Justice for the Victims of the Meles Massacres

በኢትዮጵያ ከአስር ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ በ2005 በአምባገነኑ እና በአረመኔው መለስ ዜናዊ የተፈጸመውን የግድያ እልቂት እናስታውስ፣

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

Ethiopian Martyrs of June and November, 2005
Ethiopian Martyrs of June and November, 2005

ሰይጣናዊ ድርጊት እየተፈጸመ በተጨባጭ በማየት እና በመስማት ዝም ማለት፣ እንዲሁም እንደዚህ ያለውን በሰው ልጆች   ላይ የሚፈጸም አረመኒያዊ ድርጊት በመካከላችን ጥልቀት ባለው ሁኔታ ደብቆ እና ቀብሮ ምንም ነገር ሳያደርጉ መመልከት ይህ ዓይነቱ ሰይጣናዊ እና መቅኖቢስ ዕኩይ ድርጊት በህብረተሰቡ ዘንድ አንድ ሺህ ጊዜ ደግሞ እና ደጋግሞ እንዲፈጸም መፍቀድ ማለት ነው፡፡

ሰይጣናዊ ድርጊት ፈጻሚዎችን ካልቀጣናቸው ወይም ደግሞ በፈጸሙት ዕኩይ ድርጊ ተገቢውን ትችት ካላቀረብንባቸው በስተቀር የእነርሱን እርባናቢስ የእርጅና እድሜ ማራዘምን መጠበቃችን ብቻ አይደለም ጎልቶ የሚታየው፣ ሆኖም ግን ይህንን ባደረግን ቁጥር ፍትህን በጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ በመቅበር ለአዲሱ ትውልድ ማስተላለፋችን መሆኑ ጭምር በውል ሊጤን ይገባል፡፡

በዚህም ምክንያት ነው አዲሱ ትውልድ በሚደረገው የቅስቀሳ ደካማነት ስራ ብቻ ሳይሆን ግዴለሽነት እና ደንታቢስነትን እየተላመደው ያለው፡፡

ወጣቱ ትውልድ በመሬት ላይ የሚፈጸሙ ዕኩይ ድርጊቶች ሁሉ ሀብትን እና ብልጽግናን እስካስገኙ ድረስ ቅጣት ሊጣልባቸው አይገባም የሚልአመክንዮን ያራምዳል፡፡

እንደዚህ ያለ አስተሳሰብ በተጠናወታት ሀገር ውስጥ መኖር ምቹነት የሌለው እና አስፈሪ ነገር ነው! (አሌክሳንደር ሶልዘኒትሲን፣ የደሴቱ የፖለቲካ ሰው/The Gulag Archipelago፣ 1918-1956፡፡)

ጊዜ እንዴት ይበራል እባካችሁ!

ቀጭ… ቀጭ… ቀጭ… ቀጭ…

ዓመታቱ ከነፉ፣ ግን እንደዚያ ባለ አሰቃቂ ሁኔታ የተገደደሉትን ወገኖቻችንን እናስታውሳለን?

እስከ አሁን ጊዜ እንዴት እንደሚቆም!

ቀጭ!

ሰዓቱ ቆሟል፡፡

እ.ኤ.አ ህዳር 2015 እ.ኤ.አ በ2005 አረመኔው ሟቹ መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ የፈጸመውን የግፍ እልቂት 10ኛ ዓመት የምናስብበት ዓመት ነው፡፡

እንደዚያ ዓይነት እልቂት የሚፈጸምበት ሌላ ህዳር አልመኝም!

እንደዚያ ዓይነት በደም የሰከረ መለስ በዓይኔ ማየት አልፈልግም፡፡

እንደዚያ ዓይነት አጋንንት የተዋኸደው ህወሀት ተመልሶ እንዲፈጠር በፍጹም አልሻም፡፡

በህዳር ወር እንደዚያ ዓይነት ሰይጣናዊ ተውኔት እንዲኖር አልፈቅድም!

እ.ኤ.አ ከህዳር 2005 እስከ አሁን ድረስ በእርግጠኝነት አስር ዓመታት ተቆጠሩን?

የአምባገነኑ መለስ የእልቂት ሰለባዎች ምንም ዓይነት ፍትህን ሳያገኙ እንደቀልድ አስር ዓመታት ተቆጠሩ ማለት ነውን?

የመለስን እልቂት የፈጸሙት ወሮበላ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች ምንም ዓይነት ተጠያቂነት ሳይኖርባቸው አስር ዓመታት ዝም ብለው ነጎዱ ማለት ነውን?

ለመለስ የእልቂት ሰለባዎች ምንም ዓይነት ካሳ ሳይሰጥ አሰር ዓመታት ዝም ብለው ከነፉ ማለት ነውን?

መቅኖቢስ፣ እርባናቢስ ህዳር!

ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሁልጊዜ ህዳር እ.ኤ.አ በ2005 በሀገራችን በኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ መስፈን ሲሉ ውድ ህይወታቸውን የሰውትን እና በአረመኔው መለስ እልቂት የተፈጸመባቸውን የግፍ ሰለባዎች በማስታወስ የሚዘክር ጽሁፍ እያዘጋጀሁ አወጣለሁ፡፡

እ.ኤ.አ በ2005 የተካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ተከስቶ በነበረው ውዝግብ የህዝቡ ድምጽ በቀን ብርሀን በአደባባይ ተዘርፏል በሚል ምክንያት ሰላማዊ ዜጎች ተቃውሟቸውን ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስታወቅ ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣቸው ብቻ    አሁን በህይወት የሌለው እና በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በስልጣን ላይ ያለው የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን (ዘ-ህወሀት) ስብስብ እያልኩ የምጠራው የማፊያ እና ወንጀለኛ ድርጅት መሪ አምባገነኑ መለስ ዜናዊ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እልቂት እንዲፈጸም አግዓዚ ለሚባለው ቅጥር ነፍሰ ገዳይ ቀጥተኛ የሆነ የግል ትዕዛዝ በመስጠት በመቶዎች የሚቆጠሩ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ያልታጠቁ ንጹሀን ዜጎች እንዲያልቁ አደረገ፡፡

አጠቃላይ የይስሙላ የቅርጫ ምርጫው ከተካሄደ ከአንድ ቀን በኋላ እ.ኤ.አ ግንቦት 16/2005 መለስ ዜናዊ ሁሉንም የፖሊስ፣ የደህንነት እና ወታደራዊ ኃይል አዛዥነቱን በእራሱ ቁጥጥር ስር በማድረግ በህዝብ ምንም ዓይነት ስብሰባ እንዳይካሄድ በማለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የሀገሪቱን መናገሻ ከተማ የፖሊስ እና ልዩ ኃይሉን በማሰማራት የጦር ቀጣና አውድማ አደረጋት፡፡

በቀጣዮቹ ሳምንታት እና ወራት አምባገነኑ እና አረመኔው መለስ በእርሱ አገዛዝ ላይ ተቃውሞ በሚያሳዬው በማንኛውንም ዜጋ ላይ የፖሊስ እና የደህንነት ኃይሉ ነጻ እርምጃ እንዲወስድ በግሉ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

እ.ኤ.አ በግንቦት እና በህዳር 2005 በጨካኙ መለስ የእልቂት ትዕዛዝ ግድያ የተፈጸመባቸው ንጹሀን ዜጎች ቁጥር ቁጥራቸውን አሳንሰው በሚያቀርቡት የመንግስት ባለስልጣኖች እና እራሱ መለስ ባቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን በቀረበው ዘገባ እንኳ 193 ምንም ዓይነት መሳሪያ ያልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች የተገደሉ ሲሆን ሌሎች 763 የሚሆኑት ደግሞ ቁስለኛ ሆነዋል፡፡ (ትክክለኛው የሟቾች እና የቁስለኞች ቁጥር ግን አጣሪ ኮሚሽኑ ካቀረበው ዘገባም በላይ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ የግርጌ ማስታወሻ ተራቁጥር 2ን ይመልከቱ፡፡)

እነዚያ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ያልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች የመለስን በሸፍጥ የተካሄደ የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ በመቃወም መብታቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመጠቀም በመሞከራቸው ምክንያት ብቻ እንደ አውሬ እየታደኑ በየመንገዱ እና በየቤቶቻቸው ውስጥ በግፍ ተገድለዋል፡፡

እነዚያ ሰላማዊ ተቃዋሚዎች በኢትዮጵያ እውነተኛ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ሰማዕት ሆነው አልፈዋል፡፡

የጨካኙን የመለስን የእልቂት ሰለባዎች ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሁልጊዜ ሰኞ በማዘጋጃቸው ትችቶቼ ወይም ደግሞ አንዳንዶች እንደሚሉት ረዣዥም ጽሁፎቼ ሳስታውሳቸው ቆይቻለሁ፡፡

አምባገነኑ እና አረመኔው መለስ ከመሞቱ በፊት እና ከሞተም በኋላ አሁን በስልጣን ላሉት የእርሱ ግብረ አበር ለሆኑት ወሮበላ የዘ-ህወሀት ስብስብ ሎሌዎቹ ስለሰይጣናዊነት፣ ጨካኝነት፣ መጥፎነ፣ የሞራል ዝቅጠት፣ ጭራቃዊ ባህሪ፣ ጨፍጫፊነት፣ ንቀት እና በጥላቻ መሞላትነት ስሰብክ እና ሳስተምር ቆይቻለሁ፡፡

ኢትዮጵያን በታሪክ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደ አሁኑ ያለ ሰይጣናዊነት፣ አስከፊ ጉዳት፣ አውዳሚነት እና አሰቃቂ ሁኔታ ከአምባገነኑ መለስ ዜናዊ እና ከግብረ አበሮቹ ከዘ-ህወሀት የበለጠ ተፈጽሞባት እንደማያውቅ የመጨረሻ የሞራል እርግጠኝነት አለኝ፡፡

እ.ኤ.አ በ2005 አረመኔው መለስ በኢትዮጵያ ሰላማዊ ወገኖቻችን ላይ በፈጸመው አስከፊ እልቂት ምክንያት ብቻ ወደ ሰብአዊ መብት ተሟጋችነት ትግል ውስጥ ዘው ብዬ ገብቻለሁ፡፡

መለስ እ.ኤ.አ በ2005 የተካሄደውን ያንን አሳዛኝ እልቂት ለይስሙላ እና ምንም ዓይነት እውነተኛ የሀዘኔታ ስሜትን ባልተላበሰ አንደበቱ “አሰቃቂ ክስተት” ብሎ ጠርቶታል፡፡ ድንቄም አሰቃቂ ክስተት! በአሰቃቂ ሁኔታ ንጹሀን ዜጎችን በጥይት አረር እያስጠበሱ አሰቃቂ ብሎ የይስሙላ ንግግር ለማድረግ መንተባተብ በግፍ ባለቁ ወገኖቻችን ላይ ሁለተኛ የእልቂት ሞት እንደመፈጸም ይቆጠራል፡፡

እንደ ስታሊን ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ መለስ “የአንድ ሰው ሞት አሰቃቂ ነው፣ የሚሊዮኖች ሞት ግን የቁጥር ጉዳይ ነው” በሚለው አባባል ላይ በጽኑ ያምናል፡፡

በመቶዎች የሚቆጠሩ የጦር መሳሪያ ያልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች የጅምላ እልቂት አሰቃቂ ክስተት ነውን?

ለማን?

