ትበራለች፣ ኢትዮጵያ እንደ ወፍ ክንፍ አውጥታ ትበራለች!!!

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም   

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

Fly 2“ኢትዮጵያውያን በእርግጠኝነት ነጻ ቢሆኑ ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?“

ይህ ከላይ በመንደርደሪያነት የቀረበው ጥያቄ ባለፈው ሳምንት ዘኢኮኖሚስት የተባለው መጽሄት ባዘጋጀው ጹሁፍ በርዕሰ አንቀጹ ላይ ያቀረበው ነበር፡፡

መጽሔሄቱ እራሱ ላቀረበው ጥያቄ እንዲህ በማለት እራሱ የሰጠው መልስም አስደማሚ ነበር፡

“መንግስት ዜጎች የሰላም አየር እንዲተነፍሱ እና በነጻነት እንዲኖሩ ቢፈቅድ ኖሮ እንደ ወፍ ክንፍ  አውጥተው ይበሩ ነበር፡፡“

እነዚህ አስራ ስድስት ቃላት ዓይኖቼ እንባ እንዲያቀሩ፣ ልቤ በሀሴት እንዲሞላ እና መንፈሴም በማይበገር ብሩህ ተስፋ በጽናት እንዲሞላ አደረጉኝ፡፡

እኔም እንደዚሁ ሁሉ ላለፉት አስር ዓመታት በእያንዳንዷ ቀን ለእራሴ አንድ ዓይነት ጥያቄ እያቀረብኩ ተደጋጋሚ ምላሽ ስሰጥ ቆይቻለሁ፡፡

