናው ዓላማቸው በዘር፣ በቋንቋ፣ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ በጎሳ፣ በባህል፣ ወዘተ ላይ መሰረት ባደረገ መልኩ ለደቡብ አፍሪካ ጥቁር ህዝቦች እራሳቸውን በእራሳቸው እንዲያስተዳድሩ በማለት የተዘጋጀ ነበር፡፡ የመጨረሻው ዋናው ዓላማ ባንቱስታንስ አንድ ቀን የእራሳቸው ሀገር እንደሚኖራቸው እና (የእራስን ዕድል በእራስ የመወሰን) ነጮችም እንደዚሁ የእራሳቸው ሀገር እንደሚኖራቸው በሚያስገርም ሁኔታ በሀገሪቱ ውስጥ አሉ የተባሉትን ምርጥ ለም መሬቶች ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረው ነበር፡፡“

ክልል የሚለው የአማርኛው ቃል ከጎሳ ፌዴራሊዝም ትርጉም አንጻር በአንድ አካባቢ ያለን መሬት የሚገልጽ እና ለልዩ ጠቀሜታ እና የቡድን አባላትን አስተዳደር ለማሳለጥ ተመሳሳይ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ባህል፣ወዘተ የሚጋሩ ህዝቦችን የያዘ ነው፡፡ ክልል የታጠረ፣ የተወሰነ ወሰን፣ ግዛት እና የመሬት ስፋት ያለው መሆኑን ይገልጻል፡፡ ዘ-ህወሀት የማያቋርጥ የመልክዓ ምድር ልዩነትን ለመፍጠር እና በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ልዩነትን በመፍጠር ህዝቦችን ብሄሮች እና ብሄረሰቦች በሚል ፈሊጥ እንደ ከብት መንጋ በአንድ በረት ውስጥ ለማጎር ዋና ዓላማው አድርጎ በመነሳት የጎሳ ፌዴራሊዝሙን ቀየሰ፣ ነደፈ፣ ፈጠረ፣ አዋቀረ እናም ረቂቅ ካርታውን ሰርቶ አወጣ፡፡

የኢትዮጵያን ህዝቦች በቡድን፣ በቋንቋ፣ በባህል እና በክልላዊ ቡድኖች በህገ መንግስታዊ ማዕቀፍ በመከፋፈል ዘ-ህወሀት ለዘላለም እና ሊመለስ በማይችል መልኩ የማህበራዊ ትስስሮችን ለማጥፋት እና የመቻቻልን፣ የፍቅርን እና የመግባባትን ክሮች ለመበጣጠስ እና ለዘመናት አንድ ሆኖ የኖረውን የኢትዮጵያን ህዝብ ለመከፋፈል የተሰራ የሸፍጠኞች ዕኩይ ምግባር ነው፡፡

አንቀጽ 39 እየተባለ በሚጠራው ስር የዘ-ህወሀት የጎሳ ፌዴራሊዝም የመጨረሻ ዓላማው ኢትዮጵያን በጎሳ ለመከፋፈል እና በግንብ ላይ በቋፍ ላይ የተቀመጠች እና በቀላሉ የምትወድቅ የሚለውን ተረት ሆኖ ይታያል፡፡ ሁሉም የንጉሱ ፈረሶች እና የንጉሱ ሰዎች አጭሩን ፍጡር እንደገና አንድ ሊያደርጉት አይችሉም፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮጵያ ከክልል ህንጸ ላይ በምትወድቅበት ጊዜ ዘ-ህወሀት ይፈጠራል፣ የንጉሱ ፈረሶች እና ሰዎች ጀርባዋን አንድ ለማድረግ የሚጥሩት አይደሉም፡፡ ይህንን የሚያደርጉት በአምላክ ፈቃድ የተነሳሱት የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ አባላት ናቸው!

