በካሊፎርኒያ ግዛት በሳንበርናርዲኖ የተጀመረው የሳምንቱ ፍቅር በጥላቻ ላይ ድልን ተቀዳጀ፣

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም    

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

ጥላቻ ይገድላል፣ ፍቅር ይፈውሳል!

Terror 7እ.ኤ.አ ታህሳስ 2/2015 ዕለት በካሊፎርኒያ ግዛት በሳንበርናርዲኖ ከተማ ታሪክ ውስጥ በአሰቃቂነቷ ስትታወስ ትኖራለች፡፡

የአሸባሪነት የእልቂት ጥፋት በከተማችን እና በሀገራችን ላይ በውድቅት ሌሊት እንደሚፈነዳው የመብረቅ ነጎድጓድ በማዥገምገም ላይ ይገኛል፡፡

እ.ኤ.አ መስከረም 11/2011 በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ምድር ላይ ከተፈጸመው የአሸባሪዎች እልቂት ወዲህ ይህ በሳንበርናርዲኖ ከተማ የተፈጸመው ዓለም አቀፋዊ የአሸባሪዎች ጥቃት በአስከፊነቱ የተመዘገበ ዕኩይ ምግባር ነበር፡፡

የ28 ዓመት እድሜ ያለው ሰይድ ፋሩክ እና የ27 ዓመት ዕድሜ ያላት ባለቤቱ ታሽፊን ማሊክ የውጊያ ልብስ ለብሰው የጦር መሳሪያ ታጥቀው የሀገሪቱ የጤና ሰራተኞች ተሰብስበው በነበረበት ቦታ በመግባት የጥይት ዝናብ አወረዱባቸው፡፡

አስራ አራት የማህበረሰባችን አባላት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ፡፡ ወደ ሁለት ደርዘን የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ቁስለኛ ሆነዋል፡፡ በእነዚህ ሁለት ግለሰቦች አማካይነት በማህበረሰባችን ላይ ጥሎት ያለፈው ስቃይ እና መከራ ሊለካ እና ሊታሰብ የሚችል ጉዳይ አይደለም፡፡

የፋሩክ የሚስቱ ወንድም የሆነው ፋርሃን ክሀን በዚህ አሰቃቂ ወንጀል የተሰማውን መሪር ሀዘን እንዲህ በማለት ገልጾታል፣ “እንደዚህ ያለው አሰቃቂ ድርጊት በማህበረሰቤ ውስጥ በመፈጸሙ እጅግ በጣም ጥልቅ የሆነ ሀዘን ተሰምቶኛል፣ አዝኛለሁ፣ ደንግጫለሁም…በቤተሰቦቼ ስም ሁላችንም በተፈጸመው ድርጊት በድን ሆነናል፣ ደንግጠናል፡፡“

በሎስ አንጀለስ ከተማ የሚገኘው የአሜሪካ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ሁሳም አይላውሽ ይህንን አረመኔያዊ እና አሰቃቂ የህሊና ቢሶች ዕኩይ ድርጊት በጽኑ አውግዘዋል፡፡ እንዲህ በማለትም አክለዋል፣ “በዚህ በተፈጸመው እልቂት ከአሜሪካውያን ጓዶቻችን ጋር በህብረት በመቆም ሀዘናችንን አንገልጻለን፡፡ አንደዚህ ያለ በሰው ልጆች ላይ እልቂትን የሚያስከትል ርዕዮት ዓለምን የሚከተሉትን እና የዚህ ዓይነት ሀሳብ በማቀንቀን ዕኩይ ተልዕኮ የሚያራምዱትን በጽናት በመቆም እንቃወማለን፡፡“

ፋሩክ እና ባለቤቱ በእኛ ማህበረሰብ ውስጥ ከእኛ ጋር አብረው ኖረዋል፡፡

ፋሩክ የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በእኛ ዩኒቨርስቲ ነው፡፡ በእኛ ግዛት ውስጥ ተቀጥሮ ሲሰራ ነበር፡፡ በነጻ የመናገር፣ በሰላማዊ መንገድ የመደራጀት እና በማህበረሰባችን ውስጥ ያለምንም ጣልቃ ገብነት ሀሳቡን በመግለጽ ዴሞክራሲያዊ መብቶቹን በመጠቀም ህይወትን በማጣጣም ይኖር ነበር፡፡

የእኛን የአሜሪካውያንን ህልሞች ከእርሱ እና ከባለቤቱ ጋር በጋራ ለማሳካት እንደምንችል ሀሳባችንን አጋርተናቸው ነበር፡፡

ሆኖም በሌላ በማንም ሳይሆን በእነርሱ ብቻ በሚታወቅ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ኢምክንያታዊ በሆነ መልኩ የአሸባሪነት፣ የጽንፈኝነት፣ የጀብደኝነት እና የኃይማኖት ጽንፈኝነት በቀልተኝነታቸውን የሌሊት ቅዠት ሊያካፍሉን መረጡ፡፡

በዚህ እልቂት ምክንያት ከደረሰብኝ ሀዘን ለመጽናናት እንድችል በማሰብ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ሁሉ ሀዘናችሁን ለገለጻችሉልኝ በዓለም ላይ ለምትገኙ ለሁሉም ጓደኞቼ፣ ደጋፊዎቼ እና የሳምንታዊ ትችት አንባቢዎቼ በሙሉ ልባዊ የሆነ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ የአሸባሪነት ቀንድ እንዴት አድርጎ ከፓሪስ ሳንበርናርዲኖ ከመቅጽበት መድረስ እንደቻለ ስናገር ሁላችሁም እንቆቅልሽ እና ታዕምራዊ ሁኔታ እንደሚሆንባችሁ እገምታለሁ፡፡

እራሴን በእራሴ እንዲህ የሚል ጥያቄ እጠይቃለሁ፡፡

ሳንበርናርዲኖ ለእንደዚህ ዓይነቱ አሰቃቂ የአሸባሪዎች ጥቃት ዒላማ ለመሆን የቻለችው እንዴት ነው? ይህንን ስል በየትም ቦታ በየትኛውም ከተማ ቢሆን ለማንኛውም የሽብር ጥቃት መዳረግ መቻል ነበረበት የሚል ሀሳብ ማቅረቤ አይደለም፡፡

