የግል ደብዳቤ፡ ይድረስ ለሴናተር ቴድ ክሩዝ 

Gayle Smithከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም    

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ 

ለተግባራዊ  ድርጊት የቀረበ ጥሪ፣

ልዩ ምልከታ እና ጥያቄ፡ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የምትገኙት አንባቢዎቼ በተለይም ደግሞ በታላቁ የቴክሳስ ግዛት እና በዋሽንግተን ዲሲ ሜትሮፖሊ አካባቢ የምትኖሩ ኢትዮ-አሜሪካውያን በሙሉ በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትሰ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ)/United States Agency for International Development እየተባለ የሚጠራውን ዓለም አቀፍ ድርጅት በበላይነት እንድትመራው ለሹመት የተጠቆመችውን ጋይሌ ስሚዝን በመቃወም ሹመቱ በሴኔቱ እንዳይጸድቅላት እያደረግሁ ያለውን ተቃውሞ እንድትቀላቀሉኝ እና በጋራ ይህችን የኢትዮጵያ ጸር የሆነች ሴት ሹመት እንዳይጸድቅ እና እንዲመክን በማድረግ ለውድ ሀገራችን ያለንን ተቆርቋሪነት እና ፍቅር በግልጽ እንድናሳይ በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ስም ሀገራዊ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት/ሴኔት የጋይሌ ስሚዝን የጥቆማ ሹመት ላለማጽደቅም ሆነ ተቀብሎ ለማጽደቅ ነጻ እና ሙሉ ስልጣን አለው፡፡

በተለይ የኢትዮ-አሜሪካ ዜግነት ያላችሁ ወገኖቼ ሁሉ ሴናተር ቴድ ክሩዝ በሚገኙበት ግዛት በቅርንጫፍ  ቢሮዎቻቸው  ወይም ደግሞ በዋሽንግተን ዲ.ሲ ኮንግረስ እየቀረባችሁ  የስሚዝ ሹመት እንዳይጸድቅ ጥረታችሁን ሁሉ እንድታደርጉ ተማጽዕኖየን አቀርባለሁ፡፡

በቴክሳስ ግዛት እና በዋሽንግተን ዲ.ሲ የሚገኙትን የሴናተር ክሩዝን የወረዳ ጽ/ቤቶች ዝርዝር እዚህ ጋ በመጫን ይመልከቱ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በነጻነት፣ በዴሞክራሲ እና በሰብአዊ መብት ጥበቃ ለምታምኑ ኢትዮ-አሜሪካውያን ሁሉ በየአካባቢያችሁ ወይም ደግሞ በዋሽንግተን ዲ.ሲ አካባቢ ለሚገኙ የሴናተሩ ጽ/ቤቶች ስልክ በመደወል፣ በመጻፍ፣ እና የፋክስ መልዕክት በመላክ የሚስስ ስሚዝ ሹመት በሴኔቱ እንዳይጸድቅ ተቃውሟችሁን እንድታሰሙ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙትን ሴናተሮቻችሁን ለማግኘት እዚህ ጋ ይጫኑ፡፡

“በሴኔቱ ምክር እና ስምምነት መሰረት ፕሬዚዳንቱ አምባሳደሮችን፣ ሚኒስትሮችን እና አማካሪዎችን፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ዳኞች እና ሌሎችን የዩናይትድ ስቴትስ ኃላፊ ኦፊሰሮችን በሕግ በልዩ መልኩ ካልተደነገገ በስተቀር የመጠቆም እና የመሾም ስልጣን አለው…”  የዩናይትድ ስቴትስ ሕገ መንግስት አንቀጽ II ክፍል 2 ተራ ቁጥር 2፡፡

በደብዳቤዬ ከዚህ በታች ለሴናተር ቴድ ክሩዝ ግልጽ ለማድረግ እንደሞከርኩት ሚስስ ስሚዝ ዩኤስኤአይዲን/USAIDን በበላይነት እንድትመራው የቀረበው ጥቆማ ጸድቆ ሹመቱን የምታገኝ ከሆነ ለአፍሪካ ከፍተኛ የሆነ ጥፋት እና ለኢትዮጵያ ደግሞ መቋቋም የማይቻል መቅሰፍትን ያስከትላል የሚል እምነት አለኝ፡፡

መንግስታችን ትክክለኛውን መንገድ በመከተል ሊሰራ የሚችልበትን የዩናይትድ ስቴትስን ሕገ መንግስት በመጠቀም አቤቱታችንን እንዲህ በማለት እናቅርብ፡

የጋይሌ ስሚዝ ለዩኤስኤአይዲ/USAID የሹመት ጥቆማ ውድቅ ይደረግ!