እንደዚህ ዓይነቱ ጉዳይ ለመለስ እና ለዘ-ህወሀት አሰቃቂ ክስተት ለመሆኑ እጠራጠራለሁ፡፡

መለስ ከስሜታዊነት በጸዳ እና ፍቅርን በተላበሰ በሚስል መልኩ በአመጽ እና በሰላማዊ ሰልፍ መካከል ያለውን ልዩነት ለማሳሰብ ሞክሯል፡፡

ሊታመን በማይችል እና አሳፋሪ በሆነ መልኩ መለስ እራሱን ከሞራል ስብዕና ኪሳራ እና በእልቂቱ ምክንያት ሊደርስበት ከሚችለው የሕግ ተጠያቂነት እራሱን ነጻ ለማድረግ በማሰብ የእልቂት ድርጊቱን ሙሉ በሙሉ ለቅጥር ነፍሰ ገዳይነት አሰማርቷቸው በነበሩት በፖሊስ እና የደህንነት ኃይሎች ላይ ደፍድፎታል፡፡

መለስ እንዲህ የሚል ባዶ ዲስኩርም አሰምቶ ነበር፣ “ድሀረ ምርጫውን ተከትሎ ተከስቶ የነበረው የኃይል እርምጃ እንደዚህ ዓይነት ክስተቶችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ሙያዊ ብቃት የፖሊስ ኃይሉ የሚያንሰው በመሆኑ ነው፡፡ ፖሊስ ለስራው ብቁ ስልጠና የሌለው እና ለሚያከናውናቸውም ተግባራት በበቂ ሁኔታ አስፈላጊ የሆኑ አጋዥ መሳሪያዎች ያልያዘ መሆኑን ግንዛቤ ወስዷል፡፡ በዚህም የተነሳ በዚህ ጉዳይ ላይ ጠንክረን የሰራን ስለሆነ በአሁኑ ጊዜ ይህ ጉዳይ እልባት አግኝቷል ብዬ አምናለሁ“ ብሎ ነበር፡፡

መለስ ያሰማውን ዲስኩር በሌላ አባባል ስናቀርበው እንዲህ የሚል ሆኖ ይገኛል፣ “ቅሬታችሁን ሁሉ በእኔ ላይ ማድረጉን ተውትና ተበድለናል የምትሉትን ማንኛውንም ነገር ሁሉ የኃይል እርምጃ በመውሰድ ባልታጠቁ ህዝቦች ላይ ጥቃት እንዲሰነዝሩ ባዘዝኳቸው ደንቆሮ በሆኑት ገዳይ ሚሊሻዎች ላይ አድርጉ“ የሚል ነው፡፡ ይህ ዓይነት ዝባዝንኪ ንግግር ዓይናችሁን ጭፍኑ እና ላሞኛችሁ ከማለት ሌላ ምን ሊባል ይችላል?

Meles Zenawiጨካኙ መለስ የእልቂቱ ዋና አዛዥ አድራጊ ፈጣሪ (የእልቂቱ ዋና መሀንዲስ) በሰው ልጆች ላይ ለሰራው የሰብአዊ እልቂት ወንጀል እራሱን ከሕግ ተጠያቂነት ነጻ በማድረግ እልቂትን እንዲፈጽሙ ትዕዛዝ ሰጥቷቸው የነበሩት ታጣቂዎች ኃላፊነቱን እንዲወስዱ ደፍድፎባቸዋል፡፡

ሆኖም ግን ስልጠና የጎደላቸው ያልሰለጠኑ እንዲሁም የታዘዙትን ከማድረግ ያለፈ ምንም ዓይነት የውሳኔ ሰጭነት ሚና ያልነበራቸው የፖሊስ እና የደህንነት ኃይሎች ሳይሆኑ መለስ እና ሎሌዎቹ ለዚህ እልቂት ቀጥተኛ እና ግንባርቀደም ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ ይህም ሲባል ፖሊስ እና የደህንነት ኃይልም ቢሆን ሰውን የመሰለ ታላቅ ፍጡር ያውም በሰላማዊ መልኩ ተቃውሟቸውን ለማሰማት በወጡ ንጹሀን ዜጎች ላይ ምላጭ ስቦ ህይወት እስካጠፋ ድረስ ሁለተኛ ተጠያቂ ይሆናል በማለት እንጅ የታዘዙትን አደረጉ አበጃችሁ ለማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ማንም ቢሆን የወንጀል ኃላፊነት የለውም፡፡ ህይወትን ያህል ክቡር ነገር ማጥፋት ሲሆን ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ ታላቅ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ መለስ እና ግብረ አበሮቹ በዚህ አሳበው እራሳቸውን ነጻ በማውጣት የእልቂት ወንጀሉን ሁሉ በገዳይ ሚሊሻዎች ላይ ለመደፍደፍ እያደረጉት ያለው ሙከራ ከምንም ነገር ላይ እንደማያደርሳቸው በውል ሊገነዘቡት ይገባል፡፡

ለወራት ያህል የዘለቀውን እና በተለይም እ.ኤ.አ ከህዳር 1-4 14/2005 ድረስ  ባልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የተደረገውን የግድያ እልቂት የፈጸሙሙት የመለስ ቅጥር ነፍሰገዳይ የደህንነት እና የፖሊስ ኃይሎች እንዲተኩሱ እና እንዲገድሉ የተለዬ የኃላፊነት ስልጣን ካልተሰጣቸው በስተቀር ንጹን ዜጎችን በጥይት እየደበደቡ እንዲያልቁ አያደርጉም ነበር፡፡

የደህንነት እና የፖሊስ ኃይሉን እንዲከታተሉ እና እንዲገመግሙ የተመደቡ ኃይሎች ገና በመጀመሪያው ግድያ እንዳይፈጸም ድርጊቱን ማቆም ነበረባቸው፡፡ ማቆም ይችሉ ነበር።

ሆኖም ግን ይህንን አላደረጉም፡፡ አንድ ጊዜ አንክዋን እልቂቱን ለማስቆም አልሞከሩም፣ ከዚህም በባሰ መልኩ እስከመቸውም ድረስ ለማስቆም ምንም ዓይነት ሙከራ በፍጹም አላደረጉም፡፡ በአጭሩ እነርሱ ሰላማዊውን ህዝብ እያስጨረሱ አሻሻ ገዳሜ በማለት ላይ ነበሩ፡፡

የደህንነት ኃይሉ ግድያውን ለወራት ያህል እንዲፈጽም ፈቅደውለት መንገዶች ሁሉ የጦርነት አውድማ ሆነው እንዲቆዩ አድርገዋል፡፡

እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ግን መለስ አሰማርቷቸው የነበሩት ቅጥር ነፍሰ ገዳይ የደህንነት ኃይሎች እና ምንም እንደማያውቁ ሚሊሻዎች አድርጎ አቅርቧቸው የነበሩት ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች በደንብ የሰለጠኑ እና የሰላማዊ ተቃዋሚዎችን ግንባር እና ደረት እያነጣጠሩ የሚመቱ እንዲሁም ጭንቅላቶቻቸውን የሚፈጠፍጡ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች እንደነበሩ መለስ እራሱ ያቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን መጠነ ሰፊ የሆነ ምርመራውን ማጠናቀቀ ተከትሎ እ.ኤ.አ በ2006 ይፋ አድርጓል፡፡

የደህንነት ኃይሉን እንዲከታተሉ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የነበሩ ባለስልጣን ተብዬዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ እልቂት የፈጸሙ ቅጥር ነፍሰ ዳዮችን ለፍትህ አካል ማቅረብ ይችሉ ነበር፡፡ ሆኖም ግን አላደረጉትም ምክንያቱም ሰላማዊ የሆኑ ንጹሀን ዜጎችን እንዲገድሉ ፈቃዱ ተሰጥቷቸው ነበርና ነው፡፡

ያንን የመሰለ በሰው ልጆች ላይ ሊፈጸም ቀርቶ ሊታሰብ የማይገባውን የመለስ ዕኩይ የእልቂት ሰይጣናዊ የግድያ ተግባር የፈጸሙትን 237 የደህንነት እና የፖሊስ ኃይሎች አንድ በአንድ በስም እናውቃቸዋለን፡፡ ፍትህ የቅጣት ሰይፏን መዝዛ ስትነሳ የትም ገብተው እና ወጥተው አያመልጡም፡፡ ከእግዚአብሔር ሞት እና ከፍትህ አደባባይ ተሰውሮ ለዘላለም የሚኖር በዚህ ዓለም ላይ የለምና፡፡

ከዚህም በተጨማሪ እንደዚያ ዓይነቱን እ.ኤ.አ በ2005 የመለስን ተኩሰህ ግደል አሰቃቂ እልቂት እንዲፈጸም ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ የነበሩትን ባለስልጣን ተብዬዎች ከቁንጮው እስከ ታችኛው ድረስ እያንዳንዳቸውን በስም እናውቃቸዋለን፡፡

እስቲ እንደገና አንድ ጊዜ እንዲህ የሚል ጥያቄ ልጠይቅ፡ እ.ኤ.አ በ2005 የቅርጫ ምርጫ ውዝብግን ተከትሎ ምንም ዓይነት መሳሪያ ያልታጠቁ ንጹሀን ዜጎችን የገደሉ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች እስከ አሁን ድረስ ለፍትህ አካል እንዲቀርቡ በማድረግ ጉዳያቸው እንዲታይ ያልተደረገው ለምንድን ነው? የዘ-ህወሀት አገዛዝ ጥቂት ጦማሪያን ሀሳቦቻቸውን በመገናኛ ድረ ገጽ በመግለጻቸው ምክንያት አሸባሪ ብሎ በመፈረጅ ክስ ለመመስረት በብርህን ፍጥነት ተጉዞ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በሰው ልጆች ላይ ሰብአዊ የእልቂት ወንጀልን ፈጽመው ደረታቸውን ነፍተው በአዲስ አበባ እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም ሲንገዋለሉ የሚውሉትን ታዋቂ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች እስከ አሁን ድረስ ለፍትህ አካል ያላቀረባቸው ለምንድን ነው?

እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ግን በንጹሀን ዜጎች ላይ የደረሰው እልቂት የመለስ እና የዘ-ህወሀት የረዥም ጊዜ ስልታዊ ዕቅድ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ መጨረሻ ለሌለው ጊዜ በስልጣን ማማ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ለመኖር ካላቸው ዕኩይ አስተሳሰብ እና ምግባር የሚመነጭ ነው፡፡

አምባገነኑ መለስ በስልጣን ኮርቻ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ ለመኖር እንዲችል ይቃወሙኛል ብሎ በሚያስባቸው ወገኖች ላይ ሁሉ ድንገተኛ በሆነ መልኩ መጠነ ሰፊ እና የጅምላ ጥቃት በመሰንዘር ሽባ ሆነው እንዲቀሩ ለማድረግ የተሰራ ነገር ነበር።

መለስ እራሱን እና የእርሱን ወሮበላ ስብስብ መቋጫ ለሌለው እና ገደብ ለማይጣልበት ጊዜ በስልጣን ላይ ለማቆየት ሲል የፈለገውን ያህል ህዝብ በመግደል፣ በማረድ እና እልቂትን በመፈጸም ለወዳጆቹ እና ለጠላቶቹ ጉልህ የሆነ መልዕክት ማስተላለፍ ፈልጎ ነበር፡፡

መለስ እራሱ ርህራሄ የለሽ፣ አረመኔ፣ ኃይለኛ፣ ምህረት የለሽ፣ ጨካኝ፣ በቀልተኛ፣ ሀዘንየለሽ እና በግቢ ውስጥ ታስሮ ከሚገኝ ጨካኝ ውሻ የከፋ ጨካኝ መሆኑን ለወዳጆቹ እና ለጠላቶቹ ጉልህ የሆነ መልዕክት ማስተላለፍ ፈልጎ ነበር!