ሳንበርናርዲኖ ከፍተኛ ጠቀሜታነት ያላት የዓለም አቀፍ አሸባሪዎች የጥቃት ዒላማ እንዴት ለመሆን እንደበቃች ለማሰብ አልችልም፡፡

ሳንበርናርዲኖ የሀገር አቀፍ ወይም ደግሞ የዓለም አቀፍ የፖለቲካ ማዕከል አይደለችም፡፡ የዴፕሎማሲ የትኩረት ቦታም አይደለችም፡፡ የንግድ ዓለሙ መናኸሪያ ከተማም አይደለችም፡፡ ግዙፍ እና ታላቅ ከተማም አይደለችም፡፡ የደህንነት እና የወታደራዊ ግዳጆች የነርቭ ማዕከልም አይደለችም፡፡ ሀብታም እና ልታይ ልታይ የምትል ከተማም አይደለችም፡፡

የሳንበርናርዲኖ ከተማ በአንድ ወቅት የእጅ ሙያ ያላቸው እና የመካከለኛ መደብ አባላትን ያካተተች ከተማ ነበረች፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ የደረሰው የምጣኔ ሀብት ቀውስ እና የመኖሪየ ቤት እጥረት ከተማይቱን ክፉኛ መትቷት ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 ከተማዋ ወደ 50 ሚሊዮን ዶላር ገደማ የሚሆን ግምት ያለው የነጮች ንብረት ኪሳራን አስተናግዳለች፡፡

የስድስት ወራት ህጻን ያላቸው ባል እና ሚስቶች በስብሰባ ላይ ያሉትን የጤና ሰራተኞችን እና በአካባቢው ያሉትን ሰዎች ሁሉ በጦር መሳሪያ ለመግደል ወስነው መሄዳቸው ለምን እንደሆነ ለእኔ ግልጽ አይደለም፡፡

አንድ ሰው እንደዚህ ዓይነቱን የጅምላ እልቂት የኃማኖት ጽንፈኝነት ብቻ ነው በማለት ሊገልጸው ይችላልን? እንደዚህ ዓይነቱ የጅምላ እልቂት ከጭፍን ግላዊ ጥላቻ የሚመነጭ ሊሆን ይችላልን?

እነዚህ ሁለት ጥንዶች የጥቃት ዒላማቸውን ያነጣጠሩት የሰውን ህይወት የመታደግ ተልዕኮ ባላቸው የጤና ባለሙያዎች ላይ ለመፈጸም የመረጡት በምን መክንያት እንደሆነ ላውቀው አልችልም፡፡

ሆኖም ግን በኃይማኖት ጽንፈኝነት እና በግል ጥላቻ በወንድ እና በሴት ልብ ውስጥ የተጸነሰውን ዕኩይ ምግባር ማን ነው ለማወቅ የሚችለው?

የዚህን ምክንያት ለማወቅ ጨለማውን የአሸባሪዎችን ልብ በጥልቅ ሊመረምር የሚችለው ማን ሊሆን ይችላል? በበቀል እና በጥላቻ የተሞሉ ዓይኖችን ሊገነዘብ የሚችለው ማን ሊሆን ይችላል? እነዚህን ህሊና የሌላቸውን ህሊና ቢስ ጽንፈኞች ልብ ምን እንደሆነ በትክክል ሊገነዘብ የሚችለው ማን ሊሆን ይችላል?

የእነዚህን ነበስ አልባ በድን አሸባሪዎች ባዶነት በትክክል ሊመረምር የሚችለው ማን ነው? የአሸባሪዎችን የነብስ በሽታ ለማከም እና ለማዳን የሚችለው ማን ሊሆን ይችላል?

ሆኖም ግን የብዙ ማህበረሰቦችን ህይወት ይታደጉ የነበሩትን እና እ.ኤ.አ ታህሳስ 2/2015 የሞቱትን እና የቆሰሉትን እነዚያን የጤና ባለሙያዎች አውቃቸዋለሁ፡፡

እያንዳንዳቸው የእኛን ማህበረሰቦች ጤንነት እና ደህንነት ለመጠበቅ ሲሉ በእያንዳንዷ ዕለት መከራ እና ስቃያቸውን ሲያዩ የነበሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ ለግዛቷ የጤና መምሪያ ይሰሩ የነበሩ የጤና ባለሙያዎች የወረርሽኝ በሽታ እና ሌሎችም በሽታዎች እንዳይስፋፉ ህክምና የመስጠት ኃላፊነትን የተሸከሙ ዜጎች ነበሩ፡፡ ህብረተሰቡን ከአካባቢይዊ ብክለት ለመከላከል በግንባር ቀደምትነት ተሰልፈው ሲታገሉ የነበሩ ጀግኖች ነበሩ፡፡ ጭንቀትን የሚያስወግዱ እና ቤተሰቦች ሁሉ ማገገም እንዲችሉ እርዳታ የሚያደርጉ ሰዎች ነበሩ፡፡ በግዛቱ ውስጥ ጤናማ ህይወትን መምራት እንዲቻል እና የጤና አገልግሎቶች ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ እንዲሆኑ ሀሳቦቻቸውን ሲያራምዱ እና ሲያበረታቱ የነበሩ ሰዎች ነበሩ፡፡

እ.ኤ.አ ታህሳስ 2/2015 በአሸባሪዎች ጥቃት ህይወታቸውን ያጡት ዜጎች በከተማው እና በሳንበርናርዲኖ ግዛት ውስጥ የምርጦች ሁሉ ምርጦች ነበሩ፡፡

እኔ በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርስቲ ለማስተማር ወደ ሳንበርናርዲኖ የመጣሁት ከ25 ዓመታት በፊት ነው፡፡

በከተማዋ፣ በግዛቷ እና በዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ ተፈጥሯዊ ውበት ወዲያውኑ ነበር የተማረኩት፡፡

