በፕሮፌሰር መስፍን “አዳፍኔ“ መጽሐፍ ላይ አንዳንድ የሀሳብ ፍንጣቂዎች፡ ኢትዮጵያውያንን ከእራሳቸው መጠበቅ?

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

Mesfin 3

አሁን ከቅርብ ጊዜ በፊት “አዳፍኔ፡ ፍርሀት እና መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀው እና ታትሞ የወጣው የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የአማርኛ መጽሐፍ የኢትዮጵያ ህዝቦች በብልሹ አስተዳደር፣ በአምባገነናዊነት የጭቆና አገዛዝ እና በሞራል ስብዕና መብከት ምክንያት ተዘፍቀው ከሚገኙበት የኃጢአት ባህር ውስጥ እራሳቸውን በንስሀ በማደስ ከሀጢአት እንዲጸዱ የማያዳግም እርምጃ እንዲወስዱ የሚያሳስብ ነው፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ቀደም ሲል ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ እየተባለ ይጠራ በነበረው አሁን ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመባል በሚታወቀው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ የመልክዓ ምድር/Geogeraphy ትምህርት ያስተምሩ ነበር፡፡

አዳፍኔ በሚል ርዕስ የተዘጋጀው መጽሐፋቸው ፕሮፌሰሩ እውነታን በተላበሰ መልኩ ወይም ደግሞ ምክንያታዊ አመክንዮን ባካተተ ድምጸት እና አንደበታቸው ሀገር ወዳዱ የምሁር ቁንጮ አርበኛ በጎሳ ፖለቲካ ተዋቅሮ ሀገራቸውን እያተራመሰ ባለው የደናቁርት ስብስብ ዕኩይ ድርጊት በከፍተኛ ደረጃ በመበሳጨት ይህንን ሀገር አውዳሚ የሆነ ድርጊት የሀገር ተረካቢ የሆነው ወጣቱ ትውልድ ፍቅር እና ሰላም የሰፈነባት፣ እድገት በባዶ ፕሮፓጋንዳ በደናቁርት ስብስብ የውሸት የቁጥር ድርደራ የሚነዛባት ሳይሆን በተጨባጭ እውን የሚሆን ዕድገት የሚመዘገብባት፣ እድገት እና ሹመት በፖለቲካ ታማኝነት እየተዘገነ የሚታደል ሳይሆን በትምህርት ብቃት እና ችሎታ የሚሰጥባት፣ በሀብት መክበር በማጭበርበር እና የሕዝብን ሀብት በማን አለብኝነት በመዝረፍ ሳይሆን ነጭ ላብን አፍስሶ፣ አዕምሮን እና አካላዊ ብቃትን ተጠቅሞ ሀብት የሚፈራባት፣ ሙስና፣ ዘረኝነት፣ ጎጠኝነት፣ የጥላቻ እና የበቀልተኝነት ሰይጣናዊ አስተሳሳብ፣ የኃይማኖት ጽንፈኝነት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የሚወገድባት ሀገር እንድትሆን ጨዋነትን በተላበሰ መልኩ ለሀገር ተረካቢው ለወጣቱ ትውልድ ምሁራዊ እና አባታዊ ምክርን ለመስጠት የሞከሩበት መጽሐፍ ነው፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን በስልጣን ማማ ላይ ተንጠልጥለው እና ለዘመናት ሕዝቡን በመጨቆን ላይ ለሚገኙት ኃይል አምላኪ አምባገነኖች ሁሉ እኔ ላስታውሰው ከምችለው በላይ ለበርካታ ዓመታት ምንም ነገር ሳይፈሩ ፊት ለፊት እውነታውን እስከ አፍንጫቸው ድረስ ሲናገሩ የቆዩ እና ያሉ ብርቅዬ አንደበተ ርትኡ ምሁር ናቸው፡፡

“አዳፍኔ“ የተባለው መጽሐፋቸው አሁን በስልጣን ላይ ለሚገኙትም ሆነ ለሌሎቹ የመጨረሻውን እውነታ የገለጹበት አዋጃቸው ነው፡፡

በእኔ አመለካከት ፕሮፌሰር መስፍን ቢያንስ ላለፉት አራት አስርት ዓመታት ሲታገሉ የቆዩ የአደባባይ ምሁር ናቸው፡፡

በ21ኛው ክፍለ ዘመን ምሁራን የሰው ልጆችን ነጻነት እና እውቀት ለማበልጸግ እየወሰዱ ያለውን ተልዕኮ ከግንዛቤ በማስገባት ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ሳይድ የተባሉ ምሁር እንዲህ ብለው ነበር፣ “በስልጣን ላይ ላሉት እውነታውን መናገር ለመሰቃየት፣ መከራን ለመቀበል ምስክርነት መሆን እና ለፍትህ እና ለርትዕ ሲባል የአመጽ ድምጽን ከፍ አድርጎ በማሰማት በስልጣን እርካብ ላይ ተቆናጥጠው ከሚገኙት ገዥዎች ጋር ከቅራኔ ውስጥ መግባት ማለት ነው“ ብለው ነበር፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን በተጠናቀቀው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ጀምረው በኢትዮጵያ እውነትን በስልጣን ላይ ላሉ ገዥዎች ሁሉ በይፋ የመናገር ተግባራቸውን ጀመሩ፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያ ሕዝብ እየተቀበለ ላለው ስቃይ እና መከራ ዋና ምስክር ናቸው፡፡

እኒህ ምሁር ባፈጀው እና ባረጀው ንጉሳዊ አገዛዝ እና ደም በጠማው እና እራሱን “ደርግ” እያለ ይጠራ የነበረው ወታደራዊ አምባገነን ስርዓት አስከትለውት በነበረው ጭቆና ስርዓቱን በመቃወም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በመጮህ ተቃውሟቸውን በአደባባይ አሰምተዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በዓለም አቀፍ ምጽዋዕት እና ልመና በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጥጠው ሕዝቡን በማተራመስ ላይ ለሚገኙት ወሮበላ የዘራፊ ብድን ስብስቦች የጭቆና አገዛዝ ምስክር ናቸው፡፡

ምናልባትም እኒህ ምሁር ለዘመናት ተከታታይነት ባለው መልኩ በስልጣን እርካብ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው በሕዝብ ላይ ብልሹ አስተዳደር እንዲንሰራፋ እና በሰው ልጆች ላይ ሰብአዊ መብትን በመደፍጠጥ የሚኖሩ ጨቋኝ አገዛዞች ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ ምድር እንዲወገዱ እውቀታቸውን እና ምሁራዊ ክህሎታቸውን በመጠቀም የምክንያታዊነት እና አመክንዮአዊ አስተሳሰብ ዋና ድምጽ ናቸው ብሎ መናገር የበለጠ ገላጭ ይሆናል፡፡

ጥረታቸው ሁሉ ሲመክን ሲመለከቱ ገደቡን አልፎ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ጭቆና በማጋለጥ እና ገደብ እዲበጅለት ድምጽ ለሌለው ሕዝብ ድምጽ በመሆን በአደባባይ መጮህ ጀመሩ፡፡

እንደ ዕድል ሆኖ የእርሳቸው የጭቆና የእምቢተኝነት ትግል ለማህበራዊ እና ለፖለቲካዊ ለውጥ ምቹ መደላድል መፍጠሩ ቀርቶ በተቃራኒው እርሳቸውን የስቃይ ዒላማ አደረጋቸው፡፡

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እራሳቸውን መንግስት አስመስለው እርኩሰትን የተላበሰ የገዳይ ወሮበላ ዕኩይ ስብስብ በመፍጠር የጭቆና አገዛዝ አንሰራፍተው የሚገኙት እና በሙስና እስከ አፍንጫቸው ድረስ ሰምጠው ለሚገኙት ዘራፊ ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ዘ-ህወሀት) በማለት ለሚጠሩት የደናቁርት ስብስብ ወሮበሎች ፕሮፌሰሩ ፍርሀት የለሽ ብቸኛው የሰብአዊ መብት ጥበቃ ድምጽ እምቢተኛ አመጸኛ ለመሆን በቅተዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ ለእምነታቸው እና በአመክንዮ ላይ ለተመሰረተው ጽኑ አስተሳሰባቸው ከፍተኛ መስዋዕትነትን ከፍለዋል፡፡

ላለፉት 24 ዓመታት ፕሮፌሰር መስፍን በ ዘ-ህወሀት በግፍ እንዲሰቃዩ ተደርገዋል፣ እንዲሁም ሸፍጥን በተላበሰ መልኩ ምንም ዓይነት ጥፋት ሳያጠፉ እውነትን ፊት ለፊት በመናገራቸው ብቻ በዝንጀሮው የይስሙላ ፍርድ ቤት በየጊዜው እየተመላለሱ እንዲቀርቡ በማድረግ ከፍተኛ የሆነ የማጉላላት ድርጊት ተፈጽሞባቸዋል፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ሰላማዊ በሆነ መልኩ የፖለቲካ እና የሰብአዊ መብት ጥበቃ እንቅስቃሴዎችን በማድረጋቸው ዘ-ህወሀት ለአስከፊ እስራት ዳርጓቸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜም እንኳ ቢሆን ከፍተኛ ለሆነ የመሽማቀቅ እና የማስፈራራት ዕኩይ የወያኔ ድርጊቶች የጥቃት ዒላማ ሆነዋል፡፡

ዘ-ህወሀት ፕሮፌሰር መስፍን እትብታቸው የተቀበረበትን ሀገራቸውን ትተው እንዲሰደዱ ይፈልጋል፡፡

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2015 ፕሮፌሰር መስፍን እያሰቃዩአቸው ላሉት የዘ-ህወሀት ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስቦች እንዲህ የሚል የመሞገቻ ጽሑፍ በድረ ገጽ በአማርኛ ቋንቋ ጽፈው አስነብበዋል፡

“…ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ እየሰራሁ በነበርኩበት ጊዜ ወያኔዎቹ በቀጥታም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መልኩ ሀገር ለቀቅን እንድንሰደድ ወይም ደግሞ ወንጀል እድንሰራ የማስገደድ ድርጊት ይፈጽሙብን ነበር፡፡

ስለእራሴ ትንሽ ልናገር፡፡ እኔን ለምን እደሚያስፈራሩኝ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በአሁኑ ጊዜ እያስፈራሩኝ ያሉት ምናልባትም እየኖርኩበት ያለውን አፓርትመንት በመፈለጋቸው ምክንያት እንደሁ በእርግጠኝነት አላውቅም፡፡ በእኔ ቤት ውስጥ ያሉ እና የወያኔ ሎሌዎች ትልቅ ዋጋ ያወጣሉ ብለው የሚያስቧቸው ነገሮች አሉ ከተባለ ምናልባትም በገብረ ክርስቶስ ደስታ የተሳሉ ሁለት ስዕሎች ብቻ ናቸው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን በቤቴ ውስጥ ሊገኙ የሚችሉት ለወያኔ ምንም ዓይነት ዋጋ ሊያወጡ የማይችሉት መጽሐፍት ብቻ ናቸው፡፡ ስለሆነም እኔ በወያኔ እጅ እየተሰቃዬሁ ያለሁት ሀገሬን ትች እንድሰደድ ከመፈለግ ዓላማ የመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን ድርጊት እ.ኤ.አ በ1992 ሞክረውት ነበር፡፡ ሆኖም ግን አልሰራላቸውም፡፡ እኔን መጠነ ሰፊ በሆነ መልኩ እያሰቃዩኝ ያሉበትን ምክንያት በእርግጠኝነት ላውቀው የማልችል ቢሆንም በአንድ በደህና ቦታ ላይ በተቀመጠ የወያኔ ሰው ግልጽ እንደተደረገልኝ በእኔ ላይ መጠነ ሰፊ የሆነ የማሰቃየት ዘመቻ ተከፍቶብኝ ይገኛል፡፡

