የኢትዮጵያውያን የጸደይ አብዮት በበጋው ወቅት መጀመሩ ነውን? 

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም  

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ 

TTPLFየአረቡ ዓለም የጸደይ አብዮት .. ታህሳስ 18/2010 የቱኒስያን አብ በማቀጣጠል ይጀምራል ብሎ የገመተ ማንም ሰው አልነበረም፡፡ 

መሐመድ ቡአዚዚ የሚባል በመንገድ ላይ እየተንቀሳቀሰ ለዕለት ኑሮው መደጎሚያ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት ጥቃቅን ሸቀጦችን የሚሸጥ ወጣት በከተማው ማዘጋጃ ቤት እና በፖሊሶች ኃላፊነት የጎደለው አሰራር መሰረት በዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን የማሸማቀቅ፣ ከሕግ አግባብ ውጭ ስልጣንን የመጠቀም እና የማዋረድ ዕኩይ ድርጊቶችን በመቃወም በእራሱ ላይ እሳት በመለኮስ እራሱን በማቀጣጠል በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪካ ሀገሮች ላይ የአብዮት ማዕበልን ያስከትላል ብሎ የገመተ ማንም ሰው አልነበረም፡፡ 

ለህዝቦች ነጻነት ሲል እራሱን በእሳት ያቀጣጠለው ዜጋ ዚን ኤል አቢዲን ቤን አሊን በቱኒስያ፣ ሆስኒ ሙባረክን በግብጽ፣ ሙአመር ጋዳፊን በሊቢያ፣ አሊ ሳለህን በየመን እና ሌሎችንም በእሳት ተቃጥለው ዶግ አመድ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ 

ሶቭየት ህብረት በብርሀን ፍጥነት እና ከመቅጽበት ፍርክስክሷ ይወጣል ብሎ የገመተ ማንም አልነበረም፡፡ .. ታህሳስ 25/1991 ሚካኤል ጎርባቾቭ እራሳቸውን ከፕሬዚዳንትነት ያገለሉ መሆናቸውን በማወጅ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የገና ስጦታ አድርገው አቅርበዋል፡፡ ጎርባቾቭ ለሰባት አስርት ዓመታት ያህል በሶቭየት ህብረት ውስጥ ነግሶ የቆየውን የኮሙኒስት አገዛዝ ገመድ ውጤታማ በሆነ መልኩ ስበው በጥሰው በመጣል ለዓለም ህዝብ አስደናቂነታቸውን በተግባር አስመስክረዋል፡፡ 

ትላንት ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅትበኢትዮጵያ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ እንደገና ሌላ ደም አፋሳሽ የኃይል ጥቃትበሚል ርዕስ በድረ ገጹ ላይ በመልቀቅ ህዝብ እንዲያውቀው አድርጓል፡፡ 

ሂዩማን ራይትስ ዎች እንዲህ የሚል ዘገባ አቅርቧል፣የተማሪዎች ተቃውሞ በኦሮሚያ ክልል በሁሉም አካባቢዎች ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ በመሰራጨት ላይ ይገኛልየማህበራዊ ድረ ገጾች በደም በተነከሩ እና በተጨማለቁ ሰላማዊ ሰዎች ፍቶግራፎች ተሞልተዋል፡፡ በበርካታ ቦታዎች ላይ በርካታ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ቁስለኞች እና በቁጥጥር ስር የዋሉ በርካታ ሰዎች የሚገኙ መሆኑን ታማዕኒነት ያላቸው ምንጮች ዘግበዋል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ የአካባቢ ፖሊሶች እስከ አሁን ድረስ ሶስት ተማሪዎች መሞታቸውን ይፋ አድርጓል፡፡ 

ሂዩማን ራይትስ ዎች በአሁኑ ጊዜ በተማሪዎች  እየተካሄዱ ላሉት ሰላማዊ ሰልፎች አንቀሳቃሽ ምክንያቶች ናቸው ያላቸውን ጉዳዮች እንደሚከተለው አቅርቧቸዋል፡ 

ሰላማዊ ሰልፍ አድራጊዎች እውነትነት ያለው በሚመስል መልኩ እና ሆኖም ግን ከጥርጣሬ ውስጥ በሚጥል መልኩ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ወሰን ከድንበሩ አልፎ ወደ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ እየተስፋፋ በመሆኑ እና የኦሮሞን አርሶ አደሮች ከመሬታቸው የሚያፈናቅል መሆኑን ከመፍራት አንጻር ነው፡፡ በርካታ ኦሮሞዎች በኢትዮጵያ ላይ ስልጣን በያዙ ተከታታይ ነገስታት የማግለል አድልኦ እንደተፈጸመባቸው አድርገው ይሰማቸዋል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ በኢትዮጵያ ተከታታይ መንግስታት ሁልጊዜ በመንግስት ፖሊሲዎች ላይ ተሳትፎ ማድረግ እንደማይችሉ እና ድምጽ እንዳይኖራቸው አድርገዋል የሚል እምነት አላቸው፡፡ 

በኢትዮጵያ በስልጣን ወንበር ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ የሚገኘው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ህወሀት) እንደዚህ ያለ መጥፎ ዜናን የሚያሰራጩ ዜናዎችን ወዲያውኑ ማጥፋት ተቃውሞዎችን ጸጥ ማድረግ በሚለው ስልታቸው ላይ ሁልጊዜ ትክክል እና ውጤታማ እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ፡፡ ሆኖም ግን ዜጎች በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞዎቻቸውን በሰላማዊ ሰልፍ መግለጽ እንዳይችሉ ማስፈራራት እና ማሸማቀቅ ማለት ነገሮችን ከማወሳሰብ ባለፈ መልኩ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ወገኖች በተደጋጋሚ ለአካባቢያቸው ማህበረሰቦች ሲሉ ወደ አደባባይ በመውጣት የሚፈጽሙት እና የማያቋርጥ ትግል ስለሆነ በአንድ ወቅት እውነታው ቁልጭ ብሎ ሊወጣ ይችላል፡፡ 

ጥያቄው እውነታው ፍንትው ብሎ የሚወጣው መቼ ነው የሚለው ብቻ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ጥያቄ ሆኖ የሚቀርበው ህወሀት እውነታን መያዝ ይችላል ወይ? የሚለው ነው፡፡ 

በእርግጠኝነት እውነታው ምንድን ነው? 

እውነታው ሁሉም ሊመልሰው በሚችልበት መልኩ እንዲህ በሚሉ ጥያቄዎች ዓይነት ሊቀርብ ይችላል፡ 

1) ለመሆኑ ህወሀት 100 ሚሊዮን በላይ ቁጥር ያለውን ህዝብ የመሬት ላይ ባሮች በማድረግ እንደ ሰም አቅልጦ እንደ ብረት ቀጥቅጦ የሚገዛው እስከመቼ ድረስ ነው? 

2) ለመሆኑ ህወሀት እራሳቸው ጌታ እና እያንዳንዱ ዜጋ ደግሞ ገባር በመሆን የኢትዮጵያን ህዝብ የመሬት ማሳ ላይ ጢሰኛ ባሮች አድርገው የሚቆዩት እስከምን ያህል ጊዜ ነው? 

3) ለመሆኑ ህወሀት አርሶ አደሮችን ከእራሳቸው መሬት ላይ በማፈናቀል በድህነት አረንቋ ማዕበል ውስጥ እየዘፈቁ በችጋር ሲያሰቃዩአቸው የሚኖሩት እስከ መቼ ድረስ ነው? 

4) ለመሆኑ ህወሀት የመኖሪያ ቤት ያላቸውን ዜጎች ከመኖሪያ ቤታቸው እያፈናቀሉ፣ የንግድ ስራ ባለቤቶችን ከንግድ ስራዎቻቸው በግፍ እየነቀሉ እና እያባረሩ በእራሳቸው፣ በደጋፊዎቻቸው እየተኩ እና የተቀደሱትን የእምነት ማደሪያ የሆኑትን ቤተክርስቲያኖችን እና መስጊዶችን እያረከሱ እና መሬቶቻቸውን እየነጠቁ የእነርሱን የማይሞላ ኪሳቸውን በገንዘብ ሲያጭቁ የሚኖሩት እስከ መቸ ድረስ ነው? 

5) ለመሆኑ ህወሀት ከአያት ቅድመ አያቶቻቸው ጀምሮ የኢትዮጵያውያን የነበረውን በርካታ መጠን ያለውን መሬት እየነጠቁ እና እየዘረፉ ለቻይኖች፣ ለህንዶች፣ ለሳውዲዎች፣ ለቱርኮች እና ለሌሎችም የጥቅም ተጋሪዎቻቸው በቁርጥራጭ ሳንቲም እየቸበቸቡ ኪሳቸውን ሲሞሉ የሚኖሩት እስከ መቼ ድረስ ነው? 