ሳንበርናርዲኖ ከዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች ትልቁ ግዛት ነው፡፡ የሳንበርናዲኖ ልዩ የሆነው ብሄራዊ ደን ለሳምንት በካምፕ ውስጥ በመቆየት የእግር ጉዞ በማድረግ ለሚንሸራሸሩት፣ የስፖርት እንቅስቃሴዎችን ለሚያዘወትሩት እና ለሚጎበኙት በሚሊዮኖች የሚሆኑ ዜጎችን የመሳብ ኃይል ያለው የተፈጥሮ ደን ነው፡፡ የሞጃቭ ብሄራዊ ጥብቅ ደን አካባቢን በመቃኘት ከደኑ በላይ ከጠራው ሰማይ ላይ እየተንሳፈፉ እንደ መብረቅ በሚጮኹ ወርቃማ ጭልፊቶች እና አሞራዎች ከብርሀን በሚልቅ ፍጥነት ከወዲያ ወዲህ ሲከንፉ ማየት ስሜትን ይገዛል፡፡ የጆሹዋ ደን ብሄራዊ ፓርክ ከበርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች ሚስጥራዊ በሆነ መልኩ ስሜትን ለመግዛት የሚያስችል አስደናቂ የስነምድር ምህንድስና የሚታይበት ፓርክ ነው፡፡ ከዚህ ብዙም የማይርቀው የሙት ሸለቆ/Death valley ልናየው የምንችለው ብቻ ሳይሆን ልንዳስሰው የምንችለው በሬስ ትራክ ፕላያ አድማስ ላይ የሚልኪ ወይ ተፈጥሯዊ ውበት ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ1970 “ክርስቲ“ የሚባለው የእንግሊዝ ቡድን “ሳንበርናርዲኖ“ ለምን ቁጥር አንድ ሙዚቃ ብሎ እንደሰየመው ግንዛቤው አለኝ ብዬ አምናለሁ፡፡

ያ ሙዚቃ ለዓለም ውስጣዊ ሰላም ምርምር ለሚያድርግ እና ለሳንበርናርዲኖ ለአሁኑ እልቂቱ ምንም ዓይነት ምላሽ ያላስገኘውን ዘላለማዊ ጸሐይ ላገኘው ሰው ተብሎ የተዘመረ ሙዚቃ ነው፡፡ “ሳንበርናርዲኖ“ ከሚለው የሙዚቃ የግጥም ስንኞች መካከል ከአምስቱ ክፍሎች ሁለቱ በዚህ መልክ ከዚህ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡

እኔ ቆይቻለሁ በዚህ ታላቅ ዓለም፣

በውብ ከተማዎች ከፓሪስ እስከ ሮም፣

ከበርሊን ቶኪዮ ከኒዮርክ ስቶኮልም፣

ከዚህም በማለፍ ከሌላም ከሌላም፣

ብክንፍ ብዘዋወር ከዋልታ እስከ ዋልታም፣

ግን እንዲህ ያለውን ተመልክቼ አላውቅም፡፡

 

አንድ ቦታ ብቻ እኔ የማውቀው፣

ጸሐይ ማህለቋን ሁሌ እምጥለው፣

ተፈጥሮ ስሜቴን ቀልቤን የገዛው፣

የአእዋፉ ጩኸት ልቤን የበላው፣

በተፈጥሮ ውበት የተንጣለለው፣

ከእኔ እይታ ውጭ ማንም ያላየው፡፡

 

እናም ይኸ ቦታ በእጀ ይደሰሳል፣

ከአድማስ አድማስ ገጥሞ ኮርቶ ተኮፍሷል፣

በባህር ዳርቻ ተንጣሎ ይገኛል፣

የተፈጥሮን ቀሚስ አረንጓዴ ለብሷል፣

እዩኝ ተመልከቱኝ አትለፉኝ ይላል፡፡

 

እናም ይኸን ቦታ ማወቅ ከፈለግሁኝ፣

በእውኔ ገነትን ማየት ካስፈለገኝ፣

እርካታን በማግኘት ቀልቤን ለሚገዛኝ፣

ሳንበርዲኖ ብዬ መፈትለክ አለብኝ፡፡

 

ህጻን እንደነበርኩ በ16 ዓመት፣

ቁም ነገርን ገና ከምር ባላጤንኩት፣

አባቴ ሰጥቶኛል እንዲህ የሚል ትምህርት፡፡

 

በዚህች ዓለም ዙሪያ ብትኳትን ብትኳትን፣

በደቡብ በሰሜን ብትከንፍ ብትባዝን፣

በምስራቅ በምዕራብ ብትዞር ዓለምን፣

ባየር ላይ ብትበር በጀት አውሮፕላን፣

በባህር ብትቀዝፍ ብታቋርጥ ወንዝን፣

ምንም አታገኝም የሚሰጥ እርካታን፣

ለአዕምሮ ጤንነት የሚሰጥ ሰላምን፡፡

 

ሆኖም ግን ደስታን ለማግኘት ሀሴትን፣

በምድር ላይ እየኖርክ ለማየት ገነትን፣

ወደ አፈር ሳትገባ ሳትጨርስ እድሜህን፣

ሳንበርዲኖ ተጓዝ ሌሊት እና ቀኑን…

 

ሳይድ ባሩክ እና ታሽፊን ማሊክ ለአእምሯቸው ሰላም ከማያገኙበት አካባቢ፣ የእራሳቸው የሚሉት መሬት ለመፈለግ ባህሩን አቋርጠው ወደ ሳንበርናርዲኖ በመምጣት እንደዚህ ያለ ሰይጣናዊ ድርጊት በመፈጸማቸው ከመገርም እና ከማዘን በስተቀር ልረዳቸው የምችለው ነገር አይኖርም፡፡

እ.ኤ.አ ታህሳስ 2/2015 የሳንበርናርዲኖ ሰዎች የአእምሮ ሰላም ተቃውሶ አፈር ድሜ በልቷል፡፡

እ.ኤ.አ ታህሳስ 2/2015 ፓሪስን፣ ለንደንን፣ ሮምን፣ ናይሮቢን እና ሌሎችን በዓለም ውስጥ በሚገኙ በበርካታ ከተሞች ላይ ሲያንዣበብ የቆየው አሸባሪነት ሳንበርናርዲኖ ደርሷል፡፡

በሳንበርናርዲኖ ያለምንም ገደብ ለዘላለም ስታንጸባርቅ የነበረችው ጸሐይ በአሁኑ ጊዜ መሀለቋን በመሰብሰብ ወደ ድንኳኗ ውስጥ ገብታለች፡፡ እ.ኤ.አ ታህሳስ 2/2015 ከሰዓት በኋላ በሳንበርናርዲኖ ድቅድቅ ያለ ጨለማ ነበር፡፡

