ኢትዮጵያ እንደ ጋና መሆን የማትችለው ለምንድን ነው?

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም    

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

በአደባባይ በይፋ አምናለሁ፡፡

በጋናውያን ላይ መንፈሳዊ ቅናት አድሮብኛል፡፡

ባራክ ኦባማ የመጀመሪያ ጉዞውን ወደ አፍሪካ ባደረገበት ወቅት በአፍሪካ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ወዳላት እና የከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ባለቤት ወደሆነችው ወደ ናይጀሪያ ለመሄድ አልመረጠም፡፡

በአሁጉሩ በምጣኔ ሀብት ደረጃዋ የሁለተኛነት ደረጃ ወደያዘችው የኔልሰን ማንዴላ ሀገር ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ አልመረጠም፡፡

እንደዚሁም ደግሞ ኦባማ የወላጅ አባቱ የትውልድ ሀገር ወደሆነችው ወደ ኬንያ ለመሄድ አልመረጠም፡፡

ዜጎችን በማጎሪያ እስር ቤት እያጋዘች አሳር ፍዳ በማሳዬት በአስከፊነቷ በምትታወቀው እና በአፍሪካ የሁለተኛነት ደረጃን ይዛ ወደምትገኘው ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ አልመረጠም፡፡ ቻይና በዓለም ላይ በአስከፊ ደረጃ ዜጎችን በማሰር የቀዳሚነቱን ደረጃ ይዛ ትገኛለች፡፡ ወይ ጉድ! አንድ ዓይነት ላባ ያላቸው ወፎች አብረው ይበራሉ እንዲሉ መሆኑ ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ይፋ ፕሬዚዳንታዊ ጉብኝት ለማድረግ የሕዝብ ብዛቷ 27 ሚሊዮን የሆነውን ጋናን መረጠ፡፡

ኦባማ ጋናውያን እያራመዱት ላለው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ክብር ለመስጠት በማሰብ ነበር ወደ ጋና ጉዞ ያደረገው፡፡

ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስብ በእኔ አመለካከት ኦባማ እንደ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ፕሬዚዳንትነት አፍሪካን ባይጎበኝ ግድም አይሰጠኝ ነበር።

እኔ አንዴ ዛሬ አያረገዉና የኦባማ ዋና አድናቂ ነበርኩ፣ ሆኖም ግን እ.ኤ.አ ሀምሌ 2015 ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ በአዲስ አበባ በመገኘት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ከህዝቡ ፈቃድ ውጭ በኃይል በስልጣን እርካብ ላይ ተንጠልጥለው ለሚገኙት ወሮ በላ አምባገነኖች የጠሩ ዴሞክራቶች ናቸው ብሎ በጆሮዬ በሰማሁበት ጊዜ አቅለሽልሾኝ ለማስመለስ ተናንቆኝ ነበር።

እንዲያው የነገሮችን ሁኔታ ለመገንዘብ ያህል አዛውንቱ እና አምባገነኑ ሮበርት ሙጋቤ እ.ኤ.አ በ2013 በተደረገው ሀገረ አቀፍ ምርጫ 61 በመቶ አሸነፍኩ ብሎ ሲያውጅ ኦባማ ምርጫው ተጭበርብሯል በማለት አውግዞ ነበር፡፡

በሚያስገርም ሁኔታ ከሕዝቦች ፈቃድ ውጭ በጠብመንጃ ኃይል በሕዝቦች ጫንቃ ላይ ተፈናጥጦ የሚገኘው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እ.ኤ.አ ግንቦት 2015 በተደረገው ሀገር አቀፍ የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ መቶ በመቶ (100%) አሸነፍኩ ብሎ ያወጀበትን የቅጥፈት እና የወሮበላ አካሄድ በመደገፍ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ነው ብሎ የቀጣፊ እና የአስመሳይነት የምስክርነት ቃሉን ሰጠ፡፡

የአሜሪካ የተውኔት ጸሐፊ የሆኑት ታላቁ ቴኔስ ዊሊያምስ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ “ከውሸታምነትም በላይ እጅግ በጣም የከፋው ነገር ደግሞ አስመሳይነት ሲጨመርበት ነው!” በእውነት ይህ ትክክለኛ በሆነ መንገድ የኦባማ ስብዕና መገለጫ ባህሪ ነው!

ያም ሆነ ይህ…

የኦባማ የጋና ጉብኝት የመጀመሪያ ነው ሆኖም ግን በጋናውያን ላይ ለምን እንደምቀና ትኑሹ ምክንያት ነው።

ኦባማ ጋናን በመጀመሪያ ስለጎበኘ አልቀናሁም ብዬ አለከራከርም።

እንደ ፕሬዚዳንት ጉብኝት ኢትዮጵያ የኦባማ የመጀመሪያ ጉብኝት መዳረሻ ሀገር መሆን እንደነበረባት አምናለሁ፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የኩራት ፈርጥ እንደሆነች አለትርጥር አምናለሁ፡፡ ኢትዮጵያ መቸውንም ጊዜ ቢሆን ቅኝ ተገዥ ሆና አታውቅም፡፡

ኢትዮጵያ በዘመናዊ የጦር መሳሪያ እስከ አፍንጫው ታጥቆ እና ተደራጅቶ የመጣውን የጣሊያን የቅኝ ግዛት ወራሪ ኃይል በጦር ሜዳ አሳፋሪ ሽንፈትን በማከናነብ ድል አድርጋ በመጣበት እግሩ ጨርቄን ማቄን ሳይል እንዲመለስ ያደረገች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ናት፡፡

አፍሪካን እንደ ቅርጫ ስጋ ለመቀራመት እና የየድርሻቸውን ግዛት ህጋዊ በማድረግ ለማስያዝ የሚያስችለው የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ስምምነት ጉባኤ እ.ኤ.አ በ1896 በበርሊን ከተማ ከተካሄደ ከሁለት ዓመታት በኋላ ኃያሉ የኢጣሊያ ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ሙከራ አድርጎ ነበር፡፡

በዲፕሎማሲው እና በወታደራዊው መስክ ከሁሉም የላቁት ጀግናው ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የመጣውን ወራራ ኃይል አፈር ድሜ በማብላት አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው የጣለውን ጥሎ የያዘውን ይዞ ወደ ሮም እንዲፈረጥጥ አድርገዋል፡፡

የዳግማዊ አጼ ምኒልክ የ19ኛው ክፍለ ዘመን የታላቁ የአድዋ የጦርነት ዘመቻ ከዚያ በፊት ከተካሄዱት ታላላቅ የዓለም ጦርነቶች ማለትም ከአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት እና እ.ኤ.አ በ1812 ናፖሊዮን ከራሽያ ጋር ካደረገው የጦርነት ዘመቻዎች ሁሉ በእርግጠኝነት የበለጠ ዘመቻ ነው፡፡ (የቪዲዮ ምስሉን ለመመልከት እዚህ ጋ ይጫኑ፡፡)

ጣሊያኖች ከዚያ ታሪካዊ እና የአፍሪካውያን እና የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኩራት ከሆነው ጦርነት ትምህርት ሳይቀስሙ እ.ኤ.አ በ1935 እንደገና ለዳግም ወረራ እና ኢትዮጵያን ቅኝ ተገዥ ለማድረግ ተመልሰው ወረራ ፈጸሙ፡፡

ከስድስት ዓመታት በኋላ በዱር በገደሉ በተሰማሩት በጀግኖቹ የኢትዮጵያ አርበኞች መውጫ መግቢያ በማጣት ተቀጥተው እንደገና ቅራቅንቧቸውን ሸክፈው ወደ ሮም ለመመለስ ተገደዱ፡፡

እንግዲህ ከአንድ ክፍለ ዘመን በፊት የኢትዮጵያ ሁኔታ እንደዚህ ነበር፡፡ እውነት ለመናገር ኢትዮጵያ የነጻነት እና የጀግኖች ሀገር ነበረች። አሁንም  ናት ለማለት በሙሉ አፍ ይከብደኛል!

