ኢትዮጵያ፣ እምነታችን፣ አገራችን ባንድነታችን
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
እራሱን ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እያለ የሚጠራው አምባገነን ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ለረጅም ጊዜ በኃይማኖት ላይ ስልታዊ የሆነ ጥቃት በመሰንዘር በኢትዮጵያ ለብዙ ጊዜ ሊቆይ የሚችል የኃይማኖት ቅራኔ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡
እ.ኤ.አ በ1991 የወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የፖለቲካ ስልጣን እርካብን በሕዝብ ፈቃድ ሳይሆን በጠብመንጃ ኃይል ከተቆጣጠረ በኋላ የአስመሳይነት ባህሪውን በመጠቀም በተግባር ሳይሆን በባዶ ፕሮፓጋንዳ ሌት ከቀን የሚለፈልፍለትን የይስሙላ የእኩልነት እና የመቻቻል መርሆ ሰፍኗል በማለት በኢትዮጵያ የእስልምና እምነት ተከታይ ማህበረሰብ ዘንድ እርካሽ ተወዳጅነትን ለማትረፍ ሲፍጨረጨር ቆይቷል፡፡
ወያኔው የሙስሊሙን ማህበረሰብ የእምነት ግንዛቤ አሳንሶ በመመልከት እና እኔ አውቅልሀለሁ በማለት ከእምነቱ ተከታይ ህዝብ ልቆ በመታየት የትሮጃን ፈረስ በመሆን በመጋለብ ሲዳክር ይታያል፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ሰይጣናዊ የፖለቲካ ዓላማውን ተግባራዊ ለማድረግ በሙስሊሙ ማህበረሰብ መሪዎች እና ተቋማት ላይ የእራሱን ድብቅ አጀንዳ እና ፖለቲካ መጫን ነው፡፡
የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የጸረ ሽብር ጦርነት (መለስ ዜናዊ “ከአምላክ የተላከ” ለወያኔ እያለ ይጠራው የነበረው) ነገሮችን ሁሉ ፍጹም በሆነ መልኩ እንዲቀየሩ አደረገ፡፡
የሰውን ሉዓላዊ ሀገር ድንበር ጥሶ በመግባት በሶማሌ ውስጥ ሲደረግ የነበረው የመለስ የውክልና ጦርነት ፖሊሲ የኢትዮጵያን የሙስሊም ማህበረሰብ ጥላሸት በመቀባት የርዕዮት ዓለም መሰረቱን ለመጣል በቃ፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በጣም አስፈሪ እና ቆጥቋጭ የሆነ እርባናየለሽ ንግግራቸውን አጉልቶ በማሰማት እራሳቸውን በስልጣን እርካብ ላይ የኮፈሱ እና እራሳቸውን አዋቂ አድርገው የሰየሙ ለእምነቱ ተቆርቋሪ ሳይሆኑ ለርካሽ ጥቅም ያጎበደዱ ስብዕናየለሽ ጥቂት የሙስሊም ማህበረሰብ መሪዎችን እምነቱ ከሚፈቅደው ዶግማ እና የቁራን ሕግ ውጭ ለእኩይ የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያነት ለመጠቀም በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ በአመራር ደረጃ አሻንጉሊት አድርጎ በማስቀመጥ የኢትዮጵያን ሙስሊም ማህበረሰብ ጥላሸት የመቀባት እና የማዋረድ ስልታዊ የጥቃት ዘመቻውን ጀመረ፡፡
እ.ኤ.አ ታህሳስ 2011 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ “አኬልዳማ“ በሚል ርዕስ እርባናየለሽ ዘጋቢ ፊልም በማቅረብ መጠነ ሰፊ የሆነ የመጀመሪያ እርብናየለሽ ዘመቻውን መጀመሩን በማስመልከት “ኢትዮጵየ ፡ የደም ወይስ የሙስና መሬት?“ በሚል ርዕስ አቅርቤው በነበረው ትችቴ ላይ ታላቅ ቅሌት እና በህዝቡ ላይ ማቆሚያ የሌለው ፍርሀትን ለማንገስ የተሸረበ ተንኮል ነው በማለት አውግዠው እና በህዝብ ፊት ከፍተኛ የሆነ ትችትን አቅርቤበት ነበር፡፡
በዚያ እርባናየለሽ ዘጋቢ ፊልም የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በኢትዮጵያ የሙስሊሙ ማህበረሰብ እስልምና እምነት ስም ዓለም አቀፍ አሸባሪዎች በሰው ልጆች ላይ የፈጸሙትን ወንጀል ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አጉልቶ ለማሳየት የተሸረበ የተንኮል ድር ነበር፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ዋና ዓላማ በዓለምም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው ሕዝብ ይህንን ዘጋቢ ፊልም ከተመለከተ በኋላ በድርጊቱ ላይ ስሜታዊ እንዲሆን እና በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ ጥላቻ እንዲያድርበት በማድረግ አጋጣሚውን እንደመልካም ነገር በመጠቀም ያለምንም ስጋት በሙስሊሙ ማህበረሰብ ወገኖቻችን ላይ የፈለጉትን ዓይነት እርምጃ ለመውሰድ የታቀደ እኩይ ምግባር ነበር፡፡
እ.ኤ.አ ሰኔ 2012 “ኢትዮጵያ የእምነት አንድነት!“ በሚል ርዕስ አቅርቤው በነበረው ትችቴ ላይ አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ “በሀገር በቀል የሙስሊም አሸባሪዎች” ስም በክርስትና እና በእስልምና እምነቶች መካከል የኃይማኖት ጥላቻ ብጥብጥን ለመፍጠር ሸርቦት የነበረውን እኩይ ድርጊት በማጋለጥ ተዋግቻለሁ፡፡
መለስ ትልቁን መርዛማ እባብ በመምሰል ይፋ ባልሆነ መልኩ ቀስ በማለት የኢትዮጵያን የሙስሊም ማህበረሰብ “ሳላፊዎች” እና “ዋህቢዎች” የሆኑ ጽንፈኞች እና የአልቃይዳ እኩይ ምግባር አስፈጻሚዎች ናቸው በማለት ሰላማዊ የሆኑ ወገኖቻችንን ጥላሸት ለመቀባት ጥረት አድርጎ ነበር፡፡
መለስ በሰይጣናዊ አስተሳሰቡ ወጣት የሙስሊም ማህበረሰብ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን የዓለም አቀፍ ጽንፈኛ የእስላሚስት እና ጂሀዲስቶች እኩይ ምግባር አስፈጻሚዎች እና በኢትዮጵያ እንዲያገለግሉ የተዘጋጁ ወኪሎች ናቸው በማለት ፈረጃቸው፡፡
መለስ ለእርሱ የይስሙላ የዝንጀሮ ፓርላማ አባላት እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር፡
ማንም ቢሆን ሁሉም ሳላፊዎች አልቃይዳ ናቸው ለማለት አይችልም፡፡ ይኸ አባባል በመሰረታዊ ይዘቱ ስህተት ነው፣ ወንጀልም ነው፡፡ ሆኖም ግን ሁሉም አልቃይዳዎች ሳላፊዎች ናቸው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የአልቃይዳ ሴል በኢትዮጵያ ተገኝቷል፡፡ አብዛኞቹም በባሌ እና በአርሲ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ የዚህ ሴል ሁሉም አባላት ሳላፊዎች ናቸው፡፡ ይህም ማለት ሁሉም በኢትዮጵያ ያሉ ሳላፊዎች የአልቃይዳ አባላት ናቸው ማለት አይደለም፡፡ አብዛኞቹ ሳላፊዎች የአልቃይዳ አባላት አይደሉም፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ሳላፊዎች እውነተኛውን የእስልምና እምነት አስተምህሮ ከእምነቱ በተጻረረ መልኩ አዛብተው ሲያስተምሩ እየተስተዋሉ ነው፡፡ እነዚህ ሳላፊዎች በኢትዮጵያ ያሉ አብዛኞቹ ህዝቦች ሙስሊም ናቸው ይላሉ፡፡ ይፋ የሆኑት የስታቲስቲክስ ዘገባዎች የውሸት ናቸው ይላሉ፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ሙስሊም በመሆኑ የእስልምና መንግስት መሆን አለበት ይላሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንደዚህ ዓይነቱ ቅስቀሳ በጽንፈኛ አክራሪዎቹ መጠነ ሰፊ በሆነ መልኩ በመካሄድ ላይ ነው…