መለስ ለእንደዚህ እና ለመሳሰሉት ነገሮች የቆመ ስብዕና ያለው ፍጡር ነበር፡፡ እንደዚህ ያለ ለመሆኑም ከጥርጣሬ የሚጥል አይደለም!!!

መለስ ዓለም አቀፍ ሕግን በመጨፍለቅ እ.ኤ.አ በ2006 ሶማሌን በኃይል በመውረር ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፎ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ታህሳስ 2006 መለስ ይፋ በሆነ መልኩ በአዳባባይ አሸባሪ የሚለውን አልሸባብ ድል በማድረግ ከሶማሌ በሁለት ወራት ውስጥ እንደሚወጣ አውጆ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ነሐሴ 2007 የመለስ ወራሪ ኃይል በሶማሌ ውስጥ የሚያደርገው ግስጋሴ እንዲገታ ሆኖ ሽንፈቱን ተከናንቦ ተዋርዶ እንደ አበደ ውሻ ጅራቱን በጉያው ወትፎ ወጣ፡፡

መለስ ሶማሌን “አስከፊ የሰብአዊ ቀውስ ከሚታይባቸው ሀገሮች መካከል አንዷ እንድትሆን አድርጓል፡፡”

የመለስ የሶማሌ ወረራ በ10 ሺዎች ለሚቆጠሩ ሲቪል ሶማሌያውያን እልቂት እና ከመቅዲሾ ብቻ ለ870 ሺ ሶማሌያውያን ዜጎች ስደት መንስኤ ለመሆን በቅቷል፡፡ ይኸ ሊካድ የማይችል የጠራ ሐቅ ነው!

በመለስ የእብሪት እና የግፍ የሶማሌ ወረራ ጊዜ ህይወታቸውን ላጡት የሶማሌ የመለስ የእልቂት ሰለባ የሆኑ ዜጎች ሁሉ በአሁኑ ጊዜ ማን ነው የሚያስታውሳቸው?

እንደዚሁም ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ መለስ እ.ኤ.አ በ2007 – 08 ኦጋዴን እየተባለ በሚጠራው የኢትዮጵያ የግዛት ክልል ውስጥ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እልቂትን በመፈጸም ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እንዲህ የሚል ዘገባ አውጥቶ ነበር፣ “መንግስት በኦጋዴን በ10 ሺዎች በሚቆጠር የሲቪል ህዝብ ላይ ጥቃት፣ የንግድ እንቅስቃሴ እገዳ እና በእርዳታ ተቀባዩ ህዝብ ላይ የጅምላ ቅጣት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ወታደሮች የሲቪል ህዝብን ይገድላሉ፣ ስቃይ ያደርሳሉ እንደዚሁም ደግሞ አስገድዶ የመድፈር ወንጀሎችን ይፈጽማሉ፡፡“

በመለስ የእብሪት እና የግፍ እልቂት ህይወታቸውን ላጡት የኦጋዴን ዜጎች ሁሉ በአሁኑ ጊዜ ማን ነው የሚያስታውሳቸው?

መለስ በተመሳሳይ መልኩ በጋምቤላ በንጹሀን ዜጎች ላይ እልቂትን ፈጽሟል፡፡

በሌሎች በርካታ የተለያዩ የኢትዮጵያ የግዛት አካባቢዎች ተመሳሳይ ዕኩይ መልዕክቶችን ሲያስተላልፍ ቆይቷል፡፡

የመለስ/ዘ-ህወሀት የእልቂት ሰለባዎችን የሚያስታውሳቸው ማን ነው?

እ.ኤ.አ በ2005 በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ በመለስ የተካሄደውን ጭፍጨፋ አስታውሳለሁ፡፡

መለስ ከስሜታዊነት በጸዳ እና ፍቅርን በተላበሰ በሚስል መልኩ “በአመጽ እና በሰላማዊ ሰልፍ” መካከል ያለውን ልዩነት ለማሳሰብ ሞክሯል፡፡

የእልቂቱ ሰለባዎች ተራ ሰላማዊ ሰልፍ አድራጊዎች ሳይሆኑ ስርዓተ አልበኞች እና የዱርዬ ስብስብ ወሮበሎች ናቸው ብሎ ነበር፡፡

እውነታዎች በእራሳቸው ይናገራሉ፡

እ.ኤ.አ በ2006 ከውጭ እርዳታ ሰጭ ጌቶቹ በተደረገ ተጽዕኖ ማክንያት መለስ እራሱ “የድህረ ምርጫ ብጥብጦች” እያለ ከሚጠራው ጉዳይ ጋር በተያያዘ መልኩ በዜጎች ላይ አድርሶት የነበረውን እልቂት የሚያጣራ አጣሪ ኮሚሽን አቋቋመ፡፡

አጣሪ ኮሚሽኑ 16,990 የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን የመረመረ ሲሆን እደዚሁም ደግሞ ከ1,300 ምስክሮች የምስክርነት ቃል ተቀብሏል፡፡

አጣሪ ኮሚሽኑ እስር ቤቶችን እና ሆስፒታሎችን የጎበኘ ሲሆን የመለስ አገዛዝ አባላት የሆኑ ባለስልጣናትን ለበርካታ ወራት ቃለ መጠይቅ አድርጓል፡፡

አጣሪ ኮሚሽኑ እ.ኤ.አ በ2005 በተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ በሁሉም መመዘኛዎች መለስ ዜናዊ እና እረዳቶቹ ሙሉ በሙሉ ጥፋተኞች እና ተጠያቂዎች መሆናቸውን በአብላጫ ድምጽ በመወሰን ከድምዳሜ ላይ ደረሰ፡፡

እ.ኤ.አ ህዳር 16/2006 አጣሪ ኮሚሽኑ ያገኛቸውን የምርመራ ውጤቶች ጉዳዩን ለሚሰማው አካል በተደረገ ስብሰባ ላይ ግልጽ በማድረግ ይፋ አደረገ፡፡

የአጣሪ ኮሚሽኑን ትክክለኛ ድምጽ ለማረጋገጥ በቪዲዮ ተቀርጾ የተዘጋጀውን ከዚህ ላይ በመጫን መመልከት ይችላሉ፡፡

የአጣሪ ኮሚሽኑን የመጨረሻ የድምጽ ሂደት ዝርዝር ሁኔታ ለመመልከት ደግሞ ከዚህ ጋ ይጫኑ፡፡

አጣሪ ኮሚሽኑ 8-2 በሆነ አብላጫ ድምጽ ከዚህ በታች የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስታላልፏል፡

የጦር መሳሪያ ባልታጠቁት ሰላማዊ ሰልፍ አድራጊዎች አማካይነት የወደመ ንብረት የለም፡፡

ከሰላማዊ ሰልፍ አድራጊዎቹ መካከል ጠብመንጃ ወይም ደግሞ የእጅ ቦንብ የያዘ (በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ የብዙሀን መገናኛ ዘዴዎች በሚያቀርቧቸው ዘገባዎች መሰረት ጥቂት ሰላማዊ ሰልፍ አድራጊዎች ጠብመንጃ እና ቦምቦችን ታጥቀዋል የሚል ዘገባ ያቀረቡ ቢሆንም) አንድም የታጠቀ ሰው አልነበረም፡፡

በመንግስት ታጣቂ ኃይሎች ሲደረጉ የነበሩት ተኩሶች የሰላማዊ ሰልፈኞችን ስብስብ ለመበተን እንዲቻል አልነበረም፡፡ ይልቁንም ከዚህ በተጻረረ መልኩ በሰላማዊ ሰልፈኞች ጭንቅላቶች እና ደረቶች ላይ በማነጣጠር የሚደረጉ ተኩሶች ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት ሕግ የተጣሰ መሆኑን በግልጽ ያመላክታል፡፡ እናም የመንግስት ታጣቂ ኃይሎች ከመጠን ያለፈ ኃይልን ተጠቅመዋል፡፡

የፖሊስ እና የደህንነት ኃይሎች ሆን ብለው ተኩስ በመክፈት 193 ዜጎችን የግድያ እና 763 የሚሆኑትን ደግሞ የቁስለኛ ሰለባ አድርገዋል፡፡

እ.ኤ.አ ህዳር 3/2005 በቃሊቲ እስር ቤት ረብሻ ተነሳ በሚል ውንጀላ እና ለ15 ደቂቃዎች በተካሄደ የመሳሪያ ተኩስ የእስር ቤቱ የጥበቃ አባላት 1500 ጥይቶችን በእስር ቤት ክፍሎች ላይ በመተኮስ 17 እስረኞችን ሲገድሉ 33 የሚሆኑት እስረኞች ደግሞ የከባድ ቁስለኛ ሰለባ ለመሆን ተዳርገዋል፡፡

ሰላማዊ ሰልፍ በወጡ ዜጎች አማካይነት በተኩስ ተሰማርተው በነበሩ የደህንነት ኃይሎች ላይ የተደረገ ምንም ዓይነት ጥቃት ወይም ደግሞ ግድያ የለም፡፡

በሰላማዊ ሰልፈኞች ተገድለዋል የተባሉ የደህንነት ኃይሎች የሬሳ ምርመራ ውጤት የለም፣ ከዚህም በላይ ስለሞቱ የደህንነት ኃይሎች ሊያመላክቱ የሚችሉ የተሱ ፎቶግራፎች ወይም ደግሞ ስለሞቱበት ሁኔታ ከሲቪል ሰላማዊ ሰልፈኞች በተጻረረ መልኩ ሊገልጽ የሚችል የሬሳ የምስክር ወረቀት ወረቀት የለም፡፡

የአጣሪ ኮሚሽኑ ሊቀመንበር የሆኑት ዳኛ ፍሬህይወት ሳሙኤል እንዲህ የሚል ምልከታቸውን አስቀምጠዋል፡

“በርካታ ሰላማዊ ሰዎች በዘፈቀደ ተገድለዋል፡፡ በእድሚያቸው የገፉ አሮጊት ወንዶች እቤታቸው ባሉበት ተገድለዋል፡፡ እንደዚሁም ልጃች በመጫወጫ ሜዳ ላይ በመጫወት ላይ እንዳሉ የግድያ ጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል፡፡“

በአረመኔው መለስ የግድያ እልቂት 30,000 ሲቪሎች ያለምንም ዋስትና በቁጥጥር ስር በመዋል ወደማጎሪያ አስር ቤቶች ተወስደው ታስረዋል፡፡

የመለስ የእልቂት ሰለባዎች ሁከት ቀስቃሽ አመጸኞች ወይም ደግሞ የኃይል ድርጊት ፈጻሚዎች ለመሆናቸው የቀረበ ምንም ዓይነት መረጃ የለም፡፡

መለስ እና የእርሱ ዘ-ህወሀት የተባለው ወሮበላ የማፊያ ድርጅት ምንም ዓይነት መሳሪያ ባልታጠቁ ንጹሀን ሰላማዊ ሰልፍ በሚያካሂዱ ዜጎች ላይ የግድያ እልቂትን በመፈጸም በሰው ልጆች ላይ ሰብአዊ ወንጀልን ፈጽመዋል፡፡

