ኢትዮጵያውያን ጦማርያን በዝንጀሮ ችሎት፣
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
ባለፈው ሳምንት በጥቅል ስማቸው “የዞን 9 ጦማሪያን” (ከዋና መዲናይቱ እምብርት በስተደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ከሚገኛው እና ንጹሀን ዜጎችን በማሰቃየት በአስከፊነቱ ከሚታወቀው ከአምባገነኑ የመለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት 8ኛ ህንጻ/Block ቀጥሎ የተገነባው ህንጻ) እየተባሉ የሚጠሩት ወጣት ኢትዮጵያውያን ጦማሪያን እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2014 በቁጥጥር ስር ከዋሉበት ጊዜ ጀምሮ ለ33ኛ ጊዜ እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እያለ ለሚጠራው ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ስርዓት የዝንጀሮው ፍርድ ቤት ችሎት ቀርበው ነበር፡፡
(ፖሊስ በጥርጣሬ የሚታይን ሰው በቁጥጥር ስር በማዋል እና በወንጀል የተጠረጠረን ሰው በእስር ቤት ካሰረ በኋላ ተጠርጣሪው ፈጽሟቸዋል ለተባሉት የውንጀላ ጥፋቶች መረጃዎችን ለመፈለግ እና ለማሰባሰብ በሚል ከሕግ አግባብ ውጭ ለሆነ ድርጊት ለወራት ከዚያም አልፎ ለዓመታት በእስር ቤት በማማቀቅ የሚያቆይ ሀገር አለ ከተባለ ብቸኛይቱ ሀገር ኢትዮጵያ ናት!)
“የዘገዬ ፍርድ እንደተነፈገ ይቆጠራል፡፡” ለ33 ጊዜ የተንዛዛ የችሎት የጊዜ ቀጠሮ በመስጠት የዘገዬ ፍርድ 33 ጊዜ ፍትሕ እንደተነፈገ ይቆጠራል፡፡
ወጣት ጦማሪያኑ ለፍትህ አካል ከመቅረባቸው በፊት ለበርካታ ጊዚያት በእስር ቤት ታጉረው እየማቀቁ፣ ዋስትና ተከልክለው፣ ውጤታማ የሆነ የሕግ የምክር አገልግሎት እንዳያገኙ ተነፍገው፣ ፈጣን የሆነ የፍትሕ አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸው፣ ከአድልኦ የጸዳ እውነት አፈላላጊ አካል አለመመደብ እና ለ33 ጊዜ የተንዛዛ የችሎት የጊዜ ቀጠሮ መስጠት በፍትሕ አካል ላይ እንደመቀለድ እና እንደተነፈገ ፍትሕ ይቆጠራል፡፡
ባለፈው ሐምሌ 2015 ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኝ በመገመት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ሁለት ጦማሪያንን እና ሶስት ጋዜጠኞችን ከማጎሪያው እስር ቤት ባልተሰበ እና ባልተጠበቀ ሁኔታ ለቋቸዋል፡፡ ለማድለብ እንደተዘጋጀ ሰንጋ ሲፈልግ የሚያስር ሲፈልግ የሚፈታ እንደዚህ ያለ አምባገነን ስርዓት በኢትዮጵያ ካልሆነ ሌላ በየትኛው ሀገር ይገኛል!
እ.ኤ.አ ከ2006 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ስለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ስርዓት የዝንጀሮ ፍርድ ቤት ትችቶችን ስጽፍ እና ሳቀርብ ቆይቻለሁ፡፡
“የዘበት ፖሊሶች፣ አቃቤ ሕጎች እና ዳኞች ሚና በፖሊስ መንግስት” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ ታህሳስ 2006 የመጀመሪያውን ትችቴን አቅርቤ ነበር፡፡ ያ ትችት እ.ኤ.አ የ2005 ሀገር አቀፍ ምርጫን ተከትሎ ተከስቶ በነበረው ሁከት ሳቢያ በአሁኑ ጊዜ በህይወት በሌለው በአምባገነኑ በመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ በቃሊቲ የማጎሪያ እስር ቤት ታስረው በነበሩት “የቃላቲ ተከላካዮች” (የተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎች) ላይ እየተካሄደ ባለው የችሎት ሂደት ላይ ምርመራ የሚያደርግ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ ታህሳስ 2007 “የጦጣ የፍትሕ ችሎት በዝንጀሮው ፍርድ ቤት“ በሚል ርዕስ በዚያን ጊዜ የአክሽን ኤይድ ዓለም አቀፍ በኢትዮጵያ ማኔጀር/Manager of Action Aid International in Ethiopia በነበሩትና በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ዴስክ ዋና ክፍል ኃላፊ /Executive Director of the African Division of Human Rights Watch ሆነው ባማገልገል ላይ ባሉት በአቶ ዳንኤል በቀለ እና የማሕበራዊ ፍትሕ በኢትዮጵያ ድርጅት/Organization for Social Justice in Ethiopia መሰራች እና አመራር ሰጭ በነበሩት በአቶ ነጻነት ደምሴ ላይ ላይ ተመስርቶ የነበረውን የፍትሕ ሂደት የሚመረምር ትችት አቅርቤ ነበር፡፡ የእነርሱን የፍትሕ ሂደት የፍራንዝ ካፍካን የፍርድ ሂደት ከሚዘግበው የጆሴፍ ኬ.ን አስቀያሚ እና ተስፋ አስቆራጭ ልብወለድ የፍትሕ ታሪክ ጋር በማነጻጸር አቅርቤ ነበር፡፡
ለበርካታ ዓመታት ስለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የተሰበጣጠረ መንግስት እና በአብዛኛው ግን በውጭ የገንዘብ ድጋፍ እርዳታ ላይ ተንጠልጥሎ ስለሚገኘው አምባገነን ስርዓት እንዲሁም ስለዝንጀሮው የፍርድ ስርዓቱ ብዙ ትችቶችን ስጽፍ ቆይቻለሁ፡፡
