ኢትዮጵያ እና የዓለም ባንክ ቅጥፈቶች፣ እርባናቢስ ውሸቶች እና የሀሰት የቁጥር ቁማር ጨዋታዎች፣ 

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም    

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ 

World Bank10ጆን ሚልተን ገነትን ማጣት/Paradise Lost በሚለው መጽሀፋቸው “የቱም ዓይነት ቅጥፈት ቢሆን ዘለቄታዊነት የለውም የሰማይ ቁጣንም ይስባል።” በማለት ጽፈዋል፡፡

በእርግጥ ሚልተን ሊጨበጥ ሊዳሰስ ስለማይችለው ባዶ ምናብ ስለሚፈጥረው ስለሰይጣን እና ስለዕኩይ ምግባሩ ነበር የጻፉት፡፡

የዓለም ባንክ በሰይጣናዊ የቅጥፈት የምጣኔ ሀብት ዕድገት የቁጥር ጨዋታ ዕኩይ ምግባሩ፣ ከአፍሪካ  ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አምባገነኖች ጋር በሚያደርገው የማታለል ስምምነት እና ባዶ ምናባዊ ሀሳብን ከሚፈጥሩት፣ ከሚቀጥፉት፣ እርባናቢስ ውሸትን ከሚያራምዱት እና የእራሳቸውን የስራ ዕድል ደህንነት ለማረጋገጥ ብለው ሀሰትን መተዳደሪያቸው እና መርሀቸው አድርገው ህሊናቸውን ሸጠው በሚኖሩት በርካታ ሰራተኞቹ ዘንድ በየግዜው ስበሳጭ ቆይቻለሁ፡፡

የዓለም ባንክ አሁን በቅርቡ ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ ባወጣው ዘገባ ብስጭቴን ከፍ እንዲል አድርጎታል (ደሜን አፍልቶታል)፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት የዓለም ባንክ “የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ” በሚል ርዕስ በኢትጵያ ላይ ባለ166 ገጽ ዘገባ አቅርቧል፡፡

ያ ዘገባ እስከ አሁን ድረስ በህይወቴ ካነበብኳቸው ነገሮች ሁሉ የበለጠ እርባናየለሽ፣ አስመሳይነትን የተላበሰ እና በቅጥፈት ላይ ተመስርቶ በሰዎች ላይ እምነትን ለማሳደር የሚሞክር የቅጥፈት እና ሸፍጥ የታጨቀበት ባዶ የማደናገሪያ  የሐሰት የጥናት  ሰነድ ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ2010 አሁን በህይወት የሌለው እና የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) መሪ የነበረው መለስ ዜናዊ በጠራራ ጸሐይ በአደባባይ ምርጫውን የዘረፈበትን ክስተት በመታዘብ የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን አቅርቦት የነበረውን ዘገባን “ለምንም ነገር የማይውል እርባናቢስ እና ወደ ቅርጫት መጣል ያለበት ዘገባ” በማለት በእብሪት የተሞላ ዘለፋውን አሰምቶ ነበር፡፡

ማንም ሰው ቢሆን እ.ኤ.አ በ2015 ባለ24 ካራት እርባናየለሽ እና ወደ ቅርጫት መጣል ያለበትን ቆሻሻ ዘገባ ማንበብ ለሚፈልግ ሁሉ “የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ” በሚል ርዕስ በዓለም ባንክ የተዘጋጀውን ድሪቶ ዘገባ ከማንበብ የበለጠ ሌላ ፅሁፍ  ምንም ዓይነት ነገር ሊያገኝ አይችልም፡፡

ወገኖቼ እስቲ እግዚአብሔር ያሳያችሁ! እነዚህ ዓለም ባንክ በሚባለው አለም አቀፋዊ ድርጅት ተሰግስገው የሚገኙት አስመሳይ እና አስቀያሚ የለየላቸው ውሸታሞች አርሳቸውን በሚያዋርድ እና የሞራል ስብዕና ባልተላበሰ መልኩ እንደ ጎማ በመለንበጥ እውነታውን በመደበቅ የህዝቦችን ስጋ እሰከ አጥንታቸው ድረስ ድረስ ዘልቆ በመጋጥ ላይ ያለውን አምባገነናዊ ስርዓት ከመጠን ያለፈ የታዛዥነት ሎሌነትን በመላበስ የሀሰት እንቁላል መፈልፈላቸውን፣ የበሬ ወለደ ውሸት ፈጠራቸውን እና የቅጥፈት አሀዝ መደርደራቸውን ሊያስቆም የሚችል ምንም ዓይነት ገደብ የለም ማለት ነውን?

ደህና! ስለኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ እራሳቸውን ከእባብ ደረት በበለጠ መልኩ እንዲለነበጥ አድርገው የአስመሳይነት ጉዟቸውን ቀጥለው ይገኛሉ፡፡

ቀጣፊዎችን ምርር አድርጌ እጠላለሁ፡፡

በተለይም ደግሞ ተቀጣሪ ውሸታሞችን በጣም አድርጌ እጠላለሁ፡፡ ለጥቂት ቁርጥራጭ ገንዘብ ሲሉ የሚቀጥፉትን ቀጣፊዎች አምርሬ እጠላለሁ፡፡ ሙያቸውን እና ክህሎታቸውን ለአንድ ወይም ለሁለት ዶላር ሲሉ ሽርሙጥና የሚሰሩትን ባለሙያ ተብዬዎችን በጣም እጠላለሁ፡፡ አስመሳይ ቀጣፊዎችን አምርሬ እጠላለሁ፡፡ አይን አውጣ ቀጣፊዎችን በጣም እጠላለሁ፡፡

የተማሩ እና የሰለጠኑ ቀጣፊዎች ሙስናን የተከበረ ነገር ለማድረግ፣ ማጭበርበርን እንደ ክብር የመቁጠር፣ ስርቆትን፣ ማባከንን እና ስልጣንን ከሕግ አግባብ ውጭ በመጠቀም የሀገሪቱን ጥሪት ሙጥጥ ጥርግ አድርጎ መዝረፍን እንደ ክብር እና ሞገስ አድርገው ሊያሳዩ የሚሞክሩ የቃላት አጠቃቀሞችን በስራ ላይ ለማዋል አበርትተው ይሰራሉ፡፡

የዓለም ባንክ ቀጣፊዎች ውሸትን ለማምረት እንዲችሉ እውነትን በመግረፍ ያሰቃያሉ፣ እውነቱን እንዳይገኝ አድርገው በስድስት ሜትር ጥልቀት ጉድጓድ ውስጥ ለመቅበር እንዲችሉ የሀሰት አሀዞችን ይፈበርካሉ እናም ከአጠቃላይ የቅጥፈት ከረጢታቸው እውነትን የፈጠሩ አስመስለው ለማቅረብ ሲውተረተሩ እና ሲዳክሩ ይታያሉ፡፡

በዓለም ባንክ ውስጥ ዓለም አቀፍ ኤክስፐርቶች፣ አማካሪዎች እና ዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪዎች እየተባሉ የሚጠሩት ቀጣፊዎች በኢትዮጵያ ላይ በሸፍጥ የታጀበ የምጣኔ ሀብት ዘገባ በማውጣት እንድታመም ያደርጉኛል፡፡ በየጊዜው የእነርሱን እርባናየለሽ ዘገባ ባነበብኩ ቁጥር ፅሁፋቸዉን  አሽቀንጥሬ ለመጣል እፈልጋለሁ፡፡

ለእራሴም እንዲህ የሚል ጥያቄ በማቅረብ እጠይቃለሁ፡ የመጽሐፍት መደርደሪያ ቁም ሳጥኖቼ በተከበሩ እና በእውነተኛ የስነጽሑፍ ውጤቶች ታጭቀው ሳለ ለምንድን ነው የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ላይ በየጊዜው የሚያወጣቸውን ሸፍጥን የተላበሱ እና እርባናየለሽ ዘገባዎችን ለማንበብ እራሴን የማስገድደው?

