ረሃብ በኢትዮጵያ በባቡር ይጋልባል፣

Famine4ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም    

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

የኢትዮጵያ ዓመታዊ የረሃብ አዝመራ፣

ባለጥቁሩ ፈረስ የረሃብ የምጽዓት ቀን አስፈሪውን ፊቱን በኢትዮጵያ እንደገና ማሳየት ጀመረ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በባቡር ተቀምጦ በመጋለብ ላይ ይገኛል፡፡

እ.ኤ.አ የካቲት 2014 በዚሁ ወር ኤንቢሲ/NBC የተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ያወጣውን የምርመራ ዘገባ መሰረት በማድረግ “እየተንፏቀቀ የመጣው ረሃብ በኢትዮጵያ “ በሚል ርዕስ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ኤንቢሲ/NBC እንዲህ የሚል ዘገባ አቅርቦ ነበር፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የዓለም የምግብ ቀውስ መግለጫ ሆናለች፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ በአንድ መንደር ውስጥ እናቶች በተመጣጣኝ የምግብ እጥረት ከተጎዱ ህጻናት ልጆቻቸው ጋር ለአስቸኳይ የምግብ ምፅዋት (ራሽን) ተደርድረው ታይተዋል፡፡ እነዚህ የረሃብ ሰለባ የሆኑ ወላጆች ህጻናት ልጆቻቸውን ለመመገብ የሚያስችል አቅም የላቸውም፡፡ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ የውጩ ዓለም የእርዳታ እጁን ለመዘርጋት የሚችል አይመስልም፡፡ የረኃብ ምልክት የሆነው የህጻናት ሆድ መነፋት ከሁለት ተከታታይ ደካማ የምርት ዓመታት በኋላ የተከሰተ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በየዕለቱ ተጨማሪ ሰዎች የረኃብ ሰለባዎች እየሆኑ ነው… [የገዥው አካል ተወካይ የሆኑት አቶ ዑመር አብዲ] ጉዳዩን አስመልክቶ እንዲህ በማለት ሀሳባቸውን ገልጸዋል፣ “ለእነርሱ ሁለት የማያሻሙ አማራጮች አሉኝ፣ መሞት ወይም መሬቱን መጫር፡፡” ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ በዚህች አገር ላይ ከውጭ የሚደረገው እርዳታ ሚሊዮኖች በህይወት እንዲቆዩ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ባልተመጣጠነ ምግብ ምክንያት ለአደጋ የተጋለጡ ዜጎች ብዛት እድገት በማሳየት ላይ ይገኛል፣ እናም ይህንን ክስተት ለመግታት የሚደረግ ምንም ዓይነት የጥረት ምልክት አይታይም፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ የምግብ ቀውስ በምዕራቡ ዓለም ለምግብ መሸመቻ ገንዘብ ችግር ቢፈጥርም ግን እዚህ [ኢትዮጵያ ውስጥ] ያሉት ህዝቦች በጣም ከፍተኛ የሆነ ዋጋ እንዲከፍሉ ያደርጋል፡፡

እ.ኤ.አ ነሐሴ 2015 የተባበሩት መንግስታት እንዲህ የሚል ለምግብ እርዳታ የአስቸኳይ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ዘገባ አውጥቷል፡

በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና እጦት መጠኑ እየሰፋ እና እየተስፋፋ መጥቷል፣ እንደዚሁም ከፍተኛ የሆነ የተመጣጠነ የምግብ ንጥረ ነገር እጥረት መጠን ከዓለም አቀፉ መስፈርት መለኪያ በላይ በእጅጉ በመጨመሩ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ቀውስ ክስተትን ፈጥሯል፡፡ ሁለት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች (የበልግ እና የመኸር) የሰብል አዝመራ ምርት የሳተ በመሆኑ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በእርዳታ ላይ ጥገኛ የሆነው የምግብ ፈላጊው ህዝብ ቁጥር (ከዚህ ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ 2.9 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን) ከፍተኛ በሆነ መልኩ ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ (ኢሲኤችኦ/ECHO፣ እ.ኤ.አ ነሐሴ 13/2015) (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

በኢትዮጵያ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር የሆነው ሬድዋን ሁሴን የተባለው ቀልደኛ የሆነ ደንቆሮ በሀገሪቱ ውስጥ አስከፊ የሆነ የምግብ ቀውስ መኖሩን አምኖ ይፋ ያደረገ ሲሆን ይህም ሆኖ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ምንም ዓይነት የምግብ እርዳታ እንደማያስፈልግ ዓይኑን በጨው ታጥቦ የተራ ቅጥፈት እና ክህደት ቃሉን ሰጥቷል፡፡

ሬድዋን እንዲህ ብሏል፣ “እራሳችንን መመገብ እንችላለን፣ እናም በዝናቡ እጥረት ምክንያት ለችግሩ ሰለባ የሆኑትን አካባቢ ህዝቦች ጨምሮ የረሃቡ ስፋት እና መጠን በአብዛኛው ህዝብ ላይ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ አያመጣም፡፡“ ይህ ሰው ያለምንም ተጨባጭ መረጃ ይህንን የመሰለ  ነገር ሲናገር የረሃቡ ሰለባ የሆኑ ሰዎች መራባቸውን አያውቁትም ማለቱ ነውን? አሁን በህይወት የሌለው እና የሬድዋን ትንሹ አምላክ የነበረው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ስላለው ዓላማ ለቀረበለት ጥያቄ ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በፊት አዲስ አበባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “ኢትዮጵያውያን በቀን ሶስት ጊዜ መመገብ ከቻሉ የመንግስቴ ስኬት የሚለካው በዚህ ነው” ብሎ ነበር፡፡ (ከዚህ ጋ ጫን በማድረግ የቪዲዮ ምስሉን ይመልከቱ፡፡)

በአሁኑ ጊዜ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የዓለም አቀፉ የምግብ እጥረት መስፈርት እና መለኪያ ከሚያሳየው በላይ በመሄድ ለአስቸኳይ እና ለአስከፊ የምግብ እጥረት ቀውስ ተዳርገዋል፡፡

እ.ኤ.አ በጃንዋሪ 2010 የአምባገነኑ መለስ ዜናዊ መለስ የግብርና ሚኒስትር ተሿሚ የነበረው አቶ ምትኩ ካሳ እንዲህ በማለት አውጆ ነበር፣ “በኢትዮጵያ ሁኔታ ረሃብ የለም፣ ቸነፈር/ጠኔ የለም… [ረሃብ ወይም ቸነፈር አለ] የሚለው መሰረተቢስ ነው፣ ረሃብ አለ የሚለው አባባል በመሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ በተቃራኒው ነው፡፡ በመረጃ የተደገፈ አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ችግሮቹን ለማስወገድ መንግስት እርምጃ በመውሰድ ላይ ነው፡፡“ አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊም በተመሳሳይ መልኩ ስለረሃብ መኖር እንዲህ በማለት ሙልጭ አድርጎ ያፈጠጠውን እና ያገጠጠውን እውነታ ዓይኑን በጨው ታጥቦ በመካድ አስተባብሏል፣ “ረሃብ በኢትዮጵያ ለረዥም ጊዚ እልቂትን ሲያስከትል ቆይቷል፣ እንደዚህ ዓይነት አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ አስቀድሞ መገንዘብ አለመቻል ደደብነት ነው፣ ሆኖም ግን በእኛ እይታ ረሃብ የለም… የአስቸኳይ ጊዜ፣ እንጂ ረሃብ የለም፡፡“ ረሃብ በፍጹም የለም! የፖለቲካ እስረኞች የሉም! የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሉም! አምባገነናዊነት የለም! በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት ችግሮች የሉም! አዎ እውነት ነው እንደ እናንተ ዓይነት የክህደት እና የሸፍጥ አካሄድ ምንም ዓይነት ችግሮች የሉም፣ እኛ ግን ቅጥፈት ብቻ ነው ያለው እንላለን!