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በጣም ከባድ የሆነው የህልውና ጥያቄ ችግር (በኢትዮጵያ ውስጥ የሁሉም ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እናት የሆነው) ያለምንም ጥያቄ የጎሳ ፌዴራሊዝም እንደሆነ አምናለሁ፡፡

በእጅ ላይ ያሉት አምስት የተለያዩ ጣቶች በአንድ ላይ ተሰባስበው ወደ መዳፋችን መሀል በመምጣት ጭብጥ ሲሰሩ እና ቡጢን ሲመሰርቱ ጣቶቹ ብቻ ተነጣጥለው ለየብቻ ሲሆኑ የነበረበት ሁኔታ ከቡጢው በጣም ያነሰ ኃይል ብቻ እንደሚኖራቸው ዘ-ህወሀት ተገንዝቦታል፡፡ ዘ-ህወሀት የኢትዮጵያ አምስት ጣቶች በአንድነት እንዳይሰለፉ እና በዘ-ህወሀት ፊት ጠንካራውን ቡጢን እንዳይመሰርቱ እና ጣቶችን ለየብቻ በታትኖ ለብቻው ሀገሪቱን እንደብረት ቀጥቅጦ እንደ ሰም አቅልጦ ሲገዛ ለመኖር እንዲመቸው የጎሳ ፌዴራሊዝምን ህገመንግስታዊ አድርጎታል፡፡

የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ የዘ-ህወሀትን የጎሳ ፌዴራሊዝምን ለመቀበል ከመፈለጋቸው በፊት ስለስርዓቱ ምንነት በጥሞና መገንዘብ፣ መገምገም እና መወሰን አለባቸው፡፡

ከምንም በላይ በመጀመሪያ ደረጃ የአቦ ሸማኔው ትውልድ ዘ-ህወሀት በኢትዮጵያ ላይ ስላለው የመሰረት ድንጋይ ታሳቢዎች ላይ መስማማት አለመስማማታቸውን ማወጅ እንዳለባቸው ለመጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡

ታሳቢ ቁጥር 1 የኢትዮጵያውያን ብሄራዊ የሚባል ነገር የለም ምክንያቱም ኢትዮጵያ የብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ስብስብ ናት፡፡ ዘ-ህወሀት ኢትዮጵያ እየተባለች በምትጠራ ምትሀታዊ መሬት ላይ በመቆየት ወቅቱን ጠብቆ ወደ ጎሳ መበታተን ላይ የሚወስድ አደገኛ የጥፋት ስርዓት በመዘርጋት በወጥመድ ውስጥ አስሮ በመያዝ የውሸት የእዩልኝ እመኑልኝ የብሄሮች እና የብሄረሰቦች ኮንፌዴሬሽን መስርቶ በማጭበርበር ላይ ይገኛል፡፡ ሁሉም በአጠቃላይ ሲታይ ከእያንዳንዱ ድምር ውጤት አይበልጥም፣ ምክንያቱም ክፍልፋዮቹ ዋናውን ትልቁን በፍጹም አይሆኑምና፡፡

የዘ-ህወሀት ህገመንግስት ታሪካዊ ኢፍትሀዊነቶችን ትክክለኛ አድርጎ በማቅረብ እራሱን መሳሪያ አድርጎ አቅርቧል፡፡ ብሄሮችን እና ብረሰቦችን የእራስን እድል በእራስ መወሰን በሚል ታሪካዊ ኢፍትሀዊነትን በማካተት መሳሪያ አድርጎ አቅርቧል፡፡ ብሀሮች እና ብሄረሰቦች ለእያንዳንዳቸው የፈንጅ ሳጥን በመስጠት ለብዙሀን እልቂት እራሳቸውን የኒኩሊየር መሳሪያ አስታጥቋል፡፡ እናም መላዋን ሀገሪቱን ወደ ትናንሽ ቁርጥራጭ አገዛዞች በመከፋፈል በተግባር እያበጡ ይገኛሉ፡፡

ታሳቢ ቁጥር 2 የኢትዮጵያ ባህል ፍጹም የለም፡፡ በእራሱ የቆመ እና ምንም ዓይነት የጋራነት በሌለው መልኩ የብዙህን ባህሎች አሉ፡፡ በዘ-ህወሀት የጎሳ ፌዴራሊዝም ፍልስፍና መሰረት የአንድነት በልዩነት አጠቃላይ መሰረተ ሀሳብ ብዝሀነትን በልዩነት፣ በጥላቻ እና ዘገምተኛ ምላሽን በመስጠት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