“ለኢፍትሐዊነት ቁንጫ መሆን ይኖርባችኋል፡፡ በቂ የሆኑ እና ስልታዊ በሆነ መልኩ ጥቃታቸውን የሚሰነዝሩ ቁንጫዎች ከእነርሱ በእጅጉ የሚገዝፈውን ታላቁን ውሻ ምቾት ይነሱታል፣ እናም ታላቅን ሀገርም እንደዚሁ መለወጥ ይቻላል፡፡“ — ማሪያን ራይት ኤድልማን

==== ===   =============    ====================   =========

መስከረም 18፣ 2015

ለሴናተር ቴድ ክሩዝ

ዩ.ኤስ ሴኔት

ሱይቴ ኤስአር- 404

ዋሽንግተን ዲ.ሲ 20510

ውድ ሴናተር ክሩዝ፣

.. ሀምሌ 16/2015 ለፕሬዚዳንት ኦባማ የጻፉትን ደብዳቤ ይመለከታል፡

በዚያ ደብዳቤ ላይ ያለዎትን ሀሳብ ግልጽ እንዳደረጉት ሁሉ ፕሬዚዳንቱ የተወሰኑ ማረጋገጫ ዋስትናዎችን እስከሚሰጥዎት ድረስ “ሁሉንም የዉጭ ጉዳይ መምሪያ ተሿሚ ተጠቋሚዎችን ሹመት ከመጽደቅ አግዳለሁ “ ብለው ቃል ገብተው ነበር፡፡

ፕሬዚዳንቱ የተጠየቀውን የማረጋገጫ ዋስትና እስከ አሁን ድረስ ከመስጠት ታቅቧል፡፡

በደብዳቤዎ ላይ እንዳቀረቡት ተማጽዕኖ ሁሉ እኔም የእርስዎን ሀሳብ በመደገፍ ጋይሌ ስሚዝ በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትሰ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ)/United States Agency for International Development (USAID) አስተዳዳሪነት የቀረበላት የሹመት ጥቆማ እንዳይጸድቅ ይህንን ደብዳቤ ለመጻፍ ፈልጊያለሁ፡፡

እ.ኤ.አ ሰኔ 17/2015 የሚስስ ስሚዝ የሹመት ጥቆማ ለሴኔቱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ቀርቧል፡፡ ሴኔቱ በእርሷ የሹመት ጉዳይ ላይ ውሳኔውን አስካሁን አልሰጠም፡፡

እኔ በሚስስ ስሚዝ የሹመት ስየማ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ አለኝ፡፡

እ.ኤ.አ ግንቦት 12/2015 “ሴኔቱ የጋይሌ ስሚዝን የሹመት ስየማ እንዳያጸድቀው“ በሚል ርዕስ የተቃውሞ ጽሑፍ አቅርቤ ነበር፡፡

ሚስስ ስሚዝ ለስራ መደቡ የተሳሳተ ምርጫ ናት ብዬ አምናለሁ፡፡

በተለይም የሚስስ ስሚዝን ሹመት መጽደቅ በሚከተሉት ምክንያቶች እቃወማለሁ፡

1ኛ) በአፍሪካ በዴሞክራሲ፣ በነጻነት እና በሰብአዊ መብት ጥበቃ መስፋፋት እና ድጋፍ ላይ ያላት ደካማነት፣

2ኛ) ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ለአፍሪካ አምባገነን መሪዎች ስታሳየው የቆየችው ያልተቆጠበ ድጋፍ መስተዋሉ፣

3ኛ) አፍሪካውያን የደህንነት ዋስትና ተቀባይ ሆነው ከአሜሪካ ግብር ካፋይ ህዝብ ጋር እጅ ከወርች በመታሰር ተቆራኝተው ቀጣይነት ባለው መንገድ ጥገኛ ሆነው እንዲኖሩ እያራመደችው ባለው የተሳሳተ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አመለካከቷ ምክንያት የሚሉት ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ሚስስ ስሚዝ አፍሪካውያን በአሜሪካ ግብር ከፋዮች ቸርነት እና ለጋስነት ምክንያት ለደህንነታቸው ዋስትና የሚያገኙ፣ የልመና እርዳታ የሚቀበሉ እና ምጽዋት የሚቸራቸው ህዝቦች ናቸው በማለት የእራሷን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በጥገኝነት ላይ ጣራ እና ማገር አድርጋ በማዋቀር ሆኖም ግን አፍሪካውያን ወገኖቻችንን ለእድገት የሚያበቁ እና በሰው ልጆች እኩልነት ላይ ያነጣጠሩ ጓዳዊ የእድገት እና የልማት አጀንዳዎችን ወደ ጎን አሽቀንጥራ በማስወገድ አፍሪካውያን ለዘላለሙ ለጥገኝነት እና ለተመጽዋችነት ተዳርገው እንዲኖሩ ለማድረግ የምትንቀሳቀስ ትምክህተኛ ሰው ናት፡፡

በዩኤስኤአይዲ/USAID አማካኝነት በእርዳታ ስም በአፍሪካ በብዙ ቢሊዮን ከሚፈስሰው ዶላር የአሜሪካ ግብር ከፋይ ህዝብ ምን አገኘ?

በዩኤስኤአይዲ/USAID አማካኝነት በእርዳታ ስም በኢትዮጵያ በብዙ ቢሊዮን ከሚፈስሰው ዶላር የአሜሪካ ግብር ከፋይ ህዝብ ምን አገኘ?

ይህንን ጉዳይ ማንም ቢሆን በእርግጠኝነት አያውቀውም፡፡ እራሱ ዩኤስኤአይዲ/USAIDም ቢሆን!