የጥያቄውንም መልስ እኔው እራሴ እንዲህ በማለት እመልሳለሁ፡ ዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪዎች ትምህርት ሊሰጠን የሚችል የውሸት ታሪክ፣ ምናባዊ ኃይል ስላለው ነገር፣ ባዶ ሀሳባዊ አመለካከትን የሚያመላክት፣ ከእውነታ ውጭ ባፈነገጠ መልኩ የሚቀርብ ትረካ እና ልብወለድ ትረካ የሚጽፉ ስለሆነ ያንን ሚስጥራዊ ነገር ለማወቅ ጉጉት የሚያድርብኝ ስለሆነ እና ቅጥፈቱን በማጋለጥ እውነታውን ለማውጣት ካለኝ ጥረት አኳያ ሊሆን ይችል ይሆን? የሚል ምላሽ እሰጣለሁ፡፡

ሁለት ዓይነት የመዋሸት መንገዶች አሉ እየተባለ ይነገራል፡፡ አንደኛው እውነተኛውን ባለመናገር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የውሸት አሀዞችን በመደርደር የሚቀርብ ውሸት ነው፡፡

የዓለም ባንክ “የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ” ሁለቱንም ዓይነት የውሸት መንገዶች ይጠቀማል፡፡

የዓለም ባንክ ውሸቶች፣ እርባናየለሽ ቅጥፈቶች እና “የሀሰት አሀዞች” (የዓለም ባንክ የድህነት አቃጣሪዎች ውሸቶችን እና እርባናየለሽ ቅጥፈቶችን ለመግለጽ የሚጠቀሙባቸውን ቃላት በማጣመር የተጠቀምኩበት) በውሸት ሰነዱ በመግቢያው ማጠቃለያ ገጽ 4 ላይ ዓይን ባወጣ መልኩ ያለምንም ሀፍረት በመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር ላይ እንዲህ በማለት የመቀደድ ዕኩይ ምግባሩን ይጀምራል፡

የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ አስደናቂ የሆነ ፈጣን ዕድገትን ያስመዘገበ እና ዘለቄታዊነትም ያለው ነው፡፡ መንግስታዊ የመረጃ ምንጮች እንደሚያመላክቱት እውነተኛው የሀገር ውስጥ ምርት/Real GDP እ.ኤ.አ ከ2004-2014 ድረስ በአመት በአማካይ 10.9 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል” ይላል፡፡

የዚህ ዓረፍተ ነገር የግርጌ ማስታዋሻ (ማንም አያነበውም የሚል ተስፋ ይዘው የጻፉት ይመስለኛል) እንዲህ በማለት ይገልጻል፡

የዓለም ቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) (2013b) የመንግስት እውነተኛው የሀገር ውስጥ ዕድገት መጣኔ/official real GDP growth rate ከእኛ ግምት በሶስት በመቶ ያንሳል ብሏል፡፡ በዚህ ዝቅ ተደርጎ በታሰበው ግምትም ቢሆን እንኳ ፈጣን ዕድገት ለመኖሩ የሚያወዛግብ አይደለም” ይላል፡፡ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

በመግቢያው ላይ የቀረበው የሰነዱ ዘገባ የማጠቃለይ ጽሁፍ የመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር ታማኝነትን እና ቅን ልቦናን አሽቀንጥሮ በመጣል በዚያው ገጽ የግርጌ ማስታዋሻ ላይ የተገለጸው ተራ እና ዓይን ያወጣ አሀዛዊ ቅትፈት (የቁጥር ፍብረካ ውሸት) ነው፡፡

የቅጥፈት አሀዛዊ ዘገባው እውነተኛ ትርጉም ሲገለጽ ግን እንዲህ የሚል ሆኖ ይገኛል፡ “የኢትዮጵያ እውነተኛው የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት/Ethiopia’s real GDP growth በእርግጠኝነት 10.9 በመቶ አይደለም (6.5 በመቶ፣ 7 በመቶ ወይም ደግሞ 8.9 በመቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ማን ነው ይህንን ስሌት የሰራው?  ማን ደንታ አለውና!?“

ያም ሆነ ይህ የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ምርት መጣኔ ዕድገት 10.9 በመቶ ሊሆን ይችላል በማለት አንባቢ እምነት አንዲኖረውና ለማሳመን  ነበር በመጀርያ አርፍተ ነገር ላይ የሰፈረው።  (በእርግጥ 10.9 እንጂ  11 በመቶ አይደለም ?!)

ከሁሉም በላይ የዓለም ባንክ የመረጃ አሰባሰብ እና ትንተና በጣም ትክክለኛ እና እርግጠኛ በመሆን የቁጥር ክፍልፋይ እንኳ ሳይቀር ስሌቱን በመስራት 10.9 በመቶ እንጅ 11 በመቶ አይደለም በማለት መግለጽ ይችላሉ፡፡

የዘገባው የማጠቃለያ ጽሁፍ የመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር የአንባቢዎችን ስሜት ለመግዛት ሲባል እና አድናቆትን ለማግኘት የማሰብ አላማን ሰንቆ ለመጀመር ስለተፈለገ ነው፡፡ የተውገረገረ የቅጥፈት ዘገባ አላማን በማቅረብ በአንባቢው ዘነድ የአድናቆት እና የመገረም ስሜትን ለመፍጠር የቀረበ አስመሳይ የማወናበጃ አሀዛዊ ቅጥፈት ነው!

ባለፉት አስርት ዓመታት ውስት የ10.9 በመቶ ዓመታዊ አማካይ የምጣኔ ሀብት ዕድገት አንድ ጊዜ በአንባቢው አዕምሮ ውስጥ አምነውበት በጽናት እና ባለማወቅም እንዲሰርጽ ከተደረገ በኋላ እና አንባቢው በማወቅ ወይም ደግሞ ባለማወቅ ይህንን የመንግስት መረጃ እንደ እውነት እና ትክክለኛ አድርጎ ከተቀበለ በኋላ ይህ አወዛጋቢ ያልሆነው ፈጣን የሆነ የምጣኔ ሀብት ዕድገት እንዴት እንደተገኘ የሚገልጸው የ165 ገጹ ዘገባ ተራ የትረካ ፕሮፓጋንዳ በመሆን የሚገልጽ ይሆናል፡፡

አስቲ እኮ!  የዓለም ባንክ እባክህ ይህን ቱሪናፋህን አቁም!አቁም! አቁም! ምንም ዓይነት ፈጣን ዕድገት በፍጹም የለም!

ከምንም በላይ አወዛጋቢ የምጣኔ ሀብት ዕድገት አለ የሚለው ከምንም በላይ አወዛጋቢ የሆኑ ነገሮችን አካትቶ ይዞ ይገኛል፡፡

ስለሆነም እስቲ አሁንም ወደኋላ መለስ እንበል እና ጥቂት ቀላል የሆኑ ጥያቄዎችን ለዓለም ባንክ ባለሙያዎች እናቅርብ፡፡

በ8.9 እና በ11.9 በመቶ የምጣኔ ሀብት ዕድገት መጣኔዎች መካከል አሀዛዊ የሆነ ጠቃሚነት ያለው ልዪነት ሊታይ ይችላልን?

ለምሳሌ ባለፈው ሳምንት በዩኤስ አሜሪካ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ በወጣው ዘገባ ጠቅላላ በ2015 የበጀት ዓመት ውስጥ በሀገሪቱ የሚመዘገበው የምጣኔ ሀብት ዕድገት እ.ኤ.አ በ2014 ከተመዘገበው የምጣኔ ሀብት ዕድገት ብዙም ልዩነት በሌለው መልኩ በ2.5 በመቶ ዕድገት እንደሚመዘገብ ይጠበቃል የሚል ዘገባ አቅርቦ ነበር፡፡

የዓለም ባንክን የስህተት ህዳግ/margin of error ብሎ ያቀረበውን 3 በመቶ ዕድገት (?) ብንቀበል እና በዩኤስ አሜሪካ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ ተግባራዊ ብናደርገው ዩኤስ አሜሪካ አሉታዊ/negative የምጣኔ ሀብት ዕድገት በማስመዝገብ ማቆሚያ በሌለው ጥልቅ የምጣኔ ሀብት ውድቀት ወይም ዝቅጠት ውስጥ ገብታለች ማለት ነው፡፡

በዘ-ሀዋሃት አስተዳደር  ይፋ የሆነው የ10.9 በመቶ የምጣኔ ሀብት ዕድገት (11 በመቶ ማለቱ አይቀልም ?) ወይም ደግሞ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት/IMF 7 በመቶ (?) 8 በመቶ (?) የዕድገት መጣኔ አሀዝ ትክክለኛ ነውን?

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለምሳሌ እ.ኤ.አ በ2012/2013 ኢትዮጵያ አስመዝግባው ከነበረው የ8.5 በመቶ የምጣኔ ሀብት ዕድገት እ.ኤ.አ በ2013 6.5 በመቶ በመውረድ የቀነሰ ዕድገት ማስመዝገቧን የሚያመላክት ዘገባ አቅርቦ ነበር፡፡

ዘ-ሀዋሃት አገዛዝ  እራሱን እንዲያገለግለው በማሰብ በሚያዘጋጀው መረጃ ላይ በመመስረት የዓለም ባንክ የሚያዘጋጀው ዘገባ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ካቀረበው መረጃ በላይ አስተማማኝነት እንደሚኖረው በማመን በማጠቃለያ ዘገባው በመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር ላይ ይፋ ማድረጉ የበለጠ ታማዕኒነት ሊኖረው ይችላል ብሎ ሊያምን ይችላልን? (የዓለም ባንክ በርካታዎቹ በአመክንዮ ላይ የሚያምኑ አንባቢዎች ይህንን እርባናየለሽ ዘገባ እንደማያነቡት ያውቃል፣ ደፍረው ከሚያነቡት ጥቂት አንባቢዎችም ሁሉም በሚባል መልኩ የሚያነቡት የማጠቃለያዋን ዘገባ ነው (ምክንያቱም ሁሉንም መተው ባለመፈለጋቸው ነው))፡፡ ከአመክንዮም በላይ ዘልቀው የማያምኑ እንደ እኔ ያሉ ሰዎች ብቻ የ166 ገጽ እርባናየለሽ ቆሻሻ ዘገባውን እያገላበጡ በማየት ጊዚያቸውን ያባክናሉ፡፡

የዘ-ሀዋሃት አገዛዝ መረጃዎች ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ግምት የበለጠ አስተማማኝነት አላቸውን?