ታሳቢ ቁጥር 3 የኢትዮጵያ ታሪክ የሚባል ነገር የለም፡፡ ታሪክ የሌለው ህዝብ ያለፈ ህዝብ እና ወደፊትም የሚኖር ህዝብ እንደሌለ ዓይነት ነው፡፡ የዘ-ህወሀት ጭንቅላት የነበረው እና አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ በ1993 በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፡ “ኢትዮጵያ የ100 ዓመት እድሜ ብቻ ነው ያላት፡፡ ከዚህ በተለየ መልክ የሚያቀርቡ ሰዎች ካሉ እራሳቸውን በትረካ ውስጥ የዶሉ ናቸው፡፡“ እንደ ዘ-ህወሀት የጎሳ ፌዴራሊዝም የብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ታሪክ ብቻ ነው ያለው፡፡

ታሳቢ ቁጥር 4 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ማንነት የለም፡፡ ብሄራዊ ማንነት አንድ ሰው ለአንድ መንግስት ወይም ደግሞ ለአንድ ብሄር የእኔነት ስሜት የሚንጸባረቅበት ሁኔታ ነው፡፡ ብሄራዊነት እንደ አያያዥ ጠቅላይ ሆኖ፣ ይህም መገለጫው ልዩ በሆኑ ልማዶች፣ ባህል፣ ቋንቋ እና ፖለቲካ የሚገለጽ ነው፡፡

እኔ እስከማውቀው ድረስ ኢትዮጵያውያን ጎሳቸውን ለአገዛዙ ባለስልጣኖች እንዲያሳውቁ በህግ የተገደበባቸው ህዝቦች ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው፡፡ የህዝብ አገልግሎትን ለማግኘት ሲባል አንድ ሰው ጎሳውን እንዲናገር የሚገደድበት ሁኔታ ታላቅ ስድብ፣ ታላቅ ውርደት ሊሆን አይችልምን?

የእንግሊዝ ዜጎች የእንግሊዞችን ስሜት እንደሚያንጸባርቁ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ የፈረንሳይ ህዝቦች የፈረንሳዮች ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ለብራዚላውያን፣ ለህንዳውያን፣ ለግብጻውያን እና ወዘተ አንድ አይነት ነው፡

የአሜሪካ ህዝቦች የአፍሪካ እና የአሜሪካ፣ የፖላንድ፣ የአሜሪካን፣ የጃፓን አሜሪካን እና የመሳሰሉትን ስሜት ከመያዛቸው በፊት አሜሪካውያንነት ስሜት ይሰማቸዋል፡፡

በደፍጣጮቹ የዘ-ህወሀት ጫማ ስር ሆኖ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የኢትዮጵያዊነት ስሜት ሊሰማቸው ይችላልን?

እንዲያው ሌላው ቢቀር ኦሮሞ ኢትዮጵያውያን፣ አማራ ኢትዮጵያውያን፣ ትግራይ ኢትዮጵያውያን፣ ወዘተ የሚል ስሜት ሊሰማቸው ይችላልን?

ወይም ደግሞ ከብሄራዊነታቸው ውጭ፣ ሰው ከመሆናቸው ውጭ ስለ ጎሳቸው ሊያስቡ ይችላሉን?

ታሳቢ ቁጥር 5 ለብሄራዊ ማንነት ምልክትነት፣ ለክብር እና ለአርብኝነት ሊውል የሚችል የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የለም፡፡ ከባንዲራ ጋር በተያያዘ መልኩ አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ በአንድ ወቅት ዘ-ህወሀት በባንዲራ ላይ ስላለው አቋም ተጠይቆ እንዲህ የሚል ተደጋጋሚ ምላሽ ሰጥቶ ነበር፣ “የኢትዮጵያ ባንዲራ ጨርቅ ነው፡፡“