እ.ኤ.አ በ2010 የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት መምሪያ ዋና ኦዲተር ጽ/ቤት /U.S. State Department Office of the Inspector General በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ምርመራውን በማካሄድ ከሚከተለው መደምደሚያ ላይ ደርሷል፣ “በዩኤስኤአይዲ የድርጊት ዕቅድ እና በአፈጻጸም ዘገባ መካከል ያለውን የኦዲት ውጤት ዘገባ ለመወሰን የሚያስችል ታማዕኒነት የሌለው ነው፣ ምክንያቱም የድርጅቱ ሰራተኞች ተገኙ ያሏቸውን ውጤቶች እንዴት እንደተገኙ ለመግለጽ አልቻሉም ወይም ተገኙ ለሚሏቸው ውጤቶችም ድጋፍ መስጠት አልቻሉም፡፡“ የዩኤስኤአይዲ ኢትዮጵያ የግብርናው ዘርፍ የምርታማነት ተግባራት (የኦዲት ዘገባ ቁጥር 4 -6663-10-003-P፣ መጋቢት 30/2010፣ ገጽ 1፡፡)

እ.ኤ.አ በ2014 የዋና ኦዲተር ተቆጣጣሪ ድርጅቱ በኢትዮጵያ የዩኤስኤአይዲ የኤች አይቪ ፕሮጀክት አፈጻጸም በጣም የዘገየ እና ከፍተኛ የሆነ የዕቅድ ዝግጅት ጉድለት የተንጸባረቀበት፣ ጥሩ ዕይታ ያልተስተዋለበት እና ምንም ዓይነት የጥራት ቁጥጥር ክትትል ያልተካሄደበት ነበር የሚል ድምዳሜ ሰጥቷል፡፡ (የዩኤስኤአይዲ ኢትዮጵያ ኤች አይቪ ክብካቤ እና ሕክምና እንቅስቃሴ አፈጻጸም፣ የኦዲት ዘገባ ቁጥር 4- 663-14-006-P፣ ግንቦት 23/2014፡፡)

በአንድ በዩኤስኤአይዲ የገንዘብ እርዳታ በሚተዳደር ሆስፒታል የዋና ኦዲተር ተቆጣጣሪ ድርጅቱ (በፎቶ ግራፍ በተደገፈ መልኩ) ዓይጦች እየበሉት እና እያበላሹት የሚገኝ በርካታ የአልሚ ምግብ ካርቶኖችን በመጋዘን ውስጥ አግኝቷል፡፡ በምግብ ማከማቻ መጋዘኑ በሁለቱም ክፍሎች ውስጥ የዓይጥ ትራፊ የወዳደቁ ምግቦች ታይተዋል፡፡ የመጋዝኑ ክፍሎች የፍሳሽ ውርዘት ያለባቸው እና የቆሸሹ ነበሩ፡፡ አንደኛው ክፍል መስኮት የለውም፣ ወይም ደግሞ ብርሀን የለውም፣ ሌላኛው ክፍል ደግሞ ፍሳሽ የሚያንጠባጥብ ጣራ ነበረው (ገጽ 12፡፡)

እንደ ግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ/Global Financial Integrity/GFI ዘገባ “የነፍስ ወከፍ ገቢዋ 365 ዶላር ብቻ የሆነው ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ2000 – 2009 በነበሩት ዓመታት ውስጥ በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ምክንያት ከአሜሪካ ግብር ከፋይ ህዝብ የተሰበሰበው እና በዩኤስኤአይዲ አማካይነት፣ በሙስና በተዘፈቁት የኢትዮጵያ ገዥዎች እና በውጭ ሀገር በሚገኙ የጥቅም ተካፋይ የጥቅም ተጋሪ ባንኮቻቸው አማካይነት 11.7 ቢሊዮን ዶላር አጥታለች፡፡“

GFI እንዲህ የሚል መደምደሚያ ሰጥቷል፣ “የኢትዮጵያ ህዝብ ደሙ እስኪደርቅ ድረስ እንዲመጠጥ ተደርጓል፡፡ ከአስከፊ እጦት እና ድህነት ለመውጣት በሚል ኢትዮጵያውያን ያለ የሌለ ጥረታቸውን እያደረጉ የሚገኙ ቢሆንም ቅሉ አሁን እየተደረገ ባለው ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ምክንያት በወንዙ ወደላይ አቅጣጫ በመዋኘት ላይ ይገኛሉ፡፡“

ወደታች ነው እንጅ ዉኃ አወራረዱ፣

ሽቅብ ሽቅብ አለኝ እኔንስ ለጉዱ፣ እንዲሉ መሆኑ ነው!

የሚስስ ስሚዝ ሹመት የሚጸድቅላት ከሆነ የሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውሩ በኢትዮጵያ አደገኛ የሆነ ኪንታሮት/hemorrhage እና የሱናሜ ማዕበል ይሆናል! የሚስስ ስሚዝ ሹመት የሚጸድቅላት ከሆነ ያለኮርቻ መደላድል የሚጋለብ አስቸጋሪ የፈረስ ሩጫ ይሆናል!