ይህች ሀገር ለአንድ በጥባጭ ለሆነ ወሮበላ ስብስብ ብቸኛ ሀብት ናት የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይህች ሀገር የተመሰረተችው በእኛ እናት እና አባት፣ በአያት እና ቅድመ አያቶቼ ነው፡፡ ማንም ቢሆን እኔን አስገድዶ ከሀገሬ በማባረር ስደተኛ ሊያደርገኝ ፍጹም አይችልም፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊነቴ ማንም ቢሆን እኔን በማስፈራራት መብቴን ነጥቆ ሊወስድ በፍጹም አይችልም፡፡ ይህ ድርጊት ይፈጸም ዘንድ በፍጹም አልፈቅድም፡፡ ለወያኔዎች በጠራ መልኩ ግልጽ እንዲሆንላቸው እንዲህ በማለት ያለኝን አቋም በአጽንኦ ልነግራቸው እፈልጋለሁ፡ በህይወት እየኖርኩባት ያለሁት እና ስሞትም የምቀበረው በዚህችው በኢትዮጵያ ምድር ነው፡፡

ለወያኔ እና ለሎሌዎቹ አንድ ሊካድ የማይችል እውነታን ልንገራቸው፡ እኔን የጥቃት ሰለባ ለማድረግ ሲሉ ሕገወጥ ድርጊት እና ወንጀሎችን ቢሰሩ ያለምንም ጥርጥር ነገ ከዚህ የበለጠ ታላቅ መሰቃየትን እና ቅጣቶችን ይቀበላሉ፡፡ እነዚህ ስልጣናቸውን ከሕግ አግባብ ውጭ በሚጠቀም ነጹሀን ዜጎችን በመግደል ኃያል የሆኑ የሚመስላቸው እብሪተኞች አንድ ጊዜ ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባቸዋል፡፡ ማንም ሰውን በመግደል ድልን ሊቀዳጅ ይችላል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ማንም ሰው በመሞት ድልን በገዳዮቹ ላይ ሊቀዳጅ ይችላል፡፡“

“አዳፍኔ” የእርሳቸው የግላቸው ሙያዊ ተሞክሮ እና የእራሳቸው የነገሮችን ታሪካዊ አመጣጥ ዳህራ በውል የመገንዘብ እና ትንታኔ በመስጠት ችሎታ ላይ መሰረት በማድረግ በእኩዮሽ የታሪክ መስመር ላይ የማይሄደውን የሀገሪቱን ታሪክ እና ኋላቀር የስልጣኔ ደረጃ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተሰጠ የሀሳብ ፍንጣቂ ነው፡፡

ፕሮፌሰሩ ከወያኔ ማሰቃየት በፊት በሌሎች አገዛዞችም ስቃይ ሲደርስባቸው የቆዩ ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ ሁለተኛ አጋማሽ የመጨረሻዎቹ እና በ1980ዎቹ ዓመታት በሙሉ “ደርግ” እየተባለ ይጠራ በነበረ ወታደራዊ አምባገነን ወሮበላ አገዛዝ  ስቃይ ደርሶባቸዋል፡፡

ደርግ በሰው ልጆች ላይ ሲፈጽም ከነበረው የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ጋር አመለካከታቸው ሊሄድ ስላልቻለ ስማቸውን ማጥፋት እና ማብጠልጠል ጀመሩ፡፡

እንደዚሁም ሁሉ የግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ አገዛዝ እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ ዓመታት በሙሉ የማሸማቀቅ እና የማስፈራራት ድርጊቶችን ሲፈጽማቸው ነበር፡፡ ስርዓቱ እርሳቸውን የማይበገሩ ቆጥቋጭ እና ካመኑበት በፍጹም ፍንክች የማይሉ ሞገደኛ አድርጎ ይቆጥራቸው ነበር፡፡

ሆኖም ግን በስልጣን ላይ የነበሩት ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ እና ሚኒስትሮቻቸው እንዲሁም ልዑላን መሳፍንት እና መኳንንት ፕሮፌሰሩ አንድም ነገር እንዳይናገሩ በፈለጉበት ጊዜ እንኳ ሳይቀር እርሳቸው መንፈሳቸው የመራቸውን እና የማኑበትን ነገር ፊት ለፊት ከመናገር የታቀበቡት ጊዜ ሳይኖር በእምነታቸው ቀጥለውበት ሄደዋል፡፡

በተለያዩ ስርዓቶች የተለያዩ ከበሮዎች ቢደለቁም ቅሉ እርሳቸው ግን ረዥሙን የነጻነት ጉዙ ተያይዘውት እስከ አሁን ድረስ በጉዞ ላይ ይገኛሉ፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ከመሆናቸው በፊት የነጻነት ሙያዊ እምቢተኝነትን የሚያራምዱ ሰው እንደነበሩ በድፍረት መገመት እችላለሁ፡፡

እርሳቸው በጭንቅ ኑሮ እየተሰቃዩ የኖሩ ስለሆኑ፣ ለፍትህ እና ለርትዕ ሲሉ ሁልጊዜ የእምቢተኝነትን ዓላማ ሲያራምዱ ስለኖሩ እና ምንጊዜም በስልጣን ላይ ተጣብቀው ሊሚገኙት፣ ስልጣናቸውን ከሕግ አግባብ ውጭ ለሚጠቀሙት ገዥዎች እና ከስልጣን ለተወገዱት ሁሉ  እውነታውን ፊት ለፊት ከመናገር የማይቆጠቡ ምሁር ስለሆኑ ከስማቸው በስተመጨረሻ በአህጽሮተ ቃል ሙ.እ/P.D (ሙያዊ እምቢተኛ/Professional Dissenter) በመባል መጠራት አለባቸው ብየ አስባለሁ፡፡

በስልጣን እርካብ ላይ ተፈናጥጠው የሚገኙት ገዥዎች አመልካች ጣታቸውን ወደ እርሳቸው በመቀሰር፣ ቡጢዎቻቸውን በመጨበጥ በሀይል መገፍተር እና ወደ እስር ቤት እየወሰዱ በማጎር  ይበቀሏቸው ነበር፡፡

እርሳቸው ግን እንደማትበገርዋ ግመል ረዥሙን ጉዝ መጓዝ ቀጥለዋል፡፡ የመንግስት ውሾች እየተከተሉ ይጮሀሉ፣ እናም ውሾቹ ጥርሶቻቸውን ያፋጩባቸዋል፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን በመስበክ፣ በማስተማር፣ ያልተደረሱ ሕዝቦችን በመድረስ እና በህዝቦች ላይ ወንጀል የሚሰሩትን ባለስልጣኖች በማጋለጥ እና በመክሰስ ላይ ቀጥለው ይኖራሉ፡፡

አዳፍኔ በሚለው መጽሐፋቸው ላይም ያንኑ ባህል ነው ቀጥለውበት የሚታዩት፡፡

እንደምሁር፣ እንደ አደባባይ ልሂቅ፣ እንደ ኢትዮጵያ ታሪካ ተቆርቋሪ እና እንደ መልካም እና እንደ እውነተኛ የሰው ተፈጥሮ ለፕሮፌሰር መስፍን ከፍተኛ የሆነ ከበሬታ አለኝ፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን የአጭበርባሪነት የቁማር ካርታን አይጫወቱም፣ በሁለት ቢላዋ አይቆርጡም እናም ቆሻሻ የማታለል ዕኩይ ድርጊቶችን አይፈጽሙም፡፡

ማለት ያለባቸውን በግልጽ ይናገራሉ፣ የተናገሩትንም በተግባር ይፈጽማሉ፣ በመንታ ምላስ አይናገሩም፡፡ የምታየው ነገር በእርሳቸው ላይ ያለውን እውነታ ብቻ ነው፡፡

እርሳቸው የሚናገሩትን እውነታ የማትወድ ከሆነ ምንጊዜም ቢሆን ቀዝቅዞ ወደማያውቀው ወደ ገሀነም በቀጥታ መጓዝ ትችላለህ፡፡

እውነት መናገር እውነት ተናጋሪዎችን ለመኖር በሚዋሹት እና እየዋሹ በሚኖሩት ዘንድ አይወደዱም፡፡

በእኔ አመለካከት ፕሮፌሰር መስፍን በኢትዮጵያ የቦቅቧቃ ምሁራን፣ በፖለቲካ አድርባይነት እና በአስመሳይ ሎሌ ምሁራን የጨለማ ሰማይ ዘንድ ለዘመናት በማይደበዝዝ መልኩ የተቀጣጠሉ ብቸኛ የመቅረዝ ላይ ሻማ ናቸው፡፡

ፕሮፌሰር መስፍንን “የሚያስብ ሰው“ በማለት እንደጻፉት እንደ ራልፍ ዋልዶ ኢመርሶን አድርጌ እቆጥራቸዋለሁ፡፡

Adafneኢመርሰን እ.ኤ.አ. ነሐሴ 1837 በሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ በመገኘት አንድ አሜሪካዊ ምሁር እጅግ በጣም ጠቃሚ እና አስፈላጊ ነው የሚባለው የሚከተለውን ማድረግ ሲችል ነው በማለት እንዲህ ተናግረው ነበር፡

“ምሁር ከሌሎች በተለየ መልኩ ተለይቶ የሚኖር፣ በጣም ከፍተኛ በሆነ መልኩ ስለጤንነት የሚያስብ- ጩቤ በመጥረቢያ ላይ እንደሚያደርገው ሁሉ በአንድ ሰው ወይም በህዝብ ጉልበት በተሰራው ስራ ላይ ስምምነት የማያደርግ ነው የሚል ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰብ አለ… ለጠንቃቃ የህብረተሰብ ክፍሎች እውነት እንደሆነ ሁሉ…ድርጊት በምሁር ቁጥጥር ስር ነው፣ ሆኖም ግን በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ከድርጊት ውጭ ሰው እራሱ ገና ሰው አልሆነም ማለት ነው፡፡ ከድርጊት ውጭ ሀሳብ በምንም ዓይነት መልኩ ወደ እውነትነት ሊደርስ አይችልም፡፡ ዓለም የቆንጆዎች ሁሉ ቆንጆ ሆኖ በዓይናችን ላይ ቢደቀንም ቆንጆ መሆኑን እንኳ ልናየው አንችልም፡፡ የድርጊት ሰው ያለመሆን የቦቅቧቆች እና የፈሪዎች ወራዳ ተግባር ነው፡፡ ስለሆነም ከጀግና አዕምሮ ውጭ ምንም ዓይነት ምሁራዊነት የለም፡፡ የሀሳብ መግቢያ ካለማሰብነት ወደ ማሰብ ደረጃ የሚደረገው ሽግግር የሚገለጸው በድርጊት ነው፡፡ በህይወት እስከኖርኩ ድረስ እኔ የማውቀው ይህንን ያህል ብቻ ነው፡፡ ወዲያውኑም ቃሎቻቸው በህይወት የተሞሉትን እና ያልተሞሉትን እናውቃለን፡፡“

ፕሮፌሰር መስፍን ጀግና አዕምሮን የተጎናጸፉ የኢትዮጵያ “አሳቢ ሰው” ምሁር ናቸው፡፡

ከሌሎች ህዝቦች ተለይተው በፍጹም ኖረው የማያውቁ እና ለጤናማ የአኗኗር ህይወት ጠንቃቃ የሆኑ ሰው ናቸው፡፡

እርሳቸው ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል የተግባር ሰው ሆነው የቆዩ ሰው ናቸው፡፡