6) ለመሆኑ ህወሀት ዜጎች በሰላማዊ መንገድ ህገመንግስታዊ መብታቸውን በመጠቀም ተቃውሟቸውን በሚገልጹበት ጊዜ በጥይት እየተደበደቡ የሚገደሉበት ጊዜ የሚዘልው እስከ መቼ ድረስ ነው? 

7) ለመሆኑ ህወሀት 100 ሚሊዮኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ድምጽ አፍኖ ጸጥ ረጭ በማድረግ በድንቁርና አገዛዙ የሚቀጥልበት እስከ መቼ ድረስ ነው? 

8) ለመሆኑ ህወሀት 100 ሚሊዮን ህዝቦችን አንገት እረግጦ የያዘውን ጫማውን ዘለቄታዊ እንዲሆን በማድረግ ቀጥቅጦ የሚገዛው እስከ መቼ ድረስ ነው? 

እኮ እስከ መቼ? 

ሩቅ አይሆንም እላለሁ! 

ሩቅ አይሆንም! 

አሁን .. ታህሳስ 2015 ላይ ሆኘ ህወሀት በኢትዮጵያ ውስጥ መቼ እንደሚወድቅ ለመተንበይ አልችልም፡፡ 

ሆኖም ግን የውድቀት የእጅ ጽሁፉ በግድግዳው ላይ ነው፡፡ 

የዘህወሀት አድራጊ እና ፈጣሪ ዘዋሪ የነበረው ከስልጣን ኮርቻው ላይ .. ነሐሴ (?) ተሽቀንጥሮ ለዘላለሙ ይጠፋል ብሎ ያሰበ ማንም አልነበረም፡፡ 

አሁንም በስልጣን ኮርቻ ዙፋኑ ላይ ተጣብቆ የሚገኘው ህወሀት ይወድቃል፡፡ ብን ብሎም ይጠፋል፡፡ 

በአሁኑ ጊዜ መቅረብ ያለበት ጥያቄ ህወሀት ይወድቃል ወይ የሚለው ሳይሆን መቼ ነው የሚወድቀው የሚለው ነው፡፡ 

ይኸ አስደማሚ እና አሳሳቢ የሆነው የዘህወሀት ረዥሙ የጨለማ ጉዞ የአገዛዝ ጥቄያ በጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን እየተብላላ እና እየተሰለቀ ቆይቶ ተገቢውን ምላሽ የሚያገኘው መቼ ነው? ይህንን ጉዳይ አንድን ህጻን በዛፍ ጫፍ ላይ በተሰራለት የመኝታ አልጋ ላይ መተኛት እንዲችል እንድናባብለው ከሚደረግ የዋህ ድርጊት ጋር በማመሳሰል እስቲ በዚህ የግጥም ስንኝ እንቃኘው፡፡ 

ህጻኑን አባብለው ከዛፍ ጫፍ ይተኛ፣

በተሰራው አልጋ ለሷም ሳይሆን ለኛ፣

መጠበቅ አትችልም ከነፋስ ቀበኛ፣

ከማት ልታድነው ከኃይል ሞገደኛ፡፡

 

ነፋስ በሰዓቱ በነፈሰ ጊዜ፣

ቢነቃም ባይነቃም ከያዘው አባዜ፣

ወድቆ መንኮታኮት በደረሰ ጊዜ፣

ሁሉም መልክ ይይዛል የልጁ ኑዛዜ፡፡

 

የዛፉ ቅርንጫፍ ዘንበል ያለ እንደሆን፣

የህጻን መኝታው እንዳይሆን እንዳይሆን፣

ከመሬት ተላትሞ አፈር ትቢያ ሊሆን፣

ከማይቀረው ዓለም ምንም ጊዜ ቢሆን፣

ህጻን ተሸክሞ ያያታል ሲኦልን፡፡

 

አይ የህጻኑ አልጋ በዛፍ ላይ ያለኸው፣

ይህንን ሞኘ ህጻን አታለህ የያዝኸው፣

ምቹ በማስመሰል እንዲተኛ አርገኸው፣

 

ትንሽ እንደተኛ እውነት አልጋ መስሎት፣

ከመቅጽበት ወድቆ ከዛፉ ስር አለት፣

ሳይበቃ ቀረ አሉ ለኑዛዜ ስርየት፡፡

 

አወይ በሬ ሞኙ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ፣

እልም ካለው ገደል ወድቀህ ቀረኽ ወይ፣

የሚባለው ተርት ይህ አይደለም ወይ? 

የህዝቡን ደስታ ያራቀ፣ ከፍተኛ የሆነ ቁጡነት እና ብስጭትን የተላበሰ ህዝባዊ ማዕበል በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ እየነፈሰ ነው፡፡ 

ይህንን ህዝባዊ ማዕበል በመጋፈጥ የዘህወሀት ዛፍ ታላቁ ቅርንጫፍ መቋቋም አቅቶት ተቆርጦ የሚወድቀው መቼ ነው? 

አሁን ይህ ነው ለማለት አልችልም፡፡ ሆኖም ግን ቅርንጫፉ ተገንድሶ የመውደቂያ ጊዜው እየደረሰ ነው ለማለት እችላለሁ፡፡ 

ታላቁ ቅርንጫፍ ተገንድሶ ሲወድቅ ምን ይከተላል የሚለውን ጥያቄ መመለስ ቀላል ነገር ነው! 

የዘህወሀት ታላቁ ቅርንጫፍ ተዘንጥሎ ሲወድቅ የሙስና አገዛዝ ከነጉግ ማንጉጉ ተንኮታኩቶ ይወድቃል፣ ሰይጣናዊው አገዛዝ እና አልጋውም ሁሉም ነገር ተንኮታኩቶ ወድቆ አፈር ድሜ ይበላል፡፡

.. ታህሳስ 2015 ነገሮች ሁሉ ሲታዩ ሚስጥራዊ የሆነ ብሩህ ቁስ አካል በሰማይ ጨለማውን ሰንጥቆ የሚሄድ መስሎ ይታያል፡፡ ምልክቱን ማየት ቀላል ነገር ነው፣ ሆኖም ግን ሁኔታውን ለማወቅ እና ግንዛቤ ለመውሰድ በጣም ከባድ ነገር ነው፡፡ 

ባለፈው ሳምንት የዘህወሀት የኃይል እርምጃ እና የቁጣ መንስኤ የሆኑት እና የሚይዝ የሚጨብጠውን ያሳጣው አመጹን የቀሰቀሱት የተማሪዎች ጉዳይ ብቻ አልነበረም፡፡ 

በአንድ በሀገሪቱ ሰሜናዊ ከፍል በአንድ እስር ቤት ላይ በተነሳው የእሳት ቃጠሎ ከአደጋው ለማምለጥ በሚንቀሳቀሱ የህግ እስረኞች ላይ የዘህወሀት ታማኝ የሆኑ ፖሊሶች ተኩስ በመክፈት ግድያዎችን እንደፈጸሙ የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ይፋ አድርጓል፡፡ (የቪዲዮ ምስሉን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡) 

ይኸ ዕኩይ የአረመኔዎች ድርጊት .. ህዳር 2/2005 በቃሊቲ እስር ቤት ግቢ ውስጥ አሁን በህይወት በሌለው በአምባገነኑ በመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ ታጣቂዎች ተኩስ በመከፍት በርካታ እስረኞች እንዲሞቱ እና ብርካታዎቹ ደግሞ ቁስለኛ እንዲሆኑ የተደረገበትን ዘግናኝ ክስተት አስታወሰኝ፡፡ (እልቂቱ የተፈጸመባቸውን እስረኞች ስም ዝርዝር ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡) 

.. ህዳር 1983 የዩኤስ አሜሪካ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ኸርበርት . ሜየር የዩኤስኤስአርን/USSR መንኮታኮት ዋና ዋና ምክንያቶችን አስቀድመው በማወቅ ያቀረቡት ምልከታ .. ታህሳስ 2015 እየተከሰተ ካለው እውነታ ጋር ልዩ የሆነ መስተጋብር እና ጠቀሜታ አለው የሚል እምነት አለኝ፡፡ 

ሜየር ሁሉም ነገር በራሽያ የቁጥጥር አስተዳደር ምክንያት አንድም ብሄራዊ የሆነ ድርጅት ደስ ተሰኝቶ በማይኖርበት ሁኔታ ዩኤስኤስአር ፍጹም በሆነ መልኩ ተንኮታኩታ ትወድቃለች የሚል ጽሁፍ በማዘጋጀት የክርክር ጭብጣቸውን አቅርበው ነበር፡፡ 

21ኛው ክፍለ ዘመን ተስማሚ የሆነ የምጣኔ ሀብት እና የስነ ተዋልዶ ሁኔታዎች በሌሉበት እና በማይኖሩበት መንገድ የዓለም የመጨረሻዋ ግዛት የሆነችው ሀገር ህልውና ሊኖራት እንደማይችል አረጋግጠዋል፡፡ 