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የለማኝ መሪዎች ሀገር ሆናለች!

ለኢትዮጵያ አለቅሳለሁ!

ወይ አገሬ!  የወሮ በላ መጫወቻ ሆነሽ ትቀሪ !

ኢትዮጵያ አጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ይላል ዳዊት።

ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ጊዜ በአባቶቻቸው አጥንት የተገነባውን እና በቀድቶቻቸው ደም እና ላብ የተለሰነውን ክብራቸውን እና ሞገሳቸውን አጥተዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ልጆች ዘራፊ የሆነው ወሮበላ ቡድን ሀገሪቱን ሲመዘብር እና ሲዘርፍ የበይ ተመልካች ሆነው በመመልከት ላይ ይገኛሉ፡፡

ያም ሆኖ ግን አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብርሀን ቀንዲል ናት ብዬ እከራከራለሁ።

እ.ኤ.አ በ1963 መሰረቱን በቋሚነት በአዲስ አበባ ከተማ በማድረግ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ) ተመሰረተ፡፡

ለድርጅቱ መመስረት ታላቁን ሚና የተጫወቱት ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ በ1972 በተደረገው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሀገሮች ርዕሰ ብሄሮች እና መንግስታት 9ኛ ጉባኤ ላይ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ በአቻዎቻቸው “የአፍሪካ አንድነት አባት“ ተብለው ተመረጡ፡፡

ከሶስት አስርት ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የክርስትና አባትነት ደረጃን ያዘች፡፡ ንጉሱ በትግላቸው ያቋቋሙት እና እውን ያደረጉት ድርጀት መሆኑ ተረስቶ ሀገር ባበቀላቸው ጃርቶች እና ሸፍጠኞች ዕኩይ ምግባር አማካይነት እራሳቸው ንጉሱ መስርተው እና መርቀው በከፈቱት ድርጅት ቅጥር ግቢ ውስጥ የእርሳቸው ስም እንዳይነሳ እና ሀውልትም እንዳይቆምላቸው ተደረገ፡፡

ለሁሉም ጊዜ አለው ነው እና ታሪክ ዕውነታውን ስለማይስት ንጉሱ በትክክለኛው ስማቸው እና ክብራቸው የሚዘከሩበት ወቅት እሩቅ እንደማይሆን እነዚህ በምቀኝነት ናላቸው የዞረው የታሪክ አተላዎች ሊገነዘቡት ይገባል፡፡

ለሱማ ከጫካ የወጡ ዱር ዉየዎች ስልጣን ላይ ተፈናጠው የለምን?

ወደ ኦባማ እንመለስ፡፡

ኦባማ እ.ኤ.አ ሀምሌ 2009 ጋናን በጎበኘበት ወቅት ለሁሉም አፍሪካውያን ዴሞክራሲ እና የሰብአዊ መብት እንዲስፋፋ እና እንዲጠናከር ዲስኩር አሰምቶ ነበር፡፡

ጋናውያን ለአፍሪካውያን ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው እንዲናገሩ እንዲህ የሚል መልዕክት አስተላልፎ ነበር፣ “አፍሪካ ጠንካራ ተቋማትን እንጅ ኃይለኛ ሰዎችን አትፈልግም፡፡ ታሪክ ከእነዚህ ጀግኖች አፍሪካውያን ጎን እንጅ መፈንቅለ መንግስት በማድረግ ወይም ደግሞ ሕገ መንግስትን በመለወጥ ስልጣንን ይዞ ለመቆየት ከሚጥሩት ጎን አይደለም፡፡“

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2015 ኦባማ ኢትዮጵያን በመጎብኘት ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካውያን ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው እንዲናገሩ እንዲህ የሚል መልዕክት አስተላለፈ፣ “በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጠን ማንኛውንም መንግስት በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጠውን የኢትዮጵያን መንግስት ጨምሮ ከስልጣኑ በኃይል ለማስወገድ የሚደረገውን ማንኛውንም ቡድን እናወግዛለን፡፡“ ኦባማ እየተናገረለት ያለው እ.ኤ.አ ግንቦት 2015 በተደረገው ሀገር አቀፍ የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ 100% (መቶ በመቶ) አሸንፊያለሁ ብሎ ስላወጀው ስለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ነው፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በስልጣን ለመቆየት ሕገ መንግስቱን ለውጧል፡፡

በሌላ አባባል የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በስልጣን እርካብ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ ለመቆየት በጠራራ ጸሐይ በአደባባይ ምርጫውን እየዘረፈ ይኸው እንግዲህ ወደ ሩብ ምዕት ዓመት ያህል ያለሕዝብ ፈቃድ በኃይል በጠብመንጃ አፈሙዝ በስልጣን ላይ ተንጠልጥሎ ይገኛል፡፡

ኦባማ እ.ኤ.አ ሀምሌ 2009 ጋና ላይ በመገኘት ያሰማውን ዲስኩር ፍጹም በሆነ መልኩ እረስቶታል፡፡

በቂ መረጃዎች ያላቸው እና በአመክንዮ የሚያምኑ ሰዎች 90 ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባለቡት የምርጫ ምህዳር አንድ ብቸኛ የፖለቲካ ፓርቲ ምርጫውን መቶ በመቶ አሸነፍኩ ሲል እና ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ብሎ ሲያውጅ ኦባማ ያንን ተቀብሎ ማስተጋባቱ ሊታመን የማይችል እና በኦባማ ምንነት ላይ የሚያስገርም ሁኔታን ይፈጥራል፡፡

እኔ እንደዚህ ያለ ነገር አላውቅም፡፡ እንደዚህ ያለ የምርጫ ውጤት ዴሞክራሲያዊ ነው በሚለው አሰጥ አገባ ውስጥ ወያኔ እና አቦማ ካልሆኑ በስተቀር እኔ ፍጹም የለሁበትም!