አፋቸውን ለጉመው አውዳሚ የጦር መሳሪያዎችን በታጠቁ የሰይጣን መልዕክተኞች ዕኩይ ምግባር አማካይነት በርካታ ንጹሀን ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በርካታ ህይወቶች ከመቅጽበት ለዘላለም ወደ በድንነት ተቀይረዋል፡፡

ሆኖም ግን በሳንበርናርዲኖ ለተፈጸመው የአሸባሪዎች ጥቃት ግለሰባዊ ታሪክ እንዳለው በዓለም ላይ ያሉ አንባቢዎቼ ሁሉ በውል እንዲገነዘቡት እፈልጋለሁ፡፡

ሰይድ ፋሩክ እኔ ከማስተምርበት ዩኒቨርስቲ ማለትም ከካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርስቲ ከሳንበርናርዲኖ እ.ኤ.አ በ2010 በጤና ሳይንስ ዲግሪ ተመረቀ፡፡

እንደዚሁም ሁሉ ከአንድ እህት ተቋም የተመረቀውን ጨምሮ ስድስቱም የሞት ጥቃት ሰለባው የሆኑት ንጹሀን ዜጎች እርሱ ከተመረቀበት የትምህርት ተቋም የተመረቁ ናቸው፡፡ ዝርዝሩን በሚከተሉት ተከታታይ አንቀጾች እንደሚከተለው እንመልከት፡

1ኛ) ሮበርት ሲ. አዳምስ እ.ኤ.አ በ2011 በጤና ሳይንስ የትምህርት መስክ ተመረቀ፡፡ ከዚያም የአካባቢ ጤና ተቆጣጣሪ በመሆን ሲሰራ ቆይቶ ነበር፡፡

2ኛ) ጁዋን ሲ. ኢስፒኖዛ እ.ኤ.አ በ2002 በስነህይወት የትምህርት መስክ በዲግሪ ተመረቀ፡፡ ከዚያም የአካባቢ ጤና ተቆጣጣሪ በመሆን ሲሰራ ቆይቶ ነበር፡፡

3ኛ) ሻኑን ኤች. ጆንሰን እ.ኤ.አ በ2004 በአካባቢ በጤና ሳይንስ የትምህርት መስክ በዲግሪ ተመረቀ፡፡ በቀጣይነትም የአካባቢ ጤና ተቆጣጣሪ በመሆን ሲሰራ ቆይቶ ነበር፡፡

4ኛ) ቬቴ ኤ. ቬላስኮ እ.ኤ.አ በ2013 በአካባቢ የጤና ሳይንስ የትምህርት መስክ በዲግሪ ተመረቀች፡፡ ከዚያም በአካባቢ ጤና ልዩ ባለሞያ ሆና ስትሰራ ቆይታለች፡፡

5ኛ) ማክል አር. ዌትዜል እ.ኤ.አ በ2001 በአካባቢ የስነሕይወት የትምህርት መስክ በዲግሪ ተመረቀ፡፡ ከዚያም የአካባቢ ጤና ልዩ ባለሞያ በመሆን ሲሰራ ቆይቶ ነበር፡፡

6ኛ) ቲን ጉዬን እህት ተቋም ከሆነው ከካል ስቴት ፉለርተን የመረቀች ሲሆን ስቃይን ለማምለጥ ስትል ገና በስምንት ዓመቷ ወደ ቬትናም ከእናቷ ጋር ተሰደደች፡፡ ከዚያም የምግብ ተቆጣጣሪ በመሆን ስትሰራ ቆይታ ነበር፡፡

ሁለት የጥቃት ሰለባዎች ደግሞ በትውልድ ሀገራቸው ካለው ሽብር እና ጭቆና ለማምለጥ ሰላምን በመፈለግ ባህርን አቋርጠው ወደ ሳንበርናርደዲኖ የመጡ ነበሩ፡፡

7ኛ) ይስኃቅ አማኒኦስ ገብረ ስላሴ በአሜሪካ አዲስ ህይወት ለመኖር ከምስራቅ አፍሪካ ከኤርትራ ሀገር ወደ ካሊፍርኒያ የመጣ ሰው ነበር፡፡ እዚህም ከመጣ በኋላ በአካባቢ ጤና ተቆጣጣሪነት በመስራት ላይ ቆይቶ ነበር፡፡

8ኛ) ቤኔታ ቤት ባዳል የኢራንን አብዮት ተከትሎ በተፈጠረው ትርምስ ስቃይን በመሸሽ ገና ህጻን እንደነበረች ተሰድዳ የመጣች ነበረች፡፡ እዚህ ከመጣች በኋላ በአካባቢ ጤና ተቆጣጣሪነት በመስራት ላይ ቆይታ ነበር፡፡

     ሌሎቹ በከተማዋ እና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ይኖሩ ነበር፡፡

9ኛ) ሲራ ክለይቦርን ወጣት ሴት ስትሆን የአካባቢ ጤና ጥበቃ ልዩ ባለሞያ ሆና በመስራት ላይ ቆይታለች፡፡

10ኛ) ሀሪ ቦውማን ወደዚህ ግዛት ከመምጣቱ በፊት በብሄራዊ ደህንነት እና በሽብርተኝነት ስራ ቁጥጥር ላይ ባለሞያ ሆኖ ሲሰራ ቆይቶ ነበር፡፡

11ኛ) አውሮራ ጎዶይ የቢሮ ረዳት ሰራተኛ ሆኖ ሲሰራ ቆይቶ ነበር፡፡

12ኛ) ላሪ ዲ. ካውፍማን የሽብር ጥቃት ወንጀሉ በተፈጸመበት አካባቢ ሻይ ቤት በመክፈት በንግድ ስራ በመሰማራት ቆይቶ ነበር፡፡

13ኛ)  ኖኮላስ ታላሲኖስ የጤና ተቆጣጣሪ በመሆን ሲሰራ ቆይቶ ነበር፡፡

14ኛ) ዳሚያን ሜይንስ የጤና ተቆጣጣሪ በመሆን ሲሰራ ቆይቶ ነበር፡፡

እንደዚሁም ሁሉ ሌሎች በርካታ ቁስለኞች ማለትም ጁሊ ስዋን ፔዝን፣ ጀኒፍር ሰቴቬንስን፣ ዴኒስ ፔራዛን፣ ኬቪን ኦርቲዝን፣ አኒስ ኮዶኮርን፣ ኒኮላስ ኮሁን፣ አማንዳ ጋስፓርድን እና ፓትሪክ ባካሪን ጨምሮ የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል፡፡