እ.ኤ.አ ሰኔ 2014 “የኢትዮጵያን ጦማሪያን ማን ይፈራቸዋል?“ በሚል ርዕስ በዞን 9 ጦማሪያን ላይ እየተፈጸመ ያለውን የሕግ ሸፍጥ የሚያጋልጥ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን የይስሙላ ኢፍትሐዊ ስርዓት ለመግለጽ ከተንኮል በመነጫ ሳይሆን ከገለጻ ትክክለኛነት ፍላጎት አንጻር የዝንጀሮ እና የጦጣ ፍርድ ቤት የሚሉ ተመሳስሎዎችን እጠቀማለሁ፡፡
“የዝንጀሮ (ካንጋሮ ) ፍርድ ቤት” የሚለው ሀረግ የአውስትራሊያ አጥቢ እንስሳት ከሆኑት ማርሱፒያል ካንጋሮዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም፡፡
ይህ ሀረግ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በምዕራብ አሜሪካ እራሳቸውን የሾሙ የሸፍጥ፣ ሀፍረተቢስ እና አታላይ የፍትሕ ሂደትን ያራምዱ የነበሩ ሰዎችን ለመግለጽ በስራ ላይ የዋለ ነው እየተባለ ይነገርለታል፡፡
ይህ ሀረግ አብዛኛውን ጊዜ ከሚከተሉት ጋር አንድ ዓይነት ትርጉም እንዳለው ሆኖ ሲገለጽ ቆይቷል፣
1ኛ) የሕግ እና የፍትሕ መርሆዎች ወደ ጎን የተጣሉበት ወይም ደግሞ የተዛቡበት አስመሳይ የፍርድ ችሎት፣
2ኛ) ዓይን ባወጣ መልኩ እና ሆን ብሎ ታስቦበት ዕውቅና ያላቸውን የሕግ ወይም ደግሞ የፍትህ መርሆዎችን እና መስፈርቶችን ወደ ጎን ገሸሽ አድርጎ መተው፣
3ኛ) የፍርድ ቤቱን ሕጋዊ ወይም ደግሞ የስነምግባር ግዴታዎችን ሆን ብሎ ወደ ጎን የሚተው ሕጋዊ የፍትሕ ስልጣን ያለው ፍርድ ቤት፣ እና
4ኛ) የፍርድ ውሳኔው በእርግጠኝነት የፍርድ ችሎቱ ሂደት ከመጀመሩ በፊት የተወሰነ እና የታወቀ ቢሆንም እንኳ “የፍርድ ሂደቱ ለሕዝብ ፍትሐዊ እና ትክክለኛ ቅርጽ ያለው እንዲመስል” እየተነበዬ የሚሰራ ፍርድ ቤት የሚሉት ናቸው፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የፍርድ ሂደት ስርዓት ከዚህ በላይ ከተገለጹት ሁሉም ትርጉሞች ጋር መሳ ለመሳ ነው፡፡
ይህ ሀረግ በዩናይትድ ስቴትስ የሕግ ታሪክ ውስጥ በጣም ጠቃሚ እንደምታ ካላቸው የወንጀል የሕገ መንግስት ጉዳዮች መካከል የእራሱን መንገድ አግኝቷል፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት “ፖሊሶች ጉዳዮችን በእራሳቸው እጆች የሚይዙበትን ሁኔታ፣ የጥቃት ሰለባዎችን የሚይዙበትን መንገድ፣ የጥቃት ሰለባዎች በግድ የእምነት ቃል እስኪሰጡ ድረስ የሚደበድቡበትን እና በኃይል የሚመቱበትን ጥንታዊ የሆኑ የሕግ ጉዳዮች አወገዘ፡፡ ክስ የቀረበበት ማንኛውም ሰው ጉዳዩ በይስሙላ የዝንጀሮ ፍርድ ቤት ሳይሆን ሕጋዊ በሆነ የፍትህ አካል የመታየት እና የመዳኘት መብት አለው፡፡”
እንግዲህ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የይስሙላ የዝንጀሮ ፍርድ ቤቶች ዋና መለያ ባህሪ ይኸው ነው፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ወሮበላ ዘራፊ ፖሊሶች በፖለቲካ ወንጀል የሚጠረጥሯቸውን ንጹሀን ዜጎች በፖለቲካ ኃላፊ ጌቶቻቸው ትዕዛዝ መሰረት በቁጥጥር ስር ያውላሉ፣ ጭካኔ በተመላበት ሁኔታ ድብደባ በመፈጸም በግድ የእምነት ቃል እንዲሰጡ ያደርጋሉ፣ ክስ ሳይመሰረት በእስር ቤት ታጉረው እንዲቆዩ ያደርጋሉ፣ የሕግ የምክር አገልግሎት እንዳያገኙ ያደርጋሉ፣ እንዲሁም በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የሚሾሙ ሸፍጠኞች የይስሙላ የፍርድ ሂደቱን እስከሚጀምሩ ድረስ እስረኞችን ከወዲያ ወዲህ እያመላለሱ ያሰቃያሉ፣ ፈጣን የሆነ የፍትሕ አገልግሎት እንዳያገኙ ያደርጋሉ፣ አይጦችና ቅማል ቱሃን ሌላም ተውሳክ በሚተራመሱበት እና ጽዳቱ ባልተጠበቀ ክፍል (በረት ማለቱ ይቀላላ) ውስጥ ለወራት ወይም ደግሞ ለዓመታት በእስራት እንዲማቅቁ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ሁሉ ህግን ያልተከተለ ድርጊት የሚፈጸመው ሸፍጠኛ የሆኑ እና ለርካሽ ጥቅም ሲሉ ለስርዓት ያጎበደዱ ዳኞች አቃብያነ ሕግ ተብዬዎች የቆሸሸ የስብዕና ድሪቶ መንፈሳቸውን በመጠቀም በንጹህን ተጠርጣሪዎች ላይ የሀሰት ማስረጃዎችን ፈብርከው እስከሚያጠናቅቁ ድረስ መጨረሻ የሌለው የጊዜ ቀጠሮ እየሰጡ እጅ እና ጓንት ሆነው ፍትህን በመደፍጠጥ በንጹሀን ዜጎች ላይ ደባን እና ሸፍጥን ስለሚሰሩ ነው፡፡
በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ፕላኔት (ዓለም) ላይ የይስሙላ የዝንጀሮ/የጦጣ ፍርድ ቤቶች ይኖራሉ፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ኢፍትሐዊ ስርዓት የዝንጀሮ/የካንጋሩ ችሎት በማለት ለትዮጵያውያን አንባቢዎቼ ተመሳስሏቸውን ለመግለጽ እጠቀማለሁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የዝንጀሮ የፍርድ ስርዓት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አመራሮች እና አባላት ተቀናቃኞቻቸውን ለማጥቂያነት የሚጠቀሙባቸው መሳሪያዎቻቸው መሆናቸውን ላሰምርበት እፈልጋለሁ፡፡