የእርሳቸው አመለካከቶች እና የሚያቀርቧቸው እና የሚጽፏቸው ሀሳቦች  በርግጥ እውነተኛ ድርጊቶች ናቸው፡፡

እኔ እርሳቸውን ጀግና አሳቢ ሰው ከሆኑት ከኢመርሰን የበለጠ “የሚያስቡ ሰው” አድርጌ እቆጥራቸዋለሁ፡፡

እኔ ፕሮፌሰር መስፍንን ስለኢትዮጵያ “የሚጽፉ ሰው”፣ “የሚናገሩ ሰው”፣ “የሚያዳምጡ ሰው”፣ “የሚያነሳሱ ሰው”፣ “የሚቀሰቅሱ ሰው” ለፍትህ እና ለርትዕ ሲሉ በአመኑበት ጉዳይ ላይ በጽናት እና በአይበገሬነት የሚቆሙ “የእምቢተኝነት” ሰው አድርጌ እቆጥራቸዋለሁ፡፡

እርሳቸው የሚያምኑበትን ነገር ለስርዓቱ ተጠቃሚዎች እና ስልጣናቸውን ከሕግ አግባብ ውጭ በስራ ላይ ለሚያውሉ ብቻ አይደለም ከፍርሀት ውጭ የሚናገሩት፡፡ ሆኖም ግን እርሳቸው አስረግጠው እና በጽናት በመቆም የሚናገሩት ኃይል ለሌላቸው፣ ለስልጣን ረሀብተኞች እና በስልጣን ለሰከሩ ህዝቦች እንዲሁም መስማት ለሚፈልጉ ሁሉ ለእውነት እና ለእውነት ብቻ ነው የሚናገሩት፡፡

ኢመርሰን “የዓለም ዓይን” በማለት እንደጻፉት ሁሉ ፕሮፌሰር መስፍንም ”አዳፍኔ” በሚለው መጽሐፋቸው ላይ የኢትዮጵያን ያለፈ ታሪክ ታላቅነት በመጠበቅ፣ ፍቅርን በተላበሰ መልኩ ይህንን ታላቅነት ለአቻ ምሁራን ጓደኞቻቸው (አብዛኞቹ ከእርሳቸው ጎን ቆመው ለሀገራቸው እና ለሕዝባቸው ሰላም እና ደህንነት በጋራ በአደባባይ ከመታገል ይልቅ በግል እያብጠለጠሉ የሚያሟቸው) ለመግለጽ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን እርሳቸው “የኢትዮጵያ ዓይን” በመሆን ከኢትዮጵያ ተነጥሎ ላለው እና ከአያቶቹ እና ከቅድመ አያቶቹ ታቅነት ጋር ተለያይቶ ለሚገኘው ለአዲሱ እና ለሀገር ተረካቢው ወጣት ትውልድ ለማመላከት ነው፡፡

“አዳፍኔ” በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ፕሮፌሰር መስፍን በዳሳሹ ዓይናቸው ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት የት ላይ እንደነበሩ እና አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ወይም ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በሚሰሩት ስራ ምርጫ ላይ ተመስርቶ ወደፊትስ የት ላይ እንደሚሆኑ እና እንደማይሆኑ በግልጽ የተመለከቱበትን ዘገባቸውን አቅርበዋል፡፡

ይህ መጽሐፍ ጥንት ታላቅ የነበረችው ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚ ምስቅልቅ ሁኔታ ላይ የምትገኝ መሆኗን እና የኢትዮጵያ የተሻሉ ቀኖች እየመጡ  እና ከአድማስ ጫፍ ላይ እየታዩ መሆናቸውን የግል ሀሳባቸውን በውል እያስቀመጡ ጥልቀት  እና ስፋት ባለው ሁኔታ ትንታኔ የሰጡበት ነው፡፡

“አዳፍኔ” በሚገባ የተቀቀሉ ታሪካዊ እና የዘመኑ የፖለቲካ ትንታኔዎችን በማጣመር እንዲታዩ የተደረገበት እና በርካታ ኢትዮጵያውያን የሞራል ግዴታቸውን ባለመወጣት እና ከዳር ቆመው እየተመለከቱ ሀገሪቱ ወደከፋ አዘቅት ውስጥ እየተጋዘች ባለበት ሁኔታ ኢትዮጵያውያን ታላቅ ጥንቃቄን በተላበሰ መልኩ እንዴት አድርገው እራሳቸውን ከእራሳቸው መጠበቅ እና ማዳን እንደሚችሉ ለማሳየት ጥረት የተደረገበት ብሩህ መስተዋት ነው፡፡

የመጽሐፉ ርዕስ ተመሳስሎ በርካታ የተወሳሰቡ ስሜቶችን እና ትርጉሞችን አካትቶ ይዟል፡፡

“አዳፍኔ” የሚለው ቃል የመቅበር ሂደትን የሚያሳይ ወይም ደግሞ አንድን ነገር በአፈር መሬት  ወይም ደግሞ በአመድ ውስጥ መደበቅን የሚያመላከት መሆኑን ግንዛቤ ሊሰጥ ይችላል፡፡

እንደዚሁም ደግሞ የእሳት መጥፋትን እና የቀረዉን ፍም በአፈር ወይም ደግሞ በውኃ ማጥፋት መሆኑን ሊገልጽ ይችላል፡፡

በሌላ መልኩ ይታይ ከተባለ ደግሞ ጥቂት ተግባራት ገና በመጀመሪያው የአፈጻጸም ደረጃቸው በድንገት የመክሰማቸውን ሁኔታ ሊያመላክት የሚችል ይሆናል፡፡

በኢትዮጵያ የወታደራዊ ስርዓት የቋንቋ አጠቃቀም “አዳፍኔ” በተለምዶ “ባዙቃ” እየተባለ የሚጠራው ጸረ ታንክ መሳሪያ ነው፡፡

በአጠቃላይ “አዳፍኔ” የሚለው ቃል አንድን ነገር ወይም ደግሞ ሂደትን የሚያፍን፣ የሚያንቅ፣ ትንፋሽ የሚያሳጣ፣ የሚያጠፋ፣ የሚከለክል እና የሚያደናቅፍ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ይህንን “አዳፍኔ” የሚለውን ተመሳስሎ በአሁኑ ጊዜ እና ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ስልጣናቸውን ከሕግ አግባብ ውጭ የሚጠቀሙትን አምባገነን አገዛዞች፣ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ እና ፍልስፍና አዘል የሆኑ እውነታዎችን በመጠቀም ለመክሰስ እና ለፍትህ አካል ለማቅረብ ሲሉ የገለጹበት ቃል ነው፡፡

እንደዚሁም ደግሞ ኃይል የለሾችን፣ የስልጣን ጥመኞችን እና በስልጣን የሰከሩትን ለመሞገት እና ለመገዳደር በማሰብ ከስልጣን ጋር ተያይዘው የሚመጡትን በርካታ የሆኑ ኃላፊነቶችን ለመገንዘብ እና ህዝቡን በቅንነት ለማገልገል ሲባል የህንን ተመሳስሎ ይጠቀማሉ፡፡

“አዳፍኔ” የሚለው ቃል ድብቁ መልዕክት የበለጠ አሳማኝ ነው፡፡ (እርሳቸው አዳፍኔን በአሁኑ ጊዜ ላለው ለወጣቱ ትውልድ እና ለመጭው ትውልድ ማስታወሻ እንዲሆን በማሰብ የሰጡት ስያሜ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡)

በአዳፍኔ ውስጥ በአሁኑ ወቅት እና ቀደም ሲል የደረሰውን የትውልድ ውድቀት በሚገባ አጢኖ በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ከደረሰባቸው አስፈሪ እና አስደንጋጭ ሁኔታ ውግዘት ለማላቀቅ እና ኢትዮጵያን ከአስከፊ ውድቀት በማውጣት ንስሀ ለመግባት የማይቀረውን ታሪካዊ፣ በጋራ መስራት አለመቻልን ወይም ራዕይ ያለው አመራር ያለመኖርን ወጣቱ ትውልድ በውል ተገንዝቦ የእራሱን ኃላፊነት መወጣት እንዲችል የተሰጠ ማስጠንቀቂያ መሆኑን እገነዘባለሁ፡፡

የኢትዮጵያ ውጣቶች የ“አዳፍኔን“ አስፈሪ ሁኔታ በውል አጢነው ያለፉት አባቶች፣ አያቶች እና ቅድመ አያቶች የፈጸሟቸውን ስህተቶች በመድገም እራሳቸውን ከውሸት ተራራ ስር ቀብረው እንዳይገኙ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ለኢትዮጵያ ወጣቶች በሶስት ቀላል ሀሳቦች ሊገለጽ የሚችል ታላቅ መልዕክት አላቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ እነርሱም፡

1ኛ) ከተወሰኑ ቡድኖች የእራስን በእራስ ከማጥፋት አስከፊ አደጋ ኢትዮጵያን ሊታደጓት የሚችሉት የኢትዮጵያ ወጣቶች ብቻ ናቸው፡፡

2ኛ) ኢትዮጵያን ከጎሰኝነት እሳት እና ከኃይማኖት ጽንፈኝነት ሊታደጓት የሚችሉት የኢትዮጵያ ወጣቶች ብቻ ናቸው፡፡

3ኛ) የማህበረሰቡን የግንኙነት ክር ከበጠሱት የድሮዎቹ እና የአሁኖቹ ትውልዶች፣ አውዳሚ ከሆነው የፖለቲካ መዋቅር፣ ግራ ከተጋባው የኢኮኖሚ ስርዓት እና የህዝቡን መንፈሳዊ ህይወት ሊመለስ በማይችል መልኩ ካጠፋው ትውልድ ኢትዮጵያን ሊመልሱ እና ሊያድኑ የሚችሉት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ብቻ ናቸው፡፡

“አዳፍኔ” በአንድ ወቅት ምናልባትም በቅኝ ግዛት ዘመን የተገኘ ስር የሰደደ የአፍሪካ በሽታ ነው፡፡

“አዳፍኔ” አህጉሪቱን ሙሉ በሙሉ በመበከል ታላላቅ መልካም ባህሪ፣ እውቀት፣ ታማኝነት እና ክብረ ሞገስ ያላቸውን ወንዶች እና ሴቶች እንዳታፈራ በማድረግ ምድረበዳ አድርጓታል፡፡

“አዳፍኔ” አህጉሪቱን የጊንጥ ማጠራቀሚያ ቅርጫት አድርጓታል፡፡ አንድ ጊንጥ  ከቅርጫቱ ውስጥ ለመውጣት ሙከራ በሚያደርግበት ጊዜ ሌሎቹ ጊንጦች ወደ ቅርጫቱ ውስጥ ስበው ያስቀሩታል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ “አዳፍኔ” የአዕምሮ በሽታ ነው፡፡ የ”አዳፍኔ” በሽታ ሰለባዎች በዘላቂነት ጸረ ነጻነት፣ ጸረ እኩልነት፣ ጸረ ፍትህ እና ጸረ ዕድገት ናቸው፡፡

በሌላ አባባል ለማስቀመጥ ለ”አዳፍኔ” በሽታ ሰለባዎች ነጻነት ማለት የእነርሱ ነጻነት ብቻ ነው፣ እኩልነት ማለት የእነርሱ እኩልነት ማለት ብቻ ነው፣ ፍትህ ማለት ለራሳቸው ብቻ ነው ፣ ልማት ማለት በሚያስገርም ሁኔታ ብዙሀኑ ሕዝብ በረሃብ እየተሰቃዬ ባለበት ሁኔታ እነርሱ ግን ከመሬት እና ከሌላም ሀብት በርካታ የታሰረ ረብጣ ገንዘብ እያግበሰበሱ ወደ ኪስ ማጨቅ ማለት ነው፡፡

እንደዚሁም ሁሉ “አዳፍኔ” የአምባገነናዊ የጭቆና አገዛዝ መለያ የስብዕና ባህሪ መገለጫ ነው፡፡ “አዳፍኔ” መሬቱን፣ ማዕድናቱን እና ጌጣጌጡን ሁሉ በእራሱ ደብቆ ይይዛል፡፡ “አዳፍኔ” ሐይቆችን እና ወንዞችን ሁሉ በእራሱ ቁጥጥር ስር ያደርጋል፡፡ አዳፍኔ አምላክ መሰል ስልጣን አለው፡፡ የ”አዳፍኔ” ምኞት ለሌላው ህዝብ ትእዛዝ ነው፡፡