ቀላል በሆነ አባባል ግልጽ ለማድረግ የኦዲት ምርመራ ቡድን በሰጠው መደምደሚያ ዩኤስኤአይዲ የተባለው ድርጅት ሊመለስ በማይችል መልኩ በኢትዮጵያ እስከ አፍንጫው በሙስና ተዘፍቆ ከሚገኘው ገዥ አካል ጋር እጅ እና ጓንት ሆኖ በመስራት እና እንደተሞላ ሰዓት ጸጥ ብሎ በመተኛት ወይም ደግሞ እንደ ውኃ ቧንቧ መቆጣጠሪያ ፎሴት ሆኖ በመቀመጥ ልበለው፣ የአሜሪካንን ግብር ከፋይ ህዝብ ዶላር ከአሜሪካ ኪሶች በማውጣት በቀጥታ በሙስና ወደተዘፈቀው ገዥ አካል ባለስልጣኖች እና ለእርሱ አገልጋይ ሎሌ ኮንትራክተሮች ኪሶች በመክተት በህዝብ ስም የመጣውን ገንዘብ ለግል መጠቀሚያ ያደርጉታል፡፡

ሚስስ ስሚዝ የዩኤስኤአይዲ/USAID አስተዳዳሪ እንድትሆን ሹመቷ የሚጸድቅ ከሆነ የዩኤስኤአይዲ ሙስና በኢትዮጵያ በነበረው መሰረት እንዲቀጥል መፍቀድ ይሆናል፡፡

የዩኤስኤአይዲ ሙስና በኢትዮጵያ በነበረው መሰረት እንዲቀጥል መፍቀድ ማለት በኢትዮጵያ ላሉ ገዥዎች “የለማኞች ፌሽታ“ ይሆናል፡፡

አዩ ሴናተር ክሩዝ! ሚስስ ስሚዝ ለበርካታ አስርት ዓመታት ለአፍሪካ አምባገነኖች መደበቂያ ጓደኛ ዋና ዋሻ ሆና ቆይታለች፡፡

አሁንም ቢሆን ሚስስ ስሚዝ በአፍሪካ የሚገኙ ጥቂት ጨካኝ አረመኔ አገዛዞችን በመደገፉ ረገድ ሰም እና ወርቅ ሆና ትቀጥላለች፡፡

ሚስስ ስሚዝ እራሱ መርጦ ባቋቋመው የምርመራ አጣሪ ኮሚሽን በሰው ልጆች ላይ እልቂትን የፈጸመ ለመሆኑ ለተረጋገጠበት እና አሁን በህይወት ለሌለው ደም ለጠማው እና ለአረመኔው መለስ ዜናዊ ቀንደኛ ደጋፊ ነበረች፡፡

ሚስስ ስሚዝ እ.ኤ.አ በ1980ቹ አጋማሽ እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እያለ ለሚጠራው ወሮበላ አማጺ ድርጅት ተቀጣሪ ሠራተኛ ሆና ትሰራ የነበሩበት እውነታ በጥቂቱ ነው የሚታወቀው፡፡

እ.ኤ.አ ግንቦት 1991 ክርስቲያን ሳይንስ ሞኒተር የተባለው ድርጅት እንዳወጣው ዘገባ ከሆነ ሚስስ ስሚዝን በሚመለከት እንዲህ የሚል እውነታን ይፋ አድርጎ ነበር፣ “ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ያህል ከዜናዊ ጋር በርካታ ግንኙነት ካላቸው የምዕራብ ሀገሮች ትግርኛ ተናጋሪዎች መካከል ለማህበረ ረድኤት ትግራይ (ማረት)/Relief Society of Tigray (REST) እየታበለ ለሚጠራው ድርጅት የቅጥር ሰራተኛ ሆና እ.ኤ.አ በ1985-6 ተከስቶ በነበረው ድርቅ ስትሰራ የነበረችው አሜሪካዊት ጋይሌ ስሚዝ ናት፡፡“

ሚስስ ስሚዝ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያን እያተራመሰ እና አሳር ፍዳዋን እያሳዬ በመግዛት ላይ ለሚገኘው ወሮበላ የአማጺ ቡድን ዋና ሽርክ እና የደመወዝ ቅጥረኛም ሆና ይህንን ዘረኛ እና የሞራል ስብዕና የሌለውን ከፋፋይ እና በታኝ ድርጅት ስታገለግል  የነበረች ሸፍጠኛ ሴት ናት፡፡

ስሚዝ የአምባገነኑ መለስ ዜናዊ ዋና ጠበቃ እና የአስተሳሰቡ ሎሌ በመሆን ተሟጋች ነበረች፡፡ በአሁኑ ጊዜም የወያኔ ተከላካይ እና ዋና ጠባቂ ዘብ ናት፡፡

በተጻራሪ መልኩ የሚያስገርመው ነገር ደግሞ ከበርካታ አስርት ዓመታት በፊት ሚስስ ስሚዝን ቀጥሮ ሲያሰራት የነበረው ወያኔ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በመግዛት ላይ ያለው እና ስሙ በዓለም አቀፍ አሸባሪዎች የመረጃ ቋት ዝርዝር ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው ወሮበላ የማፊያ ድርጅት ስብስብ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡

እውነታው ፍርጥርጥ ብሎ ሲታይ ግን ሚስስ ስሚዝ እስከ አንገቱ በማርክሲዝም የርዕየት ዓለም ፍልስፍና ውስጥ ሰምጦ የነበረውን እና በአሁኑ ወቅት በህይወት የሌለውን መለስ ዜናዊን እና የእርሱን የወያኔ ተከታይ ሎሌዎቹን ርዕዮት ዓለሞች ምንም ዓይነት ጉዳት የማያመጡ ለስላሶች ናቸው በማለት ሰብአዊ መልክ ለማስያዝ እያደረገቸው ያለው የሸፍጥ ድርጊት ነው፡፡

ሚስስ ስሚዝ የመለስ ዜናዊን አስፈሪ ስር ነቀል መግለጫዎች “የግራ ዘመም አማጺ ድርጅት ቋንቋ ነው“ በማለት ደካማ የሆነ አመክንዮዋን ታቀርባለች፡፡

ሚስስ ስሚዝ ከዚህም በማለፍ ዜናዊ ምክንያታዊ የሆነ የሊበራል ዴሞክራት እና  “ሰፊ መሰረት ያለው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችን ያካተተ ጥምረት ብቻ ነው ኢትዮጵያን ማስተዳደር የሚችለው“ በማለት ቀለም ለመቀበት ጥረት ታደርጋለች፡፡

ሚስስ ስሚዝ ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ በስልጣን ማማ ላይ ተኮፍሶ አስፈሪ በሆነ መልኩ የሰብአዊ መብቶችን ሲደፈጥጥ ለቆየው እና መጥፎ ሪከርድ ላስመዘገበው አምባገነን ገዥ ቡድን ጋሻ እና መከታ በመሆን ስትከላከል ቆይታለች፡፡

እውነታዎች በእራሳቸው ይናገራሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ2003 የሚስስ ስሚዝ የቀድሞ ጓዳኛ የሆነው እና አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ በምዕራብ ኢትዮጵያ በጋምቤላ ከተማ ከ400 በላይ የሆኑ ሰላማዊ ዜጎች በመንደሮቻቸው ላይ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮችን በማዝመት እንዲያልቁ አድርጓል፡፡

ሚስስ ስሚዝ ጓደኛዋ የነበረው አረመኔው እና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ እንደዚህ ያለ አስፈሪ እና አስቀያሚ ሰብአዊ እልቂት ሲፈጽም አላየሁም፣ አልሰማሁም የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ በማለት ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ጸጥ ብላ ተመልክታዋለች፡፡

እ.ኤ.አ በ2005 መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ተካሂዶ የነበረውን የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ ውዝግብ ተከትሎ ተከስቶ በነበረው ብጥብጥ ምርጫው በቀን ብርሀን መዘረፉን በመመልከት ያላቸውን ተቃውሞ ሰላማዊ በሆነ መልኩ በአደባባይ በመውጣት ለኢትዮጵያ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለመግለጽ በሞከሩበት ጊዜ ጨፍጫፊው እና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ አግዓዚ የተባለውን ቅጥር ነፍሰ ገዳይ ወሮበላ ቡድን በአዲስ አበባ ከተማ በማሰማራት ወደ 200 አካባቢ የሚጠጉ መሳሪያ ያልያዙ ሰላማዊ ወገኖቻችን በጥይት እየተደበደቡ እንዲያልቁ እንዲሁም 800 የሚሆኑት ደግሞ ቁስለኛ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡

ሚስስ ስሚዝ በጠራራ ጸሐይ በአደባባይ ይህን የመሰለ አሰቃቂ እልቂት በወገኖቻችን ላይ ሲፈጸም እነዚያ የግፍ ሰለባ የሆኑ ወገኖቻችን እንደተቀበሩበት የቀብር ቦታ ሁሉ ጸጥ ዝም በማለት የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ በማለት ቆይታች፡፡

የተከበሩ ሴናተር ክሩዝ፣ እ.ኤ.አ በ2005 በኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ላይ የደረሰው አሰቃቂ እና አሳፋሪ እልቂት በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ተሟጋችነት ዘው ብዬ እንድገባ እና በእልህ ፍትህ እውነታውን እስክትፈርድ ድረስ በጽናት ለመታገል አንድ የታሪክ አጋጣሚ ፈጥሮልኛል፡፡

በአንድ ጀምበር በአንዲት የእጅ መደጋፊያ ባላት የአካዳሚክ ወንበር ተቀምጨ የአካዳሚክ ስራን ብቻ ከምሰራበት ሙያ በተጨማሪ ሊበገር የማይችል በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋችነት እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ገብቸ እስከ አሁን ድረስ በመታገል ላይ እገኛለሁ፡፡

ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በጣም ረዣዥም የሆኑ ትችቶችን (አንድም ሳምንት ሳላሳልፍ በየሳምነቱ በመጻፍ) አሁን በህይወት በሌለው በአምባገነኑ መለስ ዜናዊ ሲፈጸም የቆየውን የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ እና በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ቀጥሎ የሚገኘውን የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ በማቅረብ ላይ እገኛለሁ!