በዞን 9 ጦማሪያን የፍርድ ሂደት ላይ እንደዚህ ያለ የማስመሰል የፍትሕ ሸፍጥ እየተካሄደ በመሆኑ ምክንያት ነው በአሁኑ ጊዜ ዋና ዋና የሆኑት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እኩይ ድርጊቱን በማውገዝ ላይ የሚገኙት፡፡
በእርግጥ ከፖለቲካ እና ትክክለኛ ከመሆን አንጻር ማናቸውም ቢሆኑ ስርዓቱን የበቀል መወጫ መሳሪያ የዝንጀሮ ፍርድ ቤት ወይም ደግሞ የጦጣ ፍርድ ቤት ብለው ለመጥራት ድፍረቱ የላቸውም፡፡
ሆኖም ግን የዘንጀሮ/የጦጣ ፍርድ ቤት በየትኛውም በሌላ ስያሜ ቢሰየምም ያው የዝንጀሮ/ጦጣ ፍርድ ቤት ከመሆን የሚለየው ነገር በፍጹም የለም፡፡ በሌላ አባባል ለመቆንጀት ሲባል ፉንጋዋ ዓሳማ የከንፈር ቀለም ብትቀባም እንኳ በዕለቱ መጨረሻ የከንፈር ቀለሙ ያው ፉንጋ ዓሳማነቷን አይቀይረውም፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የዝንጀሮ/የጦጣን ፍርድ ቤት ስርዓት የፖለቲካ ተቀናቃኞቹን ለማጥቃት የሚጠቀምበት መሳሪያ ነው በማለት ገልጾታል፡፡ ሂዩማን ራይትስ ዎች የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ላይ እንዲህ በማለት ተቃውሞውን አቅርቦበታል፣ “ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም፡፡“
የጋዜጠኞች ተከላካይ ኮሚቴ (ጋተኮ) ሽብርተኝነትን ከጋዜጠኝነት ጋራ በማቀላቀል በመንግስት እየተደረገ ያለውን ሰላማዊ ዜጎችን የማሰቃየት የፍርድ ሂደቱን አውግዟል፡፡
ፍሪደም ሀውስ/Freedom House የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በጦማሪያን ላይ የተመሰረተው የክስ ጉዳይ በእውነታ ላይ ያልተመሰረተ ቅንነት የጎደለው ነው፣ መንግስት የግንቦቱ ምርጫ እየተቃረበ በሚመጣበት ወቅት በዴሞክራሲ ወትዋቾ ላይ ፖለቲካዊ እንደምታ ያለው የሀሰት ክስን በመፈብረክ ጥቃት በመሰንዘር ላይ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ይህንን ኢፍትሐዊ የሆነ ድርጊት ለማስቆም ለጋሽ ድርጅቶች በመንግስት ላይ ጫና በመፍጠር ድርጊቱን ማስቆም ይኖርባቸዋል ብሎ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ ጥር 2015 የአሜሪካ መንግስት መምሪያ በ6 ጦማሪያን እና በ3 ጋዜጠኞች ላይ በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የተሰጠው የፍርድ ውሳኔ ላይ የጸረ ሽብር አዋጁ እየተተገበረ መሆኑ አሳስቦኛል በማለት ስጋቱን ገልጾ ነበር፡፡
መምሪያው እንዲህ በማለት አውጆ ነበር፣ “ውሳኔው ነጻ እና ለሁሉም ክፍት የሆነ የሜዲያ ከባቢ አየር እንዳይሰፍን የሚያደርግ፣ እ.ኤ.አ ግንቦት 2015 በኢትዮጵያ ታማዕኒነት ያለው እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዳይካሄድ ያደርጋል፡፡“
እ.ኤ.አ ሰኔ 2015 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በግንቦት የተካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ መቶ በመቶ አሸንፊያለሁ በማለት አወጀ፡፡
እ.ኤ.አ ሀምሌ 2015 ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያ ከደረሰ በኋላ “በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠው የኢትዮጵያ መንግስት“ በማለት ስምምነቱን ገልጿል፡፡ (ኦባማ ይህንን ነገር የተናገረ የአታላይነቱን ጉብዝና ለማሳየት ፈልጎ ነውን?)
በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ፕላኔት ውስጥ የመጦመር ወንጀለኝነት፣
በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የዝንጀሮ/ጦጣ ፍርድ ቤት የሸፍጥ ክስ የተመሰረተባቸው ተከላካይ ጦማሪያን የሚከተሉትን ያካትታል፡ በፈቃዱ ኃይሉ ተጫኔ፣ ናትናኤል ፈለቀ አበራ፣ ማህሌት ፋንታሁን ተፈራ፣ አጥናፍ ብርሀኔ አያሌው፣ ዘላለም ክብረት ቤዛ፣ አቤል ዋቤላ ሱጌቦ፣ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ ግዛው፣ ኤዶም ካሳዬ ገላን፣ ተስፋለም ወልደዬስ አራጌ እና (በሌለበት የሸፍጥ ክስ የተመሰረተበት ሶሊያና ሽመልስ ገብረማርያም) ናቸው፡፡
ተከላካይ ጦማሪዎች በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ እና በወያኔ ጸረ ሽብር ሕጉ አዋጅ ቁጥር 652/2009 በሁለት ክሶች በአንድ ላይ ከስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
በአንደኛው ክስ “ዋና ወንጀለኞች” ወይም ደግሞ በወንጀለኛ ሕጉ አንቀጽ 32 በተራ ቁጥር 1 እና 2 ላይ የተጠቀሰውን በመተላለፍ ዋና ወንጀል የመፈጸም ሙከራ የሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