እ.ኤ.አ መስከረም በ2010 አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ እራሱን ከፍ ከፍ በማድረግ እንዲህ በማለት የግነት አዋጅ አውጆ ነበር፣ “ትርፍ ምርት ለማምረት የሚያስችሉ ዕቅዶችን ቀይሰናል፣ እናም በ2015 ያለምንም የውጭ እርዳታ ፍላጎት ህዝባችንን መመገብ እንችላለን“ ብሎ ነበር፡፡

ይቅርታ ጉዳዩን በተሻለ መልኩ የሚገልጽ ቃል ስላላገኘሁለት ነው፣ ሁሉም ቢሆኑ እውነታውን ሙልጭ አድርገው በመካድ ትንሽ ትንሽ ብቻ መዋሸት ሳይሆን እንደ አቡጀዲ ይቀደዳሉ፣ እንደማዳበሪያ መያዣ ከረጢት ይተረተራሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ2015 “በቀን ሶስት ጊዜ ምግብ መመገብ“ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን የማላይ ሆኗል፡፡ እንደዚሁም “ካለውጭ የምግብ  እርዳታ አቅርቦት“ አምባገነኑ መለስ “እንደቀየሰው” ኢትዮጵያ በ2015 እራሷን ትመግባለች ማለት ዘበት ነው፡፡ እንዲያውም ከዚህም አልፎ እ.ኤ.አ በ2030 እንኳ የህዝቧ ቁጥር ከ130 ሚሊዮን በላይ ከፍ እንደሚል በሚገመትበት ጊዜም ቢሆን ይህ መንግስት እና የተሳሳተ ፖሊሲው እስካልተቀየሩ ድረስ ሀገሪቱ በፍጹም እራሷን ልትመግብ አትችልም፡፡

በአሁኑ ጊዜ የይስሙላ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ በአሻንጉሊትነት እያገለገለ የሚገኘው ኃይለማርያም ደሳለኝ እ.ኤ.አ በ2011 የውጭ ጉዳይ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በነበረበት ጊዜ እርሱ የሚመራው መንግስት ረኃብን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መንግሎ ማስወገድ እንደሚችል እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ድህነትን ተረት እንደሚያደርግ በጣም እርግጠኛ በመሆን ተናግሮ ነበር፡፡

ኃይለማርያም ከአፍሪካ ኮንፊደንሻል ጋር በተደረገ ቃለመጠይቅ እንዲህ በማለት ድንፋታ አሰምቶ ነበር፣ “ላለፉት ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያ ባለሁለት አሀዝ የምጣኔ ሀብት እድገት አስመዝግባለች፣ ይህም የሚያመላክተን የምጣኔ ሀብት ፖሊሲያችን በጥሩ ሁኔታ እየሰራ ያለ መሆኑን ነው፡፡ ይህንን የምጣኔ ሀብት እድገት በዚሁ ፍጥነት የምናስቀጥል ከሆነ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የምጣኔ ሀብታችንን አሁን ካለበት በእጥፍ ማሳደግ እንችላለን፡፡ ይህም ማለት የማህበረሰባችንን ገቢ በእጥፍ እናሳድጋን፣ ይህንንም በማድረግ ድህነትን 50 በመቶ እንቀንሳለን፡፡” በማለት ጠብደል እና ዓይን ያወጣ ውሸት ዋሽቶ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ ለሚገኘው ረሃብ ዋና መንስዔዎች የመልካም አስተዳደር እጦት እንጂ ድርቅ አይደለም፡፡ የችግሩ መንስዔ አንኳር ችግር በየደረጃው የሚገኘው የመንግስት አካላት ብቃት የለሽነት እና ብልሹ አስተዳደር እንጅ አካባቢያዊ ነገሮች አይደሉም፡፡

በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው ረሃብ ሰው ሰራሽ ነው፡፡ ይህም ማለት ለረሃቡ መንስዔ ሙስና፣ ብልሹ አስተዳደር፣ የሙያ እና የአስተዳደር ብቃትየለሽነት እና በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ ላይ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ችግር ለማስወገድ የሚያስችል የፖለቲካ ፈቃደኝነት እና ፍላጎት የሌለው አምባገነን እና ጨካኝ የወሮበላ መንግስት በስልጣን እርካብ ላይ ተፈናጥጦ የመገኘቱ ሁኔታ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በስልጣን እርካብ ላይ ተንጠልጥለው የሚገኙት ቡድኖች ትክክለኛ ለሆነ ዕቅድ እና ለህዝቦች ደህንነት ጠቀሜታ ያላቸውን ፖሊሲዎች ለመንደፍ የማይችሉ ሀሳበ ግትር እና ለለውጥ በምንም ዓይነት መልኩ ዝግጁ ያልሆኑ የጫካ ወሮበላ የአስተሳሰብ አድማስን የተላበሱ ፍጡሮች ናቸው፡፡

የዓለም ባንክ ዋና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት ወልፍጋንግ ፌንግለር እ.ኤ.አ ነሐሴ 17/2011 ቀጥተኛ በሆነ መልኩ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ይህ በኢትዮጵያ ያለው የረሃብ/ቸነፈር ቀውስ ሰው ሰራሽ ነው፡፡ የድርቅ አደጋዎች ደግመው ደጋግመው በየጊዜው ይከሰታሉ፣ ሆኖም ግን እነዚህ ድርቆች ወደ ረሃብ እንዲያመሩ የሚያደርጋቸው ትልቁ ነገር መጥፎ ፖሊሲን የመንደፍ ሁኔታ ነው፡፡“

በእርግጥ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ህዝቦቻቻውን በተሻለ ሁኔታ ከማይመግቡ በዓለም ላይ ከሚገኙ 125 አገሮች በ123 ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ እንደ አዲሱ የኦክስፋም የምግብ መረጃ ቋት ከሆነ “በዓለም ላይ የተትረፈረፈ፣ የተመጣጠነ፣ ጤናማ እና ህዝቡ እንደልብ ሊገዛው የሚችል ምግብ በማግኘት ኔዘርላንድ በቁጥር አንድ ላይ የምትገኝ ስትሆን ቻድ በ125ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ የመጨረሻ በመሆን ኢትዮጵያን እና አንጎላን ታስከትላለች፡፡”

አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እየመነመነ ስለመጣው የዝናብ ስርጭት እና በኢትዮጵያ ስጋት ሆኖ በመቅረብ ላይ ስላለው ረኃብ ያሳሰበው መሆን አለመሆኑን በተጠየቀ ጊዜ ለሰጠው መልስ እንዲህ የሚል ቀልድ ወጥቶበታል፣ “ስለዝናብ ሁኔታ በኢትዮጵያ አንጨነቅም፣ እኛ የምንጨነቀው በአሜሪካ እና በካናዳ ስለሚኖረው ዝናብ ነው፡“ እኛ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በውጭ ሀገር ባሉ ባንኮች ስናጭቅ አሜሪካውያን እና ካናዳውያን የእኛን ረሃብተኛ ህዝብ ይመግባሉ፡፡

አሜሪካ የከባቢ አየር ለውጥ ክህደት ፈጻሚዎች አሏት፣ ኢትዮጵያ ደግሞ የረሃብ/ቸነፈር ክህደት ፈጻሚዎች አሏት፡፡ እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እያለ እንደሚጠራው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ  ረሃብ በኢትዮጵያ ማታለያ ነው!