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትም መንግስት የሚሰጠውን የተቀቀለ መረጃ ከመጠቀሙ አንጻር በመንግስት ይፋ በሆነው እና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ግምታዊ የምጣኔ ሀብት ዕድገት አሀዞች መካከል መሰረታዊ የሆነ ልዩነት ይኖራል ተብሎ ሊታሰብ ይችላልን?

በዘ-ህወሀት አገዛዝ እና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ወይም ደግሞ በዓለም ባንክ ወይም በሌሎች አበዳሪ እና ለጋሽ ድርጅቶች የሚወጣ ማንኛውም መረጃ ቅንጣት ያህል ታማዕኒነት ሊኖረው ይችላልን?

የዓለም ባንክ፣ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ሌሎች አበዳሪ እና ለጋሽ ድርጅቶች መረጃዎችን የሚያገኙት በዘ-ሀዋሃት አገዛዝ ባለስልጣኖች በማንኪያ አጉራሽነት መሆኑ እየታወቀ በዚህ መልክ ታሽቶ የሚወጣው መረጃ እንዴት ታማዕኒነት ይኖረዋል ተብሎ ሊታመን ይችላል?

ዘ-ህወሀት በእርግጠኝነት ስለምጣኔ ሀብት ዕድገቱ ትክክለኛ መረጃ ሊያወጣ ይችላል ወይስ ደግሞ እራሳቸውን ጥሩ አድርገው ለማሳየት በማሰብ አሀዞቹን ከልሰው እና በርዘው በቅጥፈት የተሞሉ መረጃዎችን ሊያቀርቡ ይችላሉ?

የዓለም ባንክ፣ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ሌሎች አበዳሪ እና ለጋሽ ድርጅቶች ለምንድን ነው ስለኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ትንታኔ ለመስጠት እና ዘገባ ለማቅረብ ሲፈልጉ የመረጃ ምንጫቸውን በመንግስት ባለስልጣናት ላይ መሰረት የሚያደርጉት?

ከሁሉም በላይ እነዚህ ዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪ ወትዋቾች ይህችን ደኃ ሀገር በዕዳ ጫና ጉድጓድ ውስጥ እየቀበሩ እነሱ በአዲስ አበባ ውድ ሆቴሎች እየተዘዋወሩ ወድ ምግቦችን እና መጠጦችን ኮኛካቸውን እየተጋቱ ልብወለድ ትረካ የይስሙላ ዘገባ በማቅረብ የግል ፍላጎታቸውን በማስጠበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

አቦ ! ይህንን ሸፍጣችሁን አቁሙ!

እ.ኤ.አ በ2010 በ99.6 በመቶ እና እ.ኤ.አ በ2015 መቶ በመቶ ምርጫን አሸነፍኩ ባለ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አገዛዝ የተሰጠን መረጃ በማመን የቀረበን ዘገባ እውነተኛነት ማመን ይቻላልን?

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ባለስልጣን ኤጀንሲ እና በገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የብሄራዊ ሀብት አካውንት መምሪያ በኢትዮጵያ በዘ-ህወሀት ቁጥጥር ስር ያሉ እና ማንኛውንም አሀዛዊ መረጃ ለመፈለግ እና ለማውጣት ኃላፊነት ያላቸው ድርጅቶች ናቸው በማለት የዓለም ባንክ በኩራት እና ኃለፊነትን የተላበሰ ድርጅት በማስመሰል ዲስኩሩን ሲያሰማ ይደመጣል፡፡

ሆኖም ግን ከላይ የተጠቀሱት አንዳቸውም መንግስታዊ ተቋማት ቢሆኑ አስተማማኝ በሆነ መልኩ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ትንበያን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል እውቀት እና ክህሎት ይቅርና እውነተኛ እና ትክክለኛ የሆነ የምጣኔ ሀብት ጥሬ መረጃን እንኳ ለመሰብሰብ የሚያስችል ምንም ዓይነት አቅም የሌላቸው ናቸው፡፡

ይህ እውነታ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የቡድን መሪ በሆኑት በፓውል ማቲው እ.ኤ.አ መጋቢት 24/2010 የኢትዮጵያን የግማሽ ዓመት የምጣኔ ሀብት አፈጻጸም ግምገማ ካካሄዱ በኋላ እንዲህ የሚል ይፋ የሆነ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡ “የሀገሪቱ የአሀዛዊ መረጃ የመሰብሰብ ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ የሚያሰፈልገው ነው፣ እናም መንግስት ያንን ነገር እንዲያደርግ እንመክራለን“ በማለት እቅጩን ተናግረው ነበር፡፡

ይህ ዴፕሎማሲያዊ አቀራረብ ወደ ተራ ቋንቋ ሲመነዘር የማቲው መግለጫ ዘ-ህወሀት የኢትዮጵያን የምጣኔ ሀብት አፈጻጸም ለመገምገም እና ትንበያ ለመስጠት የሚያስችሉት መረጃዎች ተቀቅለው የወጡ እና ምንም ዓይነት እርባና የሌላቸው በውሸት ላይ ተመስርተው የተዘጋጁ ስለሆነ እነዚህን መረጃዎች መሰረት በማድረግ የምጣኔ ሀብት ትንበያ መስራት ማለት ቆሻሻ አስገብቶ ቆሻሻ ማውጣት/Garbage in Garbage Out (GIGO) ማለት ነው የሚለውን ትክክለኛ ትርጉም ይሰጠናል፡፡

የዓለም ባንክ የዘ-ህወሀትን የመረጃ መሰብሰብ ጉዳይ ለማስጀመር እንኳ 4 ዓመታትን ወስዶበታል፡፡

እ.ኤ.አ ግንቦት 28/2014 በተደረገ በአንድ የፕሮጀክት ማጽደቅ ሰነድ ላይ የዓለም ባንክ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲን አቅም በድርጅታዊ፣ በሰው ኃይል እና በተቋማዊ ደረጃ ለማጎልበት እና አስተማማኝ፣ ተደራሽነት ያለው እና በሚፈለገው ጊዜ መረጃ ማግኘት የሚያስችል ተቋም ለማድረግ በሚል እሳቤ የ10 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብቶ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ መስከረም 4/2014 አይቢኤም/IBM የተባለው የባለሙያዎች ቡድን ስለበርካታ ዓይነት የስታቲስቲክስ መረጃዎች መሰብሰቢያ ዘዴዎች እና ስለሂደታቸው የጽሁፍ ግንኙነትን ጨምሮ ስለተቀናጀ የአይቲ/IT ስርዓት፣ ስለ ቁልፍ የሰው ኃይል የገበያ መረጃ አሰባሰብ እና ትንታኔ አሰጣጥ፣ ስለምግብ፣ ውኃ፣ ስለንጽህና እና የጤና አጠባበቅ ሁኔታ እንዲሁም ስለተንቀሳቃሽ ስልክ እና የቴክኖሎጂ ትንታኔ ሰፋ ያለ የመፍትሄ ሀሳቦችን ለኢትዮጵያ መሪዎች ሰጥቶ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ መስከረም 2015 (“የአይኤምኤፍ ሀገራዊ ዘገባ ቁጥር 15/300/IMF Country Report No. 15/300” ለምሳሌ ከገጽ 4-6፣ ከ22-29 በግርጌ ማስታዋሻ ላይ የቀረበውን ማየት ይቻላል) በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ላይ ባወጣው ዘገባ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሆን ብሎ በድንቁርናው በመግፋት ያንኑ ተመሳሳይ የሆነውን ዘ-ህወሀት እየፈበረከ የሚያወጣውን የስታቲስቲክስ መረጃ እንዳለ በመውሰድ እንዲህ የሚል ዘገባ አቅርቦ ነበር፡ “በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የታተመው የሀገር ውስጥ ምርት/GDP ዘገባ በመሰረቱ በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ባለሙያዎች ለGDP ትንበያ ተብሎ ካዘጋጁት ሰነድ ላይ በመውሰድ መንግስት ካወጣው የምጣኔ ሀብት ዕድገት ያነሰ እና በብሄራዊ አካውንት መረጃ ላይ (አንቀጽ 45ን ይመልከቱ) ተለይተው በግልጽ የተቀመጡ ድክመቶችን  ባካተተ መልኩ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው“ ይላል፡፡

ስለመረጃ ጥራት በቂነት ሲያደርገው በነበረው ፍተሻ የዘ-ህወሀት ይፋ የሆኑ ምንጮች የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዘገባ ቁጥር 15/300 .. ነሐሴ 26/2015 (ገጽ 8) ላይ እንዲህ በማለት በግልጽ አስቀምጦታል፡

አጠቃላይ፡ በምርመራ ስራው ላይ ችግርን ሊፈጥር የሚችል የመረጃ አቅርቦት ችግር ተስተውሏል…

የመንግስት የፋይናንስ ስታቲስቲክስ፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሻሻሎች እየታዩ ያሉ ቢሆንም የመንግስት የፊስካል ስታቲስቲክስ በሽፋን በኩል በጉድለት የሚጠቃ መሆኑ እንደቀጠለ ነው…

