ኢትዮጵያ በዘ-ህወሀት አውሬ የሸክላ እግር ስር፣
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
የጸሐፊው ማስታወሻ፡ ይህ ጽሑፍ ከመሬት ጋር በተያያዘ መልኩ፣ ስለመሬት አጠቃቀም፣ መሬትን ከህግ አግባብ ውጭ ስለመጠቀም፣ ስለመሬት ከበርቴነት እና በኢትዮጵያ ስለመሬት ባለቤትነት በተከታታይነት ካቀረብኳቸው ጽሁፎች መካከል 4ኛ ትችቴ ነው፡፡ በመጀመሪያው ትችቴ በመቶዎች እና በሺዎች ሄክታር የሚቆጠር መሬት በምዕራብ ኢትዮጵያ ካራቱሪ ግሎባል በሚባል ድርጅት ተይዞ የነበረ ቢሆንም ካራቱሪ እየተዳከመ እና እየወደቀ መምጣቱን መርምሪያለሁ፡፡ በሁለተኛው ትችቴ የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) በሚሊዮኖች ሄክታሮች የሚቆጠር መሬት ለጎረቤት ሀገሮች ወይም ደግሞ ለዓለም አቀፍ የመሬት ተቀራማች ሸፍጠኞች በመሸጥ እና በመስጠት ተግባር ባተሌ ሆኖ በመገኘቱ ለኢትዮጵያውያን የሚተርፍ መሬት አለ ወይ በማለት ጥያቄ አቅርቤ ነበር፡፡ በሶስተኛው ትችቴ ደግሞ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን እየተባለ የሚጠራው በእርግጥ ብልጦቹ የዘ-ህወሀት ጌቶች የከተማውን ህዝብ ወደ አካባቢው ያባርራሉ፣ እናም የዘ-ህወሀት ወንጀለኛ ቤተሰቦች እና የእነርሱ ግብር አበሮች ዋናውን የከተማውን እና ጥቂት ገጠርነት ያላቸውን መሬቶች በመያዝ ሰበዘብዙ ይታያሉ የሚለውን የሚገልጽ ነበር፡፡
መቸም ጉዱና ሃፍረቱ የማያልቅ!
ባለፈው ሳምንት እንዲህ የሚል ዘገባ ቀርቦ ነበር፡
“በካታር ንጉስ በዶ/ር ክሀሊድ ቢን ታኒ ቢን አብዱላህ አል ታኒ የሚመራው የዝዳን ሆልዲንግ ቡድን የኢትዮጵያን የወደፊት ጠንካራ የኢኮኖሚ ሁኔታ በመመልከት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 150 ካሬ ኪ/ሜ ማለትም በአሁኑ ጊዜ ካለው ከከተማዋ ስፋት በሩብ መጠን ብልጫ ያለው ሪሶርት (መዝናኛ) በመገንባት እድገቱን ለመደገፍ ይፈልጋል…ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በኢትዮጵያ ውስጥ ከቡድኑ ጋር በግንባር ፊት ለፊት በመገናኘት ለዕቅዱ ጠንካራ ድጋፍ እንደሚሰጡ ያላቸውን ሀሳብ ገልጸዋል፡፡ እናም ለዝዳን እ.ኤ.አ ጥር 31/2016 በዚህ ዕቅድ ላይ የሚጋረጡትን ማናቸውም ዓይነት መሰናክሎች ወይም ተግዳሮቶች መፍትሄ ለመስጠት ቃል ገብተዋል፡፡“
መራራዎቹን እውነታዎች እንጋፈጥ፡ አዲስ አበባን የመካከለኛው ምስራቅ ወይም የአፍሪካ የሽርሙጥና ቱሪዝም ከተማ ለማድረግ ነው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሪሶርት የሚገነቡት?
የሽርሙጥና ቱሪዝም ለዘ-ህወሀት አዲስ የውጭ ምንዛሬ ማስገኛ ዘዴ መሆኑ ነውን? እንደ እነርሱ አካሄድ መሬቱን መሸጥ ብቻ በቂ አይደለም፣ በድጋሜም የኢትዮጵያን ሴቶች ሰውነትም ለመሸጥ ይፈልጋሉ!
“አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በዕቅዱ ትግበራ ወቅት የሚከሰቱትን ማናቸውም ዓይነት መሰናክሎች ወይም ተግዳሮቶች መፍትሄ ለመስጠት ጠንካራ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ያለዉን እምነት ገለፀ” ሲባል ምን ዓይነት ሰይጣናዊ አነጋገር እኮ ነው?
የልማት ዕቀድ ነው ወይስ የማጭበርበር ዕቅድ? ማጭበርበርን ማቃጠር?
ከ9 ሺ ኪሎሜትር ርቀት በላይ አንድ ጠረን ይሸተኛል፡፡ ወገኖቼ እውነታውን ፍርጥ አድርጌ ልንገራችሁ፣ በኳታር ሪሶርት ስምምነት ውስጥ እጅግ በጣም ግዙፍ የሆነ የዓይጥ ጥንብ ይሸተኛል፡፡
እረ እሪ በሉ ጎበዝ! የኢትዮጵያ መደፈር መቼ ነው የሚቆመው?!!!
እጅግ በጣም የሚያበሳጭ ነገር ነው! ምን አይነት የሆድ ቁርጠት ነው!
ከአውሬዎች የእግር መዳፍ ስር ፈንቅሎ በመነሳት ማመጽ፣
በዚህ ትችት በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ወይም ደግሞ በዘ-ህወሀት ማስተር የመሬት ዘረፋ ፕላን (ዘ-ፕላን) ላይ ከደረሰው አሳፋሪ ሽንፈት ትምህርት በመውሰድ ዓላማ ላይ ትኩረት አደርጋለሁ፡፡
በነገራችን ላይ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጉዳይ ገና አልሞተም፡፡ በዘ-ህወሀት ፕሮፓጋንዳ መሰረት ፕላኑ ተጥሏል እናም ተትቷል፣ እንደዚሁም የፕላን ጽ/ቤቶቹም ተዘግተዋል፣ እናም ሁሉም ነገር የሀሳብ ፈጠራ ብቻ ነው ብሎ የሚያምን ካለ ሞኝ የሆነ እና የሚያናድድ ነገር ነው፡፡ ለዚህ ነገር ምንም ዓይነት ይቅርታ የለውም!