ኦባማ እ.ኤ.አ ሀምሌ 2009 አክራ ላይ በመገኘት ያደረገውን ንግግር ተከትሎ “የጋና መንግስት ያለው እና እኛ የሌለን ነገር ምንድን ነው?“ በሚል ርዕስ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡

በዚያ ትችት ላይ ጋና በዴሞክራሲ ግንባታው ላይ እንዴት ስኬታማ እንደሆነች እና ኢትዮጵያ ለምን የመከነ መንግስት እንደሆነች ግልጽ ለማድረግ ተሞክሮ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ በ2009 ኢትዮጵያ ከመከኑ መንግስታት/Failed states በ16ኛ ተራ ቁጥር ላይ ተቀምጣ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ በ2009 ጋና በየትኛውም የመከኑ መንግስታት መለኪያ ግንባር ቀደም ዝርዝር ውስጥ አልነበረችም፡፡

በዚያን ጊዜ ለእራሴ እንዲህ የሚል ጥያቄ አቅርቤ ነበር፣ “ጋናውያን ያሏቸው ሆኖም ግን ኢትዮጵያውያን የሌሏቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?“

ይህንን መነሻ በማድረግ የጋናን የፖለቲካ ታሪክ ማጥናት እና መመራመር ጀመርኩ፡፡

የጋና የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት የሆኑት ክዋሜ ንክሩማህ ታላቅ ጸረ ቅኝ አገዛዝ መሪ እና የፓን አፍሪካ አቀንቃኝ ነበሩ፡፡

ንክሩማህ ጋና እ.ኤ.አ በ1957 ነጻነቷን እንድትቀዳጅ የመሪነቱን ሚና ተጫውተዋል፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በመመስረቱ ረገድ ከቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ ቀጥለው ሁለተኛው ተጽዕኖ ፈጣሪ እና ታላቅ መሪ ነበሩ፡፡

ሆኖም ግን ንክሩማህ ባልታሰበ እና ድንገተኛ በሆነ መልኩ የመንሸራተት እና ሕግን ያልተከተለ የአካሄድ መንገድን መረጡ፡፡

እ.ኤ.አ በ1964 ንክሩማህ እራሳቸውን የእድሜ ልክ ፕሬዚዳንት አድርገው በመሰየም የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የውድድር ተሳትፎ በመገደብ እንዲህ የሚል የመከራከሪያ ጭብጥ አቀረቡ፣ “ዴሞክራሲዊ ስርዓትን በተከተለ መልኩ የተዘጋጀ ሕገ መንግስት የቅኝ ተገዥነት የነጻነት ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ የቅላይነት ባህሪ ባላቸው እርምጃዎች አስቸኳይነት ምክንት ወደ ኋላ ተንሸራተተ፡፡“

እ.ኤ.አ በ1966 ንክሩማህ ቻይናን እየጎበኙ በነበሩበት ጊዜ በተካሄደ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ተወገዱ፡፡

የንክሩማህ የአፍሪካ መራራ ትሩፋት እ.ኤ.አ ከ1966 በኋላ በአፍሪካ በስፋት ተሰራጭተው ህዝብን ሲጨርሱ እንደነበሩት እንደ ወባ እና የሳንባ ነቀርሳ በሽታዎች ሁሉ የእድሜ ልክ ፕሬዚዳንትነት እና የወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት በሽታዎች ናቸው፡፡

አሁን ደግሞ በጋና ላይ ያደረብኝ የሁለተኛው ቅናቴ ምክንያት እንዲህ ይገለጻል፡፡

እ.ኤ.አ በ1979 በስም ጀሪ ጆን ራውሊንግስ በመባል የሚታወቅ ወጣት የጋና አየር ኃይል ባልደረባ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣንን በመቆጣጠር ፕሬዚዳንት ሆነ፡፡

ራውሊንግስ መፈንቅለ መንግስቱን ካካሄደ በኋላ በሙስና ተዘፍቀው በነበሩት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ላይ ቤትን የማጽዳት እርምጃ ወሰደ፡፡

እ.ኤ.አ በ1981 በሌላ በተደረገ መፈንቅለ መንግስት ራውሊንግስ ስልጣኑን ለሲቪል መንግስት በማስረከብ እርሱ የጊዚያዊ የብሄራዊ መከላከያ ምክር ቤት ሊቀመንበር/Provisional National Defense Council (PNDF) ሆነ፡፡

ራውሊንግስ እ.ኤ.አ በ1981 ስልጣንን ሲቆጣጠር ወታደራዊ አምባገነን ሆነ፡፡

ሕገ መንግስቱን አፈረሰው፣ ፓርላማውን በመበተን ተቃናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከሕግ ውጭ በማድረግ እንዳይሳተፉ አደረገ፡፡

ራውሊንግስ ጋናን እና የጋናን ሕዝብ ለመካስ ሲል አብዮት በማካሄድ ተግባራት ላይ ተጠምዶ እንደሚገኝ አወጀ፡፡

እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ የጋና የምጣኔ ሀብት ዕዳ ተቆልሎበት፣ በውጭ ምንዛሬ ክምችት እጥረት ተቀስፍፎ በመያዝ፣ የሀገር ውስጥ ገንዘብ በከፍተኛ ደረጃ የምንዛሬ ዋጋው ዝቅ እንዲል/devaluation የተደረገበት እና የፍጆታ ዕቃዎች እጥረት የሚታይበት በመሆን በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቆ ይገኝ ነበር፡፡

የራውሊንግስ መንግስት እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ቀጣይነት ባለው ተጽዕኖ ስር ወደቀ፡፡

እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ መጀመሪያዎቹ አካባቢ የራውሊንግስ መንግስት እና የጋና የምጣኔ ሀብት በመንከታኮት ደረጃ በቋፍ ላይ ሆነው ተገኙ፡፡

ራውሊንግስ የፕሬስ ነጻነትን፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተሳትፎ ዘጋ፣ እንዲሁም በመንግስቱ ላይ ትችት የሚያቀርቡትን አገደ፡፡

ኃይለኞቹ የኒዮሊበራል አቀንቃኞች ማለትም የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት፣ የዓለም ባንክ፣ እና ሌሎች ለጋሽ ሀገሮች ጋናን እንደተራበ እና ጥንብ እንዳዬ ጆቢራ ከበቧት፡፡

እነዚህ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ የኒዮሊበራል አቀንቃኞች ለራውሊንግስ የተሀድሶ ማገገሚያ/bail out ድጋፍ እንደሚያደርጉለት ሆኖም ግን የመዋቅራዊ ማስተካከያ እና የዴሞክራሲን እና ነጻ ኢኮኖሚን ወርቃማ ክኒኖች መዋጥ እንዳለበት በአጽንኦ ነገሩት፡፡

በጋና የሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች የማሻሻያ ፕሮግራሙን በመቀበል የዴሞክራሲ ካባን እዲደርቡ ተደረጉ፡፡

ራውሊንግስ በተለይ ለብዙሀን ፓርቲ ዴሞክራሲ መጠናከር ደንታው አልነበረም፣ ሆኖም ግን የጋና ሕዝብ ለዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ዝግጁ ነው የሚል ሀሳብን ያራምድ ነበር፡፡

ራውሊንግስ የለየለት አምባገነን ሆኖም ግን ብልጥ የሆነ አምባገነን ነበር፡፡

ራውሊንግስ እና የእርሱ PNDC ለአፍሪካ ሊታሰብ እና ሊታለም የማይችል ድርጊትን ፈጸሙ፡፡

ራውሊንግስ እና PNDC እስከ አሁን ድረስ ሲያራምዱት የቆዩትን አምባገነናዊ አገዛዝ ዘመናዊነትን በተላበሰ እና ስርዓት ባለው መልኩ እርግፍ አድርገው ለመተው ወሰኑ!