ሜየር እንዲህ በማለት አውጀው ነበር፣የሶቭየት የምጣኔ ሀብት ወደ አደገኛ የቀውስ ቅርቃር ውስጥ ገብቷል፡፡ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ብለው ነበር፣የሶቭየት ዩኒየን የስነ ተዋልዶ ቅዠት ነው፡፡ 

ሜየር እንዲህ የሚል የማጠቃለያ ሀሳብ ሰጥተው ነበር፣የሶቭየት አመራር አስፈላጊ የሆኑትን ለውጦች ለማምጣት ወይም ደግሞ እነዚህን ሁኔታዎች ለመመለስ የሚያስችል ወይም መፍትሄ በመስጠት ከነገሮች ጋር አብሮ ለመሄድ የሚያስችል ድርጊት ሊያከናውን አይችልም፡፡ 

.. ታህሳስ 2015 እኔም እንደዚሁ በኢትዮጵያ ላይ ተመሳሳይ የሆነ የክርክር ጭብጤን አቀርባለሁ፡፡ 

ኢትዮጵያ በፖለቲካ ቀውስ ቅርቃር ውስጥ ገብታለች፣ 

ኢትዮጵያ በዘህወሀት የአገዛዝ ስርዓት ውስጥ እንደ ሀገር የመቀጠሏ ሁኔታ ፍጹም በሆነ መልኩ ወድቆ ይገኛል፡፡ 

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ህወሀት በብችኝነት ህዝቡን በጎሳ ፌዴራሊዝም ስርዓት ውስጥ እጅ ከወርች በመጠፍነግ ተቆጣጥሮ ይዞት ባለበት ሁኔታ የትኛውም ትልቅ ብሄራዊ የሆነ የፖለቲካ ቡድን ደስ ብሎት ሊኖር አይችልም፡፡ 

ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ የዘህወሀት የእራሱን የአገዛዝ ስርዓት እና ስልጣን ለማጠናከር ሲል የጎሳ ፌዴራሊዝም አባዜን እና በፖለቲካ የከፋፍለህ ግዛን ፖሊሲ በማራመድ ተግባራት ላይ ሲውተረተር ይገኛል፡፡ ህወሀት በስልጣን እርካብ ላይ ተፈናጥጦ ለመኖር እንዲመቸው የፍርሀት፣ የጥልቅ ጥላቻ እና በኢትዮጵያ ውስጥ አንዱን ጎሳ ከሌላው ጋር በማናቆር ዕኩይ እስትራቴጂ ነድፎ በመተግበር ስራ ላይ ተጠምዶ ይገኛል፡፡ 

እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ የዘህወሀት የጎሳ ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ ውስጥ ታሪካዊ የፖለቲካ ቅሬታ ላላቸው ቡድኖች እና ግለሰቦች በትክክለኛው የፌዴራሊዝም አወቃቀር መስፈርት መሰረት እራሳቸውን በእራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ የፈቀደ በማስመሰል የህዝብ ንብረት የሆነውን መሬቱን ለባዕዳን እየሸጠ እና ሌላውንም የሀገሪቱን አንጡራ ሀብት እየመዘበረ ኪሱን በዶላር በማጨቅ ላይ ይገኛል፡፡ 

የዘህወሀት ተልዕኮ አስፈጻሚዎች በኢትዮጵያ ተገልለው ለቆዩት ብሄረሰቦች የጎሳ ፌዴራሊዝም ሀውልት በማቆም በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ ውስጥ የጎሳ ፌዴራሊዝም ሰፍኗል በማለት ህወሀት እራሱን የበላይ ጠባቂ አድርጎ አስቀምጧል፡፡ ፍጹም የሆነ ሸፍጥ! 

ላለፈው ሩብ ምዕተ ዓመት ህወሀት የጎሳ ፌዴራሊዝም የመጫወቻ ኳስ በማዘጋጀት አንዱን የጎሳ ቡድን ከሌላኛው የጎሳ ቡድን ጋር እያጋጨ ሀገሪቱን በትክክል ባልታሰበበት ሁኔታ ከፍሎ እና ሸንሽኖ ህዝቦችን በኃይማኖት እየለያየ እያጋጨ እያተራመሰ ከፋፍሎ በመግዛት ላይ ይገኛል፡፡ 

ላለፈው ሩብ ምዕት ዓመት ህወሀት ለጥቅም የሚገዙ የይስሙላ የፖቲካ ፓርቲዎችን በማቋቋም አስመሳይነት የሸፍጥ ጨዋታ ሲጫወት ቆይቷል፡፡ እራሱን የኢትዮጵይያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ብሎ በመጥራት የዘህወሀትን የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች (ጅቦች አላልኩም) የኢትዮጵያን ህዝብ የሚጠብቁ በመምሰል እየገደሉት እና እያሰቃዩት ይገኛሉ፡፡ 

ህወሀት የጎሳ ታማኝነትን እያዘጋጀ እና የጎሳ ፍርሀትን እና ጥልቅ ጥላቻን እያራመደ ሲያካሂድ የነበረው የሸፍጥ ጨዋታ ከእንግዲህ ወዲያ የሚቀጥል አይሆንም፡፡ 

በአሁኑ ጊዜ ያለው እውነታ ህወሀት በኢትዮጵያ በሚገኝ በእያንዳንዱ የጎሳ ቡድን እየተጣለ ነው ያለው፣ ምንም ደጋፊ የለውም! 

የማስመሰል ጨዋታው ተጠናቅቋል፣ እናም ይህንን ጉዳይ ህወሀት በሚገባ ተገንዝቦታል፡፡ 

የኢትዮጵያ ህዝብ ከሩብ ምዕተ ዓመታት በኋላ በዘህወሀት አማካይነት ለእራሱ የተፈጠረለትን የጎሳ ክፍፍል እያንዳንዳቸውን ምንም ዓይነት ጥቅም የማያገኙበት እና በዘለቄታዊነት ህወሀት ብቻ አሸናፊ ሆኖ ተጠቃሚ የሆነበትን ስርዓት አንድ በአንድ ተገንዝበውታል፡፡ 

ህወሀት የእራሱን ፍላጎት ፍጹም በሆነ መልኩ በህዝቦች ጫንቃ ላይ እየጣለ ያለው ሁኔታ ሊያሰኬደው እንዳልቻለ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተገነዘበው መጥቷል፡፡ 

በአሁኑ ጊዜ ተማሪዎች እና ወጣቶች ለሀገሪቱ ጥቅም እና ነጻነታቸውን ለማስከበር ወደፊት ገፍተው በመሄድ ላይ ናቸው፡፡

ሆኖም ግን እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ከዋናው የግድብ ውኃ አንዲት ጠብታ ብቻ ናቸው፡፡ ህወሀት የሌባ ጣቱን ወደ ንጹሀን ዜጎች ላይ በመቀሰር እና የተማሪዎችን ተቃውሞ በግድያ በመጨፍለቅ ሊያስቆመው እንደሚችል አድርጎ ያስባል፡፡ 

ህወሀት ያልተገነዘበው ጉዳይ ቢኖር እያንዳንዷ የተማሪዎች ቅሬታ ተሰባስባ ህዝባዊ በሆነ ቁጣ፣ ማዕበል፣ ጥላቻ እና መቃቃርን ፈጥራ ወደ ግብዓተ መሬቱ የሚያደርሰው መሆኑን ነው፡፡ 

የዘህወሀት ትልቁ ቅርንጫፍ በሚገነደስበት ጊዜ የጎሳ ፌዴራሊዝም አልጋ ተንኮታኩቶ ይወድቃል፣ እናም ህወሀት ወደ ታሪክ ቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ውስጥ ይወረወራል፡፡ 

የዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪ ወትዋች የስራ ጌቶች ህወሀት .ኤአ. ግንቦት 2015 ምርጫውን መቶ በመቶ አሸነፊያለሁ ብሎ ካወጀ በኋላ ኢትዮጵያ በዴሞክራሲ ጎዳና ላይ በመገስገስ ላይ ናት በማለት እየነገሩን ይገኛሉ፡፡ 

ባራክ ኦባም ቢሆን የአእምሮ ክህሎታችንን በሚፈታተን መልኩ በመዘለፍ ይህንን ቡድን .. ሀምሌ 2015 ተቀላቅሏል፡፡ አስመሳዩ ፕሬዚዳንት ተብዬ እንዲህ ብሏል፣.. ግንቦት 2015 በተካሄደው ምርጫ ህወሀት መቶ በመቶ ያሸነፈበት ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ባራክ ኦባማ ስለኢትዮጵያ እውነት እንዲናገር ነግሬው ነበር፡፡ ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ስለኢራቅ የጦር እልቂት አምጭ መሳሪያዎች የፈጠጠ ውሸት ዋሽቷል፡፡ ባራክ ኦባማ ስለዘህወሀት ሀሳብን የማስቀየሻ የውሸት የምርጫ ውጤት ሙልጭ አድርጎ ዋሽቷል፡፡ 