ሁሉንም ቁስል ጊዜ ይሽረዋል የሚሉትን እንዳትረሱ፡፡

“መሻር” ማለት እ.ኤ.አ በ2005 የተካሄደውን ይስሙላ የቅርጫ ምርጫ ተከትሎ በንጹሀን ዜጎች ላይ በመለስ እና በዘ-ህወሀት እብሪተኛ ጨካኞች የተፈጸመውን ሰብአዊ ወንጀል መርሳት ማለት አይደለም፡፡

ላለፉት ዘጠኝ መታት በእያንዳንዱ ሰኞ አንድም ሳምንት ሳላሳልፍ የመለስ የእልቂት ሰለባ የሆኑ ሰላማዊ ወገኖቻችንን በማስታወስ የሚዘክር የጽሁፍ ትችት አቀርባለሁ፡፡

ጥቂት ሰዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ቃላትን ያካተቱ ጹሁፎችን ሁልጊዜ በየሳምንቱ ሰኞ እንዴት ለማውጣት እንደምችል በመደነቅ ሀሳባቸውን ይገላጻሉ፡፡

መልሱ ግን ቀላል እና እንዲህ የሚል ነው፡ ሁሉም ነገር የማይሳነው አምላክ እግዚአብሔር የእነርሱ ድምጽ ሆኘ እንድናገርላቸው እስከፈቀደልኝ ጊዜ ደረስ ለእነዚህ ድምጽ ለሌላቸው የመለስ እልቂት ሰለባ ወገኖቻችን ድምጽ ለመሆን ቃል ገብቻለሁ የሚል ነው፡፡

በአንድ ወቅት አንድም ጊዜ አይቻቸው ለማላውቃቸው፣ በግንባር ተገናኝተን ላላየኋቸው ወይም ደግሞ ሰምቻቸው ለማላውቃቸው ሰዎች ለምን እንደምጨነቅ ተጠይቄ ነበር፡፡

“በቃ ለምን አትተወዉም ያለፈ ነገር ነው!“

“በእናትህ፣ በአባትህ፣ በወንድምህ፣ በእህትህ፣ በጓደኛህ ላይ እንደዚህ ያለ ችግር ቢደርስባቸው ዝም ብለህ ትመለከታለህን…?“ የሚል ጥያቄ ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡

እንደ መቃብር ጸጥ ይላሉ፡፡

በእርግጥ በመለስ የእልቂት ሰለባ የደረሰባቸው ንጹሀን ዜጎች ከእኔ ጋር የስጋ ዝምድና የላቸውም፡፡ ማናቸውንም ቢሆን አላውቃቸውም፡፡

እንግዲህ ጉዳዩ እንደዚህ በመሆኑ በእነርሱ ላይ እንደዚያ ያለ የግድያ እልቂት ወንጀል ተፈጽሞባቸው መረሳት አለባቸው? እንዲሁ እንዳልባሌ ነገር መተው አለባቸው?

ኤሊ ዊሴል በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ “ኢፍትሀዊነትን ለመከላከል አቅም የምናጣበት ጊዜ ይኖራል፣ ሆኖም ግን መቃወም የምንችልበት ጊዜ በምንም ዓይነት መንገድ በፍጹም ማጣት የለብንም፡፡“

እኔ ኢፍትሀዊነትን ለመከላከል ወይም ደግሞ በሰው ልጆች ላይ የመጨረሻ ወንጀል የሰሩትን ወንጀለኞች ወደ ፍትህ አካል አስቅርቤ የማስቀጣት አቅም የሌለኝ ሰው መሆኑ እውነት ነው፡፡

ሆኖም ግን በእነዚህ የጥቃት ሰለባ በሆኑ ዜጎች ላይ ስለሚፈጸሙት ኢፍትሀዊ ድርጊቶች መናገር ወይም ደግሞ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙትን ኢፍትሀዊ ነገሮች በይፋ መቃወም በምንም ዓይነት መልኩ አቅም ቢስ ሊያደርገኝ አይችልም፡፡

ሌሎች ወጎኖቻችን የየትም የት ዘር ይሁኑ፣ የየትም ብሄር ይሁኑ፣ የየትኛውም ኃይማኖት እምነት ተከታይ ይሁኑ… ሲሰቃዩ በምናይበት ጊዜ ዝም ብለን በግዴለሽነት የምንመለከትበት ጊዜ በፍጹም ሊኖር አይገባም፡፡

ሶቅራጥስ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ “ያልተፈተነ ህይወት የመኖር ጥቅም የለውም፡፡“

እኔም እንደዚሁ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙትን አስቀያሚ ነገሮች ማለትም ጨካኝነት፣ ኢፍትሀዊነት፣ ጭቆና እና ስልጣንን ከህግ አግባብ ውጭ በመጠቀም በሰው ልጆች ላይ ሲፈጸሙ ዝም ብለን እየተመለከትን የምንኖር ከሆነ በህይወት የመኖር ትርጉም ምንም ዓይነት ጠቃሚነት የሌለው እርባናየለሽ ነገር ነው እላለሁ፡፡

ማናቸውንም የመለስን የእልቂት ሰለባዎች የማላውቃቸው መሆኔ እርግጥ ነው፡፡

ሆኖም ግን እያንዳንዳቸው የጥቃቱ ሰለባዎች አሁን በህይወት እየኖረ ላለ ሰው እህት፣ ልጅ፣ አባት፣ እናት፣ አጎት፣ አክስት፣ የአጎት ልጅ ወይም ደግሞ ጓደኛ መሆናቸውን አሳምሬ አውቃለሁ፡፡

እያንዳንዳቸው የጥቃቱ ሰለባዎች አባታቸውን፣ እናታቸውን፣ ሴት ልጃቸውን፣ ወንድ ልጃቸውን፣ አጎታቸውን፣ አክስታቸውን፣ የአጎታቸውን ልጅ ወይም ጓደኛቸውን ጥለው የሄዱ መሆናቸውን እና በወገኖቻቸው ላይ የተሰበረ ልብ ጥለው ማለፋቸውን በሚገባ አውቃለሁ፡፡

ሁሉም የጥቃቱ ሰለባዎች ፍቅር ካለበት የቤተሰብ መሰረት የነበሩ መሆናቸውን አውቃለሁ፡፡ ማናቸውም ቢሆኑ በሙስና የተዘፈቁ እና ሌሎችን ዜጎች በማሰቃየት የማይኖሩ እና እራሳቸውን ከሌላው ህብረተሰብ በላይ አድርገው የማያያዩ የእውነተኛ ፍትህ ጥመኞች እንደነበሩ በውል እገነዘባለሁ፡፡

የእልቂቱ ሰለባዎች በህይወት ያሉ ወገኖች በግፍ በአሰቃቂ ሁኔታ ለተገደሉባቸው ብርቅዬ ወገኖቻቸው ካሳ የሚሆን ምንም ዓይነት ነገር ለወሮበላው ለዘ-ህወሀት አገዛዝ በመጠየቅ በጽናት የቆመ ምንም ዓይነት ሰው እንደሌለ አሳምሬ አውቃለሁ፡፡

ማንም ቢሆን በአረመኔው መለስ በግፍ ለተጨፈጨፉበት ወገኖቹ የዘ-ህወሀት ወሮበላ ቡድን በሰው ልጆች ላይ ለፈጸመው ወንጀል ተጠያቂ ነው በማለት ደፍሮ በሕግ ፊት ሊያቆማቸው የሚችል ምንም ዓይነት ሰው እንደሌለ እገነዘባሁ፡፡

በአረመኔው መለስ የግድያ እልቂት የተፈጸመባቸው የቤተሰብ አባላት እና በአሁኑ ጊዜ በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ በህይወት የሚኖሩ ወገኖች አንዳቸውም ቢሆኑ በግፍ በተገደሉባቸው የጥቃቱ ሰላባዎች ስም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የሚናገሩ ሰዎች እንደሌሉ አውቃለሁ፡፡

በአረመኔው መለስ የግድያ እልቂት የተፈጸመባቸው የቤተሰብ አባላት በሚወዷቸው የጥቃቱ ሰለባዎች ስም በመቆም ወንጀለኞችን ለፍትህ አካል ያቀረበ ማንም እደሌለ በሚገባ አውቃለሁ፡፡

በአረመኔው መለስ የግድያ እልቂት የተፈጸመባቸው የቤተሰብ አባላት እና አሁን በህይወት የሚገኙት ወገኖች ለእልቂቱ ሰለባዎች በጽናት በመቆም በየዕለቱ እና በየሳምንቱ እያስታወሰ በእነዚህ ንጹሀን ዜጎች ላይ እልቂትን የፈጸሙ ወሮበሎች ወደ ፍትህ አዳባባይ ለማምጣት እየሞከረ ያለ ሰው እንደሌለ አሳምሬ አውቃለሁ፡፡

በአረመኔው መለስ የግድያ እልቂት የተፈጸመባቸው የቤተሰብ አባላት በሚወዷቸው የጥቃቱ ሰለባዎች ስም በመቆም ወንጀለኞችን ለፍትህ አካል ያቀረበ ማንም እደሌለ በሚገባ አውቃለሁ፡፡

ሆንም ግን ለመለስ የእልቂት ሰለባዎች ድምጽ በመሆን ድምጼን ከፍ በማድረግ በመጮህ ላይ እገኛለሁ፡፡

ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በእያንዳንዱ ሳምንት ለዓለም ለአቀፉ ህዝብ የህሊና ዳኝነት በማቅረብ የእነዚህ ወገኖቻችን ደም የውሻ ደም ሆኖ እንዳይቀር በማሰብ ወደፊት ለፍትህ አካል ለማቅረብ እንዲቻል እያደረግሁት ላለው በጣም ትንሽ የሆነ ነገር ማካካሸ የሚሆን ልዩ ጥቅም የምፈልግ ሰው አይደለሁም፡፡

ለዘጠኝ ተከታታይ ዓመታት ከሰይጣናዊነትጋር በሚደረግ እልህ አስጨራሽ ትግል ምክንያት ሊደረግ የሚችል ምንም ዓይነት ከልክ ያለፈ ኩራት ሊያዝ የሚችልበት ጉዳይ እንዳልሆነ ግልጽ ለማድረግ እፈልጋለሁ፡፡

እኔ የአረመኔው መለስ የእልቂት ሰለባዎች ድምጽ ነኝ፣ ሆኖም ግን ስኬታማ ላልሆነው ጩኸቴ ምንም ዓይነት ምናባዊ ነገር አይታየኝም፡፡

ማንም እንደሚያስበው ሁሉ የእኔ ድምጽ ፍትህን ለማግኘት በጫካ ውስጥ ሆኖ ጥሪ እንደሚመኝ ሰው አይነት ነው፡፡

ህዳር ከማናቸውም ወራት የበለጠ ጨካኝ ወር ሆና ልትፈረጅ ትችላለችን?