አብዛኞቹ አሜሪካውያን ለባንዲራቸው ክብር እና ኩራት ይሰጣሉ፡፡ ባንዲራቸውን የጥንት ዝና የሚል ቅጽል ስም ሰጥተዋል፡፡ በአብዛኛው በህዝብ፣ በስፖርት እና በአርበኝነት አጋጣሚዎች የጥንት ዝናቸውን ለማሳየት “በጠቃጠቆ ኳክብት ውበት ያማርሽው“ እያሉ ይዘምራሉ፡፡ በመጨረሻዎቹ ሶስት የግጥም ስንኞች ላይ እንዲህ እያሉ ይዘምራሉ፡ “ የእኛ ዓላማ ይህ መሆን አለበት-እግዚአብሄር የእኛ ታማኝ አምላክ ነው፡፡ ባንዲራዋ በነጻው መሬት እና በጀግኖቹ ቤት በኳክብት ጠቃጠቆ በመዋብ በድል አድራጊነት ትውለበለባለች፡፡“ ይኸ ነው እንግዲህ በዋናነት ለአብዛኞቹ አሜሪካውያን ከየትኛው የዓለም ማዕዘን ቢመጣም ወይም ደግሞ ጥንታውያን ቀደምቶቻቸው ከየትም ይምጡ አሜሪካውያን ቁብ አይሰጡትም፡፡

በተመሳሳይ መልኩ አረንጓዴ፣ ብጫ እና ቀይ እንዲሁም በመካከሏ ላይ ሰማያዊ መደብ ባላት ሀገር ውስጥ ኢትዮጵያውያን አንድ ዓይነት ስሜት ሊኖራቸወ ይችላልን? ኢትዮጵያ ለምንድን ነው የነጻነት መሬት እና የጀግኖች መጠለያ የማትሆነው? በዚህ ጉዳይ ላይ አሜሪካኖች ብቻ ነው የጠቅላይነት መብት ያላቸው? ኢትዮጵያ እኮ የጀግና አገር ነበረች!

ዘ-ህወሀት በባንዲራቸው መካከል ላይ ኮከብ ያስቀምጣሉ፡፡ የኮከብ ምልክትነት አስፈላጊ የሆነ የዓለም መልክት ነው፡፡ የኮከብ ምልክቱ በውስጡ ያለበት ባንዲራ በየትኛውም ሀገር አይገኝም፡፡ ለነገሩ የነሱ የባንዲራ ኮከብ በዓለም የሚታወቀው የጭለማው ንጉስ (ዳቢሎስ) ተከታዮች ብቻ ነው:: ወይ ጉድ!

ታሳቢ ቁጥር 6 የኢትዮጵያ ህልም የሚባል ነገር የለም፡፡ ያለው የዘ-ህወሀት የሌሊት ቅዠት ብቻ ነው፡፡ ዘ-ህወሀት ኢኮኖሚውን፣ ፖለቲካውን እና ማህበረሰቡን ተቆጣጥሮታል፡፡ ማንም ቢሆን አየር መተንፈስ አንክዋን ያለ ዘ-ህወሀት ፈቃድ አይችልም፡፡ ማንም በቅዠት ህልም ሊያልም አይችልም!

የዘ-ህወሀትን የጎሳ ፌዴራሊዝም በአሁኑ ጊዜ እንደ ዘመናዊ አፓርታይድ ለመገንዘብ የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ትውልድ የአፓርታይድን ህጎች ማጥናት እና ባንቱስታንስ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ እንዴት እንደመጡ መገንዘብ አለበት፡፡ ዘ-ህወሀት የጎሳ ፌዴራሊዝምን ከአፓርታይድ የጨዋታ መጽሀፍ የተኮረጀ ነው፡፡ በእርግጥ የጎሳ ፌዴራሊዝም የደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ መንግስት መገለጫ ነው፡፡