ኢትዮጵያ በማህበራዊ የቀውስ ቅርቃር ውስጥ ወድቃለች፣ 

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አንገብጋቢው ጥያቄ ረኃብ ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት .. 2016 የመጀመሪያው ግማሽ በኢትዮጵያ ቢያንስ 15 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ለረኃብ እንደሚጋለጡ ይፋ አድርጓል፡፡ 

ህወሀት ከዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪ ወትዋቾች እና ከአበዳሪ እና ለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ ውስጥ ተከስቶ ህዝቡን በችጋር እየጠበሰ እና እልቂትን እየፈጸመ ያለውን የረሀብ ቀውስ ከምንም ባለመቁጠር ረኃብ በሀገሪቱ ውስጥ በፍጹም የለም፣ አለ እንኳ ቢባል የሚኖረው የምግብ ዋስትና እጦት እና የአልሚ ምግብ ንጥረ ነገር እጥረት እጦት ነው እያሉ የሚጠሩት ነው በማለት የፕሬስ መግለጫዎችን ሁሉ አጨናንቀው ይገኛሉ፡፡ 

ህወሀት የሚጠቀምበት አዲሱ ፋሽን ደግሞ ረኃቡን ያመጣው ኤል ኒኖ እየተባለ የሚጠራው ፍጡር ነው በማለት ከደሙ ንጹህ ነን በማለት ላይ ይገኛሉ፡፡ ረኃቡን በየጊዜው የሚያመጣው እና የሚፈጥረው ብልሹ አስተዳደራቸው እና የማይለወጠው ገታራው ፖሊሲያቸው መሆኑን ለአምዲትም ሰከንድ ቢሆን ማመን አይፈልጉም፡፡ ምክንያቱ የተግምባር ድሁሮች መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በምሁራን እና በባለሙያዎች የሚሰጥን ማንኛውንም ዓይነት አዎንታዊ ምክረ ሀሳብ አእምሯው ሊቀበል አይችልምና ነው፡፡ ተፈጥሮን ተመክሮ አይመልሰውም የሚባለው ዓይነት ነገር መሆኑ ነው፡፡ 

ባለፈው ሳምንት የቪኦኤ ሬዲዮ የአማርኛው አገልግሎት በድርቅ በተመቱ አካባቢዎች በመገኘት ለአርሶ አደሮች ቃለ መጠይቆችን በማካሄድ የሚከተሉትን ዘገባዎች በመግለጫ መልክ አቅርቧል፡ 

ሰዎች ስለረኃቡ እና ስላለባቸው መከራ እንዲናገሩ አይፈቀድም፡፡ እነርሱ (ህወሀት ማለታቸው ነው) ስለረኃቡ ያለውን መረጃ ሁሉ ይደብቃሉ፡፡ ስለዚህ ነገር አንድም ነገር መናገር አይፈልጉም፡፡ ስለረኃቡ ሲናገር የተገኘ ሰው የነፍስ ማጥፋት ወንጀል እንደፈጸመ ወንጀለኛ እኩል ጥፋተኛ ተብሎ ይፈረጃል፡፡ ስለረኃቡ መናገር ወንጀል ነው፡፡ ስለረኃቡ የሚናገሩ ሰዎችን ያስራሉ፡፡ ሰዎችን ይደበድባሉ፡፡ ሰዎችን ያስፈራራሉ፡፡ ሰዎች ተርበዋል፡፡ በእርግጠኝነት ተርበዋል፡፡ በርካታ የሆኑ ሰዎች ምንም ዓይነት የሚላስም ሆነ የሚቀመስ ነገር የላቸውም፡፡ 4-5 የሚሆኑ የበቆሎ ራሶች 10 ብር ያወጣሉ…“ 

ህወሀት እና ዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪ ወትዋቾች የረኃቡን እውነተኛ ገጽታ ለመደበቅ ከሚል ዕኩይ ምግባር ባዶ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በማራመድ ስራ ላይ ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ እናም እስከ ጥርሳቸው ድረስ በዋሹ ቁጥር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በረኃብ የሞት ነጣቂ ተኩላ ይነጠቃሉ፡፡ 

ህወሀት“ ሀብ የምትለዋን ፊደል በፍጹም መጠቀም አይፈልግም፡፡ 

.. ነሐሴ 2008 አሁን በህይወት የሌለው የዘህወሀት አድራጊ ፈጣሪ አምባገነን መሪ ለታይም መጽሔት እንዲህ የሚል ቃለ ምልልስ ሰጥቶ ነበር፣በኢትዮጵያ የረኃብ አደጋ ለበርካታ ጊዚያት ሲከሰት ቆይቷል፡፡ እንዲህ ዓይነት አደጋ ሲከሰት ለጉዳዩ ትኩረት የማያደርግ ደደብ ነው፡፡ ሆኖም ግን በእኛ ሁኔታ ምንም ዓይነት ረኃብ የለምየአስቸኳይ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ረኃብ በፍጹም የለምበአንዳንድ አካባቢዎች በአንዳንድ ኪስ ቦታዎች የአልሚ ምግብ ንጥረ ነገር እጥረት ብቻ ነው ያለውበማለት በድፍረት በቅጥፈት ተናግሯል፡፡  

ህወሀት እና የዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪ ወትዋቾች 15 ሚሊዮን የሚሆነውን ህዝብ የረኃብ ሰለባ ያደረገውን የረኃብ አደጋ እንደዚህ ባለ አሳፋሪ የቃላት እና የሀረጎች አጠቃቀም በመሸፋፈን ያለው የምግብ እጥረት፣ የምግብ ክፍተት፣ የአልሚ ምግብ ንጥረ ነገር እጥረት፣ የምግብ ዋስትና እጦት እና በኤል ኒኖ ድርቅ ምክንያት የተከሰተ የግብርና ምርት እጥረት እና በመሳሰሉት ነው በማለት የቅጥፈት ልብስ ለማልበስ ይሞክራሉ፡፡ 

አሁን በቅርብ ጊዜ ያለው ጥረት ደግሞ የኢትዮጵያን ረኃብየስነ ምግብ ቀውስእያሉ የሚጠሩበት አካሄድ ነው፡፡ አዎ፣የስነምግብ ቀውስይሉታል ፡፡ 

 .. መስከረም 2015 የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ /ቤት እንዲህ በማለት አስጠንቅቋል፣በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተጠናከረ ምላሽ እስካልቀረበ ድረስ ከፍተኛ የሆነ የምግብ ዋስትና እጦት እና የስነምግብ ቀውስ ሊከሰት ይችላል፡፡ 

ዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪ ወትዋቾች“/”F) የምትለዋን ፊደል ለማስወገድ ሲባል የእንግሊዝኛን ቋንቋ እያሰቃዩ እንዳሉ ስነገነዘብ ምን ያህል የወረዱ ፍጡሮች እንደሆኑ እንገነዘባለን! ያም ሆነ ይህ ምን ዓይነት የውሸት የማጭበርበር አነጋገር ነው እባካችሁ? 

በመቶዎች እና በሺዎች የሚቆጠሩ ህዝቦችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳተኝነት እና በሚሊዮኖች ለሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ለመፈናቀል የሚያበቁነው  የመሬት መንቀጥቀጥ እና ሱናሜን ጨምሮየተፈጥሮ አደጋሲባል ሰምቻለሁ፡፡ 

ምግብ በማያገኙ ሰዎች ላይ የሚከሰተውየስነምግብ ቀውስአደጋ በተመሳሳይ መልኩ እንደ ተፈጥሮ አደጋ እኩል ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል ለማለት ነዉን? 

ወደኋላ መለስ ብለን ስንመለከተውየስነምግብ ቀውስአደጋ ረኃብ ተብሎ የሚጠራውን ነገር ለመጥራት የሚጠቀሙበት ሐረግ ነው፡፡ 

ቢቢሲ ብቻ ነው ረኃበን ረኃብ ብሎ በመጥራት ድፍረት ያለው፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ምጣኔ ሀብት ቀውስ ቅርቃር ውስጥ ገብታለች፣ 

ውሸቶች፣ ተራ ቅጥፈቶች እና የሀሰት የቁጥር ድርደራ ጨዋታዎች በዓለም ባንክ፣ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ እና በሁሉም የአውሮፓ እና አበዳሪ እና ለጋሽ ድርጅቶች አማካይነት የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት 11 በመቶ (ይቅርታ የዓለም ባንክ .. ህዳር 2014 ባወጣው ዘገባው የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ዕድገት 10.9 በመቶ ይል ነበር) የምጣኔ ሀብት ዕድገት ባለፉት አስር ዓመታት ዕድገት አስመዝግቧል በማለት የሚዘግቡ ቢሆንም የምጣኔ ሀብቱ በአሁኑ ጊዜ በአስከፊ የቀውስ ቅርቃር ውስጥ ገብቶ ይገኛል፡፡ 

ዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪ ወትዋቾች ሁሉም ኢትዮጵያውን ከአለት በበለጠ መልኩ የደደቡ ናቸው ብለው እራሳቸውን የሚያሳምኑበትን እውነታ እገነዘባለሁ፡፡ 

የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት በፍጥነት እያደገ ያለ እና በዓለም ፈጣን የምጣኔ ሀብት ዕድገትን ከሚያስመዘግቡ ሀገሮች መካከል አንዱ ነው በማለት ሌት ከቀን እንደበቀቀን እየደጋገሙ ውሸትን በመዋሸት የኢትዮጵን ህዝብ እና የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳመን ቅጥፈትን ከቶ ሲያራምዱ የሚውሉት ለምንድን ነው? 