ሆኖም ግን ታዋቂ ከነበሩት ህዝባዊ ተቃውሞዎች እና ለዘ-ህወሀት ታማኝነትን በመተው የእምቢተኝነት ድርጊቶችን በመተግበር ከአዲስ አበባ ዳርቻዎች አካባቢ በዘ-ህወሀት የመሬት ዘረፋ ላይ ከተደረገው ተቃውሞ ምን ዓይነት ጠቃሚ ትምህርቶችን ልንወስድ እንችላለን?
የዘ-ህወሀትን የጭቆና አገዛዝ እና በይበልጥም ደግሞ በድህረ ዘ-ህወሀት ኢትዮጵያ በዘ-ህወሀት የመሬት ዘራፊዎች ላይ እየተካሄደ ያለው የተሳካ ተቃውሞ ምን እንደምታዎች ሊኖሩት ይችላል?
የዘ-ህወሀት የመሬት ዘረፋ የማስተር ፕላን ህዝባዊ እና የተቀናጀ ብሄራዊ የህዝብ አልታዘዝም ባይነት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩን ሊያሸጋግረው እንደሚችል ሊያረጋግጥ ይችላልን?
እ.ኤ.አ መጋቢት 2007 “የምትዘምርዋ ትንሿ ወፍ እና የጫካው እሳት“ በሚል ርዕስ አንድ የተመሳስሎ ትችት ጽፌ ነበር፡፡ በዚያች ዘማሪዋ ትንሽዬ ወፍ ባህሪ ሁኔታ ላለፉት አስር ዓመታት በየሳምንቱ በማወጣቸው የሰኞ ትችቶቼ ዘ-ህወሀት እያከማቻቸው ባሉት በጎሳ ጥላቻ፣ በመከፋፈል እና በኃይማኖት የጽንፈኝነት ግጭት ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ውድቀት እንዳይከተል በማሰብ የጫካውን እሳት ሳጠፋ ቆይቻለሁ፡፡ በዚህ ረገድ በትንሹ ኩንቢዋ ከወንዝ ውኃ በመያዝ ወደ ጫካው እሳት እያመላለሰች በመድፋት እሳቱን እንደተቆጣጠረችው ሁሉ እኔም እንደ ጫካዋ ወፍ ስኬታማ ሆኛለሁ ብዬ አስባሁ፡፡
ሆኖም ግን እሳት የማጥፋት ስራውን ለኢትዮጵያ ወጣቶች መተው ተመራጭ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ እ.ኤ.አ በ2007 እንዲህ በማለት ያመለከትኩት ይህንኑ ጉዳይ ነበር፡
“የእኛ እሳት አጥፊ ወጣቶቻችን ለበርካታ አስርት ዓመታት በፖለቲካ ጭቆና እና በሰብአዊ መብት ረገጣ የተጎሳቆለ ህብረተሰብ የወረሱ ቢሆንም ቅሉ ከዕለታት በአንዱ ቀን ማንም ወንድ ወይም ሴት የእርሱን ወይም የእርሷን መንግስት የማይፈራበት ወይም የማትፈራበት፣ መንግስት የዜጎችን መብት እና ነጻነት በተግባር የሚያከብርበት፣ ማንም ሰው ቢሆን አንገቱን ቀጥ አድርጎ አእምሮው የፈቀደለትን ያለምንም ፍርሀት እና መሸማቀቅ መናገር የሚችልበት፣ እንዲሁም ማንም ወንድ ወይም ሴት ወይም ህጻን ህይወቱን፣ የንብረት ባለቤትነት ነጻነቱን ከሕግ አግባብ ውጭ የማያጣበትን ከተማ በተራራ ጫፍ ላይ በመገንባት ትክክለኛ የሆነ ፍትህ፣ ሰብአዊነት እና የሞራል ስብዕናው የተጠበቀ ህብረተሰብ እንደምንገነባ ለአፍታም ያህል ቢሆን አንጠራጠር፡፡“
እ.ኤ.አ በ2007 የተናገርኩለት የጫካው እሳት በአሁኑ ጊዜ የተንቦለበለ የእሳት አደጋ እየፈጠረ የኢትዮጵያን ቤት በማቀጣጠል ላይ ይገኛል፡፡
ስነምግባር እና የአርበኝነት ስሜት ያላቸው ኢትዮጵያውን ወንዶች እና ሴቶች ሀገራቸውን ከጥፋት ለማዳን ወደ አንድነት ካልመጡ አመድ ብቻ ተቆልሎ ይቀራል፡፡ ያ ለዘ-ህወሀት የሚመኙት ህልም ዉን ይሆናል፣ ሆኖም ግን ለሌላው ኢትዮጵያውያን ግን አሰቃቂ መርዶ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ወጣት እሳት አጥፊዎች በጅምላ ታስረዋል፡፡ የሚናገሩ እና የሚጽፉ ከሆነ ይሰቃያሉ እናም በይስሙላው የዝንጀሮ ፍርድ ቤት ማለቂያ በሌለው የተንዛዛ ቀጠሮ እየተመላለሱ ያለምንም እልባት አሳር ፍዳቸውን እንዲያዩ ይደረጋሉ፡፡ ሰላማዊ አመጽ የሚያደርጉ ከሆነ ደግሞ በጠራራ ጸሐይ በአደባባይ በመንገዶች ላይ እንደ አውሬ በጥይት ይደበደባሉ፡፡ የፖለቲካ ገለልተኝነት ወይም ደግሞ ነጻነት የሚጠይቁ ከሆነ ከስራቸው ይባረራሉ፣ የትምህርት ዕድልም እንዲያጡ ይደረጋሉ፡፡ የንግድ ስራ ለመስራት የሚፈልጉ ከሆነም የንግድ ድርጅቱን መልሰው እንዲሸጡት ወይም ደግሞ ጉቦ እንዲከፍሉ በማድረግ ነብሳቸውን ሁሉ ለዘ-ህወሀት እንዲሸጡ ይገደዳሉ፡፡ ለመብታቸው ቀጥ ብለው የሚቆሙ ከሆነ ከዘ-ህወሀት ጌቶች ፊት ቀርበው በጉልበታቸው እንዲንበረከኩ ይደረጋሉ፡፡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወጣቶች በየዓመቱ ሀገራቸውን እየለቀቁ ወደ ውጭ ሀገር ይሰደዳሉ፡፡ ወጣቶቹ ዘ-ህወሀትን ርካሽ በሆነ መልኩ ካላገለገሉ እንዲሸማቀቁ፣ እንዲፈሩ እና እንዲቀጡ ይደረጋሉ፡፡
እየተቃጠለ ያለውን የኢትዮጵያን ቤት ከእሳቱ የሚያድነው ማን ነው?