እውነታዎች እንዲህ ይናገራሉ፡፡

እ.ኤ.አ የካቲት 2014 እንዲህ የሚል ዘገባ ቀርቦ ነበር፣ “2.7 ሚሊዮን የሆኑ ለረሃብ የተጋለጡ ዜጎችን ለመመገብ ኢትዮጵያ የውጭ እርዳታ ሰጭዎችን እገዛ ትፈልጋለች፡፡“ ይህ እ.ኤ.አ በ2014 መጀመሪያ አካባ ነበር የተደረገው፡፡

እ.ኤ.አ በ2013 ኢትዮጵያ ከ4 ሚሊዮን በላይ የሆኑ የረሃብ ሰለባ የሆኑ ዜጎቿን ለመመገብ ወደ 700 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ የሰብአዊ እርዳታ ተቀበለች፡፡

እ.ኤ.አ መስከረም 2012 “የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ሳምንት 3.7 ሚሊዮን የሚሆኑ የኢትዮጵያ ዜጎች በዚህ ዓመት ከነሐሴ እስከ ታህሳስ ላሉት ወራት እስከ ጥር ደግሞ 3.2 ሚሊዮን ለሚሆኑ ለረሃብ ለተጋለጡ ዜጎች እንደሚያስፈልግ ይፋ አደረገ፡፡“

እ.ኤ.አ በ2011 በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ የምግብ እርዳታ አብዛኛው ከዩናይትድ ስቴትስ የሆነ 500 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ተገኘ፡፡

እ.ኤ.አ ነሐሴ 2010 የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የግብርና ድርጅት ኢትዮጵያን በማስመልከት እንዲህ የሚል አገባ አቀረበ፣ “ወደ 5.2 ሚሊዮን የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን እስከ አሁን ድረስ ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ጥገኛ ሆነው የዘለቁ ሲሆን በረዥም የጊዜ ዕይታ ደግሞ ሀገሪቱ ወደ ከፋ የምግብ ቀውስ ሁኔታ ውስጥ ልትገባ እንደምትችል ድርጅቶቹ ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡“

እ.ኤ.አ ነሐሴ 2009 እንዲህ የሚል ዘገባ ቀርቦ ነበር፣ “በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ድሆች አስከፊ ለሆነ የምግብ ንጥረ ነገር ጉድለት በቀጣይነትም ወደ ረሃብ ቀውስነት ሊለወጥ ወደሚችል ችግር ተጋልጠዋል፣ እናም ለበርካታ አስርት ዓመታት በሀገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከዚህ የበጋ ወቅት ጀምሮ አስከፊ የምግብ ቀውስ ሊከሰት ይችላል፡፡ የምግብ እርዳታ ፈላጊው ቁጥር በዚህ ዓመት በጥር ወር ከ4.9 ሚሊዮን እስከ ግንቦት ድረስ 5.3 ሚሊዮን እንዲሁም እስከ ሰኔ ድረስ 6.2 ሚሊዮን የሚሆን ተረጅ ህዝብ ይኖራል ተብሎ ይገመታል፡፡“

ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በእያንዳንዱ ዓመት ለረሃብ ሰለባነት የተጋለጡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ለመመገብ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡

እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች በረሃብ ለተጎዳው በ10 ሚሊዮኖች ህዝብ የእርዳታ እጃቸውን ሳይዘረጉ የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ በማለት ጆሮ ዳባ ልበስ ባሉበት ወቅት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ምንም ዓይነት ኃላፊነትን ሳይቀበል በርካታ ህዝቦች በረሃብ እንዲያልቁ አድርጓል፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በኢትዮጵያ ለረሃቡ ያለው ኃላፊነት መለመን፣ አኩፋዳውን እየከፈተ ጨምሩልኝ እያለ መለመን እንጅ ሌላ ረሃብን ሊያስወግዱ የሚችሉ ፖሊሲዎችን በመንደፍ በስራ ላይ ማዋል አይደለም፡፡

በየዓመቱ የምግብ እርዳታ መለመን እና ምጽዋዕት መጠየቅ ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የክብር መገለጫ ባህል ሆኖ በመዝለቅ ላይ ይገኛል፡፡

ለማኝ መንግስት መሆን ምን ያህል አሳፋሪ ነገር ነው!!!

በአሁኑ ጊዜ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በኢትዮጵያ ስም በመለመን ላይ ይገኛል፡፡ ምን ዓይነት የወረደ ነገር ነው፣ ምን ዓይነት የሚያሳፍር እና የሚያበግን ነገር ነው!

ረሃብ በቀላል ባቡር በመጋለብ ላይ ይገኛል፣

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ የባቡር አገልግሎት መጀመሩን ለህዝብ ይፋ አድርጓል፡፡

ይህ በህዝብ መገናኛ ብዙሀን ለህዝብ በሰፊው በመነገር ላይ ያለው ፕሮፓጋንዳ በአሁኑ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣውን ረሃብ ለመሸፋፈን ሲባል የፕሮፓጋንዳ ዒላማ አድርጎ የተነሳ እንደሆነ አምናለሁ፡፡

ህዝብ ስለቀላል ባቡሩ “በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው“ እና ሌላም እንቶ ፈንቶ እና የማይረቡ ነገሮችን የሚያወራ ከሆነ ከዚህ አልፎ እየተንፏቀቀ ስለሚመጣው ከባድ ረሃብ አያወራም፣ እንደዚሁም ደግሞ ስለ4.5 ሚሊዮን እና ከዚያ በላይ ስለሚሆነው ህዝብ የረሃብ ሰለባነት ጉዳይ ቀስ በቀስ ነው እየተገነዘበ የሚመጣው የሚል እምነት አለው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እኔ እነርሱ የሰሩትን ስራ ሁሉ እንደማንቋሽሽ አድርገው እንደሚያስቡ አውቃለሁ፡፡

እነርሱ የሚያስመዘግቧቸውን ስኬቶች ሁሉ እንደማንኳስስባቸው አድርገው ይናገራሉ፡፡

እነርሱን መጥፎ አድርጌ የማቀርብ እና ምንጊዜም እነርሱን የምቃወም አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ ለእነርሱ ምንም ዓይነት እውቅና የማልሰጥ አድርገው ይገምታሉ፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ስለእኔ አንድም ጊዜ ቢሆን የማይናገሯት ነገር ብትኖር  በእነርሱ ጉዳይ ላይ ውሸት አቅርቧል የምትለዋን ነገር ነው! አንድም ጊዜ ቢሆን በፍጹም አይሉም!!! 

በእርግጠኝነት ለመናገር የእኔ ሀሳብ ታዋቂ በሆነው ተንቀሳቃሽ ፊልም ይፋ እንደሚሆነው ሁሉ በተጨባጭ ሁኔታ የሚታይን እውነታ በመያዝ እንጅ “የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን የፈለገዉን ቢያስብ ቢናገር ጉዳዬ አይደለም።

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በሰብ ሰሀራ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የባቡር ሀዲድ እንደገነቡ አድርገው ጉራቸውን ይቸረችራሉ፡፡

አሐ! አሐ! አሐ! ያስቃል በፍጹም አላደረጉም፣ ሀሰት ነው፡፡

ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የቻይና የብድር ገንዘብ ነው የሰራው፡፡

ይኸ 28 (34?) ኪ/ሜ ርዝመት ይኖረዋል ተብሎ የሚገመተው የባቡር ሀዲድ ወደ 500 ሚሊዮን ዶላር በሚሆን ገንዘብ ተገነባ ሲባል በጣም አስገራሚ እና ታምራዊ ነገር ነው፡፡ በዚህ ስሌት መሰረት በአንድ ኪ/ሜ የባቡር ሀዲድ 18 ሚሊዮን ዶላር ውጭ ተደርጓል ማለት ነው፡፡

በአሜሪካ እንደዚህ ያሉት ግንባታዎች አጅግ በጣም ባነሰ ወጭ ይፈጸማሉ፡፡

በዚህ የባቡር ግንባታ ፕሮጀክት ተብዬ ስራ በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ውስጥ ያለ ወሮበላ እርባናቢስ ሀብትን ዘርፏል የሚል እምነት አለኝ!