በሳንበርናርዲኖ የካል ስቴትን ዩኒቨርስቲን ከተቀላቀሉት ከአንድ ሺ በላይ የሚሆኑ የተማሪ ማህበረሰብ አባላት፣ የፋካሊቲ መምህራን እና ሰራተኞች እንዲሁም ሴት ተመራቂዎች የ14ቱን ንጹሀን ዜጎች እልቂት እና የሌሎችን የ22 የአካል ጉዳት ሰለባ የሆኑትን ዜጎች ስሜት የለሽ የሽብር ጥቃት ለማስታወስ የሻማ መብራት ስነስርዓት አካሂደዋል፡፡

የካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርስቲ ሳንበርናርዲኖ ፕሬዚዳንት ቶማስ ሞራልስ ጽኑ አቋምን በመያዝ ማህበረሰባችንን በሚያስፈራሩት ላይ የዩኒቨርስቲውን ቅጥር ግቢ ሀዘን፣ የኃይል ጥቃት፣ እምቢተኝነት እና የትብብር አንድነት ስሜት እንዲህ በማለት ተቆጣጥረውት ተስተውሏል፡

“እ.ኤ.አ ታህሳስ 2/2015 የተፈጸመው የአሸባሪዎች ጥቃት የካሊፎርኒያን ስቴትስ ዩኒቨርስቲ ሳንበርናርዲኖን ተማራዎች እና የአካባቢውን ማህበረሰብ ህይወት አጥፍቷል፡፡ ከተገደሉት 14 ሰዎች መካከል ጓደኞቻቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ትተው በኢንላንድ ሪጂናል ማዕከል የእኛ 5 ሴት ተመራቂዎች ህይወት ጠፍቷል“ ብለዋል ቶማስ.ዲ፡፡

የካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርስቲ ሳንበርናርዲኖ ፕሬዚዳንት ሞራልስ በመቀጠልም እንዲህ ብለዋል፣ “ከዚህም በተጨማሪ የሳንበርናርዲኖን ህዝብ ኃይል እና አይበገሬነት በሚገባ እገነዘባለሁ፡፡ ህይወታቸውን ላጡት ሀዘናችንን ስንገልጽ የምንፈራ እና የምንዳከም አይሆንም፡፡ ይህ ሰቆቃ ሁላችንንም ያስተሳሰረንን ገመድ የበለጠ እንዲጠብቅ ያደርገዋል፡፡“

የሳንበርናርዲኖ ፖሊስ ፈጣን እና ሙያዊ የሆነ ምላሽ ባይሰጥ ኖሮ እና በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ለተጎጂዎቹ ቅድሚያ በመስጠት ወደ ሕክምና ማዕከላት እንዲደርሱ ባይደረግ ኖሮ እና ጥቃቱን ያደረሱት አሸባሪዎች በፍጥነት እንዲለዩ እና ከዚህ የጥፋት እርምጃቸው ባይታገዱ ኖሮ አደጋው ከዚህም የከፋ ይሆን ነበር፡፡

የአሸባሪዎችን ጥቃት መልሶ በማጥቃት የሕግ አስፈጻሚውና እና የክልል እና የፌዴራል መንግስታት በተቀናጀ መልኩ ያሳዩት ጥረት ለብሄራዊ እና እንዲያውም ለዓለም አቀፍ አሸባሪዎችን በመቆጣጠሩ በኩል ያሳየውን መልካም ጥረት በአርአያነት የሚታይ ይሆናል፡፡ በዚህ ህይወት በማዳን ጥረቱ ላይ ርብርብ ያደረጉት ሁሉም አካላት እና ግለሰቦች እጅግ በጣም ሊመሰገኑ ይገባል፡፡

ፍቅር አካልን እና ነብስን ይፈውሳል!

ከዚህም በተጨማሪ እ.ኤ.አ ታህሳስ 2/2015 የዋለው ሳምንት በሳንበርናርዲኖ የፍቅር እና የፈውስ ጊዜ ነበር፡፡

በዓለም ላይ ለሚገኙት ለሁሉም አንባቢዎቼ እ.ኤ.አ ታህሳስ 2/2015 የሳንበርናርዲኖን ማህበረሰብ ልብ የሰበረ እንዳልሆነ ሊገነዘቡት እንደሚገባ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ እኛ ከሁሉም በላይ የተፈወስን ማህበረሰቦች ነን፡፡

እ.ኤ.አ ታህሳስ 2/2015 አጥልቶብን ሸፍኖን በነበረው ድቅድቅ ጨለማ ላይ የብርሀን ፍንጣቂ በውል ፈንጥቆ ታይቷል፡፡

በሳንበርናርዲኖ የተፈጸመው የሽብር ጥቃት የዓለምን የዜና ሽፋን ተቆጣጥሮት በነበረበት ጊዜ ትንሽ የተስፋ ጭላንጭል፣ ልግስና እና ጽኑ እምነት በማህበረሰባችን ውስጥ በድሆች እና በመጠለያ የለሽ ዜጎች እንደገና ፈንጥቆ ታይቷል፡፡

ታድ ወርቁ የተባለ የ29 ዓመት ኢትዮ-አሜሪካ ዜግነት ያለው ወጣት “ፍቅር ሁሉም ነገር ነው“ በማለት በሎማ ሊንዳ አካዳሚ ጂም የነጻ ሕክምና አገልግሎት በመስጠት ፍቅር ሁሉንም ነገር መሆኑን በተግባር አሳይቷል፡፡

ታድ የፓስፊክ ዩኒየን ኮሌጅ የቢዝነስ ምሩቅ የሆነው ሰው በተከታታይ በነርሲንግ ዲግሪውን ያገኘ ሲሆን በሎማ ሊንዳ የሕክምና ማዕከል ከሳንበርናርዲኖ ቀጥሎ ባለው በአንድ የአስቸኳይ ጊዜ ሕክምና መስጫ ክፍል ውስጥ ሆኖ የአስቸኳይ ጊዜ የሕክምና እርዳታ ሲሰጥ ነበር፡፡