በኢትዮጵያ በተቀጣጣዩ የባሩድ ሳጥን ላይ ያለውን የእሳት ማጥፊያ ፊውዝ ነቅሎ በመጣል እሳቱን የሚያጠፋው ማን ነው?
ሰላሟ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ማለም፣
እኔ በህልም ላይ ሙሉ እምነት አለኝ፡፡
ሰላሟ በእራሷ እና በዓለም ላይ የተጠበቀች አሜሪካንን ያልሙት በነበሩት በዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ እጅግ በጣም እመሰጣለሁ፡፡ በተራራ ላይ የተቆለለውን ተስፋቢስነት በማስወገድ እና ቆጥቋጭ በሆነ መልኩ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ያለመግባባት እና ጥላቻ ፍቅር እና መተሳሰብ ወዳለበት ወንድማማችነት ማሸጋገር እንደሚቻል ሲያቀርቡት በነበረው ቁምነገር ላይ እምነት አለኝ፡፡ በዚህ እምነት መሰረት አንድ ቀን ነጻ እንደምንሆን በመገንዘብ በአንድነት በአንድ ዓላማ በአንድነት ለመስራት፣ በአንድነት ለመጸለይ፣ በአንድነት ለመታገል፣ በአንድነት ወደ እስር ቤት ለመጋዝ፣ በአንድነት ለነጻነት ለመቆም እንችላለን፡፡ ከዚህ በላይ የተጠቀሰው እያንዳንዱ ቃል እውነት እንደሆነ አምናለሁ!
ኔልሰን ማንዴላ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ “ሰላሟ የተጠበቀ አፍሪካን እመኛለሁ፡፡“ ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ማንም ቢሆን በቆዳ ቀለሙ ምክንያት ወይም ደግሞ በታሪካዊ አመጣጡ ምክንያት ወይም ደግሞ በሚከተለው ኃይማኖት ምክንያት ሌላውን እንዲጠላ ሆኖ የተወለደ የለም፡፡ ሰዎች መጥላትን መማር አለባቸው፡፡ እናም መጥላትን የሚማሩ ከሆነ ፍቅርንም ሊማሩ ይችላሉ፣ በተፈጥሮ ፍቅር የበለጠ ከተቃራኒው ይልቅ ለልብ ቀድሞ ይመጣል፡፡” ከዚህ በላይ የተጠቀሰው እያንዳንዱ ቃል እውነት እንደሆነ አምናለሁ!
ዶ/ር ኪንግ ስለህልማቸው በሚናገሩበት ጊዜ እንደ አፍሪካ አሜሪካዊ የነብይነት ባህል ነበር የሚናገሩት፡፡ በነጮች የኃይል የበላይነት ባርነት፣ አድልኦ እና መድልኦ በትኩረት ነብይነትን በተላበሰ መልኩ በማሰብ ምን እንደሆነ እንገነዘባለን እናም ምስክርነትን እንሰጣለን፡፡ እናም ጭቆናን ዞረን ለመዋጋት በተባበረ ድርጊት በቀለም፣ በጎሳ እና በዘር ሳንለያይ በአንድነት፣ በታማኝነት አና በመልካም ነገር እራሳችንን ማደራጀት እና ንቅናቄ በመፍጠር መታገል የተለመደ ባህሪ ነው፡፡
በሀውልት ላይ ተቀርጸው የተጻፉ ነብያዊ መልዕክት ያላቸው ነገሮችም ስሜቴ እንዲሳብ ያደርጉኛል፡፡ የባቢሎን ንጉስ የነበሩት ኔቡከደነሶር ከወርቅ፣ ከብር፣ ከነሐስ እና ከሸክላ ግዙፍ የሆነ የአራዊት ምስል ህልም አይተው ነበር፡፡ ኔቡከደነሶር በህልማቸው በሰው ልጆች ያልተሰራ ሀውልት፣ ሀውልቱን ያወደመ እና ዓለምን ሁሉ የሚሞላ ተራራ አዩ፡፡ ዶ/ር ኪንግም ከተራራው ላይ የተቆለለውን ተስፋቢስነት ማስወገድ ሲሉ በተመሳሳይ መልኩ መግለጻቸው ነው፡፡
ነቢዩ ዳንኤል ኔቡከደነሶር ሀውልቱ ከባቢሎን የሚጀምሩ አራት ተከታታይ መንግስታትን ይወክላል፣ ድንጋዩ እና ተራራው በአምላክ የተመሰረተውን መንግስት ያመላክታል፣ ሆኖም ግን በምንም ዓይነት መንገድ አይወድምም ወይም ደግሞ ለሌላ ሰው አይሰጥም፡፡
ዘ-ህወሀት ላለፉት ሩብ ምዕተ ዓመታት ለኢትዮጵያ የሌለት ቅዠት ሆኖ ቆይቷል፡፡ የዘ-ህወሀት የሌሊት ቅዠት የጎሳ ክፍፍልን፣ የኃይማኖት ጽንፈኝነት ግጭትን፣ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣን፣ ሙስናን፣ የተሰረቀ የምርጫ ድምጽን እና የጅምላ ስቃይን ጎብኝቷል፡፡
የእኔ ህልም ዘ-ህወሀት ተንኮታኩቶ ወድቆ ወደ ታሪክ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫት ውስጥ ወድቆ ማየት እና ሰላሟ የተጠበቀ እና እውነተኛ የዴሞክራሲያዊ ህብረተሰብ በጽናት ሲነሳ ማየት ነው፡፡ እ.ኤ.አ ሀምሌ 2012 ሰላሟ ስለተጠበቀችው ኢትዮጵያ ህልም ጽፌ ነበር፡፡ እንደዚሁም ሁሉ እንዲህ የሚል ትንበያ ሰጥቸ ነበር፡
“ቀስ በቀስ እያደገ የመጣ የአሳተ ገሞራ ግፊት አለ፣ ሆኖም ግን በእርግጠኝነት ይህ ነገር በኢትዮያ ውስጥ ነው፡፡ ትንንሽ የአሳተ ገሞራ ፍንጣሪዎች እዚህ እዚያም ሆነው ይታያሉ፡፡ የህዝብ ደስተኛ አለመሆን ከመቅጽበት ፍጹም ወደሆነ የተስፋ እጦት ስሜት ይቀየራል፡፡ ህዝቦች እንደ የዋጋ ንረት እና የኑሮ ሁኔታ እንደ ሮኬት ተተኩሶ ወደላይ በመውጣቱ ምክንያት የህዝብን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት አቅም ሊገኝ አልቻለም፡፡ ሙስና፣ ስልጣንን ከሕግ አግባብ ውጭ መጠቀም፣ የጅምላ ጭቆና እና ደካማ አስተዳደር የአሳተ ገሞራን ለማፈንዳት በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ ሁኔታው ዕለት ከዕለት እየተበላሸ ሄዷል፡፡ የአረብን የጸደይ አብዮት ከተመለከቱ በኋላ የኢትዮጵያ ጡንቻማ (ዘ-ህዋህት) ገዥዎች ጥቂት እየፈሩ የመጡ እንደሆነ ማንም መገመት ይችላል፡፡“
የዘ–ህወሀት የሌሊት ቅዠት ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ ነውን?
ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን አሳፋሪ ሽንፈት ምን የምንማራቸው ነገሮች አሉ?
ትምህርት ቁጥር 1፡ ዘ–ህወሀት እግሩ ብረት ይምሰል አንጂ ሸክላ ነው፡፡
ዘ-ህወሀት ሰይጣናዊ አውሬ ነው ብየ አምናለሁ፡፡ ትኩረት በማድረግ ሲታይ ዘ-ህወሀት የማይበገር፣ አስቸጋሪ እና ለዘላለም ኃይለኛ መስሎ ይታያል፡፡ ዘ-ህወሀት ጠብመንጃዎቸ፣ ታንኮች፣ ሮኬቶች፣ አውሮፕላኖች እና ቦምቦች አሉት፡፡ ዘ-ህወሀት ለመተኮስ እግሮች ያሉት ቢሆንም እግሮቹ የተሰሩት ከሸክላ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ላይ የተነሳው ህዝባዊ እምቢተኝነት የዘ-ህወሀትን እግሮች ሸክላ ያደረገ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ዘ-ህወሀት ከሁሉም በላይ የሚፈራውን እና ሁልጊዜ የሚርበተበት እና እንቅልፍ የሚነሳው አንድ ነፍስ ዉጪ ነፍስ ግቢ ነገር አለ፡ ህዝባዊ እምቢተኝነት!
ዘ-ህወሀት ከማስተር ፕላኑ ጋር በተያያዘ መልኩ በአዲስ አበባ ዳርቻ የሚኖሩ አርሶ አደሮችን ትግል በመኮላሸት ጉሮሯቸውን ለማነቅ ሞክሯል፡፡ ይህ ፕላን ጭራቃዊ በሆኑ ሰዎች የተቀየስ እና በመቶዎች እና በሺዎች እንዲሁም በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ደኃ አርሶ አደሮች መሬትን ለመዝረፍ ነበር፡፡
ሆኖም ግን አውሬው ዘ-ህወሀት የህዝብን ያህል ኃይል አልነበረውም፡፡ ዘ-ህወሀት በመቶዎች የሚቆጠሩ መሳሪያ ያልታጠቁ አመጸኞችን በጥይት እየደበደበ በመግደል ሌሎችን በመቶዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ወደ ማጎሪያው እስር ቤት እየወሰደ አስሯቸዋል፡፡ ሆኖም ግን እዚህም፣ እዚያም፣ በሁሉ ቦታም አሻፈረኝ ብለው ከዘ-ህዋሀት ጋር ተፋጠጡ፡፡ ዘ-ህወሀት በመጨረሻ እስከ አጥንቱ መቅኔ ድረስ እንዲህ አይነት ፍርሀት ወሮት አያቅም:: ህዝቦች ከተባበሩ ማንም አያሸንፋቸዉም፡፡ በኦሮሚያ እየተካሄደ ያለው ውጥረት እየጠነከረ ሲሄድ ጠንካራዎቹ የኦሮሚያ ህዝቦች ዘ-ህወሀትን ወጥረው ይይዙታል፡፡ የኦሮሚያ ህዝቦች ከሸክላ እግር ካለው ከአውሬው ከዘ-ህወሀት በላይ የጠነከሩ ናቸው፡፡
አውሬው እንዲህ በማለት ህዝብን እንዲያሳምኑ ታዛዥ ሎሌ አሽከሮቹን ልኳል፡ “ከህዝብ ጋር የተደረገውን ውይይት ተከትሎ የተደረገ ምንም ዓይነት ፕላን የለም፡፡ ሙያዊ ወይም ደግሞ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ለመጨረሻ የፖለቲካ ውሳኔ ለማሳለፍ የተዘጋጀ ፕላን አልነበረም፡፡“ የሌባ አይነ ደርቅ እንዲሉ::
ተግባራዊ ትምህርት ቁጥር 1፡ አውሬው በህዝብ ኃይል ተወጥሮ ሲያዝ ወደ ኋላ ይመለሳል፣ ወደ ታች ያፈገፍጋል፣ እናም በመጨረሻ ነብሴ አውጭኝ በማለት በሩጫ ይፈረጥጣል፡፡
ትምህርት ቁጥር 2፡ ህዝባዊ እምቢተኝነት እና ሰላማዊ ተቃውሞ ዘ–ህወሀት አውሬውን ሊያሸነፍ ይችላል፣
ዊንስተን ቸርቺል አስቀድመው ያወቁት እንዲህ የሚል ትምህርት ነው፡
እነዚህን አምባገነኖች በወታደሮቻቸው እና በታማኝ የፖሊስ ኃይሎቻቸው ጎራዴዎች ታጅበው በተሽከርካሪ ወንበሮቻቸው ላይ ታዩአቸዋላችሁ… ሆኖም ግን በልባቸው ውስጥ አንድ ያልተነገረለት ፍርኃት አለ፡፡ ቃላትን እና ሀሳቦችን ይፈራሉ፡፡ በውጭ የሚነገሩ ቃላት፣ በሀገር ውስጥ የሚብላሉ ሀሳቦች-ሁሉም በጣም ኃይለኞች ናቸው፣ ምክንያቱም እነርሱን ይከለክሏቸዋል፣ ያስፈራሯቸዋል፡፡ በክፍል ውስጥ ትንሽ ሀሳብ በተነሳች ጊዜ በጣም ጠንካራ የተባሉት ሁሉ የፍርሀት ብርክ ይያዛቸዋል፡፡
ኃይለኛው ዘ-ህወሀት ሁሉም ዓይነት ጎራዴዎች፣ ታንኮች፣ ጠብመንጃዎች እና አውሮፕላኖች ሁሉ አሉት፡፡ ሆኖም ግን የወጣት ቡድኖች ጎራዴዎችን፣ ታንኮችን፣ ጠብመንጃዎችን እና አውሮፕላኖችን (ሄሊኮፕተሮችን) መገዳደር ሲጀምሩ ዘ-ህወሀት በድንጋጤ ብርክ ይይዘዋል፡፡ ዘ-ህወሀት ቃላትን እና ሀሳቦችን በጣም ከመፍራቱ የተነሳ ጋዜጠኞችን ማሰር ይፈቅዳል፣ ሆኖም ግን የተሸበረበት እና ብርክ የገባበትን የሚሰማው ከሆነ ወጣቱ ኃይል በአይበገሬነት ወኔ መሬቱን ለማስመለስ ሲል በእምቢተኝነት በዋና መንገድ ላይ በመውጣት ትግሉን ያጧጡፋል፡፡