እ.ኤ.አ በ2005 በኢትዮጵያ በአረመኔው መለስ እንደተፈጸመው እልቂት ሁሉ በፓሪስ ውስጥ የተፈጸመውንም ሰይጣናዊ የእልቂት ድርጊት እንደዚሁ በተመሳሳይ መልኩ አስታውሰዋለሁ፡፡

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2015 ከፍተኛ ሰይጣናዊ ኃይል ያለው እና እራሱን “የኢራቅ እና የሌቫንት እስላማዊ መንግስት/Islamic State of Iraq and the Levant” (ISIL) (ከዚህም በተጨማሪ እራሱን በሊቢያ የኢራቅ እና የሶርያ አል ሻም እስላማዊ መንግስት/Islamic State of Iraq and (Syria) al-Sham (ISIS) in Libya” እያለ የሚጠራው አሸባሪ ጽንፈኛ ቡድን በሊቢያ 30 የኢትዮጵያ ስደተኞች አንገትን በአሰቃቂ ሁኔታ እየቀላ ጥሏል፡፡

እ.ኤ.አ ህዳር 13/2005 ከISIL ጋር አንድ ዓይነት የሆነው ጽንፈኛ አሸባሪ ቡድን በፓሪስ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎችን እልቂት ፈጽሟል፡፡

ISIL ንጹሀን የፈረንሳይ ዜጎችን እና የሌሎች በፓሪስ ውስጥ ከሚገኙት የ15 ሀገሮች ዜጎችን በመፍጀት እስልምናን እጠብቃሁ ብሏል፡፡

የሸክስፒርን አባባል በመዋስ “ሰይጣን ለእራሱ እኩይ ምግባር ሲል ከመጽሀፍ ቅዱስ (ከቁራን) ይጠቅሳል“ ብለዋል፡፡

በፓሪስ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እልቂት በፈጸመው እና በሊቢያ የኢትዮጵያውያን ንጹሀን ዜጎችን አንገት ለቀላው የአጋንንት ፈረስ የሆነውን የISILን ሰይጣናዊ ድርጊት አስታውሳለሁ እንደዚሁም ደግሞ እጸልያለሁ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ እ.ኤ.አ ህዳር 1938 ሰይጣናዊነት አስከፊ ገጽታውን በተሰበረው የጨለማ መስታወት ውስጥ ያሳየበትን እርጉም ክስተት አስታውሳለሁ፡፡

እ.ኤ.አ ከህዳር 9 -10/1938 ናዚዎች ወደ 100 ገደማ ሚሆኑ ሰላማዊ የአይሁድ ዜጎችን በመግደል 30 ሺህ የሚሆኑትን ደግሞ በቁጥጥር ስር በማዋል እንዲጋዙ አደረጉ፡፡

ናዚዎች በሺዎች የሚቆጠሩ የአይሁዶችን የእምነት ቦታዎች እና የንግድ ተቋማት አቃጠሉ፡፡ ያ ጊዜ የተሰበረ መስታወት የጨለማ ዕለት ነበር፡፡ ያ ጊዜ ለአይሁዶች እልቂት ቀዳሚው ክስተት ነበር፡፡

የጨለማ መስታወት ስባሪን ዕለት ማን ያስታውሰዋል?

አልበርት አነስታይን በአንደ ወቅት እንዲህ በማለት አስጠንቅቀው ነበር፣ “ዓለም ሰይጣናዊ ሰዎች በመኖራቸው ምክንያት ብቻ አይደለም ለመኖር አስቸጋሪ የሆነች ቦታ የሆነችው፡፡ ሆኖም ግን ስለዚህ ሰይጣናዊ ሁኔታ ምንም ነገር ሳያደርጉ ዝም ብለው በሚመለከቱ ሰዎች ምክንያት እንጅ፡፡”

እኔም እንደዚሁ ኢትዮጵያ ሰይጣናዊ ገዥዎች በመኖራቸው ምክንያት አይለደም ለመኖር አስቸጋሪ ሀገር እየሆነችው፣ ሆኖም ግን ስለዚህ ሰይጣናዊ ድርጊት በሀገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ዲያስፖራው ምንም ዓይነት ነገር ባለማድረጋቸው ምክንያት እንጅ እላለሁ፡፡

ሰይጣናዊ ድርጊት በምንም ዓይነት መልኩ በህዳር፣ በታህሳስ፣ በጥቅምት፣ በመስከረም… እንዲፈጸም በፍጹም ልንፈቅድለት አይገባም፡፡

ኦ! ጨካኝነት የህዳር ወር አፍ ነው፡፡

እስቲ እንዲህ ዓይነቱን ሰይጣናዊ ድርጊት በማስመልከት በቶማስ ሁድ የተቋጠሩትን የግጥም ስንኞች እንመልከት፡

ምንም ሙቀት የለም ደስታም ርቋል፣

ጤንነት ተቃውሷል ምቾት ገደል ገብቷል፡፡

የደስታ ስሜት ሁካታ ጫጫታው፣

ከቤተሰብ ነጥፏል አባላት አዝነዋል፡፡

ምንም ጥላ የለም ቢሄድ ሀገር ቢዞር፣

ብርሀኑ ጠፍቷል በአህጉር በሀገር፣

ቢራቢሮ የለም በለምለሟ ምድር፣

ንቧም አቁማለች መስራቷን በመብረር፣

ፍራፍሬ ጠፍቷል ከየብስ ከምድር፣

አበቦች መክነዋል ከወንዝ ሸንተረር፣

ቅጠሎች ጠፍተዋል ከደጋ ከሀሩር፣

ወፎች ተሰውረው ጠፍቷል የሚበር፣

በዚህ በክፉው ወቅት በወርሀ ህዳር፡፡

በአረመኔው መለስ የጥቃት ሰለባ የሆኑ ወገኖቻችን እስከ አሁን ድረስ ፍትህ ያለማግኘታቸውን ጉዳይ በማስመልከት እና በሀገሪቱ ውስጥ ፍትህ የሌለ መሆኑን ይገልጻሉ በሚል እሳቤ እራሴ የቋጠርኳቸውን የግጥም ስንኞች ደግሞ እነሆ፡

መለስ ለፈጃቸው የእልቂት ሰለባዎች፣

መቶ ዘጠና ሶስት ለሚሆኑ ዜጎች፣

ምንም ፍትህ የለም ከቁንጮው እስከታች፡፡

 

ለማን አቤት ይባል ከቶ ምን ይሻላል፣

የንጹሀኖች ደም ከጉድጓድ ይጮሀል፣

ትዛዝ ሰጭው አካል አለሙን ይቀጫል፣

ቅጥር ነፍሰገዳይ ሳይሰጋ ይዞራል፣

ለድጋሜ ጥፋት ጆሮው አቆብቁቧል፣

ደም የጠማው ሆዱ አስሬ ይጮሀል፣

እንደራበው ዘንዶ ደጋግሞ ያዛጋል፡፡

 

መለስ ለፈጃቸው ለወንዱ ለሴቱ፣

ላዋቂው ለልጁ ላሮጊት ባልቴቱ፣

ለወንድም ለህቱ ለናቱ ላባቱ

ህይወት ለሚገፋው በተከፋ አንጀቱ፣

ምንም ካሳ የለም ቢጮህ ቢታክቱ፡፡

 

በሕገወጥ መንገድ ታስረው ለማቀቁት፣

የጋነምን እሳት በቁማቸው ላዩት፣

ለበርካታ ጊዚያት እስር ቤት ለኖሩት፣

የተለየ ሀሳብ ደፍረው ላራመዱት፣

ወንጀልን ሳይሰሩ በግፍ ለታሰሩት፡፡

 

እውቅና እኮ አይሰጥ ለነጻነታቸው፣

ምንም ዓይነት ወንጀል ላለመስራታቸው፣

እንደበግ ተስበው ለመታሰራቸው፣

ሲፈልጉ ፈተው ለሚያባርሯቸው፡፡

በግፍ ተሰውረው በሸፍጥ ለጠፉት ፣

 

ይሙቱ ይኑሩ ለማይታወቁት፣

ዳብዛቸውን ላጡት እርም ላላወጡት፣

ለመከራ ስቃይ አጋሰስ ለሆኑት፣

ይብላኝ ለወላጆች በክንቱ ለቀሩት፣

በሀሳብ በሀዘን ለተኮማተሩት፡፡

 

ለፈጸሙት እልቂት ንስሀ ሳይገቡ፣

ለሌላ ዙር ጥፋት እያነበነቡ፣

በእብሪት ተወጥረው ምንም ሳያስቡ፣

እንደ ሰው ሳይኖሩ እንደበግ ደለቡ፡፡

ጥቅምት መስከረም ህዳር እና ታህሳስ፣

 

ህዝብን ያስፈጀበት እብሪተኛው መለስ፣

ሌት ቀን እንጸልይ ደግሞ ላይመለስ፡፡

ይቅርታ አይደረግ መለስ ላረዳቸው፣

ቅጥር ነፍሰ ገዳይ ላዘመተባቸው፣

እንደ አውሬ ታድነው አፈር ለበላቸው፣

 

የማለዳ ጤዛ ለሆነ ዕቅዳቸው፣

ፍትህ እስክትመጣ እስኪታይ ፍዳቸው፣

ለምን ጊዜም ቢሆን ልዩ ሰማት ናቸው፡፡

 

እልቂት እና ህዳር፣

ወንጀል ላለመፍጠር፣

ምለው ተገዝተው፣

ላንገናኝ ብለው፣

ስንብት አርገዋል

ግፍ በዝቶባቸዋል፡፡

ግፍ እና መከራን የምንጠላ ከልብ፣

ህዳርን ሳንሰለች ምንጊዜም እናስብ፡፡

የአረመኔውን የመለስን እልቂት ሁልጊዜ አስባለሁ ምክንያቱም ልረሳው እና ልተወው እአልችልም! በፍጹም!

እ.ኤ.አ በ2005 በመለስ እብሪት የእልቂት ሰለባ የሆኑትን ወገኖቼን አስታውሳቸዋለሁ፡፡

እያንዳንዳቸውን አንድ በአንድ አስታውሳቸዋለሁ፡፡

እነዚህ ንጹሀን ዜጎች ለእኔ የቁጥር ጉዳይ አይደሉም፡፡

ለእኔ መለስ እና የዘ-ህወሀት ወሮበላ እልቂት የፈጸሙባቸው እያንዳንዳቸው ልዩ ናቸው፡፡

በምንም ዓይነት መልኩ እናት የመሆን ጸጋውን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የተነጠቁትን ወጣት ሴቶች ምንጊዜም አስታውሳቸዋለሁ፡፡

በምንም ዓይነት መልኩ አባት የመሆን ጸጋውን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የተነጠቁትን ወጣት ወንዶች ምንጊዜም አስታውሳቸዋለሁ፡፡

ወላጆቻቸው በጠራራ ጸሀይ እንደበግ የታረዱባቸውን ወላጅ ያጡ ህጻናት ምንጊዜም አስታውሳቸዋለሁ፡፡

መለስ እና ዘ-ህወሀት በአሰቃቂ ሁኔታ ልጃቻቸውን በግፍ ያረዱባቸውን እና ምንጊዜም ቢሆን ማግኘት የማይችሉትን የልጅ ልጃቻቸውን አቅፈው ለመሳም ፍጹም ያልታደሉትን አባቶች እና እናቶች ምንጊዜም አልረሳቸውም፡፡

በአረመኔው የመለስ እልቂት ተዋናይ የሆኑትን ወንጀለኞች በምንም ዓይነት መልኩ ምንጊዜም ቢሆን በፍጹም አልረሳቸውም፡፡

የእልቂቱ ዋና መሪ ተዋናይ በመሆን ድርጊቱን ሲፈጽሙ የነበሩትን 237 ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች ምን ጊዜም ቢሆን በፍጹም አልረሳቸውም፡፡