“አዳፍኔ” የኢትዮጵያውያን ነብሶች በሽታ ነው፡፡

“አዳፍኔ” በምን መልኩ ይታያል ፡

1ኛ)  እውነትን በመጨቆን እና በማጥፋት፣

2ኛ) ትምህርትን እና እውቀትን በመጨቆን እና በማጥፋት፣

3ኛ) እውነት ሊሰራጭበት እና ሊስፋፋበት የሚችለውን ማናቸውንም ቀዳዳ ሁሉ በመዝጋት፣

4ኛ) መንታ ምላስ ያላቸውን ቅጥፈት እና ውሸት ሲገምዱ የሚውሉ እና የሚያድሩ ደናቁርት ካድሬዎችን እና አስመሳዮች ሆድ አደርን በመቅጠር፣ እና

5ኛ) ሀሳቦች እና እውቀቶች በሕዝብ መካከል እንዳይሰራጩ የህትመት ውጤቶችን በሁሉም መንገዶች በመዝጋት ኢትዮጵያን የባዶ ዲስኩር ማሰሚያ መሬት አደረጋት፡፡

የ”አዳፍኔ” የሶስትዮሽ ውልደት በኢትዮጵያ የእህት እና ወንድሞችን ፍርሀት እና ውድቀት ጨምሮ ሰይጣናዊ ስብዕና ያላቸው፣ ተቋማዊ ስርዓትን የተላበሱ፣ መንፋሳዊ እሳቤን እንዲላበሱ የተደረጉ፣ ሞራል የለሽ እና በሞራል ስብዕና የከሰሩ እንዲሁም ምሁራዊ አስመሳይነትን የተላበሱ ዕኩይ ምግባራት ናቸው፡፡

“አዳፍኔ” የሚለው ተመሳስሎ ሮበርት ጄ. ኦፔንሃይመር ፣ አለምን  ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያጠፋ ስለ አቶሚክ ቦምብ ተናግረው ነበር ።  ኦፐንሄይመር የሂንዱ አምላክ የሆነውን ቪሽኑን በመጥቀስ እንዲህ ብሎ ተናግሮ ነበር፣ “እኔ በአሁኑ ጊዜ ዓለምን ለማጥፋት የምችል ሞት ሆኛለሁ፡፡“

በኢትዮጵያ የሞት ስብዕናን የተላበሰው “አዳፍኔ” ሆኗል፡፡

“አዳፍኔ” ከኢትዮጵያ እና ከሕዝቦቿ ቀስ በቀስ የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና መንፋሳዊ ህይወትን በመጭመቅ ዕኩይ ምግባር ላይ ተጠምዶ ይገኛል፡፡

አዳፍኔ በኢትዮጵያ የተስፋ፣ የእምነት፣ የልግስና፣ የፍላጎት መነሳሳት፣ የቃል ኪዳን፣ የክብር፣ የታማኝነት፣ የክብረ ሞገስ፣ የትክክለኛነት፣ የሞራል ስብዕና፣ የመልካም ፈቃድ ማውደሚያ ዕኩይ ምግባር መሳሪያ ሆኖ ይገኛል…

አዳፍኔ በእውቀት ብቻ ሊወገድ ይችላል፡፡ እውቀት እና ትምህርት የአዳፍኔ ጠላቶች ናቸው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ አዳፍኔ የሚሞት የእውቀት እና የትምህርት ጠላት ነው፡፡

አዳፍኔ ተጽእኖው በወጣቶች ላይ የጠነከረ ነው፡፡ እነዚህ ወጣቶች አያት እና ቅድመ አያቶቻቸው በሰሯቸው ስኬታማ ስራዎች ላይ ኩራት እንዲኖራቸው ከማድረግ ይልቅ በአባቶቻቸው እና በእናቶቻቸው ላይ ስለደረሰው ስቃይ እንዲጸጸቱ ይገደዳሉ፡፡  በኢትዮጵያዊነታቸው እራሳቸውን እንዲያሳትፉ ከማድረቅ ይልቅ ወጣቶች በጠባብ የጎሰኝነት እና የኃይማኖት ጽንፈኝነት ላይ ኩራት እንዲሰማቸው ይገደዳሉ፡፡ ወጣቶች መብቶቻቸውን እንዳይጠቀሙ ኃይል እንዲያጡ እና አቅመቢስ እንዲሆኑ ይደረጋሉ፡፡ ወጣቶቹ ድምጾቻቸውን እንዲያጡ እና በእራስ የመተማመን ስሜት እንዲያጡ ይገደዳሉ፡፡

የአዳፍኔ የሶስትዮሽ ውልደት ግዙፍ የሆነ የስርዓት መውደቅን እና በማህበረሰቡ ደረጃ መዋቅራዊ የውድቀት ቀውስ መንስኤን ያስከትላል፡፡ እንግዲህ ያንን የህልውና ውድቀት (መክሸፍ) ነው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ኢትዮጵያውያንን እንደ ኢትዮጵያውያን በመጽሐፋቸው ለማሳየት ጥረት ያደረጉት፡፡

የፕሮፌሰር መስፍን የመክሸፍ ትንታኔ በርካታ መገለጫዎች አሉት፡፡ አንድ የማህበረሰብ ፕሮጀክት የአፈጻጸም ብቃት ሳይኖረው እና ከፍጻሜ ሳይደርስ ሲቀር ወይም ደግሞ ለማህበረሰቡ ፍሬ ሳያፈራ ሲቀር “መክሸፍ” ሊከተል ይችላል፡፡ አንድ ሰው ዓላማውን ሳያሳካ ሲቀር እና እድገትን ማስመዝገብ ሳይችል ሲቀር መክሸፍ ይመጣል፡፡ በጋራ ልማት እና ማህበራዊ ለውጥ ማምጣት ሳይቻል ሲቀር መክሸፍ ይከተላል፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውን መክሸፍ ሶስት ዋና ዋና ምክንያቶችን እንደሚከተለው ግልጽ አድርገው አቅርበዋል፡፡ እነርሱም፡

1ኛ) የአስተዳደር ስርዓቱ በሕግ የበላይነት ቁጥጥር ስር መዋል ሲሳነው፣

የዚህ መክሸፍ ውጤት አምባገነን ጨቋኝ መንግስትን ያለምንም ችግር መቀበል ወይም ደግሞ በእግር በመወሰን ወደ ስደት መንጎድ ይሆናል፡፡

2ኛ) የኢትዮጵያ ምሁራን መክሸፍ፣ ምሁራን እና የልሂቃኑ መደብ በማንኛውም ጊዜ ለሚመጡ እና ስልጣንን በሕዝብ ድምጽ ሳይሆን በመሳሪያ ኃይል ለሚቆጣጠሩ አምባገነኖች እራሳቸውን እና ስብዕናቸውን ይሸጣሉ፡፡ በእያንዳንዱ አገዛዝ ዘመን ምሁራን ምንም ዓይነት ሰይጣናዊ ድርጊት አልሰማሁም፣ ምንም ዓይነት ሰይጣናዊ ድርጊት አላዬሁም እና ምንም ዓይነት ሰይጣናዊ ነገር አልተናገርኩም በሚሉ እና እራሳቸውን እንደ ሶስት ጦጣዎች እንደተሰየሙ አድርገው ይቆጥራሉ፡፡

ምሁራን እና የተማረው ህብረተሰብ መደቦች በስልጣን ላይ ያለው አካል ትክክለኛ የሆኑ ነገሮችን በመያዝ ሕዝቡን አስተባብረው በመምራቱ ረገድ ሳይሳካላቸው ቀርቶ ከሽፈዋል፣ እንደዚሁም ሁሉ በስልጣን ላይ ያለው አካል ወንጀሎችን ሲሰራ እና የተሳሳቱ ስራዎችን ሲሰሩ መዝግበው በመያዝ ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ ምንም ነገር የማያደርጉ ስለሆነ ከሽፈዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የእራሰቸውን ስህተቶች እንደገና ለማባዛት በሚመስል መልኩ ከሁሉም በላይ አስከፊ የሆነው ነገር ያለፈውን ትውልድ ስህተት እንደ ትክክለኛ ነገር እና አግባብነት እንዳለው ሁሉ ለመጭው ትውልድ ሌት ቀን እንደበቀቀን እየደጋገሙ የመንዛታቸው ሁኔታ ነው፡፡

የኃይማኖት መሪዎች መንፈሳዊ አመራር መስጠት ባለመቻላቸው እና ምንም የተሻለ ነገር ባለመኖሩ ከሽፈዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ልብን የሚሰብረው እውነታ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በስልጣን ኮርቻ ላይ ተንጠልጥለው የሚገኙት የደናቁርት ስብስብ የአካዳሚ የትምህርት ማስረጃዎችን ከዲፕሎማ መቀፍቀፊያ የኢንተርኔት ወፍጮዎች በሕዝብ ገንዘብ እየገዙ ልከበር እያሉ የማስቸገራቸው ጉዳይ ነው፡፡ ስልጣናቸውን ለማሳመር እና ማስዋቢያ ነገሮችን በመቀባባት በስልጣን ላይ ያሉት የደናቁርት ስብስቦች ባለስልጣን መሳይ አካል የፈረመበት ማህትሞችን በመጠቀም እና የሸፍጥ የምስክር ወረቀቶችን በመግዛት ዶክተር፣ ፕሮፌሰር፣ የመንግስት አማካሪ እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች በማለት እራሳቸውን በመጥራት የአስመሳይነት ስራቸውን በመተግበር ላይ ይገኛሉ፡፡

በእኔ አመለካከት የደናቁርት ስብስቦቹ ያልተረዱት ነገር ቢኖር አንድ አህጽሮተ ቃል የተጻፈበት ብጣሽ የተጭበረበረ የዲፕሎማ ወረቀት አንድን ወንድ ወይም ሴት ታላቅ መሪ ሊያደርግ እንደማይችል በውል ያለመገንዘባቸው ጉዳይ ነው፡፡

አንድን ሰው ታላቅ የሚያደርገው ራዕዩ፣ አዕምሮው እና የወንዱ ወይም ደግሞ የሴቷ ልብ ነው እንጅ በስርቆት የተገዛ ዲፕሎማ አይደለም፡፡

ቢል ጌትስ እንደ ስቴቭ ጆብስ እና ማርክ ዙከርበርግ ሁሉ ከኮሌጅ ትምህርት ያቋረጡ ናቸው፡፡

ዋልት ዲስኔይ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያቋረጡ ናቸው፡፡

አብርሃም ሊንከን የአንደ ዓመት መደበኛ ትምህርት ብቻ ነበር ያላቸው፡፡ ቁም ነገሩ እዚህ ላይ ግልጥ ነው ፡፡

3ኛ) ለኢትዮጵያውያን አርዓያ ሊሆናቸው የሚችል አካል ያለመኖሩ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዙሪያዋ ስኬታማ የሆኑ ሀገሮች ባለመኖራቸው ምክንያት ኢትዮጵያውያን ስለተሻለ አመራር እና ህብረተሰብ ለመማር እና ለማወቅ አልቻሉም፡፡

አዳፍኔ በኢትዮጵያ ሰፊ መሰረት ባለው ታሪካዊ እና ማህበረ ፖለቲካ ከባቢ አየር ላይ የተዋቀረ ነው፡፡ መጽሐፉ ኢትዮጵያን ለዘመናት ቀጣይ ሆና እንድትዘልቅ የሚያግዙ ዋና ዋና እሴቶችን ግልጽ አድርጓል፡፡

“አዳፍኔ” እና የእርሱ እህቶች እና ወንድሞች ፍርሀት እና መክሸፍ (የማይነገርለት የእነርሱ የአጎት ልጅ የሆነው የፍርሀት ፍርሀት) በኢትዮጵያ ባህል እየሆነ እና እያደገ በመምጣት የሕዝቡን ደስታ፣ ብልጽግና እና ፍቅር እንዲሁም ግለሰቦች በእራስ የመተማመን እና የእራስ ክብር አለመስጠት ነገሮች እንዲከስሙ አድርጓል፡፡

በኢትዮጵያ የአዳፍኔ እና የእህት እና ወንድሞቹ ዋና መነሻ ምክንያት ምንድን ነው?