ራውሊንግስ ታሪክ ሰራ፡፡

ወታደራዊ መለዮውን በሲቪል ማህበረሰብ ልብስነት ቀየረ፡፡

የአፍሪካ አምባገነኖች ሰላማዊ በሆነ መልኩ ስልጣናቸውን ለህዝብ ሊያስረክቡ ይችላሉን? በቀላሉ አነጋገር በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ከራውሊንግስ በፊት ወይም ደግሞ በኋላ ከራውሊንግስ ልዩ የሆነ እና አስደናቂ የሆነ ነገር ውጭ ስልጣንን ለህዝብ ጥቅም ሲል ያስረከበ አምባገነን ታይቶ ይቅርና ተሰምቶ አይታወቅም፡፡

ራውሊንግስ በጋና የብዙሀን ፓርቲ ዴሞክራሲን እና የሕገ መንግስታዊ ሕግን የበላይነት ለማምጣት እና የእርሱን አምባገነናዊ ስርዓት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ሲል የወሰዳቸው እርምጃዎች ልዩ እና ሁለንተናዊ የሆኑ ስርነቀል ክንዋኔዎች ነበሩ፡፡

ራውሊንግስ እና PNDC ጋናን ከአምባገነናዊ ስርዓት ወደ ዴሞክራሲዊ ስርዓት በማሸጋገሩ ረገድ ፈጣን የሆኑ እርምጃዎችን ወስደዋል፡፡

ስለወደፊቱ የሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሊመክሩ እና ሊዘክሩ የሚችሉ የእነርሱ ሀሳብ አራማጅ የሆኑ ዜጎችን ከያሉበት ፈልገው በመምረጥ ሀገር አቀፍ አደራጅ ኮሚሽን አቋቋሙ፡፡

እ.ኤ.አ ግንቦት 1991 ረቂቅ ሕገ መንግስት ለማዘጋጀት የሕገ መንግስት ሀሳቦችን ማመንጨት የሚችሉ ባለሙያዎችን በማፈላለግ የሕገ መንግስት አርቃቂ ኮሚቴ አቋቋሙ፡፡

እ.ኤ.አ ነሐሴ 1991 ሕገ መንግስቱን ለማርቀቅ የሚያስችል 260 አባላትን ያካተተ የአማካሪዎች ጉባኤ መሰረቱ፡፡

እ.ኤ.አ መጋቢት 1992 አማካሪ ጉባኤው የተሰጠውን የማርቀቅ ስራ አጠናቅቆ በማስረከብ የሽግግር የምርጫ ኮሚሽን ተቋቋመ፡፡

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 1992 በቀረበው ረቂቅ ሕገ መንግስት ላይ ድምጽ ለመስጠት የሚችሉ ዜጎች ተሳትፈውበት ድምጽ እንዲሰጥበት ተደርጎ 93 በመቶ ድምጽ በማግኘት እንዲጸድቅ ተደረገ፡፡

እ.ኤ.አ ግንቦት 1992 ራውሊንግስ በተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ጥሎት የቆየውን ገደብ በማንሳት የፖለቲካ ፓርቲ በመመስረት መሳተፍ የሚያስችል ሕግ አወጣ፡፡

እ.ኤ.አ በ1992 መጨረሻ አካባቢ የፕሬዚዳንታዊ እና ፓርላማ ምርጫ እንዲካሄድ የምርጫ ዕቅድ ይፋ ተደረገ፡፡

ራውሊንግስ እራሱን ከጦር ኃይሎች በማግለል የብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ኮንግረስ/National Democratic Congress ፓርቲን መሰረተ፡፡

እ.ኤ.አ ሕዳር 3/1992 በተደረገው የመጀመሪያ ሀገር አቀፍ ምርጫ ራውሊንግስ አሸንፎ የአራተኛዋ ሬፐብሊክ የመጀመሪያው የሲቪል ፕሬዚዳንት ለመሆን በቃ፡፡

ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ራውሊንግስ የምርጫ ካርዶችን በማጭበርበር ነው ያሸነፈው በማለት ቅሬታቸውን እና ስሞታቸውን ማሰማት ጀመሩ፡፡

የአውሮፓ የጋራ ገበያ/Commonwealth የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን በዚያን ጊዜ የተካሄደውን ምርጫ በማስመልከት እንዲህ የሚል ማጠቃለያ ስጥቶ ነበር፣ “ምርጫው ነጻ እና ፍትሐዊ እንዲሁም ከፍርሀት የጸዳ ነበር፡፡“

ሆኖም ግን ራውሊንግስ በምርጫው አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት የሚያስችሉትን የወታደሩን መዋቅር እና የድርጅቶችን ድጋፍ ያገኘ ለመሆኑ በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረብ የሚያስችሉ ሁኔታዎቸ ነበሩ፡፡

ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደህና መሰረትን በያዘ መልኩ የተደራጁ አይደሉም፣ እንደዚሁም ደግሞ አስተማማኝ የሆነ የገንዘብ ድጋፍ ስለማያገኙ የራውሊንግስን ፓርቲ ለመገዳደር በሚያስችላቸው ቁመና ላይ አልተገኙም፡፡

ራውሊንግስ እንደገና እ.ኤ.አ በ1996 በተደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ ለ4 ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ተመረጠ፡፡

ራውሊንግስ እ.ኤ.አ በ2000 የፕሬዚዳንትነት ጊዜው በሕግ ተፈፀመ፡፡

የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች ባለፉት ጥቂት ወራት ሲያደርጉት ከነበረው በተጻረረ መልኩ በሚያስደንቅ ሁኔታ ራውሊንግስ እንደገና ለሶስተኛ ጊዜ ለመመረጥ እንዲችል ያበቃው የነበረውን ሕገ መንግስት ለመለወጥ ያደረገው ምንም ዓይነት ሙከራ ያለመኖሩ ጉዳይ ነው፡፡

የሕዝቡን ውሳኔ በጸጋ በመቀበል በሰላማዊ መንገድ ስልጣኑን በማስረከብ ተሰናብቷል፡፡

እ.ኤ.አ በ2000 በተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ከአዲሱ አርበኞች ፓርቲ/New Patriotic Party ጆን ኩፎር አሸናፊ ሆነዋል፡፡

ጋና እ.ኤ.አ በ2016 ሌላ ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ ዕቅድ ይዛ ትንቀሳቀሳለች፡፡