በጥላቻ የተሞሉትን እና እንደዚያ ዓነቱን የእልቂት ዕቅድ ዋና ስልት ነዳፊ የሆኑትን እና እራሳቸውን ከተዘፈቁበት የሰብአዊ እልቂት ወንጀል ነጻ ለማድረግ ጣቶቻቸውን ወደ ፖሊስ ኃይል የሚቀስሩትን አረመኔ እና ጨካኝ አውሬ ፍጡሮችን ምንጊዜም ቢሆን በምንም ዓይነት ሁኔታ አልረሳቸውም፡፡

ምንጊዜም ቢሆን ህዳርን፣ ታህሳስን እና ጥርን እንዲሁም የካቲትን እና ሚያዝያን… ሁሉንም ሁልጊዜ አስታውሳለሁ፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ አልረሳቸውም፡፡

ተ.ቁ         ስም          ጾታ          እድሜ      ስራ

1              ሬቡማ ኢርጋ           ወ             34           ግንበኛ

2              መልሳቸው አለምነው               ወ             16           ተማሪ

3              ሀድራ ኦስማን          ወ             22           አይታወቅም

4              ጃፋር ኢብራሂም     ወ             28           ቢዝነስ

5              መኮንን     ወ                           17             አይታወቅም

6              ወልደሰማያት           ወ             27

7              ባህሩ ደምለው         ወ                            አይታወቅም

8              ፈቃደ ነጋሽ               ወ             25           መካኒክ

9              አብርሀም ይልማ      ወ             17           ታክሲ ነጂ

10           ያሬድ እሸቴ              ወ             23           ቢዝነስ

11           ከበደ ገ/ህይወት       ወ             17           ተማሪ

12           ማቴዎስ ፍልፍሉ      ወ             14           ወንድ

13           ጌትነት ወዳጆ           ወ             48           ቢዝነስ

14           ቃሲም ራሽድ           ወ             21           መካኒክ

15           ሸውሞሊ  ወ                            22            ቢዝነስ

16           አሊየ ኢሳ ወ                             20           የቀን ስራ

17           ሣምሶን ያዕቆብ         ወ             23           የህዝብ ማመላለሻ

18           አለባለው አበበ        ወ             18           ተማሪ

19           በልዩ ዛ     ወ                             18           ትራንስፖርት ረዳት

20           የሱፍ ጀማል             ወ             23           ተማሪ

21           አብርሃም አገኘሁ     ወ             23           ትራንስፖርት ረዳት

22           መሀመድ በቃ           ወ             45           አርሶ አደር

23           ረዴላ አወል             ወ             19           የታክሲ ረዳት

24           ሀብታሙ ኡርጋ       ወ             30           ቢዝነስ

25           ዳዊት ጸጋዬ              ወ             19           መካኒክ

26           ገዛኸኝ ገረመው        ወ             15           ተማሪ

27           ዮናስ አበራ              ወ             24           አይታወቅም

28           ግርማ ወልዴ           ወ             38           ሾፌር

29           ደስታ ብሩ                ሴ                             37                          ቢዝነስ

30           ለገሳ ፈይሳ                ወ             60           ቢዝነስ

31           ተስፋዬ ቡሽራ         ወ             19           ጫማ ጠጋኝ

32           ቢንያም ደገፋ           ወ             18           ስራ አጥ

33           ሚሊዮን ሮቢ           ወ             32           ትራንስፖርት ረዳት

34           ደረጀ ደኔ  ወ                             24           ተማሪ

35           ነብዩ ኃይሌ               ወ             16           ተማሪ

36           ምትኩ ምዋለንዳ      ወ             24           ዶመስቲክ ሰራተኛ

37           አንዋር ሱሩር           ወ             22           ቢዝነስ

38           ንጉሴ ዋብግነ           ወ             36           ዶመስቲክ ሰራተኛ

39           ዙልፋ ሀሰን              ሴ             50           የቤት ሰራተኛ

40           ዋሲሁን ከበደ           ወ             16           ተማሪ

41           ኤርሚያስ ከበደ       ወ             20           ተማሪ

42           00428    ወ             25           አይታወቅም

43           00429                                   አይታወቅም

44           00430                                   30           አይታወቅም

45           አዲሱ በላቸው         ወ             25           አይታወቅም

46           ደመቀ አበበ              ወ                            አይታወቅም

47           00432                                   22           አይታወቅም

48           00450                                   20           አይታወቅም

49           13903                                   25           አይታወቅም

50           00435                                   30           አይታወቅም

51           13906                                   25           አይታወቅም

52           ተማም ሙክታር      ወ             25           53

53           በየነ በዛ    ወ                             25           አይታወቅም

54           ወሰን አሰፋ              ወ             25           አይታወቅም

55           አበበ አንተነህ           ወ             30           አይታወቅም

56           ፈቃዱ ኃይሌ            ወ             25           አይታወቅም

57           ኤልያስ ጎልቴ            ወ                            አይታወቅም

58           ብርሃኑ ዋርካ            ወ                            አይታወቅም

59           አሸብር መኩሪያ       ወ                            አይታወቅም

60           ዳዊት ሰማ               ወ                            አይታወቅም

61           መርሀጽድቅ ሲራክ   ወ                            አይታወቅም

62           በለጠ ጋሻውጠና      ወ                            አይታወቅም

63           በኃይሉ ተስፋየ        ወ             20           አይታወቅም

64           21760                                   18           አይታወቅም

65           21523                                   25           አይታወቅም

66           11657                                   24           አይታወቅም

67           21520                                   21           አይታወቅም

68           21781                                   60           አይታወቅም

69           ጌታቸው አዘዘ          ወ             45           አይታወቅም

70           21762                                   75           አይታወቅም

71           11662                                   45           አይታወቅም

72           21763                                   25           አይታወቅም

73           13087                                   30           አይተወቅም

74           21571                                   25           አይታወቅም

75           21761                                   21           አይታወቅም

76           21569                                   25           አይታወቅም

77           13088                                   30           አይታወቅም

78           እንዳልካቸው ገብርኤል            ወ             27           አይታወቅም

79           ኃይለማርያም አምባዬ              ወ             20           አይታወቅም

80           መብራቱ ዘውዱ                       ወ             27           አይታወቅም

81           ስንታየሁ በየነ                          ወ             14           አይታወቅም

82           ታምሩ ኃይለሚካኤል               ወ                            አይታወቅም

83           አድማሱ አበበ                          ወ             45           አይታወቅም

84           እቴነሽ ይማም                          ሴ             50           አይታወቅም

85           ወርቄ አበበ                              ወ             19           አይታወቅም

86           ፈቃዱ ደግፌ                            ወ             27           አይታወቅም

87           ሸምሱ ካሊድ                            ወ             25           አይታወቅም

88           አብዱዋሂብ አህመዲን             ወ             30           አይታወቅም

89           ታከለ ደበሌ                             ወ             20           አይታወቅም

90           ታሰሰ ፈይሳ                              ወ             38           አይታወቅም

91           ሶሎሞን ተስፋይ                       ወ             25           አይታወቅም

92           ቅጣው ወርቁ                           ወ             25           አይታወቅም

93           ደስታ ነጋሽ                               ወ             30           አይታወቅም

94           ይለፍ ነጋ  ወ                                             15           አይታወቅም

95           ዮሀንስ ኃይሌ                           ወ             20           አይታወቅም

96           በኃይሉ ብርሃኑ                        ወ             30           አይታወቅም

97           ሙሉ ሶሬሳ                               ወ             50           አይታወቅም

98           አይታወቅም                             ሴ                            የቤት እመቤት

99           ቴዎድሮስ ወ                                             23           አይታወቅም

100         አይታወቅም                             ወ                            ጫማ ሰሪ

101         በኃይሉ ብርሃኔ                         ወ             30           አይታወቅም

102         ሙሉ ሶሬሳ                               ሴ             50           የቤት እመቤት

103         ቴዎድሮስ ኃይሌ                       ወ             23           ጫማ ሻጭ

104         ደጀኔ ይልማ                             ወ             18           መጋዝን ጠባቂ

105         ኡጋሁን ወልደገበርኤል            ወ             18           ተማሪ

106         ደረጀ ማሞ                               ወ             28           አናጺ

107         ረጋሳ ፈይሳ                               ወ             55           ላውንድሪ ሰራተኛ

108         ቴዎድሮስ ገብረወልድ              ወ             28           የግል ንግድ

109         መኮንን ገብረእግዚአብሔር      ወ             20           መካኒክ

110         ኤሊያስ ገ/ጊዮርጊስ                 ወ             23           ተማሪ

111         አብርሃም መኮንን                     ወ             21           የቀን ሰራተኛ

112         ጥሩወርቅ ገ/ጻዲቅ    ሴ             41           የቤት እመቤት

113         ሄኖክ መኮንን           ወ             28           አይታወቅም

114         ጌቱ መረታ               ወ             24           አይታወቅም

115         ክብነሽ ታደሰ            ሴ             52           አይታወቅም

116         መሳይ ስጦታው       ወ             29           የግል ንግድ

117         ሙልዓለም ወይሳ     ሴ             15           ተማሪ

118         አያልሰው ማሞ        ወ             23           አይታወቅም

119         ስንታሁ ለመሰ         ወ             24           የቀን ሰራተኛ

120         ጸዳለ ቢራ                ሴ             ሴ             50           የቤት እመቤት

121         ዓባይነህ ሴራሴድ     ወ             35           ልብስ ስፌት

122         ፍቅርያም ተሊላ        ወ             18           ሾፌር

123         ዓለማየሁ ገርባ         ወ             26           አይታወቅም

124         ጆርጅ አበበ              ወ             36           የግል ትራንስፖርት

125         ሀብታሙ ዘገዬ         ወ             16           ተማሪ

126         ምትኩ ገ/ስላሴ        ወ             24           ተማሪ

127         ትዕዛዙ መኩሪያ       ወ             24           የግል ንግድ

128         ፈቃዱ ዳልጌ             ወ             36           ልብስ ሰፊ

129         ሸዋረጋ ወ/ጊዮርጊስ ወ             38           የቀን ሰራተኛ

130         ዓለማየሁ ዘውዴ      ወ             32           የቴክስታይል ሰራተኛ

131         ዘላለም ገ/ጻዲቅ        ወ             31           የታክሲ ሾፌር

132         መቆያ ታደሰ             ሴ             19           ተማሪ

133         ሀይልዬ ሁሴን          ወ             19           ተማሪ

134         ፍስኃ ገ/ጻዲቅ          ሴ             23           የፖሊስ ተቀጣሪ

135         ወጋየሁ አርጋው       ወ             26           ስራ ፈላጊ

136         መላኩ ከበደ             ወ             19           አይታወቅም

137         ዓባይነህ ኦራ             ወ             25           ልበስ ሰፊ

138         አበበች ሆለቱ           ሴ             50           የቤት እመቤት

139         ደመቀ ጀንበሬ           ወ             30           አርሶ አደር

140         ክንዴ ወረሱ             ወ             22           ስራ ፈላጊ

141         እንዳለ መድህን        ወ             23           የግል ቢዝነስ

142         ዓለማየሁ ወልዴ      ወ             24           መምህር

143         ብስራት ደምሴ         ወ             24           መኪና አስመጭ

144         መስፍን ኃ/ጊዮርጊስ ወ             23           የግል ቢዝነስ

145         ወሊኦ ዳሪ                ወ                             18           የግል ቢዝነስ