ላለፉት አምስት ዓመታት የኦክስፎርድ የድህነት እና የሰው ኃይል ልማት ተነሳሽነት ዘርፈ ብዙ የድህነት አመልካቾች /Oxford Poverty and Human Development Initiative (OPHDI) Multidimensional Poverty Index ባወጣው የድህነት እና የሰው ኃይል ልማት መለኪያ መስፈርት መሰረት ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ በፕላኔቷ ውስጥ ካሉ ሀገሮች በሙሉ በድህነት በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች መሆኗን ይፋ አድርጓል፡፡ 

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የዓለም ባንክ ባወጣው ዘገባ መሰረት በአጠቃላይ በአገልግሎት እና በግብርና ዘርፉ ላይ ትኩረት ባደረገ መልኩ ኢትዮጵያ አስደናቂ የሆነ ፈጣን የምጣኔ ሀብት ዕድገት እያስመዘገበች መሆኗን እንዲህ በማለት ይፋ አድርጓል፡ 

የግብርና የምርት ውጤቶች ዕድገት ሊመዘገብ የቻለው የግብርናውን ምርታማነት በማሳደግ እና ሊታረስ የሚችለውን የመሬት መጠን በመጨመር ነው፡፡ ለግብርናው ምርት ማደግ እንደ ዋና ዋና ነገሮች ሊቆጠሩ የሚችሉት የኤክስቴንሽን አገልግሎት እና ለአርሶ አደሮች ስልጠና መሰጠት በመቻሉ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ እየተመዘገበ ያለው የግብርና ምርት ዕድገት በዋናነት መንግስት በኤክስቴንሽን አገልግሎት፣ በመንገዶች ግንባታ እና በትምህርት ላይ ከፍተኛ የሆነ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰሱ እንደዚሁም ደግሞ ምቹ የሆኑ የዋጋ ማበረታቻዎችን ማድረግ በመቻሉ ነውብሏል፡፡ 

አንግዲህ እግዚአብሔር ያሳያችሁ የግብርናውን ምርታማነት በማሳደግ እና ሊታረስ የሚችለውን የመሬት መጠን በመጨመር መንግስት እያደረገ ባለው ከፍተኛ ጥረት .. 2015 የግብርና ምርት ዕድገትን ሳይሆን ረኃብን ለማምረት ቻለ ማለት ነው፡፡ የሚታየው እውነታ ይኸ እና ይኸ ብቻ ነው መቀነስም መጨመርም የሚቻል ነገር ሊሆን አይችልም፡፡ 

የዘህወሀት መሪዎች ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ ህብረት እና ከቻይና እርጥባን በመለመን እና ለማኝ መንግስት በመሆን እራሳቸውን በስልጣን ላይ እንደ መዥገር አጣብቀው መቆየት እንደሚችሉ አድርገው ያስባሉ፡፡ 

እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ግን  ከለጋሽ እና አበዳሪ ድርጅቶች በምጽዋት ከሚያገኘው እርጥባን ውጭ ለአንድም ቀን ቢሆን በስልጣን ላይ ሊቆይ አይችልም፡፡ 

ታዋቂ የሆነችው አፍሪካዊት የምጣኔ ሀብት ባለሙያ እና የሙት እርዳታ/Dead Aid መጽሐፍ ደራሲ ዳምቢሳ ሞዮ የኢትዮጵያን የምጣኔ ሀብት ሁኔታ በማስመልከት እንዲህ ብላለች፣በኢትዮጵያ 97 በመቶ የሚሆነው ግዙፍ የመንግስት በጀት የሚገኘው ከውጭ እርዳታ ነው፡፡በእርዳታ እና በብድር እስትንፋስ ህይወት ዘርቶ ስለሚንቀሳቀስ አገዛዝ ከዚህ በላይ ምን ማለት ይቻላል? 

በኢትዮጵያ ውስጥ ተቀባይነት ሊኖረው የሚገባውን ጠቃሚ ነገር ግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት እንዲህ በማለት አስቀምጦታል፣የኢትዮጵያ ህዝቦች አጥንታቸው እስኪቀር ድረስ ተግጠዋል፡፡ ፍጹም ከሆነ እጦት እና ድህነት አረንቋ ውስጥ ለመውጣት በከፍተኛ ሁኔታ ትግል የሚያደርጉ ቢሆንም ቅሉ በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ምክንያት በወንዙ ውስጥ ወደ ላይ በመዋኘት ላይ ይገኛሉበማለት በግልጽ አስቀምጦታል፡፡ እንግዲህ የዘህወሀት ጉድ “ወደ ታች ነው እንጅ ውኃ አወራረዱ ሽቅብ ሽቅብ አለኝ እኔንስ ለጉዱ” እንደሚባለው መሆኑ ነው፡፡ 

ኢትዮጵያ በስነ ህዝብ የቀውስ ቅርቃር ውስጥ ገብታለች፣ 

የዘህወሀት መሪዎች ባለፈው አስርት ዓመታት ውስጥ 10.9 በመቶ ዓማካይ አመታዊ የምጣኔ ሀብት ዕድገት አስመዝግባለች በማለት ሁልጊዜ ያናፋሉ፡፡ (ንደ አህያ “ያናፋሉ” አላልኩም።)   

ሆኖም ግን የዘህወሀት መሪዎች ለመናገር የሚጠሉት 3 በመቶን ሊዘል ትንሽ ስለሚቀረው እና የኢትዮጵን ህዝቦች ህልውና ስለሚፈታተነው ልቅ የተደረገ የስነ ህዝብ መጣኔ ጉዳይ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ህዝብ ዕድገት ለበርካታ አስርት ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ አገዛዙ እንደ አንድ ኃላፊነት እንደሚሰማው ቡድን እንኳ ስለ ስነህዝቡ ሁኔታ አንድም ትንፍሽ የሚለው ነገር የለም፡፡ በሙስና መብከት እና መበስበስ እንጅ ይህ ነገር ለእርሱ ጉዳዩ አይደለምና፡፡ 

.. 1967 የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር 23.5 ሚሊዮን ነበር፡፡ 

.. 1990 ወደ 51 ሚሊዮን ከፍ አለ፡፡ እንደዚሁም ደግሞ .. 2003 68 ሚሊዮን ደረሰ፡፡ 

.. 2008 የህዝቡ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እያደገ በመምጣት 80 ሚሊዮን ደረሰ፡፡ 

.. 2011 የዩኤስ አሜሪካ የስነ ህዝብ ቆጠራ ቢሮ በሰጠው ግምት መሰረት የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር 91 ሚሊዮን ደረሰ፡፡ 

.. 1995 ጀምሮ የኢትዮጵያ ህዝብ አማካይ ዓመታዊ የህዝብ ዕድገት መጣኔ 3 በመቶ በላይ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ይኸ ነገር እንዴት ነው የሚል እና ኃላፊነት የሚሰማው አካል ጠፍቷል፡፡ 

.. 2011 የዩኤስ አሜሪካ የስነ ህዝብ ቆጠራ ቢሮ ስለኢትዮያ ህዝብ ብዛት በጣም አስፈሪ የሆነ ትንበያ በመስጠት .. 2050 በወቅቱ ካለበት የህዝብ ቁጥር በሶስት ጊዜ እጥፍ በማደግ 278 ሚሊዮን ይደርሳል ብሏል፡፡ 

.. 2025 ማለትም ከዛሬ አስር ዓመታት በኋላ የዩኤስ አሜሪካ የስነ ህዝብ ቆጠራ ቢሮው በሰጠው ትንበያ መሰረት የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር 131 ሚሊዮን ይደርሳል ብሏል፡፡ 

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ 99 ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብ መመገብ አትችልም፡፡ 

.. 2010 ደግሞ 87 ሚሊዮን ህዝብ መመገብ አትችልም ነበር፡፡ 

.. 2006 78 ሚሊዮን ህዝብ መመገብ አትችልም ነበር፡፡ 

እንደዚሁም ሁሉ .. 1984 40 ሚሊዮን ህዝብ መመገብ አትችልም ነበር፡፡ 

.. 1974 32 ሚሊዮን ህዝብ መመገብ አትችልም ነበር፡፡ 

.. 2025 ኢትዮጵያ 131 ሚሊዮን ህዝቦቿን ለመመገብ ምን ያህል ገሀነም እንደሚሆንባት ልናስበው እንችላለን? 