ራውሊንግስ እና PNDC ጋናን በሰላማዊ መንገድ ከወታደራዊ አምባነንነት ስርዓት ወደ ብዙሀን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት የተደረገውን ሽግግር በጥሩ ሁኔታ መርተዋል፡፡ ይህ ክስተት በአፍሪካ አህጉር ታሪክ ውስጥ እጅግ በጣም ጠቃሚ እና ሌሎችም ተመሳሳይ ተግባር ለማከናወን እንዲችሉ እና ኃይል እንዲሰንቁ ያደረገ በአርዓያነት የሚታይ መልካም ሁኔታ ነው፡፡

ራውሊንግስ በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በርካታ የሆኑ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣዎችን ከሕግ አግባብ ውጭ የዘፈቀደ ግድያዎችን መፈጸምን ጨምሮ የሰብአዊ መብቶችን ሲጥስ ቆይቷል፡፡

ባለፈው ዓመት ራውሊንግስ እ.ኤ.አ በ1979 ቤቱን ለማጽዳት በማሰብ እርምጅ የወሰደባቸው ጥቂት ወታደራዊ መኮንኖች ምንም ዓይነት ወንጀል ያልፈጸሙ ነጻ ሆነው ተገኝተዋል፣ሆኖም ግን በወቅቱ በሀገሪቱ በነበረው ቁጣ እና ምስቅልቅል ሁኔታ ምክንያት ድርጊቱ ተፈጽሟል፡፡

በራውሊንግስ የአገዛዝ ዘመን ከሕግ አግባብ ውጭ የዘፈቀደ እስራቶች፣ ንብረት መውረስ፣ ሰላማዊ ዜጎችን አፍኖ መሰወር፣ መግደል እና የማሰቃየት ድርጊቶቸ ይፈጸሙ ነበር፡፡

ጀሪ ራውሊንግስ በእርሱ የአመራር ዘመን ጊዜ በርካታ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች እና ሌሎች ህጸጾችም ቢኖሩበትም ቅሉ ልዩ የሆነ እና ፍቅርን የተላበሰ (በአሁኑ ጊዚ በአፍሪካ በስልጣን ላይ ተኮፍሰው እንደሚገኙት መጥፎ ባህሪ እንዳላቸው መሪ ተብዬዎች ሳይሆን) አፍሪካዊ መሪ ነው፡፡

ሌሎች የአፍሪካ መሪዎች ከስልጣናቸው ሲወገዱ ሀገራቸውን ትተው በስደት በሌሎች ሀገሮች ሄደው በግዞት እንደሚኖሩት አምባገነን መሪዎች ሳይሆን ራውሊንግስ አሁንም ቢሆን በሀገሩ በጋና በሰላም በመኖር ላይ ይገኛል፡፡

እ.ኤ.አ ግንቦት 2005 በሚሊኒየሙ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የፖለቲካ በረሃ ምህዳር የፍጹማዊ ንጉሳዊ አገዛዝ፣ ወታደራዊ አምባገነንነት እና በወሮበላ ዘራፊነት የስርዓት ጠባሳ ላይ ላይ የዴሞክራሲ ዘር በቅሏል፡፡

እ.ኤ.አ በ2005 በኢትዮጵያ የተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ እስከ አሁንም ድረስ ያልሞተ እና በህይወት ላለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጽኑ ፍላጎት እና የተግባራዊ እንቅስቃሴ የትግል መንፈስ አለ፡፡

በዚያ ምርጫ ጊዜ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ገና የድምጹ መስጫ ካርዱ ቆጠራ ተጠናቅቆ ሳይቆጠር አሸንፊያለሁ ብሎ አወጀ፡፡ ከዚያም በመቀጠል አሁን በህይወት የሌለው አረመኔው እና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ፡፡

ከምርጫዎች ማግስት ጀምሮ መለስ እና የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ሀገሪቱን ኢትዮጵያውያንን የመግደያ የጦር ሜዳ አደረጓት፡፡

ያንን እልቂት፣ ግፍ እና ሸፍጥ የተፈጸመበትን የይስሙላ ምርጫ መጠናቀቅ ተከትሎ መንግስት ይፋ ባደረገው መሰረት የአፋኙ ስርዓት ፖሊስ እና ልዩ ታጣቂ ኃይሉ በሁለት ዙር ባካሄዱት ሰላማዊ ዜጎችን የመግደል ዘመቻ 193 ወንዶች፣ ሴቶች እና ህጻናት የግድያ ዕልቂቱ ሰለባ የተደረጉ ሲሆን 763 የሚሆኑት ሌሎች ሰላማዊ ዜጎች ደግሞ በጽኑ እንዲቆስሉ ተደርገዋል፡፡ (የድህረ ምርጫው ዕልቂት በትክክል ነጻ በሆነ አካል የሚቆጠር ቢሆን ኖሮ የዕልቂቱ ሰለባ ዜጎች ቁጥር መንግስት ካቀረበው ይፋ የሆነ ዘገባ ሊበልጥ ይችላል፡፡)

ሁሉም የተቃዋሚ የፖለቲካ አመራሮች በሚባል መልኩ እና የሲቪል ማህበረሰቡ ተወካዮች እና ጋዜጠኞች በአምባገነኑ መለስ እና በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ከ30,000 ከሚበልጡ ሌሎች ተራ ሰላማዊ ዜጎች እስረኞች ጋር በማጎሪያ እስር ቤቶቻቸው ታስረው እንዲማቅቁ አደረጉ፡፡

እ.ኤ.አ በ2008 በተደረገው የአካባቢያ እና የማሟያ ምርጫ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከ3.6 ሚሊዮን መቀመጫዎች ውስጥ 3 (ሶስት) መቀመጫዎችን ብቻ አሸነፉ!

እ.ኤ.አ በ2010 በተደረገው የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ 99.6 በመቶ የሆነውን የፓርላማ ወንበር አሸነፍኩ ብሎ አወጀ፡፡

በኢትዮጵያ እና በጋና ጠንካራ የሆነ የብሄር እና የጎሳ አለመቻቻል ኃይሎች ይታያሉ፡፡

ሁለቱም ሀገሮች በጎሳ ልዩነት እና በታሪክ ሽሚያ ውድድር ላይ የተመሰረተ የብዙሀን ብሄር ብሀረሰቦች እና ህዝቦች መኖሪያ ናቸው፡፡

አንዳንድ ጊዜ በጋና በማህበራዊ እና በኢኮኖሚያዊ ልዩነቶች በሚፈጠሩ ችግሮች ምክንያት የጎሳ ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ የሚደርስበት ሁኔታ አለ፡፡

ጥቂት የጋና ፖለቲከኞች ድምጽ ለመሰብሰብ ሲሉ የጎሳ ቅሬታን የሚጠቀሙ ቢሆንም ቅሉ በፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እና ደጋፊዎች አማካይነት ጎሳን መሰረት ያደረገ የኃይል እርምጃ የቅስቀሳ ትንኮሳ በጣም በጠበበ መልኩ ሊኖር ይችላል፡፡