146         በኃይሉ ገ/መድህን   ወ             20           የግል ቢዝነስ

147         ሲረጅ ኑሪ ሰይድ      ወ             18           ተማሪ

148         ኢዮብ ገ/መድህን     ወ             25           ተማሪ

149         ዳንኤል ሙሉጌታ     ወ             25           የቀን ሰራተኛ

150         ቴዎድሮስ ደገፋ        ወ             25           የጫማ ፋብ. ሰራተኛ

151         ጋሻው ሙሉጌታ       ወ             24           ተማሪ

152         ከበደ ኦርኬ              ወ             22           ተማሪ

153         ሌቺሳ ፋታሳ             ወ             21           ተማሪ

154         ጃጋማ በሻ                ወ                             20           ተማሪ

155         ደበላ ጉታ ወ                             15           ተማሪ

156         መላኩ ፈይሳ             ወ             16           ተማሪ

157         እልፍነሽ ተክሌ         ሴ             45           አይታወቅም

158         ሀሰን ዱላ ወ                             64           አይታወቅም

159         ሁሴን ሀሰን ዱላ       ወ             25           አይታወቅም

160         ደጀኔ ደምሴ             ወ             15           አይታወቅም

161         የማይታወቅ

162         የማይታወቅ

163         ዘመድኩን አግደው   ወ             18           አይታወቅም

164         ጌታቸው ተረፈ         ወ             16           አይታወቅም

165         ደለለኝ አለሙ          ወ             20           አይታወቅም

166         ዩሱፍ ኡመር            ወ             20           አይታወቅም

167         መኩሪያ ተበጀ          ወ             22           አይታወቅም

168         ባደመ ተሻማሁ        ወ             20           አይታወቅም

169         አምባው ጌታሁን      ወ             38           አይታወቅም

170         ተሾመ ኪዳኔ            ወ             65           የጤና ሰራተኛ

171         ዮሰፍ ረጋሳ               ወ                            አይታወቅም

172         አብዩ ንጉሴ              ወ                            እንግሊዝ

173         ታደለ በሀጋ              ወ                            አይታወቅም

174         አበበ ሀማ                ወ             ወ            አይታወቅም

175         ገብሬ ሞላ ወ             ወ                          አይታወቅም

176         ሰይዴን ኑረዲን        ወ                            አይታወቅም

177         እነየው ጸጋዬ            ወ             32           የትራንስፖርት ረዳት

178         አብዱራህማን ፈረጂ                ወ             32           የእንጨት ሰራተኛ

179         አምባው ብጡል       ወ             60           ቂዳ ፋብሪካ ሰራተኛ

180         አብዱለመናን ሁሴን ወ             28           የግል ቢዝነስ

181         ጅግሳ ሰጠኝ             ወ             18           ተማሪ

182         አሰፋ ነጋሳ                ወ             ወ          33           አናጺ

183         ከተማ እንቁ             ወ             23           ልብስ ሰፌት

184         ክብረት እልፍነህ      ወ             48           የግል ጥበቃ

185         ኢዮብ ዘመድኩን     ወ             24           የግል ቢዝነስ

186         ተስፋዬ መንገሻ        ወ             15           የግል ቢዝነስ

187         ካፕቴን ደበሳ ቶሎሳ  ወ             58           የግል ቢዝነስ

188         ትንሳኤ ዘገዬ             ወ             14           ልብስ ስፌት

189         ኪዳና ሽኩር             ወ             25           የቀን ሰራተኛ

190         አንዷለም ሽበለው   ወ             16           ተማሪ

191         አዲሱ ተስፋሁን       ወ             19           የግል ቢዝነስ

192         ካሳ በዬነ   ወ             ወ          28           ልብስ ሽያጭ

193         ይታገሱ ሲሳይ          ወ             22           አይታወቅም

194         አይታወቅም                            22

ፖሊስ እና የደህንነት ኃይሎች ወደ ሰላማዊ ሰልፈኞች ሲተኩሱ በተባራሪ ጥይት ተመትተው ህይወታቸውን ያጡ የሚከተሉት ናቸው፡ ነጋ ገብሬ፣ ጀበና ደሳለኝ፣ ሙለታ እርቆ፣ ዮሀንስ ሶሎሞን፣ አሸናፊ ደሳለኝ፣ ፈይሳ ገብረመንፈስ፡፡

እ.ኤ.አ ህዳር 2/2005 በቃላቲ እስር ቤት በሕግ ከለላ ጥላ ስር የነበሩትን እና በመንግስት ታጣቂዎች በዚያው በእስር ቤት ክፍሎቻቸው ውስጥ በጥይት እየተደበደቡ ያለቁትን የሕግ አስረኛ ወገኖች አስታውሳለሁ፡፡ አነዚያ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ወገኖች የሚከተሉትን ያካትታል፡

ተ.ቁ         ስም          ጾታ          አድሜ                                                   ስራ

1              ጠይብ ሸምሱ መሀመድ            ወ                            የጦር መሳሪያ ደብቀሀል በሚል ክስ የተመሰተተበት

2              ሳሊ ከበደ                                 ወ                            ምንም ዓይነት የተመሰረተበት ክስ የለም

3              ሰፊው እንድሪስ ታፈሰ ወረደ   ወ                            በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

4              ዘገዬ ተንኮሉ በላይ                   ወ                            በዘረፋ ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

5              ቢያድግልኝ ታመነ                    ወ                            የክሱ ምክንያት ያልታወቀ

6              ገብሬ መስፍን ዳኘ                    ወ                            የክሱ ምክንያት ያልታወቀ

7              በቀለ አብርሀም ታዬ                                ወ                            ሁከት በመፍጠር ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

8              አበሻ ጉታ ሞላ                         ወ                            የክሱ ምክንያት ያልታወቀ

9              ኩርፋ መልካ ተሊላ                  ወ                            በመስፈራራት ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

10           በጋሻው ተረፈ ጉደታ                            ወ                            ሰላም በማደፍረስ ክስ የተመሰረተበት

11           አብዱልወሀብ አህመዲን          ወ                            በዘረፋ ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

12           ተስፋዬ አብይ ሙሉጌታ          ወ                            የጦር መሰሪያ ደብቀሀል በሚል ክስ የተመሰረተበት

13           አዳነ ቢረዳ                              ወ                            በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

14           ይርዳው ከርሰማ                      ወ                            የክሱ ምክንያት የማይታወቅ

15           ባልቻ አለሙ ረጋሳ                   ወ                            በዘረፋ ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

16           ቡሽ በለው ወዳጆ                    ወ                            የክሱ ምክንያት የማይታወቅ

17           ዋለልኝ ታምሬ በላይ                ወ                            በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

18           ቸርነት ኃይሌ ቶላ                     ወ                            በዘረፋ ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

19           ተማም ሸምሱ ጎሌ                    ወ                            የክሱ ምክንያት የማይታወቅ

20           ገበየሁ በቀለ አለነ                     ወ                            የክሱ ምክንያት የማይታወቅ

21           ዳንኤል ታዬ ለኩ                     ወ                            የክሱ ምክንያት የማይታወቅ

22           መሀመድ ቱጂ ቀኔ                     ወ                            የክሱ ምክንያት የማይታወቅ

23           አብዱ ነጅብ ኑር                       ወ                            የክሱ ምከንያት የማይታወቅ

24           የማታው ሰርቤሎ                     ወ                            በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

25           ፍቅሩ ናትናኤል ሰውነህ            ወ                            በማስፈራራት ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

26           ሙኒር ከሊል አደም                 ወ                            ሁከት በመፍጠር ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

27           ኃይማኖት በድሉ ተሾመ           ወ                            ሕግ በመጣስ ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

28           ተስፋዬ ክብሮም ተክኔ             ወ                            በዘረፋ ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

29           ወርቅነህ ተፈራ ሁንዴ              ወ                            የክሱ ምክንያት የማይታወቅ

30           ሲሳይ ምትኩ ሁነኝ                   ወ                            በማጭበርበር ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

31           ሙሉነህ አይናለም ማሞ           ወ                            የክሱ ምክንያት የማይታወቅ

32           ታደሰ ሩፌ የኔነህ                      ወ                            በማስፈራራት ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

33           አንተነህ በየቻ ቀበቻ                 ወ                            የጦር መሳሪያ ደብቀሀል በሚል ክስ የተመሰረተበት

34           ዘሪሁን መረሳ                           ወ                            በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ክስ የተመሰረተበት

35           ወጋየሁ ዘሪሁን አርጋው           ወ                            በዘረፋ ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

36           በከልካይ ታምሩ                       ወ                            የክሱ ምክንያት የማይታወቅ

37           የራስወርቅ አንተነህ                  ወ                            በማጭበርበር ወንጀል ክስ የተመሰረተብት

38           ባዝዘው ብርሀኑ                       ወ                            በግረሰዶማዊነት የድርጊት ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

39           ሶሎሞን ኢዮብ ጉታ                 ወ                            በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

40           አሳዩ ምትኩ                             ወ                            በማስፈራራት ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

41           ጋሜ ኃይሉ ዘገዬ                       ወ                            ሁከት በመፍጠር ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

42           ማሩ እናውጋው ድንበሬ           ወ                            በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

43           እጅጉ ምናለ                             ወ                            በግድያ ሙከራ ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

44           ኃይሉ ቦስኔ ሀቢብ                    ወ                            ለወንጀለኛ መጠለያ በመስጠት ወንጀል የተከሰሰ

45           ጥላሁን መሰረት                       ወ                            የክሱ መክንያት የማይታወቅ

46           ንጉሴ በላይነህ                          ወ                            በዘረፋ ወንጅል ክስ የተመሰረተበት

47           አሸናፊ አበባው                        ወ                            የክሱ ምክንያት የማይታወቅ

48           ፈለቀ ድንቄ                              ወ                            የክሱ ምክንያት የማይታወቅ

49           ጀንበሬ ድነቅነህ ቢለው            ወ                            ጸጥታ በማደፍረስ ውንጀል ክስ የተመሰረተበት

50           ቶለሳ ወርቁ ደበበ                     ወ                            በዘረፋ ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

51           መካሻ በላይነህ ታምሩ              ወ                            ሁከት በመፍጠር ወንጅል ክስ የተመሰረተበት

52           ይፍሩ አደራው                         ወ                            የክሱ ምክንያት የማይታወቅ

53           ፋንታሁን ዳኘ                          ወ                            የክሱ ምክንያት የማይታወቅ

54           ጥበቡ ዋከኔ ቱፋ                      ወ                            የጦር መሳሪያ ደብቀሀል በሚል ክስ የተመሰረተበት

55           ሶሎሞን ገብረአምላክ                ወ                            ሁከት በመፍጠር ክስ የተመሰረተበት

56           ባንጃው ቹቹ ካሳሁን                 ወ                            በዘረፋ ወንወጀል ክስ የተመሰረተበት

57           ደመቀ አበጀ                             ወ                             በግድያ ሙከራ ወንጀል ክስ የተመሰረተበት

58           እንዳለ እውነቱ መንግስቴ         ወ                            የክሱ ምክንያት የማይታወቅ

59           ዓለማየሁ ገርባ                         ወ                            እ.ኤ.አ በ2004 የአ.አ.ዩ ተማሪዎች ካደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የታሰረ