ይህንን የመሰለ የህዝብን መንፈስ ለማናወጥና ፍርሃትን ለማስፋፋት የተደረገ ንግግር ነበር፡፡ በዚህ አስፈሪ ንግግሩ መለስ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ፍርሀት፣ ጭንቀት፣ ጥርጣሬ፣ እጅግ በጣም መጨነቅ እና በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ድንገተኛ የሆነ ድንጋጤን ለመፍጠር ተስፋ አድርጎ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ1949 የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ጀምስ ፎሬስታል እንዲህ ብለው ነበር፣ “ሩሲያዎች እየመጡ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በዚህ አካባቢ ናቸው፡፡ የሩሲያን ወታደሮች ተመልክቻለሁ፡፡“
ለይስሙላው የዝንጀሮ ፓርላማ የተደረጉት እዲህ የሚሉት የመለስ ንግግሮች ከዚህ ብዙም የተለዩ አልነበሩም፡፡ “የኢትዮጵያ ሙስሊም ጂሀዲስቶች እና አሸባሪዎች እየመጡ ነው፡፡ እዚሁ በእኛው አካባቢዎች ናቸው ወይም ደግሞ ከቀጣዩ ቋጥኝ ጀርባ ናቸው፡፡ በባሌ እና በአርሲ አይቻቸዋለሁ፡፡“
በእርግጥ መለስ እነዚህን የተዘበራረቁ እና የተመሰቃቀሉ ኢአመክንዮአዊ መግለጫዎች ከሰጠ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አመራሮች ምሁራዊ፣ ማህበራዊ ወይም ደግሞ በስነልቦና የከሰረ ምዕናባዊ አእምሮ ውስጥ ካልሆነ በስተቀር በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የአልቃይዳ አማጺዎች ወይም ሳላፊዎች እየተጠናከሩ የመጡበት ሁኔታ ፈጽሞ የለም፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ በሙስሊም ተቃዋሚዎች ኃይልን መሰረት ያደረገ እንቅስቃሴ ለመኖሩ እስከ አሁን ድረስ ነጻ በሆነ መልኩ የተረጋገጠ ማስረጃ የለም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በእርግጠኝነት አባሎቻቸው የኃይል ጥቃት እንዲሰነዝሩ ለማድረግ ሙከራ ያደረጉ እና ያስተማሩ “አክራሪ የሙስሊም ምሁራን/ሰባኪዎች” ለመኖራቸው ነጻ በሆነ አካል የተረጋገጠ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም፡፡
እ.ኤ.አ ነሐሴ 15/2012 ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት “የኢትዮጵያ መንግስት በአዲስ አበባ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን በገለጹት 18 የሙስሊም ማህበረሰብ መሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ የጭካኔ ኃይልን መጠቀሙን አቁሞ በአስቸኳይ እንዲፈታቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት የእራሱን የሙስሊም ማህበረሰብ ቅሬታ ኃይልን በመጠቀም ሳይሆን በውይይት እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት አለበት፡፡“ የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ2013 አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን በገለጹት በኢትዮጵያ የሙስሊም ማህበረሰብ አባላት ላይ እየፈጸመ ያለውን ማሰቃየት እንዲህ በማለት አውግዞ ነበር፡፡
መንግስት የሙስሊሙ ማህበረሰብ ያቀረበውን ቅሬታ ኃይልን በመጠቀም ምላሽ መስጠቱን፣ ከሕግ አግባብ ውጭ የዘፈቀደ እስራትን በማካሄድ እና ለትርጉም ሰፊ እና አሻሚ የሆነውን የጸረ ሽብር ህግ አዋጅ በመጠቀም የንቅናቄውን መሪዎች እና ሌሎች ግለሰቦችን የማጥቃት ድርጊቱን እንደቀጠለ ነው፡፡ ይህ ድርጊት በኢትዮጵያ ሕገመንግስት በግልጽ ሰፍሮ የሚገኘውን ሕግ በመጣስ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን በሚያሰሙ ሰዎች ላይ መብትን ለማፈን የሚፈጸም የኃይል እርምጃ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በሰላማዊ አማጺዎች ላይ የሚወስዳቸውን እንደዚህ ያሉትን ጨቋኝ ስልቶች እና እርምጃዎች ማቆም አለበት፡፡
እ.ኤ.አ መጋቢት 2015 የአፍሪካ ህብረት የሰብአዊ መብት ተከላካይ የሆነው የአፍሪካ የሰዎች እና የሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን/African Commission on Human and People’s Rights የተባለው አህጉራዊ ድርጅት ለኢትዮጵያ የይስሙላ ጠቅላይ ሚኒስትር ለኃይለማርያም ደሳለኝ እንዲህ የሚል ጥያቄዎችን ያዘለ ደብዳቤ ልኮ ነበር፡፡
በእስረኞች ላይ የማሰቃዬት፣ ሌሎችን በሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ወይም ደግሞ በ29ኙ የሙስሊም ተከላካዮች ላይ የሚፈጸሙትን ቅጣቶች እና ጥሩ ያልሆነ የእስረኞች አያያዝን፣ እስረኞች ከጠበቆቻቸው ጋር እንዳይገናኙ የሚከለክለውን ውንጀላ ለማጣራት እንዲሁም አንድ ሰው በፍትህ አካል ጥፋተኝነቱ እስካልተረጋገጠ ድረስ ነጻ መሆኑን እና የመንግስት ባለስልጣኖች እና የመንግስት መገናኛ ዘዴዎች የድርጊቱን ሰለባዎች ስም ከማጠልሸት መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡
እ.ኤ.አ ነሐሴ 6/2015 የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የኃይማኖቶች ነጻነት ኮሚሽን/U.S Commission on International Religious Freedom (USCIF) የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት “በ18ቱ የኢትዮጵያ የሙስሊሙ ማህበረሰብ መሪዎች ላይ የተሰጠውን ፍርድ እና ብይን ጠንካራ በሆነ መልኩ አውግዟል፡፡”
የUSCIRF ሊቀ መንበር የሆኑት ዶ/ር ሮበርት ፒ. ጆርጅ እንዲህ ብለው ነበር፣ “እነዚህ ሰዎች ሰላማዊ በሆነ መልኩ ስለኃይማኖት ነጻነት ሲያስተምሩ የነበሩ ናቸው፡፡ ይህ የፍርድ ሂደት የኢትዮጵያ መንግስት የጸረ ሽብር ሕጉን በመጠቀም የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን እና ሰላማዊ አመጸኞችን ለማፈን ቀጥሎበት ያለ ነበር፡፡“
የኢትዮጵያን ሙስሊም ማህበረሰብ ስም በህወሀት እና በመለስ ዜናዊ ማጠልሸት፣
እ.ኤ.አ የካቲት 2013 በህወሀት ተዘጋጅቶ የቀረበውን እና “ጂሀዳዊ ሀራካት“ (የቅዱስ ጦርነት ንቅናቄ) እየተባለ ይጠራ የነበረውን እርባናየለሽ ዘጋቢ ፊልም እና የሙስሊሙን ማህበረሰብ ስም የማጠልሸት እና የዘለፋ ፕሮፓጋንዳ የዘመቻ እኩይ ምግባር “የፍርሀት እና ስም የማጠልሸት ፖለቲካ“ በሚል ርዕስ አዘጋጅቸ ባቀረብኩት ትችቴ ለመከላክል እና ለማጋለጥ ጥረት አድርጊያለሁ፡፡
ያ እርባናየለሽ ዘጋቢ ፊልም በመለስ እና በህወሀት ወሮበሎች ተዘጋጅቶ የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ሰብአዊ መብቱን ለማስከበር በሰላማዊ መንገድ የሚያቀርበውን ጥያቄ ወደ ሌላ አዙረው የጂሀዲስት አሸባሪዎች ንቅናቄ ለሆኑት ለሀማስ (ሀራካት አል-ሙካዋማ አል-ኢስላሚያ)፣ ሀራካት አል-ጂሀድ አል-ኢስላሚ አል-ፊላስቲኒ እና አቡ ሳያፍ (በዱቡብ ፊሊፒንስ የሚንቀሳቀስ አሸባሪ ቡድን) እና ለሀራካት አል-እስላሚያ ተቀጽላዎች እና የእነርሱ የኢትዮጵያ አስፈጻሚዎች አድርገው ለማሳየት ያደረጉት ከንቱ ሙከራ ነው፡፡