ዘ-ህወሀት የወጣቱን ኃይል በሚጋፈጥበት ጊዜ ዓይኑን ሳያሽ በመቶዎች የሚቆጠሩትን ወጣቶች በመግደል በየቦታው የግድያ ጦር ግንባሮችን ይፈጥራል፡፡ ዘ-ህወሀት ”በእኛ እሬሳ ላይ መሬታችንን ትሰርቃላችሁ“ የሚል ግልጽ እና ቀላል መልዕክት ሲያገኝ ተደናግጦ ወደ ኋላ ያፈገፍጋል፡፡ የዘ-ህወሀት አውሬ ለጊዜው ጅራቱን በእግሮቹ መካከል በጉያው ወትፎ ሸሽቷል፡፡
ዘ-ህወሀት የህዝብን ልብ እና አዕምሮ ማግኘት ባለመቻሉ ምክንያት መጥፎ ዕድል እንደገጠመው ያውቃል፡፡ የጭካኔ ኃይልን በመጠቀም ብቻ ማንም ጨቋኝ እና ማንም አምባገነን መግዛት መቀጠል አይችልም፡፡ ዘ-ህወሀት መሳሪያ በመጠቀም በኃይል እርሱን መገዳደር ዓላማ ላደረጉ ህዝቦች ደንታው አይደለም፡፡ ደም የተጠማው ዘ-ህወሀት እርሱን ከሚቃወሙት ጠላቶቹ የበለጠ ህልቆ መሳፍርት የሌለው የጦር መሳሪያ አለው፡፡ ሆኖም ግን ዘ-ህወሀት በአስር ሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ህዝቦች ልብ እና አዕምሮ ውስጥ ያለውን ነገር ለማወቅ እንቅልፍ አጥቶ ሲውተረተር ይገኛል፡፡ ዘ-ህወሀት በእርሱ ተቃዋሚ ጠላቶች ልብ እና አዕምሮ ውስጥ በአጭር የማፈንጃ ፊዩዝ ተቀብሮ የሚገኝ ፈንጅ እንዳለ ያውቃል፡፡
ተግባራዊ ትምህርት ቁጥር 2፡ የዘ–ህወሀት አውሬ በወጣቱ ቁጣ እና ጠንካራ ውሳኔ ተወጥሮ ሲያዝ የሸክላ እግሩ ይፈረካክሳል፡፡
ተግባራዊ ትምህርት ቁጥር 3፡ የዘ–ህወሀት አውሬ እጅግ በጣም አጭበርባሪ፣ ሚስጥራዊ፣ አታላይ፣ ሸፍጥ እና ደባ ሰሪ፣ ሰይጣናዊ፣ ሕጋዊ ያልሆነ፣ አደገኛ እና ኃይለኛ፣ አውዳሚ፣ ክፉ፣ ድብቅ፣ እና በፕላኔቷ በየትኛውም ቦታ የሌለ ተንኮለኛ የማቻቬሊያን ፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡
ዘ-ህወሀት ከመሬት ዘረፋው በቀላሉ ሊመለስ ይችላል ብለው በተሳሳተ መልኩ የሚያምኑ በእርግጥ ተሳስተዋል፡፡ ዘ-ህወሀት በመናገሻ ከተማዋ አካባቢ የሚገኘውን የመሬት ዘረፋ በማንኛውም መንገድ ለምን እንደሚቀጥልበት ሁለት አሳማኝ ምክንያቶች አሉ፡፡ እነርሱም፡
አንደኛ፡ ዘ-ህወሀት ለረዥም ጊዜ በስልጣን ላይ ያለምንም ስጋት ለመቆየት የሚችለው በመናገሻዋ ከተማ የሚገኘውን ተቃዋሚ ኃይል በመበታተን እንደሆነ እምነት አለው፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 የተካሄደውን የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ ውዝግብ ተከትሎ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመናገሻ ከተማዋ ያሉትን 23ቱን መቀመጫዎች አሸነፉ፡፡ ዘ-ህወሀት ህልውናውን ይዞ ሊቆይ የሚችልበት እና ስልጣኑን በመናገሻ ከተማዋ ሊያጠናክር የሚችልበት መንገድ ሁሉምን ታሪካዊ መኖሪያዎች፣ የማህበረሰብ ጥምረቶች እና የጉርብትና መርሆዎችን ፍጹም በሆነ መልኩ በማጥፋት ነው፡፡ ከዓለም ባንክ በሚገኝ የገንዘብ ምንጭ የከተማ ዕቅድ እና የመናገሻ ከተማዋ ልማት በሚል ስልት ዘ-ህወሀት ዜጎችን ከመኖሪያ ቦታቸው በኃይል በማፈናቀል እና በከተማ ቀመስ ገጠር አካባቢዎች እንዲኖሩ በማድረግ የከተማ ማስወገድ ትልቅ ፕርግራም ሲያካሂድ ዘመናት አልፈዋል፡፡ የተበታተነ ህዝብ ተጽዕኖ ለመፍጠር ችሎታ የለውም፣ ወይም ደግሞ መብቱን በጋራ ለማስከበር ብቃቱ አይኖረውም፡፡
የዘ-ህወሀት የመጀመሪያው ስልት (ስትራቴጂ) የዘ-ህወሀት አስመሳይ ዘራፊ ጌቶች እና የእነርሱ አጫፋሪ ሎሌዎች እንዲሁም ጥገኛ ልሂቃን ደኃ ጎረቤታሞችን እና አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ከከተማው በማፈናቀል የተወሳሰበ ፕሮግራምን በማራመድ ላይ ይገኛሉ፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ዘ-ህወሀት በተቻለ መጠን በከተማይቱ ያለውን ሁሉ ቦታ በወንጀለኛ ቤተሰቦቻቸው አማካይነት እንዲያዝ ማድረግ ነው፡፡ አዲስ አበባ የሀገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚ እና የፖለቲካ መዲና በመሆኗ እና የአህጉሪቱ መናገሻ በመሆኗ ምክንያት ዘ-ህወሀት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ፍጹም በሆነ መልኩ መቆጣጠር ይፈልጋል፡፡ ዘ-ህወሀት በርካታ ቦታዎችን በመናገሻ ከተማዋ በተቆጣጠረ ጊዜ የበለጠ የግንባታ ስራዎችን ያካሂዳል፣ ግዙፍ ገንዘብም ያንቀሳቅሳል፣ የኢኮኖሚ ጡንቻውንም ያፈረጥማል፡፡