በሚያስገርም ሁኔታ ታድ እ.ኤ.አ ታህሳስ 25/2015 በህክምና መስጫ ቢሮው ውስጥ ስራ የመስራት ዕቅድ አልነበረውም፡፡ ሆኖም ግን በአሸባሪዎች የተፈጸመውን የሽብር ጥቃት በሰማ ጊዜ ጥቂቶች የሽብር ጥቃቱ ዒላማ የሆኑ ወገኖች ወደ እርሱ የአስቸኳይ ጊዜ ሕክምና መስጫ እየተላኩ ሌሎቹ ከስራ ውጭ የሆኑ ጓደኞቹ እንደሚያደርጉት ሁሉ ለጉዳት ሰለባዎቹ አስፈላጊውን ሕክምና ሁሉ ሲያከናውን ነበር፡፡

ታድ በሳንበርናርዲኖ ለድሆች እና መጠለያ ለሌላቸው ዜጎች ከእንግሊዝ አድቬንቲስት ጥምረት ጋር አንድ ላይ በመሆን በሳምንት ሁለት ቀናት ነጻ የሕክምና አግልግሎት ይሰጣል፡፡

ታድ ፈቃደኛ የሆኑ የጥርስ ሕክምና ባለሞያዎችን፣ ሐኪሞችን፣ የጥርስ ንጽህና የጤና ባለሞያዎችን፣ የጥርስ ሕክምና ረዳቶችን፣ ነርሶችን፣ የምክር አገልግሎት ሰጭዎችን፣ የሰውነት ማሸት ባለሞያዎችን እና ሌሎችን የሕክምና ባለሞያችን እና የሕክምና ባለሞያ ያልሆኑትን ሰዎች በማስተባበር የእርሱን ለፍቅር ሁሉም ነገር ነው ለሚለው መርሆው ተግባራዊነት በሎማ ሊንዳ አካዳሚ ጂም የሁለት ቀናት ነጻ የሕክምና አገልግሎቶችን በመስጠት ቃልን ከተግባር ያዋኸደ እውነተኛ ዜጋ ነው፡፡

“ፍቅር ሁሉንም ነገር ነው” ክሊኒክ ጥርስ ማጽዳትን፣ መሙላትን፣ መንቀልን፣ የኤክስ ሬይ ምስል ማንሳትን እና እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችም ተጓዳኝ የጥርስ ሕክምና ዓይነቶች ይሰጣል፡፡ የጥርስ በሽተኞች በሳንበርናርዲኖ በሳክ ክሊኒክ የክትትል ስራ ይደረግላቸው ነበር፡፡

ነጻ የዓይን ሕክምና የዓይን ምርመራን እና የመድኃኒት ማዘዝን እንዲሁም ነጻ መነጽር እና ሌንስ ማዘዝን ጨምሮ የዓይን ጤንነት እና የሞራ ግርዶሽ ምርመራ ይደረግ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ታህሳስ 5 እና 6 ከሳንበርናርዲኖ ማህበረሰብ በጠቅላላው 817 በሽተኞች “በፍቅር ሁሉም ነገር ነው” ክሊኒክ ታይተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 381 የሚሆኑት የጥርስ ሕክምና፣ 300 ለሚሆኑት ደግሞ የዓይን ሕክምና እና 136 ለሚሆኑት የአጠቃላይ ሕክምና አገልግሎት ተደርጎላቸዋል፡፡

በ“ፍቅር ሁሉም ነገር ነው“ ክሊኒክ ውስጥ በመገኘት ሕክምና የሚደረግላቸውን ሰዎች እዚያ ሆኘ ለመመልከት በመቻሌ እና ቀኑን እዚያው ግቢ ውስጥ ማሳለፍ በመቻሌ ለእኔ ታላቅ ክብር ተሰምቶኛል፡፡ ይህ ክሊኒክ ባይሆን ኖር ከሌላ ከየትም ተቋም በመሄድ በነጻ ማግኘት የማይችሉትን ሕክምና ማየት እንዴት ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሕክምናው የተደረገላቸው በርካታ ሰዎች ደስ ተሰኝተው በብሩህ ፊት ታጅበው ሲወጡ እና በደስታ እርምጃ እየተጓዙ ሲወጡ ማየት ልብን በደስታ የሚሞላ ነገር ነው፡፡

ታድ እና የእርሱ ቡድን የእኛን ማህበረሰብ በፍቅር ለመፈወስ ለወራት ያህል ለበርካታ ጊዚያት መከራን ተቀብሏል፡፡

ታድ “የእኛ የሳንበርናርዲኖ ጎረቤቶች” መደበኛ የሕክምና ወጭውን ለመሸፈን የማይችሉ እጅግ በጣም ድሆች መሆናቸውን ያምናል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ኪራይ በመክፈል እና የዕለት ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ሲሉ የጥርስ ህመም ወይም ደግሞ የስኳር በሽታቸውን ወይም የልብ ህመማቸውን ሳይታከሙ ሲዞሩ በመዋል ምርጫ ይገደዳሉ፡፡

ገና በመጀመሪያ ጊዜ ታድን ባገኘሁት ጊዜ በሎማ ሊንዳ ዩኒቨርስቲ የነርሲንግ ፕሮግራም ለመጀመር ከሙዚቃ ኮንትራት ለምን እንዳፈገፈገ ጥያቄ አቅርቤለት ነበር፡፡

ታድ የእርሱን ሙዚቃ የሰውን ልጆች ፍላጎት ለማሟላት በጥቅም ላይ የማይውል ከሆነ የሰውን ልጆች ህይወት በመለወጥ ወዲያውኑ ለውጥ ወደሚያሳየው ወደ ነርሲንግ ሞያ ፕሮግራም መዛወሩ የተሻለ ስለሆነ ነው በማለት ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ታድ እንዲህ በማለት ነግሮኝ ነበር፣ “እምነቴን በጣም ተጨባጭነት ባለው ሁኔታ የሚገልጽልኝን እና በሰዎች ህይወት ላይ ለውጥ ሊያመጣ በሚችል ነገር ለመሰማራት እና ሌሎችም ሰዎች እንደዚሁ እንዲያደርጉ በማየት መኖር እፈልጋለሁ፡፡ ሊሆን የሚችለውን ቦታ በማከክ ላይ እንዳለን እምነት አለኝ“ በማለት ሀሳቡን አጠናክሯል፡፡