በእርግጥ ቻይናዎች ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የቀላል ባቡር ግንባታ በተቀበሏቸው የገንዘብ ቁርጥርጮች የብሩክላይንን ድልድይ ለወያኔዎቹ እሸጥላቸው ነበር፡፡ ለወደፊቱ ስምምነት እናደርጋለን፡፡

እንደ ዌልስ አገር በጎች የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ኢትዮጵያን አስላጭቷታል።

ሆኖም ግን የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በኢትዮጵያ ልማትን እንዴት እንዳመጡ እንዲህ በማለት ሌት ቀን እንደ በቀቀን ይለፈልፋሉ፣ “የቀላል ባቡር ሀዲዱን ተመልከቱ… ከሰብ ሰሀራ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን…“

በደናቁርት ስብቦቹ እስቃለሁ፡፡

አንድ ደራሲ ነኝ ባይ ከፍሎ በሌላ ሰው ስላስፃፈው መፅሐፍ አስታወሰኝ። ከፍሎ መፅሐፍ ማስጻፍ ደራሲነት አያረግም።

(ያነጋገሬ  ዘይቤ ስለ ደራሲው ለምሳሌ ብቻ አይደለም። እንደምርመራ ጋዜጠኛ አበበ ገላው በግልጽ አንዳሳየው አብዛኞቹ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አመራሮች የአካዳሚክ ዲግሪዎቻቸውን እና የትምህርት ውጤቶቻቸውን ከየቦታው ከፍለው ነው ያገኙት፡፡ እ.ኤ.አ መስከረም 2010 “ማጥመቅ“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት መሰረት አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ከኦፕን የኒቨርሲቲ ዲግሪው በቀጥታ ከቢሮው መጥቶለት እንዲቀበል ተደርጓል፡፡ በዚሁ ዓመት በየካቲት ወር አበበ ገላው እንዲህ በማለት አጋልጧል፣ “የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ“ የሆነው አባ ዱላ ገመዳ የሕዝብ አስተዳደር የባችለር እና የማስተርስ ዲግሪዎችን ከኢንተርኔት የሸፍጥ የዲፕሎማ መፈልፈያ ወፍጮ ከሆነው ከአሜሪካ ሴንቹሪ ዩኒቨርሲቲ እ.ኤ.አ እንደ ቅደም ተከተላቸው በ2001 እና በ2004 ተቀብሏል፡፡)

እውነታው ፍርጥርጥ ብሎ ሲታይ ግን 28 ኪ/ሜ የሆነው የባቡር ሀዲድ በቻይናዎች ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የመገንባቱ ሁኔታ ምንም ትልቅ ጉዳይ አይደለም፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ኢትዮጵያ ከቻይና ኢኤክስ-አይኤም/EX-IM ባንክ ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድር እንደወሰደች ሆኖ በእዳ መረብ ውስጥ የማስገባት ክስተት ነው፡፡

ስለባቡር ሀዲድ እየተነጋገርን እስከሆነ ድረስ እ.ኤ.አ በ1894 ዳግማዊ ምኒልክ 2ኛ በአደዋ ጦርነት የጣሊያን ወራሪ ኃይሎችን ድባቅ በመምታት ድል ከመቀዳጀታቸው ሁለት ዓመታት በፊት 617 ኪ/ሜ ርቀት ያለውን ከባድ የባቡር ሀዲድ እንዲገነቡት እና እንዲያስተዳድሩት ከፈረንሳዮች ጋር ስምምነት አድርገው ነበር፡፡

በአሁኑ ጊዜ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አሁን በህይወት የሌለው እና ትንሹ አምላካቸው የነበረው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ጀምሮት የነበረውን የባቡር ሀዲድ ፕሮጀክት እንደታላቅ ነገር በመቁጠር በሰብ ሰሀራ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው እያሉ የዳግማዊ ምኒልክ 2ኛን ክብር እና ሞገስ በማሳነስ የአምባገነኑን የመለስን ስብዕና ከፍ ለማድረግ በማሰብ አደንቋሪ ልፍለፋቸዉን በማሰማት ላይ ይገኛሉ፡፡

ይኸ እውን የሚሆነው በህልማቸው ብቻ ነው!!!

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የንጉስ ዳግማዊ ምኒልክ 2ኛን የስልጣኔ መዝገብ ከአምባገነኑ መለስ ዜናዊ ጋር ለማነጻጸር የሚፈለግ ከሆነ ይህንን ንጽጽር ከህዝብ አስተዳደር ጀምሮ እስከረቀቀው ቴክኖሎጂ ድረስ ያሉትን ጉዳዮች በማካተት ልንወያይ እንችላለን፡፡

ንጉስ ዳግማዊ ምኒልክ 2ኛ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የስልክ እና የቴሌግራፍ መስመር ዝርጋታ ስርዓትን ተግባራዊ ያደረጉ ብቸኛው የአፍሪካ መሪ ነበሩ፡፡

አሌክሳንደር ግርሃም ቤል የድምጽ መነጋገሪያ መሳሪያውን የባለቤትነት መብት ማረጋገጫውን ፓተንት ከማግኘታቸው ከ13 ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ በ1889 የመጀመሪያው የስልክ መስመር በምኒልክ ቤተመንግስት ውስጥ በተዘረጋበት ጊዜ የስልጣኔ አደናቃፊ አዛውንት መኳንንቶች እና መሳፍንቶቻቸው ንጉስ ምኒልክን ይህ ነገር የሰይጣን ስራ ነውና ከቤተመንግስትዎ ውስጥ ያስወግዱት ብለዋቸው ነበር፡፡

የብሩህ አዕምሮ ባለቤት የሆኑት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ግን በፍጹም አይሆንም በማለት ሳይቀበሏቸው በመቅረት ቴክኖሎጂውን እያስፋፉ በጥቅም ላይ እንዲውል ያደረጉ ብልህ እና ጀግና ንጉስ ነበሩ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አምባገነናዊ ስርዓት ውስጥ አሳር ፍዳዋን በመቀበል ላይ ያለችው ኢትዮጵያ በኢንተርኔት ስርጭት ምጣኔ ከሰብ አፍሪካ ሀገሮች ውስጥ ከመጨረሻው በመሆን በ2ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ሀሳብን በነጻ የመግለጽን እና የነጻ ፕሬስ መስፋፋትን ኢንተርኔት የተባለው የግንኙነት ሰይጣን ይቆጣጠረዋል በማለት ፍርሀት እና ስጋት ያለው እንደሆነ አድርጌ እገምታለሁ፡፡

በእርግጥ ቻይናዎች ለእነርሱ የግል ጥቅማቸው ሲሉ መንገዱን ዘርገተዋል፡፡ በማታለል የመሰረተ ልማትን መሸጣቸው ይሆን?

በእርግጠኝነት እ.ኤ.አ በ2012 በአፍሪካ ላይ የተደረገውን ታላቅ የቅሌት ክስተት በርካታ አንባቢዎቼ ታስታውሱታላችሁ ብዬ አስባለሁ፡፡

ስምን በመቀያየር እድገት እና ልማት ይመጣ ይመስል ከአውሮፓ ህብረት በመኮረጅ ቀደም ሲል የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ይባል የነበረውን ስም በመቀየር እና አሁን የአፍሪካ ህብረት ትብሎ እንዲጠራ ያደረጉትን ህንጻ ቻይናዎች በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሚሆን ገንዘብ ገንብተው ለአፍሪካ መሪዎች በስጦታ መልክ ሰጡ፡፡

ሊታመን የማይችል ጉድ ነገር ነው!