ዘ-ህወሀት ለረዥም ጊዜ የፖለቲካ ህልውና ዕድል እንዲኖረው ከተፈለገ የአዲስ አበባን ማህበራዊ ትስስር፣ የማህበረሰብ ጥምረት እና የኑሮ ዘይቤ በመበጠስ ከተማዋ በእራሱ አምሳል እንድትሄድ አድርጎ መቀየር ነው፡፡ ዘ-ህወሀት በአዲስ አበባ አካባቢ ያለውን መሬት ለመዝረፍ የሚያስችል ማንኛውንም ነገር ያደርጋል፡፡ ከሁሉም በላይ በአዲስ አበባ ዙሪያ አካባቢ ዕቅዱ ቢሰምርለት ኖሮ 36 ትላልቅ እና ትናንሽ ከተሞችን ይበላ ነበር፡፡ ይኸ ለዘ-ህወሀት ጌቶች ብዙ ገንዘብ ነው!
ዘ-ህወሀት ህዝቡን ከመናገሻ ከተማዋ በማፈናቀል ወደ ከተማዋ አካባቢ በማስፈር እና ከአካባቢዎች ወደ ከተማዋ ፍልሰት እንዲኖር በማድረግ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ዓላማዎቹን ለማሳካት የሚጠቀምበት ብቸኛው መንገድ ነው፡፡
የዘ-ህወሀት የመሬት ዝርፊያ ፕላን ቢ (B) (ሚስጥራዊ የዘረፋ ፕላን) ማብቂያ የሌለው ክፍሎች አሉት፣ እናም በድብቅ፣ ግልጽ ባልሆነ መንገድ እና በማይታይ ሁኔታ፣ ሊቆም በማይችል እና አስመሳይነት በሚመስል መልኩ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ ጥቂት የፕላን ቢ (B) ክፍሎች እንደሚከተለው ይቀርባሉ፡
1ኛ) ማስተር ፕላን የሚባል ነገር እንደሌለ አድርገው በተጎዳው አካባቢ ያለው ህዝብ የጥበቃ አባላቱን እስከሚያስወግድ ድረስ እያንዳንዱን ሰው ማታለል፣
2ኛ) ማስተር ፕላኑን “የአሮሚያ ልማት ፕሮጀክት“ በማለት በሌላ ጣፋጭ የሆነ ስያሜ በመስጠት ማስተር ፕላኑን እንደገና መቀስቀስ፣
3ኛ) ሌላ የማህበረሰብ የፕሮጀክት ፕላን (ማወናበጃ ፕላን) ከኦሮሚያ ህዝብ ጋር ለመስራት ማስመሰል፣
4ኛ) ከአካባቢው ሰዎች ጋር በመሆን የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ከግል አልሚዎች ጋር አብረው የሚያለሙ ማስመሰል፣
5ኛ) በድብቅ መሬት በመግዛት እና ለማዘዋወር እንዲቻል የአካባቢውን ግንባር ቀድም ሰዎች መጠቀም፣
6ኛ) የመሬት ዝርፊያውን ትንሽ በትንሽ በመተግበር የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ሰዎች ዓይናቸውን እንኳ እርግብ አያደርጉም፡፡
7ኛ) መሬት ለማግኘት ሲባል የእዩልኝ እመኑኝ የማስመሰያ ፕሮጀክቶችን መፍጠር፣
8ኛ) ስልታዊነትን ባካተተ እና ዘዴ በተመላበት ሁኔታ የመሬት ዛረፋውን የሚቃወሟቸውን ሰዎች ሀ) እነርሱን በመግዛት፣ ለ) እነርሱን ማስፈራራት፣ ሐ) ማሸማቀቅ እና ማስበርገግ፣ መ) ማሰር እና ማሰቃየት ሠ) እነርሱን በመግደል ነው፡፡ በሌላ አባባል የዘ-ህወሀትን የተለመደዉን መስፍርት የአሰራር ስርዓት መጠቀም፡፡
ተግራባራዊ ትምህርት ቁጥር 3፡ ዘ–ህወሀት የእርሱን ማስተር ፕላን ቢን ለመተግበር እና የመሬት ዝርፊያውን ለመተግበር እና በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን አንድ ዓይነት ቦታ ለማመላከት ዘ–ህወሀት ቂሙን ቋጥሮ እንደገና መመለሱ አይቀሬ ነው፡፡ ዘ–ህወሀት ምንም ዓይነት ምርጫ የለውም፣ ዝርፊያውን በመናገሻ ከተማዋ አካባቢ አጠናክሮ መቀጠል ብቻ ነው፣ ምክንያቱም ከፖለቲካውም ሆነ ከኢኮኖሚያዊ ውጭ ያለው ምርጫ ይህ ብቻ ነው፡፡
ትምህርት ቁጥር 4፡ የብዙሀን ሰላማዊ የሆነ ተቃውሞ ኃይለኛውን እና ጨካኙን ጨቋኝ ቡድን ማሸነፍ ይችላል፡፡ ዘ–ህወሀት በሰራው ወንጀል የሚጠየቅበት ቀን እየደረሰ መሆኑን ያውቃል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ማስተር ፕላኑን በመቃወም የሕዝብ እምቢተኛነት በመጠናከር አመርቂ የሆነ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ማንም ያውቀዋል፡፡ እንደዚህ ያለው የህዝብ እምቢተኝነት እና ተባባሪ ያለመሆን በእያንዳንዱ መንደር፣ ከተማ፣ እና ክልል በስፋት የሚቀጥል ቢሆን ምን ሊመጣ ይችላል?