በሚያስገርም ሁኔታ የጋናውን ሕገ መንግስት ጎሳን እና ብሄርን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ፓርቲን እንቅስቃሴ እንዲህ በማለት ይገድባል፡ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ህብረ ብሄራዊ ስብዕናን ሊላበስ የሚችል ባህሪ ሊኖረው ይገባል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ የፖለተካ ፓርቲ አባልነት ጎሳን፣ ኃይማኖትን፣ ክልላዊ ወይም ደግሞ ሌሎች ልዩነትን ሊያስከትሉ በሚችሉ ክፍፍሎች ላይ መሰረት አድርጎ ሊቋቋም አይችልም፡፡ (አንቀጽ 55 (4)፡፡)

በኢትዮጵያ ውስጥ የብሄር እና የጎሳ አፍቃሪነት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የስልጣን ህይወት ማራዘሚያ መሰረቶች ናቸው፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ሕገ መንግስት አንቀጽ 46 (2) የሚከተለውን መብት ያጎናጽፋል፡ “የክልል መንግስታት በአሰፋፈር ባህል ዘይቤ፣ በቋንቋ፣ በማንነት እና በሕዝቦች ስምምነት መሰረት ይዋቀራሉ፡፡“

በሌላ አገላለጽ “የክልል መንግስታት” በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ የጥቂት ነጮች የበላይነት የዘር አገዛዝ ባንቱስታንስ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ በእነዚህ በአራት መስፈርቶች መሰረት አንድ ዓይነት ጎሳ ያላቸውን መሰረት በማድረግ የአካባቢ መንግስታት ይዋቀራሉ፡፡

በኢትዮጵያ የጎሳ መሰብሰቢያ እና ማጎሪያ በረቶች “ክልሎች” በመባል በይፋ ይጠራሉ፡፡

ባለፉት ትችቶቼ ለህዝብ ግልጽ ሳደርግ እንደቆየሁት ሁሉ ክልሎች የሚለውን ስያሜ የበለጠ ግልጽ አድርጎ ለመጥራት እንደ አፓርታይዱ ባንቱስታንስ “ክልሊስታንስ” በሚለው ስያሜ ቢጠሩ ለይስሙላ ምንም ዓይነት እውነተኛው ስልጣን ሳይኖራቸው በአንድ አካባቢያዊ ስነምህዳር ተሰባስበው ለሚገኙ የብሄር እና የጎሳ ቡድኖች እንዲጠሩበት የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ፍጹም የሆነ እና ከእውነታ ጋር የማይገኛኝ እና በፖለቲካ ሳይንስ አድማስ ስር የማይካተት ወይም ደግሞ እነዚህን “ክልሊስታንስ” እየተባሉ የሚጠሩትን ስም ለማጉላት እና ለመካብ እንዲሁም እንደዚህ ዓይነቱን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲያቸውን በ80 ሚሊዮን ህዝብ ላይ ለመጫን ለሩብ ምዕት ዓመት ያህል የጎሳ ፌዴሪያሊዝም ህልዮትን በማራመድ ላይ ይገኛል፡፡

ጋና ከጎረቤት ሀገሮች ጋር መልካም የሆነ ግንኙነት አላት፣ እንደዚሁም ሁሉ በአህጉሪቱ ውስጥ መልካም ትብብር እንዲኖር፣ ሰላምን በማስጠበቅ እና ውጥረትን በማርገብ በኩል የእራሷን ሚና በመጫወት ላይ ትገኛለች፡፡

እንደ ትጉህ የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መንግስታት/Economic Community of West African States (ECOWAS) ተሳታፊ አባል ሀገር ጋና ወደ ውጭ የሚወጡ ምርቶቿን በማሳደግ እና እና የአካባበውን ገበያ በመጠቀም ቆይታለች፡፡

እንደዚሁም ሁሉ ጋና በላይቤሪያ እና በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ሲደረግ ለቆዬው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ  የእራሷን ድርሻ ስታበረክት ቆይታለች፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በአፍሪካ ቀንድ እ.አ.ኤ ከ1990ዎቹ ጀምራ በጎሳ የጦር አበጋዞች በመታመስ ላይ እና እየተሰቃየች ያለችውን ሶማሌ እ.ኤ.አ በ2007 በመውረር በቀንዱ ሀገራት ችግሮች ላይ ነዳጅ በማርከፍከፍ ላይ ይገኛል፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በሶማሌ ላይ እያካሄደ ያለውን ወረራ በሶማሌ የሽግግር መንግስት ጥሪ መሰረት እና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመከላከል ሲባል የተደረገ ነው በማለት ማሳመኛ በመደርደር ላይ ተጠምዶ ይገኛል፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አሸባሪ ቡድኖችን ከሶማሌ ጠራርጎ በማስወጣት በጥቂት ወራት ውስጥ ከሀገሪቱ ለቅቆ እንደሚወጣ በየጊዜው ጉራውን ይቸረችራል፡፡

ከሁለት ዓመታት ቆይታ አሰቃቂ ግድያ እና ዕልቂት በኋላ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ጭራውን እንዳበደ ውሻ በጉያው ውስጥ ወትፎ እግሬ አውጭ በማለት ወጥቷል፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እ.ኤ.አ በ2008 “በርካታ የሚያስፈሩ ነገሮች፡ የጦር ወንጀለኝነት እና የሶማሌ ውድመት“ በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት የጦር ወንጀሎችን፣ የተገደሉ የሲቪል ህዝቦችን እና በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ወራሪነት የደረሰውን ጉዳት እንዲህ በማለት ይፋ አድርጓል፡ “እ.ኤ.አ ከ2007 ጀምሮ በመቋዲሾ ከተማ በደረሰው ቀውስ ምክንያት የከተማው ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት ቢያንስ 870,000 የሚሆኑ ሲቪል ሰዎች ከተማውን ትተው ተሰደዋል፡፡ በደቡባዊ-ማዕከለዊ ሶማሌ 1.1 ሚሊዮን ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል፡፡“

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የአህጉሩ አስፈሪ ጠንቅ ኃይል ሆኗል፡፡

ሶስተኛው እና በጋናውያን ላይ  የምቀናበት ምክንያት ሕገ መንግስታቸው ነው፡፡ የጋና ሕገ መንግስት የጋና ሬፐብሊክ የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ ነው፡፡ በጋና የሕግ የበላይነት ሰፈፍኗል፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አመራሮች ሙሉ በሙሉ ግራ ተጋብተዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ የሕግ የበላይነት? ምን ይመስላል?