ሳቀርባቸው የቆዩት  ትችቶች

almariam.com  እና

http://www.huffingtonpost.com/alemayehu-g-mariam

በሚለው የግንኙነት ድረ ገጽ ይገኛሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ2007 አረመኔው እና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ምስራቃዊ ክፍል በኦጋዴን ክልል አካባቢ የእሩምታ ተኩስ በመክፈት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ወገኖቻችን እንዲያልቁ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ በኦጋዴን የተፈጸመው እልቂት የዘር ማጥፋት ተብሎ ተገልጿል፡፡

ሚስስ ስሚዝ በእርሷ ውድ ጓደኛ እና አሁን በህይወት በሌለው በአምባገነኑ እና በአረመኔው መለስ ዜናዊ ይህንን የመሰለ የሚዘገንን እልቂት በሰው ልጆች ላይ ሲፈጽም አሁንም አላየሁም፣ አልሰማሁም፣ የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ በማለት በጸጥታ አንድም ነገር ትንፍሽ ሳትል አልፋዋለች፡፡

እርስዎም እንደሚያውቁት እርግጠኛ ለሆንኩበት እና ሚስስ ስሚዝ ከአስርት ዓመታት በፊት የቅጥር ሰራተኛ ሆና ተቀጥራ ስትሰራበት የነበረው ህወሀት የተባለው ከፋፋይ እና እምነተቢስ ዘረኛ የፖለቲካ ፓርቲ በዚህ ባለፈው ግንቦት ወር ተደርጎ በነበረው የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ መቶ በመቶ በማሸነፍ የፓርላማ ወንበሮችን ተቆጣጠርኩ በማለት አወጀ፡፡

እ.ኤ.አ በ2010 ይኸው ተመሳሳይ ፓርቲ 99.6 በመቶ የሆነ ድምጽ በማግኘት አሸነፍኩ በማለት አውጆ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ በሀምሌ 2015 ፕሬዚዳንት ኦባማ ለዓለም ህዝብ እንዲህ በማለት አስደንጋጭ እና አስፈሪ የሆነ መልዕክት አስተላልፎ ነበር፣ “እ.ኤ.አ በ2015 መቶ በመቶ ያሸነፈው የኢትዮጵያ መንግስት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የተመረጠ መንግስት ነው፡፡“

ፕሬዚዳንቱ አዲስ አበባ በመሄድ ይህን የመሰለ የተፋለሰ መግለጫ ሲሰጥ ሚስስ ስሚዝ ከእርሱ ጎን ነበረች፡፡

ባለፉት ጥቂት ወራት ጥቂት የሚስስ ስሚዝ የግል ጓደኞች እና ተባባሪዎች እርሷን አንበሳ የሚያደርግ የሚያወድስ እና የሌላትን ስብዕና እንዳላት በማድረግ እንዲያውም የሰብአዊ መብት ተሟጋች እንደሆነች የሚያስመስል የሀሰት ጽሑፍ በመጻፍ አሰራጩ፡፡ የመጨረሻው እ.ኤአ. መስከረም 18/2015 “የጋይሌ ስሚዝን ሹመት የማጽደቂያ ጊዜው አሁን ነው“ በሚል ርዕስ ፅሁፍ ቀረበ፡፡

ይልቁንስ የጋይሌ ስሚዝ የሹመት ጥቆማ የሚወገድበት ጊዜው አሁን የሚል መልዕክት የያዘ ደብዳቤ ለኋይት ሀውስ ሊቀርብ ይገባል፡፡

በሌላ መድረክ ላይ ደግሞ የሚስስ ስሚዝን የሹመት ጥቆማ በመቃወም በማደርገው ጥረት ላይ ድጋፍ ለማግኘት በቂ የሆነ መረጃ አቅርቤ ነበር፡፡

ሴኔቱ የሚስስ ስሚዝን ሹመት የሚያጸድቅ ከሆነ በአሜሪካ ግብር ከፋይ ህዝቦች ገንዘብ ላይ ለአፍሪካ አምባገነኖች ሰርግ እና ምላሽ ነው የሚለውን ስጋት እንደገና ግልጽ ላድርገው፡፡

በጋይሌ ስሚዝ የዩኤስኤአይዲ ኃላፊ ሆና መመደብ ምክንያት የአፍሪካ አምባገነኖች የአሜሪካንን ግብር ከፋይ ህዝብ ደም ለመምጠጥ እጆቻቸውን የሻሻሉ፣ ለሀጫቸው በጃኬቶቻቸው ላይ ይንጠባጠባሉ፡፡ ጥንብ እንዳዬ ጅብ ይጠራራሉ፡፡

ዩኤስኤአይዲ/USAID ለአፍሪካ አምባገነኖች የመጋዘን ከረሜላ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ጋይ ስሚዝ ሹመቱን በምታገኝበት ጊዜ ዩኤስኤአይዲ/USAID ለአፍሪካ አምባገነኖች የቾኮሌት ፋብሪካ ይሆንላቸዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ2016 ዩኤስኤአይዲ/USAID ጠቅላላ በዓለም ላይ ሊሰራጭ የሚችል ወደ 22 ቢሊዮን ዶላር ይኖረዋል፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 25 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆነው ከአሜሪካ ግብር ከፋይ ህዝብ ኪስ የሚወጣው ገንዘብ የአፍሪካን አምባገነኖች ኪስ ለማድለብ የሚወጣ ገንዘብ ነው፡፡