ሞኒተሪ ስታቲስቲክስ፡ የንግድ ባንኮች የሞኒተሪ መረጃ ጥናት ለበርካታ መሻሻሎች የተጋለጠ ነው…

ፋይናንሻል ስታቲስቲክስ፡ ስለፋይናንስ ክፍለ ኢከኖሚው ያለው የመረጃ ክፍተት ስለፋይናንስ ክፍለ ኢኮኖሚው ጤንነት ጥልቀት ያለው ጥናትን ለማከናውን የሚያስችል አይደለም…

የገቢ ወጭ ክፍያ ንጽጽር/balance of payment: የገቢ ወጭ ክፍያ ንጽጽር መረጃን በተመለከተ የሽፋን፣  የዋጋ ግመታን፣ የጊዜ እና የከረንት አካውንት ግብዮቶች መሻሻልን ይጠይቃል…በኢትዮጵያ ውስጥ የፈሰሰውን መዋዕለ ንዋይ ለማረጋገጥ እና ድንበርን ተሻግረው ከሚገቡ የግል ድርጅቶች ካፒታል ጋር  ያለውን ተዛምዶ ለማጠናከር ገላጭ የሆነ ጥናት ሊደረግ ይገባል፡፡

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ በርካታ የሆኑ ጉድለቶች ባሉበት እና የመረጃ ክፍተት ተንሰራፍቶ በሚገኝበት ሁኔታ እ.ኤ.አ በ2015 በፋይናንስ ክፍለ ኢኮኖሚው እና በሞኒተሪው ላይ ጥልቀት ያለው ጥናት በማካሄድ ከፍተኛ የሆነ መሻሻል ይኖርበታል ለማለት የሚያስችል እንደምታ እንዲኖረው የሚያስችለው፣ ወዘተ በምን ዓይነት ሁኔታ ነው?

በኮምፒውተር የመግባቢያ ኮዶች ላይ በሚገኙት ነገሮች ላይ ብቻ መሰረት በማድረግ ስለምጣኔ ሀብት ሞዴሎች ሊያሳምኑን ይችላሉን? (ሊያታልሉን አላልኩም፡፡)

ቀላሉ እና ምንም ዓይነት አወዛጋቢ ያልሆነው እውነታ ግን በዓለም ባንክ፣ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና በሌሎች በሁሉም በዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪ ወትዋቾች እያጋነኑ የሚያቀርቧቸውን የውሸት መረጃዎች ለመደገፍ እና እንደሮኬት እየተተኮሰ ነው እያሉ ሌት ቀን ለሚለፈልፉለት የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ዕድገት እና ቁልፍ የሆኑ የምጣኔ ሀብት ክፍለ ኢኮኖሚዎች የዕድገት ሁኔታ ታዋቂ ሆኗል በማለት የሚናገሩት በዘህወሀት ዋና አድራጊ ፈጣሪ ባለስልጣኖች ቀጥተኛ ትዕዛዝ እና ቁጥጥር ስር በብቸኝነት ተጠርንፎ ተይዞ በሚገኘው በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ባለስልጣን የመረጃ መቀቀያ ቶፋ ውስጥ (ከጥቂት ግምቶች በስተቀር) የሚሰበሰበውን፣ የሚከተፈውን፣ የሚቆራረጠውን፣ የሚቀመመውን፣ ለብለብ የሚደረገውን፣ በጣም የሚጠበሰውን፣ በመካከለኛ ደረጃ የሚጠበሰውን፣ የሚቀቀለውን እና እንዲጣፍጥ ለማድረግ የሚሞከረውን የቅጥፈት መረጃ መሰረት በማድረግ ነው፡፡

እስቲ ባጭሩ ወደኋላ መለስ ብለን ጥቂት እንመልከት!

እ.ኤ.አ ወደኋላ 2008 መለስ ብለን ስንመለከት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በዘ-ህወሀት የስታቲስቲክስ ቢሮ የዘ-ህወሀትን የምጣኔ ሀብቱን ዕድገት ለማወደስ እና የተፈበረኩትን እና አስተማማኝ ያልሆኑትን እርባናየለሽ መረጃዎች  በማጽደቅ በማሰብ የፌዝ ቀልዱን አከናወነ፡፡

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሀገራዊ ዘገባ (ኢትዮጵያ) ቁጥር 08/264 (እ.ኤ.አ በ2008) የተዘጋጀው እንዲህ በማለት መግለጫውን አውጥቷል፡

“ዓመታዊ አማካይ የምጣኔ ሀብት ዕድገቱ እ.ኤ.አ ከ2003/04 ጀምሮ በ11 በመቶ እድገት በማስመዝገብ ፈጣን እና ዘላቂነት ያለው የልማት ፕሮግራም/Program for Accelerated and Sustainable Development (PADEP) በትንሹ ተይዞ ከነበረው የ7 በመቶ ዕቅድ በእጅጉ በመብለጥ ከፍተኛ ዕድገት ያስመዘገበበ በመሆኑ የሚሊኒየሙን የልማት ግቦች በአስተማማኝነት ሁኔታ የሚደርስበት መሆኑን ያመላክታል“ በማለት ዘገባውን አቅርቧል፡፡

በዚያ በቀረበው ዘገባ የግርጌ ማስታዋሻዎች ላይ ከገጽ 20-24 11 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበው የምጣኔ ሀብት ዕድገት የመረጃ ምንጩ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ወይም ደግሞ የሌላ በገለልተኝነት የሚሰራ ድርጅት የተሰበሰበ እና የተተነተነ መረጃ ሳይሆን ያው የተለመደው የዘህወሀት ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ /ቤት መረጃ መሆኑን በመግለጽ ምንጩን ሲገልጽ እንዲህ ይላል

“ምንጭ፡ የኢትዮጵያ ባለስልጣኖች፣ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ግምት እና ትንበያዎች፡፡“

እንደዚሁም ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ለባንክ ስራ ውጤታማነት የፋይናንሻል አመልካቾች/Financial Soundness Indicators for Banking የመረጃ ምንጭ ሆኖ ያገለገለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የስሌት ስራዎች ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ የ2013 የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዘገባ (የአይኤምኤፍ ሀገራዊ ዘገባ ቁጥር 13/308/IMF Country Report NO. 13/308 ከላይ ከተጠቀሰው የተለየ አይደለም፡፡

እ.ኤ.አ በ2013 ለተዘጋጀው ዘገባ መረጃው የመጣው ያው በተለመደው መልኩ ከዘሀዋሃት  ባለስልጣኖች እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች የትንበያ ስሌት ነው፡፡ (ለምሳሌ ከገጽ 9-10፣ 17፣ ከ32-37 የተመለከቱትን ይመልከቱ፡፡)

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት እ.ኤ.አ በ2012/13 ከነበረበት ከ8.5 በመቶ ዕድገት እ.ኤ.አ በ2013 በመቀነስ የ6.5 በመቶ ዕድገትን አስመዘግቧል የሚል ዘገባ አቅርቦ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ በ2012 የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እንዲህ የሚል ዘገባ አቅርቦ ነበር፣ “የዋጋ ግሽበት ከፍተኛ እንደሆነ ቢቀጥልም (እ.ኤ.አ በ2012/13 መጨረሻ ላይ 21 በመቶ በመሆን)  ትክክለኛው የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት/real GDP growth አሁን ባለው የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ መሰረት እ.ኤ.አ በ2011/12 ወደ 7 በመቶ ያህል ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ ተተንብዮ የነበረው እና በቀጣዮቹ ተከታታይ ዓመታት ወደ 6.5 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባል“  የሚል ዘገባ አውጥቶ ነበር፡፡

የዘ-ህወሀት ፖሊሲዎች እስከ አሁንም ድረስ ምንም አልተለወጡም፣ ስለሆነም በቀጣዮችም ተከታታይ ዓመታት የምጣኔ ሀብት ዕድገቱ 6.5 በመቶ እየቀነሰ እንደሚሄድ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ መገመት እንችላለን፡፡

እንደ ዓለም ባንክ ደግሞ ይህ አይደለም!

እ.ኤ.አ ህዳር 2015 “የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ” በሚል ርዕስ የዓለም ባንክ ባወጣው ዘገባ መሰረት በዘ-ህወሀት አገዛዝ ቁጥጥር ስር ያለችው ኢትዮጵያ ባለፉት አስርት ዓመታት 11 በመቶ አመታዊ አማካይ ዕድገት (ይቅርታ 10.9 በመቶ ማለቴ ነው) አስመዝግባለች በማለት የዓለም ባንክ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡

በዓለም ባንክ እየተካሄደ ያለ ምን ዓይነት የማጭበርበር ስራ ነው እባካችሁ!