ያ እርባናየለሽ ዘጋቢ ፊልም በጣም አናሳ የሆነ የፕሮፓጋንዳ የአፈጻጸም ስኬት ብቻ ነበረው፡፡
እውነታው ፍርጥርጥ ብሎ ሲታየ ግን የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በእራሱ የደህንነት ኃይሎች አማካይነት የሀገር ውስጥ አሸባሪ ዋና ኃላፊ ሆኖ ይገኛል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ቪኪ ሁድለስተን ከሆነ እ.ኤ.አ መስከረም 16/2006 አዲስ አበባ ውስጥ ስለደረሰው የቦምብ ፍንዳታ እና ድርጊቱን በአሸባሪዎች ላይ ለማላከክ የተደረገው ጥረት እውነት ሳይሆን ይልቁንም ድርጊቱ በእርግጠኝነት የተፈጸመው በኢትዮጵያ መንግስት የደህንነት ኃይሎች ነው በማለት አጋልጠው ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ2011 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በአፍሪካ ህብረት ላይ ሌላ የቦምብ ፍንዳታ ሙከራ ተደርጓል በሚል እሳቤ ለማጥቃት የሚፈልጋቸውን ጥቂት ግለሰቦች ሰብስቦ በመያዝ በይስሙላው የዝንጀሮ ፍርድ ቤት ክስ መስርቶባቸው ነበር፡፡
ባለፉት በርካታ ዓመታት፣
መለስ እና የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የኢትዮጵያን ሙስሊሞች በይፋ የማውገዝ፣ ውጤታማ እንዳይሆኑ የማድረግ፣ ሞራላቸው እንዲሰበር የማድረግ፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ተፈላጊ እንዳይሆኑ የማድረግ፣ የሚከተሉትን እምነት የማውገዝ፣ ሕጋዊነትን የመግፈፍ፣ የጭካኔ ድርጊት የመፈጸም፣ ወንጀለኛ የማድረግ፣ ትችት የማቅረብ፣ ሰይጣናዊ አድርጎ የማቅረብ፣ ያልተደራጁ የተበታተኑ አድርጎ የማቅረብ፣ የመነጠል፣ እና ሕገ ወጥ አድርጎ በመፈረጅ አበርትተው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
መለስ እና የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በኢትዮጵያ ኃይማኖቶች ላይ የጥላቻ መንፈስን ለመዝራት ነዳጅ በማርከፍከፍ ቤተክርስቲያናት እና መስጊዶች እንዲቃጠሉ ያላደረጉት ጥረት አልነበረም፡፡
መለስ እና የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በክርስትና እና በእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል የኃይል ጥቃት እንዲጀመር ወኪሎቻቸውን በየአጋጣሚው አስርገው በማስገባት ያልፈነቀሉት ድንጋይ ያልቧጠጡት አቀበት የለም፡፡
መለስ እና የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ቅዱሱን ቁራንን በመዘለፍ የሚል የሀሰት ወሬን በሙስሊሙ ማህበረሰብ ውስጥ በማሰራጨት የእምነቱ ተከታዮች ስሜታዊ እንዲሆኑ እና ከሌሎች የክርስትና እምነት ተከታዮች ጋር ግጭት እንዲፈጥሩ ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ፡፡
መለስ እና የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በእስልምና እና በክርስትና እምነት ተከታዮች መካከል የሸፍጥ የሕዝብ ቆጠራ ስታቲስቲክስ በማካሄድ በሁለቱም እምነት ተከታዮች ዘንድ ጥላቻ እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡
መለስ እና የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የሙስሊም ማህበረሰቦችን በተሳሳተ መንገድ ለመግዛት ሳላፊዎች፣ ዋህቢዎች፣ የአልቃይዳ ጉዳይ አስፈጻሚዎች፣ አሸባሪዎች እና ሌላ ሌላም በማለት ከፋፍሎ ለመግዛት የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት አድርገዋል፡፡
መለስ እና የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ጎሳን እና ኃይማኖትን በማቀላቀል በኢትዮጵያውያን ላይ ልዩነትን አጉልቶ በማሳየት በኃይማኖቶች መካከል ግጭቶች እና ጥላቻዎች እንዲፈጠሩ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፡፡
መለስ እና የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በኃይማኖቶች እና በጎሳዎች መካከል ጥላቻ እንዲፈጠር ከኮሮጆዎቻቸው ሁሉንም ዓይነት ሰነዶች ይመዛሉ፡፡ ሁሉም ነገር ለማይሳነው አምላክ ምስጋና ይግባውና እነርሱ ባሰቡት መንገድ ምንም ነገር ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
መለስ እና የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን፣ የኃይማኖት ጣልቀገብነትን የማይቀበሉ ተቃዋሚዎችን፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎችን እና አባላትን በመያዝ ለረዥም ዓመታት የእስራት ብይን በመስጠት የተቻላቸውን ያህል ጥረት ቢያደርጉም አስቀያሚዎቹ የፕሮፓጋንዳ ጥረቶቻቸው በሙሉ ውድቅ ሆነውባቸዋል፡፡
ከዓመታት በፊት በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በኢትዮጵያ የሙስሊም ማህበረሰብ ላይ የፈጸመውን ማሰቃዬት በማስመልከት የጻፍኳቸውን እና ያቀረብኳቸውን ትችቶች በድጋሜ ለውይይት የማቀርባቸው ለምንድን ነው?
በመጀመሪያ ደረጃ የኢትዮጵያን የሙስሊም ማህበረሰብ በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የሚደርስባቸውን ማሰቃየት ለመከላከል ለምን ከፍተኛ ተነሳሽነት እንደነበረኝ ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡
ስልጣናቸውን ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማስቀጠል እንዲቻል በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እጅ ላይ ያለው ከፍተኛ መሳሪያ የኢትዮጵያን ሕዝብ በኃይማኖት እና በጎሳ መከፋፈል ነው፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የሸፍጥ የጎሳ ፌዴራሊዝም የኢትዮጵያን ሕዝብ በጎሳ፣ በኃይማኖት፣ በቋንቋ እና በክልል ለመከፋፈል ፈልጓል፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታዮችን በማጋጨት እና በመካከላቸው የጥላቻ መንፈስን በመዝራት እርሱ ለዘላለም የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጌታ ሆኖ ለመቆየት ይፈልጋል፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የአፓርታይድ ዓይነት ክልል ወይም ደግሞ ባንቱስታን ስርዓትን በኢትዮጵያ ላይ ተግባራዊ ለማደረግ እጅግ በጣም ትንሽ የሆነ ስኬትን ተጎናጽፏል፡፡ (ከጫካ የወጡ ጥቂት ስነምግባር የለሽ የጫካ ዘራፊ ወሮበሎች እንደዚህ ዓይነት የፖለቲካ ሸፍጥ መፈብረካቸው እና በጎሳ እና በኃይማኖት ቡድኖች መካከል ታሪካዊ ቅሬታዎችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም እንደዚህ ያለ ካንሰርን ያዘለ ወንጀለኛ ተቋም መገንባታቸው አዕምሮን የሚበጠብጥ ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድን አገዛዝ ላዋቀሩት የቦር ተከታይ ዝርያዎች ተመሳሳይ ጥያቄ ማቅረብ ይቻላል፡፡ አለቀ!)