ዶ/ር ኪንግ ማንኛውም ህብረተሰብ ኢፍትሀዊነትን ለመታገስ የማይችልበት ደረጃ ይመጣል በማለት አስተምረዋል፡፡ ጨቋኙ ቡድን የእርሱን የስቃይ ሰለባዎች በፈቃደኝነት ነጻ ወይም ደግሞ የእርሱን ክብር እና ጥቅም በፈቃደኝነት ሊተው አይችልም፡፡ ነጻነት ከጨቋኙ በነጻ አይገኝም፡፡ ተጨቋኞች ነጻነታቸውን መጠየቅ አለባቸው፡፡ ያ ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እየደረሰ ነው!
በኢትዮጵያ ማህበረሰብ ውስጥ መጠነ ሰፊ የሆነ ሰላማዊ የህዝብ ንቅናቄ ቢደረግም እንኳ በአሁኑ ጊዜ በስልጣን ላይ ያለውን ዘ-ህወሀትን በኃይል ማስወገድ አይቻልም የሚሉ ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ አንድ ሰው እሳትን በእሳት ማጥፋት ወይም ደግሞ ዓይንን ያጠፋ ዓይኑ መጥፋት አለበት ብለው የሚያምኑ አሉ፡፡ በአንድ ወቅት ጋንዲ እንዲህ ብለው ነበር፣ “በፍርሀት እና በኃይለኝነት መካከል ብቻ ምርጫ የሚኖር ቢሆን ኃይለኝነትን እንደምመርጥ አምናለሁ…ህንድ ክብሯን ለማስመለስ በፍርሀት ተውጣ ከማየት ወይም ደግሞ ምንም ዓይነት ተስፋ የሌላት ሆነ ከመቀመጥ መሳሪያ በማንሳት የእራሷን ክብር ማስመለስ አለባት፡፡“
ኃይል ሊያቋርጥ በማይችል መልኩ ኃይልን፣ ጥላቻን፣ በቀልን እና በቀልተኝነትን በመውለድ ወደ መጥፎ አቅጣጫ እንደሚወስድ ለእኔ ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ግን የኢትዮጵያን ክብር ለመመለስ ብቸኛው አማራጭ ከፍርሀት እና ከኃይለኝነት አንዱን መምረጥ ነው ብላችሁ ለምታስቡ የእራሳችሁን መንገድ ተከተሉ እላለሁ፡፡
ከተለመደው ሕግ የወጣ በእራሱ ሕግ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ ያ ኃይል እጅግ በጣም ልዩ በሆነበት ጊዜ ውስጥ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፣ ሆኖም ግን በተለመደው ሁኔታ ግን የግድ አስፈላጊ ነው ማለት አይደለም፡፡ ቢያንስ ተቃራኒው አመክንዮ እውነትነት ያለው ይመስላል፡፡
ለውጥን በሰላማዊ መንገድ እንዲመጣ የማይፈቅዱ ሁሉ አብዮትን እንዲያስተናግዱ ይገደዳሉ የሚል አመለካከት አለኝ፡፡ ስለሆነም በመጨረሻው ሰዓት ለውጥ በሰላማዊ መንገድ ወይም በኃይል እንዲመጣ የመወሰኑ ሁኔታ በተጨቋኞች እጅ ሳይሆን በጨቋኞች እጅ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ሰላማዊ ለውጥን በመቃወም እና የህዝቦችን ተስፋ እና ምኞት በመገደብ ጨቋኞች ተጨቋኞችን በኃይል ለውጥ እንዲያመጡ ያስገድዳሉ፡፡
የህዝብ እምቢተኝነት ዓላማ ፍትሀዊ ባልሆኑ ህጎች ላይ ለውጥ በማምጣት ትክክለኛ እና ፍትሀዊ ማህበረሰብ ለመገንባት ነው፡፡ ለቡድኑ ወይም ለግለሰቦች ሳይሆን ለብዙሀኑ ጥሩው ነገር ምን እንደሆነ የፖለቲካ ስራ በመስራት የሚመጣ ነገር ነው፡፡ የህዝብ እምቢተኝነት ስራ ለረዥም ጊዜ የቆየን በስልጣን መባለግ እና የዜጎችን መብት መከልከልን ለማስወገድ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡
ዶ/ር ኪንግ በሰላማዊ አመጽ ዘመቻ ውስጥ አራት መሰረታዊ ደረጃዎች (የሕዝብ እምቢተኝነት) እንዳሉ አስተምረውናል፡፡ እነርሱም፡ “ኢፍትሀዊነት በእውንነት መኖር አለመኖሩን ለመወሰን እውነታዎችን መሰብሰብ፣ ስምምነት ማድረግ፣ እራስን ከኃጢያት ንጹህ ማድረግ እና ቀጥተኛ የሆነ እርምጃ መውሰድ“ ናቸው፡፡