የዓለም ባንክን ውሸት፣ እርባናየለሽ ቅጥፈት፣ እና ተራ የቁጥር ጨዋታ የማታለል ቅጥፈት እስከ አሁን ድረስ እየተከታተልኩ በማጋለጥ ላይ የቆየሁ መሆኔን የረዥም ጊዜ አንባቢዎቼ ይገነዘባሉ፡፡ (እባካችሁ በዓለም ባንክ ተራ ቅጥፈት እና ውሸት ላይ ብዕራቸውን መዝዘው እየተቃወሙ ያሉ ኢትዮጵያውያን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የት እንደሚገኙ እንዳትጠይቁኝ፡፡)

እ.ኤ.አ ጥር 2015 “በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ኪሳራ“ በሚል ርዕስ ስለዘ-ህወሀት የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስኬት የዓለም ባንክ እየለቀቀው ያለውን ቅጥፈት እና በምዕራብ ኢትዮጵጵያ በጋምቤላ ህዝቦች ላይ እየተፈጸመ ያለውን የማፈናቀል፣ የማስወገድ፣ አስገድዶ የማስፈር እና የዘር ማጥፋት ዓይነት ሁኔታ እየተካሄደ እንዳለ ግልጽ በሆነ መልኩ “የማጭበርበር ጨዋታዎች” እየተካሄዱ እንዳሉ በማጋለጥ ትችት በማቅረብ በግንኙነት ድረ ገጽ ላይ እንዲታተም አድርጌ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ የካቲት 2/2015 “የዓለም ባንክ እና የኢትዮጵያ የዕድገት እና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ“ በሚል ርእስ ብድር እና ልማትን መሰረት ያደረገ አካሄድን (ካለው ተጨባጭ እውነታ ተጻራሪ በሆነ መልኩ) ዘ-ህወሀት እና የእራሱ አድናቂዎች እንዲሁም  ለጋሽ  እና ሌሎች አበዳሪ ድርጅቶች ዋና እና ወሳኝ ሚና በመጫወታቸው በአንድ ወቅት የረሀብ ተጠቂ የነበረችን ሀገር አንጸባራቂ የሆነ ከድህነት ማጥ ውስጥ መንጥቆ በማውጣት ታላቅ ስራን ሰርቷል በማለት የዓለም ባንክ ዘ-ህወሀት ጥበብን በተላበሰ መልኩ የኢትዮጵያን የምጣኔ ሀብት አሳድጓል በማለት የቀረበውን ተራ ቅጥፈት እና ዓይን ያወጣ ውሸት አጋልጫለሁ፡፡

እ.ኤ.አ የካቲት 8/2015 “የኢትዮጵያ አስከፊው ዕዳ በአስከፊው የዓለም ባንክ በሚል ርዕስ“ ትችት በማዘጋጀት በድረገ ገጽ ላይ እንዲታተም አድርጌ ነበር፡፡ አስከፊ ዕዳ ለህዝቡ ጥቅም እና ፍላጎት ዓላማ ሳይሆን ህጋዊ ያልሆነ ብሄራዊ ዕዳ ስለሆነ የባለዕዳው ሀገር ህዝብ ከህግ አንጻር ይህንን ዓይነት ዕዳ የመክፈል ግዴታ እንደሌለበት ግልጽ አድርጌ ነበር፡፡

በዚያ ትችቴ ላይ እንዲህ የሚል ጥያቄ ጠይቄ ነበር፡ “የኢትዮጵያ ህዝቦች በዘ-ህወሀት ለዓመታት የተጠራቀመውን የዓለም ባንክ አስከፊ ዕዳ ለመክፈል ኃላፊነት ሊኖርባቸው ይችላልን፡፡”

እንደዚሁም ሁሉ ለጥያቄው እኔው እራሴ እንዲህ የሚል መልስ ሰጥቸ ነበር፡ ይህን ማድረግ ግፍ እና መከራ ነው፡፡ በፍጹም! ገሃነም ለምን አይወርዱም ራሳቸው !

የዓለም ባንክን ተራ ውሸት፣ ቅጥፈት እና የማታለል የቁጥር ጨዋታዎችን በየጊዛዜው እየጻፍኩ ያጋለጥኩባቸውን ሁሉንም ትችቶቼን ለማቅረብ አልፈልግም፡፡ ሁሉም ትችቶቼ almariam.com በሚለው ድረገ ገጽ ላይ ስለሚገኙ ከዚያ መመልከት ይቻላል፡፡

የዓለም ባንክን ቅጥፈት ብቻ አይደለም እያጋለጥኩ ያለሁት ሆኖም ግን የእነርሱን ተመጽዋች ለማኝ ሎሌ የሆነውን ዘ-ህወሀትን ጭምር እንጅ፡፡

እ.ኤ.አ ሰኔ 2010 “የመለስ ዜናዊ ምዕናባዊ ኢኮኖሚ“ በሚል ርዕስ 12 በመቶ ዓመታዊ የምጣኔ ሀብት ዕድገት አስመዝግቢያለሁ እያለ ቡራ ከረዬ በማለት ተራ ቅትፈቱን ሲያሰራጭ የነበረውን እና አሁን በህይወት የሌለውን መለስ ዜናዊን የበሬ ወለደ (መለስ የምጣኔ ሀብት ዕድገትን ወለደ አላልኩም) ውሸት በማጋለጥ የሰላ ትችት በማቅረብ ሞግቼ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ሰኔ 2011 “የመለስ ዜናዊ የቅትፈት ኢኮኖሚክስ“ በሚል ርዕስ የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽኑን ዕቅድ በባህር ሀረጎች፣ መፈክሮች፣ የማተለያ ቃላት፣ መሰረተቢስ መድረክ፣ በትርጉመቢስ ድግግሞሽ፣ እና በአስመሳይ እና ሸንጋይ ቃላት ላይ የተንሳፈፈ ዕቅድ ነው በማለት በጽኑ አጋልጨ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ መጋቢት 2009 አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ዕድገት በ12..8 በመቶ ያድጋል በማለት የቦስጥ ዲስኩር አሰምቶ ነበር፡፡

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በዚያው በተመሳሳይ ወር በወቅቱ ዓለም አቀፋዊ የምጣኔ ሀብት ቀውስ በመኖሩ ምክንያት ኢትዮጵያ 6 በመቶ ዓመታዊ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ብቻ ታስመዘግባለች በማለት ከመለስ ጋር የማይስማማ መሆኑን ግልጽ አድርጓል፡፡

መለስ ዜናዊ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ያቀረቡትን ልዩነት ሙልጭ አድርጎ በመካድ እንዲህ የሚል መግለጫ ሰጥቶ ነበር፡

ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር በምጣኔ ሀብት ትንበያችን ላይ ብቻ ልዩነት አለን፣ ሆኖም ግን በእያንዳንዱ ዓመት መጨረሻ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ ተመሳሳይ የሆነ ስምምነት አለን በማለት ምንጊዜም ዕድገት በመኖሩ ላይ የሚስማሙ መሆኑን በመግለጽ ልዩነታቸው ግን በምን ያህል የምጣኔ ሀብት አሀዝ እድገት እንደተመዘገበ ከመግለጹ ላይ እንደነበር ጠቁሞ ነበር፡፡

ይህም ማለት ምንም ቢያንስ እንኳ ዕድገት አለ በማለት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከመሰከሩልኝም አንድ ስኬት ነው በሚል ስሌት ነው እንግዲህ ከስሌት ቁጥሩ ላይ እንጅ ዕድገት ስለመኖሩ ስምምነት አለን በማለት ተደጋጋሚ ዲስኩሮችን ሲያሰማ የነበረው፡፡

ሆኖም ግን ሊቀርብ የሚችለው ጥያቄ እንዲህ የሚል ይሆናል፡ በእርግጥ የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ባለፉት አስርት ተከታታይ ዓመታት ጊዜ ውስጥ በየዓመቱ በአማካይ በ10.9 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧልን? የሚል ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ታላቁ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ግስጋሴ፡ ቆሻሻ ማስገባት ቆሻሻ ማስወጣት፣

በቅርብ ጊዜ የዓለም ባንክ ያወጣው የኢትዮጵያ ታላቁ ግስጋሴ ዘገባ ቆሻሻ መረጃን በማስገባት እና የዚህኑ ስሌት ቆሻሻ በማስወጣት የተዘጋጀ እና አሁን በህይወት የሌለውን የመለስ ዜናዊን አባባል በመዋስ ወደ ቅርጫት መጣል ያለበት ፋይዳየለሽ ዘገባ ነው፡፡

“የኢትዮጵያ ታላቁ የምጣኔ ሀብት የዕድገት ግስጋሴ” በአዲስ አበባ በየዓመቱ ከሚደረገው “ከታላቁ ሩጫ” ጋር በተመሳስሎ ይቀርባል፡፡

እ.ኤ.አ ህዳር 29/2006 ልክ ከዛሬ 6 ዓመታት በፊት “የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ ለነጻነት” በሚል ርዕስ በዚያን ዓመት ስለተደረገው የኢትዮጵያ ዓመታዊ ታላቁ ሩጫ ትችት ጽፌ ነበር፡፡

በዚያ ባቀረብኩት ትችቴ “የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ” ለነጻነት የሚደረግ የኢትዮጵያ ታላቅ ሩጫ ነው በማለት የክርክር ጭብጤን  አቅርቤ ነበር፡፡

ያ ሩጫ በመሰረቱ የህዝባዊ እምቢተኝነትን ድርጊት ስውር በሆነ መልኩ ሊገልጽ የሚችል ዓመታዊ ክስተት እንደሆነ ተናግሬ ነበር፡፡ አብዛኞቹ ለነጻነት የሚሮጡ ብቻ አልነበሩም ሆኖም ግን በዘ-ህወሀት ከሚፈጸመው ከጭቆና እና ከአምባገነንነት፣ ከዕምነትየለሽ እና ከተስፋቢስነት እንዲሁም ከየዕለታዊ የህይወት ክብር እና ውርደት ለማምለጥ የሚደረግ ሩጫ ጭምርም ነው ብዬ ነበር፡፡

የዓለም ባንክ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ግስጋሴ እያለ የሚጠራውን ከታላቁ ሩጫ ጋር በማመሳሰል ዘ-ህወሀት በምጣኔ ሀብት ዕድገቱ ድል የተቀዳጀ መሆኑን ለመግለጽ የሚፈልግ መሆኑን ሀሳብ ያቀርባል፡፡

የዓለም ባንክ ዘገባ እንዲህ የሚሉ ሁለት ዋና ዋና ጥያቄዎችን ለመመለስ የተዘጋጀ ነው፡

1) የኢትዮጵያ ፈጣን የምጣኔ ሀብት ዕድገት የሚገለጸው በምንድን ነው? 