የኢትዮጵያን የሙስሊም ማህበረሰብ በመከላከል ረገድ ሳቀርባቸው የነበሩት ሁሉም ትችቶቼ በሚከተሉት ምክንያቶች ላይ መሰረት ያደረጉ ነበሩ፡
1ኛ) አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያን ሙስሊሞች የአልቃይዳ ጉዳይ አስፈጻሚዎች እና አሸባሪዎች ናቸው በማለት የማጠልሸት እና ዘለፋ የማካሄድ የፕሮፓጋንዳ ጥረቶቹን በግሌ ለመጋፈጥ እና ዓላማውን ለማስፈጸም እያደረገ ያለውን ቀጥፈት በማጋለጥ ለሚያቀርባቸው መሰረተቢስ ውንጀላዎች ተጨባጭነት ያላቸው ማስረጃዎችን እንዲያቀርብ በመጠየቅ ማረጋገጫ ለመያዝ ነው፣
2ኛ) “ኃይማኖት የግል ነው፣ ሀገር የጋራ ነው” የሚለውን መርህ መሰረት በማድረግ በኢትዮጵያ የእምነት ነጻነት ለይስሙላ ሳይሆን በተጨባጭነት ሊከበር በሚችልበት ሁኔታ ላይ አጽንኦ ለመስጠት በማሰብ፣
3ኛ) በኢትዮጵያ የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ለዘመናት ሰፍኖ የቆየውን በሰላም አብሮ የመኖር እና በመከባበር እና ተቻችሎ የመኖር መርሆን ለማረጋገጥ እና በቀጣይነትም ስር ሰድደው እንዲቀጥሉ ለማድረግ፣
4ኛ) የክርስትና እና የእስልምና እምነት መሪዎች የኃይማኖት ግጭትን ለመከላከል እና የጋራ መግባባቶች እንዲዳብሩ ድልድዮችን ለመገንባት፣ በሁለቱ ኃይማኖቶች ማህበረሰብ መካከል የጋራ መከባበር እና የትብብር የስራ ግንኙነትን ለማጠናከር ሲባል ከፍተኛ የሆነ ሚና መጫወት እንዲችሉ ለማድረግ፣
5ኛ) በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እና በሌላም በማንም ቢሆን የሙስሊሙን ማህበረሰብ በማንኛውም ኃይማኖት ለመከፋፈል ሲባል ስለሚደረገው እኩይ ምግባር ድምጼን ከፍ በማድረግ ለመጮህ፣
6ኛ) ተራው የሙስሊም እና የክርስትና እምነት ተከታዮች በመካከላቸው የኃይማኖት ካውንስሎችን በመመስረት በመካከላቸው እህትማማችነት እና ወንድማማችነት እንዲጠናከር ለማስቻል እና ኃይማኖትን ከፖለቲካ ተጽዕኖ ለማድረግ እንዲችሉ ለማደፋፈር፣ እና
7ኛ) የክርስትና እና የእስልምና እምነት መሪዎች እና በአንድነት የቆሙት እና እጆቻቸውን በመጨባበጥ የኃይማኖት ነጻነቶችን ለማስከበር እና እያንዳንዱም ሰው ህሊናው የፈቀደለትን ያለምንም መሸማቀቅ መብቱን በመጠቀም እንደልቡ መናገር እንዲችል ለማስቻል ነው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ እና በይበልጥ ደግሞ 18ቱን ወጣት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የይስሙላ የዝንጀሮ ፍርድ ቤት አማካይነት የበርካታ ዓመታት እስር በመበየን በሰው ልጆች ላይ እየፈጸሙት ያለውን ወንጀል እና እንደዚህ ያለውን ቆሻሻ ወራዳ እና አሳፋሪ ተግባር በማጋለጥ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የህሊና የሀሳብ ዳኝነት ለማቅረብ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የይስሙላ የዝንጀሮ ፍርድ ቤት በ18 የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ላይ (ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ WSCRIF የአፍሪካ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና ሌሎችም የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሰላማዊ ተቃዋሚ መሪዎች እና ወትዋቾች እያሉ የሚጠሯቸውን) ከ7 እስክ 22 ዓመታትን ያካተቱ የእስራት ቅጣት ተበይኖባቸዋል፡፡
ወጣቶቹ ኢትዮጵያውያን የጸረ ሽብር ድርጊት ሙከራ ለማድረግ፣ በኢትዮጵያ የእስላም መንግስት ለማቋቋም የተደረገ እና በህዝብ ዘንድ ብጥብጥን እና ሁከትን ለመፍጠር የሚል ሸፍጥን የተላበሰ ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የይስሙላው የዝንጀሮ ፍርድ ቤት በአቡባከር አህመድ፣ በአህመዲን ጀቤል፣ በያሲን ኑሩ እና በከማ ሸምሱ እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በእያንዳንዳቸው ላይ የ22 ዓመታት የእስር ብይን ፈርዶባቸዋል፡፡
ሌሎቹ ተከላካዮች ማለትም ሙኒር ሁሴን፣ ሳቢር ይርጉ፣ በድሩ ሁሴን፣ መሀመድ አባተ እና አቡበከር አለሙ እያንዳንዳቸው እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በ18 ዓመታት እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡
15 ዓመታት እስራት የተበየነባቸው ደግሞ አህመድ ሙስጠፋ፣ ካህሊድ ኢብራሂም፣ ሙራድ ሽኩር እና ሸክ መከተ ሙሄ፣ ሸክ ሰይድ ዓሊ እና ሙባረክ አደም ናቸው፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የይስሙላ የዝንጀሮ ፍርድ ቤት ዩሱፍ ጌታቸውን፣ ኑሩ ቱርኪን፣ ሙራድ ሽኩርን እና ሸክ ባህሩ ኦማርን እያንዳንዳቸውን እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሚታሰብ የ7 ዓመታት የእስር ቅጣት በይኖባቸዋል፡፡
በእርግጠኝነት ወጣት ሙስሊም ወትዋቾች የፈጸሙት ጥፋት ምንድን ነው?
በወጣት ሙስሊም ወትዋቾች ላይ ጥፋት ተደርጎ የተወሰደው ትልቁ ነገር መስጊድ እና መንግስት መለያየት አለባቸው የሚል ቀላል ጥያቄ ማቅረባቸው ብቻ ነው፡፡
USCRIF ግልጽ እንዳደረገው የሙስሊም መሪዎች እ.ኤ.አ ሀምሌ 2012 ከሌሎች በመቶዎች ከሚቆጠሩ ሙስሊሞች ጋር በመሆን መንግስት በእስልምና እምነት ጉዳዮች ላይ እያደረገ ያለውን ጣልቃገብነት በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን በማሰማታቸው ብቻ እንደ ድፍረት ቆጥሮት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓል፡፡ እንግዲህ ነገሩ ሁሉ የዚህን ያህል በጣም ቀላል ነገር ነው!