የጋይሌ ስሚዝ ሹመት መጽደቅ ማለት በእርግጠኝነት አንድ ነገር ማለት ነው፡ ለአንድ ለአፍሪካ ህዝቦች መደህየት ክስተት መፈጠር እና ለአፍሪካ አምባገነኖች ግዙፍ የሆነ የገንዘብ ማግኛ እና ማካበቻ መድረክ የመፍጠር ክስተት ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሚስስ ስሚዝ በአሜሪካ ግብር ከፋይ ህዝብ ገንዘብ አፍሪካውያን ህይወታቸውን ዘለቄታዊ ባለው መንገድ መቀየር ይችላሉ ስለምትለው እምነቷ የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን ላሰምርበት እፈልጋለሁ፡፡

ሚስስ ስሚዝ ለአፍሪካ ስለሚመጣው የአሜሪካ ህዝብ ግብር ከፋይ ዶላር ያላት አመለካከት የተሳሳተ ነው፡፡

የአፍሪካ ፖሊሲ ተንታኝ ከሆኑት መካከል በጣም ክብር ያላቸው ዳምቢሶ ሞዮ በሚያሳምን  መልኩ እንዳቀረቡት እና እንዳመላከቱት “ይኸ ሸፍጥ የተቀላቀለበት የእርዳታ ባህል የአፍሪካን ሀገሮች በእዳ እንዲዘፈቁ ያደረገ፣ ከፍተኛ በሆነ የዋጋ ግሽበት እንዲሰቃዩ ያመቻቸ፣ በገንዘብ ልውውጥ ገበያው ላይ ተለዋዋጭነትን እና አደገኛ ሁኔታን የፈጠረ እና ጥራት ያለው እና የሚስብ ኢንቨስትመንት እንዳይፈጠር ያደረገ ክስተት ነው” ብለዋል፡፡

ምጽዋት ወይም ደግሞ በተሳሳተ መንገድ የደህንነት ዋስትና ክፍያዎችን በመቀበል ከድህነት ያመለጠ ማንም የለም፡፡

በአሁኑ ጊዜ ዩኤስኤአይዲ/USAID የሚፈልገው አምባገነኖችን ወይም ደግሞ የአፍሪካን ጠንካራ ሰዎች ለመፍጠር መሆን የለበትም፡፡

ዩኤስኤአይዲ/USAID ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ጀልባውን የሚዘውሩት እጆች በጽናት እንዲንቀሳቀሱ ይፈልጋል፡፡

ጋይሌ ስሚዝ የአፍሪካ አምባገነኖች እጆች እና ጣቶች በአሜሪካ ግብር ከፋዮች ገንዘብ ላይ ቢሆንም እንኳ በጀልባው ላይ ያለ አንቀሳቃሽ እጅ አይደለችም፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የዩኤስኤአይዲ/USAID የልማት ፕሮግራሞች እየተስፋፋ በመጣው የሙስና ወንጀል፣ ብክነት እና ዘረፋ አስከፊ ሁኔታ እየተመታ ለመሆኑ እንደምትገነዘበው ጥርጥር የለውም፡፡

የዎል ስትሪት መጽሄት ግኝት ግልጽ እንዳደረገው ዩኤስ አሜሪካ እ.ኤ.አ ከ2002 እስከ 2012 ባሉት ዓመታት ውስጥ ለአፍሪካ ከሰጡት የእርዳታ ገንዘብ ውስጥ በርካታው የተመደበው ለጤና ፕሮጀክቶች ማለትም ለወባ በሽታ መከላከያ እና ለኤች አይቪ መቆጣጠሪያ ቢሆንም ቅሉ ከፊሉ በተሳሰሩ መረቦች የውንብድና አሰራር መሰረት ብዛት ያለው የወባ መከላከያ መድኃኒት በአቋራጭ እንዲዘረፍ ሆኖ ከምስራቅ ወደ ምዕራብ አፍሪካ በመርከብ እንዲጓጓዝ ተደርጎ በመንገድ ገበያዎች ላይ እየተቸበቸበ ወደ ዘራፊዎች ኪስ እንዲገባ ነው የተደረገው፡፡

የዋናው ኦዲተር ልዩ ጽ/ቤት እ.ኤ.አ በ2013 ለአፍጋኒስታን መልሶ ግንባታ ስለለተመደበው በመቶ ሚሊዮን ዶላር የአሜሪካ ግብር ከፋይ ህዝብ ገንዘብ ውጤታማ የሆነ ምልከታ እና ክትትል ባለመደረጉ ምክንያት ለብክነት፣ ለሙስና እና ለምዝበራ አደጋ ተጋልጦ እንደነበር በምርመራ ግኝቱ አረጋግጦ ነበር፡፡

ዩኤስኤአይዲ/USAID ጥንካሬ በሌለው ሽባ አመራር ቁጥጥር ስር መውደቅን አይፈልግም፡፡

ዩኤስኤአይዲ/USAID ከፍተኛ ትኩረትን የሚፈልጉ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ከዚህ ቀደም በተጨባጭ ተሞክሮ በተረጋገጠ ጠንካራ የሆነ ስምምነት በተደረሰበት መንገድ መመራት እንዳለበት ይፈልጋል፡፡