“አዳፍኔ” አንድ ልዩ ዓይነት የሆነ “ፍርሀት” እንደሆነ አምናለሁ፡፡

የእውነትን መሰረታዊ ሀሳብ የመፍራት ጉዳይ ነው፡፡

እውነትን የማሰብ ፍርሀት ነው፡፡

እውነትን የመናገር ፍርሀት ነው፡፡

እውነትን የመስማት ፍርሀት ነው፡፡

እውነትን የማየት ፍርሀት ነው፡፡

በእውነት መኖር ፍርሀት ነው፡፡

ከእውነት ጋር የመኖር ፍርሀት ነው፡፡

እውነትን የመስበክ ፍርሀት ነው፡፡

እውነትን የማስከበር/የመጠበቅ ፍርሀት ነው

ከዚህም በተጨማሪ ፍርሀት እና እርስ በእርስ ያለመተማመን ጉዳይ ነው፡፡ ህሊናዎቻችንን መፍራት ማለት ነው፡፡ ትክክለኛውን ነገር ለመስራት መፍራት ነው፡፡ ከሁሉም ነገር የከፋው ደግሞ እራሳችንን መፍራት እና በግል እና በጋራ ለእራሳችን እና ለሀገራችን ምን ማድረግ እንዳለብን የመፍራት ጉዳይ ነው፡፡

በአዳፍኔ “እውነትን የመፍራት ነገር” በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስልጣን መክሸፍ፣ የትምህርት መክሸፍ፣ የባህል መክሸፍ፣ የኢኮኖሚ መክሸፍ፣ የምሁርነት መክሸፍ፣ የመንፈሳዊት መክሸፍ፣ እና የሞራል ስብዕና መክሸፍ ምክንያት ቀጥተኛ ተጠያቂ ነው፡፡

የፕሮፌሰር መስፍን ታሪካዊ የጽሑፍ ዘገባ በኢትዮጵያ የአዳፍኔ የሶስትዮሽ ውልደት ተጽእኖ ጥልቅ የሆነ ሀዘንን ያባብሳል፡፡

ኢትዮጵያውያኖች ጥሩ ዕድል ሲያገኙ ጥሩ ዕድል ያገኙትን ለማጣት አይከሽፉም፡፡

የኢትዮጵያ ምሁራን እና ልሂቃን ለቀጣዩ ትውልድ መዝግበው ለማስተላለፍ ትልቁ ትኩረት በመስጠት ስራዎችን እስካከናወኑ ድረስ የአዳፍኔ የሶስትዮሽ ትውልድ ታሪክ ብቻ ሊነገር ይችላል፡፡

አዳፍኔ በኢትዮጵያውያን እና በአውሮፓውያን በጣም የሚፈሩትን እና የአቢሲኒያ ጀግና እያሉ ና የሚርበተረቱላችው እንደ ራስ አሉላ እንግዳ (አባ ነጋ) የመሳሰሉትን ጀግኖች የሚያጠፋ ገደል የሚጥል ነገር ነው፡፡

ራስ አሉላ እ.ኤ.አ በ1887 የጣሊያን ወራሪ ብርጌዶችን በዶጋሊ ጦርነት ላይ አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ድል አድርገዋቸዋል፡፡ የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች አፍሪካን እንደ ዳቦ ቅርጫት ሲቀራመቷት እና ግዛቶቿን ቅኝ ግዛት ሲያደርጉ እና ዜጎቿን ባሮች ሲያደርጓቸው ራስ አሉላ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት እና ክብር አስጠብቀዋል፡፡

ከአውሮፓ ኃያላን ሀገራት ጋር ህብረት ፈጥረው የነበሩት አጼ ዮሐንስ 4ኛ ለራስ አሉላ ማግኘት ከነበራባቸው ማዕረግ በታች ዝቅ አድርገው በመስጠት ክህደት ፈጽመውባቸዋል፡፡ ያ ዓይነት ድርጊት ገና በመጀመሪያ መደረጉ ጣሊያን ወደ መሀል ሀገር ዘልቃ እንድትባ እና ወረራ እንድታደርገ አግዟታል፡፡ አዳፍኔ! ግዙፍ የሆነ የአመራር እና አስተዳደር ክሽፈት፡፡

እንደ አጋጣሚ ሆኖ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ እ.ኤ.አ በ1896 በአድዋ ላይ በተካሄደው ጦርነት ለጣሊያኖች ሊረሱት የማይችሉት ዓይነት ትምህርት ሰጥተዋቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የእራሷ ፊደል ያላት ብቸኛዋ የአፍሪካ ሀገር ናት፡፡ ሆኖም ግን የእውቀትን የመጨረሻውን ጠርዝ ለመመርመር ወይም ደግሞ በግብርና፣ በመስኖ፣ በስነ ሕንጻ እና በመጓጓዣ የነበረውን የጥንቱን እውቀት መዝግቦ እና ጠብቆ ለአዲሱ ትውልድ እንዲደርስ ለማድረግ አላስቻለም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ትንሽ ጠንከር ባለ ሁኔታ እውቀት የለውጥ መሳሪያ ነው በማለት ይጽፋሉ፡፡ እውቀት ለፍትህ፣ ለእኩልነት እና ለመልካም አስተዳደር ቅድመ ሁኔታ ነው…በጥንት ጊዜ እውቀት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚወደድ ወይም ዋጋ የሚሰጠው ጉዳይ አልነበረም፡፡ ያ ሁኔታ እስከ አሁንም ድረስ አልተለወጠም…  አዳፍኔ! ሌላው የህብረተሰብ ታላቅ መክሸፍ!

በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ጊዜ ዘመናዊ የመንግስት ስርዓት ተመስርቶ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ብቸኛው የስልጣን ባለቤት ሆኑ፡፡ የወታደሩ ክፍል፣ የፖሊስ እና የደህንነት ኃይሉ በእርሳቸው ቀጥተኛ ቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ከእርሳቸው የበለጠ አምባገነን እና ጨካኝ በነበረ ወታራዊ አምባገነን መንግስት በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣናቸው በኃይል እስከሚወገዱ ድረስ እራሳቸውን ጠቃሚ ሰው በማድረግ በአምባገነንነት በስልጣናቸው ተጣብቀው ቆይተዋል፡፡ አዳፍኔ! ግዙፍ የሆነ የአመራር እና አስተዳደር ክሽፈት፡፡

የኢትዮጵያ ልሂቃን ለበርካታ ዘመናት የውጭ ጠላቶችን በሚወጉ ጀግኖች (አርበኞች) እና ከውጭ ጠላቶች ጋር ተባባሪ በመሆን የእራሳቸውን ወገኖች በሚወጉ (ባንዳዎች) ተብለው በሁለት ይከፈላሉ፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን እንዲህ በማለት ይጽፋሉ፡ “በአሁኑ ጊዜ በስልጣን ላይ ያሉ የባንዳ ልጆች የከሀዲ ወላጆቻቸውን አሳፋሪ እና ዲቃላ ታሪክ ይደብቃሉ፡፡ አሳፋሪ የሆነ የወላጆቻቸውን ታሪክ ለመደበቅ ሲሉ ወዲያ እና ወዲህ ሲወራጩ ይታያሉ፡፡ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ስለመሆን እና አለመሆናቸው በእራስ የመተማመን ስሜት ይጎድላቸዋል፡፡ እራሳቸውን ከከፍታ ቦታ ላይ ለማውጣት በማሰብ የኢትዮጵያን ታሪክ ለእነርሱ በሚመቻቸው መልኩ እየነጣጠሉ እና እያዛቡ በመከለስ ያቀርቡታል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ100 ዓመታት አይበልጥም በማለት ያለምንም ሀፍረት በመናገር ላይ ገይኛሉ… በእራሳቸው የሚፈበርኩትን ታሪክ አጉልተው ለማሳየት ሲፈልጉ የኢትዮጵያን ታሪክ በጠማማው አዕምሯቸው አጥቁረው እና አዛብተው ያቀርባሉ፡፡” በአጭሩ የዘ-ህወሀት ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ታሪክ የለሽ የፍብረካ ታሪክ ይደሰኮራል፡፡ አዳፍኔ! ታላቅ የታሪክ እና የታሪክ ትንተና መከሸፍ፡፡

በጦር ሜዳዎች አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍስሰው የሀገራቸውን ነጻነት አስከብረው ስለቆዩት ስለኢትዮጵያ ጀግኖች የተጻፈው በጣም ትንሽ ነገር ነው፡፡ እውነተኛ አርበኛ ጀግኖች በሰላሙ ጊዜ እንደ ባንዳ እና ከሀዲ ዓይነት አያያዝ ሲደረግላቸው በተቃራኒው ደግሞ ባንዳ ለነበሩት እና ሀገራቸውን ከውጭ ጠላት ጋር በመተባበር ሲወጉ ለነበሩት እንደ ጀግና የሚቆጠሩበት እና የሚሸለሙበት እንዲሁም ስልጣን እና ሀብት የሚታደሉበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን እንዲህ በማለት ይጽፋሉ፣ “እስከ አሁን ድረስ የተጻፈው የእውነተኛ ጀግኖች ታሪክ ከቁጥር የሚገባ አይደለም፡፡ ስለ አርበኛ እና ጀግናው ስለ ደጃዝማች ገረሱ ዱኬ፣ ስለ ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ፣ ስለሻለቃ በቀለ ወያ ትንሽ ተጽፏል፡፡

[ከዚህ ዝርዝር ውስጥ እ.ኤ.አ በ1930ዎቹ ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ በኩል በጥቂት ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ በጦር ሜዳ ዉጊያ ጣሊያንን መግቢያ ቀዳዳ እያሳጡ በመዋጋታቸው ብቻ ሳይሆን ከዚህም በተጨማሪ በእርጅና ዘመናቸው የደርግን አምባገነን መንግስት ለሶስት ተከታታይ ዓመታት በጀግንነት ሲዋጉ ለነበሩት እና በእግዚአብሔር እንጅ በሰው ዘንድ ሳይታወቁ የቀሩትን ያልተዘመረላቸውን የጦር ሜዳ ጀግና የኢትዮጵያ አርበኛ የነበሩትን አርበኛ ደጃዝማች ከበደ ብዙነሽ (አባ መርዞ) ግልጽ በሆነ መልኩ እጨምራለሁ፡፡ በእነዚህ ጀግኖች በጣም እኮራለሁ፣ ከፍ ያለ ምስጋናም አቀርባለሁ!]