ሆኖም ግን የእኔ ጥያቄ ትንሽ ለየት ይል ነበር፡፡ የጥያቄዉም ልዩነት ለእኔ አስተያየት ከፍተኛ ለውጥ አለው።  ማለትም —

የኢትዮጵያ ወጣቶች ነጻ ቢሆኑ ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች ነጻ ሆነው ማሰብ የሚችሉ ቢሆን ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች በእርግጠኝነት በነጻ ሀሳባቸውን መግለጽ የሚችሉ ቢሆን ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች በእርግጠኝነት በነጻነት መጻፍ፣ መጦመር እና መዘገብ የሚችሉ ቢሆን ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች በነጻነት እምነቶቻቸውን ማራመድ ቢችሉ ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች በነጻነት የመደራጀት እና በፖለቲካ ፓርቲዎች እና በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ውስጥ በእርግጠኝነት በነጻነት መሳተፍ የሚችሉ ቢሆን ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች ያሉባቸውን ቅሬታዎች ያለምንም ፍርሀት እና መሸማቀቅ በእርግጠኝነት በነጻነት ማቅረብ የሚችሉ ቢሆን ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች የእራሳቸውን መሬት በነጻነት የሚይዙ ቢሆን እና በነጻነት ማረስ፣ ማከራየት ወይም ደግሞ መሸጥ የሚችሉ ቢሆን ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምንም ዓይነት የመሸማቀቅ ስሜት ሳይኖርባቸው እና በጎሳ በተሸነሸነችው ምድር (በአሁኑ ጊዜ ክልል እየተባለ በሚጠራው የአፓርታይድ ባንቱስታንስ ዓይነት የሰዎች የጎሳ የማጎሪያ በረት ሳይቀፈደዱ) በሀገራቸው በነጻነት በፈለጉበት ቦታ የመኖር እና የመንቀሳቀስ ነጻነት ቢኖራቸው ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምንም ዓይነት የጎሳ የዘረኝነት ምልክት/ማጣሪያ/limus test ሳይደረግ በዜግነታቸው፣ በችሎታቸው፣ በትምህርት ዝግጅታቸ እና በስራ ብቃታቸው ብቻ እየተመዙ በነጻነት ሊሰሩ እንዲችሉ ቢፈቀድላቸው ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች ለሙስና፣ ለግዞት እና ለጭቆና እንዲያጎበድዱ ሳይገደዱ በነጻነት ሰርተው ሊኖሩ የሚችሉበት መልካም ስርዓት ቢፈጠርላቸው ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች የጎሳ ጥላቻ ምግብ የፕሮፓጋንዳ ትምህርት በማንኪያ እየተዘገነ በማጉረስ እንዲማሩ ባይደረጉ እና በነጻነት የሚማሩ ቢሆን ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች የሚፈልጉትን የፖለቲካ ፓርቲ፣ ማህበር/union እና የሲቪክ ድርጅቶችን በእራሳቸው ፍላጎት ብቻ በመምረጥ መቀላቀል እና መሳተፍ እንዲችሉ ነጻነት ቢኖራቸው ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች ከሕግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር ከመዋል እና በየማጎሪያ እስር ቤቶች እየተጋዙ ዘብጥያ የማይጣሉ እና ነጻ ቢሆኑ ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች በሸፍጥ ከተሞላው እና ነጻ ዜጎችን የማጥቂያ መሳሪያ ሆኖ አገዛዙን እያገለገለ ካለው የጸረ ሽብርተኝነት ክስ ነጻ ሆነው የሚኖሩ ቢሆን ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች በነጻነት የሰብአዊ መብቶቻቸውን እያጣጣሙ መኖር የሚችሉ ቢሆን ኖሩ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች የሕግ የበላይነት ተከብሮ እያጣጣሙት ነጻ በመሆን የሚኖሩ ቢሆን ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች ሁሉም ሕጎች በእኩልነት እየተጠበቁ ነጻ ሆነው ፍትህን እያጣጣሙ የሚኖሩ ቢሆን ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች በየጊዜው ነጻ እና ፍትሀዊ ምርጫ እየተደረገ በነጻነት ድምጻቸውን እየሰጡ መኖር የሚችሉ ቢሆን ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች በወሮበሎች የሕግ የበላይነት ሳይሆን የሕግ የበላይነት በተከበረባት ሀገር መኖር የሚችሉ ቢሆን ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች በጎሳ ማንነታቸው ሳይሆን በውስጣዊ ባህሪያቸው ይዘት ብቻ ሊገመገሙ የሚችሉበት ስርዓት መኖር ቢችል ኖሮ የት የደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች ካሰቡበት ከፍተኛ ደረጃ ለመድረስ እንዲችሉ ነጻ መሆን የሚችሉ ቢሆን ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች ከጭቆና አገዛዝ፣ ከጎሳ አድልኦ፣ በሕገወጥ ወሮበላ ከመደቆስ፣ በባርነት፣ ከመሰቃየት፣ በኃይል አገዛዝ ከመንገላታት፣ ከማስፈራራት፣ ከጨቋኝ አምባገነናዊ ስርዓት፣ ከወሮበላ ዘራፊነት… ነጻ ሆነው መኖር የሚችሉ ቢሆን ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች አምባገነናዊው አገዛዝ ነጻ ሆነው መኖር እንዲችሉ የሚፈቅድላቸው ቢሆን ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

የኢትዮጵያ ወጣቶች ነጻ፣ ነጻ፣ ነጻ… ሆነው መኖር የሚችሉ ቢሆን ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?

በእግዚአብሄር ቸርነት! የኢትዮጵያ ወጣቶች በሰማይ ላይ እንደሚበሩት በሚሊዮን እንደሚቆጠሩት ቢራቢሮዎች ሁሉ ይበራሉ፣ ይበራሉ፣ ክንፍ አውጥተው ይበራሉ፡፡

እንደ አሞራ ከፍ ከፍ ብለው ይበራሉ፡፡

“የኢትዮጵያ ወጣቶች ምንም ዓይነት የድካም ስሜትን ሳያስተናግዱ በፍጥነት ይሮጣሉ፣ ረዥሙን ጉዙ በጽናት ይጓዛሉ፡፡”

የዘኢኮኖሚስት መጽሄት ኢትዮጵያውያን ለምን እንደማይበሩ እንዲህ የሚሉ በርካታ ምክንያቶችን ሰጥቷል፡ 

በሀገሪቱ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች አሉ፡፡ ዜጎችን ማሰቃየት የዕለት ከዕለት ስራ ነው፡፡

ሁሉም መሬት የመንግስት ነው፣ ስለሆነም መሬት ብድር ለመጠየቅ በማስያዣነት ሊያገለግል አይችልም፡፡

የተለመደ አንድ ቤተሰብ ከአንድ ሄክታር ያነሰች የተበጣጠሰች መሬት ብቻ ነው ያለችው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ቢያንስ 25 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ለአስከፊ ድህነት ተዳርገው ይገኛሉ፡፡