ወጣት ወትዋቾች ገዥው አካል ከአወሊያ ኮሌጅ እና ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአመራር ጣልቃገብነት እጁን እንዲያነሳ እና የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እ.ኤ.አ ታህሳስ 2011 ከትምህርት ቤቱ የአመራር ስልጣን ላይ ያባረራቸውን ሰዎች ወደ ቀድሞው ቦታቸው እንዲመልስ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡
እነዚህ ወጣቶች የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ የአመራር አካሉን (መጅሊሱን) እራሱ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ያለማንም ጣልቃገብነት የመምረጥ መብት እንዳለው ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡
ገዥው አካል ሰርጎ ገቦችን ወደ እምነቱ አመራር አስርጎ በማስገባት እና ተቋማትን ለማዳከም የሚያደርገውን እኩይ ምግባር ማቆም እንዳለበት ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ግብረ በላ ስብዕናየለሽ ጉዳይ አስፈጻሚዎችን በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ እየሾመ የእምነቱን መርሆ ማጉደፉን ማቆም አለበት የሚል ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የሙስሊሙ ማህበረሰብ የአል ሀባሽን ኃይማኖት ሀሳቦች በግድ መቀበል እንዲችል እያደረገ ያለውን መንግስታዊ ጫና እና ቅስቀሳ ማቆም አለበት የሚል ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡
እነዚህ ወጣቶች መንግስት እና ኃይማኖት መለያየት አለባቸው የሚል ጥያቄ አቅርበው ነበር!
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የከፋፍለህ ግዛ የቁማር ጨዋታ፣
የከፋፍለህ ግዛው ስልት (ስትራቴጂ) ቢያንስ አራት ነገሮች አሉት፡ እነርሱም፣
1ኛ) በስልጣን እርካብ ላይ ተፈናጥጦ የሚገኘውን ገዥ አካል መገዳደር እንዳይቻል የአንድነት እና የጥምረት ኃይሎችን ለመከላከል በህዝቡ ዘንድ ክፍፍሎች እንዲፈጠሩ ማበረታታት፣
2ኛ) በተቃውሞው ጎራ ያሉትን እና ለእኩይ ምግር ተባባሪ የሆኑትን እና እርካሽ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ በህዝብ ላይ ክህደት ለመፈጸም ፈቃደኛ የሆኑትን ከርሳሞች በመደለል ተቋማትን ለመበታተን ጥረት ማድረግ፣
3ኛ) በህብረተሰቡ መካከል በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በፖሊቲካ ጉዳዮች ላይ ያለመተማመን እና የጥላቻ አመለካከቶች እንዲጠናከሩ ማድረግ፣ እና
4ኛ) በአጠቃላይ በህብረተሰቡ ዘንድ ስልታዊ የሆነ አፍራሽ ቅስቀሳ/ፕሮፓጋንዳ በማካሄድ አጠቃላይ የሆነ ውዥንብር እና የጥላቻ ከባቢ አየር እንዲንሰራፋ፣ ፍርሀት እና ጥልቅ ጥላቻ እንዲነግስ ማድረግ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
በጣም ጥቂት የነበሩት የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች በአህጉሩ የከፋፍለህ ግዛ መርሆዎችን በመተግበር በመቶዎች ሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን አፍሪካውያን ውጤታማ በሆነ መልኩ ህዝቡን መቆጣጠር ችለው ነበር፡፡
እንግሊዞች እና ፈረንሳዮች የጎሳ፣ የቋንቋ፣ የኃይማኖት እና አህጉራዊ ልዩነቶችን በማራገብ የአፍሪካ ህዝቦች ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ግጭት ውስጥ እንዲዘፈቁ በማድረግ የእራሳቸውን ቁጥጥር ማፋጠን እና ማጠናከር የቻሉበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡
ፍሬደሪክ ሉጋር “እንግሊዝ በትሮፒካል አፍሪካ የሁለትዮሽ ተልዕኮ/The Dual Mandate in British Tropical Africa“ በተሰኘው ታላቅ ተጽእኖን በፈጠረው ስራቸው (በምዕራፍ 10 እና 11) በእርግጥኝነት የከፋፍለህ ግዛን መርህ በማራመድ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ህልዮትን መተግበር እንደሚቻል ግልጽ አድርገው ነበር፡፡
ጀርመኖች እና ቤልጀሞች በሩዋንዳ ታሪካዊ የሆነውን እና የማይሽር ጠባሳ ጥሎ ያለፈውን እ.ኤ.አ በ1994 የተከሰተውን የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት እልቂት እንዲፈጠር በማድረግ የከፋፍለህ ግዛን መርህ ተግባራዊ አድርገዋል፡፡
ባለፉት ሩብ ምዕተ ዓመታት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ሲያራምድ በቆየው የከፋፍለህ ግዛ መርሆው እንደማስበው ከሆነ የማርቲን ኒሞለር ቃላት እንዲከሰቱ ያደረገ ነው፡፡
ኒሞለር የፕሮቴስታነት እምነት ተከታይ ፓስተር የነበሩ እና የአዶልፍ ሂትለርን እና የናዚን አገዛዝ በከፍተኛ ደረጃ ሲተቹ የነበሩ ሰው ነበሩ፡፡ እኒህ ሰው ለበርካታ ዓመታት በጦርነት ጊዜ እንዲገደሉ የተወሰነባቸው የፖለቲካ እና የሲቪል እስረኞች በሚቆዩበት እስር ቤት ሆነው እና በኋላም ጀርመኖች በናዚ አገዛዝ ላይ ለምን ጩኸታቸውን አያሰሙም በሚለው መግለጫቸው ላይ ታዋቂ የነበሩ ሰው ነበሩ፡ እንዲህም የሚልዊ ታሪካዊ ንግግርም አድርገው ነበር፡
በመጀመሪያ በሶሻሊስቶች መጡባቸው፣ እናም እኔ ምንም ነገር አልተናገርኩም ነበር፡፡ ምክንያቱም እኔ ሶሻሊስት አልነበርኩምና፡፡
በመቀጠልም በሰራተኛ ማህበራት ላይ መጡባቸው፣ እናም እኔ ምንም ነገር አልተናገርኩም፡፡ ምክንያቱም እኔ የሰራተኛ ማህበር አባል አልነበርኩምና፡፡
ከዚያም በአይሁዶች ላይ መጡባቸው፡፡ እናም እኔ ምንም ነገር አልተናገርኩም፡፡ ምክንያቱም እኔ አይሁድ አልነበርኩምና፡፡
በመጨረሻም በእኔ ላይ መጡ፡፡ እናም ለእኔ የሚጮህልኝ አንድም ሰው አልነበረም፡፡
እኔ እንዳየሁት አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍርሀት ቆፈን ውስጥ ተዘፍቆ፣ በጥላቻ እና በተስፋ መቁረጥ ምክንያት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ኢሰብአዊ የሆኑ ወንጀሎችን እየፈጸመበት ሳለ ጸጥ ብሎ መመልከትን ምርጫው አድርጎ ይገኛል፡፡
በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የከፋፍለህ ግዛ መርሆዎች ላይ በከፍተኛ ደረጃ ጩኸታቸውን ማሰማት ባለመቻላቸው (በተለይም በውጭ ሀገር በሚገኙ የኢትዮጵያ ምሁራን የዲያስፖራ አባላት ላይ) እና ጸጥ ብሎ በሚመለከተው በብዙሀኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ አመልካች ጣቴን ቀስሪያለሁ፡፡
ለውድቀታቸው ምክንያት እንዲህ እላለሁ፡
በመጀመሪያ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ላይ መጡባቸው፡፡ እናንተ ምንም ነገር አልተናገራችሁም፣ እናም ጸጥ ማለትን ምርጫችሁ አደረጋችሁ፡፡ ምክንያቱም እናንተ የተቃዋማ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አልነበራችሁምና፡፡ ወይም ደግሞ እራሳችሁ ጸጥ ብሎ በሚመለከተው ተቃዋሚ ስብስብ ውስጥ ነበራችሁና፡፡
በመቀጠል የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በጋምቤላ ሕዝቦች ላይ መጡባቸው፡፡ አሁንም እናንተ ምንም ነገር አልተናገራችሁም፡፡ ምክንያቱም እናንተ አኙዋክ ወይም ደግሞ ኑዌር አልነበራችሁምና፡፡
ከዚያም የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በኦጋዴን ሕዝቦች ላይ መጡባቸው፡፡ አሁንም እናንተ ምንም ነገር አልተናገራችሁም፡፡ ምክንያቱም ኦጋዴናዊ አልነበራችሁምና፡፡
በቀጣይነትም የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ገዳሞቻቸውን በማውደም እና ለእነርሱ ጉዳይ አሰፈጻሚ የሆነ ግብረበላ ፓትሪያርክ ተብዬ ወሮበላ በክርስትና እምነት ተከታዮች ላይ ከቤተክርስቲያን ቀኖና እና መርህ ውጭ በጉልበት በመሾም መጡባቸው፡፡ እናንተ ምንም ነገር አልተናገራችሁም፡፡ ምክንያቱም እናንተ ክርስቲያን አልነበራችሁምና፡፡
ከዚያም የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በጋዜጠኞች እና በጦማሪያን ላይ መጡባቸው፡፡ እናንተ ምንም ነገር አልተናገራችሁም፡፡ ምክንያቱም እኛ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን አልነበራችሁምና፡፡
በቀጣይነትም የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ መጡባቸው፡፡ እናንተ ምንም ነገር አልተናገራችሁም፡፡ ምክንያቱም እናንተ ሙስሊም አልነበራችሁምና፡፡
በመጨረሻም በእራሳችሁ፣ በቤቶቻችሁ፣ በንግዳችሁ፣ በሙያችሁ፣ በስራችሁ፣ በክብራችሁ፣ በዜግነታችሁ፣ በሰብአዊ ፍጡርነታችሁ እና በኢትዮጵያዊነታችሁ ላይ መጡባችሁ፡፡
ህሊናችሁ በማታ፣ በጧት፣ ከሰዓት በኋላ እና በድቅድቅ ጨለማ ይመጣል፡፡ ሆኖም ግን ምንም መናገር የማትችሉ በድን፣ አፋችሁን የለጎማችሁ፣ አንድም ቃል መናገር የማትችሉ፣ ጸጥ ባዮች እና ጥፋተኞች ሆናችኋል!
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን የከፋፍለህ ግዛ እኩይ መርሆ በያላችሁበት ሆናችሁ በጽናት ተዋጉ፣ “መብቶቻችሁን ለማስከበር ህብረት ፍጠሩ!”
በቅርቡ “የሙስሊም መሪዎች ፍትሀዊ ያልሆነ የፍርድ ሂደት እና በኢትዮጵያ ጸረ ሽብርተኝነትን ለምን ማዳከም እንዳልተቻለ“ በሚል ርዕስ አባድር ኢብራሂም የክርክር ጭብጣቸውን እንዲህ በማለት አቅርበዋል፣ “ለሕዝቡ ተቃውሞ እንቅስቃሴ መንግስት እየሰጠው ያለው ምላሽ ኢሰብአዊ እና ቢያንስ ተመጣጣኝነት የሌለው ነገር ነው፡፡ በጣም ታዋቂ የሆኑትን የተቃውሞ መሪዎች በቁጥጥር ስር በማዋል የግርፋት ማሰቃየት ድርጊቶች ተፈጽመውባቸዋል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ሕዝብ ግብር እየከፈለ በሚያስተዳድረው ቴሌቪዥን ብሄራዊ የማሳፈር እና ጥላሸት የመቀባት ድርጊቶች እንዲደረጉ ጥረት ተደርጓል፣ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በአሸባሪነት ክስ ተመስርቶባቸው በሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡“
አባድር አብዛኛው ሕዝብ የማያውቃቸውን በጣም ልዩ የሆኑ እውነታዎችን ፈልፍለው በማውጣት ለሕዝብ ጆሮ በዘገባ አቅርበዋል፡፡
አባድር እንዲህ ብለዋል፡ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ተሟጋች እንዳገኘው ግኝት ከሆነ የጸረ ሽብር በዓል ከኢትዮጵያ የመብት ተሟጋች ማህበረሰብ ጋር እንዲከበር ይደረጋል፡፡ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ህገ ወጥ ፍርድ ከተሰጠው በሁዋላ “እንኳን ደስ አለህ ” የሚሉ የስልክ ጥሪዎች እና የኢሜል መልዕክቶች ደርሰዉት ነበር ፡፡ እንደዚህ ዓይነቱን ጉዳይ እንዴት እንደዚህ አድርጎ አቅልሎ እንደያዘው ሲጠየቅ የሚሰጠው ምላሽ እንዲህ የሚል ጀግንነት የተቀላቀለበት ነገር ነው፡ በአሁኑ ጊዜ ያሉኝን እምነቶች ከጋንዲ፣ ከማንዴላ እና ከኪንግ ማርቲን ሉተር ጋር በጋራ ማክበር አለብኝ…ከፈለጋችሁ ይህንን የወረደ የበዓል አከባበር ልትሉት ትችላላችሁ፣ ሆኖም ግን በማንኛውም ስኬታማ የሆነ ኢትዮጵያዊ ወትዋች፣ ፖለቲከኛ ወይም ጋዜጠኛ ላይ የሚመሰረት የሽብር ክስ በየዕለቱ የሚስተዋል ክስ ነው፡፡
አባድር እንዲህ የሚሉ ምልከታዎችን አካሂደዋል፡
የሙስሊሙ ሲቪል ማህበረሰብ መሪዎች ክስ በተመሰረተባቸው ጊዜ ምንም ነገር ሳይሆኑ የደስታ ስሜትን ያንጸባርቁ ነበር፡፡ ዳኛው የጥፋተኝነት ክሱን ውሳኔ በሚያሰማበት ጊዜ ተከላካዮቹ እርስ በእርስ በመተቃቀፍ እያንዳንዳቸውን እንኳን ደስ ያለህ ይባባሉ እና ለየትኛው ተሳታፊ እንኳን ደስ ያለህ እንደሚባባሉ ይነጋገሩ ነበር፡፡ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)
የሙስሊሙ ማህበረሰብ ምንም ዓይነት ኃይል ያልተቀላቀለበት ሰላማዊ ተቃውሞን በማራመድ በኢትዮጵያ የነጻነት የትግል ታሪክ ውስጥ ጉልህ ድርሻን ይዞ ይኖራል፡፡
እነዚህ ወጣት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በእርግጠኝነት “ሳቲአግራሀ“ ወይም ደግሞ አረመኒያዊ ሰይጣኖችን ኃይል ባልተቀላቀለበት ሰላማዊ መንገድ መገዳደር የሚለውን የጋንዲን ሰላማዊ የትግል ፍልስፍና በመተግበር ላይ ነበሩ፡፡