በዚህ ጽሁፍ ላይ የእኔ ዓላማ በአፓርታይድ ህጎች ላይ እና በዘ-ህወሀት አዋጆች መካከል ያሉትን ተመሳሳይነቶች እና ልዩነቶችን ነቅሶ በማውጣት ለማሳየት አይደለም፡፡ አስፈላጊ ሆኖ የሚገኝ ከሆነ በቀላሉ እና በደስታ ማድረግ እችላለሁ፡፡ ሆኖም ግን ልክ አሁን ዘ-ህወሀት በአትዮጵያ ውስጥ ፍጹም በሆነ መልኩ የሀገሪቱን መሬቱ ተቆጣጥሮት እንደሚገኘው ሁሉ በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የጥቂት ነጮች መንግስት የደቡብ አፍሪካን ብዙሀን ጥቁር ህዝብ በቁጥጥሩ ስር በማድረግ እና ፍጹም በሆነ መልኩ አኮኖሚውን በቁጥጥሩ ስር በማድረግ የተጠኑ እርምጃዎችን ይወስድ እንደነበር ቀላል የሆነውን ነጥብ ለማሳየት ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ1995 የጸደቀው የዘ-ህወሀት ህገ መንግስት እንዲህ በማለት ያውጃል፣ “የገጠር እና የከተማን መሬት እንዲሁም ሁሉንም የተፈጥሮ ሀብቶች የመያዝ መብት ብቸኛ ለኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝቦች የተተወነ ነው፡፡ መሬት የብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች የጋራ ሀብት ነው፡፡ ስለሆነም አይሸጥም፣ አይለወጥም፡፡ (አንቀጽ 40 (3)፡፡)“

መንግስት የገጠር እና የከተማን መሬት በብቸኝነት የመያዝ መብት ካለው ግልጽ የሆነው ጥያቄ እንዲህ የሚል ነው፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛ የመንግስትነቱን ስልጣን ተቆጣጥሮት የሚገኘው ማን ነው?

ላለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግስትነቱን ስልጣን በብቸኝነት በመያዝ እየዘወረው ያለው ማን ነው?

እ.ኤ.አ በባንቱ የ1993 ድንጋጌ (የመጀመሪያው የኗሪዎች የመሬት ድንጋጌ [የ1913 ድንጋጌ ቁጥር 27] የነጭ ሰፋሪዎች ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ እንደምታ የሚያስከትለውን የደቡብ አፍሪካን ብዙሀን ጥቁር ህዝቦች የመሬት ባለቤትነት መብትን በመንፈግ የገባርነት የመሬት ስርዓትን ፈጥሮ ነበር፡፡ የባንቱ የመሬት አዋጅ በአፓርታይድ ስር የአካባቢ መንግስት እና አስተዳደር በመፍጠር የተለየ ልማትን በመዘርጋት የደቡብ አፍረካን መንግስት ለተለያዩ ኗሪዎች በመከፋፈል የጭቆና አገዛዙን ቀጠለ…አዋጁ ብዙሀኑን የደቡብ አፍሪካን ጥቁር ህዝብ መሬት የመያዝ መብት ሙሉ በሙሉ ነጠቀ፡፡

የባንቱ ባለስልጣኖች የ1951 ድንጋጌ (የጥቁሮች ባለስልጣኖች የ1951 ድንጋጌ) ጥቁር ህዝቦችን ወደተከለሉላቸው አካባቢዎች እንዲጣሉ በማድረግ የጎሳ፣ የክልል እና የግዛት ባለስልጣኖችን ፈጠረ፡፡ ይህ ድንጋጌ በተከታይነት የባንቱ ዜጎች የመኖሪያ ቦታን ድንጋጌ እ.ኤ.አ በ1970 በማዘጋጀት (የጥቁር መንግስታት ዜጎች ድንጋጌ እና የብሄራዊ መንግስታት ድንጋጌ 1970) የባንቱ ኗሪዎችን የህግ ደረጃ የሚለውጠውን እና የባንቱስታንቶችን የዜግነት ተጠቃሚነት እንደ ደቡብ አፍሪካዊነት ፍጹም በሆነ መልኩ በመከልከል የተዘጋጀ ነበር፡፡ እነዚህ ህጎች በጥቁር የደቡብ አፍሪካ ህዝቦች ንቅናቄ ላይ አሳሪ የሆኑ የክልከላ ህጎችን ጣሉ፡፡ እነዚህ ህጎች ከዚህም በተጨማሪ ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን የአፍሪካን ብዙሀን ህዝብ በመወከል ድምጽ የመስጠት መበት እና የመንግስትን እንቅስቃሴ በአጠቃላይ በብቸኝነት በመያዝ ማረጋገጥ ፈለጉ፡፡