ጋናውያን ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ነጻነት ደረጃ ያላቸው ህዝቦች ለመሆናቸው የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም፣ እናም የሕግ የበላይነት በጋና መሪዎች ዘንድ በሚገባ ይከበራል፡፡

እ.ኤ.አ በ1992 የጋናውያን ሕገ መንግስት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የባህል መብት መድብሎችን ለዜጎች አጎናጽፏል፡፡

በጋና የፕሬስ ነጻነት ጋናውያን ነጻነቶቻቸውን የሚያጣጥሙበት የተሻለ መገለጫ ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ2015 በዓለም የፕሬስ ነጻነት መለኪያ መስፈርት መሰረት ጋና ከ173 ሀገሮች መካከል  የ22ኛ ደረጃን ይዛለች (ኢትዮጵያ ከ180 ሀገሮች በ142ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡)

በጋና ከ150 በላይ የግል ጋዜጦች እና ሁለት ዕለታዊ የመንግስት ጋዜጦች ይገኛሉ፡፡

በመላ ሀገሪቱ ወደ 110 የሚሆኑ የኤፍ ኤም የሬዲዮ ማሰራጫ ጣቢያዎች አሉ፡፡ የውጭ የመገናኛ ዘዴዎች በነጻ ይሰራሉ፡፡ የኢንተርኔት አገልግሎት በመንግስት ቁጥጥር አይደረግበትም፡፡ ዜጎች የመንግስትን በቀል ሳይፈሩ ሀሳቦቻቸውን ነጻ በሆነ መልኩ ይገልጻሉ፡፡ እንደዚሁም የመገናኛ ብዙሀን ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ የመንግስትን ፖሊሲዎች እና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣኖችን ያለምንም ቁጥጥር እና ምርመራ መተቸት ይችላሉ፡፡

የጋና መንግስት ሕገ መንግስቱን ይከተላል በጽናትም ያከብራል፡፡ መንግስት በፍርድ ቤቶች እና በሌሎች እውነት አፈላላጊ ኮሚሽኖች ሕጎች እና ውሳኔዎች ይገዛል፡፡

የጋና መንግስት የሚያወጣቸው ሕጎች ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና ስምምነቶች መለኪያ መስፈርቶች አንጻር የተቃኙ መሆናቸውን ለማረጋገጥ አስፈላጊዎቹን እርምጃዎች ይወስዳል፡፡

የጋና ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕግ የበላይነትን እንዲጠበቅ የሚያገለግል የመጨረሻ ተቋም ነው፡፡ የእራሱን ተቋማዊ ነጻነት የሚያስጠብቅ እና ሕገ መንግስታዊ ባልሆኑ የመንግስት ፖሊሲዎች እና ውሳኔዎች ላይ ቁጥጥሮችን በማጠናከር ላይ የተጠመደ ተቋም አይደለም፡፡ በሚያስደንቅ ሁኔታ በጋና ሕገ መንግስት በአንቀጽ 2 (4) ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዞች ተገዥ በማይሆኑት ዜጎች ላይ ታላቅ ወንጀል በመሆኑ በዚህ ሕገ መንግስት መሰረት ፕሬዚዳንቱን ወይም ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንቱን ከስራ ገበታቸው እስከማባረር ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡

በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 2 (1) የሚከተለውን መብት አጎናጽፈዋል፣ “ሕገ መንግስታዊ ባልሆነ መልኩ ወይም ደግሞ በሌላ በማንኛውም ሰው የሚፈጸም የውንጀላ ተግባር ሲኖር ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የማገጃ አቤቱታ በማቅረብ ጉዳዩን ማሳገድ ይቻላል፡፡ በሚያስገርም ሁኔታ በአንቀጽ 64 ማንኛውም የጋናዊ ዜግነት ያለው ሰው የጠቅላ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ምርጫ በተጠናቀቀ በ21 ቀናት ውስጥ ምርጫው በትክክለኛ መንገድ ስለመከናወኑ የመጠየቅ መብት አለው፡፡“

ነጻ የሆነ የፍትህ አካል የሕግ የበላይነት መከበሩን እና የሲቪል ነጻነቶች መጠበቃቸውን በመከታተሉ ረገድ ከፍተኛ የሆነ ጠቃሚነት አለው፡፡

አንቀጽ 125 ለጋናውያን የሚከተለውን ነጻነት ያጎናጽፋል፣ “የፍትህ አካሉ ነጻ እና ለሕገ መንግስቱ ብቻ ተጠያቂ መሆን አለባቸው፡፡“ ከዚህም በተጨማሪ አንቀጽ 127 (2) የሚከተለውን መብት ያጎናጽፋል፣ “ፕሬዚዳንቱም ሆነ ፓርላማው ወይም ደግሞ ማንኛውም ዜጋ ቢሆን ዳኞች የፍርድ ቤት ስራዎቻቸውን በሚያከናውኑት ሰዎች ላይ ምንም ዓይነት ጣልቃገብነት ማድረግ አይችልም፡፡“ ሁሉም የመንግስት አካላት ለፍርድ ቤቶች ትዕዛዝ ተገዥ መሆን አለባቸው፡፡ የጋና ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕግ ስርዓቱን እንደገና የማየት እና የመፈተሸ መብት አለው፡፡

ጋና በውድድር ላይ የተመሰረተ የብዙሀን የፖለቲካ ፓርቲ ስርዓት አላት፡፡ የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 55 የሚከተለውን መብት ያጎናጽፋል፣ “ማንኛውም ዕድሜው ለምርጫ የደረሰ የጋና ዜጋ የፈለገውን የፖለቲካ ፓርቲ የመቀላቀል መብት አለው፡፡“ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለማደራጀት እና ሀገር አቀፍ ባህሪ ያላቸውን የፖለቲካ ሀሳብ፣ የማህበራዊ እና የኢኮኖሚ ፕሮግራም  መረጃዎችን ለማሰራጨት  ነጻ ናቸው፡፡

በሀገሪቱ ውስጥ ስምንት የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ሆኖም ግን ሁለቱ ታላላቅ ፓርቲዎች ማለትም አዲሱ የአርበኞች ፓርቲ/New Patriotic Party (NPP) እና ብሄራዊ ዴሞክራቲች ኮንግረስ/National Democratic Congress (NDC) የጋናን 80 በመቶ የሆኑትን ድምጽ ሰጭዎች ይሸፍናሉ፡፡

የጋና የምርጫ ከሚሽን የጋና ሕዝቦች እራሳቸውን በእራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ እና ምርጫዎችም ምንም ዓይነት ችግር ሳይኖርባቸው ንጹህ ሆነው እንዲጠናቀቁ በማሰብ በሕገ መንግስቱ ተካትቶ የተቋቋመ ነጻ ተቋም ነው፡፡ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 46 ኮሚሽኑ የሚከተለውን የነጻነት መብት ተጎናጽፏል፡ “ከጥቂቶች ልዩ የሆኑ ጉዳዮች በስተቀር ኮሚሽኑ በማንኛውም ሰው ጉዳይ ላይ ወይም ባለስልጣን ጣልቃ ሊገባ አይችልም…“

እ.ኤ.አ በ2008 የተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በምርጫ ኮሚሽኑ አማካይነት የተከናወነ ሲሆን ኮሚሽኑ ዴሞክራሲን በዘለቄታዊ መላኩ ለማጠናከር፣ የፖለቲካ ብዝሀነትን ለማስፋት እና ሕገ መንግስቱን ለመጠበቅ በሚያሳያቸው እንቅስቃሴዎች በጋና እና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ የተማዕኒነት ስሜትን ተጎናጽፏል፡፡