ኢትዮጵያ ወደፊት የምግቡ ደረጃ ካለበት የእድገት መጠን ጋር ሊሄድ የሚችል የስነ ህዝብ ዕድገት እንዲኖራት ለማስቻል የህዝቡን የዕድገት ሁኔታ ከምጣኔ ሀብት ዕድገቱ ጋር ለማመጣን እንዲቻል የማልተስ እልቂት ወደሚባለው የተቃወሰ የህልወት እርምጃ (ማለትም በሽታ፣ ረኃብ፣ ጦርነት፣ ወዘተ የመሳሰሉት ነገሮች የህዝቡን ቁጥር ይቀንሱታል) በማለት ዝም ብሎ በግዴለሽነት የማየት ሁኔታ የሚታይ ይመስላል፡፡ 

በአንድ ወቅት አሁን በህይወት ለሌለው ለአምባገነኑ የዘህወሀት መሪ በይስሙላ ፓርላማ ተብየው የስነ ህዝብ ጉዳይን የሚመለከት ጥያቄ ቀርቦለት የሚወለደው ሰው ሆድ ብቻ ሳይሆን የሚሰሩ እጆች ጭምር ይዞ ነው የሚመጣው የሚል ምላሽ በመስጠት ተሳልቆ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ እንግዲህ ይኸ የሚያሳየው ሰውየው ስለ ስነህዝብ ጉዳይ ምንነት ምንም ነገር እወቀቱ የሌለው መሆኑን እና እርሱ የሚመራው መንግስት ስለዚህ አንገብጋቢ ጉዳይ ምንም ዓይነት እርምጃ ለመውሰድ ክህሎቱ የሌለው መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያመላክታል፡፡ እንደ እርሱ አባባል ቢታይ እንኳ የኢትዮጵያ ህዝብ በየጊዜው ለረኃብ ሰለባ የሚጋለጠው የሚወለዱት ህጻነት ሆድ ብቻ ይዘው የሚመጡ እንጅ የሚሰሩ እጆች የሌሏቸው ስለሆኑ ይሆን? 

.. መስከረም 2010 አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ የዘህወሀት መሪ መለስ ዜናዊ እራሱን ከፍ ከፍ በሚያደርግ መልኩ እንዲህ በማለት አውጆ ነበር፣ትርፍ ምርት ለማምረት የሚያስችለንን ስትራቴጂ ቀይሰናል፣ እናም .. 2015 ከውጭ ምንም ዓይነት የምግብ እርዳታ ሳይደረግልን እራሳችንን መመገብ እንችላለንብሎ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ብሎ ነበር፣ከተባበሩት መንግስታት የሚሊኒየም የልማት ግቦች ጋር በሚመሳሰል መልኩ .. 2015 በኢትዮጵያ ፍጹም ድህነት 50 በመቶ ከአልሚ ምግብ ንጥረ ነገር እጦት ጋር ይቀንሳልብሎ ነበር፡፡ ምን ዓይነት ዲያብሎሳዊ ውሸት ነው! 

ህወሀት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን ኢትዮጵያን ህዝብ ዕድገት ለመቆጣጠር የሚያስችል እና 15 ሚሊዮኑን ህዝብ ከአሰቃቂ ረኃብ ለማዳን ወይም ደግሞ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ምንም ዓይነት ዕቅድም ሆነ ፕሮግራም የለውም፡፡ 

ህወሀት እራሱ ወደ ቀውስ ቅርቃር ውስጥ እየገባ ነው፣ 

ህወሀት አስተማማኝ የሆነ ወታደራዊ ኃይል አለኝ፣ በውሸት ላይ የተፈበረከ የምጣኔ ሀብት ስኬት አለኝ፣ በሀገሪቱ ውስጥ አስተማማኝ የፖለቲካ መረጋጋት አለ፣ ወዘተ በማለት በእራሱ የቅጥፈት ትረካ እራሱን ሕጋዊ አስመስሎ ለማቅረብ ሙከራ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ 

ህወሀት እና ዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪ ወትዋች ግብረ አበሮቹ መልካም እና ጥሩ ስም ያለው እያስመሰሉ በማቅረብ ስለምጣኔ ሀብቱ ዕድገት የሀሰት የቁጥር አሀዞችን በመደርደር የነቀዘ እና የበከተ ገጽታውን ለመደበቅ በመሞከር ላይ ይገኛሉ፡፡ 

ህወሀት የኃይል እና የጭቆና አገዛዙን ለማስቀጠል የመጨረሻውን አቅሙን አሟጦ በመጠቀም ለህዝብ ለማሳየት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ 

ሆኖም ግን ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ከዚህ በኋላአንዲት ጋት ወደ ኋላ አናፈገፍግምበማለት በጽናት የተሞላ ስሜቱን በማሳየት ላይ ይገኛል! 

እውነታውን ሙልጭ አድርጎ መካድ የአምባገነኖች ሁሉ መለያ ባህሪ ነው፡፡ ህወሀት ለዚህ የተለዬ ብችኛ ሊሆን አይችልም፡፡ 

ለሁሉም አምባገነኖች የማይቀየሩ ዘላለማዊ እውነታዎች አሉ የምንል ከሆነ እምባገነኖች ሆን ብለው እያወቁ ደንቆሮዎች፣ እውሮች እና ዱዳዎች ናቸው፡፡ 

ለህዝቦች ጩኸቶች እና እንባዎች ሆን ብለው ጆሮ ዳባ ልበስ የሚል ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ 

ስለደኃ ህዝቦች መሰቃየት፣ ለድርቅ አደጋ ሰለባ ለሆኑ እና አቅም ለሌላቸው ሁሉ አላየሁም በማለት አድፍጠው ይቀመጣሉ፡፡ 

መከራን የሚገፉ ህዝቦችን ለይቶ በማውጣት አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ ከችግሮቻቸው ለማውጣት ባለመቻል ዱዳ ሆነው በመቀመጥ ይመለከታሉ፡፡ 

ህዝቡ እነርሱን የሚወዳቸው ለመሆኑ ሌላ ማንንም ሶስተኛ ወገን ሳያስፈልጋቸው እራሳቸውን በእራሳቸው ያሳምናሉ፡፡ 

በማስመሰያው የቅርጫ ምርጫ ከህዝቡ መቶ በመቶ ድምጽ ያገኙ በመሆናቸው እና በዚህም መሰረት ስልጣን እንደያዙ አድርገው የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳመን ይሞክራሉ፡፡ 

እነርሱ እብዶች ናቸው፡፡ ልክ እንዳበደ ቀበሮ፣ እውነታው ይኸው ነው፡፡ 

.. የካቲት 2011 የሊቢያ ህዝባዊ አብዮት እየተቀጣጠለ ባለበት ሁኔታ አምባገነኑ ሙአማር ጋዳፊ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲህ የሚል ቱልቱላውን ነፍቶ ነበር፣ህዝቡ እኔን ይወደኛል፡፡ ሁሉም ህዝቦች ከእኔ ጋር ናቸው፣ እናም ይወዱኛል፡፡ የእኔ ህዝቦች እኔን ለመጠበቅ ሲሉ ይሞቱልኛልነበር ያለው፡፡ 

እርሱን ከስልጣኑ ላይ ለማስወገድ የሚታገሉ የነጻነት ኃይሎችንአይጦች እና በረሮዎችበማለት ነበር የጠራቸው፡፡ እራሱን የንጉሶች ሁሉ ንጉስ በማድረግ በቆሻሻ መውረጃ ፉካ ውስጥ የህይወቱ እስትንፋስ እስከምታልፍ ድረስ ሊቢያን እስከሚሞት ድረስ የመግዛት መብት እንዳለው አድርጎ ነበር የሚያምነው፡፡ በሊቢያ ውስጥ እራሱን 42 ዓመታት ያህል አምላክ አድርጎ የሚቆጥር አምባገነን በወሮበላ የዘራፊ ዓይነት አሟሟት ዓይነት ወደማይቀረው ዓለም በውርደት ተሰናበተ፡፡ 

በመጨራሻዋ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የተቃራኒው ዕጣ ፈንታ አሸናፊ ሆኖ የገዳፊ ዕድል በምታዘቀዝቅበት ጊዜ ጋዳፊ ተቃዋሚ ታጋዮቹ ምህረት እንዲያደርጉለት ፍትህን ጠየቀ፡፡ እንደ ቆሻሻ አይጥ ተስቦ እና እንደበረሮ በኃይል ተደልዞ ምህረት እየጠየቀ ከፉካው ውስጥ በመውጣት እንዲህ አለ፡አትግደሉኝ!“ 