የአገልግሎት ዘርፉ በዓለም ላይ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ክልከላ ከተጣለባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ነው፡፡

መንግስት የተንቀሳቃሽ ስልክ እና የባንክ አገልግሎቶችን ወደ ግል ዘርፉ ማዛወሩን ስለሚቃወም ግልጽ በሆነ መልኩ እራሱን እየጎዳው ይገኛል፡፡

አንድ በስነ ሕይወት የትምህርት መስክ ከዩኒቨርስቲ የተመረቀ ወጣት በወር 26 የአሜሪካ ዶላር ምንዳ የሚያገኝ ከሆነ በደስታ ይፈነድቃል፡፡ የቀን ሰራተኛ ደግሞ ከዚህ በእጅጉ ያነሰ የክፍያ ምንዳ ያገኛል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከአፍሪካ በተንቀሳቃሽ ስልክ የባለቤትነት መጣኔ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙት መካከል ውስጥ ናቸው፡፡

ከአራት በመቶ የሚያንሱ አባዎራዎች ብቻ ቋሚ የስልክ መስመር ያላቸው ሲሆን ሶስት በመቶ የማይሞሉት ደግሞ ባለብዙ መስመር የስልክ ግንኙነት/የብሮድ ባንድ የስልክ ግንኙነት መስመር አላቸው፡፡

መንግስት ኬንያ እንዳደረገችው ሁሉ የአየር ሞገዱን ለውድድር ክፍት የሚያደርግ ከሆነ የንግድ ፈቃዱን ቢያንስ በ10 ቢሊዮን ዶላር መሸጥ ይችላል፣ እንደዚሁም ደግሞ ከግብር እና ከባለቤትነት መብት ብዙ ገንዘብ ማግኘት ይችላል፡፡ በኬንያ ውስጥ የሚገኘው ሳፋሪኮ በሀገሪቱ ውስጥ ትልቁ ግብር ከፋይ ኩባንያ ነው፡፡

መንግስት ጎበዝ ቢሆን እና የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት ለውድድር ነጻ ቢያደርገው እነዚህ ሁሉ ቸግሮች ይወገዳሉ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ መንገዶች እና የባቡር ሀዲዶች በፍጥነት ይገነባሉ፡፡ ከከተማው በስተምስራቅ አቅጣጫ በጠንካራ መሰረት ባልተሰራ መንገድ ላይ መኪና በመንዳት በተሻለ የጥንካሬ ሁኔታ ወደተሰራ መንገድ ለመቀላቀል ወደ 80 ወይም ከዚያ በላይ ኪሎ ሜትሮች ያህል ጋዜጠኛህ ለሁለት ሰዓታት ያህል ቢቆይ እንኳ ሌላ ተሽከርካሪ ለማየት አይችልም፡፡

በቅርብ ጊዜ ውስጥ ዘኢኮኖሚስት ባዘጋጀው እና አዲስ አበባ ላይ ተደርጎ በነበረው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ምንም ዓይነት የኢትዮጵያ ወይም የውጭ የቢዝነስ ሰው መገኘት አለመቻሉ ማንኛውንም የመንግስትን ፖሊሲ ለመተቸት ድፍረቱን ይሰጣል፡፡ ግልጽ በሆነ መልኩ ኢትዮጵያውያን በግሉ ዘርፍ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት በትክክል የሚያምኑበት ቢሆንም እንኳ የመንግስቱን መስመር እንዲከተሉ ጫና ይደረግባቸዋል፡፡

ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ መሰረታዊ የወጥ ቤት መለዋወጫ ዕቃዎች ብዙውን ጊዜ በአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ውስጥ ይያዛሉ፣ ሆኖም ግን የሚጣልባቸው የቀረጥ ክፍያ ሰማይ ይነካል፡፡ በቅርቡ ለሰራተኞች መለያ ሎጎ ያለባቸው ቲ ሸርቶች ተይዘው ከዋናው ዋጋቸው በላይ ሶስት ጊዜ እጥፍ ቀረጥ እንዲከፍሉ ተደርጓል፡፡

የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ይደፈጠጣሉ፣ እንዲሰነጣጠቁ እና ምንም ዓይነት ነገር ማድረግ የማይችሉ ሽባ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ ታዋቂ የሆኑ የሰላማዊ ትግል አራማጆች አንድም ከሀገር ጥለው እንዲሰደዱ ተደርገዋል ወይም ደግሞ በእስር ቤት ውስጥ ዘብጥያ ተጥለው ማብቂያ በሌለው በፍርድ ቤቶች ቀጠሮ በመመላለስ እና በመሰቃየት ላይ ይገኛሉ፡፡

ገዥው ፓርቲ የምጣኔ ሀብቱን እና የፖለቲካውን ስርዓት ክፍት ለማድረግ ድፍረቱ ቢኖረው ኖሮ ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና እና ወደ መረጋጋት የምታደርገው ጎዞ እጅግ በጣም የተፋጠነ ይሆን ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች መብረር ይችሉ እንደሆነ እስቲ እናስብ፡

መብረር የሚችሉ ቢሆን የኢትዮጵያ ወጣቶች ለመሞት ሲባል በባህር ውስጥ አይገቡም ነበር፡፡

መብረር የሚችሉ ቢሆን የኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች ወደ መካከለኛው የአረብ ሀገሮች በመብረር በእርግጠኝነት ባሮች አይሆኑም ነበር፡፡

መብረር የሚችሉ ቢሆን ወጣት ኢትዮጵያውን ምድረበዳ በረሀዎችን በማቋረጥ ደም እንደ ውኃ ለጠማቸው ለአሸባሪዎች ሰለባ አይሆኑም ነበር፡፡

መብረር የሚችሉ ቢሆን ኖሮ ወደ ሰው ሀገር ስደት አይሄዱም ነበር፡፡

መብረር የሚችሉ ቢሆን ኖሮ እንደ አፍሪካ ጭልፊት ዓሳዎች ይበሩ ነበር፡፡

መብረር የሚችሉ ቢሆን ኖሮ እንደ አፍሪካ የባህር ወፍ ይንሳፈፉ ነበር፡፡

መብረር የሚችሉ ቢሆን ኖሮ እንደ ታላቁ ግዙፉ የአፍሪካ የባህር ወፍ ወደ ላይ ይወጡ ነበር፡፡

መብረር የሚችሉ ቢሆን ኖሮ ክንፎቻቸውን ከፍ አድርገው ወደ ላይ ወደ ሰማይ ይበሩ ነበር፡፡

መብረር የሚችሉ ቢሆን ኖሮ እንደ ትንሿ ድምጻዊ ተርገፍጋፊ ወፍ ይበሩ ነበር፡፡

ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ወጣት ዜጎች መብረር አይችሉም፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች በሸፍጠኞች እንደ እንስሳት በበረት ውስጥ ታጉረው ባሉበት ሁኔታ እንዴት መብረር፣ እንደ አሞራ መክነፍ ይችላሉ?

የኢትዮጵያ ወጣቶች በወሮበሎች ገነት በረት ውስጥ ታጉረው ባሉበት ሁኔታ እንዴት መብረር ይችላሉ?

ስለሆነም የኢትዮጵያ ወጣቶች በወሮበሎች ገነት በረት ውስጥ እንደ ከብት ታጉረው  ይዘምራሉ፣ ያለቅሳሉ እናም ይጮሀሉ፡፡

በማቆያ ጎጆ ውስጥ የታጎረ ወፍ የሚዘምረው ለምንድን ነው?

በማቆያ ጎጆ ውስጥ የታጎረ ወፍ የሚዘምረው ለነጻነቱ ሲል ነው በማለት ማያ አንጌሉ ተናግረዋል፡፡

የታጎረ ወፍ ለነጻነት ይዘምራል፣

አስፈሪ የሆነ ቅላጼውን ያሰማል፣

ላሳሪዎቹ መርዶ ያረዳል፣

ለወዳጆቹ ብስራትን ይነግራል፣

ደግሞ ደጋግሞ ይዘምራል፡፡

 

በጨቋኝ ስር ለወደቁ፣

በግፍ ታንቀው ለደቀቁ፣

እና እስካሁን ለዘለቁ፣

ምጻት ቀርቧል በረቂቁ፣

 