የታላላቅ ጀግኖች ኢትዮጵያውያንን ታሪክ ስማቸውን በትክክል መዝግቦ እና ያልታወቁትን እና በጦር ሜዳ ለውድ ሀገራቸው ሲሉ የወደቁትን ጀግኖች ደግሞ ዩኒቨርስቲዎች እያጠኑ እና እየተመራመሩ ስማቸው ለመጨው ትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ የድርሻቸውን ሚና መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ሆኖም ግን ለእንደነዚህ ዓይነት ጀግኖች ትኩረት በመስጠት ጥረት የሚያደርጉ ጥቂት ሰዎች አሉ፡፡ እናም ታሪካቸውን መዝግቦ ማስቀመጥ ጠቀሜታው ለእነዚህ ጀግኖች ሳይሆን ለመጭው ትውልድ ነው፡፡ አዳፍኔ! ግዙፍ የሆነ የኢትዮጵያ ምሁራን እና ልሂቃን መክሸፍ፡፡

በአዳፍኔ ውስጥ ፕሮፌሰር መስፍን ቀደም ሲል በሰሯቸው ስራዎች ላይ ትችት ላቀረቡላቸው (ከገጽ 165 – 268) ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በርካታዎቹ ትችቶች በስብዕናቸው ላይ ያነጣጠሩ ቀጥታ ግለሰባዊ ናቸው፡፡ ጥቂቶች ግን የእራሳቸውን ሀሳቦች ወይም ትንታኔዎች የምር የሚገዳደሩ ናቸው፡፡

ያ ግንዛቤ ሊወሰድበት የሚችል ጉዳይ ነው ምክንያቱም በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ፖለቲካ እና ማህበረሰብ ላይ ጥልቅ እውቀት እና የመከራከር ብቃቱ ያላቸው ምሁራን ናቸው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ፕሮፌሰሩ ግልጽ በሆነ መልኩ በአደባባይ ጠንካራ እና ጽናትን በተላበሰ መልኩ ለምንም ለማንም ሳይበገሩ ሀሳቦቻቸውን ማቅረብ የሚችሉ ምሁር በመሆናቸውም ትችት ቀርቦባቸዋል፡፡

ይኸ ጉዳይ እኔን የሚያሳስበኝ አይደለም ምክያቱም ፊቱን ሳያጥፍ፣ ምንም ዓይነት ድርድር ሳያቀርብ ጠንካራ እና በመርህ ላይ የተመሰረተ የነጻነት እና የሰብአዊ መብት ጥበቃ ተማጓች ሰው ጠላት ተደርጎ መፈረጅ እንደሌለበት እምነት ያለኝ ስለሆነ ነው፡፡

ሆኖም ግን ፕሮፌሰር መስፍን ቀደም ሲል ባቀረቧቸው ስራዎች ላይ በቀረቡት ትችቶች እና እርሳቸውም አሳማኝ በሆነ መልኩ እና በቂ አመክንዮዎችን እየዘረዘሩ በሰጧቸው ምላሾች ብዙ ተምሬባቸዋለሁ፡፡

በሀሳቦች ግጭት እና ጠንካራ በሆኑ ክርክሮች እምነት አለኝ፡፡ በአዳፍኔ መጽሐፍ ላይ በርካታ ክርክሮች ይኖራሉ የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

በዚህ ትችቴ ላይ ያሉኝን ሀሳቦች ፈነጠቅሁ እንጅ የመጽሐፍ ግምገማ ያካሄድኩ ያለመሆኔ እንዲታወቅልኝ እጠይቃለሁ፡፡

የመጽሐፍ ግምገማ በይዘቱ፣ በአቀራረቡ እና መጽሐፉ ባካተታቸው ፋይዳዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የሚሰጥ የስነጽሑፍ ትችት ነው፡፡

እኔ ሀሳቦቼን መፈንጠቅ ነው የመረጥኩት ምክንያቱም ፕሮፌሰር መስፍን በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ህዝብ እና ፖለቲካ ላይ ስላላቸው ጥልቅ እውቀት፣ ግንዛቤ እና ትንታኔ ላይ ሀሳቤን እንድገልጽ እና ያለኝን ከፍተኛ አድናቆት እንድገልጽ ዕድሉን የሚሰጠኝ ሆኖ ስላገኘሁት ነው፡፡

በአዳፍኔ ፕሮፌሰር መስፍን የእራሳቸውን የልጅነት ዘመናቸውን አንጸባርቀዋል፡፡

ልጅ በነበሩበት ጊዜ ሲያድጉ ምን ለመስራት ይፈልጉ እንደነበር ሲጠየቁ “ትምህርቴን በሚገባ ተምሬ ሀገሬን አገለግላለሁ“ የሚል ምላሽ ነበር የሰጡት፡፡

እኔም በልጅነት ዘመን እንደዚህ ለማድረግ ነበር የማስበው፡፡

በእርግጠኝነት እንዲህ በማለት አውጃለሁ፣ “በአሜሪካ ትምህርቴን እማራለሁ፣ እናም ትምህርቴን ካጠናቀቅሁ በኋላ ተመልሸ ሀገሬን አገለግላለሁ፡፡“

በኢትዮጵያ የሚገኙ ወጣቶች ሁሉ በኔ ጊዜ በልጀነታቸው የሚከተሉት መርህ እንደዚህ ያለ እንደሆነ እምነት አለኝ፡፡

እ.ኤ.አ በ1975 ሀገሬን ለማገልገል ለአጭር ጊዜ ወደ ሀገር ቤት ተመልሸ ነበር፡፡ እዚያ ሄጀ ሁኔታውን ሁሉ በቃኘሁት ጊዜ ምንም ዓይነት እገዛ ከማንም እንደማይፈልጉ ግንዛቤ ወሰድኩ፡፡

እየተንፏቀቀ ለመጣው የመፈንቅለ መንግስቱ ዋና አድራጊ ፈጣሪ ማኔጀሮች እራሳቸውን ብቻ በደህና ሁኔታ ይረዱ ነበር፡፡

በዋና ዋና የከተማይቱ መንገዶች ላይ ታንኮች ሲርመሰመሱ አስተውያለሁ፡፡ የወታደር መለያ ዩኒፎርም የለበሱ ወታደሮች በጅፖች ላይ ሆነው ባለ 50 ካሊበር ጠብመንጃዎቻቸውን እየወደሩ ሲዞሩ ተመልክቻለሁ፡፡

በውስጣቸው የታጠቁ ወታደሮችን ያጨቁ ወታደራዊ ካሚዮኖች ከተማዋን እያቋረጡ ሲፈተለኩ እመለከት ነበር፡፡

ለውጥን እንኳን መጣህ ብዬ ደስ ብሎኝ ነበር፣ ዳሩ ምን ያደርጋል ንጉሳዊውን አገዛዝ የተኩት ወታደሮች ናቸው፡፡ በሌላ አገላለጽ ንጉሳዊ አምባገነንነት በወታደራዊ አምባገነንነት ተተካ ማለት ነው፡፡

ይህም ማለት ከመጥበሻው ወደ እሳቱ ወይም ከድጡ ወደ ማጡ እንደማለት ነው፡፡

ይህንን ጉዳይ ካስተዋልኩ በኋላ ቀኝ ኋካ ዙር አልኩ እና ወዲያውኑ ወደ ዩኤስ አሜሪካ ፈትለክ አልኩ እና የድህረ ምረቃ ትምህርቴን ቀጠልኩ፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ በ1975 በበጋው ወቅት ከፕሮፌሰር መስፍን ጋር አዲስ አበባ ተገናኘን፡፡

ይህንን ጊዜ እና ከስተት የሚያስታውሱት አይመስለኝም፡፡

ከትምህርት ሚኒስቴር አጠገብ ካለች አንዲት የሻይ ቡና መሸጫ ክፍል ውስጥ አሁን በሕይወት ከሌለው እና በኢትዮጵያ ታሪክ ታዋቂ ከሆነው እና ከሰብአዊ መብት ተሟጋች ከነበረው አጎቴ ከፕሮፌሰር አለሜ እሸቴ ጋር ለመገናኘት ሄድን፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን እኔ ምንድን እንዳጠናሁ እና በአሜሪካ ሀገር ውስጥ ምን ተሞክሮ እንዳለኝ ጠየቁኝ፡፡ ለብዙ ጊዜ ከኢትዮጵያ ርቄ በመቆየት ከተመለስኩ በኋላ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ስላለኝ ምልከታ እንድናገርም ጠየቁኝ፡፡

በዚያን ጊዜ በእርግጠኝነት ምን ምላሽ እንደሰጠኋቸው አላስታውስም፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን እና ፕሮፌሰር አለሜ እሸቴ ሁለቱም ዘ-ህወሀት ስልጣን ከያዘ በኋላ በነበሩት ዓመታት ውስጥ ስለሰብአዊ መብት ጥበቃ ጠንካራ በሆነ መልኩ ገቡበት፡፡

ዘ-ህወሀት ስልጣን ከያዘ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉበኤን እንዳቋቋሙት አምናለሁ፡፡

ምናልባትም በተመሳሳይ ጊዜ ፕሮፌሰር አለሜ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ሊግን አቋቋሙ፡፡ በዚያን ጊዜ የነበሩኝ በርካታ ትውስታዎች አሁን ላይ ሆኝ ሳይ እረስቻቸዋለሁ፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን እና ፕሮፌሰር አለሜ በፖለቲካ እና በሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ዙሪያ ባከናወኗቸው ምሁራዊ ክንውኖች ታላቅ ኩራት ይሰማኛል፡፡ ያልከሸፈው የወደፊቱ ትውልድ የእነዚህን ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ልሂቆች አስተዋጽኦ ለታሪክ መዝግቦ መያዝ እና ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅበታል፡፡

እውነታውን ፍርጥርጥ አድርጎ ለመናገር በአዳፍኔ ላይ በሰጠሁት የሀሳብ ፍንጣቂ ፕሮፌሰር መስፍን በታላቅ ሀዘን ከተናገሯቸው ሰዎች መካከል እንደ አንዱ ሆኘ ተሰማኝ፡፡

እ.ኤ.አ በ1975 ኢትዮጵያን ተሰናብች በሄድኩ ጊዜ ዳግም ላልመለስ ምዬ ተገዝች ነበር፡፡ የእራሴ የሆኑ ግላዊ ምክንያቶች ነበሩኝ፡፡

እ.ኤ.አ በ1975 እንዲህ የሚሉ ግልጽ እና ቀላል ምርጫዎች ነበሩኝ፡ በስደት ነጻ ሆኖ መኖር ወይም ደግሞ በወሮበላ ወታደራዊ አምባገነን ስርዓት መዳፍ ስር ሆኖ ሲሰቃዩ መኖር፡፡

ያለምንም ማቅማማት ነጻ ሆኖ መኖርን መረጥኩ፡፡

ከደንቆሮ እና ያልሰለጠነ ወታደራዊ እና ወሮበላ አምባገነን መንግስት ነጻነትን መምረጥ የሞራል ስብዕና ዝቅጠት ወንጀል ነውን?