2) የምጣኔ ሀብት ዕድገቱ ዘላቂነት ሊሆን የማይችለው እንዴት ነው?

በዚህም መሰረት የዓለም ባንክ እንዲህ በማለት አስተያየቱን ግልጽ አድርጓል፡

የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ባለፉት አስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በጣም ፈጣን እና ዘላቂነት ያለው ነበር፡፡ ፈጣን የምጣኔ ሀብት ዕድገት የጀመረው እ.ኤ.አ ከ1992 ጀምሮ ሲሆን በከፍተኛ ደረጃ ማርሹን በመቀየር ዕድገት በማስመዝገብ ወደላቀ ደረጃ የተሸጋገረው እ.ኤ.አ በ2004 ነው፡፡ በቅርቡ እየታዬ ያለው ፈጣን የምጣኔ ሀብት ዕድገት የአጠቃላይ የምጣኔ ሀብቱ ዕድገት አንዱ አካል እና ሀገሪቱ የተሳካ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ልምድ እያሳካች መሆኑን በግልጽ ያመላክታል፡፡ የምጣኔ ሀብት ዕድገቱ በአገልግሎት እና በግብርናው ዘርፎች የምርት አቅርቦቶች እና በግል የፍጆታ እና የመዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ፍላጎቶች ላይ ተከማችቶ ይገኛል፡፡ “

ዕድገቱ በዘርፍ ተነጣጥሎ ሲታይ ከፍተኛ የሆነ የግብዓቶች ምርታማነት እና የመዋቅራዊ ሽግግርን/factor productivity and structural change ድርሻ እንዳለው በግልጽ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያ ለስኬት የሚያበቃውን የምጣኔ ሀብት ስትራቴጂ ጨምሮ በርካታ የተለያዩ በርካታ የምጣኔ ሀብት የዕድገት መንገዶችን ትጠቀማለች፡፡

የተለያዩ የገንዘብ ማግኛ ዘዴዎች በዓለም ላይ አንዱ እና ከፍተኛ የሆነውን የመንግስት መዋዕለ ንዋይ የማፍሰስ ዕድገት መጣኔ ስልትን ይደግፋል፡፡

የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ስትራቴጂ ከየትኛውም ሀገር ልዩ የሆነ ነገር ነበር፡፡

የምጣኔ ሀብት ዕድገቱ በዋናነት ትኩረት አድርጎ የተንቀሳቀሰው በመዋቅራዊ ሽግግር መሻሻል ላይ ነበር፡፡

የመንግስት የመሰረተ ልማት የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት በተገደበ የመንግስት የፍጆታ ወጭ ስሌት መሰረት ላይ ትኩረት ያደረገ ዋና የመዋቅራዊ ለውጥ ዕድገት ማሳያ አንቀሳቃሽ ሞተር ነበር፡፡

ከፍተኛ የሆነ የመሰረተ ልማት መዋዕለ ንዋይ ፍሰት ድርሻ የታየው በመሰረተ ልማት ግንባታ እና ከዚህ ጋር ተያይዞ ከሚገኘው ጠቀሜታ አንጻር የሚመነጭ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ፈጣን የምጣኔ ሀብት ዕድገት በህዝብ የውልደት መጠን አዎንታዊ ድጋፍም የታጀበ ነበር፡፡

ከፍተኛ የግብርና ምርት ውጤት የተገኘው ምርትን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ እና የሚታረሰውን የመሬት መጠን በመጨመር ነበር፡፡

ለግብርና ምርት ዕድገት መጨመር ዋና ዋና ምክንያቶች የኤክስቴንሽን ስራዎችን በተቀላጠፈ መልኩ በመስራት እና ለአርሶ አደሮች ተገቢውን ትምህርት መስጠትን ያካተተ ነበር፡፡

በቅርቡ የተገኘው የግብርና ምርት ዕድገት በዋናነት መንግስት በኤክስቴንሽን ስራዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰሱ፣ መንገዶችን በመገንባቱ እና ለአርሶ አደሩም ተገቢው ትምህርት እንዲሰጥ በማድረጉ ምክንያት ነው፡፡”

ዘገባው የሚከተሉትን ያካትታል፡

“ላለፉት አስርት ዓመታት የተመዘገበውን ባለሁለት አሀዝ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ተከትሎ የሩቅ ምስራቅ ሀገሮችን የምጣኔ ሀብት ዕድገት ስትራቴጂ የቻይናን ጨምሮ በስራ ላይ የዋለ ከመሆኑ አንጻር ባለፈው ጊዜ በስኬታማነት ጎዳና ያስኬደውን የምጣኔ ሀብት ዕድገት ተሞክሮ በመከተል ዕድገቱ ቀጣይነት እና ዘላቂነት ያለው ሊደረግ ይገባል፡፡“

ምን ዓይነት ግራ የሚያጋባ ቅትፈት ነው እባካችሁ!!!

እስቲ በዓለም ባንክ ዘገባ ላይ ስለቀረበው ስለግብርና ዕድገት አንድ ወይም ሁለት ነገሮችን ልበል፡፡

እ.ኤ.አ በ2010 አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ህዝብ በቀን ሶስት ጊዜ መመገብ ከቻለ የእርሱ መንግስት ስኬታማነት የሚለካው በዚህ ነው በማለት አውጆ ነበር፡፡

ያልተሳሳትኩ ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ ምግብ የሚገኘው ከግብርና ምርት ነው፡፡

ይቅርታ! ከዓለም አቀፍ የእርጥባን ልመና ማለቴ ነው፡፡

እ.ኤ.አ ህዳር 2015 የተባበሩት መንግስታት 15 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ዓለም አቀፉ የምግብ እርዳታ ካልደረሰላቸው እና ዕርዳታ የማቅረቡ ሁኔታ በአስቸኳይ ተግባራዊ ካልሆነ በስተቀር በምግብ እህል እጦት ምክንያት ለአስከፊ አደጋ ይጋለጣሉ የሚል ማስጠንቀቂያ አውጥቷል፡፡

እ.ኤ.አ የካቲት 2014 ኢትዮጵያ 2..7 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎቿን ለመመገብ ወሳኝ በሆነ መልኩ የለጋሽ ድርጅቶችን እርዳታ ትሻለች የሚል ዘገባ ወጥቶ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2014 በቀረበው ዘገባ እ.ኤ.አ በ2013 የበጀት ዓመት 231 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቷል የሚል ዘገባ የቀረበ ቢሆንም እንኳ በዚሁ ጊዜ ከ2..7 ሚሊዮን ያላነሰ እርዳታ ፈላጊ ህዝብ እንደነበር በዘገባው ግልጽ ተደርጓል፡፡

እ.ኤ.አ መስከረም 2012 “የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ወር 3.7 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች በዚሁ ዓመት በነሐሴ እና በታህሳስ መካከል እና በጥር ደግሞ 3.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ሰብአዊ እርዳታ ይፈልጋሉ“  የሚል ዘገባ ቀርቦ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ በ2011 ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሰብአዊ እርዳታ አብዛኛው ከዩኤስ ኤሜሪካ የሆነ ወደ 500 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ እርዳታ ቀርቦ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ነሐሴ 2010 የተባበሩት መንግስታት የግብርና እና የምግብ ድርጅት “ወደ 5.2 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን እስከ አሁን ድረስ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ጥገኛ ናቸው፡፡ ይህም ሆኖ በረዥሙ ዕቅድ ደግሞ ሁኔታው እንዲቀየር ካልተደረገ በስተቀር ወደ ከፍተኛ ረሀብነት በመቀየር ሁኔታውን የከፋ ያደርገዋል የሚል ስምምነት በድርጅቶች መካከል ተደርሷል“ የሚል ዘገባ ቀርቦ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ነሐሴ 2009 “በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ያጡ የነጡ ኢትዮጵያውን ድሆች አስከፊ የሆነ የምግብ ንጥረ ነገር እጥረት እና የረሀብ አደጋ እንዳጋጠማቸው እና ይህም ባለፉት አስርት ዓመታት ከታየው በአስከፊነቱ የመጀመሪያውን ደረጃ ይይዛል፡፡ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ብዛት ግምት በዚህ ዓመት በጥር ወር ላይ ከነበረው ከ4.9 ሚሊዮን ተረጅ ከግንቦት እስከ ሰኔ ባሉት ወራት ውስጥ ቁጥሩ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመሄድ ወደ 6.2 ሚሊሆን ይደርሳል“ የሚል ዘገባ ቀርቦ ነበር፡፡

የዓለም ባንክ ስለዘ-ህወሀት የግብርና ምርት ዕድገት የተምታታ፣ ተያያዥነት የሌለው እና ኃላፊነት የጎደለው ዲስኩር በማሰማት ላይ ይገኛል፡፡

እንደተባበሩት መንግስታት ዘገባ .. 2016 መጀመሪያ ላይ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያሉ 15 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የዓለም ባንክ ግንዛቤው አለውን?