በቀጥታ እርምጃ የመውሰድ ዓላማ ምንድን ነው? ዶ/ር ኪንግ በቀጥታ እርምጃ የመውሰድ ዓላማ በፈጠራ የታጀበ ውጥረትን በመፍጠር እና ቀውሱን ወደ በጎ ነገር በመቀየር ማህበረሰቡ ያለምንም ማቋረጥ መስማማት ካልቻለ ጉዳዩን ፊት ለፊት ይጋፈጠዋል…የቀጥተኛ እርምጃ ዓላማ በቀውስ ውስጥ ያለን ሁኔታ በሩን ክፍት በማድረግ ወደ ስምምነት ለማምጣት የሚደረግ ዘዴ ነው፡፡
የህዝብ እምቢተኝነት አንዱ የቀጥተኛ ድርጊት መገለጫ ነው፡፡ የህዝብ እምቢተኝነት ምንነት ፍትሀዊ ያልሆነን ህግ ለመቀበል የሞራል ግዴታ የሌለበት እና ምንም ዓይነት ሕግ የለም በሚል መርህ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የጨቋኞች ሕግ አስመሳይ ህግ ነው፣ ጨቋኙ ተጨቋኙን ለመጨቆን እና የኢፍትሀዊነት ሰለባዎቹን ለማሰቃየት የሚጠቀምበት ህግ ነው፡፡ ማንኛውም የሰው ልጆችን መሰረታዊ የሰብአዊ መብት የማያከብር ሁሉ ፍትሀዊ ያልሆነ ሕግ እና ለመታዘዝም ጠቃሚነት የሌለው ሕግ ነው፡፡ በእርግጥ ለኢፍትሀዊ ሕግ አለመታዘዝ የሞራል መብት እና ተጨቋኞች ሊተገብሩት የሚገባ አብይ ጉዳይ ነው፡፡
ለዶ/ር ኪንግ ሁሉም አድሎአዊ ሕጎች ፍትሀዊ አይደሉም ምክንያቱም እነዚያ ሕጎች ከተፈጥሯዊው ወይም ደግሞ ከአምላክ ሕግ ጋር የሚጻረሩ ናቸው፡፡ አድሎአዊ ህጎች የእነርሱን ሰለባዎች ከሰውነት ውጭ የሚያደርጉ እና ደባ ፈጻሚዎችን የማጠናከር ዓላማ ያላቸው ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ዶ/ር ኪንግ ሰላማዊ አመጽ የሚያደርጉትን እና ለአድሎአዊ ህጎች የማይታዘዙትን የህዝብ የእምቢተኝነት አመጾች ሁሉ በአድሎአዊ ሕጎች ላይ እንዲነሱ የሚማጸኑት፡፡
ጨቋኙ ሁልጊዜ ማንኛውንም የህዝብ እምቢተኝነት ድርጊቶችን ሁሉ ኃይልን በመጠቀም ለመጨፍለቅ ጥረት ሲያደርግ ይስተዋላል፡፡ ጨቋኙ ከመጠን ያለፈ ኃይልን ይጠቀማል፡፡ ጨቋኙ ሰላማዊ አመጸኞች ባመጹ ጊዜ ወሮበላ፣ ወንበዴ፣ ኃይለኛ እና ወንጀለኛ በማለት ጥላሸት ለመቀባት ጥረት ያደርጋል፡፡ ጨቋኙ የበለጠ ኃይልን በሚጠቀምበት ጊዜ ተጨቋኞች ደግሞ የእምቢተኝነት እና ያለመተባበር ድርጊቶችን በጨቋኙ ላይ በመፈጸም ከዚያ የበለጠ የመልሶ ማጥቃት ኃይልን ይጠቀማሉ፡፡
ተግባራዊ ትምህርት ቁጥር 4፡ ህዝባዊ እምቢተኝነት በትርጉሙ ህዝባዊ መሆን አለበት ምክንያቱም የሰለጠኑ ህዝቦች በጫካው ሕግ የሚመሩትን የጨካኞች እና የኋላቀሮችን የጫካ ሕጎች በሰለጠነ ህዝባዊ እምቢተኝነት ለማስወገድ ጥረት የሚያደርጉ ናቸው፡፡
ሰላማዊ ለውጥን በሰላማዊ መንገድ እንዲመጣ የማይፈቅዱ ሁሉ የአብዮትን አይቀሬነት እንዲያስተናግዱ ይገደዳሉ፡፡
ዘ-ህወሀት በሰራው የጥፋት ወንጀል ቅጣቱን የሚቀበልበት ጊዜ በፍጥነት እየመጣ ነው፡፡ በዘ-ህወሀት ላይ ምን ሊመጣ እንደሚችል ውሳኔው ያለው በእራሱ እጅ ላይ ነው፡፡ የሰላማዊ መንገድን መምረጥ ይችላል ወይም ደግሞ ኃይል የተቀላቀለበትን አብዮት ሊጋብዝ ይችላል፡፡
ያም ሆነ ይህ የዘ-ህወሀት አውሬ ዋጋዉን ያገኛል:: “የዚያን ጊዜም ብረቱና ሸክላው፥ ናሱና ብሩ ወርቁም በአንድነት ተፈጨ፥ በመከርም ጊዜ በአውድማ ላይ እንዳለ እብቅ ሆነ፤ ነፋስም ወሰደው፥ ቦታውም አልታወቀም፤ ምስሉንም የመታ ድንጋይ ታላቅ ተራራ ሆነ ምድርንም ፈጽሞ ሞላ”
ስለሆነም አፈፃፀሙ የታወቀ ነው፡፡ “የኢትዮጵያን ቤት የሚበጠብጡ ሁሉ ጉምን ይዘግናሉ” ተብሎ ተጽፏልና!
ይቀጥላል…
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
የካቲት 4 ቀን 2008 ዓ.ም