የአፍሪካ መሪዎች እየተባሉ የሚጠሩት ስብስቦች ለሁሉም አፍሪካውያን ልዩ የክብር መገለጫ የሚሆነውን ህንጻ ትንሽ የሆነቸውን 200 ሚሊዮን ዶላር ከእራሳቸው ካዝና በማዋጣት ለማሰራት አልቻሉም፡፡

ከቻይናን ምጽዋት በመለመን ማሰራት ነበር የፈለጉት፡፡

የአፍሪካ መሪዎች የአፍሪካ አህጉርን የለማኞች እና የምጽዋት ፈላጊዎች አህጉር በማለት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳየታቸው ምን ያህል የወረደ እና አሳፋሪ ድርጊት ነው!

አፍሪካዊ በመሆኔ ብቻ በህይወቴ ውስጥ እስከ አሁን ድረስ በሀፍረት እንድሸማቀቅ ያደረገኝ ድርጊት ቢኖር ክስተት ብቻ ነው

“የአፍሪካ ለማኞች አዳራሽ” በሚል ርዕስ አቅርቤው በነበረው ትችቴ ላይ በአፍሪካ ለማኝ ፕሬዚዳንቶች እና ጠቅላይ ሚኒስትሮች በጣም ተበሳጭቸ እና በሀፍረት ተሸማቅቄ እንደነበር ግልጽ አድርጌ ነበር፡፡ በዚያ ትችቴ ላይ የአፍሪካውያን ክብር እና ሞገስ በትንሿ 200 ሚሊዮን ዶላር ለቻይናዎች ተሸጠ ብየ ነበር፡፡

ይቅርታ ሊደረግለት የማይችል ድርጊት!

ታዋቂ የሆኑት ጋናዊ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ጆርጅ አይቴይ የተባበሩት መንግስታትን መረጃ ዋቢ በማድረግ እንዲህ የሚል የክርክር ጭብጣቸውን አቅርበዋል፣ “እ.ኤ.አ በ1991 ብቻ 200 ቢሊዮን ዶላር ወይም ደግሞ የሰብ ሰሀራን ሀገሮች ዓመታዊ ጥቅል ምርት/Gross Domestic Product (GDP) 90 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ ወደ ውጭ ሀገር ባንኮች ወጭ ተደርጎ ታጭቋል፡፡“

እ.ኤ.አ በ2011 ግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ/Global Financial Integrity የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ኢትዮጵያን በማስመልከት እንዲህ የሚል ዘገባ አቅርቦ ነበር፣ “በአፍሪካ አህጉር ካለችው ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2009 ካለፈው ዓመት በእጥፍ በሚበልጥ ሁኔታ በሕገ ወጥ መልክ 3.2 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ገንዘብ በሙስና፣ በስጦታ እና በጉቦ ከሀገር እንዲወጣ ተደርጓል፡፡“

ሁሉም 54ቱ የአፍሪካ ሀገሮች ለአህጉሩ ታላቅ ውበትን እና ልዩ የሆነውን ህንጻ ለመግንባት 200 ሚሊዮን ዶለር በማዋጣት ለመስራት አልቻሉም፡፡

እንግዲህ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ነው አፍሪካውያን የአፍሪካን ህብረት የለማኞች የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለማግኘት የቻሉት!

ሆኖም ግን ቻይናዎች የቀላል ባቡር ሀዲድ ፕሮጀክት እየተባለ የሚጠራው የባቡር ሀዲድ ቻይናዎች እንደሚሉት “በመስታወት ውስጥ እንደሚታይ አበባ” ወይም ደግሞ “በውኃ አካል ላይ እንደምትታየዋ ጨረቃ” ዓይነት ነው፡፡

ይህንን አባባል የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ደናቁርት ምን ለማለት እንደፈለግሁ አይገነዘቡትም፣ ሆኖም ግን ቻይናዎች በትክክል ምን ለማለት እንደፈለግሁ ይገነዘቡታል!

ይኸ ሁሉ የሚደረገው ነገር ለማስመሰያ እና ቀልብን ወደ ሌላ አቅጣጫ ለማስቀየስ ነው፡፡ የአፍሪካ ህብረት መናገሻ በሆነችው በአዲስ አበባ ከተማ የባቡር ሀዲድ ስራና ለቀሪው ዓለም በማሳዬት በቀሪዎቹ የአፍሪካ ሀገሮች አንቴና ቀንዶችን በደንብ አድርጎ በማስገባት ደማቸው እስኪደርቅ ድረስ ሙልጭ አድርጎ መምጠጥ ነው፡፡

ታላቅ ቅሌት!

ሆኖም ግን የእኔ ትልቁ ጥያቄዬ እንዲህ የሚል እና ፍጹም በሆነ መልኩ የተለዬ ነው፡ 28 ኪ/ሜ ርዝመት ያለው የጉራ እና የታዕይታ ፕሮጀክት በግማሽ ቢሊዮን ዶላር ከመገንባት ይልቅ በረሃብ የተጎዱ ኢትዮጵያውያንን ህይወት ለማዳን በሚያስችል ነገር ላይ ማዋል የበለጠ ትርጉም የሚሰጥ ሊሆን አይችልምን?

ድምጼን ከፍ በማድረግ እንዲህ በማለት ደግሜ እለዋለሁ፡ 28 / ርዝመት ያለው የጉራ እና የታዕይታ ፕሮጀክት በግማሽ ቢሊዮን ዶላር ከመገንባት ይልቅ በረሃብ የተጎዱ ኢትዮጵያውያንን ህይወት ለማዳን በሚያስችል ነገር ላይ ማዋል የበለጠ ትርጉም የሚሰጥ ሊሆን አይችልምንአለቀ ይኸው ነው በቃ!!!

ለዘመናት የረኃብን የማስጠንቀቂያ ደወሎች መደወል!

የረሃብን የማስጠንቀቂያ ደወል ለጥቂት ዓመታት ያህል ደውያለሁ፡፡

እውነት ለመናገር የለጋሽ ሀገሮች እና የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች እንዲሁም የውጭ ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ እየተንፏቀቀ የሚመጣውን ረሃብ በዓለም ላይ የአደባባይ ታላቅ ሚስጥር አድርገው ለመያዝ ይሞክራሉ፡፡ በረሃቡ አደጋ የሞቱትን የረሃብ ሰለባ ፍቶግራፎች በእርግጠኝነት እስከ አሁን ድረስ ያዬ ይኖራልን?

በረሃብ አደጋ ከተጠቁ አካባቢዎች ማንኛውም ዓይነት ዘገባ እንዳይወጣ ከፍተኛ የሆነ እገዳ እና ፍጹም የሆነ ቁጥጥር እንዳለ ግልጽ የሆነ ነገር ነው፡፡

እ.ኤ.አ. ጥቅምት 2012 “ኢትዮጵያ፡ በ2013 ስለሚከሰተው ረሃብ ቅድመ ማስጠንቀቂያ“ በሚል ርዕስ የረሃብ ማስጠንቀቂያ ደወሉን በመደወል ትችት አቅርቤ ነበር፡፡