ሰዎችን በመርዳት እና እራስን በዝና እና በዕድል እራስን በማሰለፍ መካከል ካሉት ምርጫዎች ውስጥ ቴድ ለሰው ልጆች እርዳታ በመስጠት ላይ መሰለፍን እንደሚመርጥ እና የሳንበርናርዲኖን ማህበረሰብ ለመርዳት መምረጣቸውን ግልጽ አድርጓል፡፡

ለዚህም ነው ታድ እኔ የሚለውን ሙዚቃ ወደ ጎን በመተው እጅግ ልዩ በሆነ መልኩ መንገዱን ሌሎችን ሰዎች በመርዳት ዝንባሌ ላይ አድርጎ ሰዎችን በመርዳት እና ከማስመሰል ከተማነት በመውጣት እውነተኛ ወገናዊ እርዳታ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ግልጽ ያደረገው፡፡ ይህ ሁኔታ እራሱ ዝና እና መልካም ዕድል ለማግኘት ከሚደረግ ጥረት ይልቅ ለህዝብ ሲል እራሱን አሳልፎ መስጠቱን ግልጽ ያደርጋል፡፡ በጣም ጥልቅ የሆነ ስሜትን የያዘ ሙዚቃ ነው፡፡

ታድ እንዲህ በማለት ግልጽ ያደርጋል፣ “የእኔ ሙዚቃ ዋና ዓላማ ተስፋ መስጠት እንደሆነ አስባለሁ፡፡ በዚህች ዓለም ላይ በየጊዜው እየጨመሩ የሚሄዱ በርካታ ፍላጎቶች እንዳሉ ሊታሰብ ይገባል፡፡ የዚህችን ዓለም የተሰበረ ልብ ለመመለስ የእኔን ሙዚቃ እንደዚሁም ከእኔ ሙዚቃ የሚከተለውን ለመጠቀም እፈልጋለሁ፡፡ የእኔን ሙዚቃ በአንድ ወይም በሌላ ማንገድ የወንጌሉን ታሪክ እጽፋለሁ ምክንያቱም እየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ተስፋ ለመስጠት ሲል ባደረገው ነገር ላይ እምነት ስላለኝ ነው፡፡“

ቴድ እና የእርሱ አሜን ቡድን በሳንበርናርዲኖ ከምንም በላይ የምንፈልገውን ተስፋ እና እውነተኛ ፍቅር እና ፈውስ አምጥተዋል፡፡

ታድ እና የእርሱ አሜን ቡድን በሽብርተኝነት እና ለመናገር በሚዘገንን መልኩ ኃይልን በመጠቀም በድንገት ተበጥሶ የነበረውን ድርጊት በማጥፋት ለማህበረሰቡ ተስፋ እና ፈውስን አምጥተዋል፡፡

ታላቁን የሳንበርናርዲኖን ማህበረሰብ በማገልገል ላይ በሚገኘው በታድ ወርቁ እጅግ በጣም ኮርቸበታለሁ፡፡

በጥላቻ ምክንያት ሰዎችን የሚገድሉ ሰዎች አሉ፡፡ በፍቅር ምክንያት የተፈወሱ ሰዎች አሉ፡፡ ይህንን ጉዳይ እ.ኤ.አ ታህሳስ 2/2015 መጀመሪያ ሳምንት ላይ በግልጽ የታዬ መሆኑን ተመልክተናል፡፡

ጥቂቶች “በጣም ተጨባጭነት ባለው መንገድ የሚፈልጉትን ውጤት ሊያመጣ በሚችለው ጠቃሚ ነገር ላይ እምነት በማድረግ እና ሌሎችም ተመሳሳይ ስራ እንዲሰሩ“ ይመርጣሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ መግደል እና አካለ ጎደሎ ማድረግን ይመርጣሉ፡፡

እ.ኤ.አ ታህሳስ 2 የመጀመሪያ ሳምንት ላይ በሁለት የትዳር አጋሮች በተፈጠረው እልቂት ላይ ትኩረት ሰጥቶ የመዘገቡን ያህል ለሳንበርናርዲኖ ለሚኖሩ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ድሆች እና መጠለያ ለሌላቸው የማህበረሰብ አባላት ትርፍ ጊዚያቸውን ሳይቀር ነጻ ሕክምና በመስጠት  ከፍተኛ የሆነ አገልግሎት ሲሰጡ ለነበሩት በደርዘኖች ለሚቆጠሩ ዶክተሮች፣ ነርሶች እና ሌሎች የሕክምና ባለሞያዎች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ምስጋና ሊደረግላቸው ይገባል፡፡

መጥፎ ዜናዎች እና ውሸት በብርሀን ፍጥነት ይጓዛሉ ሆኖም ግን መልካም ዜናዎች እና እውነት እንደ ባቡር ሁልጊዜ ይዘገያሉ፡፡

እ.ኤ.አ በታህሳስ ወር 2015 መጀመሪያ ሳምንት በሳንበርናርዲኖ በመልካም እና በመጥፎ ነገሮች  እንዲሁም በፍቅር እና በጥላቻ መካከል የነበሩትን ተቃርኖዎች በተጨባጭ በማየታችን ምስክርነታችንን መስጠት እንችላለን፡፡ መልካም ነገር እና ፍቅር ሰይጣናዊ ድርጊትን እና ጥላቻን ድል ያደርጋሉ እላለሁ፡፡

በፍቅር እና በጥላቻ እንዲሁም በመልካም እና በሰይጣናዊ ድርጊቶች መካከል ያለው እንደዚህ ባለው በአፈጠጠ እና ግለሰባዊ በሆነ ስግብግብነት ሊፈታ ይችላል በሚል ምስክርነት ለመስጠት በፍጹም አልጠብቅም፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከምንም ጥርጣሬ በላይ በጥላቻ እና በፍቅር መካከል ባለው ትግል ውስጥ ፍቅር ሁልጊዜ በጥላቻ ላይ ድልን እንደሚቀዳጅ አምኛለሁ፡፡

ዶ/ር ማርቲን ሉተር እንዲህ ብለዋል፣ “ጨለማን ጨለማ አያስወግደውም፡፡ ይህንን ማድረግ የሚችለው ብርሀን ብቻ ነው፡፡ ጥላቻን በጥላቻ ማስወገድ አይቻልም፡፡ ይህንን ማድረግ የሚችለው ፍቅር ብቻ ነው፡፡“