በሁለተኛው ክስ ላይ ደግሞ ተከላካዮቹ በወንወጀለኛ መቅጫ ሕጉ በአንቀጽ 27 በተራ ቁጥር (1 እና 2) የተጠቀሱትን በመተላለፍ (ወንጀል የመፈጸም ሙከራ)፣ በአንቀጽ 38 በተራ ቁጥር (1) በሕገ መንግስቱ ወይም ደግሞ በመንግስት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች የሚሉ ክሶች ተመስርተውባቸዋል፡፡
የውንጀላ ክሶቹ እንደማስረጃ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ገጾች ያሏቸውን የእምነት መግለጫዎች ፈርመዋል ተብሏል፡፡ የገጾቹ ብዛትም እንደተከላካዮቹ ፊርማ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡ በፈቃዱ ኃይሉ ተጫኔ (31 ገጾች)፣ ናትናኤል ፈለቀ አበራ (27 ገጾች)፣ ማህሌት ፋንታሁን ተፈራ (12 ገጾች)፣ አጥናፍ ብርሀኔ አያሌው (16 ገጾች)፣ ዘላለም ክብረት ቤዛ (16 ገጾች)፣ አቤል ዋቤላ ሱጌቦ (12 ገጾች)፣ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ ግዛው (13 ገጾች)፣ ኤዶም ካሳዬ ገላን (10 ገጾች) እና ተስፋለም ወልደዬስ አራጌ (13 ገጾች፣ እና በሌለበት ክስ የተመሰረተበት ሶሊያና ሽመልስ ገብረማርያም ናቸው፡፡)
ተከላካዮቹ በውንጀላ የእምነት ቃል እንዲሰጡ በሚደረግበት ጊዜ የሕግ ምክር አገልግሎት እንዳያገኙ ተከልክለዋል።
ለሕዝብ የህሊና ዳኝነት ክፍት ለማድረግ እንዲቻል በማሰብ በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የሸፍጥ ውንጀላ የተከሰሱት ጦማሪያን በዝርዝር እና የቀረቡባቸው የጽሁፍ እና የቁስ ማስረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡
1ኛ) በፈቃዱ ኃይሉ ተጫኔ፡ የተመሰረተበት ክስ “የሀገር ውስጥ የሚስጥር የሽብር ድርጅት ማቋቋም“ እና “ለአባላቱ ዕቅድ ማውጣት እና የሚከናወኑ ተግባሮችን እና ኃላፊነቶችን ለአባላቱ መመደብ“ የሚሉ ናቸው፡፡ በፍቃዱ መንግስትን በኃይል ለማስወገድ በማሰብ “የሳጥን ደህንነት ” እየተባሉ የሚጠሩትን ጽሁፎችን ወደ ኮድ የሚለውጡ መሳሪያዎችን እና የግንኙነት ስልጠናዎችን በመውሰድ ግንቦት 7 እየተባለ የሚጠራውን “አሸባሪ” ድርጅት ለማገዝ ስትራቴጂ በመንደፍ ድጋፍ አድርጓል የሚል ነው፡፡
በበፈቃዱ ላይ የቀረበው የሰነድ ማስረጃ የሚከተሉትን ያካትታል፡ 31 ገጽ የእምነት ቃል እና ከእራሱ ላፕቶፕ ኮምፒውተር እና ከቤቱ የተሰበሰበ መረጃ፡ “ለለውጥ ፈላጊዎች እና ለጀግኖች” በሚል ርዕስ የተጻፈ ጽሁፍ እና “ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ለትግራይ እንዴት ሕጋዊ እንደሆነ”፣ “80 ሚሊዮን እስከምንሆን ድረስ እንዋጋለን“፣ “እኛ ህብረት ከፈጠርን አምባገነኖች ምንድን ሊሆኑ ይችላሉ“፣ “በድረ ገጾች የሚለቀቁ ጽሁፎችን የመመርመር ዘመቻ ይቁም“፣ “ዋኤል ጎኒም ኢትዮጵያዊ ቢሆን ኖሮ የሚል (ከግብጽ ምዕናባዊ የኢንተርኔት አክቲቪስት ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ-18 ገጾች“፣ “የሲቪል ነጻነቶች ተሟጋቾች የስልጠና ሰነድ“፣ “መንግስት አለን? ወይም ደግሞ መንግስት የማን ነው? እና ምን ዓይነት ነው? -10 ገጾች“፣ “የኢሕአዴግ አባል ያልሆነ ዳኛ ይኖራልን?”፣ “የቴሌኮም የሸፍጥ ሕግ ሀሳብን የመግለጽ ነጻነትን ለመሸበብ የወጣ መሳሪያ – 12 ገጾች“፣ “የተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት እና የድረ ገጽ ዘመቻ ዕቅድ – 3 ገጾች“፣ እና “ለዘጋቢ ፊልም ዝግጅት በኢትዮጵያ ሀሳብን በነጻ በመግለጽ ሁኔታ ላይ ያተኮሩ በእጅ የተጻፉ ቃለመጠይቆች ዝርዝር“ በሚሉ የተለያዩ ርዕሶች የተዘጋጁ ጽሁፎች ናቸው፡፡
2ኛ) ናትናኤል ፈለቀ አበራ፡ የአሸባሪ ቡድኑ ዋና አቀነባባሪ የሚል የውንጀላ ክስ ተመስርቶበታል፡፡ “በሀገር ውስጥ የሚስጥር የሽብር ድርጅት ማቋቋም“ እና “ሁሉንም የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴዎች ማስተባበር“፣ “ናትናኤል ከግንቦት 7 ጋር በመተባበር ሕብረተሰቡ የአመጽ ድርጊት እንዲጀምር በርካታ ስልጠናዎችን ለመስጠት ተነሳሽነትን በማሳየት ማደራጀት፣ ሙሉ ተሳታፊ መሆን፣ ስራዎችን ሁሉ ማሳለጥ” የሚሉ ውንጀላዎች ቀርበውበታል፡፡
የጽሁፍ ማስረጃ ተብለው የቀረቡት የሚከተሉትን ያካትታል፡ የእምነት ቃል የተሰጠባቸው 27 ገጾች፣ “ከላፕቶፕ ኮምፒውተሩ የተሰበሰቡ እና ከኢሜይል ድረ ገጽ የወረዱ/download የተደረጉ ጽሁፎች“፣ ሌሎች ሰነዶች ማለትም በሚከተሉት ርዕሶች የተዘጋጁ፣ “ዋኤል ጎኒም ኢትዮጵያዊ ቢሆን ኖሮ የሚል (ከግብጽ ምዕናባዊ የኢንተርኔት አክቲቪስት ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ-18 ገጾች – በበፈቃዱ ኃይሉ የተጻፈ“፣ “ዳቦ እና ነጻነት በሚል፣ ለጽሁፍ ምርመራ ይቁም ዘመቻ የተጻፈ“፣ “የጽሁፍ ምርመራ ዋጋ – 8 ገጾች ጽሁፍ“፣ “አሁን በህይወት የሌለውን መለስ ዜናዊን የሚተች የግንቦት 7 ደብዳቤ – 4 ገጾች“፣ “ከቢዝነስ እና ኮንስትራክሽን ባንክ ገንዘብ የተቀበለበት ደረሰኝ“፣ “በኢንተርኔት የደህንነት ጉዳይን በማስመልከት ከሶሊያና ሽመልስ ፓስፖርት ጋር በተያያዘ የተደረገ የኢንተርኔት መልዕክት ልውውጥ – 26 ገጾች“፣ “ስለኢትዮጵያ በናትናኤል ፈለቀ በእጅ ጽሁፍ የተዘጋጀ ግጥም እና ከቤቱ የተሰበሰበ – 1 ገጽ“ በሚሉ ርዕሶች የተዘጋጁ ናቸው፡፡