ከአምባገነኑ ሳዳም ሁሴን በፊት የጣሊያን ፋሽሽት መሪ የነበረው ቤኒቶ ሙሶሊኒ እንዲህ በማለት ጉራውን ቸርችሮ ነበር፣በእያንዳንዷ የልቤ ምት ሁሉ ለጣሊያን ህዝብ አገልግሎት እሰጣለሁ፡፡ በመሆኑም ሁሉም ጣሊያናዊ እኔን እንደሚወደኝ እና እንደሚረዳኝ ይሰማኛል፡፡ 

የኡጋንዳ ህዝብ አራጅ የሆነው ኢዲ አሚን ዳዳ እንዲህ የሚል አነስተኛ የሆነ ስሜታዊነትን አንጸባርቆ ነበር፣ህዝቦች መሪያቸውን መውደድ አለባቸው!“ ይህንን የማያደርጉ ከሆነ መሪያቸውን እንዲወዱ የሚያደርግባቸው ጠንካራ የሆኑ የእራሱ መሳሪያዎች በመጠቀም ስራውን ይሰራል፡፡  

የዛየሩ ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ በጸጥታ ቀስ ብሎ በመሳቅ ለውጭ ግንነት አድራጊዎቹ ሲናገር ህዝብ እርሱን ስለሚወደው ህዝቡ እርሱን መውደድ ብቻ አይደለም እንዲያውም በስልጣኑ ላይ እንዲቆይ ይፈልጋል በማለት ባዶ ጉዳውን ሲቸረችር ነበር፡፡ 

ደም መጣጩ ወታደራዊ አምባገነን መንግስቱ ኃይለማርያም ከአርበኝነት እና ከሀገር ወዳድነት የይስሙላ ማታለያ ተልዕኮው አንጻር ህዝቡን እንደ ሰም አቅልጦ እንደ ብረት ቀጥቅጦ የመግዛት ዓላማ ነበረው፡፡ እርግጥ ነው መንግስቱ ለድፍን 17 ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውንን በገፍ እንደ ቄራ ሰንጋ እያረደ ሲገድል የቆየ ስለነበር እንደ እርሱ እምነት ያለምንም ጥርጥር ሀገር ወዳድ ነው፡፡ 

.. ግንቦት 2010 አሁን በህይወት የሌለው የአፍሪካው ልዩ የሆነው ወሮባለ አምባገነኑ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ህዝብ የእርሱን ወሮበላ ፓርቲ እና በውስጠ ታዋቂነት ደግሞ የእርሱን የፓርቲ መሪነት በመውደዱ ምክንያት 99.6 በመቶ የህዝብ ደጋፍ በማግኘት ምርጫውን አሸንፈናል በማለት የሸፍጥ እና የቅጥፈት ቱሪናፋውን ዘረገፈ፡፡ ህዝቡ እነርሱን እና ኢህዴግን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው እናም ምንም ዓይነት ኃይል የእርሱን ድርጅት ሊነቀንቀው እንደማይችል በእብሪት አፉን ሞልቶ ተናግሯል፡፡ ህዝቡ የእርሱን ፓርቲ በመምረጥ ላሳየው መልካም የህሊና ዳኝነት እና ፍትሀዊነት ከልብ እንደሚያመሰግን እና የህዝቡን ይሁንታ በካርዳቸው እንደሰጡት በማድረግ የድርቅና ቅጥፈቱን በአደባባይ አሰራጭቷል፡፡ 

በመጨረሻም የዘህወሀት ችግር በነብሩ ጀርባ ላይ ወጥቶ እንደሚጋልበው ነብር ጋላቢ ሁሉ ለመውረድ አስፈሪ ሆኖ የመገኘቱ ሁኔታ እየተባለ እንደሚነገረው ተረት ነው፡፡ ለድፍን 25 ዓመታት ህወሀት የነብሩን ጭራ ይዞ ለመልቀቅ እየፈራ በመወራጨት ላይ ያለ የዕኩዮች ስብስብ ነው፡፡ 

መሄድ እንዲችሉ ልቀቋቸው፡፡ ለመሄድ እንዲችሉ ፍቀዱላቸው፡፡ 

ነብር ጋላቢው ለበርካታ ጊዜ በመጋለቡ ምክንያት ታምሟል እናም በጣም ድካም ይዞታል፡፡ ህወሀት ከስልጣን እርካብ ላይ እንዲወርድ በሚገደድበት ጊዜ በፈጣጣዎቹ ዓይኑ አፍጥጦ ይመለከታል፣ ጥርሶቹን ያንገጫግጫል፣ እናም የተንጨፈረሩ ጥፍሮቹን ይሰነዝራል! 

በጋንዲ የተነገሩትን እንዲህ የሚሉትን ዘላለማዊ እውነታዎች ህወሀት እንዲያስብበት እነግረዋለሁ፡በታሪክ ሂደት ሁሉም የእውነት እና የፍቅር መንገዶች ያሸንፋሉ፡፡ አምባገነኖች እና ገዳዮች ለጊዜው የማይበገሩ አሸናፊዎች መስለው ይታያሉ፡፡ ሆኖም ግን በመጨረሻ ሁልጊዜ ይወድቃሉ፡፡ ይህንን ነገር አስቡት  ሁልጊዜ ይወድቃሉ፡፡ 

ህወሀት ከዚህ ዘላለማዊ እውነታ ሊያመልጥ አይችልም፡፡ 

የድሀረ ህወሀት ኢትዮጵያ፣ 

በዘህወሀት ላይ ጉዳት በማያደርስ መልኩ እና ከምንም አድልኦ በጸዳ መልኩ፣ በሰለጠነ አኳኋን፣ በጓዳዊነት፣ ቅንነትን በተላበሰ መልኩ የእራሴን ምልከታ ከዚህ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡ 

እውነቱን እንዳየሁት፣ አብሬው እንደኖርኩት፣ እንደሚሰማኝ፣ እንዳሰብኩት፣ እንደተገነዘብኩት አድርጌ አቀርባለሁ፡፡ 

ለኢትዮጵያውያን ድምጽ የለሾች፣ ኃይል የለሾች እና ለተስፋ የለሾቸ እናገርላቸዋለሁ፡፡ አዎ፣ እራሴን በእራሴ ሾሚያለሁ፣ ሆኖም ግን ጥልቅ በሆነ መከባበር እና አገልግሎት ላይ በተመሰረተ መልኩ ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ በዘህወሀት ከተፈጠረው የሌሊት ቅዠት ሊወጣ የሚቻልበት መንገድ ይኖራል፡፡ 

ህወሀት ያንን መንገድ አይጠቀምበትም፡፡ 

የዘህወሀት አመራር እንደሞተው የሶቪዬት አመራር ሁሉ ያሉትን የጥፋት አደጋዎች ወይም ባሉበት መፍትሄ ለመስጠት እና ለውጥ ለማምጣት ሊሰራ አይችልም፡፡ 

ሆኖም ግን የመውጫ መንገዱ አለ፡፡ 

ስለውይይት መድረክ ነው፣ ስለጽኑ አርበኝነት መንገድ ነው፣ ስለማህበረሰቡ የማሰብ መንገድ ነው፣ ስለ መንፈሳዊ ህይወት የማሰብ መንገድ ነው፡፡ 

ወደ ብርሀን ወይም ደግሞ ቀጣይነት ወዳለው ጨለማ ውስጥ ስለመግባት መንገድ ነው፡፡ 

ስለሆነም ለእኛ በመስታወቱ ላይ የተጻፈልን ጥያቄ እና ለዘህወሀት፣ ለደጋፊዎቹ እና ለግብረ አበሮቹ በግድግዳው ላይ የተጻፈላቸው ጥያቄ እንዲህ የሚል ነው፡ህወሀት በሚወድቅበት ጊዜ ምን መደረግ አለበት?“ 

ለዘህወሀት መልሱ ቀላል ነው፡፡ ተመትተው፣ እየጮኹ እና እያከኩ ወደ ታሪክ የቆሻሻ ማስቀመጫቸው ይሄዳሉ፡፡ 

ለእኔ የድህረ ህወሀት ኢትዮጵያ የሸክስፒርን ጣያቄዎች ያቀርባል፡፡ 

ለጋራ ዕድል መተባበር ወይም አለመተባበር ነው ጥያቄው፡፡ 

በዘህወሀት የጋህነም መንገድ ላይ መጓዝ መቀጠል እና እራስን ወደ ገደል አፋፍ ላይ ወስዶ መጣል የሚለው ሌላው ጥያቄ ነው፡፡ 

እኔ በዘህወሀት  ወዳጅ አይደለሁም ፡፡ (እሺ፣ ለቧልት ያህል ነው ያልኩት፡፡) 