በልባችን ውስጥ እየተስፋፋ ያለውን የጥላቻን ጨለማ በፍቅር ብርሀን ማስወገድ እንደምንችል እርግጠኛ ነኝ፡፡ እ.ኤ.አ ታህሳስ 2/2015 በሳንበርናርዲኖ ከተማ በአሸባሪዎች ከተፈጸመው ጥቃት አሳዛኝነት ሆኖም ግን ለመልካም ነገር ቀስቃሽነት የተማርኩት ነገር ቢኖር ይኸ ነው፡፡

መተኪያ የሌላትን ህይወታቸውን ያጡት 14 ንጹሀን ዜጎች እና ከሁለት ደርዘን በላይ የሚሆኑ የአካል ጉዳት የጥቃት ሰለባዎች ሁል ጊዜ ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡ የሚታወሱት ለተፈጸሙት ወንጀሎች ሳይሆን የማህበረሰባቸውን ህይወት፣ በመለወጥ እና ከበሽታ እና ከሌሎች ጉዳት አምጭ ነገሮች ሁሉ የተካለከሉላቸው እና ጥቅም እየሰጡ ላሉት ጅገኖች ነው፡፡

የጥላቻን አስከፊነት በማስወገድ ለወገኖቻችን እና በሰብአዊነት ፍቅር በመተካት ህጋዊነትን በመተግበር የሚደረገውን ግለሰባዊ ተነሳሽነት፣ ፍትሀዊነት እና እኩልነትን በሁሉም የህብረተሰብ ክፎሎች ዘንድ ማስፈን የጠበቅብናል፡፡

ብዙ ሰዎችን በግፍ የገደሉት ጥንድ ባል እና ሚስት በማህበረሰባችን ውስጥ ጥልቅ የሆነ ቁስል እና ለመናገር የሚዘገንን ነገርን ፈጽመዋል፡፡ ለመግለጽ የሚያስቸግር ሀዘን እንዲደርስብን እና የልብ ስብራት እና ጸጸት እንዲያድርብን አድርገዋል፡፡

ሆኖም ግን ይህንን ሁሉ እኩይ ድርጊት ፈጽመው ሊያሸንፉ ይችላሉን? የእነዚህ የስብዕና ኪሳራ የደረሰባቸው ዕኩይ ምግባር ፈጻሚዎች ፈሪ እና በጥላቻ የተሞሉ ዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጭዎቻቸው እና መሪዎቻቸው ድልን ሊቀዳጁ ይችላሉን?

አሸባሪዎች ሊያሸንፉ የሚችሉት በአንድ ሁኔታ ብቻ ነው–እኛንም እንደ እነርሱ በጥላቻ የተሞላን እንድንሆን ያስቻሉን ጊዜ ነው፡፡

በሳንበርናርዲኖ ውስጥ ፍቅር ጥላቻን አሸንፏል ወደፊትም ድልን ይቀዳጃል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ጸሐይ ያለምን ማቋረጥ ታበራለች፣ እናም በአንድ ወቅት ተሰርቆ የነበረውን ሰላማችንን በሳንበርናርዲኖ በቤታችን ውስጥ መልሰን እናገኘዋለን፡፡

በዓለም ላይ ያሉ ታላላቅ እምነቶች ሁሉ ሰዎች መልካም ነገርን እንዲያደርጉ ማነሳሳት ይኖርባቸዋል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ደግ ሰዎች እና በፍቅር የተሞላን እንድንሆን ማስተማር ይኖርባቸዋል፡፡ ሆኖም ግን ከደግ እምነት መራቅ ቀላል እና ሰይጣናዊ ድርጊቶችን መፈጸም አንድንችል ያደርጉናል፡፡ ቢሆንም ግን እንደዚህ ያለ መጥፎ ነገርን መስራት የማንኛውም እምነት የጠቅላይነት ባህሪ አይደለም፡፡

በእምነት ስም ሰይጣናዊ ድርጊት በሚፈጸምበት ጊዜ ጥፋቱ ያለው በእምነቱ በእራሱ ላይ አይደለም፡፡ ጥፋቱ ያለው በእራሳችን፣ በልባችን እና በአእምሯችን ውስጥ ነው፡፡ ሁላችንም የእምነታችንን ትምህርት በሰይጣናዊ መልኩ ለማስተማር ወይም በመልካም ጎኑ ደግ ነገርን ለመተግበር የሚያስችል ምርጫ አለን፡፡

ስለ ሽብርተኝነት የተሻለው እና በጣም ውጤታማ የሆነው መሳሪያ በቀላሉ ጥላቻን መጥላት እና እምቢ አሻፈረኝ ማለት መቻል ነው፡፡

ከጭፍን ጥላቻ ውጭ ምንም ዓይነት አሸባሪነት ሊኖር አይችልም፡፡ ለዚህም ነው ዓይኖቻችንን ቦግ አድርገን ከፍተን የኃይል እርምጃን ለማጥፋት እና ሁልጊዜ ፍቅርን በልባችን ውስጥ በማኖር ሰብአዊነትን በማሳየት የጥላቻን መርዝ በመቀፍቀፍ የሚያሰራጩትን የዕኩይ ምግባር አራማጆች ሁልጊዜ መቆጣጠር ያለብን፡፡

ጋንዲ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ ፍቅር እና ኃይል አልባ እንቅስቃሴዎች “በሰው ልጆች የማድረግ አቅም ላይ ታላቅ ኃይሎች ናቸው፡፡ ቅን ልቦና ከሚጎድላቸው እና ከኃይለኞች መሳሪያዎች ሁሉ የበለጡ ኃይለኞች ናቸው፡፡“

ጸሐይ በሳንበርናርዲኖ ላይ ያለምንም ማቋረጥ ለዘላለም ስታበራ ትኖራለች፣ እናም የአሸባሪነት ጨለማ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንደ ጥላሞት በኖ ይጠፋል፡፡

ስለሆነም ስለሳንበርናርዲኖ አብዛኞቻችን የእናኛ ብለን የምንጠራው፣ እኛ የምናውቀው ቦታ እና ጸሐይ ለዘላለም የምታበራበት ሌላ የተደረሰ ሙዚቃ ይኖራል፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!         

ህዳር 5 ቀን 2008 ዓ.ም