3ኛ) ማህሌት ፋንታሁን ተፈራ፡ “የግንቦት 7ን አሸባሪ ቡድን ዓላማዎች ለማስፈጸም በርካታ የሚስጥር መረብ በመዘርጋት ተባባሪ ሆና መገኘት”፣ “በርካታ የሆኑ የአመጽ እና የሽብር ስልጠናዎችን በማዘጋጀት እና በመሳተፍ ትብብር አድርጋለች“ የሚሉ ውንጀላዎች ቀርበውባታል፡፡
በማህሌት ላይ የቀረቡባት የጽሁፍ ማስረጃዎች የሚከተሉትን ያካተተ ነው፡ “የእምነት ቃል እንድትሰጥ የተደረገችበት – 12 ገጾች”፣ እንደዚሁም ሌሎች ማስረጃዎች “ከኮምፒውተር የተሰበሰቡ ሰነዶች“፣ “የኃይል አመጽ ለመቀስቀስ መንቀሳቀስ እና የምጣኔ ሀብት ዕድገቱን ዕውቅና ያለመስጠት የሚሉ ጹሁፎችን ያካተተ – 2 ገጾች“፣ እና “ከሲዲ እንዲታተም የተደረገ የኦነግ የፖለቲካ ፕሮግራም – 22 ገጾች“ የሚሉ የውንጀላ ክሶች ናቸው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባልታሰበ እና ባልተጠበቀ ሁኔታ ክሱ እንዲቋረጥ ተደርጎ እ.ኤ.አ ሀምሌ 9/2015 ከማጎሪያው እስር እንድትለቀቅ ተደርጓል፡፡
4ኛ) አጥናፍ ብርሀኔ አያሌው፡ “ሆን ብሎ እያወቀ በሚስጥር ከሚንቀሳቀሰው የግንቦት 7 አሸባሪ ቡድን ጋር በሚድብቅ ተሳትፎ አድርጓል“፣ “የመንግስት የደህንነት ኃይሎችን እንዴት አድርጎ መቀስቀስ እንደሚቻል እና በመካከላቸው የጎሳ ክፍፍልን በመፍጠር ሁከት ለማስነሳት እና እራስን እንዴት አድርጎ ፊትን በመሸፈን፣ ሄልሜቶችን በእራስ ላይ በማድረግ ከአደጋ መከላከል እንደሚቻል፣ የሚፈነዱ ነገሮችን እና ድንጋይን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ስልጠና ወስዷል፡፡“ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)
በአጥናፍ ላይ የቀረቡት የጽሁፍ ማስረጃዎች የሚከተሉትን ያካትታል፡ “የእምነት ቃል እንዲሰጥ የተደረገበት – 16 ገጾች”፣ እና ሌሎች ሰነዶች ማለትም “ነጻነት በኢትዮጵያ – 34 ገጾች“፣ “ስለኢንተርኔት ደህንነት የስልጠና ሰነድ“፣ “በእጅ ጽሁፍ የተዘጋጀ የሚስጥር የአመጽ ቅደምተከተል ሰነድ – 61 ገጾች“፣ “በፍላሽ ላይ ያለ ስለደህንነት ቅደምተከተል የተዘጋጀ ሰነድ“፣ “በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ስለነጻነት ሊታዩ የሚችሉ አጫጭር ፊልሞችን ለማዘጋጀት የቀረበ ንድፈ ሀሳብ – 7 ገጾች“፣ “ለሚመጣው ምርጫ ዓላማ ሊውል የሚችል የኢንተርኔት አድራሻ ስያሜ ለመግዛት ዕቅድ መያዝ – 8 ገጾች“፣ “እ.ኤ.አ በ2015 በኢትዮጵያ ስለሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ የማህበራዊ ድረ ገጽ ሚና- 9 ገጾች“፣ “የጽሁፍ ምርመራን እንዴት ማስቀረት እንደሚቻል በሲቪል መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች አስተባባሪነት የተዘጋጀ የስልጠና ሰነድ“፣ “በኢንተርኔት የመጠቀሚያ የሚስጥር ኮዶችን እና ፓስወርዶችን የመለወጥ ዘዴ – 129 ገጾች“፣ “የዲጂታል የደህንነት ስልጠና ለመውሰድ ለእርሱ የተላለፈ የግብዣ ደብዳቤ“፣ “የጉዞ ዕቅድ እና ቲኬት – 18 ገጾች“ የውንጀላ ክሶች ቀርበውበታል፡፡
5ኛ) ዘላለም ክብረት ቤዛ፡ “የሀገር ውስጥ የሚስጥር የሽብር ድርጅት ማቋቋም“ እና “ሆን ብሎ እያወቀ በሚስጥር ከሚንቀሳቀሰው የግንቦት 7 አሸባሪ ቡድን ጋር በሚስጥር የግነኙነት መረብ ዘርግቷል“፣ “ህዝቡን ለማነሳሳት አመጽ እንዲጀመር ለማድረግ እንዲቻል በሀገር ውስጥ እና ከኢትዮጵያ ውጭ በርካታ ስልጠናዎች እንዲዘጋጁ አድርጓል፣ ተሳትፏል፣ እንዲሳለጡም አድርጓል፡፡“
በዘላለም ላይ የቀረቡት የጽሁፍ ሰነድ ማስረጃዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡ “የእምነት ቃል እንዲሰጥ የተደረገበት – 16 ገጾች“፣ እና ሌሎች የተሰበሰቡ ሰነዶች ማለትም “ከውጭ ሀርድ ዲስክ ጭቆና እና የሰብአዊ ልማት ጽሁፍ“ የሚል ያለበት፣ “ዋኤል ጎኒም ኢትዮጵያዊ ቢሆን ኖሮ የሚል (ከግብጽ ምዕናባዊ የኢንተርኔት አክቲቪስት ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ-18 ገጾች – በበፈቃዱ ኃይሉ የተጻፈ“፣ “የጽሁፍ ምርመራ ዋጋ“፣ “ድምጻችን ከሚዘረፍ እንዲሰማ ማድረግ“፣ “በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ስለነጻነት ሊታዩ የሚችሉ አጫጭር ፊልሞችን ለማዘጋጀት የቀረበ ንድፈ ሀሳብ“፣ “የመለስ ዜናዊ ራዕይ እና ትሩፋት – 4 ገጾች“፣ “የሞተው ፓርላማ – 22 ገጾች“ የሚሉ ውንጀላዎች ቀርበውበታል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባልታሰባ እና ባልተጠበቀ ሁኔታ ክሱ እንዲቋረጥ ተደርጎ እ.ኤ.አ ሀምሌ 9/2015 ከማጎሪያው እስር እንዲለቀቅ ተደርጓል፡፡