ጋንዲ ሕንድ ከእንግሊዝ ኢምፔሪያሊዝም ነጻ ለመውጣት እና ነጻነቷን ለመቀዳጀት ስታደርግ በነበረው ትግል ጊዜ እነዚህን የሳቲአግራሀ መርሆዎች ተጥቀመዋል፡፡
የጋንዲ ሳቲአግራሀ በእውነት ላይ የታወጁ ተብለው ተተርጉመዋል፡፡ ይህም ማለት ሳቲያ “እውነት” ማለት ሲሆን አግራሀ ደግሞ “በተደጋጋሚ ማወጅ ወይም መያዝ”’ ማለት ነው፡፡ የሀረጉ ሙሉ ትርጉም እውነታውን በኃይል ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ መያዝ ማለት ይሆናል፡፡
ጋንዲ የእርሳቸውን የሳቲአግራሀ ፍልስፍና በደቡብ አፍሪካ ሕንዶች ለነጻነታቸው በሚያደርጉት ትግል እና በኋላም መብቶቻቸውን ማስከበር እንዲችሉ ተጠቅመውባቸዋል፡፡ (ጋንዲ ፍጹም በሆነ በሚያስደንቅ ሁኔታ በመጀመሪያ ጊዜ ሳቲአግራሀን ድፍረትን በተቀላቀለ ሁኔታ እንዴት አድርገው እውነተን በከፍተኛ ደረጃ ለመያዝ እና የእንግሊዞችን አመራር እንዴት መገዳደር እንደቻሉ ለማወቅ በቻምፓራ የራጀንድራፕራሳድ ሳቲአግራሀን መመልከት ይቻላል፡፡)
ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ በአሜሪካ ባደረጉት የሲቪል መብቶች ትግል ጊዜ የጋንዲን ሳቲአግራሀ ስልት ተጠቅመውበታል፡፡
ኔልሰን ማንዴላ ተመሳሳይ መርሆዎችን በመጠቀም ደቡብ አፍሪካን ከአፓርታይድ የጥቂት ነጮች የዘርኝነት ጥላቻ አድነዋል፡፡
ወጣት ሙስሊም የመብት ተሟጋቾች ፍትሀዊ ያልሆኑ እምነቶችን በዓል በማክበር የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን እና ቆሻሻውን የማጎሪያ እስር ቤታቸውን እንደማይፈሩ ለዓለም ሕዝብ በማሳየት በተግባር አስመስክረዋል፡፡
ወጣት ሙስሊም የመብት ተሟጋቾች ፍትሀዊ ያልሆኑ እምነቶችን በዓል በማክበር ሰይጣናዊ ድርጊትን ለመዋጋት የእውነትን ኃይል መጠቀምን ለዓለም ሕዝብ በተግባር አስመስክረዋል፡፡
ወጣት ሙስሊም የመብት ተሟጋቾች ፍትሀዊ ያልሆኑ እምነቶችን በዓል በማክበር “በሰብአዊነት ላይ ያለ እምነት መሸርሸር የለበትም፡፡ ሰብአዊነት እንደ ውቅያኖስ ነው፣ ጥቂት የውኃ ጠብታዎች ከቆሸሹ ሁሉም የውቅያሱ ውኃ በሙሉ ቆሻሻ ሊሆን አይችልም፡፡“ የሚለውን የጋንዲን መርሆዎች ለዓለም ሕዝብ በተግባር አሳይተዋል፡፡
ወጣት ሙስሊም የመብት ተሟጋቾች ፍትሀዊ ያልሆኑ እምነቶችን በዓል በማክበር “በአንድነት ወንድማማቾች ሆነን መኖር አለብን ወይም ደግሞ እንደ ሞኝ ጅላጅል በአንድነት መጥፋት አለብን፡፡ ነጻነት በምንም ዓይነት መልኩ በጨቋኞች መልካም ፈቃድ የሚገኝ አይደለም፡፡ በተጨቋኞቹ በግድ መጠየቅ እና መገኘት አለበት፡፡“ የሚሉትን የማርቲን ሉተር ኪንግን መርሆዎች ለዓለም ሕዝብ በተግባር አሳይተዋል፡፡
ወጣት ሙስሊም የመብት ተሟጋቾች ፍትሀዊ ያልሆኑ እምነቶችን በዓል በማክበር “ነጻ ለመሆን የእጅ ማሰሪያ ካቴናዎችን ከእጆቻቸው አንገት ላይ ማውለቅ ማለት አይደለም፣ ሆኖም ግን የሌሎችን ነጻነቶች በማክበር እና በማሳደግ የመኖር ዘዴ ነው፡፡“ እነዚህ ትንታግ ወጣቶች የኔልሰን ማንዴላን ሰላማዊ የትግል መርሆዎች ለዓለም ሕዝብ በተግባር አሳይተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለነጻነት እየተደረገ ባለው ትግል ውስጥ ወጣት ሙስሊም የመብት ተሟጋቾች የሳቲአግራሀን መርሆዎች በመተግበራቸው ከፍተኛ ክብር ያለኝ መሆኑን የዓለም ሕዝብ እንዲገነዘበው እፈልጋለሁ፡፡ እነዚህ ትንታግ ወጣቶች ሰላማዊ ትግል ለነጻነት የሚያበቃ መሳሪያ መሆኑን እና የሚሰራ መሆኑን በተግባር አስመስክረዋል፡፡
ለእነዚህ ጀግኖች ወጣት የመብት ተሟጋቾች ለማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር ከምሰጠው የበለጠ ክብር አለኝ፡፡ እየከፈሉት ያለውን መስዋዕትነት በቃላት ለመግለጽ ከምችለው አቅም በላይ ነው፡፡
ለእነዚህ ሁሉም ትንታግ ጀግኖች ማለት የምፈልገው ነገር ቢኖር ሲቪል እና ሰላማዊ በመሆን ቀንዳሙን ሰይጣን በሰላማዊ ትግል ድል በመንሳት ማንበርከክ እንደሚቻል ለኢትዮጵያውያን ማስተማር በመቻላችሁ አመሰግናለሁ የሚል ነው፡፡
እነዚህ 18 ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የእራሳቸውን ፍላጎቶች እያራመዱ ባሉበት ጊዜ እግረ መንገዳቸውን እኔ በግሌ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች መከበር ላይ እያደረግሁት ያለውን ትግል ተጨባጭነት እና ትክክለኛነት ከማረጋገጣቸውም በላይ እውነትን በስልጣን ላይ ላሉት ደፍሮ መናገር ብቻ ሳይሆን ከዚህም በተጨማሪ በከፍተኛ ስልጣን ላይ ላሉት ሰይጣኖችም ያለምንም ፍርሀት እውነትን መናገር እንደሚያስፈልግ በተግባር አሳይተዋል፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በኢትዮጵያ በሙስሊም ወጣቶች እየተካሄደ ያለውን የኃይማኖት ነጻነት ትግል በማኮላሸት ድባቅ መትቸዋለሁ በማለት ቂጥ ለቂጥ በመያያዝ መደነስ እንደማይችሉ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡
እነዚህ የነጻነት እና የሰላም ጸሮች በኢትዮጵያ ለኃይማኖት ነጻነት የሚደረገውን ትግል አከርካሬውን በመስበር ለእንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ድባቅ መትተነዋል በማለት እጆቻቸውን መጨባበጥ እንደማይችሉ ጥርጣሬ የለኝም፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እነዚህን ወጣት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በማሰር የዘራውን የውድመት አዝመራ ፍሬ የሚያጭድ መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡
እነዚህ የተዘሩ ዘሮች እንደ አረም ይበቅላሉ እና የወያኔ ወሮበላ የዘራፉ ቡድን የሙስና ግዛትን ከነግሳንግሱ ጠራርገው እንደሚጥሉት ግንዛቤ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡
በምሁራዊ፣ በማህበራዊ እና በስብዕና የዘቀጡት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አመራሮች መሰረታዊ እና ቀላል የሆነውን የኢትዮጵያን ታሪክ ይገነዘባሉ ብዬ ባስብ እንኳ እንዲህ የሚሉትን የጆን ኤፍ. ኬኔዲን መርሆዎች እውነታዎች አስታውሳቸው ነበር፡