60           መርኮታ ኢዶሳ                         ወ                            የክሱ ምክንያት ያልታወቀ

የኔሰው ገብሬን አስታውሳለሁ፣

Yenesewእ.ኤ.አ በ11/11/11 የኔሰው ገብሬ የሚባል የ29 ዓመት እድሜ የነበረው ኢትዮጵያዊ የትምህርት ቤት መምህር እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች በደቡብ ኢትዮጵያ ዳውሮ ዞን በተርጫ ከተማ ከህዝብ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ወጣ ብሎ በሚገኝ በአንድ ቦታ ላይ በእራሱ ላይ እሳት በመለኮስ እራሱን አቃጠለ፡፡ ለሶስት ቀናት ቁስለኛ ሆኖ ከቆዬ በኋላ ህይወቱ ሊያልፍ ችሏል፡፡ በእራሱ ላይ ያንን የመሰለ አሰቃቂ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት የኔሰው ከመሰብሰቢያ አዳራሹ ውጭ ተሰብስቦ ለነበረው የአካባቢው ህዝብ እንዲህ የሚል ንግግር አድርጎ ነበር፣ “ፍትህ እና ፍትሀዊ አስተዳደር በሌለባት ሀገር፣ ሰብአዊ መብቶች በሚደፈጠጡባት እና በማይከበሩባት ሀገር እራሴን መስዋዕት በማድረግ እነዚህን ወጣቶች ነጻ አወጣለሁ፡፡“

ሀናህ አረንት በተራ ሰዎች በመንግስት ስም፣ በኃይማኖት ስም፣ በርዕዮት ዓለም ስም…”ስለሰይጣናዊነት አሰልቺ ባህሪ“ ይፈጠራል በማለት ተናግረው ነበር፡፡

እኔ የበለጠ ትኩረት የምሰጠው ግዴለሽነትን ለሚያስከትለው እና ለአጭር ጊዜ ብቻ ለሚቆየው ለሰይጣናዊነት ድርጊት ነው፡፡

በእኛ ጊዜ እጅግ አስከፊ የሆነ ሰይጣናዊነት ድርጊት መፈጸም በህሊናችን ውስጥ ሊታሰብ የማይገባ እና የማይሞከር ነበር፡፡ አሁን ግን ሰይጣናዊ ድርጊት አይኖርም ብሎ ማሰብ በጠራራ ጸሐይ ላይ አንድ ኩብ በረዶ ምንም ነገር ሳይቀልጥ ይቀመጣል እንደማለት ያህል ነው፡፡

ለስጣናዊነት ስሜትን ልንሰጥ አይገባም፡፡

በጣም በአስደንጋጭ ሁኔታ ውስጥ ነን፣ ሆኖም ግን ይህ የሚቆየው በጣም ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለቀጣዩ ታሪካዊ የሰይጣናዊነት ድርጊት ተዘጋጅተን እንጠብቃለን፡፡

ለሰይጣናዊ ድርጊት ግዴለሾች ሆነናል፡፡ ሰይጣናዊነት የሞራል ስብዕና ኃይላችንን እንደ መድኃኒት መስጫ መርፌ ሲሪንጅ ጥርግ አድርጎ መጦታል፡፡ ሰይጣናዊነት ድርጊት ነብሶቻችንን አዳክሟል፡፡

የሞራል ኃይላችንን ጠብቀን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለመሸጋገር አቅም አንሶናል፡፡

ግዴለሽነት ለሞራል ልዕልና የሞት መንስኤ ለመሆን በቅቷል፡፡

በሞራል ልዕልና አመድ ውስጥ ሰይጣናዊ ድርጊት ድልን ይቀዳጃል፡፡

ተናገሩ! ስኳር ለካንሰር ምክንያት እንደሚሆን ሁሉ ዝምታም ለሰይጣዊ ድርጊት ይዳርጋል ሲሉ

እውነትም ሶልዘኒተሲን ትክክል ናቸው፡፡

ሰይጣናዊ ድርጊት ሲፈጸም በግዴለሽነት ዝም ብለን ተቀምጠን የምንመለከት ከሆነ እና ምንም ነገር ሳናደርግ ጉዳዩን በጥልቅ ቀብረን በመያዝ ህይወትን የምንገፋ ከሆነ ሰይጣናዊነትን እንደ ችግኝ እየተከልነው ነው፣ እናም በቀጣይ ጊዚያት በሺዎች እጥፍ እየሆነ እየተፈጸመ ሲያወድመን ይኖራል፡፡

ስለዘ-ህወሀት፣ መሪዎቹ፣ ደጋፊዎቹ እና ግብረአበር ሎሌዎቹ ሰይጣናዊነት ድርጊት ከዳር ቆመን ዝም ብለን የምንመለከት ከሆነ ሰይጣናዊነትን እራሱን እንደችግኝ እየተከልነው ነው፣ እና በቀጣይ ህይወታችን ውስጥ ሺህ ጊዜ በስብዕናች እና በህይታችን ላይ ይፈጸማል፡፡

በእውነት ሶልዘኒተሲን ያሉት ትክክል ነው፡፡

ሰይጣናዊ ድርጊት ፈጻሚዎችን ሳንቀጣቸው ወይም ሳንተቻቸው የምንቀር ከሆነ እነዚህ ሰይጣናዊ ድርጊቶች እስከ እርጅና ዘመናቸው ድረስ እንዲቀጥሉ መፍቀዳችን ብቻ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ከዚህም በላይ ፍትህን ከመሬት ውስጥ በጥልቀት ቀብረን መሰረቱን በመጣል ሰይጣናዊነት ድርጊትን ለቀጣዩ ትውልድ ማውረሳችን ነው፡፡

የዘ-ህወሀትን ሰይጣናዊ ድርጊት ፈጻሚዎች ካልቀጣናቸው ወይም ደግሞ በትችት ካላስተካከልናቸው የፍትህን በጥልቀት መቀበር መሰረት እየጣልን እና የሰይጣዊ ድርጊትን እንዳለ ለመጨው ትውልድ ማስተላለፋችን ማለት ነው፡፡

ሶልዘኒተሲን ትክክል ናቸው፡፡

ወጣቶች በመሬት ላይ የሚፈጸሙ መጥፎ ድርጊቶች ሁልጊዜ ሀብትን ሊያስገኙ እስከቻሉ ድረስ ቅጣት ሊጣልባቸው አይገባም የሚል ሀሳብን ያራምዳሉ፡፡ ይህም እስከሆነ ድረስ ሰይጣናዊ ድርጊቶች ሁልጊዜ እያደጉ ይሄዳሉ፡፡

በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውን የዘ-ህወሀት፣ መሪዎች፣ ደጋፊዎች እና ግብረ አበር ሎሌዎቻቸው ሁልጊዜ ሀብትን እስካስገኙ ድረስ በመሬት ላይ መቀጣት የለባቸውም፡፡ በዚህም መሰረት ወጣት ኢትዮጵያውያን ግዴለሽነትን አያጠናከሩ ይሄዳሉ የሚል አመክንዮ አለ፡፡

ሶቪዬት ራሽያ ለህዝቦቿ ግልጽ እስር ቤት እንደነበረችበት ጊዜ ሁሉ በአሁኑ ጊዜም 100 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንም በዘ-ህወሀት ግልጽ እስር ቤት ውስጥ እጅ ከወርች በመቀፍደድ ታስረው አሳር ፍዳቸውን በመቀበል ላይ እንደሚገኙ አምናለሁ፡፡

እንደ ሶቪዬት ራሽያ ሁሉ በዘ-ህወሀት አገዛዝም በእንደዚህ ያለች ሀገር መኖር ምቾትን የሚነሳ፣ አስፈሪ ነገር ነው!

በዚህም ምክንያት ነው የኔሰው ገብሬ እንዲህ የሚሉትን ቃላት በማስፈር ህይወቱን ያጠፋው፣ “ፍትህ እና ፍትሀዊ አስተዳደር በሌለባት ሀገር፣ ሰብአዊ መብቶች በሚደፈጠጡባት እና በማይከበሩባት ሀገር እራሴን መስዋዕት በማድረግ እነዚህን ወጣቶች ነጻ አወጣለሁ፡፡“

እ.ኤ.አ በ2005 በአረመኔው መለስ እልቂት የተፈጸመባቸውን የጥቃት ሰለባ ወገኖች እግዚአብሔር አምላክ ነብሳቸውን በገነት ያኑርልን፡፡

የእነዚህ ንጹሀን ዜጎችን ህይወት በከንቱ የቀጠፉ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች አንድ ቀን ፍትህ ወደ አደባባይ በመምጣት ማጅራታቸውን አንቃ ለፍርድ እስከምታቀርባቸው ድረስ ደረታቸውን ነፍተው እስኪያቀረሻቸው እየበሉ እና አልኮላቸውን እየገለበጡ የእንስሳነት ዓይነት ኑሮን ይኖራሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ2005 በአረመኔው መለስ የግድያ ጥቃት ሰለባ የሁኑትን ንጹሀን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ታስታውሳላችሁን?

======================

[1] በአረመኔው መለስ እልቂት ለተፈጸመባቸው ወገኖቻችን ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ለምትፈልጉ “በኢትዮጵያ በሰው ልጆች ላይ የተፈጸመ ወንጀል፡ እ.ኤ.አ በሰኔ እና በህዳር በአዲስ አበባ የተካሄደ እልቂት/Crime Against Humanity in Ethiopia: The Addis Ababa Massacres of June and November“ በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ተሟጋች በሆነው በያሬድ ኃይለማርያም የተዘጋጀውን እና እ.ኤ.አ ግንቦት 15/2006 ለአውሮፓ ፓርላማ የልማት እና የውጭ ጉዳይ እና ለሰብአዊ መብት ጥበቃ ንኡስ ኮሚቴ/Extraordinary Joint Committee Meeting The European Parliament Committees on Development and Foreign Affairs, and Sub-Committee on Human Rights, May 15, 2006 አስቸኳይ የጋራ ኮሚቴ ጉባኤ የቀረበውን ምስክርነት መመልከት ይቻላል፡፡

[2] በአጣሪ ኮሚሽኑ የተያዘው የ193 የእልቂት ሰለባ የሆኑ ንጹሀን ዜጎች ስም ዝርዝር እ.ኤ.አ ከሰኔ 6-8/2005 እና ከህዳር 1-4/2005 ድረስ እና ኮሚሽኑ በእነዚህ ቀናት ብቻ ያለውን ሁኔታ እንዲያጣራ የተገደደ በመሆኑ ከዚያ ውጭ በተለያየ ጊዚያት እና ቦታዎች ያለቁትን ኢትዮጵያውን ስም ዝርዝር ያላካተተ መሆኑ ይታወቅ፡፡ ሆኖም ግን ኮሚሽኑ እንዲያጣራው ከተሰጠው ቀናት ውጭ በፖሊስ እና በደህንነት ኃይሎች የተገደሉትን ንጹሀን ዜጎች ስም ዝርዝር ከላይ ከተጠቀሰው እና ከታዘዘው ቀናት ውጭ አጣርቶ የያዘው ሆኖም ግን ከተሰጠው ጊዜ ውጭ እንዲያጣራ ስልጣን ያልተሰጠው በመሆኑ ምክንያት ይፋ ያላደረገው መረጃ በእጁ ተይዞ የሚገኝ መሆኑን ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ህዳር 7 ቀን 2008 ዓ.ም

 

 

 

Similar Posts