6ኛ) አቤል ዋቤላ ሱጌቦ፡ የተመሰረተበት ክስ “የሀገር ውስጥ የሚስጥር የሽብር ድርጅት ማቋቋም“፣ “ከግንቦት 7 ጋር በመተባበር ህዝቡን ለአመጽ ለማነሳሳት፣ አመጽ እንዲጀመር ለማድረግ እንዲቻል በሀገር ውስጥ እና ከኢትዮጵያ ውጭ በርካታ ስልጠናዎች እንዲዘጋጁ አድርጓል፣ ተሳትፏል፣ እንዲሳለጡም አድርጓል፡፡“
በአቤል ላይ የቀረቡት የጽሁፍ ሰነድ ማስረጃዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡ “የእምነት ቃል የተሰጠበት – 12 ገጾች“፣ እና ሌሎች ሰነዶች ማለትም “ለሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ዲጂታል የደህንነት ሰነድ – 18 ገጾች“፣ “በእርሱ ቤት ውስጥ የተመደቡ የቡድን አባላት ሚናዎች እና ኃላፊነቶች – 26 ገጾች“፣ “ለሚመጣው ምርጫ ዓላማ ሊውል የሚችል የኢንተርኔት አድራሻ ስያሜ ለመግዛት ዕቅድ መያዝ – 8 ገጾች“ የሚሉ ውንጀላዎች ቀርበውበት ነበር፡፡
7ኛ) አስማማው ኃይለጊዮርጊስ ግዛው፡ የተመሰረተበት የክስ ውንጃላ “የሀገር ውስጥ የሚስጥር የሽብር ድርጅት ማቋቋም“፣ “አስቦበት እና ሆን ብሎ እያወቀ ግንቦት 7 እየተባለ ከሚጠራው “አሸባሪ” ድርጅት ጋር ግንኙነት ፈጥሯል፡፡“ የሚል ነው፡፡
በአስማማው ላይ የቀረቡት የጽሁፍ ማስረጃዎች የሚከተሉትን ያካትታል፡ “የእምነት ቃል የሰጠበት – 13 ገጾች“፣ እና ሌሎች የተሰበሰቡ ሰነዶች ማለትም “ከምግብ በፊት ፍትሕ እና ሰላም”፣ “ሙስሊሞች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ተሳትፎ ማድረግ መጀመር አለባቸው – 6 ገጾች“፣ “የሁሉም ንቅናቄ ተከሳሾች የምርመራ ውጤት በኢትዮጵያ የመረጃ ደህንነት ተመዝግቦ እንደተያዘ- 31 ገጾች“፣ “በኢትዮጵያ የፌዴራል የመረጃ ደህንነት አገልግሎት የተጻፈ ደብዳቤ 56 ገጾች“፣ “የዲጂታል ደህንነት ለጋዜጠኖች“፣ “በኢትዮጵያ መንግስት ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብትን የሚነጥቅባቸው መንገዶች“፣ “በዳሽን ባንክ የተጻፈ ደብዳቤ – 31 ገጾች“፣ “የተከሳሹ የፓስፖርት ፎቶኮፒ ቅጅዎች ለተከሳሹ ውንጀላ ማጠናከሪያ እንዲመጡ ተደርጓል፡፡“ የሚሉት ናቸው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባልታሰባ እና ባልተጠበቀ ሁኔታ ክሱ እንዲቋረጥ ተደርጎ እ.ኤ.አ ሀምሌ 9/2015 ከማጎሪያው እስር እንዲለቀቅ ተደርጓል፡፡
8ኛ) ኤዶም ከሳዬ ገላን፡ የተመሰረተባት የክስ ውንጀላ “ሆን ተብሎ ታስቦበት እና እያወቀች የግንቦት 7 አሸባሪ ቡድንን ስትራቴጂዎች ባካተተ መልኩ ለተፈጻሚነታቸው ተሳትፎ አድርጋለች“፣ “ከግንቦት 7 ጋር በመተባበር ህዝቡን ለአመጽ ለማነሳሳት እና አመጽ እንዲጀመር ለማድረግ እንዲቻል በሀገር ውስጥ እና ከኢትዮጵያ ውጭ በርካታ ስልጠናዎች እንዲዘጋጁ አድርጋለች፣ ተሳትፋለች፣ እንዲሳለጡም አድርጋለች“ የሚሉ ናቸው፡፡
በኤዶም ላይ የጽሁፍ ሰነድ ማስረጃ ምንም ዓይነት ዝርዝር አልቀረበም!
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባልታሰበ እና ባልተጠበቀ ሁኔታ ክሱ እንዲቋረጥ ተደርጎ እ.ኤ.አ ሀምሌ 9/2015 ከማጎሪያው እስር እንድትለቀቅ ተደርጓል፡፡
9ኛ) ተስፋለም ወልደዬስ: የተመሰረተበት የክስ ውንጀላ “ሆን ተብሎ ታስቦበት እና እያወቀ የግንቦት 7 አሸባሪ ቡድንን ስትራቴጂዎች ባካተተ መልኩ ለተፈጻሚነታቸው ተሳትፎ አድርጓል“፣ “ከግንቦት 7 ጋር በመተባበር ህዝቡን ለአመጽ ለማነሳሳት እና አመጽ እንዲጀመር ለማድረግ እንዲቻል በሀገር ውስጥ እና ከኢትዮጵያ ውጭ በርካታ ስልጠናዎች እንዲዘጋጁ አድርጓል፣ ተሳትፏል፣ እንዲሳለጡም አድርጓል“ የሚል ነው፡፡
በተስፋለም ላይ የጽሁፍ ሰነድ ማስረጃ ምንም ዓይነት ዝርዝር አልቀረበም!
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባልታሰበ እና ባልተጠበቀ ሁኔታ ክሱ እንዲቋረጥ ተደርጎ እ.ኤ.አ ሀምሌ 9/2015 ከማጎሪያው እስር እንዲለቀቅ ተደርጓል፡፡
የአሸባሪነት ቁሳዊ ማስረጃዎች፣
የውንጀላ ክስ የተመሰረተባቸው የቁስ አካል ማስረጃዎች የሚከተሉትን ያካትታል፡ 2 ቶሽባ ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች፣ 3 ሳምሰንግ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ከ2 ሲምካርዶች ጋር፣ 1 አሰስ ላፕቶፕ ኮምፒውተር፣ 1 ቴክኖሞባይል ተንቀሳቃሽ ስልክ ከ2 ሲምካርዶች ጋር፣ 1 ሳምሰንግ ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ 2 የመቅጃ ፍላሾች፣ 1 ተች ሰክሪን ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ 2 በሳጥን ውስጥ ያሌ የደህንነት መጽሐፎች፣ 3 ኖኪያ ተንቀሳቀሽ ስልኮች፣ 1 ዴል ላፕቶፕ ኮምፒውተር፣ 1 አፕል ላፕቶፕ ኮምፒውተር፣ 1 ሁአዌ ተንቀሳቃሽ ስልክ ከ3 ሲም ካርዶች ጋር፣ 12 የቪዲዮ ማጫዎቻ ሲዲዎች ናቸው፡፡
በኃይል በማስገደድ የተገኘ የእምነት ቃል እና በሕገወጥ መልክ ኃይልን በመጠቀም የሕግ የምክር አገልግሎት እንዳያገኙ በማድረግ የተገኘ የአሸባሪነት ማስረጃ ሆኖ ሊቀርብ ይችላልን?