“ሰላማዊ አብዮትን በሰላማዊ መንገድ እንዳይመጣ የሚያደርጉት ሁሉ የኃይል አብዮትን እንዲያስተናግዱ ይገደዳሉ፡፡“
ምንም ዓይነት ሙከራ እንኳ አላደርግም ደንቆሮዎችን ለማስተማር ፡፡
ቦድሂሀርማ እንዲህ የሚል ትምህርት አስተምረዋል፣ “ደንቆሮው አዕምሮ ስፍር ቁጥር ከሌላቸው ጭንቀቶች፣ ከፍተኛ የሆኑ ስሜታዊነቶች እና ሰይጣናዊ ስሜቶች እንዲህ በሚሉት ሶስት መርዞች ላይ ይበቅላሉ፡ ስግብግብነት፣ ንዴት እና የውሸት እምነት፡፡“
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አደገኛ እና ኃይልን የሚጠቀም ድርጅት ሲሆን መሪዎቹ በጥልቅ ጥላቻ የተሞሉ፣ ስግብግቦች፣ ቁጡዎች እና የውሸት እምነት አራማጆች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰውነት ላይ መርዛማ ዘርን ረጭተዋል፡፡
የኃይማኖት ነጻነት የትግል ታሪክ በሚጻፍበት ጊዜ የ18ቱ ወጣቶች ስም ዝርዝሮች በሰላማዊ እና ኃይልን የማይጠቀሙ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ተብሎ ከክብር ዝርዝሩ ውስጥ የመጀመሪያውን ረድፍ የሚይዙ ይሆናል፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በኢትዮጵያ ወጣት የሙስሊም የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ እያደረገ ያለውን ጥላሸት የመቀባት፣ የማበሳጨት፣ የማውገዝ እና የማዋረድ ድርጊትን ከልብ በመነጨ መልኩ እና ያለምንም ማቋረጥ አወግዛለሁ፡፡
ሆኖም ግን ለእነዚህ ወጣት የሰብአዊ መብት ተሟጋች ወጣቶች ከፍተኛ ውለታ ተደርጎ ሊከፈል የሚገባው ነገር እነርሱ የጀመሩት እና አሁንም በመተግበር ላይ ያለው ሰላማዊ የትግል መንፈስ በዚሁ በሰላማዊ አካሄዱ እንዲቀጥል ከማረጋገጥ ላይ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች ሊጋፈጡት የሚገባ የደረቅ እውነታ ጊዜ፣
ኢትዮጵያውያን ያፈጠጠውን እና ያገጠጠውን ደረቅ እውነታ የሚቀበሉበት ጊዜው አሁን ነው! የመጥፎ ዜና ተሸካሚ መሆንን ጠልቻለሁ፡፡ እውነታው ግን እንዲህ ነው፡
ባራክ ኦባማ ከእኛ በተቃራኒው ጎራ በኩል የቆመ ሰው ነው!
ቻይና ከእኛ ጋር አይደለችም!
እንግሊዝ ከእኛ በተቃራኒው ጎራ የቆመች ሀገር ናት!
የአውሮፓ ህብረት ከእኛ በተቃራኒው ጎራ የቆመ ድርጅት ነው!
የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከእኛ በተቃራኒው ጎራ የተሰለፉ ደርጅቶች ናቸው!
የአፍሪካ ህብረት ከእኛ በተቃራኒው ጎራ የተሰለፈ ድርጅት ነው!
እያንዳንዱ ሰው ከእኛ በተቃራኒው ጎራ የቆመ ነው!
ዓለም ከእኛ በተቃራኒው ጎራ ተሰልፋለች!
ሆኖም ግን ሁሉም ነገር/ዩኒቨርስ ከእኛ በተቃራኒው ጎራ ቢቆም ምንም አይደል!
ከኃይለኛዋ ከዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ እና ከሌሎች በመሬት ላይ ኃያል ከሆኑት የተቀላቀሉ ኃይሎች ሁሉ የበለጠ ኃይለኛ የሆነ ኃይል አለ፡፡
ያ ኃይል እኛን አንድ አድርጎ አስተሳስሮ የሚይዘን እና ለዘላለሙ ሳይሰበር መኖር የሚችለው የእውነት ኃይል ነው፡፡
ያ የማይሰበረው የእውነት ኃይል የእኛ ዜግነት አይደለም፡፡
በእርግጠኝነትም የእኛ ጎሳዊነት አይደለም፡፡
እንደዚሁም ደግሞ የእኛ ሰው ሆኖ የመፈጠር ሁኔታም አይደለም፡፡
የእኛ የማይሰበረው ሰንሰለት የእውነት ኃይል እምነታችን ነው፡፡
የእኛ እምነት የሆነው የእውነት ኃይል እና ወጣት ሙስሊም የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የወጣትነት ዘመናቸውን እየከፈሉት ያለው መስዕዋትነት እና ከወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የይስሙላ የዘንጀሮ ፍርድ ቤት ፊት ቆመው የተወሰኑባቸውን ረዥም የእስራት ጊዜዎች እያከበሩት ያሉበት የእምነታችን ሁኔታ ነው፡፡
በጋራ መከባበር፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ይቅርታ አድራጊነት፣ ለጋስነት፣ ታጋሽነት እና ለፍትህ ተነሳሽነትን ማሳየት እኛን ዘላለማዊ በሆነ የማስተሳሰሪያ ገመድ በመያዝ በእምነታችን የጸናን እንድንሆን ያስችለናል፡፡
ታጋሽነት፣ በእራስ ታማኝነት፣ ድፍረት፣ የፈጠራ ችሎታ፣ ታማኝነት፣ የሞራል ጽናት እና አይበገሬነት በመጨረሻው ሰዓት በሰይጣን ላይ ድልን እንድንቀዳጅ የሚያስችሉን እና የሚያረጋግጡልን ዋና መሳሪያዎቻችን ናቸው፡፡
ወደ ሮሜ ሰዎች በቁጥር 8፡31 ላይ እንዲህ የሚል ቅዱስ ቃል ተጽፎ ይገኛል፣ “እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሐሄር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?“
በቁራን ሱራት አሊ ኢምራን ቁጥር 3፡103 እንዲህ የሚል ቅዱስ ቃል ተጽፎ ይገኛል፣ “ልቦቻችሁ በአላህ ገመድ በአንድነት በጽናት ታስረው ከተያዙ በፍጹም ሊከፋፍላችሁ የሚችል ኃይል ሊኖር አይችልም፡፡ ጠላቶች በነበራችሁ ጊዜ አላህ እንዴት አድርጎ እንደወደዳችሁ እና በእርሱ ቸርነት ከልብ ወንድማማቾች እንድትሆኑ እንዳስቻላችሁ እስቲ አስታውሱ፡፡“
ስለሆነም ለኢትዮጵያ ክርስቲያን እና ሙስሊም ወንድሞቼ እና እህቶቼ በአደገኛው ኃይለኛ ጠላት ላይ በአላህ ገመድ በመተሳሰር ሳትከፋፈሉ በአንድነት በጽናት ቁሙ እላለሁ፡፡
ሁላችንም በአንድነት ተያይዘን በጽናት በመቆም የፍትህን ኢፍትሀዊ ገታራ ደጋን ወደ ፍትሀዊ ደጋን እንዲለነበጥ ማድረግ እንችላለን፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?”
የ18ቱ ወጣት ኢትዮጵያውያን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሙስሊሞች እየከፈሉት ላለው ከፍተኛ የሆነ መስዋዕትነት ምስጋና ለማቅረብ ሁላችንም እንደ አንድ የኢትዮጵያ ልጆች በአንድነት በመቆም ነጻነታችንን ለመጎናጸፍ በእምነታችን ጽናትን በመላበስ በጽናት መዋጋት አለብን፡፡
በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ኃይል ያልተቀላቀለበት ሰላማዊ ትግል መቀጠል አለበት!
ትግሉ ይቀጥላል!
“ኃይማኖት የግል ነው፣ ሀገር የጋራ ነው፡፡”
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ነሐሴ 13 ቀን 2007 ዓ.ም