ህወሀት እራሱን ከመጥፋት ለማዳን ቀደም ሲል ያወደማትን ኢትዮጵያን መጠበቅ መቻል ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ 

እራሱን ለማዳን ህወሀት እስከ ዛሬ ድረስ በመላ ኢትዮጵያ በጎሳ ፌዴራሊዝም ስም ሲገነባው የቆየውን የጥላቻን ግድግዳ የግርዶሽ ግንብ መናድ አለበት፡፡ 

ህወሀት ለዓመታት የገነባው የጥላቻ ግንብ በእራሱ ላይ ከመደርመሱ በፊት የጥላቻን ግንብ ቀድሞ ማፍረስ እና ማስወገድ ይኖርበታል እላለሁ፡፡ 

ህወሀት ከጀርባ የእናንተ አመራር፣ ግብረ አበሮች እና ደጋፊዎች ያሉበትን በግድግዳው ላይ የተጻፈውን የእጅ ጽሁፍ ማንበብ ይኖርባችኋል እላለሁ፡፡ 

ህወሀት ኢትዮጵያውንን እንደ በረት ከብት በነገድ፣ በጎሳ፣ በኃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በመደብ ወዘተ በመከፋፈል በገነባችሁት የክልል ግንብ ላይ የተጻፈውን የእጅ ጽሁፍ ማንሳት ይኖርባችኋል እላለሁ፡፡ 

ህወሀት ከቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እንዳትገናኙ ከቪላችሁ ጀርባ የገነባችሁትን  ግንብ እና እስር ቤት ላይ የጻፋችሁትን የእጅ ጽሁፍ አንብቡት እላችኋለሁ፡፡ 

ህወሀት ላለፉት ሩብ ምዕተ ዓመታት ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በገነባችሁት የጥላቻ ግንብ ላይ የጻፋችሁትን የእጅ ጽሁፍ አንብቡት እላችኋለሁ፡፡ 

የዘህወሀት አመራሮች የጥላቻ ግንብ በእራሳችሁ ላይ ከመናዱ በፊት እራሱን የጥላቻን ግንብ አስቀድማችሁ ናዱት እላችኋለሁ፡፡ 

ምናልባትም በመጽሐፍ ቅዱስ የአቀራረብ ዘይቤ ህወሀትን (አሕዛቦቹን አላልኩምለመስበክ እችላለሁ፡፡ 

የኢያሪኮ ከተማ ግንቦች በጣም ጠንካሮች፣ ኃይለኛ ምሽጎች እና ለመስበርም የማይሞከሩ ነበሩ፡፡ የኢያሪኮን ግንብ መስበር የሚችል ምንም ዓይነት ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል አልነበረም፡፡ 

ሆኖም ግን ህዝቡ የኢያሪኮን ግንብ ለመስበር የወታደር ኃይል አላስተባበረም ነበር፡፡ ህዝቡ ጸጥታን በተላበሰ መልኩ ቀስ ብሎ ለስድስት ቀናት በመጓዝ ወደ ግንቡ ተቃረበ፡፡ በሰባተኛው ቀን ህዝቡ ብሎ ጮኸ፡፡ የኢያሪኮ ግንብ ወዲያውኑ ፈረሰ፡፡ 

የዘህወሀት ግንብ በወታደራዊ ኃይል አይፈርስም፡፡ የጦር እና አውዳሚ መሳሪያዎችን በገፍ እና በብዙ ቁጥር በህዝብ ሀብት እየገዛ አከማችቷል፡፡ የአውዳሚ እና የጦር መሳሪያዎችን ከቻይና፣ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ ወይም ኬሎችም ከሚፈልጋቸው ሀገሮች ወሰን በሌለው መጠን አከማችቷል፡፡ 

ህዝቡ አንድ ሆኖ ከሰሜን እስከ ደቡብ እና ከምስራቅ እስከ ምዕራብአምባገነናዊ አገዛዝ በቃን! ስልጣንን ከሕግ አግባብ ውጭ መጠቀም ይብቃ! ሙስና ይብቃ! የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ይቁም! በቃ በቃ ነው!“ በማለት በአንድ ድምጽ ሲጮህ የዘህወሀት ግንብ እሳት እንዳልነካው ሸክላ ፍርክስክስ ብሎ ይወድቃል፡፡ 

የዘህወሀት ግንብ ህዝቦች ስለ ህወሀት ስያቅለሸላቸው አና ሲያስታዉካቸው ህወሀት ይወድቃል ይደረመሳል፡፡ 

ህወሀት ይወድቃል ምክንያቱም ህወሀት የኢትዮጵያን ህዝቦች አእምሮ እና ልብ ሊቆጣጠር አልቻለምና፡፡ 

በወታደራዊ ኃይል ማቋረጫ የሌለው ጽናት ሊኖር አይችልም፡፡ ለረዥም ጊዜ ለጭቆና ተዳርጎ የቆየን የህዝብ ቁጣ እና ብስጭት እንደዚሁም ሁሉ በየዕለቱ ክብሩን አጥቶ በውርደት ተዘፍቆ ኑሮን በመግፋት ላይ ያለን ህዝብ ማቆም የሚያስችል በምንም ዓይነት መንገድ በመሬት ላይ የሚገኝ ምድራዊ ወታደራዊ ኃይል ሊኖር አይችልም፡፡ 

የአንድ ሀገር እውነተኛ ጥንካሬዋ፣ የአንድ ሀገር መንግስት እውነተኛ ጥንካሬው የሚለካው የአንድን ሀገር ህዝብ አእምሮ እና ልብ መቆጣጠር ሲችል ነው፡፡ 

የወደፊቷ ኢትዮጵያ አሁን በሚደረጉ ድርጊቶች፣ በማይደረጉ ድርጊቶች ወይም ደግሞ በዘህወሀት ምላሾች ወይም በእርሱ ግብረ አበሮች ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ 

የወደፊቷ ኢትዮጵያ መሰረት የምታደርገው የወጣት ህዝቧን አእምሮ እና ልብ በመቆጣጠር እና ለሀገራቸው ባላቸው ፍቅር፣ በህዝቡ፣ ህዝቡ እራሱን ለማሻሻል በሚያደርገው ጥረት፣ ወንድሞቹን እና እህቶቹን ከገቡበት አዘቅት ውስጥ መንጥቆ የማውጣት ፍላጎት ሲኖረው እና ከድህነት ብቻ ሳይሆን ከሞራል ስብዕና ኪሳራ ጭምር ነጻ ማድረግ ሲችል ነው፡፡ 

ህወሀት ይህንን ያልኩትን ሁሉ ማድረግ ከቻለ የሚፈራውን ቀውስ ማስወገድ ይችላል፡፡ 

እኩልነትን በማረጋገጥ፣ አንድነትን በማራመድ፣ ወንድማማችነትን በማጠናከር፣ የስልጡንነት አካሄዶችን በመተግበር እና ጨካኝነትን በማስወገድ፣ አረመኔያዊነትን እና ጭራቃዊነትን በማጥፋት የጥፋት ቀውስን ማስወገድ እችላለሁ፡፡ 

ህወሀት ፍትህን በማስፈን፣ ፍትሀዊነትን በማስተማር፣ እውነተኛው ነገር እንዲሰራ በማደፋፈር፣ በተጠያቂነት ላይ አጠንክሮ በመስራት፣ የጭካኔ ድርጊቶችን ከመፈጸም ይልቅ አዲስ የፈጠራ ባህልን በማዳበር እና በመጠቀም፣ ችግሮችን ሰላማዊ በሆነ መንገድበመፍታት፣ ፍቅርን በማሳየት፣ ልግስናን በመውደድ፣ በሰለጠነ መልኩ በመንቀሳቀስ፣ ቅዱስ የሆኑ ሀሳቦችን በመከተል፣ በታማኝነት እና ክብርን በጠበቀ መልኩ በመራመድ የህዝቦችን አእምሮ እና ልብ መቆጣጠር ይችላል፡፡ 

ሆኖም ግን ህወሀት የኢትዮጵያን ወጣቶች አእምሮ እና ልብ ለመያዝ እና ለማሸነፍ ያለችው ጊዜ በጣም ትንሽ ናት፡፡ (70 በመቶ የሚሸፍነውን በኢትዮጵያ ወጣቶች ላይ ትኩረት በማድረጌ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡) 

ምናልባትም ህወሀት ከተለያዩ ዘመናት በርካታ የሆኑ ሰብአዊ መከራዎችን ከተቀበለው እና የእነርሱ ቅርብ ጓደኛ እንዲህ በማለት የጠቀሰው መልዕክት የበለጠ ግልጽ ሊያደርግላቸው ይችላል፡አስቀድሞ ወጣቱን የያዘ የወደፊቱን መጻኢ ዕድል ይቆጣጠራል፡፡ 

ይቀጥላል…    

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር

ህዳር 28 ቀን 2008 .

 

 

Similar Posts