የሚከተሉትን ሁሉንም ወይም ደግሞ አንደኛቸውን ነገሮች እንደበቂ ማስረጃዎች በመያዝ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል የሽብር ድርጊት ፈጽመዋል ወይም ደግሞ የሽብር ድርጊት ሙከራ አድርገዋል በማለት በችሎት በማቅረብ የሕግ ሂደት ስርዓት ማከናወን ይቻላልን?:
“ለለውጥ ፈላጊዎች እና ለጀግኖች የተጻፈ ጽሁፍ” በሚል ርዕስ የተጻፈ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“ህወሀት ለትግራይ ህዝብ እንዴት ያለ ህጋዊ ድርጅት ሊሆን እንደሚችል የሚጠይቅ ጽሁፍ” በሚል ርዕስ ተዘጋጀ ሰነድ ይዞ መገኘት፣
“80 ሚሊዮን እስከምንሆን ድረስ እንዋጋለን” በሚል ርዕስ የተጻፈ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“እኛ ህብረት ከፈጠርን አምባገነኖች ምንድን ሊሆኑ ይችላሉ?“ በሚል ርዕስ የተጻፈ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“በድረገ ገጽ በሚወጣ ጽሁፍ ላይ የሚደረግ የጽሁፍ ምርመራ ዘመቻ ይቁም” በሚል ርዕስ የተጻፈ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“ዋኤል ጎኒም ኢትዮጵያዊ ቢሆን ኖሮ (ከግብጽ ምዕናባዊ የኢንተርኔት አክቲቪስት ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ – 18 ገጾች“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“ለሲቪል ነጻነት ተሟጋቾች የስልጠና ሰነድ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሰነድ ይዞ መገኘት፣
“መንግስት አለን? ወይም ደግሞ መንግስት የማን ነው? ምንስ ዓይነት ነው? – 10 ገጾች” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“የኢህአዴግ አባል ያልሆነ ዳኛ ሊኖር ይችላልን?“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“የቴሌኮም የሸፍጥ ሕግ ሀሳብን የመግለጽ ነጻነትን ለመሸበብ የወጣ መሳሪያ – 12 ገጾች“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“የተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት እና በደረ ገጽ ላይ የሚደረግ ዘመቻ ዕቅድ“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“ለዘጋቢ ፊልም ዝግጅት በኢትዮጵያ ሀሳብን በነጻ በመግለጽ ሁኔታ ላይ ያተኮሩ በእጅ የተጻፉ ቃለመጠይቆች ዝርዝር“ በሚል ርዕስ በእጅ የተጻፈ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“ዳቦ እና ነጻነት፣ ለጽሁፍ ምርመራ ይቁም ዘመቻ“ በሚል ርዕስ የተጻፈ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“የጽሁፍ ምርመራ ዋጋ – 8 ገጾች“ በሚል ርዕስ የተጻፈ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“አሁን በህይወት የሌለውን መለስ ዜናዊን የሚተች የግንቦት 7 ደብዳቤ – 4 ገጾች“ የተጻፈ ትችት ይዞ መገኘት፣
“ከቢዝነስ እና ኮንስትራክሽን ባንክ ገንዘብ የተቀበለበት ደረሰኝ“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ደረሰኝ ይዞ መገኘት፣
“በኢንተርኔት የደህንነት ጉዳይን በማስመልከት ከሶሊያና ሽመልስ ፓስፖርት ጋር በተያያዘ የተደረገ የኢንተርኔት መልዕክት ልውውጥ – 26 ገጾች” በሚል ርዕስ የተጻፈ የመልዕክት ልውውጥ ይዞ መገኘት፣
“ስለኢትዮጵያ በናትናኤል ፈለቀ በእጅ ጽሁፍ የተዘጋጀ ግጥም እና ከቤቱ የተሰበሰበ – 1 ገጽ“ በሚል ርዕስ የተጻፈ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“የኃይል አመጽ ለመቀስቀስ መንቀሳቀስ እና የምጣኔ ሀብት ዕድገቱን ዕውቅና ያለመስጠት የሚሉ ጹሁፎችን ያካተተ – 2 ገጾች” በሚል ርዕስ የተጻፈ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“ከሲዲ የታተመ የኦነግ የፖለቲካ ፕሮግራም – 22 ገጾች“ በሚል ርዕስ የቀረበ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“ነጻነት በኢትዮጵያ – 34 ገጾች“ በሚል ርዕስ የተጻፈ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“ስለኢንተርኔት ደህንነት የስልጠና ሰነድ“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሰነድ ይዞ መገኘት፣
“በእጅ ጽሁፍ የተዘጋጅ የሚስጥር የአመጽ ቅደምተከተል ሰነድ – 61 ገጾች“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“በመቅጃ ፍላሽ ላይ ያለ ስለደህንነት ቅደምተከተል የተዘጋጀ ሰነድ“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ስለነጻነት ሊታዩ የሚችሉ አጫጭር ፊልሞችን ለማዘጋጀት የቀረበ ንድፈ ሀሳብ – 7 ገጾች“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“ለሚመጣው ምርጫ ዓላማ ሊውል የሚችል የኢንተርኔት አድራሻ ስያሜ ለመግዛት ዕቅድ መያዝ – 8 ገጾች“ በሚል ርዕስ የተዘጋጅ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“እ.ኤ.አ በ2015 በኢትዮጵያ ስለሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ የማህበራዊ ድረ ገጽ ሚና- 9 ገጾች“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“የጽሁፍ ምርመራን እንዴት ማስቀረት እንደሚቻል በሲቪል መብት ተሟጋች ድርጅቶች አስተባባሪነት የተዘጋጀ የስልጠና ሰነድ“፣
“በኢንተርኔት የመጠቀሚያ የሚስጥር ኮዶችን እና ቁልፎችን የመለወጥ ዘዴ – 129 ገጾች“፣ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“የዲጂታል የደህንነት ስልጠና ለመውሰድ ለእርሱ የተላለፈ የግብዣ ደብዳቤ“ “የጉዞ ዕቅድ እና ቲኬት – 18 ገጾች“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“የጉዞ ዕቅድ እና ቲኬት – 18 ገጾች“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሰነድ ይዞ መገኘት፣
“ከውጭ ሀርድ ዲስክ ጭቆና እና የሰብአዊ ልማት ጽሁፍ“፣ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“ዋኤል ጎኒም ኢትዮጵያዊ ቢሆን ኖሮ የሚል (ከግብጽ ምዕናባዊ የኢንተርኔት አክቲቪስት ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ-18 ገጾች – በበፈቃዱ ኃይሉ የተጻፈ“ ሰነድ ይዞ መገኘት፣
“የጽሁፍ ምርመራ ዋጋ“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“ድምጻችን ከሚዘረፍ እንዲሰማ ማድረግ“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ስለነጻነት ሊታዩ የሚችሉ አጫጭር ፊልሞችን ለማዘጋጀት የቀረበ ንድፈ ሀሳብ“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“የመለስ ዜናዊ ራዕይ እና ትሩፋት – 4 ገጾች“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“የሞተው ፓርላማ – 22 ገጾች“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“ለሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ዲጂታል የደህንነት ሰነድ – 18 ገጾች“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሰነድ ይዞ መገኘት፣
“በእርሱ ቤት ውስጥ የተመደቡ የቡድን አባላት ሚናዎች እና ኃላፊነቶች – 26 ገጾች“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“ለሚመጣው ምርጫ ዓላማ ሊውል የሚችል የኢንተርኔት አድራሻ ስያሜ ለመግዛት ዕቅድ መያዝ – 8 ገጾች“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“ከምግብ በፊት ፍትሕ እና ሰላም” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“ሙስሊሞች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ተሳትፎ ማድረግ መጀመር አለባቸው – 6 ገጾች“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“የሁሉም ንቅናቄ ተከሳሾች የምርመራ ውጤት በኢትዮጵያ የመረጃ ደህንነት ተመዝግቦ እንደተያዘ – 31 ገጾች“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“በኢትዮጵያ የፌዴራል የመረጃ ደህንነት አገልግሎት የተጻፈ ደብዳቤ 56 ገጾች“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“የዲጂታል ደህንነት ለጋዜጠኖች“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“የሁሉም ንቅናቄ ተከሳሾች የምርመራ ውጤት በኢትዮጵያ የመረጃ ደህንነት ተመዝግቦ እንደተያዘ – 31 ገጾች“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“በኢትዮጵያ የፌዴራል የመረጃ ደህንነት አገልግሎት የተጻፈ ደብዳቤ – 56 ገጾች“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“የዲጂታል ደህንነት ለጋዜጠኖች“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“በኢትዮጵያ መንግስት ሀሳብን በነጻ መግለጽ መብትን የሚነጥቅባቸው መንገዶች“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ይዞ መገኘት፣
“በዳሽን ባንክ የተጻፈ ደብዳቤ – 31 ገጾች“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ደብዳቤ ይዞ መገኘት፣
“የተከሳሹ የፓስፖርት ፎቶኮፒ ቅጅዎች ለተከሳሹ ውንጀላ ማጠናከሪያ እንዲመጡ ተደርጓል” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሰነድ ይዞ መገኘት የሚሉ ናቸው፡፡
የሚከተሉት ቁሶች በአሸባሪነት የሕዝብ ዕልቂትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ተመራጭ መሳሪዎች ናቸውን?