ቅላጼው ይሰማል ከላይ ከተራራ፣

ከዚያ ከሩቅ ስፍራ ከሸለቆው ጎራ፣

መብት ለማስከበር ነጻነት ሲጣራ፣

ፍትህን ለማስፈን በጸሐይ ጠራራ፣

ጉልበተኛን ሊያርድ ከትዕቢት ከጉራ፡፡

 

የታገተው ወፉ መብቱ ተጥሶ፣

ነጻነት የሚያዜም መልሶ መላልሶ፣

ትዕቢትን አራክሶ ፍትህ አወድሶ፣

ሸፍጠኛን አውግዞ ወንጀለኛን ከሶ፣

የታሰረበትን ገመዱን በጥሶ፣

ተስፈንጥሮ ሄዶ ከሰማይ ላይ ደርሶ፣

ይመለሳል መሬት በፍቅር ተላብሶ፡፡

 

ነጻው ወፍ ለመኖር ምቾት ይፈልጋል፣

የምድር ወገብ ነፋስ ሽው እንዲል ይመኛል፣

ተፈጥሮ በራሱ ትንግርት ይስራ ይላል፡፡

 

ጠፍጣፋዎች ነብሳት በምሽት ይቆዩ፣

ጠፍጣፋዎች ነብሳት በመስኩ ይታዩ፣

ማንም ሳይነካቸው በሳት ፍም ሳይጋዩ፡፡

 

እናም ይሰይማል ሰማይን አክብሮ፣

ሄዶ እንደሚያገኘው ጭቆናውን ሰብሮ፣

ለራሱ ለማድረግ በሮ ተዟዙሮ፡፡

 

ሆኖም ግን እስረኛው መከረኛው ወፍ፣

በህልም መቃብር ላይ የቆመው በቋፍ፣

በሌሊት ቅዠት ላይ ጥላው የሚቀስፍ፣

መች ይቀመጥና ነጻነት ሳያቅፍ፡፡

 

ክንፎቹ ተቆርጠው እግሮቹ ታስረዋል፣

እናም ለመዘመር ጉሮሮ ይከፍታል፣

ለህይወቱ ቤዛ ለነጻነት ሲባል፡፡

ታስሮ የሚገኘው ያ መከረኛው ወፍ፣

ቅስሙን ያደቀቀው ጭቆናውና ግፍ፣

ነጻነት ይዘምር በሰላም እንዲከንፍ፣

ባየር በሰማይ ላይ እንዲፏልል በክንፍ፡፡

 

ሆኖም ግን በማጎሪያው ጎጆ ውስጥ ያለው ወፍ የሚጮኸው፣ የሚያለቅሰው ለምንድን ነው? ድምጹን ከፍ አድርጎ ጆሮን በሚሰነጥቅ ዓይነት ቅላጼ የሚዘምረው ለምንድን ነው?