ዩኤስኤአይዲ/USAID በአፍሪካ ማረሻ እና ማጭድ በመያዝ ልማትን ሊያመጣ ራዕይ ያለው መሪ ትፈልጋለች እንጅ በእጆቹ ሙሉ የመለመኛ አኩፋዳውን ይዞ የአሜሪካንን ግብር ከፋይ ገንዘብ ዶላር ለማግኘት ሲውተረተር የሚውለውን አውደልዳይ እና መሰሪ ሌባ አትፈልግም፡፡

ዩኤስኤአይዲ/USAID ቤቱን የሚያጸዳ እንጅ በቆሸሸው ቤት ውስጥ የሚቀመጠውን ስራ ፈት መሪ አይፈልግም፡፡

ዩኤስኤአይዲ/USAID ቆሻሻውን የሚያጸዳ መሪ እንጅ ቆሻሻውን የሚደብቅ አስመሳይ እና ሸፍጠኛ መሪ አይፈልግም፡፡

ዩኤስኤአይዲ/USAID ለአፍሪካ አምባገነኖች ደህንነት የሚውልን ፕሮግራም አይፈልግም፡፡

ዩኤስኤአይዲ/USAID ሙስናን፣ ብክነትን እና ስልጣንን ከሕግ አግባብ ውጭ ለግል ጥቅም በዩኤስኤአይዲ/USAID የሚያውለውን የሚያስወግድ ችሎታ እና ብቃት ያለውን መሪ ይፈልጋል፡፡

የሚስስ ስሚዝ የጥቆማ ሹመት የሚጸድቅ ከሆነ በቢሊዮኖች ዶላር የሚቆጠረውን በአፍሪካ የዩኤስ አሜሪካንን ገንዘብ አስተዳደር በአንክሮ እንድትከታተለው በእርሷ ላይ ክትትል ሊደረግባት ያስፈልጋል፡፡

የሚስስ ስሚዝ ከአፍሪካ አምባገነኖች ጋር ያላት ረዥም እና ጓዳዊ ግንኙነት እርሷን ጠንካራ የሆነ የሰብአዊ መብት ተሟጋች፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበር የምታታገል እና በአህጉሩ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ጥረት የምታደርግ አያደርጋትም፡፡

ሚስስ ስሚዝ ለአፍሪካ ለማኝ አምባገነኖች ከአምላክ የተላከች መልዓክ ናት፡፡

ፕሬዚዳንት ኦባማ ሁልጊዜ ከታራክ በስተቀኝ በኩል የሚል ተመሳስሎ ይናገራል፡፡

ሚስስ ስሚዝ በተሳሳተው የታሪክ ጎን የቆመች ናት፣ ስሚዝ ሁልጊዜ ከአፍሪካ አምባገኖች እና ጠንካራ ሰዎች ጎን ነው የምትሰለፈው፡፡

ፕሬዚዳንት ኦባማ ሚስስ ስሚዝ የዩኤስኤአይዲ/USAID አስተዳዳሪ እንድትሆን የሴኔቱን ምክር እና ስምምነት ይጠይቃል፡፡

ሴኔቱ የስሚዝን ሹመት ያለመቀበል እና ከታሪክ በስተቀኝ በኩል የቆመን፣ ለሕግ የበላይነት መስፈን የሚታገልን፣ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በጽናት የሚታገልን እና ለሰብአዊ መብቶች መከበር በቁርጠኝነት የተሰለፈን ትክክለኛ ተጠቋሚ ሰው የማቅረቢያ ጊዜው አሁን ነው፡፡

ከአምባገነኖች፣ ከጠንካራ ሰዎች እና በጠብመንጃ አፈሙዝ ስልጣን ከሚቆናጠጡ ዘራፊዎች ጎን የሚቆምን ተጠቋሚ ሹመኛ ጥቆማን አሽቀንጥሮ በመጣል ያለመቀበል ጊዜው አሁን ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ሴኔቱ ሚስስ ስሚዝን ለአፍሪካ ለዩኤስኤአይዲ/USAID አስተዳዳሪ አድርጎ ማጽደቅ እና መሾም የነጻነትን፣ የዴሞክራሲን እና የሰብአዊ መብት ጥበቃን ሰዓት ወደኋላ ከማሽከርከር ጋር መሳ ለመሳ ነው፡፡

እ.ኤ.አ ሀምሌ 16/2015 ለፕሬዚዳንት ኦባማ ካቀረቡት ደብዳቤ ቃልኪዳን ጋር ጽኑ ሆነው ሊዘልቁ እንደሚችሉ እና የሚስስ ስሚዝ ሹመት በሴኔቱ እንዳይጸድቅ እንደሚያሳግዱ እምነት የጣልኩበዎት መሆኔን ልገልጽልዎት እፈልጋለሁ፡፡

ከሠላምታ ጋር፣

ዓለማየሁ (ሰል) ማሪያም፣ ፒኤች ዲ.፣ ጀ.ዲ

የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር እና የሕግ ጠበቃ

የፖለቲካ ሳይንስ መምሪያ

ካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ፣ ሳን በርናርዲኖ

ሳን በርናርዲኖ፣ ሲኤ 92402

 

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

መስከረም 10 ቀን 2008 .

Similar Posts