2 ቶሽባ ላፕቶፖች፣ 3 ሳምሰንግ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ከ2 ሳም ካርዶች ጋር፣ 1 አሰስ ላፕቶፕ ኮምፒውተር፣ 1 ቴክኖሞባይል ተንቀሳቃሽ ስልክ ከ2 ሲም ካርዶች ጋር፣ 1 ሳምሰንግ ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ 2 የመቅጃ ፍላሾች፣ 1 ተች ስክሪን ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ 2 በሳጥን ውስጥ ያሉ የደህንነት መጽሐፎች፣ 3 ኖኪያ ተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ 1 ዴል ላፕቶፕ ኮምፒውተር፣ 1 አፕል ላፕቶፕ ኮምፒውተር፣ 1 ሁአዌ ተንቀሳቃሽ ስልክ ከ3 ሲምካርዶች ጋር፣ 12 የቪዲዮ ማጫዎቻ ሲዲዎች የሚሉ ናቸው፡፡
ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች ከAK 47 ጋር እኩል ናቸውን?
ተንቀሳቃሽ ስልኮች ከእጀ ቦምቦች ጋር እኩል ናቸውን?
የመቅጃ ፍላሽ ድራይቮች ከፍላሽ ቦምቦች ጋር እኩል ናቸውን?
በሳጥን ውስጥ ያሉ የደህንነት መጽሐፍት የተሻሻሉ የፍንዳታ መሳሪዎች ናቸውን?
የቪዲዮ ማጫዎች ሲዲዎች ከአርፒጂዎች/RPGs (ፈንጂ መተኮሻ ) እኩል ናቸውን?
ሲም ካርዶች ከጥይቶች ጋር እኩል ናቸውን?
በአጠቃላይ ከዞን 9 ጦማሪያን ጉዳይ ጋር በተያያዘ መልኩ እነዚህ ጦማሪያን የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ግንቦት 7 የተባለውን ድርጅት አሸባሪ ብሎ የሰየመው የነጻነት ንቅናቄ ድርጅት አባላት ናቸው በማለት በምዕናቡ ፈጥሮ የሚያራምደው እና የሚያናፍሰው እኩይ ምግባር ነው፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እነዚህ ለመብቶቻቸው በጽናት በመቆም ሰላማዊ ትግል የሚያካሂዱ እና ለሀገራቸው ለውጥ በሰላማዊ መንገድ ይመጣል በማለት እምነታቸውን የሚያራምዱ ትንታግ ወጣት ጦማሪያን ለግንቦት 7 ይቅር እና ለሌላ ለየትኛውም ድርጅት አባል ስለመሆናቸው ቅንጣት ታህል ማስረጃ የለውም፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እራሱ በፈጠረው ባዶ ምዕናቡ በመመራት በእነዚህ ጦማሪያን ላይ የደቦ ክስ በመመስረት ጥፋተኛ እንዲባሉለት ይፈልጋል፡፡
የዞን 9 ጦማሪያን ምንም ዓይነት የሰሩት ወንጀል የለም፡፡ በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ወንጀል ተብሎ የተያዘባቸው ሀሳባቸውን የመግለጽ መብታቸውን በመጠቀማቸው ብቻ ነው!
ይልቁንም የዞን 9 ጦማሪያን እራሳቸው የወንጀል እና የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የሽብር ሰለባዎች ናቸው፡፡
እንዲያው ለመሆኑ እትብታቸው በተቀበረችበት በእራሳቸው ሀገር ዘመኑ ያፈራቸውን የግንኙነት ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት የተከበረባት ሀገር አድርጊያታለሁ እያለ ሌት ከቀን እንደበቀቀን ከሚለፈልፍባት ሀገር ሆነው ሀሳባቸውን የመግለጽ መብታቸውን በመጠቀም ሰላማዊ እና የምሁራዊ አንደበት ክህሎታቸውን በማከል ግንኙነት ማድረጋቸው በየትኛው መለኪያ እና መስፈርት እንዲሁም የሕግ አንቀጽ ነው ሽብረተኞች ተብለው ከሕግ አግባብ ውጭ በእስር ቤት እየማቀቁ እንዲኖሩ የሚደረገው?
ምን ዓይነት የፍትሕ አካል ቢኖርስ ነው ለእንደዚህ ያለው የሸፍጥ መንግስታዊ ውንብድና እኩይ ምግባር ተባባሪ ሆኖ በዜጎቹ ላይ እንደዚህ ያለ ግፍ እየሰራ የአምባገነኖች ተባባሪ ሊሆን የሚችለው?
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ፕላኔት የዝንጀሮዎች ፕላኔት አፈታሪክ ቢሆን ኖሮ የዞን 9 ጦማሪያን እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ የማምለጫ ዕድል ይኖራቸው ነበር፡፡
የመከላክል ጥረቱ በምንም ዓይነት መንገድ ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ቡድን አያጎበድድም፡፡
ሆኖም ግን ጉዳዬን በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ፕላኔት ላይ ላለው የዝንጀሮ/ጦጣ ችሎት ትቻለሁ!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ነሐሴ 20 ቀን 2007 ዓ.ም