እ.ኤ.አ የ1950 የቡድን የአካባቢ ድንጋጌዎች (እ.ኤ.አ በ1966 እንደገና የጸደቁት ድንጋጌዎች) ደቡብ አፍሪካን ለነጮች እና ለጥቁሮች በማለት ወደተለያዩ አካባቢዎች በመከፋፈል መንግስት ለጎሳ እና ለዘር ቡድኖች ሲባል ካልተመደቡባቸው አካባቢዎች በኃይል ማበረር ጀመረ፡፡ በዚህ ድንጋጌ ስር ማንም በተሳሳተ ቦታ ሲኖር የተገኘ ሰው ወደ ቡድናዊ መኖሪያ ቦታው/ቦታዋ ይወሰዳል/ትወሰዳለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ህጉ በደቡብ አፍሪካ በማንኛውም ቦታ አፍሪካውያንን ከመሬት ባለቤትነት እና የፖለቲካ መብቶች ሁሉ ይከለክላል፡፡ በዚህ ህግ አማካይነት ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ህዝቦች ለጉዳት ተዳርገዋል፣ እንደዚሁም ደግሞ በኃይል እዲጋዙ እና በባንቱስታንስ ቡድኖች እንደ ከብት መንጋ በአንድ በረት እንዲታጎሩ ተደርገዋል፡፡

የክልላዊነት ፍልስፍና የአፓርታይድን ባንቱስታኒዝም በርካታ መገለጫዎች ይጋራል፡፡

በአንቀጽ 39 እና በአምባገነኑ የመለስ ዜናዊ የይስሙላ ፓርላማ በጸደቁት ሌሎች ህጎች መለስ ልክ አፓርታይድ በደቡብ አፍሪካ የባንቱ (ጥቁሮች) ባለስልጣኖች ድንጋጌን እ.ኤ.አ በ1951 እንደመሰረተ ሁሉ እንደዚሁ በተመሳሳይ መልኩ የጎሳ መንደሮችን መሰረተ፡፡ አንቀጽ 39 እንዲህ ይላል፣ “ብሄሮች ብሄረሰቦች ወይም ህዝቦች በዚህ ህገ መንግስት የጋራ ባህል ወይም ደግሞ ተመሳሳይ ልማዶች፣ የጋራ ቋንቋዎች የጋራ እምነቶች ወይም ተመሳሳይ ማንነቶች እና ማን በከፍተኛ ሁኔታ በግዛቱ ላይ የመቆጣጠር ኃይል እንደሚኖረው በግልጽ ያስቀምጣል፡፡“ ሁሉቱም ፍልስፍናዎች በተከለሉት የጎሳ ቡድኖች ላይ ትኩረት በማድረግ አንድ ዓይነት ቋንቋ ያላቸው ህዝቦች የራስ ገዝ አስተዳደሮች በሚል ፈሊጥ በአንድ አካባቢ እንዲሰፍሩ አደረጉ፡፡

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2012 “አረንጓዴ ፍትህ ወይም የጎሳ ኢፍትሀዊነት“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት የጎሳ ፌዴራሊዝም ዋና ቀማሪ እና አድራጊ ፈጣሪ መሀንዲስ የነበረው እና አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ በእራሱ ቃላት ዘመናዊ የአፓርታይድ ስርዓትን እያራመደ መሆኑን ግልጽ አድርጓል በማለት በማስረገጥ ተናግሬ  ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2012 አምባገነኑ መለስ እራሱ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ አማራዎችን ከደቡብ ኢትዮጵያ እንደባረሩ እና እንዲጋዙ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ የእራሱን ዕኩይ ድርጊቶች ምክንያታዊ ለማድረግ “ከአማራ ከምስራቅ ጎጃም የመጡ አማራ ሰፋሪዎች“ እና በወንጀለኝነት ደን እየመነጠሩ የሚኖሩ መሬት ተቀራማቾች ናቸው ነበር ያለው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖርን ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ በህገወጥ መልክ መሬትን የያዘ ብሎ በመፈረጅ በዘረኝነት ለማጥቃት ሲሞከር ያቅለሸልሸኛል፡፡ (የመለስ ዜናዊን ቨዲዮ ለመመልከት እዚህ ጋ ይጫኑ)፡፡