በጋና የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ቀስ በቀስ ጠቃሚ የህብረተሰቡ ማህበራዊ ኃይሎች በመሆን እየተጠናከሩ መጥተዋል፡፡ ማህበሮች፣ ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅቶች፣ የሙያ የህዝብ መገናኛ ዘዴዎች፣ የሕግ፣ የትምህርት እና የምርምር ድርጅቶች እንዲሁም የእምነት ተቋማት አገልግሎት ቡድኖች እና ማህበራት በነጻ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት በሕግ እና በሕግ ማሻሻያ ስራዎች ላይ ለተወከሉባቸው አካላት ጠንካራ የሆነ የውትወታ ተግባራትን በማከናወን  እየተጠናከሩ በመምጣት ላይ ሲሆኑ በአሁኑ ጊዜ መተኪያ የሌለውን ሚና ይጫወታሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ2015 ሂዩማን ራይትስ ዎች እንዲህ የሚል ዘገባ አቅርቧል፣ “የኢትዮጵያ መንግስት በነጻ የህዝብ መገናኛ ዘዴዎች ላይ እያካሄደ ያለው ስልታዊ ጭቆና ሀሳብን በነጻ በመግለጽ ከባቢ አየር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖውን አሳርፏል… ባለፈው ዓመት ስድስት በግል የተያዙ የሕትመት ውጤቶች መንግስት ማስፈራሪያ ከሰጠ በኋላ እንዲዘጉ ተደርገዋል፣ ቢያንስ 22 ጋዜጠኞች፣ ጦማሪዎች እና አታሚዎች በወንጀል እንዲከሰሱ ተደርገዋል፣ እናም ከ30 በላይ የሚሆኑ ጋዜጠኞች ባለው ጨቋኝ አገዛዝ ሕግ እና በቁጥጥር ስር መዋልን በመፍራት ሀገር ለቀው ተሰድደዋል፡፡“

እንደዚሁም እ.ኤ.አ በ2015 ሂዩማን ራይትስ ዎች እንዲህ የሚል ዘገባ አወጣ፣ “የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኖችን፣ ጦማሪያንን፣ ተቃዋሚዎችን እና የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊዎችን ጸጥ ለማድረግ ከሕግ አግባብ ውጭ እስራቶችን ይፈጽማል፣ እንዲሁም በፍርድ ቤት ክስ በመመስረት እንዲጉላሉ ያደርጋል፡፡ ፖሊስ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን በሚያሰሙ ዜጎች ላይ ከመጠን ያለፈ ኃይልን በጠቀም በቁጥጥር ስር ያውላል፣ እንደዚሁም ደግሞ የዓለም አቀፉን የሕግ ማዕቀፍ የማያሟሉ እና ለዓለም አቀፉ ሕግ የማይገዙትን እና ጨቋኝ የሆኑ ሕጎችን ለማሻሻል ምንም ዓይነት የመንግስት ፈቃደኝነት አይታይም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት የሚያወጣቸውን የሕግ መስፈርቶችን የሚጥሱትን ኢትዮጵያን ጨምሮ በየጊዜው በማውገዝ ላይ ይገኛል፡፡“

እ.ኤ.አ በ2014 እንዲህ የሚል ዘገባ አውትቶ ነበር፣ “እ.ኤ.አ ከ2009 ጀምሮ የጸረ ሽብር እና የማህበራት እና በጎ አድራጎት ድርጅቶች አዋጅ ሕግ ሆነ ከወጣ በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ እና የመደራጀት መብቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ ክልከላ ተጥሎባቸዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰቡ ሕግ በዓለም ላይ የሚደረጉትን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ ለመገደብ የሚወጣ ጨቋኝ ሕግ ነው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ይህ ሕግ ከ10 በመቶ በላይ የሚሆነውን የገንዘብ ምንጫቸውን ከውጭ በሚያገኙ ድርጅቶች እና በሰብአዊ መብቶች፣ በመልካም አስተዳደር፣ በግጭት አፈታት እና በውትወታ ስራዎች ላይ እንዲሁም በሴቶች መብቶች፣ በልጆች እና በአካል ጉዳተኞች ስራዎች እንቅስቃሴ በሚያደርጉት ድርጅቶች ላይ ክልከላ ያደርጋል፡፡“

የጋና ሕዝቦች ዴሞክራሲ ለአፍሪካ ሕዝቦች ከምዕራቡ ዓለም እየተቆነጠረ የሚሰጥ የቅንጦት ዕቃ ሳይሆን አፍረካውያን በእራሳቸው ለእራሳቸው ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እያገናዘቡ የሚተገብሩት ውጤታማ የአስተዳደር ስርዓት መሆኑን በግልጽ አመላክተዋል፡፡

የጋና ሕዝቦች በብሄር እና በጎሳ ላይ መሰረት አድርጎ ያልተመሰረተ የብዙሀን ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ማራመድ በአፍሪካ አለመረጋጋትን ለማስወገድ፣ ፍትሀዊነትን እና የምጣኔ ሀብት እድገትን ማስመዘገብ እንደሚያስችል ምሳሌ ሆነው አሳይተዋል፡፡

እንግዲህ ለጋና ህዝብ ስኬት ዋና መሰረቱ ይኸው ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብሄርን እና ጎሳን መሰረት ባደረገ መልኩ እንዳይቋቋሙ በሕገ መንግስት በመገደብ ጋናውያን የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባት ጠንካራ የሆነችውን ጋናን ለመመስረት ችለዋል፡፡ የብሄር እና የጎሳ ምስቅልቅላዊ ችግሮችን የሚያስወግድ የብዙሀን ፓርቲ ዴሞክራሲን ማጠናከር ችለዋል፡፡

በሚያስገርም ሁኔታ ጋናውያን የሀገራቸውን አንድነት በማስጠበቅ እና የእራሳቸውን የሰብአዊነት ማዕቀፍ ከግምት ውስጥ በማስገባት አንዲሲቷን ጋና በመመስረት ፍቅርን እንደ ሸማ የተላበሰች ሀገር ባህልን ለመመስረት ችለዋል፡፡

አሁን በጋናውያን ላይ ለምን እንደምቀና ግልጽ የሆነላችሁ ይመስለኛል!

“የአሜሪካ ሕገ መንግስት አርቃቂ ቀደምት አባት” የሆኑት ጀምስ ማዲሰን በ51 ፌዴራል መንግስታት ላይ እንዲህ የሚል ምልከታቸውን አድርገው ነበር፣ “ሰዎች መላዕክት ቢሆኑ ኖሮ የመንግስት መኖር አስፈላጊ አይሆንም ነበር፡፡“

ማዲሰን በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ያሉ ቢሆን ኖሮ እንዲህ በማለት እጠይቃቸው ነበር፡ “ በመንግስት ስልጣን ላይ ያሉት በሰው አምሳል የተፈጠሩ የሚመስሉ ሰይጣኖች ሲሆኑ ምን ማድረግ ይቻላል?“

ማዲሰን እንዲህ በማለት ምላሽ ይሰጡ ይሆን ነበር፣ “በእርግጥ አዎ ሰው መሳይ ሰይጣኖች ናቸው፣ ታዲያማ ሰው መሳይ ሰይጣኖችንማ ደልቆ ማስወጣት ነው።

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

መስከረም 24 ቀን 2008 .

 

 

 

Similar Posts