ሳልሞን ሩሽዲ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ “ሀሳብን በነጻነት መግለጽ ሁሉንም ነገር ማለት ነው፣ አዲስ የሆነ ልዩ ክስተት፡፡ ሀሳብን በነጻነት መግለጽ በእራሱ ህይወት ነው፡፡“

ከዚህም በተጨማሪ ሀሳብን በነጻነት መግለጽ ህይወት ያለውን ከሞተው እና እየሞተ ካለው የሚለይ ነው፡፡ ሀሳብን በነጻነት መግለጽ በማይቻልበት ጊዜ እና ሀሳብን በነጻነት መግለጽ ህይወት የለሽ በሆነበት ጊዜ በድን የሆኑ ሙት ነብሶች ብቻ አሉ ማለት ነው፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን መብቶቻቸውን በነጻነት ለመጠቀም እዚያው ሀገራቸው ውስጥ ቀጥለው በመታገል ላይ ይገኛሉ፡፡

ኢትዮጵያን ትቻት ሄድኩ፣ ሆኖም ኢትዮጵያ እኔን አልተወችኝም ለማለት እውዳለሁ፡፡

አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ በ2005 የተካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ተከስቶ በነበረው ውዝግብ ድምጻቸው በጠራራ ጸሐይ መዘርፉን በመቃወም ለኢትዮጵያ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰላማዊ በሆነ መልክ ተቃውሟቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ባሰሙ ንጹሀን ዜጎች ላይ ወሮበላ ነፍሰ ገዳይ ሎሌዎቹን በአዲስ አበባ ከታማ በማሰማራት እልቂትን እንዲፈጽሙ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ በዚያ እልቂት የግድያ ጥቃቱ ሰለባ ለሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን እና በዚያ እልቂት ቁስለኛ ለነበሩ ሌሎች ወገኖች በመቆም መናገር ጀመርኩ፡፡

ባለፉት 9 ዓመታት ውስጥ ሁልጊዜ ሰኞ ለእነዚህ ኢትዮጵያውያን ሰማዕቶች ጥብቅና በመቆም ጩኸቴን ማሰማት ቀጥዬ እገኛለሁ፡፡

ሆኖም ግን ሁልጊዜ በፕሮፌሰር መስፍን ጽሑፎች፣ በድረ ገጽ የሚለቀቁ ጽሑፎች እና በሚያሰሟቸወ ንግግሮች እመሰጣለሁ፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ያንን የቅጥፍና ምሁር እና አስመሳይ ባህሪ ተላብሶ ይቀርብ የነበረውን መለስን ስለኢትዮጵያ የጠራ ታሪክ እና ፖለቲካ ሲያስተምሩ ስመለከት ደስ ይለኝ ነበር፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ለዘ-ህወሀት ታማኝ ሎሌዎች ጠንካራ ትችት ሲያቀርቡ እና ጥልቅ የሆነ ትንታኔ እና አመክንዮ እየሰጡ ሲያሳፍሯቸው እና አንገታቸውን ሲያስደፏቸው በቪዲዮ በምመለከትበት ጊዜ ታላቅ እርካታ ይሰማኛል፡፡

እውነታውን ፍርጥርጥ አድርጎ ለመናገር ፕሮፌሰር መስፍንን በሕዝብ ፊት አደባባይ ለመሞገት በማሰብ የሚቀርቡ የዘ-ህወሀት ታማኝ ሎሌዎችን ድፍረት ስመለከት አንዳንድ ጊዜ ይገርመኛል ፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን አስደማሚ በሆነው የታሪክ እውነታዎችን በማስታወስ ልዩ እውቀታቸው እነዚያን የደናቁርት ስብስብ ድባቅ መተው እና በሕዝብ ፊት አሳፍረው በቅሌት ሲያሰናብቷቸው፣ በሰላው አንደበታቸው እና በማራኪ አመክንዮአዊ አቀራረባቸው ሲያሸማቅቋቸው ስሜትን የሚገዛ ትይንት መመልከት ማለት ነው፡፡

ምን ዓይነት አስገራሚ እይታ!

ባለፉት በርካታ አስርት ዓመታት ውስጥ ሲያቀርቧቸው ለነበሩት አስደማሚ የሆኑ ጽሁፎች እና ለሚሰጧቸው ትንታኔዎች በቂ እውቀት የለኝም ፡፡

ይኸ የእራሴ ስህተት ስለሆነ ወደፊት እንደማስተካክል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሆኖም ግን ከፕሮፌሰር መስፍን የመልክዓ ምድር/የጀኦግራፊ እና ወሰን ድንበሮች ምርምሮች እና ጥናቶች ጋር ተላምጃለሁ፡፡

ዘ-ህወሀት የኢትዮጵያን አንጡራ ግዛት ለሱዳን እና ለሌሎች አሳልፎ የሰጠበትን  ፕሮፌሰር መስፍን ለወደፊቱ ለዘ-ህወሀት መሞገቻ በቂ ማስረጃ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታዎችን ምርምሮች እና ጥናቶች የመስክ ስራዎች በኃላፊነት መርተዋል ወይም ደግሞ ተሳታፊ ሆነው አግለግለዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ዘ-ህወሀት ለእራሳቸው የፖለቲካ ግብ እና የባንክ አካውንቶቻቸውን ለማድለብ በማሰብ የኢትዮጵያን ሕዝብ መሬት ለጎረቤቶቻቸው በመስጠት ተመችቶን ተቀምጠናል በማለት ተቀምጠዋል፡፡

ቀደም ሲል እንዳቀረብኩት ትችት ሁሉ የዘ-ህወሀት አመራሮች ሁሉንም የድንበር ስምምነቶች ሚስጥር አድርገው ይዘዋል፡፡

ሆኖም ግን በዚህ ትውልድ ወይም ደግሞ በቀጣዩ ትውልድ የኢትዮጵያ ልጆች ሕጋዊ በሆነ መልኩ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ የግዛት መሬት ለባለቤቷ ለኢትዮጵያ የሚያስመልሱበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ጊዜውን ጠብቆ ይመጣል፡፡

ወደፊት ምን ያህል መሬት እንደምናስመልስ ፕሮፌሰር መስፍን እና የስራ ጓዶቻቸው ለዘመናት በያዙት መጠነ ሰፊ የመረጃ መጠን የሚወሰን ይሆናል፡፡

ዘ-ህወሀት የፈለገውን ያህል መሬታችንን እየቆረጠ መሸጥ ይችላል፣ ሆኖም ግን የፍርድ ቀን በመጣ ዕለት እድሜ ለፕሮፌሰር መስፍን የምርምር እና ትንተና ተግባራት ይሁን እና እያንዳንዷን የተቀደሰችዋን ቅንጣት መሬት ሳትቀር አናስመለሳለን እየቆጠርን እንረከባለን፡፡

በሽያጭ፣ በዝውውር እና ሊዝ እየተባለ በሚጠራው ወይም ደግሞ በኢትዮጵያ መሬት ላይ ዘ-ህወሀት ስለሚያድርገው ማንኛውም ዓይነት የመሬት ስምምነት ድርድር አንዳንድ ማስታዎሻዎችን ላቅርብ፡፡

ወያኔ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ለባዕድ ሀገር አሳልፎ የሰጠበተ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ክሽፈቶች ሁሉ ከፍተኛው እና በመጀመሪያው ረድፍ ላይ የማስቀምጠው ይሆናል፡፡

በእኔ አመለካከት ዘ-ህወሀትም እንደዚሁ እንዲህ የሚሉት የዊሊያም ኮውፐር የግጥም ስንኞች እንደሚያስገነዝቡን ሁሉ ጊዜውን ጠብቆ ወደ ማይቀረው ሞት ይሄዳል፡

“በረቀቀ መንገድ እግዚአብሔር ይሰራል፣

ታምራቱን ሁሉ በግልጽ ያሳየናል፣

ዕቅዱን በባህር ዘርግቶ ይነድፋል፣

ሞገድ ማዕበሉን ጸጥ አርጎ ይነዳል…”

የተጠናከረ የማዕበል ስብስብ ከፊታችን ተደቅኖ ይታያል፡፡ ሆኖም ግን  በሙስና ተዘፍቆ ዓይኑ የታወረው እና በስልጣን ጥማት የሰከረው ዘ-ህወሀት ከፊት ለፊቱ እየመጣ ያለው ማዕበል ሊታየው አይችልም፡፡

ዘ-ህወሀት የአፍሪካ ባሮች ቀደም ሲል ወደ አሜሪካ በሚጋዙበት ወቀት የተዘመረውን እንዲህ የሚለውን የሙዚቃ የግጥም ስንኝ ምክር በአንክሮ መከታተል ይኖርበታል፡ “እግዚአብሔር ለኖህ የቀስተደመናን ምልክት ሰጠው፡፡ ከዚያ በኋላ ምንም ዓይነት ውኃ አልነበረም፡፡ በቀጣዩን እሳትን ጠብቅ!“

በዚህ የሀሳብ ፍንጠቃዬ ለትንታጉ ልሂቅ እና የሕዝብ ልጅ ለፕሮፌሰር መስፍን ክብር መስጠት እፈልጋለሁ፡፡

እርሳቸውን እንደ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ልሂቅ ጀግና አርበኝነታቸው ከፍተኛ የሆነ ክብር ልሰጣቸው እፈልጋለሁ፡፡

ኔልሰን ማንዴላ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ “እንደ አፍሪካ አርበኝነቴ ሁልጊዜ እራሴን ከፊተኛው ረድፍ በማድረግ በጽናት እቆማለሁ፡፡“

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን ለሚወዷት ሀገራቸው በግንባር ቀደምትነት ከፊት የሚቆሙ ልሂቅ አርበኛ አድርጌ እቆጥራቸዋለሁ፡፡

ለምሁራዊ ስራቸው እና ለበርካታ አስርት ዓመታት ለሀገራቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ የሆነ አድናቆት እና ክብር አለኝ፡፡

ኢመርሰን በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ “የምሁራን ቢሮ ዋናው ተግባሩ ዜጎችን ማበረታታት፣ ማነሳሳት እና ከሚታየው በርካታ ነገር ሁሉ መርጦ እውነታውን በማሳየት ለስኬታማ ውጤት አመራር መስጠት ነው፡፡ ልሂቅ ለነገሮች ጊዜ ወስዶ ጠንክሮ በመስራት የማይከበር እና ክፍያ የማይፈጸምበት ብርቱ ምልከታ አለው፡፡“

የምሁርነት የጊዜ ህይወት ቀላል አይደለም፡፡ ረዥም የዝግጅት ጊዜ እና ጥናትን ይጠይቃል፡፡ምሁር ሰይጣናዊነትን አስቀድሞ የሚገነዘበው በመሆኑ በአገዛዙ መከራ እና ስቃይ ይደርስበታል፡፡ እንደዚሁም ሰይጣናዊነትን እንዴት ማስወገድ እንዳለበት የእውቀት እጥረት ሊያጋጥመው ይችላል፡፡

እውነተኛ ምሁር የጥላቻ መንፈስ ከባቢ አየር በተንሰራፋበት ጊዜ ለነገሮች እልባት ለመስጠተ ከብዙሀኑ ሕዝብ ጎን በተለይም ከተማረው የህብረተሰብ ጋር በጽናት በመቆም ይታገላል፡፡

ምሁር ምንጊዜም የዘለፋ እና የውንጀላ ክስ ዒላማ ነው፡፡

ለዚህ ሁሉ ማዋረድ እና ዘለፋ የምሁሩ ማካካሻ ምንድን ነው?

ለሰው ልጅ ታላቅ የተባለውን ስራ በመስራት እርካታን እና ደስታን ማግኘት ነው፡፡ ከግል ጉዳይ እራሱን መዞ ያወጣው እራሱ ምሁሩ ነው እናም በሚያፈልቀው ሀሳብ እና በሚያከናውናቸው ህዝባዊ ስራዎች ኮርቶ እና ተደስቶ በህብረተሰቡ ዘንድ ይኖራል፡፡ ምሁር የዓለም ሕዝብ ዓይን ነው፡፡ ምሁር የዓለም ሕዝብ ልብ ነው፡፡ ወደ ኋላ የጀግንነት ስሜቶችን በመንከባከብ እና በህብረተሰቡ ውስጥ ግንኙነቱን በማጠናከር፣ የተከበሩ ሰዎችን የህይወት ታሪክ በመመዝገብ፣ የሙዚቃ ግጥሞችን በመድረስ የታሪክን መደምደሚያ በማዘጋጀት የታሪክ ጎማን ወደኋላ ለማሽከርከር ጥረት የሚያደርጉ ያልሰለጠኑ ኋላቀሮችን እና ጋጠወጥ ወሮበሎችን ያለምንም ማቅማማት በጽናት በመቆም ይታገላቸዋል፡፡

እንግዲህ የፕሮፌሰር መስፍን ምሁራዊ ተግባር እና የአደባባይ ህይወት ይህንን እንደሚመስል አምናለሁ፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ስቃይ ደርሶባቸዋል፣ በፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶባቸው ያለምንም ጥፋታቸው በአምባገነኖች መጉላላት እና ውርደት እንዲደርስባቸው ተደርገዋል፡፡

እንግዲህ የእርሳቸው ሽልማት ምንድን ነው? ምናልባት ህዝባቸውና  ባልደረቦቻቸው ፍቅር፣ አድናቆት እና ምስጋና?