እስከ አሁን ሳቀርበው ከቆየሁት ማገናዘቢያ ማስረጃ ከዚህም በላይ ብጨምር አስፈላጊ ሊሆን ይችላልን?

ለዓለም ባንክ፣ ለዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ለሌሎች ለዘ-ህወሀት የሚያቃጥሩ ለሁሉም ዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪ ወትዋቾች የአንድ ሰው መሞት ለእነርሱ አሰቃቂ ነው፡፡ ሆኖም ግን መከላከል ለሚቻለው እና አስከፊ በሆነው ረሀብ የ15 ሚሊዮን ዜጎች ሞት የቁጥር ጉዳይ ብቻ ነው፡፡

አሁን ደረስኩበት! የዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪ ወትዋቾች ለዘ-ህወሀት ምን ለመስራት እንደሚሞክሩ በሚገባ አውቃለሁ፡፡

ዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪ ወትዋቾች ዘ-ህወሀት በስልጣን ኮርቻ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ እንዲቆይ ይፈልጋሉ ምክንያቱም ዘ-ህወሀት በኢትዮጵያ ቢዝነስን ለእነርሱ ጥሩ አድርጎ እንደሚሰራላቸው ይገነዘባሉና፡፡

ዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪ ወትዋቾች በኢትዮጵያ ውስጥ መልካም ነገርን እንደሰሩ እና በድህነት ውስጥ የነበሩትን ዜጎች ከድህነት እንዳላቀቁ እና ኑሯቸውም እንዲሻሻል እንዲሁም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ከረሀብ አስከፊ አደጋ እንዳላቀቁ አድርገው ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለመናገር ይፈልጋሉ፡፡

ታማዕኒነት የሌለው የምጣኔ ሀብት ዕድገት እንደሌለ በዓለም ባንክ እና በሌሎችም የድህነት አቃጣሪ ወትዋቾች በተጨባጭ የተደረገ የማረጋገጥ እርምጃ ያልታየ የሌለ ቢሆንም ቅሉ በዘ-ህወሀት የተዛባ አገዛዝ እና ፖሊሲ ምክንያት በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውን ዜጎች በየጊዜው ለረሀብ ሰለባ እየተጋለጡ በመሞት እና በመሰቃት ላይ ይገኛሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን ስራ አጥ በመሆን እና በቀቢጸ ተስፋነት ህይወትን በመግፋት ላይ ይገኛሉ፡፡

ይፋ የሆነ የስራ አጥ መጣኔ አሀዝ እስከ አሁን ድረስ የለም ሆኖም ግን ጥቂት ባለሙያዎች እንደሚያስቡት የወጣት ስራ መጣኔው እስከ 70 በመቶ እንደሚደርስ ግምታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ይኸ ነገር እ.ኤ.አ በ2007 ትክክል መሆኑ ታይቷል፣ አሁንም ቢሆን እውነት ነው፡፡ እውነታው ፍርጥ እና ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ግን በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት የሌለ የመሆኑ እና የዜጎች የሰብአዊ መብት ድፍጠጣም ከምንጊዜውም በላይ ተስፋፍቶ እና ተጠናክሮ የመገኘቱ ሁኔታ ነው!

የዓለም ባንክ በዘ-ህወሀት መልካም አስተዳደራዊ ብቃት በኢትዮጵያ ፈጣን የምጣኔ ሀብት ዕድገት ለማስመዝገብ ተችሏል በማለት የእራሱን ሀሳብ በማራመድ መብቱ ላይ ምንም ዓይነት የመቃወም መብት እንደሌለኝ ከጥርጣሬ ውስጥ አልገባም፡፡

ሆኖም ግን የዓለም ባንክ በምንም ዓይነት መልኩ የእራሱን እውነታ በመፍጠር እና በመፈብረክ በጠራራ ጸሐይ በአደባባይ የህዝብን ድምጽ እየዘረፉ ምርጫውን መቶ በመቶ አሸንፈናል እያሉ በሚቀላምዱ ፈጣጣ የደናቁርት ስብስቦች እውነት እንደሆነ አድርጎ የማቅረብ መብት በፍጹም የለውም፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ከሌሎች ሸፍጠኞች ጋር ህብረት በመፍጠር በቀጣፊዎች የተፈበረከውን የምጣኔ ሀብት የትንበያ ቅጥፈት (እነርሱ ግምት እያሉ የሚጠሩት) እንደ እውነት አድርጎ የማቅረብ መብት በፍጹም የለውም፡፡ ከዚህም በላይ በተቋማዊ የተከባሪነት የአስመሳይነት ካባን ተከናንቦ የሚያቀረሸውን ክፋቱን በተሰላቹ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ የመትፋት መብት በፍጹም የለውም፡፡

ዘ-ህወሀት ባለፉት አስርት ዓመታት ባለሁለት አሀዝ የምጣኔ ሀብት ዕድገት አስመዘገበም አላስመዘገበም ይህ ድርጊት የተራ ምኞት አስተሳሰብ ጉዳይ አይደለም፣ እንደዚሁም ደግሞ ለህዝብ ግንኙነት የፕሮፓጋንዳ ስራ ሲባል በዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪ ወትዋቾች የሚዘላበድ የቅጥፈት አሀዝ ድርደራ ሊሆን አይችልም፡፡

ይኸ ጉዳይ የማስረጃ ጉዳይ ነው፡ የትክክለኛነት፣ የምሉዕነት፣ የአስተማማኝነት እና በጥንቃቄ የተሰበሰቡ፣ የተተነተኑ እና የተረጋገጡ የአጠቃላይ የስታቲስቲካዊ አሀዞች የማስረጃ ጉዳይ ነው፡፡

እንደዚህ ዓይነቱ ማስረጃ ዝም ብሎ የሚፈበረክ፣ የሚመረት፣ ቅንነት በጎደለው መልኩ የሚሰጥ፣ አዲስ ቅልቅልን ለማምጣት ተብሎ የሚፈጠር ወይም ደግሞ ከአጠቃላይ ብትን ጣቃ ጨርቅ ላይ ለዘ-ህወሀት፣ ለዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት፣ ለዓለም ባንክ ወይም ደግሞ ለሌሎች ቅዱስ ላልሆኑት የዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪ ወትዋቾች ተብሎ ተቆርጦ የሚሰጥ እራፊ/ቁራጭ ጨርቅ አይደለም፡፡

በአእምሮ በሽተኛ መሪዎቻ  ምክንያት ኢትዮጵያ በአስከፊ ችግር ውስጥ ወድቃ ትገኛለች፡፡ ዘኢኮኖሚስት መጽሔት

ዘኢኮኖሚስት መጽሔት እ.ኤ.አ ግንቦት 2015 “አጭር ፈጣን ወይም የማራቶን ያልሆነ ሩጫ“ በሚል ርዕስ እንዲህ የሚል ጽሁፍ አዘጋጅቶ ነበር፡

በየካቲት ወር አዲስ የቻይና አምባሳደር አዲስ አበባ ከተማ በደረሰ ጊዜ ለተቀባዮቹ ያልተጠበቀ እና አስቀያሚ የሆነ መልዕክት አስተላለፈ፡፡ ላይፋን ለአገዛዙ ምሁራን በጽኑ ዝግ በነበረ የውይይት መድረክ ላይ በመገኘት ቀደም ሲል ስታራምዱት የነበረውን የብቸኝነት ፖሊሲ አውልቃችሁ ጣሉት፣ እናም በአሁኑ ወቅት ገንዘብ እና መረጃ አሁንም ገደብ የሚጣልበትን አዲስ አይነት አሰራር ተግባራዊነት ክፍት በማድረግ ተንቀሳቀሱ፡፡ የባንክ እና የቴሌኮም ስራዎች ፋሽንነታቸው ያለፈበት ሁኔታ ነው፡፡  (ሠንጠረዡን ይመልከቱ)፡፡ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ተስፋ እየቆረጡ ናቸው፡፡ ንግድ ከሚጠበቀው በላይ ወደኋላ ቀርቷል፡፡ መንግስትን ለበርካታ ዓመታት ያህል በማሞገስ ከቆዩ በኋላ ቻይናዎች በአሁኑ ጊዜ እንደ ምዕራቡ ዓለም ያሉ ትችቶችን በኢትዮጵያ ላይ ማዥጎድጎድ ጀመሩ፡፡