የረሃብ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት መረብ/Famine Early Warning Systems Network (FEWS NET)ን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ድርጅቶች ማለትም ኦክስፋም፣ የተባበሩት መንግስታት የምግብ ፕሮግራም፣ የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የግብርና ድርጅት እና የአዲሲቷ እንግሊዝ ውስብስብ ስርዓት ተቋም/New England Complex Systems Institute (NECSI) (የአካባቢ ስነምህዳር ለውጦች እንዴት አድርገው ወደ ፖለቲካ አለመረጋጋት እና ቀውስ ሊሸጋገሩ እንደሚችሉ የተለየ ልምድ ያካበቱት ከሐርቫርድ/Harvard እና ከኤምአይቲ/MIT ዩኒቨርሲቲዎች የትንበያ ሙያ ካላቸው የአካዳሚክ ቡድን የተውጣጣ ስብስብ) ያወጧቸውን ግኝቶች በጥንቃቄ በማጥናት እና በመተንተን እ.ኤ.አ 2013 በኢትዮጵያ ረሃብ የሚጀምረበት ወይም ደግሞ እነርሱ በተለያየ ስያሜ እንደሚጠሩት አሰቃቂ የምግብ ቀውስ እንደሚከሰት ግልጽ ሆኖልኝ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ በ2012 ሁለተኛው አጋማሽ ከአምራች ሀገሮች ወደ ውጭ የሚወጡ ምርቶች መቀነስ እ.ኤ.አ በ2013 በዓለም አቀፍ የምግብ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ ነውጥ ሊያስከትል እንደሚችል ጠቅላላ ስምምነት ተደርሶ ነበር፡፡

በአሁኑ ጊዜ የናሙና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መንግስት የውጭ ምንዛሬ ክምችቱ እየተሟጠጠ ባለበት ሁኔታ እና ከማይቀረው የዓለም የምግብ ቀውስ አንጻር በሀገሪቱ ውስጥ አስከፊ በሆነ መልኩ ወደፊት ሊከሰት የሚችለውን ረሃብ እንዴት አድርጎ ሊቋቋመው እንደሚችል ለማወቅ እፈልጋለሁ፡፡

የበለጠ ምጽዋዕት መጠየቅ እና የምግብ ልመናን የማካሄድ ዕቅድ ብቻውን በማድረግ በአስቸኳይ የምግብ እርዳታ መጠየቅ ችግሩን ሊቋቋመው አይችልም፡፡ በምግብ ለስራ ፕሮግራም/Productive Safety Net Program ላይ ጥገኛ በመሆን መስራት የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም፡፡

ላለፉት 5 ዓመታት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አገዛዝ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ረሃብ ለማስቆም ምንም ዓይነት የሰራው ነገር የለም፡፡ ይቅርታ ማስተካከያ፡ የሰራውማ ስራ አለ እንጅ፣ ለምግብ እርዳታ የዓለምን ህዝብ ለምኗል!

ዓመት ከዓመት የይስሙላው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እና የወያኔ ግብረ አበር ሸፍጠኞች አንድ ላይ ተቀምጠው የለመና አጃቸዉን ቀሰረው  የአሜሪካንን ግብር ከፋይ ህዝብ ዶላር የምግብ እርዳታው እስከሚመጣ ድረስ ቁጭ ብለው ዝንቦችን ከፊታቸው አያባረሩ ይጠብቃሉ።

በተጻራሪው አስገራሚው ነገር ደግሞ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በረሃብ እያለቁ በሚገኙበት ጊዜ የሀገሪቱ በጣም ለም የሆኑ መሬቶች በእነዚህ መሬቶች ላይ አምርተው ወደየሀገሮቻቸው በመውሰድ የእራሳቸውን ዜጎች መመገብ እንዲችሉ ለሳውዲ አረቢያ፣ ለህንድ እና በግብርና ስራ ላይ ለተሰማሩ የንግድ ኩባንያዎች እየታደሉ እና ቻይና በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ጠልቃ በመግባት ዕቅዷን በቆሸሸ መልኩ በመተግበር ላይ ትገኛለች፡፡ ምን ዓይነት አዋራጅ እና አሳፋሪ ነገር ነው!

ባለሁለት አሀዝ የምጣኔ ሀብት ዕድገት፣ የምጣኔ ሀብቱን በእጥፍ ማሳደግ፣ ትርፍ እና የተትረፈረፈ ምርት፣ እና በቀን ሶስት ጊዜ መመገብ! ምን የማይባል ነገር አለ!

በእርግጥ ሰብአዊ እርዳታ ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አመራሮች የገቢ ምንጭ ነው፡፡ (“የሌብነት ሕጋዊነት” በሚል ርዕስ ከዚህ ቀደም አቅርቤው የነበረውን ትችቴን ይመልከቱ፡፡)

በኢትዮጵያ የተደበቀውን ረሃብ ማጋለጥ፣

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዚያት በተለይ ስለሚከሰቱት ረሃቦች ወይም ደግሞ በሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ትችት ሳቀርብ ቆይቻለሁ፡፡ (በግርጌ ማስታዋሻ ላይ የተቀመጡትን የግንኙነት መስመሮች ይመልከቱ፡፡)

ከምግብ እጦት ምክንያት ከሚሞቱት እና ከሚሰቃዩት በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የረሃብ ሰለባ ህዝቦችን ከዓለም አቀፍ እና ከሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች ለመደበቅ እና ረሃብን ድብቅ አድርጎ ለማቆየት ገዥዎች የሚያደርጉትን ድብብቆሽ እና ክልከላ በተደጋጋሚ ግልጽ ለማድረግ ሞክሪያለሁ፡፡

የመለስ/ኃይለማርያም አገዛዞች ረሃብን ሚስጥራዊ አድርጎ ለመቆየት ከእነርሱ በፊት የነበሩትን ገዥዎች እግር ተከትለዋል፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ እ.ኤ.አ በ1974 ተከስቶ የነበረውን “ድብቁ ረሃብ” የሚለው ዘጋቢ ፊልም ለህዝብ ዕይታ በአየር ላይ እስከዋለ ድረስ ርሃብ መኖሩን አላውቅም ብለው ነበር፡፡

የቀድሞው ወታደራዊ አምባገነን መሪ የነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማርያም እ.ኤ.አ በ1985-86 ተከስቶ በነበረው ረሃብ እብሪት በተቀላቀለበት መልኩ ሙልጭ አድርገው በመካድ ድንገተኛ በሆነ መልኩ “የምን ረሃብ?” የሚል ጥያቄ ያዘለ ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡

መለስ፣ ኃይለማርያም እና ግብረአበሮቹ እንዲሁም ከእርሱ በፊት የነበሩት ገዥዎች የረኃብን መከሰት ጉዳይ በማስመልከት ከህዝብ እይታ ለመደበቅ በሚያደርጉት ጥረት የበለጠ አታላዮች ነበሩ፡፡ ይህንን እኩይ ምግባራቸውን ለመደበቅ የሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ደግሞ፣ 1ኛ) የአገር ውስጥ ብዙሀን መገናኛዎች እንዳይዘግቡ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እና ሊያመጣ የሚችለውን እና ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ ቀውስ ሊያስከትል የሚችለውን ረኃብ ለመዘገብ ፍላጎት ላላቸው ለዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች እና ለብዙሀን መገናኛ ወኪሎች ሁሉ አገሪቱ ዝግ እንድትሆን ማድረግ፣ 2ኛ) ከሚያብረቀርቁ የልመና አኩፋዳዎቻቸው ጋር በመሆን ከምዕራቡ ዓለም ኤምባሲዎች ቅጥር ግቢ ውጭ ለልመና መቆም ዋና ዋናዎቹ ናችው፡፡

እ.ኤ.አ በ2015 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ፣ የእነርሱ ታዛዥ ሎሌዎች፣ ተባባሪዎች እና ካድሬዎች በአስር እና በሺዎች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ልዩ ለሆኑ ልብሶች፣ ጫማዎች፣ የእጅ ቦርሳዎች እና ሽቶዎች፣ እንዲሁም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዶላሮችን በቅንጦት ተሽከርካሪ መኪኖች፣ በእስፖርት አገልግሎት መኪኖች ግዥዎች ወጭ ማድረግ እና በብዙ ሚሊዮን ዶላሮች ወጭ የተደረገባቸውን ህንጻዎች እና ለእነዚህ ውድ ህንጻዎች ማስዋቢያ የቤት ቁሳቁሶችን እና የምግብ ቤቶችን ዕቃዎች ከአውሮፓ ያስመጣሉ፡፡

ከግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ ከተገኘው ዘገባ መገንዘብ እንደሚቻለው በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን በውጭ ሀገር በሚገኙ ባንኮች እና ድብቅ በሆኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ ያጭቃሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ2015-16 በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለአስከፊ ረሃብ ይጋለጣሉ፡፡

እንግዲህ ይህ ሁኔታ አሳዛኝ ክስተት ሆኖም ግን በኢትዮጵያ በእውን ያለ ተጨባጭነት ያለው ታሪክ ነው፡፡

ለህዝብ ዘገባ የሚያቀርበውን ፕሬሱን በማስፈራራት፣ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው ገዥ አካል በኢትዮጵያ ያለው ረሃብ ድብቅ ሆኖ እንዲቀር እና በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ እንዳይታወቅ ሚስጥር ሆኖ እንዲቀመጥ ጥረት ያደርጋል፡፡

ሆኖም ግን ለማርቲን ጌይስለር፣ አይቲኤን/ITN እና ለኤንቢሲ/NBC ድፍረት ምስጋና ይግባውና ባለፈው ዓመት ስለነበረው ሰብአዊ ቀውስ የተወሰነ ግንዛቤ እንድንጨብጥ አስችሎናል፡፡

ለጋሽ ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች፣ የውጭ ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ ስላለው የረሃብ ሁኔታ እውነታውን ይናገራሉ!

በኢትዮጵያ የተከሰተውን ረሃብ ከህዝብ ለመደበቅ ጸጥ የማለት ዓለም አቀፋዊ ሸፍጥ አለ፡፡

ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል  በኢትዮጵያ ላይ ባለው ገዥ አካል እና በዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች፣ እርዳታ ሰጭ ባለሙያዎች፣ ዓለም አቀፍ ሰራተኞች እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች መካከል በሚገባ በተቀነባበረ የዝምታ ሸፍጥ ምክንያት አስፈሪውን በ “ረ” (ረሃብ ) በማለት የሚጀምረዉን ቃል በኢትዮጵያ ውስጥ አይጠቀሙም፡፡ ሆን ተብሎ ህዝብን ለማሳሳት በሚነገር በቢሮክራሲ የተተበተበ የሀሰት ቃላትና ንግግር ለህዝብ ግልጽ አንዳይሆኑ ዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪዎች/International Poverty Pimps (IPPs) እያልኩ የምጠራቸው በብዙሀን መገናኛ ዘዴዎች እንዳይለቀቅ በሚል እሳቤ እውነታውን ሸፍኖ ረኃቡን ከህዝብ ደብቆ ለማቆየት ረዥም ርቀት ተጉዘዋል፡፡

የዚህን ሸፍጥ ውስጣዊ ባህሪ “እ.ኤ.አ በ2013 መጀመሪያ አካባቢ ስለሚከሰተው ረሃብ ማስጠንቀቂያ“ በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ ጥቅምት 2012 አቅርቤው በነበረው ትችቴ ውስጥ ገለጻ አቅርቤበታለሁ፡፡

እነዚህ ዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪዎች ስለምግብ ዋስትና እጦት የተለያዩ ደረጃዎች እንጅ ረሃብን በትክክለኛው ስሙ በፍጹም ረሃብ ብለው አይጠሩትም፡፡

የሰዎች የምግብ መራብ ፍላጎት እና የምግብ እጦት/Hungry and Starving “ኃይለኛ የምግብ ዋስትና እጦት”/”Acute Food Insecurity”፣ አሳሳቢ የምግብ ሁኔታዎች ማጋጠም/Face “stressed” food situations፣ ወደ ቀውስ አዝማሚያ የሚሄድ ምግብ እጦት/Go into “crisis” mode፤ ወደ አስቸኳይ የሆነ ምግብ እጦት ደረጃ/Graduate to “emergency” status፣ እና በመጨረሻም ወደ አስከፊ የምግብ እጦት/Catastrophic food shortages የሚሉ ደረጃዎች ስያሜን አያወጡ ይተርካሉ፡፡ በየትኛውም ቦታ ቢሆን “ረኃብ” ወይም “ጠኔ”/”Famine” or “Starvation” የምትል ቃል በአፋቸው አይጠሯትም፡፡

ረኃብ/Famine የሚለው ቃል በኢትዮጵያ ባለው ገዥ አካል እና በብዙ በዓለም አቀፍ ደረጃ በድህነት ስም ለርካሽ ጥቅማቸው በቆሙ አቃጣሪዎች ለምን እንደማይጠራ የተከለከለበት ምክንያት አለ፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች በ”ረ” የምትጀምረውን ቃል ትንፍሽ አይሉም፡፡

ምናልባትም የሙዝ ጋሪው እንዳይገለበጥ ወይም ደግሞ አስከፊ የረሃብ ዘገባ በመቅረቡ ምክንያት ቀላሉ ባቡር እንዳይቆም ተፈልጎ ይሆናል፡፡ (ለመሆኑ ቀኑን ሙሉ ምንድን ሲያደርጉ ይውላሉ?)

በ”ረ” የምትጀምረውን ቃል ለምን ደፍረው እንደማይናገሩባት ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1980ዎቹ ጀምሮ በረኃብ ብዙ ሆዳቸው የተነፋ በበረሃ በተቃጠለ የመሬት ገጽታ ላይ የሚንከላወሱ፣ እግር እና እጃቸው የተጠማዘዘ የረኃብ ሰለባ እሬሳዎችን በግራር ዛፎች ስር እና ሆዳቸው ተነፍቶ በዝንቦች የተወረሩ ህጻናት እናታቸውን አጥብቀው እንደያዙ በመመገቢያ ካምፖች ውስጥ ሆነው በአእምሮ ላይ ስሎ ያሳያልና ነው፡፡

በኢትዮጵያ ስለረኃብ በግልጽ ማውራት በለጋሽ ድርጅቶች/በመንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እና በገዥው አካል አደገኛ ሁኔታ ነው፣ ምክንያቱም የፖለቲካ አመጽን የሚጋብዝ ነውና፡፡

ፕሮፌሰር አንጌላ ራቬን ሮበርትስ እና ፕሮፌሰር ሱዊ ላውዜ በኢትዮጵያ ያለውን ተደጋጋሚ የረሃብ መከሰት በማስመልከት ባቀረቡት ትንታኒያቸው እንዲህ ይላሉ፣ “ረሀብን ይፋ ማድረግ ማለት ለኢትዮጵያ መንግስት የተወሳሰበ ጥያቄ ነበር፡፡ ረሃብ ለኢትዮጵያ ገዥዎች መውደቅ ምክንያት አስተዋጽኦ አድርጓል… አንዳንድ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ስኬቶቻቸውን በከፊል ረሃብን በማስወገድ ይለኳቸዋል፡፡“

የዝምታ ሸፍጥ ከረሃብ ጋር በተያያዘ መልኩ በኢትዮጵያ በመስራት ላይ ለሚገኙ ተዋንያን ሁሉ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ያገለግላል፡፡ ገዥው አካል፣ ለጋሽ ድርጅቶች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የእርዳታ ሰራተኞች የረሃብን መኖር አምነው ለመቀበል መሞከር የሌባ ጣትን ወደ እራስ እንደመቀሰር ተደርጎ ይቆጠራል፡፡

ለረሃብ መኖር በአዎንታዊነት ማረጋገጫ የሚሆኑት በሌላው መልኩ ሲታይ ረሃብ ከሌለ ለምግብ እርዳታ የሚሰጡት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር፣ በስርጭት መስመሮች ላይ የሚገኙት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ከፍተኛ ተከፋይ የሆኑት ዓለም አቀፍ የእርዳታ ሰራተኞች መከኑ ማለት ነው፡፡

በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እርዳታ ቢኖርም ቅሉ ኢትዮጵያ በምግብ እህል እራሷን እንድትችል የሚያስችል ዕቅድ ለማውጣት ውድቀትን ያሳያሉ፡፡ የኢትዮጵያ ገዥ አካል ረሃቡን ለማስወገድ እንዲችል የሚያግዝ ጥረት የማድረግ ድፍረቱ የላቸውም፡፡

በኢትዮጵያ የምግብ እርዳታ ላይ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የሞራል ዝቅተት፣

ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የምግብ እርዳታ አስመልከቶ ህሊናን የሚቆጠቁጥ አስገራሚ እና የማይገናኝ ሁኔታ አለ፡፡ በየዓመቱ ባለፉት አስርት ዓመታት የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ለአንድ ዓይነት የህብረተሰብ ክፍሎች በእርግጠኝነት እያወቀች በየዓመቱ የምግብ እርዳታ ትሰጣለች፡፡

እ.ኤ.አ በ2003 እና በ2012 ባሉት ዓመታት መካከል ኢትዮጵያ 29 ቢሊዮን ዶላር የውጭ የልማት እርዳታን/Overseas Development Assistance በመቀበል ከዓለም ታላቁን የ4ኛነት ደረጃን ይዛ ትገኛለች፡፡

አንዳንድ ለአጠቃላይ ደህንነት የሚውሉ እና እንደ ምርታማነት ደህንነት ፕሮግሞች/Productive Safety Net Programs (ገዥው አካል በገጠር ከሚኖሩ ገበሬዎች እና ኗሪዎች የፖለቲካ ድጋፍ ለማግኘት እየተጠቀመበት ይገኛል) የመሳሰሉ ፕሮጀክቶች በስተቀር ከረሃብ እርዳታው ጋር በተያያዘ መልኩ አሜሪካ በገዥው አካል ላይ የምትጥላቸው ጥቂት ቅድመ ሁኔታዎች እንኳ የሉም፡፡ እንዲህም ሆኖ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከዓመት ዓመት ከፍተኛ በሆነ ችግር ውስጥ መውድቅ እና በሚሊዮን የሚቆጠር አሜሪካውያን ግብር ከፋይ ዶላሮች ለድርቁ ችግር መዋላቸው ቀርቶ ለማጭበርበር፣ ለሙስና እና ለብክነት ይዳረጋል፡፡

በአሜሪካ በምግብ እርዳታ ፖሊሲ ላይ ያለው ችግር የሚያሳየው እውነታ የመጣው የእርዳታ ገንዘብ በኢትዮጵያ በትልቅ የረሃብ አደጋ ጫፍ ላይ ተንጠልጥለው ያሉ ዜጎችን ከችግራቸው በማውጣት ተግባር ላይ መዋሉ በሚገባ ሊጤን ይገባዋል፡፡

ፓውል ሄበርት የተባሉት የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ አስተባባሪ ቢሮ ኃላፊ በኢትዮጵያ በቅርቡ የተመለከቱትን አንደሚከተለው አቅርበውታል፣ “[በኢትዮጵያ ውስጥ] እየገጠመን ያለው ችግር ብዙው እና በርካታው የህብረተሰብ ክፍል ውጥረት ላለው ሁኔታ እና ለአካላዊ አደጋ ይጋለጣሉ… ከዚያ አደጋ ለማውጣት የተደረገ ጥረት የለም፡፡ ከዚህም በላይ የሚያስፈራው ነገር በዚህች አገር ሌላ ትልቅ የድርቅ አደጋ ከተከሰተ እና ያለውን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እና አሳሳቢ የሆነውን የምግብ እጦት ለመቅረፍ  አስተማማኝ ስራ ካልሰራን ነገሮችን በእጅጉ ቀድሞ ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ ሊያደርግ ይችላል፡፡ የበርካታ ሰዎች የኑሮ ሁኔታ በጣም አደገኛ በሆነ ሁኔታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ በቀላሉ አደገኛ ወደ ሆነ የድርቅ ረሃብ ውስጥ ልትገባ ትችላለህ፡፡“

ዩናይትድ ስቴትስ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች  በችግር ጠርዝ ላይ ሆነው እያዩ ወደ ጎን ሆነው ለወንጀሉ ተባባሪነታቸውን በማሳየት በጸጥታ እየተመለከቱ ዝምታን ይመርጣሉን?

በተለይም ደግሞ ጋይሌ ስሚዝ የዩናይትድ ስቴትስን ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት/United States Agency for International Development (USAID)ን በበላይነት እንድትመራው የቀረበው ሹመት የሚጸድቅ ከሆነ ሁኔታው ምን ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ ፍላጎት የለኝም!

ዓመታዊ የረሃብ አዝመራ፡ የግልጽነት እና ተጠያቂነት አስፈላጊነት አንገብጋቢነት፣

የምግብ እጥረት፣ የምግብ ዋስትና እጦት ወይም ደግሞ ማንም ሰው ሌላ የፈለገውን ዓይነት ስያሜ በመምረጥ በኢትዮጵያ ውስጥ በጥቅም ላይ ቢያውለውም ቅሉ በምግብ ተመጽዋችነት የረሃቡ ችግር ሊፈታ አይችልም፡፡

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከሙስና ቀጥሎ እርዳታ ልመና በኢትዮጵያ ላለው ገዥ አካል ዋና አስፈላጊው ነገር ነው፡፡

ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ረሃብ እና ሀፍረትን ሲያጭድ ቆይቷል፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የምግብ ልመና ባህል ተዋህዶታል፣ በአሁኑ ጊዜ ተስፋን በቆረጠ ሁኔታ ለምግብ እርዳታ ሱሰኛ ሆኖ ይገኛል፡፡

ድሆቹ የኢትዮጵያ የረሃብ ሰለባዎች በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ችሎታ ወይም ደግሞ እርዳታ የማቅረብ አቅም ላይ እምነት የላቸውም፡፡

የረሃብ ሰለባዎቹ የአሜሪካንን እና የምዕራቡን ዓለም ለጋሽ ድርጅቶች እንዲረዷቸው ነው የሚመለከቱት፡፡

የአሜሪካ ግብር ከፋይ ህዝብ ለእራሱ ህዝቦች ደንታ ለሌለው አገዛዝ እየሰበሰቡ ዶላር ሲያስታቅፉት የሚኖሩት ለምን ያህል ጊዜ ነው?

የአሜሪካ ግብር ከፋይ ህዝብ በኢትዮጵያ በእራሱ ህዝቦች ስም የዶላር እርዳታ በመቀበል  ለሚያባክን፣ ከህግ አግባብ ውጭ ለሚጠቀም እና በሙስና ለሚያጠፋ ገዥ አካል ምን ዓይነት እና ለምን ያህል ጊዜ ታጋሽነት ሊኖረው ይችላል?

ባለጥቁሩ የምፃት ፈረስ በኢትዮጵያ እየጋለበ ነውን?

አይ አይደለም ረሃብ በኢትዮጵያ የቀላል ባቡር ላይ እየጋለበ ነው!

ድምጼን ከፍ በማድረግ እንዲህ በማለት ደግሜ እለዋለሁ፡ 28 / ርዝመት ያለው የጉራ እና የታዕይታ ፕሮጀክት በግማሽ ቢሊዮን ዶላር ከመገንባት ይልቅ በረሃብ የተጎዱ ኢትዮጵያውያንን ህይወት ለማዳን በሚያስችል ነገር ላይ ማዋል የበለጠ ትርጉም የሚሰጥ ሊሆን አይችልምንአለቀ ይኸው ነው በቃ!!! ምንም ዓይነት ይቅርታ የለውም!!! 

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

መስከረም 19 ቀን 2008 .

 

Similar Posts