የእርሳቸው እውነተኛው ሽልማታቸው የእርሳቸውን ሰው ሆኖ የመፈጠር ከፍተኛ የሆነ የነጻነት መብት መተግበር መቻላቸው ነው፡፡ አዕምሯቸው ያሰበውን የመናገር ነጻነታቸው ትክክለኛው ሽልማታቸው ነው፡፡

ለበርካታ አስርት ዓመታት ከእርሳቸው የግል ጉዳዮች ይልቅ ለኢትዮጵያውያን መብት፣ ዕድገት እና ልማት አበርትተው ሰርተዋል፣ በመስራት ላይም ይገኛሉ፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያ ዓይን እና ልብ ለመሆን በቅተዋል፡፡

ሀገሪቱን ወደ ኋላ በመጎተት ሰላሟን እና ልማቷን በማደናቀፍ ላይ ለሚገኙት ወሮበላ ያልሰለጠኑ የደናቁርት ስብስቦች ፊት ለፊት በመሞገት የህዝቡ የጀግንነት አስተሳሰቦች እንዲጠናከሩ፣ የተከበሩ ልማዶች እና ለህዝባቸው የሀገራቸው ታሪክ ትምህርት በህዝቡ ዘንድ እንዲታወቅ ለማድረግ የሰሩ እውነተኛ ቁንጮ ምሁር ናቸው፡፡

ያለምንም ፍርሀት የልባቸውን እና ያሰቡትን በአደባባይ አውጥተው መናገር እና የጨቋኞችን፣ የአምባገነኖችን፣ የወሮበሎችን፣ በስልጣን እርካብ ላይ ሆነው በህዝብ ላይ ወንጀል የሚፈጽሙትን  ዕኩይ እና ድብቅ ሚስጥር በህዝብ ፊት በአደባባይ አውጥተው የሚያጋልጡ መንፈሰ ጠንካራ የአደባባይ ምሁር ናቸው፡፡

ፕሮፌሰሩ በግል ሀሳቦቻቸው እጅግ በጣም የመጠቁ እና መቸውንም ጊዜ ቢሆን በስልጣን ኮርቻ ላይ ላሉት ለጨቋኞች እና ለወሮበሎች እርሳቸው በሚያውቁት ቋንቋ ብቻ ማለትም እውነት በመናገር ብርክ ያስይዟቸዋል፣ በመጠቀው ሀሳቦቻቸውም ድባቅ ይመቷቸዋል፡፡

በአዳፍኔ ፕሮፌሰር መስፍን ከአምሳ ዓመት አካባቢ ጀምሮ ሲያቀርቡት የነበረውን ጥያቄ እኔ አሁን እንዲህ በማለት አቀርበዋለሁ፡

አንዲህ በማለት ጽፈው ነበር፡

እ.ኤ.አ በ1950ዎቹ በዩኒቨርስቲው ውስጥ ውይይት ይካሄድ ነበር፡፡ ከውይይቱ በኋላ እንዲህ የሚል አንድ ጥያቄ አቀረብኩ፡ ኬንያ ጆሞ ኬንያታ አሏት፡፡ ታንዛኒያ ጁሊየስ ኔሬሬ አሏት…ኢትዮጵያ ለምንድን ነው ታላቅ ሰው የሌላት? አንድ ጮሌ አስደንጋጭ በሆነ መልኩ እኛም ጃንሆይ (ቀ.ኃ.ሥ) አሉን በማለት መለሰ፡፡ ከተቀመጥኩበት ተነሳሁና ትክክል አለመሆኑን እንዲህ በማለት ተናገርሁ፡፡ ጃንሆይ በእድሜ ታላቅ ናቸው፡፡ እኔ እየጠየቅሁ ያለሁት በስራው ታላቅ የሆነ እና ከፍተኛ ስኬቶችን የተጎናጸፈ ኢትዮጵያዊ ለምን የለም ነው ያልኩት በማለት ጥያቄውን የበለጠ ግልጽ አደረግሁት፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያለኝ ጥያቄም ያው ጥያቄ ነው፡፡ እስከ አሁንም ድረስ ታላቅ ሰው የለንም፡፡

እኔ ደግሞ ይህንን አባባል ሙሉ በሙሉ እቃወማለሁ!

ሐቁ አይካድም አንድ ታላቅ ሰውማ አሉን፡፡

ስማቸውም መስፍን ወልደማርያም ይባላል፡፡ መምህር ናቸው፡፡ የሙያ እምቢተኛ ናቸው፡፡ እውነት ተናጋሪ ናቸው፡፡ ተቃዋሚ ናቸው፡፡ ላመኑበት ነገር ምንም ዓይነት ነገር የጥገና ለውጥ የማያደርጉ መንፈሰ ጠንካራ ሰው ናቸው፡፡ በተጫባጭ እውናዊ ነገሮች ላይ ብቻ የሚያምኑ ሰው ናቸው፡፡ የሕዝብ ቀስቃሽ ናቸው፡፡ አመጸኛ ልሂቅ ናቸው፡፡ የሀሳብ ሰው ናቸው፡፡ የሚጽፉ ሰው ናቸው፡፡ የሚያነሳሱ ሰው ናቸው፡፡ ህዝብን ለመልካም ነገር የሚቀሰቅሱ ሰው ናቸው፡፡

ጆርጅ ኦርዌል እንዲህ ብለው ነበር፣ “ዓለም አቀፋዊ ማጭበርበር በተንሰራፋበት ዓለም ውስጥ እውነትን መናገር አብዮታዊ ድርጊት ነው፡፡“

ደህና፣ ለፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እንዲህ የሚል አንድ ሌላ ማዕረግ እሰጣቸዋለሁ፡ “እውነት ተናጋሪ አብዮተኛ”!

በአዳፍኔ ጨለምተኛ መልዕክት ላይ ሀሳቤን እንደፈነጠቅሁ በርካታ ክሽፈቶችን ድል ያደረገው እና እንዲህ በሚሉት የአቤ ሊንኮልን ቃላት ምቾትን ተጎናጽፊያለሁ፡ “የእኔ ትልቁ ስጋት የአንተ መክሸፍ ያለመክሸፍ አይደለም፣ ሆኖም ግን ውድቀትህን ተቀብለሀል ወይ ከሚለው ላይ ነው፡፡“

እንደ ኢትዮጵያውያን ሁላችንም አስከፊ በሆነ መልኩ ወድቀናል፡፡ ከሽፈናል። መጥፎ አስተዳደር ተጭኖብናል፡፡ ለሀገር መሪነት ወሮበሎችን ተሸክመናል፡፡ ሕዝቦቻችንን መመገብ አልቻልንም፡፡ ሀገራችን ዓለም አቀፍ የረኃብ ማስታወቂያ የስዕል ሰሌዳ ሆና ቀጥላለች፡፡ እውነትን እንፈራለን፡፡ እርስ በእርሳችን እንፈራራለን፡፡ እራሳችንን እንፈራለን፡፡ ጥቂቶቻችን እራሳችንን በፈቃደኝነት ስደተኛ አድርገናል፡፡ እጅግ በርካቶቻችን ደግሞ እንድንሰደድ ተገድደናል፡፡

በቀላሉ ለማስቀመጥ ምስቅልቅል ባለ ሁኔታ ላይ እንገኛለን!

“አዳፍኔ” ሆነናል፡፡

በእኔ ትውልድ እና ከእኔ በፊት በነበረው ትውልድ ላይ እምነት የለኝም ብዬ ስናገር ሀፍረት ይሰማኛል፡፡ ስለሆነም አሁን መናገር አልችልም፣ ሆኖም ግን ሰላሜን ለብዙ ጊዜ ይዠ ማቆየት አልችልም፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን በአሁኑ ጊዜ ላለው ኢትዮጵያዊ ወጣት እና ለመጭው ትውልድ ሶስት ቀላል ጥያቄዎችን መዝግበው አቅርበዋል፡፡ እነርሱም፡

1ኛ) የወላጆቻችሁን ትውልድ መክሸፍ በጸጋ ተቀብላችኋልን?

2ኛ) የአያቶቻችሁን እና የቅድመ አያቶቻችሁን ትውልድ መክሸፍ በጸጋ ተቀብላችኋልን?

3ኛ) የእራሳችሁን ትውልድ መክሸፍ በጸጋ ተቀብላችኋን?

እነዚህ ከላይ በዝርዝር የቀረቡት ጥያቄዎች በአንድ ወይም በሌላ መልኩ በአዳፍኔ መጽሐፍ በእያንዳንዱ ገጽ ላይ የሚንቀሳቀሱ አንገብጋቢ ጉዳዮች ናቸው፡፡

በአዳፍኔ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሊማሩት ይገባል የምንለው አንድ ታላቅ ጉዳይ አለ ብለን የምናስብ ከሆነ ከብዙ ዓመታት በፊት ሸክስፒር የተናገሩት እንዲህ የሚለው አባባል ነው፡ “የወደፊት ዕጣ ፈንታችን በእኛው በእራሳችን እንጅ በሌላ በማንም የሚወሰን አይደለም፡፡“

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እንደ ቀደምቶቻቸው ሁሉ የጀግና ህይወትን የሚኖሩ ምሁር በመሆናቸው ለእንደዚህ ያሉ ጥያቄዎች ምንም የሚየስጭንቃቸው ጉዳይ አይደለም፡፡ እርሳቸው በስልጣን ላይ ያሉትን ወሮበላ የደናቁርት ስብስብ ብቻ ሳይሆን የእነርሱን በውጭ የሚገኙትንም አጭበርባሪ እና በጥቅም ስሌት ብቻ የሚጓዙትን ንጉሳዊ አለቆቻቸውን ጭምር የሚተገሏቸው ብዕሮቻቸውን፣ እርሳሶቻቸውን፣ ወረቀቶቻቸውን እና አስደማሚ የሆነ ከታቢ አዕምሯቸውን በመጠቀም ነው፡፡

ስለሆነም ለአይበገሬው ለፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እንዲህ የሚሉትን እና በዊሊያም ኤርነስት ሄንሌይን የተቋጠሩትን ግጥም ስንኞች ላቀርብላቸው ወደድኩ፡

ከምንጊዜም በላይ በሩ ቢጣመም
የተንሸዋረረው ፍትህ ቢጓደልም፣
በኔ ላይ ደጋግሞ ቅጣት ቢቆልልም፣
ከዓላማዬ ፍንክች በፍጹም አልልም፡፡

የእራሴ እጣፈንታ ወሳኙ እራሴ ነኝ፣
ማንም አምባገነን የማይጨፍርብኝ፣
በዲያብሎስ መንገድ የማያስገድደኝ
የነብሴ መርከቡ ካፕቴኑ እራሴ ነኝ፡፡

ካፒቴን መስፍን ለእርስዎ የህይወት እና የፍቅር ምንጭ ለሆነችው ለአንዷ ኢትዮጵያ እስከ አሁን ድረስ ለሰሩት ስራ፣ አሁን በመስራት ላይ ላሉት እና ለወደፊቱ ለመስራት ላቀዱት ስራ ሁሉ እግዚአብሔር የተመኙትን እንዲያሳካልዎት እና ስኬታማ እንዲሆኑ ምኞቴን እየገለጽኩ እጅግ በጣም አድርጌ አመሰግናለሁ፡፡

በሀገርዎ እውነተኛ ዴሞክደራሲ እና ሰላም ሰፍኖ፣ እንዲሁም በሸፍጠኞች የቁጥር የቁማር ጨዋታ ሳይሆን እውነተኛ የምጣኔ ሀብት ዕድገት እና ልማት ተመዝግቦ፣ የሚታገሉለት ሕዝብዎ ከችጋር እና በየጊዜው በረሃብ ከመሰቃዬት ተላቆ ለማየት እንዲያበቃዎት እመኛለሁ፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ጥቅምት 23 ቀን 2008 ዓ.ም

 

Similar Posts