…  ችግሩ በአብዛኛው በኢትዮጵያ መንግስት፣ በገዥው ፓርቲ እና በደህንነት መዋቅሩ ድፍረት የማጣት ጉዳይ ነው… በኃይል ከስልጣን እንወገዳለን የሚለው የምሁራኑ ፍርሀት መሻሻል እንዳይኖር ደንታቢስነትን ማራመድ መርጠዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 መለስ ዜናዊ ከሞተበት ጊዜ በኋላ ምንም የተሻሻለ ነገር አይታም… ያኔ በግለሰባዊ ጫና፣ በምሁራዊ እና በትስስር ጦርነት ስርዓቱን አልፎ አልፎ ወደፊት ያስኬደው ነበር፡፡ ሆኖም ግን የግል ዘርፉን እና የሲቪል ማህበረሰቡን ጥምድ አድርጎ ጠላው፡፡ ያም ሆኖ ግን ቢያንስ አደናቃፊ የሆኑትን የጎርፍ ግንዲላዎች ያስወግድ ነበር…

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እንደ መለስ አይደለም…በአሁኑ ጊዜ ሚኒስትሮች ውሳኔ ከማሳለፋቸው በፊት አብዛኛውን ጊዜ የአሮጌውን ጠባቂ የስውር አመራር ዘበኛ ስምምነት ይጠይቃሉ፡፡ እናም ዘርን መሰረት አድርገው የተነሱት እና መለስም አንዱ የነበረበት ትግራውያን እስከ አሁንም ድረስ የጦር ኃይሉን፣ የደህንነተ አገልግሎቱን፣ የቴሌኮሙን እና የውጭ ጉዳይን ሙሉ በሙሉ በብቸኝነት ተቆጣጥረውት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች ጡረታ ለመውጣት ወይም ለመሞት ሌላ አስርት ዓመታትን ይፈልጋሉ…

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ከሞላ ጎደል በአምክንዮ የሚያምን ሲሆን ለውጥን ለማምጣት የሚያስብ አእምሮን ይዟል፡፡ ሆኖም ግን እሱ ምንም ማድረግ የማይችል በጣም ደካማ የሆነ ሰው ነው…

አንድ ነባር የሆነ በኢትዮጵያ የቻይና ማህበረሰብ አባል የሆነ ሰው ጥቂት ፍርሀትን ባካተተ መልኩ በሀገሪቱ ውስጥ እየተመለከተው ያለውን ትልቅ ችግር እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፡ በቻይና ማዕከላዊ መንግስቱ ክልሎችን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል፣ በኢትዮጵያ ግን ሁሉም ነገር ፌዴራል ነው…ከሁሉም በላይ በርካታ ቻይናውያን ኃይልን የተቆናጠጡ በርካታ ባለስልጣኖቸን ይመለከታሉ፡፡

ቻይናዎች ሊናገሩት የሚፈልጉት ሆኖም ግን የማይናገሩት እና በርካታ ምዕራባውያን ታዛቢዎች የሚያደርጉት ነገር ቢኖር የፖለቲካ ጭቆናው ስርዓቱን ደካማ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ወጣት ዜጎች ብስጩዎች እና ስራ አጦች ሆነዋል፡፡ ለተስፋቢስነታቸው ቀዳዳ የሚከፍቱ ነገሮቸ ሁሉ ቶሎ ተብለው እንዲዘጉ ይደረጋሉ፡፡

ትርጉም ያላቸው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች አንድም ሀገር ጥለው እንዲሰደዱ ተደርገዋል ወይም ደግሞ የጨዋታ ሜዳውን ለደመ ቁጦዎቹ በመተው በእስር ቤት ውስጥ እንዲማቅቁ ይፈረድባቸዋል፡፡ ዩኒቨርስቲዎች ቀድሞ ከነበሩበት በአስር እጥፍ አድገዋል፣ ሆኖም ለእነዚህ በተስፋ ለተመረቁት ወጣቶች የስራ እድል የለም፡፡

በአእምሮ በሽተኛ ምሁሮቿ ምክንያት ኢትዮጵያ በአስከፊ ችግር ውስጥ ወድቃ ትገኛለች“ በማለት ዘኢኮኖሚስት መጽሔት ሀሳቡን ያጠቃልላል፡፡

ስለሆነም በዓለም ባንክ፣ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚገኙ ዓለም አቀፍ የድህነት አቃጥሪ ወትዋቾች ሁሉ የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ የአጭር ወይም ደግሞ የማራቶን ሩጫ ውድድር ያለመሆኑን በውል ሊያጤኑት ይገባል፡፡ “የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ” ሌላ ምንም ሳይሆን ነጭ ውሸት፣ እርባናቢስ ተራ ቅጥት እና የቁጥር የቁማር ጨዋታ ነው! ምንም ዓይነት እውነታነት የሌለው መንታ ምናባዊ ሀሳብ ነው፡፡

ለዓለም ባንክ እስቲ አንድ እንዲህ የሚል የመጨረሻ ጥያቄ ላቅርብ፡ ኢትዮጵያ እንደዚህ ያለ አንጸባራቂ የምጣኔ ሀብት ዕድገት የምታስመዘግብ ከሆነ ለምንድን ነው ኢትዮጵያ በፕላኔቷ ከሚገኙት ሀገሮች ሁሉ ሁለተኛዋ ደሀ ሀገር የሆነችው? (ለዚህ ጥያቄ ምላሽ እ.ኤ.አ ሰኔ 2014 በተመሳሳይ ርዕስ ያዘጋጀሁትን ትችት ይመልከቱ፡፡)

18 U.S. Code # 1001- “በማወቅ እና ሆን ተብሎ የሀሰት ጽሁፍን የተጠቀመ ወይም ደግሞ ሆን ብሎ ሀሰት፣ ልብወለድ ወይም የተጭበረበረ መግለጫ ወይም ጽሁፍ ያሰራጨ ወይም ይዞ የተገኘ

በዩናይትድ ስቴት መንግስት ሕግ መሰረት ሀሰት፣ አሳሳች እና አታላይ የሆኑ ሰነዶችን በመጠቀም መግለጫዎችን የሰጠ ወይም ደግሞ መረጃዎችን በህዝብ ዘንድ እንዲሁም ለድርጅቶች እና ለተቋማት ሲያሰራጭ የተገኘ ወንጀል ነው፡፡

18 U.S. Code # 1001 የተሰኘው ድንጋጌ የሚከተሉትን የሕግ ክልከላዎች በግልጽ ያስቀምጣል፡፡

ማንም ይሁን ማን…በማንኛውም መንገድ በአስፈጻሚው፣ በሕግ አውጭው ወይም ደግሞ በማናቸውም በዩናይትድ ስቴት የመንግስት ቅርንጫፍ አካል እያወቀ እና ሆን ብሎ፣

1ኛ) እውነተኛውን ነገር ወደ ጎን በመተው ሀሰትን ያራመደ፣ እውነታውን የደበቀ ወይም ደግሞ ማናቸውንም የማጭበርበር ድርጊቶችን በመፈጸም፣ ሸር በመስራት የማስመሰል ድርጊት የፈጸመ ወይም ደግሞ እውነታውን ለመደበቅ የሞከረ፣

2ኛ) ማናቸውንም ልብወለዳዊ የውሸት ሰነዶችን ያዘጋጀ ወይም ደግሞ የተጭበረበሩ የሸፍጥ መግለጫዎችን ወይም ውክልናዎችን የሰጠ፣

3ኛ) እያወቀ እና ሆን ብሎ ማንኛውንም ሀሰት የሆኑ ጽሁፎችን ወይም ደግሞ ሰነዶችን የተጠቀመ እንደዚሁም ሀሰት፣ ልቦለዳዊ ውሸት ወይም የተጭበረበሩ መግለጫዎችን ወይም ሰነዶችን ይዞ የተገኘ በዚህ አንቀጽ መሰረት የእስራት ቅጣት ይበየንበታል… ይላል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት በዓለም ባንክ ቡድን ውስጥ ትልቁ ባለድርሻ አካል እንደሆነ ከተባራሪ ወሬ ሰምቻለሁ፡፡

የዓለም ባንክ ቡድን በዩናይትድ ስቴትስ አስፈጻሚ አካል ቅርንጫፍ ስር ነው ሊተዳደር የሚችለውን?

የዓለም ባንክ ሊቃወመው የማይችል አንድ ስጦታ እሰጠዋሁ!

የዓለም ባንክ በዘ-ህወሀት መሪነት በኢትዮጵያ ተመዘገበ ለሚባለው የምጣኔ ሀብት ዕድገት ውሸት መናገሩን፣ እርባናቢስ ቅጥፈቱን እና የቁጥር ቁማር የመጫወት ስራውን የሚተው ከሆነ እኔም በበኩሌ  ስለዓለም ባንክ ውሸት መናገሩን፣ እርባናቢስ ቅጥፈቱን እና የቁጥር ቁማር የመጫወት ስራውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማጋለጥ እውነቱን ከመናገር አቆማለሁ፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!         

ህዳር 21 ቀን 2008 .

 

 

 

Similar Posts