በማቆያ በጎጆ ውስጥ ተይዘው ያሉ ወፎች ለምን እንደሚዘምሩ አውቃለሁ፡፡

በማቆያ ጎጆ ውስጥ ያሉ ወፎች የሚጮሁት ሀገር ስለሌላቸው ነው፡፡ ማለትም መጠለያ ጎጆ ስላጡ ነው፡፡ ክልል፡፡

በማቆያ ጎጆ ውስጥ ተይዞ ያለ ወፍ የነገው ህይወቱ ስለተሰረቀበት ዛሬ ይጮሀል፡፡

በማቆያ ጎጆ ውስጥ ተይዞ ያለ ወፍ በመንገዶች ላይ ይጮሀል ምክንያቱም ጉዳት እየደረሰበት ነው፣ ስቃይ እየደረሰበት ነው፡፡

በማቆያ ጎጆ ውስጥ ተይዞ ያለ ወፍ ለፖሊስ የተኩስ መለማመጃ የተጋለጠ በመሆኑ ምክንያት ድምጹን ከፍ አድርጎ ይጮሀል፡፡

በማቆያ ጎጆ ውስጥ ተይዞ ያለ ወፍ መሬቱን እና መጠለያ ዛፎቹን ሲወስዱበት ለምን እንደሚበሳጭ አውቃለሁ፡፡

በማቆያ ጎጆ ውስጥ ተይዞ ያለ ወፍ ለአንድ ተጨማሪ ቀን ለመቆየት የማይፈልግ በመሆኑ ምክንያት ትዕግስት እንደሌለው አውቃለሁ፡፡

በማቆያ ጎጆ ውስጥ ተይዞ ያለ ወፍ ለምን የተስፋ መቁረጥ እና የተስፋ የለሽነት ስሜት እንደሚሰማው አውቃለሁ፡፡

በማቆያ ጎጆ ውስጥ ተይዞ ያለ ወፍ ለምን የነጻነት መዝሙሮችን መዘመር እንደማይችል አውቃለሁ፡፡

አውቃለሁ፡፡ አውቃለሁ በሚገባ!!!

በማቆያ ጎጆ ውስጥ ተይዞ ያለ ወፍ በማጎሪያው ጎጆ ውስጥ በመሆኑ እና ክንፎቹም በመቆረጣቸው ምክንያት መብረር እንደማይችል አውቃለሁ፡፡

በአሁኑ ጊዜ ግን በማቆያ ጎጆ ውስጥ ተይዞ ያለ ወፍ ለነጻነት ሲባል ማድረግ የሚችለው ብቸኛ አማራጭ መጮህ፣ ማልቀስ፣ አስፈሪ እና አስደሳች የሆነ ጩኸትን እና ድምጽን ከፍ አድርጎ በማሰማት የተለያዩ ቅላጼዎችን በማውጣት መዘመር ነው፡፡

በማቆያ ጎጆ ውስጥ ተይዞ ያለ ወፍ በከፍተኛ እንቅልፍ ውስጥ እንደነበረ ሰው በድንገት ከእንቅልፉ ለምን እንደሚነቃ አውቃለሁ፡፡

በጎጆ ውስጥ ተይዞ ያለ ወፍ ለምን እንደሚነሳ እና ተመልሶም እንደማይተኛ አውቃለሁ፡፡

ተነሳ! የጎጆው ወፍ! ተነሳ! ከተኛህበት ተነሳ!

ተቀፍድደህ ከተያዝክበት ጎጆህን በጣጥሰህ ውጣ እና ብረር፡፡

ተነሳ! ክንፎችህን ዘርጋ እና ሰማዩን እስክትነካ ድረስ ብረር፡፡

ተቀፍድደህ የተያዝክበትን ጎጆህን በጣጥሰህ ውጣ እና የነጻነትን ንጹህ አየር ተንፍስ፡፡

በነጻነት እንዳትበር የሚያደርግህ ከክንፎችህ በታች ምንም ነገር የለም፣ ነፋስ የለም፡፡

ለዚህም ነው ነጻ ሆነህ መብረር እንደምትችል በእራስህ ላይ መተማመን ያለብህ፡፡

አውሎ ነፋስ ቢኖርም በእራስህ ላይ ተማመን፡፡

ምንም እንኳ ጭጋግ፣ ዝናብ እና የበረዶ ዶፍ ቢኖርም በእራስህ ላይ ተማመን፡፡

በእራስህ ተማመን! የኃያሉ አምላክ የኃይል ጸጋ ከአንተ ጋር እንደሆነ እመን!

ተነስ፣ ተነስ እና በነጻነት ብረር፣ በነጻነት ብረር…ምክንያቱም ያ የአንተ መጻኢ ዕድል ነውና!

በነጻነት ተንፍስ፡፡ መሆን የምትችለውን ሁሉ ሁን፡፡ ነጻነት!

ከማቆያ ጎጆ የወጣህ ነጻ ሁን! እንደ ወፍ ነጻ ሁን! እንደ ነፋስ እና እንደ ባህር ነጻ ሁን! እንደ ማለዳ ጸሐይ ነጻ ሁን!

ተነስ! በማቆያ ጎጆ ውስጥ ያለኸው ወፍ ተነስ! ተነስ!

ተነስ እና የነጻነት አየር ተንፍስ!

Fly 3ተነስ እና ነጻነትህን አስከብር ምክንያቱም ያ የአንት መጻኢ ዕድል ነውና!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ጥር 3 ቀን 2008 ዓ.ም

 

 

 

Similar Posts