…በታሪክ አጋጣሚ ባለፉት አስር ዓመታት ከምስራቅ ጎጃም የመጡ በርካታ ህዝቦች-ወደ 30,000 የሚሆኑ ሰፋሪዎች (ህገወጥ) በደቡብ ኢትዮጵያ በቤንች ማጂ ዞን ሰፍረው ነበር፡፡ በጉራ ፈርዳ ውስጥ 24,000 ሰፋሪዎች ነበሩ፡፡ አካባቢው በደን የተሸፈነ በመሆኑ ምክንያት በርካታ ህዝብ በዚያ አካባቢ አይኖርም፡፡ ሆን ተብሎ ለዓላማቸው ማስፈጸሚያ በሚመች መልኩ የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ጉራ ፈርዳን ትንሿ ምሽራቅ ጎጃም እያሉ ይጠሯት ነበር፡፡ ያ ምንም ዓይነት ችግር የለውም፡፡ በቤንች ማጂ ዞን ሊታረስ የሚችል መሬት አለ፣ እናም ይህንን ስራ ሊሰሩ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ፡፡ እያንዳንዱ አሸናፊ ነው፣ ማንም ተሸናፊ አይሆንም፡፡ አንድ ችግር ብቻ አለ፡፡ ህገወጥ ሰፋሪዎች ስራውን እየሰሩ ያሉት በተበታተነ መልኩ ነው፡፡ ህገወጥ ሰፋሪዎች በግል እና በዘፈቀደ እንዲሁም አካባቢውን ሊያወድም በሚችል መልኩ ነው የሰፈሩት፡፡ የሰፈሩበት ቦታ የደን ውድመትን ሊያስከትል እንደሚችል የአካባቢ የስነ ምህዳር ጥናት አልተደረገበትም፡፡ በአካባቢው ያለው ብርቅዬ ደን መጠበቅ አለበት፡፡ ህገወጥ ሰፋሪዎች በቀላሉ ሊለማ የሚችል የሚታረስ መሬት ይፈልጋሉ፡፡ ደን ሆነ አልሆነ ደንታቸው አይደለም፡፡

ደኑን ይቸፈጭፋሉ እናም ከሰል ያከስላሉ፡፡ ይህም በመሆኑ መጠነ ሰፊ የሆነ የአካባቢ ውድመት ተፈጥሯል…ሰፋሪዎች ወደ አካባቢው በመሄድ ደኑን ለመኖሪያነት ሊያወድሙ አይችሉም፡፡ ይህ ህገወጥ ነገር ነው፣ እናም መቆም አለበት፡፡ ይህንን ነገር አዛብተው የሚያቀርቡ ኃላፊነት የጎደላቸው ናቸው፡፡ እውነታውን ማጣራት ተገቢ ነገር ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን መብቶች ሁሉ በእኩልነት መጠበቅ አለባቸው፡፡ አማራዎች እየተሰቃዩ እና ከቦታቸው እየተፈናቀሉ ነው እያሉ የሚያራግቡ ኃይሎች ኃላፊነት የጎደላቸው እና ለምንም የማይጠቅም ነገር ነው…

ይኸ ዓይነት ነገር ነው እንግዲህ በአፓርታይ ዘረኛ የጥቂት ነጮች የበላይነት አገዛዝ በደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች ላይ የተፈጸመው፡፡ ህገወጥ ሰፋሪዎች ተብለው ይፈረጁ ነበር እናም ከሚኖሩበት አካባቢ በኃይል ይባረሩ ነበር…

የኢትዮጵያን የአቦ ሸማኔ ወጣት ትውልድ ከነጻነት ብልጭታ ጋር ከእኔ ጋር እንዲበሩ እጠይቃለሁ፡፡ ነጻ ሆናችሁ ተወልዳችኋል፡፡ አሁን በነጻነት መኖር አለባችሁ ምክንያቱም ያ አምላካዊ ዕጣ ፈንታችሁ ነውና፡፡

አክባሪያችሁ፣

የእናንተው “የአቦ ሸማኔጉማሬ” ጓደኛችሁ!

መልዕክቱ ይቀጥላል

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!            

የካቲት 15 ቀን 2008 .

 

Similar Posts